የኢትዮጵያ ርዕዮት ተናገረች፣

ከፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማርያም    

ትርጉም በነጻነት ለሀገሬ

Reeyot Alemu
Reeyot Alemu

አይበገሬዋ ጀግናዋ ርዕዮት! 

በንጹሀን ዜጎች ላይ ስቃይን በመፈጸም ከሚታወቀውና ከአዲስ አበባ ከተማ እምብርት በስተደቡብ ምስራቅ ተንጣሎ ከሚገኘው እና በተለምዶ ቃሊቲ እየተባለ ከሚጠራው የመለስ ዜናዊ የማጎሪያ እስር ቤት (የኢትዮጵያ “ሮቤን ደሴት” ማለትም ነልሶን ማንደላ የታሰሩበት) ባልተጠበቀ ጊዜ የተለቀቀችው ጀግናዋ ርዕዮት ዓለሙ ከማጎሪያው እስር ቤት በወጣች በሰዓታት ጊዜ ውስጥ ለአሜሪካ ድምጽ የአማርኛው አገልግሎት ቃለ መጠይቅ ሰጠች፡፡

ዴሞክራሲ እና ፍትህ የሰፈኑባት ኢትዮጵያ እውን እስከምትሆን ድረስ ሙሉ በሙሉ ትግሌን እቀጥላለሁ፡፡ እንደዚህ የሆነች ኢትዮጵያን እስከማይ ድረስ ትግሌን በተጠናከረ መልኩ እቀጥላለሁ በማለት የዓላማ ጽናቷን በድጋሜ አረጋግጣለች፡፡

ርዕዮት በአምባገነኑ ገዥ አካል የ14 ዓመታት እስር ተበይኖባት ይህ እስር እንደገና ወደ 5 ዓመታት ከተቀየረ በኋላ 4 ዓመታት ከ17 ቀናት (1480 ቀናትን) በእስር ቤት አሳልፋለች፡፡

አሁን በህይወት በሌለው በመለስ ዜናዊ እና በእርሱ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ በህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ (ህወሀት) የጸረ ሽብር ሕግ እየተባለ በሚጠራው ሰላማዊ ዜጎችን የማጥቂያ መሳሪያ የፈጠራ እና የሸፍጥ ክስ ተመስርቶባት ነበር ወደ ዘብጥያ የተወረወረችው፡፡

ታላቁ መሪ ኔልሰን ማንዴላ ለዘረኛው የጥቂት ነጮች ፈለጭ ቆራጭ አምባገነን ስርዓት ጭቆና አራማጆች እንዲህ የሚል ማስጠንቀቂያ ሰጥተው ነበር፣ “በማዘግየት በኩል ውጤታማ ልትሆኑ ትችላላችሁ፣ ሆኖም ግን ደቡብ አፍሪካ ወደ ዴሞክራሲ የምታደርገውን ሽግግር በምንም ዓይነት መልኩ በፍጹም ልታስቀሩት  አትችሉም፡፡“

የርዕዮት ዋናው መልዕክት ማጠንጠኛውም ይኸው በታላቁ መሪ በኔልሰን ማንዴላ የተነገረው  የአፓርተይድ ዓይነት ወሮበላ የዘራፊ አምባገነን ቡድን ስብስብ ለሆነው ለወያኔ ትክክለኛ የሆነ ገላጭ ድርጊት ነው፡፡ “ዴሞክራሲ እና ፍትህ የሰፈኑባት ኢትዮጵያ እውን እስከምትሆን ድረስ ሙሉ በሙሉ ትግሌን እቀጥላለሁ፡፡” ነው ያለችው፡፡

ትግሉ ይቀጥላል!

ማንዴላ ከዚህ በተጨማሪም እንዲህ ብለው ነበር፣ “እስር ቤት እራሱ ትዕግስትን እና ጽናትን የሚያላብስ ተዝቆ የማያልቅ ትምህርት የሚሰጥ ተቋም ነው፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ የአንድን ሰው የአድራጊነት እና የመፈጸም ችሎታ የሚመዝን ፈተና ነው፡፡“

ርዕዮት እ.ኤ.አ ሀምሌ 9/2015 ከመለስ ዜናዊ የማጎሪያ እስር ቤት በመውጣት በኢትዮጵያ ለዴሞክራሲ እና ለፍትህ መስፈን ያላትን ለድርድር የማይቀርበውን ቁርጠኛ የሆነውን የዓላማ ጽናቷን በተግባር አረጋግጣለች፡፡ ይህንን ያደረግችው ግን እንዲሁ ከምንም ሳይሆን ከፍተኛ የሆነ ዋጋ ከፍላ ነው፡፡

ለአራት ዓመታት እና ለ17 ቀናት ርዕዮት በመለስ ዜናዊ የማጎሪያ እስር ቤት በየዕለቱ ውርደት፣ ለብቻ ተነጥሎ መታሰር፣ ዝቅተኛ አድርጎ የመመልከት እና ከሰብአዊነት የወረደ አስቀያሚ ድርጊት ይፈጸምባት ነበር፡፡

ሆኖም ግን ጀግናዋ ርዕዮት ሁሉንም ነገር በጽናት ተቋቁማዋለች፡፡

ለአራት ዓመታት እና ለ17 ቀናት ርዕዮት በአምባገነኑ የመለስ ዜናዊ የማጎሪያ እስር ቤት የበቀል እና የሰይጣናዊ ጥላቻ መፈጸሚያ ከርስ ውስጥ ምርኮኛ ሆና ቆይታለች፡፡

በማጎሪያው እስር ቤት ውስጥ እጅግ በጣም አስቀያሚ የሆነውን የሰብአዊ መብት ድፍጠጣ እና ከህግ አግባብ ውጭ በሆነው አያያዝ የሚፈጸምባትን ስቃይ እየገለጸች ድምጿን ከፍ አድርጋ ስታሰማ ቆይታለች፡፡

ታጋሽ ሆናም በጽናት ቆይታለች፡፡

ለአራት ዓመታት እና ለ17 ቀናት ርዕዮት በመለስ ዜናዊ የማጎሪያ እስር ቤት ውስጥ ጭንቅላቷ እየደማ ሆኖም ግን ለአንዲት ቅንጣት ሰከንድ እንኳ ለአምባገነኖች ሳታጎበድድ በጽናት ግዳጇን የተወጣች ጀግኒት ናት፡፡

ርዕዮት እንደ አረብ ብረት እየጠነከረች የመጣች ጀግኒት ናት!!!

ርዕዮት በአምባገነኑ የመለስ ዜናዊ የማጎሪያ እስር ቤት ለዓመታት ስቃይ እና ግፍ ስትቀበል ቆይታለች፡፡ ሆኖም ግን ምንም ዓይነት ፍርሀት ሳይጎበኛት በጽናት ቆይታለች፡፡

ጀግኒቱ ምንም ዓይነት ፍርኃት የለባትም ምክንያቱም ርዕዮት የዕጣ ፈንታዋ እመቤት ባለቤት እና የነብሷ መርከብ ካፒቴን ሌላ ማንም ወሮበላ ዘራፊ ሳይሆን እራሷ ናትና፡፡

ታዋቂው ገጣሚ ዊሊያም ኢርነስት ሄንለይ ከበርካታ ዓመታት በፊት “የማይበገሩ ጀግኖች” በሚል ርዕስ እንዲህ የሚሉ የግጥም ስንኞችን የቋጠሩት ለካስ ለእነ ርዕዮት ዓለሙ፣ እስክንድር ነጋ፣ ውብሸት ታዬ፣ ተመስገን ደሳለኝ፣ አብርሃ ደስታ፣ ለዞን 9 ጦማሪያን እና እንደ እነርሱ ላሉት ለሌሎች ጀግና የፖለቲካ እስረኞች ኖሯል፡

ጋርዶኝ ከነበረው ድቅድቁ ጨለማ፣
ጥልቀትን ከያዘው ከጉድጓዱ ወማ፣
ጥቁር ከለበሰው የመሬት ውስጥ ካስማ፣
አሻግሮ ከያዘው የምድር ላይ ማማ፡፡

ገብቸ በመሀል ሳንድዊች ተደርጌ፣
ባልፈጸምኩት ጥፋት ተጥዬ ከግርጌ፣
ሀበሳ ግፍ አየሁ ከጨቋኝ በርግጌ፡፡

እናም ፈጣሪዬን አምላኬን ላመስግን፣
ለመንፈሴ ጽናት ለሰጠኝ ብርታቱን፣
ከወገኔ ፍቅር እንዳይ በረከቱን፣
ግፍን ለማስወገድ ለመስበር መርገምቱን፡፡

በግፈኞች መዳፍ ስደቆስ ታፍኘ፣
ያለፍትህ አካል መጫወቻ ሆኘ፤
የይስሙላ ዳኛ መጨፈሪያ ሆኘ፡፡

አጥቸ ፍርድ ቤት፣
አቤት የምልበት፣
ፍትህ የማይበት፣
ግፍ የሚመታበት፡፡

ፍትህ ካደባባይ ከመንበሩ ጠፍቶ፣
አምባገነን ነግሶ ስርዓቱ ከርፍቶ፣
ህዝብን አተራምሶ ሀገርን አራቁቶ፣
ዜጋን አሰድዶ ወገን አስከፍቶ፣
በህዝቦች ጫንቃ ላይ ገኖ ተንሰራፍቶ፣
ለዘላለም ሊኖር ሁሉንም አጥፍቶ፣
በተንኮል በደባው ምሎ ተገዝቶ፣
አልሞ ተነስቷል ንጉስ ሊሆን ከቶ፡፡

ለማይበገረው ጠንካራው መንፈሴ፣
አምላክን ለመስግን በመርካቷ ነብሴ፡፡

በግፈኞች መዳፍ በወጥመድ ብወድቅም፣
ሰብአዊነት ክብሬ ቢጣስ ቢረገጥም፣
ብሩሁ አእምሮዬ አካሌ ቢቆስልም፣
ስሜንም ቢያጎድፉት ጥላሸት ቢቀቡም፣
ከዓላማዬ ጽናት አንዲት ጋት አልሸሽም፣
ግርፋት ስቃዩ ጡጫው ቢጨምርም፣
እራሴ ቢደማም አልተንበረከኩም፣
ተሰቃየሁ ብዬ አላፈገፍግም፣
ለጨቋኞች ደስታ አላጎበድድም፡፡

ከዚህ በላይ በቀል አድልኦ ጥላቻ፣
ስምን የማጠልሸት የሰይጣን ዘመቻ፣
ይፈጸማል እኮ በዕኩዮች ሽኩቻ፡፡

እናም የዘመናት ስቃይ ይቀጥላል፣
እኔን ግን መንፈሴ ቆራጥ ያደርገኛል፣
የወገኔ ፍቅር ያንገበግበኛል፡፡

ከምንጊዜም በላይ በሩ ቢጣመምም፣
የተንሸዋረረው ፍትህ ቢጓደልም፣
በኔ ላይ ደጋግሞ ቅጣት ቢቆልልም፣
ከዓላማዬ ፍንክች በፍጹም አልልም፡፡

የእራሴ እጣፈንታ ወሳኙ እራሴ ነኝ፣
ማንም አምባገነን የማይጨፍርብኝ፣
በዲያብሎስ መንገድ የማያስገድደኝ፣
የነብሴ መርከቡ ካፕቴኑ እራሴ ነኝ፡፡

አራቱ የዞን 9 ጦማሪያን ባስቸኳይ ይፈቱ፣

የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ገዥ አካል 5 ወጣት ጦማሪያንን እና ጋዜጠኞችን የህግ አማካሪዎቻቸው፣ እራሳቸው ግፉ የተፈጸመባቸው እና ወላጆቻቸውም ሳይቀር ምንም ነገር ሳያውቁ ባልተጠበቀ ሁኔታ በድንገት ከመለስ ዜናዊ የማጎሪያው እስር ቤቱ ለቋቸዋል፡፡ ከሕግ አግባብ ውጭ በዘፈቀደ ከአንድ ዓመት በላይ በእስር ቤት ሲማቅቁ ቆይተዋል፡፡ ዴሞክራሲ እና ፍትህ በዓለም ላይ ሁሉ በአደባባይ እየሰፈነ እና እየለመለመ ባለበት በአሁኑ ጊዜ በማጎሪያ እስር ቤት አስገብቶ እንደ እባብ የሚቀጠቅጥ፣ በንጹሀን ዜጎች ህይወት ላይ ቁማር የሚጫወት እና እንደፈለገ ወስዶ እንደ ጥጃ የሚያስርና የሚፈታ የዘራፊ ወሮበላ ቡድን ስብስብ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ኢትዮጵያ መታየቱ እጅግ ያሳዝናል፡፡ እነዚህ ንጹሀን ዜጎች በወጡባት እግራቸው ነገም ተመልሰው የማይገበቡት ምን ዋስትና ሊኖር ይችላል! ምንም፡፡

የጋዜጠኞች ተከላካይ ኮሚቴ (ጋተኮ) “የኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣኖች የዞን 9 ጦማሪያንን ከሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ጋር በመስራት እና የማህበራዊ የግንኙነት መስመሮችን በመጠቀም በኢትዮጵያ ውስጥ አለመረጋጋት እንዲፈጠር በመስራት ላይ ናቸው:: ቡድኑ በኢትዮጵያ ስላለው የፖለቲካ ጭቆና እና ማህበራዊ የፍትህ መጓደል ሲጽፍ የነበረ ሲሆን የእነዚህ ጦማሪያን ድረ ገጾች በሀገሪቱ ውስጥ በየጊዜው ይታፈኑ ነበር፡፡” በማለት ስለተናገረው ስለዞን 9 ጦማሪያን ነው እየጻፍኩ ያለሁት፡፡

እ.ኤ.አ ሀምሌ 8/2015 የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ገዥ አካል ሁሉንም የውንጀላ ክሶች በመጣል ባልታሰበ ሁኔታ ጦማሪያኑን እና ጋዜጠኞችን ከመለስ ዜናዊ የማጎሪያ እስር ቤት ለቋቸዋል፡፡

እስረኞቹ ለሌሎቹ ከአንድ ዓመት በላይ በግፍ ታስረው በመማቀቅ ላይ ለሚገኙት ንጹሀን ወገኖቻቸው እና ጓደኞቻቸው እንኳ በሉ ደህና ሁኑ ለማለት ጊዜ አላገኙም ነበር፡፡

ከማጎሪያው እስር ቤት የወጡት ጦማሪያን እና ጋዜጠኞች የሚከተሉትን ያካትታል፡ ዘላለም ክብረት፣ ማህሌት ፋንታሁን፣ ተስፋለም ወልደየስ፣ አስማማው ኃ/ጊዮርጊስ እና ኤዶም ካሳዬ ናቸው፡፡

ከማጎሪያው እስር ቤት የተፈቱት ጦማሪያን እና ጋዜጠኞች ከእነርሱ ጋር በተመሳሳይ የፈጠራ ክስ ተመስርቶባቸው በማጎሪያው እስር ቤት የሚገኙት ሌሎች አራት ጓደኞቻቸው ለምን እንዳልተፈቱ ያሳሰባቸው መሆኑን እና የእነርሱ መፈታት ምሉዕ ደስታ ያልሰጣቸው መሆኑን ለህዝብ ግልጽ አድርገዋል፡፡ ደህና፣ እንግዲህ የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ የይስሙላው የዝንጀሮ ፍርድ ቤት ሚስጥራዊ እንቆቅልሽ እዚህ ላይ ነው፡፡ በተመሳሳይ ውንጀላ ያሰራቸውን ዜጎች እውነት ባይሆንም እንኳ ተመሳሳይ ፍትህ የማይሰጥ በፖለቲካ ቡድኑ የሚጦዝ ድሁር የፍትህ አካል መሆኑን በግልጽ ያመላክታል፡፡

ኢትዮጵያ ርዕዮት ዓለሙን የመሰለች ጀግኒት አለቻት፣

ሁሉም ሀገሮች ከጊዜ ወደ ጊዜ በሚፈጠሩ ጀግኒቶች እና ጀግኖች በመታደል ላይ ናቸው፡፡

አሜሪካ በርካታ ጀግኖች እና ጥቂት ጀግኒቶች አሏት፡፡ አብዛኞቹ የአሜሪካ ጀግኒቶች ያልተዘመረላቸው ናቸው፡፡

አሜሪካዊት ጀግኒት ሐሪዬት ቱብማን እ.ኤ.አ በ1950ዎቹ ባሮች ነጻነታቸውን እንዲቀዳጁ በማሰብ “የምድር ስር ባቡር” ማለትም ከባርነት ወደ ነፃነት ለመጥፋት የሚሞክሩትን የባርነት ተገዢዎች ህቡዕ በሆነ መልኩ በማደራጀት እና በማስተባበር የስብሰባ ቦታዎችን፣ የሚስጥር መንገዶችን፣ በመጓጓዣ ቦታዎች እና በሰላማዊ የህዝብ መኖሪያ ቤቶች በመጠቀም ትግሉ በተጠናከረ መልኩ እንዲካሄድ ጥረት ሲያደርጉ ነበር፡፡

እ.ኤ.አ በ1870ዎቹ የመጀመሪያዎቹ ዓመታት አካባቢ ሱሳን ቢ.አንቶኒ የአሜሪካ ሴቶች የመምረጥ፣ የንብረት የባለቤትነት መብት እና ከዚህም በላይ በመሄድ የሰራተኞች ማህበር አባል እንዲሆኑ የሚያስችሏቸውን መብቶቻቸውን ለማስከበር አመራር ይሰጡ የነበሩ ጀግኒት ሴት ነበሩ፡፡

የዩናይትድ ስቴትስ ምክር ቤት “የሲቪል መብቶች ተከራካሪ የመጀመሪያዋ አመቤት” እና እ.ኤ.አ በ1950ዎቹ አጋማሽ የአሜሪካ የሲቪል መብቶች ንቅናቄ እናት እያለ የሚጠራቸው ሮሳ ፓርክስ ቀላል የሆነውን ህዝባዊ እምቢተኝነትን እንደ ትግል ስልት በመጠቀም ለነጻነት፣ ለእኩልነት እና ለፍትህ ሲካሄድ የነበረውን ትግል አቀጣጥለዋል፡፡ ከፊት ለፊት የተቀመጠችበትን የአወቶብስ መቀመጫ እንድትለቅ እና ወደ ኋላ ሄዳ እንድትቀመጥ የሚያዝዘውን የጨቋኞች ትዕዛዝ አሻፈረኝ፣ እምቢ በማለት ለሴቶች መብት መከበር ስትል የመጀመሪያዋ ሆናለች፡፡

ይህች ጀግኒት እንዲህ ብላ ነበር፣ “የለም፣ በፍጹም ከዚህ መቀመጫ አልንቀሳቀስም!“ በማለት ዜጎችን በጾታ ለሚከፋፍለው ሸውራራ የፖሊስ እና የፍትህ ስርዓት በአደባባይ በግልጽ ተናግራለች፡፡

በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ አፍሪካ አሜሪካውያን ወዲያውኑ ትግሉን በመቀላቀል ከመብት ታጋዩዋ ጋር አብረው መዘመር ጀመሩ፡፡

“የትም አንንቀሳቀስም!/ልክ በውኃ አጠገብ እንደቆመ ዛፍ/ ህብረት ከእኛ ጎን ነው የተሰለፈው/እኛ ለነጻነታችን እንታገላለን/ ለልጆቻችን ስንል እንታገላለን/ ጠንካራ የሆነ ማህበር እንመሰርታለን/ጥቁሮች እና ነጮች በአንድነት ሆነን/ወጣቶች እና አዛውንቶች በአንድ ላይ በመቆም/ የትም አንንቀሳቀስም፣ የትም፡፡“

የአፍሪካ አሜሪካዊ ሴቶች ለሲቪል መብቶች እንቅስቃሴ ትግል ዋና የጀርባ አጥንት ነበሩ፡፡ ሆኖም ግን ያልተዘመረላቸው ጀግኖቶች ናቸው፡፡

የዘመናዊ ሰብአዊ መብቶች ንቅናቄ እናት የሆኑት ኢሊኖር ሩዝቬልት ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ፍጻሜ በኋላ ለሰብአዊ መብቶች ስምምነት መሰረት የሆነውን የዓለም አቀፉን የሰብአዊ መብት ድንጋጌ በማርቀቁ ሂደት ከፍተኛ ኃላፊነትን ይዘው የነበሩ ብቸኛዋ ሴት ነበሩ፡፡

በእኔ አመለካከት ርዕዮት ዓለሙ የዚህ ዓይነት አብዮተኞች ቡድን አባል ናት ማለት እችላለሁ፡፡ እንደዚህ ያሉት ለፍትህ፣ ለእኩልነት፣ ለሲቪል እና ሰለብአዊ መብቶች ዓይናቸውን ሳያራግቡ በመንፈሰ ጠንካራነት ታሪክን የሚለውጡ ደፋር፣ በአመክንዮ የሚያምኑ እና ለህዝብ ሲሉ መስዋዕትነትን ለመክፈል ዝግጁ የሆኑ ሴቶች ናቸው፡፡

እውነት ተናጋሪዋ፣

ርዕዮት “የኢትዮጵያ እውነት ተናጋረዊ ሴት” በመባል ትጠራለች፡፡

ዘመናዊው የአፍሪካ ታሪክ በሚጻፍበት ጊዜ እና በአፍሪካ አዳራሽ የዝነኞች ስም ዝርዝር ከአፍሪካ አዳራሽ ተዋራጆች ስም ዝርዝር ተለይቶ ሲጻፍ የርዕዮት ስም “በእሳት ውስጥ ተፈትነው ያለፉ” ከሚለው ከጀግኖቹ የክብር ስም ዝርዝር ውስጥ በግንባር ቀደምትነት የሚጻፍ ይሆናል፡፡

ርዕዮት ዓለሙ አራት ዓመታት ከ17 ቀናት በቆየው ጊዜ ውስጥ የመለስ ዜናዊን የገኃነም ቅጣት ተጋፍጣለች፡፡

እ.ኤ.አ ሀምሌ 9/2015 ወጣት የሆነችዋ የአረብ ብረቷ ሴት ከመለስ ዜናዊ የማጎሪያ እስር ቤት በመውጣት ለዓለም ህዝብ እንዲህ በማለት አውጃለች፡

ዴሞክራሲ እና ፍትህ የሰፈኑባት ኢትዮጵያ እውን እስከምትሆን ድረስ ሙሉ በሙሉ ትግሌን እቀጥላለሁ፡፡ እንደዚህ የሆነች ኢትዮጵያን እስከማይ ድረስ ትግሌን በተጠናከረ መልኩ እቀጥላለሁ፡፡

የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ አገዛዝ እርሷን በቁጥጥሩ ስር አድርጎ በጉልበቷ እንድትንበረከክ ለማድረግ ያልፈነቀለው ድንጋይ ያልቧጠጠው አቀበት አልነበረም፡፡

የስነ ልቦና ስብራት ለማድረስ እና ያላትን ጠንካራ ተስፋ ለማዳፈን ለብቻዋ ለይቶ በአንድ ክፍል ውስጥ እንድትታሰር አደረገ፡፡

ለህይወት አስጊ በሆነ በሽታ ተይዛ በነበረበት ጊዜ ህክምና እንዳታገኝ አበርትቶ ሰርቷል፡፡

ሴትነቷን እና ሰብአዊ ፍጡር መሆኗን ክደው ተንቀሳቅሰዋል፡፡

መንፈሷን ለመግደል የሞት ሽረት ትግል አድርገዋል፡፡

የመለስ ዜናዊ የማጎሪያ እስር ቤት በመባል በሚታወቀው እስር ቤት የጥላቻ እና የበቀል ቦታ ማድረግ የሚችሉትን ሁሉ አድርገዋል፡፡

ሆኖም ግን በምንም ዓይነት መልኩ የርዕዮትን ቅስም መስበር ሳይቻላቸው ቀርቷል፡፡

አዕምሯዋን መቆጣጠር አልቻሉም፡፡

መንፈሷን መስበር አልቻሉም፡፡

ለመኖር ያላትን ምኞት ማጥፋት ሳይቻላቸው ቀርቷል፡፡

በኩራት ደረቷን ነፍታ በመቆም ለዓለም እንዲህ ትላለች፡

ዴሞክራሲ እና ፍትህ የሰፈኑባት ኢትዮጵያ እውን እስከምትሆን ድረስ ሙሉ በሙሉ ትግሌን እቀጥላለሁ፡፡ እንደዚህ የሆነች ኢትዮጵያን እስከማይ ድረስ ትግሌን በተጠናከረ መልኩ እቀጥላለሁ፡፡

የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ አሳሪዎቿ ከመለስ ዜናዊ የማጎሪያ እስር ቤት እንድትወጣ ከማድረጋቸው ከደቂቃዎች በፊት አሁን እንዳለችው እንደምትሆን ነግራቸዋለች፡፡ ከማጎሪያው እስር ቤት እንድትወጣ አይፈቅዱላትም ምክንያቱም ከአራት ዓመታት በፊት ታደርግ እንደነበረው ሁሉ አሁንም ትግሏን እንደምትቀጥል ያውቃሉና፡፡

ርዕዮት የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብን እንዲህ በማለት አስጠንቅቃለች፣ “ባላጠፋሁት ጥፋት ምንም ዓይነት ይቅርታ ሳልጠይቅ ከማጎሪያው እስር ቤት ወጣሁ ብዬ ለህዝብ ስናገር መልሳችሁ ወደ ማጎሪያው እስር ቤት ልታመጡኝ ትችላላችሁ፣ እኔ ግን በዓላማዬ ጸንቼ እቆያለሁ፡፡ ስለእኔ ከእስር መፈታት ሀሰት ብትናገሩ እውነቱን ለህዝብ ይፋ አደርጋለሁ እናገራለሁ፡፡“

በተለያዩ በርካታ አጋጣሚዎች የርዕዮት አሳሪዎች ይቅርታ ጠይቃ ነጻ ሆና እንድትወጣ የምትፈርምበትን ፎርም እያዘጋጁ ፈርሚ እያሉ በተደጋጋሚ ለምነዋታል፡፡

እርሷግን ወረቀቱን ወስዳ እንደምትጥለው ነግራቸዋለች፡፡

“ብረቷ ወይዘሮ ” እየተባለች እንደምትጠራው  የንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ማጊ ታቼር በህይወት ብትኖር ኖሮ እንዲህ እላት ነበር፣ “ማጊ እባክሽን ወደ ጎን ሁኝ፣ ቦታውን ለርዕዮት ልቀቂ!“

ርዕዮትን እና ሌሎችን ጦማሪያን እና ጋዜጠኞችን የፈቷቸው ለምንድን ነው?

የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ርዕዮት ለፍትህ ወይም ደግሞ ስለእርሷ የልብ ሀዘን መናገር እንድትችል እኔንም ጨምሮ አይፈቅዱላትም ምክንያቱም ተጻራሪ በሆነ መልኩ እነርሱ የሚያዝኑበት ልብም ሆነ መልካም ነገር የላቸውምና፡፡

ርዕዮት ከእስር ቤት ወጥታ ስትሄድ ጥርሳቸውን እንደሚነክሱ እና የሆድ ቁርጠት እንደሚይዛቸው ጥርጥር የለውም፡፡ ቢቻላቸው ኖሮ እርሷ በክፉ በሽታ ምክንያት ህይወቷ አልፏል በማለት ለዓለም ህዝብ ማሳወቅን ይመርጡ ነበር፡፡ በዚህ ጊዜ ግን ዕድል ከወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ጋር አይደለችም፡፡

ይህንን ድርጊት ያደረጉት ለግንባር መሸፈኛ እና በዚህ ወር የሚመጡትን የኦባማን ልብ ለመማረክ ታስቦ የተደረገ ነው፡፡

ይህንን በማድረግ ለኦባማ ጥሩ ነገር እየሰሩ እንዳሉ ለማስመሰል የተደረገ የቅጥፈት ተውኔት ነው፡፡ የኦባማ ጉብኝት ርዕዮትን እና ሌሎችን የታሰሩ ጋዜጠኞች እና የፖለቲካ እስረኞችን ለመጠየቅ ከሆነ የሚፈልጉት ነገር አይደለም፡፡

ኦባማ ለሚከተሉት ጥያቄዎች ምላሽ እንደሚሰጡ እናስብ፡ “ክቡር ፕሬዚዳንት ወደ መለስ ዜናዊ የማጎሪያ እስር ቤት በመሄድ የእርስዎን መሄድ የሚጠባበቁትን እና በግፍ በእስር ላይ እየማቀቁ የሚገኙትን እስክንድር ነጋን፣ ርዕዮት ዓለሙን፣ ውብሸት ታዬን፣ ተመስገን ደሳለኝን፣ የዞን 9 ጦማሪያንን እና በሺዎች የሚቆጠሩትን ሌሎችን የፖለቲካ እስረኞች ሊጎበኙ ይችላሉን? በደርዘን በሚቆጠሩ ኪሎ ሜትሮች ርቀት ላይ ይገኛሉ፡፡ እባክዎትን ሄደው ለመጎብኘት ይችላሉን?“

የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ በልካቸው የተሰፋ የማስመሰያ ልብስን በመልበስ ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተከራካሪ ድርጅቶች በተደጋጋሚ እንደሚሉት የሰው ልጆችን መብት በመጣስ ታላቅ እና አስቀያሚ ሰይጣኖች ናቸው የሚሉትን በመተው ኦባማ ይኸ መንግስት እንደሚባለው አይደለም ብለው እምነት እንዲያድርባቸው ለማድረግ ተዘየደ የሸፍጥ ስራ ነው፡፡ ከልብ እና ከፍቅር ያለመሆኑን አይደለም የኢትዮጵያ ህዝብ ይቅርና የዓለም ህዝብም አሳምሮ እንደሚያውቀው ጥርጥር የለውም፡፡

አይዟችሁ የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ምንም መጨነቅ አያስፈልግም፡፡

የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ጠባቂ መላዕክት አሏቸው – ሱሳን ራይስ እና ዌንዲ ሸርማን በኦባማ ጉብኝት ሁሉ እየተከታተሉ የሚከላከሉላችሁ መላዕክት ናቸው፡፡ ወታደራዊ ማነጻጸሪያ ቃል በመጠቀም እናንተን ለመጠበቅ በቁጥር 1 በተጠንቀቅ ላይ ይገኛሉ፡፡ ሶስት ቢራቢሮ የሚመስሉ ፍጡሮች የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ አናት ላይ እያንዣበቡ በመዞር ይጠብቋችኋል ጠንቅቃቺሁ ተመልከቱ ፡፡

ርዕዮት በፍጹም ብቻዋን አልነበረችም፣

ርዕዮት ዓለሙ በመለስ ዜናዊ የማጎሪያ እስር ቤት ለአራት ዓመታት ከ17 ቀናት በፍጹም ብቻዋን አልነበረችም፡፡

ከቤተሰቦቿ፣ ከጓደኞቿ እና ከዘመዶቿ ተለይታ ቆይታለች፡፡

እናት እና አባቷ ብቻ እንዲያዩዋት ተፈቅዶ ነበር፡፡ (የእርሷ አባት ከሆኑት እና በተጨማሪም የሕግ አማካሪ ጠበቃዋ ከሆኑት አባቷ ጋር እንኳ የሕግ ምክር ውይይት እንዲያደርጉ አየፈቀድላትም ነበር፡፡)

ቢሆንም ግን ርዕዮት በፍጹም ብቻዋን አልነበረችም፡፡

እርሷን የሚወዷት እና የሚደግፏት በዓለም ዙሪያ ሁሉ በሺዎች የሚጠቆሩ ሰዎች አሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች ለሁልጊዜ በአዕምሯቸው እና በመንፈሳቸው ከእርሷ ጋር ነበሩ፡፡

በፌስቡክ ድረ ገጽ እና በማህበራዊ የመስመር የግንኙነት ዘዴዎች አማካይነት የሚጽፉላት ወጣት እና ቁጡ የሆኑ ወገኖች አሏት፡፡

በምንም ዓይነት መልኩ በፍጹም ብቻዋን አልነበረችም፡፡

ታላቅ ክብርን ለሚያጎናጽፉ ዓለም አቀፍ የፕሬስ ድርጅቶች ተሸላሚ እንድትሆን ስሟን በጥቆማ የሚሰጡ በርካታ ወገኖች ነበሩ፡፡

በፍጹም ብቻዋን አልነበረችም፡፡

ሌሎችም ለቁጥር የሚያዳግቱ እንደ እኔ ያሉ የእርሷን እና ሁሉንም በወያኔ እስር ቤት በመማቀቅ ላይ ለሚገኙት የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች እና ጀግኖች የማይበገሩትን የእስክንድር ነጋን፣ ዉብሸት ታዬን፣ ተመስገን ደሳለኝን፣ አብርሃ ደስታን፣ የዞን 9 ጦማሪያንን እና እንደ እነርሱ ያሉትን ሌሎች የፖለቲካ እስረኞችን ጉዳይ የእራሳቸው የግል ተልዕኮ አድርገው የሚከታተሉ ወገኖች ነበሩ፡፡

ባገኘሁት አጋጣሚ ሁሉ በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የህሊና ፍርድ አደባባይ በመቆም ስለ ርዕዮት ጥብቅና ቆሜ ስሟገት ታላቅ ክብር ይሰማኛል፡፡

በርዕዮት ጉዳይ ላይ በተለይም ወይም ደግሞ በኢትዮጵያ ጋዜጠኞች እና በአጠቃላይ በሰው ልጆች ላይ በወያኔው አምባገነን ገዥ አካል ስለሚፈጸመው ወንጀል በርካታ ትችትችን ጽፊያለሁ፡፡

እ.ኤ.አ ግንቦት 2012 “ርዕዮት ዓለሙ፡ የኢትዮጵያ ፕሬስ ነጻነት ወጣቷ ጀግኒት“ በሚል ርዕስ አቅርቤው በነበረው ትችቴ ላይ ርዕዮት ለምን እንደታሰረች ግልጽ አድርጌ ነበር፡፡

ርዕዮት እና ከእርሷ ጋር እንዲከላከል የተያዘው ውብሸት ታዬ እ.ኤ.አ ሰኔ 2011 በቁጥጥር ስር ውለው በስልክ እና በኤሌክትሪክ መስመሮች ላይ አደጋ ለመጣል የሚል የፈጠራ ክስ በወያኔው ስብስብ የሀሰት ውንጀላ ተፈብሮኮ ወደ መለስ የማጎሪያ እስር ቤት እንዲወረወሩ ተደረገ፡፡ ለወራት ያህል ምንም ዓይነት ግንኙነት ሳይኖር በእስር ቤት ታጉረው ቆዩ፡፡ ሌላው ቀርቶ የግፍ ሰለባዎችን የሕግ ጠበቃዎች እንኳ እንዲጎበኟቸው አይፈቀድም ነበር፡፡

ርዕዮት በቁጥጥር ስር ለመዋሏ ትክክለኛው ምክንያት በዚያው ዓመት ሰኔ 17 በወጣ ፍትህ እየተባለ ይጠራ በነበረው እና በተከታታይ ከህትመት ውጭ ሆኖ በታገደው ሳምንታዊ መጽሔት ላይ ጽፋ ባወጣችው ጽሁፍ ነበር፡፡

በዚያ ባወጣችወ ጽሁፏ ላይ ርዕዮት አሁን በህይወት የሌለውን አምባገነኑን መለስ ዜናዊን ታላቁ የሕዳሴ ግድብ እየተባለ ሌት ቀን ስለሚደሰኮርለት የቅንጦት ግድብ የገንዘብ ማሰባሰብ ዘመቻ በቁጥር አንድ የሀገሪቱ አምባገነን ላይ ደፍራ ጥያቄ በማቅረቧ ነበር፡፡

እ.ኤ.አ መስከረም 2011 አሁን በህይወት የሌለው መለስ በግል ትዕዛዝ በመስጠት ውብሸት እና ርዕዮት “የሽብር ድርጊት ለመፈጸም እና ከአሸባሪ ድርጅት ጋር ተሳትፎ በማድረግ ደባ ለመስራት አሲረዋል” የሚል የፈጠራ የክስ ወንጀል ተፈብርኮ ክስ እንዲመሰረትባቸው አደረገ፡፡

በርዕዮት ላይ የቀረበው “ደባ ለመፈጸም እየተባለ በመለስ ዜናዊ የይስሙላ የዝንጀሮ ፍርድ ቤት ይጠራ የነበረው ማስረጃ በኢሜል የተጻጻፈቸው እና በባለሽቦ ስልክ ስለሰላማዊ ተቃውሞ እና ለውጥ ስለማምጣት በሚል ከሌሎች ጋዜጠኞች ጋር የተነጋገረችው ተቀድቶ የቀረበ ነበር፡፡

ርዕዮት እና ውብሸት ወደ ችሎት ከመቅረባቸው በፊት በነበሩት ሶስት የእስር ወራት ጊዜ ውስጥ የህግ አማካሪ የማግኘት እድሉ አልነበራቸውም፡፡

ሁሉቱም ጋዜጠኞች የህግ አማካሪ እንዳያቀርቡ ተከልክለዋል፡፡

የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ የይስሙላ የዝንጀሮው ፍርድ ቤት እስር ቤቱ የማሰቃየት ድርጊት እያስፈጸመብን ስለሆነ፣ ከህግ አግባብ ውጭ የሆነ አያያዝ ያለ በመሆኑ እና ህክምና እንዳናገኝ ክልከላ ተደርጎብናልና ምርመራ ይደረግልን በማለት የቀረበውን ውንጀላ አልቀበልም በማለት ውድቅ አደረገ፡፡

ከእስር ቤት እንድትለቀቅ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥያቄ በቀረበላት ጊዜ ርዕዮት ከህግ አማካሪዎቿ ጋር መገናኘት እንዳትችል ከተፈረደባት ጊዜ ጀምሮ ለሁለት ዓመታት ያህል ተከልክላ የቆየች መሆኑን አረጋግጣለች፡፡

እ.ኤ.አ ጥቅምት 2012 “የኢትዮጵያ ርዕዮት፡ የጥናካሬዬ ዋጋ“ በሚል ርዕስ ባቀረብኩት ትችት “ክብር በእሳት ፈተና ላይ” በማለት ትክክለኛ ትርጉሙን ግልጽ አድርጌ ነበር፡፡

እ.ኤ.አ የ2012 የደፋር ጋዜጠኝነት ሽልማት/Courage in Journalism Award አሸናፊ መሆኗን ተከትሎ በእጅ ጽሁፏ አዘጋጅታ በዓለም አቀፍ የሴቶች ሜዲያ ፋውዴሽን/International Women’s Media Foundation (IWMF) ስነስርዓት ላይ ቀርቦ እንዲነበብላት በድብቅ ከማጎሪያው እስር በት እንዲወጣ ባደረገችው ደብዳቤ ላይ “ድምጽ ለሌላቸው ድምጽ” ከመሆን የበለጠ ዋጋ የሚያስከፍለኝ ምንም ዓይነት ነገር የለም በማለት ግልጽ አድርጋ ነበር፡፡ ለድፍረቷ ከፍተኛ የሆነ ዋጋ ሊያስከፍላት እንደሚችል እና እውነታውን በጽናት መቀበል እንዳለባት አሳምራ ታውቅ ነበር፡፡

ርዕዮት እ.ኤ.አ ሀምሌ 9/2015 ከመለስ የማጎሪያ እስር ቤት በተለቀቀችበት ዕለት የክርክር አመክንዮዋን እንደገና በድጋሜ አረጋግጣለች፡፡

የፈለገውን ያህል ዋጋ ቢያስከፍልም በኢትዮጵያ ዴሞክራሲ እና ፍትህ እንዲሰፍኑ በጽናት ለመታገል ቆርጣ የተነሳች መሆኗን አውጃለች፡፡ ትክክለኛ የድፍረት ትርጉሙ ምን እንደሆነ ለእኔ እና ለሁሉም ደጋፊዎቿ አስተምራናለች፡፡

የስዊድን ጋዜጠኞች ማርቲን ሽብዬ እና ጆሀን ፔርሰን እራሳቸው አሁን በህይወት በሌለው በመለስ ዜናዊ እ.ኤ.አ ሰኔ 2011 አሸባሪነት በሚል የሸፍጥ ክስ ተመስርቶባቸው ለመጀመሪያ ጊዜ ርዕዮትን በእስርኞች የማማላለሻ አውቶብስ ውስጥ ሆና እጆቿ በካቴና ታስረው ለፌዴራል የመጀመሪያ ፍርድ ቤት በመቅረብ ላይ እንዳለች ያገኟት መሆናቸውን ግልጽ አድርገዋል፡፡

ሽብዬ “ምን እያደረግሽ ነው?” በማለት ጥያቄ አቀረበላት፡፡

ርዕዮት እንዲህ በማለት ምላሽ ሰጠች፣ “እኔ ጋዜጠኛ ነኝ፣ ብቻችንን አይደለንም፣ በርካታ የፖለቲካ እስረኞች ነን እዚህ በአሸባሪነት ወንጀል ተከስሰን ያለነው“ በማለት እስር ቤቶቹን አመላከተችው፡፡

ርዕዮት ለሽብዬ እንዲህ በማለት ነገረችው፣ “በምትፈታበት ጊዜ እኔ ምንም ዓይነት አሸባሪ ያለመሆኔን ለእውነት የምሰራ ጋዜጠኛ መሆኔን ለዓለም ህዝብ ሁሉ ንገርልኝ፡፡“

ሽብዬ ትኩር አድርጎ ተመለከተ እና እንዲህ አለ፣ “እነዚህ ሁሉም ወጣት ኢትዮጵያውያን ጋዜጠኞች ለአንድ ምርጫ ተዳርገዋል፡፡ ብሩህ አዕምሮ ያላቸው እና የተማሩ ናቸው፣ ቀላል የሆነ ህይወትን መምረጥ ይችሉ ነበር፡፡ ሌሎችን የሙያ ዘርፎች መርጠው መሰማራት ይችሉ ነበር፡፡ ሆኖም ግን እውነትን፣ ሀገራቸውን እና ወገኖቻቸውን በማፍቀራቸው ጋዜጠኞች የመሆን ምርጫቸውን ይዘዋል፡፡“

ርዕዮት በፍጹም ብቻዋን አልነበረችም፣

ርዕዮት ዓለሙ፣ እስክንድር ነጋ፣ ውብሸት ታዬ፣ ተመስገን ዳሳለኝ፣ አብርሃ ደስታ፣ የዞን 9 ጦማሪያን እና ሌሎቹ እንደ እነርሱ ተመሳሳይ የሆኑት በኢትዮጵያ የሚገኙት በርካታዎቹ የፖለቲካ እስረኞች ብቻቸውን አይደሉም፡፡ በእያንዳንዷ ዕለት እና ሰከንድ በእዕምሮ እና በመንፈስ ከእነርሱ ጋር ነን፡፡

ርዕዮት ከፍተኛ ተጽዕኖ ማሳደር የሚችሉ ጓደኞች ነበሯት፣

የጋዜጠኞች ተከላካይ ኮሚቴ (ጋተኮ)/CPJ የእርሷ ጉዳይ ከሌሎች በእስር ላይ ከሚገኙት ጋዜጠኞች ጉዳይም ጋር ተመሳሳይ እንደሆነ በማስረጃ የተደገፈ ዘገባ ስላለው ለበርካታ ዓመታት ከፍተኛ የሆነ ጥረት በማድረግ ሲከታተለው ቆይቷል።

ጋተኮ/CPJ በኢትዮጵያ በተደጋጋሚ የሽብር ወንጀል እየተባለ በነጻ ዘገባ ላይ የሚደረገውን የጽሑፍ ምርመራ አውግዟል፡፡

ጋተኮ/CPJ እንዲህ በማለት የኢትዮጵያን መንግስት ለማስተማር እና ወደ ህሊናው እንዲመለስ ሲያስተምር ቆይቷ፣ “የኢትዮጵያ ጨካኝ አምባገነኖች መንግስት አሸባሪ ናቸው ብሎ ከፈረጃቸው ድርጅቶች እና ቡድኖች ጋር ዘጋቢዎች መነጋገር መቻላቸውን አይወድም፡፡ ሆኖም ግን ጋዜጠኞች ማድረግ ያለባቸው እንደ እነዚህ ያሉ ተግባራትን ነው፡፡ ከዚህ ያነሰ ስራን የሚያከናውኑ ከሆነ ዝም ብሎ ተራ ወሬ የሚያስተላልፍ አፈ ቀላጤ የመሆን ትግባራትን መፈጸም ብቻ ነው የሚሆነው፡፡ ባለስልጣኖቹ እንደዚህ ዓይነቶቹን የሞኝ የውንጀላ ክሶች በአስቸኳይ እርግፍ አድርው በመተው ጓደኞቻችንን መልቀቅ አለባቸው፡፡”

ሂዩማን ራይትስ ዎች/HRW በአጠቃላይ ከርዕዮት ጎን ነበር፣

ሂዩማን ራይትስ ዎች/HRW በርዕዮት እና በውብሸት ላይ ተመስርቶ የነበረውን የድድብና ክስ እንዲህ በማለት አውግዟል፡፡ “እንደ ክሱ ፋይል ከሆነ ማስረጃው በዋናነት በድረ ገጽ መስመሮች በመጠቀም በመንግስት ላይ ሸንቋጭ የሆነ ትችቶችን የሚያቀርቡትን እና በስልክ የተደረጉትን ውይይቶች በተለይም በምንም ዓይነት ሁኔታ ከሽብር ወንጀል ጋር ሊገናኙ የማይችሉትን ስለሰላማዊ ተቃውሞ ድርጊቶች የሚደረጉት ውይይቶች ናቸው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በመጀመሪያ በቀረበው የክስ ፋይል ላይ ተከላካዮች ለተከሰሱበት ወንጀል ሌላው ቀርቶ መሰረታዊ የሆኑ የወንጀል ዝርዝሮችን እንኳ ያላሟ ነው…“ በማለት በይፋ ተቃውሞታል፡፡

አምነስቲ ኢነተርናሽናል የተባለው ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅትም ከርዕዮት ጎን በመሰለፍ የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ የይስሙላ የዝንጀሮ ፍርድ ቤት በእርሷ ላይ እያደረገ ባለው የችሎት ሂደት ላይ ያለውን ቁጣ እንዲህ በማለት ገልጿል፡፡ “ምንም ዓይነት የወንጀል ጥፋት ለማጥፋታቸው ሊያስረዳ የሚችል ማስረጃ የለም፡፡ እነዚህ እስረኞች ህጋዊ በሆነ መልኩ መንግስትን በመተቸታቸው ምክንያት እየተቀጡ ያሉ የህሊና እስረኞች ናቸው ብለን እናምናለን፡፡ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ባስቸኳይ መፈታት አለባቸው፡፡“

ፓምባዙካ የዜና ወኪል/Pambazuka News ርዕዮት መፈታት እንድትችል የውትወታ ዘመቻ አደራጅቶ ነበር፡፡ ፓምባዙካ እንዲህ በማለት አውጆ ነበር፣ “የመንግስትን ኢፍትሀዊነት መርህን መሰረት ባደረገ መልኩ ለእውነት እና ለፍትህ በጽናት በመቆሟ ምክንያት ዓለም አቀፍ ዝናን እንድትጎናጸፍ አስችሏታል፡፡“

ደፋር ጋዜጠኞችን እየመረጠ ሽልማት የሚሰጠው  ዓለም አቀፍ የሴቶች ሜዲያ ፋውንዴሽን ሽልማት/International Women’s Media Foundation’s Award የሎስአንጀለስ ታይምስ/Los Angeles Times መጽሔት እ.ኤ.አ በ2012 የአሸናፊነት ሽልማቱን በሰጠበት ወቅት ለርዕዮት እንዲህ በማለት ተሟግቶላት ነበር፣ “ርዕዮት ዓለሙ በቬርሊ ሂልስ በተደረገው ጠቃሚ እራት ግብዣ ላይ ሳትገኝ ቀርታለች፡፡ ሆኖም ግን ጥሩ ይቅርታ ይደረግላታል፡፡ የ31 ዓመቷ ጋዜጠኛ የኢትዮጵያ መናገሻ በሆነችው በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኘው እና በጣም አስከፊ በሆነው አይጦች በሚተራመሱበት እና ቃሊቲ እየተባለ በሚጠራው እስር ቤት ውስጥ ታስራ ትገኛለች፡፡ ስለድህነት፣ ስለተቃውሞ ፖለቲካ እና ስለጾታ እኩልነት በድፍረት በመጻፏ ምክንያት ከተበየኑባት አምስት ዓመታት ውስጥ በአሁኑ ጊዜ በሁለተኛው ዓመት እስር ላይ ትገኛለች፡፡“ 

ርዕዮት ከጎኗ የቆሙ ወንድሞችም አሏት፣

ኤሊያስ ወንድሙ፣ የጸሐይ አሳታሚዎች አሳታሚ፣ በርዕዮት ስም ሽልማቱ ከሚገኝበት ቦታ በመገኘት IWMF ያዘጋጀላትን እና አሸናፊ የሆነችበትን ሽልማት ተቀብሎላታል፡፡

ኤሊያስ በርዕዮት ስም ሽልማቱን ከተቀበለ በኋላ እንዲህ ብሎ ነበር፣ “ርዕዮትን ለዚህ ሽልማት ስጠቁም በእርሷ ላይ ያለውን ድፍረት ለማሳየት ነበር የፈለግሁት፣ ስለሆነም በሀገራችን ያሉ ልጃገረዶች ድምጽ ለሌላቸው ድምጽ የለሾች ድምጽ ለመሆን ከመደፋፈር ወደኋላ አይሉም፡፡ የአንድን መንግስት ፖሊሲ በመጻፍ ትችት የሚያደርግን ሰው በአሸባሪነት መክሰስን እንዴት አድርጎ በመሬት ላይ ማነጻጸር ይቻላል?“

ኤሊያስ እንዲህ የሚል ሌላ አማራጭ ሰጥቶ ነበር፣ “ተገቢ በሆነ ስልጠና እጥረት መሰረት ጋዜጠኞቻችን ፍጹም አይደሉም ሊሆኑም አይችሉም፣ ሆኖም ግን ለዚህ መፍትሄ ሊሆን የሚችለው የሚሰሯቸውን ስህተቶች እየተከታተሉ ወንጀለኛ በማድረግ መቅጣት ተገቢ አይደለም፣ ሆኖም ግን ማረም እና ማስተማር ተገቢ ይሆናል፡፡“

የርዕዮት የእጅ ጽሁፍ ደብዳቤ ከመለስ ዜናዊ የማጎሪያ እስር ቤት ሾልኮ በመውጣት ለIWMF በመድረስ እውነተኛውን የጋዜጠኝነት ድፍረት በተገባር አሳይቷል፡፡ በቁራጭ ወረቀት ላይ በመጠቀም የሚከተሉትን ቃላት አስፍራ ነበር፡

በኢትዮጵያ ወደፊት የተሻለ ነገርን ለማምጣት አንድ ነገር ማበርከት እንዳለብኝ እምነት አለኝ፡፡ በኢትዮጵያ በርካታ ኢፍትሀዊነቶች እና ጭቆናዎቸ ስላሉ በማወጣቸው ጽሁፎቼ አማካይነት ማጋለጥ እና መቃወም አለብኝ፡፡ ምክንያቱም ጋዜጠኝነት እራሴን በፅናት ላሰማራበት የሚገባ ሙያ በመሆኑ ነው፡፡ ለኢህአዴግ ጋዜጠኝነት ማለት ለፕሮፓጋንዳ ስራ ለገዥው ፓርቲ መጠቀሚያ ብቻ አድርጎ እንደሚያየው አውቃለሁ፡፡ ሆኖም ግን ለእኔ ጋዜጠኞች ድምጽ ለሌላቸው ድምጽ የለሾች ድምጽ ናቸው፡፡ ለዚህም ነው የተጨቆኑትን የሚያጋልጡ በርካታ ጽሁፎችን የጻፍኩት፡፡

ነጻነትን ዴሞክራሲን ለመጠየቅ ወደ አደባባይ በመውጣት በመንገዶች ላይ ሰላማዊ ሰልፍ የሚያደርጉ ንጹሀን ዜጎችን በጥይት መደብደብ፣ የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎችን እና ጋዜጠኞችን ወደ እስር ቤት ማጋዝ…እንዲሁም የመናገር፣ የመደራጀት ነጻነትን መከልከል እና ፕሬስን ማፈን፣ በሙስና መዘፈቅ፣ የአንድ ጎሳ ቡድን በሌሎች ላይ የበላይ ሆኖ መቅረብ የመሳሰሉት ነገሮች የመንግስታችን ጥቂት መጥፎ ስህተቶች ናቸው፡፡ እንደዚህ ያሉ ዘገባዎችን ፈልፍዬ በማውጣት በማሳየው ድፍረት ዋጋ ሊያስከፍለኝ እንደሚችል አስቀድሜ አውቃለሁ፡፡ እናም ያንን ዋጋ ለመቀበል ዝግጁ ነበርኩ፡፡

እ.ኤ.አ በ2013 ርዕዮት የዩኔስኮን የጉሌርሞ ካኖንን ዓለም አቀፍ የፕሬስ ነጻነት ሽልማት/UNESCO Guillemo Cano World Press Freedom Prize አሸናፊ ሆና ተሸልማለች፡፡

ሽልማቱን ከሰጠ በኋላ ዩኔስኮ እንዲህ የሚል ጥቆማ ሰጥቶ ነበር፣ “ወ/ት ርዕዮት ነጻ በሆነ ዓለም አቀፍ የሜዲያ ባለሙያዎች የዳኞች ቡድን ላሳየችው ልዩ የሆነ ድፍረት፣ እምቢተኝነት እና ሀሳብን በነጻ ለመግለጽ ባላት የዓላማ ጽናት ለእርሷ ዕውቅና በመስጠት ለሽልማቱ እንድትቀርብ ተደርጓል፡፡“

ርዕዮት ዓለሙ እ.ኤ.አ ሀምሌ 9/2015 ከአሜሪካ ድምጽ የአማርኛው አገልግሎት ጋር ያደረገችው ቃለመጠይቅ፣

ርዕዮት ዓለሙ በአሜሪካ ደምጽ የአማርኛው አገልግሎት ጋዜጠኛ በሆነው በሰለሞን አባተ ቃለ  መጠይቅ ተደርጎላታል፡፡ (ከዚህ በታች ያለው በእንግሊዝኛ ከተረጎምኩት በመውሰድ እንደገና ወደ አማርኛ የተተረጎመ የእራሴ ትርጉም ነው፡፡ የርዕዮትን ቃላት በተቻለ መጠን ትክክለኛ ትርጉማቸውን በማዘጋጀት የቃላት ትርጉማቸውን ብቻ ሳይሆን ተመሳስሎዎችን እና የተለመዱ የቋንቋ አባባሎችንም በማከተት ለማቅረብ ሞክሪያለሁ፡፡)

ወደ እንግሊዝኛ ተተርጉሞ የነበረው ቃለመጠይቅ እንደገና ወደ አማርኛ ተመልሶ ለአንባቢዎች እንደሚከተለው ቀርቧል፡

ሰለሞን፡ ርዕዮት ዓለሙ፣ እንኳን ደስ ያለሽ (ከእስር ቤት በመፈታትሽ ምክንያት) እናም እንኳን በሰላም ወደ ቤትሽ ለመመለስ አበቃሽ፡፡

ርዕዮት፡ እናንተንም እንኳን በሰላም ለማግኘት አበቃኝ፡፡

ሰለሞን፡ ከእስር ቤት በመለቀቅሽ ምክንያት ደስ የተሰኙ በርካታ ሰዎች አሉ፡፡ ለመሆኑ በስንት ሰዓት ነው ከእስር ቤት የተለቀቅሽው?

ርዕዮት፡ ወደ 4 ሰዓት አካባቢ ይሆናል ብዬ አስባለሁ፡፡ ሆኖም ግን ሰዓቱን በእርግጠኝነት አላረጋገጥኩም፡፡

ሰለሞን፡ ጧት ነበር የተፈታሽው?

ርዕዮት፡ አዎ፡፡

ሰለሞን፡ የመፈታትሽ ሁኔታ እንዴት ነበር? ከእስር ቤት ሲለቅቁሽ ምንድን ብለው ነገሩሽ? ከእስር ቤት እንደምትለቀቂ ቀደም ሲል የምታውቂው ነገርስ ነበርን?

ርዕዮት፡ የማውቀው ነገር አልነበረም፡፡ ወደ እኔ በቀጥታ በመምጣት ሂጂ አሉኝ፡፡ ቀልድ ነው የሚል ሀሳብ ነበረኝ፡፡ ለምን እና በምንድን ምክንያት ነው ከእስር ቤት የምለቀቀው በማለት ጥያቄ አቅርቤ ነበር፡፡ እንዲህ አሉ፣ “ከዚህ ውጭ!“ ምክንያቱም ከሌሎች እስረኞች ጋር ምን እንደሚያደርጉ ስለምገነዘብ ነው ለምን እና በምንድን ምክንያት ነው ከእስር ቤት የምለቀቀው በማለት ጥያቄ አቅርቤ የነበረው፡፡ ስለእኔ ከእስር ቤት የመለቀቅ ሁኔታ ያልተጣራ እና የተድበሰበሰ ዘገባ ለህዝብ እናቀርባለን የሚል ሀሳብ ካላችሁ እኔ እውነቱን እንደምናገር ታውቁታላችሁ፡፡ ስለሆነም እውነቱን ለህዝብ ከተናገርኩ በኋላ መልሳችሁ ወደዚህ እስር ቤት የምታመጡኝ ከሆነ ከእስር ቤት አለመቀቄን እወዳለሁ፡፡

ከዚያ በኋላ እንዲህ የሚል ጥያቄ አቀረብኩላቸው፣ “ምንድን ነው እየተካሄደ ያለው?“ እንዲህ አሉ፣ “ይኸው ነው፡፡“ እኔ ይቅርታ ወይም ደግሞ ምንም ዓይነት ቅደመ ሁኔታ አልጠይቅም፡፡ ይቅርታ የመጠየቂያ ጊዜዬ ቀደም ሲል አልፏል እና እርሱንም አልቀበልም በማለት ውድቅ አድርጌዋለሁ ምክንያቱም በመጸጸት ቀርቦልኝ በነበረው ቅጽ ላይ “ወደ ቀድሞው ሁኔታ ተመልሻለሁ የሚል ቋንቋ ነበረበት፡፡” ያጠፋሁት ጥፋት ስላልነበር ያንን ጥፋት ያላጠፋሁ መሆኔን አምኘ ያንን ቅጽ አልሞላም በማለት እንዲመለስ አድርጌ ነበር፡፡

መፈታት የነበረብኝ እ.ኤ.አ ጥቅምት 2014 ነበር፡፡ የእኔ በቅድመ ሁኔታ የመፈታት ሁኔታ አልፏል አሉ፡፡ ስለሆነም ከእስር ቤት እንለቅሻለን፡፡ እንግዲህ የሰጡኝ አጭሩ መልስ ይኸ ነበር፡፡ ለእኔ ከእስር ቤት መለቀቅ መሰረቱ ያ ነበር፡፡

ሰለሞን፡ በነገራችን ላይ የጤንነትሽ ሁኔታ እንዴት ነው?

ርዕዮት፡ ሁላችሁም እንደምታውቁት ከጥቂት ዓመታት በፊት በአንደኛው ጡቴ ላይ የቀዶ ህክምና ተደርጎልኛል፡፡ሌላኛው ጡቴ በአሁኑ ጊዜም እብጠት ይታይበታል፡፡ ቀዶ ህክምና ያስፈልገዋል ብለውኛል፡፡ በእስር ቤት ውስጥ ቀዶ ህክምና እንዲደረግልኝ አልፈለግሁም ምክንያቱም ከዚህ ቀደም በአንደኛው ጡቴ ላይ ቀዶ ህክምና ተደርጎልኛል እናም ጥቂት ወሰብሰብ ያሉ ነገሮች ተፈጥረውብኝ ነበር፡፡ ይህንን ነገር አላደረግሁትም፡፡ በአሁኑ ጊዜ እግዚአብሔር የሚፈቅድ ከሆነ አሰራዋለሁ የሚል ሀሳብ አለኝ፡፡

ሰለሞን፡ የምርመራ ውጤቶች በሁለቱም ጡቶችሽ ላይ ምን ያመላክታሉ?

ርዕዮት፡ ከሁለቱ አንደኛው የተሻለ ነገር ያሳያል፡፡ ሌላኛው ከጊዜ ወደ ጊዜ እያመመኝ ነው የመጣው፡፡

ሰለሞን፡ ከነገርሽኝ ሌላ በተጨማሪ መደበኛ የሆነ የህክምና ምክር እና የትኩረት ድጋፍ አላገኘሽም ነበርን? ጥብቅ የሆነ የሕክምና ክትትል ታደርጊ ነበርን?

ርዕዮት፡ በፍጹም እንደዚያ አልነበረም፡፡

ሰለሞን፡ በየዕለቱ እና በየሳምንቱ የሕክምና ምክር ይሰጥሽ ነበርን? የሕክምና ምክር  ወይም ደግሞ የሕክምና ምርመራ ይደረግልሽ ነበርን?

ርዕዮት፡ የለም፡፡ በፍጹም እንደዚያ አልነበረም፡፡ ቀደም ሲል እንዳልኩት ቀዶ ሕክምና መደረጉን ከተውኩት በኋላ እንደ ሳይነስ ለመሳሰሉት ነገሮች ካልሆነ በስተቀር ለዚህኛው ጉዳይ የሕክምና ትኩረት አላገኘሁም ነበር፡፡ የሕክምና ክብካቤ አላገኘሁም፡፡ ምንም ዋጋ የሌለው ነገር ቢሆንም እንኳ የቀዶ ሕክምና እንዳደርግ ነግረውኝ በፍጹም አላደርገውም ብያለሁ፡፡ ምንም ዓይነት የቀዶ ሕክምና ላለማድረግ ወስኘ ነበር፡፡ ምክሮች ያስፈልጋሉ የሚል አስተሳሰብ አልነበረኝም፡፡ ቀደም ሲል እንደተናገርሁት ከወር በፊት የሕክምና ትኩረት አግኝቼ ነበር፡፡ ስለእኔ ጡቶች ጉዳይ ከእነርሱ ጋር ምንም ዓይነት ንግግር አላደረግሁም፡፡

ሰለሞን፡ በእስር ቤት ስለቆየሽበት ሁኔታ ጥቂት ልትነግሪኝ ትችያለሽን? ይቅርታ አድርጊልኝ ወደዚያ መልሸ ልወስድሽ አልፈልግም ነበር፡፡ ሆኖም ግን ስለዚያ ጉዳይ ማወቅ የሚፈልጉ በርካታ አድማጮች ስላሉ ነው፡፡

ርዕዮት፡ አዎ፡፡ ስለዚያ ጉዳይ እንዴት አድርጌ እንደምነግርህ አላውቅም፡፡ እንደ እስረኛው ሁኔታ ይለያያል፡፡ አጠቃላይ በሆነ ለመናገር ስለእስረኞች ያለው አያያዝ ጥሩ ነው የሚባል አይደለም፡፡ ሆኖም ግን የፖለቲካ እስረኞች በተለዬ ሁኔታ ጥሩ በሆነ ሁኔታ የሚያዙ አይደለም፡፡ የእኔን ጉዳይ ብትወስድ ለአንድ ዓመት ከ8 ወራት ያህል ቤተሰቦችን እንዳላይ ተከልክየ ነበር፡፡ እናት እና አባቴን ብቻ እንዳይ ይፈቀድልኝ ነበር፡፡ ባለፉት ሶስት ወራት ብቻ ነው እህቴ መጥታ እንድትጎበኘኝ የተፈቀደው፡፡

ስለሆነም ከቤተሰቦቼ ጉብኝት ጀምሮ መብቶቼ አይጠበቁም ነበር፡፡ ሕጉ የሚለው ነገር ቢኖር የኃይማኖት አባቴን፣ የሕግ አማካሪ ጠበቃዬን እና ሌሎችንም ሰዎች የማግኘት እና እርዳታ እና ምክር የማግኘት መብት እንዳለኝ በግልጽ ተቀምጧል፡፡ ቀደም ሲል እንደተናገርኩት ባለፉት ሁለት እና ሶስት ወራት ብቻ ነበር እህቴ እንኳ መጥታ እንድታየኝ የተፈቀደው፡፡ ለአንድ ዓመት እና ለ8 ወራት ሙሉ እናቴ እና አባቴ ብቻ ናቸው እየመጡ እንዲጎበኙኝ ተፈቅዶላቸው የነበረው፡፡

በእስር ቤት ውስጥ በርካታ ችግሮች ነበሩ፡፡ ለምሳሌ ያህልም የመጽሐፍት ችግር፡፡ መጽሐፍት በተለይም የፖለቲካ መፅሐፍ ለማግኘት እንዲያውም ፖለቲካ የምትል ቃል ያለበት መጽሐፍ በተለይም በአሁኑ ጊዜ ከታዬ እንኳ ከፍተኛ የሆነ ቸግር ነበር፡፡ እንግዲህ መጽሐፍትን ከውጭ ለማግኘት ነው ይኸ ሁሉ ችግር ያለው፡፡ ሌሎችን በርካታ ነገሮችን መግለጽ እችላለሁ፡፡ በአጠቃላይ በእስር ቤት የነበረው ቆይታዬ ጥሩ አልነበረም፡፡ እስር ቤት በፍጹም ጥሩ ነገር ሊሆን አይችልም፡፡ ለእኔ የስቃይ ጊዜ ነበር፡፡

ሰለሞን፡ አባትሽ የአንች የሕግ አማካሪ ጠበቃ ነበሩን?

ርዕዮት፡ አዎ አባቴ የእኔ የሕግ አማካሪ ጠበቃዬ ነበር፡፡ እንደዚሁም ሌላም ጠበቃ ነበረኝ፡፡

ሰለሞን፡ አባትሽን እንደ እራስሽ የሕግ ጠበቃ እንጅ እንደሌላ የሕግ ጠበቃ አልነበረም የምታያቸው?

ርዕዮት፡ አይደለም፡፡ ሁለቱንም በአንድ ጊዜ ማግኘት አልችልም ነበር፡፡ ላለፉት ሁለት ዓመታት ከማንም ጋር ግንኙነት አልነበረኝም፡፡ አባት እና እናቴ ወደ እስር ቤት በመምጣት ይጎበኙኝ ነበር፡፡ ሆኖም ግን አባቴ ለሕግ ምክር አገልግሎት አይመጣም ነበር፡፡ ስለአኔ የህግ ጉዳዮች ምንም ነገር መነጋገር አንችልም ነበር፡፡ ወይም ደግሞ ሌላ የሕግ አማካሪም እንዳገኝ እና ምክር እንድቀበል አይደረግም ነበር፡፡

ሰለሞን፡ በእስር ቤቱ ውስጥ የነበረው ንጽህና ስለምግቡ፣ ውኃው እና ስለሌሎች ተመሳሳይ ነገሮች የነበረው ሁኔታ እንዴት ነበር?

ርዕዮት፡ እኔ በቤተሰቦቼ የሚመጣልኝን ምግብ ነበር የምመገበው፡፡ የእስር ቤቱን ምግብም አይቸዋለሁ፡፡ ጥሩ ብለህ ይመትጠራው ነገር አይደለም፡፡ መጥፎ ነው፡፡ ከፍተኛ ወንጀል ፈጽመዋል ለተባሉ የፖለቲካ አስረኞች የሚቀርበው የተለመደው የኢትዮጵያ እንጀራ እና ወጥ ምግብ በጣም አስቀያሚ ነው፡፡

ሰለሞን፡ የኢትዮጵያ ባለስልጣኖች ስለፖለቲካ እስረኞች ጥያቄ ሲቀርብላቸው የሚሰጡት መልስ “ምንም ዓይነት የፖለቲካ እስረኞ የሉም” የሚል ምላሽ ይሰጣሉ፡፡

ርዕዮት፡ ያ ዓይን ያወጣ ውሸት ነው፡፡ እዚያ በርካታ የፖለቲካ እስረኞች እንዳሉ አውቃለሁ፡፡ ሌላው ቀርቶ ስለ እራሴ ሁኔታ እንኳ ልነግርህ እችላለሁ፡፡ የእኔ ጉዳይ እራሱ በርካታ የፖለቲካ እስረኞች እንዳሉ በቂ ማስረጃ ነው፡፡ እኔን ለእስር የሚያበቃ ምን ወንጀል ሰራሁ? ምናልባትም የእኔን የችሎት ክርክር ሂደት ተከታትለኸው ይሆናል፡፡ ሰለሆነም እነርሱ አሸባሪ የሚል ውንጀላ በመለጠፍ የሀሰት ክስ መስርተውብኝ የችሎት ሂደት ሲካሄድ በነበረው እና ሲቀርብ በነበረው ማስረጃ እንዳያችሁትም ምንም ዓይነት ሽብርተኝነትን ለመፈጸሜ ወይም ደግሞ የሽብር ድርጊት ሙከራ ለመፈጸሙ ሊያቀርቡ የሚችሉት ማስረጃ አልነበራቸውም፡፡

ይልቁንም እውነታው እና ትክክለኛው ነገር በስልጣን ላይ ስላለው ገዥ አካል ትችት በመጻፌ ምክንያት ነበር፡፡ ሆኖም ግን ስለአንዳንድ ነገሮች ትችት በመጻፋቸው ወይም ደግሞ የተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጀት አባል በመሆናቸው፣ ወይም ሰዎች ስለመብታቸው በመጠየቃቸው ብቻ የታሰሩ እያሉ ምንም ዓይነት የፖለቲካ እስረኞች የሉም የሚል መልስ መስጠታቸው ይቅርታ አድርግልኝ እና የመካድ አካሄድ ነው፡፡ ሆኖም ያንን የመሰለ ምላሽ በመስጠታቸው በጣም ጥቂት የሆኑ ሰዎችን ብቻ ሊያታልሉ ይችላሉ ብዬ ነው የማምነው፡፡

ሰለሞን፡ አብረውሽ የነበሩት ሌሎች እስረኞች ሁኔታስ ምን ይመስል ነበር? አያያዛቸው፣ መንፈሶቻቸው፣ እንዲሁም ሀሰቦቻቸው ምን ይመስል ነበር? በአጠቃላይ እዚያ በነበርሽበት ጊዜ ያለው የእስር ቤት ሁኔታ ምን ይመስል ነበር?

ርዕዮት፡ ወንጀል ለፈጸመ ሰው እና በእስር ቤት ላለ እንዲሁም ምንም ዓይነት ወንጀል ሳይፈጽም በቁጥጥር ስር ውሎ በእስር ቤት ያለ ሰው ሁሉም እስረኞች ቢሆኑም እንኳ ሰብአዊ መብቶቻቸው ሊጠበቁላቸው ይገባል፡፡ መሆን ያለበት ነገር ይህ ነው፡፡

በአሁኑ ጊዜ ያለው ከምግቡ ሁኔታ ጀምሮ መጥፎ ነገር ነው፡፡ በተለይም በአሁኑ ጊዜ በርካታ እስረኞኝ እየተያዙ እየገቡ እና እስር ቤቱን አጨናንቀውት ባለበት ሁኔታ የሚታየው ነገር ሁሉ አስከፊ ነው፡፡

ባለፉት ሁለት ዓመታት እስር ቤት በቆየሁባቸው ጊዚያት ከአጠቃላይ እስረኛ ህዝብ ተነጥለን ከሌሎች አራት እስረኞች ጋር ነበርኩ፡፡  ሆኖም ግን ሌሎች በጣም በተጨናነቀ ሁኔታ ላይ እየተጠበቁ ያሉበት ሁኔተ ነው የሚታየው፡፡ ስለመድኃኒት፣ ስለህክምና ያለው ሁኔታ በቂ ነው የሚባል አይደለም፡፡

የሕክምና ምርመራ የሚባል ነገር የለም፡፡ የህክምና ምርመራ የምታገኘው በከፍተኛ ሁኔታ በምትታመምበት ጊዜ ብቻ ነው፡፡ ሆኖም ግን ከዚያ ውጭ ለስቃይ ማስታገሻ መድኃኒቶችን ያዝዛሉ፡፡ በአብዛኛው በእስር ቤቱ ያለው ሁኔታ ይህንን ይመስላል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ ከፖለቲካ እስረኞች ጋር ሰላምታ ለማቅረብ የሚሞክር ሰው ካለ በርካታ የሆኑ ችግሮችን እንዲጋፈጥ ይደረጋል፡፡ ቦታው የጭንቀት ቦታ ነው፡፡ ከውጭው ሁኔታ ጋር ሲነጻጸር እንኳ ፍርሀት ንጉስ የሆነበት ግቢ ነው፡፡ በእስር ቤቱ ግቢ ውስጥ የምናየው ነገር እንግዲህ ይህንን ይመስላል፡፡

ሰለሞን፡ በርካታ ችግሮች በምትይበት ጊዜ ምን ዓይነት ችግሮች አሉ? የአካል ስቃይ የማሰቃየት ድርጊቶች ይፈጸማሉን? ድብደባዎች እና ሌሎች ነገሮችም ይፈጸማሉን?

ርዕዮት፡ እኔ እየነገርኩህ ያለሁት ስለሴት እስረኞች ሁኔታ ነው፡፡

ሰለሞን፡ ስለእዚያ ጉዳይ ዘርዘር ባለ ሁኔታ ብትነግሪኝ፡፡ የሴት እስረኞች አጠቃላይ ሁኔታ እና አያያዝ ምን ይመስላል? ከሕግ አግባብ ውጭ የሆነ አያያዝ ፈጸምባቸዋልን?

ርዕዮት፡ አዎ፡፡ይህንን ነው እየነገርኩህ ያለው፡፡ አንድ ሰው የፖለቲካ እስረኛ ጋር ሰላምታ በመለዋወጡ ምክንያት ችግር ሊደርስበት አይገባም ነበር፡፡ ሆኖም ግን ለፖለቲከ እስረኛ ሰላምታ ሲሰጥ ከታዬ ማስጠንቀቂያ ይሰጠዋል፣ ወይም ደግሞ ስለዚያ እስረኛ ጉዳይ የተለየ ትኩረት በመስጠት ይከታተሉታል፡፡ የተለየ ምርመራ ወይም እንደዚህ ያለ ነገር የሚካሄድበት ሆኖ ይቀመጣል፡፡ አየህ ነገሮች በእስር ቤት እንደዚህ ናቸው፡፡

ሰለሞን፡ የወደፊት ዕቅዶችሽ ምንድን ናቸው? በአጭሩ አጠቃላይ ያለሽ ምልከታ ምንድን ነው? ከዚህ በኋላ ምንድን ለማድረግ ታስቢያለሽ?

ርዕዮት፡ ቀደም ሲል እንደተናገርኩት ይህ ድንገተኛ የመፈታት ነገር ነው፡፡ ስለሆነም የነበረህን ጊዜ አጠናቅቀህ ስትወጣ ወይም በድንገት ስለተፈታህበት ነገር ስታውቅ ነው መናገር የምትችለው፡፡ ስለሆነም በድንገት እስከተፈታህ ድረስ ይህ ጥያቄ ለየት ያለ ሊሆን ይችላል፡፡

ሆኖም ግን በአሁኑ ጊዜ የማስበው ነገር ቀደም ሲል ተቋርጦ የነበረውን ህይወቴን እንደገና መምራት መቀጠል ነው፡፡ ለምሳሌ ያህል ምንም ዓይነት ትግል ያካሄድኩ ቢሆንም እንኳ በጽሁፍም ሆነ በማንኛውም በምችለው ነገር ሁሉ ዴሞክራሲ እና ፍትህ የሰፈኑባት ኢትዮጵያ እውን እስከምትሆን ድረስ ሙሉ በሙሉ ትግሌን እቀጥላለሁ፡፡ እንደዚህ የሆነች ኢትዮጵያን እስከማይ ድረስ ትግሌን በተጠናከረ መልኩ እቀጥላለሁ፡፡

(የቃለ መጠይቁ መጨረሻ)

ለርዕዮት እና በእስር ቤት ለቀሩት ለሌሎች ወንድሞቿ እና አህቶቿ ያለኝ የእኔ የግሌ አክብሮት፣

ሸክስፒር እንዲህ በማለት ጽፈው ነበር፣ “ጥቂቶች ታላቅ ሆነው ይወለዳሉ፣ ጥቆቶች በሂደት ስኬትን ይጎናጸፋሉ፣ ጥቂቶች ደግሞ በእራሳቸው ላይ በመተማመን ታላቅ ይሆናሉ፡፡“

ለጀግኖች እና ጀግኒቶች በተመሳሳይ መልኩ ማለት ይቻላል ብዬ አስባለሁ፡፡

እንደ ርዕዮት ዓለሙ፣ እስክንድር ነጋ፣ ውብሸት ታዬ፣ ተመስገን ደሳለኝ፣ አብርሃ ደስታ፣ የዞን 9 ጦማሪያን እና ሌሎችም እንደ እነርሱ ያሉ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ የፖለቲካ እስረኛ ዜጎች ጀግኖች እና ጀግኒቶች ሆነው አልተፈጠሩም፡፡ ጀግንነትንም አልፈለጉም ነበር፡፡ እድሉ የሚሰጣቸው ከሆነ ጀግንነትን ብቻውን ይተውታል፡፡ ጀግንነት እና ጀግኒነት ሲባል ብቻቸውን መተው ማለት አይደለም፡፡ ዕድል እና እጣ ፈንታ በጀግንነት ላይ ይተማመናሉ፡፡

በርዕዮት ዓለሙ እና በኢትዮጵያ የመጀመሪያዋ ሴት የፖለቲካ መሪ በነበረችው በብርቱካን ሚደቅሳ መካከል በርካታ በትይዩ የተሰመሩ ልዩነቶችን አስተውላለሁ፡፡ ብርቱካን ተመሳሳይ የሆኑ ከህግ አግባብ ውጭ የሆኑ የእስር ቤት አያያዞች ማለትም ለብቻ ነጥሎ ማሰር እና ማዋረድ  ተፈጽመውባታል፡፡ ብርቱካን በፖለቲካው ዘርፍ የመጀመሪያዋ መንገድ ፈጣሪ ብቻ አልነበረችም ሆኖም ግን ለኢትዮጵያ ወጣት ሴቶች ሞዴል እና አርአያ ጭምር የነበረች እንጅ፡፡ በአምባገነኑ የመለስ ዜናዊ የማጎሪያ እስር ቤት በጽናት በመቆም መንፈሰ ጠንካራነቷን በተግባር በማሳየት ትምህርት ሰጥታለች፡፡

ብርቱካን በአሁኑ ጊዜ እርሷ ተሸክማው የነበረውን ዓይነት ኃላፊነት ርዕዮት ተሸክማ ስታይ በኩራት በመሞላት በኢትዮጵያ የሩጫ ቅብብሎሽ ዱላውን ለሌላ በማስተላለፍ በማበረታታት ትመለከታለች፡፡ በእሳት የተፈተነ ክብር ምሳሌ የነበረች መሆኗን ወደ ኋላ መለስ ብላ ስትመለከት ትንሽ ፈገግ ትላለች፡፡

ርዕዮትን እና ብርቱካንን በማሰር ብቸኛ ኃላፊነቱን መውሰድ የሚገባው እና አሁን በህይወት የሌለው አምባገነኑ መለስ ዜናዊን ታሪክ የሰይጣን መልዕክተኛ በመሆኑ ብቻ ሳይሆን የተረገመ እና መቅኖ ያጣ ሰብአዊ ፍጡር ሆኖ ሲታወስ ይኖራል፡፡ ገሀነም በእራሱ እንዳለ ሆኖ መለስ ዜናዊ ሲጨመርበት ግን የገሀነም ገሀነም ይሆናል!

እነዚህ ደፋር ወጣት ጋዜጠኞች እንደ ሌሎች አብዛኞቻችን ሳይሆን የተወሰነላቸውን የዕድል ዕጣ ፈንታ በሚያገኙበት ጊዜ በአካል ጉዳት ስቃይ ወይም በፍርኃት ተሸብበው ወደኋላ አያፈገፍጉም፡፡

እስክንድር ነጋ በራሱ ድረ ገጽ በመጻፉ ብቻ የ18 ዓመታት እስራት ሲበየንበት በመፍራት አንገቱን አልደፋም፡፡

ርዕዮት ዓለሙ የይስሙላው የዝንጀሮ ፍርድ ቤት የ14 ዓመታት እስር ሲበይንባት በሎሌነት መልኩ አላጎበደድችም፡፡

ውብሸት ታዬ ነጻነቱን ለመቀዳጀት የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብን አልለመነም፡፡

ተመስገን ደሳለኝ ለነጻነቱ ሲል ነብሱን አልሸጠም፡፡

አበርሃ ደስታ ደስታ ከሚያምንበት ነገር በመፍራት አላፈገፈገም፡፡

በወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ከመታሰሩ በፊት እ.ኤ.አ ሀምሌ 9/2014 በራሱ የግንኙነት ድረ ገጽ አብርሃ ደስታ ህወሀት እራሱ ነጻነት ያለው ድርጅት እንዲሆን አጥብቆ ተከራክሯል፡፡ ከህወሀት አባላት ጋር ጠላትነት የማልሆንበት ምክንያት የህወሀትን ካድሬዎች የምሁርነት እጥረት እና ክስረት ስለማውቅ ነው ብሎ ነበር፡፡

ሁሉም የኢትዮጵያ ደፋር ጋዜጠኞች እና የፖለቲካ እስረኞች ሁሉንም ነገር የላይኛው ከንፈራቸው ሳይንቀጠቀጥ ይቀበላሉ፡፡

በምንም ዓይነት መልኩ ለጭቆና አያጎበድዱም፡፡

መሰረታቸውን በመያዝ በጽናት ይቆማሉ፡፡

በፍርኃት እና በባርነት ተቀፍድደው በዘራፊ ወሮበላ አምባገነኖች መዳፍ ስር ነጻነታቸውን ተነፍገው ከሚኖሩ ይልቅ በእስር ቤት ነጻ ሆነው መኖራቸውን መርጠዋል፡፡

ዌንዲ ሸርማን እንዲህ ብለው ነበር፣ “ኢትዮጵያ በመጎልበት ላይ ያለ ዴሞክራሲ የምታካሂድ ሀገር ናት፡፡“ በአባባላቸው ትክክል ናቸው ሆኖም ግን ጊዜው ገና ነው፡፡

ርዕዮት እና የእርሷ ትውልድ የሚገባቸውን ቦታ ሲይዙ ኢትዮጵያ ትክክለኛ በመጎልበት ላይ ያለ ዴሞክራሲን እውን ታደርጋለች፡፡ ርዕዮት ላለፉት አራት ዓመታት ከ17 ቀናት በአምባገነኑ የመለስ ዜናዊ የማጎሪያ እስር ቤት በእስር ስትማቅቅ ባትቆይ ኖሮ ለኢትዮጵያ ዴሞክራሲ ምን ያህል አስተዋጽኦ ታደርግ እንደነበር የሚያስገርም አይሆንም፡፡

ለእስክንድር ነጋ፣ ለውብሸት ታዬ፣ ለተመስገን ደሳለኝ፣ ለአብርሃ ደስታ እና ለሌሎችም በእስር ቤት በመማቀቅ ላይ ለሚገኙት ጋዜጠኞች፣ ጦማሪያን እና የፖለቲካ እስረኞች ታላቅ ክብር አለኝ፡፡

ለኢትዮጵያ የመጀመሪያዋ ጀግኒት እና ለእኔ ኢትዮጵያዊት ጀግና ለርዕዮት ታላቅ ክብር አለኝ!

አምላክ ረዥም እድሜ እንዲያጎናጽፋት እና ትግሏን እንድትቀጥል እመኛለሁ፡፡

“ዴሞክራሲ እና ፍትህ የሰፈኑባት ኢትዮጵያ እውን እስከምትሆን ድረስ ሙሉ በሙሉ ትግሌን እቀጥላለሁ፡፡ እንደዚህ የሆነች ኢትዮጵያን እስከማይ ድረስ ትግሌን በተጠናከረ መልኩ እቀጥላለሁ፡፡” ርዕዮት ዓለሙ፣ .. ሀምሌ 9/2015 

ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!

ሀምሌ 7 ቀን 2007 .

 

 

Similar Posts