ኢትዮጵያ፡ በገንዘብ ዕጦት ምክንያት የተገደበ ግደብ? (ፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማርያም)

ከፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማርያም
ትርጉም በነጻነት ለሀገሬ

ከላይ ለዚህ ትችት የተሰጠው ርዕስ እንደሚያመለክተው በአንድ በኩል በገንዘብ እጦት ችግር ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ ለማድረግ ባለመቻሉ ምክንያት የተገደበ ወይም ደግሞ እንደ ጅብራ ተገትሮ የቀረ ግድብ የሚል ትርጉምን የሚይዝ ሲሆን ሌላው ትርጉሙ ደግሞ ከፍተኛ በሆነ የገንዘብ እጦት ችግር ምክንያት የተመደበለትን ገንዘብ በማብቃቃት ለመስራት በማሰብ ደረጃቸውን ባልጠበቁ ግብዓቶች በመጠቀም ለርካሽ የፖለቲካ ፕሮፓጋንዳ ፍጆታ ሲባል እንደምንም ተውገርግሮ የተሰራ ግድብ ብዙም ዘለቄታ ሳይኖረው በአንድ ወቅት አውዳሚ በሆነ መልኩ ተንዶና ተደርምሶ የህዝብ ሀብት እና ጉልበት መና ሆኖ ይቀራል የሚል ፍሬ ሀሳብን የያዘ ነው፡፡Ethiopia is building a huge dam in the Nile Valley…

እ.ኤ.አ መጋቢት 2013 “በዓባይ ወንዝ ላይ ያንዣበበ የጦርነት አደጋ ጉምጉምታ“ በሚል ርዕስ ባቀረብኩት ትችት እንዲህ የሚል የክርክር ጭብጥ አቅርቤ ነበር፡

… ታላቁ የኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብ (ታኢሕግ)/Grand Ethiopian Renaissance Dam (GERD) በ5 ቢሊዮን ዶላር ግንባታ ስራው ተጠናቅቆ በእርግጠኝነት እውን የመሆን ያለመሆኑ ጉዳይ የክፍለ ዘመኑ ዋና ጥያቄ ሆኖ ቀርቧል፡፡ ግብጽ የብዙሀን ሀገሮች የልማት እና የገንዘብ አበዳሪ ድርጅቶች እና ባንኮች ለዚህ ከአቅሙ በላይ በእጅጉ ለተለጠጠ የግድብ ስራ ፕሮጀክት ብድርም ሆነ እርዳታ እንዳይሰጡ አጠንክራ በመስራቷ እና ስኬታማ በመሆኗ ምክንያት በኢትዮጵያ ያለው አገዛዝ ብድሩ እና ልመናው እንዳከተመለት በመገንዘብ ያለበቂ ጥናት በድፍረት እና በእብሪተኝነት ጠቅላላ የግድብ ግንባታ የፕሮጀክቱን ወጭ እራሴ እሸፍነዋለሁ በማለት ዘሎ ገብቶበታል፡፡ ሆኖም ግን በትክክል ይታሰብ ከተባለ የአፍሪካ የግድቦች ሁሉ ቁንጮ የተባለውን ይህንን ግዙፍ ግድብ ገዥው አካል በእራሱ አቅም ግንባታውን አጠናቅቆ እውን ሊያደርገው ይችላልን?….በአሁኑ ጊዜ ገዥው አካል ማጣፊያው ሲያጥረው እና ቀደም ሲል ሲደሰኮር የነበረው ሁሉ ባዶ መሆኑ ሲረጋገጥ በኑሮ ውድነት እና በችጋር ምክንያት የዕለት ጉርሱን ማሟላት ተስኖት በመሰቃዬት ላይ የሚገኘውን የኢትዮጵያን ህዝብ በድህነት ጎኑ በመግባት በሎተሪ መልክ (ቤት፣ መኪና፣ ቴሌቪዥን፣ ኮምፒውተር ወዘተ) ታገኛላችሁ፣ ስለዚህ ከተንቃሳቃሽ ስልካችሁ ሂሳብ ይቆረጣል በሚል መንግስታዊ የቁማር ጨዋታውን በስፋት ቀጥሎበት ይገኛል፡፡ ይህንንም በድህነት የተቆራመደ ህዝብ እንደ ገንዘብ ማግኛ ስልት በመቁጠር ዕለት በዕለት፣ ሰዓት በሰዓት በተንቀሳቃሽ ስልኮቻቸው ገንዘብ ላኩ እየተባሉ ዜጎች የስልኮቻቸው ባለቤቶች መሆናቸውን እስኪጠራጠሩ ድረስ ስልኮቻቸውን በማጣበብ እና በማደናቆር ላይ ይገኛል፡፡

ወደተነሳሁበት ጭብጥ ስመለስ በዚያ ባቀረብኩት ትችቴ ላይ በዓለም ከሚገኙ ታላላቅ ግድቦች መካከል በ8ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠ ነው እየተባለ ሌት ከቀን ባዶ ፕሮፓጋንዳ ስለሚነዛለት ፕሮጀክት እንዲህ የሚሉ ተራ የሆኑ ጥያቄዎችን በማንሳት ጥያቄ አቅርቤ ነበር፡

1ኛ) በዓለም ከሚገኙ ሀገሮች በድህነት ከመጫረሻዎቹ ሀገሮች በሁለተኛ ደረጃ ላይ ከተቀመጠች እና አብዛኛው ሕዝቧም በቀን ከአንድ ዶላር በታች የነፍስ ወከፍ ገቢ ከሚያገኝባት ሀገር ህዝቦች ላይ እ.ኤ.አ በ2015 አምስት ቢሊዮን ዶላር ማሰባሰብ ይቻላልን?

2ኛ) ከአፍሪካ የዓለም አቀፍ እርዳታን በመቀበል ከፍተኛውን እና የመጀመሪያውን ደረጃ ከያዘች ሀገር ሕዝብ ለግድብ ግንባታ ተብሎ ብዙ ቢሊዮን ዶላር መሰብሰብ ይቻላልን?

3ኛ) እ.ኤ.አ ከ2000 – 2009 ባሉት ዓመታት ውስጥ በህገወጥ መልክ 11.7 ቢሊዮን ዶላር የሕዝብ ገንዘብ በጠራራ ጸሐይ እየተዘረፈ ምዝበራ በተፈጸመባት ሀገር 5 ቢሊዮን ዶላር (ያውም ለስራ ማስኬጃ ለሚውለው ገንዘብ ከጊዜው የገበያ ዋጋ ጋር ተመሳክሮ ስሌት ያልተሰራለት) የሚያወጣ ግዙፍ ግድብ መገንባት ይቻላልን?

4ኛ) የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት/International Monetary Fund እ.ኤ.አ ሰኔ 2012 ባወጣው መግለጫ መሰረት “ገቢ ዕቃዎችን ወደ ሀገር ውስጥ ለማስገባት የሚያስችል የውጭ ምንዛሬ ክምችቷ ከሁለት ወር በላይ ሊያቆይ የሚያስችል አቅም የሌላት ሀገር“ መሆኗን ግልጽ አድርጎ እያለ በምን መስፈርት እና መለኪያ ነው በአፍሪካ ታሪክ በታላቅነቱ የመጀመሪያ የሆነውን ግድብ በእርግጠኝነት በእራሷ ወጭ ለመገንባት የምትችለው?

5ኛ) የውጭ ብድሯ እ.ኤ.አ በ2012 ከ12 ቢሊዮን ዶላር በላይ መሆኑ የተረጋገጠላት ሀገር ከሰማይ መና ካልወረደ በስተቀር በምን ዓይነት ሁኔታ ነው የ5 ቢሊዮን ዶላር የግድብ ፕሮጀክት ልትገነባ የምትችለው?

ትችቴን ባቀረብኩበት በዚያን ጊዜ እራሱን “የናይል ተፋሰስ ሀገሮች ተመራማሪ“ እያለ ይጠራ የነበረ አንድ ወገኔ “በአሁኑ ጊዜ ዕርቃናቸውን የቀሩት ዕንፈኛ የዲያስፖራ አባላት” በማለት እና የእኔን በተጨባጭ መረጃዎች ላይ እና በምክንያታዊነት ላይ ተመስርተው የቀረቡትን ትችቶቼን የተዛቡ እንደሆኑ አድርጎ በመገናኛ ብዙሀን ማቅረቡ እና “ይህ ትችት አስፈላጊ የሆነውን የግድቡን ገንዘብ በምን ዓይነት ሁኔታ ማሰባሰብ እንደሚቻል እየቀረበ እና እያሳሰበው ያለው አለማየሁ (Al Mariam)ብቸኛ ስሜቱ ነው፡፡ ሆኖም ግን የግድቡን ተፈጻሚነት በሚመለከት በእራሱ የግል ፍላጎት ላይ የተጠመደ በመሆኑ ምክንያት ዓላማውን ስቷል፡፡” (አጽንኦ ተደርጓል፡፡)

እ.ኤ.አ ሚያዝያ 2014 “በኢትዮጵያ የቅንጦት ግድብ መገንባት” በሚል ርዕስ ባቀረብኩት ትችት ላይ “ታላቁ የኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብ” (ታኢሕግ)/Grand Ethiopian Renaissance Dam (GERD) አየተባለ የሚጠራው ማንም በግልጽ ያልተወያየበት እና ጉዳዩ በአጽንኦ ያልታዬ እንዲሁም የግንባታ ወጭውም እጅግ በጣም ውድ የሆነ ነው በማለት የክርክር ጭብጤን በማስረገጥ አቅርቤ ነበር፡፡ መለስ ከእርሱ በፊት እንደነበሩት ሌሎች የአፍሪካ አምባገነን መሪዎች ሁሉ የታላቅነት ቅዠት በአዕምሮው ውስጥ እንዳለ ግልጽ አድርጌ ነበር፡፡ እንደሌሎቹ የእርሱ ተመሳሳይ አጋር የአፍሪካ አምባገነኖች ሁሉ ስሙ እንዳይሞት እና የእርሱን ታላቅነት አጉልቶ የሚያሳይ “የአፍሪካ ትልቅ ሰው” ሊያሰኝ የሚያስችል ታላቅ የግድብ ፕሮጀክት ለመገንባት አሰበ… ታኢሕግ/GERD እየተባለ ከመጠን በላይ ገዝፎ የሚጠራው የግድብ ፕሮጀክት በዋናነት የመለስን ህልፈት ተከትሎ እርሱ እና ግብረአበሮቹ በሀገር ሉዓላዊነት እና በኢትዮጵያ ህዝቦች ላይ የፈጸሙትን ክህደት፣ የዘር ማጥፋት እና ሌሎች በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ የፈጸሟቸው ወንጀሎች እንዳይታወቁ ለማደብዘዝ ሲባል ስሙን ከልክ ባለፈ መልኩ አጉልተው በማውጣት ህዝቡ ግብር በሚከፍልበት መገናኛ ብዙሀን ሌት ከቀን እንደ በቀቀን ሲደግሙ እና ሲደጋግሙ ይደመጣሉ… ሆኖም ግን ይህ የገዥው አካል ዕኩይ ድርጊት ለኢትዮጵያ ሕዝብ “መርፌ ወስዶ ማረሻ ቢተኩ ልብ አይሆንም” ከማለት ውጭ የሚፈይደው ነገር አይኖርም፡፡

እንደዚሁም ሁሉ በዚያው አቅርቤው በነበረው ትችት “የተዛቡ ትችቶች” በማለት ሌላኛው በቁጣ የገነፈለ ትችት አቅራቢ ደግሞ ከእኔ ትችት ጋር ምንም ዓይነት ስምምነት እንደሌለው መናገር አልበቃ ብሎት አንድታዉም “በሀገር ላይ ሊታሰብ የማይችል የፖለቲካ ክህደት ወንጀል” እና የሞራል ስብዕና ብልሹነት እንደፈጸምኩ አድርጎ እንዲህ በማለት ከሶኝ ነበር፡

… እንደ አንድ የተለዬ ቡድን አባል ሆኖ ሀሳብን መግለጽ እና መጻፍ ያልተለመደ ነገር አይደለም፡፡ ሆኖም ግን በዓለማየሁ ጽሁፍ ላይ እንደታዬው እና ከላይ ለመግለጽ እንደተሞከረው ዓይነት ከፍተኛ የሆነ የሞራል ስብዕና ብልሹነት የተንጸባረቀበትና ታላቅ አሉታዊ ውጤትን ሊያስከትል የሚችል አገላለጽ በምንም ዓይነት መልኩ ይቅርታ ሊደረግለት የሚገባ ጉዳይ አይደለም፡፡ እናም በመጨረሻ ዓለማየሁ ሊታሰብ የማይገባውን ድርጊት ፈጽሟል፡ ከግብጽ ጋር በመወገን በኢትዮጵያ ላይ የሀገር ክህደት ወንጀል ፈጽሟል፡፡ እናም ታላቁን የኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ እጅግ በጣም ከፍተኛ ወጭ የሚወጣበት ውድ እና በሰከነ መልኩ ታስቦበት ያልተዘጋጀ ፕሮጀክት በማለት በድፍረት ተናግሯል… ዓለማየሁ ይህንን ትችት ከመጻፉ እና ከአይአርኤን/IRN ጋር ሆኖ ከማጨብጨቡ እና የኢትዮጵያን መንግስት ጥላሸት ከመቀባቱ እንዲሁም ኢትዮጵያ በእራሷ ወንዝ ላይ ያላትን ሉዓላዊነት ሊገድብ የሚችል ትችት ከማቅረቡ በፊት ጥንቃቄ ሊያደርግባቸው የሚገቡ በርካታ ነገሮች ሊኖሩ ይገባ ነበር፡፡ (አጽንኦ ተጨምሯል፡፡)

ባለፈው ሳምንት ፍራንስ 24 ቲቪ/FRANCE 24 TV የተባለው የዜና ወኪል በኢትዮጵያ የዓባይ ግድብ ፕሮጀክት በገንዘብ እጥረት ምክንያት ስራው ተጓትቷል የሚል ዘገባ ለቋል፡፡ ዘገባው እንዲህ የሚል ሀተታ አስነብቧል፡

ኢትዮጵያ በናይል/ዓባይ ሸለቆ ላይ ታላቅ ግድብ በመግንባት ላይ ትገኛለች…ዓለም አቀፍ ለጋሽ እና አበዳሪ ድርጅቶች ለግድቡ ግንባታ ሊውል የሚችል የገንዘብ ብድር የማይሰጡት ለምንድን ነው?… የፕሮጅክቱ ግንባታ በዕቅድ ከተያዘለት የጊዜ መርሀ ግብር ለበርካታ ዓመታት ወደ ኋላ ተጎትቷል፡፡ ታላቁ እንቅፋት ሆኖ የተገኘው ኢትዮጵያ የፕሮጀክቱን ጠቅላላ ወጭ በእራሷ አቅም እሸፍናለሁ ማለቷ ነው፡፡ ይህ ፕሮጀክት በዓለም አቀፉ መድረክ አወዛጋቢ መሆኑ ግልጽ ከሆነ በኋላ ማንም ዓለም አቀፋዊ ተቋም ይህንን ፕሮጀክት ለመደገፍ አልፈለገም… ግብጾች ስለግድቡ ያላቸው ስጋት እ.ኤ.አ በ2013 በሁለቱ ሀገሮች በሚኒስትሮች ደረጃ ተካሂዶ በነበረው እና በፕሬዚዳንት መሀመድ ሙርሲ ሊቀመንበርነት በተመራው ስብሰባ ላይ [በቪዲዮ ምስል እንደሚታየው አንድ የግብጽ ሚኒስትር በስብሰባው ላይ እንዲህ የሚል ንግግር ያሰሙ ነበር] ‘ሁሉም አማራጮች በሁላችንም እጅ በጋራ የሚገኙ መሆናቸውን ድምጼን ከፍ አድርጌ እና ግልጽ በሆነ መልኩ እናገራለሁ፡፡ ይህ ሁኔታ ዲፕሎማሲያዊ በሆነ መልኩ እልባት የማያገኝ እና የማይቋጭ ከሆነ ወደ ዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት እንውስደዋለን፣ ይህም የማይሳካና ውጤት የማያስገኝ ከሆነ ውኃ በህይወት የመኖር ወይም ያለመኖር የሞት ጉዳይ በመሆኑ ምክንያት ህይወታችንን ለማዳን ስንል ማንም ሰው እንደሚገምተው እና እንደሚያስበው ሁሉ የውኃ ደህንነታችንን ለመጠበቅ እንገደዳለን…[ሌላው የግብጽ ሚኒስትር በዚሁ በሚኒስትሮች ስብሰባ ላይ እንዲህ የሚል ንግግር ሲያሰሙ በቪዲዮ የተቀረጸው ምስል ያሳያል] ‘እነዚህ ሁሉ እያደረግናቸው ያሉት ሁሉም ጥረቶች ስኬታማ ካልሆኑ እና ከወደቁ የግብጽን ደህንነት ከአደጋ ላይ የሚጥለውን ማንኛውንም ነገር ለማውደም ሁሉንም ያለንን እውቀት እና ክህሎት ሁሉ እንጠቀማለን…ያ ግንባታ ይህ ግድብ በግብጽ ላይ ጦርነትን ከማወጅ እኩል ነው…‘ (አጽንኦ ተጨምሮበታል፡፡)

ባለፈው ሳምንት እራሱን ህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ (ህወሀት) እያለ የሚጠራው ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ በህዝብ ግንኙነት ታዛዥ ሎሌው አማካይነት በዓለም አቀፉ ብዙሀን መገናኛ ዘዴዎች በመጠቀም አሁንም ደግሞ ወጭው እጅግ በጣም ከፍተኛ የሆነ “የኢትዮጵያ የነዳጅ ዘይት ማጣሪያ ኩባንያ በ10 ዓመታት ጊዜ ውስጥ በ5 ቢሊዮን ዶላር እንገነባለን“ የሚል ትረካ አሰራጭቷል፡፡ እንደዚያ ዘገባ ከሆነ (ተርት ተርት ነው አላልኩም)፡

የኢትዮጵያ ዋና የግል የነዳጅ ዘይት ኩባንያ የሆነው ድርጅት በኢትዮጵያ እያደገ የመጣውን የተጣራ የነዳጅ ዘይት ፍላጎት ለማርካት እና ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት በማስመዝገብ ላይ ላለ ቀጣና በአስር ዓመታት ጊዜ ውስጥ እውን ለማድረግ 5 ቢሊዮን ዶላር የሚፈጅ የነዳጅ ማጣሪ ኩባንያ ለማቋቋም ዕቅድ ነድፏል…የብሔራዊ ነዳጅ ዘይት ዋና ስራ አስፈጻሚ የሆኑት ታደሰ ጥላሁን ይህንን ጉዳይ በማስመልከት በቀን ከ200,000 እስከ 300,000 በርሜል የሚያጣራ የነዳጅ ዘይት ማጣሪያ ፋብሪካ ለማቋቋም የሚያስችለው የመጨረሻው ውሳኔ ገና በመጠበቅ ላይ ነበር ብለዋል፡፡ ይህ የማይናወጥ ጽኑ ዕቅድ ነው ምክንያቱም በኢትዮጵያ የነዳጅ ዘይት ፍላጎት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣ በመሆኑ እና በግምት በየዓመቱ 10 በመቶ በማደግ በዓመት 300 ሚሊዮን ኪዩቢክ ሜትር የሆነው ዓመታዊ ፍጆታ በሚቀጥሉት አስር ዓመታት ጊዜ ውስጥ በእጥፍ እንደሚጨምር በመገመት ነው… የብሔራዊ የነዳጅ ዘይት ኩባንያ ባለአክሲዮኖች በግንባታ፣ በወርቅ ማዕድን ስራ፣ በሆቴሎች እና በኃይል አቅርቦት ዘርፎች ላይ ከ10 ቢሊዮን ዶላር በላይ መዋዕ ንዋይ ያፈሰሱትን የሳውዲ ቢሊየነር የሆኑትን መሀመድ ሁሴን አል አሙዲንን ያካትታል…

እ.ኤ.አ መጋቢት 2011 የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ 5 ቢሊዮን ዶላር ይፈጃል የተባለውን ታኢሕግ/GERD እየተባለ የሚጠራውን ግድብ ይፋ አደረገ፡፡

እ.ኤ.አ መጋቢት 2015 የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ 5 ቢሊዮን ዶላር ይፈጃል የተባለውን የነዳጅ ዘይት ማጣሪያ ፋብሪካ ባለ 10 ቢሊዮን ዶለር ባለቤት በሆኑት ቢሊየነር በአል አሙዲን እንደሚገነባ ይፋ አደረገ፡፡

ምን ዓይነት ግጥምጥሞሽ እንደሆነ የሚገርም ነው! ወይም ደግሞ የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ እንደዚህ ያሉትን ግዙፍ እና የፕሮጀክት ወጪያቸው በጣም ከፍተኛ የሆኑ ፕሮጀክቶችን ተውኔት በመጋቢት ወር ይፋ ማድረግ ስለሚወዱ ነውን?

ባለፈው ሳምንት ኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ግብጽ “የመርሆዎች ድንጋጌ” (ዴክላራሺን) በሚል ርዕስ “በዓባይ ተፋሰስ ሀገሮች መካከል የውኃ አጠቃቀም ስምምነት”ን በሚመለከት የተፈራረሙ መሆናቸውን የተለቀቀው የፕሬስ መግለጫ ይፋ አድርጓል፡፡

ታኢሕግ/GERD ለፖለቲካ ፕሮፓጋንዳ ፍጆታ ሲባል ወጭው እጅግ በጣም ውድ የሆነውን ፕሮጀክት ሊፒስትክ (የከንፈር ቀለም) መቀባት፣

ባለፉት ሁለት ዓመታት ቀደም ሲል ያቀረብኳቸው ትንተናዎች እና መደምደሚያዎች ወይም ደግሞ በታኢሕግ/GERD ላይ ተቃውሞ አቅርቧል በሚል ምሁራዊ አመክንዮ ሳይሆን ተራ የካድሬ ፕሮፓጋንዳነትን በተላበሰ መልኩ ጥላሸት የመቀባት የውንጀላ ክስ ቀርቦብኝ የነበረው ስህተቱ ከምን ላይ እንደሆነ ሊያሳምነኝ የሚችል ምንም ዓይነት ነገር አላየሁም፡፡ እውነታው ፍርጥ እና ፍርጥርጥ ብሎ ሲታይ ግን እ.ኤ.አ መጋቢት 2013 አቅርቤው በነበረው ትችቴ ላይ ምላሽ እንዲሰጥባቸው አንስቻቸው የነበሩት ገንዘብ ነክ ጥያቄዎች እስከ አሁንም ድርስ ምንም ዓይነት ምላሽ አላገኙም፡፡

እ.ኤ.አ ሚያዝያ 2013 የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ 32 በመቶ የሚሆነው የግድቡ የግንባታ ስራ ተጠናቅቋል በማለት መግለጫ ሰጥቷል፡፡ ከዚያ ወዲህ የግንባታ ፕሮጀክቱን አፈጻጸም በሚመለከት ምንም ዓይነት መግለጫጭ አልተሰጠም ነበር፡፡ ሆኖም ግን እንደ አንደ ይፋ የሆነ ዘገባ እ.ኤ.አ ጥቅምት 2014 የግድቡ ጠቅላላ የግንባታ አፈጻጸም ከ40 በመቶ በላይ የተጠናቀቀ መሆኑ ተመልክቷል፡፡

ቀደም ሲል አቅርቤው በነበረው ትችቴ ላይ ግልጽ እንዳደረግሁት ሁሉ ታኢሕግ/GERD የተባለውን የግድብ ፕሮጀክት እውናዊነት ሊገዳደሩ የሚችሉ በርካታ ተጨባጭነት ያላቸው ማስረጃዎች አሉ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ጥቂቶችን ለመጥቀስ ያህል፣

1ኛ) በዓለም ላይ እንዳሉት ታላላቅ ግድቦች ሁሉ እና በተለይም ደግሞ በአፍሪካ እንደሚገኙት ታላላቅ ግድቦች ሁሉ በተመሳሳይ መልኩ ከፍተኛ የሆነ የስራ ማስኬጃ ወጭ እንደጠየቁ እና ወደፊትም እንደሚጠይቁ እውነት ነው፣

2ኛ) እንደዚህ ያሉት ከፍተኛ የግድብ ፕሮክቶች ከተያዘላቸው የጊዜ መርሀ ግብር በላይ ረዥም የመጓተት ባህሪን የተላበሱ ሆነው የቆዩ እና ወደፊትም የሚጓተቱ ናቸው፣

3ኛ) ታኢሕግ/GERD ምንም ዓይነት ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ የማይሰጥ እና ወጭው እጅግ በጣም ውድ የሆነ እንዲሁም ከሀገሪቱ የገንዘብ አቅም በላይ የታሰበ ምባዊ አስተሳሰብ ነው፣

4ኛ) ታኢሕግ/GERD ከፍተኛ የሆነ የአካባቢያዊ ስነምህዳር ውድመትን ሊያስከትል የሚችል የቅንጦት ፕሮጀክት ነው፣

5ኛ) በእርግጠኝነት የሚገነባ የሚጠናቀቅ ቢሆንም እንኳ አስቸጋሪ በሆነ የጥገና ወጭ መሰረት በሚለገው መጠን ኃይል የማመንጨት አቅም እንደማይኖረው እና በተከሰተው የገንዘብ እጥረት ምክንያት ደረጃውን ባልጠበቀ የግንባታ ግብዓት የሚሰራ ከመሆኑ አንጻር በረዥም ጊዜ እይታ ሲቃኝ ደግሞ ግድቡ ለአደጋ የሚጋለጥ እና ለአሰቃቂ ውድመት የሚዳረግ ሆኖ ይገኛል፣

6ኛ) የታኢሕግ/GERD በቀጣናው ታላቅ ያለመረጋጋት መንስኤ ምንጭ ሊሆን ይችላል፡፡

ገና ከመጀመሪያው በዚህ ጉዳይ ላይ ባሉኝ የክርክር ጭብጦች አንዳንድ ወገኖቸ ሀገራዊ የአርበኝነት ስሜት የሌለኝ፣ ግብጽ የምትባለዋን ሀገር ለመርዳት የቆምኩ፣ የሀገር ክህደት የፈጸምኩ እርባና ያለው ነገር እንዳልሰራሁ፣ ወዘተ በሚል ውንጀላ ፈርጀውኛል፡፡ እኔ ለዚህ በአመክንዮ እና በምሁራዊ አስተሳሰብ ሳይሆን በግልብ እና በስሜታዊነት ላይ ለተመሰረተ ጥላሸት የመቀባት አባዜ እና የጭቃ ጅራፍን በማጮህ ከምሁራዊ አንደበት ሳይሆን ከተራ መሃይም ካድሬ የስርዓቱ አገልጋይ ሎሌነት ለሚሰነዘር ተራ ነገር ጉዳዬ አይደለም፡፡ ለዚህ ጉዳይ ምላሽ መስጠትም ጊዜ ከማባከን ያለፈ የሚፈይደው ነገር የለውም፡፡ ሆኖም ግን እኔ ባቀረብኳቸው ትንታኔዎች እና መደምደሚያዎች ላይ ተከሰተ ባሏቸው ህጸጾች ላይ አሳማኝ እና አስገዳጅ የሆኑ እውነታዎችን በማቅረብ ለማሳመን የሚሞክሩ ከሆነ ደስታየ ከፍ ያለ ይሆናል፣ እንዲያውም ከዚህም አልፎ ሊያሳምን የሚችል ነጥብ ማቅረብ ከቻሉ ሀሳቤን ለውጨ የእነርሱን ሀሳብ ለመያዝ ዝግጁ ነኝ፡፡ በእኔ ትችቶች ላይ በመርህ ላይ በመመስረት የሚቀርቡ ትችቶችን ለመቀበል እና ስህተቶቸን በአደባባይ በማመን ይቅርታ ለመጠየቅ ዝግጁ ነኝ፡፡ ከዚያ ውጭ ግን በዱልዱም አንደበት እና ለከርስ ሲባል እንዲህ ብሎ ተናገረ ለመባል በሚደረግ ተራ የቅጥፈት እና የድንቁርና ትነታኔ እራስን ከትዝብት ላይ ከመጣል ያለፈ የሚያመጣው ለውጥም ሆነ ፋይዳ የለውም፡፡

ስለእውነታዎች በግልጽ በአደባባይ እንነጋገር፣ ማስረጃዎችን እንመርምር፣

እስከ አሁን ድረስ የኢከኖሚያዊ አዋጭነታቸው በጣም ዝርዝር እና አጠቃላይ የሆኑ ሳይንሳዊ ጥናት ከታካሄደባቸው የግድብ ግንባታ ፕሮጀክቶች መካከል በኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ ተመራማሪዎች ማለትም በአቲፍ አንሳር፣ በቤንት ፍላይቭ ጀርግ፣ በአሌክሳንደር ቡዜር እና በዳንኤል ሉል እ.ኤ.አ ከ1934 – 2007 ድረስ ባሉት ዓመታት ውስጥ ዝርዝር ጥናት ከተካሄደባቸው ታላላቅ የግድብ ግንባታ ፕሮጀክቶች መካከል አስተማማኝ የግንባታ ወጭ እና የጊዜ መርሀ ግብር ያላቸው ፕሮጀክቶች ተገኝተዋል፡፡ የእነዚህ ተመራማሪዎች የመረጃ ቋት 245 ፕሮጀክቶችን በ65 ሀገሮች ላይ የተደረገ እና ጠቅላላ የፕሮጀክት ወጪያቸው 353 ቢሊዮን ዶላር (እ.አ.አ በ2010 በነበረው የገባያ ዋጋ መሰረት) የሆኑ የግድብ ግንባታ ፕሮጀክቶቸን ያካተተ ነበር፡፡

“ታላላቅ ግድቦችን በተጨማሪ መገንባት ይኖርብናልን? በእውነታ ላይ የተመሰረተ ግዙፍ የውኃ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ የፕሮጀክት ልማት ተጨባጭ ወጭ“ በሚል ርዕስ እነዚህ ከዚህ በላይ የተጠቀሱት ተመራማሪዎች ባደረጉት ጥናት እና በደረሱበት ግኝት እና ትንታኔ መሰረት ለታኢሕግ/GERD በግልጽ ሊያመላክቱ የሚችሉ ልዩ የሆኑ እንደምታዎችን እንደሚከተለው አቅርበዋል፡

…ታላላቅ ግድቦች ተለዋዋጭ ባልሆነ የሀገሬው ገንዘብ መሰረት በየዕለቱ የፕሮጀክቱን ስራ ለማከናወን በአማካይ 96 በመቶ የሆነ (ማለትም አስከ የሁለት እጅ አጥፍ ድረስ የሚስወጣ ) የስራ ማስኬጃ ወጭን ይጠይቃሉ፡፡ የፕሮጀክቱ ስፋት እና መጠን በጨመረ ጊዜ ደግሞ የስራ ማስኬጃ ወጭዎች የዚያኑ ያህል የጭማሪ ዕድገት ያሳያሉ፡፡ የማህበራዊ እና የአካባቢ ስነምህዳር ወጭን እንኳ ከግምት ውስጥ ሳናስገባ ታላላቅ ግድቦች በአማካይ የምጣኔ ሀብታዊ ፋይዳ የላቸውም…

…የፕሮጀክት ትግበራ አፈጻጸም የጊዜ ሰሌዳ በአማካይ 44 በመቶ የመዘግየት ባህሪን ያሳያሉ፡፡ የትግበራ አፈጻጸም የጊዜ ሰሌዳ ረዥም ጊዜ የሚውስደውን የፕሮጀክት ሰነድ ዝግጅቱን እንኳ የሚያካትት አይደለም፡፡ የግድብ ግንባታ ስራውን የሚተገብሩት እና የገንዘብ አቅራቢዎች ቀደም ሲል ተጠናቅቀው አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኙት ፕሮጀክቶችን ችግሮች በተደጋጋሚ ይገነዘባሉ፣ ሆኖም ግን ከስህተቶቻቸው እንደተማሩ ይናገራሉ… እንደዚሁም ደግሞ በጊዜ ሂደት የፕሮጀክት ወጭዎችም ሆኑ የጊዜ መርሀ ግብሮች ሲሻሻሉ አይታይም፡፡ ካለፉት ስህተቶች በተሞክሮነት የሚወሰዱ ትምህርቶች በጣም ጥቂት ናቸው…በአሁኑ ጊዜ የሚካሄዱትን የግድብ ግንባታ ወጭዎችን መተንበይ እ.ኤ.አ. ከ1934 – 2007 ሲደረጉ እንደነበሩት ዓይነት የግድብ ፕሮጀክቶች ስህተቶች ተመሳሳይ ነገር ነው…

…የግድብ ግንባታ ወጭዎች መናር እና የግንባታ የጊዜ መርሀግብር መጓተት ሁለቱም በዓለም ላይ የሚገኙ የሁሉንም አህጉሮች ፕሮጀክቶች በእጅጉ ይጎዳሉ፡፡ ደኃ ሀገሮች ደካማ የሆነ የመንግስት አወቃቀር እና ግዙፍ የሆኑ የግድብ ግንባታ ፕሮጀክቶችን ለመደገፍ የሚያስችል የምጣኔ ሀብት አቅም ችግር ያለባቸው ስለሆኑ በጣም ከፍተኛ የሆነ የጊዜ መጓተት ያጋጥማቸዋል፣ በሚያስደንቅ ሁኔታ ግን የዴሞክራሲ ስርዓት በተዘረጋባቸው ሀገሮችም እንደዚሁ የፖለቲካ ዕጩ ተወዳዳሪዎች ምርጫውን ለማሸነፍ በሚል ምክንያት በእውነታ ላይ የተመሰረተ ሳይሆን ዝም ብሎ ግምትን መሰረት ያደረግ ትንበያ በማድረግ ፕሮጀክቶቻቸውን ለመሸጥ ጥረት ያደርጋሉ…

… ከበርካታዎቹ የግድብ ፕሮጀክቶች መካከል እንደ ቤሎ ሞንቴ፣ ሚትሶኔ ወይም ደግሞ የግልገል ጊቤ 3 ያሉ ታላላቅ ፕሮጀክቶች የምጣኔ ሀብት አዋጭነታቸውን በአስከፊ ሁኔታ ሊጎዳ በሚችል መልኩ ገና በመጀመሪያው የዕቅድ ዝግጅት ስራዎች ላይ ከፍተኛ የሆነ የስራ ማስኬጃ ወጭ እና የጊዜ መርሀግብር መጓተትን እንዲጋፈጡ ሊያደርጋቸው ይችላል…

በዓለም ላይ የሚገኙ ታላላቅ የግድብ ግንባታዎችን ለመተግበር ዕቅድ የሚያዘጋጁ ባለሙያዎች ቢያንስ 80 በመቶ የሆነ የትግበራ ስኬታማነታቸውን ለማረጋገጥ [በጀት እና የጊዜ መርሀግብር ተዘጋጅቶለት ከነበረው ውጭ ተጨማሪ ማለት ነው] እንዲችሉ 99 በመቶ የስራ ማስኬጃ የወጭ ጭማሪ እና 66 በመቶ ደግሞ የግንባታ መርሀግብር መጓተት ይደርስባቸዋል፡፡ (አጽንኦ ተጨምሮበታል)፡፡

የኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ የጥናት ግኝቶች በተለይ በፓኪስታን ሀገር የሚገኘው የዲያመር ባሻ የግድብ ፕሮጀክት እንሚያመላክተው ለታኢሕግ/GERD አቀንቃኝ ለሆኑት ሹመኞች እና ካድሬዎች ልዩ የሆነ ማስጠንቀቂያ እና ማሳሰቢያ የሚሰጥ በጣም ጠቃሚ ተሞክሮ ነው፡፡ የኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ የባለሙያዎች ጥናት በኢንዱስ ወንዝ ላይ ግድብ ለመገንባት ተይዞ የነበረው 12.7 ቢሊዮን ዶላር አጠቃላይ ወጭ በ80 በመቶ እርግጠኝነት የግንባታ ስኬትን ለመጎናጸፍ እንኳ እንዲቻል ወደ 25.4 ቢሊዮን ዶላር እና የማጠናቀቂያ የጊዜ መርሀ ግብሩ እ.ኤ.አ በ2021 ይጠናቀቃል ተብሎ የተያዘው እ.ኤ.አ ወደ 2027 ከፍ እንደሚል በግልጽ አስቀምጧል፡፡ እነዚህ ተመራማሪዎች በጎንጎ ወንዝ ላይ ለሚገነባው የኢንጋ ግድብ፣ በአማዞን ወንዝ ላይ ለሚገነባው ለቤሎ ሞንቴ ግድብ እንዲሁም በሜኮንግ ዋና ወንዝ እና በሌሎችም በርካታ ታላላቅ ግድቦች ላይ ተመሳሳይ መደምደሚያዎችን ሰጥተዋል፡፡

የታኢሕግ/GERD የበላይ ጠባቂዎች እንዲህ የሚሉትን የኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ ተመራማሪዎችን የመፍትሄ ምክረ ሀሳቦች በአጽንኦ መመልከት ይኖርባቸዋል፡ “በርካታ ትናንሽ፣ የበለጠ ተለዋዋጭ የሆኑ የግድብ ግንባታ ፕሮጀክቶችን በመውሰድ በቀላሉ ሊገነቡ እና በተያዘላቸው የጊዜ መርሀ ግብር መሰረት ሊተገበሩ የሚችሉ እንዲሁም ከፍተኛ አደጋ ከተጋፈጠባቸው እና በየዘመናቱ ተግንብተው በአስከፊ ሁኔታ ተደርምሰው ከጠፉት ግዙፍ የግድብ ግንባታዎች ይልቅ የማህበራዊ እና የአካባቢ ስነምህዳር ጉዳዮችን ከግምት ውስጥ ሊያስገቡ የሚችሉ ትናንሽ የግድብ ፕሮጀክቶች ተመራጭ ናቸው፡፡” ብለዋል፡፡ ይኸ በተጨባጭ በዳበረ አዕምሮ በምሁራን ተጠንቶ፣ የዘመናት ልምድ ተቀምሮበት እና በመረጃ ቋት ውስጥ ገቢ ተደርጎ ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፍ የሚኖር መርህን እና እውነታን መሰረት በማድረግ የተሰጠ ምክረ ሀሳብ እንጂ በስሜት ለከርስ እና ለባዶ ፕሮፓጋንዳ ሲባል በመገፋፋት በይሆናል እና በመሰለኝ የተሰጠ ተራ የካድሬ እና የደብተራ አስተያየት አይደለም፡፡

ማንኛውንም የግድብ ግንባታ ስራዎችን በሚመለከት እንደግለሰብ የእኔ ግላዊ አመለካከት ከአክስፎርድ ዩኒቨርስቲ ተመራማሪዎች ቡድን ግኝቶች ጋር ተመሳሳይ ሆኖ ይገኛል፡፡ ታኢሕግ/GERD አሁን በህይወት በሌለው በመለስ እና በወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ብድን ስብስብ በመጠንሰሱ ምክንያት አዕምሯቸውን ለማሰብ ሳይሆን ለከርስነት ያዘጋጁት እበላ ባይ ሆድ አምላኩ ካድሬዎች እና ደብተራዎች እንደሚሉት እንዲሁ በደፈናው ጭፍን ጥላቻን ለማራመድ ወይም ደግሞ ስሜታዊነትን የተላበሰ ተቃውሞ ለማድረግ በማሰብ አይደለም ገንቢ እና ለሀገሬ የሚጠቅሙ ምክረ ሀሳቦችን በመሰንዘር ላይ የምገኘው፡፡ እራሴን እንደ ተምኔታዊ ኢትዮጵያዊ የምቆጥር ብሆንም እንኳ ተጨባጭነት ባላቸው መረጃዎች ላይ መሰረት በማድረግ የእራሴን ምሁራዊ ትንተናዎችን፣ ትንበያዎችን እና መደምደሚያዎችን እሰጣለሁ፡፡ ምንም ዓይነት ማስተባበያ የማይደረግበት የኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ ጥናት እንዲህ ይላል፣ “ከፍተኛ አደጋ የተደቀነባቸው የሚጠፉ የግድብ ፕሮጀክቶች በየዘመኑ እንደሚገነቡት ታላላቅ ግድቦች የግንባታ ወጪያቸው እጅግ በጣም ውድ ነው፣ እንደዚሁም ሊከሰት የሚችለው አደጋ በጣም አስከፊ ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ትናንሽ የግድብ ፕጀክቶች የበለጠ ተግባራዊ የሚሆኑ እና በቀላሉ ለማስተዳደር ምቹ የሆኑ፣ ጠንካሮች እና ትርፋማ የሆኑ ናቸው።“

በእኔ አስተያየት የሌላትን ውበት ለማምጣት ሲባል ሊፒስቲክ የተቀባች ፉንጋ አሳማ እና እጅግ ውድ የሆኑ የቅንጦት የድብ ግንባታ ፕሮጀክቶችን የሌላቸውን ውበት ለማሳመር ሲባል ሊፒስቲክ መቀባት አንድ እና ተመሳሳይ ናቸው፡፡ በዕለቱ መጨረሻ ሊፒስቲክ የተቀባቸው አሳማ ያው ከፉንጋነቷ ያልተላቀቀች አስቀያሚ ናት፡፡ እንደዚሁም ሁሉ የግድብ ግንባታ ወጭው እጅግ በጣም ከፍተኛ የሆነ የቅንጦት ግድብ የፈለገውን ያህል ሌት ቀን የፕሮፓጋንዳ ስራ ቢሰራለት እና ያሳምራል በሚል ባለኮከብ አረንጓዴ፣ ብጫ እና ቀይ ቀለም ባለው ባንዲራ ቢሸፍን እና ቢሸፋፈን የምጣኔ ሀብት አዋጭነትን የማያመጣ፣ ትርፍን የማያስገኝ በማህበራዊ እና በአካባቢያዊ ስነምህዳር ላይ ጉዳትን ከማስከተል ውጭ ምንም ነገር የማያመጣ ያው ባዶ የሆነ የቅንጦት ግድብ ከመሆን የሚቀይረው ነገር የለም፡፡

በትልቅነቱ ከዓለም በ8ኛ ደረጃ ላይ ለተቀመጠው የግድብ ፕሮጀክት የግንባታ ትግበራ መልካም ነገርን ለማቅረብ ለሚያስቡ እና ከዚያም አልፎ በጥናት ላይ የተደገፈ ሳይሆን የአርበኝነት የክርክር ጭብጥ በሚያቀርቡ ወገኖቼ ላይ ችግር የለኝም፡፡ ከግድቡ ግንባታ ታላቅ ነገሮችን ለማግኘት ሲባል በሚያስቡ ወገኖቼ ላይ ችግር የለኝም፣ ጥያቄም አላነሳም፡፡ እንደዚሁም ሁሉ ኢትዮጵያ በዓባይ (ብሉ ናይል) ወንዝ ላይ ግድብ የመስራት የማይቀለበስ መብት አላት ወይም ደግሞ ባሏት የተፈጥሮ ሀብቶቿ ለመጠቀም ሙሉ ሉዓላዊነት አላት በሚሉት ነገሮች ላይ ጥያቄ አላነሳም፡፡ ይህንን በሚመለከት ምንም ዓይነት ለድርድር የሚቀርብ ጥያቄ አላነሳም ሊኖርም አይችልም ፡፡

ሆኖም ግን በእኔ ሊነሳ የሚችለው ዋናው ጥያቄ ሊጠፋ በሚችል የግዙፍ ግድብ ምጣኔ ሀብታዊ እውንነት ላይ ወይም ደግሞ ያለምንም ችግር ውጤታማ ሆኖ ለወገኖቼ ማህበራዊ፣ ምጣኔ ሀብታዊ እና የአካባቢ ስነምህዳራዊ ጠቀሜታ ላይ ያነጣጠረ ነው፡፡ የእኔ ትልቁ ጥያቄ በሀሰት እና በቅጥፈት ላይ ተውገርግሮ በቆመው ታማዕኒነት በሌለው ቀጣፊ አገዛዝ ውሸት እና የቅጥፈት አሀዝ ድርደራ ላይ ነው፡፡ የእኔ ጥያቄ የሚነሳው በሙስና እስከ አንገቱ ድረስ ተዘፍቆ በመንገዳገድ ላይ ስለሚገኘው አገዛዝ እና በተጨባጭ ማስረጃዎች ላይ በመመስረት ከምንም ጥርጣሬ በላይ ውሸት፣ ቅጥፈት እና ባዶ ትረካ ሆኖ የቆየውን በርካታ ዓመታት በማን አለብኝነት በህዝብ ላይ ጥርሱን ነክሶ ሲቀጥፍ እና ሲዋሽ የቆየውን እና ባለሁለት አሀዝ የምጣኔ ሀብት ዕድገት አስመዝግቢያለሁ እያለ የሚተርከውን እና ተራ ፕሮፓጋንዳ በመንዛት ላይ ያለውን አገዛዝ በማጋለጥ ላይ ነው፡፡

እኔ ጥያቄ አድርጌ የማቀርበው የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ “ታላቁ መሪ” እና ቁንጮ ለነበረው እና እ.ኤ.አ በ2005 የተደረገውን የይስሙላ ምርጫ ውዝግብ ተከትሎ ተቀስቅሶ በነበረው ሁከት በግፍ አሰቃቂ በሆነ መልኩ ንጹሀን ወገኖቻችንን በጠራራ ጸሐይ በአደባባይ በጥይት የጨረሰውን እና ያስጨረሰውን ጭራቁን ዘራፊ መሪ ተብዮ እና በኢትዮጵያ ታሪከ በዘግናኝነቱ ሲታወስ ለሚኖረው ዕኩይ ማስታወሻ በሚል ግዙፍ የሆነ የስሚንቶ ግድብ ሃውልት የማቆሙን አስፈላጊነት ነው፡፡

እኔ ጥያቄ አድርጌ የማነሳው እምነት ሊጣልበት የማይችል አጭበርባሪ፣ እስከ አንገቱ ድረስ በሙስና ለተዘፈቀ፣ በዜጎች ላይ እምነት የማይጣልበት ከሀዲ እና አስመሳይ ገዥ አካል ለኢትዮጵያ ህዝቦች ፍላጎት ታዛዥ በመሆን ምንም ሊያደርግ የማይችል ብልዓያሰብ ቡድን ከመሆኑ ላይ ነው፡፡ እኔ ጥያቄ አድርጌ የማነሳው ማንኛውም ምክንያታዊ የሆነ ሰው ነጻ የሆነ አስተሳሰብን ከማራመድ ወይም ደግሞ ትምህርትን እና ዕውቀትን ያገናዘበ ድርጊት ከመፈጸም ይልቅ መጨረሻ ለሌለው ጊዜ ድብቅ እና ሚስጥራዊ ለሆነ ወሮበላ ገዥ አካል እንዴት እውቅና ሊሰጠው እንደሚችል ነው፡፡

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ በሁሉም ጉዳዮች እና ችግሮች ላይ መፍትሄ በመስጠት በድል አድራጊነት ለመውጣት እንድትችል ምሁራዊ መስተጋብር በጣም አስፈላጊ ነገር መሆኑን አምናለሁ፡፡ ከዚህ አንጻር ታኢሕግ/GERDን በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ በርካታ ሀሳቦች ወደ መድረክ እንደሚቀርቡ እና እንደሚንሸራሸሩ እምነት አለኝ፡፡ እንደዚህ ዓይነቶቹ የሀሳብ መለዋወጫ መድረኮች በፖሊሲ ጉዳዮች እና በመረጃ ላይ በተመሰረተ የሲቪክ ማህበረሰብ የውይይት መድርክ በመፍጠር የሰለጠነ ባህል ዕድገትን ሊያረጋግጥ ይችላል፡፡

እኔ ስለታኢሕግ/GERD የፖለቲካ እና ምጣኔ ሀብታዊ ትንተና በማቀርበው ትችት ላይ ስምምነት የሌላቸውን ወገኖች አመለካከት በቀናነት አከብራለሁ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በሙሉ እና በዋናነት ስለግድቡ ባላቸው የጋለ ፍላጎት ላይ ከእነርሱ ጋር ስምምነት አደርጋለሁ፡፡ ምን ዓይነት ስብዕና ያለው ሰው ነው በአስር ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ወገኖቹን ከድህነት አረንቋ መንጥቆ ሊያወጣ የሚችል ፕሮጀክት ወደፊት ሊተገበር ነው ሲባል ስምምነት ሊያደርግ የማይችል? በእርግጥ ጭራቃዊነት ድርጊቱ በግልጽ የሚገኘው በዝርዝር ሁኔታው ውስጥ ነው፡፡ ያም ሆነ ይህ ከእኔ ጋር በህዝብ የሀሳብ መግለጫ መድረክ ላይ ሀሳባቸውን በማቅረብ መቃወም የሚችሉትን ወገኖች መብት አከብራለሁ፡፡ እንደዚሁም ሁሉ ስለታኢሕግ/GERD ከተለመደው አስተሳሰብ ውጭ ወጣ ያለ እና ትችትን ያዘለ ሀሳብ ቢሰነዝሩ እና ክስ ቢመሰረትባቸው በፍትህ አደባባይ ነጻ የጥብቅና አገልግሎት ልሰጣቸው እንደምችል ያለኝን ሀሳብ በደስታ ልገልጽላቸው እንደምችል ላረጋግጥላቸው እወዳለሁ፡፡

በገንዘብ እጥረት ዓባይ ሲገደብ፣

የ’ዓባይ ወንዝ ተመራማሪ”ነኝ ባዩ እንዳስቀመጡት ሁሉ የእኔ ብቸኛው እና ሆኖም ግን ይህ ብቻ ያልሆነው የስጋት ምንጨ የግድቡን ገንዘብ እንዴት ማሰባሰብ እንደሚቻል እና በማንኛውም መልካም አማራጭ መንገድ ሁሉ ግድቡ ኢኮኖሚያዊ የሆነ ጠቀሜታ የሚኖረው ወይም ደግሞ የማይኖረው ከመሆኑ አንጻር የመመርመሩ ጉዳይ ነው፡፡

የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ምንም ዓይነት የውጭ ብድርም ሆነ እርዳታ ሳያገኝ ታኢሕግን/GERD በመገንባት እውን ማድረግ እንደሚችል አስቀድሞ የሚያውቀው እንደሆነ ማስተባበያ ለመስጠት የማቻልበት እውነታ ነው ፡፡ መለስ ዜናዊ እ.ኤ.አ በ2011 ገና ፕሮጀክቱ በጅምር ላይ በነበረበት ጊዜ ይህንን ታላቅ የግድብ ፕሮጀክት ያለማንም እገዛ ብቻውን ሊሰራው እንደሚችል ድፍረት ብቻ ሳያሆን ድንፋታ ጭምር የተቀላቀለበት ንግግር አሰምቶ እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡ ያ ጭራቃዊ መንፈስ በአሁኑ ጊዜም በወያኔ ወሮበላ የዘራፊዎች ስብስብ ቡድን ውስጥ በማንዣበብ ላይ ይገኛል፡፡ ከታመኑ ምንጮች በተገኘው መረጃ መሰረት የግድብ ፕሮጀክቱ በአሁኑ ጊዜ ታላቅ የሆነ የገንዘብ ችግር አጋጥሞታል፡፡

ገንዘብ ለማሰባሰብ የቦንድ ሽያጭ ሲካሄድ የነበረበት ሁኔታ በአሁኑ ጊዜ ከምን ደረጃ ላይ ደረሰ?

እ.ኤ.አ በ2013 የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ብድን ስብስብ ከቦንድ ሽያጭ 500 ሚሊዮን ዶላር እንደሰበሰበ ግልጽ አድርጎ ነበር፡፡ ሆኖም ግን እስከ አሁን ድረስ ከቦንድ ሽያጭ ምን ያህል ገንዘብ እንደተሰበሰበ ግልጽ የተደረገ ነገር የለም፡፡ በሀገር ውስጥ ያሉ የንግድ እና ሌሎች ተቋማት ቦንድ እንዲገዙ ግዴታ ተጥሎባቸዋል፡፡ ተራው ህዝብ ከሚያገኛት በጣም አነስተኛ ከሆነች ገቢ ለግድቡ መዋጮ እንዲያደርግ ግዴታ ወድቆበታል፡፡ ከቁጥጥር ውጭ የሆነውን የዲያስፖራ የእብደት የቦንድ ሽያጭ እንቅስቃሴ በአሜሪካ የፌዴራል የግዛቶች ህግ መሰረት በሀገሪቱ ውስጥ ያልተመዘገበ የቦንድ ሽያጭ በውጭ ሀገር መንግስት ወይም በተወካዩ አማካይነት የቦንድ ሽያጭ ማካሄድ ህገወጥ መሆኑን ለወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ “ምክር” ከሰጠሁ በኋላ ሙሉ በሙሉ ቆሟል፡፡

እውነታው ፍርጥ እና ፍርጥርጥ ብሎ ሲታይ ግን የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ በግድቡ ግንባታ ላይ በአሁኑ ጊዜ እና ወደፊትም የሚኖረውን የገንዘብ ችግር በውል ተገንዝቦታል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የስራ ማስኬጃ ወጭ መናርን እና የፕሮጀክት አስተዳደሩን አስከፊ ችግር በሌሎች የግንባታ ፕሮጀክቶች ላይም እየቀመሰው ይገኛል፡፡ ለምሳሌም ያህል የዓባይ ገባር በሆነው እና በሰሜን ኢትዮጵያ የሚገኘው የተከዜ የኃይድሮ ኤሌክትሪክ ኃይል ግድብ ግንባታ በመጀመሪያ ተይዞለት የነበረው ጠቅላላ ወጭ 224 ሚሊዮን ዶላር የሚገመት ነበር፡፡ ሆኖም ግን እ.ኤ.አ በ2008 ሲጠናቀቅ በስራ ላይ የዋለው ገንዘብ እንደ ሮኬት ወደ ላይ በመተኮስ ወደ 360 ሚሊዮን ዶላር ያሻቀበ ሲሆን ተይዞለት ከነበረው በጀት በላይ በ136 ሚሊዮን ዶላር ወይም ደግሞ በ38 በመቶ የዕድገት ጭማሪ አሳይቷል፡፡

እንደ አሜሪካ የሀገር ውስጥ ደህንነት መምሪያ ዘገባ ከሆነ እ.ኤ.አ የካቲት 2010 ላይ በኢትዮጵያ ኃይል በማመንጨት ከፍተኛውን ድርሻ የያዘው የግልገል ጊቤ 2 የግድብ ፕሮጀክት ዋና መፍሰሻ ቦይ ላይ ከተመረቀ አስር ቀናት እንኳ ሳይሞላው የመደርመስ አደጋ ደርሶበት ከፍተኛ ችግር ተከስቶ ነበር፡፡ “የግልገል ጊቤ ጉዳይ“ በሚል ርዕስ ተደርጎ በነበረ ታላቅ ጥናት መሰረት በጊቤ 2 ግድብ ላይ ደርሶ የነበረው የመደርመስ ዋና አደጋ ከበርካታ ጉዳዮች ጋር የተያያዘ መሆኑ ሲጠቆም ከእነዚህም ውስጥ ጥንቃቄን በተላበሰ መልኩ መገንባት ያለመቻሉ እና ተገቢነት ያለው የምህንድስና ሙያ ያልታካለበት ስለነበር እንዲሁም የአካባቢ ስነምህዳር ጥናት ያልተደረገለት በመሆኑ ምክንያት እንደሆነ ግልጽ ተደርጓል፡፡ የጣሊያን የግድብ ስራ ተቋራጭ የሆነው ሳሊኒ ኤስኤኤ ስራ ተቋራጭ/Salini Construttori S.P.A የፕሬስ መግለጫ በመስጠት ስህተቱን እንዲህ በማለት አምኗል፣ “በወቅቱ ሊታዩ ያልቻሉ መልክዓ ምድራዊ ክስተቶች በመፍሰሻ ቦዩ ላይ ዋሻ መሰል ነገርን ፈጠሩ እናም ከመፍሰሻ ቦዩ አናት ላይ 26 ኪ/ሜ ርዝመት ላለው ቦይ ታላቅ ግፊት ከሚሰጠው አናት ላይ ታላቅ ቋጥኝ ገብቶ በመዘጋቱ የተፈጠረ ችግር እንደነበር ግልጽ አድርጓል፡፡

አንድ የባንክ ጥናት እንዳመለከተው ግዙፍ በሆኑ የግድብ ግንባታ ስራዎች ላይ ግልጽ የሆነ ጨረታ ሳይወጣ እና የጥቅም ግጭት በሚፈጠርበት ጊዜ ትልቅ የሆነው የግል ተቋራጭ ኩባንያ ፕሮጀክቱ በሚሰራበት ሀገር ያለው አስተዳደራዊ መዋቅር ደካማ ከሆነ እና ገንዘቡን ከሚሰጡ የገንዘብ ተቋማት ግልጽ የሆነ ፈቃደኝነት ከሌለ የፈለገውን ያህል የፕሮጀክት ማስጠንቀቂያ ቢኖር እና የተለይ ተጽዕኖ ቢኖርም የሚመጣ ለውጥ አይኖርም፡፡ ይህም ማለት በኢትዮጵያ በመገንባት ላይ ባሉ ፕሮጀክቶች ላይ የሙስና ጥንባት ሽታ ይስተዋላል ማለት ነው!

እውነታው ፍርጥርጥ ብሎ ሲታይ ግን የግልገል ጊቤ 2ን አስከፊ የሆነ የነገሮች ተያያዥነት ጥናት ውድቀት/structural failure ቢከሰትም ቅሉ አሁንም ቢሆን ባልታሰበ ጊዜ አስከፊ የሆነ ውድመትን ሊያስከትል እንዳይችል የሚያደርግ መተማመኛ የለም፡፡ እንደዚህ ዓይነት ውድቀት ከፍተኛ የሆነ የውኃ ልቀት ሲደረግ፣ የውኃ መፍሰሻውን ቆሻሻ ነገር ሲዘጋው፣ በግድቡ ውስጥ የዘቀጡ ነገሮች ሲኖሩ፣ በተሸረሸሩ የውኃ መፍሰሻ ቦዮች ምክንያት የውኃ መስረግ ሲፈጠር፣ የእንስሶች ቁፋሮ ሲኖር እና ስንጥቅ ነገር ሲኖር፣ እንዲሁም የማቴሪያሎች ስትራክቸራል ውድቀት እና በቂ የሆነ ጥገና ካለማድረግ የተነሳ የሚከሰቱ ናቸው፡፡ እነዚህ ጉዳዮች የግልገል ጊቤ 2 ጥናት በሚካሄድበት ወቅት በሳይንቲስቶች የተነሱ ዋና ዋና ነገሮች ናቸው፡፡

ያው የመጀመሪያው የግልገል ጊቤ 2 ግድብ ግንባታ ስራ ተቋራጭ የሆነው ሳሊኒ ምንም ዓይነት ግልጽ ጨረታ ሳይወጣ የታኢሕግ/GERDን እንዲሰራው ተሰጥቶታል፡፡ ታኢሕግ/GERD በተመሳሳይ መልኩ እንደ ግልገል ጊቤ 2 ያለ ወይም ደግሞ ከዚያ የበለጠ አደጋ ሊያጋጥመው ይችላልን? የሚያስገርመው ነገር ግን ሳሊኒ በአፍሪካ በያዛቸው ፕሮጀክቶች ላይ ሁሉ ታላቅ የሆነ የስራ ማስኬጃ ወጭን በመጀመርያ ከተወጠነው በላይ የሚያስመዘግብ የስራ ተቋራጭ መሆኑ ይታወቃል፡፡

ታኢሕግ/GERD እንደ ታላቅ የግድብ ግንባታ ስራው ቢጠናቀቅም እንኳ ምጣኒያ ሀብታዊ አዋጭነት የሌለው እና በየጊዜው የሚደረገው ከፍተኛ የሆነ የጥገና ወጭ የኤሌክትሪክ ኃይል ምርት ከሚመነጨው በላይ ሊያስከትል የሚችል ጉዳትን ሊያመጣ ይችላል፡፡

አሁንም አንደገና መረጃዎችን እንመልከት፡፡ በመጀመሪያ በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን/EEPCO እና በእራሱ የኤሌክትሪክ ታሪፍ መዋቅር መካከል ጠቃሚ የሆኑ አስተዳደራዊ ጉዳዮች አሉ፡፡ እ.ኤ.አ በ2011 በዓለም ባንክ አንደተዘጋጀው የፖሊሲ ሰነድ ከሆነ፣ ዋጋን አሳንሶ ማቅረብ ጠቃሚ ጉዳይ ነው፡፡ የኢትዮጵያ የኃይል ታሪፍ ምጣኔ በኪሎ ዋት አወር ከ0.04 – 0.08 ዶላር የሆነው ታሪክ በቀጣናው ካለው መስፈርት አንጻር በጣም ዝቅተኛ የሆነ እና 46 በመቶውን ብቻ የአገልግሎት ወጭ የሚሸፍን ሆኖ ይገኛል፡፡ የረዥም ጊዜ ኤሌክትሪክ የማመንጨት የዋጋ ህዳግ ዋጋው/marginal cost በኪሎ ዋት አወር 0.04 ዶላር ብቻ የሆነ ዝቅተኛ ዋጋ ቢሆንም ቅሉ የሀገሪቱ የረዥም ጊዜ የኤሌክትሪክ ስርጭት እና ክፍፍል መረብ አጠቃላይ የረዥም ጊዜ የዋጋ ህዳጉን በኪሎ ዋት አወር ወደ 0.16 ዶላር ከፍ እንዲል ያደርገዋል፡፡ በኃይል ዘርፉ የሚደረገው ዝቅተኛ ዋጋ ከሀገሪቱ የሀገር ውስጥ ምርት/GDP ውሰጥ 1.3 በመቶ በመያዝ በአሁኑ ጊዜ ከፍተኛ ከሆኑት ዝቅተኛ ገቢ ካላቸው ሀገሮች መስፈርት ከሆነው በኪሎ ዋት አወር ከ0.8 በመቶ በላይ የሀገር ውስጥ ከሚይዘው ጋር ሲታይ በጣም ከፍተኛ መሆኑን ያመላክታል፡፡

የኃይል ታሪፍ በመካከለኛ ጊዜ ከፍ ያለ ተመን እንደሚቀመጥላቸው የማይቀር ጉዳይ ነው፡፡ እንደዚህ ዓይነቱ የታሪፍ ትመና ዘዴ የኩባንያውን የገንዘብ ሁኔታ ያጠናክረዋል፡፡ በአጠቃላይ ድብቅ የሆኑ የኃይል ዘርፉ 100 በመቶ የሚሆነውን የEEPCOን የቅልጥፍና እጦት ይሸፍናሉ፡፡ ይህም ማለት ኩባንያው ውጤታማ በሆነ መልኩ የሚሰራ ከሆነ የገቢውን ግማሽ ብቻ የሚያገኝ ይሆናል ማለት ነው… [አጽንኦ ተደርጓል፡፡]

በአሁኑ ጊዜ ሁኔታው የተቀየረ አይደለም፡፡ እንደ አንዳንድ እውቀቱ እንዳላቸው መረጃዎች ከሆነ በጣም አስከፊ ሁኔታ ተፈጥሮ ይገኛል፡፡

“የአፍሪካ የኃይል መሰረተ ልማት” በሚል ርዕስ የዓለም ባንክ እንዳቀረበው ሌላ ጥናት በሰብ ሰሀራ የአፍሪካ ሀገሮች የኤሌክትሪክ ታሪፍ ተመሳሳይ ድምዳሜን ይዟል፡፡ በሰብ ሰሀራ የኤሌክትሪክ ታሪፍ በሌሎች አህጉሮች ከሚኖረው ታሪፍ ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ ሆኖ ይገኛል፡፡ አማካይ የኃይል ታሪፍ በኪሎ ዋት አወር 0.12 ዶላር የሆነው ከሌሎች ታዳጊ ሀገሮች ለምሳሌ ያህልም ከደቡብ ኤሲያ ሁለት ጊዜ እጥፍ ብልጫ ያለው ሆኖ ይገኛል፡፡ በአብዛኞቹ የአፍሪካ ሀገሮች የኃይል ታሪፍ በከፍተኛ ሁኔታ በመደጎም ላይ ይገኛል፡፡ በአማካይ የኃይል ታሪፎች 87 በመቶ የሚሆነውን ሙሉ ወጪያቸውን ብቻ ይሸፍናሉ፡፡ የሚከሰተው ድብቅ የድጎማ አገልግሎት በዓመት እስከ 3.6 ቢሊዮን ዶላር ወይም ደግሞ የአፍሪካን ጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት 0.56 በመቶ የሚሸፍን ይሆናል… እነዚህ ድጎማዎች ከአገልግሎቱ ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት የሌላቸውን ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን ቤተሰቦች የሚዘሏቸው ይሆናል…

በአፍሪካ ሀገሮች በአጠቃላይ እንደሚታየው ውጤት ወደ ደኃው የቤተሰብ ክፍል የሚሄደው የድጎማ ድርሻ በህዝቡ ላይ ካላቸው ብዛት ከግማሽ ያነሰ ነው…

የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ከታኢሕግ/GERD ይገኛል ብሎ የሚያስበውን ኃይል የግድብ ስራው ከተጠናቀቀ በኋላ ለሱዳን፣ ለግብጽ፣ እና ለአረቢያ ፔንሱላ ለመሸጥ ዕቅድ ይዟል፡፡ ባለፈው ሳምንት በአንቀጽ 6 ስር የታተሙት “የድንጋጌ መርሆዎች” ግብጽ እና ሱዳን ከግድቡ ኃይል ለመግዛት የቀዳሚነት መብት ይኖራቸዋል ይላል፡፡ እንደዚህ ያለው ነገር ውጤቱ ሀሳባዊ ነው፡፡ ጥያቄው ግብጽ ወደ እራሷ የሚሄደው የውኃ ፍሰት በህዳግ ደረጃ ጉዳት የሚያደርስባት መሆኑ እየታወቀ እና የእራሷን የግብርና ስራ እና በአስዋን ግደብ ላይ የምታመርተውን የኃይል አቅርቦት እየቀነሰባት ባለበት ሁኔታ ላይ ከኢትዮጵያ ኃይል ተግዛለች የሚለው አባባል ከሀሳብ ባለፈ ለተጨባጭ ተግባራዊነቱ ማስተማማኛ የለውም፡፡ ሌላው አማራጭ ምንድን ነው? ማንም ሰው የመለስን እና የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብን የኃይል አቅርቦት መሪ ዕቅድ የሚከተል ከሆነ ምንም ነገር የለም፡፡ እንደ ባንክ ዎች/Bankwatch ዘገባ ከሆነ የኢትዮጵ መንግስት የኃይል መሪ ዕቅድ ለአዲስ ኃይድሮ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት ፕሮጀክቶች እንጅ ሌላ የኃይል አማራጮችን ለማግኛት እና አማራጭ ምንጮችን ለማስፋት የሰጠው የትኩረት አቅጣጫ የለም፡፡

አስደንጋጩ እና ህሊናን የሚበጠብጠው ነገር የመለስ የኃይል መሪ ዕቅድ ለጸሐይ እና ለነፋስ የኃይል አማራጮች የሰጠው ትኩረት ያለመስጠቱ ጉዳይ ነው፡፡ ሌላው የበለጠ የሚያስደነግጠው እውነታ ደግሞ ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ሙሉ በሙሉ በሚባል መልኩ በኃይድሮ ኤሌክትሪክ ኃይል ላይ ጥገኛ ሆና የምትገኝ ሀገር ብትሆንም ቅሉ የኃይድሮ ኤሌክትሪክ ጠቀሜታ በሀገሪቱ የስነምህዳር እና የአየር ንብረት ለውጥ ዘለቄታዊ በሆነ መልኩ ሊያስከትል የሚችለውን አደጋ የመንግስት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች በጋራ ያዩት ነገር ያለመኖሩ እና ምንም ዓይነት የስጋት ምልክት ያለማሳየታቸው ሁኔታ ነው፡፡ እንደዚህ ዓይነቱ ድርጊት በወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ደናቁርት የሚፈጠር እውነታ ነው፡፡ የዕለቱን እንጅ የወደፊቱን ማን አስቦት ቀድሞ!

የታኢሕግ/GERD የግንባታ ስራ ቢጠናቀቅ ምን ያህል ወጪ ሊያስወጣ እንደሚችል የማንም ግምት ነው! አንድ ሰው በፓኪስታን ሀገር ከተገነባው ዲያመር ባሻ እየተባለ ከሚጠራው ግድብ የግንባታ ወጭ አንጻር ለመገመት ቢሞከር ታኢሕግ/GERD ቢያንስ 10 ቢሊዮን ዶላር ሊፈጅ ይችላል፣ (ወያኔ ገና ከጅምሩ የፕሮጀክቱን ወጭ አሳንሶ አቅዶት ካልሆነ በስተቀር እና የውስጥ መረጃ ያላቸው ሰዎች በእርግጥም እንደተባለው አሳንሶ እንደተመነው ነው እየተናገሩ ያሉት) እንግዲህ የፕሮጀክት ወጭውን በማሳነስ ተሰርቶ ከሆነ ጠቅላላ ወጭው ወደ 15 ቢሊዮን ዶላር ከፍ ሊል እንደሚችል ይገመታል፡፡

ሌላው በክፍል ውስጥ ተቀምጦ የሚገኘው ሊፒስቲክ ያልተቀባው ዝሆን፣

በሁለተኛ ደረጃ ሊፒስቲክ ያልተቀባው ዝሆን ታላቅ ወጭን የሚጠይቀው እና ሊፒስቲክ ከተቀባው ዝሆን ጎን ለጎን በክፍል ውስጥ ተቀምጠው ይገኛሉ፡፡ ታኢሕግ/GERD በቀጣናው ውሰጥ ጦርነትን ለመቀስቀስ እንደ ሰበብ ወይም ደግሞ መንስኤ ሊሆን ይችላልን?

አሁን በስልጣን ከሌሉት እና ቀደም ሲል ከተወገዱት ፕሬዚዳንት መሀመድ ሙርሲ እና ግብረ አበር ሚኒስትሮቻቸው ሲያራምዱት በነበረው የጥላቻ አመለካከት ላይ ጥልቅ የሆነ ችግር ይታየኛል፡፡ በእኔ አመለካከት እነዚያ ሚኒስትሮች ከስልጣን የተወገደውን የሙርሲን መንግስት አቋም እና አመለካከት ብቻ የሚያራምዱ ናቸው ለማለት የሚያረጋግጥ ማስረጃ የለም፡፡ ሆኖም ግን የሌሎችን ማለትም ከአንዋር ሳዳት በፊት የነበሩትን እና የአሁኑን ሲሲንም አስተሳሰብ ጨምሮ የግብጽ መንግስታትን ጠቅላላ አቋም የሚያንጸባርቅ ጉዳይ ነው፡፡ የእነዚህ መንግስታት አስተሳሰቦች ሁሉ በግብጽ ህዝብ ላይ በአጠቃላይ መልኩ የሚንጸባረቀውን ሁኔታ ያመላክታል፡፡ የሙርሲ ሚኒስትሮች “የውኃ ደህንነት የሞት እና የሽረት ጉዳይ ነው” የሚለው እምነታቸው የእነርሱ ብቻ ይሆናል ብየ አላስብም፡፡ በግልጽ ለመናገር በከፍተኛ የስልጣን እርካብ ላይ ያሉ የግብጽ ባለስልጣናት በታኢሕግ/GERD ጉዳይ ጦርነት የታወጀባቸው ያህል ሆኖ ይሰማቸዋል የሚል ግምት አለኝ፡፡ ለዚህ ነው በታኢሕግ/GERD ጉዳይ በቋፍ ላይ ስላለው ዲፕሎማሲ እና እየተደረገ ስላለው ክርክር እና ዲስኩር የበለጠ እያሳሰበኝ ያለው፡፡

ባለፈው ሳምንት ስለመርህ ድንጋጌ ስምምነት የተፈረመ ቢሆንም ወይም ደግሞ ሌላ ዓለም አቀፍ ስምምነት የሚደረግ ቢሆንም አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ታኢሕግ/GERD የአህጉር አቀፍ የግጭት እና ያለመረጋጋት ምንጭ ሊሆን ይችላል የሚል እምነት አለኝ፡፡ የሙርሲ ሚኒስትሮች ስለታኢሕግ/GERD ከግንባታ ጀምሮ እስከ ፍጻሜ ድረስ ሊፈጽሟቸው የሚገቡ የግብጽን ስልታዊ ዕቅድ ተጨባጭነት ባለው ሁኔታ መሰረቱን ጥለዋል የሚል ሀሳብ አለኝ፡፡ ግልጽ እና አጭር በሆነ አገላለጽ የሚከተሉትን ስልቶች የሚከተሉ ይሆናሉ፣

1ኛ) በተቻለ መጠን የዲፕሎማሲ (አንዳንድ ጊዜ ዳምፕሎማሲ/ዲፕሎማሲን ማስወገድ ከሚሉ ቃላት ጋር አጣምሬ እጠቀማለሁ) ጥረቶችን በሙሉ አሟጥጦ መጠቀም፣

2ኛ) የዓለም አቀፍ ሕጎችን መከተል፣ ማለትም የፍትህ እና የዕርቅ ውሳኔዎችን መፈለግ እና መሞከር፣

3ኛ) በተራ ቁጥር 1 እና 2 ላይ የተጠቀሱት ነገሮች ውጤት ካላስገኙ እና ውድቅ ከሆኑ የግብጽን ደህንነት ከአደጋ ላይ የሚጥሉ ማናቸውንም ግድቦች ለመደምሰስ የስለላ ወኪሎቻችንን መጠቀም…ያ ህንጻ ይኸ ግድብ በግብጽ ላይ ጦርነት ከማወጅ ጋር እኩል ነው…

የጦርነት ጉምጉምታ ሁልጊዜ እውነተኛ ጦርነት ሊካሄድ እንደሚችል አስቀድሞ የሚነግር ትንበያ ሰጭ ነው፡፡ በግብጽ ከፍተኛ መሪዎች እና በሌሎች በግብጽ ተመሳሳይ ነገር ይካሄዳል ብለው በሚገምቱ ሰዎች እምነት መሰረት በግብጽ ምንም ዓይነት የጦርነት ጢስ አይታይም ብሎ መደምደም ከባድ ነገር ነው፡፡ እ.ኤ.አ የካቲት 2013 የሳውዲ አረቢያ ምክትል መከላከያ ሚኒስትር የሆኑት ልዑል ካሊድ ቢን ሱልጣን በካይሮ በተካሄደው የአረብ የውኃ ምክር ቤት ጉባኤ ላይ በመገኘት ሀገራቸው የታኢሕግ/GERDን ሁኔታ በደበዘዘ መልኩ እንደምትመለከተው በኢትዮጵያ ላለው ገዥ አካል ግልጽ በማድረግ የቀስት ደጋናቸውን አነጣጥረው ተኩሰዋል፡፡ እንደ ልዑል ካልዲ ግድቡ የሚደረመስ ከሆነ ሱዳን ሙሉ በሙሉ በጎርፉ ትሰጥማለች፣ እና የዚህ ጦስ ጉዳይ ወደ አስዋን ግድብም ይደርሳል… ልዑሉ ግድቡ ለፖለቲካ ጠቀሜታ ሳይሆን ለፖለቲካ ሸፍጥ ሲባል የሱዳንን እና የግብጽን ደህንነት አደጋ ላይ ለመጣል ታስቦ ከሱዳን ወሰን አጠገብ በቅርብ ርቀት ላይ እየተገነባ ነው ያለው… ልዑሉ በኢትዮጵያ ያለውን ገዥ አካል የአረብን ህዝብ በመጉዳት በሚል ከሶታል፡፡ እንዲህ ብሎታል፣ “በሱዳን እና በግብጽ የውኃ ሀብቶች ላይ ምስቅልቅል ሁኔታን የሚፈጥሩ በኢትዮጵያ አዕምሮ እና አካላት ላይ መሰረት ያደረጉ እጆች አሉ፡፡ አነርሱ እራሳቸው ጥቅማቸውን ሳያገኙ አረቦችን ሊጎዱ የሚችሉባቸውን አጋጣሚዎች ሊያዘጋጁ አይችሉም…“

ባለፈው ሳምንት “በመርሆዎቹ ድንጋጌዎች” እና “የዓባይ ተፋሰስ ሀገሮች የጋራ የውኃ አጠቃቀም ስምምነት” በሚል ርዕስ የተፈረመው በዓለም አቀፍ የመገናኛ ዘዴዎች የተዘገበው ስምምነት በአህጉሩ ቀጣና የጦርነት መከሰትን ሊያሰቀር ይችላልን? በቅርብ ጊዜ ውስጥ በድንጋጌው ላይ ዝርዝር የሕግ እና የፖለቲካ ትንተና ይዠ የምመለስበት ይሆናል፣ (ከዚህ በታች የመግቢያ ምልከታዎችን እንድታነቡ እጋብዛለሁ) ሆኖም ግን አሁን ለማለት የምፈልገው በዚህ ጉባኤ ከማስመሰል ውጭ ምንም ፋይዳ ያለው ነገር እንደማይኖር እና የሶስቱ ሀገሮች ባለስልጣናት በረዥም ወንበሮች ተቀምጠው ፊት ለፊት ከመተያየት ያለፈ ታላቅ ወጭ የሚጠይቀውን ጦርነት ለማስወገድ የማስመሰያ ተውኔት ከመስራት በስተቀር ወደ ቋት ጠብ የሚል ነገር እንደሌለ በግልጽ የሚያመላክቱ በርካታ ጉዳዮች አሉ፡፡

ግብጽ በግድቡ ምክንያት ወደ ጦርነት ሊያስኬዱ የሚችሉትን ምክንያቶች አስቀድማ በዝርዝር አስቀምጣለች፡፡ ጦርነትን እንደ መጨረሻ አማራጭ አድርጋ እንዳስቀመጠች እና ይህም ጦርነት ፍትሀዊ የሆነ ጦርነት እንደሆነ አድርጋ እንደምትቆጥር እምነት ማሳደሯን ግልጽ አድርጋለች፡፡ ምንም ዓይነት ድንጋጌ የለም፣ ከፓርላማ በፊት ምንም ዓይነት ንግግር የለም፣ ፍቅርን የመግለጽ፣ ወይም ደግሞ ፈንጠዝያ እና ቸበርቻቻ ማድረግ ያለውን እውነታ ሊደብቀው በፍጹም አይችልም፡፡

አሁንም እንደገና እውነታዎችን እና የማስረጃ አካሎችን እንመልከት፣

ፕሬዚዳንት አንዋር ሳዳት እ.ኤ.አ በ1978 እንዲህ በማለት አውጀው ነበር፣ “በናይል ወንዝ ውኃ ላይ መቶ በመቶ ለህይወታችን ጥገኛ ነን፣ ስለሆነም ማንም ሰው ቢሆን በማንኛውም ጊዜ የእኛን ህይወት ለማቆም ሙከራ የሚያደርግ ከሆነ ወደ ጦርነት ከመሄድ በፍጹም አናወላውልም፡፡“

ቡትሮስ ቡትሮስ ጋሊ የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴዔታ በነበሩበት ጊዜ (በኋላ የተባበሩት መንግስታት ዋና ጸሐፊ የነበሩ) “በአሁጉራችን በቀጣይነት የፖለቲካ ጦርነት ሳይሆን በናይል ውኃ የሚደረግ ጦርነት ነው“ በማለት ሀሳባቸውን የገለጹበት ሁኔታ ይህንኑ ሀቅ የሚያረጋግጥ ተመሳሳይ ነገር ነው፡፡ በህይወታችን ላይ ቀውስን የሚያስከትል ሁኔታ የሚፈጠር ከሆነ ግድቡን ሊያደባይ የሚችል ጀት እንልካለን እናም በአንድ ቀን ውስጥ እንዲመለስ እናደርጋለን፣ የዚያን ያህል ቀላል ነገር ነው፡፡

ከአሜሪካ የግል የደህንነት ድርጅት ከስትራትፎር፣ ከግል የጅኦፖለቲካ የስለላ ድርጅትና አማካሪ ድርጅት በተላከ ኢሜይል ምንጩን ጠቅሶ ዊኪሊሊስ ይፋ እንዳደረገው ከፍተኛ የግብጽ የደህንነት ኃይሎች በቀጥታ ከሙባረክ እና ከሱሌማን ጋር በየጊዜው እየተገኙ ይለዋወጡት የነበረውን ጉዳይ እንዲህ በማለት ግልጽ አድርጎታል፣ “ቀውስ የሚከተል ከሆነ ግድቡን በቦምብ ለማጋየት ጀት እንልካለን እናም በአንድ ቀን እንመለሳለን፣ የዚያን ያህል ቀላል ነገር ነው፡፡ ወይም ደግሞ ግድቡን ለማስቆም የእኛን ልዩ ኃይል እንልካለን፡፡ ሆኖም ግን አሁን የወታደራዊ አማራጭን እንደ ዋና አማራጭ አንወስደውም፡፡ ይኸ በእርግጥ የመጠባበቂያ ዕቅዳችን ነው፡፡ እ.ኤ.አ በ1970ዎቹ ሁለተኛው አጋማሽ ላይ ግብጽ የወሰደችውን ወታደራዊ ግዳጅ እስቲ መለስ ብለን እንመልከት፡፡ እንደዚሁም እ.ኤ.አ በ1976 ኢትዮጵያ ልትገነባው ሞክራ የነበረውን ታላቅ ግድብ ላስታውስ፣ ሁሉንም መሳሪያዎች በባህር ጉዞ ላይ እንዳሉ ዶግ አመድ ነው ያደረግናቸው፡፡“

ባለፈው ሳምንት ስትራትፎር ስለስምምነቱ ድንጋጌ በሰጡት ትንታኔ እንዲህ ከሚል መደምደሚያ ላይ ደርሰዋል፣ “ከእነዚህ ድርድሮች የፈለገውን ያህል ስምምነት ቢደረግም ግብጽን ማስገደድ የሚቻልበት ሁኔታ ሊፈጠር አይችልም፡፡ ከወታደራዊ አማራጭ ውጭ እና ከውጭ ዋስትና መስጠት ውጭ ኢትዮጵያ በምትፈልግበት ጊዜ ስምምነቱን ለመጣስ ትችላለች፡፡ ስለሆነም የቱንም ያህል ስምምነት ቢኖርም በአጭር ጊዜ የዕይታ አድማስ በፕሮጀክቱ ላይ ቀጣይነት ያለው ውጥረት እንዳንዣብብበት የሚቀጥል ይሆናል“ (አጽንኦ ተደርጓል፡፡)

የስትራትፎር ትንተና ትክክል ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡ ግብጽ አንድ ጊዜ ውስጣዊ መረጋጋትን ካረጋጋጠች እና አልሲስ ስልጣናቸውን እያጠናከሩ ከመጡ የእርሳቸው የእድሜ ልክ የፕሬዚዳንትነት መቆያ ትኬታቸው አድርገው እንደዋስትና የሚይዙት በኢትዮጵያ ላይ ጦርነትን ለመክፈት በታኢሕግ/GERD ላይ የጦርነት ነጋሪትን መጎሰም ነው፡፡ ቃሎቼን ግልጽ ላድረግ! አልሲሲ በግብጽ ላይ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየከፋ የመጣውን የምጣኔ ሀብት ችግር ኢትዮጵያን እንደዋና ችግር ፈጣሪ አድርጎ የማቅረብ ዘዴን ሊጠቀሙ ይችላሉ የሚል እምነት አለኝ፡፡ “የአምባገነኖች መጽሐፍ የመጀመሪያው ምዕራፍ ስልጣናቸውን ለማቆየት ሲሉ ውጫዊ ጠላት የመፈለግ እና የህዝቡን አመለካከት ሁሉ ወደዚያው እንዲያዘነብል የማድረግ አባዜ ነው፡፡” አልሲሲ ስልጣናቸውን ለማራዘም እና የህዝቡን ስሜት ለማስቀየስ ሀገራቸው ከገጠሟት በርካታ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ምጣኔ ሀብታዊ ቀውሶች ውስጥ ለመውጣት ሲሉ በኢትዮጵያ ላይ ጭራቃዊነት ድርጊትን መፈጸም እና ታኢሕግ/GERDን ጥላሸት መቀባት ይጀምራሉ ብየ እገምታለሁ፡፡ በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ ስልታዊ የሆነ የአየር ላይ ጥቃት አናሳነት ምክንያት የግብጽ የጦር ኃይል በግድቡ ላይ ወታደራዊ እርምጃ ከመውሰድ ሊታቀብ ይችላል ከሚሉት ከስትራፎር ግምቶች እና ትንታኔዎች ጋር አልስማማም፡፡ ከዚህ አንጻር የእንግሊዝ የወታደራዊ ግዳጅ ፈጻሚ ቡድን እ.ኤ.አ ግንቦት 1943 በጀርመን ግድቦች ላይ ፈጽሞት የነበረውን ድርጊት ማስታወስ ለዚህ እንደጉልህ ማስረጃ ሊሆን ይችላል፡፡ በእርግጥ የእኔ ሀሳቦች መሰረት ያደረጉት ቀላል የሆኑ እና የተለመዱትን ወታደራዊ ታሪኮችን በቢሮ ሆኖ የማጥናት እና የሰነድ ዳሰሳ ማድረግ ነው፡፡

በድንጋጌ መርሆዎች ላይ የሚታዩ ቅድመ ሁኔታዎች፣

ወደፊት በጊዜ ሂደት በድንጋጌ መርሆዎች ላይ ሰፋ ያለ ትንታኔ እንደምሰጥ እገምታለሁ፡፡ አሁን ጥቂት ቅድመ ሁኔታዎች ላይ ያለኝን ምልከታ ግልጽ አደርጋለሁ፡፡

በመጀመሪያ ደረጃ በጠረጴዛ ዙሪያ የተደረገው የድንጋጌ መርሆዎች ሰነድ ምንም የሚያመጣው አዲስ ነገር የለም፡፡ እንዳረጀው እና እንዲህ እንደሚለው የጀምስ ብራውን ሙዚቃ ነው፣ “ድምጽን ከፍ አድርጎ መናገር ሆኖም ግን ምንም ነገር አለማለት ወይም አለማድረግ፡፡“ የሶስቱ ሀገሮች መሪዎች ከስምምነቱ በኋላ ታላቅ የፎቶግራፍ መነሳት ስነስርዓትን አካሂደዋል፣ እናም ብዙ ነገሮችን ተናግረዋል ሆኖም ግን እኔ እንደተመለከትኩት ከሆነ በወረቀት ተጠቅልሎ እንደሚሸጠው ከረሜላ ዓይነት ነገር ነው፡፡

እስቲ በድንጋጌው ላይ የሰፈረውን የጽሁፍ ማስረጃ ለመመርመር እንሞክር፡፡ መርሆዎችን ለመተግበር እንዲችሉ ተደራዳሪዎቹ ጥሩ ጎረቤታሞች መሆን መቻላቸውን ማረጋገጥ አለባቸው (መ1)፣ ኃይል ለምጣኔ ሀብት ዕድገት አስፈላጊ መሆኑን ማወቅ አለባቸው (መ2)፣ ከናይል ወንዝ ጋር በተያያዘ መልኩ ጉዳት ሊያስከትል የሚችል ማንኛውንም ነገር ማስወገድ አለባቸው (መ3)፣ የናይል ተፋሰስ ሀገሮች የማህበራዊ፣ የምጣኔ ሀብት ተጠቃሚነት ፍላጎታቸውን በማካተት ፍትሀዊ የውኃ አጠቃቀም እንዲኖር ፍጎታቸውን መግለጽ (መ4)፣ በግድቡ የመጀመሪያ የመሙላት ሂደት ላይ እያንዳንዳቸው እየተመካከሩ እና በቀጣይነትም የግድቡን አሰራር በጋራ ለማየት ፍላጎት ማሳደር (መ5)፣ ለታችኛው ተፋሰስ ሀገሮች የኃይል ሽያጭ ቅድሚያ መብት በመስጠት እያንዳንዳቸው በሌላኛቸው ላይ እምነት እንዲኖራቸው ጥረት ማድረግ (መ6)፣ ግድቡን የሚመለከቱ ማናቸውንም የመረጃ ልውውጦች ማድረግ መቻል (መ7)፣ የግድቡን አጠቃላይ የግንባታ ስትራክቸር ደህንነት ለመጠበቅ ትብብር ማሳየት (መ8)፣ እኩል በሆነ ሉዓላዊነት፣ አንድነት እና የግዛት አንድነት ላይ በተመሰረተ መልኩ በጋራ መስራት (መ9)፣ እንደዚሁም ሁሉ የሚነሱ ውዝግቦችን በውይይት እና በስምምነት መፈጸም የሚሉ ናቸው፡፡

በድንጋጌው ላይ ተደራዳሪዎቹ ያስቀመጡት ዋስትና፣ ማስገደጃ፣ ማረጋገጫ ወይም ደግሞ ቃል የተገባባቸውን ስምምነቶች በተገባው ቃል መሰረት ወደ ተግባር መሸጋገራቸውን ሊያሳዩ የሚችሉ ነገሮች ወይም ከስምምነቱ ውጭ የሄደ አካል ካለ በምን መልኩ እልባት ሊያገኝ የሚችልበት መንገድ እንዳለ ሊያመላክት የሚችል ነገር በግልጽ አልተቀመጠም፡፡ ድንጋጌው ወደፊት በቀጣይነት ሁሉም የሚገዙበት ስምምነት መሆን አለመሆኑን ሊያሳይ የሚችል ነገር አልታየም፡፡ ሁልጊዜ እንደሚደረገው የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ የድንጋጌውን ዝርዝር ሁኔታዎች ሁሉ ሚስጥር አድርጎ ይዟል፡፡ ስምምነቱን ከመፈራረማቸው በፊት በህዝብ ፊት በአደባባይ ውይይት እንዲደረግባቸው አልተደረገም፡፡ የይሰሙላው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ሁሉጊዜ አደናጋሪ ሆኖ በሚቀርበው ልምዱ መሰረት እንዲህ በማለት ንግግር አሰምቷል፣ “የታኢሕግ/GERD በሶስቱም መንግስታት በተለይም በግብጽ ህዝቦች ላይ ምንም ዓይነት ጉዳት እንደማያስከትል ላረጋግጥላችሁ እወዳለሁ:: የግብጹ ፕሬዚዳንት በተመሳሳይ መልኩ እንዲህ ብለዋል፣ “ለልማት ስንል በትብብር መስራትን እና እርስ በእርሳችን መተማመንን መርጠናል፡፡” እንዲህ የሚለውን የአባቶችን አባባል አስታወሰኝ፣ “በሌቦች መካከል መከባበር አይኖርም፡፡” በዘራፊ ወሮበላ አምባገኖኖች መካከል መተማመን ሊኖር አይችልም እላለሁ፡፡ በሀገሮች መካከል እንደዚህ ያለ መተማመን ይኖራል የሚል እምነት የለኝም፡፡ የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት ኔቪል ቻምበርሊን ከድንጋጌ የበለጠ ጠቃሚ የነበረውን መሳሪያ እ.ኤ.አ በ1938 ሂትለር የሙኒክን ስምምነት በፈረመበት ጊዚ አምነውት ነበር፡፡ ቻምበርሊን እንዲህ በማለት በእምነት ብቻ ከሁሉም ማረጋገጫ በፊት አወጁ፣ “በአሁኑ ጊዜ ሰላም“ ያስፈልጋል፡፡ በአሁኑ ጊዚያችን ሰላምን ከማስፈን ይልቅ ዓለም ከምንጊዜውም በላይ አስከፊ የሆነውን ጦርነት ተከሰተ፡፡

ይኸ ሁሉ ነገር ምን ማለት ነው?

በእኔ አመለካከት ድንጋጌው በርካታ የሆኑ አስቸጋሪ ጥያቄዎችን የሚያስነሳ ጉዳይ ነው፡፡ ሶስቱም ተደራዳሪዎች ሌሎች የበለጠ ተግባራዊ ሊሆኑ የሚችሉ ወደፊትም ጠቃሚ ሊሆኑ የሚችሉ መሳሪያዎችን ለምሳሌም ሀሳብን መለዋወጥ፣ የጋራ ግንዛቤ ማስታዋሻ፣ ተቻችሎ በሰላም መኖር፣ ስምምነት፣ ወዘተ የሚሉትን የዲፕሎማሲ ቃላት ከመጠቀም ይልቅ ለምንድን ነው ድንጋጌ የሚለውን የዲፕሎማሲ ቋንቋ ለመጠቀም የመረጡት?

በዓለም አቀፍ ሕግ መርሆዎች ስር ድንጋጌ ማለት ለህጻናት የልደት ስጦታ ከሚያቀርበው የገና ስጦታ አባት ባዶ ተስፋ ጋር እኩል ነው፡፡ ይህ የዲፕሎማሲ ቋንቋ በህግ ዝቅተኛ የሆነ የተፈጻሚነት ደረጃ ያለው እና መንግስታት ጊዜ ለመሸመት ሲሉ በጥቅም ላይ የሚያውሉት መሳሪያ ነው፡፡ ድንጋጌ በጣም አልፎ አልፎ ከተቻለም ከስንት አንድ ጊዜ ብቻ የሕግ አስገዳጅነት ሚናን ሊጫወት ይችላል፡፡

ድንጋጌ በዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት የህግ ሂደት ላይ ተፈጻሚነት የሚኖረው አይደለም፡፡ (አንቀጽ 92፣ የተባበሩት መንግስታት ቻርተርን ይመለከቷል፡፡) ‘ድንጋጌ’ የጦርነት ዳመና ሲያንዣብብ እና ተጎጂዎችን ለመርዳት ሲፈለግ መልካም ምኞትን፣ ዝንባሌን እና ተስፋን ለመግለጽ ሲባል በአገልግሎት ላይ የሚውል የሕግ መሳሪያ ነው፡፡

ድንጋጌ በሚለው የቃል እና የቋንቋ አጠቃቀም ላይ ሁሉም ተደራዳሪ ወገኖች በመጨረሻ መርሆዎችን ወደ ተግባር በማሸጋገር የመንግስታቱ የድርጊት መገለጫ የማድረግ እና እራሳቸውንም ለመርሆዎቹ ተገዥ እንዲሆኑ ሊያስገድዳቸው የሚችል የሕግ ማዕቀፍ አይታይም፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ስለድንጋጌው ፖለቲካዊ ጠቀሜታ ያየሁት ምንም ዓይነት ነገር የለም፡፡ ድንጋጌ ከሚለው ቃል በመነሳት ተደራዳሪዎች ምን ለማከናወን እንዳሰቡ በተለይም ደግሞ ቀደም ሲል ከነበራቸው ያለመተማመን እና ጥላሸት የመቀባባት ግንኙነት አኳያ ሊያደርጉ የፈለጉት ነገር ግልጽ አይደለም፡፡ እንዳለ በጥሬው ሲታይ ግን ለሕዝብ ግንኙት ስራ ሲባል አንድ ጋዜጠኛ እንደሚያዘጋጀው ዜና ዓይነት በመሆን በነገሩ ላይ እንድደመም አድርጎኛል፡፡ እኔ እንደሚሰማኝ እና እንደሚታየኝ የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ አመራሮች ለታኢሕግ/GERD ማንቀሳቀሻ ግንዘብ በማጣት በውጥረት ላይ ባሉበት በአሁኑ ጊዜ እንደዚህ ያለ የአደባባይ ስምምነትን ማድረግ ዓላማው የህዝብን ስሜት ወደ ሌላ አቅጣጫ ለማስቀየስ የታቀደ ሊሆን ይችላል፡፡ ድንጋጌ ቆንጆ የሆነ የማስቀየሻ መሳሪያ፣ ብልጣብልጥነት የታከለበት አካሄድ እና ማንኛውንም የህዝብ ፍላጎት እና ጥያቄን ወደ ጎን በመጣል ወይም ደግሞ በግድቡ ዙሪያ ያለው የገንዘብ እጦት ችግር እንዳይታወቅ ለማድረግ አዋጭ በሆነ መልኩ የተዘየደ ብልሀት ሊሆን ይችላል፡፡ የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ህዝቡ ከግብጽ ጋር ስለተደረገው ስለትልቁ ስምምነት እንጅ ምንም ነገር ስለሌለው ባዶ የግድብ ገንዘብ ቦርሳ እንዳይሰማ ይፈለጋል የሚል እምነት አለኝ፡፡ የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ምርጫ ተብየው እየተቃረበ በመጣ ጊዜ ድንጋጌ የሚል ስምምነትን በማናፈስ ጊዜ የመግዛትን ስሌት የመቀመር ቁማር ሊሆን ይችላል፡፡

እውነታው ፍርጥ እና ፍርጥርጥ ብሎ ሲታይ ግን ለገዥው ፓርቲ የስልጣን እድሜ ለማራዘም ለይስሙላ የተቀመጠው የህዝብ ተወካዮች ተብየ አሻንጉሊት ስብስብ በግድቡ ግንባታ ዙሪያ ያለውን ገንዘብ በሚመለከት የተጠያቂነት እና ግልጸኝነት ጥያቄን አንግቦ ለህዝብ ሀብት ሲባል ጥያቄ ሊያቀርብ የሚገባበት አጋጣሚ ነው፡፡ በእርግጥ ይህ ሊደረግ እንደማይችል ይታወቃል፡፡

ስለአወዛጋቢ ጉዳዮች ምክንያታዊ የሆኑ ጥርጣሬዎችን እንዳነሳ ሙያየ የፈጠረብኝ ችግር ነው፡፡ ስለሆነም ከታመኑ የውስጥ የመረጃ ምንጮች ባገኘሁት መረጃ መሰረት የግድቡ የግንባታ ስራ ከፍተኛ በሆነ በገንዘብ እጥረት ችግር ውስጥ ተተብትቦ እንደሚገኝ በምሰማበት ጊዜ የገንዘብ እጦት ኪሳራ፣ በእዳ ኪሳራ ውስጥ መውደቅ የሚሉት ቃላት በጆሮዎቼ ውስጥ አቃጨሉ፡፡

ይህ በእኔ ስሌታዊ አንደበት የሚተነበይ ተራ ነገር አይደለም፡፡ ከጥቂት ሳምንታት በፊት ካሩቱሪ ግሎባል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ የተባለ በዓለም ላይ ከፍተኛ የሆነ የተቀጠፈ የጽጌረዳ አበባ በገፍ ወደ ውጭ ሀገር እያወጣ ለገበያ የሚያቀርብ ኩባንያ ኢትዮጵያን በአጭር ጊዜ ውስጥ የአፍሪካ የዳቦ ቅርጫት ለማድረግ ምሎ እና ተገዝቶ ምርጥ እና ለም የሆኑትን በጋምቤላ ክልል ህዝብን በማፈናቀል ከገዥው አካል ከተረከበ በኋላ በአስር ሚሊዮን ዶላር የሚገመት ኪሳራውን ተከናንቦ ከሀገር ጥርግ ብሎ ወጥቶ ሄዷል፡፡ የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ በታኢሕገ/GERD ግድብ ግንባታ ዙሪያ በደረሰበት ኪሳራ መሰረት ከፍተኛ ቦንድ የገዙትን በማሞኘት እንደ ካሩቱሪ ፕሮጀክቱን እርግፍ አድርጎ ትቶ ይቀመጥ ይሆን አይሆን እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ እጅግ በጣም ተጠራጣሪ ለመሆን አልፈልግም ሆኖም ግን ታኢሕግ/GERD በአንጎላ እንዳለችው ባለ4 ቢሊዮን ዶላር አሮጌ ከተማ ወይንም ደግሞ በቻይና እንደሚገኙት በርካታ አሮጌ እና ያፈጁ እና ያረጁ ከተሞች ሁሉ ተገትሮ እንደሚቀር የሚያረጋግጥ ሁኔታ ነው፡፡ የተተወ የወደቀ ግድብ!?

ስለግድቡ የገንዘብ አሰባሰብ ሁኔታ የነበረኝ ስጋት በእርግጠኝነት ስህተት ነበርን? የግድቡን የግንባታ ስራ ገንዘብ ለማግኘት የነበረው ስጋቴ ኢላማውን ስቷልን?

እ.ኤ.አ በ1969 በተፈረመው የቬና ስምምነት መሰረት “በተባበሩት መንግስታት ቻርተር በሕግ ስምምነቶች፣ እና በአንቀጽ 102 እና በተለይም በአንቀጽ 36 (2) “በእያንዳንዱ የተባበሩት መንግስታት አባል ሀገር በአሁኑ ጊዜ ያለው ቻርተር ተፈጻሚነት እንዲኖረው ከተደረገ በኋላ እያንዳንዱ ስምምነት ወዲያውኑ በሴክሬታሪያቱ ተመዝግቦ ይፋ ይደረግ እና እንዲታተም ይደረጋል ከሚለው ድንጋጌ ጋር ሌላ አስቸጋሪ የሆነ የሕግ ጉዳይ የሚነሳ ይሆናል፡፡

ከዚህ አንጻር እነዚህ ሶስቱ ተደራዳሪ ሀገሮች ያደረጉትን ድንጋጌ ከግምት ውስጥ በማስገባት እያንዳንዳቸው ለሚያሳዩት ለመልካም ፍላጎት እና ለመርሆዎቹ ተፈጻሚነት ከሴክሬታሪያቱ በመቅረብ ለመመዝገብ ጥረት አድርገዋልን? የድንጋጌው አንቀጽ 6 ስለመተማመን ያትታል፡፡ እነዚህ ሶስቱ ተደራዳሪዎች ከታኢሕግ/GERD ጋር በተያያዘ መልኩ ቀደም ሲል ከነበራቸው የጥላቻ ቁርሾ አንጻር ተደራዳሪዎቹ በአንቀጽ 36 (2) መሰረት ለድንጋጌው ምዝገባ ቢያደርጉ ኖሮ መተማመን እና በእራስ ላይ የመተማመን ሁኔታ ሊያድግ እና ሊጨምር ይችል ነበርን? የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ የድንጋጌውን የስምምነት መርሆዎች አክብሮ ተግባራዊ ያደርጋል የሚል እምነት የለኝም፡፡ አሁንም እንደገና ማስረጃዎችን እንፈትሽ፡፡

የኢትዮጵያ ሕገ መንግስት አንቀጽ 13 (2) የሚከተሉትን መብቶች ያጎናጽፋል፣ “በዚህ ምዕራፍ ላይ የተዘረዘሩት መሰረታዊ መብቶች እና ነጻነቶች ከተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብቶች ድንጋጌ/Universal Declaration of Human Rights (UDHR) ትርጉም ጋር በተጣጣመ መልኩ ተተርጉመው ተፈጻሚ ይሆናሉ…“ UDHR እንደ ድንጋጌ የሕግ አስገዳጅነት የለውም፣ እራሱንም አያስገድድም፡፡

UDHR ለምሳሌ እንዲህ የሚልን መብት ያጎናጽፋል፣ “ማንም ቢሆን ከሕግ አግባብ ውጭ በዘፈቀደ በቁጥጥር ስር አይውልም፣ አይታሰርም ወይም ደግሞ ወደ ግዞት እንዲወርድ አይደረግም“ (አንቀጽ 9)፡፡ ሁልጊዜ የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችን እና ሰላማዊ አመጸኞችን ከሕግ አግባብ ውጭ ያስራል፡፡ እንደዚሁም ሁሉ ሕገ መንግስቱ የሚከተሉትን መብቶች ያጎናጽፋል፣ “ማንም ሰው ቢሆን ጉዳዩ ነጻ እና ከወገንተኝነት በጸዳ የፍትህ አካል በመቅረብ ሙሉ እኩልነት ያለው እንዲሁም ፍትህ የማግኘት እና በህዝብ ዘንድም የመሰማት መብት አለው“ (አንቀጽ 10)፡፡ ሆኖም ግን የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ለሩብ ምዕተ ዓመት ያህል የይስሙላ የዝንጀሮ ፍርድ ቤት በማቋቋም ፍትህን እርሱ በሚፈልገው መልኩ ሲያዛባ እና ሲያጣምም ቆይቷል፣ አሁንም በስፋት ቀጥሎበት ይገኛል፡፡ UDHR እንዲህ የሚል መብትን ያጎናጽፋል፣ “ማንም በወንጀለኛ መቅጫ ሕጉ ክስ የተመሰረተበት ሰው ጥፋተኝነቱ በፍርድ ቤት እስካልተረጋገጠ ድረስ ከወንጀለኛነት ነጻ ነው፡፡“ (አንቀፅ 11)፡፡ ሆኖም ግን የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ከዚህ ተጻረሪ በሆነ መልኩ በማህበራዊ መገናኛ ደረ ገጾቻቸው አማካይነት የእራሳቸውን ሀሳብ በመግለጻቸው ብቻ ወጣት ጦማሪያኑን በማጎሪያ እስር ቤቱ አስግብቶ እያማቀቀ እና ምንም ዓይነት ዋስትና እንዳይሰጣቸው በመከልከል በዝንጀሮው የይስሙላ ፍርድ ቤት በተንዛዛ ቀጠሮ እያመላለሰ እያሰቃያቸው ይገኛል፡፡

UDHR እንዲህ የሚለውን መብት ያጎናጽፋል፣ “ማንም ሰው ቢሆን ሀሳቡን የመግለጽ እና የመጻፍ መብት አለው፡፡ ይህ መብት ያለማንም ጣልቃገብነት ሀሳብን ያለመገለጽ፣ መረጃ የመሻት፣ የመቀበል እና የማካፈል እንዲሁም በማንኛውም መገናኛ ዘዴ ማንም ጣልቃ ሳይገባ ሀሳቡን የመግለጽ መብት አለው፡፡“ (አንቀጽ 19) እንደዚሁም ሁሉ የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ከዚህ አንቀጽ ጋር ተጻራሪ በሆነ መልኩ ሁሉንም የነጻው ፕሬስ መገናኛ ዘዴዎችን የዘጋ ሲሆን ጋዜጠኞችንም እያሳደደ በመያዝ በእስር ቤት አጉሯቸው ይገኛል፡፡ የተረፉት ደግሞ በቦሌም በባሌም እያሉ የትውልድ ሀገራቸውን እየለቀቁ እንዲሰደዱ አድርጓል፡፡

ስለዚህ ጥርስ የሚያስነክሱ እንዲህ የሚሉ ጥያቄዎች አሉኝ፣ 1ኛ) የናይል ድንጋጌ ወረቀቱ የተጻፈበትን ያህል ዋጋ አለውን? 2ኛ) እራሱን ህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ (ህወሀት) እያለ የሚጠራው ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ እስከ አሁን ድረስ ባለው ታሪኩ እንደሚታወቀው ከዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ድንጋጌ/UDHR ሰነድ ላይ እየኮረጀ በይስሙላው የሕገ መንግስት ሰነዱ ላይ ያካተታቸው የሕገ መንግስቱን መብቶች በጠራራ ጸሐይ እየደፈጠጠ ያለ ፈጣጣ ፍጡር ባለ10 ነጥቦችን የናይል ተፋሰስ ሶስት ሀገሮች ድንጋጌን ሊያከብር ይችላል ተብሎ ሊታመን ይችላልን

በአፍሪካ ከድንበር፣ ከጎሳ፣ እና ከማህበረሰብ ጦርነቶች ወደ ውኃ ጦርነቶች፣

ከአየር ንብረት ለውጥ፣ ከህዝብ ዕድገት፣ ከፖለቲካ እና ከአህጉራዊ አለመረጋጋት የበለጠ በአፍሪካ በቀጣዮቹ አስርት ዓመት ውኃ ዋነኛ የግጭት መንስዔ ሊሆን ይችላል፡፡

በደቡባዊ አፍሪካ የማላዊ ሐይቅ በማላዊ፣ በታንዛኒያ እና በሞዛምቢክ መካከል በይገበኛል ጥያቄ ምክንያት ሐይቁ የግጭት መንስዔ ሊሆን ችሏል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ወደ ዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት በመሄድ ጉዳዩ በፍርድ ቤቱ በመታየት ላይ ይገኛል፡፡ ከአንጎላ በመመንጨት ወደ ናሚቢያ የሚፈሰው እና ቦትስዋና የሚቀረው የኩይቶ ወንዝ ከጊዜ ወደ ጊዜ የግጭት መንስዔ ምንጭ በመሆን ላይ ይገኛል፡፡ ናሚቢያ እና ቦትስዋና በጮቤ ወንዝ ላይ የቃላት ጦርነትን ሲያካሂዱ ቆይተው በአሁኑ ጊዜ ጉዳያቸው ለዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት ቀርቦ በመታየት ላይ ይገኛል፡፡ ቡርኪና ፋሶ እና ጋና በቮልታ ሸለቆ በሚፈስሰው ውኃ በተለይም ጋና ለሀይድሮ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ የበለጠ ፍላጎት እያሳየች በመምጣቷ ምክንያት በመፋጠጥ ላይ ይገኛሉ፡፡ ስምንት የደቡብ ሀገሮችን አቋርጦ የሚፈስሰው የዛምቤዚ ወንዝ እዚህን ሀገሮች ወደ ግጭት ስቦ ሊያስገባ ይችላል፡፡

ጥላሸት የመቀባት እና መልዓክ አድርጎ የማቅረብ ጨዋታ፣ አደጋ ተንባዮች፣ ሁሉን ነገር ተቃዋሚዎች እና የቅንጦት ዕቃዎች፣

እውነታዎችን በመረጃ አስደግፌ የክርክር ጭብጤን ለዓለም አቀፉ ማህበሰቡ ለህሊና የፍርድ አደባባይ ማቅብ የኢትዮጵያን መንግስት ጥላሸት መቀባት ነው ከሚለው ጋር የማይገኛኝ እና የተሳሳተ አቀራረብ ነው፡፡ እኔ ጥላሸት የመቀባት እና አግዝፎ እና መልአክ አስመስሎ የማቅረብ ጨዋታ አልጫወትም፡፡ እንደዚሁም ሁሉ ዕድልን እና ዕጣ ፈንታን ለመወሰን ወደ ጥንቆላ የምገባ ሰው አይደለሁም፡፡ ሁሉንም ነገር እንደአየሁት የምጠራ ሰው ነኝ፡፡

እኔ እራሴን ለሁሉም በተለይም ደግሞ በሰብአዊ መብት ጉዳዮች ላይ እኩል የሆነ የትችት ዕድልን የምሰጥ ሰው እንደሆንኩ አድርጌ እቆጥራለሁ፡፡ እኔ እራሴን የሞራል ስብዕና ያለው እና ለነገሮች ሁሉ ትኩረት የምሰጥ መሆኔን አምናለሁ፡፡ ሆኖም ሁልጊዜ ፍትሀዊ ጨዋታን ለመጫወት እሞክራለሁ፡፡ ሊያሳምን የሚችል ተጨባጭ የሆነ መረጃ በእጀ ሳልይዝ ወደ ክርክር ጭብጥ ውስጥ ዘው ብዬ አልገባም፡፡ የእኔ እውነታዎችን የመተርጎም እና ትንታኔ የመስጠት ስልት ከሌሎች ሊለይ ይችል ይሆናል፡፡ የእራሴን የክርክር ጭብጦች ለማቅረብ በምሞክርበት ጊዜ አንደኛውን ዓይነት እውነታ ከሌላኛው ዓይነት እውነታ በልጦ እንዲታይ ለማድረግ አሞክራለሁ፡፡ ይኸ እንግዲህ አድሏዊ የውትወታ ስራ መሆኑ ነው፡፡ ለህግ የበላይነት፣ ለዴሞክራሲ መጎልበት እና ለሰብአዊ መብቶች መከበር ከምንም በላይ አድልኦ አድርጌ የምከራከርላቸው ጉዳዮች ናቸው፡፡ እንደ ሕግ ባለሙያ ሙያዊ ተግባሬ የእራሴን ምክንያት በማቅረብ በዚያ ላይ መከራከር እና ሌሎች በእኔ የክርክር ጭብጥ ላይ እንዲያምኑ ማስቻል ነው፡፡ የፖለቲካ ሳይንቲስት ለእኔ የውትወታ ስራ በመስራት ላይ አነስተኛ የሆነ ተግባብኦ ያለው እና ከዚህ ይልቅ የበለጠ ትኩረት የሚሰጠው ለፖለቲካ ህልወት እና ተግባራዊ እንቅስቃሴ ነው፡፡ እነዚህን ሁለቱን ነገሮች በሳምንታዊ ትችቴ ላይ እጠቀምባቸዋለሁ፡፡

ለበርካታ ዓመታት አንባቢዎቸ ሆነው የቆዩት ደንበኞቼ አሁን በህይወት የሌለውን የመለስ ዜናዊን እ.ኤ.አ በ2005 ተደርጎ በነበረው ሀገር አቀፍ ምርጫ የተፈጠረውን ውዝግብ ተከትሎ የደህንነት እና የፖሊስ ኃይሉን በእራሱ ቁጥጥር ስር አድርጎ ትዕዛዝ በመስጠት በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰላማዊ ዜጎችን ከአስጨረሰ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ጥብቃ የውትወታ ስራ በይፋ መግባቴን ያስታውሳሉ፡፡ (አዎ፣ ያንን ዘግናኝ እና አሰቃቂ ድርጊት የፈጸሙት ዕኩይ ምግባር የሰፈነባቸው ጭራቆች በሰው ልጆች ላይ ለፈጸሙት ወንጀል በህግ ፊት ቀርበው ፍትህን እስኪያገኙ ድረስ ትግሌን አጠናክሬ እንደምቀጠልና አስቀመቸረሻው አንደምተወትው ለአንባቢዎች ለማስታወስ እወዳለሁ፡፡) ከመለስ እልቂት በፊት በኢትዮጵያ ፖለቲካ ላይ ብዙም ትኩረት አልነበረኝም፡፡ በዚያን ወቅት ያንን የመሰለ ዘግናኝ ድርጊት በዓይኔ በብረቱ ለመመልከት በመቻሌ ከምንም በላይ የተበሳጨሁበት ጊዜ ነበር፡፡ እንደዚያ የነበሩት ምንም የማያውቁ እምቦቃቅላ የነገ ኢትዮጵያ ተስፋዎች ላይ የጥይት እሩምታ የሚያዘንብ ሰው መሳይ ጭራቅ ከነሙሶሊ እና ከእነ ሂትለር ፋሽስት እና ናዚዎች ምን የሚለየው ነገር ይኖራል የሚል እምነት በሂሊናየ ስለተቀረጸ ያንን ግፍ ለፍትህ አካል ለማድረስ ሽንጤን ገትሬ ድምጽ ለሌላቸው ወገኖች ድምጽ በመሆን ወደ ትግሉ ሙሉ በሙሉ ገባሁ፡፡ ሰዎች በግፍ እየተፈጁ እና እየተሰቃዩ እያዩ ዝም ማለት ከጭራቃዊ ድርጊት ፈጻሚዎች ጋር እንደመተባበር ይቆጠራል፡፡

ማንንም ጥላሸት በመቀባት ላይ እምነት የለኝም፡፡ በጭራቆች፣ በመልዓክት እና በሰዎች መካከል ያለውን ልዩነት ጠንቅቄ አውቃለሁ፡፡ ሆኖም ግን ጭራቃዊ ድርጊቶች በየዕለቱ እንደሚፈጸሙ አምናለሁ፡፡ በመቶዎች በሚቆጠሩ ምንም ዓይነት መሳሪያ ባልታጠቁ ንጹሀን ዜጎች ላይ እልቂት መፈጸም የጭራቃዊነት የመጨረሻው ደረጃ ድርጊት ነው፡፡ ከህግ አግባብ ውጭ ጋዜጠኞችን እና ጦማሪያንን ማሰር፣ የይስሙላ የዝንጀሮ ፍርድ ቤቶችን ማቋቋም፣ የህዝብን ድምጽ በይስሙላ ምርጫ ሰበብ በጠራራ ጸሐይ መዝረፍ፣ መጠኑን ያለፈ የመንግስት ድብቅነት እና በሸፍጥ ላይ የተሞላ የሀሰት ቁጥሮችን እየፈበረኩ የምጣኔ ሀብቱ አደገ ተመነደገ የሚባለው ውሸት እና ቅጥፈት ሌላ ምንም ሳይሆን ጭራቃዊነት ድርጊት ነው፡፡ የህግ የበላይነትን መደፍጠጥ፣ የሙስና ግዛትን መመስረት፣ የፖለቲካ ተቃዋሚዎችን እና ሰላማዊ አመጸኞችን ማጥፋት፣ በእስር ቤቶች ውስጥ በህግ ጥላ ስር በቁጥጥር ስር የዋሉትን ዜጎች ማሰቃየት፣ መግደል ስልጣንን ከህግ አግባብ ውጭ መጠቀም፣ ወሮበላ ዘራፊዎች ተሰባስበው መንግስት በመምሰል በዜጎች ላይ ሰይጣናዊ ድርጊትን የሚፈጽሙት ሁሉም በመጽሐፌ ውስጥ ተመዝገበው ያሉት እኩይ ምግባራት ሁሉ የእራሱ የጨለማው ልዑል ድርጊቶች ናቸው፡፡ አካፈን አካፋ ማለት ጥላሸት መቀባት አይደለም፣ በምንም ዓይነት መልኩ ጥላሸት መቀባት ሊሆንም አይችልም፡፡

እኔ በግሌ ከወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ጋር ግላዊ የሆነ ጉዳይ የለኝም ወይም ደግሞ ለህዝብ ከሚያቀርባቸው ስምየለሽ፣ ከድርጅቱ አጧዦች እና አንቀሳቃሾች ጋር የተለየ ነገር የለኝም፡፡ የእኔ ጉዳይ ያለው ከሚያደርጓቸው መሰሪ ድርጊቶች እና ከሚያወጧቸው የተንሻፈፉ ፖሊሲዎቻቸው ላይ ነው፡፡ የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብን ጥላሸት በመቀባት የማተርፈው ምንም ነገር የለኝም፡፡ የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብን ምስል በሳምንቱ በማወጣቸው ትችቶች ላይ በማቅረብ የማገኘው እርካታ የለም፡፡ የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ንጉሶች ልብስ የላቸውም እራቁታቸውን ናቸው በማለት ማጋለጥ የሚሰጠኝ እርካታ የለም፡፡ ሆኖም ግን ያሉትን ተጨባጭ መረጃዎች መሰረት በማድረግ በማቀርባቸው እና በምሰጣቸው ትንታኔዎች የኢትዮጵያን በኃይል ገዥዎች ጥላሸት ከመቀባት ጋር እኩል ነው የሚል ያልተገራ ሀሳብ ካለ ለዚህ ብቸኛው ምላሼ እንዲህ የሚል ይሆናል፡ “ጫማው ልክህ አድርገው፡፡ አልጋውን አንዳነተፍከው ተኛበት“ እንደማለት ነው፡፡

ሁልጊዜ በተደጋጋሚ እንደምለው የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ጅምላ የሰብአዊ መብት ድፍጠጣውን እና የዘር ማጥፋት ድርጊቱን ካቆመ እና የተጠያቂነትን እና ግልጸኝነትን አሰራሮች ከመሰረተ እና የህግ የበላይነትን ካረጋገጠ፣ እራሱ ያወጣዉን ህገ መንግስት የሚያከብር ከሆነ፣ የፍትህ ስርዓት ከማንም ጣልቃገብነት ነጻ ሆኖ መስራት እንዲችል ካደረገ እንዲሁም የምርጫ ዘረፋውን የሚያቆም ከሆነ የእራሱ ቁጥር አንድ አድናቂ እሆናለሁ፡፡

የ2015 ምርጫ መዝሙር እና ዳንስ፣

ባለፈው ሳምንት እና ከዚያም በፊት ስለወጡ ዜናዎች እና ስለተለቀቁ የሚነበቡ ጽሁፎች ለብዙ ሰዎች ልዩ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ጥሩ ነገር እንደተደረገ ሆኖ በወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ሌት ቀን ከበሮ የሚደለቅለት ነገር ወያኔ በእርሱ ጥረት ትልቅ ነገር እንዳደረገ ይህም ድርጊቱ በሀገር አቀፍ እና በአህጉር ደረጃ ታላቅ ነገርን እንዳደረገ ሆኖ እንዲታወቅለት ይፈልጋል፡፡ ሆኖም ግን ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት አስመዘገብን እያሉ ሌት ቀን ስለሚደሰኩሩለት ስለ 11.7 በመቶ የምጣኔ ሀብት ዕድገት ከዚህ በኋላ የሚያወሩበት ወሬ አልቆባቸዋል፡፡ በቅጥፈት ታጅቦ ሲደሰኮርለት የቆየው ዕድገት ባዶ ፕሮፓጋንዳ መሆኑ በተጨባጭ መረጃ ተጋልጦ እርቃኑን የቀረ ከመሆኑም በላይ በአሁኑ ጊዜ ህዝቡም ሳይደናገር በሚገባ እያወቀበት የመጣ ስለሆነ ነው፡፡ ስለዚህ አሁን ደግሞ ጨዋታውን በመቀየር የፊታችን ግንቦት ስለሚካሄደው የይስሙላ ምርጫ ሌላ የማጭበርበር እና የማደናገር ስራቸውን መቀጠል ነው፡፡

ሆኖም ግን በቅድመ ምርጫው ወቅት በውኃ ውስጥ የሰመጠ ሰው ህይወቱን ለመታደግ ሲል ተንሳፎ ያገኘውን ሁሉንም ነገር እንደሚጨብጥ ሁሉ የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብም በአሁኑ ጊዜ በቀጣዮቹ ዓመታትም የጭቆና አገዛዙን ለማስቀጠል በማሰብ በባህር ውስጥ እየሰመጠ ስለሆነ ያገኘውን ሁሉ ከመቧጠጥ ገለባም ቢሆን ከመጨበጥ ወደኋላ አይልም፡፡

በዚህ ዓመት ከጥር ወር ጀምሮ ታላላቅ ያሏቸውን የፕሮፓጋንዳ ስራዎች እየፈበረኩ ለህዝቡ በመጋት ላይ ይገኛሉ፡፡

በሀገሪቱ ውስጥ ልማት ምን ያህል እየተፋጠነ እንደሆነ ለማሳየት ሲባል ግልገል ጊቤ 3 እ.ኤ.አ ሰኔ 2015 (ምርጫው ከተጠናቀቀ ከሳምንት ወይም ከዚያ በላይ) ተጠናቅቆ አገልግሎት መስጠት ይጀምራል፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጸሚ የሆኑት ወ/ሮ አዜብ አስናቀ እንዳቀረቡት ዘገባ ከሆነ እ.ኤ.አ ጥር 2015 “የግልገል ጊቤ 3 ኃይድሮኤሌክትሪክ ኃይል ግድብ ስራ ግንባታ 88 በመቶ የሚሆነው ተጠናቅቋል፡፡“ ብለዋል፡፡

ስራ እንደሚጀምር ቃል የተገባለት የግልገል ጊቤ 3 የኃይድሮ ኤሌክትሪክ ኃይል ግንባታ ፕሮጀክት ፋይዳ የለውም፡፡ የኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ ተመራማሪዎች ቡድን አባል የሆኑት አቲፍ አስናር እንዲህ የሚል የክርክር ጭብጣቸውን ያቀርባሉ፣ “90 በመቶ የተጠናቀቀ ግድብ ምንም ግንባታ እንዳልተካሄደበት ግድብ ዓይነት ዋጋቢስ ሆኖ ይቆጠራል፡፡“ ይህ ሁኔታ ፖለቲከኞች በስንት ጫና እና ጥረት ያሰባሰቡትን ገንዘብ አቀናጅተው ለግድቡ ስራ ካዋሉ እና ግድቡም ተጠናቀቀ ተብሎ አሸሸ ገዳሜ ከተባለ በኋላ ታላቅ መዋዕለ ንዋይ የፈሰሰበት ፕሮጀክት ውድቅ ይሆናል፡፡ የግድብ ስራ ፕሮጀክቶች ከተጠናቀቁ በኋላ እንኳ የተፈጥሮ አደጋዎች እንቅፋት ሆነው በመገዳደር አገልግሎት እንዳይሰጥ ሊያደርጉት ይችላሉ፡፡ አስናር የክርክር ጭብጣቸውን እንዲህ በማለት ያቀርባሉ፣ “ በናይጀሪያ የሚገኘው ቃይንጅ የኤሌክትሪክ ኃይል ግድብ ፕሮጀክት ተጠናቅቆ አገልግሎት መስጠት በጀመረበት ጊዜ ኤሌክትሪክ የማመንጨት ኃይሉ በ70 በመቶ ሊቀንስ ችሏል፡፡ የውኃ መልቀቂያ እና መቆጣጠሪያ ቫልቮች የግድቡን የውኃ ፍሰት በመቆጣጠር በጎርፍ ጊዜ የግድቡን ደህንነት ከአደጋ ላይ ይጥላሉ፣ እንደዚሁም ሁሉ በድርቅ ጊዜ ደግሞ ኤሌክትሪክ የማመንጨት አቅሙን በማዳከም እና ለመስኖ ስራ ሊውል የሚችለውን የውኃ ፍሰት መጠን በመቀነስ ትልቅ የሆነ ችግርን ይፈጥራሉ፡፡ “

የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ለህዝብ ግንኙነት ስራ ሲባል የጦር አውሮፕላኖችን ወደ ኤርትራ የወርቅ ማዕድን ማውጫ በመላክ አውድመው በሰላም ሊመለሱ እንደሚችሉ በመዘገብ በጦር ውጊያው ጌቶቻቸው ጠንካራ እንደሆኑ ለማሳየት የሚታትሩ ከእውነታው በተጻረረ መልኩ እንደበቀቀን የሚለፈልፉ ቀጣፊ የህዝብ ግንኙነት ሎሌዎች አሏቸው፡፡ ከግብጽ ጋር ስምምነት እንደተደረገ እና አል ሲሲ ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት የቀጣናውን የውኃ ጌቶቻቸውን እንደሚያናግሩ ይደሰኩራሉ፡፡ እንዲህም ይላሉ፣ “የ10 ቢሊዮን ዶላር ባለቤት የሆኑት ባለሀብት በቀጣዮቹ አስር ዓመታት ጊዜ ውስጥ በ5 ቢሊዮን ዶላር ወጭ የነዳጅ ዘይት ማጣሪያ ፋብሪካ ይገነባሉ፡፡“ እነርሱ የሚሉት አያጡም አሁንም እንዲህ ይላሉ፣ “የቀድሞ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ካለው ገዥ አካል ጋር በሰላም ለመታገል ከምርጫው በፊት ከውጭ ወደ ሀገር ውስጥ ገቡ፡፡ “

እነዚህ እና ሌሎችም ተመሳሳይ ታላላቅ የማስመሰያ ውሸቶች ከምርጫው በፊት ጥቂት ሳምንታት የቀረውን ህዝብ ቀልብ ለመሳብ ተብሎ የባጥ የቆጡን የሚነገርበት አካሄድ ነው፡፡ ሆኖም ግን ለታዕይታ የሚደረጉ ሁሉም ማስመሰያዎች የሁሉም አምባገነኖች መለያ ባህሪያት ናቸው፡፡ እያንዳንዱ አምባገነን በታሪክ እንደሚታወቀው እራሱ ብቻ ልክ እንደሆነ እና ለህዝቡ ከእርሱ በላይ ሊያስብለት የሚችል እንደሌለ ፕሮፓጋንዳውን በመንዛት የስልጣን እድሜውን ለማራዘም ጥረት ያደርጋል፡፡ ለወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ታላላቅ የማስመሰያ የታዕይታ ነገሮችን ማሳየት እና ተራ ቅጥፈቶችን መዋሸት ስልጣናቸውን ለአንድ ቀን፣ ለአንድ ሳምንት፣ እና ለአንድ ዓመት እንኳ ለማራዘም የሚያስችሉ የመግዣ ገንዘብ የማግኘት ያህል አድርገው ነው የሚመለከቱት፡፡ ፕሮፓጋንዳ የመንዛት ጥረታቸው በአንድ ወቅት ዊሊያም ሀዝሊት ያደረጉትን እና እንዲህ የሚለውን መልዕክት አስታወሰኝ፣ “የሁልጊዜ ዋሹዎች ቅጥፈትን ይፈበርካሉ አንድን ዓላማ ለማሳካት ወይም ደግሞ የሚያዳምጧቸውን ሰዎች ለማሞኘት ብለው አይደለም፣ ሆኖም ግን እራሳቸውን ለማስደሰት ስለሚያስቡ ብቻ ነው፡፡ ይህ ድርጊት ለእነርሱ በአንድ በኩል የማድረግ ልምድ ነው በሌላ በኩል ደግሞ ልማድ ነው፡፡ እውነትን ለመናገር ጥረት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡“

ከጥቂት ሳምንታት በፊት እንደተመለከትኩት የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ እና አሁን በህይወት የሌለው መሪያቸው በጥንታዊት ግሪክ የቅጥፈት አምላኮች እንደገና ተወልደው ወደዚህች ምድር መጡ እንደሚለው ታሪክ ሁሉ የወያኔ የውሸት ጌቶችም እንደገና ተወልደው ወደ ኢትዮጵያ ይመጣሉ እንደማለት ነው፡፡

ከዚህ በታች ስለታኢሕግ/GERD የተሰጠው ትንታኔ በአንድ ወይም በሌላ መልኩ የተሳሳተ እና ከእውነት የራቀ ሊሆን ይችላል፡፡ ስለሆነም ባለሙያዎች እና የምርምር ሰዎች እነዚህን የተሳሳቱ እና ከእውነት የራቁ ትንታኔዎች ፈልጋችሁ እንድታወጡ ግብዣዬን አቀርባለሁ፡፡ በዚህም መሰረት የተገኙ ለተሳሳቱ ትንታኔዎች ዕውቅና በመስጠት የእራሴን ትንተና እና መደምደሚያ ያካተተ ጽሁፍ አዘጋጅቸ የማቀርብ መሆኔን በትህትና እገልጻለሁ፡፡ ምንጊዜም ለመማር ዝግጁ ነኝ፡፡

አሁን በህይወት የሌለው መለስ ከሩብ ምዕተ ዓመት በፊት ገደማ ኢትዮጵያውያን/ት በቀን ሶስት ጊዜ መመገብ ከቻሉ የእርሱ መንግስት ስኬት በዚህ የሚለካ መሆኑን ተናግሮ ነበር፡፡ በአሁኑ ጊዜም የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብም ማለፍ ያለበት ብቸኛው ፈተና ይህ ጉዳይ ብቻ ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ የኢትዮጵያ ህዝቦች በቀን ሶስት ጊዜ እየተመገቡ ነውን? ይህ ካልሆነ ግን የ5 ቢሊዮን ዶላር ግድብ ምንም የሚፈይደው ነገር እርባና ቢስ ነው!

እውነትን ለማስከበር ሲባል የሚደረጉ ጽንፈኛ አመለካከቶች እና አስተያየቶች የስብዕና እጦት ኪሳራ መገለጫዎች እና የተንኮል ወይም ደግሞ የሀገር ክህደት ወንጀል ጉዳይ አይደለም፡፡ እንደዚሁም ሁሉ በስምምነት የጭራቀዊነት ምግባር መቀበል ደግሞ የዘመናዊነት ክብር እና ሞገስን መላበስ ተደርጎ ሊወሰድ አይገባም፡፡

ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!

መጋቢት 22 ቀን 2007 ዓ.ም

Similar Posts

Leave a Reply