በአፍሪካ ገንዘብ የሚሰባሰበው ኋላቀርነትን ለማራመድ ነው እንዴ?

ከፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማርያም

ትርጉም በነጻነት ለሀገሬ

የምዕራቡ ዓለም አፍሪካን እንዴት ኋላቀር እንዳደረጋት እና በአሁኑ ጊዜ ገንዘብ ለማሰባሰብ እያደረገ ያለው ጥረት፣

ባለፈው ሳምንት “ገንዘብ ለልማት 3ኛው ዓለም አቀፍ ጉባኤ” በሚል ርዕስ በኢዲስ አበባ ዓለም አቀፋዊ ጉባኤ ተካሂዶ ነበር፡፡ በዚህ ጉባኤ ላይ በከፍተኛ የኃላፊነት ደረጃ ላይ የሚገኙ የፖለቲካ ተወካዮች፣ ርዕሳነ ብሄሮች እና መንግስታት፣ የገንዘብ ሚኒስትሮች፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች እና የልማት አጋሮች፣ የንግድ ዘርፉ እንዲሁም ሌሎች ከጉባኤው ጋር አግባብነት ያላቸው ተቋማት፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እና የንግድ ዘርፉ ተወካዮች የተሳተፉበት ጉባኤ ተካሂዶ ነበር፡፡

ጉባኤው የተካሄደበት ዋናው ዓላማ “በዶሃ መግለጫ መሰረት ተደርሶበት የነበረውን የገንዘብ ስምምነት አፈጻጸም ለመገምገም እና እ.ኤ.አ ከ2015 በኋላ በመንግስታት መካከል ለልማት የሚውል ገንዘብ የማሰባሰብ አጀንዳ በማቅረብ እና ይህንኑ ስምምነት በማጽደቅ ጠቃሚ የሆነ ገንዘብ ማሰባሰብ“ የሚል ነበር፡፡

በጉባኤው ላይ የሚቀርቡ አጀንዳዎች ዝርዝር የሚከተሉትን ያካተተ ነበር፡ በአሁኑ ጊዜ በብዙሀን መንግስታት እርዳታ እየተካሄዱ ያሉትን ጥረቶች በመገምገም ዓለም አቀፍ የልማት ስምምነቶችን ማጠናከር እና ለልማት የሚውል ገንዘብ በሁሉም አቅጣጫ በማፈላለግ ለልማት ዝግጁ እንዲሆን ማድረግ፣ በሶስቱም አቅጣጫዎች ቀጣይነት ያለው ልማት ለማምጣት ያሉትን የገንዘብ ማሰባሰብ አቅሞች መገምገም እና እ.ኤ.አ ከ2015 በኋላ የተባበሩት መንግስታትን የልማት አጀንዳ ለመደገፍ ሁሉንም መንገዶች ሁሉ መፈተሽ የሚሉት ይገኙበታል፡፡

የጉያን የታሪክ ምሁር እና የፖለቲካ ወትዋች የነበሩት ዋልተር ሮድኔይ እ.ኤ.አ በ1972  “አውሮፓ አፍሪካን እንዴት ኋላቀር እንዳስስቀረች “ በሚል ርዕስ አንድ ታዋቂ የሆነ መጽሐፍ በመጻፍ የአውሮፓ ቅኝ ገዥ በዝባዦች በአሁኑ ጊዜ በአፍሪካ አህጉር ለሚታየው ኋላቀርነት ዋና ተጠያቂዎች ናቸው በማለት የክርክር ጭብጣቸውን አቅርበው ነበር፡፡

ሮድኔይ አውሮፓውያን እ.ኤ.አ ከ15ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ ወደ አፍሪካ በመግባት ለአውሮፓውያን ጥቅም ሲባል አፍሪካውያን ሀብታቸውን ሲበዘበዙ እና ሲጨቆኑ የቆዩ መሆናቸውን በመግለጽ የአፍሪካ ኋላቀርነት የዘመናት ታሪካዊ ውጤት ነው በማለት ፖለቲካዊ ኢኮኖሚውን ጥልቅ በሆነ ምርምር አረጋግጠዋል፡፡ ሮድኔይ የክርክር ጭብጣቸውን በማጠናከር የአፍሪካ የኋላቀርነት የፖለቲካ አኮኖሚ መሰረቱ የአትላንቲክ የባሪያ ንግድ፣ የአውሮፓውያን ኃያል የመሆን ፍላጎት፣ ሀገሮችን በጦር ኃይል ወግቶ መያዝ፣ በሰዎች ላይ ኢሰብአዊ የሆነ ድርጊት መፈጸም፣ ማፈናቀል፣ በአፍሪካ ህዝቦች ላይ የበላይነት ስሜትን ማንጸባረቅ እና የአፍሪካን ቀደምት ተቋማት ማጥፋት እና መፐወዝ የሚሉት ነበሩ ይላሉ፡፡

የአውሮፓ ኢንዱስትሪ ልማት እውን የሆነው በአፍሪካ የቅኝ ግዛት የምጣኔ ሀብት ወይም ደግሞ በአፍሪካ ኋላቀርነት በተከፈለ ከፍተኛ ዋጋ ነው በማለት ሮድኔይ የክርክር ጭብጣቸውን ያጠናክራሉ፡፡ የአውሮፓ ካፒታሊዝም የአውሮፓውያንን የበላይነት ባረጋገጠ መልኩ፣ አፍሪካውያንን የበታች ባደረገ እና ጥሬ ሀብቶቻቸውን በመበዝበዝ እና በመዝረፍ ላይ ትኩረትን በማድረግ ዓለም አቀፍ የስራ ክፍፍል እንዲፈጠር አደረገ፡፡ የዓለም አቀፍ ካፒታሊዝም አወቃቀር የአፍሪካን የምጣኔ ሀብት የምርኮ ሰለባ ባደረገ መልኩ ጥሬ ዕቃ አቅራቢ በማድረግ ለአውሮፓውያን ለእራሳቸው ዘላቂነት ያለው ጥቅም እንዲያስገኝ ተደርጎ የጥገኝነት ግንኙነትን ባካተተ ሁኔታ የተቃኘ ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ ያለ የአፍሪካ መንግስት ህልውናው የሚረጋገጠው ከውጭ ኃይሎች ጥቅም ጋር ህብረትን መፍጠር ከቻለ ነው፡፡ ይህም በመሆኑ ይላሉ ሮድኔይ ከጥገኝነት ነጻ ለመውጣት ብቸኛው መንገድ ኢምፔሪያሊዝምን ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ማስወገድ ነው በማለት ይሞግታሉ፡፡

የናይጀሪያ ታዋቂ ገጣሚ እና ደራሲ የሆኑት ወሌ ሶይንካ እ.ኤ.አ በ1980 ሮድኔይ በጉያና ከተገደሉ ከ6 ዓመታት በኋላ ሮድኔይን እንደ ግለሰብ “የምሁር ምርኮኛ ሳይሆኑ አካባቢያዊ እና ዓለም አቀፋዊ የሆነ ስር ነቀል አስተሳሰብን በማራመድ ጉልህ የሆነ አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡ እኒህ ሰው በሚያምኑበት ርዕዮት ዓለም የጸኑ እና የማያወላውሉ እንዲሁም ቅኝ ግዛት እና የእነርሱ በዘመኑ በጥቁሮች ላይ የሚደረገው አስመሳይነት እና ብዝበዛ መወገድ ያለበት ነገር ነው በማለት በዘመናቸው ከነበሩት ምሁራን ሁሉ በበለጠ እና በላቀ ደረጃ የተናገሩ ምሁር ነበሩ፡፡“ በማለት የሮድኔይን ስብዕና በማሞካሸት ከገለጹ በኋላ በስነ ጽሑፍ የኖቬል ሽልማት ተቀብለዋል፡፡

ሮድኔይ እንዲህ የሚል ምልከታ አድርገዋል፣ “የካፒታልስት ስርዓት አንድ ጊዜ በጣም ጥቂት ለሆኑ ሰዎችን ሃብታም ለማረግ ሲባል ከፍተኛ ቁጥር ያለውን ህዝብ እግረ መንገዱን ሰፊዉን ሕዝብ በጥቂቱ የረዳበት ጊዜ ነበር፡፡ ሆኖም ግን በአሁኑ ጊዜ ትርፍን ለማጋበስ የሚታው ፍላጎት ከህዝቦች የቁስ እና ማህበራዊ ፍላጎቶች ማሟላት ጋር ከማይታረቅ የቅራኔ ቅርቃር ውስጥ ገብቷል፡፡“ (አጽንኦ ተጨምሯል፡፡)

በአሁኑ ጊዜ ምዕራባውያን አፍሪካን ከአራቱ የምጽዓት ፈረሰኞች ለማዳን ሲባል ሁሉንም ዓይነት የምጣኔ ሀብት ጉባኤዎች እና የማስመሰያ ሸፍጦች በመተግበር ላይ ይገኛሉ፡፡

ኋላቀር የሆኑትን አፍሪካውያንን ሀብታም ለማድረግ ሲባል በቅርቡ “ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ለልማት ጉባኤ” በሚል ርዕስ የተካሄደው ጉባኤ አንዱ የሸፍጡ ማሳያ መንገድ ነው፡፡

በጣም ወጣት በነበርኩበት ጊዜ እነዚህ ምዕራባውያን (ነጮች) ህዝቦች ለምንድን ነው ሀብታሞች ሲሆኑ አፍሪካውያን ህዝቦች ደግሞ ደሀ የሚሆኑት በማለት በእድሜ ታላላቅ ነበሩትን ሰዎች እጠይቅ ነበር፡፡ በምዕራብ የሚኖሩ ህዝቦች በአፍሪካ ከሚኖሩ ህዝቦች የተሻለ ህይወት ይኖራሉ፡፡ እነዚህ ምዕራባውያን እያንዳንዱን ሰው ሊያስቀኑ የሚችሉ ሁሉም ዓይነት የፍጆታ ዕቃዎች አሏቸው፡፡ ህይወታቸውን ቀላል ለማድረግ የሚያስችሉ አውሮፕላኖች፣ ባቡሮች እና መኪኖች አሏቸው፡፡ አፍሪካውያን እራሳቸውን ለማኖር ያህል የሚያቆዩአቸው ባለአራት እግር እንስሳት አሏቸው፡፡ በምዕራብ የሚኖሩ ህዝቦች ከፍተኛ የሆነ የኑሮ ደረጃ አላቸው፡፡ አፍሪካውያን በረሀብ፣ በቸነፈር፣ ሊወገዱ በሚችሉ የባክቴሪያ ወረርሽኝ በሽታዎች፣ በደካማ የንጽህና አያያዝ፣ ወዘተ ይሞታሉ፡፡ ይህ ድርጊት በምንም ዓይነት መንገድ ሊቀየር የማይችል የሰይጣን ድርጊት ከሆነ የሚገርመኝ ሊሆን አይችልምን?

ለዚህ የሚሆን መልስ  በሚያስደንቅ መንገድ አግኝቻለሁ፡፡ የዕድሜ ታላላቅ ሰዎች በቀልድ መልክ እግዚአብሔር ሰውን ከጭቃ ሰራው በማለት ነግረውኛል፡፡ ነጭ ሰው የሚፈጠርበት ሰዓት በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር እጁን በመታጠብ ነጩን (ፈረንጁን) እንደገና መስራት ጀመረ፡፡ ለዚህም ነው ጥቁር አፍሪካውያን ድሆች እንደሆኑ የሚኖሩት እና ነጮች ደግሞ ሀብታሞች በመሆን እየኖሩ ያሉት ብለዋል፡፡ ይህም አባባል በአማርኛው ቋንቋችን “ታጥቦ የሰራቸው” እየተባለ ሲነገር ይደመጣል፡፡

ወደኋላ መለስ ብሎ ሲታይ ቀደም ሲል ሲነገሩ የነበሩት የተለያዩ አፈታሪኮች ለእኔ ምንም የማይፈይዱ አባባሎች ናቸው፡፡

ኢትዮጵያ በአውሮፓ ቅኝ ገዥዎች አገዛዝ ስር በፍጹም ተንበርክካ አታውቅም፡፡ በእርግጥ ዳግማዊ ምኒልክ ዘመናዊውን የአውሮፓን (ጣሊያንን) ወታደር እ.ኤ.አ በ1896 አይቀጡ ቅጣት በመቅጣት እብሪተኛው ቅኝ ገዥ ያለቀው አልቆ የተረፈው ጅራቱን በእግሮቹ መካከል በመወተፍ ወደመጣበት እንዲፈረጥጥ ያደረጉ የመጀመሪያው የአፍሪካ መሪ ናቸው፡፡ ዳግማዊ ምኒልክ ይህንን ድል ከመቀዳጀታቸው ከሁለት ዓመታት ቀደም ብሎ እ.ኤ.አ በ1894 የአውሮፓ ኃያላን ቅኝ ገዥዎች አፍሪካን እንደ ቅርጫ ስጋ ለመቀራመት በማሰብ የበርሊንን ጉባኤ አካሄዱ፡፡ አፍሪካ የጸረ ቅኝ ግዛት እንቅስቃሰዋን እስካራመደችበት እ.ኤ.አ በ1960ዎቹ የመጀመሪያዎቹ ዓመታት አካባቢ ድረስ የአውሮፓ ቅኝ ገዥዎች አፍሪካን እንደ ግል ንብረት ሲጠቀሙባት ቆይተዋል፡፡ እ.ኤ.አ ጥቅምት 1935 የኢትዮ-ጣሊያን ሁለተኛ ዙር ጦርነት ቢጀመርም ኢትዮጵያ በጀግኖቿ አርበኞቿ አይበገሬነቷን በማሳየት ማንም የማይነካት ነጻ ሀገር ሆና ቆይታለች፡፡

ጥቂት ሀገሮች ለምን ሀብታም እንደሚሆኑ እና ሌሎቹ ደግሞ ለምን ድሆች እንደሚሆኑ የመጀመሪያ ዲግሪ ተማሪ በነበርኩበት ጊዜ ለኢኮኖሚክስ ፕሮፌሰር መምህሬ አንድ ጥያቄ አቅርቤላቸው ነበር፡፡ በአሁኑ ጊዜ ላስታውሰው የማልችል ማብራሪያ ሰጥተውኝ ነበር፡፡ ሆኖም ግን የአዳም ስሚዝን መጽሀፍ እንዳነብ ሀሳብ ሰጥተውኝ እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡

“የሀገሮች ሀብት/The Wealth of Nations“ የተባለውን እጅግ በጣም ታዋቂ ስራ የሆነውን እና ግልጽነት እና ምሁራዊ ክህሎት የተንጸባረቀበትን የአዳም ስሚዝን መጽሀፍ ማንበቡን ተጋፈጥኩት፡፡

ከዌልዝ ኦፍ ኔሽንስ መጽሀፍ ያገኘሁት ነገር የሀገሮች ሀብት ውጤት ከህብረተሰቡ የስራ ክፍፍል በመመንጨት ምርትን ከፍ እንዲል ያደረገው መሆኑን ነው፡፡ የኢንዱስትሪ የምርት የስራ ክፍፍል ሀብትን ለመፍጠር (የሀብትን መደለብ ለመፍጠር) ዋናው ቁልፍ መሳሪያ ነው፡፡ የተከማቸው ሀብት እንደገና ሌላ ሀብት ለመፍጠር ወደ ልማታዊ ተግባር ሲውል የምርታማነትን አቅም በማሳደግ፣ ገበያን በማስፋት፣ የቴክኖሎጂ ፈጠራን እና የስራ ቅልጥፍናን በመጨመር የበለጠ ሀብት እንዲፈጠር ያስችላል፡፡

የስራ ከፍፍልን መሰረት ያደረገ የምጣኔ ሀብት የሰዎችን ቁጥጥር እና ጣልቃገብነት አይሻም በሚለው በአዳም ስሚዝ የክርክር ጭብጥ ላይ ግራ ተጋብቸ ነበር፣ ምክንያቱም በስውር እጆች/Invisible hands አማካይነት እራሱን በእራሱ ይቆጣጠራልና፡፡ አዳም ስሚዝ ድምጻቸውን ከፍ በማድረግ እንዲህ በማለት ተናግረው ነበር፣ “እራሳችንን በእራሳችን እናስተናግዳለን፣ ይህንን የምናደርገው ለእነርሱ ሰብአዊነት በማሰብ አይደለም ሆኖም ግን በእነርሱ ፍቅር ነው እንጂ ስለእኛ ፍላጎቶች በፍጹም ከእነርሱ ጋር መነጋገር የለብንም፣ ሆኖም ግን መነጋገር ያለብን ስለእነርሱ ጥቅሞች ነው፡፡“

“ስውር እጆች/invisible hands” የሚለውን ሀረግ ግለሰባዊ ፍላጎት (ውስጣዊ ስግብግብነት ልበለው?) እና የጋራ ጥቅሞችን በማሟላት ረገድ እልባት የሚሰጥ ብዬ ተርጉሜዋለሁ፡፡ በሌላ አባባል እያንዳንዱ ግለሰብ የእራሱን ካፒታል እና ጉልበት በመጠቀም ታላቅ ዋጋ ያለውን ዕቃ ለእራሱ በማምረት ሀብታም ይሆናል፡፡ በገበያ ውድድር መሰረት ስውር እጅ ባልታቀደ እና ባልታሰበ ሁኔታ ስራውን እየሰራ ህብረተሰቡ ተጠቃሚ ይሆናል፡፡

አብዛኛው የአፍሪካ ህዝብ በገጠር የሚኖር ከመሆኑ አንጻር እና በድህነት ኑሮውን በግብርና ላይ በመመስረት እየገፋ በሚኖርበት ሁኔታ እና የምርት የልውውጥ ስርዓቱ ዕቃ በዕቃ እና ዘመናዊ የግብይት ስርዓት በማይታወቅበት ሁኔታ ይኸ ሁሉ ነገር ለአፍሪካ ምን ማለት ነው? አፍሪካ ከድህነት ማጥ ውስጥ በመውጣት በኢንዱስትሪ የበለጸገች አህጉር የምትሆነው በምን ዓይነት መንገድ ነው? የአፍሪካ ሀብት ወደ ኢንዱስትሪ በመሸጋገር አፍሪካውያን ወደ ሀብታምነት የሚሸጋገሩት እንዴት ነው?

“እያንዳንዱ ሰው እንደ ችሎታው እንደሚያበረክት እና እያንዳንዱ ሰው እንደ ፍላጎቱ የሚያገኝ” መሆኑን ዘግይቸ በኋላ ነው የተገነዘብኩት፡፡

ካርል ማርክስ እንዲህ በማለት የክርክር ጭብጣቸውን አቅርበው ነበር፣ “በስራ ክፍፍል አማካይነት እያንዳንዱ ግለሰብ ለባርነት ጥገኛ መሆኑ ከተወገደ በኋላ የአዕምሮ እና የአካል ጉልበት ይጠፋል፡፡ የሰው ጉልበት ለመኖር ዋስትና ከመሆኑም በተጨማሪ የህይወትን ዋና ፍላጎት ማርኪያም እንደሆነ እንዲሁም የምርት ኃይሎች እየዳበሩ በሄዱ ጊዜ እና ሁለገብ ልማትን በሚያስገኙበት ጊዜ እንዲሁም በጋራ የተመረተው ምርት ለህዝቡ ጥቅም በከፍተኛ ሁኔታ ወደ ህዝቡ በሚፈስስበት ጊዜ የቡርዥዋው መብት ሙሉ በሙሉ የሚቋረጥበት እንዲሁም የብዙሀኑ ህዝብ መብት እና ጥቅም የሚጠበቅበት እንዲህ የሚለው አባባል እውን ይሆናል፡ ለእያንዳንዱ እንደ ችሎታው፣ ከእያንዳንዱ እንደ ፍላጎቱ“ (አጽንኦ ተጨምሯል፡፡)

ለምርት መትረፍረፍ ሞተር የሆነው የአዳም ስሚዝ የስራ ክፍፍል ወደ ማርክስ የባርነት ሰለባ ሊቀየር የሚችለው እንዴት ነው?

ደህና “በዓለም አቀፍ ገንዘብ ለልማት ማሰባሰብ ጉባኤ” ላይ የቀረበው የፖለቲካ ኢኮኖሚ ችግር እንግዲህ ይህንን የሚመስል ነው፡፡ ለአፍሪካ የሚሰባሰበው ዓለም አቀፍ ካፒታል እንዴት ነው በአንድ ጊዜ ከድህነት ማጥ ውስጥ እና የአፍሪካን ህዝቦች ከባርነት ሊያወጣ የሚችል መሳሪያ ሊሆን የሚችለው?

እ.ኤ.አ ሀምሌ 2015 አጋማሽ በአዲስ አበባ የአፍሪካ አምባገነኖች እና የእነርሱ የምዕራብ አዳኞቻቸው አፍሪካን ከእራሷ ለመከላከል እንደገና ጉባኤ አካሂደው ነበር፡፡ ዓለም አቀፍ ፋይናንስ  በማሰባሰብ እና ካፒታል በመፍጠር አፍሪካን በልማት እናበለጽጋለን በማለት ጠንካራ ኃይሎችን በማሰባሰብ በአዲስ አበባ ጉባኤ ተካሂዶ ነበር፡፡

አውሮፓ አፍሪካን እንዴት እንዳደኸያት ሮድኔይ ካቀረቡት ሀሳብ ጀምሮ እንደገና ዓለም አቀፍ ካፒታሊዝም ሽግግሩን ለማካሄድ እንደገና እያገረሸ ነውን?

የዓለም አቀፉ ካፒታሊዝም የትርፍ ጉጉት እ.ኤ.አ በ2015 በአፍሪካ ድሀ ህዝቦች የቁስ እና የማህበራዊ ፍላጎቶች ላይ ቀስ እያለ የማጥላት ስራውን መቀጠሉ ነውን?

“ገንዘብ ለልማት” አፍሪካን ከእራሱ ለመከላከል እና የበለጸገች አፍሪካ ለመፍጠር የተገባውን ቃልኪዳን ለማደስ የአውሮፓውያን ታምራዊ ስራ ነውን?

የሮድኔይ ቃላት እንደገና በ21ኛው ክፍለ ዘመን በሁለተኛው አስርት ዓመታት በአፍሪካ ላይ አዲስ ህይወት ለመፍጠር እንዲህ የሚለውን አባባል እውን ለማድረግ የታሰበ ይመስላል፡ ለጥቂት ግለሰቦች ትርፍ ማጋበስ ሲባል የብዙሀኑን ህዝብ ደህንነት ሊጎዳ በሚችል መልኩ የካፒታሊስት ስርዓት እየተጠናከረ ሊሄድ ችሏል…

ፖይንት ፎር ፕሮግራም በኢትዮጵያ/Point Four Program in Ethiopia

ፋይናንስ ለልማት ዓለም አቀፍ ጉባኤ ከመካሄዱ በፊት ፖይንት ፎር የተባለው የዩኤስ ጉባኤ ታከሂዶ ነበር፡፡

የአሜሪካ ዓለም አቀፍ ድህነትን የመዋጋት ጉባኤ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲካሄድ በነበረበት ጊዜ እኔ ገና ትንሽ ልጅ ነበርኩ፡፡

በቀዝቃዛው ጦርነት ጊዜ ፖይንት ፎር ፕሮግራም የርዕዮት ዓለም መሳሪያ ነበር፡፡ እ.ኤ.አ በ1951 የትሩማን አስተዳደር እና የኢትዮጵያ ንጉሰ ነገስት መንግስት “የቴክኒክ እውቀትን እና የእጅ ጥበብ ሙያዎችን እና ሌሎችንም በመለዋወጥ እርስ በእርስ ለመተባበር” የሚል ስምምነትን በመፈራረም የሀገሪቱን ሀብት እና የኢትዮጵያን የማምረት አቅም በማቀናጀት የተመጣጠነ እና ሁለገብ ልማትን ያመጣል የሚል ዓላማን ሰንቆ የተነሳ ነበር፡፡

ፕሮግራሙ የመስክ ባለሙያዎችን በኢትዮጵያ እና በሌሎች በሶስት ደርዘን በሚቆጠሩ ሀገሮች ላይ የግብርናን ምርት ለማሳደግ እና የምጣኔ ሀብቱን ለማሻሻል የቴክኒክ ድጋፍ መስጠት በሚል ዓላማ አሰማራ፡፡ በተለይም ደግሞ የሰብል ተባዮችን ለማጥፋት እና በገጠሪቱ ኢትዮጵያ የወባ በሽታን ለመቆጣጠር እና ለማጥፋት ዲዲቲ በስራ ላይ ውሎ እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ ከደበዘዘው ትውስታዬ የጸረ ወባ በሽታ ፕሮግራሙ የተሳካ ይመስለኛል፡፡ ከዓመታት በኋላ ዲዲቲ በሰውነት ላይ ካንሰርን ሊያመጣ እንደሚችል ተነገረ፡፡ በአሁኑ ጊዜ የወባ በሽታ በአፍሪካ ከሚገኙ ዋና ዋና ገዳይ በሽታዎች መካከል አንዱ ሆኖ እንደቀጠለ እና ከ5 ዓመታት በታች ላሉ ህጻናት ዋና የሞት መንስኤ ሆኖ ይገኛል፡፡ ቢሊየነር የሆኑት ቢልጌትስ  የወባ በሽታን፣ ኤች አይቪ ኤይድስን እና የሳንባ ነቀርሳን ከአፍሪካ እና ከሌሎች የዓለም ክፍሎች ለማስወገድ በየዓመቱ ከ4 ቢሊዮን ዶላር በላይ ወጭ ያደርጋሉ፡፡

“ዘላቂ ልማት” እና ድህነትን ከአፍሪካ ማስወገድ፣

በእንግሊዝኛ መዝገበ ቃላት ውስጥ “ዘላቂ ልማት” እንደሚለው ሀረግ የምጠላው ምንም ዓይነት ነገር የለም፡፡ የጆርጅ ኦርዌልን አባባል በመዋስ “ዘላቂ ልማት” እውነትን በመደምሰስ ውሸት ለመዋሸት እና ድህነትን ለማጥፋት እና ብልጽግናን ለማምጣት እየተባለ ነፋስን ለመጨበጥ እየተደረገ ያለ የቅጥፈት የፖለቲካ ቋንቋ ነው፡፡

ይኸ ሀረግ እ.ኤ.አ በ1992 ሲፈጠር እንዲህ የሚሉትን ሶስት ነገሮች በአንድ ጊዜ ያሳካል ከሚል ዓላማ በመነሳት ነበር፡ “የአካባቢ ማገገም/መታደስ፣ ማህበራዊ እድገት እና የምጣኔ ሀብት ልማት” የሚሉት ነበሩ፡፡”

ይህ ዘላቂ ልማት የሚለው ሀረግ እ.ኤ.አ በ2015 ምን ለማለት እንደተፈለገ እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ ሆኖም ግን ከማንኛውም የአፍሪካ አምባገነን እና ከዓለም አቀፍ የድህነት አቃጣሪዎች ከንፈር ላይ በተከታታይ ጠብ ሲል ይደመጣል፡፡

ከዓለም አቀፍ አበዳሪ እና ለጋሽ ድርጅቶች በየጊዜው የተያዘው አባዜ “ዘላቂ ልማት፣ ዴሞክራሲ እና መልካም አስተዳደር” የሚሉት በምላስ በየዕለቱ የሚነበነቡ በተግባር ግን የማይሞከሩ የኮሰሱ ሀረጎች ናቸው፡፡

የ”ፋይናንስ ለልማት” ታሪክ የተጀመረው እ.ኤ.ኤ በ2002 ሲሆን የገንዘብ ስምምነት/Monetary Consensus እየተባለ ከሚጠራው እና “ዘላቂነት ልማትን ለማስፋፋት” የሚል ዓላማን ለማሳካት ነው፡፡

እ.ኤ.አ ሀምሌ 2015 በአዲስ አበባ የተካሄደው 3ኛው ጉባኤ ዓላማ የዶሀ የገንዘብ ስምምነት እና መግለጫን አፈጻጸም ለመገምገም እና ይህንን ዕቅድ ለማሳካት እንቅፋት ሆነው የቀረቡትን መሰናክሎች እና ችግሮች ለይቶ በማውጣት መፍትሄ ለመፈለግ እና አዲስ እና በቀረቡ ጉዳዮች ላይ ለመወያየት ነው፡፡

የፋይናንስ ለልማትን ጎማ መፍጠር፣

እ.ኤ.አ በ1990ዎቹ ሁለተኛ አጋማሽ አካባቢ የኤሲያ ሀገሮችን የፋይናንስ ቀውስ ተከትሎ በተባበሩት መንግስታት የንግድ እና ልማት ጉባኤ (ተመንል)/UN Conference on Trade and Development (UNCTAD)፣ የአውሮፓ ኃያላን እና የዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት የዓለም አቀፉን የገንዘብ ድርጅት/IMF፣ የዓለም ባንክ እና የዓለም ንግድ ድርጅትን ጨምሮ በአፍሪካ እና በሌሎችም በመልማት ላይ ባሉ ሀገሮችን የምጣኔ ሀብቶች ለማዳን በሚል የይስሙላ የሆነ ተልዕኮን በማራመድ ላይ ይገኛሉ፡፡ በዓለም አቀፍ የፋይናንስ የምጣኔ ሀብቶች ስርዓት እና በዓለም አቀፋዊነት ላይ በራስ መተማመንን መመለስ የሚል አዲስ ስምምነት ፋሽን አድርገው ይዘዋል፡፡

የመጀመሪያው ዓለም አቀፍ ፋይናንስ ለልማት ጉባኤ እ.ኤ.አ መጋቢት 2002 በሞንቴሬይ ሜክሲኮ ውስጥ ተካሂዷል፡፡

የመጀመሪያው ዓለም አቀፍ ፋይናነስ ለልማት ጉባኤ የተዘጋጀው ቁልፍ ለሆኑ የፋይናንስ እና የልማት ጉዳዮች ተገቢውን ምላሽ ለመስጠት ነበር፡፡ ያንን ጉባኤ 50 የመንግስታት መሪዎች ከ200 በላይ ሚኒስትሮች፣ በመንግስታት መካከል ያሉ የፋይናንስ ተቋማት መሪዎች፣ የምጣኔ ሀብት፣ የሰቪል ማህበረሰብ እና የገንዘብ ድርጅቶች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡ በዚያ ጉባኤ ላይ አዲስ ዓለም አቀፋዊ ፋይናንስ ለልማት አካሄድን የሚተገብር ዓላማን የሰነቀ የገንዘብ ስምምነት/Monetary consensus አውጥተዋል፡፡ የገንዘብ ማሰባሰቡን ዓላማ ለማሳካት የሀገር ውስጥ ሀብትን ለልማት ማሰባሰብ፣ ዓለም አቀፍ ሀብትን ለልማት ማሰባሰብ፣ ቀጥታ የውጭ መዋዕለ ንዋይን ማፍሰስ እና ሌሎችን የግል የሀብት ፍሰትን ማፋጠን፣ ዓለም አቀፍ ንግድን ለልማት ማዋል ዋና ሞተር መሆኑን፣ ቀጣይነት ያለው ዓለም አቀፍ የፋይናንስ እና የቴክኒካዊ የልማት ስምምነቶችን መዋዋል፣ ስለውጭ ዕዳ፣ ስልታዊ ለሆኑ ጉዳዮች ምላሽ መስጠት፡ ዓለም አቀፍ የገንዘብ እና የንግድ ስርዓቶች ልማትን በሚደግፉ መልኩ ማሳደግ የሚሉት ይገኙባቸዋል፡፡

በስምምነቱ ላይ ዋናው ዓላማ የነበረው የፋይናንስ ፍሰቱ ስምምነት ለተደረሰባቸው ቀጣይነት ያላቸው ዓላማዎች ጠቀሜታ እንዲውል፣ ውሱን ለሆነ ሀገር ልዩ ፍላጎት ማሳኪያ ዓላማዎች እንዳይሆን ተደርጎ የተዘጋጀ ነበር፡፡ አንድ ወጥ የሆነ የልማት ስልት ነበር፡፡

ሁለተኛው ዓለም አቀፍ ፋይናንስ ለልማት ጉባኤ እ.ኤ.አ በ2008 ዶሀ በኳታር ውስጥ ተካሂዷል፡፡ የዚያ ጉባኤ ዓላማ በአንደኛው የፋይናንስ ጉባኤ ላይ የተወሰኑትን ዓላማዎች ለማስፈጸም ያለመ ነበር፡፡ ሁለተኛው ጉባኤ እንዲህ የሚል ማጠቃለያ ሰጥቷል፡ የፋይናንስ አፈጻጸሞች በአብዛኛው ባይሆንም አማካይ የሆነ አፈጻጸም አስመዝግበዋል፡፡ በመንግስታት የሚደረጉ የውጭ እርዳታዎችን ለማሳደግ ጥረት ተደርጓል፣ ሆኖም ግን በተጨባጭ ሲታይ በጣም አሳዛኝ ነበር፡፡ በአሁኑ ጊዜ የእርዳታን ገንዘብ በዓለም አቀፍ ደረጃ በየዓመቱ 150 ቢሊዮን ዶላር በማድረስ እ.ኤ.አ በ2015 የሚሊኒየሙን የልማት ዕቅዶች ለማሳካት አጠራጣሪ ነገር ነው፡፡

ባለፈው ዓመት በዓለም ላይ በኢንዱስትሪ የበለጸጉ ሀገሮች የኢንዱስትሪ ምርት ዝግመታዊ ዕድገትን እያሳዬ በመምጣቱ እና የዋጋ ግሽበትም በከፍተኛ ሁኔታ እያሻቀበ በመምጣቱ ዓለም አቀፍ የገንዘብ ገበያዎች በታላቅ ችግር ውስጥ ታንቀው ቆይተዋል፡፡

ከሞንቴሬይ ጉባኤ ጀምሮ የምጣኔ ሀብት የኃይል ሚዛን የቻይና እና የህንድ የምጣኔ ሀብቶች ማደግ ምስጋና ይግባው እና በማደግ ላይ ወዳሉ ሀገሮች አዘንብሏል፡፡

እነዚህ ዕድገቶች የሚያመላክቱት ነገር ቢኖር የእነዚህ የታዳጊ ሀገሮች ውጤቶች በሞንቴሬይ ከተደረገው ጉባኤ በላይ በዶሀ በተደረገው ሁለተኛው ዓለም አቀፍ ጉባኤ ላይ የበለጠ የተሻለ አፈጻጸምን አስመዝግበዋል፡፡ (አጽንኦ ተጨምሯል፡፡)

በአዲስ አበባ የተካሄደው ሶስተኛው ዓለም አቀፍ ፋይናንስ ለልማት ጉባኤ የድርጊት አጀንዳ ረዥም እና በባዶ ተስፋ እና መግለጫዎች የታጀበ እና ውሱን የሆኑ የአጭር ጊዜ የድርጊት መርሀ ግብሮችን ያላካተተ ነው፡፡

የመንግስታት መሪዎች እና ተወካዮች የፖለቲካ ተነሳሽነታቸውን እንደገና በማደስ በጠንካራ መሰረት ላይ ለመጣል እና በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚደረገውን የፋይናንስ ማሰባሰብ ተግዳሮቶች በዓለም አቀፋዊ ትብብር እና መደጋገፍ በጋራ በማስወገድ ሁሉን አቀፍ የሆነ ዓለም አቀፋዊ ልማትን ማምጣት በሚለው መንፈስ መንቀሳቀስ እንዳለባቸው አጽንኦ ሰጥቷል፡፡

በዚህ ጉባኤ ላይ እንደዚህ የሚሉ ቃል ኪዳኖችም ገብተዋል፡ ሁሉንም የሰብአዊ መብቶች ማክበር፣ የጾታ ዕኩልነት እና ሴቶችን እና ልጃገረዶችን ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ትኩረት ተሰጥቷል፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሰላምን በማስፈን እና ሁሉን አቀፍ ልማት ለሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች በማምጣት ፍትሀዊነት የነገሰበት የምጣኔ ሀብት የሰፈነበት ስርዓት ለማምጣት ጥረት እንደሚደረግ ቃል ኪዳን ገብተዋል፡፡

በጣም ውሱን ናቸው ከሚባሉት ውስጥ የሚከተሉት ቃልኪዳኖች ይጠቀሳሉ፡ የማህበራዊ አገልግሎቶች ጥበቃ እና ለህዝብ በጣም አስፈላጊ የሆኑ አገልግሎቶች በተለይም በአደጋ ላይ ላሉ፣ የአካል ጉዳት ሰለባ ለሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች፣ ለዘመናት በአካባቢያው ለሚኖሩ የህብረተሰብ ክፍሎች፣ ለልጆች፣ ለወጣቶች እና ለአዛውንቶች ልዩ ትኩረት በመስጠት የሚከናወን ይሆናል ይላል፡፡

ረሀብን ለማስወገድ እና የምግብ ንጥረ ነገር እጥረትን በከተሞች ባሉ የህብረተሰብ ክፍሎች ላይ ተንሰራፍተው የሚገኙትን በመዋጋት ቀደም ሲል ይደረጉ የነበሩ ጥረቶችን በመጨመር ከቀድሞው በበለጠ መልኩ ከፍተኛ የሆኑ ጥረቶች ይደረጋሉ፡፡

በአሁኑ ጊዜ በብዙሀን እርዳታ ሰጭ መንግስታት መካከል ያሉትን የትብብር አድማሶች በማስፋት እና የአካሄድ መንገዶችን በመቀየር በብዙሀን ድርጅቶች የልማት ባንኮች በሚመራው በመሰረተ ልማት አውታሮች ላይ የሚደረገውን ድጋፍ የበለጠ በማጠናከር በዚህ ዘርፍ ላይ ይታይ የነበረውን ክፍተት ለማጥበብ ጥረት ይደረጋል፡፡

ዋና ዋና ተግዳሮቶችን ማለትም የምጣኔ ሀብት ዕድገት፣ የስራ አጥነት ችግሮችን በማስወገድ እንዲሁም ሀብትን እና ኃይልን ውጤታማ በሆነ መልኩ በመጠቀም የአካባቢ ብክለትን እና የአየር ለውጥ ችግርን በማስወገድ፣ ዕውቀትን ለሌሎች በማካፈል፣ ፈጠራን እና ማህበራዊ ተሳትፎን በማሳደግ ሁሉን አቀፍ እና ዘላቂነት ያለው የኢንዱስትሪ ልማት ለማምጣት ጥረት ይደረጋል፡፡

የተሟላ እና ምርታማ ስራን በማጎልበት እና ለሁሉም ተስማሚ የሆነ የስራ ከባቢ አየር በመፍጠር ዝቅተኛ፣ መካከለኛ እና ከፍተኛ የሆኑ የምርት እና አገልግሎት ሰጭ ድርጅቶችን በማሳደግ ከዚሁ ጎን ለጎንም በቂ የልማት ስልጠናዎችን በተለይም ለወጣቶች እና ለስራ ፈጣሪዎች በማቅረብ ከፍተኛ የልማት ስራዎች የሚከናወኑ ይሆናል፡፡

የውሃ እና የየብስ ስነምህዳሮችን በመጠበቅ ብክለትን በመቀነስ እና የአየር ሁኔታ ለውጥን፣ በረሀማነትን እና የመሬትን መራቆት በመዋጋት የአካባቢ ስነምህዳሮችን በተሟላ ሁኔታ እንዲጠበቅ ይደረጋል፡፡

እንደዚሁም ሁሉ መልካም አስተዳደርን፣ የሕግ የበላይነትን፣ የሰብአዊ መብት ጥበቃን፣ መሰረታዊ የሆኑ ነጻነቶችን፣ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች እኩል የፍትሀዊ ስርዓት ተጠቃሚ የሚሆኑበትን እና ሙስናን በመዋጋት፣ እና ሕገ ወጥ የገንዘብ ዝውውርን በማጥፋት ሰላማዊ እና ሁሉን አቀፍ ልማት ለሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ለማምጣት የተቀናጁ ጥረቶች ይደረጋሉ፡፡

ከዚህ በታች የሚከተሉት ዝርዝሮች የተባበሩት መንግስታት የንግድ እና ልማት ድርጅት፣ የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት፣ የዓለም ባንክ እና የዓለም ንግድ ድርጅት የሞንቴሬይ ጉባኤ ከተካሄደበት እ.ኤ.አ ከ2002 ጀምሮ ሲደግሙት እና ሲደጋግሙት የቆዩት ነገር ነው፡፡ ከዚህ ሌላ ምን አዲስ ነገር አለ!?

የፋይናንስ ለልማት አዲስ ልብሶች ራቁቱን የሄደ ዓለም አቀፋዊ ንጉስ?

በጣም በኩራት የተወጠረ እና ለምንም ነገር ደንታ የሌለው ንጉስ ሆኖም ግን በጣም የተዋቡ እና ድንቅ የሆኑ ልብሶችን እየለበሰ በስሩ ላሉት ህዝቦች ያሳያል፡፡ ንጉሱ ለሌላው ሰው የማይታይ ለእርሱ የሚሆን ካባ ሰርተን አናመጣለን ያሉ አጭህርባሪ  ልብስ ሰፊዎች ጋር ይስማማል፡፡ በተባለው መሰረት የተዘጋጀው ልብስ ከመጣ በኋላ ያንን ልብስ ለብሶ ህዝቡ በተሰበሰበበት አደባባይ ፊት ይንጎማለላል፡፡ በዚህ ጊዜ አንድ ህጻን ወደፊት በመሄድ ንጉሱ እራቁቱን መሆኑን በመጮህ ይናገራል፡፡ ንጉሱ እራሱን እንደገና ተመለከተ እና እራቁቱን መሆኑን ያይ እና አሁንም ይህንኑ ጀብዱን በመቀጠል እየተገላበጠ እራቁቱን ለህዝብ ይታያል፡፡

በዓለም አቀፍ ፋይናንስ ለልማት ዓለም አቀፋዊ ስራ ላይ ምርመር እና ትንተና ለመስጠት እስከቻልኩ ድረስ ምንም ነገር የሌለ መሆኑን አይቻለሁ፣ ሆኖም ግን በዓለም እና በአፍሪካ ደኃ ህዝቦች ላይ የሚፈጸም ማጭበርበር እና ተራ ማታለል ሆኖ ይገኛል፡፡

ለ15 ዓመታት ያህል የየሀገራቱ መንግስታት መሪ ተብዬዎች፣ ሚኒስትሮች እና ተወካዮች ምንም ዓይነት ተጨባጭነት ለሌለው እና ለታዕይታ ብቻ በዓለም አቀፍ የጉባኤ መድረክ ላይ በመቆም ያረጀውን የድህነት ፈረስ የቅጥፈት ቃል ኪዳኖችን በማዥጎድጎድ እንዲሞት ሲደበድቡት ይታያሉ፡፡ ዓለም አቀፋዊ አበዳሪ እና ለጋሽ ድርጅቶች ታላላቅ የታዕይታ ጉዳዮችን እያነሱ የኖሩትን እና አሮጌዎቹን ባዶ ቃልኪዳኖች በማዥጎድጎድ ያረጁ ቃልኪዳኖቻቸውን እንደገና በአዲስ ባዶ ቃልኪዳኖች እየሞሉ ለዘላቂ ልማት እና ለሌሎችም ተደጋጋሚ ትርጉምየለሽ ቅጥፈቶች ባተሌ ሆነው ይታያሉ፡፡

እ.ኤ.አ በ2008 የተካሄደው ዓለም አቀፍ ፋይናንስ ለልማት ጉባኤ ዋና መደምደሚያው እንዲህ የሚል ነበር፣ “የሞንቴሬይ ጉባኤ የዕቅድ ክንውን አፈጻጸሞች (እ.ኤ.አ በ2002 ለመጀመሪያ ጊዜ የተካሄደው) አጠቃላይ በሆነ መልኩ ሲታይ አማካይ በሆኑ መልኩ የተፈጸመ መሆኑን ያመላክታል፡፡“ ምክንያቱ ደግሞ ግልጽ ነው፡፡ ”የመንግስታትን የውጭ እርዳታ መጠን ለማሳደግ ቃልኪዳን ይገባል፣ ሆኖም ግን እውነታው ከምድር ወርዶ የሚታየው በጣም አስደንጋጭ ሁኔታ ነው፡፡“

እ.ኤ.አ በ2015 በተደረገው ጉባኤ ላይስ የሞንቴሬይ ጉባኤ የዕቅድ ክንውን አፈጻጸሞች በአብዛኛው ከአማካይ አፈጻጸም በላይ ሊሆኑ አልቻሉምን?

እ.ኤ.አ በ2015 በአፍሪካ በእርግጠኝነት ቃል በተገባው የእርዳታ መዋዕለ ንዋይ እና በተጨባጭ ከመሬት ላይ በወረደው መካከል ባለው ክፍተት ላይ ታላቅ ለውጥ ይታያልን?

ምዕራባውያን ሀገሮች በየዓመቱ 150 ቢሊዬን ዶላር የአፍሪካን ደሀ ህዝቦች እና ሌሎችን ታዳጊ ሀገሮች ለመርዳት የገቡትን ቃል ኪዳን በማክበር በዓለም አቀፍ ደረጃ ስምምነት የተደረሰባቸውን የሚኒሊዬም ግቦች ለማሳካት ችለዋልን?

ባንኪሙን የሚሊኒዬሙን የልማት ግቦች በማሳካቱ ረገድ በታሪክ ታይቶ በማይታወቅ መልኩ የጸረ ድህነት እንቅስቃሴ ያደረገ መሆኑን በመናገር ላይ ይገኛሉ፡፡ እ.ኤ.አ በ2000 ምዕራባውያን የሚሊኒዬም ግቦችን በማስቀመጥ የእኛን ወገኖች ወንዶችን፣ ሴቶችን እና ልጆችን ካስከፊ ድህነት እና ሰብአዊ ቀውስን ከሚያስከትለው አስከፊ የድህነት ሁኔታ ነጻ ለማውጣት ምንም ዓይነት ጥረት አላደረጉም፡፡

ስንቶቹ የአፍረካ ሀገሮች ናቸው የሚሊኒዬሙን የመጀመሪያውን ግብ አስከፊ ድህነትን እና ረሀብን ለማስወገድ የቻሉት?

እንደ አንድ የጥናት ትንተና ውጤት ዘገባ ከሆነ ከ153 ሀገሮች መካከል አስከፊውን ድህነት ያስወገዱት ሰባት ሀገሮቸ ብቻ ናቸው፡፡ በአፍሪካ ይህንን ግብ ለማሳካት የቻሉት ቦትስዋና እና ኢኳቶሪያል ጊኒ ብቻ ናቸው፡፡ ይህ ጥናት እንዲህ የሚል መደምደሚያ ሰጥቷል፣ “በድህነት ማጥ ውስጥ የሚኖሩትን የአፍሪካ ህዝቦች ቁጥር በግማሽ ለመቀነስ እ.ኤ.አ ከ2000-2015 ሌሎች የአፍሪካ ሀገሮች በሚያስደንቅ ሁኔታ በ7 በመቶ የምጣኔ ሀብት ዕድገት ፍጥነት ማደግ አለባቸው“ ብሏል፡፡

ስለእነዚህ ዓለም አቀፍ ጉባኤዎች እውነታው ለህዝብ ግንኙነት ስራ ሲባል ብቻ ለታዕይታ የሚሰሩ የመድረክ ላይ ተውኔቶች ናቸው፡፡

አበዳሪ እና ለጋሽ ድርጅቶች ስለዘላቂ ልማት ይነጋገራሉ፣ ሆኖም ግን እውነታው ተገልጦ ሲታይ የአስመሳይነት የመድረክ ላይ ተውኔታቸውን በመስራት የጠረጴዛ ላይ ውይይቶችን፣ ሴሚናሮችን እና መድረኮችን በመጠቀም እንዲሁም ንግግሮችን በማድረግ፣ ጋዜጣዊ መግለጫዎችን በመስጠት፣ ይፋ መግለጫዎችን ለህዝብ በመስጠት እና ማሳሰቢያዎችን በመልቀቅ፣ የአፈጻጸም ዘገባዎችን በማዘጋጀት፣ የሽርሽር ጉብኝቶችን እና ፓርቲዎችን በማዘጋጀት እራሳቸውን እና የእነርሱን ሎሌዎች ህልውና ዘላለማዊ በማድረግ ላይ ይገኛሉ፡፡ በመሰረቱ እርስ በእርሳቸው ይንሾካሾኩ እና ቀጣዩን የውሸት ዕቅድ በማቀድ ወደየቤታቸው ተመልሰው ይሄዳሉ፡፡

በኢትዮጵያ ድህነት በግማሽ ቀንሷልን?

በቅርቡ ከተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም/United Nations Development Program (UNDP) በወጣ መረጃ መሰረት በኢትዮጵያ ከድህነት ወለል በታች የሚኖሩት ህዝቦች ቁጥር እ.ኤ.አ በ1995/96 ከነበረበት 45.5 በመቶ እንደ እ.ኤ.አ በ2011/12 የዕድገት እና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ እስከጸደቀበት ጊዜ ድረስ ወደ ታች በመውረድ 27.8 በመቶ ሆኗል ፡፡ (የገንዘብ እና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር፣ 2011/12) ይኸ የሚያሳየው ባለፉት 16 ዓመታት ውስጥ ድህነት ከ38.9 በመቶ በመውረድ በከፍተኛ ደረጃ የቀነሰ መሆኑን ነው፡፡ ዩኤንዲፒ እንደዚህ ዓይነቱን መደምደሚያ የሰጠው በኢትዮጵያ ያለው አገዛዝ የስታቲስቲክስ ኤጀንሲ መስሪያ ቤት አዘጋጅቶ የሰጠውን አሀዝ በመጠቀም ነው፡፡ እውነት ነው አይደለም ለሚለው የችግሉ ሰለባ ለሆኑት ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እተወዋለሁ፡፡

በኢትዮጵያ ያለው አገዛዝ በሚያወጣው የስታቲስቲክስ አሀዝ ላይ እምነቱ የለኝም፡፡

ቀደም ሲል ከምንም ጥርጣሬ በላይ በተጨባጭ ለማሳዬት እንደሞከርኩት በኢትዮጵያ በህዝቦች ፈቃድ ሳይሆን በጠብመንጃ ኃይል ተንጠልጥሎ ያለው ገዥ አካል ባለሶስት ኮከቡ የሚሸሌን ሆቴል ቀቅሎ እንደሚያወጣው ምግብ ሁሉ በተመሳሳይ መልኩ አገዛዙም የምጣኔ ሀብት አሀዞችን በይስሙላው መስሪያ ቤቱ አማካይነት ቀቅሎ እንደሚያወጣው ለማስገንዘብ ሞክሪያለሁ፡፡

ገዥው አካል ባለፉት አስርት ዓመታት ባለሁለት አሀዝ የምጣኔ ሀብት ዕድገት አስመዝግቢያለሁ በማለት ሲቦስጥ እና ቡራ ከረዩ ሲል ቆይቷል፡፡ ይህንን መቦሰጥ ነጭ ውሸት እና ተራ ቅጥፈት የቁጥር ጨዋታ ነው በማለት ሳጋልጥ ቆይቻለሁ፡፡

የዩኤንዲፒ ዘገባ በተጨማሪ እንዲህ በማለት ዘገባውን ቀጥሏል፣ “በኢትዮጵያ የምግብ እህል ድህነት/እጥረት ወደ ታች ዝቅ ብሏል፡፡ የረሀብ አመላካች መለኪያዎች 3 የምግብ ንጥረ ነገር መለኪያዎችን በማካተት ማለትም የምግብ ንጥረ ነገር እጥረት፣ የህጻናት ክብደት መቀነስ እና የህጻናት ሞት እ.ኤ.አ በ1990 ከነበረበት 43.2% እ.ኤ.አ በ2010/11 ወደ 28.7% ወርዷል“ ይላል፡፡

ዩኤንዲፒ እንዲህ በማለት የማጠቃለያ ሀሳቡን ሰጥቷል፣ “በዚህ አፈጻጸም መሰረት ሀገሪቱ እ.ኤ.አ በ2015 24 በመቶ ለማድረስ ተይዞ ያለውን ግብ ለመምታት በቀሪዎቹ ሶስት ዓመታት ድህነትን በ3.8 በመቶ መቀነስ ይኖርባታል፡፡ ድህነት በገጠሩ አካባቢ በሚኖረው ህዝብ ላይ የበለጠ በከተማው ከሚኖረው ህዝብ በላይ ተንሰራፍቶ ይገኛል፡፡ ሆኖም በሁለቱ መካከል ያለው ልዩነት ባለፉት 16 ዓመታት ጊዜ ውስጥ (እ.ኤ.አ ከ1995/96 – 2011/12) በከፍተኛ ሁኔታ ቀንሷል፡፡“

ይህ ዓይነት አገላለጽ እና አጻጻፍ ትርጉምየለሽ ነው!

አሁን በህይወት የሌለው መለስ ዜናዊ በዋሽንግተን ዲሲ የኢትዮጵያ ኤምባሲ በመገኘት ለመጀመረሪያ ጊዜ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ (ከሩብ ምዕተ ዓመት አካባቢ በፊት) ላይ ለቀረበለት የግብ ዓላማ ጥያቄ መልስ ሲሰጥ የተሻለ የምጣኔ ሀብት ዕድገት እና ልማት እንዳለው አውጆ ነበር፡፡ በመቀጠልም መለስ የእርሱ መንግስት ስኬት የሚለካው ኢትዮጵያውያን በቀን ሶስት ጊዜ መመገብ ከቻሉ ብቻ ነው ብሎ ነበር፡፡ እ.ኤ.አ በ2011 ኩራትን በተላበሰ መልኩ እንዲህ ብሎ ነበር፣ “ዕቅዱን እጅግ በጣም የተትረፈረፈ ምርት በሚሰጥ መልኩ እ.ኤ.አ በ2015 ያለምንም የውጭ እርዳታ እራሳችንን ሙሉ በሙሉ ለመመገብ በሚያስችል መልኩ ከልስነዋል [የዕድገት እና ትራንስፎርሜሽኑን]“ ብሎ ነበር ድፍረትን በቀላቀለ ሁኔታ፡፡ ግሩም ነው ውሸትን በውሸት ላይ እየደረበ መኖርን ባህል አድርጎ የያዘ ስርዓት ሲዋሽ ውሎ ሲዋሽ ቢያድር አይደክመውም፡፡ እርግጥ ነው ተፈጥሮ በእራሱ ፈቃድ እንደሆነ ባያደርገው ኖሮ መለስ ያለምንም የውጭ እርዳታ እ.ኤ.አ በ2015 በምግብ እህል እራሳችንን እንደሚያስችለን ጥርጥር የለውም!

ዩኤንዲፒን፣ የዓለም ባንክን፣ የዓለም አቀፉን የገንዘብ ድርጅት እና ሌሎችን በኢትዮጵያ ስለኢኮኖሚ ዕድገቱ እየዋሹ የተሳሳተ የዕድገት አሀዝ እየሰጡ ያሉትን እና ድህነት ቀንሷል እያሉ የሚወተውቱትን ቀሪዎችን ድርጅቶች እና ግለሰቦች የሚከተሉትን ጥያቄዎች ላቀርብላቸው እወዳለሁ፡:

1ኛ) እ.ኤ.አ በ2015 አብዛኛው የኢትዮጵያ ህዝብ በቀን ሶስት ጊዜ በመመገብ ላይ ይገኛልን?

2ኛ) በአሁኑ ጊዜ አብዛኛው የኢትዮጵያ ህዝብ ከጥቂት ዓመታት በፊት ከነበረበት ሁኔታ በተሻለ ደረጃ ላይ ይገኛልን?

3ኛ) መለስ የዕድገት እና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱን እንደከለሰው እና እንደተናገረው ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ በ2015 ምንም ዓይነት የውጭ እርዳታ ሳያስፈልጋት እራሷን በእራሷ መመገብ ትችላለችን?

4ኛ) ስለኢትዮጵያ የምጣኔ ሀብት ዕድገት እና ስለድህነት ቅነሳው ያለው እውነተኛ ታሪክ ምንድን ነው?

ዘኢኮኖሚስት መጽሔት እ.ኤ.አ መጋቢት 2013 ባወጣው ዘገባ ግልጽ እንዳደረገው “በዓለም ላይ ፈጣን የምጣኔ ሀብት ከሚያስመዘግቡ ሀገሮች መካከል አንዷ ስለሆነችው ኢትዮጵያ” እውነታውን ቁልጭ አድርጎ በማውጣት እንዲህ የሚል ዘገባ አውጥቶ ነበር:፡ ዘኢኮኖሚስት መጽሔት እንዲህ በማለት ጽፏል፡:

የገዥው አካል ደጋፊዎች እንኳ መንግስት በሚያወጣቸው አሀዛዊ መረጃዎች ላይ እምነት የላቸውም፡፡ የግብርናው ዘርፍ ዓመታዊ ምርታማነት የመንግስት ይፋ የሆነ ምንጭ እንደዘገበው በግምት ከ5-6 በመቶ ይሆናል፣ ሆኖም ግን ሊሆን የሚችለው ከ2-3 በመቶ ነው፣ ይህም ሆኖ ጥሩ ዕድገትን አመላካች ነው ሊባል ይችላል፡፡ የውስጥ ምንጮች እንዲህ ይላሉ፣ “ባለስልጣኖች የዕቅድ ግብን ይጥላሉ፣ ከዚያ በኋላ እነርሱ ለመስማት የሚፈልጉት አሃዛዊ መረጃ እንዲሰጣቸው ያደርጋሉ፡፡ ዓለም አቀፍ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ገዥው አካል 11 በመቶ ዓመታዊ የሀገር ውስጥ ምርት ዕድገት በሚለው ላይ ይጠራጠራሉ፡፡ እነዚህ ባለሙያዎች ትክክለኛው የዕድገት መጣኔ እና ይህም ሆኖ አሁንም ጥሩ ነው የሚባለው ከ5-6 በመቶ ዕድገት ያስመዝግባል ይላሉ፡፡

ሌሎች ዓለም አቀፍ ምርምር የሚያካሂዱ ድርጅቶች ከዚህም የባሰ አስደንጋጭ እና አሳዛኝ እውነታዎችን ያቀርባሉ፡፡

እ.ኤ.አ በ2014 የኦክስፎርድ የድህነት እና የሰው ልማት ተነሳሽነት (ኦድሰልተ) ዘርፈ ብዙ የድህነት መለኪያ/Oxford Poverty and Human Development Initiative (OPHDI) Multidimensional Poverty Index) በቀድሞ አጠራሩ ዓመታዊ የተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም የሰዎች የድህነት መለኪያ/U.N.D.P Human Poverty Index) እየተባለ ይጠራ የነበረው ዓለም አቀፋዊ ድርጅት ኢትዮጵያ በፕላኔቱ ከሚገኙት ደኃ ሀገሮች ሁሉ በተከታታይ ለ4ኛ ጊዜ በድህነት በሁለተኛ ደረጃ ላይ እንደምትገኝ ዘገባ አቅርቧል፡፡ አዎ፣ በዓለም ላይ ሁለተኛዋ ደኃ ሀገር!

እ.ኤ.አ በ2010 ኦድሰልተ/OPHDI በኢትዮጵያ በአስከፊ ድህነት ላይ የሚገኘው ህዝብ ቁጥር  (በቀን ከአንድ ዶላር በታች የሚያገኘው ሰው) በመቶኛ ሲሰላ 72.3 በመቶ ነው የሚል ዘገባ አውጥቷል፡፡

የኦድሰልተ/OPHDI የ2014 ዓመታዊ የድህነት አሀዛዊ ዘገባ የበለጠ አስደንጋጭ ሁኔታን ያመላክታል፡፡ በገጠሪቱ ኢትዮጵያ የሚኖረው 82 በመቶ የሚሆነው ህዝብ በከተሞች ከሚኖረው እና 18 በመቶ ከሚሆነው ህዝብ በበለጠ ሁኔታ “በአስከፊ ድህነት” ውስጥ ይገኛል፡፡ እ.ኤ.አ በ2014 በኢትዮጵያ “በአስከፊ የድህነት” አደጋ ውስጥ ከሚኖረው ህዝብ መካከል በሚከተሉት ክልሎች ላይ ይገኛል፡ ሶማሊ (93%)፣ ኦሮሚያ (91.2%)፣ አፋር (90.9%)፣ አማራ (90.1%) እና ትግራይ (84.5%) ይሸፍናሉ፡፡

በኦድሰልተ/OPHDI መለኪያ መስፈርት መሰረት ድህነት ማለት ገንዘብ ማጣት ብቻ አይደለም፡፡

ድህነት በዋናነት መጥፎ የጤና አጠባበቅ፣ መጥፎ የትምህርት ስርዓት፣ መጥፎ የምግብ ሁኔታ፣ ከፍተኛ የሆነ የህጻናት ሞት፣ መጥፎ የውኃ አቅርቦት እና የኤሌክትሪክ አቅርቦት፣ እንዲሁም መጥፎ የቤት እና የንጽሀን ሁኔታ ነው፡፡

በኢትዮጵያ ዋና የድህነት መንስኤ የመልካም አስተዳደር እጦት ነው!

ባለፉት “አስር ዓመታት ውስጥ ባለሁለት አሀዝ የምጣኔ ሀብት ዕድገት ተመዝግቧል” እየተባለ የሚነዛው የቅጥፈት አባዜ እንዳለ ቢኖርም እንኳ ኢትዮጵያ በመጥፎ ሁኔታ ላይ ትገኛለች፣ እናም ለዚህም ነው ኢትዮጵያ በፕላኔቷ ከሚገኙት ሀገሮች በድህነት በሁለተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች እየተባለ ያለው!

የምዕራቡ ዓለም ፋይናንስ ለልማት አፍሪካን ከኋላቀርነት ሊያወጣት ይችላልን?

የምዕራቡ ዓለም ፋይናንስ ለልማት አፍሪካን ከኋላቀርነት በማውጣት የበለጸገች አህጉር እንድትፈጠር ያስችላል ብሎ ማሰብ ዘራፊ ቀማኛን የባንክ ዘብ በማድረግ የባንኩን ገንዘብ በታማኝነት ይጠብቃል ወይም ደግሞ ዝንጀሮ ተንተርክኮ የበሰለን ሙዝ ማንም እንዳይነካው እና እንዳይበላው ትጠብቃለች ከማለት ጋር መሳ ለመሳ ነው፡፡

የ500 ዓመታት የአፍሪካ ታሪክ እንዲህ ይላል፣ “የምዕራቡ ዓለም አፍሪካን በፋይናንስ በልማት መዋጮ ከነበረችበት ኋላቀርነት የሚያወጣት አሳሞች በአየር ላይ በሚበሩበት ጊዜ ነው፡፡”

ሮድኔይ የአውሮፓ እና የምዕራቡ ዓለም ባጠቃላይ አፍሪካን በፋይናንስ ለልማት ከኋላቀርነት መንጥቆ እንደማያወጣ የትንበያ ጥያቄ አቅርበው ነበር፡፡ ሮድኔይ እንዲህ በማለት ጽፈዋል፡:

የአውሮፓ ዜጎች የአፍሪካን መሬት እና የማዕድን ሀብት በሚይዙበት ጊዜ ይህ ድርጊት በጣም ቀጥተኛ በሆነ መንገድ የአፍሪካን አህጉር መጥባት ማለት ነው፡፡ በቅኝ ግዛት ጊዜ በወታደራዊ ኃይል የሚታገዘው እና የሚደገፈው አሸናፊ ስለነበር ባለቤቱ ማን እንደሆነ የታወቀ ነገር ነበር፡፡ በአሁኑ ጊዜ ግን ብዙዎቹ የአፍሪካ ሀገሮች የውጮቹ የባለቤትነት መብት እስከ አሁንም ድረስ አለ፣ የውጮቹ ወታደሮች እና ባንዲራዎች ቢወገዱም እንኳ፡፡ የውጭ ኃይሎች መሬቱን፣ የማዕድን ሀብቶችን፣ ፋብሪካዎችን፣ ባንኮችን፣ የኢንሹራንስ ኩባንያዎችን፣ የመጓጓዣ ዘዴዎችን፣ ጋዜጦችን፣ የኃይል ጣቢያዎችን፣ ወዘተ እስከተቆጣጠሩ ድረስ የአፍረካ ሀብቶች ወደ እነዚህ ሰዎች እጆች ከመፍሰስ አይድንም፡፡

የውጭ መዋዕለ ንዋይ በአፍሪካ ውስጥ መፍሰስ የተፈጥሮ ሀብቶችን እና የአፍሪካውያን ጉልበት ኢኮኖሚያዊ እሴትን በመፍጠር አህጉሪቱ ሀብቱን እንድታጣ ያደርጋል፡፡ የውጭ መዋዕለ ንዋይ ሁልጊዜ ለአፍሪካ መንግስታት በብድር መልክ የሚገለጥ ነው፡፡ በተፈጥሮ እነዚህ ብድሮች እንደገና ይከፈላሉ፡፡ እናም እ.ኤ.አ በ1960ዎቹ ለመንግስታት የተሰጡት ብድሮች የኋላ ቀር ሀገሮች ክፍያ በየዓመቱ ከ400 ሚሊዮን በዓመት ወደ 700 ሚሊዮን ዶላር እያደገ መጣ፡፡ በዚህም ሳያቆም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጣ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በእነዚህ ብድሮች እንደዚሁም በኢኮኖሚው በቀጥታ ኢንቨስት ከሚደረጉ ፕሮጀክቶች ትርፍ ላይ የሚከፈል የወለድ ክፍያም አለ፡፡ ከእነዚህ ሁለት ምንጮች ከኋላቀር ሀገሮች እ.ኤ.አ በ1965 ብቻ 500 ሚሊዮን ዶላር ወደ ውጭ እንዲወጣ ሆኗል፡፡ በእንደዚህ ዓይነት ጉዳዮች ላይ የሚሰጡ መረጃዎች ትርፍን በሚያጋብሱት ላይ መረጃ እንዳይወጣ አንቀው በመያዛቸው ምክንያት አልፎ አልፎ የተሟላ ይሆናል፡፡ ስለሆነም ከዚህ በላይ የቀረቡት አሃዛዊ መረጃዎች ዝቅ ተደርገው ቀርበው ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ እነዚህ አሃዛዊ መረጃዎች የአፍሪካ ሀብት መዋዕለ ንዋይ በሚያፈስሱ ሀገሮች አማካይነት እንዴት አድርጎ ወደ ውጭ እንደሚወጣ ቢያንስ ፍንጭ የሚሰጡ ሊሆኑ እንደሚችሉ እና አብዛኛዎቹን የአፍሪካውያንን የምርት መገልገያ መሳሪያዎች እንደሚይዙ የሀሳብ ፍንጭ ሊሰጡ ይችላሉ እንደሚችሉ ያመላክታሉ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ አሁን በቅርብ ጊዜ የመዋዕለ ንዋይ ፍሰቱ ቀስ ያለ እና አደገኛ ሁኔታን የሚያስከትል ነው፡፡ የአፍሪካ ኩባንያዎች አስተዳደር አልባ እያሉ የሚጠሯቸውን በማካተት በዓለም አቀፍ የካፒታሊስት ባለሙያዎች እንዲተዳደሩ ያደርጋሉ፡፡ (አጽንኦ ተጨምሯል፡፡)

ነገሮች ሁሉ እየተበላሹ እንደመጡ ሮድኔይ እነዚህን ቃላት እና ሀረጎች ጽፈዋል፡፡

እ.ኤ.አ በ2014 ዘኢኮኖሚስት የተባለው መጽሔት እንዲህ በማለት ጽፏል፡:

አፍሪካ ግልጽ በሆነ መልኩ ከአበዳሪዎቿ ማለትም፡ ከመንግስታት፣ ከዓለም ባንክ፣ ከአፍሪካ ልማት ባንክ እና ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ትበደራለች፡፡ በአሁኑ ጊዜ አብዛኛውን ብድር የምታገኘው ከግል ምንጮች ነው (ቻርቱን ይመልከቱ፡፡) የመንግስት ብድር እና እርዳታ ከፋሽንነት በመውጣት ላይ ነው፡፡ ከዚህ ይልቅ የአፍሪካን የወደፊት የመክፈል አቅም የሚፈታተነው በቦንድ ክፍያ፣ በግል ኢኩቲ መዋዕለ ንዋይ አፍሳሾች የግል መዋዕለ አፍሳሾች (የአፍሪካ መዋዕለ ንዋይ አፍሳሾችን ጨምሮ)  የመንግስት ዕዳን መግዛት የመሳሰሉት ናቸው፡፡ በአፍሪካ ከፍተኛ የግል ኩባንያዎች የሚያዙ የግል ዕዳ በቁልሉ ላይ ቁልልን ይጨምራል፡፡ ከኢትዮጵያ፣ ከሞዛምቢክ እና ከናይጀሪያ እንደዚሁም ባህላዊ በሆነ መልኩ ከምታትመው ደቡብ አፍሪካ ከፍተኛ የሆነ የኮርፖሬት ቦንድ ይታተማል፡፡ ኮርፖሬት ዕዳ አብዛኛውን ጊዜ በዶላር የጠቅላይነት ባህሪን ይይዛል፣ ይህም ደግሞ በየጊዜው የገንዘብ ከረንሲ መለዋወጥን ያስከትላል፡፡ በአሁኑ ጊዜ በርካታ መንግስታት በተለይ ሞዛምቢክን እና ጋናን ጨምሮ ከሀገራቸው ገንዘብ ይልቅ ዶላር የበላይነቱን በሚይዝበት ሁኔታ ቦንድ በማተም ላይ ይገኛሉ፡፡ ሆኖም ግን ለአፍሪካ በጣም ትልቁ የሚያስጨንቃት ነገር የግል ብደር ሁኔታ ነው፡፡ መንግስታት ከችግር ውስጥ ከወደቁ እና ዕዳዎቻቸውን ለመክፈል እንደገና ዕቀድ የሚያወጡ ከሆነ ወይም ደግሞ ትንሽ እየከፈሉ የበለጠ ለመበደር የመንግስታት አበዳሪዎች እንዲያበድሩ ይገደዳሉ፡፡ የግል አበዳሪዎች አስተማማኝ አይደሉም፡፡ (አጽንኦ ተጨምሯል፡፡)

ለአፍሪካ ኋላቀርነት ቀላል መፍትሄ፣

የምዕራቡ ዓለም አፍሪካን ፋይናንስ ለልማት በሚል መርህ ከኋላቀርነት ለማላቀቅ የሚፈልጉ ከሆነ አንድ ነገር ብቻ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡ ከአፍሪካ ሕገ ወጥ የገንዘብ ዘውውርን ማቆም፡፡ አራት ነጥብ!

እ.ኤ.አ በ2011 ግልሎባል ፋይናንሻል ኢንቴግሪቲ/Global Financial Integrity (GFI)  የተባለው ዓለም አቀፍ ድርጅት የሚከተለውን ዘገባ አቅርቦ ነበር፡:

ዓመታዊ የነፍስ ወከፍ ገቢዋ 365 ዶላር የሆነችው ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ በ2000 እና በ2009 ባሉት ዓመታት መካከል 11.7 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር በሕገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር ከሀገር እንዲወጣ ተደርጓል፡፡ እ.ኤ.አ በ2009 በሕገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር በጠቅላላ 3.26 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር እንዲወጣ በማድረግ ካለፉት ሁለት ዓመታት በሁለት እጥፍ ብልጫ ያሳየ ገንዘብ ከሀገር ውስጥ በህገ ወጥ መልክ ወጥቷል…

እ.ኤ.አ 2008 ኢትዮጵያ 829 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር በልማት ዕርዳታ ስም ተቀብላለች፣ ሆኖም ግን ይህ ገንዘብ በከፍተኛ ሕገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር እዲመነምን ሆኗል፡፡ የኢትዮጵያ ካፒታል ከሀገር ወደ ውጭ የሚያደርገው ፍልሰት ከፍተኛ የሆነ መጠንን እየያዘ በመሄድ እ.ኤ.አ ኢትዮጵያ ወደ ውጭ ከላከቻቸው ምርቶች ዋጋ 2 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር በመብለጥ በሕገ ወጥ መልክ ወደ ውጭ የወጣወው ገንዘብ 3.26 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ለመሆን በቅቷል፡፡

ግሎባል ፋይናንሻል ኢንቴግሪቲ (GFI) እንዲህ የሚል መደምደሚያ ሰጥቷል፣ “የኢትዮጵያ ህዝቦች ደማቸው በሙሉ እንዲመጠጥ ተደርጓል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ካለባቸው የከፋ ዕጦት እና ድህነት ለመውጣት በማሰብ ሕገ ወጥ የገንዝብ ዝውውርን በማካሄድ በወንዙ ላይ ወደ ላይ በመዋኘት ላይ ይገኛሉ፡፡“ (አጽንኦ ተጨምሯል፡፡)

አፍሪካ ማዕበል ከሚያመሰቃቅለው የኋላቀርነት ባህር ውስጥ በመውጣት በእራሷ መንገድ መዋኘት እንድትችል ከአፍሪካ በሕገ ወጥ መልክ ወደ ውጭ የሚወጣው ካፒታል ይቁም!

ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!

ሀምሌ 22 ቀን 2007 ዓ.ም

Similar Posts