እውን አፍሪካ ጋይሌ ስሚዝን ትፈልጋለችን?

ከፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማርያም      

ትርጉም በነጻነት ለሀገሬ

Gayle Smith Hearingጋይሌ ስሚዝ፣ ዌንዲ ሸርማን እና  ሱሳን ራይስ በጋራ ያላቸው ነገር ምንድን ነው? 

በዚህ ባለፈው ሐሙስ በአሁኑ ጊዜ የፕሬዚዳንቱ ረዳት ልዩ አማካሪ እና በሱሳን ራይስ በሚመራው በብሔራዊ ደህንነት ምክር ቤቱ ነባር ዳይሬክተር የሆኑት ጋይሌ ስሚዝ የዩናይትድ ስቴትስ ዓለም አቀፍ የልማት ኤጀንሲ/United States Agency for International Development (USAID) ቀጣይ አስተዳዳሪ እንደሚሆኑ የተረጋገጠ መሆኑ ተሰምቷል፡፡

ይህ ነገር ብዙም መደመጥ ያለለበት ጉዳይ አልነበረም፡፡ ሴትዮዋ አፋጣጭ ጥያቄዎችን አልተተየቀችም፡፡

ቀደም ሲል ተዘጋጅቶ በቀረበው መግለጫቸው ግልጽ እንደሆነው ይህንን የኃላፊነት ቦታ የሚያገኙት ከሆነ የዓለምን ህዝብ ግማሽ ህይወት መታደግ እንደሚችሉ እንዲህ በማለት በይፋ ተናግረዋል፡፡ “ዩኤስኤአይዲ/USAID ፈጣን እና ብልህነትን በተላበሰ መልኩ እንደነገሮች የአመጣጥ ሁኔታ ተለዋዋጨ በመሆን መፍትሄ የሌላቸው የሚመስሉ አስቸጋሪ የልማት ችግሮችን በመፍታት ሰብአዊ ቀውሶችን በማስወገድ ልዩ የሆነ ቦታ አለው“ በማለት አውጀዋል፡፡

መኮንን ጌታቸው የተባሉት ኢትዮጵያዊ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ይህንን ዲስኩር በሰሙበት ጊዜ ተቃወሟቸውን በማሰማት የስሚዝን ንግግር በማቋረጥ ስብሰባውን ረግጠው መግለጫ ከሚሰጥበት የስብሰባ አዳራሽ በመውጣት ጥለው ሄደዋል፡፡   

በርካታዎቹ አንባቢዎቼ የስሚዝን መሾም እና ሹመታቸውንም የምክር ቤቱ አባላት በማጽደቁ ምክንያት ለምን ተቃውሞ እያሰማሁ እንዳለሁ በሚገባ እንደሚያውቁት እገነዘባለሁ፡፡

የሴትዮዋ ሹመት በምክር ቤቱ አባላት መጽደቁን በማስመልከት እ.ኤ.አ ግንቦት 2015 ባወጣሁት ትችቴ ላይ በመርህ ላይ የተመሰረተ ተቃውሞዬን አቅርቤ እንደነበር ይታወሳል፡፡ እንዲህ የሚል የክርክር ጭብጤን አቅርቤ ነበር፣ “ስሚዝ ከአፍሪካ ጠንካራ ሰዎች ጋር ለረዥም ጊዜ የቆዬ እና እጅግ በጣም የተቀራረበ ወዳጃዊ ግንኙነት ያላቸው ሰው በመሆናቸው በአህጉሩ ውስጥ ለሰብአዊ መብት መከበር፣ ለህግ ልዕልና የበላይነት እና ለመልካም አስተዳደር መስፈን የሚኖራቸው ሚና ደካማ ይሆናል፣“ በማለት አስረግጨ ተናግሬ ነበር፡፡ 

ከዚህም በተጨማሪ በርካታዎቹ አንባቢዎቼ እንደምትገነዘቡት ሁሉ ባለፉት ጥቂት ወራት የዩኤስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ረዳት ጸሐፊ ከሆኑት ከማዳም ዌንዲ ሸርማን ጋር በተመሳሳይ መልኩ ክርክር ውስጥ ገብቼ እንደነበር የምታውቁት ጉዳይ ነው፡፡

ቀደም ሲል አቅርቢያቸው በነበሩት ሶስት ሳምንታዊ ትችቶቼ ዌንዲ ሸርማን ከእውነታው ጋር በተጻረረ መልኩ እና ሆን ብለው እያወቁ በወገኖቼ ላይ የወደቀውን እንዛዝላ ከምንም ባለመቁጠር “ኢትዮጵያ የጎለመሰ ዴሞራሲያዊ ስርዓትን የምታራምድ ሀገር ስትሆን በቀጣይም እ.ኤ.አ ግንቦት 24/2015 የሚካሄደው ሀገር አቀፍ ምርጫ ነጸ፣ ፍትሀዊ እና በህዝብ ዘንድ ታማዕኒነት ያለው ይሆናል፣“ በማለት የቀጠፉትን ቅጥፈት ፊት ለፊት በመጋፈጥ እና በማጋለጥ የክርክር ጭብጤን ሳቀርብ እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡

ስለኢትዮጵያ የጎለመሰ ዴሞክራሲ የሸርማን ቻምፒዮን ሆኖ የመቅረቡን ጉዳይ በማስመልከት ተራ ቅጥፈት እና ሸፍጥ መሆኑን በሚያመላክት ሁኔታ እራሱን ህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ እያለ የሚጠራው የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ እ.ኤ.አ ግንቦት 24/2015 ባካሄደው የይስሙላ የቅርጫ ምርጫ ውጤትን በማስመልከት በቅርቡ ባወጀው መሰረት በተቆጠረው የመራጮች ድምጽ 99.9 በመቶ ብቻ ሳይሆን መቶ በመቶ ያሸነፈ መሆኑን እና እስከ አሁን ድረስ ይፋ ሆነ በተባለው ውጤት መሰረት 442ቱን መቀመጫዎች በሙሉ መቆጣጠሩን ለሚሰማ ሁሉ የክርክር ጭብጤ መቶ በመቶ ትክክለኛ መሆኑን ለማረጋገጥ ይችላል፡፡

ቀሩ የተባሉትን 105 መቀመጫዎችም ወያኔው እራሱ በፈለገው ጊዜ በማወጅ 100 በመቶ አሸናፊ መሆኑን ከመግለጽ ወደኋላ እንደማይል ልብ ሊባል ይገባል፡፡ (የሸርማን የዴሞክራሲ ሻምፒዮንነት የሚያስገርመው ጉዳይ ደግሞ 442 የፓርላማ መቀመጫ ወንበሮችን መቶ ለመቶ አሸነፍኩ ብሎ ለመውሰድ ከሶስት ቀናት በላይ ያልወሰደ ምርጫ ቀሪዎቹን 105 መቀመጫዎችን ውጤት ለመግለጽ ግን በርካታ ሳምንታትን እየወሰደ የመገኘቱ ሁኔታ ነው)፡፡ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ፍጆታ ማታለያ ሲባል ምን እናድርግ እየተባለ የመዶለት ሁኔታ እንጅ ሌላ ምንም ነገር ሊሆን እንደማይችል የመሰሪውን ድርጅት ልቦና የሚያውቅ ሰው ሁሉ ይገነዘበዋል የሚል ግምት አለኝ፡፡

የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ እ.ኤ.አ በ2015 ይካሄዳል እየተባለ የሚደሰኮርለትን ሀገር አቀፍ የቅርጫ ምርጫ መቶ በመቶ አሸነፍኩ ብሎ እንደሚያውጅ ከዓመት ባፊት በቀረብኩት ትችቴ ላይ በትክክል ትንበያ ሰጥቸ ነበር፡፡

ሸርማን የወያኔውን የወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ምርጫው ነጻ፣ ፍትሀዊ እና በህዝብ ዘንድ ታማዕኒነት ያለው ሆኖ በመጠናቀቅ መቶ በመቶ በማሸነፋችሁ እንኳን ደስ አላችሁ የሚል መልዕክት እስከሚያስተላልፉ ድረስ የመቆየት ትግዕስቱ የለኝም፡፡ አሁንም ቢሆን ሸርማን ኢትዮጵያ የጎለበተ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እያራመደች ነው የሚለውን እወጃቸውን አይደግሙትም ለማለት የሚዳዳው ማን ነው?

የኒዮርክ ታይምስ መጽሔት እንዲህ የሚል ዘገባ አቅርቦ ነበር፣ “የኦባማ የኢራን የኒኩሌር ንግግር ዕቅድ ዋና ተደራዳሪ የሆኑት ሰው የስምምነቱ ጊዜ ከተጠናቀቀ በኋላ ከስራቸው ይለቃሉ ሲል  ዘግቧል ፡፡

የኒዮርክ ታይምስ መጽሔት ኢትዮጵያ የጎበለበተ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እያካሄደች ነው ስለሚለው የሸርማን አስገራሚ ቅሌት አንዲትም ቃል ትንፍሽ ሳይል ቀርቷል፡፡

ኦባማ ሸርማንን እንዲህ በማለት አሞካሽተዋቸው ነበር፣ “በእርሳቸው ትውልድ ካሉት ዲፕሎማቶች ሁሉ በጣም ውጤታማ የሆኑ“ ወቼ ጉድ! ውጤታማ ወይስ ውጤት አልባ ዲፕሎማት?

እውነት ነው ሸርማን በእርሳቸው ትውልድ ካሉት ሁሉ የበለጠ ውጤታማ ዲፕሎማት ከሆኑ በእርግጥም ኢትዮጵያ ያለምንም ጥርጥር የጎለበተ ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን እያራመደች ያለች ሀገር ናት!

ሸርማን በዚህ ወር መጨረሻ ከስልጣናቸው ይለቃሉ የሚለው ዜና በክሊንተን አስተዳደር ጊዜ የሰሜን ኮሪያን የኒኩሌር ስምምነት መና አስቀርተውት እንደነበረው ሁሉ አሁንም የኢራንን የኒኩሌር ስምምነት ስራ ወደከፋ እና የተበላሸ ሁኔታ ላይ በማድረሳቸው ምክንያት ነው፡፡

እንደ አንድ ይፋ እንደተደረገ ዘገባ ከሆነ “ሸርማን በክሊንተን አስተዳደር ወቅት ሲያገለግሉ በነበሩበት ጊዜ ሰሜን ኮሪያ የኒኩሌር ጦር መሳሪያ እንዳይኖራት ለመከላከል ከተቋቋመው ቡድን ጋር አብረው እንዲሰሩ ተጠይቀው ነበር፡፡ በአጭሩ ሸርማን እና ቀሪዎቹ የክሊንተን የቡድን አባላት በአንድ ቡድን ተዋቅረው የስምምነት ስራውን ከጀመሩ በኋላ ከዚህ በተጻረረ መልኩ ሰሜን ኮሪያ ያለምንም ችግር በቀላሉ የኒኩሌር መሳሪያ ባለቤት ለመሆን በቃች፡፡“

በሚያስገርም ሁኔታ ሸርማን ምንም ዓይነት የዲፕሎማሲ ልምድ ባይኖራቸውም እንኳ ከስምምነቱ በፊት ወደ ሰሜን ኮሪያ እንዲያቀኑ ተደረገ፡፡ ሴትዮዋ የዲፕሎማሲ ስምምነቱን አካሄድ ባለማወቅ ይጠበቅ የነበረውን ውጤት አፈር ድሜ በማብላታቸው ሊያስደንቅ የሚችል ጉዳይ አይደለም፡፡ ልምዱ እና ብቃቱ የላቸውምና፡፡

በመጨረሻም ሸርማን የፔተር የአስተዳደር መርሆዎች የብቃትየለሽነት ሰለባ ለመሆን በቁ፡፡ በዚህም መሰረት ሴትዮዋ በኢራን ኑከሌር ስራ የዲፕሎማቲክ አቅምየለሽነታቸውን ለሁለተኛ ጊዜ አስመሰከሩ፣ እናም በአሁኑ ጊዜ ብቃትየለሽነታቸው በይፋ በመታወቁ በበሩ ለመውጣት በማኮብኮብ ላይ ናቸው!

የኒኩሌር ጦር መሳሪያ ባለሙያ የነበረው ሰው እንዴት በአንድ ጊዜ ከመቅጽበት ስለኢትዮጵያ የቅርጫ ምርጫ ባለሙያ ለመሆን ይችላል?

ደህና! የሚያስገርም ነገር ነው ወገኖቼ! እንዴት አንድ የወባ ትንኝ ተመራማሪ የሆነ ሰው በአንድ ጀንበር በመነሳት የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሊሆን ይችላል?

ሸርማን ኢትዮጵያ የጎለበተ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት በማራመድ ላይ የምተገኝ ሀገር ናት፣ እናም ገዥው አካል እ.ኤ.አ ግንቦት 24/2015 የሚያካሂደው ምርጫ ነጻ፣ ፍትሀዊ እና በህዝብ ዘንድ ታማዕኒነት ያለው ሆኖ ይጠናቀቃል በማለት አስተላልፈውት በነበረው እርባናየለሽ እና የቅጥፈት ዲስኩር በዋሽንግተን ፖስት መጽሄት የዘገባ መጋዝ ተቆርጠዋል፡፡

በአንድ በተወሰነ የመንግስት ባለስልጣን በወጣ የአቋም መግለጫ ሸርማን በስልጣን ላይ ላለው አገዛዝ (በኢትዮጵያ በስልጣን ላይ ተፈናጥጦ ለሚገኘው ለህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ  አገዛዝ) የሲቪል ማህበረሰቡን በመጨቆን ሰብአዊ መብቱን ደፍጥጦ እና የነጻውን ፕሬስ ስልታዊ በሆነ መልኩ ለዓመታት እያሽመደመደ ነጻ አስተሳሰብ እና እምነት እንዳይኖር በይፋ እና በአደባባይ እየተጋ ላለው አገዛዝ የማይገባውን እና እርባናየለሽ ሙገሳ በማድረጋቸው ዋሽንግተን ፖስት በትችት በመሸንቆጥ በቅጣት ሳጥን ውስጥ እንዲቀመጡ አድርጓቸዋል… ካለፈው ዓመት ጀምሮ የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች፣ አባላት እና ደጋፊዎቻቸው በቁጥጥር ስር እየዋሉ ስቃይ ይደርስባቸዋል፡፡

የዋሽንግተን ፖስት መግለጫ ዩኤስኤ ከእንደዚህ ዓይነት የሞኞች የዥዋዥዌ ጨዋታ እራሷን በማውጣት እና ትክክለኛ እና እውነተኛ የኢትዮጵያን ፖሊሲ ማራመድ እንዳለባት እንዲህ በማለት የማጠቃለያ አስተያየቱን አስፍሯል፡

…ሆኖም ግን በአሁኑ ጊዜ እንደዚህ ያለ የዩልኝ እመኑልኝ ዓይነት መግለጫ መስጠት ወይም ደግሞ እንደዚህ ያለ ከእውነታው የራቀ ልስልስ ያለ ነገር ማራመድ አይሰራም፡፡ የዩናይትድ ስቴትስ መንግስት የብዙሀን መገናኛ ዘዴዎችን ለሚያፍን፣ የተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶችን ተሳትፎ ለሚያቀጭጭ እና ትችት የሚያቀርቡበትን ዜጎች ጸጥ ለማድረግ ለሚተጋ አገዛዝ በእርዳታ ስም በሚሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር መስጠት ማቆም አለባት:: በነጻ የምርጫ ታዛቢ ያልተረጋገጠውን የምርጫ ሁኔታ ሸርማን በእራሳቸው ስሜት በመነሳሳት ሙገሳ የቸሩትን መንግስታቸው ስህተቱን አምኖ በመቀበል መዋጥ እና ቀጣይ የአካሄድ መንገዱን ማስተካከል ይኖርበታል፡፡

ለዋሽንግተን ፖስት አርታኢ በተጻፈ ደብዳቤ ሸርማን ቀጥ በማለት ወደኋላ ተንሸራተዋል፡፡ እርሳቸው ምን ለማለት እንደፈለጉ ትክክለኛ ባልሆነ መልኩ ግንዛቤ ተይዟል የሚል አቤቱታ አቅርበዋል፡፡ የሌባ አይነ ደረቅ መልሶ ልብ ያወልቅ ነውና ሸርማን እኔ ያልኩት እንዲህ የሚል ነበር ብለዋል፣ “ኢትዮጵያ ዴሞክራሲን በማራመድ ረገድ ገና ያልጎለበተች ሀገር ናት፣ እናም በጊዜ ሂደት የፖለቲካ ስርዓቱ እየበሰለ በመሄድ ወደፊት ለህዝቦች እውነተኛ ምርጫ ያቀርባል የሚል ሀሳብ አለኝ፡፡“ በእርግጥ እንደዚህ ዓይነቱ ንግግር በተለምዶ ዲፕሎማሲያዊ እርባናየለሽ የማደናገሪያ የቃላት ጡዘት እና ቅጥፈት ይባላል፡፡ እኔ ደግሞ እንደዚህ ዓይነቱን የዥዋዥዌ ጨዋታ የአሜሪካ ዲፕሎአስመሳይነት እለዋለሁ፡፡

ቀደም ሲል ሱሳን ራይስ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እንዲሆኑ የቀረበውን ጥቆማ ጠንካራ በሆነ መልኩ ስቃወም እንደነበር አብዛኞቻችሁ አንባቢዎቼ የምታውቁት ጉዳይ ነው፡፡

ሱሳን ራይስ በአሁኑ ጊዜ የኦባማ ብሄራዊ የደህንነት አማካሪ ናቸው፡፡ ከላይ እንደተጠቀሰው የብሄራዊ ደህንነት ምክር ቤቱ ነባር ዳይሬክተር ናቸው፡፡

“የሱሳን ራይስ የቅጥፈት ትረካ“ በሚል ርዕስ ባቀረብኩት ትችቴ ላይ የሱሳን ራይስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት ስልጣናቸው የሚጸድቅላቸው ከሆነ ያለምንም ጥርጥር ራይስ እውነተኛ ስብዕናቸው ይጋለጣል፣ እውነተኛው ታላቁን እውነት የመደበቅ ስውር ባህሪያቸው፣ አስመሳይ ሸፍጠኝነታቸው እንዲሁም የፖለቲካ ድራማ ተጫዋች እና ደባ ሸራቢነታቸው ያለምንም መሸፋፈን ጎልቶ ይወጣል፡፡” የሚል ጠንካራ ትችት አቅርቤ ነበር፡፡

እ.ኤ.አ ታህሳስ 9/2012 “ሱሳን ራይስ እና የአፍሪካ ያልተባረከው ቅድስና“ በሚል ርዕስ ባቀረብኩት ትችት እንዲህ የሚል የክርክር ጭብጥ ሰንዝሬ ነበር፣ “በአሁኑ ጊዜ በተባበሩት መንግስታት የዩናይትድ ስቴትስ አምባሳደር የሆኑት ሱሳን ራይስ ከአፍሪካ አጭበርባሪ፣ እምነት የማይጣልባቸው መንታፊዎች እና አረመኔ ጨካኝ አምባገነኖች ጋር ለሁለት አስርት ዓመታት ያህል የእሽክርክሪት ዳንስ (ወይም ደግሞ ቂጥ ለቂጥ ተያይዞ መደነስ ልበለው) በመደነስ ላይ ይገኛሉ፡፡“

የሱሳን ራይስን ለውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት ቦታ መታጨት ጥቆማን በመቃወም በተለይም ለአፍሪካ አምባገነኖች ድጋፍ መስጠት እና እ.ኤ.አ መስከረም 2012 በሊቢያ በቤንጋዚ ላይ ከደረሰው የአሸባሪዎች አደጋ በኋላ ለዚያ ቁንጮ የሆነው የስልጣን ቦታ የነበራቸው ጉጉት ተጨናግፎ ቀርቷል፡፡ በዚህም መሰረት እ.ኤ.አ ታህሳስ 13/2012 ሱሳን ራይስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት ከሚለው ርዕስ ስማቸውን እንዲሰረዝ አድርገዋል፡፡

ያልተባረከው ቅድስና፡ የሞላጭሆች  

የሸጋይል ስሚዝን፣ የሸርማንን እና የራይስን የትብብር ስብስብ የምቃወመው ለምንድን ነው?

ለአንድ ዓይነት ምክንያቶች የአፍሪካን ያልተቀደሱ የሩዋንዳውን የፓውል ጋሜን፣ የኡጋንዳውን የዮሪ ሙሴቬኒንን፣ የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ መሪ የነበረውን መለስ ዜናዊን እና ሌሎችንም እነዚህን የሚመስሉ የአምባገነን ስብስብ የሶስትዮሽ ትብብሮች ስቃወም ቆይቻለሁ፡፡

ሂዩማን ራይትስ ዎች የተባለው ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅት እ.ኤ.አ በ2012 ባወጣው ዘገባ መሰረት የመለስ ዜናዊን አገዛዝ እንዲህ በማለት ገልጾት ነበር፣ “ኢትዮጵያ ሀሳብን በነጻ የመግለጽ፣ የመደራጀት እና የመሰብሰብ ነጻነትን በመገደብ፣ በሲቪል እና የፖለቲካ መብቶች ዙሪያ አስደንጋጭ በሆነ መልኩ ወደኋላ የመንሸራተት አዝማሚያ ተስተውሎባታል፡፡ ገዥው ፓርቲ ቀጣይነት ባለው ሁኔታ ስልጣኑን ከምንጊዜውም በላይ በማጠናከር ቁልፍ ተቋማት የሚባሉትን እና ለህግ የበላይነት መከበር ሁነኛ ሚና የሚጫወቱትን ፍርድ ቤቶችን እና ነጻውን ፕሬስ በማዳከም ላይ ይገኛል፡፡“

እንደዚሁም ሁሉ ሂዩማን ራይትስ ዎች እ.ኤ.አ በ2014 ባወጣው ዘገባ የፓውል ጋሜንን አገዛዝ በማያሻማ መልኩ እንዲህ በማለት ገልጾታል፣ “በካጋሜ ቁጥጥር ስር ያለችው ሩዋንዳ ለሰላማዊ የሲቪል ተቃዋሚ አመጸኞች እና ለፖለቲካ ተቃዋሚዎች ትዕግስቱ የላትም፡፡ ለበርካታ ዓመታት የዘለቀው የመንግስት ማስፈራራት እና በፖለቲካ ድርጅቶች ላይ ሰርጎ በመግባት ሲያደርግ የቆየው የመበታተን የሸፍጥ ስራ የሩዋንዳን የሲቪል ማህበረሰብ ሽባ እንዲሆን አድርጎታል፡፡“

በተመሳሳይ መልኩ ሂዩማን ራይትስ ዎች እ.ኤ.አ በ2014 ባወጣው ዘገባው የሙሴቬኒንን ተንፏቃቂ ጭቆና እንዲህ በማለት ገልጾት ነበር፣ “ለ27 መታት በስልጣን ላይ ከቆዬ በኋላ የፕሬዚዳንት ዮሪ ሙሶቬኒ መንግስት የመሰብሰብ፣ ሀሳብን በነጻ የመግለጽ እና የመደራጀት መብትን ተከታታይነት ባለው ሁኔታ በመገደብ እና በመጨቆን የሲቪል ማህበረሰቡ ሽባ እንዲሆን እያደረገ መሆኑን ይፋ አድርጓል፡፡“

ያለ ስሚዝ፣ ሸርማን እና ራይስ ድጋፍ እነዚህ የአፍሪካ ጨካኝ አምባገነኖች እና ሌሎች በአፍሪካ ውስጥ ያሉ እንደእነርሱ ያሉ የሰብአዊ መብት ደፍጣጮች ለአንዲት ቀን እንኳ በስልጣን ላይ ለመቆየት አይችሉም፡፡ በሸቪል እና እንደእነርሱ ባሉ ድጋፍ ሰጭዎች አማካይነት የአፍሪካ አምባገነኖች በአሜሪካ ግብር ከፋይ ህዝብ ድጋፍ ህዝብን በማሰቃየት ላይ ገኛሉ፡፡

የጋይሌ ስሚዝ የዩኤስኤአይዲ/USAID አስተዳዳሪ ሆነው መሾማቸው ለአፍሪካ ጥሩ ነውን? 

ቆሻሻ ለሆኑት ለሀብታም የአፍሪካ አምባገነኖች ጥሩ የሆነው ነገር ሁሉ ምንም ለሌላቸው እና በድህነት ውቅያኖስ ውስጥ በመዋኘት ላይ ለሚገኙት አፍሪካውያን ድሆችም ጥሩ ነገር ነውን?

የጀኔራል ሞተርስ ዋና ኃላፊ የነበሩት እና እ.ኤ.አ በ1953 የኢሰንሀወር ለመከላከያ ሚኒስትርነት የተጠቆሙት ቻርለስ ዊልሰን እንዲህ ብለው ነበር ተብሎ ይነገራል፣ “ለጀኔራል ሞተርስ ጥሩ የሆነው ነገር ሁሉ ለአሜሪካም ጥሩ ነገር ነው፡፡“ እ.ኤ.አ በ2009 ጄኔራል ሞተርስ በኪሳራ የተዘጋ መሆኑን አወጀ፡፡

ለአፍሪካ አምባገነኖች ጥሩ የሆነው ነገር ሁሉ ለአሜሪካ ጥሩ ነገር አይደለም፡፡ ለአፍሪካ አምባገነኖች ጥሩ የሆነው ነገር ሁሉ ለአፍሪካ እና ለአፍሪካውያን/ት በፍጹም ጥሩ ነገር ሊሆን አይችልም፡፡

በሞራል ስብዕና የከሰሩት የአፍሪካ አምባገነን መሪ ተብዬዎች አፍሪካን አክስረዋታል፣ እንደዚሁም ደግሞ የአፍሪካን የተፈጥሮ ሀብቶች ከህግ አግባብ ውጭ በመጠቀም እና ለግል ጥቅም በማዋል በሚሊዮኖች ዶላሮች የሚቆጠር ገንዘብ ህዝብ በረኃብ እና በችጋር እየተሰቃዬ እነርሱ በእራሳቸው ስም ለእራሳቸው የድሎት ህይወት በውጭ ባንኮች በማጨቅ ላይ ይገኛሉ፡፡ የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ የኢትዮጵያ ህዝብ ለምን ኬክ እንደማይበላ እየተደነቁ ባሉበት ሁኔታ የእትዮጵያ ህዝብ ግን በረሀብ አለንጋ በመጠበስ ላይ ይገኛል፡፡

ጋይሌ ስሚዝ የዩኤስኤአይዲ/USAID ቁንጮ ኃላፊ የመሆናቸው ዜና እንደተሰማ የአፍሪካ አምባገነን መሪ ተብዬዎች እጆቻቸውን ያሻሻሉ፣ እንዲሁም የአሜሪካንን ግብር ከፋይ ህዝብ ደም ሙልጭ አድርጎ ለመምጠጥ ለሀጮቻቸውን በጃኬቶቻቸው ላይ ያንጠባጥባሉ፡፡ ምራቆቻቸውን በማንጠባጠብ ጥንብ እንዳዬ ጅብ እያሽካኩ ያናፋሉ፡፡

ዩኤስኤአይዲ/USAID የሚባለው ድርጅት ለበርካታ ዓመታት የአፍሪካ አምባገነን መሪ ተብዬዎች የከረሜላ ማጀያ መጋዝን ሆኖ ቆይቷል፡፡

ጋይሌ ስሚዝ የዩኤስኤአይዲ/USAID ኃላፊ በሚሆኑበት ጊዜ ዩኤስኤአይዲ/USAID የአፍሪካ አምባገነን መሪ ተብዬዎች የቸኮሌት መጋዝን ይሆንላቸዋል፡፡

እ.ኤ.አ በ2016 ዩኤስኤአይዲ/USAID በመላው ዓለም የሚሰራጭ 22 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር ይኖረዋል፡፡ ከዚህ ግዙፍ ገንዘብ ውስጥ 25 በመቶ ወይም ከዚያ በላይ የሚሆነው የአፍሪካን አምባገነኖች ኪስ ለመሙላት ወደ አፍሪካ የሚመጣ ገንዘብ ነው፡፡

የጋይሌ ስሚዝ የድርጅቱ ኃላፊነት የመጽደቁ ጉዳይ አንድ ነገርን ይነግረናል፡ ይኸውም አንድ በጣም ትንሽ የሆነች የማትረባ ሆኖም ግን ለአፍሪካ ህዝብ በድህነት ማጥ ውስጥ መዘፈቅ አስተዋጽኦ የሚኖረው እና በሌላ መልኩ ደግሞ ለአፍሪካ አምባገነኖች አንድ ግዙፍ የሆነ የገንዘብ ማካበቻ ዕድል ሆኖ ይታያል፡፡

የስሚዝ ዩኤስኤአይዲ/USAID ኃላፊ የመሆናቸው ጉዳይ የመጨረሻው የማጽደቅ እርምጃ ይፋ ከሆነ በኋላ የአፍሪካ አምባገነን መሪ ተብዬዎች የቸበርቻቻ ዕለት እንደሚሆንላቸው ምንም ዓይነት ጥርጥር የለውም፡፡

የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ በአዲስ አበባ የዘራፊዎች ፌሽታ ይኖረዋል፡፡

ካጋሜ እና ግብረ አበሮቹ የዋቱሲን የእሽክርክሪት ዳንስ በኪጋሊ ያቀልጡታል፡፡

ሙሴቬኒ እና ወሮበላ አጫፋሪዎቹ የጃምቦሌን ሙዚቃ በመዘመር የእሽክርክሪት ዳንሳቸውን እያቀለጡ ሀብታሞች ነን! ሀብታሞች ነን! ሀብታሞች ነን! እያሉ ይቦርቃሉ፡፡

የአፍሪካ አምባገነኖች እንደገና አሸነፉ!

የስሚዝ ዩኤስኤአይዲ/USAID ኃላፊ መሆናቸው ከጸደቀበት ማግስት ጀምሮ የአፍሪካ አምባገነኖች ዋና መስሪያ ቤቱ ዋሽንግተን ከሚገኘው ዩኤስኤአይዲ/USAID ለእርዳታው እና ለምዕጽዋቱ ጉቦ በመስጠት ጋይሌ እያሉ ልመናቸውን ያጧጡፋሉ፡፡ 

የጋይሌ ስሚዝ የዩኤስኤአይዲ/USAID አስተዳዳሪ ሆነው መሾማቸው ለኢትዮጵያ ጥሩ ነውን?

ወደ ትክክለኛው እና ወደ እውነታ በመቅረብ ሲታሰብ ጋይሌ ስሚዝ እራሱን ህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ እያለ የሚጠራው የወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ቀንደኛ ደጋፊ እና አሁን በህይወት በሌለው በመለስ ዜናዊ የተመሰረተ እና በእርሱ እና የቅርጫ ምርጫውን እ.ኤ.አ ግንቦት 24/2015 መቶ በመቶ ባሸነፈው እና እ.ኤ.አ በ2010 ተደርጎ በነበረው የመለስ ፓርቲ የቅርጫ ምርጫም 99.6 በመቶ አሸንፎ በነበረው እራሱን ህወሀት እያለ በሚጠራው የማፊያ ድርጅት ቁጥጥር ስር በዋለው ማህበረ ረድኤት ትግራይ/Relief Society of Tigray (REST) እየተባለ የሚጠራው ህገወጥ የንግድ ድርጅት ተቀጣሪ ሰራተኛ በመሆን ዋና ደጋፊ ነበሩ፡፡

እ.ኤ.አ ግንቦት 1991 የክርስቲያን ሳይንስ ሞኒተር ዘገባ ስለእስሚዝ አጠቃላይ ሁኔታ እና ከህወሀት ጋር ስለነበራቸው ግንኙነት እንዲህ የሚል ዘገባ አቅርቦ ነበር፣ “የትግርኛ ቋንቋ ከሚናገሩት ጥቂት ምዕራባውያን መካከል አንዷ የሆኑት እና ከመለስ ዜናዊ ጋር ለ9 ዓመታት ያህል ግንኙነት የነበራቸው እና እ.ኤ.አ በ1985-6 ተከስቶ በነበረው ረሀብ ለማህበረ ረድኤት ትግራይ (ማረት)/REST ለተባለው ድርጅት ይሰሩ የነበሩት አሜሪካዊት ጋይሌ ስሚዝ ነበሩ፡፡“ (አጽንኦ ተጨምሯል፡፡)

ስሚዝ በጽናት የቆሙ የመለስ ዜናዊ ቀንደኛ ደጋፊ እና የመለስ ዜናዊ የተንሻፈፉ እና የተንሸዋረሩ ፖሊሲዎች ጠጋኝ እና ተሟጋች ነበሩ፡፡ ስሚዝ አሁን በህይወት የሌለውን የመለስን የማርክሲስት ፍልስፍና ጎጂ እንዳልሆነ አድርገው ሰብአዊነት ያለው አስመስለው ለማቅረብ ጥረት ያደርጉ ነበር፡፡ እንዲህ ብለውም ይናገሩ ነበር፣ “በርካታዎቹ የዜናዊ ግራ ዘመም መግለጫዎች ግራ ዘመም ከሆነ የሽምቅ ውጊያ ከሚያካሂድ ድርጅት ሊነገር የሚችል ቋንቋ ነው፡፡“

ስሚዝ ዜናዊን ምክንያታዊ የሆነ የሊበራል ዲሞክራት እንደሆነ እና የሀገሪቱን በርካታ ብሄረሰቦች ፍላጎት ለማሳካት እንዲቻል ሰፊ መሰረት ያለው ጥምረት አስፈላጊ መሆኑን አስቀድሞ የተገነዘበ በማለት የሌለውን ይዘት ቀለም ለመቀባት ጥረት ያደርጉ ነበር፡፡

ወዲያውኑ መለስ ስልጣን እንደያዘ የእራሱን ታዛዥ ሎሌ የሆኑትን ጥምረቶች በማዘጋጀት የኢትየጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ)/Ethiopian Peooples Revolutionary Democratic Front (EPRDF) በሚል ስያሜ እንዲጠራ አደረገ፡፡ የዓሳማን ፉንጋ ለማቆንጀት ሲባል የከንፈር ቀለም መቀባት ይቻላል፣ ሆኖም ግን በዕለቱ መጨረሻ ያው የዓሳማ ፉንጋ ከመሆን የሚያግዳት ነገር አይኖርም፡፡ እንደዚሁም ሁሉ ኢህአዴግን/EPRDFን እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት ለማስመሰል ሲባል ቀለም በመቀባባት የኢትዮጵያን ህዝቦች የሚወክል ግንባር ነው ማለት ይቻላል፡፡ ሆኖም ግን በዕለቱ መጨረሻ ኢህአዴግን/EPRDF ብለው ቢሰይሙት ሌላ ማንንም ሳይሆን ህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ (ህወሀት)/Tigrian People Liberation Front (TPLF) የተባለውን ፈላጭ ቆራጭ አምባገነን ድርጅት ሆኖ ይገኛል፡፡ በአንድ ወቅት አሁን በህይወት የሌለው መለስ ዜናዊ የኦሮሞ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦህዴድ)/Oromo People Democratic Organization (OPDO) እያለ የሚጠራውን ከአራቱ ተለጣፊ ድርጅቶች አንዱ እና ወደ ኦሮሞው ህዝብ መግቢያ የሆነውን የቋንቋ አስተርጓሚውን ስብዕና የለሽ ድርጅት መሪ ተብዬዎች እና ካድሬዎች ሰብስቦ ዲስኩር በሚያሰማበት ወቀት አሁን ልባችሁ እንደ ፈጣን ሎተሪ ቢፋቅ የኦሮሞ ነጻ አውጭ ግንባር (ኦነግ)/Oromo Liberation Front (OLF) አባላት ሆናችሁ ትገኛላችሁ ያለው ከዚህ እውነታ በመነሳት ሳይሆን ይቀራል ትላላችሁ!

መለስ መሰረተ ሰፊ ለሆነ ግንባር እና አስተዳደር ምን ያህል ጠንካራ ሆኖ እየሰራ እንዳለ ለማስመሰል ያህል ቀለሞችን እየቀባባ በተግባር ግን ከረዥም ጊዜ ጀምሮ ኢትዮጵያን ለመበታተን እና ክልሎች እያለ የሚጠራቸውን የተለያዩ ግዛቶች በመተግበር አልሞት የነበረውን ህልሙን እውን አድርጓል፡፡

በመጨረሻም ጋይሌ ስሚዝ ቀንደኛ ደጋፊ መሆናቸውን በተግባር አስመስክረዋል!

እ.ኤ.አ በ2005 የተካሄደውን የቅርጫ ምርጫ ተከትሎ ከምርጫ ድምጽ ዘረፋው ጋር ተያይዞ በተነሳው ውዝግብ መለስ ዜናዊ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰላማዊ አመጸኞችን ለፖሊስ እና ለጦር ኃይሉ ትዕዛዝ በመስጠት በጥይት በማስደብደብ እንዲያልቁ በማድረግ እውነተኛ ማንነቱን በተግባር አስመስክሯል፡፡ ሁልጊዜ አንባቢዎቼን ለማሳሰብ እንደምሞክረው ሁሉ መለስ በወገኖቻችን ላይ የፈጸመውን እልቂት በመመልከት በአንዲት ባለእጅ መደገፊያ ወንበር ላይ ተቀምጦ የአካዳሚ ስራን ከሚሰራ እና ከህግ ጥብቅና ሙያ ከሚያከናውን ባለሙያነት በተጨማሪ በወገኖቼ ላይ የሚፈጸመውን ዘግናኝ ግፍ እና በደል በመመልከት ሳላወላውል ወዲያውኑ ወደ ኢትዮጵያ እና የአፍሪካ የሰብአዊ መብት ተሟጋችነት ሙያ በንዴት ዘው ብዬ እንድገባ አደረገኝ፡፡

መለስ ዜናዊ ማዳም ስሚዝ እንደሚሉት የግራ ዘመም ዋና አቀንቃኝ አልነበረም፣ ሆኖም አያውቅም፡፡ ከዚህ ይልቅ ርህራሄ የለሽ ጨካኝ፣ የለየለት አጭበርባሪ እና ጠቀሜታውን ያጠናቀቀ መኪና እንደሚሸጥ ደላላ እና እስታሊናዊ ወሮበላነት እርሱንነቱን ለስሚዝ ደብቆ ሲያታልላቸው ቆይቷል፡፡

እ.ኤ.አ ግንቦት 1990 መለስ ዜናዊ እና የእርሱ ወሮበላ ድርጅት ህወሀት የኢትዮጵያ መናገሻ ከተማ ወደሆነችው አዲስ አበባ ሲገቡ የቀድሞዋ የማረት/REST ሰራተኛ የነበሩት ስሚዝ በዚያን ጊዜ ኢትየጵያን ሲገዛ በነበረው የወታደራዊ አምባገነን መንግስት ላይ ጥብቅ የሆነ ማዕቀብ እንዲጣል የተማጽኖ ልመና አቅርበው ነበር፡፡

ስሚዝ በዩኤስ ምክር ቤት አባላት ፊት በመቅረብ የምስክርነት ቃላቸውን እንዲህ የሚል የክርክር ጭብጥ አቅርበው ነበር፣ “በመንግስቱ አገዛዝ ላይ ቀጣይነት ያለው ተጽዕኖ በማሳደር መጠነ ሰፊ በሆነ መልኩ የህወሀት/TPLF እና የኤርትራ ነጻ አውጭ ግንባር/EPLF የሆነው ድርጀት በጋራ የኢትዮጵያን ድንበር እየተሻገሩ ይዞታቸውን እንዲያስፋፉፉ እና እነዚህ ድርጅቶች እገዛ እንዲደረግላቸው“ የሚል ምክረ ሀሳብ ይሰጡ ነበር፡፡

በተለይ እንዲህ የሚል ምክረ ሀሳብ አቅርበው ነበር፣ “የድንበር አቋራጩ እርዳታ በተለይ የምግብ እርዳታን ብቻ የሚያካትት መሆን የለበትም፣ ሆኖም ግን ከዚህም ባለፈ ሁኔታ የተሸከርካሪ፣ የመለዋወጫ ዕቃ፣ የነዳጅ፣ የመጋዝን፣ የህክምና እና ሌሎች የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታዎች እና አስተዳደራዊ ወጭዎችም መካተት አለባቸው፡፡“ ከዚህም በተጨማሪ ለዩኤስ መንግስት እ.ኤ.አ ከየካቲት 8/1990 በኋላ እርዳታው በመጀመሪያበምጽዋ ወደብ እንዲቀርብ ስምምነት ተደርጎ የነበረው እንዲቀር እና በሱዳን ወደብ/Port Sudan በኩል እንዲቀርቡ ከፖርት ሱዳን ጋር ሌላ ስምምነት እንዲደረግ የሚል ምክረ ሀሳብ አመንጭተው ነበር፡፡ (አጽንኦ ተጭምሯል፡፡)

ቀደም ሲል በመካከለኛው ምስራቅ አድርገውት በነበረው የምርምር እና የመረጃ ፕሮጀክት/Research and Information Project ትንተና ስሚዝ የማረት/REST ቅጥር ሰራተኛ ከመሆናቸው በፊት እ.ኤ.አ በ1984 የመጨረሻዎቹ ወራት ረሀብ በትግራይ ክፍለ ሀገር በአስከፊነት ሁኔታ በተከሰተበት ወቅት ሁለተኛው እና ሶስተኛው የእርዳታ ምግብ እደላ ፕሮግራሙ ሁለቱም በአንድ ላይ በፖርት ሱዳን በኩል በምስራቃዊ ሱዳን ወሰን አካባቢ ወዳሉት የኤርትራ እና የትግራይ አካባቢዎች እየገባ ተግባራዊ ይደረግ እንደነበር ግልጽ አድርገዋል፡፡ ይህ የእርዳታ ፕሮግራም በኤርትራ የእርዳታ ማህበር (ኤእማ)/Eritrean Relief Association (ERA) እና በማህበረ ረድኤት ትግራይ (ማረት)/Relief Society of Tigray (REST) አማካይነት እንደየአግባባቸው ተግባራዊ ይደረግ ነበር፡፡

በጣም አስገራሚው እውነታ ግን በፖርት ሱዳን በመግባት ወደ ተረጅው የህብረተሰብ ክፍል መድረስ የነበረበት ምግብ፣ የማጓጓዣ ተሽከርካሪዎች፣ የመለዋወጫ ዕቃዎች፣ የማከማቻ መጋዝኖች፣ የህክምና እና ሌሎች የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታዎች ሁሉ የመለስ ዜናዊን የህዝባዊ ወያኔን ሀርነት ትግራይ የማፍያ ወሮበላ የዘራፊ ድርጅትን አማጺ ቡድን እንዲደግፍ ይደረግ ነበር፡፡

መለስ ዜናዊ እና የእርሱ ማረት የተባለው ድርጅት እ.ኤ.አ በ1984-85 ከእርዳታ ሰጭ ድርጅቶች ያገኙትን እርዳታ አስደንጋጭ በሆነ መልኩ የስርቆት ድርጊት በመፈጸም ለሰብአዊ እርዳታ በሚል ህይወትን ለማዳን የመጣውን እርዳታ ከዓላማው ውጭ በማዞር የመለስ ዜናዊን አማጺ ኃይሎች መመገብን ጨምሮ ለወታደራዊ ጉዳይ እንዲውል አድርገዋል፡፡

የዚያን ጊዜ የዘረፋ እና የመጣውን እርዳታ ከታቀደለት ዓላማ ውጭ መዋሉን በማስመልከት እ.ኤ.አ ህዳር 2014 “ህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ ለመዝረፍ ፈቃድ የተሰጠው ድርጅት“ በሚል ርዕስ ትችት አቅርቤ የነበረ መሆኑ የሚታወስ ነው፡፡

በአንድ ወቅት የህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ መስራች እና አባል እንዲሁም የመለስ ዜናዊ ጓደኛ በነበሩት በዶ/ር አረጋዊ በርሄ አሳማኝ የሆነ ማስረጃ ተሰጥቷል፡፡

በዚያን ጊዜ በረሀብ ለተጎዳው ህዝብ ተብሎ የመጣውን እርዳታ መለስ እና ህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ በጣም ውስብስብ በሆነ መልኩ ዝርፊያ የፈጸሙ መሆናቸውን በማስመልከት የቢቢሲ ጋዜጠኛ በሆኑት በማርቲን ፕላውት ቀርቦለቸው ለነበረው ቃለ መጠይቅ ዶ/ር አረጋዊ በርሄ እንዲህ በማለት ግልጽ አድርገዋል፡

…አንዳንድ ጊዜ ለእርዳታ ከመጣው ገንዘብ የጦር መሳሪያ እንገዛበት ነበር፡፡ ወደ መካከለኛው ምስራቅ ሀገሮች በምትመጣበት ጊዜ ገንዘቡ ካለህ የጦር መሳሪያ ልትገዛ ትችላለህ፡፡ ስለሆነም በእርዳታ ካገኘነው ጥቂት ገንዘብ ውስጥ የጦር መሳሪያ እንገዛ ነበር፡፡ ማህበረ ረድኤት ትግራይ እየተባለ የሚጠራውን ድርጅት ታውቁታላችሁ፡፡ ይህ ድርጀት የህወሀት የሰብአዊ እርዳታ ክንፍ ነበር፣ እናም በማረት አማካይነት የእርዳታ ገንዘብ ለህወሀት ይቀርብ ነበር፡፡ ስለሆነም ይህንን የገንዘብ እርዳታ በምታገኝበት ጊዜ በጀቱን በግንባር ላሉ አማጺዎች እርዳታ፣ ወይም ደግሞ ለጦር መሳሪያ ግዥ፣ ለህክምና እና ለመሳሰሉት ልታውለው ትችላለሀ፡፡ ትግሉን ቀጣይነት እንዲኖረው ለማድረግ በእርዳታ በሚገኘው ገንዘብ ላይ እንመካ እንደነበር ለመግለጽ እወዳለሁ፡፡

በሚሊዮን ስለሚቆጠሩ ዶላሮች ነው እያወራን ያለነው፡፡ ተጨባጭነት ያለው ምሳሌ ልጠቅስልህ እችላለሁ፡፡ እ.ኤ.አ በ1985 ትግራይ አስከፊ በሆነ ድርቅ በተጠቃችበት ጊዜ የእርዳታ ገንዘብ በማረት አማካይነት ለህወሀት ይደርሰው ነበር፡፡ ስለሆነም የትግራይ ማርክሲስት ሌኒኒስት ሊግ እና የህወሀት አመራሮች በየትኛውም መልኩ አንድ አይነት የሆኑ ድርጅቶች መቶ ሚሊዮን በሚሆነው የአሜሪካ ዶላር እርዳታ ላይ የበጀት ዕቅድ አውጥተው ነበር፡፡ አስታውሳለሁ መለስ ዜናዊ 50 በመቶ የሚሆነው ለህወሀት እንቅስቃሴዎች ማስፈጸሚያ፣ 45 በመቶ የሚሆነው ለትግራይ ማርክሲስት ሌኒኒስት ሊግ፣ 5 በመቶ የሚሆነው ደግሞ ለረሀብ ሰለባ ለሆነው ህዝብ እንዲመደብ የሚል ሀሳብ አቅርቦ ነበር… (አጽንኦ ተጨምሯል፡፡)

እ.ኤ.አ ጥቅምት 2012 በኒዮርክ ከተማ በአንድ ቤተክርስቲያን ቅጥር ግቢ ውስጥ ለመለስ ሙት ዓመት መታሰቢያ ተዘጋጅቶ በነበረው ስነስርዓት ላይ በመገኘት ስሚዝ መለስ ሊታሰብ ከሚችለው በላይ ሁሉን ነገር ለማወቅ ፈጣን አእምሮ የነበረው ሰው ነበር በማለት የማይገባውን ከንቱ ሙገሳ በመስጠት በዶ ዲስኩራቸውን አሰምተው ነበር፡፡

ስሚዝ መለስን የኢትዮጵያ አዳኝ አድርገው ይክቡት ነበር፡፡ መለስ ለኢትዮጵያ ልማትን እና እድገትን ያመጣ ሰው ነበር ብለዋል፡፡ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ረኃብን ያቆመ ሰው ነው በማለት ተራ ቅጥፈትን አራምደዋል፡፡ እንደዚሁም ደግሞ ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ የመለስ ገጽታ ነጸብራቅ ናት ብለዋል ስሚዝ፡፡

በአጭሩ ስሚዝ መለስ ለኢትዮጵያ ለሁለተኛ ጊዜ መምጣት ያለበት ሰው ነው ብለዋል፡፡

ስሚዝ በአምባገነኑ መለስ ጭራቃዊ አመራር በኢትዮጵያ በኦጋዴን አካባቢ፣ በምዕራብ ኢትዮጵያ በጋምቤላ፣ በሶማሊያ በሶስት ዓመታት የሶማሊያ የወረራ ጦርነት ጊዜ እና እ.ኤ.አ የ2005 ሀገራዊ ምርጫን ተከትሎ ተከስቶ ስለነበረው እልቂት አንዲትም ቃል ትንፍሽ የማለት ደፍረቱ አልነበራቸውም፡፡ ለምን ቢባል ውሻ በበላበት ቤት ይጮሀል ከማለት በስተቀር ሌላ የምለው ነገር የለኝም፡፡

ስሚዝ መለስ የጸረ ሽብር አዋጅ እያለ ይጠራው ስለነበረው እና ይቃወሙኛል በማለት የሚጠረጥራቸውን ሰዎች ለማጥቂያነት ከመጠቀም ውጭ ለሌላ ለምንም ስለማይውለው አፋኝ ህግ አስቀያሚነት አንዲት ቃል እንኳ ትንፍሽ ማለት አልፈለጉም፡፡ መለስ ነጻውን ፕሬስ ለማፈን እና ለመዝጋት ስላዘጋጀው አፋኝ እና ቀያጅ ህግ አንዲትም ቃል ትንፍሽ ማለት አልፈለጉም፡፡

ጋይሌ ስሚዝ መለስ በሰው ልጆች ላይ የፈጸመውን ሰብአዊ ወንጀል መልጭ አድርገው በመካድ አታላይ የሆኑ ተራ እና የቅጥፈት ሙገሳዎችን በመደርደር የሰራውን ተቆጥሮ የማያልቅ ኃጢያት ለማንጻት እና ለመደበቅ ሙከራ አድርገዋል፡፡

ሸክስፒር በማክቤዝ ላይ እንዲህ የሚል ጽሁፍ አስፍረው ነበር፡ በአንድ ወቅት በምላሳችን ላይ ቆጥቋጭ ቁስል ያስቀምጥ የነበረ ይህ አምባገነን በሌላ ጊዜ ታማኝ ሰው የነበረ ነው፡፡ እርሱን በሚገባ ትወዱታላችሁ፡፡

ጓድ ጋይሌ ስሚዝ በአሁኑ ጊዜ በህይወት የሌለውን እና በምላሳችን ላይ ቁስል አስቀምጦ የሄደውን አምባገነኑን ጓድ መለስ ዜናዊን ወድደውት ነበር፡፡

የጋይሌ ስሚዝ በቃ” ፕሮጀክት፣

ጋይሌ ስሚዝ በቃ እየተባለ የሚጠራ የድረ ገጽ ፕሮጀክት በማራመድ ላይ ይገኛሉ፡፡

በሩዋንዳ ከ800 ሺህ በላይ ንጹሀን ዜጎች ላለቁበት እና በአሁኑ ጊዜ በአፍሪካ አስደንጋጭ በሆነ መልኩ እልቂት እየተፈጸመ ስላለበት ሁኔታ የዓለም ህዝብ ምንም ዓይነት ምላሽ ባለመስጠቱ ምክንያት በሞራል ዝቅጠት ውስጥ ያለ መሆኑን ለመግለጽ ዓላማ ያደረገ ፕሮጀክት ነው፡፡

ሊታመን በማይችል መልኩ በቃ ፕሮጀክት በእነዚህ ሀገሮች ላይ በድርጊት እና በተጠያቂነት ነገሮች ላይ አስቸኳይ እና የመጨረሻ ለውጥ ለማምጣት ተብሎ የታቀደ ዓላማ ነው፡፡ ጉድ ነው ተጠያቂነት?! ይኸ ነገር የዶሮዎችን ማደሪያ ቤት ቀበሮ እንዲጠብቀው በአደራ መልክ ከመስጠት ድርጊት ጋር መሳ ለመሳ ነው፡፡ ወይ ተጠያቂነት!

ለምንድን ነው በሩዋንዳ በግፍ ከ800 ሺህ በላይ በዘር ማጥፋት ወንጀል ስለተጨፈጨፉት ንጹሀን ዜጎች ተጠያቂነት የማይኖረው?

ጋይሌ ስሚዝ የአዞ እንባ በማንባት ላይ ይገኛሉ፡፡

የመጨረሻው እና አስገራሚው ነገር በክሊንተን አስተዳደር ጊዜ ሲሰሩ በነበሩበት ጊዜ እ.ኤ.አ በ1994 በሩዋንዳ ንጹሀን ዜጎች ላይ ለመናገር በሚዘገንን መልኩ ስለተፈጸመው የዘር ማጥፋት ወንጀል ምንም ነገር የማያውቁ በመምሰል የተቀመጡት እና በአሁኑ ጊዜ የኦባማ የብሄራዊ ደህንነት አማካሪ እና የጋይሌ ስሚዝ አለቃ የሆኑት ሱሳን ራይስ በማስመሰል ስብዕናቸውን ሸጠው የተቀመጡ ሰው ናቸው፡፡

በዚያን ወቅት ራይስ በኋይት ሀውስ በብሄራዊ ደህንነቱ ምክር ቤት ገና ወጣት ዳይሬክተር እንደመሆናቸው መጠን የሩዋንዳን እልቂት ለማስቆም ምንም ዓይነት ፈጣን እርምጃ ባለመውሰዳቸው ለጉዳዩ ምንም ዓይነት ትኩረት እንዳልተሰጠው ማረጋገጫ ነው፡፡ ከዚህ ይልቅ ሱሳን የሩዋንዳን የዘር እልቂት ፍጅት በፖለቲካው ላይ ሊያስከትል የሚችለውን እንደምታ በመውሰድ የዘር እልቂት ተብሎ በመጠራቱ ላይ በመበሳጨት ያዙኝ ልቀቁኝ ይሉ ነበር፡፡

የሞራል ኪሳራን ለመሸፋፈን እና እልቂቱ በመፈጸሙ ምክንያት ለህሊናቸው ተገዥ ሳይሆኑ ዝም ብለው ለሚመለከቱት ጓደኞቻቸው ራይስ እንዲህ የሚል መልዕክት አስተላልፈው ነበር፣ “እ.ኤ.አ ሚያዝያ 1994 በሩዋንዳ ስለተፈጸመው ግድያ ዘር ማጥፋት የሚለውን ቃል የምንጠቀም ከሆነ እና ለዚያም ምንም ዓይነት ምላሽ ሳንሰጥ የቆየን ከሆነ በህዳር የሚካሄደው ምክር ቤታዊ ምርጫ ውጤቱ ምን ሊሆን ይችላል?“

ራይስ በኋላ ትረጉምየለሽ መግለጫ መስጠታቸውን በማስታወስ የአዞ እንባ እንዳነቡ እና ያንን ድርጊት መፈጸማቸውንም በፍጹም ማስታወስ እንደማይችሉ ግልጽ አድርገው ነበር፡፡

በአሩሻ የሰላም አስከባሪ ጓድ የዩኤስ ወታደራዊ ኃይል ዋና አዛዥ የነበሩት ሌተናል ኮሎኔል ቶኒ ማርሌይ (እ.ኤ.አ በ1993 በሩዋንዳ ለሁቱ እና ለቱትሲ ስልጣንን ለማጋራት በአሩሻ የሰላም ጉባኤ ላይ ተደርጎ የነበረ ስምምነት) የሱሳን ራይስን ንግግር ካደመጡ በኋላ ንግግራቸው እንቆቅልሽ እና በቀላሉ የማይገባ መሆኑን እንዲህ በማለት ተናግረው ነበር፣ “በሁኔታው ህዝብ ይደነቃል ብለን እናምናለን፣ ሆኖም ግን በእርግጠኝነት ድምጻቸውን ይሰጣሉ፡፡“

“ሱሳን ራይስ እና የአፍሪካ ያልተባረከው ቅድስና“ በሚል ርዕስ ባቀረብኩት ትችቴ ላይ ሱሳን ራይስ በሩዋንዳ ንጹሀን ዜጎች ላይ የዘር ማጥፋት ወንወጀል ሲፈጸም ምንም ዓይነት እርምጃ ሳይወስዱ መቅረታቸውን በማስመልከት እና የሞራል ኪሳራ እንዳለባቸው በማስረገጥ ሰፊ ትንታኔን ያካተተ ትችት አቅርቤ ነበር፡፡

በዚያን ወቅት በዩናይትድ ስቴትስ ፈጣን የሆነ የህይወት ማዳን እርምጃ ቢወሰድ ኖሮ በርካታ ንጹሀን ዜጎች ከዘር እልቂት ፍጅቱ ይድኑ ነበር፡፡ ያ የዘር ማጥፋት ወንጀል ከተፈጸመ ከሁለት አስርት ዓመታት በኋላ ፕሬዚዳንት ቢል ክሊንተን እንዲህ ብለው ነበር፣ “በዚያን ጊዜ በደረሰው እልቂት በወቅቱ ወዲያውኑ ብንደርስላቸው ኖሮ ያጣናቸውን ንጹሀን ዜጎች ቢያንስ አንድ ሶስተኛ የሚሆኑትን ዜጎች ህይወት ማትረፍ እንችል ነበር… ለእኔ በጣም ዘግናኝ የሆነ ስሜት ጥሎብኝ አልፏል፡፡“

ወዲያውኑ!!!

አስገራሚው እውነታ ግን ከ100 ባነሱ ቀናት ውስጥ የዓለም ህዝብ ዓይኑን በሰፊው ከፍቶ እየተመለከተ 800 ሺህ የሚሆኑ የሩዋንዳ ዜጎች እንዲያልቁ ተደርገዋል፡፡

የዘር ማጥፋት እልቂቱ እየተካሄደ ባለበት በሳምንታት ጊዜ ውስጥ ራይስ፣ የእርሳቸው አለቃ የነበሩት አንቶኔ ሌክ እና ሌሎች ቱባ ቱባ ቁንጮ የዩናይትድ ስቴትስ ባለስልጣኖች አሰቃቂውን እና የንጹሀን ዜጎችን ህይወት የቀጠፈውን ያንን የመሰለ አሰቃቂ እና አስከፊ የዘር ማጥፋት ወንጀል ዘር ማጥፋት ብለው ለመጥራት ወኔው አልነበራቸውም፡፡ የተለመደውን የቢሮክራሲ የማደናገሪያ ዥዋዥዌ ጨዋታ ስልታቸውን ነበር መጠቀም የጀመሩት፡፡ ከሩዋንዳ እልቂት ጋር በተያያዘ መልኩ የዘር ማጥፋት ወንጀል የሚባል ነገር እንደሌለ እና እልቂቱ ከዘር ማጥፋት ወንጀል ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት እንደሌለው ለማስመሰል የተቻላቸውን ጥረት ሁሉ አድርገው ነበር፡፡

ሆን ብለው የሩዋንዳን የዘር ማጥፋት እልቂት እና ጅምላ የሰብአዊ መበት ድፍጠጣን ጉዳይ አሳንሰው በማቅረብ እና ትኩረት እንዳይሰጠው በማድረግ ሱሳን ራይስ በሩዋንዳ የዘር ማጥፋት ፍጅት የመጸጸት ስሜት ካለማሳየታቸውም በላይ ባለፉት አስር ዓመታት ጊዜ ውስጥ በአፍሪካ ሲደረጉ ለቆዩት ከህግ አግባብ ውጭ ግድያዎች፣ ነጻውን ፕሬስ የማፈን ጭቆናዎች፣ የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችን እና አባላት ላይ የሚካሄደውን ግድያ እና በገፍ የሚቆጠሩ ነጻ ሰላማዊ የአፍሪካ አመጸኞች እየተጋዙ ወደ እስር ቤት እየተወረወሩ ያሉበትን ሁኔታ እየተመለከቱ እንዲሁም ዩናይትድ ስቴትስ ጨካኝ አምባገነን ለሆኑ ወሮበላ የዘራፊ መሪ ተብዬዎች ማለትም ለካጋሜ፣ ለዮሪ ሙሴቬኒ እና አሁን በህይወት ለሌለው ለመለስ ዜናዊ የእርዳታ ዶላር ሲጎርፍ አይተው እንዳላዩ፣ ሰምተው እንዳልሰሙ እና ምንም ዓይነት ቃል ትንፍሽ ሳይሉ አልፈውታል፡፡ ሱሳን ራይስ ለእነዚህ አረመኔ እና ጨካኝ አምባገነን መሪ ተብዬዎች ተከላካይ ጠበቃ በመሆን፣ በምቾት እንዲሞላቀቁ በማድረግ እና በድርጊቶቻቸው እንዲቀጥሉ በማድረግ እና በመንከባከብ የማይገባ መዝሙር እና ሙገሳ ይደረግላቸዋል፡፡    

የጋይሌ ስሚዝ ድረ ገጽ እንዲህ በማለት አውጇል፣

በሱዳን፣ በቻድ፣ በኮንጎ ዴሞክራቲክ ሬፐብሊክ፣ በሰሜን ኡጋንዳ እና በአፍሪካ ቀንድ የሲቪል ማህበረሰቦች እየተስፋፋ ለመጣ የሰብአዊ መብት ረገጣ ወንጀሎች ሰለባ ሆነዋል፡፡ ይህ የተንሰራፋ ሰው ሰራሽ የእልቂት እና የማሰቃየት ችግር እጅግ በጣም ፈጣን እና ጠንካራ የሆነ ምላሽን ይፈልጋል፡፡ ሆኖም ግን በዓለም ላይ ካሉ መሪዎቻችን በሚሰጠው አናሳ ትኩረት ምክንያት እነዚህ አስፈሪ ገጽታዎች እንዲቀጥሉ ፈቃድ ሰጥተዋል፡፡

ፕራይ እንዲህ በማለት ይናገራሉ፣ “በአፍሪካ ቀንድ በሰው ልጆች ላይ ለሚፈጸሙት ወንጀሎች በስልጣን ላይ ያሉ እና በተናጠል ተጠያቂ የሚሆኑት ሰዎች እነማን ናቸው?“

በኢትዮጵያ በኦጋዴን አካባቢ፣ በምዕራብ ኢትዮጵያ በጋምቤላ፣ እ.ኤ.አ በ2005 ተካሄደ የተባለውን የቅርጫ ምርጫ ተከትሎ ተከስቶ በነበረው ውዝግብ በጠራራ ጸሐይ በአደባባይ ግንባራቸውን እና ደረታቸውን እያነጣጠሩ በጥይት በመንገድ ላይ እንዲደበደቡ ለተደረጉት ምንም ዓይነት መሳሪያ ያልታጠቁ ነጻ ዜጎች የትኛው ግለሰብ ወይም ደግሞ የትኛው ድርጅት ነው ጥቃቱን የፈጸመው?

ጋይሌ ስሚዝ ይህንን ጥያቄ እንዲመልሱ እንፍቀድላቸው፣

ጋይሌ ስሚዝ በአሁኑ ጊዜ በነጭ ፈረስ ላይ ተፈናጥጠው በቃ የሚለውን አዋጅ አውጀዋል፡፡ እኔ በበኩሌ ደግሞ የአዞ እንባ ማንባቱ በእራሱ በቃ ሊባል ይገባል እላለሁ! ጋይሌ ስሚዝ እባክዎትን በቃ!

የጋይሌ ስሚዝ ተከላካይ እና ተከታይ እረዳት እየመጣ ነው፡፡

እ.ኤ.አ ሰኔ 15/2015 በቦስተን ሪቪው አሌክስ ዲ ዋል የተባሉ ሰው ለስሚዝ ጠበቃ በመሆን ተናግረው ለነበረው ቅጥፈት ሙገሳ በመስጠት የስሚዝን የፍቅር ታሪክ እና በአፍሪካ ስለከፈሉት መስዋዕትነት ጥሩንባ በመንፋት ግልጽ ደብዳቤ ጽፈዋል፡፡

ዲ ዋል ግልጽ የሆነ ደብዳቢያቸውን ግልጽ በሆነ መልኩ እንዲህ በማለት አቅርበዋል፣

ለሰላሳ ዓመታት ያህል እርስ በእርሳችን እንተዋወቃለን፣ እናም በአፍሪካ ስላለው ጦርነት እና ረሀብ በአንድ ዓይነት ልምድ የተሳሳርን ነን፡፡ ለአፍሪካ ህዝቦች በተለይም ለአፍሪካ ቀንድ እና ለታላላቅ ሐይቆች ህዝቦች በሚፈልጓቸው ነገሮች ላይ ትኩረት በመስጠት ተመሳሳይነት ያለው ልምድ እና ጥረት አድርገናል፡፡ በአሁኑ ጊዜ የዩኤስአይዲ/USAID አስተዳዳሪ ለመሆን በመታጨትዎ የተሰማኝን ደስታ በመግለጽ ጥቂት ሀሳቦችን እንድወረውር ይፍቀዱልኝ፡፡

ወይ ነዶ!

የወፍ ምስክሯ ድንቢጥ አይደል ነገሩ፡፡ አንድ ዓይነት ላባ ያላቸው ወፎች በአንድ ላይ ይበራሉ ነው ነገሩ፡፡

እራሳችንን ትክክለኛ እና ፍጹም አድርገን በመሰየም በአሁኑ ጊዜ ታላቅ ፍላጎት ባለበት ዘመን ሀሳዊ መሲህ ሆነን እንዳንቀርብ የማይሳነው አምላክ ይጠብቀን!

ኢትዮጵያውያን እራሱን በሰየመ እና ርካሽ ጥቅም ለማግኘት ሲል የሌለውን ስብዕና እንዳለው አድርጎ ለህወሀት ሰዎች የሚጽፍን ግብዝ ሰው የወያኔን ባህሪ የሚያውቅ ማንኛውም ሰው የመለስ ደጋፊ እና እርሱን መላዕክ አስመስሎ የመጻፍ ሁኔታ ሲታሰብ የዲ ዋል ጽሑፍ ይታወሳል፡፡ የዲ ዋል የመለስ ዜናዊን ሙገሳ እና መላዕክ አስመስሎ የመጻፍ ሁኔታ ከዚህ በታች እንደሚከተለው ተጽፎ ይገኛል፡፡

መለስን በመካቡ ረገድ ዲ ዋል በኒዮርክ ታይምስ መጽሔት ላይ መለስ እኩል ከሆኑ ሰዎች የመጀመሪያው የሆነ ጓድ እና የምሁራዊነት ኃይልን የተላበሰ ሰው ነው ይላሉ፡፡

ዲ ዋል መለስን ያመልኩት ነበር፣ እናም መለስ በሚናገራቸው ቃላት እና ሀረጎች ይደነቁ እና ይገረሙ ነበር:: ከዚህም በተጨማሪ ሰውዬው የመለስን ንግግሮች ጫፍ በመያዝ እያሰማመሩ በማቅረብ በተጨባጭ ሳይሆን ሆን ብለው አጉል ሙገሳ በመስጠት መለስ የምሁርነት ኃይልን የተላበሰ እያስመሰሉ ያቀርቡ ነበር፡፡

ዲ ዋል እንዲህ በማለት ጽፈው ነበር፣ “ምሁራዊነትን የመላበስ ባህሪ መለስን ለበርካታ ዓመታት በቢሮ ውስጥ እንዲቀመጥ ያደረገው ነገር ነው…መለስ ኢትዮጵያውያን በቀን ሶስት ጊዜ መመገብ የሚችሉ ከሆነ እርሱ የሚመራው መንግስት ስኬታማነቱ የሚለካው በዚህ እንደሆነ ተናግሮ ነበር፡፡ የመለስ ሁሉም ብሄራዊ ፖሊሲዎቹ የሀገሪቱን ድህነት በማጥፋት ረገድ የተቃኙ ነበሩ፡፡“ (አጽንኦ ተጨምሯል፡፡)

መለስ ለእርሱ ምሁራዊ አስመሳይነት አበርትቶ ሲታገል የነበረ የፓሊስታይን የእግር መንገደኛ ነበር፡፡ መለስ በሰይጣናዊ የማታለል ስራው የምዕራቡን ዓለም ለጋሽ እና አበዳሪ ደርጅቶችን እንዲሁም የእርሱን ምሁራዊነት እየሰበኩ የሚኖሩ አሽከሮቹን እያታለለ እራሱን የሁሉም ነገር አዋቂ ምሁር አድርጎ ይኖር ነበር፡፡ ፍጹም የሆነው እውነታ ግን መለስ የለየለት የጥላቻ አራጋቢ ሰይጣዊ ባህሪን የተላበሰ እኩይ ፍጡር ነበር፡፡ ሌላ የሚጨመርም ሆነ የሚቀነስ ነገር የለም፡፡ የእርሱን ምሁራዊነት ወደዚያ!

ዲ ዋል  የመለስ ብሄራዊ ፖሊሲዎቹ ድህነትን ከማጥፋት ጋር የተቃኙ ነበሩ ይላሉ፡፡ ይኸ የለየለት ቅጥፈት ነው!

የመለስ ብሄራዊ ፖሊሲ የመጀመሪያው እና ዋናው አጀንዳ የሀገሪቱን ዋና ግምጃ ቤት በመዝረፍ የእርሱን እና የግብረ አበር አሽከሮቹን ኪስ በገንዘብ መሙላት ነበር፡፡

ከሁለት አስርት ዓመታት በኋላ የኢትዮጵያን ማንነት እና ዜግነት ለማጥፋት ሌት ከቀን ሲሰራ የነበረ የጥፋት መልዕክተኛ እና የኢትዮጵያ አንድነት ከአደጋ ላይ እንዲወድቅ በማድረግ የእርሱን የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ የበላይነት ለማረጋገጥ ሲሰራ የነበረ ቀንዳም ሰይጣን ነበር፡፡

ሁሉንም ነገር በዚሁ ልተወውና በእራሳቸው በዲ ዋል የመለኪያ መስፈርት መለስ ሲደሰኩር እና በየስብሰባው ሲያነበንባቸው የነበሩት ምትሀታዊ ንግግሮች ሁሉ ስኬታማ ስለመሆናቸው እስቲ ዲ ዋልን እንዲህ የሚል አንድ ቀላል የሆነ ጥያቄ ልጠይቃቸው፡

ኢትዮጵያውያን በቀን ሶስት ጊዜ መመገብ ችለዋልን?

ደህና! ደህና! ዲ ዋል እስቲ እውነትን ይናገሩ በእርግጥ እነዚህ የመከራ ቀንበር ተሸካሚ ህዝቦች በቀን ሶስት ጊዜ መመገብ ችለዋልን? ታዲያ ይህ ካልሆነ የእርስዎ የአጉል ሙገሳ መቀላመድ ከምን የመጣ ነው?

ዲ ዋል በአሁኑ ጊዜ እራሳቸውን የስሚዝ ምስክርነት ሰጭ አድርገው አቅርበዋል፡፡ ስሚዝን ቅዱስ አድርገው አቅርበዋል፡፡ የእርስዎን ችሎታ እና ልምድ ማንም አይጠይቅም ሊባል አይችልም፡፡ ሊጠየቅ የማይችለው የጳጳሱ ችሎታ እና ልምድ ብቻ እንደሆነ አምናለሁ!

ለዲ ዋል ስለመለስ ዜናዊ ምሁራዊ ብቃት እና ስላለው ችሎታ ማንም ጥያቄ ሊያቀርብ አይችልም፡፡

በተመሳሳይ መልኩ የጋይሌ ስሚዝን በአፍሪካ ጦርነትን እና ረሀብን በመዋጋት ከ30 ዓመታት በላይ መስዋዕትነት ከፍያለሁ ስለሚሉት ስለጋይሌ ስሚዝ ብቃት እና ችሎታም ማንም ቢሆን አይጠይቅም፡፡

መለስ ምንም ዓይነት ተጠያቂነት የለበትም፡፡ ስሚዝም ምንም ዓይነት ተጠያቂነት የለባቸውም፡፡ እንደዚሁም ሁሉ ለዘራፊ አምባገነኖች እና ለእነርሱ ደጋፊዎች ምንም ዓይነት ተጠያቂነት የለባቸውም፡፡

ዲ ዋል የስሚዝን ብቃት እና ችሎታ ብቻ በመጠየቅ እያደረጉት ያለውን ያልተገባ የሙገሳ ዘመቻ በመኮነን የምናልፈው ሳይሆን እርሳቸው የሚያሞግሷቸው የዩኤስኤአይ/USAID አስተዳደሪ እና ኃላፊ ሆነው የሚያገለግሉት ስሚዝ ስለድርጅቱ ፖሊሲ እና ስለሚውስዷቸው እርምጃዎች እንዲሁም ስለሚከታተሏቸው የተጠያቂነት ግዴታዎች እንደሚጨነቁ ሁሉ እኛም ይህንኑ በመከተል ወገኖቻችንን እየጨረሱ እና እያሰቃዩ ስላሉ የቀን ጅቦች የተጠያቂነት ስርዓት እንዲኖር ስለምንፈልግ ነው፡፡

እኛ የምንኖረው በአሜሪካ ነው እንጅ የለየላቸው አምባገነኖች በሚያተራምሷቸው በኢትዮጵያ፣ በሩዋንዳ ወይም ደግሞ በኡጋንዳ ውስጥ አይደለም፡፡

የአሜሪካንን የሕግ ማዕቀፍ በመጠቀም ስሚዝ እያደረጓቸው ያሉትን ድርጊቶች እና ውሳኔዎች የፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማንም ሳይቀር የተገኘውን የህግ አማራጭ ሁሉ መበጠቀም በህግ የመጠቀም መብታችንን እናስከብራለን፡፡

የእርስዎን አቅም እና ችሎታ ማንም ሊጠይቅዎት አይችልም፡፡!!! ድምጼን ከፍ አድርጌ ለመጮህ እንድችል ትንሽ ፋታ ይስጡኝ!

በዓለም አቀፍ የአሸባሪ የስም ዝርዝር መዝገብ ውስጥ ያለን ድርጅት መርዳት እና ማገዝ አቅምን እና ችሎታን ከመጠየቅ አንጻር ሊቆጠር ይችላልን ዲ ዋል?

ለአባማ አስተዳደር አፍሪካ ለአእምሮ ቀላል የሆነ ጥያቄ ነው፣ 

የኦባማ አስተዳደር በአፍሪካ ጉዳይ ላይ ምንም የማያሳስብ ቀላል የሆነ ነገር ተደርጎ ይወሰዳል ወደሚል መደምደሚያ ላይ ደርሻለሁ፡፡ ለዚህ ማስረጃው አወዛጋቢ የማይሆነው የኦባማ አስተዳደር ከአፍሪካ አምባገነኖች ጎን የመቆሙ ሁኔታ ነው፡፡

የኦባማ የአፍሪካ ፖሊሲ የሚከተሉትን በርካታ ታሳቢዎች መሰረት ያደረገ ነው፣

  • በአፍሪካ ቀንድ አጠቃላይ የሆነ ውስጣዊ ወይም ውጫዊ ውድቀት እና ትርምስ እንዳይፈጠር የህወሀት ኃይል የመሰረት ድንጋይ ነው፡፡
  • በአፍሪካ ሽብርተኝነትን መዋጋት እና ሰብአዊ መብት እንዲከበር ማድረግ አንዳቸው ከሌላቸው የሚለዩ አይደሉም፡፡
  • የአፍሪካ አምባገነን መሪዎች የዜጎቻቸውን መብቶች እንዲያከብሩ በተጠናከረ መልኩ መገፋፋት ዩናይትድ ስቴትስ እያካሄደች ካለችው ዓለም አቀፍ የአሸባሪነት ጦርነት ላይ የሚደረገውን ተባባሪነት እና እገዛ ይቀንሳል፡፡
  • ዩናይትድ ስቴትስ በአፍሪካ የሚገኙ ጨቋኝ መንግስታትን ማገዝ፣ መከላከል፣ ታጋሽነትን ማሳየት እና ሆደ ሰፊ መሆን ይኖርባታል ምክንያቱም እነዚህ ጨቋኝ መንግስታት ዩናይትድ ስቴትስ ለምታካሂደው ዓለም አቀፍ የአሸባሪነት ጦርነት ተባባሪ ይሆናሉና፡፡
  • በአፍሪካ አምባገነንነት፣ ዴሞክራሲያዊነትን ሳይሆን የአሜሪካንን ደህንነት እና የብሄራዊ ጥቅሟን ለማራመድ እና ለማስጠበቅ የሚውል ነገር ነው፡፡

እነዚህ ከላይ የተዘረዘሩት ታሳቢዎች የተዛቡ እና በትክክለኛ መረጃ ላይ ያልተመሰረቱ ውሸቶች ናቸው፡፡ ሆኖም ግን በተቻለ መጠን ከነባራዊ እና ከተጨባጩ እውነታ በመነሳት ትንበያ የተደረገባቸው ናቸው፡፡

ሁሉም የአሸባሪነት ድርጊቶች ሰይጣን ለአፍሪካ አምባገነን መሪ ተብዬዎች የተላኩ ናቸው፡፡ እነዚህ አምባገነኖች ዕለት በዕለት ለለሚፈጽሟቸው ወንጀሎች ሁሉ ተጠያቂ እንዳይሆኑ የሚከላከሉላቸው ነገሮች ናቸው፡፡ የአሜሪካ የዓለም አቀፍ የጸረ ሽብርተኝነት ጦርነት ለአፍሪካ አምባገነን መሪዎች ላሜ ቦራ ነው፡፡

የአፍሪካ አምባገነን መሪዎች ሽብርተኝነትን እንዲዋጉ መርዳት እና በአምባገነኖች እብሪት በንጹሀን ዜጎች ላይ የሚፈጸሙ መጠነ ሰፊ የሆኑ የጅምላ ሰብአዊ መብት ጥሰቶች ሲፈጸሙ እያዩ እንዳላዩ፣ እየሰሙ እንዳልሰሙ በማስመሰል በማለፉ ጉዳይ ላይ ታላቅ ልዩነት አለ፡፡ ዩኤስ አሜሪካ በዜጎች ላይ የሚደረግን የሰብአዊ መብት ድፍጠጣ ወንጀል ለጸረ ሽብር ጦርነቱ ማካካሻ በማድረግ አምባገነኖች የፈለገውን ያህል ንጹሀን ዜጎችን ቢገድሉ፣ ቢያፍኑ፣ ቢያሰቃዩ እና ሌላም በሰው ልጆች ላይ ሊፈጸሙ የማይገባቸው ነገሮች ቢያደርጉ ኬረዳሽ በማለት ታልፈዋለች፡፡

የኦባማን አስተዳደር መርሆዎች ግልጽ ለማደረግ ልሞክር፡፡ ከመጠን በላይ ባለፈ ጥርጣሬ ላይ ተመስርቶ የተሰጠ ታሳቢ ቢሆንም በአፍሪካ አህጉር በተለይም በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ያለ ዩኤስኤ እርዳታ አምባገነኖቹ መሪዎች ተጠራርገው በአንድ ጊዜ ወደ ሲኦል ገሀነም እንደሚወርዱ ይገመታል፡፡

ዳንቴ “ህይወት በገሀነም፣ ከገሀነም በር ትዕዛዞች፡ እዚህ ስትደርስ ሁሉንም ተስፋ እርግፍ አድርገህ ተወው“ በሚል ርዕስ እንደተናገሩት ሁሉ በአፍሪካ አምባገነኖች ህይወታቸውን ያሳለፉ በርካታ ዜጎች እንዳሉ እና ሁሉንም ነገር ትተው እንደተቀመጡ አውቃለሁ፡፡

የአፍሪካ ቀንድ ሀገሮች በትንሹ ለማስቀመጥ በከፋ ችግር ውስጥ ተተብትበው የሚገኙ ናቸው፡፡

የኦባማ አስተዳደር የአፍሪካ ቀንድ በትንሽ ኮሽታ በቀላሉ ሊናድ እንደሚችል አሳምሮ ያውቃል ሆኖም ግን በይፋ ዕውቅና ለመስጠት አይፈልግም፡፡ እናም ሁሉም የንጉስነት ሰዎች እና የሚወጡባቸው ፈረሶች በአንድነት ሳይገናኙ እንደሚኖሩ ያውቃሉ፡፡

የሶማሊያ ጠንካራው ወታደራዊ መሪ ሲያድ ባሬ በተቃዋሚዎች ጥምረት ከስልጣን መንበሩ ላይ ከተባረረ በኋላ ትናንሽ የጎሳ መንግስታትን በመመስረት በመታመስ ላይ ትገኛለች፡፡

ማንም ቢሆን የጎሳ መሪዎችም ቢሆኑ፣ ለሶስት ዓመታት ያህል የሶማሊያን ህዝብ ሲወጋ እና ሲያተራምስ የቆየው ጦርነት ናፋቂው እና ጦረኛው መለስ ዜናዊም ቢሆን፣ የአፍሪካ ህብረት ተብየውም ቢሆን፣ ዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካም ብትሆን ወይም የአውሮፓ ህብረትም ቢሆን እነዚህ ወይም ሌሎችም ቢሆኑ ሶማሊያን ቀድሞ ወደነበረችበት መመለስ አልቻሉም፡፡

ኢትዮጵያ በቀጣነት በውድቀት አፋፍ ላይ ያለች ሀገር ናት፣

የወያኔ ወሮባላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ እና አመራሮች በደቡብ አፍሪካ አፓርታይድ የተባለው ዘረኛ የነጮች የበላይነት ቡድን ሲያደርግ እንደነበረው ሁሉ ኢትዮጵያን በትንንሽ የጎሳ መንደሮች እና ክልል እያሉ በሚጠሩት የማጎሪያ በረት ሸንሽነዋታል፡፡

የወያኔ ወሮባላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ 13 ወራት የጸሐይ ብርሀን የማይለያትን ሀገር የክልላዊ ሀገር አድርገዋታል፡፡

አንድ ጥንታዊ ገጣሚ “የጽጌረዳ አበባ የፈለገውን ያህል በሌላ ስያሜ ቢጠራም ያው ጣፋጭ የሆነ ሽታውን አይለቅም፣“ በማለት ጽፈዋል፡፡ ሆኖም ግን ባንቱስታን በሚል ስያሜ ይጠራ የነበረውን የአፓርታይድ ስርዓት ክልል የሚል ገራገር እና አስመሳይ ስያሜ በመስጠት ክልልነት እንደ ጽጌረዳው የሚያውድ ጥሩ መዓዛ ያለው ሽታ ሳይሆን የሚሰነፍጥ እና የሚጠነባ ጠረንን እያስጋተ ይገኛል፡፡

የወያኔ ወሮባላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ በስልጣን ላይ መቆየት ለኢትዮጵያ እና ለአፍሪካ ቀንድ መረጋጋት ይበጃል የሚል እምነት ቢኖራቸውም ሀቁ ግን በጊዜ ሂደት እየተቀጣጠለ ያለ እና በአንድ ወቀት ሊፈነዳ የሚችል በጊዜ የተሞላ ቦምብ መሆኑን ሊገነዘቡ ይገባል፡፡

መለስ ዜናዊ እና የእርሱ የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ በአንድ ወቅት ሊፈነዳ የሚችል እነርሱን አቃጥሎ ዶግ አመድ ሊያደርግ እና ተጣብቀው ከሚገኙበት ስልጣናቸው አሽቀንጥሮ ሊጥል የሚችል በሰዓት የተሞላ ቦምብ ቀብረዋል፡፡

የወያኔ ወሮባላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ዋናው እምነቱ እነርሱ የሚገዟት ኢትዮጵያ ከሌለች ሌላ ማንም ሊያስተዳድራት የምትችል ኢትዮጵያ መኖር የለባትም የሚል ነው፡፡ ሀገሪቱን ወደ ትናንሽ ብጥስጣሽ ክፍልፋዮች መቀየር ነው ዋናው ዓላማቸው!

ሆኖም ግን የወያኔ ወሮባላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ አንድን ነገር ከምንም ጥርጣሬ በላይ ሊገነዘብ ይገባል፡፡ ኸውም ኢትዮጵያ የምትባለዋን ሀገር ታሪክ ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ከታሪክ ማህደር ለማጥፋት እያደረገ ያለው ከንቱ ዕቅድ በምንም ዓይነት መልኩ በፍጹም፣ በፍጹም፣ በፍጹም ሊሳካ አይችልም! ምክንያቱ ደግሞ አንድ እና ቀላል ነገር ነው፡፡ ይኸውም ከወያኔ ወሮባላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ኃይል እጅግ የገዘፈ እና የበለጠ በግልጽ ሊታይ በማይችል መልኩ በስውር የቆመ እና እርሱ የእራሱ ኢትዮጵያ ከሚላት በላይ ሆኖ የሚመክት እና የሚጠብቃት ኃይል እንዳለ ግንዛቤ ሊወሰድ ይገባል፡፡

ዩናይትድ ስቴትስ በኢትዮጵያ ለሰብአዊ መብት ጠንካራ የሆነ ድጋፍ አደርጋለሁ የምትለው ላም አለኝ በሰማይ አይነት አነጋገር ይልቁንም በአፍሪካ ቀንድ የምታራምደው የጸረ ሽብር ጦርነት በቀጣናው የበለጠ አለመረጋጋት እያሰፈነ እና ግጭቶች በየቦታው እየተነሱ የሚቀጣጠሉ ስለሚሆን የምታራምደውን የተሳሳተ ፖሊሲ አይረቤነት እና የማይሰራ መሆኑን በግልጽ የሚያመልክት ጉዳይ ነው፡፡

በድብቅ የተያዘው የዩናይትድ ስቴትስ አቋም ታሳቢ ያደረገው ጠንካራ ጡንቻ ያለው የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ በስልጣን ላይ እስከሌለ ድረስ ኢትዮጵያ ቀጣይዋ ሶማሊያ ትሆናለች የሚል ነው፡፡

የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ለጋሽ እና አበዳሪ ድርጅቶችን ሊያሳምን የሚችል አንድ ቆንጆ ነገር ይዟል፡፡ የኸውም ወያኔ የያዛት ኢትዮጵያ ከሌለች መላው የአፍሪካ ቀንድ ሀገሮች ሰላም ሊሆኑ አይችሉም የሚል ነው፡፡ ያ ማለት እንግዲህ የፈረስ ላባ እንደማለት ያህል ነው፡፡ (የኮርማ ላባ አላልኩም፡፡)

በአፍሪካ ቀንድ እና በሌሎች አካባቢዎችም ቢሆን ሁልጊዜም ሽብርተኝነት ይኖራል፡፡ ያ ቀላሉ እውነታ ነው፡፡ በአፍሪካ ቀንድ ሽብርተኝነትን መከላከል የወያኔ ወሮባላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ኃላፊነት አይደለም፣ ሊሆንም ከቶ አይችልም፡፡ የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ በእራሱ አሸባሪ ድርጅት ነው፡፡ በዓለም አቀፍ የሽብርተኝነት መዝገብ ዝርዝር መረጃ ቋት ውስጥ ስሙ ተጽፎ የሚገኝ ወሮበላ እና የማፊያ ድርጅት ነው፡፡ አንዱ አሸባሪ ሌላውን አሸባሪ፣ አሸባሪ ሊለው አይገባምና!

የወያኔ ወሮባላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ የቀጣናው የስጋት ምንጭ ነው፣

እ.ኤ.አ በ2007 በመለስ የመጀመሪያው የሶማሊያ ወረራ ዓመት ጊዜ የሶማሊያ ዋና መዲና በሆነችው በሞቃዲሾ ከ700 ሺህ በላይ የሚገመት ኗሪ ህዝብ ተፈናቀለ፡፡ እ.ኤ.አ በ2008 ደግሞ 16210 ሲቪል ሰዎች የተገደሉ ሲሆን 29000 የሚሆኑ ዜጎች ቁስለኛ ሆኑ፡፡ በሶማሊያ ላይ ይህ ሁሉ ጉዳት ሊደርስ የቻለው በመለስ ቀጥተኛ ጣልቃገብነት ምክንያት ነበር፡፡

የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ለአፍሪካ ቀንድ ሰላም ጠባቂ ፖሊስ ይሆናል ብሎ ማሰብ  ዶሮዎች የታጨቁበትን አንድ ሙሉ ቤት የቀበሮ ባህታዊ እንዲጠብቀው ሙሉ እምነት ከመስጠት ድርጊት ጋር መሳ ለመሳ ነው፡፡

ይልቁንም የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብን ከስልጣን መንበር ከኢትዮጵያ ማባረር ሀገሪቱ በቀጣይነት ካልተረጋጋ ወደተረጋጋ ስርዓት ትሸጋገራለች፡፡ ወደመበታተን የሚያመራት ምንም ዓይነት ኃይል የለም፡፡ እንዲያውም ወደ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እና መልካም አስተዳደርን ወደማስፍን ስርዓት ትሸጋገራለች፡፡

የቀውስ ቡድኖች እንዲህ የሚል የክርክር ጭብጥ ያቀርባሉ፣ “በኤርትራ ጠንካራ የሆነ የስልጣን ትግል ለአፍሪካ ቀንድ እና በቀጣይነትም ለቀይ ባህር አካባቢ አስጊ ሁኔታ ሊፈጥር ይችላል፡፡“

እውነታው ፍርጥርጥ ተደርጎ ሲታይ ግን የአፍሪካ ቀንድ የጨነገፉ መንግስታት ስብስብ ነው፡፡ ማናቸውም የአፍሪካን ቀንድ አምባገነኖች የሚከላከሉ ለጋሽ እና አበዳሪ ድርጅቶች እንዲሁም ሌሎች ድርጅቶች ያንን ያፈጠጠ እና ያገጠጠ ችግር አምነው መቀበል እና እውቅና መስጠት ይኖርባቸዋል፡፡

ከትንሿ ጂቡቲ በስተቀር ሌሎቹ 4ቱ የአፍሪካ ቀንድ ሀገሮች እ.ኤ.አ በ2015 ከወጣው አመላካች መለኪያ ውስጥ የጨነገፉ መንግስታት ከሚለው የመጀመሪያው ደረጃ ረድፍ ውስጥ ናቸው፡፡ በዓለም ላይ ለውድድር ከቀረቡ 187 ሀገሮች መካከል ከጨነገፉ ሀገሮች የመጀመሪያዋ ደቡብ ሱዳን ስትሆን ሶማሊያ በ2ኛ ተራ ቁጥር፣ ሱዳን በ4ኛ፣ ኢትዮጵያ በ20ኛ፣ እና ኤርትራ በ24ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ፡፡

በእነዚህ ሀገሮች ጠንካራ የሰብአዊ መብት ጥበቃ ማድረግ ጥላቻ እንዲፈጠር እና ሀገሮቹ እንዳይረጋጉ ያደርጋቸዋል የሚለው የዩናይትድ ስቴትስ የክርክር ጭብጥ መሰረተቢስ እና ውኃ የማይቋጥር እርባናየለሽ ነው፡፡ የአፍሪካ ሀገሮች አሁን ካሉበት ሁኔታ የበለጠ የጨነገፉ መንግስታት ሊሆኑ የሚችሉበት ሁኔታ ምንድን ነው?

የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ለኢትዮጵያ አንድነት እና የፖለቲካ መረጋጋት ዋና መሰረት ነው የሚለውን የዩናትድ ስቴትስን ታሳቢ የማይሰራ እና ተራ ነገር መሆኑን ለመሞገት እፈልጋለሁ፡፡ ይህ ታሳቢ የኢትዮጵያን ህዝብ እና ታሪክ ዝቅ አድርጎ የመመልከት አመላካከት ነው፡፡

ኢትዮጵያ የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ወደማይቀረው የታሪክ ቆሻሻነት ተጠራርጎ ሲጣል ኢትዮጵያ ወደ ተለያዩ ክልላዊነት እና መንደርተኝት አትከፋፈልም፡፡ ኢትዮጵያ በወያኔ ወሮባላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ሰይጣናዊ አመራር ከወደቀችበት የክልል አመድ በጽናት ትነሳለች፡፡ ያንን ዕለት የኢትዮጵያ ትንሳኤ ብለን የምንጠራው ይሆናል፡፡

ኢትዮጵያ ከ3 ሺህ ዘመናት በላይ ነጻነቷን አስከብራ የኖረች ሀገር ናት፡፡ በ19ኛው ሁለተኛ አጋማሽ የአውሮፓ ኃያላን አፍሪካን እንደ ቅርጫ ስጋ ሲከፋፈሉ ኢትዮጵያ ለአውሮፓ ቅኝ ገዥዎች እጅ ሳትሰጥ እና ሳትንበረከክ ነጻነቷን አስጠብቃ የቆየች የጀግኖች ሀገር ናት፡፡ ኢትዮጵያ ለአውሮፓ የቅኝ ግዛት ማሽን ለሁለት ጊዜ ያህል ተሞክሮባት እጅ ያልሰጠች የመንፈሰ ጠንካሮች እና የጀግኖች ሀገር ናት፡፡

ኢትዮጵያ ከወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ጠንካራ ጡንቻ አገዛዝ ውጭ ልትበታተን ትችላለች የሚለው የሸፍጥ ማደናገሪያ ከዩናይትድ ስቴትስ እና ከሌሎች ሀገሮች ድጋፍ እያገኙ ሲገዙ ለመኖር በወያኔው የእራስ አገልጋይነት ስሜት ላይ ተመስርቶ የተቀየሰ ሸር ከመሆን ያለፈ ሌላ ፋይዳ የለውም፡፡

ዩናይትድ ስቴትስ በጭፍንነት የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብን እየረዳች የምትቀጥል ከሆነ የቀጣናው የምጽአት ዕለት መምጣቱ የማይቀር ጉዳይ ነው፡፡ ለዚህም ነው በአሁኑ ጊዜ ዩናይትድ ስቴትስ ጭንቅላቷን ከቀበረችበት አሸዋ ውስጥ ብቅ በማድረግ ጊዜው ከመምሸቱ በፊት ትክክለኛውን ነገር መፈጸም ያለባት፡፡

ዋሽንግተን ፖስት ኤዲቶሪያል ክፍል በቅርቡ የኦባማ አስተዳደር እየተከተለ ያለውን አካሄድ እንዲቀይር እንዲህ የሚል ምክር ለግሷል፡

ጥንታዊ ከሆነ ባህሏ ጋር፣ 94 ሚሊዮን የሆነውን ህዝብ ይዛ ስትራቴጂካዊ በሆነ ቀጣና ላይ የተቀመጠችው ኢትዮጵያ ለወደፊቱ ለምስራቅ አፍሪካ ቁልፍ ቦታን ትይዛለች፡፡ ሆኖም ግን የእዩልኝ እመኑልኝ መግለጫ ማውጣት ወይም ደግሞ የተለሳለሰ አቋም በመያዝ ለመጓዝ መሞከር የማይሰራ አካሄድ ነው፡፡ ዩናይትድ ስቴትስ የብዙሀን መገናኛን ለሚያፍን፣ የተቃዋሚ ፓርቲዎችን ተሳትፎ ለሚገድብ እና ትችት የሚያቀርቡበትን ሁሉ ጸጥ ለማድረግ ለሚሞክር አገዛዝ በሚሊዮኖች የሚቆጠረውን የእርዳታ ገንዘብ መስጠቷን ማቆም ይኖርባታል፡፡ ዩናይትድ ስቴትስ ተካሄደ የተባለውን የቅርጫ ምርጫ ነጻ በሆነ አካል ሳይረጋገጥ ማዳም ሸርማን የሰጡት መግለጫ ስህተት መሆኑን አምና በመቀበል ከዚህ በኋላ ግን አካዷን ማስተካከል ይጠበቅባታል፡፡

ዩናይትድ ስቴትስ ያለምንም ማቅማማት አካሄዷን መለወጥ አለባት፡፡ በአሁኑ ጊዜ የሰብአዊ መብት ማስክበርን ቀዳሚው እና ዋናው አጀንዳዋ ማድረግ አለባት፡፡

ዋሽንግተን ፖስት ዩናይትድ ስቴትስ የፖሊሲ አካሄዷን መቀየር አለባት ሲል የሰጠው ምክረ ሀሳብ በእርግጥም ትክክል ነው፡፡

የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ወደማይቀረው የቆሻሻ ማጠራቀሚያ ቅርጫት ተጠራርጎ ሲጣል ዩናይትድ ስቴትስ ምንድን ልታደርግ አስባለች?

የአፍሪካ ቀንድ እንዳረጀ እና እንዳፈጀ ቤት መፈረካከስ ሲጀምር ዩናይትድ ስቴትስ ምንድን ለማድረግ አስባለች?

ዩናይትድ ስቴትስ በአፍሪካ ቀንድ እንደገና ሌላ የተሳሳተ እና እብሪት የታከለበት ወታደራዊ እርምጃን ለማራመድ የሚያስችል ፖሊሲ ልትነድፍ ትችላለችን?

ዩናይትድ ስቴትስ ባለፉት አስርት ዓመታት ጊዜ ውስጥ በኢራቅ፣ በአፍጋኒስታን፣ በኢራን፣ በሊቢያ እና በየመን መረጋጋትን ለማስፈን በሚል በትሪሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር ወጭ አድርጋለች፡፡ እነዚህ ሀገሮች ዩናይትድ ስቴትስ ጣልቃ ከመግባቷ በፊት ከነበሩበት ሁኔታ አንጻር ሲገመገም የበለጠ መረጋጋትን አሳይተዋልን?

የአፍሪካ ቀንድ ቁጠባን የሚፈልግ ከሆነ ይህ ጉዳይ መፈጸም ያለበት በአፍሪካ ቀንድ ላይ በሚኖሩት ህዝቦች እንጅ በሌላ በቀንድ ላይ በተቀመጠ ሌላ ቀንድ መሆን የለበትም፡፡ ሆኖም ግን በዩናይትድ ስቴትስ የሚሰጠው የክርክር ጭብጥ አስመሳይነት የተሞላበት እና በሁለት ቢላዋ የመብላት ያህል ነው፡፡

ሮበርት ሙጋቤ እ.ኤ.አ ከ1980 ጀምሮ በስልጣን ወንበር ላይ ተፈናጥጦ ይገኛል፡፡ ይህ ማለት እንግዲህ ዚምባብዌ የተረጋጋች ሀገር ናት ማለት ነው፡፡ ሮበርት ሙጋቤ እ.ኤ.አ ነሀሴ 2013 ተቀናቃኙን በ61 በመቶ ሲያሸንፍ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የሆኑት ጆን ኬሪ የምርጫው ውጤት የዚምባብዌን ህዝብ እንደማይወክል እና የህዝቡን ፍላጎት ያላሟላ ነው በማለት ውድቅ እንዲደረግ ተናግረው ነበር፡፡

ባለፈው ወር የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኬሪ በካሜሩን እ.ኤ.አ ከ1987 ጅምሮ በስልጣን ወንበር ላይ ተፈናጥጦ ለሚገኘው አምባገነን መሪ ደብዳቤ ጽፈው ነበር፡፡ እንግዲህ ካሜሩን የተረጋጋች ሀገር ናት ማለት ነው፡፡ ኬሪ ለቢያ እንዲህ በማለት ተናገሩ፣ “በፕሬዚዳንት ኦባማ እና በአሜሪካ ህዝብ ስም እ.ኤ.አ ግንቦት 20 የካሜሩንን ብሄራዊ ዕለት በማክበራችሁ እንኳን ደስ ያላችሁ፡፡ ከነጻነት በኋላ ካሜሩያውያን የተረጋጋ፣ የበለጸገ እና ዴሞክራሲያዊ የሆነ ስርዓትን በመገንባት ላይ ናችሁ፡፡ ይህንን ስኬት በመቀዳጀታችሁ ዩናይትድ ስቴትስ ሀገርዎን እንኳን ደስ ያላችሁ ለማለት ትፈልጋለች፡፡   “

ቢያ አሁን በህይወት ካሉ 20 አምባገነን መሪዎች መካከል አንዱ እና የይስሙላ የታዕይታ ምርጫ በማካሄድ እውቅና ተሰጥቶት ስሙ ተመዝግቦ ይገኛል፡፡ ቢያ ቀደም ሲል የአሜሪካ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የነበሩ ለ6 ሰዎች እና ለሌሎች ዓለም አቀፍ የምርጫ ታዛቢዎች ክፍያ ከፍሎ ምርጫወው ነጻ እና ፍትሀዊ ተብሎ እንዲነገርለት አድርጓል፡፡

እ.ኤ.አ ሚያዝያ 2015 የሱዳኑ ኦማር አልባሽር 94.01 በመቶ ድምጽ በማምጣት ምርጫውን አሸነፍኩ ብሎ ሲያውጅ ትሮይካ (ዩናይትድ ስቴትስ፣ እንግሊዝ እና ኖርዌ) ምርጫው ተጭበርብሯል በማለት አውግዘዋል፡፡ በሽር መፈንቅለ መንግስት በማካሄድ እ.ኤ.አ ከ1989 ጀምሮ በስልጣን ወንበር ላይ ተፈናጥጦ ይገኛል፡፡ ሱዳንም እንግዲህ የተረጋጋች ሀገር ናት ማለት ነው፡፡

ከጥቂት ሳምንታት በፊት የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ መቶ  በመቶ ድምጽ በማግኘት አሸነፍኩ ብሎ ሲያውጅ ዩናይትድ ስቴትስ ቀጣይነት ባለው ሁኔታ በሲቪል ማህበረሰቡ፣ በነጻው ፕሬስ እና በተቃዋሚ ፓርቲዎች እንዲሁም ነጻ አስተሳሰብ እና አመለካከት ባላቸው ሰዎች ላይ እየተደረገ ያለው ክልከላ እና አፈና አሳስቦኛል የሚል መግለጫ አውጥታለች፡፡ እንግዲህ ያለው ሁኔታ ይኸ ነው!

ሆኖም ግን አንዳንድ ጊዜ ዝምታ ከመናገር በላይ ይናገራል፡፡

በአንድ ወቅት ፕሬዚዳንት ፍራንክሊን ዲ. ሩዝቬልት ለኒካራኳው አምባገነን መሪ ለአናስታሲኦ ሶሞዛ እንዲህ ብለውት እንደነበር አፈታሪክ ሆኖ ሲወሳ ይኖራል፣ “ሶሞዛ የተጠላ እና የተናቀ ሰው ነው፣ ሆኖም ግን የእኛ የተጠላ እና የተናቀ ሰው ነው፡፡“

በተመሳሳይ አመክንዮ ሙጋቤ እና ባሽር የእኛ የተጠሉ እና የተናቁ ልጆች አይደሉም፣ ሆኖም ግን የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ የእኛ የተጠላ እና የተናቀ ልጅ ነውን!

ባለፈው ዓመት ዩናይትድ ስቴትስ በዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ጉዳይ ተይዞ የነበረው የኬንያው አምባገነን መሪ ኡሁሩ ኬንታ ከተያዘበት በሰው ልጆች ላይ ከፈጸማቸው በርካታ የወንጀል ዝርዝር ነጻ ሆኖ እንዲለቀቅ በድብቅ ስትሰራ ነበር፡፡

እውነታው ፍርጥርጥ ተደርጎ ሲታይ ግን የአፍሪካ አምባገነኖች የአሜሪካንን ደህንነት ሊያጠናክሩ አይችሉም፡፡ ኦባማ የአፍሪካን አምባገነኖች በማጎልበት የአሜሪካንን ደህንነት በማዳከም ላይ ይገኛሉ፡፡

የአሜሪካ ብሄራዊ ጥቅም ከአፍሪካ አረመኔ፣ ጨካኝ፣ በሙስና የተዘፈቁ እና ጨቋኝ አምባገነን መሪ ተብዎች ህልውና ጋር ለድርድር መቅረብ የለበትም፡፡

እንደ ኢትዮ-አሜሪካዊ የሕገ መንግስት ባለሙያነቴ የዴሞክራሲያዊ ስርዓት መገንባትን እና መሰረታዊ የሰብአዊ መብት ጥበቃን የምታከብረው አሜሪካ የአፍሪካ አምባገነኖች በዴሞክራሲ ላይ ንቀትን ሲያሳዩ እና በሰብአዊ መብት ጥበቃ ላይ አፍንጫቸውን እየነፉ ሰብአዊ መብትን በየዕለቱ ሲደፈጥጡ ስትመለከት ሳይ በእጅጉ የውርደት ስሜት ይሰማኛል፡፡

በሰው ልጆች ነጻነት ላይ እምነት ያላት ሀገር ከአፍሪካ ገዳዮች፣ አሰቃዮች እና ጨቋኞች ጋር ለምን ወደ አልጋ እንደምትሄድ የሚገርመኝ ጉዳይ ነው፡፡ ማለት የተፈለገው በአፍሪካ የሚገኙትን አምባገነን መሪ ተብዬዎች መርዳት ማለት እነዚህ አምባገነኖች የሰብአዊ መብቶችን በመጨፍለቅ በአምባገነንነት ምግባራቸው የበለጠ እንዲቀጥሉበት መፍቀድ ማለት ነው፡፡ አሜሪካ እራሷን ከእነዚህ አምባገነኖች መነጠል አለባት፣ እናም በግዴለሽነት ወይም ደግሞ ንቁ ተሳትፎ በማድረግ በአፍሪካ ጭቆና እና ጨካኝነት የተመላበት ስርዓት እንዲኖር መፍቀድ የለባትም፡፡

በሰብአዊ መብት ጥበቃ አያያዝ የአሜሪካ የሞራል ስብዕና ለተራው የአፍሪካ ህዝብ ግልጽ እና መሳቂያ እየሆነ የመጣ እንዲሁም የአሜሪካንን እሴቶች እየናቁ እና ዋጋቢስ እያደረጉ የመምጣታቸው ጉዳይ ግልጽ እየሆነ በመምጣት ላይ ይገኛል፡፡

ፕሬዚዳንት ጂሚ ካርተር እንዲህ ብለው ነበር፣ “አሜሪካ ሰብአዊ መብትን አልጋበዘችም፡፡ ይልቁንም ሰብአዊ መብት አሜሪካንን እየጋበዘ ነው፡፡“

ሰብአዊ መብት አፍሪካን ለመጋበዝ የማትችለው ለምንድን ነው?  አፍሪካውያን/ት ሰብአዊ ፍጡር አይደሉምን? 

30ኛው የትብብር ዓመት መልካም ቀን ይምጣ! 

እ.ኤ.አ 2015 የጋይሌ ስሚዝ እና የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ 30ኛ የትብብር ዓመት ክብረ በዓል ነው፡፡ እ.ኤ.አ 1985 ስሚዝ ለማረት/REST ሌላው የአህጽሮ ቃል ህወሀት/TPLF ለሚባለው ድርጅት ሲሰሩ የነበረበት ዓመት ነው፡፡

ስሚዝ ይጸድቅላቸዋል፣ ዩኤስኤአይዲን/USAIDን ይገዛሉ (ያስተዳድራሉ ወይም ደግሞ ይመራሉ አላልኩም፡፡)

የአሜሪካ የግብር ዶላር ለአፍሪካ አምባገነኖች በተለይም ለወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ እንደ ሚሲሲፒ ወንዝ ውኃ ይፈስሳል፡፡

ሆኖም ግን ፍትህ እንደ ወንዝ ውኃ እየፈሰሰች እንደምትመጣ፣ እውነት ምንም ዓይነት ውድቀትን ሳታስከትል በኢትዮጵያ እና በአፍሪካ አህጉር እንደምትመጣ እንደ አይሁድ ነብይ አስቀድሞ ሊታየኝ ይችላል፡፡ ያ ቀን እየመጣ መሆኑ ቁልጭ ብሎ ይታየኛል፡፡

የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ አምባገነኖችን መንከባከብ ለአሜሪካ ደህንነት ዋና እና አስፈላጊ ነገር ነውን? እኔ በበኩሌ በፍጹም እላለሁ!

የጋይሌ ስሚዝ መልስ ፍጹም በሆነ መልኩ አዎ የሚል ይሆናል!

ደህና፣ የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ እ.ኤ.አ በ2015 ተካሄደ የተባለውን የቅርጫ ምርጫ ብቻ አይደለም መቶ በመቶ ያሸነፈው ሆኖም ግን በአሁኑ ጊዜ ደግሞ የቀድሞዋን ሰራተኛውን ነጻ ለሆነው ለአፍሪካ አምባገነኖች ባንክ (አአባ)/African Dictators’ Bank (BAD) የሆነውን ዩኤስኤአይዲን/USAIDን እንዲመሩላቸው ተሾመውላቸዋል፡፡

በአሁኑ ጊዜ ሽንፈትን አምኘ እቀበላለሁ፡፡

የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ እና ጋይሌ ስሚዝ አሸንፈዋል፡፡

ለስሚዝ እና የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ እንደ ዱሮው ጊዜ እሆንላቸዋለሁ፡፡

በአሜሪካ ግብር ከፋይ ህዝብ ስም እናንተ ሰርግ እና ምለሽ አድርጉ እያልኩ ምኞቴን እገልጽላቸዋለሁ፡፡

እ.ኤ.አ በ1984-85 ለሰብአዊ መብት ገንዘብ ሲሰጡ የነበሩ ለጋሾችን እንደገና በማግኘታቸው ለእነርሱ ጥሩ ጊዜ ነው፡፡

በአሁኑ ጊዜ የአሜሪካንን ግብር ከፋይ ህዝብ ለመቦጥቦጥ ሌላ ጥሩ አጋጣሚን ያገኛሉ፡፡

ከሶስት አስርት ዓመታት በኋላ የቀድሞዎቹ የእርዳታ ሰጭ ቡድን አባላት በአንድ ላይ ሆነው እንደገና ተመልሰዋል

እንኳን ደስ ያላችሁ እላለሁ፡፡ በፌሽታቸው ዕለት ግን አልገኝም፡፡

ለኢትዮጵያ ህዝብ የሚበጅ መልካም ጊዜ ይምጣ እላለሁ!!!

ህወሀት፣ ጋይሌ ስሚዝ መልካም ጊዜ ይሁንላችሁ!!! 

ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!

ሰኔ 21 ቀን 2007 . 

 

 

Similar Posts