እ.ኤ.አ ሀምሌ 4/2015 ለኢትዮ-አሜሪካውያን/ት ትምህርት የሰጠች ዕለት፣

ከፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማርያም   

ትርጉም በነጻነት ለሀገሬ

የዚህ ሳምንት የሰኞ ትችቴ ርዕስ ለኢትዮ-አሜሪካውያን/ት ትምህርት ስለሰጠች ዕለት አልነበረም፡፡ እንደተለመደው ሁሉ ቀደም ሲል በዕቅድ ይዠ አስቤበት ላቀርብ የነበረውን ርዕስ በመተው ይህንን ጽሁፍ ለማቅረብ ተገደድኩ ምክንያቱም ተከስቶ በተመለከትኩት ሁኔታ ከተናዳፊ ተርቦች የበለጠ ተበሳጭቼ ነበርና ነው፡፡

ከጥቂት ሳምንታት በፊት የጋዜጠኞች ተከላካይ ኮሚቴ (ጋተኮ)/Committee to Protect Journalists (CPJ) “በምዕራብ ኬንያ ተቀስቅሶ በነበረው ተቃውሞ ላይ በመገኘት ሲዘግቡ በነበሩ ጋዜጠኞች ላይ ጥቃት ተሰነዘረ/Journalists Assaulted While Covering Protests in Western Kenya“ በሚል ርዕስ ያዘጋጀውን ዘገባ አንብቤ ነበር፡፡ ዘገባው እንዲህ የሚል ነው፡ “የአመጹ ተሳታፊዎች እና አመጹን ያደራጁት ሰዎች በተቆጡ የአካባቢው ኗሪዎች ከተወረሩ በኋላ የእራሳቸውን ደህንነት ለመጠበቅ ሲሉ አካባቢውን ጥለው ሸሽተዋል በማለት ጋዜጠኛ ሳካ ሪቻርድ ለጋተኮ/CPJ ተናግሯል፡፡ ጋዜጠኛ ሳካ ፖሊስ የተቃውሞ ሰልፉን ያደራጁትን ሰዎች ደህንነት በመጠበቅ ላይ ነበር በማለት ተናግሯል፡፡ ወደ ተቃውሞ አደራጆች አነጣጥሮ የነበረው የአመጽ ትርምስ ከመቅጽበት በአካባቢው ቀርተው የነበሩትን ጋዜጠኖች ወደማጥቃት ዞረ፡፡ የአመጽ ትርምሱ ጋዜጠኛ ዋስዋን መቦቀስ፣ በጥፊ መምታት እና በቆመጥ መደብደብ ጀመረ፡፡ ‘ከዚያም የስራ ባልደረባችንን ለማገዝ ስንል ጣልቃ ለመግባት ሙከራ አደረግን እና እራሳችንም መደብደብ ጀመርን” (አጽንኦ ተጨምሯል፡፡)

በሁኔታው በመከፋት እራሴን በመነቅነቅ ለእራሴ እንዲህ የሚል ጥያቄ አቀረብኩ፣ “አፍሪካ መቼ ነው ንጹሀን ዜጎችን ከማሸማቀቅ፣ ከማስፈራራት፣ ከማሰር፣ የኃይል እርምጃ ከመውሰድ እና ከማሰቃየት ነጻ የሆነ የፕሬስ ስርዓት የሚኖራት?“

ምንም ዓይነት ጋዜጠኛ የማይደበደብበት፣ ማሸማቀቅ፣ ማስፈራራት፣ ማሸበር እና ማሰር ወይም ደግሞ ምንም ዓይነት ማሰቃየት የማይፈጸምበት እና ነጻ ፕሬስ ከሰፈነበት ሀገር መኖር ምን ያህል ታላቅ ነገር ነው በማለት ለእራሴ አረጋገጥኩ፡፡ ወዲያውኑም ያለምንም የሕግ ተጠያቂነት ስለአንዳንድ ታዋቂ እና ምልክት ሰዎች ጉዳይ ብቻ ለምንም ነገር የማይጠቅም እርባናየለሽ አጭር ጽሁፍ ስለሚያወጡ የተዋረዱ ጋዜጦች ማሰብም ጀመርኩ፡፡

በነጻ ሀሳብን በመግለጽ እና ነጻው ፕሬስ ያለምንም ስጋት ነጻ በሆነ መልኩ መዘገብ እንዲችል ምንም አይነት ጣልቃገብነት እንዳይደረግ የህግ ጥበቃ በሚደረግበት ሀገር እንድኖር ያደረገኝን ዕጣ ፈንታዬን አመሰገንኩ፡፡

ይኸ ጉዳይ የአሜሪካንን ሕገ መንግስት ላረቀቁት እና እ.ኤ.አ በ1791 ላሻሻሉት እንዲሁም ምንም ዓይነት ቅድመ ምርመራ እንዳይኖር የሚል ቋንቋ ለተጠቀሙት እና በሕግ ለደነገጉት ቀደምት አባቶች ታላቅ ስኬት ነበር፡፡ በመጀመሪያው የሕግ ማሻሻያ ምክር ቤቱ ሊታሰብ የማይችል እና ከግንዛቤ በላይ የሆነ ታላቅ እና ክቡር የሆነ ተግባርን አከናውኗል፡፡ በእራሱ ላይ እንዲህ የሚል ሕገመንግስታዊ ማሻሻያ አስቀምጧል፣ “ምክር ቤቱ የፕሬስ ነጻነት መብትን የሚገድቡ እና የሚሸራርፉ ማናቸውንም ዓይነት ሕግ አያወጣም…“

የመጀመሪያው የአሜሪካ ሕገመንግስት ማሻሻያ አዋጅ የዜጎች የዕውቀት ጥበብ ብልጭታ የሚገለጽበት ብቻ ሳይሆን የሰው ልጅ አዕምሮ የክህሎት ምግባርን ያመላከተ ሁኔታ ነበር፡፡

የአሜረካንን ሕገመንግስት ያረቀቁት ቀደምት አባቶቸ ለአሜሪካ መንግስት ሁሉንም ዓይነት የሕግ ስልጣን ሰጡት፡፡ ምክር ቤቱ ሕግ ለማውጣት እና በማንኛውም ሀገር ላይ ጦርነት ለማወጅ እና ያንንም ጦርነት በድል አድራጊነት ለመደምደም የሚያስችል ስልጣን አለው፡፡ ምክር ቤቱ በዜጎች ላይ ግብር ለመጣል እና እንደ ሰካራም መርከብ ነጅ የፈለገውን ያህል ወጭ ማውጣት ይችላል፡፡ (በአሁኑ ጊዜ የአሜሪካ መንግስት ከ13 ትሪሊዮን ዶላር በላይ ዕዳ ተቆልሎበታል፡፡) ምክር ቤቱ ገንዘብ እንዲታተም ያደርጋል፣ ማንኛውንም ንግድ እና ሌሎችንም በርካታ ተግባራት ያከናውናል፡፡

ሆኖም ግን ኃይለኛው የዩኤስ አሜሪካ ምክር ቤት በነጻው ፕሬስ ላይ ቅድመ ምርመራ ለማድረግ አቅመቢስ ነው፡፡ በፕላኔታችን ላይ የኒኩሌር ባለቤት የሆነው እና ዓለምን በአጭር ጊዜ ውስጥ ዶግ አመድ አድርጎ ወደ ፍርስራሽነት ሊለውጥ የሚያስችል ኃይል ያለው የአሜሪካን ፕሬዚደንት ታላቅ ሰው እንኳ የፕሬስ ነጻነት መብት ክልከላ ሲነሳ ፍጹም በሆነ መልኩ አቅምየለሽ ይሆናል፡፡

የሚከተሉትን ምልከታዎች የማደርገው በነጻነት ዕለት የተደረጉትን ተጋድሎዎች እና አዋጆች ለማድነቅ አይደለም ሆኖም ግን ለኢትዮ-አሜሪካውያን/ት ዜጎች ትምህርት ይሰጣል ከሚል ግንዛቤ በመነሳት ነው፡፡

እ.ኤ.አ ሀምሌ 3/2015 ቃላት ሊገልጹት ከሚችሉት በላይ በሆነ መልኩ እጅግ በጣም አስደንጋጭ የሆነ እና ያሳዘነኝን ነገር በዩቱቤ ቪዲዮ ተመልክቻለሁ፡፡ በዚያ ቪዲዮ የተለመከትኩት ነገር ከአሜሪካ ነጻነቶች ሁሉ ዋና እና ምሰሶ በሆነው በፕሬስ ነጻነት መብት ላይ የተሰነዘረ የመጨረሻ ዘለፋ ነበር፡፡

በዚያ ቪዲዮ የተለመከትኩት ነገር ለእራሳቸው ብቻ እንጅ ለሌላ ለማንም ዜጋ የመናገር ነጻነትን፣ የፕሬስ ነጻነትን፣ የመሰብሰብ መብት ነጻነትን እና ለመንግስት ቅሬታን በማቅረብ ረገድ አስመሳዮች የሚያደርጉትን የሸፍጥ ስራ ነው ለማረጋገጥ የቻልኩት፡፡

በዚያ ቪዲዮ የተለመከትኩት ነገር በዜጎች ላይ የተሰነዘረውን የመጨረሻውን ጥቃት እና በመጀመሪያው የአሜሪካ ሕገመንግስት ማሻሻያ ሕግ ላይ የጦርነት አዋጅ እንደታወጀ አድርጌ ነው የተገነዘብኩት፡፡

ቪዲዮው በእራሱ ይናገራል እናም ለእራሱ ያሳያል፡፡ በጣም ጥቂት የሆኑ በቁጣ የገነፈሉ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ዜጎች በዚህ ወር መጀመሪያ አካባቢ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ በኢትዮጵያ የሚያደርጉትን ይፋ ጉብኝት በማስመልከት ተቃውሟቸውን ለመግለጽ ጩኸታቸውን በማሰማት ከኋይት ሀውስ ፊት ለፊት ተሰባስበዋል፡፡ የአሜሪካ ድምጽ የአማርኛው አገልግሎት (ቪኦኤ) ዘጋቢ ጋዜጠኛ የሆነው ሄኖክ ሰማእግዜር የተቃውሞ ሰልፉን አጠቃላይ ሁኔታ ለመዘገብ እና ከአንዳንድ የተቃውሞ ሰልፍ ተሳታፊዎች ጋር ቃለ መጠይቅ በማድረግ በአጭር ሞገድ ለኢትዮጵያውያን አድማጮች በሬዲዮ ለማስተላለፍ እንዲቻል የተቃውሞ ሰልፉ እየተካሄደ ባለበት ቦታ ላይ ደረሰ፡፡

በተቃውሞ ሰልፉ ቦታ ላይ የሄኖክ መገኘት ከደርዘን በላይ በሚቆጠሩ የተቃውሞ ሰልፋ ተሳታፊዎች ላይ ቁጣን ቀሰቀሰ፡፡ ተቃዋሚ ሰልፈኞች የቪኦኤ ሬዲዮ ድምጽ የአማርኛው አገልግሎት ዘጋቢ የሆነውን ጋዜጠኛ የቆሰለን አጋዘን ለመቀራመት እና ለመቦጫጨቅ አሰፍስፈው እንደሚጠባበቁ ተኩላዎች ሁሉ ከሁሉም አቅጣጫ ከበቡት፡፡ እንደዚህ ዓይነቱን በቁጣ የተሞላ ተቃዋሚ ሰልፈኛ በጋዜጠኛው ላይ ወንጀል ለመስራት ብቻ ሳይሆን የአሜሪካ ህዝብ የመሰረት ድንጋይ የሆነውን የመጀመሪያውን የነጻነት የሕግ ማሻሻያ አዋጅም በርቅሶ የመጣስ አካሄድ ስለሆነ ይህንን ማየት እጅግ በጣም ያስፈራል፡፡

ለእራሴ እንዲህ የሚል ጥያቄ አቀረብኩ፣ “በእርግጥ ይህ የምመለከተው ነገር በእርግጠኝነት እውን የሆነ ነገር ነውን? ይህ በቪዲዮ ምስል የምመለከተው ነገር በኋይት ሀውስ በምዕራባዊ አቅጣጫ እየተደረገ ያለ ነገር ነው ወይስ ደግሞ በምዕራብ ኬንያ የሆነውን ነገር ነው እያየሁ ያለሁት?“

ተቃዋሚ ሰልፈኞች በሄኖክ ዙሪያ ተሰባስበዋል፡፡ አንድ ተቃዋሚ ሰልፈኛ የቪኦኤ ድምጽ የአማርኛው አገልግሎት ዘጋቢ ጋዜጠኛ “የማይረባ ደደብ” ነው እያለ ሲጮህ ይሰማ ነበር፡፡ ሌላው ተቃዋሚ ሰልፈኞች ደግሞ እንዲህ በማለት ይጮሀሉ፣ “ሌባ፣ ሌባ፣ ሌባ“ እያሉ በመጮህ ሄኖክን በኃይል መግፋት እና መጎነታተል ጀመሩ፡፡ ሄኖክን አንተ የዩኤስ አሜሪካ የሚስጥር አገልጋይ ኃላፊ ነህ “አፈርንብህ!” በማለት እየጮሁ ማባረር ጀመሩ፡፡ የሚስጥር ኃላፈ አገልጋይ ሆነህ አስመሳይ ነህ እያሉ የንቀት ጩኸት እና የኃይል የዘለፋ ቃል በቪኦኤ ድምጽ የአማርኛው አገልግሎት ዘጋቢ ጋዜጠኛ ላይ እየሰነዘሩ ተቃውሟቸውን ገልጸዋል፡፡ በሁለት ቢላዋ የምትበላ ወያኔ (በኢትዮጵያ ያለው ገዥ አካል) ነህ በማለትም ከስሰው አካላዊ ጉዳት ለማድረስ አስፈራርተውታል፡፡

ሌሎች የተቃውሞው ሰልፍ ተሳታፊዎች ደግሞ ቆመው ይመለከቱ ነበር፡፡ ሄኖክን የሚያባርረውን የአመጽ ትርምስ ለማስቆም የሞከረ ማንም አልነበረም፡፡ እንደዚሁም ሌሎቹ የተቃውሞ ሰልፍ ተሳታፊዎች የመሰብሰብ እና ለፕሬዚዳንቱ ቅሬታቸውን የማቅረብ መብት እንዳላቸው እና በመጀመሪያው የአሜሪካ ሕገመንግስት ማሻሻያ ላይ ሁለት መብቶችን የተጎናጸፉ መሆናቸውን ይናገሩ ነበር፡፡

እጅግ በጣም የሚያስገርመው እውነታ ደግሞ የቪኦኤ ድምጽ የአማርኛው አገልግሎት ዘጋቢ ጋዜጠኛ በሆነው ግለሰብ ላይ አደጋ በማድረስ ላይ ያሉት ተቃዋሚዎቹ በዓለም ላይ የፕሬስ ምርመራ ከሚደረግባቸው ሀገሮች የጋዜጠኞች ተከላካይ ኮሚቴ (ጋተኮ/CPJ) በ4ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች በማለት የፈረጃትን ሀገር ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ለመጎብኘት እንዳይሄዱ ተቃውሟቸውን ሲገልጹ ነበር፡፡ በኢትዮጵያ በስልጣን ማማ ላይ ተፈናጥጦ የሚገኘው የህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ (ህወሀት) ገዥ አካል የሚያስረው እና የሚያሰቃየው በሙያው የሰለጠኑ ጋዜጠኞችን ብቻ አይደለም፣ ሆኖም ግን የነጻውን ፕሬስ ጋዜጦች እና መጽሔቶችን መዝጋት እና በድረ ገጽ ሀሳቦቻቸውን የሚገልጹትን ወጣት ጦማሪያን ሳይቀር የሚያስር እና የሚያባርር የእራሱ ጥላ የሚያስደነብረው ዕኩይ ድርጅት ነው፡፡ የዞን 9 ጦማሪያን እየተባሉ የሚጠሩት እና ወጣት ወንዶች እና ሴቶች ነጻ ሀሳቦቻቸውን በድረ ገጽ የግንኙት ዘዴ በመግለጻቸው ብቻ ወያኔው ተቃዋሚዎቼ ናቸው የሚላቸውን የሀገሪቱን ንጹሀን ዜጎች ለማጥቃት ባወጣው እና የጸረ ሽብር ህግ እያለ በሚጠራው አራሚ ሳይሆን ቀያጅ እና የማጥቂያ ህግ በመጠቀም በእስር ቤት አጉሮ በማሰቃየት ላይ ይገኛል፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ጋዜጠኝነት እና ጸሐፊ መሆን ወንጀል ነው!

የተቃዋሚ ሰልፈኞች በቪኦኤ ድምጽ የአማርኛው አገልግሎት ጋዜጠኛ ላይ ከእውነታው ውጭ በጭፍንነት ጉዳት ለማድረስ ጥረት እያደረጉ በሌላ በኩል ደግሞ በኢትዮጵያ የፕሬስ ነጻነትን አፈር ድሜ እያስበላ ተንፈራጥጦ በተቀመጠው የወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ጋር በመቆም ኢትዮጵያን ለመጎብኘት በሚሄዱት በፕሬዚዳንት ኦባማ ላይ ሌባ ጣታቸውን ሲሰነዝሩ ሌሎቹ ሶስቱ ጣቶቻቸው ወደ እነርሱ ያነጣጥሩ እንደነበር ግንዛቤ መውሰድ ይኖርባቸዋል፡፡

ጉዳት ለማድረስ የተንቀሳቀሱት ኃይሎች ከኋይት ሀውስ ፊት ለፊት በመሆን የመቃወም መብታቸውን መጠቀም እንደሚችሉ ሁሉ የሄኖክን ድርጊቶችን የመዘገብ መብትም በተመሳሳይ መልኩ ማክበር እንጀ መጨፍለቅ አይጠበቅባቸውም ነበር፡፡

የኦባማ የሚስጥር የደህንነት አገልግሎት እነዚህ ጉዳት ለማድረስ የተንቀሳቀሱት የተቃዋሚ ኃይሎች ከኋይት ሀውስ ፊት ለፊት ሲሰለፉ እና ተቃውሟቸውን ሲያሰሙ አይደበድብም፣ ወደ እስር ቤትም አያግዝም፣ ምክንያቱም እነዚህ ዜጎች ተቃውሟቸውን ለማሰማት ሕገ መንግስታዊ መብት እንዳላቸው ሁሉ የቪኦኤ ዘጋቢ ጋዜጠኛም ድርጊቶች በየሚፈጸሙበት አካባቢዎች ሁሉ በመገኘት የመዘገብ ሕገ መንግስታዊ መብት እንዳለው ሊገነዘቡ ይገባል፡፡

የቪኦኤ ድምጽ የአማርኛው አገልግሎት ዘጋቢ ጋዜጠኛን ከሚዘግብበት ቦታ ያባረሩት ተቃዋሚ ሰልፈኞች ሄኖክ ያዘጋጀውን እና የሚያቀርበውን ዘገባ እና የትንታኔ ጉዳዮች ያለመቀበል እና ያልተረጋገጠ ዘገባ ካለበትም የመተቸት እና በትክክለኛው መንገድ በመረጃ እና በዕውቀት ላይ በተመሰረተ መልኩ የማጋለጥ እና የመሞገት መብት አላቸው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የሄኖክን ወገንተኛነት እና የተሳሳተ ዘገባ ነው የሚሉትን ነገር ሁሉ ነቅሶ በማውጣት የማጋለጥ የሕግ፣ የሞራል እና የተግባር ኃላፊነትም አለባቸው፡፡

የቪኦኤ ድምጽ የአማርኛው አገልግሎት ዘጋቢ ጋዜጠኛ በአካባቢው ለመዘገብ በተገኘበት ጊዜ ተቃዋሚ ሰልፈኞች ምንም ነገር ሳያደርጉ ዝም ማለት ነበረባቸው፡፡ ቃለመጠይቅ ባለመስጠትም ተባባሪ ያለመሆናቸውን መግለጽ ይችሉ ነበር፡፡ ለዘጋቢ ጋዜጠኛው ቃለመጠይቃቸውን በመስጠት ጋዜጠኛው በሚዘግበው ዘገባ ላይ የሚያሳየውን ትክክለኛ ያልሆነ የአዘጋገብ ዘይቤ ማስተካከል እንዳለበት በግልጽ  ሊነግሩት ይገባ ነበር፡፡ ሆኖም ግን እንዲሁ የሕግ መሰረትን ሳይዙ አሜሪካ ለዘመናት የገነባችውን የዴሞክራሲያዊ መብት ህጎች ለመጭፍለቅ መነሳት አንድም ካለማወቅ ወይም ደግሞ አውቆ ሕግን ለመጣስ የሚደረግ የተሳሳተ አካሄድ ነው ከማለት ውጭ ሌላ ሊባል አይችልም፡፡

ተቃዋሚ ሰልፈኞቹ ያንን የመሰለ ህጋዊ ያልሆነ ነገር ከመፈጸም ይልቅ ዘጋቢ ጋዜጠኛውን የእነርሱን መልክቶች በኢትዮጵያ በሀገር ቤት ያሉት ጓደኞቻቸው እና በአጠቃላይ ወገኖቻቸው መገንዘብ እንዲችሉ አጋጣሚውን መጠቀም ነበረባቸው፡፡ የሄኖክ ዘገባ ወገንተኛ እና አሳሳች ከሆነ ቅሬታዎቻቸውን ለቪኦኤ ድምጽ የአማርኛው አገልግሎት አስተዳደር ማቅረብ ይችሉ ነበር፡፡

የሄኖክን ወገንተኝነት የተንጸባረቀበት ዘገባ እና ተሞክሮ በሌሎች አማራጭ የዜና መገናኛ ዘዴ ወኪሎች በመጠቀም ማጋለጥ ይችሉ ነበር፡፡ የቪኦኤ ድምጽ የአማርኛው አገልግሎት ዘጋቢ ጋዜጠኛ ሙያዊ ያልሆነ እና የጋዜጠኝነት ስነምግባርን በጣሰ መልኩ ዘገባ አቅርቦ ከሆነ ተቃዋሚ ሰልፈኞቹ ዘገባው የተሳሳተ እና ወገንተኝነት የተንጸባረቀበት ነው ለማለት እና ለማጋለጥ በርካታ መንገዶችን ሊጠቀሙ የሚችሉባቸው አያሌ ዘዴዎች ነበሯቸው፡፡

ማንም ቢሆን ሌላው ቀርቶ የምክር ቤቱ አባላት እና የዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ ፕሬዚዳንትም ቢሆኑ በሌሎች ዜጎች ላይ አደጋ የማድረስ፣ የማሸማቀቅ፣ የማስፈራራት እና በሄኖክ ወይም በሌላ በማናቸውም ዘጋቢ ጋዜጠኛ ሰው ላይ ስራውን ወይም ስራዋን በመስራቱ እና በመስራቷ ብቻ የአካል ጉዳት ለማድረስ አይችሉም፡፡ ይህ የተከበረ አስተሳሰብ የሕግ የበላይነትን እንጅ ክፉውን እና በዕኩይ ምግባር ላይ የተዋቀረውን የሰው ልጆችን ጉልበት አያመላክትም፡፡

ሄኖክ ባቀረበው የሬዲዮ ዘገባ ስርጭቱ በተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፉ ወቅት በእርሱ ላይ ኃይልን ይጠቀሙ የነበሩትን ዜጎች አስመልክቶ የተመጠነ እና ሚዛናዊ የሆነ ዘገባ አቅርቧል፡፡

በእኔ አመለካከት በእርሱ ላይ አደጋ ለማድረስ ሲያባርሩት እና በታላቅ ቁጣ እና ንዴት ሲያዋክቡት በነበሩት ኃይሎች ላይ ያቀረበው ዘገባ ከሚጠበቀው በታች ያነሰ ነው፡፡ የቪኦኤ ድምጽ የአማርኛው አገልግሎት ዘጋቢ ጋዜጠኛ ተቃዋሚ ሰልፈኞችን በዚያ ክስተት ላይ ሲያደርጉት የነበረውን ድርጊት እና ዘለፋ በኦዲዮ ድምጽ ቀርጾ በማቅረብ ዜጎች ምን ያህል የሌሎችን ዜጎች መብት ለመደፍጠጥ ይሽቀዳደሙ እንደነበር በማቅረብ ሊጠቀምበት ይችል ነበር፡፡ ለሙያው እና ለክብሩ ሲል ብዙም ነገር አላደረገም፡፡ ባቀረበው ዘገባ ላይ አንድ ወይም ከአንድ በላይ የሆኑ ተቃዋሚዎች እርሱን በመሳብ በአንገቱ ላይ ያደረገውን የጋዜጠኝነት መለያ የሆነውን ምልክት በኃይል ወስደውበታል፡፡

አብዛኞቼ አንባቢዎቼ እንደሚያውቁት የቪኦኤ ድምጽ የአማርኛው አገልግሎትን በበርካታ ጉዳዮች ላይ ስከላከልለት ቆይቻለሁ፡፡ እንደዚሁም ደግሞ የሬዲዮ አገልግሎቱ በጣም ጠቃሚ ናቸው ብዬ የማስባቸውን እና በድምጽ አገልግሎቱ ችላ ባይነት አልተዘገቡም ብዬ የመዘግብኳቸው እና የያዝኳቸው በርካታ ቅሬታዎች አሉኝ፡፡

እ.ኤ.አ ጥቅምት 2010 “ኢትዮጵያውያን/ት የአሜሪካ ድምጽ አገልግሎትን እናዳምጥ“ በሚል ርዕስ በሁፊንግተን ፖስት አንድ ባቀረብኩት ትችት ላይ እንዲህ የሚል የክርክር ጭብጥ አቅርቤ ነበር፣ “ኢትዮጵያውያን/ት የአሜሪካን ድምጽ አገልግሎት የማዳመጥ ሕገመንግስታዊ መብት አላቸው፡፡“

እ.ኤ.አ ሀምሌ 2011 “አምባገነኖችን ማስተማር“ በሚል ርዕስ ባቀረብኩት ትችት ላይ አሁን በህይወት በሌለው እና አምባገነኑ መለስ ዜናዊ በአሜሪካ ድምጽ የአማርኛው አገልግሎት በመጠቀም በዲያስፖራው የሚገኙ ግለሰቦች በእርሱ እና በገዥው አካል ላይ ሸንቋጭ የሆኑ ትችቶችን የሚያቀርቡ ግለሰቦች በአገልግሎት ድምጹ መስተናገድ እንዳይችሉ ቃለ መጠይቅ እንዳይሰጡ ማዕቀብ ይጣልባቸው በማለት አቅርቦት የነበረውን ፈጣጣ እና የተረገመ አስተያየት የቪኦኤ ድምጽ የአማርኛው አግልግሎት የቦርድ አመራር ውድቅ በማድረጉ የተሰማኝን ደስታ ጎሽ! በማለት ለአገልግሎቱ ያለኝን አድናቆት ግልጽ አድርጌ ነበር፡፡ እንደዚሁም ደግሞ ከአራት ዓመታት በፊት በዚሁ ወር መለስ ዜናዊ በቪኦኤ ድምጽ የአማርኛው አገልግሎት ላይ እያደረገ ያለውን የማፈን አደጋ በማስመልከት “የቪኦኤ ድምጽ የአማርኛው አገልግሎት (ቪኦኤ)/VOA የዜናዊ ድምጽ አገልግሎት (ቪኦዜድ)/VOZ አይደለም” በሚል ርዕስ ባቀረብኩት ትችቴ ላይ ለቪኦኤ ጥብቅና በመቆም ሽንጤን ገትሬ ተሟግቼ ነበር፡፡

እ.ኤ.አ ጥር 27/2014 በተጻፈ ደብዳቤ እኔ የማምንባቸው እና ለህዝብ መድረሳቸው ጠቃሚነት አላቸው ባልኳቸው ጉዳዮች ላይ የቪኦኤ ድምጽ የአማርኛው አገልግሎት በቂ ሽፋን አይሰጥም፣ አንዳንዴም ሳይዘግብ ዝም ብሎ በዘፈቀደ ያልፋቸዋል በማለት ለአገልግሎቱ ድምጽ ለቦርድ አመራር የነበረኝን ቅሬታ አቅርቤ ነበር፡፡ መረጃ የማግኘት ነጻነት ጥያቄ በሚል ጉዳዩን ስከታተል ቆይቼ ብዙ ሂደቶችን ካለፈ በኋላ ኤጀንሲው ተግባራዊ ምላሽ ሰጥቷል፡፡

ለቪኦኤ ድምጽ የአማርኛው አገልግሎት በተለያዩ ጉዳዮች እና ጥያቄዎች ላይ በተለያዩ ጊዜያት ቃለመጠይቅ ሰጥቻለሁ፡፡ በኢትዮጵያ ከህዝቦች ፈቃድ ውጭ በጠብመንጃ ኃይል በስልጣን እርካብ ላይ ተንጠልጥሎ በሚገኘው ገዥ አካል ላይ ሸንቋጭ እና መቅን የሚያሳጡ ትችቶችን በየጊዜው የማቀርብ በመሆኑ በኢትዮጵያ ያለው ገዥ አካል ለአሜሪካ ድምጽ አገልግሎት የቦርድ አመራር በተለያዩ ፕሮግራሞች ላይ የድምጽ አገልግሎቱ እንዳያቀርበኝ አቤቱታ ያቀረበለት እንደሆነ አድርጌ አስባለሁ፡፡ ይህም ለመሆኑ ቀደም ሲል ከነበሩት እና በአሁኑ ጊዜ ካሉት ተጫባጭ ሁኔታዎች አንጻር በማየት መገምገም የሚቻል ይመስለኛል፡፡

በቪኦኤ ድምጽ የአማርኛው አገልግሎት ፕሮግራም ላይ የስርጭት ሽፋን ያልተሰጣቸው በርካታ ጉዳዮች እና ርዕሶች እንዳሉ እገነዘባለሁ፡፡ ጥቂት በሆኑ የቪኦኤ ድምጽ የአማርኛው አገልግሎት ዘገባ እና የትንታኔ አካሄድ ላይ ፍጹም የሆኑ ልዩነቶች አሉኝ፡፡

ከቪኦኤ ድምጽ የአማርኛው አገልግሎት በሚዘግባቸው እና በማይዘግባቸው ጉዳዮች ላይ ልዩነቶች ያሉኝ ቢሆንም በዚህ አጋጣሚ የአማርኛው አገልግሎት ዘጋቢ ጋዜጠኞች ከፍተኛ የሆነ የሙያ እና የጋዜጠኝነት ስነምግባር ክህሎትን የተላበሱ በመሆናቸው ላይ ያለኝን ክብር ለመግለጽ እወዳለሁ፡፡ እኔ በድምጽ አገልግሎቱ ህገ ደንብ መሰረት ያልሰራችኋቸው በርካታ ጉዳዮች አሉ እናም ኃላፊነታችሁን አልተወጣችሁም በማለት በየጊዜው ስሞግት የቆየሁ ቢሆንም በቪኦኤ ሕገ ደንብ መሰረት ስራቸውን በሚገባ የሚሰሩ እንደሆኑ እምነት አለኝ፡፡

ከሄኖክ ሰማእግዜር ጋር አንድ ጊዜ የስልክ ቃለመጠይቅ አድርጌአለሁ፡፡ ሆኖም ግን የሰጠሁት ቃለመጠይቅና ርእሱና ግዜው  መች እንደሆነ በትክክል ለማስታወስ እቸገራለሁ፡፡ ሆኖም ግን ጋዜጠኛው ወጣት የጋዜጠኝነት ስነምግባርን የተላበሰ ለማወቅ የሚጓጓ መሆኑን በሚገባ አውቃለሁ፡፡ ሄኖክን በሰውነት አግኝቸውም አላውቅም።

ሄኖክ ካለፈው ዓመት ወይም ከዚያ በፊት ጀምሮ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ የሚያቀርባቸው ዘገባዎች ለገዥው አካል ወግንተኝነትን የሚያንጸባርቁ እና ወገንተኛነትን የተላበሱ ናቸው የሚል አንዳንድ ክሶች ተሰንዝረዉበታል።

ለአድማጮት የተሳሳቱ ዘገባዎችን፣ ሆን ብሎ መቅረብ ያለባቸውን ዘገባዎች ባለማቅረብ እና ከሚዘግባቸው ዘገባዎች ውስጥ ከግማሽ የማይበልጡት ብቻ እውነትነት የሌላቸው ናቸው በማለት በየጊዜው ውንጀላ ይቀርብበታል፡፡ በሄኖክ በተሰራ ቢያንስ በአንድ ዘገባ ውስጥ ደረጃውን ያልጠበቀ ዘገባ ይቀርባል የሚል ውንጀላ ይቀርባል፡፡ ለእንደዚህ ያሉ ውንጀላዎች ነጻ በሆነ መልኩ እውነታውን አጣርቸ ለመያዝ የሚያስችለኝ ነገር አላገኘሁም፡፡

እንደቀረበበት ውንጀላ ሄኖክ በአዲስ አበባ ተቀምጦ ለሚገኘው ገዥ አካል አገልጋይ ሎሌ ነው ብለን ብናስብ፣ እና ምን ይደረግ?

እውነት ለመናገር አዲስ አበባ ለሚገኘው ገዥ አካል ወገንተኝነትን ያሳያል የሚለው ነገር ለእኔ ቅንጣት ያህል የሚያሳስበኝ ጉዳይ አይደለም፡፡ ይህ ማለት ሌሎችም የቪኦኤ ድምጽ የአማርኛው አገልግሎት ዘጋቢ ጋዜጠኞች ለገዥው አካል ወገንተኝነትን ያሳያሉ ወደሚል ሊያመራ ይችላል፡፡ እኔ እንደዚህ ዓይነቱን ነገር አላምንም፡፡

የወገንተኛነት ስሜት የማይንጸባረቅበት ወይም ደግሞ በሚያቀርቡት ዘገባ ላይ ከምንም በላይ ትችት የማይቀርብበት ወይም የማይቀርብባት ጋዜጠኛ ይኖራል ብዬ አላምንም፡፡

በኢትዮጵያ በማተራመስ ላይ ከሚገኘው አምባገነን ጋር ወገንተኝነትን ከሚያሳይ ይቅር እና እንደ እኔ ካለው በኢትዮጵያ ያለውን ገዥ አካል በእውነታ ላይ በተመሰረተ ጠንካራ ትችት ከሚሸነቁጥ ግለሰብ ጋርም እንኳ ቢሆን ወገንተኝነት እና ሚዛናዊ ያልሆነ ዘገባን ከሚያቀርብ የቪኦኤ ድምጽ የአማርኛው አገልግሎት ዘጋቢ ጋዜጠኛ ካለ በጽናት በመቆም አግባብነት የሌለው ድርጊት እየፈጸመ/ች መሆኑነን/ኗን እሞግታለሁ፡፡ “የቪኦኤ ድምጽ የአማርኛው አገልግሎት (ቪኦኤ)/VOA የዜናዊ ድምጽ አገልግሎት (ቪኦዜድ)/VOZ አይደለም” በሚል ርዕስ እንዳቀረብኩት የክርክር ጭብጥ ሁሉ ቪኦኤም የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ድምጽ አይደለም የሚል እምነት አለኝ፡፡

የቪኦኤ ድምጽ የአማርኛው አገልግሎት ድምጽ ለሌላቸው ኢትዮጵያውያን/ት ድምጽ ለመሆኑ ጥያቄ የሚያስነሳ ጉዳይ አይደለም፡፡

እኛ የቪኦኤ አድማጮች የቪኦኤ ድምጽ የአማርኛው አገልግሎት ድምጽ ለሌላቸው የኢትዮጵያ ህዝቦች ድምጽ መሆን እንዳለበት የመጠየቅ መብት አለን፡፡ ይህ የመጠየቅ መብት በቪኦኤ ዘጋቢ ጋዜጠኞች ላይ ከተጣሉባቸው በርካታ ግዴታዎች መካከል የኃይል ሚዛንን መመርመር እና ድምጽ ለሌላቸው ህዝቦች ድምጽ መሆን መቻል ነው፡፡

ማንም ጋዜጠኛም ሆነ ማንኛውም ሰው ቢሆንም ከወገንተኝነት የጸዳ አይደለም፡፡ አንዳንድ ጊዜ እነዚህ ወገንተኝነቶች ከተንሰራፋ ድንቁርና የሚመነጩ ሲሆን አንዳንደ ጊዜ ደግሞ ከክፋት እና ከተንኮል የሚቀዱ ናቸው፡፡ እነዚህን ወገንተኝነቶች ለማስወገድ የምንችለው የእራሳችንን ወገንተኝነት በማሰራጨት እና በማዛመት ሳይሆን ወይም ደግሞ በእራሳቸው ወገንተኝነትን የሚያራምዱትን ወገኖች በአካላቸው ላይ ጉዳት ለማምጣት በማሰብ በማስፈራራት አይደለም፡፡ ዶ/ር ማርቲን ሉተር ኪንግ እንዳስተማሩን “ጨለማን እራሱ ጨለማ ሊያስወግደው አይችልም፣ ይህንን ማድረግ የሚችለው ብርሀን ብቻ ነው፡፡“

ሄኖክ በወገንተኝነት ስሜት ውስጥ ወድቆ እና የጋዜጠኝነት ስነምግባርን አዛብቶ ከሆነ እውነተኛ ማስረጃዎችን ነቅሶ በማውጣት እንደጋዜጠኛ ባለሙያነቱ የእራሱን ድርጅት የጋዜጠኝነት ስነምግባር መርህን ያልተከተለ ነው በማለት ማጋለጥ እና ማሳፈር ከእኛ ይጠበቃል፡፡

ሆኖም ግን ማንም ሰው ቢሆን ሌላው ይቅር እና የዓለም ቁንጮው ስልጣን ያላቸው የዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማም ቢሆኑ እንኳንስ የጋዜጠኝነት መለያ የሆነውን ምልክት ከአንገት ላይ አውልቆ በኃይል ነጥቆ መውሰድ፣ የስድብ ናዳ ማውረድ ወይም ደግሞ አካላዊ ኃይልን በመጠቀም መጎሻሸም እና የጋዜጠኝነት ስራውን በመስራት ላይ ያለን ጋዜጠኛ ማስፈራራት ይቅርና ከአንድ ሰብአዊ ፍጡር አናት ላይ አንዲት ቅንጣት ጸጉር ነቅሎ መውሰድ በፍጹም አይቻልም፡፡

በቪኦኤ ድምጽ የአማርኛው አገልግሎት ዘጋቢ ጋዜጠኛ ላይ አካላዊ እና የስነልቦና ጉዳት ለማድረስ የተንቀሳቀሱት የተቃውሞ ሰልፈኞች በተመሳሳይ መልኩ እነርሱ እንዳደረጉት ሁሉ የዋሽንግተን ዲሲ ፖሊሶች ወይም ደግሞ የዩኤስ የደህንነት አገልግሎት ኃላፊዎች መንገላታት እና ድብደባ ቢደርስባቸው ኖሮ ምን ይሰማቸው እንደነበር የማውቀው ቢሆን በጣም የሚያስገርመኝ ይሆናል፡፡ የፖሊስ ጨካኝነት በማለት ጩኸታቸውን ያቀልጡት እንደነበር ጥርጥር የለውም፡፡

የተቃውሞ ሰልፍ በጥባጭ ጨካኝነት ከፖሊስ ጨካኝነት ምግባር ጋር ተለይቶ አይታይም!

በቪኦኤ ድምጽ የአማርኛው አገልግሎት ዘጋቢ ጋዜጠኛ ላይ የደረሰው ክስተት እጅጉን አሳዝኖኛል፡፡

በቪኦኤ ድምጽ የአማርኛው አገልግሎት ዘጋቢ በሆነው ጋዜጠኛ ሄኖክ ሰማእግዜር ላይ የተፈጸመው ጥቃት ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ጊዜ ውስጥ በአምባገነኖች 8 ወይም 9 ጊዜ እንደ ጥጃ እየታሰረ እና እየተፈታ ሲሰቃይ በቆየው እና በአሁኑ ጊዜ ደግሞ በስልጣን እርካብ ላይ ተቆናጥጦ የሚገኘው እና በተለይ አሁን በህይወት የሌለው አምባገነኑ መለስ ዜናዊ በእኔ ወንድም እና ጀግና በሆነው እንዲሁም በጋዜጦች ላይ በሚያወጣቸው ዘገባዎች እና በድረ ገጹ በመጠቀም ሀሳቡን በሚገልጽባቸው ጽሁፎች ላይ ደስተኛ ባለመሆናቸው ምክያት ብቻ 18 ዓመታት እስር ተበይኖበት በመሰቃየት እስክንድር ነጋ እየከፈለው ባለው መስዋዕትነት ላይ መቀለድ ካልሆነ በስተቀር ሌላ ምንም ሊባል የሚችል ጉዳይ አይደለም፡፡ እስክንድር  የገዥው አካል ውሸት እና የተሳሳተ መረጃን እንደበቀቀን እየደጋገሙ ሲያነበንቡ የሚውሉትን ለከርስ የቆሙ ቀጣፊ ጋዜጠኛ ተብየዎችን ጨምሮ ፍጹም ለሆነው የፕሬስ ነጻነት የቆመ ጀግና ጋዜጠኛ ነው፡፡.

በቪኦኤ ድምጽ የአማርኛው አገልግሎት ዘጋቢ በሆነው ጋዜጠኛ ሄኖክ ሰማእግዜር ላይ የተፈጸመው ጥቃት አሁን በህይወት የሌለውን መለስ ዜናዊን ስኬታማነታቸው ከምንም በላይ አጠራጣሪ በሆኑት ፕሮጀክቶች ላይ የነጠረ ሀሳቧን በማቅረብ እና በግንባር ስትሞግት በነበረችው እና ሀሳብሽን እንደዚህ ደፍረሽ የመግለጽ መብት ከየት አገኘሽ በሚል እብሪት በመነሳሳት የ14 ዓመት እስራት ተበይኖባት በአሁኑ ጊዜ በእስር ቤት በመማቀቅ ላይ ባለችው እህቴ ርዕዮት ዓለም እየከፈለችው ባለው የጋዜጠኝነት ሙያ ላይ መቀለድ ካልሆነ በስተቀር ሌላ ምንም ሊባል የሚችል ጉዳይ አይደለም፡፡

በቪኦኤ ድምጽ የአማርኛው አገልግሎት ዘጋቢ ጋዜጠኛ ሄኖክ ሰማእግዜር ላይ የተፈጸመው ጥቃት ሳምንታዊ መጽሄቱን አልዘጋም ብሎ ከአምገነኖች ጋር በጽናት ሲታገል በነበረው እና  በጭራቅ አምባገነኖች 14 ዓመታት እስር ተበይኖበት በአሁኑ ጊዜ በእስር ቤት በመማቀቅ ላይ በሚገኘው በእኔ ወንድም እና ጀግና የሆነው ውብሸት ታዬ እየከፈለው ባለው መስዋዕትነት ላይ ማፌዝ ካልሆነ በስተቀር ሌላ ምንም ሊባል የሚችል ጉዳይ አይደለም፡፡

በቪኦኤ ድምጽ የአማርኛው አገልግሎት ዘጋቢ ጋዜጠኛ ሄኖክ ሰማእግዜር ላይ የተፈጸመው ጥቃት ነጻ የጋዜጠኝነት ሙያን እና ስነምግባርን ተላብሰው ለወገኖቻቸው ዘገባ በማቅረባቸው ብቻ በአምባገነኖች እየተያዙ በአሁኑ ጊዜ በየእስር ቤቶች ታጉረው በሚገኙት እና እትብታቸው ከተቀበረችበት ውድ ሀገራቸው በኃይል ተባርረው በባዕዳን ሀገር በሚንከራተቱት ውድ የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ጋዜጠኞች መስዋዕትነት ላይ ውኃ የመቸለስ እኩይ ምግባር ካልሆነ በስተቀር በሌላ በምንም ዓይነት መልኩ መብትን የማስከበር ወይም ሌላ ሰላማዊ እና ፍትሀዊ ትግል ሊሆን ከቶውንም አይችልም፡፡

እኔ የተመለከትኩትን የቪዲዮ ምስል “እስክንድር፣ ርዕዮት እና ውብሸት ቢመለከቱት ኖሮ ምን ሊያስቡ ይችላሉ?” በማለት ለእራሴ ጥያቄ በማቅረብ ሳሰላስል ሰውነቴን ሁሉ ብርክ ይይዘዋል፣ ዛር እንደሰፈረበት ሰው እንድንቀጠቀጥ ያደርገኛል፡፡ እነዚህ የጋዤጠኝነት ሙያ ፈርጥ የሆኑት ጀግና ኢትዮጵያውያን እና ኢትዮጵያዊት በቪኦኤ ድምጽ የአማርኛው አገልግሎት ዘጋቢ ጋዜጠኛ ሄኖክ ሰማእግዜር ላይ የጋዜጠኝነት ሙያን እና ስነምግባርን የጣሰ ነው በማለት ዕውቅናን በመንሳት በአደባባይ ለተቃውሞ በወጡ ቁጣን የተላበሱ ሰዎች ሲንገላታ እና ሲባረር ቢመለከቱ ኖሮ ምን ዓይነት ምላሽ ይሰጡ ነበር?

ሊሆኑ የሚችሉ መልሶቻቸውን ባሰብኩ ጊዜ እጅግ በጣም ደነገጥኩ አዘንኩ ፡፡

እስክንድር፣ ርዕዮት እና ውብሸት በአምባገነኖች የእስር ቤት ማጎሪያ ገብተው በመሰቃየት ላይ ያሉት እንዲሁም ሌሎች ጀግና የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች ውድ ሀገራቸውን ትተው ወደ ባዕድ ሀገር የተሰደዱት ሌላ በምንም ዓይነት ምክንያት ሳይሆን በሀገራቸው ላይ በነጻነት የሚያምኑበትን ሀሳብ ቀምረው እና አቀናብረው ለወገኖቻቸው ዜና መዘገብ እንዳይችሉ አምባገነኖች የጎሮሮ ላይ አጥንት ሆነው አላሰራ አላንቀሳቅስ ስላሏቸው ብቻ ነው፡፡ በአጭሩ በሀገሪቱ ውስጥ የፕሬስ ነጻነት ስለሌለ ብቻ ነው፡፡ ይህ ነው እንግዲህ እነርሱን ከሌሎች ኢትዮጵያውያን እና ኢትዮጵያውያት ጀግኖች እና ጀግኒቶች ልዩ ባህሪ የሚያደርገው፡፡

ሄኖክ ከኋይት ሀውስ ቅጥር ግቢ ውጭ በመሆን ለህዝብ ዕይታ የበቃው ስራውን ለመስራት በማሰብ ነበር ፡፡

የእርሱን የጋዜጠኝነት ስነምግባር እና ልዩ የጋዜጠኝነት ሙያ ልንጠራጠር እንችላለን፡፡ ከእርሱ የዘገባ አቀራረብ ዘዴ ጋር ስምምነት ላይኖረን ይችላል፡፡ ከዚህም በላይ እርሱን እንደ ሰው ላንወደው እንችላለን፡፡ ሆኖም ግን ከላይ የጠቀስናቸው ማናቸውም ነገሮቸ ቢሆኑ ዘጋቢ ጋዜጠኛውን አካላዊ ጉልበትን በመጠቀም ከአካባቢው ለማባረር፣ የቃላት ስድቦችን በማዥጎድጎድ ስብዕናውን መዳፈር እና በአካሉ ላይ ጉዳት ለማድረስ በምንም ዓይነት መልኩ ዋስትና ሊሰጡን ወይም ድርጊቱን ለመፈጸም አመክንዮአዊ ሊሆኑ አይችሉም፡፡

ሄኖክ በቦታው ላይ በመገኘት እንደማንኛውም ጋዜጠኛ ለመዘገብ ፍጹም የሆነ እና ለድርድር የማይቀርብ ህገመንግስታዊ መብት አለው፡፡

ከኋይት ሀውስ ቅጥር ግቢ ውጭ ተቃውሟቸውን ለመግለጽ የተሰባሰቡት ኢትዮጵያውያን/ት እንደ ቪኦኤ ድምጽ የአማርኛው አገልግሎት ዘጋቢ ጋዜጠኛ ሁሉ በሌሎች የሲኤንኤን/CNN ወይም ደግሞ የዋሽንግተን ጋዜጠኞች ላይ ማስፈራራት እና ከህግ አግባብ ውጭ የሆነ የአያያዝ ድርጊቶች ፈጽመውባቸው ያውቃሉን ወይም ደግሞ ወደፊት ሊፈጽሙባቸው ያቀዱት ነገር ሊኖር ይችላልን?

በጋዜጠኞች ላይ የአካል ጉዳት ማድረስ ወሮበላነት ነው፡፡ እንደዚህ ያለ ስነምግባር የሌለውን ተግባር በሚፈጽሙ ዜጎች ላይ ምንም ዓይነት ትዕግስት ሊደረግላቸው አይገባም፡፡

በቪኦኤ ድምጽ የአማርኛው አገልግሎት ዘጋቢ ጋዜጠኛ በሆነው ሄኖክ ሰማእግዜር ላይ የተፈጸመው ጥቃት በኮሎምቢያ የፌዴራል እና የአካባቢ ግዛት ሕግ መሰረት ወንጀል ነው፡፡

ሰላማዊ ተቃውሞን ለመግለጽ ወደ አደባባይ በመውጣት በቪኦኤ ድምጽ የአማርኛው አገልግሎት ዘጋቢ ጋዜጠኛ ላይ ማስፈራራት፣ ማሸማቀቅ እና ጉዳት በሚያደርሱ ግለሰቦች ላይ ስለሚሰጠው ቅጣት የኮሎምቢያ ግዛት የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ አንቀጽ ቁጥር 22-404 (ሀ) (1) እንዲህ የሚል መብትን ያጎናጽፋል፣ “ማንም ይሁን ማን በሕገ ወጥ መልክ በሌላ ሰው ላይ አደጋን ያደረሰ ወይም ደግሞ ሌላውን ለአደጋ በሚጥል መልኩ ያስፈራራ በወንጀለኛ መቅጫ ሕጉ በአንቀጽ ቁጥር 22-3571.01 የተጠቀሰው ተፈጻሚነት ይኖረዋል ወይም ደግሞ ከ180 ቀናት ላላበለጠ ጊዜያት ሊታሰር ይችላል፣ ወይም ደግሞ በሁለቱም አንቀጾች በተጠቀሱት ሊቀጣ ይችላል“ ይላል፡፡

አደጋ ማድረስ የሚለው ቃል በሕግ ቋንቋ እንዲህ በማለት ይተረጎማል፣ “ማስፈራራት ወይም ደግሞ ሌላውን ሰው ለማጥቃት በማሰብ ኃይልን በመጠቀም በግለሰቡ ላይ ሊከተል የሚችል ጉዳት ወይም ደግሞ ስብዕናን ሊያዋርድ የሚችል ዘለፋን ማስከተል“ በማለት ያስቀምጠዋል፡፡ በወንጀለኛ መቅጫ ሕጉ በአንቀጽ 22-404 (ሀ) (1) በግልጽ በተቀመጠው መሰረት አካላዊ ግንኙነት ብቻ ሳይሆን በቅርብ ጊዜ ውስጥ የጥቃት ሰለባ ሊሆን በሚችል ማንኛውም ግለሰብ ላይ ጥቃት ለመፈጸም የሚደረግን ተጨባጭ ሁኔታ ሁሉ በመመርመር ከግንዛቤ ያስገባል፡፡

በግዛቱ ውስጥ የተለያዩ ቀላል የሆኑ የጥቃት አደጋዎች ማለትም ከህግ አግባብ ውጭ ኃይልን መጠቀም (በተከላካዩ ላይ ጉዳት በሚደርስበት ጊዜ ወይም ደግሞ በሌላ ሰው ላይ ጉዳት ለማድረስ ሙከራ በሚደረግበት ጊዜ) እና አደጋ ለማድረስ የታቀደ ዓላማ በመያዝ ማስፈራራት በሚደረግበት ጊዜ (በሌላ ሰው ላይ የሚደረገው የማስፈራሪያ ድርጊት በሚስፈራራው ግለሰብ ላይ አሳማኝነት ያለው ፍርሀትን ከፈጠረ እና ወዲያውኑ ጉዳት ሊያስከትል እንደሚችል ግንዛቤ ከተወሰደ) እንደዚህ ያሉ የሕግ ማዕቀፎች በቀላል የጥቃት ጥፋቶች ስር የሚጠቃለሉ ይሆናል፡፡

እንደዚህ ዓይነት ባህሪያት ላሏቸው የጥቃት አደጋዎች የወንጀለኛ መቅጫ ሕጉ እስከ 1000 ብር በሚደርስ ቅጣት እንዲቀጡ ወይም ደግሞ እስከ 180 በሚደርሱ ቀናት በእስር እንዲቀጡ ያደርጋል፡፡

በዚህ የሕግ ድንጋጌ ክፍል የተጠቀሰው “ጉዳት” የሚለው ቃል የአካል ጉዳት እንደሆነ ተደርጎ ይተረጎማል፣ ሆኖም ግን የፈለገውን ያህል ትንሽ ቢሆንም ስሜትን የሚጎዳ ዘለፋንም የሚያጠቃልል ነው፡፡

በቪኦኤ ድምጽ የአማርኛው አገልግሎት ዘጋቢ ጋዜጠኛ ላይ የተፈጸሙት የወንጀል ድርጊቶች እና በዩቱቤ በቪዲዮ ምስል የተለቀቁት ድርጊቶች በዋሽንግተን ዲሲ ሕግ መሰረት የቀላል አደጋ ጥቃት ሰለባዎች በሚለው የወንጀል ማዕቀፍ ውስጥ የሚጠቃለሉ ናቸው፡፡

በኮሎምቢያ ግዛት የወንወጀለኛ መቅጫ አንቀጽ ቁጥር 22-2801 ስር “ማንም በኃይል ወይም ጉልበትን በመጠቀም ወይም ደግሞ በድንገተኛ ወይም በኃይል ንብረትን በመውሰድ ወይም በመቀማት፣ ወይም ደግሞ በፍርሀት ቆፈን ውስጥ እንዲቀመጡ በማድረግ፣ ከአንድ ሰው ላይ ማንኛውም ዋጋ ያለውን ንብረት መውሰድ ወይም ደግሞ በአጭር ጊዜ ውስጥ የሌላ ሰው ንበረትን ወስዶ ባለንብረት መሆን የዝርፊያ ወንጀል ነው፣ እናም በዚህ ወንጀል የተከሰሰ እና በማስረጃ የተረጋገጠበት ማንኛውም ሰው ከ2 ዓመታት ባላነሰ እና ከ15 ዓመታት ባልበለጠ እስራት ሊቀጣ ይችላል“ (አጽንኦ ተጨምሯል፡፡) በዋሽንግተን ዲሲ ሕግ መሰረት ከሄኖክ አንገት ላይ የጋዜጠኝነት መታወቂያ ምልክቱን በኃይል ነጥቆ መውሰድ በዘረፋ ወንጀል የሚያስቀጣ ነው፡፡

በዩናይትድ ስቴትስ የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ አንቀጽ 18 በተራቁጥር 111 (ሀ) (2) መሰረት ማንኛውም ሰው አደጋ ለማድረስ ሙከራ ያደረገ ሁሉ በቀላል አደጋ የሚካተት ሲሆን “በዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ የሚኖር ማንኛውም በኃላፊነት ቦታ ላይ ያለ ባለስልጣን ወይም ደግሞ ሰራተኛ ወይም ማንኛውም በዩናይትድ ስቴትስ መንግስት ቅርንጫፍ መስሪያ ቤት ውስጥ የሚሰራ ሰራተኛ“ በዩኤስ 18 የወንወጀለኛ መቅጫ ሕግ አንቀጽ 1114 መሰረት በገንዘብ ወይም ደግሞ ከአንድ ዓመት ባልበለጠ እስራት ሊቀጣ ይችላል፡፡”

በዩኤስ 18 በአንቀጽ 115 (b) (B) መሰረት፣

1ኛ) “የደረሰው አደጋ ቀላል አደጋ መሆኑ ከተረጋገጠ ከአንድ ዓመት ባልበለጠ እስራት የሚያስቀጣ ይሆናል፣

2ኛ) አደጋው አካላዊ ኃይል በመጠቀም የአደጋ ሰለባው ላይ ጉዳት ያስከተለ ከሆነ ወይም ደግሞ ሌላ አደጋ ለማድረስ የተቀነባበረ ዕቀድ ያለው መሆኑ በማስረጃ ከተረጋገጠ እስከ 20 ዓመታት በሚደርስ እስራት ይቀጣል፣

3ኛ) ጥቃቱ በጥቃት ሰለባው ላይ የአካል ጉዳት አስከትሎ ከሆነ ከ20 ዓመታት በላይ በሚደርስ እስራት እንዲቀጣ ይደረጋል…” በማለት ሕጉ በግልጽ አስቀምጦታል፡፡

የቪኦኤ ድምጽ የአማርኛው አገልግሎት ዘጋቢ ጋዜጠኞች ሄኖክ ሰማእግዜርን ጨምሮ  የአሜሪካ መንግስት ተቀጣሪ ሰራተኞች ናቸው፡፡

የጥቃት ጉዳት በማንኛቸውም የሰቪል ማህበረሰብ ተንኮል እና ደባ የሚፈጸም ስህተት ከሆነም ያንን ድርጊት ያቀነባበረው የሰቪል ማህበረሰብ ለደረሰው ጥፋት ተጠያቂ ይሆናል፡፡

በነጻው ፕሬስ ላይ የሚደረግ ማስፈራራት እና ስቅይት፣

ነጻውን ፕሬስ ማስፈራራት እና ማሰቃየት በአፍሪካ አምባገነኖች የሚፈጸም የሁልጊዜ ክስተት መሆኑ የተለመደ ነው፡፡ እንደ ዓለም አቀፍ የጋዜጠኞች ተከላካይ ድርጅት ዘገባ ከሆነ በኢትዮጵያ ያለው ገዥ አካል ነጻውን ፕሬስ ከሚያሽመደምዱ የፕሬስ ቀበኛ አምባገነኖች መካከል አራተኛ ደራጃን ይዞ ይገኛል፡፡

በአሜሪካ  በዘጋቢ ጋዜጠኞች የዘገባ የይዘት አቀራረብ እና ከያዙት ሀሳብ ጋር ባለመስማማት ወይም ደግሞ በሚከተሉት ርዕዮት ዓለም ወይም በሌላ ፍላጎት እና ወገንተኝነትን በማሳየታቸው እና ልዩነት በመኖሩ ምክንያት ብቻ ጋዜጠኞችን በህዝብ ፊት አናሳድድም፡፡ የጆርጅ አይቴን አባባል በመዋስ አሜሪካ የኢትዮጵያ የኮኩናት ሬፐብሊክ አይደለችም፡፡ በአሜሪካ ጋዜጠኞች ልዩ የሆነ ሚና ይጫወታሉ፡፡ ዘገባዎቻቸውን ለህዝብ ከማቅረባቸው በፊት ወጣ በማለት መረጃ በመሰብሰብ የምርምር ስራን ይሰራሉ፡፡ ሁልጊዜ ተራ የሆኑትን ዜጎች እና በሙያው ክህሎቱ ወይም በዚያ ነገር ላይ ሀሳብ መስጠት የሚችሉትን አስፈላጊ ባለሙያዎችን ቃለመጠይቅ ያደርጋሉ፡፡ የህዝብ ተቃውሞ በሚደረግባቸው አካባቢዎች በመገኘት የተሳታፊዎችን ሀሳቦች በማጣራት ለህዝብ ዘገባ ያቀርባሉ፡፡

የአሜሪካ ፕሬስ ከሁሉም በላይ ዋና ሚናው ለህብረተሰቡ መረጃ ማቅረብ እና ማስተማር ነው፡፡ ፕሬሱ የሙስና ምልክቶችን አነፍንፎ በማግኘት እና ስልጣንን ከህግ አግባብ ውጭ መጠቀምን በማጋለጥ እንዲሁም የመንግስት ባለስልጣኖች በህዝቡ ዘንድ ተጠያቂነት እንዳለባቸው ለህዝቡ በማሳወቅ የህዝቡን ደህንነት ዋና ጠባቂ ውሻ ነው፡፡ (ፕሬሱ በእንቁላል ቅርጹ የኋይት ሀውስ ቤተመንግስት ተፈጽሞ የነበረውን ድብቅ ወንጀል ፈልፍሎ በማውጣት እንዲሁም ወንጀሉን ለመሰሸፋፈን ሲደረግ የነበረውን ደባ ነቅሶ በማውጣት እና ለህዝብ ይፋ እንዲሆን እና እንዲጋለጥ በማድረጉ ምክንያት ፕሬዚዳንት ኒክሰን እራሳቸውን ከስልጣናው እንዲያሰናብቱ ማድረጉን ልብ ይሏል፡፡) ፕሬሶች የህዝብ ዓይን እና ጆሮ እንዲሁም አፍ ናቸው፡፡ ፕሬሶች የሙያ ስነምግባር ግዴታን ከግንዛቤ በመውሰድ የበርካታ ባለድርሻ አካላትን አስተያየት እና ሀሳቦችን አካትቶ ፍትሀዊ እና ሚዛናዊ የሆነ ዘገባ ለህዝብ ማቅረብ ነው፡፡ ዋናው ተግባራቸው በህረተሰቡ ላይ የበላይነት አስተሳሰብ ያለውን የህብረተሰብ ቡድን ወይም ደግሞ በስልጣን ላይ ያለውን ቡድን አስተሳሰብ እና ፍላጎት ብቻ በመያዝ እንደ በቀቀን መደጋገም፣ ማራገብ እና ማስተጋባት አይደለም

የፕሬስ ነጻነት ትርጉም፣

በአንድ ወቅት ጆን ሚልተን አሪዮፓጊቲካ በሚለው መጽሐፋቸው እንዲህ ብለው ነበር፣ “እውቀት እንድሸምት፣ መናገር እንድችል እና ለህሌናዬ ተገዢ በመሆን በነጻነት መከራከር እንድችል  ነጻነቴን ስጠኝ፣ ከሁሉም በላይ ነጻነቴን እፈልጋለሁ” ሚልተን የፕሬስ ነጻነትን ለመንከባከብ ጥረት ያደረጉ የመጀመሪያው የእንግሊዝ ገጣሚ እና ተቺ አዋቂ ባለሙያ ነበሩ፡፡ በእንግሊዝ ፓርላማ በተላለፈው ውሳኔ መሰረት የ1643 መጽሐፎች የህትመት ስራ ከመጠናቀቁ በፊት ቅድመ ምርመራ እንዲደረግ እና የፈቃድ ትዕዛዝ እንዲሰጥ ተላልፎ የነበረውን ውሳኔ ለመከላከል እንዲቻል አሪዮፓጊቲካ የሚለውን መጽሐፍ ጽፈዋል፡፡

አሳማኝ በሆነ መልኩ አሪዮፓጊቲካ የመጀመሪያው እና አሳማኝ የሆነ የመንግስትን የፕሬስ የቅድመ ምርመራ ስራ የሞገተ ታላቅ ስራ ነው፡፡ ሚልተን በአንደበተ ርትኡነት እንዲህ በማለት የክርክር ጭብጣቸውን አቅርበው ነበር፣ “ተጠራጣሪነት በስራ ላይ እስከዋለ ድረስ ጥሩን ሰው መግደል ጥሩ የሆነን መጽሐፍ እንደመግደል ያህል ነው፡፡ ሰውን የሚገድል ምክንያታዊ የሆነን ፍጡር እና የአምላክን አምሳያ ገደለ ማለት ነው፣ ሆኖም ግን ጥሩ የሆነን መጽሐፍ የሚያጠፋ ሰው ምክንያትን እራሱን ወይም ደግሞ በዓይናችን ላያ ያለውን የአምላክን አምሳያ ገደለ ማለት ነው፡፡“  የፕሬስ ነጻነትን መጨቆን ሁሉም ማቆያዎቻችን እና ወደቦቻችን እንዳይሰሩ ከማገድ ጋር እኩል ነው፡፡ ይህም ማለት አስፈላጊ የሆኑት ሸቀጦች ወደ እኛ እንዳይደርሱ ማዘግየት እና ማገድ ማለት ነው፡፡ (አጽንኦ ተጨምሯል፡፡)

በተመሳሳይ ሁኔታ የአሜሪካ አርበኛ የሆኑት ፓትሪክ ሄንሪ እ.ኤ.አ መጋቢት 23/1775 በቨርጂኒያ እንዲህ የሚል ንግግር አድርገው ነበር፣ “ነጻነቴን ወይም ሞቴን ስጠኝ“ እናም የቨርጂኒያን ቅኝ ግዛት ለመመለስ እና ለመጠበቅ ነው…ለዚህ ተግባር በቂ ቁጥር ያላቸውን ወታደሮች መመድብ እና እነርሱም በወታደራዊ ስነምግባር የተካኑ መሆን እንዳለባቸው የሚያሳስብ ነው… (ለቅኝ ተገዥዎች ጥሪ በማቅረብ ጠብመንጃዎቻችሁን አንሱ እና የአመጽ አብዮት አካሂዱ በማለት ጥሪ አቅርበዋል)፡፡ በመቀጠልም እንዲህ ብለዋል፣ “የነጻነት ወይም ደግሞ የባርነት ጥያቄ ከማንሳት ያነሰ ምንም ዓይነት ነገር የለም፣ እናም የጉዳዩ ርዕስ የመዋያያው ዋናው ርዕስ መሆን አለበት፡፡ እንግዲህ በዚህ ዓይነት መንገድ ብቻ ነው ወደ እውነት ለመድረስ ተስፋ የምናደርገው እና ለአምላክ እና ለሀገራችን የያዝነውን ትልቅ የሆነውን ኃላፊነት ለመወጣት የምንችለው፡፡“ (አጽንኦ ተጨምሯል፡፡)

“የ13ቱ የተባበሩት የአሜሪካ የክልል መንግስታት ነጻነት ስምምነት“ የሚለው መጽሐፍ ደራሲ የሆኑት ቶማስ ጀፈርሰን እ.ኤ.አ ሀምሌ 4/1776 በተደረገው የምክር ቤት ጉባኤ አሁን ካለንበት ከ239 ዓመታት በፊት እንዲህ ብለው ነበር፣ “መንግስት ከጋዜጦች ውጭ እና ጋዜጦች ከመንግስት ውጭ ከሚሉት ሁለት አማራጮች መካከል አንዱን ምረጥ የሚል ምርጫ ቢቀርብልኝ የመጨረሻውን እንደምመርጥ ጥርጥር የለኝም፡፡“ 

የፕሬስ ነጸነት መጠበቅ፣

በኢትዮጵያ የፕሬስ ነጻነትን በመጠበቅ ከማንም በላይ በተሻለ ሁኔታ እየተንቀሳቀስኩ መሆኑን አንባቢዎቼ ይገነዘባሉ፡፡

እ.ኤ.አ መስከረም 2010 አሁን በህይወት የሌለው መለስ ዜናዊ ወደ ኮሎምቢያ ዩኒቨርስቲ አሜሪካ በመምጣት ንግግር የማድረግ መብት እንዳለው ሽንጤን ገትሬ ተከራክሪያለሁ፡፡

ሆኖም ግን እንደ ዩኒቨርስቲ ፕሮፌሰር እና የሕገ መንግስት የሕግ ባሉሙያ በነጻ ለመናገር መብት በጽናት በመቆም ነጻ ንግግርን በሚመለከት ለሁሉም ጉዳዮች እንዲህ የሚል አንድ ዓይነት መለኪያ መስፈርትን አቅርቢያለሁ፡ የዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ድንጋጌ አንቀጽ 19 እንዲህ ይላል፡ ማንም ሰው ሀሳቡን በነጻ የመግለጽ መብት አለው፡፡ ይህ መብት ማንም ሰው ያለማንም ጣልቃገብነት ሀሳቡን የማራመድ እና በማንኛውም መገናኛ ብዙሀን የዕውቀት ውሱንነት ቢኖርም እንኳ መረጃ የመፈለግ፣ የመቀበል እና የማካፈል መብት አለው፡፡ ማንም ሰው እና የዕውቀት ውሱንነት ቢኖርም እንኳ በሚሉት ቃላት ላይ ላሰምርባቸው እፈልጋለሁ፡፡

እ.ኤ.አ መስከረም 2010 በሁፊንግተን ፖስት “አቶ መለስ ዜናዊ ወደ ኮሌጅ ሄደ!“ በሚል ርዕስ ባቀረብኩት ትችት መለስ በኮሎምቢያ ዩኒቨርስቲ በመገኘት ንግግር ማድረግ እንዳይችል የቀረበውን የክልከላ ጥሪ ተቃውሚያለሁ፡፡ መለስ እንዲናገር እንዲፈቀድለት በሚለው ሀሳብ ላይ የነበረኝን አቋም በማጠናከር በዚህ ጉዳይ ላይ ከእኔ ጀግና ከእስክንድር ነጋ እና የእርሱ ባለቤት ከሆነችው ከእኔ ጀግኒት ከሰርካለም ፋሲል ጋርም እንኳ ስምምነት አልነበረንም፡፡

መለስ ወደ ስብሰባ ቦታው ተጋብዞ ንግግር ማድረግ እንዳይችል የቀረበውን ጥሪ ወይም ደግሞ መለስ በሰው ልጆች ላይ በሰራቸው በርካታ የሰብአዊ መብት ረገጣዎች እጁ በደም ተጨማልቆ የሚገኝ ወንጀለኛ መሆኑን ባውቅ እና በዚህ እኩይ ምግባሩ ምክንያት ለእርሱ ከፍተኛ የሆነ ንቀት ያለኝ ቢሆንም በኮሎምቢያ በመገኘት ንግግር ከማድረግ መከልከል የሌለበት እና የመናገር መብት እንዳለው ሞግቼ ነበር፡፡ ምንም ዓይነት ማዕቀብ ሳይደረግ መለስ መናገር እንዲችል ከጎኑ ቆሜ ስከራከር ነበር፡፡ ለእርሱ ንግግርም ምላሽ የመስጠት ሙሉ መብት እንዳለ ግልጽ አድርጌ ነበር፡፡ በዚያን ጊዜ እንዲህ የሚለውን የኗም ቾምስኪንን አባባል  ግልጽ አድርጌ ነበር፣ “የምንንቃቸው ህዝቦች ነጻነትን ማግኘት እንዳለባቸው እስካለመንን ድረስ በነጻነት በእራሷ ላይ ሙሉ በሙሉ እምነት የለንም፡፡“

ማንም ሰው በመገናኛ ብዙሀን መረጃ የመቀበል እና የማካፈል መብት እንዳለው ያለኝ እምነት አሁንም የጸና ነው፡፡ ሀሳብ ያላቸው ጸሀፊዎች እንደ እኔ ያሉትን እና የአሜሪካ ድምጽ የአማርኛው አገልግሎትን ያካትታል፡፡

እ.ኤ.አ ሀምሌ 2012 እ.ኤ.አ በ1991 በተመሳሳዩ በመለስ ዜናዊ ከተተካው እና ደም ከጠማው አምባገነን ከነበረው ከመንግስቱ ኃይለማርያም ጎን ቆሜ ነበር፡፡ የተወሰኑ ሰዎች ከህግ አግባብ ውጭ የመንግስቱን መጽሐፍ በማባዛት በፒዲኤፍ ፎርም በግንኙነት መስመር ማሰራጨት ጀምረው ነበር፡፡ የህትመት ባለቤትነትን የካዱ እነዚህ ሰዎች መንግስቱ ገዳይ እና ውሸታም ነበር፣ እናም መጽሐፉ መነበብ እና መደመጥ የለበትም ወይም ደግሞ ከመጽሐፉ ሽያጭ ጥቅም እንዳያገኝ መፈቀድ የለበትም የሚል አቋምን ያራምዱ ነበር፡፡

መጽሐፉ  ህገወጥ በሆነ መልኩ በግንኙነት መስመር ተባዝቶ እንዲሰራጭ በማድረግ እነዚህ የአዕምሮ ንብረት ባለቤትነት መብት ደፍጣጮች በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን ድምጽ ጸጥ ያደርግ የነበረውን መንግስቱን በተራው ጸጥ በማድረግ ድምጽየለሽ ለማድረግ ያቀዱት ዕቅድ ነበር፡፡ በመቃብር ያሉ የእርሱ ሰለባዎች እንደ መለስ ሰለባዎች ሁሉ በመቃብር ሆነው ይናገራሉ፡፡ እኛ እየኖርን ባለነው ሰዎች አይደመጡም፣ ሆኖም ግን መብረቃዊ በሆነ ድምጽ ኃይል ባለው ሁኔታ ድምጻቸውን ከፍ አድርገው ይናገራሉ፡፡

ላለፉት 9 ዓመታት ሙሉ በስልጣን ላሉት በተለይም ስልጣናቸውን ከህግ አግባብ ውጭ ለሚጠቀሙ እና በኢትዮጵያ ላሉ ባለስልጣኖች እውነቱን ስናገር ቆይቻለሁ፡፡ በኢትዮጵያ በስልጣን ማማ ላይ ተንጠራርቶ ስለሚገኘው ገዥ አካል ሀሳቤን እና አመለካከቴን ለሚጋሩት በዚህ በዲያስፖራው ለሚኖሩት ኢትዮጵያውያን/ት ወገኖቼ እውነታውን መናገር በጣም የሚቆጠቁጠኝ ነገር ነው፡፡

በኢትዮጵያ ዲያስፖራ እና በኢትዮጵያ ተቃዋሚ ኃይሎች ላይ በርካታ የሆኑ የተከላካይነት እና የአውዳሚነት ባህሪ ተመልክቻለሁ አይቻለሁም፡፡ ዝምታዬን ይዠ ተቀምጫለሁ ምክንያቱም በአሁኑ ባለው ገዥ አካል ላይ ተመሳሳይ አመካከት እና ሀሳብ ያለን ወገኖቼን ብደብድባቸው በኢትዮጵያ ባለው የወያኔ ገዥ አካል ሁላችንም እንደበደባለንና ነው፡፡

ለዚያም ጉዳይ በእራሴ አፈርኩ እላለሁ፣ አስመሳይ ሆኘ ቆይቻለሁ፡፡

ለእውነት ስል በሁለት ቢላዋ ስጠቀም ቆይቻለሁ፡ ስምምነት ከሌለኝ ሰዎች ጋር በመለሳለስ እና ስምምነት ካለኝ ሰዎች ጋር ደግሞ ጃሮ ዳባ ልበስ አልሰማም፣ አላይም በማለት ነው፡፡ ሆን ብዬ እያወቅሁ ምንም የማላውቅ ማይም ሆኛለሁ እናም ስምምነት ያለን ሰዎች በእኔ አስተሳሰብ ስህተት ሲሰሩ ዝም ብዬ እየተመለከትኩ ነው፡፡

በስልጣን ላይ ላሉት እና ስልጣናቸውን ከህግ አግባብ ውጭ በሚጠቀሙት ሰዎች ላይ እውነታውን መናገር አለብኝ፡፡ የለም እውነታውን ለእራሴ መናገር አለብኝ፣ ማለትም ስምምነት ላለን ሰዎች፣ ምንም ዓይነት ኃይል ለሌላቸው፣ ስልጣን እንደ ምግብ ለተራቡ እና በስልጣን ላበዱ እውነታውን መናገር አለብኝ፡፡

ለሄኖክ ሰማእግዜር የእራሴ ይቅርታ፣

እ.ኤ.አ ሀምሌ 3/2015 በእራሱ ላይ ስለተፈጸመው ነገር ለሄኖክ ሰማእግዜር የእራሴ የግል ይቅርታ አቀርባለሁ፣ ምክንያቱም በእርሱ ላይ ሁከት እና ብጥብት ያስነሳው ኃይል ለእርሱ ይቅርታ የመጠየቅ የሞራል ድፍረቱ የለውም ብዬ ስለማምን ነው፡፡

እውነት ለመናገር ለእርሱ ይቅርታ ለማቅረብ ቃላት የሉኝም፡፡ እርሱን የሚያባርሩ ተቃዋሚ ነውጠኞችን የቪዲዮ ምስል ካየሁ በኋላ በእርግጠኝነት ምን ለማለት እችላለሁ?

በነውጠኛ ተቃዋሚዎች እጅ ለተደረገለት አያያዝ በእርግጠኝነት አፍሪያለሁ ልበል?

ለእርሱ የሚስማሙ ቃላት ልስጠው? ስለዚህ ጉዳይ አታስብ፡፡ ይህ ክስተት በአጋጣሚ የተደረገ ድንገተኛ ነገር ነው፡፡ በሌላ ጊዜ እንደዚህ ያለ ነገር በፍጹም አይደረግም፡፡

በእርግጠኝነት ምን ማለት እንዳለብኝ የማውቀው ነገር የለም፣ እንዲያው በደፈናው በአንተ ላይ ጉዳት በመሰንዘሩ፣ የውርደት ድርጊት በመፈጸሙ እና ስራህን በመስራትህ የንቀት ድርጊት የተፈጸመብህ በመሆኑ አዝናለሁ፡፡ ይህ ስለሆነም ሄኖክ አዝናለሁ!

ለሄኖክ እንዲህ ለማለትም እፈልጋለሁ፣ “እንደ ዘጋቢ ጋዜጠኛ የእራሱን ስራ እየሰራ ባለበት ሁኔታ እንዲሰቃይ በመደረጉ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርትን ቀስሟል የሚል ተስፋ አለኝ፡፡“ ሀምሌ 3 ያጋጠመው ነገር በኢትዮጵያ ያሉ ወንድም እና እህት ጋዜጠኞች ዓመቱን ሙሉ በየቀኑ የሚደርስባቸው ድርጊት ነው፡፡ ማስፈራሪያ ይደርስባቸዋል፣ ከህግ አግባብ ውጭ ያያዛሉ፣ እናም ሀምሌ 3 በእርሱ ላይ እንደደረሰው ሁሉ እነርሱ ደግሞ በአምባገነኖች እየተያዙ እንደ ጥጃ ይታሰራሉ፡፡

ለዚህም ነው ምንም ዓይነት ጥያቄ ሳላቀርብ ሄኖክ ምንም ዓይነት ድምጽ ለሌላቸው ወንድሞቼ ለእስክንድር ነጋ እና ለውብሸታ ታዬ እንዲሁም ምንም ዓይነት ድምጽ ለሌላት ለእህቴ ለርዕዮት ዓለሙ እና ለሌሎችም እንደ እነርሱ በእስር ቤቶች ታጉረው እና ለሀገር ለተሰደዱ ኢትዮጵያውያን ድምጽ የለሾች ሁሉ ድምጽ እንድትሆናቸው ምንም ዓይነት ጥያቄ በፍጹም አላቀርብም፡፡  ግዴታህ ነው ማድረግ አለብህ አለዋለሁ።

በአሁኑ ጊዜ በአምባገነኑ ገዥ አካል ተይዘው በመሰቃየት ላይ ላሉት ድምጽ ለሌላቸው ኢትዮጵያውያን/ት ጋዜጠኞች ሁሉ ደምጽ እንዲሆናቸው እጠይቃለሁ ምክንያቱም የእኔ ፍላጎቶች ወይም ደግሞ የእርሱ ሀሳቦች ወይም ሩህሩህነት በአንድ ወይም በሌላ መንገድ እነርሱን እንዲያስብ የሚያስገድደው ነገር አለበትና፡፡

ሄኖክ ለእስክንድር ነጋ፣ ለውብሸት ታዬ፣ ለርዕዮት ዓለሙ እና ለሌሎችም እንደ እነርሱ ላሉት በርካታ ጋዜጠኞች ድምጽ እንዲሆን እጠይቃለሁ ምክንያቱም በቪኦኤ የአድማጮች መብት ሰነድ ላይ በግልጽ የሰፈረው ይህንን ነገር እንዲያደርግ ያስገድደዋልና፡፡

ሄኖክን ይቅርታ እንድጠይቅ የሞራል ግዴታ አለብኝ፡፡ ሆኖም ግን ሄኖክ እና የቪኦኤ ድምጽ የአማርኛው አገልግሎት ዘጋቢ እና የምርመራ ጋዜጠኞች ሁሉ ድምጽ ለሌላቸው ኢትዮጵያወያን/ት ወገኖቻችን ሁሉ ድምጽ እንድትሆኑ የመጠየቅ መብት አለኝ፡፡

ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!

ሰኔ 30 ቀን 2007 ዓ.

 

Similar Posts