በደቡብ አፍሪካ የተፈጸመውን የሻርፕቪሌን ዕልቂት ማስታወሻ (ፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማርያም)
ከፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማርያም
ትርጉም በነጻነት ለሀገሬ
ደቡብ አፍሪካ እ.ኤ.አ በ1960፣
እ.ኤ.አ መጋቢት 21/1960 ልክ ከዛሬ 55 ዓመታት በፊት ወደ 5 ሺ የሚገመቱ ሰልፈኞች (እንደ አፓርታይድ ፖሊስ የተጋነነ መረጃ ከሆነ ደግሞ 20 ሺ ሰዎች) በደቡብ አፍሪካ በሻርፕቪሌ ከተማ በትራንስቫል ግዛት (በአሁኑ ጊዜ ከደቡብ አፍሪካ 9 ግዛቶች መካከል አንዷ በሆነችው እና ጋውቴንግ እየተባለች በምትጠራው ግዛት) ፖሊስ ጣብያ ፊት ለፊት ተሰባሰቡ፡፡ አብዛኞቹ ተቃዋሚዎች የተቃውሞ ሰልፉ አስተባባሪዎች ባደረጉላቸው ጥሪ መሰረት የዉስጥ ፓስፖርት (ፓስ ቡክ) ህጉን (በሀገር ውስጥ የጥቁር አፍሪካውያንን ዘጎችን እንቅስቃሴ ለመቆጣጠር) እና ከህግ አግባብ ውጭ በቁጥጥር ስር መዋልን ለመቃወም በማሰብ ወደ ፖሊስ ጣቢያው አመሩ፡፡ የመጀመሪያዎቹ የተቃዋሚ ሰልፈኞች ቡድን በፖሊስ ጣቢያው በደረሱ ጊዜ በፖሊስ ጣቢያው ውስጥ ከሁለት ደርዘን የሚያንሱ ፖሊሶች ነበሩ፡፡ በአጭር ጊዜ ውስጥ የተቃውሞ ሰልፈኞች ቁጥር እጅግ በጣም ጨመረ፡፡ ከአካባቢው ተጨማሪ ጦር እና መሳሪያ፣ ብረት ለበስ ተሸከርካሪ በማምጣት ሰላማዊ ሰልፈኞቹ ቁጥሩ እየጨመረ ሲሄድ ደግሞ ወደ መሬት በጣም ዝቅ ብለው የሚበሩ የጦር ጀት አውሮፕላኖች ተጠርተው ህዝቡን ለመበተን ሙከራ ማድረግ ጀመሩ፡፡
ተቃዋሚዎች ድንጋይ እያነሱ ወደ ፖሊሶች በመወርወር የፖሊሶችን መከላከያ አጥር ጥሰው ለመግባት ሙከራ አደረጉ፡፡ በመጨረሻ የህግ ምርመራ ቡድን ለማረጋገጥ እንደቻለው ከተቃዋሚዎች አንድም የጦር መሳሪያ የታጠቀ ሰው አልነበረም፡፡ ፖሊስ አስለቃሽ ጋስ እና ቆመጥ ወይም ዱላ በመጠቀም ለተቃዋሚ ሰልፈኞች ምላሽ መስጠት ጀመረ፡፡ የአፓርታይድ ፖሊሶች የተቃዋሚ መሪዎችን እያሳደዱ በቁጥጥር ስር በማዋል የማሰር ሙከራ በሚያደርጉበት ጊዜ ምስቅልቅል ያለ ትግል እና ግብግብ ተጀመረ፡፡ ጥቂት ተቃዋሚዎች ተንጋግተው ወደ ፖሊስ ጣቢያው በመሄድ በሩን በማለፍ ወደ ፖሊስ አዛዡ ሄዱ፡፡ በዚህን ጊዜ ፖሊስ የእጅ መሳሪያዎች እና አደጋ የሚጥሉ መሳሪያዎችን በመያዝ በተቃዋሚዎች ላይ ተኩስ ከፈተ፡፡ ይፋ በተደረጉ መረጃዎች መሰረት ፖሊስ 705 ጥይቶችን በመተኮስ 8 ሴቶችን እና 10 ልጆችን ጨምሮ 69 ሰላማዊ ሰልፈኞችን ገደለ፡፡ ቁስለኛ የነበሩት ወይም ደግሞ ጉዳት የደረሰባቸው ተቃዋሚዎች ብዛት 31 ሴቶችን እና 19 ልጆችን ጨምሮ በድምሩ 180 ነበሩ፡፡ የመርማሪ ቡድኑ ጉዳዩን በኋላ በሚያጣራበት ወቅት የጁሀንስበርግ ከፍተኛ የቀዶ ሕክምና ባለሙያ የምስክርነት ቃላቸውን እንደሰጡት ከሆነ አብዛኞቹ የእልቂቱ ሰለባ የሆኑት ሁሉም ተቃዋሚዎች የተገደሉት ለማምለጥ ወደኋላ በሚሸሹበት ጊዜ እየተተኮሰባቸው በጀርባቸው በኩል በጥይት የተመቱ ናቸው፡፡ የዓይን ዕማኞች እንደገለጹት ከሆነ ዕልቂቱ በሙሉ የተፈጸመው በፖሊሶች ጥፋተኝነት ነበር፡፡ አንድ የዓይን ምስክር እንደተናገረው በፖሊሶች ማስጠንቀቂያ እንኳ አልተነገረም ብሏል፡፡ ተኩሱ ከተከፈተ በኋላ በስፋት በተንጣለለው የፖሊስ ግቢ ውስጥ ምንም ዓይነት ህይወት ያለው ነገር እስከተገኘ ድረስ ተኩሱ እረገብ አላለም ነበር፡፡ ፖሊሶቹ በተቃዋሚዎች የድንጋይ ውርወራ ምክንያት ለአደጋ እንደተጋለጡ እና ምንም ዓይነት ተስፋ የሌላቸው አድርገው በመቁጠር እራሳቸውን ለመከላከል ሲሉ የፈጸሙት ድርጊት አድርገው ተናግረዋል፡፡ ያም ሆኖ ግን 3 ፖሊሶች ብቻ በድንጋይ የተመቱ እና ከ200 በላይ የሚሆኑ አፍሪካውያን/ት ግን በፖሊሶች ጥይት ተመጥተው የተገደሉ መሆናቸውን ዘግበዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ፖሊሶቹ እንደዘገቡት ከሆነ ተቃዋሚዎች በጣም አደገኛ የሆነ ጉዳትን ሊያስከትሉ የሚችሉ መሳሪያዎችን ይዘው እንደነበር እና በኋላም ግቢውን ጥለው ሲሸሹ መሳሪያዎቹ በፖሊስ ግቢው ውስጥ ተበታትነው ወድቀው እንደተገኙ ግልጽ አድርገዋል፡፡ ሌላው እንደዘገበው ከሆነ ደግሞ ጫማዎች፣ ባርኔጣዎች እና ጥቂት ብስክሌቶች ከተገደሉት እሬሳዎች ጋር ወድቀው ብቻ ተመልክቻለሁ ብሏል…
በሻርፕቪሌ በተጨማሪነት የፖሊስ ኃይሉን ለማጠናከር የመጣው ፖሊስ ዋና አዛዥ የነበሩት ሌተና ኮሎኔል ፒናር ለጋርዲያን ቃለ መጠይቅ በሚያደርጉበት ጊዜ ደረታቸውን ነፍተው ምንም ነገር እንዳልተደረገ በሚመስል መልኩ እንዲህ ነበር ያሉት፣ “ይህ ሁሉ ድርጊት የተፈጸመው የተሰበሰበው የአካባቢው ህዝብ የፖሊስ ጣቢያውን መክበብ በጀመረበት ጊዜ ነበር፡፡ መኪናዬ በድንጋይ ተመትታ ነበር፡፡ እንደዚህ ያለ ድርጊት ከፈጸሙ ከባድ ነገር ሊገጥማቸው እንደሚችል መማር አለባቸው፡፡” የፖሊስ አዛዡ ሌላም ነገር በመጨመር እንዲህ ብለው ነበር፣ “የአካባቢው ተወላጅ ሰዎች አስተሳሰብ በሰላማዊ መንገድ ተሰብስበው ሀሳባቸውን ለመግለጽ ችሎታ የላቸዉም፡፡ ለእነርሱ መሰብሰብ ማለት ኃይል የተቀላቀለበት እርምጃ መውሰድ ማለት ነው፡፡“ በተሰበሰበው ህዝብ ላይ ምንም ዓይነት ተኩስ እንዲከፈት ትዕዛዝ ያልሰጡ መሆናቸውን በመካድ ተናግረዋል፡፡
አጣሪ ቡድኑ ለዕልቂቱ ኃላፊነቱን ማን መውሰድ እንዳለበት መወሰን አልቻለም፡፡ በሳምንታት ጊዜ ውስጥ ተቃውሞውን አደራጅተዋል የተባሉት ተቃዋሚዎች በፍርድ ቤት ቀርበው እስከ 3 ዓመታት የሚያስቀጣ የእስር ብይን ተላለፈባቸው፡፡ የአፓርታይድ መንግስት የአስቸኳይ ጊዜ አወጀ፡፡ እ.ኤ.አ ግንቦት 1960 በድርጊቱ ላይ ተሳትፎ እና ድጋፍ አድርገዋል ተብለው የተወነጀሉ 18,011 ተቃዋሚዎች ተይዘው ወደ እስር ቤት ተጋዙ፡፡
የሻርፕቪሌ ዕልቂት በደቡብ አፍሪካ ታሪክ ታላቅ ቦታ ይዞ ይኖራል፡፡ የአፓርታይድን አገዛዝ በዝግታ እና ኃይልን በመጠቀም ማዳከም የተጀመረው ከሻርፕቪሌ ዕልቂት በኋላ ነው፡፡ ያ ዕልቂት ዓለም አቀፋዊ የህዝብ ድጋፍን አስገኝቷል፡፡ የሲቪል ማህበረሰቦች እና እታች እስከ ህብረተሰቡ ድረስ የሚወርዱ የድርጅት ጥምረቶችን በማቋቋም የአፓርታይድን አገዛዝ መገዳደር በስፋት ተጀመረ፡፡ ሻርፕቪሌ የጥቁር አፍሪካውያን ወጣቶችን ቁጣ ቀሰቀሰ፡፡ የተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤት የአፓርታይድን አገዛዝ በተጠናከረ መልኩ ከሌላው የዓለም ህብረተሰብ መነጠል የሚያስችል ድንጋጌ 134 እየተባለ የሚጠራውን ውሳኔ አሳለፈ፡፡ የሲቪል ማህበረሰቦች እና እታች እስከ ህብረተሰቡ ድረስ የሚወርዱ የድርጅት ጥምረቶች ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ደቡብ አፍሪካ እ.ኤ.አ በ1961 ከእንግሊዝ የጋራ ገበያ እንድትገለል አደረጉ፡፡ የአፓርታይድ አገዛዝ ከመለሳለስ ይልቅ የበለጠ ኃይሉን በማጠናከር የኃይል እርምጃዎችን በመውሰድ የግፍ ጭቆናውን በመቀጠል ከነጮች ጋር የሚያደርገውን ትብብር አጠናክሮ ገፋበት፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በደቡብ አፍሪካ የሚገኙ የጸረ አፓርታይድ ድርጅቶች እራሳቸውን የማጠናከር ሚናቸውን አጠናክረው ቀጠሉበት፡፡ የአፍሪካ ብሄራዊ ኮንግረስ/African National Congress በጸረ አፓርታይድ ትግሉ ንቅናቄ የመሪነት ደረጃውን በመያዝ የእራሱን ወታደራዊ ክንፍ አቋቋመ፡፡ በዚህ ዓይነት ሁኔታ በደቡብ አፍሪካ ታላቁ የነጻነት ጉዞ ተጀመረ፡፡
የአፓርታይድን አገዛዝ ከህዝብ ለመነጠል እና ማዕቀብ ለመጣል የሚደረጉ ዓለም አቀፍ ጥረቶች የጊዜው ወቅታዊ እርምጃዎች ሆነው ቀጠሉ፡፡ የውጭ መዋዕለ ንዋይ አፍሳሾች መዋዕለ ንዋያቸውን በደቡብ አፍሪካ በጥቂት የነጮች አገዛዝ ባለበት ሁሉ ላለማፍሰስ ወሰኑ፡፡ የሻርፕቪሌን ዕልቂት ተከትሎ የውጭ መዋዕለ ንዋይ አፍሳሾች ገንዘባቸውን ከደቡብ አፍሪካ እያወጡ መሄድ ጀመሩ፡፡ የደቡብ አፍሪካ ምጣኔ ሀብት በመንኮታኮት አፋፍ ላይ ሆኖ መንገዳገድ ጀመረ፡፡ በቀጣዮቹ ዓመታት በደቡብ አፍሪካ ላይ ተከታታይነት ያላቸው የምጣኔ ሀበት ዕቀባዎች መጣል ጀመሩ፡፡ እ.ኤ.አ በ1986 አጠቃላይ የጸረ አፓርታይድ የ1986 ድንጋጌ የሚለው ማዕቀብ በዩናይትድ ስቴትስ ምክር ቤት/Congress ጸደቀ፡፡ ፕሬዚዳንት ሮናልድ ሬጋን የህንን የምጣኔ ሀብት ማዕቀብ ሕግ “የምጣኔ ሀብት ጦርነት” በማለት የድምጽ መሻር መብታቸውን በመጠቀም አላጸድቅም አሉ፡፡ ሆኖም ግን አብዛኞቹ የሁለቱም የምክር ቤት አባላት ይህንን በመቃወም የፕሬዚደንቱን ዉሳኔ ሻሩት፡፡ የነጮች የጥቂት አገዛዝ በስልጣን ላይ የመቆያ ቀኖቹ እያጠሩበት እንደሆነ እና የብዙሀን አገዛዝ አይቀሬነቱ ገሀድ እየሆነ የመምጣቱን ክስተት ተገነዘበ፡፡
እ.ኤ.አ በ1996 የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት የሆኑት ኔልሰን ማንዴላ አዲሱን ህገ መንግስት ለመፈረም እንዲቻል ሻርፕቪሌን ምርጫቸው አደረጉ፡፡
እ.ኤ.አ የ2005 የኢትዮጵያ ሻርፕቪሌ
እ.ኤ.አ ግንቦት 16/2015 የሕዝብ ተወካዮች ምርጫ ከተካሄደ ከአንድ ቀን በኋላ የተቃዋሚ ፓርቲዎች የእርሱን ህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ እየተባለ የሚጠራውን ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብሰብን (የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር በሚል የቅጥፈት ጭንብላ እራሱን ደብቆ የሚገኘውን) በዝረራ ማሸነፋቸውን በመገንዘብ አሁን በህይወት የሌለው መለስ ዜናዊ “የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ” አወጀ፡፡ መለስ በእራሱ ስልጣን የወታደሩን እና የደህንነቱን ኃይል በእራሱ ቁጥጥር ስር አደረገ እና በመዲናይቱ የሚገኘውን ፖሊስ ከፌዴራል ፖሊስ ጋር እንዲቀናጅ በማድረግ ከፍተኛ ጥቃት ሊሰነዝር የሚችል ልዩ የፖሊስ መች ቡድን አደራጀ፡፡ መለስ ማንኛውም የሚደረግ ስብሰባ ሁሉ ህገወጥ መሆኑን እና ይህንን ትዕዛዝ ተላልፎ በተገኘ ተቃዋሚ ላይ አስፈላጊ የሆነውን ጥብቅ እምጃ ሁሉ እንዲወሰድ በይፋ አወጀ፡፡
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ቢታወጅም ቅሉ እራሱን ህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ተግራይ እያለ የሚጠራውን ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ በመቃወም በመላ ሀገሪቱ ግብታዊ የሆነ ተቃውሞ ተቀሰቀሰ፡፡ ተቃዋሚዎች በቀን ብርሀን እና በጠራራ ጸሐይ ድምጻቸው በወሮበላው አገዛዝ እየተዘረፈ ቅሬታቸውን እና ተቃውሟቸውን በሰላማዊ መንገድ ማቅረብ እንዳለባቸው ተነገራቸው፡፡ የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ የጦር ኃይል፣ ፖሊስ እና የደህንነት ኃይሎች ከፍተኛ አደጋን በሚያስከትሉ የጦር መሳሪዎች በመጠቀም በተቃዋሚዎች ላይ በሀገሪቱ በገሚኙ የተለያዩ ቦታዎች ላይ የእሩምታ ተኩስ በመክፈት በርካታ የሆኑ ያልታጠቁ ሰላማዊ ሰልፍ የወጡ ንጹሀን ዜጎችን በግፍ ገደሉ፡፡
እ.ኤ.አ በ2006 ከፍተኛ በሆነ ዓለም አቀፍ ጫና መሰረት መለስ የድህረ ምርጫውን ውዝግብ ተከትሎ ለተፈጠረው ምስቅልቅል ሁኔታ ምርመራ የሚያደርግ አጣሪ ኮሚሽን አቋቋመ፡፡ በማታለል እና ሸፍጥ በመስራት ዕኩይ ምግባሩ የሚታወቀው መለስ ሁሉም ድህረ ምርጫውን ተከትሎ የተከሰተው ምስቅልቅል ሁሉም መጣራት እንዳይኖርበት ለማድረግ ከፍተኛ ጥንቃቄ አደረገ፡፡ የአጣሪ ኮሚሽኑን የምርመራ አድማስ ውሱን እንዲሆን በማድረግ እ.ኤ.አ ሰኔ 8/2005 በአዲስ አበባ እና በሌሎች አካባቢዎች ደግሞ ከህዳር 1 እና 10/2005 እንዲሁም ከህዳር 14 እስከ 16/2005 ባሉት ቀናት የተፈጸሙት ብቻ መጣራት እንዲጣሩ አደረገ፡፡ (አዋጅ ቁጥር 478/2005ን ልብ ይሏል)
አጣሪ ኮሚሽኑ ባደረገው ምርመራ የ16,990 ሰነዶችን እና የ1,300 የዓይን ምስክሮችን በማካተት የምርመራ ሂደቱን አከናውኗል፡፡ የአጣሪ ኮሚሽኑ አባላት እስር ቤቶችን እና ሆስፒታሎችን የጎበኙ ሲሆን የወያኔን ወሮባላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ አገዛዝ አባላትን ለበርካታ ወራት ቃለ መጠይቅ በማድረግ የምርመራ ስራውን አካሂዷል፡፡
የአጣሪ ኮሚሽኑ የምርመራ ውጤቶች አስደንጋጭ እና ዘግናኝ ነበሩ፡፡ አጣሪ ኮሚሽኑ ባደረገው የማጣራት ስራ የሚከተሉት ተጨባጭ እውነታዎች መገኘታቸውን ይፋ አድርጓል፡
1ኛ) ፖሊስ ጥይት በመተኮስ 193 ሰላማዊ ዜጎችን የገደለ እና 763ቱን ደግሞ ያቆሰለ መሆኑን እና አጣሪ ኮሚሽኑ በተወሰኑት ቦታዎች እና ቀናት በአዋጁ በተቀመጠው መሰረት የማጣራት ስራውን አከናውኗል፤
2ኛ) እ.ኤ.አ ህዳር 3/2005 ቃሊቲ እየተባለ በሚጠራው እስር ቤት ለ15 ደቂቃዎች ያህል በተፈጠረ ትርምስ የእስር ቤቱ የጥበቃ አባላት 1,500 ጥይቶችን እስረኞች ወደታሰሩበት በመተኮስ 17 እስረኞችን እንደገደሉ እና 53 የሚሆኑትን ደግሞ ያቆሰሉ መሆናቸውን ይፋ አድርገዋል፡፡ የአጣሪ ኮሚሽኑ ሊቀመንበር የሆኑት ዳኛ ፍሬህይወት እንዲህ የሚል ትችት አቅርበው ነበር፣ “በርካታዎች የጥቃቱ ሰለባ የሆኑት ሰዎች ከሕግ አግባብ ውጭ በዘፈቀደ የተገደሉ ናቸው፡፡ አቅመ ደካማ የሆኑ በእድሜ የገፉ ሰዎች በቤታቸው ባሉበት ሁኔታ ተገድለዋል፣ እንደዚሁም ህጻናት በሜዳ በጫዋታ ላይ እንዳሉ እንዲገደሉ ተደርገዋል፡፡“
3ኛ) 30,000 የሚሆኑ የሲቪል ሰዎች ምንም ዓይነት ዋስትና እንዲያቀርቡ ሳይጠየቁ በእስር ቤት ታስረው ይገኛሉ፡፡
አጣሪ ኮሚሽኑ 8 በ2 በሆነ ድምጽ ዝርዝር እውነታዎች ላያ ያገኛቸውን ግኝቶች እና ስለተፈጠረው ብጥብጥ የደረሰበትን መደምደሚያ እንዲህ በማለት አቅርቦታል፡
1ኛ) ጠብመንጃ ያነገተ ወይም ደግሞ የእጅ ቦምብ የያዘ አንድም ተቃዋሚ አልነበረም (በመንግስት ቁጥጥር ስር ባሉት መገናኛ ብዙሀን እንደተዘገበው ጥቂት ተቃዋሚዎች ጠብመንጃ እና ቦምብ ታጥቀው እንደነበር መዘገቡ ይታወሳል)፡፡
2ኛ) በተቃዋሚዎች ምንም ዓይነት የወደመ ንብረት አልነበረም፡፡
3ኛ) በመንግስት ታጣቂ ኃይሎች ወደ ተቃዋሚዎች የተደረጉት የጥይት ተኩሶች የተቃዋሚዎችን ስብስብ ለመበተን በሚል ዓላማ ላይ የተመሰረተ አልነበረም፡፡ ሆኖም ግን በተቃዋሚዎች ጭንቅላት እና ደረት ላይ ኢላማ አድርጎ በማነጣጠር የተፈጸመ ግድያ እና ዕለቂት ነበር፡፡
4ኛ) በተቃዋሚዎች ተገድለዋል የተባሉት የመንግስት የደህንነት ኃይሎች አስከሬኖች ለአስከሬን ምርመራ ወደ ሆስፒታል አልተወሰዱም፡፡ እንዲያውም የፎቶግራፍ ማስረጃ እንኳ አልተወሰደም ወይም ደግሞ በምን ሁኔታ እንደሞቱ የሚያመላክት የሞት ማረጋገጫ ሰርቲፊኬት ለሲቪሉ ሳይሆን ለፖሊሶች እንኳ አልተያዘም፡፡
እ.ኤ.አ በሰኔ እና በህዳር 2005 ስለተፈጸመው ዕልቂት በጣም የሚያስደንቁ ሁለት እውነታዎች አሉ፡፡ የመጀመሪያው ብጥብጡን እንዲቆጣጠሩ ተልከው የነበሩት ፖሊሶች የፖሊስ ስነምግባርን በተላበሰ መልኩ አመጹን ለማብረድ በፖሊስ መደረግ ያለባቸውን ድርጊቶች ወደ ጎን በመተው በመንገዳቸው ላይ ያገኙትን ማንኛውንም ሰው ሁሉ ተኩሰው በመግደል የፖሊስ አመጽን ፈጥረዋል፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ የዕልቂቱ ሰለባ የሆኑትን ትክክለኛ የግድያዎችን እና የደረሱ ጉዳቶችን ብዛትና መጠን ግልጽ በሆነ መልኩ አሳንሶ የማቅረብ ሁኔታ ነው፡፡ ዳኛ ፍሬህይወት የአጣሪ ኮሚሽኑን የምርመራ ውጤት ለህዝብ ይፋ ሲያደርጉ ኮሚሽኑ እንዲያጣራ ከተሰጠው ቀን እና ቦታ አቅራቢያ ያሉ ሆኖም ግን ኮሚሽኑ በማጣራት ስራው ላይ እንዲያካትታቸው በአዋጁ ባልተደቀዱለት አዋሳኝ አካባቢዎች የተገደሉት እና ጉዳት የደረሰባቸው የጥቃቱ ሰለባዎች በዚህ ዘገባ ላይ ያልቀረቡ መሆናቸውን ግልጽ አድርገዋል፡፡ የድህረ ምርጫ ቀውሱን ተከትሎ በተከሰተው ብጥብጥ ላይ የተሟላ እና አጠቃላይ የሆነ የማጣራት ስራ ቢካሄድ ኖሮ የሞቱት እና ጉዳት የደረሰባቸው የጥቃት ሰለባዎች ብዛት በአጣሪ ኮሚሽኑ ከቀረበው ዘገባ የበለጠ ሊሆን እንደሚችል የሚያጠራጥር ጉዳይ አይደለም፡፡
በመለስ አገዛዝ የተቋቋመው አጣሪ ኮሚሽን ጥናት ዘግይቶ ባወጣው ዘገባ መሰረት እ.ኤ.አ በ2005 በመለስ ትዕዛዝ በመሳተፍ ንጹሀን ዜጎችን የገደሉ እውቅና ያላቸው የ237 ቅጥር ነፍሰ ገዳይ ፖሊሶች ስም ዝርዝር ተይዟል፡፡
እ.ኤ.አ በ2005 በመለስ የተፈጸመውን ዕልቂት ተከትሎ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እንደ ሻርፕቪሌ ዕልቂት ሁሉ መለስ ዜናዊን ለፍርድ እንዲቀርብ ያደረገው ምንም ዓይነት እርምጃ የለም፡፡ ቁጥራቸው 193 በሆኑት ሰላማዊ ተቃዋሚዎች ላይ ግድያ (በሻርፕቪሌ ከተፈጸመው ዕልቂት በላይ በሁለት እጅ የሚበልጥ መሆኑ እየታወቀ) የፈጸሙት ወሮበላ ነፍሰ ገዳይ ፖሊሶች እና ግድያው እንዲፈጸም ትዕዛዝ የሰጡት አለቆቻቸው ወደ ፍትህ አካል እንዲቀርቡ እና እንዲጠየቁ አልተደረጉም፡፡ መለስም ሆነ የእርሱ አገዛዝ በዓለም አቀፍ ለጋሽ እና አበዳሪ ድርጅቶች ምንም ዓይነት ማዕቀብ አልተጣለበትም፡፡ እ.ኤ.አ መጋቢት 2006 እንደወጣው የሰብአዊ መብት ዘገባ ከሆነ ዩናይትድ ስቴትስ የመለስ ዜናዊን ዕልቂት እንዲህ በማለት ለይስሙላ ያህል ብቻ ለመግለጽ ሞክራለች፡፡ “ከግንቦት ምርጫ በኋላ በተቀሰቀሰው አመጽ በፖሊስ እና በወታደሮች በተወሰደው ተመጣጣኝ ያልሆነ ኃይል በመጠቀም አስከፊ የሆነ የሰብአዊ መብት ድፍጠጣ ተካሂዷል…“ ይህንን ዕልቂት አስመልክቶ የተባበሩት መንግስታት ዕልቂትን የሚያወግዝ ምንም ዓይነት ውሳኔ አላሳለፈም፡፡ የተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት በሮም ስምምነት በአንቀጽ 16 የተሰጠውን ስልጣን በመጠቀም መለስ ዜናዊ እና የዕኩይ ምግባሩ አባሪ እና ተባባሪ የሆኑት የሰብአዊ መብት ድፍጠጣ ወንጀለኞች ላይ በዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ክስ እንዲመሰረትባቸው እንኳ ጥያቄ አላቀረበም ወይም ደግሞ አላሳሰበም፡፡ (የጸጥታው ምክር ቤት እ.ኤ.አ በ2008 በሱዳኑ ፕሬዚዳንት በኦማር አልባሽር ላይ ክስ እንዲመሰረት ትዕዛዝ መስጠቱን ልብ ይሏል)፡፡
የዩኤስ ምክር ቤት/ኮንግረስ ተወካይ የሆኑት ክሪስ ስሚዝ በኢትዮጵያ ደህንነትን ለማበረታታት እና ለማረጋገጥ፣ የዴሞክራሲ እና የምጣኔ ሀብት ነጻነትን ለማጎናጸፍ ኤች.አር 5680 የተባለውን በማጸደቅ ተግባራዊ እንዲሆን አቅርበውት ነበር፡፡ በመለስ ትዕዛዝ ዕልቂት ከተፈጸመባቸው የጥቃት ሰለባዎች ጎን በመቆም እና በሰው ልጆች ላይ የሚፈጸመውን ወንጀል በማውገዝ እና በመመዝገብ ከሚታገሉት ዓለም አቀፍ ድርጅቶች መካከል ሂዩማን ራይትስ ዎች አንዱ ነው፡፡
እ.ኤ.አ በ2005 በኢትዮጵያ የተካሄደውን ሀገር አቀፍ ምርጫ ተከትሎ መለስ ንጹሀን ዜጎችን ጭካኔ በተሞላበት መልኩ በቁጥጥር ስር ማዋል እና ማሰር ጀመረ፡፡ የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችን፣ የሲቪክ ማህበረሰብ አደራጆችን፣ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾችን እና የነጻው ፕሬስ ጋዜጠኞችን በሀገር መክዳት እና በዘር ማጥፋት የፍብረካ ወንጀል በመቀፍቀፍ ሙሉ በሙሉ በሚባል መልኩ በጅምላ እያፈሰ አሰረ፡፡ የነጻው ፕሬስ ጋዜጠኞችን ለማሽመድመድ እና ነጻ ጋዜጦችን ለመዝጋት በሚል ዕኩይ ድርጊት እና የሲቪል ማህበረሰቡን አንደበት ለመሸበብ እና ለመዝጋት ሲል የእባብ ዓይነት መርዙን በመርጨት ቀያጅ እና ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ እንዳይደረግ የሚከለክሉትን የሸፍጥ አዋጆች አውጆ መተግበር ጀመረ፡፡
እ.ኤ.አ በ2010 መለስ በምርጫ ሰበብ በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ በቀሉን ለመወጣት ቆርጦ ተነሳ፡፡ በዚያው ዓመት በግንቦት ወር ተደረገ በተባለው የይስሙላ ምርጫ የእርሱ የሸፍጥ ፓርቲ 99.6 በመቶ በማሸነፍ የፓርላማውን ወንበር ተቆጣጥሯል በሚል እና ነጻ እና ፍትሀዊ የሆነ ምርጫን አካሂዶ ድልን እንደተቀዳጀ ሁሉ እምቧ ከረዩ በማለት ህዝብን በግዳጅ በአደባባይ አሰብስቦ ቀረርቶ እና ፉከራ አደረገ፡፡ እንደዚህ የሚል ለእራሱ እና ለአገዛዙ ያለምንም ሀፍረት እና መሸማቀቅ የአጭበርባሪነት እርባና የለሽ ንግግር ያደርግ ነበር፡፡ የመለስ ግዙፉ ምዕናባዊ ህልም ቀጠለ፡፡ ያለምንም ሀፍረት እንዲህ በማለት አወጀ፣ “ባለፉት አስርት ዓመታት የኢትዮጵያ የምጣኔ ሀብት በየዓመቱ በአማካይ በ11.7 በመቶ ዕድገት አስመዝግቧል፡፡“ የእርሱ አፋሽ አጎንባሽ ሎሌዎቹ፣ ዓለም አቀፍ አበዳሪ እና ለጋሽ ድርጅቶች የሁለት አሀዝ የቅጥፍና እና የቅሌት የምጣኔ ሀብት ዕድገቱን ከእርሱ አፍ በመንጠቅ ማስተጋባት እና መስበኩን ቀጠሉበት፡፡ በመለስ፣ በእርሱ አገዛዝ፣ በዓለም ባንክ፣ የልማት ድጋፍ ቡድን እየተባለ የሚጠራው (የዓለም አቀፍ የድህነት ወትዋች የአቃጣሪ ቡድን እያልኩ የምጠራው)፣ ዩኤስኤአይዲ እና ሌሎች ይህንን ባለፉት አስርት ዓመታት ውስጥ ባለሁለት አሀዝ የምጣኔ ሀብት ዕድገት ተመዝግቧል የሚለውን ድፍረት የተሞላበት ቅጥፈት፣ ተራ ውሸት እና የቁጥር ጨዋታ ጉዳይ በማለት ከጥርጣሬ በላይ በሆነ መልኩ ተጨባጭነት ያላቸውን ማስረጃዎቼን በማቅረብ ሀሰትነቱን ሳጋልጥ ቆይቻለሁ፡፡
የመለስ ዕልቂት ዋናው የተውኔት እውነታ የምዕራቡ ዓለም በየጊዜው በቢሊዮን የሚቆጠር እርዳታ ስለሚያንበሸብሹለት ነበር፡፡ ዩኤስ አሜሪካ እ.ኤ.አ በ2005 ለአገዛዙ በእርዳታ ከሰጠችው 1.8 ቢሊዮን ዶላር ከነበረበት እያደገ በመምጣት እ.ኤ.አ በ2008 ወደ 3.5 ቢሊዮን ዶላር ከፍ እንዲል ሆኗል፡፡ እ.ኤ.አ በ2011 እንግሊዝ ኢትዮጵያ ለሚቀጥሉት አራት ዓመታት ዋና የልማት ዕርዳታ ተቀባዩዋ እንድትሆን መርጣታለች፡፡
ሻርፕቪሌዎች በአፍሪካ፣
በየዓመቱ በአፍሪካ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሻርፕቪሌዎች ይፈጸማሉ፡፡ ሂዩማን ራይትስ ዎች በአብዛኛዎቹ የሰብ አፍሪካ ሀገሮች ከፍተኛ የሆነ ከህግ አግባብ ውጭ በዘፈቀደ የሚፈጸሙ ግድያዎች እንደሚደረጉ መረጃዎች አሉት፡፡ በአፍሪካ ውስጥ የሻርፕቪሌዎች የዕልቂት አደጋዎችን በተደጋጋሚነት የመከሰት ሁኔታ ለማወቅ የሚፈልግ ማንኛውም ሰው ሂዩማን ራይትስ ዎች የሚያወጣቸውን ዘገባዎች ማየት ብቻ በቂ ነው፡፡ በዳርፉር፣ በላይቬሪያ፣ በሴራሊዮን፣ በመካከለኛው የአፍሪካ ሬፐብሊክ፣ በማሊ፣ በኮንጎ ዴሞክራቲክ ሬፐብሊክ እና በሌሎችም የአፍሪካ ሀገሮች የተከተው ዕልቂት ለዚህ ጉልህ ማስረጃ ነው፡፡ በአፍሪካ ከህግ አግባብ ውጭ በዘፈቀደ በአገዛዙ የደህንነት ኃይሎች፣ ወታደሮች እና የፖለስ ኃይሎች የሚደረጉ ዕልቂቶች እና ግድያዎች በየቦታው ሲፈጸሙ እየተመለከተ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ አላየሁም በማለት ፊቱን አዙሮ አዕምሮውን እና ልቡን ለዘላለም ዘግቶ በመመልከት ላይ ይገኛል፡፡
እ.ኤ.አ ነሀሴ 2012 የደቡብ አፍሪካ ጥቁር የፖሊስ ኃላፊዎች በሰሜናዊ ምዕራብ አፍሪካ ማራኪና በምትባለው የማዕድን ቁፋሮ ቦታ የማዕድን ሰራተኞች ማመጽን ተከትሎ በከፈቱት ተኩስ 44 ንጹሀን ዜጎችን ሲገድሉ 78ቱ ደግሞ ቁስለኛ ሆነዋል፡፡ (ለማመን የሚያስቸግር እና ልብ ሰባሪ የሆነውን መሳሪያ ባልታጠቁ በሰላማዊ አማጺያን ላይ የሚደረገውን የግድያ እልቂት የሚዘግበውን የቪዲዮ ፊልም ቀረጻ በመመልከት የእራስን ግንዛቤ መውሰድ ይቻላል)፡፡ ፕሬዚዳንት ጃኮብ ዙማ እንዲህ ብለው ነበር፣ “በእንደዚህ ያለው አስደንጋጭ እና ስሜትየለሽ የኃይል እርምጃ በጣሙን አዝነናል፡፡ በመሰረትነው ዴሞክራሲያዊ ስርዓት በመወያየት ብቻ ያለውን ችግር ያለምንም ችግር በሰላማዊ መንገድ መፍታት የሚያስችል በቂ የሆነ ምህዳር ያለን እንደሆነ አምናለሁ፡፡“ ዙማ እ.ኤ.አ በ1960 በሻርፕቪሌ የተካሄደውን ዕልቂት በማስመልከት በተመሳሳይ መልኩ ከዚህ በላይ ለመጥቀስ እንደሞከርኩት የሚሉ ከሆኑ በጣም የምደነቅ ይሆናል፡፡
እ.ኤ.አ ግንቦት 2014 እራሱን ህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ (ህወሀት) እያለ የሚጠራው የገዥው አካል ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ የፖሊስ እና የደህንነት ኃይሎች ከመናገሻ ከተማዋ በስተምዕራብ በኩል በ80 ማይሎች ርቀት ላይ በምትገኘው የአምቦ ከተማ ውስጥ ተኩስ በመክፈት 47 ያልታጠቁ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎችን እና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎችን እንዲያልቁ አድርገዋል፡፡ በዚህ አሳፋሪ ዕልቂት ላይ በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ላይ ጥቂት የሆነ ትኩረት ብቻ ነበር የተቸረው እናም ምንም ቢሆን ይህ ዕኩይ ድርጊት እንዲጣራ እና ወንጀሉን የፈጸሙት ሰዎችም ለህግ እንዲቀርቡ እንዲደረግ የጠየቀ ማንም አልነበረም፡፡ እነዚህ ቅጥር ነፍሰ ገዳዮች እ.ኤ.አ በ2005 በኢትዮጵያ የተካሄደውን ሀገር አቀፍ ምርጫ ተከትሎ ተከስቶ በነበረው ውዝግብ ሳቢያ ብጥብጥ በማንሳት ሰላማዊ ንጹሀን ዜጎችን በመግደል ምንም ዓይነት የሕግ ተጠያቂነት ሳይኖርባቸው በአዲስ አበባ መንገዶች ደረታቸውን ነፍተው ሲንገዳወሉ እንደሚውሉት ሁሉ እነዚህም በአምቦ ከተማ ንጹሀን የዩኒቨርስቲ እና የሁለተኛ ደረጃ እምቦቃቅላ ባለራዕይ ህጻናት እና ወጣቶችን በመግደል ያለምንም ተጠያቂነት በየመንገዶች እንደ ሰላማዊ ሰው ምንም ሳይባሉ እና ለህግ ሳይቀርቡ እንደልባቸው ደረታቸውን ነፍተው በመንከላወስ ላይ ይገኛሉ፡፡ የንጹሀን ደም ግን ድረሱልኝ እያለ ጩኸቱን ማሰማቱን ቀጥሏል፡፡
ወሰን ያልገደበው ጭራቃዊነት፣
የሻርፕቪሌ ዕልቂት፣ የመለስ ዕልቂት፣ የማራኪና ዕልቂት፣ የአምቦ ዕልቂት እና ሌሎች በአፍሪካ በተለያዩ ቦታዎች የሚፈጸሙት ዕልቂቶች እንዲሁ ሳይታሰብባቸው የተደረጉ ተራ ዕልቂቶች ናቸው የሚል እምነት የለኝም፡፡ ሁሉም ዕልቂቶች በውል ተመክሮባቸው እና ተዘክሮባቸው በስሌት የተከናወኑ ዕልቂቶች ናቸው፡፡ የአፓርታይድ አገዛዝ በሻርፕቪሌ ዕልቂት እና አ.ኤ.አ በ2005 በመለስ የተካሄደው ዕልቂት ሁሉቱም ገዥዎች ስልጣናቸውን ለማቆየት ሲሉ በህዝቦች ላይ ግድያን፣ ዕልቂትን እና ማንኛውንም ነገር ከመደምሰስ እንደማይመለሱ እና ከልክ ያለፈ ኃይልን እንደ ስልት የሚጠቀሙ መሆናቸውን ያረጋግጣል፡፡ የሻርፕቪሌ ዕልቂት የካፊር ህዝቦች ሊረሱት የማይችሉት ትምህርት እንዲወስዱ ያደረገ የጥቂት ነጮች የበላይነትን ያረጋገጠ እኩይ ድርጊት ነበር፡፡ የመለስ እና እራሱን ህዝባዊ ወያኔ እያለ የሚጠራው ወሮበላ የዘራፊዎች ቡድን ስብስብ ዓላማ ከዚህ የተለዬ አልነበረም፡፡ የእነርሱ ተቃዋሚዎች የሆኑት ምንም ዓይነት ልዩነት ሳያደርጉ ወንድ፣ ሴት እና ልጅ ሳይሉ በጅምላ በአደባባይ በመንገዶች ላይ እና በመኖሪያ ቤቶች ቅጥር ገቢ ውስጥ የእሩምታ ጥይቶችን በመተኮስ የማይረሳ ትምህርት እንዲወስዱ አድርገዋል፡፡ መለስ እና የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ታስቦበት እና ሆነ ተብሎ በተቀነባበረ መልኩ የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችን አከርካረ በመስበር ሁለተኛ እንዳያገግሙ እና እንዳያንሰራሩ ማድረግ መቻል ነበር፡፡ በአምቦ የዩኒቨርስቲ እና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎች ላይ ዕልቂት እና የሰብአዊ መብት ረገጣ በመፈጸም የማያዳግም ትምህርት በመስጠት ያለምንም ተቃውሞ እና ስጋት በስልጣን ኮርቻቸው ላይ ፊጥ ብለው ለመቆየት ሲሉ ያደረጉት ስልት ዕኩይ ምግባር ነበር፡፡ መለስ እና ግብረ አበሮቹ እ.ኤ.አ በ2005 በንጹሀን ዜጎች ላይ ለፈጸሙት የዕልቂት ዕኩይ ድርጊት በህግ አግባብ ተጠያቂ ቢሆኑ ኖሮ የአምቦው ዕልቂት በምንም ዓይነት መልኩ ሊፈጸም አይችልም ነበር፡!
በደቡብ አፍሪካ አፓርታይድ ጥሎት ያለፈው ትሩፋት አሁንም ቢሆን ደቡብ አፍሪካን እየጎበኛት እና በአስጊ ሁኔታ ላይ ጥሏት የሚገኝበት ሁኔታ እየተፈጠረ ነው፡፡ ደቡብ አፍሪካ በጣም ጥልቅ በሆነ መከፋፈል ላይ ያለች እና በጊዜ የተሞላ ቦምብ ሆና ዕጣ ፈንታዋን በመጠባበቅ ላይ ያለች ሀገር ናት ብለው የሚያምኑ ጥቂት ሰዎች አሉ፡፡ አሁን በቅርቡ በተደረገ አንድ ጥናት (እ.ኤ.አ ከ2003 ጀምሮ በየዓመቱ የሚደረግ ጥናት) መሰረት የጥቂት ነጮች የፈላጭ ቆራጭነት አገዛዝ ካከተመ ከሁለት አስርት ዓመታት በኋላ 43.5 በመቶ የሚሆኑት ደቡብ አፍሪካውያን በጣም አጠራጣሪ በሆነ ሁኔታ ወይም ደግሞ በምንም ዓይነት መልኩ የሌላ ጎሳ አባል ከሆነ ሰው ጋር የሀሳብ ልውውጥ ወይም ግንኙነት እንደማያደርጉ ያመላክታል፡፡ ከሩብ በመቶ ትንሽ ከፍ በሚል ሁኔታ (27.4 በመቶ) የሚሆኑት ዜጎች ከሌሎች ጎሳዎች አባላት ከሆኑ ዜጎች ጋር ሁልጊዜ ወይም ደግሞ በተለመዱ የሳምንት ቀናት ውስጥ ግንኙነት የሚያደርጉ ሲሆን 25.9 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ አንዳንድ ጊዜ ግንኙነት እንደሚያደርጉ ግልጽ አድርጓል፡፡ ከአምስት አንድ (17.8 በመቶ) የሚሆኑት የደቡብ አፍሪካ ዜጎች ደግሞ ሁልጊዜ ወይም ደግሞ ከሌሎች ጎሳዎች አባላት ጋር በቤቶቻቸው በመገኘት ወይም ደግሞ ከጓደኞቻቸው ቤት በመሄድ የማህበራዊ ግንኙነታቸውን አጠናክረው ይገኛሉ፡፡ እንደዚሁም ሁሉ 21.6 በመቶ የሚሆኑት አንዳንድ ጊዜ ማህበራዊ ግንኙነቶችን የሚያደርጉ ሲሆን 56.6 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ በጣም አጠራጣሪ በሆነ መልኩ ወይም ደግሞ ፍጹም ከሌሎች የጎሳ አባላት ጋር የማህበራዊ ግንኙነቶችን በፍጹም እንደማያደርጉ ይፋ ሆኗል፡፡ ፡፡
መለስ ዜናዊ ጥሎብን የሄደው የጭራቃዊነት ትሩፋት በክልሎች (በደቡብ አፍሪካ ባንቱስታንስ ከሚባለው ጋር አንድ አይነት የሆነ) ላይ እንደ ፈጣን እና ተስፋፊው ነቀርሳ በማደግ ላይ ያለ “ክልል” የሚባል መጥፎ ውርስን ጥሎልን አልፏል፡፡ በቀሪዎቹ የአፍሪካ ሀገሮች የጎሳ፣ የኃይማኖት፣ የቋንቋ፣ የአካባቢያዊነት እና ሌሎች ክፍፍሎችን በመፍጠር በየጊዜው የሚፈነዳ በጊዜ የተሞላ ቦምብ ጥሎብን አልፏል፡፡ አሁን በቅርቡ የተፈጸመን የጎሳ ብጥብጥ በምሳሌነት ብንመለከት በደቡብ ሱዳን በመንግስት በሚደረግ ዘመቻ እና በአማጺ ኃይሎች በሚደረግ የጎሳ ጥላቻ በርካታ የሆኑ መንደሮች እንዲወድሙ፣ በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ ሲቪል ህዝቦች የጅምላ ግድያ እንዲፈጸምባቸው፣ ለቁጥር የሚያዳግቱ ሴቶችን እና ልጃገረዶችን አስገድዶ መድፈር እና ሌሎች በሰው ልጆች ላይ የሚፈጸሙ የሰብአዊ መብት ድፍጠጣ ወንጀሎች እንዲፈጸሙ ሆኗል፡፡ የመለስ እና የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ያተረፈልን ዕኩይ ትሩፋት እነርሱ ያቀጣጠሉት እሳት አንድ ቀን ተቀጣጦሎ እራሳቸውን ሊፈጅ የሚችል የጎሳ ፌዴራሊዝም ነው፡፡
“ጭራቃዊነት መሰረቱን እንዲጥል እና ድልን እንዲቀዳጅ የሚያደርገው ጥሩ ሰዎች ምንም ነገር ሳያደርጉ ሲቀሩ ነው…”
ኤድመን ቡርክ እንዲህ ብለው ነበር፣ “ጭራቃዊነት መሰረቱን እንዲጥል እና ድልን እንዲቀዳጅ የሚያደርገው ጥሩ ሰዎች ምንም ነገር ሳያደርጉ ሲቀሩ ነው…“ እንደዚሁም ደግሞ ምንም ዓይነት ጭራቃዊነትን ላለመስማት፣ ላለማየት እና ምንም ዓይነት ጭራቃዊነት ላለመናገር ጽኑ ውሳኔ ማሳለፍ እና መተግበር በሚሳነን ጊዜ ጭራቃዊነት እንደ ዋርካ ዛፍ መሰረቱ እየሰፋ ይሄዳል የሚል እራሴ ልጨምርበት እፈልጋለሁ፡፡
በሰው ልጆች የኑሮ ስንክሳር ውስጥ አብዛኞቹ ህዝቦች በትንሹ የጠበቁትን ውስን የሆነ ዕጣ ፈንታ ያገኛሉ፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ያ አጋጣሚ በጎ ነገሮችን ወይም ደግሞ መጥፎ ነገሮችን ለማድረግ ምርጫዎችን እንድናደርግ ወይም ደግሞ ምንም ነገር ሳናደርግ መሀል ሰፋሪ ሆነን እንድንቆይ የምንገደድበት ጊዜ ይመጣል፡፡ ምክንያቱም ምንም ዓይነት ደንታ የለንምና፡፡ ምንም ዓይነት ምርጫ ያለማድረግ ወይም ደግሞ ደንታቢስ መሆን ቀላሉ ምርጫ ነው፡፡ ምንም ዓይነት ማሰብን የሚጠይቅ ነገር አይደለም፡፡ በደግ እና በመጥፎ መካከል ምርጫ ማድረግ አጠቃላይ መጥፎ ነገር አይደለም ምክንያቱም ትክክለኛ የሆነ የሞራል ስብዕና ግልጽ አለመሆን ወይም ደግሞ በመምረጥ ረገድ እርግጠኛ ያለመሆን ጉዳይ አይደለም ሆኖም ግን ጭራቃዊነት የበለጠ የመሳብ ኃይል ስላለው፣ የማቅረብ እና ትልቅ ትርፍን የሚያስገኝ ስለሆነ ነው፡፡ ጭራቃዊነትን መምረጥ ሁለተኛው ቀላሉ መንገድ ነው፡፡ የሞራል ስብዕና እሳቤን አይጠይቅም፡፡ ጭራቃዊነት ጥሩ ነገር ነው፡፡ ስግብግብነት ጥሩ ነገር ነው፡፡ ሙስና ጥሩ ነገር ነው፡፡ ሀብት ለማከማቸት በጣም ቀላሎቹ መንገዶች ናቸው፡፡
ለእውነት ለመቆም የትኛው ጥሩ እና ትክክለኛ ነገር ነው የሚለው ምርጫ ለሁሉም ከባዱ ነገር ነው፡፡ ምክንያቱም የሞራል ስብዕና ግልጽልነትን እና ድፍረትን የተላበሰ የህሊና ድርጊትን ይጠይቃል፡፡ አንድ ሰው እውነትን ለመናገር እና በጎ እና ትክክልኛ ነገርን በመስራት በአጋጣሚው ከመወሰን ይልቅ እራሱ አጋጣሚውን ለመወሰን የሚያስችል የሞራል ስብዕና መሰረታዊ አመክንዮ እና የሞራል ስብዕና መርሆዎች ሊኖሩት ይገባል፡፡ በጭራቃዊነት ፊት በህሊናችን ሊቀርብ የሚችለው ጥያቄ ሁልጊዜ ግልጽ ነው፡፡ ዝም ጭጭ ማለትን ምርጫ ልናደርግ እንችላለን፡፡ የጭራቃዊነት ድርጊት ጥፋተኛ እና ይቅርታ ጠያቂዎች ልንሆን እንችላለን፡፡ ጭራቃዊነት በሚፈጸምበት ጊዜ አላየሁም አልሰማሁም በማለት በጭራቃዊነት እና ጭራቃዊነትን በሚፈጽመው ሰው መካከል እራሳችንን የማናይ እውር ማድረግ እንችላለን፡፡ ጭራቃዊነትን ለማውገዝ፣ ለማወደስ ወይም ደግሞ አምኖ ለመቀበል ምርጫ አለን፡፡
የመለስን ዕልቂቶች ማውገዝን እመርጣለሁ፡፡ እ.ኤ.አ በሰኔ እና በህዳር 2005 በመለስ የተካሄዱት ዕልቂቶች ለእኔ እንደ ግለሰብ ማንነቴን እንድወስን ያደረጉኝ ክስተቶች ናቸው፡፡ በመለስ እና በተባባሪዎቹ ለተፈበረከው ጭራቃዊነት ሁኔታ የእራሴን የሞራል ስብዕና ምርጫ ማድረግ እንዳለብኝ መወሰን እና የእራሴን ጽኑ አቋም መያዝ ነበረብኝ፡፡ ጭራቃዊነት ተንሰራፍቶ ባለበት ሁኔታ ለምን ዝም ማለት እንደሌለብኝ እ.ኤ.አ በ2010 በሁፊንግ ፖስት ባወጣሁት ትችቴ በግልጽ እንዳስቀመጥኩት “እ.ኤ.አ በህዳር 2005 ያለቁትን ወገኖቻችን እናስታውስ“ በሚል ርዕስ ምክንያቶቹን ዘርዝሬ ማስቀመጤ የሚታወስ ነው፡፡
ስለመለስ ዕልቂቶች ግንዛቤ ከወስድኩ በኋላ የመጀመሪያው ምላሸ ሁሉንም ነገር ያለማመን ነበር፡፡ ይህ ሁኔታ እውነታ ሊሆን አይችልም! የእኔ አለማመን ቀስ በቀስ ሙሉ በሙሉ ወደ መካድ መንገድ እያመራ ሄደ፡፡ እንደዚህ ያሉ ነገሮች በአፍሪካ ሁልጊዜ ይፈጸማሉ፡፡ እጅ ሰጠሁ! ድብርት እና ተስፋቢስነት ሙሉ ለሙሉ አለመቀበልን እና መካድን ተከትለው የሚመጡ ነገሮቸ ናቸው፡፡ ማን ነው ይህ አስፈሪው ጭራቅ መለስ የሚባለው? ዕልቂቱ እስከሚፈጸምበት ድረስ ስለመለስ ወይም ደግሞ ህወሀት እየተባለ ስለሚጠራው ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብሰብ ምንም ዓይነት የማውቀው ነገር አልነበረም፡፡ እ.ኤ.አ እስከ 2005 በነበረው የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሁኔታ የእኔ ተሳትፎም ሆነ ግንዛቤ በጣም አናሳ ነበር፡፡ እ.ኤ.አ በ1990ዎቹ አካባቢ ስለመለስ እና ድብቅ ሸፍጡ በኢትዮጵያ ሪቪው መጽሔት ላይ አንድ መጣጥፍ አውጥቼ እንደነበር ትንሽ ትንሽ አስታውሳለሁ፡፡ ዝርዘር ሁኔታውን በጥልቅ አላስታውሰውም ሆኖም ግነ የክርክር ጭብጤ ዋነኛ ዳህራ መለስ እና አገዛዙ ለዴሞክራሲያዊ ለውጥ ማምጣት እና የገባውን ቃል ሳያጥፍ ለህዝቡ ሰላም እና ዴሞክራሲ እንዲሰራ እና የመሳሰሉትን ነገሮች እንዲፈጽም ማሳሰብና አድል አንድሰጠው ነበር፡፡፡፡
የመለስን የዕልቂት ሰለባዎች ለመርሳት ሞክሬ ነበር፡፡ ሆኖም ግን በምንም ዓይነት መንገድ አልቻልኩም፡፡ በጣም እንግዳ እና አስፈሪ የሆነ ነገር እየመጣ ህሊናዬን ሁሉ ተቆጣጠረው፡፡ እነዚያ የጥቃቱ ሰለባ የሆኑ ወገኖቻችን የሙት መንፈስ እየመጣ ስለምን አትናገርልንም እያለ በህሊናዬ ላይ ያቃጭልብኝ ነበር፡፡ በጥይት አረር የተበጣጠሱትን የጥቃት ሰለባ ወገኖቻችንን ሬሳዎች ፎቶግራፎች በምመለከትበት ጊዜ በአይኖቸ እንባ አውጥቼ አለቀስኩ፡፡ በህሊናዬ ውስጥ እንዲህ የሚል የለሆሳስ ድምጽ በጆሮዬ ላይ ሹክ ሲል ሰማሁ “ወገኖችህ እንደበሬ እየታረዱ ባለበት ሁኔታ እንዴት ዝም ብለህ አስችሎህ ልትቀመጥ ትችላለህ? እንዴት አያገባኝም ብለህ ልትቀመጥ ትችላለህ? በጣም እራስ ወዳድ እና ገብጋባ ነህ ልበል?“
ቁጭት የእራሴን ውሳኔ እንድወሰድ ገፋፋኝ፡፡ ሆኖም ግን ምን ማድረግ እችላለሁ? ምን ልናገር እችላለሁ? ከዚያ በኋላ እንዲህ የሚል ሀሳብ መግተልተል ጀመረ፡ “ጭራቃዊነት መሰረቱን እንዲጥል እና ድልን እንደቀዳጅ የሚያደርገው ጥሩ ሰዎች ምንም ነገር ሳያደርጉ ሲቀሩ ነው፡፡“ ጭራቃዊነትን ለመዋጋት ላደርገው የምችለው በጣም ትንሽ ነገር አለ፡፡ ብዕሬን መጠቀም ነው (ግልጽ ለማድረግ የኮምፒውተር መክፈቻ ቁልፎችን መጠቀም ነው)፡፡
እ.ኤ.አ መጋቢት 31/2007 ከዚህ ሳምንት ከዛሬ 8 ዓመታት በፊት የእራሴን ማኒፌስቶ “ትንሿ ወፍ እና የጫካው እሳት፡ የዲያስፖራው የሞራል ትረካ/The Humming Bird and the Forest Fire: Diaspora Morality Tale“ በሚል ርዕስ የመጀመሪያውን የትችት ሰነዴን በመጻፍ ጭራቃዊነትን ለምን እንደምዋጋ ግልጽ አደረግሁ፡፡ ለማስተላለፍ የፈለግሁት ዋና ቁም ነገር እንዲህ የሚል አንድ ቀላል ነገር ነበር፡፡ “ለኢፍትሀዊነት ቁንጫ ሁኑበት፡፡ ብቃትን የተላበሱ ተነሳሽነቱ እና ቁርጠኝነቱ ያላቸው ጥቂት ቁንጫዎች ስልታዊ በሆነ መልኩ እየተናከሱ ማጥቃት ከቻሉ ታላቁን ውሻ ምቾት እንዲያጣ በማድረግ ከዚህም በላይ በሀገር ደረጃ ያለን ጭራቃዊነት ምቾት እና ሰላምን በመንሳት ማንበርከክ ይቻላል“ የሚል ነበር፡፡
በመለስ የተደረጉ ዕልቂቶችን እና ከእርሱ ህልፈት በኋላም ሙት መንፈሱን ተከትለው በአምቦ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች እና በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ላይ የተፈጸመውን ዕልቂት ለአንባቢዎቼ በማቅረብ የበለጠ እንዲታደስ እና እንዳንረሳው ለማድረግ መጻፉን እቀጥላለሁ፡፡ እንደዚሁም ሁሉ የሻርፕቪሌን ዕልቂት፣ የማራኪናን ዕልቂት፣ የዳርፉርን ዕልቂት፣ እ.ኤ.አ በ2007 የኬንያን ሀገር አቀፍ ምርጫ ተከትሎ ተቀስቅሶ በነበረው ሁከት ሳቢያ የተፈጸመውን ዕልቂት እና በአሁኑ ጊዜ በአፍሪካ እየተፈጸሙ ያሉትን ዕልቂቶች ሁሉ ለማስታወስ እና እንዳይደበዝዙ ለማድረግ እጽፋለሁ፡፡ በሰው ልጆች ሰብአዊነት ላይ ፍጹም የሆነ እምነት የማጣት እና ተስፋ በመቁረጥ አዘቅት ውስጥ ለወደቁት ወገኖች ድምጻቸውን ቀስ አድርገው በሚጮኹት ትናንሽ ወፎች እና የቁንጫዎችን ምሳሌ በማቅረብ እነዚህ በአስተሳብም፣ በአቅምም፣ በስነልቦናም ከሰው ልጆች ሁሉ የማይመሳሰሉ እና ለውድድርም ሊቀርቡ የማይችሉ ፍጡሮች የዓላማ ጽናታቸውን ይዘው እና ምንም ዓይነት የተስፋ መቁረጥ ስሜትን ሳይፈጥሩ ጠንክረው በመታገላቸው የደረሰባቸውን ጭራቃዊ ፍጡር ሁሉ ድል እያደረጉ ለውጤት እንደበቁ እና ለውጥ እንዳመጡ የምንማርበት ጉልህ ምሳሌዎች መሆናቸውን ለማመላከት ሞክሪያለሁ፡፡
የእኔ ብቻ ደምጽ በአፍሪካ አውሬዎች ጫካ ውስጥ የሚፈጸሙትን የግድያ ዕልቂቶች ለማስቆም ወይም ደግሞ የአፍሪካ ወሮበላ የዘራፊ አገዛዞች የመሻሻል ሁኔታ ያሳያሉ ብየ ማመኔ እንደ የዋህነት ሊያስቆጥር የሚያስችል እምነት ይፈጥርብኝ ይሆን? በአፍሪካ በጥፋተኝነት ያለመጠየቅ ባህልን ለማስቆም እችላለሁ የሚል እምነት ሊኖረኝ ይችላልን? በእርግጥ ላይኖረኝ ይችላል!
ሆኖም ግን ሮበርት ኬኔዲ በአንድ ወቅት በአንደበተ ርዕትነት እንዲህ በማለት እንደተናገሩት በኢትዮጵያ ሐይቅ እና በአፍሪካ ተስፋ የለሽ ባህር ላይ የተስፋ ፍንጣቂዎችን እንደምጨምር እምነት አለኝ፡ “በአውሮፓ በሺዎች የሚቆጠሩ የማይታወቁ ወንዶ እና ሴቶች የናዚን ዘረኛ ወረራ በመቃወም ተግዳሮት ፈጠሩበት እናም ብዙዎቹ ሞቱ ሆኖም ግን ሁሉም ለሀገራቸው ጥንካሬ እና ነጻነት አስተዋጽኦ አድርገው አልፈዋል፡፡ እንግዲህ እንደዚህ ካለው ለቁጥር አታካች ከሆነ ድፍረትን ከተላበሰ ድርጊት ነው የሰው ልጅ ታሪክ የተመሰረተው፡፡ በእያንዳንዱ ጊዜ እያንዳንዱ ወንድ ወይም ሴት ለመልካም ሀሳብ በሚቆሙበት ጊዜ ወይም ደግሞ የሌሎችን ድርጊቶች ለማሻሻል ወይም ደግሞ በኢፍትሀዊነት ላይ አመጽን በሚያካሂዱበት ጊዜ ትንሽ የሆነ የተስፋ ፍንጣቂን ይሰጣል እናም በሚሊዮኖች ከሚቆጠሩ የተለያዩ የኃይል እና የድፍረት ማዕከሎች ከአንዱ ወደ አንዱ እየተሸጋገሩ እነዚህ የተስፋ ፍንጣቂዎች ታላቅ ማዕበልን በመፍጠር ኃይለኛ የተባለውን የጭቆና እና የተግዳሮት ግንብ ንደው እና ጠራርገው ሊጥሉት ይችላሉ፡፡“ እውነታው ፍርጥ እና ፍርጥርጥ ብሎ ሲታይ ግን እኔ ትችቶቼን የምጽፈው የአፍሪካን ወሮበላ ዘራፊዎች አንድን ነገር እንዲያደርጉ ወይም ደግሞ እንዳያደርጉ ለማግባበት ወይም ለማሳመን አይደለም፡፡ እኔ ትችቶቸን የምጽፈው የወደፊቶቹ የኢትዮጵያ እና አፍሪካ ትውልዶች እኔ በአሁኑ ጊዜ በጽናት እንደማደርገው ሁሉ እነርሱም የሕግ የበላይነት፣ መሰረታዊ የሆኑት የሰው ልጅ መብቶች እንዲከበሩ እና ዴሞክራሲያዊ አስተዳደር እንዲሰፍን እምነት ኖሯቸው ለዚያ ዓላማ ትግል እያደረጉ ሰላም እና ፍትህ የሰፈነበት ህይወትን እንዲያሳልፉ ለማድረግ ነው፡፡ በየትኛውም ሁኔታ ብትገመግሙኝም ባትገምግሙኝም እኔ ግን ስሜታዊ የሆንኩ ኢትዮጵያዊ ወይም ደግሞ ተምኔታዊ የሆንኩ ኢትዮጵያዊ እንደሆንኩ በፍጹም ልክድ አልችልም፡፡
በአፍሪካ ጭራቃዊነት ድል ተደርጎ እንዲወገድ ከተፈለገ ወጣት አፍሪካዊ/ት ወንዶች እና ሴቶች የወንጀለኝነትን እና በወንጀል ተጠያቂነት ያለመሆንን ባህል ለማስወገድ በጎ ነገርን ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፣
በተቃዋሚዎቻቸው ላይ ዕልቂትን መፍጠር እና መፍጀት አምባገነኖች ጥንካሬን እንዳገኙ ያህል የመቁጠር መለያ ባህሪያቸው ነው፡፡ ሆኖም ግን ጨቋኝ አገዛዞች ዕልቂቶችን የመፈጸማቸው ሁኔታ ሌላ ምንም ሳይሆን የደካማነት፣ የአደጋ እና ከፍተኛ የህዝብ ተቃውሞ የፍርኃት ምልክት እና መገለጫ እንደሆነ ታሪክ ያሳያል፡፡ ደቡብ አፍሪካውያን በሻርፕቪሌ ዕልቂት ፍርኃት አላደረባቸውም ነበር፣ የአፓርታይድ የጥቂት ነጮች የዘር አገዛዝ አስከፊ እና ለመንገር የሚዘገንን የኃይል እርምጃ ቢወስድባቸውም በዘር ላይ የተመሰረቱትን ህጎች በመቃወም ሙሉ ኃይላቸውን በማስተባበር በትላልቅ ከተሞች ወደ አደባባይ ወጡ፡፡ የሻርፕቪሌ ክስተት ስንቅ ሆኗቸዋል፡፡ የሻርፕቪሌ ዕልቂት እንደ ምክንያት ባይሆን ኖሮ ደቡብ አፍሪካውያን በአንድነት በመነሳሳት ነጻነታቸውን ሊያስከብሩ አይችሉም ነበር፡፡
በድርጊቶች ተያያዥነት ላይ እምነት አለኝ፡፡ እ.ኤ.አ በ1994 በሩዋንዳ የዘር ማጥፋት ወንጀል በሚፈጸምበት ወቅት አብዛኛው የዓለም ህዝብ ጸጥ ብሎ ነበር የሚመለከተው፡፡ ያ የዘር ማጥፋት ድርጊት ከተፈጸመ ከሁለት አስርት ዓመታት በኋላ ክሊንተን እንዲህ ብለው ነበር፣ “ቶሎ ብንደርስላቸው ኖሮ ከጠፋው ህይወት ቢያንስ አንድ ሶስተኛውን ማትረፍ እንችል ነበር…ይህ ድርጊት በእኔ ላይ በጣም የሚያብሰለስል ነገርን ጭኖብኝ አልፏል…“ እንግዲህ እንደ ክሊንተን አባባል ወደ 300 ሺህ የሚሆኑ ሩዋንዳዎችን ከሞት ዕልቂቱ መታደግ ይቻል ነበር ማለት ነው፡፡ የአፍሪካ ህብረት እንዲህ ብሏል፣ “ምንም ዓይነት ጭራቃወኒነት አላይም፣ ምንም ዓይነት ጭራቃዊነት አልሰማም፣ ስለጭራቃዊነት ምንም ዓይነት ነገር ትንፍሽ አልልም፡፡“
ድሮስ ከ53 እና ከ54 ሀገሮች በላይ አካትቶ የያዘው የአምባገነን ዘራፊዎች አህጉር ለእራሱ እንኳ የሚሆን አንድ ጽህፈት ቤት መገንባት አቅተቶት የቻይናን እርጥባን ከሚቀበል ህሊናየለሽ የዝንጀሮ ስብስብ ምን ሊጠበቅ ኖሯል!?
የሩዋንዳን የዘር ማጥፋት ወንጀል ጸጥ በማለት ለመከላከል ባለመቻል ምክንያት እ.ኤ.አ በ2003 በሱዳን የዳርፉር የዘር ማጥፋት ወንጀል ሊፈጸም ችሏል፡፡ የኦማር አልባሽር አገዛዝ የዳርፉርን የአረባዊነት ዝርያ የሌላቸውን እየመረጠ የዘር ማጸዳት ዘመቻ በማከናወን፣ በርኃብ፣ በማፈናቀል እና በሌሎች የጦር ወንጀሎች ግማሽ ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች እልቂትን ፈጸመ፡፡ በሰው ልጆች ላይ የሚፈጸመው ወንጀል በአሁኑ ጊዜም በዳርፉር ላይ እየተተገበረ ይገኛል፡፡
እ.ኤ.አ በ2005 በኢትዮጵያ የተካሄደውን ሀገር አቀፍ ምርጫ ተከትሎ ተከስቶ በነበረው ሁከት መለስ ዜናዊ የፖሊስ እና የደህንነት ኃይሉን በእራሱ ቁጥጥር ስር በማድረግ ትዕዛዝ በመስጠት በመቶዎች የሚቆጠሩ ንጹሀን ዜጎች እንዲያልቁ ሲያደርግ ምንም ዓይነት ተጠያቂነት ሳይደርስበት በአምላክ ትዕዛዝ ከዚህ ዓለም ተሰናብቷል፡፡ መለስ ከሩዋንዳ እና ከዳርፉር የዘር ማጥፋት ዕልቂቶች ማንም አፍሪካዊ መሪ ተጠያቂ ሲሆን እና በህግ አግባብ ሲዳኝ ያላየ በመሆኑ ከዚያ ትምህርት ወስዷል፡፡ የመለስ ደቀ መዝሙሮች እ.ኤ.አ በ2014 በአምቦ ዕልቂትን ፈጸሙ ምክንያቱም አሁን በህይወት ከሌለው አለቃቸው የዕልቂት መፈጸምን ክህሎት ተምረዋልና፡፡
ኡሁሩ ኬንያታ እና ግብረ አበሮቹ እ.ኤ.አ በ2007 በኬንያ የተካሄደውን ምርጫ ተከትሎ በተቀሰቀሰው ሁከት በሰው ልጆች ላይ ወንጀልን ለመፈጸም ህገወጥ ድርጅቶችን በመሳሪያነት ተጠቅሞባቸዋል፡፡ ምክንያቱም መለስ ዜናዊን እና አልባሸር ከጥቂት ዓመታት በፊት በህዝብ ላይ ዕልቂትን ፈጽመው ምንም ነገር እንዳልተደረጉ በመመልከት እኔስ ምን እሆናለሁ በማለት ያንን የመሰለ ዕልቂት እንዲፈጸም አድርገዋል፡፡
እ.ኤ.አ በ2010 የኮትዲቯሩ ሎሬት ባግቦ ተደርጎ በነበረው ምርጫ መሸነፉን ካረጋገጠ በኋላ ስልጣን አላስረክብም በማለት ተቃወመ፡፡ ለአምስት ወራት ያህል ለእርሱ ደጋፊዎች ቀጥታ ትዕዛዝ በመስጠት በተቃዋሚዎቹ ላይ ከፍተኛ የሆነ የሰብአዊ መብት ድፍጠጣ አካሄደ፡፡ ከዚያም የፈረንሳይ የጦር ኃይል ባግቦንን በቁጥጥር ስር አዋለው፡፡ በአሁኑ ጊዜ ይኸ አምባገነን መሪ ተብዬ በዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት የፍርድ ሂደቱን በመከታተል ላይ ይገኛል፡፡ ባግቦ በህግ ባለመጠየቅ መብት ላይ ቁማር ሲጨወት ነበር ሆኖም ግን በቁማሩ ተበልቶ ኪሳራ ደርሶበታል በስር ላይ ይገኛል ፡፡
እ.ኤ.አ በ2012 በደቡብ አፍሪካ የማራኪና ዕልቂት ተፈጸመ ምክንያቱም የአፍሪካ ብሄራዊ ኮንግረስ ለፈጸመው የሰብአዊ መብት ድፍጠጣ እና ዕልቂት ምንም ዓይነት ተጠያቂ እንደማይሆን አሳምሮ ያውቀልና፡፡ በአፍሪካ የጥቁር ፖሊስ ኃይል መሳሪያ በመጠቀም በሰላማዊ መንገድ ያመጹ ዜጎችን በአምላክ አረንጓዴ መሬት ላይ እንዴት ዕልቂትን መፈጸም ይችላል? እንዴትስ አድርጎ ነው እንደዚህ ያለ ፍጅት ያደርሳል ተብሎ የሚታሰበው? እንዴት ነው ያን የመሰለ አሰቃቂ ዕልቂት ሊፈጸም የሚችለው!?! እንደዚያ አይነቱን ጥያቄ በማነሳበት ጊዜ እና ቪዲዮውን በምመለከትበት ጊዜ ለአህጉሩ ያለኝ ተስፋ ሁሉ ተሟጥጦ ይጠፋል፡፡ እ.ኤ.አ በ2012 የማራኪና ዕልቂት በደቡብ አፍሪካ የሚፈጸም ከሆነ እና ከግማሽ ምዕተ ዓመት በሻርፕቪሌ ዕልቂት በተፈጸመባት በደቡብ አፍሪካ ሌላ ዕልቂት በማራኪና የሚፈጸም ከሆነ እ.ኤ.አ ግንቦት 2015 ተመሳሳይ የሆነ ዕልቂት በአትዮጵያ ወይም ደግሞ በማናቸውም ጊዜ በሌሎች ቀሪ የአፍሪካ ሀገሮች ዕልቂት መፈጸሙ ምን ሊያስደነቅ ይችላል?
እውነታው ተፍረጥርጦ ሲታይ ግን ሻርፕቪሌዎች በአፍሪካ በየዕለቱ ይፈጸማሉ፡፡ ማንም ቢሆን ስለእነዚህ ምንም ዓይነት ንግግር አያደርጉም ወይም ደግሞ እነዚህን ድርጊቶች እንዳይፈጸሙ ለመከላከል የሚደረግ ነገር አይታይም ምክንያቱም ወንጀለኞቹ ጥቁሮች ናቸው፣ ነጮች አይደሉም፡፡
የአፍሪካ አምባገነን ወሮበላ ዘራፊዎች በድፍረት ወጥተው በይፋ ለህዝብ እንዲህ ይላሉ፣ “የአፍሪካ ቅምጥል መሪዎች በሰው ልጆች ላይ ስለሚፈጽሙት ወንጀል በዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት አይጠየቁም፡፡“ የኢትዮጵያ አሻንጉሊት የይስሙላ ጠቅላይ ሚኒስትር እና የወባ ትንኝ ተመራማሪው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እ.ኤ.አ ጥቅምት 2013 በአፍሪካ ህብረት ተብዬው የስብሰባ አዳራሽ በመገኘት የክርክር ጭብጥ በማድረግ ጉንጭ አልፋ ንግግር አሰምተው ነበር፡፡
የአፍሪካ መሪዎች እየተባሉ የሚጠሩትን ያለመከሰስ መብት ማግኘት ብዙዎቹ የአፍሪካ እና ከአፍሪካ ውጭ የሆኑ ከፍተኛ ስልጣን ያላቸው የሚደግፉት ሁለት ዓይነት የህግ ሂደት ነው፡፡ ይህ ካልሆነ ልክ ከዛሬ 50 ዓመታት በፊት በሻርፕቪሌ በተደረገው ዕልቂት የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ድርጊቱን እንዳወገዘው ሁሉ አሁንም የደቡብ አፍሪካን የዙማን መንግስት የማራኪናን ዕልቂት ማውገዝ ይኖርበታል፡፡ እንደዚሁም በተመሳሳይ መልኩ እ.ኤ.አ በአትዮጵያ በአምቦ ከተማ በወያኔ ወሮበላ የዘራፊዎች ቡድን አገዛዝ ስብስብ የተፈጸመውን ዕልቂት ማውገዝ ይኖርባቸዋል፡፡
በሰው ልጆች ላይ የሚፈጸመው የሰብአዊ መብት ረገጣ እና የዘር ማጥፋት ወንጀል በአሁኑ ጊዜ በመካከለኛው አፍሪካ ሬፐብሊክ፣ በኮንጎ ዴሞክራቲክ ሬፐብሊክ እና በእርግጥም በኢትዮጵያ ቀጥሎ ይገኛል፡፡ አፍሪካ ጨለማው አህጉር እየተባለ ይጠራል ምክንያቱም ስለአህጉሩ በውጮቹ ብዙ ነገር አይታወቅም ነበር፡፡ አፍሪካ በአሁኑም ጊዜ ጨለማው አህጉር ሆኖ ቀጥሏል ምክንያቱም አሁጉሩ በሰብአዊ መበት ረገጣ፣ በዘር ማጥፋት ወንጀል፣ በጦር ወንጀለኝነት እና በአምባገነን ወሮበላ ዘራፊነት ተሸፍኖ ያለ አህጉር በመሆኑ ነው፡፡
እንደገና ሊከሰት ይችላል፡ የአፈሪካን እና የኢትዮጵያን የማስታወስ ችግር ማስወገድ እና ዕልቂቱን የማስታወስ ግዴታ፣
እ.ኤ.አ በ1960 በሻርፕቪሌ የተፈጸመውን ዕልቂት እንደማስታውሰው ሁሉ እ.ኤ.አ በ2013 የተፈጸመውን የማራኪናን ዕልቂት እና እ.ኤ.አ በ2005 የተፈጸመውን የመለስን ዕልቂት፣ እ.ኤ.አ በ2014 በአምቦ የተፈጸመውን እና በሌሎች አካባቢዎችም የተፈጸሙጸሙትን ዕልቂቶች አስታውሳለሁ፡፡ አንድን ሰው እራሱን አንዲያታልል ለማድረግ ቀላል ነገር ነው እናም በአጋጣሚ የተከሰተ፣ ለብቻው ተለይቶ የተፈጸመ ነው ለማለት ይቻላል፡፡ ቀጣይነት ያለው መከራን የሚያስተናግዱ ሰዎች ያለፈውን ከማስታወስ ይልቅ ይረሳሉ፡፡ ማስታወስ በጣም አስቸጋሪ ነገር ነው፡፡ ለመርሳት በጣመ ቀላል ነገር ነው ወይም ደግሞ የዕልቂቶችን መከሰት ከጥርጣሬ ላይ ይጥላል፡፡ ወጣቱ ትውልድ እንደዚህ ያሉ ወንጀሎች ለመፈጸማቸው ከጥርጣሬ ላይ ይጥለዋል፡፡
ከታሪክ የማይማሩ እራሱን ይደግሙታል ይባላል፡፡ የአፍሪካ እረሽዎች እና የኢትዮጵያ ረሽዎች (ሁለት አዲስ ቃሎችን በማያያዝ አንድ በማድረግ በጋራ ስለሰው ልጆች የሰብአዊ መብት ወንጀል መርሳት እና አለማስተዋስ) አጠቃላይ የአፍሪካ ወጣቱ እና መጭው ትውልድ የመርሳት ቸግርን እፈራለሁ፡፡ ያለፈው ወንጀል ጠንካራ በሆነ የታሪክ ትንታኔ መመርመር አለበት፡፡ በመሆኑም ወጣቱ እና መጭው ትወልድ ከዚህ ትምህርትን መቅሰም ይችላል፡፡ ለዚህ ነው ለወጣት አፍሪካውያን የሻርፕቪሌን፣ የማራኪናን፣ የመለስን እና የሌሎችን ዕልቂት ማስታወስ ጠቃሚ ሆኖ የሚገኘው፡፡ የጅምላ ጭፍጨፋዎችን ዋና መንስኤ መገንዘብ እና የጥቃቱን ሰለባ በቋሚነት ማስታወስ የወደፊቱ ትውልድ ዕልቂትን እንዳይፈጽም ለመከላከል ዋና ጠንካራ መሳሪያ ነው፡፡ ታሪካዊ የሆኑ መወሰድ ያለባቸው ትምህርቶች እነዚያን እምነቶች እና የአካሄድ ዘይቤዎች መለየት እና ማገናዘብ መቻል እና እንዳይፈጸሙ መከላከል መቻል ነው፡፡
ጥቂት ወጣት የአፍሪካ ወጣቶችን በተለይም የኢትዮጵያን ወጣቶች በሳምንታዊ ትችቴ ማስተማሪያዎች (ጥቂቶቹ ትችቶቼን ረዥም የማስተማሪያ ጽሁፎች እያሉ እንደሚጠሯቸው) አንድ ሰው ለእምነቱ የሚቆምበት፣ ላመነበት ነገር በጽናት የመቆም እና በሰው ልጆች ላይ ወንጀልን በሚሰሩ ሰዎች ላይ ጣት የሚሰነዘርበት እና ድምጽን ከፍ አድርጎ ይቅርታ በማለት የሚጠየቅበት ጊዜ ይመጣል፡፡ ለመብት የሚቆምበት እና የመንግስትን ስህተት ማስተካከል የሚቻልበት ጊዜ ይመጣል፡፡ ምንም ዓይነት የሚከላከልላቸው ሰው የሌላቸው ሰዎች መብቶች ሲጣሱ በማየት ዝም ብሎ መቀመጥ ታላቅ ስህተት ነው፡፡
ለውጥን ለማምጣት የሁሉም ሰው ተሳትፎ መኖር አስፈላጊ ነገር ነው፡፡ ማርቲን ሉተር ኪንግ በአንድ ወቅት እንዲህ ብለው ነበር፣ “ለውጥ በወደፊት ጎማ ላይ የሚሽከረከር ነገር አይደለም፡፡ ሆኖም ግን ለውጥ የሚመጣው ቀጣይነት ባለው ትግል ነው፡፡ ስለሆነም ጀርባችንን ቀጥ አድርገን ለነጻነታችን መስራት ይኖርብናል፡፡ ጀርባህ ለመቀመጫነት ምቹ እስካልሆነ ድረስ ማንም አይጋልብህም፡፡“ ለውጥ በመረጃ ላይ ከተመሰረተ እና ከሰለጠነ ክርክር ከሚመነጭ ውይይት መምጣት አለበት፡፡ ከድንቁርና የሚወለድ ለውጥ አሁንም የተወለደ ለውጥ ነው፡፡ ከትምህርት የሚመነጭ ለውጥ ዘለቄታዊነት አለው፣ ለብዙ ጊዜ የሚቆይ እና የሰውን ስብዕና መሰረት ያደረገ ነው፡፡ ለዚህም ነው የአፍሪካ ወጣቶች (አቦ ሸማኔዎች) የአፍሪካን አዲስ አታላዮችን (አሮጌ ጉማሬ ትውልድ) ቃሎች እንዳለ መውሰድ የሌለባቸው፡፡ ወጣቶቹ የእራሳቸውን ጀግናይቱን አፍሪካ፣ ኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ደቡብ አፍሪካ ለመመስረት በእራሳቸው መንገድ መጓዝ አለባቸው…
አልበርት አነስታይን በአንድ ወቅት እንዲህ ብለው ነበር፣ ዓለም ለመኖር በጣም አደገኛ የሆነች ቦታ ናት ምክንያቱም በውስጧ የሚኖሩ ጭራቃዊ ሰዎች ስላሉ አይደለም ነገር ግን ስለዚህ ጉዳይ ምንም ነገር የማያደርጉ እና የማይሰሩ ሰዎች ስላሉ ብቻ ነው፡፡“ እንደዚሁም ሁሉ አፍሪካ ለመኖር አደገኛ የሆነች አህጉር ናት…የተንሰራፉ የሰው ልጆች መብት ድፍጠጣ፣ የዘር ማጥፋት እና የጦር ወንጀለኝነት በመኖሩ እንዲሁም ጭራቃዊ አምባገነኖች ብቻ በመኖራቸው ምክንያት አይደለም፣ ሆኖም ግን በዋናነት ደግ የሆኑ የአፍሪካ ሰዎች በተለይም ወጣቶች (እና የአፍሪካ ወዳጆች) በአንድነት ሲቆሙ እና በአህጉሩ ስላለው ጅምላ የሰብአዊ መብት ድፍጠጣ በአንድ ድምጽ መቆም እና መናገር ሲችሉ ነው፡፡
ከአፍሪካ በጣም አስቸጋሪ እና ዘለቄታዊ ባለው መንገድ ሰዎች ላጠፉት ጥፋት በወንጀል ተጠያቂ ያለመሆን ባህል ተንሰራፍቶ ይገኛል፡፡ በስልጣን ላይ ማንኛውንም ጥፋት የመፈጸም መብት ያላቸው ወይም ደግሞ ወንጀል መስራት እንደሚችሉ እና ምንም ተጠያቂነት ሳይኖረው በነጻ መሄድ እንደሚችሉ አድርገው ያምናሉ፡፡ የአፍሪካ መሪዎች እራሳቸውን ከህግ በላይ አድርገው ይቆጥራሉ፣ በእርግጥም እራሳቸው ህግ እንደሆኑ አድርገው ያስባሉ፡፡ የዚህ ዓይነት አስተሳሰብ እና በጥፋተኝነት እና በወንጀል ያለመጠየቅ ባህል ሊቆም እና ሊወገድ ይገባል፡፡ እናም የሕግ የበላይነት የተከበረበት፣ ስልጣኔ እና የመልካም አስተዳደር አዲሱ የሲቪክ ባህል ተቋማዊ መሆን አለበት፡፡
የሻርፕቪሌን ዕልቂት ባስታወስኩ ጊዜ ለደቡብ አፍሪካ፣ ለኢትዮጵያ እና ለሌሎች በአህጉሩ ውስጥ ላሉ ወጣቶች ያለኝ ዋናው መልዕክቴ ከስቴቭ ቢኮ (አሁን በህይወት የሌለው የደቡብ አፍሪካ ወጣቶች መሪ የነበረው እና የጥቁሮችን የትግል ንቅናቄ እና የከተማውን ጥቁር ህዝቦች ለማጠናከር እና ለማንቀሳቀስ ሲታገል የነበረ) እንዲህ የሚለውን አስተሳሰብ ለአሁኑ ላለው ለእኔ ትውልድ ሰጥቶ ነበር፡ “የጨቋኞች ዋናው እና ጠንካራው መሳሪያቸው የተጨቋኙ ህዝብ አዕምሮ ነው፡፡“
ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!
መጋቢት 15 ቀን 2007 ዓ.ም