ለፕሮፌሰር ዶናልድ ሌቪን እልፈት ማስታወሻ (ፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማርያም)
ከፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማርያም
ትርጉም በነጻነት ለሀገሬ
ፕሮፌሰር ዶናልድ ሌቪን፡ የልሂቃን ሁሉ ልሂቅ
ፕሮፌሰር ዶናልድ ሌቪን በዚህ ባሳለፍው ጥር ወር ኢትዮጵያን ለመጎብኘት የነበራቸው የረዥም ጊዜ ዕቅድ በህመማቸው ምክንያት የተጨናገፈ መሆኑን በኢሜይል መልዕክት ልከውልኝ ነበር፡፡ በዚያ አስበውት በነበረው ጉብኝት የሚከተሉትን ሶስት ዓላማዎች የማሳካት ዕቅድ ነበራቸው፡፡ እነርሱም፣
1ኛ) “አዲስ አበባ ውስጥ ሆኖ ኢትዮጵያን መተርጎም/Interpreting Ethiopia in Addis Ababa” በሚል ርዕስ አዘጋጅተውት በነበረው መጽሐፍ የምረቃ ስነስርዓት ላይ ለመገኘት ፈልገው ነበር፡፡
2ኛ) ከሀገሪቱ ማዕከል በስተደቡብ በኩል በ270 ኪ/ሜ ርቀት ላይ በምትገኘው የሐዋሳ ከተማ አዲስ የወጣቶች አዳራሽ የምርቃ ስነስርዓት ላይ ለመገኘት ፈልገው ነበር፡፡ የተለያዩ የስፖርት እና የስነውበት አገልግሎት ዕድሎችን ለአካባቢው ወጣቶች ለማቅረብ በሚል አላማ ላይ በመመስረት ከበርካታ ዓመታት በፊት “የሐዋሳ ወጣቶች ካምፓስን” ከሌላ አካል ጋር በመተባበር መስርተው ነበር፡፡ (እዚህ ጋ ይጫኑ እና አስደናቂ የሆነውን የቪዲዮ ምስል ይመልከቱ፡፡) ሌቪን የግቢውን/የካምፓሱን ሁለንተናዊ ፋሲሊቲዎች ለማስፋፋት ሲባል የገንዘድ አርዳታ አግኝተው ነበር፡፡ በአይቂዶ ራስ መከላከያ ጥበብ (ማለትም አንድ ሰው ልያጠቃው የመጣዉን አጥቂ ጉዳት ሳይደርስበት አራስን ለመከላክእል የምያስችል ጥበብ) አርዓያ የሚሆኑትን የመጀመሪያዎቹን የኢትዮጵያ ወጣት ወንዶች እና ሴቶች ቡድኖችን አስመርቀው ለማዬት ጉጉት አድሮባቸው ነበር፡፡ ሆኖም ግን አንድም የተፈጸመ ነገር የለም፡፡ በ”መዘግየት” ምክንያት የወጣቶችን ፋሲሊቲዎች የማስፋፋት የግንባታ ስራ ማከናወን ሳይቻል ቀርቷል፡፡
3ኛ) ፕሮፌሰር ሌቪን ታላቅ ትኩረትን በመስጠት በአምባገነኑ ገዥ አካል እስር ቤት ታጉረው በመማቀቅ ላይ የሚገኙትን የኢትዮጵያን ደፋር እና በዓለም ላይ ታዋቂ የሆኑትን ጋዜጠኞችን የእኔን ጀግና እስክንድር ነጋን እና ጀግናይቱን ርዕዮት ዓለሙን ከታሰሩበት ቦታ ድረስ በመሄድ የመጎብኘት ዕቅድ ነበራቸው፡፡ እስክንድር እና ሰርክዓለም (ሁለቱም በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅና ያላቸውን የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች) አስከፊ ለሆነ እስራት እና የመብት ድፍጠጣ ሰለባ ሆነው ከቆዩ በኋላ እ.ኤ.አ በ2007 ነጻ ተብለው ከእስር ቤት ከመለቀቃቸው በፊት ዶናልድ ሌቪን አሁን በህይወት የሌለውን መለስ ዜናዊን በግል በመለመን በታሰሩት እስረኞች ላይ ርህራሄ እንዲያሳይ እና ሰርክዓለምም ህክምና ማግኘት እንድትችል ጠይቀውት ነበር፡፡ ከዚያ በኋላም መለስ መለሳለስ አሳዬ፡፡
ጫና ያደረገ ህመም ስለወደቀባቸው እና የጤንነታቸው ሁኔታም ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሽቆለቆለ በመሄዱ ምክንያት ኢትዮጵያን ለመጨረሻ ጊዜ ለመጎብኘት አስበውት የነበረውን ዕቅድ ማሳካት ያልቻሉ መሆናቸውን አምናለሁ፡፡ ልከውልኝ የነበረውን ኢሜይል እንዳነበብኩት ከሆነ በዕቅዳቸው ይዘውት በነበረው ጉብኝት ከፍተኛ የሆኑ ተግባራትን ለማሳካት ይችሉ እንደነበር ይሰማኛል፡፡
ሌቪን ህይወታቸው ከማለፉ በፊት 13 ወራት የጸሐይ ብርሀን ባለባት ሀገር ላይ አንድ ጊዜ ወይም ከዚያ በላይ በመገኘት ህይወታቸውን ማስደሰት ይፈልጉ እንደነበር ተገንዝቢያለሁ፡፡ በኔ እምነት ወደ ኢትዮጵያ መሄድ ይፈልጉ ነበር፡፡ ለመጨረሻ ጊዜ። እናም የኢትዮጵያን አዲስ አየር መተንፈስ ይፈልጉ ነበር፡፡ ከመንዝ ህዝብ ጋር ሁልጊዜ ይሰበሰቡበት የነበረውን ቦታ መጎብኘት ፈልገው ነበር፣ በኢትዮጵያ ካሉ ጓደኞቻቸው ጋር መሳቅ እና መጫወት ፈልገው ነበር፣ እንደዚሁም ሁሉ በሐዋሳ የወጣት ክለብ በማቋቋም ወጣት ወንዶች እና ሴቶችን በማማከር ተግባር ላይ በመሳተፍ ወጣቶቹ በአካላዊ እና አዕምሯዊ ብቃት ላይ ብቻ ሳይወሰኑ ከዚህም ባለፈ መልኩ በተለይ እውነተኛነት፣ ራስን ለዲሲፕሊን ማስገዛት፣ ለራስ ክብር መስጠት፣ በእራስ የመተማመን እና ጠንካራ ሰራተኛ የመሆን ስብዕናዎችን እንዲያዳብሩ የማድረግ ጽኑ ፍላጎት ነበራቸው፡፡ ሌቪን አንድ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ በመሄድ ጉብኝታቸውን አጠናቅቀው ሲመለሱ አውሮፕላኑ የኢትዮጵያን የአየር ክልል ለመጨረሻ ጊዜ በመልቀቅ ወደ አሜሪካ ጉዞ ሲጀምሩ “ደህና ሰንብች ኢትዮጵያ” ለማለት ፈልገው እንደነበር ይሰማኛል፡፡ እንግዲህ ልከውልኝ በነበረው የኢሜይል መልዕክት በእያንዳንዱ መስመር ያነበብኩት፣ የሰማሁት እና ያየሁት ነገር ሁሉ ይህንን ያነሳሁትን ጉዳይ የሚያንጸባርቅ ነበር፡፡
ፕሮፌሰር ሌቪን ምንጊዜም መማርን የሚወዱ፣ ስነውበትን እና ስነጽሑፍን የሚያደንቁ ታላቅ ልሂቅ ሰው ነበሩ፡፡ ወደ ሀገራቸው ወደ ኢትዮጵያ ለመጨረሻ ጊዜ ሊያደርጉት የነበረውን የጉዞ ዕቅድ ሲያዘጋጁ እንዲህ የሚለውን የክሀሊል ጊብራን የግጥም ስንኞች አስታውሰው ከሆነ በጣም የሚገርመኝ ይሆናል፤
እናንተ ወጣቶች በደህና ሰንብቱ፣
እናንተ ልሂቃን በደህና ሰንብቱ፣
ሁሉም ወገኖቸ በደህና ሰንብቱ፣
መገናኘት ቀርቷል ይፋ መሞገቱ፣
ስላገር መምከሩ ነገር መፈትፈቱ፡፡
አብሪያችሁ ሆኘ ብዙ አሳልፊያለሁ፣
መከራ ደስታን በዓይኔ አይቸዋለሁ፣
ማግኘትን ማጣትን ዋኝቸበታለሁ፣
ከእንግዲህስ ወዲያ ሁሉንም ንቂያለሁ፣
ከሰማይ ደጅ ሆኘ እመለከታለሁ፡፡
እንደዚያ ነበር ተግባሩ፤
መሞገት እና መከራከሩ፣
ባለማጎብደድ ምንም ሳይፈሩ፣
እውነትን መሻት በምርምሩ፡፡
ትናንት በህልሜ ተገናኝተናል፡፡
በእኔ መነጠል አልቅሳችኋል፣
የሀዘን እንባ አፍስሳችኋል፣
ጽናቱን አምላክ ይሰጣችኋል፡፡
እናንተ ብርቱዎች መንፈሰ ጠንካሮች፣
በምድራዊው ዓለም ፈጣኖች ትጉሆች፣
ለወገኖቻችሁ አለኝታ ዋልታዎች፣
በሉ ደህና ሁኑ የዛሬ አበባዎች፣
አፈር ትቢያ ገቢ የነገ ከንቱዎች፡፡
የእኔን ነገርማ አታንሱት ብያለሁ፣
በምድር የሌለኝን እዚህ አግኝቻለሁ፣
በሰማይ ላይ ማማ ፎቁን ገንብቻለሁ፣
ሰይጣን ዲያብሎስን በግራ ጥያለሁ፣
መልዓዕክት ጻድቃንን በቀኘ ይዣለሁ፡፡
እንቅልፋችን ጠፍቷል፣
ህልማችንም መክኗል፣
ጨለማው በርትቷል፣
ብርሀንም ጠፍቷል፡፡
የቀኑ ግማሽ በእጃችን ላይ ነው፣
ግማሽ ጉዟችን ሙሉውን ቀን ነው፡፡
እናም ይበቃል እንለያይ፣
ዳግመኛ በውን ላንተያይ
ለመጨረሻው እንወያይ፡፡
መገናኘቱ አይቀርም አንዴ፣
በመላ ሳይሆን በውን በዘዴ፡፡
እናም ማውራቱ መወያየቱ፣
አንድ ላይ ሆኖ ሁሉም ባይነቱ፡፡
ትዘምሩና ለኔ ሁላችሁ፣
ምኞታችሁን በህልም አይታችሁ፡፡
ላንዳንዶቻችሁ የማይስማማ፣
የሚታይ እንጅ የማይሰማ፣
እንገነባለን በሰማይ ማማ…
የዶናልድ ሌቪንን ጠንካራ ፍላጎት እና ጥረት ወደ ኋላ መለስ ብለን ስንመለከተው ህልም ነው፡፡ ሆኖም ግን ያ ህልም፣ ያ ተስፋ እና ያ ደስታ በእኔ እይታ ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ ዶናልድ ሌቪን በኢትዮጵያ ላይ የነበራቸውን ፍቅር እና ውስጣዊ ስብዕና ፍንትው አድርጎ ያሳያል፡፡
ፐሮፌሰር ሌቪን እ.ኤ.አ ሚያዝያ 4/2015 ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡ ልጃቸው ቢል ሌቪን እንዲህ በማለት ማረፋቸውን በመግለጽ የሀዘን መግለጫቸውን አስተላልፈዋል፣ “የኢትዮጵያው ልሂቅ፣ የኢትዮጵያ አፍቃሪ እና በኢትዮጵያ የአይቂዶ ፕሮጀክት መስራች የሆኑት ጋሽ ሊበን በዛሬው ዕለት ከቀኑ በ7፡00 ሰዓት ህይወታቸው አልፏል፡፡“
ልሂቁ ዶናልድ ሌቪን ለኢትዮጵያኒስቶች (ምሁራዊ ዕውቀታቸውን ለዓለም ህዝብ ተደራሽ ለማድረግ እና የፍቅር ኃይላቸውን ኢትዮጵያን በማጥናት ተግባር ላይ የሚያውሉ ኢትዮጵያዊ ያልሆኑ ኢትዮጵያዊ ልሂቃን) በማያሻማ መልኩ ዋና ዲን ነበሩ፡፡ እ.ኤ.አ በ1970ዎቹ የመጀመሪያ ዲግሪ ተማሪ በነበርኩበት ጊዜ ሰም እና ወርቅ/Wax and Gold የሚለውን የፕሮፌሰር ሌቪንን ምሁራዊ ወጥ ስራ አስታውሳለሁ፡፡ ያ መጽሐፍ ስለኢትዮጵያ ማህበረሰብ እና ባህል ልዩ በሆኑ ምልከታዎች የተሞላ ነበር፡፡ ውስብስብ እና ጥልቅ የሆኑትን የኢትዮጵያን ባህሎች ጠልቀው በማጥናቱ ረገድ ፕሮፌሰር ሌቪን ልዩ ብቻ አልነበሩም፣ እጅግ በጣም አስደናቂ ልሂቅ ጭምር እንጅ፡፡ ፕሮፌሰር ሌቪን የሚያውቁትን ያህል እውቀት ያላቸው ማንኛውም ዓይነት ዜግነት ያላቸው ጥቂት ልሂቃን ብቻ ናቸው ያሉት፡፡
ሰም እና ወርቅ የሚለውን መጽሐፋቸውን በመገምገም ወይም ደግሞ በእርሳቸው ሰፊ የልሂቅነት ክህሎት ላይ የምጨምረው በጣም ትንሽ ነገር ብቻ ነው ያለኝ፡፡ የኒውዮርክ ታይምስ መጽሔት “ሰም እና ወርቅ” የሚለውን ወጥ የሆነውን ስራቸውን ቀዳሚ የሆነ ምርጥ ስራ በማለት አሞካሽቶታል፡፡ የታይምስ መጸሔት ጽሁፍ እንዲህ የሚል ምልከታ አስቀምጧል፣ “ኢትዮጵያን ከረዥም ጊዜ ጀምሮ ቀፍድዶ ይዟት ያለው ችግሯ ጥንታዊ ስልጣኔዋ በአሁኑ ጊዜ ካለው ዘመናዊ ስልጣኔ ጋር ሊታረቅ የሚችል ሆኖ ያለመገኘቱ ጉዳይ ነው…የዚህን እንቆቅልሽ፣ መሰረት፣ መጠን እና ከፍተኛ ችሎታን እና ግንዛቤን ባካተተ መልኩ እስከ አሁን ድረስ ማንም ሊፈታው አልቻለም፡፡“ የአሜሪካ የማህበረሰብ ጆርናል/American Journal of Sociology እንዲህ የሚል አስተያየት ሰጥቶ ነበር፣ “በጣም ጠቃሚ፣ በምልከታዎች የተሞላ እና እጅግ በጣም ጥሩ መጽሐፍ…ስኬታማው ሌቪን ሙሉ ነጻነትን በተላበሰ መልኩ እና ልዩ በሆነ ችሎታ የማህበረሰብ ሳይንስ/sociology መሰረቱን አድርጎ ሆኖም ግን ከሌሎች የሙያ ዘርፎች ማለትም ከሰው ዘር አመጣጥ ጥናት፣ ከስነልቦና፣ ከታሪክ እና ከቋንቋ ባለሙያዎች ለየት ባለ እና ባልተለመደ መልኩ የሚያቀርቡ ልሂቅ“ ብለዋቸዋል፡፡ የአሜሪካ የማህበረሰብ ጥናት/American Sociological Review እንዲህ የሚል አስተያየት ሰጥቶ ነበር፣ “ሌቪን በጣም ጥንታዊ የሆነውን የምሁርነት ተግባር ማለትም ብልህነትን በተላበሰ መልኩ በእያንዳንዱ ቀን ጉዳይ እና ድብቅ ወደሆነው ዘላለማዊ እውቀት ሊወስደን ወደሚችል መንገድ ይመሩናል፡፡“
በእርግጥ የፕሮፌሰር ሌቪን ምሁርነት ሰፊ የሆነ የማህበራዊ ሳይንስ ህልዮት እና ትንተናን ያካተተ ነው፡፡ የዘመናዊ ማህበራዊ ሳይንስ መስራች አባት በሆኑት ላይ ማለትም በአጉስጤ ኮምጤ፣ ኢሚሌ ደርክሄይም፣ እና ማክስ ዌበርን የመሳሰሉ ልሂቃንን ጨምሮ ሲሰጧቸው የነበሯቸው ጥልቅ ትንታኔዎች ታላቅ ከበሬታን አጎናጽፈዋቸዋል፡፡ ሌቪን ማህበረሰብ ውስብስብ በሆነ መልኩ ድር የመሰረቱትን እና የማህበረሰብ ሳይንስ ጥናት ማካሄድ እና በማህበረሰቦች መካከል ያሉትን እና የሚከናወኑትን ሰፊ ታሪካዊ ጊዜዎች እና ባህላዊ ሁነቶችን መመርመር እንዳለባቸው ህልዮት ከቀመሩት ከጆርጅ ሲመል በፊት ታላቅ ስልጣን የነበራቸው ልሂቅ ነበሩ፡፡ የሲመል ስራዎች በሌላ በተጻራሪ መልኩ ከቆሙት ታላላቅ የማህበራዊ ሳይንስ ልሂቃን ማለትም የተፈጥሮ ሳይንስን የጥናት ዘዴዎች የሰው ልጆችን ባህላዊ ልማዶች፣ እሴቶች፣ ምልክቶች እና ማህበራዊ ሂደቶችን በሚመለከት ጥልቅ በሆነ መልኩ መጠናት እንዳለባቸው የክርክር ጭብጣቸውን ከሚያቀርቡት ከዌቨር የተለዩ ነበሩ፡፡ የሲመልስ ስራዎች በኢትዮጵያ ላይ የሚደረጉትን ምርምሮች እና ትንተናዎች በስፋት ግንዛቤን እንዲጨብጡ ያስቻላቸው እንደሆነ አምናለሁ፡፡
ከፕሮፌሰር ሌቪን ጋር ግንኙነት ማድረግ የጀመርነው እ.ኤ.አ በ2005 የተደረገውን ሀገር አቀፍ ምርጫ ተከትሎ ነበር፡፡ ከዚያ በፊት በኢትዮጵያ ፖለቲካ እና የሰብአዊ መብት አጠባበቅ ላይ ብዙም ተሳትፎ አልነበረኝም፡፡ በዚያው ዓመት በመለስ ትዕዛዝ 193 መሳሪያ ባልታጠቁ ንጹሀን ዜጎች ላይ በአነጣጥሮ ተኳሾች እልቂት መፈጸሙን እና ወደ 800 በሚጠጉ ወገኖች ላይ ደግሞ ከባድ የሆነ የአካል ጉዳት እንዲደርስ ማድረጋቸውን ተከትሎ ነው ወደ ኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ጥበቃ ዘው ብዬ የገባሁት፡፡
ከፕሮፌሰር ሌቪን ጋር ያደረግሁት የመጀመሪያው ግንኙነቴ መቼ እንደነበር በውል አላስታውስም፡፡ ሆኖም ግን እ.ኤ.አ በ2006 በበርካታ የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት አያያዝ ጉዳዮች ላይ ማለትም “የኢትዮጵያ ነጻነት፣ ዴሞክራሲ እና የሰብአዊ መብት ማስፋፋት የ2006 ድንጋጌ“ በሚል ርዕስ የአሜሪካ የምክር ቤት አባል ከነበሩት ከክሪስ ስሚዝ ጋር H.R 5680 ተብሎ ይጠራው በነበረው ሰነድ ጉዳይ ላይ የኢሜይል ልውውጥ እናደርግ በነበረበት ጊዜ ነው፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ለበርካታ ዓመታት በየጊዜው የኢሜይል ግንኙነት እናደርግ ነበር፡፡ ፕሮፌሰር ሌቪን የእኔ የሳምንታዊ ትችቴ የብዙ ጊዜ መደበኛ አንባቢዬ የነበሩ መሆናቸውን ስገልጽ ታላቅ ክብር ይሰማኛል፡፡ ትችቶቼን በጣም ያደንቋቸው ነበር፡፡ በእርግጥ ሁልጊዜም ቢሆን በሁሉም ነገሮች ላይ ስምምነት አልነበረንም፡፡ ሆኖም ግን ከእኔ ጋር ለምን እንደሚስማሙ እና እንደማይስማሙ ሁልጊዜ ደግነትን እና ትህትናን በተላበሰ መልኩ ይነግሩኝ ነበር፡፡ ስሜትን ቀስቃሽ በነበሩት ጽሑፎቼ ላይ የምጠቀምባቸውን የአጻጻፍ ስልቶች ግንዛቤ ነበራቸው፡፡ የአሜሪካን አርበኛ የነበሩትን እና በአምባገነኖች ላይ አደጋ በመጣል ነጻነትን እንዴት በፍቅር ማምጣት እንደሚቻል እና ህዝቦች በመጨረሻ በእነርሱ ላይ የሰብአዊ መብቶችን በመደፍጠጥ ግፍ ይሰሩ የነበሩትን አምባገነኖች ድል አድርገው የእራሳቸውን ዕጣ ፈንታ እንደሚወስኑ ያስተምሩ የነበሩትን ቶማስ ፔይኔን በምን ዓይነት ሁኔታ እመሳሰል እንደነበር ከጊዜ ወደ ጊዜ ይጠቁሙኝ ነበር፡፡ ፔይኔ ከእኔ የበለጠ ስር ነቀል እና ልማድን አጥብቆ የሚዋጋ ጽሑፍ ያወጡ እንደነበር ባምንም ንጽጽሩን በእራሱ እንደታላቅ ሙገሳ እቆጥረዋለሁ፡፡
እኔም እንደ እርሳቸው አጥብቄ የምይዝ ሰው ነኝ። እርሳቸው ጠቃሚ የሆኑትን የኢትዮጵያን ማህበረሰብ፣ ህዝብ እና ባህል እሴቶች ጠብቆ ለማቆየት ከፍተኛ የሆነ ምሁራዊ ተግባራትን ይፈጽሙ ስለነበር የታላቅ ክብር መገለጫ የሆነውን ፍታውራሪ (ዋነኞችን ተዋጊዎችን የሚያሰማራ መሪ) የሚለውን ስያሜ ሊይዙ ይገባቸዋል በማለት ነግሪያቸው ነበር፡፡ በነበረኝ ግንኙነት ሁሉ እስከመጨረሻዋ የኢሜይል ግንኙነት ድረስ እርሳቸውን ፊታውራሪ ሊበን ገብረ ኢትዮጵያ በማለት እጠራቸው ነበር፡፡ ወይም ደግሞ በአጭሩ “ፊት” እላቸው ነበር፡፡
ከበርካታ ዓመታት የኢሜል እና የስልክ ግንኙነት በኋላ እ.ኤ.አ በሕዳር 2012 መጨረሻ አካባቢ በፊላደልፊያ የአፍሪካ ጥናቶች ማህበር (አጥማ)/African Studies Association (ASA) ጉባኤ በሚካሄድበት ጊዜ ለመጀመርያ በግንባር አግኝቻቸው ነበር፡፡ በዚያ ጉባኤ ላይ አጥማ ለፕሮፈሰር ሌቪን ክብር ሲል “ሰም እና ወርቅን እንደገና መጎብኘት” በሚል ርዕስ የሙሉ ቀን ሲምፖዚየም አዘጋጅቶላቸው ነበር፡፡ በዚያ ሲምፖዚየም ላይ ለእኔ ታላቅ ክብር በመስጠት አንዱን የውይይት ክፍል በአወያይነት እንድመራላቸው እና በሌላም ጊዜ ጽሑፍ አቅራቢ እንድሆን ጋብዘውኝ ነበር፡፡ ይህ ሁኔታ ለእኔ እጅግ ልዩ የሆነ ክብር ነበር ምክንያቱም “ሰም እና ወርቅ” የተባለው በኢትዮጵያ ማህበረሰቦች ላይ የተደረገው የማህበረሰብ ጥናት እስከ አሁን ድረስ ተወዳዳሪ ያልተገኘለት ወጥ ስራ መሆኑን ስለማምን ነው፡፡ ይህ ልዩ የሆነ ጥልቀት እና ምጥቀት የተንጸባረቀበት ልዩ ስራ የፕሮፌሰር ዶናልድ ሌቪንን ልዩ ምሁራዊ ልቀት እና የአዕምሮ ብሩህነትን ቁልጭ አድርጎ የሚያመላክት ነው፡፡ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ከእኔ በላይ በርካታ ስራዎችን የሰሩትን ልሂቃን መጠየቅ ይችሉ ነበር ሆኖም ግን የተለያዩ የአካዳሚ እና የሞያ መሰረት ቢኖረኝም ቅሉ ለዚያ ስራ መርጠው ስለሰየሙኝ ደስታ ተሰምቶኛል፡፡ ከእርሳቸው በቀረበልኝ ጥያቄ ደስታ እና ክብር ተሰምቶኝ ስራውን ክልብ በመነጭ ደስታ አከናዉኝዋለሁ ፡፡ አብዛኞቹ የእርሳቸው የቀድሞ ተማሪዎች የነበሩት እጅግ በጣም ጥሩ የሆኑ ጽሑፎችን በዚያ ሲምፖዚየም ላይ ያቀረቡ ሲሆን የውይይት መድረኮቹ በጣም በሚስብ ሁኔታ ተሳትፎ ተካሂዶባቸዋል፡፡ ፕሮፌሰር ሌቪንም በጣም ደስ ብሏቸው ነበር፡፡
ፕሮፌሰር ሌቪን ከወጣቱ እና በጥረት ከተሞላው በስደት ከሚገኘው ኢትዮጵያዊ ጋዜጠኛ ከአበበ ገላው ጋር በኢትዮጵያ ሳቴላይት ቴሌቪዥን/ኢሳት አካሂደውት የነበረውን ሁሉን አቀፍ ቃለ መጠይቅ በርካታ ሰዎች ተመልክተውታል፡፡ የፕሮፌሰር ሌቪን የአማርኛን ቋንቋ አቀላጥፎ የመናገር ችሎታ እጅግ በጣም የሚያስደምም ነገር ነው፡፡ (እዚህ ጋ በመጫን የቪዲዮውን ምስል ይመልከቱ፡፡)
ሆኖም ግን ሌቪን እንዲሁ በደስታ ጊዜ የሚፈነድቁ በመከራ ጊዜ ደግሞ የሚተክዙ ኢትዮጵያን በማጥናት ላይ የነበሩ የማህበራዊ ሳይንስ ሳይንቲስት አልነበሩም፡፡ እኒህ ፕሮፌሰር በርካታ የሆኑ የአርበኝነት ተግባራትን በመፈጸም የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት እና ነጻነት በመጠበቅ ከፍተኛ ስራዎችን አከናውነዋል፡፡ ባለፈው ዓመት ኢትዮጵያ በአደዋ ጦርነት በኢጣልያኖች ላይ የተቀዳጀችውን አንጸባራቂ ድል በመዘከር ያ አንጸባራቂ ድል ለኢትዮጵያ እና ለቀሪዎቹ የአፍሪካ ሀገሮች ምን ማለት እንደሆነ ግልጽ አድርገዋል፡፡ (እዚህ ጋ በመጫን የቪዲዮውን ምስል ይመልከቱ፡፡)
እኔ እራሴ እንደ አካዳሚክ ሰው ሀሳብን የመግለጽ እና የአካዳሚክ ነጻነትን ለመጠበቅ ፕሮፌሰር ሌቪን የሚያደርጉትን መልካም ተግባር ከልብ አደንቃለሁ፡፡ እ.ኤ.አ በ2012 በቀድሞው የኢትዮጵያ አምባገነን መሪ በነበሩት በኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማርያም ተጽፎ በነበረው መጽሐፍ ላይ ህገወጥ በሆነ መልኩ ከባለቤቱ ፈቃድ ውጭ ተገልብጦ በድረገ ገጽ የግንኙነት መስመር መለቀቁን ተከትሎ ፕሮፌሰሩ ያንን እኩይ ድርጊት በቁጣ እና ባልተቆጠበ መልኩ እየተከታተሉ አውግዘው እንደነበር ይታወሳል፡፡ ያንን መጽሐፍ ገልብጠው በድረ ገጽ የግንኙነት መስመር በለቀቁት ሰዎች ላይ እንዲህ የሚል ጽሑፍ ጽፈው ነበር፣ “ህገ ወጥ፣ ከስነ ምግባር ውጭ የሆነ እና ያፈነገጠ፣ ብልህነት የጎደለው ድርጊትን ፈጽመዋል፡፡ በእኔ አስተሳሰብ ያ ድርጊት ኢትዮጵያዊ ያለመሆንን ያመላክታል፡፡“
ፕሮፌሰር ሌቪን በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ያለው የከፍተኛ ትምህርት ከባቢ አየር ለፖለቲካ ጣልቃገብነት ተጽዕኖ ተጋልጦ የመገኘቱ ሁኔታ በጣም ያሳስባቸው ነበር፡፡ ይህንኑ ጉዳይ በማስመልከት የተሰማቸውን ሀዘን እንዲህ በማለት ገልጸው ነበር፣
“ወታደራዊው አምባገነን መንግስት መወገዱን ተከትሎ በኢትዮጵያ ውስጥ እና ከኢትዮጵያ ውጭ ባሉ ዜጎች ላይ የመናገር እና የማሳተም ነጻነትን በመጎናጸፍ ልዩ የሆነ እድገትን ማየት ተችሎ ነበር፡፡ ይህ ሁኔታ ቢኖርም እንኳ ዋስትና በሌለው የመንግስት ችግር ፈጣሪነት ፈጣን በሆነ መልኩ በዩኒቨርስቲው ውስጥ ወደ አርባ የሚሆኑ ከፍተኛ ልምድ ያላቸውን እና በዩኒቨርስቲው ልዩ ልዩ ፋኩልቲዎች ውስጥ ከፍተኛ የስራ ብቃት ያላቸውን ምርጥ የዩኒቨርስቲ መምህራን መርጦ እንዲባረሩ አደረገ፡፡ የተማሪዎች ቅበላ እና የየፋኩልቲዎችን ዓለም አቀፍ መስፈርት ባስጠበቀ መልኩ እንዳለ ይዞ መጓዝ እስከ አሁንም ድረስ የዩኒቨርስቲው ታላቅ ፈተና ሆኖ ቀጥሏል፡፡ ከፍተኛ ጥራት ያለው ዩኒቨርስቲ ምን ያህል በቋፍ ላይ ያለ እና ለአደጋ የተጋለጠ እንደሆነ መንግስት መገንዘብ ተስኖታል፡፡”
ፕሮፌሰር ሌቪን በኢትዮጵያ ለአካዳሚክ ነጻነት ለረዥም ጊዜ ተሟጋች እና ካላቸው ጽናት ንቅንቅ የማይሉ ምርጥ ልሂቅ ነበሩ፡፡ እ.ኤ.አ በ1958 በቀዳማዊ አጼ ኃይለ ስላሴ ዩኒቨርስቲ የተጠባባቂ ምክትል ፕሬዚዳንቱ የሀሮልድ በንትለይ እረዳት በነበሩበት ጊዜ የሚከተለውን ምልከታ አድርገው ነበር፣
የቀዳማዊ አጼ ኃይለ ስላሴ ዩኒቨርስቲ ፕሮጀክት መሰረቱን አሁን ባለበት ቦታ ላይ የማደላደል ዕድሉን ከማግኘቱ በፊት አሁን በህይወት የሌሉትን ንጉስ በመፈንቀል መንግስት ከስልጣናቸው ለማስወገድ በተደረገ ፍልሚያ አዲስ አበባ በአደጋ ላይ ወድቃ ነበር፡፡ መፈንቅለ መንግስቱን ከሚያካሂዱት ሰዎች መካከል አንዱ ለሆኑት ለገርማሜ ንዋይ ጓደኛ እንደመሆኔ መጠን በመንግስት የጸጥታ ኃይሎች በመማረክ ከመገደሉ በፊት ከእርሱ ጋር ለመነጋገር የመጨረሻው ሰው ነበርኩ፡፡
የገርማሜ እንዲህ የሚሉት የመጨረሻ የመሰነባበቻ ንግግሮቹ ቀልቤን እንደሳቡት ቀርተዋል፡ ‘ዶን አደራህን የእኛን ታሪክ ለዓለም ህዝብ ሁሉ ተናገር፡፡ ብንሸነፍ እና ብንገደልም እንኳ በዚህች በተጭበረበረች መሬት ላይ ቢያንስ ጥቂት የእውነታ ቃላት ሊነገሩ ይችሉ ይሆናል፡፡’ ከጥቂት ወራት በኋላ ገርማሜ የነገረኝን እውነታ እንደማስረጃ ይዠ አንድ ጽሁፍ ባወጣሁበት ጊዜ ንጉሱ በዚህ ጽሁፍ በመቆጣት እኔን በቁጥጥር ስር አውሎ ወደ እስር ቤት እንዲያስገባኝ ለዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ መንግስት ጥያቄ አቀረቡ፡፡ ሆኖም ግን በዚያን ጊዜ የዩኒቨርስቲው ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት የነበሩት በንትለይ ለዘላለም ሲታወስ በሚኖረው የክርክር ጭብጣቸው ንጉሱ እንዲዚህ ያለ ነገር ከማድረግ እንዲቆጠቡ አጽንኦ በመስጠት እንዲህ የሚል የማሳመኛ ንግግር አድርገው ነበር፣ ‘የተከበሩ ጃንሆይ‘ በማለት እንዲህ የሚል ተማጽዕኖ አቅርበው ነበር፣ ‘እስቲ ለትንሽ ጊዜ እራስዎን የኢትዮጵያ መንግስት ዋና ኃላፊ እንዳልሆኑ አድርገው ያስቡ ሆኖም ግን እንደዚህ ላለው አዲሱ ዩኒቨርስቲ ቻንስለር/ኃላፊ አድርገው ያስቡ፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና እንዲኖረው ይፈልጋሉ፡፡ ለዚያም የአካዳሚክ ነጻነት ሊሰጠው ይገባል፡፡ ይህንን ዩኒቨርስቲ ተመልሶ እንዲገነባው ዶ/ር ሌቪንን ከመጋበዝ ውጭ ሌላ የተሻለ ምን ሀሳብ ሊኖርዎት ይችላል?”
ያ ንግግር ሰርቷል፡፡ በጣም አሰቸጋሪ በሆነ መልኩ ወሳኝ እና ለንጉሱ አስፈሪ የሆነ ጽሁፍ ብጽፍም ለዚህ ዩኒቨርስቲ ደረጃውን መጠበቅ እና ዓለም አቀፍ እውቅናን እንዲያገኝ ከተፈለገ የምርምር፣ የንግግር እና የህትመት ነጻነት ዋስትናን መስጠት አስፈላጊ እንደሆነ ንጉሱ ተገነዘቡ፡፡ ስለሆነም በታላቅ ክብር እና ለጋስነት የተከበሩት ማጀስቲ እኔ ተመልሸ እንድመጣ የሚጋብዘውን ሀሳብ አጸደቁት…
እንዲህ የሚል ማስጠንቀቂያ ሰጡ፡
እውነታው ፍርጥርጥ ተደርጎ ሲታይ በአሁኑ ወቅት በስልጣን ላይ ያሉት ከምንጊዜውም በላይ ከምንም ነገር በላይ ነጻ የሆነ እና ለእውነት ግልጽ የሆነ ነገር ማግኘትን ይፈልጋሉ፡፡ እንደዚህ ዓይነቶቹ ድምዳሜዎች እና የምርምር ሂደቶች በጊዜ ሂደት በስልጣን ላይ ባሉት ሰዎች ላይ ምቾትን የሚነሱ ነገሮችን ሊያመጡ እንደሚችሉ ቢታወቅም እንደዚሁም ምንም ሊታሰቡ በማይችሉ በርካታ ውስብስብ ለውጦች የተከበብን ብንሆንም ነጻ ምርምርን እና ድምዳሜን መስጠት ለእነዚህ በስልጣን ላይ ላሉት ጠቀሜታ አለው፡፡ ይህንን ሳያደርጉ መቅረት በከፍተኛ ድንቁርና እና በመረጃ ላይ ያልተመሰረተ ፍርድ በመስጠት ከፍተኛ ለሆነ እልቂት ይዳርጋል…
ይህንን ልዩ የሀዘን መግለጫ እየጻፍኩ ባለሁበት ወቅት ጥቂት ጸጸቶች አሉብኝ ማለት ይኖርብኛል፡፡ ፕሮፌሰር ሌቪን የእኛን እውቅና እና አድናቆት መቀበል የነበረባቸው ገና በህይወት ሳሉ ነበር የሚል እምነት አለኝ፡፡ ፕሮፌሰር ሌቪን በኢትዮጵያ ማህበረሰብ እና ባህል ላይ በጻፉት አስደናቂ ምሁራዊ ስራ የኢትዮጵያ ህዝብ በሙሉ እውቅና ሊሰጣቸው ይገባ ነበር፡፡ በተለይም ደግሞ በምርምር ስራዎቻቸው ታላቅ ፋይዳን ላስገኙት ልሂቅ በኢትዮጵያ ልሂቃን ዘንድ ለስራቸው ታላቅ እውቅናን መስጠት ተገቢ ይሆን ነበር፡፡ እንደዚሁም ደግሞ አንድ ልዩ የሆነ የወጣት ሲቪክ ድርጅት እንዲመሰረት ባደረጉት ስራቸው እውቅና ሊሰጣቸው ይገባ ነበር፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ ለግማሽ ምዕተ ዓመት ለኢትዮጵያ እና ለህዝቦቿ ላበረከቱት አገልግሎት በሀገር አቀፍ ደረጃ ይፋ እውቅና ሊሰጣቸው ይገባ ነበር፡፡
ከመቀበል ይልቅ መስጠት የሞራል ስብዕና መርህ ነው፡፡ ፕሮፌሰር ሌቪን ለኢትዮጵያ በርካታ ነገርችን ሰጥተዋል፡፡ እንደ እርሳቸው ሌሎች ኢትዮጵያዊ ያልሆኑ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ለኢትዮጵያ በነጻ ሰጥተዋል፡፡ አንድ በአንደ እያሉ ይህችን ዓለም እየተዋት ሲሰናበቱ ማየቱ በጣም የሚያም ነገር ነው፡፡ እናም የልሂቃኑን ከባቢ አይር ስቃኘው እና የምሁራኑን አድማስ በመመልከት የእነዚህን ልሂቃን ጥንካሬ፣ ከፍተኛ ጥረት እና ተነሳሽነት የሚመጥን እውቅና ሳይሰጥ ሲቀር ደስታ ይርቀኛል ብርታቱም ያንሰኛል፡፡ በተፈጥሮ ህግ ትዕዛዝ የሚሄዱ ቢሆንም ቅሉ የእነርሱ ብቸኛው ሀሳብ እና ያበረከቱት አስተዋጽኦ ዘላለማዊ ሆኖ ከእኛ ጋር አብሮን ይኖራል፡፡ የኢትዮጵያ ወጣት ልሂቃን የእነዚህን አንጋፋ ልሂቃን ስራዎች እና የምሁራዊ ክህሎታቸውን ዓርማ አድርጎ በማንሳት ለቀጣዩ ትውልድ ፋይዳ ያለው ስራ ይሰራሉ የሚል እምነት አለኝ፡፡
የምሁር የመጨረሻ ትሩፋት፡ ንግግር (ዉይይት) አይደለም ክርክር
የፕሮፌሰር ሌቪን ትሩፋት ምንድን ነው ሊባል ይችላል? እጅግ በጣም ጠቃሚ እና እንከንየለሽ ምሁር ነበሩ፣ እናም እኔ እንደማምነው የልሂቅነታቸው ትሩፋት በአጭሩ እና ግልጽ በሆነ መልኩ ዶንሌቪን.ኮም/donelevine.com በሚለው በእራሳቸው ድረ ገጽ እንዲህ በሚል ተጽፎ ይገኛል፡
እነዚህን አንዱን ወይም ደግሞ ከዚያ በላይ የሆኑትን ንግግሮች እንድትቀላቀሉ እጋብዛችኋለሁ፡ እያንዳንዱ ትውልድ በምን ዓይነት መንገድ ጠንካራ፣ ብቁ እና ብልህ የሰው ዘር እና ዜጋ እንደሚሆን ለማገዝ በበርካታ ጥያቄዎች ላይ ትኩረት አድርጎ መስራት፣ ስለሰው ተፈጥሯዊ ባህሪ እና ስለማህበራዊ ስርዓት ሃሳቦች በጥሩ ሁኔታ ከተቀመሩት ህልዮቶች መካከል ምርምር በማድረግ የተሻሉትን በመምረጥ እንዲተገበሩ ማድረግ፣ በሁለቱ ሚሊኔሞች ስልጣኔዎች ላይ ትኩረት አድርጎ መስራት እና ከዘመናዊዎቹ መካከል ውስብስቦችን እና አስቸጋሪዎቹን ማስወገድ፣ የሰው ልጅ አካላት በተቀናጀ መልኩ ስራቸውን ለማቀላጠፍ ያግዛል የተባለውን የውኃ ፍሰት ግኝት ያገኘውን የኢስያ ጌታ አስተምህሮዎች እንዳለ መውሰድ፡፡ እናም በመንገዱ ላይ እነዚህን እና ሌሎችንም ንግግሮች ይዞ ለማቆየት ውጤተማ በሆነ መንገድ ሀሳቦችን መለዋወጥ…
ታላላቅ መምህራን እና ልሂቃን በፍጹም አይሞቱም እላለሁ፣ በጸጥታ፣ ያለ እረፍትና ያለማቋረጥ በንግግሮች ላይ ክርክር ከሚፈጥሩ ቀጣይ ወጣት ትውልዶች አእምሮ ላይ ይደበዝዙ ካልሆነ በስተቀር ፈጽሞ ሊሞቱ አይችሉም፡፡
ክርክር፡ እንግዲህ በእርግጠኝነት ፊታውራሪ ሊበን ገብረ ኢትዮጵያን ለማክበር ያሰብኩት በዚህ ዓይነት ሁኔታ ነው፡፡ ወይም ደግሞ በህይወት በነበሩበት ጊዜ እንደምላቸው በአጭሩ እና በቀላሉ “ፊት” ብዬ በማቆለማመጥ ነው፡፡
የማይሳነው አምላክ የጀግናውን የኢትዮጵያ ባለውለታ ልሂቅ ነብስ ከጻዲቁ ከአብረሃም ጎን በገነት ያኑርልን!
ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!
ሚያዝያ 6 ቀን 2007 ዓ.ም