የግል ደብዳቤ፡ ይድረስ ለፕሬዚዳንት ኦባማ፣

ከፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማርያም    

ትርጉም በነጻነት ለሀገሬ 

ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ

ኋይት ሀውስ

1600 ፔንሲልቫኒያ አቬኑ ኤንደብልዩ

ዋሽንግተን፣ ዲሲ 20500 

ውድ ፕሬዚዳንት ኦባማ፡

ሰላም ለእርስዎ ይሁን! ሚስተር ፕሬዚዳንት፡፡

በዚህ በያዝነው በሀምሌ ወር ሁለተኛው አጋማሽ ወደ ኢትዮጵያ በመጓዝ ከሀገሪቱ መንግስት እና ከአፍሪካ ህብረት አመራር ጋር አባላት ጋር የሁለትዮሽ ውይይት እንደሚያደርጉ በሰማሁ ጊዜ ከፍ ያለ ደስታ ተሰምቶኛል፡፡ እንደዚህ ያለ ስብሰባ በአሕጉሪቷ ማድረግ ተገቢ ነው።

የኢትዮጵያ ህዝቦች እጆቻቸውን ዘርግተው እንደሚቀበሉዎት እና ከልብ የመነጨ ሰላምታ እንደሚያቀርቡልዎት ምንም ዓይነት ጥርጣሬ የለኝም፡፡ ኢትዮጵያውያን በእንግዳ ተቀባይነታቸው ከዓለም ተወዳዳሪ የሌላቸው ህዝቦች ናቸው የሚል ጽኑ እምነት ያለኝ፡፡

ለመጨረሻ ጊዜ አንደዚህ በደስታ ተውጨ የነበረው ከስድስት ዓመታት በፊት .. ሀምሌ 2009 በጋና አክራ ላይ ተገኝተው ለጋና ፓርላማ አድርገውት በነበረው ንግግርዎ ነበር፡፡

በአክራ ከተማ በመገኘት ያደረጓቸው የንግግር ቃላት ስሜትን ቀስቃሽ እና የእኔን ልብ ብቻ የማረኩ ሳይሆን በአፍሪካ የሚኖሩ እና የነጻነት አየር ለመተንፈስ ይቋምጡ የነበሩ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ህዝቦችን ቀልብ የሳቡ ነበሩ፡፡

እርስዎ ልዩ ቦታ ላይ በመገኘት ለአፍሪካ ህዝብ መልካም ነገርን በማሰብ እንደዚህ የሚሉትን እና መሆን ያለባቸውን መሳጭ ንግግሮች አድርገው ነበር፡

እንዳትሳሳቱ፡ ታሪክ ከእነዚህ ጀግኖች አፍሪካውያን ጎን እንጅ በመፈንቅለ መንግስት ስልጣንን ከሚይዙ እና በስልጣን ማማ ላይ ተፈናጥጠው ለመኖር ሲሉ ሕገመንግስትን ከሚያሻሽሉ አምባገነኖች ጎን አይደለም፡፡ አፍሪካ ጠንካራ ሰዎችን አትፈልግም፣ ይልቁንም አፍሪካ የምተረፈልገው ጠንካራ ተቋማትን ነው፡፡

ልማት በመልካም አስተዳደር ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ በበርካታ ቦታዎች ላይ ለበርካታ ጊዚያት የጠፋው ታላቅ ነገር ይህ መልካም አስተዳደር የሚባለው ጉዳይ ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ለውጥ የሚደረግ ከሆነ ነው የአፍሪካን የወደፊት የእድገት ዕጣ ፈንታ ቁልፍ መክፈት የሚቻለው፡፡ ይህም ኃላፊነት እውን ሊሆን የሚችለው በሌላ በማንም ኃይል ሳይሆን በአፍሪካውያን ብቻ ነው፡፡

በአሁኑ ጊዜ ጋናውያን ባረጀ እና ባፈጀው የፈላጭ ቆራጭ ንጉሳዊ አገዛዝ ምትክ ሕገ መንግስታዊ አስተዳደርን በመምረጥ ህዝባችሁ ለዘለቄታው ኃይሉን አስተባብሮ በልማት ጎዳና ላይ ለመጓዝ የሚያስችሉ የዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብ ብልጭታዎች በጠንካራ መሰረት ላይ ተጥለው ይታያሉ፡፡ ለብዙሀኑ ህዝብ ጥቅም እና መብት ሲሉ ሽንፈትን በጸጋ የሚቀበሉ መሪዎችን እየተመለከትን ነው፡፡

የሕግ የበላይነት በአምባገነናዊ የጭካኔ አገዛዝ እና ሙስና በተንሰራፋበት የአገዛዝ ስርዓት ውስጥ መኖር የሚፈልግ ሰው የለም፡፡ እንደዚህ ዓይነቱ ስርዓት ዴሞክራሲ አይደለም፣ ይልቁንም የሀገሬውን ዜጋ እና የዓለምን ህዝብ ለማደናገር አንዳንድ ጊዜ ብቻ በሚደረግ የይስሙላ ምርጫ ዜጎችን በስቃይ የሚያማቅቅ አምባገነናዊ ስርዓት ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ እንደዚያ ያለው አስቀያሚ ስርዓት ከስሩ ተመንግሎ መጣል ያለበት እና የህልውናው የማብቂያ ጊዜ ነው፡፡

የውጭ እርዳታ ዓላማ አስፈላጊ የማይሆንበት እና ሀገሮች እራሳቸውን ችለው መንቀሳቀስ የሚያስችላቸው ምቹ መደላድል መፈጠር አለበት፡፡ የእኔ አስተዳደር በሚቀርቡለት የሰብአዊ መብቶች ዘገባ መሰረት ሙስናን ለመዋጋት ልዩ ትኩረት በመስጠት የሚንቀሳቀስ ይሆናል፡፡

ባለፉት ጥቂት ሳምንታት ውስጥ በርካታ ከፍተኛ ከበሬታ ያላቸው የሰብአዊ መብቶች እና የመገናኛ ብዙሀን ድርጅቶች እርስዎ ኢትዮጵያን ለመጎብኘት ባቀዱት ጉዞ ላይ ከፍተኛ የሆነ ተቃውሞ ሲያሰሙ እንደነበር ግንዛቤው አለኝ፡፡

ሮበርት ኤፍ. ኬኔዲ የሰብአዊ መብቶች ማዕከል/Roberet F. Kennedy Center for Human Rights የተባለው የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅት እንዲህ በማለት የተደቀነበትን ስጋቱን ገልጿል፣በዚህ ሳምንት ብቻ ሶስት የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ አባላት ተገድለው ባለበት ሁኔታ ፕሬዚዳንት ኦባማ ወደ ኢትዮጵያ የሚያደርጉት ጉዞ በጣም አስቸጋሪ ሁኔታን የሚፈጥር ጉዳይ ነው፡፡

በተመሳሳይ መልኩ ዋሽንግተን ፖስት የተባለው የዜና ወኪል እርስዎ ወደ ኢትዮጵያ የሚያደርጉት ጉዞ እንቆቅልሽ እንደሆነበት እና ይልቁንም ይህንን ጉዞ በመሰረዝ ሌላ ሀገር ቢጎበኙ የተሻለ ሊሆን እንደሚችል እንዲህ በማለት ሀሳቡን ግልጽ አድርጓል፣ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ በመጣው ከፍተኛ የሆነ ጭቆና፣ የነጻውን ፕሬስ ጉሮሮ አንቆ በመያዝ እና ሰላማዊ የፖለቲካ ፓርቲ አባላትን መብት በመርገጥ አላንቀሳቅስ በማለት የፖለቲካ ምህዳሩን ዘግቶ የተቀመጠ ስርዓት በመሆን ኢትዮጵያ ከአፍሪካ የቀዳሚነቱን ስፍራ ይዛ ትገኛለች፡፡ በውል ለክቶ ለማወቅ በማይቻል መልኩ ኢትዮጵያውያንን እያሰቃየ እና እየጨቆነ ላለ የሰብአዊ መብት ደፍጣጭ መንግስት ሙሉ ጊዜን ሰጥቶ ለመጎብኘት መንቀሳቀስ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ታሪካዊ፣ ሰላማዊ እና ዴሞክራሲያዊ የስልጣን ሽግግር ያደረገችውን ናይጀሪያን ጓዳዊ ያልሆነ እይታን በማሳየት ለመጎብኘት አለመፍቀድ ግራ የሚያጋባ እንቆቅልሽ ነገር ነው፡፡

የውጭ ፖሊሲ መጽሔት/Foreign Policy Magazine እርስዎ ወደ ኢትዮጵያ የሚያደርጉትን ጉዙ በመቃወም እንዲህ የሚል ትችት አቅርቦብዎታል፣ዋሽንግተን በአፍሪካ ቀንድ የተረጋጋ አጋር ትፈልጋለች፡፡ ሆኖም ግን በአዲስ አበባ ከሚገኘው ጨቋኝ መንግስት ጋር አጋርነትን መፍጠር የተሳሳተ መንገድ በመሆኑ ሌላ እውነተኛ ወዳጅነት ያለው እና የዜጎችን መብት የሚያከብር አጋርነትን መፈለግ የተሻለ መንገድ ነው፡፡

በኢትዮጵያ .. ግንቦት 24/2015 የተካሄደውን የይስሙላ የቅርጫ ምርጫ በማስመልከት የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ፖሊሲ የሚከተለውን ምልከታ በማድረግ እንዲህ የሚል ትችት አቅርቧል፣በኢትዮጵያ ያለው ገዥ አካል ሙሉ በሙሉ 547ቱንም የፓርላማ መቀመጫ ወንበሮችን በማሸነፍ እራሱን ከሰሜን ኮሪያ እና የሳዳም ሁሴን ብቸኛ የፓርቲ አገዛዝ ጋር በእኩል ደረጃ አስቀምጦ ይገኛል፡፡

ጋርዲያን የተባለው መጽሔት በርካታ የሆኑ ተቃውሞዎቹን በማጠቃለል በእርስዎ ጉብኝት ላይ እንዲህ የሚል ምልከታውን አቅርቧል፣የባራክ ኦባማ ኢትዮጵያን የመጎብኘት ውሳኔ የሰላማዊ ዜጎችን መብት በመደፍጠጥ ላይ ለሚገኙት የአፍሪካ ጨቋኝ አምባገነኖች የተሳሳተ መልዕክት ያስተላልፋል በማለት የሰብአዊ መብት ወትዋቾችን በእጅጉ ያስደነገጠ ጉዳይ ሆኗል፡፡

በርካታ የኢትዮጵያ ሲቪል የሰብአዊ መብት ተሟጋች ቡድኖች፣ ድርጅቶች እና የማህበረሰብ መሪዎች የእርስዎን የኢትዮጵያ ጉዞ በግልጽ እና ከፍተኛ በሆነ ስሜት ተቃውመውታል፡፡

.. ሀምሌ 3/2015 የኢትዮጵያ እና የኢትዮአሜሪካ ዜጎች ከኋይት ሀውስ ፊት ለፊት በመሰለፍ እርስዎ ወደ ኢትዮጵያ የሚያደርጉትን ጉዞ በመቃዋም ደማቅ ሰላማዊ ሰልፍ አካሂደዋል፡፡

በርካታ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች፣ የሲቪል ማህበረሰብ ቡድኖች፣ የብዙሀን መገናኛ ድርጅቶች እና የፖሊሲ ተንታኞች እርስዎ ወደ ኢትዮጵያ የሚያደርጉትን ጉዞ በመቃወም እያቀረቧቸው የሚገኙትን የተቃውሞ ሀሳቦች እኔም እጋራቸዋለሁ፡፡ እነዚህ ቡድኖች እና ድርጅቶች እያቀረቧቸው ላሉት ጉዳዮች ልዩ ትኩረትን እንደሚሰጡት እና ለተነሱት ጉዳዮች ተገቢውን ምላሽ እንደሚሰጡ እምነት አለኝ፡፡

እንደ ኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት ግንባር ቀደም ተሟጋችነቴ እና አንድም ጊዜ ሳይቋረጥ በየሳምንቱ ሰኞ የሚወጡ ትችቶቼ እና ባለፉት ዘጠኝ ዓመታት በኢትዮጵያ እና በአፍሪካ የሰብአዊ መብቶች እንዲከበሩ ጥረት ሳደርግ እንደመቆየቴ መጠን የአሁኑ የእርስዎ ወደ ኢትዮጵያ የሚደረገው ጉዞ ምቹ መደላድል የሚፈጥር እና ፍሪያማ ነገሮችን ያስገኛል የሚል እምነት እንዳለኝ በመግለጽ የመከራከሪያ ጭብጤን እንደሚከተለው አቀርባለሁ፡፡  

የዚህን አዎንታዊ ዕንደምታ የተስፋ ፍንጣቂ ገና ኢትዮጵያ ውስጥ ከመድረስዎ በፊት በአሁኑ ጊዜ ባሉት ቀናት ውስጥ እያየን ለመሆናችን ምስክርነት ለመስጠት እወዳለሁ፡፡

.. ሀምሌ 8/2015 የጋዜጠኞች ተከላካይ ኮሚቴ (ጋተኮ)/Committee to Protect Journalists (CPJ) “በኢትዮጵያ ያለው ገዥ አካል ዞን 9 እየተባለ የሚጠራውን እና በኢትዮጵያ ነጻ አስተሳሰብ እንዲሰርጽ በመታገል ላይ የነበሩትን ሁለት ጦማሪያንን እና ሌሎች ሶስት ጋዜጠኞችን ከእስር ቤት ለቋል፡፡ በእነርሱ ላይ ተመስርተው የነበሩት ሁሉም ክሶች ውድቅ ሆነዋል፡፡የሚል ዘገባ አውጥቷል፡፡

እነዚህ ወጣት ጦማሪያን እና ጋዜጠኞች .. ከሚያዝያ 2014 ጀምሮ በህገወጥ መልኩ በቁጥጥር ስር ውለው በአምባገነኑ የመለስ ዜናዊ እስር ቤት ሲማቅቁ የቆዩ ናቸው፡፡

እንደ እነርሱ ያሉ አሁን በማጎሪያው እስር ቤት ውስጥ ከህግ አግባብ በሆነ መልኩ ታፍነው በእስር ቤት ውስጥ በመማቀቅ ላይ የሚገኙ እና እነርሱም ካልሰሩት ወንጀል ነጻ ሆነው እንዲወጡ የእርስዎን መድረስ በመጠባበቅ ላይ የሚገኙ በርካታ ጋዜጠኞች እና ጦማሪያን ይገኛሉ፡፡

.. ሀምሌ 9/2015 የጋዜጠኞች ተከላካይ ኮሚቴ (ጋተኮ) ከፍተኛ ደስታ በተቀላቀለበት ሁኔታ እንዲህ የሚል ዘገባ አውጥቷል፣ርዕዮት ዓለሙ በመፈታቷ በጣም ደስ ብሎናል፣ ሆኖም ግን በመጀመሪያ ደረጃ በምንም ዓይነት ሁኔታ በፍጹም መታሰር አልነበረባትም፡፡ የጤንነቷ ሁኔታ ተጓድሎ ባለበት ሁኔታ እና በጣም ክልከላ በበዛበት የእስር ቤት አያያዝ ከአራት ዓመታት በላይ በእስር ቤት እንድትማቅቅ ተደርጓል፡፡

ርዕዮት ለአንዲት ቀን እንኳ መታሰር አልነበረባትም፡፡ በእስር ቤት ለመቆየት እና ላለመቆየት ቁልፉ ያለው በአንችው እጅ ነው በማለት ተነግሯታል፡፡ ርዕዮት እንድታደርግ የተፈለገው ጥፋት አጥፍቻለሁ ብለሽ በሰራሽው ስተት አምነሽ ፈርሚ እና ከእስር ቤት ትወጫለሽ የሚል ነበር፡፡

ሆኖም ግን ርዕዮት እንደዚያ ዓይነት ነጻ በሆነ መልኩ ሀሳቧን ከመግለጽ በስተቀር ምንም ዓይነት ጥፋት እና ወንጀል ባልሰራችበት ሁኔታ ለአምባገነኖች እብሪት ሲባል አሳምነን እና በትዕቢት የተወጠረን እንደጎማ አስተንፍሰን ነው የምንለቅ ከሚል ዕኩይ እብሪት በመነሳሳት ነጻዋ ጋዜጠኛ ህሊናዋን ሸጣ አዎ አጥፍቻለሁ ማሩኝ ብላ በእግር ላይ እንድትንበረከክ ነበር የተፈለገው፡፡ ጀግናዋ ርዕዮት የእናንተ የሸፍጥ ይቅርታ በአፍንጫው ይውጣ በማለት መታሰሯን መርጣ ቆይታለች፡፡

ርዕዮት ለአራት ዓመታት 17 ቀናት ያህል በእስር ቤት ስትማቅቅ መቆየቱን መርጣለች፣ ምክንያቱም ጀግናዋ ወጣት ጋዜጠኛ ከእርሷ ከእስር ቤት የመፈታት ነጻነት ይልቅ ለእውነት ሙሉ ዋጋ በመስጠቷ ነው፡፡

አሳሪዎቿ ከእስር ቤት ወጥታ እንድትሄድ ከመፍቀዳቸው በፊት ርዕዮት እንዲህ የሚል ማስጠንቀቂያ ሰጥታቸው ነበር፣ባላጠፋሁት ጥፋት ምንም ዓይነት ይቅርታ ሳልጠይቅ ከማጎሪያው እስር ቤት ወጣሁ ብዬ ለህዝብ ስናገር መልሳችሁ ወደ ማጎሪያው እስር ቤት ልታመጡኝ ትችላላችሁ፣ እኔ ግን በዓላማዬ ጸንቼ እቆያለሁ፡፡ ስለእኔ ከእስር መፈታት ሀሰት ብትናገሩ እውነቱን ለህዝብ ይፋ አደርጋለሁ እናገራለሁ፡፡

ለዚህ ነው ርዕዮት ዓለሙንየኢትዮጵያ እውነት ተናጋሪዋበማለት የሚጠሯት፡፡

ርዕዮትን በሚገባ አውቃታለሁ፡፡ በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን የጀግና ተምሳሌት ቀንዲል ናት፡፡

ርዕዮት የኢትዮጵያ ሮሳ ፓርክስ ናት፡፡

ለሌላ ለምንም ምክንያት ሳይሆን ስጋ እና ደም የለበሰችውን እና በእሳት ተፈትና የወጣችውን ታላቅ ሰው ክብር እና ሞገስ ለማየት ስትሉ ብቻ ርዕዮትን በግል እንድታገኟት እጠይቃለሁ፡፡

ፕሬዚዳንት ኦባማ የእርስዎን ወደ ኢትዮጵያ መምጣት ምክንያት በማድረግ በአሁኑ ጊዜ የጋዜጠኞች እና የጦማሪያን ከእስር መለቀቅ ለወደፊቱ ብሩህ ነገርን አመላካች ጉዳይ ነው፡፡

የእርስዎ መሄድ እና ወደ አቃቂ የማጎሪያ እስር ቤት በር የመድረስዎ እና አምስቱን ጦማሪያን እና ጋዜጠኞችን የማስፈታቱ ዜና እንደተሰማ እርግጠኛ ነኝ ለማይሳነው አምላኬም ጸሎት አደርጋለሁ፡፡ በኢትዮጵያ የሚገኙ እስር ቤቶችን በሮች ሁሉ ክፍት በማድረግ በፖለቲካ አመለካከታቸው ብቻ ለበርካታ ዓመታት ታስረው በመማቀቅ እና በመሰቃየት ላይ የሚገኙት በሺዎች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ሁሉ ነጻ ይሆናሉ የሚል እምነት አለኝ፡፡

ከዚህም በተጨማሪ የሲኤንኤን/CNN ዘጋቢ ጋዜጠኛ ኤሪን ቡርኔት .. ሀምሌ 2012 በአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ውስጥ እንደሆነችው የሚያደርግ ምንም ዓይነት አጋጣሚ እንደማይመጣብዎ ተስፋ አለኝ ጸሎትም አደርግልዎታለሁ፡፡ ቡርኔት በዚያ ቦታ ላይ የደረሰባትን ተሞክሮ እንደሚከተለው ገልጸዋለች፡

በላፈው ወር በኢትዮጵያ በነበርኩበት ጊዜ የአፍሪካ የፖሊስ መንግስት ምን እንደሚመስል በተጨባጭ ያየንበት ጊዜ ነበርበአየር ማረፊያው ቅጥረ ግቢ ውስጥ የጉምሩክ ጉዳዮችን ለመፈጸም አንድ ሰዓት ወስዶብኛልበሰልፉ መርዘም ምክንያት እንዳይመስላችሁ ሆኖም ግን በዚያ ግቢ ውስጥ በሚደረገው ፍተሻ እና የተንዛዙ ጥያቄዎች መቅረብ ምክንያት ነው፡፡ ባለስልጣኖች ለበርካታ ጊዚያት ወደ መንግስት ተሸከርካሪዎች ይወስዱናል፣ ከዚያም ወዴት እንደምንሄድ የሚያውቁት ነገር የለም፡፡ በአየር ማረፊያው ውስጥ በመቶዎች እና በሺዎች ዶላር የሚያወጡ የቴሌቪዥን ጊሮችን ስናቀርብ ብቻ ነው ትንሽ ውጥረቱ መርገብ የጀመረውፕሬዚዳንት ኦባማየአባቴ ህልሞችበሚለው የእርስዎ መጽሐፍ ላይ እንዲህ የሚሉ ቃላትን አስፍረው እንደሚገኙ አምናለሁ፡

ምንም ዓይነት ተስፋ የሌላቸውን እና አቅም የለሾችን ተመልክቻለሁ፡ በጃካርታ  ወይም ደግሞ በናይሮቢ መንገዶች የልጆች ህይወት እንዴት እንደተጣመመ የተመለከትኩት ነገር በተመሳሳይ መልኩ ደግሞ በችጋጎ ደቡባዊ ክፍል በውርደት እና ባልተቋረጠ ንዴት በህጻናቱ ላይ እደረሰ ያለው የመብት ጠባብ መንገድ ህጻናቱን ለከፍተኛ የኃይል ጥቃት እና ተስፋየለሽነት የሚዳርግ መሆኑን በውል ተመልክቻለሁ፡፡ ለእንደዚህ ዓይነቱ ስርዓተ አልበኝነት ጉልበተኞቹ ምን ዓይነት ምላሽ እንደሚሰጡ አውቃለሁ፡፡ በሌላ በኩል እንደዚህ ያለው ችግር እና የደስታ እጦት እየበዛ ሄዶ ስርዓተ አልበኝነት ገደቡን በማለፍ ከፍተኛ የሆነ ቸግር ሲፈጠር ያልታሰበ እና ቀጣይነት ያለው ኃይል መጠቀም፣ ለረዥም ጊዜ እስራት እና የተራቀቁ የጦር መሳሪያዎችን በማዘጋጀት የሚደረገው አፈና በቂ የተግባር እንቅስቃሴ ሆኖ አይገኝም፡፡ የአክራሪነት አቋም መያዝ፣ ጽንፈኝነትን መታቀፍ እና ጎሰኝነትን ማራመድ ለሁላችንም ጎጂዎች እንደሆኑ አውቃለሁ፡፡

በኢትዮጵያ በህዝቦች ፈቃድ ሳይሆን በጠብመንጃ ኃይል በስልጣን ኮርቻ ላይ ተንጠልጥሎ ያለው ገዥ አካል በጃካርታ እና በናይሮቢ ያዩትን ነገር አዲስ አበባን በሚጎበኙበት ጊዜ አንዳያዩ ሊደብቆት ይሞክራሉ፡፡

የእርስዎን ጉብኘት ከግንዛቤ በመውሰድ በሺዎች የሚቆጠሩ የመንገድ ላይ ለማኞችን እና ከገጠር ወደ ከተማ በመፍለስ የሚኖሩትን ቤት አልባ ዜጎች በማፈስ አድራሻቸውን በማጥፋት በእርስዎ የመኪና አጀብ ላይና  በሚያንጸባርቁ መስታዎት ህንጻዎች ላይ ጥላቸዉን አንዳይታይ ገዥዎቹ ይሞክራሉ።  ሆኖም ግን በአንክሮ የሚመለከቱ ከሆነ ቢያንስ ጥቂቶችን በየህንጻው እና በየአጥሮች ዳርቻ ላይ ወድቀው ሊመለከቱ ይችላሉ፡፡ 

አማካይ በሆነ መልኩ በመንገድ ላይ ከሚያገኟቸው ወጣት ኢትዮጵያውያን ጋር መነጋገር ቢችሉ በመጀመሪያ ሊነገሩዎት የሚፈልጉት እንክዋን ደህና መጡ ነው፡፡ ከዚያም በመቀጠል በጨካኙ እና በሙስና ተዘፍቆ በሚገኘው ገዥ አካል አማካይነት ህይወታቸው ምን ያህል እንደተጣመመች እና እየተሰቃዩ እንዳሉ በሹክሹክታ ድምጻቸውን ዝቅ አድርገው ይነግሩዎታል፡፡ በየዕለቱ የሚደርስባቸውን ውርደት እና በደም ስሮቻቸው ሁሉ ተሰራጭተው ስለሚዘልቁ ቁጣዎች ዝርዝር አድርገው ይነግሩዎታል፡፡ ስለተዳፈነው ተስፋቸው እና ስለመከኑት ህልሞቻቸው አንድ በአንድ ይነግሩዎታል፡፡

እንዲህ የሚሉትን የላንግስተን ሁይስ ጊዜ የማይሽራቸውን ጥያቄዎች ያቀርቡሎት ይሆን?

የዘገዬ ህልም ምንድን ነው ሊሆን የሚችለው?

በጸሐይ ላይ እንዳለ ሙጫ ከእናካቴው ይደርቃልን?

ወይስ ደግሞ እንደ ቁስል ማመርቀዝ ይጀምር እና መምገሉን ይቀጥላል?

እንደበሰበሰ ስጋ ይጠነባል ወይስ ደግሞ በላዩ ላይ ስኳር እንደተመረገበት ሹሮፕ የሚጣፍጥ ይሆናል

ምናልባትም ታላቅ ጭነት እንዳለው ነገር ወደ ታች ይለነበጣል ወይስ ደግሞ ይፈነዳል?

የዓለም የፕሬስ ነጻነት ቀን .. ግንቦት 1/2015 በተከበረበት ዕለት ላደረጉት ንግግር ታላቅ አድናቆት አለኝ፡፡

ዴሞክራሲ ባለበት ስርዓት ላይ ነጻ ፕሬስ የሚጫወተውን ጉልህ ሚና ካሰመሩበት በኋላ የሚከተለው አውጀው ነበር፡

ጋዜጠኞች  እንደ ዜጋ ለሁላችንም ስለሀገሮቻችን ስለእራሳችን እና ስለመንግስታችን እውነታውን እንድናውቅ ዕድል ይሰጡናል፡፡ ይህ ድርጊት የተሻልን እንድንሆን፣ ጠንካሮች እንድንሆን ድምጽ ለሌላቸው ድምጽ በመሆን፣ ኢፍትሀዊነትን በማጋለጥ እና እንደ እኔ ያሉት መሪዎች ተጠያቂ እንዲሆኑ ያስችላልእንደ አጋጣሚ ሆኖ በዓለም ዙሪያ ባሉ በርካታ ቦታዎች ነጻው ፕሬስ እውነታውን ለማጥፋት በሚፈልጉ መንግስታት በከፍተኛ አደጋ ላይ ይገኛልበጋዜጠኞች ላይ የማስፈራራት ድርጊቶች ይፈጸማሉ፣ እንዲያውም አንዳንድ ጊዜ ይገደላሉ፣ ነጻ የዜና ምንጮች እንዲዘጉ ይደረጋል፣ መብቶቻቸውን በሰላማዊ መንገድ የሚጠይቁ ዜጎች በኃይል ጸጥ እንዲሉ በማድረግ ሀሳብን በነጻ የመግለጽ ነጻነት ይታፈናል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ .. 2010 የዓለም የፕሬስ ነጻነት ቀንን ምክንያት በማድረግ እንዲህ በማለት የሰጡትን መግለጫ አስታውሳለሁ፣ህዝቦች ከምንጊዜውም በላይ በኢንተርኔት፣ በተንቀሳቃሽ ስልኮች እና በሌሎች ተገጣጣሚ ቴክኖሎጂዎች አማካይነት መረጃዎችን የማግኘት ዕድላቸው እየጨመረ በመጣበት በአሁኑ ጊዜ እንደ ቻይና፣ ኢትዮጵያ፣ ኢራን እና ቬንዙዌላ ያሉ ሀገሮች በተጻራሪው ሀሳብን በነጻ የመግለጽ ነጻነትን ሙሉ በሙሉ በመገደብ እና እነዚህን የቴክኖሎጂ ውጤቶችን መጠቀም እንዳይችሉ በመከልከል ላይ ይገኛሉ፡፡

.. በሀምሌ 2015 የሚጎበኟት ኢትዮጵያ የጋዜጠኞች ተከላካይ ኮሚቴ ባወጣው ዘገባ መሰረትበፕሬስ ነጻነት ጨቋኝነት ከዓለም በአራተኛ ደረጃ ላይ የምትገኝ ሀገር ስትሆን ከአፍሪካ ደግሞ በአስከፊ የፕሬስ አያያዝ የሁለተኛነት ደረጃውን ይዛ ትገኛለች፡፡

በኢትዮጵያ ጋዜጠኝነት ከአሸባሪነት ጋር እኩል የሚያስመድብ ነው፡፡

ጋዜጠኝነት በኢትዮጵያ ወንጀለኛት ነው፡፡

ጋዜጠኞች አሸባሪዎች እና የመንግስት ጠላቶች ተደርገው ይፈረጃሉ፡፡

በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ውስጥ ታስረው የሚገኙት ጋዜጠኞች እና ጦማሪያን በሽብርተኝነት ወንጀል ክስ ተመስርቶባቸው ጉዳያቸው ለበርካታ ዓመታት በፍትህ አካል ሳይቀርብ በእስር ቤት በመማቀቅ ላይ ይገኛሉ፡፡

በዚህ ባሳለፍነው ሳምንት የህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ ገዥ አካል የሐክ ቡድን/Hack Team እየተባለ ከሚጠራው ኩባንያ በርካታ የሆኑ ለስለላ ተግባር የሚያገለግሎ የሶፍት ዌር መሳሪያዎችን ግዥ በመፈጸም ብዙ ሚሊዮን ዶላሮችን ያፈሰሰ መሆኑ ተገልጿል፡፡ ይኸ ዜና እርስዎ .. 2010 የዓለም የፕሬስ ነጻነት ቀንን ምክንያት በማድረግ ያስተላለፉትን መልዕክት እናመንግስታት ለህዝቡ የኢንተርኔት ተደራሽነት እንዳይኖር በጥቅም ላይ እየዋለ ያለውን የኢንተርኔት ቴክኖሎጂ ክልከላእያደረጉ መሆናቸውን የገለጹበትን ሁኔታ አስታወሰኝ፡፡ 

እንደዚሁም ሁሉ በኢትዮጵያ ያለው ገዥ አካል የሐክ ቡድን/Hack Team እየተባለ የሚጠራውን ኩባንያ የምርመራ ቴክኖሎጂ ውጤቶች በመጠቀም ገዥው አካል የእርስዎን ወደ ኢትዮጵያ የመምጣት ዜና ሰምቶ ከጥቂት ቀናት በፊት ከእስር ቤት ፈትቶ የለቀቃቸውን ጥቂት የዞን 9 ጦማሪያንን በቁጥጥር ስር ለማዋል እና ወደማጎሪያው እስር ቤት ለመጣል እጅግ በጣም አስከፊ እና የሞራል ስብዕና የዘቀጠበት ድርጊትን አከናውኗል፡፡

በአሁኑ ጊዜ የእርስዎ ወደ ኢትዮጵያ መድረስ ለእርስዎ ጥቂት ተጻራሪ የሆኑ ነገሮች እንደሚገለጹ አውቃለሁ፡፡ 

.. ሀምሌ 2009 ለጋና ህዝብ እና በእነርሱ በኩልም ለመላው የአፍሪካ ህዝብ ባስተላለፉት መልዕክት የሕግ የበላይነት ለሕገ አራዊትነት ቦታውን በሰጠበት እና የዓለምን ህዝብ ለማታለል ሲባል አንዳንድ ጊዜ የይስሙላ ምርጫ እያካሄደ በሚያጭበረብር ስርዓት ውስጥ ማንም ዜጋ ቢሆን ለመኖር እንደማይፈልግ በግልጽ አስቀምጠው ነበር፡፡ 

.. መስከረም 2014 ከህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ የይስመላው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ እና አብሮት ወደ ኋይት ሀውስ ሄዶ ከነበረው ልዑክ ጋር በመገናኘት እንዲህ ብለው መናገርዎ የሚታወስ ነው በኢትዮጵያ በዚህ ዓመት ጠቅላይ ሚኒስትር እና መንግስታችሁ ምርጫ ታካሂዳላችሁ፡፡ ስለዚያ ጉዳይ ጥቂት የማውቀው ነገር አለስለሆነም ስለሲቪል ማህበረሰቡ እና ስለመልካም አስተዳደር እንደዚሁም የኢትዮጵያ እድገት እና ምሳሌነትን ወደ ሲቪል ማህበረሰቡ እንዴት ማስተላለፍ እንደሚቻል ለመወያየት ዕድል ይኖረናል…“

ደህና፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ዳሳለኝ እና የእርሱ መንግስት እርስዎ ስለተናገሩለት ምርጫ ጉዳይ .. ግንቦት 24/2015 የይስሙላ ምርጫ ተደርጓል፡፡ የይስሙላ የቅርጫ ምርጫውን መቶ በመቶ አሸንፈዋል፡፡ አዎ፣ በመቶ ፐርሰንት!

በዘርፉ ላይ እውቀቱ እና ክህሎቱ ያላቸው አስተያየት ሰጭዎች 21ኛው ክፍለ ዘመን እንደዚህ ያለ የምርጫ ውጤት ሊኖር የሚችለው በሰሜን ኮሪያ እና በሳዳም ሁሴኗ ኢራቅ ብቻ ነው፡፡

.. 2008 ለእጩ ፕሬዚዳንትነት የቅስቀሳ ዘመቻ እያካሄዱ ባሉበት ወቅት እንዲህ ማለትዎ የሚታወስ ነው፣ዓሳማን ለማቆንጀት የዓሳማዋን ከንፈር የከንፈር ቀለም በመቀባት ለማቆንጀት ይቻላል፡፡ እንደዚሁም ሁሉ አንድን አሮጌ ዓሳ በወረቀት ላይ ጠቅልሎ ለውጥ ማለት ይቻላል፡፡ ሆኖም ግን ከስምንት ዓመታት በኋላም ቢሆን መጠንባቱን አይተውም፡፡

.. 2015 ህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ የሚባለው ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ የአምባገነንነቱን የቅርጫ ምርጫ በድምጽ መስጫ ወረቀት በመጠቅለል ዴሞክራሲ ብሎ በመጥራት ለህዝብ አቀረበ፡፡ ሆኖም ግን ስልጣንን ከህዝብ ፈቃድ ውጭ በጠብመንጃ አፈሙዝ ይዞ መግዛቱን ከጀመሩ 23 ዓመታት በኋላም ቢሆን መጠንባቱን አልተወም፡፡ 

በየዓምስት ዓመቱ የህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ የእርሱን ኢሰብአዊነት፣ አረመኔነት እና የእርሱን የዘቀጠ ሙሰኝነት ለመሸፋፈን ሲል የይስሙላ የቅርጫ ምርጫ ያካሂዳል፡፡

.. 2005 አሁን በህይወት የሌለው አምባገነኑ መለስ ዜናዊ የቅርጫ ምርጫ አካሂዶ ነበር፡፡ በምርጫው የመራጮች ድምጽ ውጤት ሲያጣ እና በአደባባይ መሸነፉን ሲያውቅ የህዝብን ድምጽ በኃይል ነጥቆ ሲወስድ ተቃውሟቸውን ለመግለጽ ምንም ዓይነት መሳሪያ ሳይዙ ወደ አደባባይ በወጡ ባልታጠቁ ሰላማዊ ሰልፈኞች ላይ ቅጥር ነብሰ ገዳዮችን በማዘዝ እና በማሰማራት በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎች እንዲገደሉ አድርጓል፡፡

በዚያ ኃላፊነት በሌለው የዕልቂት ተግባር ላይ ያለቁትን ዜጎች ባይሆን ኖሮ ይህን ደብዳቤ አልፅፍሎትም ነበር ብዬ አምናለሁ።

መለስ በፈጸመው ዕልቂት ምክንያት በኢትዮጵያ እና በአፍሪካ እንዲሁም በሌሎች ሰብአዊ መብቶች በሚደፈጠጡባቸው ቦታዎች ሁሉ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ለመሆን የበቃሁት እና ያለምንም ማመንታት የማይበገር የሰብአዊ መብት ተሟጋች ሆኘ የቀጠልኩበት ምክንያትም ከዚሁ ድርጊት የሚመነጭ ነው፡፡ የዶ/ ማርቲን ሉተር እንዲህ የሚሉት ምክሮች ነብሴን ሁሉ ያንቀሳቅሱታል፣አንዳንድ ነገሮች ሲደረጉ እያየን ዝም በምንልበት ጊዜ በዚያች ዕለት ህይወታችን ማብቃት ይጀምራል፡፡ 

በመለስ ዕልቂት የጠፋው ህይወት ሊያሳስበን ይገባል፡፡

ለህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ እና ለመለስ ዜናዊ ምንም ነገር ያልሆ ተራ ጉዳይ እንደሆነ አድርገው ነው የሚመለከቱት፡፡     

ለህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ የህዝቦች ዕልቂት ደንታው አይደለም፡፡ እናም በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ቢያልቁም ከቁብ የሚቆጥሩት ጉዳያቸው አይደለም፡! እንደዚሁም ሁሉ በአሁኑ ጊዜ በሺዎች የሚቆጠሩ የፖለቲካ እስረኞች በመለስ ዜናዊ የማጎሪያ እስር ቤት ገብተው ቢማቅቁ ለወያኔዎች ጉዳያቸው አይደለም፡፡

ሆኖም ግን የመለስ ዜናዊ የዕልቂት ሰለባ የሆኑት ወገኖቼ በቃላት ለመግለጽ ከምችለው በላይ ለእኔ ከምንም በላይ ያሳስቡኛል፡፡

እነዚያ የጨካኞች ሰለባ የሆኑት ወገኖች እንደ ሰው ፍጡርነታቸው ለእኔ ያሳስቡኛል፡፡

ሊታረቅ በማይችል የሕግ የበላይነት ጥሰት ዕልቂት የተፈጸመባቸው ወገኖቼ ከምንም በላይ ያሳስቡኛል፡፡

ከብዙ አስርት ዓመታት በፊት ፍጹም ላለመመለስ ምሎ እንደተሰደደ የኢትዮጵያ ተወላጅ ልጅነቴ ሆኖም ግን ኢትዮጵያ ግን ትታው አንዳልሄደች ዜጋ የእነዚህ የዕልቂት ሰለባ የሆኑት ወገኖቼ ጉዳይ ያሳስበኛል፡፡

እንደ ኩሩ ኢትዮአሜሪካዊ የነጻነትን ስጦታ ዕድል እንደተጎናጸፈ ዜጋ በሬፐብለኩ ሰነድ ምሰረታ ላይ ወደፊት ብሩህ ነገር መምጣት እንዳለበት ይታየኛል፡፡ አዎ፣ የተጣረሰ እና ትክክል ያልሆነ ሰነድ ወደ ባርነት የሚያመራ እና ጆሮ ዳባ ልበስ ተብሎ አላይም፣ አልሰማም ተብሎ የተተው ሰነድ ሀዘን፣ ለቅሶ እና እንደ የአፍሪካ ህዝቦች መጽሐፍ ቅዱስ ስብስቦች ቆንጆ ነው ተብሎ የተጻፈ ነው፡፡

.. 2009 በአክራ ላይ በመገኘት እንዲህ ብለው ነበር፡

ይህ ሁኔታ ምርጫዎችን ከማካሄድ በላይ ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በምርጫዎች መካከል ምን እየተደረገ ነው ስለሚለው ጉዳይ ነው፡፡ ጭቆና ብዙ መገለጫዎች ሊኖሩት ይችላል፣ እናም ለበርካታ ሀገሮች ምርጫን ያካሄዱ እንኳ ህዝቦቻቸውን ለከፋ ድህነት በማጋለጥ በበርካታ ችግሮች ተተብትበው ይገኛሉ፡፡ የመንግስታት መሪዎች 20 በመቶ የሚሆነውን የሀገሪቱን ትርፍ በእራሳቸው ኪስ እያጨቁ የምጣኔ ሀብቱን እየበዘበዙ ባሉበት ሁኔታ የትኛውም ሀገር ቢሆን ሀብት ሊያፈራ አይችልምመንግስት 20 በመቶ የሚሆነውን የሀገሪቱን ትርፍ ለግል ጥቅሙ እያዋለ ባለበት ሁኔታ ምንም ዓይነት የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ሊኖር አይችልም፡፡

የእርስዎ ምልከታ ሙሉ በሙሉ ትክክል ናቸው፡፡

ኢኮኖሚስት የተባለው መጽሔት .. ግንቦት 2012 ባወጣው ዘገባ የሚከተሉትን ምልከታዎች አስፍሮ ነበር፡

በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ድፍረትን የተላበሰ እንቅስቃሴ አይደለም፡፡ በአሁኑ ጊዜ ለዚህ ዓመት የተተነበየው ብሄራዊ ገቢዋ 38.5 ቢሊዮን ዶላር የሆነ እና ህዝቧም 85 ሚሊዮን በመሆን ከዓለም ደኃ ሀገሮች ደረጃ ውስጥ ተመድባ ትገኛለች፡፡ የመንግስት ከፍተኛ የሆነ ወጭ አስጊ የሆኑ አደጋዎችን ከፍተኛ የዋጋ መናርን ጨምሮ (በመጋቢት 32.5 በመቶ ካለፉት ዘጠኝ ወራት ዝቅተኛው) እና ከፍተኛ የሆነ የመንግስት ብድር ሆኖም ግን ለግል ዘርፉ ብድርን የሚከለክለው አሰራር አሳሳቢ ጉዳዮች ናቸው፡፡ ከዚህ የበለጠ ለመበደር እና ግዙፍ ወጭ ለማድረግ ዕቅድ ተይዟል፣ አስፈላጊ እንደሆነም ታምኖበታል፡፡ የኢትዮጵያ መናገሻ እምብርት የሆነችው ከተማ ከቻይና በሚገኙ ብድሮች በቻይና እና በጣሊያን የስራ ተቋራጮች ግዙፍ የሆኑ ህንጻዎች እና ድልድዮች በመገንባት ላይ ናቸው፡፡ ሆኖም ግን ሌሎቹ የአዲስ አበባ ከተማ የተለያዩ ክፍሎች የቆሻሻ መጣያ መንገዶች እና በቆርቆሮ ቤቶች የተሰሩ በጣም ኋላቀር እና የተረሱ የከተማው አካል ሆነው ይገኛሉ፡፡

ክቡር ፕሬዚዳንት .. 2009 ለጋና ሕዝቦች እንዲህ በማለት ነግረዋቸው ነበር፣አመራራችሁን በማጠናከር በእኛ የሰብአዊ መብት በሚወጣው ዘገባ መሰረት ለሙስና ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት ተንቀሳቀሱ፡፡

በኢትዮጵያ ላይ ተንሰራፍቶ ስለሚገኘው ሙስና ጉዳይ የሚያስጨንቃችሁ ምንም ዓይነት ችግር የለም፡፡ የዓለም ባንክ ይህንን ስራ ጥሩ አድርጎ አንድ በአንድ ዝርዝር ጥናት በማድረግ ሰርቶ አቅርቦላችኋል፡፡

.. 2012 የዓለም ባንክበኢትዮጵያ ሙስናን መመርመር/Diagnosing Corruption in Ethiopia“ በሚል ርዕስ ባለ417 ገጽ ዘገባ አቅርቦ ነበር፡፡ 

ይህ ዘገባ ሙስና በኢትዮጵያ የፖለቲካ ሰውነት ውስጥ እንደተስፋፊው ነቀርሳ ዘርፎችን እያዳረሰ እንደመጣ ግልጽ አድርጓል፡፡ ለዚህም ነው የዓለም ባንክ ዝርዝር የሆነ የምርመራ ጥናቱን ለማካሄድ የተገደደው፡፡

በዘርፉ ልሂቃን እየተነገረ እንዳለው ሙስና በአጭር ጊዜ ውስጥ የኢትዮጵያን ህዝብ እና የምጣኔ ሀብት እንደሚያወድም ግልጽ ተደርጓል፡፡

.. 2014 የሙስና መለኪያ መስፈርት መሰረት 175 ሀገሮች መካከል ኢትዮጵያ 136 ደረጃን ይዛለች፡፡  

በሁሉም እውነተኛ መመዘኛዎች ከብዙ ጊዜ ጀምሮ ሁለት ጥያቄዎችን ሳሰላስል ቆይቻለሁ፡፡ የእርስዎ ወደ ኢትዮጵያ መሄድ እየተቃረበ በመጣ ቁጥር እነዚህ ጥያቄዎች እንቅልፍ በመከልከል እረፍት ነስተውኛል፡፡ እነዚህም ጥያቄዎች እንዲህ ይቀርባሉ፡፡

1) እርስዎ አሁን ያሉበትን የፕሬዚዳንትነት ስልጣን ከያዙበት ጊዜ ጋር ሲነጻጸር አፍሪካ በአሁኑ ጊዜ በተሻለ ሁኔታ ላይ ትገኛለችን?

2) እርስዎ አሁን ያሉበትን የፕሬዚዳንትነት ስልጣን ከያዙበት ጊዜ ጋር ሲነጻጸር ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ በተሻለ ሁኔታ ላይ ትገኛለችን

እነዚህን ጥያቄዎች የማቀርበው ለተጠያቂነት እና በሁለት ዋና ዋና ምክንያቶች ነው፡፡

በመጀመሪያ ደረጃ በቢሊዮን ዶላር የሚቆጠሩ የአሜሪካ ግብር ከፋዮች ገንዘብ ካለፉት ስድስት ዓመታት ጀምሮ በልማት፣ በደህንነት እና በዴሞክራሲ ስም ወደ በገፍ ኢትዮጵያ ይፈስሳሉ፡፡ የአሜሪካ ሕዝብ ግብር ከፋይ ገንዘብ በኢትዮጵያ ከህዝቦች ፍላጎት ውጭ በጠብመንጃ ኃይል ተንጠልጥሎ የሚገኘውን አረመኔ አምባገነን ገዥ አካል ከማጠናከር የዘለለ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ምንም የፈየደው ነገር አንደሌለ መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡

.. መስከረም 2014 ኢትዮጵያጉልህ የሆነ ምልክት እና እድገትን በአፍሪካ እያሳየች ያለች ሀገር ናት፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ እየተካሄደ ካለው ተጨባጭ ሁኔታ ውጭ ሌላ በዓለም ላይ በፈጣን ዕድገት በመገስገስ ላይ ካሉ ሀገሮች መካከል የሚሻል በምሳሌነት የሚነሳ ሀገር የለምበማለት ለወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ የልዑካን ቡድን መግለጫ መስጠትዎ የሚታወስ ጉዳይ ነው፡፡  

በፈጣን እድገት ላይ የሚገኝ የምጣኔ ሀብት የሚለው ሀረግ ከመገናኛ ብዙሀን ጠቀሜታ አንጻር ጥሩ ሊሆን ይችላል፣ ሆኖም ግን ይህ አፍ እንዳመጣው የሚነገር የዘፈቀደ አባባል በመረጃ ላይ የተደገፈ አይደለም፡፡

የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ኤጀንሲ/United States Agency for International Developmenmt (USAID) የተባለው ድርጅትበኢትዮጵያ በግብርና፣ በኢንዱስትሪ እና በአገልግሎቱ ዘርፍ መጠነ ሰፊ የሆነ እድገትን አስመዝግቢያለሁበማለት በተደጋጋሚ እና ያለምንም ማቋረጥ ሁልጊዜ እንደሚለው እምቧ ከረዩ ዓይነት አባባል ነው፡፡

USAID በኢትዮጵያ ፈጣን የምጣኔ ሀብት ዕድገት እንዲመዘገብ አስችያለሁ ስለሚለው ነገር ይህ ጉዳይ እውነተኛ ስለመሆኑ እርግጠኛ አይደለሁም፡፡

.. 2010 የመንግስት መምሪያ ዋና ተቆጣጣሪ እንዲህ የሚል ዘገባ አቅርቦ ነበር፣በኢትዮጵያ USAID/ኢትዮጵያ ያቀረበው የኢትዮጵያ ዕቅድ እና የአፈጻጸም የኦዲት ዘገባ ዕቅድ እና አፈጻጸሙን በትክክል ያመዛዘነ አልነበረም፣ ምክንያቱም የድርጅቱ ሰራተኞች ተገኘ የተባለው አፈጻጸም እንዴት እንደተገኘ ማሳየትም ሆነ ላቀረቧቸው ተገኙ ለተባሉ ውጤቶች ድጋፍ ሊሰጥ የሚችል ነገር ማቅረብ አልቻሉም፡፡

የዕድገት ቁጥሮች ናቸው ተብለው የቀረቡት አሃዞች እንዲሁ ተቀቅለው የወጡ ሊሆኑ ይችላሉን?

በቢሊዮኖች የሚቆጠሩት የአሜሪካ ግብር ከፋይ ህዝብ ዶላሮች የኢትዮጵያን ህዝብ በትክክል ለመርዳት ስለመዋላቸው ሊያሳይ የሚችል መረጃ የለም፡፡ ይልቁንም፣ ለመሪ ተብዬዎች፣ ለድርጅቱ አባላት እና ለወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ደጋፊዎች ታላቅ ነገር እንዳደረጉላቸው ግልጽ ነው፡፡

.. 2011 ግልሎባል ፋይናንሻል ኢንቴግሪቲ/Global Financial Integrity የተባለው ዓለም አቀፍ ድርጅት የሚከተለውን ዘገባ አቅርቦ ነበር፡

ዓመታዊ የነፍስ ወከፍ ገቢዋ 365 ዶላር የሆነችው ኢትዮጵያ .. 2000 እና 2009 ባሉት ዓመታት መካከል 11.7 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር በሕገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር ከሀገር እንዲወጣ ተደርጓል፡፡ .. 2009 በሕገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር በጠቅላላ 3.26 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር እንዲወጣ በማድረግ ካለፉት ሁለት ዓመታት በሁለት እጥፍ ብልጫ ያሳየ ገንዘብ ከሀገር ውስጥ በህገ ወጥ መልክ ወጥቷል

.. 2008 ኢትዮጵያ 829 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር በልማት ዕርዳታ ስም ተቀብላለች፣ ሆኖም ግን ይህ ገንዘብ በከፍተኛ ሕገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር እዲመነምን ሆኗል፡፡ የኢትዮጵያ የካፒታል ከሀገር ወደ ውጭ የሚያደርገው ፍልሰት ከፍተኛ የሆነ መጠንን እየያዘ በመሄድ .. ኢትዮጵያ ወደ ውጭ ከላከቻቸው ምርቶች ዋጋ 2 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር በመብለጥ በሕገ ወጥ መልክ ወደ ውጭ የወጣወው ገንዘብ 3.26 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ለመሆን በቅቷል፡፡

ግሎባል ፋይናንሻል ኢንቴግሪቲ እንዲህ የሚል መደምደሚያ ሰጥቷል፣የኢትዮጵያ ህዝቦች ደማቸው በሙሉ እንዲመጠጥ ተደርጓል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ካለባቸው የከፋ ዕጦት እና ድህነት ለመውጣት በማሰብ ሕገ ወጥ የገንዝብ ዝውውርን በማካሄድ በወንዙ ላይ ወደ ላይ በመዋኘት ላይ ይገኛሉ፡፡

መነሳት ያለበት ጥያቄ የትኞቹ የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ክፍሎች ናቸው በሕገ ወጥ መልክ በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር ከሀገር ውስጥ እንዲወጣ ማድረግ የሚያስችል አቅም ያላቸው የሚለው ነው፡፡

የኢኮኖሚስት መጽሔት .. መጋቢት 2013 ባወጣው ዘገባ መሰረትበዓለም በፈጣን ዕድገት ላይ ከሚገኙ ሀገሮች መካከል አንዷ በሆነችውሀገር ላይ እንዲህ የሚል አስተማማኝ ዘገባ አውጥቷል፣

በመንግስት በሚወጡ አሀዞች ላይ የገዥው አካል ደጋፊዎች እንኳ እምነት የላቸውም፡፡ በግብርና ዓመታዊ ምርታማነት ላይ የሚታየው ዕድገት ምናልባትም 5-6 በመቶ አይበልጥም የሚል ዘገባ በመንግስት በኩል በሚወጡ አሃዞች ይነገራል፡፡ ሆኖም ግን 2-3 በመቶ ያም ሆኖ በጣም የሚስብ ዕድገት ተብሎ ሊወሰድ የሚችል ዕድገት ሊኖር ይችላል፡፡ ባለስልጣኖች ዕቅዶችን ያስቀምጣሉ፣ እናም ታላላቆቹ ባለስልጣናት ምን መስማት እንደሚፈልጉ በመገንዘብ ዘገባዎች እንዲቀርቡላቸው ይደረጋል፡፡ ዓለም አቀፍ ባለሙያዎች 11 በመቶ ዓመታዊ የምጣኔ ሀብት ዕድገት ለታዕይታ ብቻ በመንግስት በኩል በሚለቀቀው አሀዝ ላይ ጥርጣሬ አላቸው፡፡ እነዚህ ዓለም አቀፍ ባለሙያዎች የሚሉት መንግስት ከሚለው በግማሽ ባነሰ ወደ 5-7 በመቶ አካባቢ የሚሆን ዓመታዊ የምጣኔ ሀብት ዕድገት ሊኖር ይችላል የሚል እስከ አሁንም ድረስ እንደተከበረ በመናገር ላይ ያሉትን ሀሳብ ያቀርባሉ፡፡ 

ሌሎች ገለልተኛ የሆኑ የምርምር ድርጅቶች ደግሞ እጅግ በጣም አስደንጋጭ እና ተስፋ አስቆራጭ የሆኑ እውነታዎችን ያወጣሉ፡፡

.. 2014 የኦክስፎርድ የድህነት እና የሰው ልማት ተነሳሽነት (ኦድሰልተ) ዘርፈ ብዙ የድህነት መለኪያ/Oxford Poverty and Human Development Initiative (OPHDI) Multidimensional Poverty Index) በቀድሞ አጠራሩ ዓመታዊ የተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም የሰዎች የድህነት መለኪያ/U.N.D.P Human Poverty Index) እየተባለ ይጠራ የነበረው ዓለም አቀፋዊ ድርጅት ኢትዮጵያ በፕላኔቱ ከሚገኙት ደኃ ሀገሮች ሁሉ በተከታታይ 4 ጊዜ በድህነት በሁለተኛ ደረጃ ላይ እንደምትገኝ ዘገባ አቅርቧል፡፡ አዎ፣ በዓለም ላይ ሁለተኛዋ ደኃ ሀገር!

.. 2010 ኦድሰልተ/OPHDI በኢትዮጵያ በአስከፊ ድህነት ላይ የሚገኘው ህዝብ ቁጥር  (በቀን ከአንድ ዶላር በታች የሚያገኘው ሰው) በመቶኛ ሲሰላ 72.3 በመቶ ነው የሚል ዘገባ አውጥቷል፡፡

የኦድሰልተ/OPHDI2014 ዓመታዊ የድህነት አሀዛዊ ዘገባ የበለጠ አስደንጋጭ ሁኔታን ያመላክታል፡፡ በገጠሪቱ ኢትዮጵያ የሚኖረው 82 በመቶ የሚሆነው ህዝብ በከተሞች ከሚኖረው እና 18 በመቶ ከሚሆነው ህዝብ በበለጠ ሁኔታበአስከፊ ድህነትውስጥ ይገኛል፡፡ .. 2014 በኢትዮጵያበአስከፊ የድህነትአደጋ ውስጥ ከሚኖረው ህዝብ መካከል በሚከተሉት ክልሎች ላይ ይገኛል፡ ሶማሊ (93%) ኦሮሚያ (91.2%) አፋር (90.9%) አማራ (90.1%) እና ትግራይ (84.5%) ይሸፍናሉ፡፡

በኦድሰልተ/OPHDI መለኪያ መስፈርት መሰረት ድህነት ማለት ገንዘብ ማጣት ብቻ አይደለም፡፡

ድህነት በዋናነት መጥፎ የጤና አጠባበቅ፣ መጥፎ የትምህርት ስርዓት፣ መጥፎ የምግብ ሁኔታ፣ ከፍተኛ የሆነ የህጻናት ሞት፣ መጥፎ የውኃ አቅርቦት እና የኤሌክትሪክ አቅርቦት፣ እንዲሁም መጥፎ የቤት እና የንጽሀን ሁኔታ ነው፡፡

በኢትዮጵያ ዋና የድህነት መንስኤ የመልካም አስተዳደር እጦት ነው!

ባለፉትአስር ዓመታት ውስጥ ባለሁለት አህዝ የምጣኔ ሀብት ዕድገት ተመዝግቧልእየተባለ የሚነዛው የቅጥፈት አባዜ እንዳለ ቢኖርም እንኳ ኢትዮጵያ በመጥፎ ሁኔታ ላይ ትገኛለች እናም ለዚህም ነው ኢትዮጵያ በፕላኔቷ ከሚገኙት ሀገሮች በድህነት በሁለተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች እየተባለ ያለው!

በሁለተኛ ደረጃ የአሜሪካ ግብር ከፋዮች ለኢትዮጵያ ለበርካታ ዓመታት ለሰጡት በቢሊዮኖች ለሚቆጠር ዶላር ምትክ የሚሆን ምን እንደሚያገኙ ለማወቅ ጉጉት አለኝ፡፡

ዩኤስ አሜሪካ ወደ ኢትዮጵያ ያዘነበለችው በደህንነት ጉዳዮች ላይ በአፍሪካ ቀንድ እና በምስራቅ አፍሪካ ያለውን ከፍተኛ ሸክም መሸከም እንድትችልላት ለማድረግ ለመሆኑ ጥርጥር የለኝም፡፡ ከዚያ ውጭ ሌላ አዲስ ነገር አለ የሚል እምነት የለኝም፡፡ በድህረ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ዩኤስ አሜሪካ ለኢትዮጵያ ዋና የጦር መሳሪያዎች እና ስልጠናዎች አቅራቢ ነበረች፡፡

ዩኤስ አሜሪካ .. 1943 እስከ 1977 ድረስ ባሉት ዓመታት ውስጥ በሰሜን ኢትዮጵያ የቃኘው ጦር ሰፈርን በመያዝየቀዝቃዛው ጦርነትን ማዳመጫ ጣቢያአድርጋ ስትጠቀምበት ነበር፡፡

የኢትዮአሜሪካ ግንኙነት .. 1974 በኢትዮጵያ የሶሻሊስት ወታደራዊ አምባገነን በመፈንቅለ መንግስት ስልጣን ከተቆጣጠረ በኋላ ተበላሸ፡፡

በኢትዮጵያ ያለው አገዛዝ ምንም ይሁን ምን የዩኤስ አሜሪካ እና የኢትዮጵያ ስልታዊ የደህንነት ትብብር እና አጋርነት በአፍሪካ ቀንድ አሸባሪነትን በማስወገዱ ረገድ የሚቀጥል ይሆናል፡፡ ኢትዮጵያውያን በአፍሪካ ቀንድ አሸባሪነትን በመዋጋት የአሜሪካንን ጥረት በመደገፉ ረገድ ምንም ጥርጣሬ የለም፡፡

ከቂት ወራት በፊት አሸባሪነት በዜግነት እና ባላቸው እምነት ምክንያት በሊቢያ 30 ንጹሀን ዜጎችን አንገት ቀልቷል፡፡ ሁሉም ኢትዮጵያውያን ባሉበት ቦታ ሁሉ የአሸባሪነትን መጥፎ ጥላ ከስሩ መንግሎ ለመጣል እና ሰላም ለማውረድ ጥረታቸውን እንደሚቀጥሉ ጥርጥር ሊኖር አይችልም፡፡ ኢትዮጵያውያን የፈለገውን ያህል ጊዜ የሚፈጅ ቢሆንም የዜጎቻቸውን አንገት የቀላውን እና በሰው ልጆች ላይ ወንጀል የፈጸሙትን አሸባሪዎች የፍትህን ረዥም ክንድ በመጠቀም ለመያዝ እና ለፍርድ እንደሚያቀርቧቸው ጥርጥር የለውም፡፡

ህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ የተባለው ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ለጸረ ሽብር ትግሉ ጠቅላይነት የለውም፡፡ በሚያስገርም ሁኔታ ዩኤስ አሜሪካ በዓለም አቀፍ ደረጃ በአሸባሪ የስም ዝርዝር የመረጃ ቋት ውስጥ ስሙ ሰፍሮ ከሚገኘው እና እራሱ አሸባሪ ተብሎ ከተፈረጀው ከህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ ድርጅት ጋር የጸረ ሽብርተኝነት አጋርነትን መስርታ የመገኘቷ ጉዳይ ነው፡፡ ዋናው አሸባሪ የማፊያ ቡድን እንዴት አሸባሪነትን ሊያጠፋ ይችላል ተብሎ ይተሰባል! ሌባን ለመያዝ ሌባን መወዳጀት የሚለውን ስልት ለመጠቀም ካልሆነ በስተቀር፡፡

ሆኖም ግን የቀድሞ አሸባሪዎች በመካከላችን ውስጥ ሆነው የበግ ለምድ ለብሰው እያተራመሱ የሚገኙ ተኩላዎች ቢሆኑም ጽዋው ሲሞላ አንድ ቀን ዶግ አመድ ሆነው እንደሚጠፉ በልባችን ውስጥ ዘላለማዊ ተስፋን ሰንቀናል፡፡

በአንድ ወቅት ሌላው አሸባሪ ቡድን ወያኔው አራሱ እንዲህ ብሎ ነበር፣በግንባር በመሆን አጋሮቻችንን በመርዳት እኛን የሚያሰጉንን አሸባሪዎች ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ለማጥፋት ይህንን ስልት ለበርካታ ዓመታት በየመን እና በሶማሌ በመተግበር ስኬታማ ሆነናል፡፡ 

የዩኤስ አየር ኃይል ለአሸባሪነት ተልዕኮ ወታደራዊ ሰው አልባ አውሮፕላኖችን/drones ሩቅ ከሆነው እና በደቡብ ኢትዮጵያ ከሚገኘው የሲቪል የአውሮፕላን ማረፊያ በማስነሳት በየመን እና በሶማሌ መሽገው የሚገኙትን አሸባሪዎች ለመደምሰስ ጥረት እያደረገ እንዳለ የሚታወቅ ነገር ነው፡፡

በእኛ ላይ ስጋትን የሚደቅኑ አሸባሪዎችን ወይም ደግሞ ማንኛውንም ሰላም ወዳድ ሀገር የሚያተራምሱትን ነውጠኛ ሽብርተኞች በማጥፋቱ ረገድ ችግር የለኝም፡፡

እንደ ሲቪል ሕገ መንግስታዊ የሕግ ባለሙያነቴ ጥፋተኝነትን ለማውጣት በሚቀመረው የፖሊሲ መርህ መሰረት በመጀመሪያ ግደል ከዚያም ጥያቄዎችን አቅርብ በሚለው መርህ ላይ ተቸግሪያለሁ፡፡

ይህንን ጉዳይ ለሌላ ጊዜ አቆየዋለሁ፡፡

የእኔ ጉዳይ በአሁኑ ጊዜ ዩኤስ አሜሪካ አሸባሪዎችን ለማደን በሚል ሀሳብ በአፍሪካ ቀንድ አሰማርታው ያለው የደህንነት እና የጸረ ሽብር አጋርነት በኢትዮጵያ ጋዜጠኞችን፣ የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎችን እና ሌሎችንም ሰላማዊ ዜጎች ሳይቀር በማደን ላይ የመገኘቱ ሁኔታ ነው፡፡

የዩኤስ አሜሪካ የመንግስት መምሪያ .. 2014 በኢትዮጵያ ስላለው የሰብአዊ መብት አያያዝ አስመልክቶ ህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ በሲቪል ህዝቦች ላይ ያደረሰውን ሰብአዊ ድፍጠጣ በማስረጃ አስደግፎ ማውጣቱ የሚታወስ ነው፡፡ ከዘገባው ከፊሉ እንዲህ የሚል ነበር፡

ዋነኛው የሰብአዊ መብት ድፍጠጣ ችግር የሚከተሉትን ያካትታል፡ ሀሳብን የመግለጽ ነጻነት በህትመት ግንኙነቶች እና በኢንተርኔት የሚደረጉ ገደቦችን ጨምሮ መገደብ፣ በነጻ የመደራጀት፣ በቁጥጥር ስር ማዋልን ጨምሮ መብትን መከልከል፣ ፖለቲካዊ እንደምታ ያላቸውን የፍትህ ሂደቶች ለይስሙላ እንዲካሄዱ ማድረግ፣ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ አባላትን እና ጋዜጠኞችን ማስፈራራት እና ማሸማቀቅ ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡ መንግስት የበጎ አድራጎት እና ማህበራት የሚል ቀያጅ አዋጅ በማውጣት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችን እና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን የስራ እንቅስቃሴ ቀጣይነት ባለው ሁኔታ በመገደብ ነጻነትን ገድቦ ይገኛል፡፡ ሌሎች የሰብአዊ መብቶች ችግሮች የሚከተሉትን ያካትታሉ፡ የዘፈቀደ ግድያ፣ ንጹሀን ዜጎችን በዘፈቀደ የማሰቃየት፣ የመደብደብ፣ ከህግ አግባብ ውጭ ስልጣንን የመጠቀም እና በደህንነት ኃይሎች የእስረኞች አያያዝ መጥፎ ሆኖ የመገኘቱ ሁኔታ፣ የእስር ቤቶች አያያዝ ሁኔታ ለህይወት አስጊ ሆነው የመገኘት ችግር፣ ከህግ አግባብ ውጭ በዘፈቀደ ንጹሀን ዜጎችን በቁጥጥር ስር ማዋል እና ማሰር፣ ምንም ዓይነት ክስ ሳይመሰረት ማሰር፣ በውንጀላ በእስር ቤት የሚገኙትን ዜጎች የፍርድ ቤት ቀጠሮ ረዥም እና የተንዛዛ ማድረግ፣ ደካማ የሆነ የፍትህ አካል መኖር እና ለፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ምቹ ሆኖ የመገኘት ሁኔታ፣ የዜጎችን ግላዊ መብቶች ማለትም ህገወጥ ፍተሻን፣ በመንግስት የሰፈራ ፕሮግራም አፈጻጸም ውንጀላን፣ የአካዳሚክ ነጻነትን፣ በነጻ የመሰብሰብ ነጻነትን፣ በነጻ የመደራጀት እና ከቦታ ወደ ቦታ የመንቀሳቀስን፣ በኃይማኖትች ጣልቃ መግባትን፣ ዜጎች በእራሳቸው ችሎታ እና አቅም የመንግስትን ፖሊሲን፣ አስተዳደራዊ እና የፍትህ ሙስናን ለመለውጥ እንዳይችሉ ማድረግን፣ ኃይልን መጠቀምን እና ህብረተሰቡን በሴቶች እና በህጻናት በማለት መከፋፈልን ጨምሮ መብቶችን መዳፈር የሚሉት ይገኙበታል፡፡

ባለፉት በርካታ ዓመታት በአፍሪካ በተለዬ ሁኔታ ያሳዩት ለነበረው ተነሳሽነት ያለኝን አድናቆት ለመግለጽ እወዳለሁ፡፡

በአህጉሩ የኤሌክትሪክ አገልግሎት በስፋት እንዲሰራጭ በማሰብአፍሪካን በኃይል ማጠናከርየሚል የህዝብ እና የግል አጋርነት መስርታችኋል፡፡

በአንድ ዓረፍተ ነገር ውስጥ ኃይል እና አፍሪካ የሚሉ ቃላትን ማየቴ እንድጨነቅ እና እንድጠራጠር አድርጎኛል፡፡

ኃይል ለአፍሪካ እውነተኛ ችግር ነው፡፡

ጥያቄዎች ግን ሁልጊዜ አንድ ዓይነት ናቸው፡ ማን ነው ኃይል ያለው? ማን ነው ኃይል የሌለው እና አቅመ ቢሱ? ኃይል ያላቸው ኃይል የሌላቸውን ዜጎች መብቶች ከህግ አግባብ ውጭ እንዳይደፈጥጡ እንዴት ነው መከላከል የሚቻለው? 

ለተራ አፍሪካውያንኃይል ለአፍሪካየሚለው ሀርግኃይል ለአፍሪካ አምባገነኖችከሚለው ሀረግ ጋር ሊያሳስት ይችላል፡፡

ይህ ተነሳሽነትአፍሪካውያንን ማጠናከርመባል ነበረበት የሚል ሀሳብ አለኝ፡፡ አፍሪካውያንን በተለይም ወጣቱን ኃይል ማጠናከር አለብን የሚል እምነት አለኝ፡፡

እንደዚሁም ሁሉ የእርስዎንወጣት የአፍሪካ መሪዎች ተነሳሽነትበሚል የማንዴላ ዋሽንግተን ፌሎውሽፕን ዋና መሰረት አድርጎ የተነሳውን ተነሳሽነት እወደዋለሁ፡፡ ይህ ተነሳሽነት በወደፊቷ አፍሪካ ላይ ኢንቨስት ለማድረግ የእርስዎን ሁለገብ ጥረት ያካተተ ነው ይባላል፡፡

500 የሚሆኑ ምርጥ እና ብሩህ አዕምሮ ያላቸውን የአፍሪካ ወጣቶችን በማምጣትየቢዝነስ እና የስራ ፈጠራ ፕሮግራሞችን እንዲሁም የህዝብ አመራር እና አሰተዳደር ስራዎችንዕድሎች እንዲያገኙ በማድረጉ ረገድ የሚደገፍ ጉዳይ ነው፡፡

ወጣት የአፍሪካ መሪዎች ተነሳሽነትየሚለው የእርስዎ ፕሮግራም (W.E.B. Du Bois) ቦይስ  ህልዮትአስሩ በተፈጥሮ የታደሉ የልዩ ተሰጥኦ ባለቤቶችየሚለውን እና ከአስር ጥቁር አፍሪካውያን አንዱ በዓለም ላይ ለዘሩ መሪ ይሆናል የሚለውን አስታወሰኝ፡፡

ቦይስ ባዘጋጁት የጥናት ጽሁፋቸው ላይ እንዲህ የሚል ነገር ጽፈው ነበር፣የባሮች ዝርያ በእርሱ ልዩ በሆኑ ሰዎች ይጠበቃል፡፡ በባሮቹ ላይ ያለው የትምህርት ችግር እንግዲህ ተሰጥኦ ባላቸው በእነዚህ አስር ሰዎች መፈታት አለበት፡፡ የዚህ ዘር ምርጥ የሆኑ ሰዎች የማግኘት ችግር ነው ሚሆነው እናም ብዙሀኑን ከብክለት እና በመጥፎ ነገር ከመሞት እንዲተርፉ መምራት አለባቸው፡፡

ምናልባትም የእርስዎወጣት የአፍሪካ መሪዎች ተነሳሽነትየአፍሪካን አስር በተፈጥሮ የታደሉ ምርጦች ያስገኝ ይሆናል፡፡

ምናልባትም የአፍሪካ ወጣት መሪዎች አፍሪካን ከብክለት፣ ከሰው ዘር ማጥፋት እና በሰው ልጆች ላይ ከሚፈጸሙ ወንጀሎች ሊታደጓት ይችሉ ይሆናል፡፡

ሆኖም ግን ምንም ዓይነት የትምህርት፣ የጤና አጠባበቅ እና የስራ ዕድል ላላገኙት፣ በመቶ ሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ የአፍሪካ ወጣቶች ምን ተነሳሽነት አዘጋጅተውላቸው እንደሆነ ለማወቅ አጓጓለሁ፡፡ የተባበሩት መንግስታት 70 በመቶ የሚሆነው የአፍሪካ ህዝብ እድሜው 35 ዓመት በታች ነው ይላል፡፡ እነዚህ ወጣቶች በአህጉሪቱ ተንሰራፍቶ ካለው አምባገነናዊ አገዛዝ ነጻ ለመውጣት የእርስዎን እገዛ ይፈልጋሉ፡፡ የቀረውን ነገር እራሳቸው መያዝ ይችላሉ፡፡

.. ነሀሴ 2014 በኋይት ሀውስ የዩኤስአፍሪካ መሪዎችን ጉባኤ ሲያካሂዱ በነበረበት ጊዜ ልቤ ተሰብሯል፡፡

በዓለም ላይ ከሚገኙ የአፍሪካ አምባገነን መሪ ተብዬዎች ጎን ቆመው ባየሁዎት ጊዜአፍሪካ ጠንካራ ሰዎችን አትፈልግም፣ አፍሪካ የምትፈልገው ጠንካራ ተቋማትን ነውብለው ሲናገሯቸው የነበሩት ቃላት ስሜትን ወረሩት፡፡

በዚያ ጉባኤ ላይ ከፓውል ቢያ፣ ከብላይሴ ኮምፓሬ፣ ከቴዶር ኦቢያንግ ንጉማ ባሶጎ፣ ከኃይለማርያም ደሳለኝ ቦሸ፣ ከፓውል ካጋሜ፣ ከጆሴፍ ካቢላ ካባንጌ፣ ከኢድሪስ ዴቢ፣ ከንጉስ ምዋ 3ኛ፣ ከዮሪ ሙሴቤኒ፣ ከዴኒስ ሳሶው ንጉሶ እና ከመሳሰሉት ትከሻ ለትከሻ ተቃቅፈው ቆመው ይታዩ ነበር፡፡

በዚያ ቦታ ላይ በዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት በፍርድ ሂደት ላይ ካለው ከኡሩ ኬንያታ ጋር ቆመው ነበር፡፡

ዊሊያም ሸክስፒር እንዲህ በማለት ጽፈው ነበር፣መጥፎ ድርጊቶች ይነሳሉ/መሬት ለሰው ልጆች ዓይን ሁሉንም ነገር እስካሳየች ድረስ፡፡“  

በአፍሪካ እና በሌላውም ዓለም ረሀብን፣ የምግብ ንጥረ ነገር እጦትን እና ድህነትን ለመቀነስ እናየወደፊቱን ትውልድ የመመገብ ተነሳሽነትየሚለውን ፕሮግራምዎን አደንቃለሁ፡፡

ኮፊ አናን እንዲህ ብለው ነበር፣የወደፊቱን ትውልድ መመገብ የሚሉት ፕሮግራሞች ፈጠራን በመደገፍ፣ የቴክኒክ የእውቀት ድጋፍ በመስጠት እና ለአነስተኛ ገበሬዎች ምርቶች የገበያ ዕድሎችን በመፍጠር ጉልህ ሚናን ይጫወታሉ፡፡ኮፊ ትክክል ናቸው፡፡ 

ሆኖም ግንወንዶች እና ሴቶች በዳቦ ብቻ አይኖሩምከሚለው ቅዱስ አባባል ጋር ከእኔ ጋር እንደሚስማሙ እርግጠኛ ነኝ፡፡

.. ሰኔ 2009 እንዲህ ብለው ነበር፡

አሜሪካ ሰላማዊ የሆነ የምርጫን ውጤት በማንሳት ትክክለኛው ይኸ ነው እንደማትል ሁሉ ለእያንዳንዱም ሰው የሚሻለው የትኛው ነው የሚለውን ለማወቅ አትፈልግም፡፡ ሆኖም ግን ሁሉም ህዝቦች ለአንድ ነገር ጥረት ማድረግ እንዳለባቸው የማይናወጥ እምነት አለኝ፡ አዕምሮ የፈቀደውን የመናገር መብት እና እንዴት እየተዳደረ እንዳለ ሀሳብ የመስጠት፣ በህግ የበላይነት ላይ እምነት የመጣል እና ሁሉንም ፍትሀዊ በሆነ መልኩ የማስተዳደር፣ ግልጽነት ያለው መንግስት እና ከህዝቡ ዘንድ ስርቆት የማይፈጽም እና አንድ ሰው እንደመረጠው የመኖር መብት ሊከበርለት ይገባል፡፡ እነዚህ ሁሉ የአሜሪካ ሀሳቦች አይደሉም፡፡ ሰብአዊ መብቶች ናቸው፡፡ ለዚህም ነው በየትም ቦታ እነዚህን እየደገፍን ያለነው፡፡

የአፍሪካ ወጣት ወንዶች እና ሴቶች የአፍሪካ የወዲፊት አለኝታዎች ያለምንም ገደብ ነጻነትን ይፈልጋሉየመናገር ነጻነት፣ የማምለክ ነጻነት፣ የመሰብሰብ እና ቅሬታዎችን የማቅረብ ነጻነት ይፍልጋሉ፡፡

የአፍሪካን ወጣት እዕምሮ እና ሰውነትን ለማጥፋት ማሰብ እና ለተግባራዊነቱ መንቀሳቀስ አስቸጋሪ ነገር ነው፡፡

በአሁኑ ጊዜ ምንም ዓይነት የመነጋገሪያ ጉዳዮች ጋር ግንኙነት ከለሌላቸው ነገሮች ጥቂት የግሌን ቃላት ለማለት ወደድሁ፡፡

ምናልባትም እነዚህ ቃላት በኢትዮጵያ እና በአፍሪካ የሰብአዊ መብቶች ውትወታ ላይ ስላለኝ አቋም የተወሰኑ ምልከታዎችን ሊሰጡዎት ይችላሉ፡፡

.. 1960ዎች ሁለተኛ አጋማሽ እና 1970ዎቹ መጀመሪያ አካባቢ ለከፍተኛ ትምህርት ወደ ዩኤስ አሜሪካ ከመጡት ሁለተኛ ዙር ወጣቶች መካከል አንዱ ነበርኩ፡፡

የእርስዎ አባት የአፍሪካ ህዝቦች የመጀመሪያውን ዙር ቅኝ ያለመገዛት ትግል ካካሄዱ በኋላ እና የከፍተኛ ትምህርታቸውን በዩኤስ አሜሪካ አጠናቅቀው .. 1960ዎች ሁለተኛ አጋማሽ ላይ ወደ አፍሪካ ከተመለሱት የመጀመሪያው ዙር የአፍሪካ ወጣቶች መካከል ነበሩ፡፡

ለከፍተኛ ትምህርቴም የፖለቲካ ሳይንስ እና ሕግን ለማጥናት መረጥኩ፡፡ በተለይም ደግሞ በአሜሪካ የሕገ መንግስታዊ ሕግን ህልዮት፣ ተግባር እና መንግስት ላይ ልዩ ፍላጎት አደረብኝ፡፡

የእርስዎ አባት ኢኮኖሚክስ ካጠኑ በኋላ ወደ ኬንያ ተለመሱ፡፡

የመጨረሻ ዲግሪዎቼን ከተቀበልኩ በኋላ እዚያው አሜሪካ ለመቅረት መረጥኩ፡፡

ከዚያ በኋላ መንግስት የእራሱን ሕዝብን በሚፈራበት ሀገር እንጅ ህዝብ የእራሱን መንግስት በሚፈራበት ሀገር መኖር እንደማልችል አስቀድሜ ተገነዘብኩ፡፡

እንግዲህ ዓይነቱ ሁኔታ እንደ ጀፈርሰን ዓይነት ዴሞክራት ሙስናን፣ ተከታታይነት ባለው ሁኔታ ክብርን መጠየቅን፣ ለሁሉም ዜጎች እኩል መብቶችን ማጎናጸፍን እና ሌሎችንም በማካተት ጽናት ያለው ተቃውሞዬን ማቅረብ ጀመርኩ፡፡

.. ግንቦት 2009 እንዲህ ብለው ነበር፡

እንደተማሪ ሕገ መንግስትን አጥንቻለሁ፣ እንደ መምህር አስተምረዋለሁ፣ እንደ ሕግ ባለሙያ እና ሕግ አውጭ አካል በዚሁ ሙያ እገዛለሁ፡፡ እንደ ዋና የጦር አዛዥ እና እንደ ዜጋ ሕገ መንግስቱን ለመንከባከብ፣ ለመጠበቅ እና ለመከላክል ቃል ገብቻለሁ፡፡ ምንም ይሁን ምን ለሕገ መንግስቱ መርሆዎች መከበር ፍጹም በሆነ መልኩ ጀርባችንን ሳናዞር በጽናት እና በአይበገሬነት እንጠብቀዋለን፣ እንንከባከበዋለን፡፡

ይህንን ስናገር እንዲሁ በዘፈቀደ እንደ ሀሳባዊ በመሆን አይደለም፡፡ የተከበሩ እሴቶቻችንን እንደ ዓይናችን ብሌን የምንከባበከባቸው ጥሩ ነገር በመሆናቸው ምክንያት ብቻ አይደለም፣ ሆኖም ግን ሀገራችንን ጠንካራ ሆና እንድትቀጥል ስለሚያግዙ እና እኛም ደህንነታችን ተጠብቆ እንድንኖር ስለሚያስችሉን ነው፡፡ የእኛ እሴቶች ከጊዜ ወደ ጊዜበጦርነት እና በሰላሙ ጊዜ፣ ደስታ በተንሰራፋበት እና ብጥብጥ እና ሀዘን በገሰበት ዘመን ሁሉ ብሄራዊ ሀብቶቻችን እና የኩራት ምንጮቻችን እየሆኑ መጥተዋል፡፡ ለእሴቶቻችን ታማኝ መሆን አሜሪክ ከትንሽ እና ከተበጣጣሰች ቅኝ ተገዥ ሀገር ወደ ጠንካራ እና የዓለም ልዕለ ኃያል የተባበረች ሀገርነት እንድትሸጋገር አስችሏታል፡፡

እኔም እንደዚሁ የሕገ መንግስትን ሕግ አጥንቻለሁ፣ እያስተማርኩትም፣ እየተገበርኩትም ነው፡፡ ለእርሱ መርሆዎች ተግባራዊነት በምንም ዓይነት መንገድ አላጎበድድም፣ ግንባሬንም አላጥፍም፡፡

ለእኔ ሕገ መንግስቱን መያዝ ቀላል የሆነ ሀሳባዊ ነገር ነው፡፡ ጠለቅ ተብሎ ሲታይ የማይበገር ጽናትን የተላበስኩ ሀሳባዊ ኢትዮአሜሪካዊ ነኝ፡፡

ስለሆነም ላለፉት ዘጠኝ ዓመታት በየሳምንቱ አንድም ሳምንት ሳላጓድል በአሜሪካ የሰብአዊ መብቶች ጥበቃ ሰነዱ ላይ የሰፈሩትን የአሜሪካንን እሴቶች እያስተማርኩ፣ እየሰበኩ እና እተገበርኩ ለመዝለቅ ችያለሁ፡፡

.. 2009 ባደረጉት መሳጭ ንግግርዎ ላይ እንዲህ ብለው ነበር፣ልንዋጋላቸው እና ልንጠብቃቸው በተቀመጡት ምርጥ ሀሳቦች ላይ መደራደር ስንጀምር ያን ጊዜ እራሳችንን እናጣለን፡፡ እናም እነዚያን ሀሳቦች ልናከብራቸው፣ ልንጠብቃቸው እና ልንዋጋላቸው የሚገባን ደህና ጊዜ በገጠመን ወቅት ብቻ ሳይሆን ፈታኝ እና አስቸጋሪ በሆነበት ጊዜ ጭምር መሆን አለበት፡፡

የህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይን አመራሮች በአዲስ አበባ በሚገናኙበት ጊዜ የአሜሪካንን ምርጥ ሀሳቦች ለድርድር ማቅረብ የለብዎትም፣ እናም ለሁሉም ነገር ጆሮ ዳባ ልበስ ብለው በኢትዮጵያ በይፋ በሚታወቀው እና በስውር እስር ቤቶች ታስረው በሚማቅቁ በሺዎች የሚቆጠሩ የፖቲካ እስረኞች ጉዳይ ላይ ኬረዳሽ ብለው ወደ አሜሪካ እንዳይመለሱ፡፡

አይበገሬዎቹ ጋዜጠኞች እስክንድር ነጋ፣ ውብሸት ታዬ፣ ተመስገን ደሳለኝ፣ አብርሃ ደስታ፣ በእስር ላይ የሚገኙትን የዞን 9 ጦማሪያን እና በሺዎች የሚቆጠሩ የፖለቲካ እስረኞችን ከእስር ቤት ለማስፈታት ጥረት እንደሚያደርጉ ተስፋ አለኝ፡፡

ከጥቂት ቀናት በፊት 6 የኢትዮጵያ የሙስሊም እርቅ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት፣ በስምንት ምሁራን፣ በሁለት ጋዜጠኞች፣ በአንድ የኪነ ጥበብ ባለሙያ እና በአንድ ተማሪ የአሸባሪነት ድርጊት በመጸም፣ ደባ በመሸረብ እና በማነሳሳት የሚል ክስ የመሰረተባቸው መሆኑ ተዘግቧል፡፡ እነዚህ ዜጎች ያለምን ፍትህ በአምባገነኖች የዘፈቀደ እስራት .. 2012 ጀምሮ በእስር ቤት ውስጥ በመማቀቅ ላይ ይገኛሉ፡፡

እነዚህ መንግስት ከአምላክ ስራ እራሱን አስወጥቶ በሌላው ስራው እንዲሰማራ በማለት ሕገ መግስታዊ መብታቸውን በመጠቀማቸው ብቻ ሰብስቦ ወስዶ በእስር ቤት በማጨቅ መከራ እና ስቃይ እየፈጸመባቸው ያሉት ወጣት የኢትዮጵያ ሙስሊም የእርቅ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላትን እንዲፈታ ግፊት እንደሚያደርጉ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡

.. ከየካቲት 2007 ጀምሮ እርስዎ ዕጩ ፕሬዚዳንት ሆነው የምረጡኝ ቅስቀሳዎን ሲያካሂዱ በነበረበት ጊዜ እኔ የእርስዎ ቁጥር 1 ደጋፊ ነበርኩ፡፡

ላለፉት በርካታ ዓመታት የእርስዎን መመረጥ በማጉላት በዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮአሜሪካውያን ሁሉ ድምጻቸውን ለእርስዎ እንዲሰጡ በርካታ ትችቶችን በመጻፍ የገንዘብ ማሰባሰብ እና የድምጽ ድጋፍ ሳሰባስብ ቆይቻለሁ፡፡

የእርስዎን ፖሊሲዎች ጠንካራ በሆነ መልኩ ስከላከል ቆይቻለሁ፣ እንዲሁም በእርስዎ ላይ በመገናኛ ብዙሁን የሚሰነዘሩትን ጎጂ የሆኑ ትችቶች የተከታተልኩ ሳመከን ቆይቻለሁ፡፡

ባለፈው ዓመት በኢትዮጵያ ላይ እየተከተሏቸው ያሉትን ፖሊሲዎች በማየት በጣም እንቆቅልሽ ስለሆኑብኝበፕሬዚዳንት ኦባማ ላይ ኩራት ማሳደሬ ለምን እንዳሳፈረኝ/Why I am Ashamed to be Proud of President Obama“ በሚል ርዕስ ትችት ጽፌ ነበር፡፡

በእርስዎ የመጨረሻዎቹ ሁለት የፕሬዚዳንትነት ስልጣን ዓመታት ጊዜ ውስጥ እንደገና በእርስዎ ላይ ኩራት ይሰማኝ እንደነበረ ከመግለጽ ውጭ ሌላ ፍላጎት አልነበረኝም፡፡

በእርስዎ አድራሻ የተጻፉ እና ያልተፈተሹ 10 ቁርጥራጭ የግንኙነት ወረቀቶችን በየቀኑ የማንበብ ልምዱ እንደነበርዎት ከሆነ ምንጭ ማነበቤን እያስታወስኩ ልምድ ለእርስዎ በጣም ጠቃሚ የሆነ የየዕለት ንባብዎ አድርገው እንደያዙት ተገንዝቢያለሁ፡፡ 

ከእነዚህ ደብዳቤዎች ውስጥ የእኔ ደብዳቤ 10ኛው ሊሆን እንደሚችል እገምታለሁ፡፡

ይህ አሁን የጻፍኩልዎ ደብዳቤ በብዙ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ድምጽ የሌላቸው እና ድምጾቻቸው ጸጥ እንዲሉ በኃይል ታፍነው የሚገኙትን ኢትዮጵያውያን ጥልቅ ስሜት ያካተተ መበመሆኑ እንድሚያነቡት ተስፋ አደርጋለሁ፡፡

በየዕለቱ በአድራሻ ለእርስዎ በቀጥታ የሚጎርፉ በሺዎች የሚቆጠሩ ደብዳቤዎችን እያጣሩ ወደ እርስዎ የሚመሩት ሰዎች የእኔን ደብዳቤ ድምጽን ከፍ አድርጎ የተጻፈ እና አስፈሪ የሆነ፣ በሰፊው የተዘጋጀ፣ ለእራስ ክብር የሰጠ፣ በእራስ ክብር መስጠት ላይ ትኩረት ያደረገ፣ በእራስ ተነሳሽነት እራስን ሰይሞ የተጻፈ፣ በስህተት ላይ የሚጓዝ የሕገ መንግስት የህግ ፕሮፌሰር እና የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ተሟጋች በማለት ለእርስዎ እንዳይደረስ ሊያደርጉ ይችላሉ ብዬ አስባለሁ፡፡

ለእርስዎ የጻፍኩት ጽሁፍ ይዘት ብዙም ትርጉም ላይሰጥዎ ይችል ይሆናል ምክንያቱም የሸክስፒርን አባባል ልዋስና በአንድ ነገሮች ሁሉ እንቆቅልሽ እና እጅግ አስቸጋሪ በሆኑበት ሰው የተጻፈ ስለሆነ በተወለደባት ሀገር እና በወገኖቹ ላይ የሚደርሰውን ሰቆቃ በማየት ከቀናት በኋላ ያመነዥከዋል ሊሉ ይችሉ ይሆናል፡፡

ምናልባትም የእኔ ደብዳቤ እጅግ በጣም እረዥም እና በቀጥታ ጣቶችን በግልጽ ወደ ጥፋተኛው የሚሰነዝር ነው፡፡

/ ማርቲን ሉተር ኪንግ እንዳሉት በገሀነም በጣም ከፍተኛው የሆነው አኮማታሪ ሙቀት የሚቀመጥላቸውከፍተኛ የሆነ የሞራል ኪሳራ በተከሰተበት ጊዜ ገለልተኛ ሆነው በተቀመጡት ሰዎች ላይ ነውበሚለው የክርክር አመክንዮ በመገፋፋት ነው፡፡

ባለፉት ዘጠኝ ዓመታት ኢትዮጵያን በገጠማት የሞራል ኪሳራ ላይ ገለልተኛ ሆኘ አልተቀመጥኩም፡፡

.. 2006 ጀምሮ በየሳምንቱ ሰኞ ከትክክለኛ የታሪክ ጎን በኩራት በመቆም ትግሌን ቀጥዬ እገኛለሁ፡፡

ባልሳሳትየተስፋ ጥንካሬበሚለው በእርስዎ መጽሐፍ ላይ ይመስለኛል የተመለከትኩት እንዲህ ይላል፣ለእሴቶቻችን ዋጋ የማንከፍል ከሆነ በእርግጥ በእነዚህ እሴቶች ላይ እምነት አለን ወይ በማለት እራሳችንን መጠየቅይኖርብናል፡፡

የእኔ ጓደኞች እስክንድር ነጋ፣ ርዕዮት ዓለሙ፣ ውብሸት ታዬ፣ ተመስገን ደሳለኝ፣ የዞን 9 ጦማሪያን፣ ወጣት የሙስሊሞች እና ሌሎችም በርካታ የፖለቲካ እስረኞች ለመርሆዎቻቸው ሲሉ ከፍተኛ የሆኑ ዋጋዎችን በመክፈል ላይ ይገኛሉ፡፡

.. መስከረም 2014 በኢትዮጵያ ላለው ገዥ አካል የልዑካን ቡድን እንዲህ ብለው ነግረዋቸው ነበር፡

ስለሆነም ስለሲቪል ማህበረሰቡ እና ስለመንግስት የመነጋገር ዕድል ይኖረናል፣ እናም ኢትዮጵያ እያስመዘገበችው ያለውን ዕድገት ምሳሌነት እንዴት በማድረግ ወደ ሲቪል ማህበረሰቡ ማስተላለፍ እንደምንችል እና በአፍሪካ አህጉር በአጠቃላይ ጥረቶቻችንን በማስፋት እና በማጠናከር ዴሞክራሲን ማጎልበት እና ሁሉንም ለፖለቲካው ጥሩ ያልሆኑትን ነገሮች ሁሉ ለኢኮኖሚው ጥሩ ሊሆኑ እንደሚችሉ ማሰብ መቻል ነው፡፡

.. ሀምሌ 2015 የሲቪል ማህረሰብ ድርጅቶች በነጻ መንቀሳቀስ እንዲችሉ እና በኢትዮጵያ የዴሞክራ ስርዓት ግንባታው እንዲሰፋ ለማድረግ ከህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ አመራሮች ጋር ተገናኝቶ የመወያየት ዕድል ይግጥመዎታል ብዬ አስባለሁ፡፡ 

.. ሀምሌ 2009 እንዲህ ብለው ነበር፣ታሪክ ከእነዚህ ከአፍሪካ ጀግኖች ጎን እንጅ መፈንቅለ መንግስት አድርገው ወይም ደግሞ በስልጣን ላይ ለመቆየት ሲሉ ሕገ መንግስትን ለውጠው ከሚቀርቡት አምባገነኖች ጎን አይደለም፡፡ አፍሪካ ጠንካራ ሰዎችን አትፈልግም፣ የምትፈልገው ጠንካራ ተቋማትን ነው፡፡

በመጀመሪያው የመክፈቻ ንግግርዎ ላይ እንዲህ ብለው ነበር፣በሙስና እና በመታለል ስልጣንን የተቆጣጠሩ እና ሰላማዊ አመጸኞችን ጸጥ ለማድረግ ጥረት የሚያደርጉ ሁሉ ትክክለኛ ባልሆነው ታሪክ ጎን የተሰለፋችሁ መሆናችሁን ማወቅ አለባችሁ፣ ሆኖም ግን የጨባጣችሁትን ቡጢ ለሰላም ስትሉ ከዘረጋችሁ እጆቻችንን ዘርግተን እንቀበላችኋለን፡፡

.. ሀምሌ 2015 ኢትዮጵያን በሚጎበኙበት ጊዜ ሀገሪቱን .. 2009 ባደረጉት ማስጠንቀቂያ መሰረት በመግዛት ላይ ያለው ህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ ሀገሪቱን በማን አለብኝነት በማተራመስ ላይ የሚገኝ የወሮበሎች ስብስብ እርስዎ ጠንካራ የአፍሪካ ሰዎች አያስፈልጉም ያሉትን ሆኖ ያገኙታል፡፡ እርስዎ እንደሰጡት ማስጠንቀቂያ ሁሉ እነዚህ የወሮበላ ስብስቦች ስልጣንን የያዙት በነጻ እና በዴሞክራሲያዊ ምርጫ ሳይሆን በሙስና እና በማታለል ሰላማዊውን ህዝብ ጸጥ በማድረግ እና በጠብመንጃ ኃይል በመፈንቅለ መንግስት ነው፡፡ 

ላለፉት ስድስት ዓመታት ከወያኔው ቡድን ጋር በመደራደር ላይ እያሉ የጨበጡትን ቡጢ ፈትተዉት ነበር ፡፡ ምናልባትም በአሁኑ ጊዜ የተጨበጠውን ቡጢ በመግዛት ላይ ያለው ህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ ማሳየት ያስፈልጋል። 

በአዲስ አበባ ከህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ ጠንካራ ሰዎች ጎን ቆመው መታየትዎ ለእኔ እና አኔን ለመሳሰሉት በርካታዎቼ ዜጎች የሚያደናግር እና በከፍተኛ ደረጃ የሚሰማ ቁስል ነው፡፡

በአዲስ አበባ ከሚገኙት ጠንካራ ሰዎች ጋር የእርስዎን ፍቶግራፎች ስመለከት በከፍተኛ ሀዘን በመዋጥ ዓይኖቼ የቅበዘበዛሉ፣ የፊቶቼ ገጽታም ይለዋወጣሉ፡፡ ለዚህ ዓይነቱ ሁኔታ እኔም እንዳለየ አይቸ ጆሮ ዳባ ልበስ እለዋለሁ፡፡

ከህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ ዘራፊ አምባገነኖች ጎን በአዲስ አበባ ቆመው ሲታዩ በታሪክ ጥላ ላይ ቆመው እንደሚታዩ ይቁጠሩት፡፡

አንድ ሰው በአንድ ወቅት እንዲህ ብሎ ነበር፣ጥላዎች በጸሐይ መስታወት እራሳቸውን ሊያዩ አይችሉምወይም ደግሞ በታሪክ መስታወት ልበለው?

የታሪክ ተመራማሪዎች እርስዎ በአፍሪካ እያወጧቸው ስላሉት ፖሊሲዎች እና እያደረጓቸው ስላሏቸው ጥረቶች አንድ ቀን ይጽፉት ይሆናል፡፡ ሰለእርስዎ ትሩፋት እና ምን እንደሰሩ እና ምን እንዳልሰሩ ይጽፉታል፡፡

ሁሉም ስለዚያ የሚደረገው ነገር ብዙ ፋይዳ ያለው ነገር ይኖረዋል ብዬ አልጠብቅም፡፡

ፋይዳ የሚኖረው ነገር ቢኖር .. 2009 አክራ ላይ በትልቅ የመቆሚያ መድረክ ላይ ሆነው አንስተውት ለነበረው የታሪክ ጥያቄ እንዴት አድርገው ከህሊናዎ ጋር በማስታረቅ መመለስ እንዳለብዎት ከማሰቡ ላይ ነው፡፡

ፕሬዚዳንት ኦባማ በአፍሪካ በተለይም በኢትዮጵያ በሚያራምዱት ፖሊሲ ላይ ከትክክለኛው ታሪክ ጎን ቆመዋልን?

ጳጳስ ዴስሞንድ ቱቱ በአንድ ወቅት እንዲህ ብለው ነበር፣ኢፍትሀዊነት ሲፈጸም ዝም ብለህ በገለልተኝነት የምትመለከት ከሆነ ከጨቋኙ ጎን መሰለፍን መርጠሀል ማለት ነው፡፡ የዝሆን እግር ባይጧ ጅራት ላይ ረግጦ ቆሞ ከሆነ እና ያንን እየተመለከትክ በገለልተኝነት ዝም የምትል እና በእግሯ ላይ መቆሙን የማትናገር ከሆነ አይጧ የአንተን ገለልተኝነት የምታደንቀው አይሆንም፡፡

እንደዚሁም ሁሉ ኢትዮጵያውያንን አንገታቸውን በቦት ጫማ ረግጠው ለጣረሞት ዳርገዋቸው ካሉት ጨቋኝ አምባገነኖች ጋር ጥቂት ፎቶግራፎችን ተነስተው ሆኖም ግን ምንም ነገር ሳይናገሩ ዝም ብለው በገለልተኝነት ወደመጡበት የሚመለሱ ከሆነ ኢትዮጵያውያን የእርስዎን ገለልተኝነት እንደማያደንቁልዎት በድፍረት ልነግርዎት እወዳለሁ፡፡

.. ጥቅምት 2011 ታላቁ ወግ አጥባቂ እና የብሔራዊ ጉዳዮች ተንታኝ ሴናተር ቴድ ክሩዝ እንዲህ ብለው ነበር፣የፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ጠንካራ ትሩፋት ለነጻነት ከቆመው ከአዲሱ ትውልድ የመጡ መሪ መሆናቸው ነው፡፡ሴናተር ክሩዝ ይህንን ሲሉ መሰረት እንዳላቸው ተስፋ አለኝ፡፡

በአፍሪካ የእርስዎ ብቸኛው ትሩፋት ለነጻነት ከቆመው ከአዲሱ ትውልድ የመጡ የመሆንዎ ጉዳይ ብቻ እንደሆነ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡

የአፍሪካን ወጣት እና የአዲሱን ትውልድ አመራሮች ባሰቡ ቁጥር አሮጌዎቹን የአፍሪካ መሪዎች ትውልድ እንደማይረሷቸው ተስፋ አደርጋለሁ፡፡

እርስዎም እንደሚያውቁት ሁሉ ታላላቆቹ የኢትዮጵያ መሪዎች ባለፉት ጥቂት ምዕተ ዓመታት የአውሮፓን ተስፋፊ ቅኝ ገዥዎች ተደጋጋሚ ወረራ በመመከት የኢትዮጵያን ነጻነት ሳያስደፍሩ ጠብቀው ከሶስት ዓመታት በላይ ነጻነቷን ጠብቃ እንድትቆይ አድርገዋል፡፡

የአውሮፓ ቅኝ ገዥዎች አፍሪካን እንደ ቅርጫ ስጋ ለመቀራመት በማሰብ አድርገውት ከነበረው የበርሊን ጉባኤ ከተካሄደ ሁለት ዓመታት በኋላ .. 1896 በአድዋ ጦርነት ዳግማዊ ምኒልክ እስካፍንጨው ዘመናዊ የጦር መሳሪያ ታጥቆ የመጣውን የሰለጠነ የጣሊያንን ወራሪ ኃይል ጋሻ እና ጦር እንዲሁም ቀስት እና ኋላቀር መሳሪያዎችን በመጠቀም አይቀጡ ቅጣት በመቅጣት ወራሪውን ጦር አሳፍረው በመመለስ የአፍሪካ ኩራት ሆነዋል፡፡ 

ንጉስ ምኒልክ ግዙፍ የሆነን እና በዘመናዊ የጦር መሳሪያ የተደራጀን የአውሮፓን ቅኝ ገዥ ሰራዊት ድል አድርገው ያንበረከኩ በአፍሪካ ታሪክ የመጀመሪያው አፍሪካዊ መሪ ናቸው፡፡ በታሪካዊ መሪዎቿ ብርታት እና ጀግንነት ምክንያት አንድም የአውሮፓ ኃያል ኢትዮጵያን ቅኝ ግዛት ማድረግ ሳይቻለው ቀርቷል፡፡

ዳግማዊ ምኒልክ በቅኝ ግዛት ወራሪው የኢጣሊያ ሰራዊት ላይ አንጸባራቂ የሆነ ድል ካስመዘገቡበት ጊዜ ጀምሮ ኢትዮጵያ የተስፋ ቀንዲል እና የክብር ምልክት እንዲሁም ለመላ የአፍሪካ እና ለዲያስፖራ አፍሪካውያን ህዝቦች የክብር እና የኩራት ምንጭ ሆና ትገኛለች፡፡

አሁን ለጉብኝት አዲስ አበባ በሚገቡበት ጊዜ ከዳግማዊ ምኒልክ ሐውልት በመሄድ ለክብራቸው ሲሉ በሐውልቱ ስር እቅፍ አበባ ሊያሰቀምጡ ይችላሉን?

ኢትዮጵያ 13 ወራት ሙሉ የጸሐይ ብርሀን ያላት ሀገር ሆና እንደሚያገኟት እርግጠኛ ነኝ፡፡

ኢትዮጵያውያን እንግዳ ተቀባዮች፣ ሰው አክባሪዎች፣ ትሁቶች፣ ስህተቶቻቸውን አምነው የሚቀበሉ ጨዋዎች ሆነው ያገኟቸዋል፡፡

ሚስተር ኦባማ ታላቅ የኢትዮጵያ ጉዞ ይሁንልዎ፡፡

የሰው ዘር መገኛ ወደሆነችዋ ሀገር የሚያደርጉት ጉዜ የደስታ እና የተቃና ይሁልንዎ እላለሁ፡፡

ለመዘመር ስነሳ ሁሉም ትናንሾቹ ወፎች በለሆሳስ ዘመሩና በፍጥነት ተነስተው ከከተማው እንደበረሩ ተነግሮኛል፡፡

ሆኖም ግን ድርጊት እንዲህ የሚለውን ጥንት የባርነት ስቃይ በነበረበት ዘመን በሚዘመረው መዝሙርእንደ ሙሴ ተጓዝ፣በሚለው መልካም ጉዞ እመኝሎታለሁ፡፡“

በሙሴ አኳኋን ወደ ኢትዮጵያ ዘልቀህ ግባ፡፡

የእኔ ህዝቦች ይለቀቁ በማለት ለሁሉም ፈርኦኖች ንገር፡፡

እንደዚህ ተጨቁነው እስከመቸም አይቆዩ፡፡

ህዝቦቸን ልቀቅ እና ይሂዱ፡፡

አምላክም ፈቀደ፣ ሂዱ ሙሴን ተከትላችሁ ወደ ኢትዮጵያ ሂዱ አለ፡፡

ህዝቦቼ እንዲለቀቁ ለሁሉም ፈርኦኖች ንገሯቸው፡፡

እነሆ ሙሴም ወደ ኢትዮጵያ ምድር ሄደ፡፡

ህዝቦቸ እንዲሄዱ ለቀቋቸው፡፡

ሁሉም ፈርኦኖች እንዲያውቁት አደረገ፡፡

ህዝቦቸ እንዲሄዱ ልቀቋቸው፡፡

አዎ አምላክ እንዲህ አለ፣ ዘምሩ ከሙሴ ጋር ወደ ኢትዮጵያ ምድር ሂዱ፡፡

ህዝቦቸ እንዲሄዱ ልቀቋቸው፡፡

ህዝቦቼ እንዲሄዱ ለሁሉም ፈርኦኖች ንገሯቸው፡፡ 

ፕሬዚዳንት ኦባማ ህዝቦቼን እንዲለቋቸው ለህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ ፈርኦኖች ይንገሩ፡፡

 

ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!

ሀምሌ 14 ቀን 2007 .

Similar Posts