የኢትዮጵያ የምርጫ ቅርጫ: አይን ያወጣ የቅጥፈት የይስሙላ ምርጫ (ፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማርያም)

ከፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማርያም
ትርጉም በነጻነት ለሀገሬ

እ.ኤ.አ በግንቦት 2015 ይካሄዳል እየተባለ ሌት ከቀን ስለሚደሰኮርለት የኢትዮጵያ የቅጥፈት የይስሙላ የታዕይታ ምርጫ የሚያውቀው እና ግንዛቤው ያለው ማን ነው?

ይህንን ትችት በምጽፍበት በአሁኑ ጊዜ የካቲት አጋማሽ ሆኗል፡፡ ሆኖም ግን ምንጊዜም ቢሆን የህዳር ወርን አስታውሳለሁ፡፡ (በህዳር ነበር መለስ ዜናዊ ሰላማዊ ወገኖችን በጥይት ያስፈጀው።)

በአሁኑ ጊዜ ጥቂት የኢትዮጵያ ጓደኞቼ ተስፋ በቆረጠ የሀዘን ስሜት ድባብ ውስጥ ሆነው እመለከታለሁ፡፡ ይህንን አስደማሚ ሁኔታ በምመለከትበት ጊዜ “ለምንም ነገር የማይውል ከንቱ የታዕይታ ስራ“ የሚሉት የሸክስፒር የግጥም ስንኞች በአዕምሮዬ ጓዳ ውስጥ ብልጭ አሉብኝ፡፡ እንዲህ ይላሉ፡

ከቶ ለምድን ነው፣ ምንድን ነው ጉዳዩ፣
ተጨፍጋጊ ፊቶች ጎልተው የሚታዩ?

ውርጭ በላዩ ላይ ፍጹም ያጠላበት፣
ማዕበል የናጠው ውርዘት የበዛበት፣
በጥቁር ደመና የተሸፈነበት የተጀቦነበት፣
እኮ ምን ሆኖ ነው ያ መከረኛ ፊት፣
ጠቁሮ ከስሎ እምናይ በወርሃ የካቲት?

የየካቲት ፊቶች ፍጹም ስሜታዊነት በተሞላባቸው ልቦች ውስጥ ሆነው ይታያሉ፡፡ ጨለምተኝነትን በተላበሰ መልኩ እንዲህ የሚሉ ጥያቄዎችን ይተየቁኛል፡፡ ስለ”ምርጫው” ይህንን ወይም ያንን ታውቃለህ? እንዴት! “ምርጫ”? ድንቄም ምርጫ! የምን ምርጫ? እስቲ ድገምልኝ! ጥያቄው አንዳልገባው አዳምጣለሁ፡፡ በእርግጥ እ.ኤ.አ ግንቦት 24/2015 ይካሄዳል ተብሎ ህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ (ህወሀት) እየተባለ በሚጠራው የወሮበላው የዘራፊ ቡድን ስብስብ ቀጠሮ ስለተያዘለት የይስሙላ ምርጫ ጥያቄ አንደሆነ አውቃለሁ፡፡

ህወሀት የወያኔው የወሮበላ እና የዘራፊ ስብስብ ቡድን የሰማያዊ (Blue Party)፣ አንድነት ለዴሞክራሲ እና ለፍትህ (Unity for Democracy and Justice/UDJ) እና የዓረና ትግራይ ለሉዓላዊነት (Arena Tigray for Sovereignty) ፓርቲዎች አመራሮችን እና አባላትን እስር ቤቶች አጉረው በማሰቃየት ላይ እንዳሉ አውቃለሁን? የወያኔው የወሮበላ እና የዘራፊ ስብስብ ቡድን ፖሊሶችስ በሰላማዊ መንገድ ተቃውሟቸውን ለመግለጽ የወጡ ወገኖችን ጭንቅላት በቆመጥ እየበረቀሱ እና እጅ አግሮቻቸውን እየሰበሩ አካለ ጎደሉ እያደረጓቸው መሆናቸውን አውቃለሁን? የወያኔው የወሮበላ እና የዘራፊ ቡድን ስብስብ የዞን 9 ጦማሪያንን የችሎት ቀጠሮዎች ለበርካታ ጊዚያት በማስተላለፍ እያጉላሉ ሰብአዊ መብቶቻቸውን በመደፍጠጥ በንጹሀን ዜጎች ላይ ወንጀልን እየሰሩ መሆናቸውን አውቃለሁን? የወያኔው የወሮበላ እና የዘራፊ ቡድን ስብስብ በየዕለቱ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾችን እና በእርሱ ላይ ገንቢ የሆነ ትችትን የሚያቀርቡትን ሰላማዊ ዜጎች እያሰረ መሆኑን አውቃለሁን?

እ.ኤ.አ በ2010 ተካሄደ እንደተባለው የይስሙላ የቅርጫ ምርጫ ሁሉ እ.ኤ.አ በግንቦት 2015 ለሚካሄደው ሀገር አቀፍ የይስሙላ የቅርጫ ምርጫ የመራጮች ድምጽ ዘረፋ ከዩናይትድ ስቴትስ፣ ከአውሮፓ ህብረት፣ ከዩናይትድ ኪንግደም፣ ከዓለም ባንክ፣ ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ለወያኔው የወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ የሚሰጠው ድጋፍ ምን ምን እንደሚሆን ለማወቅ እችላለሁን? የወያኔው የወሮበላ ዘራፊ ቡድን ስብስብ በእራሱ አገዛዝ፣ በምርጫው ወይም ደግሞ ምርጫው ላይኖር ይችላል በሚል ስጋት ያልተጠበቀ የፖለቲካ ምስቅልቅል ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል በማለት በፍርሀት ቆፈን ውስጥ ተወሽቆ ሊገኝ ይችላልን? ከደንቆሮዎች ህሊና ቢሶች ይህ የሚጠበቅ ጉዳይ ነው፡፡ ታዲያ ይህ ካልሆነማ በማህበራዊ መገናኛዎች በመጠቀም መረጃን እና እውቀትን የሚያስተላልፉ ጦማሪያንን በጅምላ እያፈሱ ወደ እስር ቤት ማጋዝን ምን አመጣው?)

በመጭው ግንቦት ይካሄዳል እየተባለ ስለሚደሰኮርለት የይስሙላ የቅርጫ ምርጫ ፕሬዚዳንት ኦባማ የሚያውቁትን ያህል እኔም አውቃለሁን? (ደህና! የኦባማ ቀደምት የነበሩት ፕሬዚዳንት ሀሪ ትሩማን “የዜጎቹን ተቃውሞ ጸጥ ረጭ ለማድረግ የሚጥር መንግስት ሁሉ ለሁሉም ዜጎች የሽብር ምንጭ ነው“ የሚለውን ብሂል ፕሬዚዳንት ኦባማ በውል የተገነዘቡት መሆን አለመሆናቸውን ለመጠየቅ እፈልጋለሁ፡፡ የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ትሩማን ይህንኑ ጉዳይ በማስመልከት እንዲህ ብለው ነበር፣ “አንድ ጊዜ መንግስት የተቃዋሚዎችን ድምጽ በኃይል ጸጥ ረጭ በማድረግ መግዛትን እንደ መርህ ከያዘ ቀጣይነት ያላቸውን የጭቆና እርምጃዎችን በመውሰድ የቁልቁለት መንገዱን በማፋጠን ላይ መሆኑን የሚያመላክት ብቸኛው መንገዱ መሆኑን ግልጽ አድርጎ ያሳያል፡፡ እናም ይህን እኩይ ድርጊቱን ደጋግሞ በመፈጸም የዜጎቹ ሁሉ የሽብር ምንጭ መሆኑን እስካረጋገጠ ደረስ ማንምኛውም ዜጋ ቢሆን በፍርሀት ቆፈን ውስጥ ተሸብቦ የሚኖርበተን ሁኔታ ይፈጥራል“ በማለት አስጠንቅቀዋል፡፡)

እ.ኤ.አ በመስከረም 2014 የመጨረሻዎቹ ወራት ኦባማ ግልብ በሆነ እና መቅን የለሽ በሆነው ንግግራቸው እንዲህ የሚል ጥቆማ ሰጥተው ነበር፣ “…ጠቅላይ ሚኒስትሩ [ኃይለማርያም ደሳለኝ] እና መንግስታችሁ በዚህ ዓመት በኢትዮጵያ ምርጫ ተካሂዳላችሁ፡፡ ስለዚያ ጉዳይ የማውቀው ነገር አለ…“ ኦባማ “የውሸቷ ኢትዮጵያ ሬፑብሊክ” የሚለውን ትችቴን ቢያነቡ ኖሮ የኢትዮጵያ ህዝብ በፖሊስ መንግስት (police state) በሽብር ውስጥ እየኖረ እንዳለ አንድ ነገር ያውቁ ነበር!

ኦባማ እ.ኤ.አ በግንቦት 2015 በኢትዮጵያ ስለሚካሄደው የይስሙላ የቅርጫ ምርጫ የማውቀው ነገር አለ ማለታቸውን በማስመልከት አዘጋጅቼ ባቀረብኩት ትችቴ ላይ ከመጠን በላይ የተገረምኩ መሆኔን፣ ስለዚህ ጥቆማቸው ለማወቅ እንደምጠይቅ ጉጉት አድሮብኝ እንደነበር እና በዚህ ኃላፊነትን ያልያዘ ንግግራቸው ላይ ከመጠን በላይ እንደተበሳጨሁ ግልጽ አድርጌ ነበር፡፡ ያንን ጥያቄ ያቀረብኩት ከመጠን በላይ በሆነ ጥንቃቄ እና ስጋት ላይ መሰረት በማድረግ ነው፡፡ ኦባማ ስለ ምርቻው አውቃለሁ ሲሉ የምርጫው ድምጽ እንደሚዘረፍ ያወቁ ነበር? ይህ ምርጫ ሸፍጥ ያለበት እንደሚሆን ያውቃሉን? የኢትዮጵያ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች በወያኔው የወሮበላ ስብስብ ማስፈራራት እና እስራት እንደሚፈጸምባቸው ያውቃሉን? በኢትዮጵያ ውስጥ የጋዜጠኝነት እና የጦማሪነት ሙያዎች መንግስታዊ ወንጀሎች መሆናቸውን ያውቃሉን? “ፕሬዚዳንት ኦባማ ስለኢትዮጵያ ምርጫ ምን የሚያውቁት ነገር አለ?“ በሚል ርዕስ ባቀረብኩት ትችቴ ላይ በኢትዮጵያ ስለሚካሄደው ምርጫ ፕሬዚዳንት ኦባማ እንዲመልሷቸው ያቀረብኳቸው ጥያቄዎች በዝርዝር አቅረበ ነበር መልስ ግን አላገኘሁም።

ሆኖም ግን እ.ኤ.አ በ2015 በኢትዮጵያ ስለሚካሄደው የይስሙላ የቅርጫ ምርጫ ጉዳይ ሌሎች የሚያውቁ እነማን ናቸው?

በሲባጎ እንደታሰረ አሻንጉሊት ተይዘው የሚንቀሳቀሱት እና እጅ እና እግር በሌለው አደናጋሪ ንግግራቸው የሚታወቁት “ጠቅላይ ሚኒስትር” ኃይለማርያም ደሳለኝ እ.ኤ.አ በ2015 የሚካሄደው ምርጫ “እንከንየለሽ” እንደሚሆን ያውቃሉ፡፡ ሰዎችን በማደናገር የሚታወቁት አሳዛኙ እና ተስፋየለሹ ኃይለማርያም ደሳለኝ ከቅርብ ጊዜ በፊት እንዲህ የሚል ንግግር አድርገው ነበር፣ “የምርጫ ሂደቱ ዴሞክራሲያዊ፣ ነጻ፣ ፍትሀዊ እና በህዝቦቻችን ዘንድ ተማዕኒነት ያለው እንዲሆን ማድረግ አለብን፡፡“ ፓርቲያቸው ነጻ እና ፍትሀዊ ምርጫን ማረጋገጥ አንደምቺል አረጋግጠዋል። ሲናገሩም “የተቋማዊ ሂደታችን፣ ህጎቻችን እና ደንቦቻችን እንከንየለሽ ናቸው፡፡ ህጉ አይደለም ችግር የሚፈጥረው ሆኖም ግን እነዚህን ህጎች ተግባራዊ በማድረጉ እረገድ ነው ችግሩ ያለው“ በማለት ተደናግሮ አደናጋሪ የሆነ የደንቆሮ ፍልስፍና ለማራመድ ሞክረዋል፡፡

እውነት ነው ችግሩ ያለው ከህጎቹ ጋ አይደለም ሆኖም ግን “እነዚህን ህጎች ከሚተገብረው ከወሮበላው የወያኔ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ላይ ነው::” እንደዚሁም ደግሞ ኃይለማርያም እና የወያኔው ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ እንከንየለሽ ምርጫ ለማካሄድ የምርጫ ህጎችን ወደተግባር ያሸጋግራሉ (ሸፍጥ ይሰራሉ ወይም የፕወዛ እኩይ ድርጊቶችን ይፈጽማሉ አላልኩም)፡፡ አንደሚታወቀው እ.ኤ.አ በ2010 እንከንየለሽ ምርጫ አካሄዱ፡፡ በዚህም መሰረት 99.6 በመቶ የሆነ አስደናቂ የድምጽ ውጤት በማምጣት ድልን ተቀዳጁ! ያንን ነው እንግዲህ ተወዳዳሪ የሌለው እና ልዩ የሆነ አስደናቂ ድል የመቀዳጀት ጥበብ (ማጭበርበር አላልኩም) ተካሄደ የምለው፡፡ ከመቶ ነጥብ አራት ከአስረኛ ማለት ምን ለውጥ ያመጣል! እጅግ በጣም ትንሽ የሆነ የቁጥር/የስታቲስቲክስ ስህተት ነውን? (በነገራችን ላይ እ.ኤ.አ በ2015 ለሚካሄደው የይስሙላ የቅርጫ ምርጫ የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ለሚያስመዘግበው እንከንየለሽ የምርጫ ውጤት ድል መቀዳጀትን አስመልክቶ የመጀመሪያውን የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕከት በማስተላለፍ የመጀመሪያው እሆናለሁ፡፡ ወዲያውኑም ኃይለማርያም “ተጠቅመህበት ጣለው” የሚለውን አባባል ትክክለኛ ትርጉም በሚገባ የሚያውቁት ይሆናል የሚል ግምት አለኝ፡፡) በዓለም ላይ ለመጨረሻ ጊዜ እንደዚህ ያለ አስደማሚ የምርጫ ውጤት (99.6) በማግኘት የዓለምን ህዝብ አስደንቆ የነበረው የምርጭ ውጤት እ.ኤ.አ በ2002 በኢራቅ ተካሂዶ የነበረው ምርጫ ነበር፡፡ ሳዳም ሁሴን በ11 ሚሊዮን ለዜሮ በሆነ ውጤት አሸንፎ ነበር፡፡

በቅርቡ ስለኢትዮጵያ ቅርጫ (ይቅርታ ምርጫ ማለቴ ነው) ጥቂት ትችቶችን አንብቤ ነበር፣ እንዲሁም በብዙሀን መገናኛ የተደረጉትን ውይይቶች ተከታትየ ነበር፡፡ በእንደዚህ ያለ አንገብጋቢ የህዝብ ጉዳዮች ላይ ጠንካራ የሆነ ውይይት መካሄዱ ጠቃሚ ነገር ነው፡፡ የተማሩ እና የተመራመሩ ልሂቃን ሰፊውን ህዝብ የማስተማር የሞራል ግዴታ አለባቸው፡፡ እኔ አብዛኛውን ጊዜ በመገናኛ ብዙሀን ምንጮች እና በሌሎች አካላት ትችቶቼን እንዳቀርብ እጋበዛለሁ፡፡ እ.ኤ.አ በ2015 በኢትዮጵያ የሚካሄደው ሀገር አቀፍ ምርጫ ነጻ እና ፍትሀዊ ስለመሆን አለመሆኑ እና ሊከሰቱ የሚችሉ ሰይጣናዊ ድርጊቶች ስለመኖር አለመኖራቸው ሙያዊ ትንታኔ እና ትንበያ እንድሰጥ እጠየቃለሁ፡፡ አጽንኦን በተላበሰ መልኩ ምርጫው በምንም ዓይነት መልኩ ነጻ እና ፍትሀዊ አይሆንም በማለት እናገራለሁ፡፡ ሆኖም ግን “እንከንየለሽ ቅርጫ” ምርጫ እንደሚሆን ዋስትና አለው ብዬ ተንበያለሁ፡፡

ሌላው ምላሸ ጥያቄዬ ነው፡፡ “የምን ምርጫ? ቅርጫ ምርጫ ይሆን አንጂ? ጽጌረዳ በሌላ በማናቸውም ስያሜ ቢጠራ እንደ ጽጌረዳ የሚያውድ ሽታውን ይሰጣል የሚለው እውነታ ትክክል ነው፡፡ ሆኖም ግን በዘራፊ ወሮበላ የፖሊስ መንግስት የሚካሄድ የምርጫ ቅርጫ በሌላ በተለያዩ ፊደሎች ቢሰየም እና ቢጠራ ሰማይ አስክደርስ ድረስ መጠንባቱ አይቀርም፡፡

በወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ፖሊስ መንግስት በተደረጉት የእብደት ምርጫዎች ላይ ለበርካታ ዓመታት ትችት ሳቀርብ ቆይቻለሁ፡፡ እ.ኤ.አ ጥቅምት 2009 “ኢትዮጵያ፡ የማይቻል ተልዕኮ/Ethiopia: Mission Impossible?“ በሚል ርዕስ ባቀረብኩት ትችት ነጻ እና ፍትሀዊ ምርጫ ለማካሄድ እኩልነትን፣ ፍትሀዊነትን፣ ስልጡንነትን፣ ታማኝነትን፣ መከባበርን፣ እና ተቻችሎ መኖርን ለማረጋገጥ እንዲቻል የሲቪክ ባህል መኖር እና ይህንንም የሚያራምድ እና የሚያጠናክር ነገር መኖር አለበት በማለት የክርክር ጭብጤን አቅርቤ ነበር፡፡ እ.ኤ.አ በ2010 የሚደረገው የቅርጫ ምርጫ አሳፋሪ፣ በዴሞክራሲ ላይ የሚፈጸም ሸፍጥ፣ ተራ ማጭበርበር እና የተጋነነ የምርጫ ውጤት ገለጻ ሊደረግ እንደሚችል አስቀድሜ ትንበያ ሰጥቸ ነበር፡፡ gin ተሳስቸ ነበር፡፡ ምርጫው ግን ከዚያም ባለፈ መልኩ በከፍተኛ ደረጃ “እንከንየለለሽ የቅርጫ ምርጫ” መሆኑን በይፋ አስመስክሯል፡፡

እ.ኤ.አ በ2010 የተካሄደው የቅርጫ ምርጫ በእርግጠኝነት የአሳማን ኮረዳ ሊፒስቲክ (የከንፈር ቀለም) ቢቀቧአት ያው አሳማነቷን አትለቅም የሚለውን አባባል ያስታውሳል፡፡ እ.ኤ.አ በ2015 ያው የቀድሞው አሳማ ሊፒስቲክ ተቀብቶ እና ሌላም ማሳመሪያ ነገሮች ተጨምረውበት ለህዝብ እንደገና እንደ አዲስ አያቀረበ ነው፡፡ የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ በአሁኑ ጊዜ የ2015ን የቅርጫ ምርጫ ህጋዊ ለማድረግ እና የአንድ ፓርቲ አምባገነናዊ አገዛዝን ለዘላለሙ ለማስቀጠል እንዲቻል የስነምገባር መመሪያ፣ የቅርጫ (በነሱ አባባል ምርጫ) ቦርድ፣ የየቅርጫ መራጮች ምዝገባ፣ የቅርጫ ታዛቢዎች እና ሌሎችንም በማጭበርበር ድርጊቱ ያግዙኛል የሚላቸውን ነገሮች ሁሉ በማድረግ ሌት ቀን ባተሌ ሆኖ ይገኛል፡፡ በሊፒስቲክ የተቀባዉን አሳማ በረጋ ሐይቅ ላይ እንደተንሳፈፈ ከሚዋኘው አንገተ ረዥሙ ዳክዬ ጋር፣ በአትክልት ቦታ በጽጌረዳ አበባ ላይ የምታንዣብበው ቢራቢሮ ወይም በመስክ ሜዳ ላይ ከሚፈነጥዘው የበግ ግልገል ጋር አንድ መሆናቸውን እንድናምንለት ሊያጭበረብረን ይሞክራል፡፡ ሊፒስቲክ መቀባት ሁሉንም ነገር የሚያሳምረው ይመስላቸዋል፡፡ ምንም ሆነ ምን ከዕለቱ መጨረሻ ግን ሊፒስቲክ የተቀባው ዓሳማ ያው አሳማ እንጀ ሌላ ሊሆን አይችልም፡፡ እንደዚሁም ሁሉ በወሮበላ የዘራፊ ፖሊስ መንግስት የሚመራ የምርጫ ሂደት ምርጫ ሳይሆን ቅርጫ ነው (‘ም’ የምትለዋ ትክክለኛዋ ፊደል በተሳሳተችዋ ‘ቅ’ በምትለዋ ፊደል መተካቷን እና በሌላ ስያሜ የዋለ አዲስ ቃል መሆኑን ልብ ይሏል፡፡)

እ.ኤ.አ በ2015 ስለሚካሄደው የቅርጫ ምርጫ ለህዝብ ውይይት እና ክርክር የቀረበ ምክረ ሀሳብ፣

የኢትዮጵያን የፖለቲካ ሂደት የሚከታተል እና እውቀቱ ያለው ማንም ሰው ቢሆን እ.ኤ.አ በግንቦት 2015 ይካሄዳል እየተባለ ለሚነገርለት ምርጫ የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ሙሉ በሙሉ ድል ተቀዳጀሁ ብሎ አያውጅም ብሎ ሊያምን አይችልም፡፡ ለዚህም ምክንያቱ የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ የቅርጫ ፍልስፍናውን እና ተሞክሮውን ጆሴፍ (አስፈሪው ኮባ እየተባለ ከሚጠራው) ከስታሊን አምባገነናዊ ስብዕና የወረሱት ሰይጣናዊ ምግባራቸው ነውና፡፡ “የድምጽ ካርዳቸውን ወደ ድምጽ መስጫ ኮሮጆው የሚያስገቡ መራጮች በካርዶቻቸው የመምረጥ ውሳኔ የላቸውም፡፡ ይልቁንም የድምጽ ካርዱን የሚቆጥሩት ናቸው ድምጹን መወሰን የሚችሉት፡፡“ በ2015 ይካሄዳል እየተባለ ለሚነገርለት የቅርጫ ምርጫ የድምጽ ቆጣሪ ሆነው የሚቀርቡት የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ካድሬዎች ናቸው፡፡ ስለሆነም የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ የ2015 የቅርጫ ምርጫ ድል አድራጊነት ሳይታለም የተፈታ ወይም ደግሞ ቀድሞ የተበላ ዕቁብ ነው፡፡ ታሪክ ወደ ኋላ እየተቃኘ መጠናቱ ቀርቶ ይህ ግን ወደ ፊት የተሰራ ታሪክ ተብሎ የተመዘገበ ኩነት ነው! ስለ2015 የቅርጫ ምርጫ ልንናገረው የሚገባን ሆኖም ግን ያልተናገርነው ምን የቀረ ነገር አለ?

እነርሱ በለመዱት የማጭበርበር እና የዝርፊያ ልምዳቸው የቅርጫ ምርጫቸውን ያካሂዱ እላለሁ፡፡ ግድየላችሁም እራሳቸውን መትተው እንዲጥሉ እንፍቀድ! አቤ ሊንኮልን እንዲህ የሚለውን አባባል ሲያሰፍሩ እውነትም ትክክል ነበሩ፣ “ሁሉንም ህዝቦች ለጥቂት ጊዚያት ልታሞኛቸው ትችላለህ፡፡ እንደዚሁም ጥቂት ሰዎችን ለሁልጊዜ ልታሞኛቸው ትችላለህ፡፡ ሆኖም ግን ሁሉንም ህዝቦች ለሁልጊዜ እያሞኘሀቸው ልትኖር ከቶውንም አትችልም፡፡“ አቤ እንዲህ የሚል ነገር መጨመር ነበረባቸው፣ “ሆኖም ግን ሁልጊዜ እራስህን እያሞኘህ ሁልጊዜ መኖር ትችላለህ፡፡“ የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ 99.6 በመቶ ወይም ደግሞ 110 በመቶ የድምጽ ውጤት በማግኘት (የሞቱትን ሰዎች ሁሉ እየቆጠሩ) በዝረራ አሽንፊያለሁ እያሉ የቅርጫ ምርጫቸውን እንዲያካሂዱ እንፍቀድላቸው፡፡

እንግዲህ ቀጥተኛ የሆነው የመጀመሪያው ጥያቄ እንዲህ ይላል፡ አስቀድሞ በተበላ ዕቁብ እና አሸናፊው ማን መሆኑ ከጥርጣሬ በላይ በታወቀበት፣ ድምጽ አስቀድሞ በተጭበረበረበት እና ተሰርቆ ባለበት ሁኔታ የቅርጫ ምርጫ ማካሄድ ትርጉም ሊሰጥ ይችላልን? በፍጹም አይሰጥም! እራሳችሁን እያሞኛችሁ ለመቀጠል ካልሆነ በስተቀር ሁሉም ኢትዮጵያዊ ነቄ ነው! የሞኝ ለቅሶ መልሶ መላልሶ! የሞኝ ዘፈን ሁልጊዜ አበባዬ! ነውና ተረቱ፡፡

ለምሳሌ ያህል በሀገር ውስጥ ባለ በአንድ ስታዲየም በቡድን 1 የሚደረግን ብሄራዊ የእግር ኳስ ጨዋታ እናስብ፡፡ ሁሉም የቡድን 1 አድናቂዎች ከቡድኑ ደጋፊዎች ወይም ደግሞ ቡድን 1ን ሊደግፉ የሚችሉ በገንዘብ የተገዙ ሰዎች በእጅ እየተለቀሙ የተመረጡ ናቸው እንበል፡፡ የተቃዋሚው ቡድን ተጫዋቾች ደግሞ ከመጀመርያው አስከ መጨረሻው ሰው ጀምሮ በቡድን 1 ሰዎች የተመረጡ ናቸው እንበል፡፡ ዋናው ዳኛ እና የመስመር ዳኞች (እረዳት ዳኞች) በሙሉ በቡድን 1 ክፍያ እየተፈጸመላቸው የሚዳኙ ዳኞች ናቸው፡፡ ውሱን ለሆኑ የጨዋታው መዳኛ ህጎች እና እነዚህ ህጎች እንዴት አድርገው በተግባር ላይ መዋል እንዳለባቸው የሚወስኑት የቡድን 1 ሰዎች ናቸው እንበል፡፡ እነዚሁ ዳኞች የተቃዋሚ ቡድን አባላትን ብቻ በሚመለከት እንደፈለጉት መቅጣት እንዲችሉ ስልጣኑ ተሰጥቷቸዋል፡፡ እነዚህ ዳኞች ከተቃዋሚ ቡድኑ ብቻ አጥፍታችኋል በማለት ማንኛውንም ምክንያት በመስጠት ከጨዋታው ውጭ በማድረግ ማባረር እንደሚችል ስልጣን ተሰጥቷቸዋል፡፡ እነዚህ ዳኞች ውሱን በሆኑ የጨዋታው ህጎች ወይም ደግሞ በአጠቃላይ ጨዋታውን በሚመለከት በሁሉም መንገድ እውነታዎች እና አወዛጋቢ ነገሮች ሲኖሩ የመጨረሻ ውሳኔ የሚሰጠው በእነዚሁ ዳኞች ነው፡፡ ዳኞች ጨዋታውን ለማስቆም፣ ማገድ፣ ወይም ደግሞ በእራሳቸው ስልጣን ተቃዋሚዉን ቡድን ብቻ ማባረር ይችላሉ፡፡ ሁሉንም መግባት ያለባቸውን ጎሎች ብዛት እና አሸናፊው ቡድን የትኛው መሆን እንዳለበት የሚወስኑት የቡድን 1 ኃላፊዎች ናቸው፡፡

በዚህ ዓይነት ሁኔታ ማንም ተቃዋሚ የሆነ ቡድን ከቡድን 1 ጋር የውድድር ጨዋታ ቢያደርግ ትርጉም ሊሰጥ ይችላልን?

በተመሳሳይ መልኩ እ.ኤ.አ በ2015 ይካሄዳ እየተባለ የሚደሰኮርለት የቅርጫ ምርጫ የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ የተቆጣጠረው፣ የሚያስተዳድረው እና የመራጮች የምዝገባ ሂደትን የሚመራው እራሱ ባቋቋመው የምርጫ ቦርድ አማካይነት ነው፡፡ ወያኔ የምርጫ ስነምግባር ደንቡን እራሱ ያዘጋጃል፣ እናም በስራ ላይ እንዲውል ያደርጋል፡፡ ወያኔው እራሱ የምርጫ ታዛቢዎችን መርጦ እራሱ ያሰማራል፡፡ ወያኔው እራሱ ከእርሱ ጋር መወዳደር የሚችሉትን የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች መርጦ ያጸድቃል፡፡ ለተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች እራሱ ወያኔ ገንዘብ ይሰጣል እንዲሁም ያስተባብራል፡፡ ወያኔ የማይፈልጋቸውን እና የዓይናቸው ቀለም አላማረኝም የሚላቸውን የፖለቲካ ፓርቲዎች ከህግ አግባብ ውጭ በሚፈልገው መልኩ ማባረር ይችላል፡፡ ወያኔ እራሱ የድምጽ ቆጠራ ያካሂዳል፡፡ የቅርጫ ምርጫው ነጻ እና ፍትሀዊ ለመሆኑ እራሱ ወያኔ መግለጫ ይሰጣል፡፡ ወያኔ ማግኘት የሚፈልገውን የድምጽ ውጤት መቶኛ እራሱ ይወስናል፡፡ ወያኔ የቅርጫ ምርጫውን ማን እንዳሸነፈ እራሱ ይወስናል፡፡

የዚህ ዓይነት ሁኔታ በተንሰራፋበት ከባቢ አየር እ.ኤ.አ በ2015 ይካሄዳል ለሚባለው ምርጫ ከወያኔ ጋር መወዳደር ትርጉም ይሰጣልን?
ከላይ እስከታች በፖለቲካ ሸፍጥ ተተብትቦ በሚገኝ ጨዋታ በአስመሳይነት ገብቶ ለመወዳደር መሞከር የለየለት አስመሳይነት መሆን አይደለምን?
አንድ የምርጫ ዕጩ ተወዳዳሪ ግለሰብ ወይም ደግሞ ፓርቲ በዚህ የሸፍጥ ፖለቲካ ውስጥ ገብቶ የሚወዳደር ቢሆን ይህ ድርጊት ለቅርጫ ምርጫው የነጻ እና ፍትሀዊነት ህጋዊነት መመስከር ሊሆን አይችልምን?

እንደዚህ ዓይነቱ የቅርጫ ምርጫ የመድረክ ላይ ተውኔት በዴሞክራሲ ጽንሰ ሀሳብ ላይ የቁማር ጨዋታ መጫወት አይደለምን?

ሁለተኛውን ጥያቄ እነሆ፡ ስለወያኔ የቅርጭ ምርጫ ከመነጋገር ይልቅ ስለሌላ ጉዳይ መነጋገሩ አይሻልምን?

ከዚህ ይልቅ ህዝባዊ መሰረትን በተላበሰ መልኩ ህዝቡ እንዲማር እና ግንዛቤውን ከፍ እንዲል በማረግ ስለነጸ እና ፍትሀዊ ምርጫ፣ ስለዴሞክራሲያዊ ተቋማት ግንባታ፣ ስለህግ የበላይነት እና ስለ ስለሰብአዊ መብቶች መከበር፣ ወዘተ የሲቪክ ትምህርት እና ስለመልካም ተሞክሮዎች ማስተማር የበለጠ ትርጉም ያለው ስራ አይደለምን? ከወያኔ የይስሙላ የቅርጫ ምርጫ ጋር እና የውሸት ዴሞክራሲ (የማጭበርበር ዴሞክራሲ) ጋር በተያያዘ ያለው ችግር ምን እንደሆነ ግንዛቤ ለመውሰድ እና በጠቅላላ የኢትዮጵያን ህዝብ የፖለቲካ የውይይት ከፍታ በማሳደግ አጋጣሚውን መጠቀም አይቻልምን?

እ.ኤ.አ በ2015 ስለሚካሄደው የወያኔ የቅርጫ ምርጫ በምንነጋገርበት ጊዜ ለምን ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለብን፣

በዚህ ትችቴ ላይ ለማስተላለፍ የምፈልገው ዋናው መልዕክት አንድ ቀላል ቁም ነገር ነው፡ ይኸውም እ.ኤ.አ በ2015 በኢትዮጵያ ይካሄዳል እየተባለ ስለሚነገረው የቅርጫ ምርጫ በጣም ጥንቁቆች፣ ሙሉ ትኩረትን የያዝን እና የነገሮችን አመጣጥ እና አካሄድ ከፍተኛ የሆነ ትኩረት በመስጠት በአንክሮ መመልከት አለብን፡፡ ጆርጅ ኦርዌል እንዲህ የሚል ምክርን ሰጥተው ነበር፣ “የፖለቲካ ቋንቋ …ነጭ ውሸቶችን እውነት ለማስመሰል እና የተከበረውን ነገር አዋርዶ ለማሸነፍ እና ቅርጽ እንዲኖረው ለማስቻል አዕምሮን ለማሳመን የሚደረግ ባዶ የሆነ ግብግብ ነው፡፡“
በ2015 የሚካሄደውን የፖለቲካ ሸፍጥ የተንሰራፋበትን የወያኔ የዘረፋ ምርጫ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ እንደተካሄደ በማስመሰል ሳናውቅ እኛው በስህተት ህጋዊ ሽፋን እንዲሰጠው እናደርጋለን፡፡ የወያኔ ካድሬዎች፣ ግብረ አበሮች እና አሽከሮች ስለ2015 የይስሙላ ቅርጫ ምርጫ ሲናገሩ ዋናው ዓላማቸው የቅርጫ ምርጫውን እውነትነት ያለው ለማስመሰል፣ ይህንን የሸፍጥ ምርጫ የተከበረ ለማስመሰል እና የኢትዮጵያን ህዝብ ለማታለል እንዲሁም እነዚህን ለጋሽ እና አበዳሪ ድርጅቶችን በባዶው በማጭበርበር ላይ ይገኛሉ፡፡

የወያኔ ወሮበላ ዘራፊ ቡድን ስብስብ የያዘውን የቅርጫ ምርጫ ሀሳብ ወደ ህዝብ በማውረድ በመጠኑም ቢሆን ያሳካው መሆኑን ሙሉ በሙሉም ባይሆን በተወሰነ ደረጃ እቀበላለሁ፡፡ የኢትዮጵያ ብዙሀን ህዝቦች እ.ኤ.አ በ2015 ለሚካሄደው የቅርጫ ምርጫ ዝግጁ እንዲሆኑ በየዕለቱ ይጮህባቸዋል፡፡ የወያኔ ጥሩንባ ነፊ የሆኑት በመላ ሀገሪቱ ተሰራጭተው የሚገኙት የምርጫ ጣቢያዎች ቢሯቸውን ክፍት አድርገው መራጮችን ለመመዝገብ በመቀስቀስ ላይ ይገኛሉ፡፡ ወያኔ 44,454 የምርጫ ጣቢያዎችን በማዘጋጀት 222,270 የህዝብ ታዛቢዎችን እና 547 የምርጫ ወረዳዎችን እንዲሁም 1,935 የምርጫ ኃላፊዎችን በመመልመል እንዳዘጋጀ በመናገር ላይ ይገኛል፡፡ አዲስ አበባ 1,523 የምርጫ ጣቢያዎች፣ 7,615 የምርጫ ታዛቢዎች እና 65 የምርጫ አስፈጻሚ ኃላፊዎች እንደሚኖሯት ወያኔ ግልጽ አድርጓል፡፡ ወያኔ የ2015 ሀገር አቀፍ ምርጫ እ.ኤ.አ በ2010 እንደተካሄደው ሀገር አቀፍ ምርጫ ሁሉ ነጻ እና ፍትሀዊ እንደሚሆን በተደጋጋሚ በመናገር ላይ ይገኛል፡፡ እኛ ደግሞ ነጻ እና ፍትሀዊ ምርጫ ወዴት አለሽ እንላለን፡፡

የተቃዋሚ የፖለቲካ አመራሮች ስለቅርጫ ምርጫው ነጻ እና ፍትሀዊ አለመሆንን በማስመልከት እዚህም እዚያም ትችትን ያቀርባሉ፡፡ ወያኔ እነዚህ የተቃዋሚ ፓርቲዎች እንዲሰባሰቡ እና ተቃውሟቸውን በሰላማዊ መንገድ እንዲገልጹ አይፈቅድላቸውም፡፡ የቅርጫ ምርጫው ለወያኔ በመጠኑም ቢሆን የበለጠ ዴሞክራሲያዊ እና ሁሉን አቀፍ አሳታፊ እንደሆነ የመምሰል እድልን ሊያጎናጽፈው የሚችል ዕድል ይኖረዋል ብለው የሚናገሩ ጥቂት ሰዎች አሉ፡፡ ሁሉን አቀፍ እና አሳታፊ የምርጫ ስርዓት የሚዘረጋ ከሆነ የወያኔ የዴሞክራሲ መሻሻል ወደ ማዕዘን የሚገፋ ይሆናል፡፡ በእውነት ለመናገር በሸፍጥ የቅርጫ ምርጫ አማካይነት ወሮበላ የዘራፊ አገዛዝ ወደ ዴሞክራሲ ይሸጋገራል ማለት ከካሮት ደም እንደመጭመቅ ይቆጠራል የሚል ሀሳብ አለኝ፡፡

የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች እና ትችት አቅራቢዎች ስለወያኔ የቅርጫ ምርጫ ይህን እና ያንን ጉዳይ እያሉ ሲነጋገሩ በሰማሁበት ጊዜ የየካቲት (የሚደብር) ወር ላይ መሆናችንን አረጋገጥኩ፡፡ እያንዳንዱ ሰው ምንም ነገር ሳያስብ በተለይም የውጭ ብዙሀን መገናኛ፣ የዲፕሎማሲው ማህበረሰብ እና አልፎ አልፎም የድብቅ ዕዳ ገንዘብ አበዳሪዎች ማለትም ዓለም አቀፍ የድህነት አቃጣሪዎች እያልኩ የምጠራቸው ስለ2015 የቅርጫ ምርጫ በሚነጋገሩበት ጊዜ ግራ ይገባኛል፡፡ የወያኔን የቅርጫ ምርጫ በትክክል ምርጫ ነው ብሎ መናገር የዴሞክራሲያዊ ምርጫ መሰረታዊ ጽንሰ ሀሳብን መዘለፍ፣ ማንኳሰስ እና በደፈናው መተቸት ማለት ነው፡፡ እ.ኤ.አ በ2015 በኢትዮጵያ የሚካሄደው ምርጫ “የዓሳማን ከንፈር ሊፒስቲክ በመቀባት ዓሳማ ቆንጆ ነው ከማለት ጋር መሳ ለመሳ ነው” በማለት የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች እና ሌሎች ትችታቸውን በማቅረብ አውጀው በዴሞክራሲያዊ ስርዓት ትክክለኛው ምርጫ፣ ድምጽ አሰጣጥ እና የፖለቲካ ተሳትፎ ምን ማለት እንደሆነ ለኢትዮጵያ ህዝብ ሲያስተምሩ እና ሲሰብኩ ማየት እፈልጋለሁ፡፡

እውነታው ተንጠርጥሮ ሲታይ ግን እ.ኤ.አ በ2015 ስለሚካሄደው የቅርጫ ምርጫ ወያኔ እያካሄደ ባለው የፕሮፓጋንዳ ጦርነት አሸናፊ እየሆነ ነው፡፡ ስለዚህ ጉዳይ የሚያወሩበት ትረካ እያገኙ ነው፡፡ በእውነት እንደዚህ ላሉት አንደኛ ደረጃ ትምህርትን እንኳ ስርዓት ባለው መልኩ ላላጠናቀቁ ተራ የሆኑ የጫካ ሽፍቶች ይህ ድርጊት ታላቅ ስኬት ነው፡፡ ከፍተኛ የሆነውን ዲግሪያቸውን በድረ ገጽ በመከታተል ከዲፕሎማ መቀፍቀፊያ (ፋብሪካ) የማፈሪያ ተቋማት ማግኘታቸውን ስሰማ ላስመዘገቡት ስኬት እውቅና እሰጣለሁ (ምን ዓይነት አሳፋሪ ነገር ነው! ምን ዓይነት አዋራጅ ድርጊት ነው!)

በማጭበርበር የተካነው የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ የእነርሱን የቅርጫ ምርጫ እውነተኛ ምርጫ እንደተካሄደ ሁሉ እውቅና በሚሰጥበት ጊዜ እርስ በእርሳቸው የተለየ የማፊያ ሰላምታ እየተሰጣጡ በመኮፈስ በሽፍጥ ወንጀላቸው ይቀጥሉበታል፡፡ ፕሬዚዳንት ኦባማ በባለፈው መስከረም “በኢትዮጵያ ስለሚካሄደው ቅርጫ ምርጫ የማውቀው ነገር አለ“ ማለታቸውን ተከትሎ በድረ ገጽ የተለቀቀ አንድ አስተያየት አንብቤ ነበር፡፡ ያንን ትችት የጻፈው ሰው ፕሬዚዳንት ኦባማ እ.ኤ.አ በ2015 ስለሚካሄደው ምርጫ ቀድሰው ነጻ እና ፍትሀዊ መሆኑን አረጋግጠዋል የሚል አስተያየት ሰጠ፡፡ (እኔ አላውቅም ምናልባትም ኦባማ ምርጫ ነው ብለው ያምኑ ይሆናል፡፡ ሆኖም ግን እ.ኤ.አ በ2015 ይካሄዳል ስለሚባለው የቅርጫ ምርጫ ኦባማ አስቀድሞ የሚያውቁት ነገር መኖሩን ለማወቅ እንድንችል ግልጽ እንዲደረግልን ቀደም ሲል ጥያቄዎቼን አዘጋጅቼ በድረ ገጽ ለህዝብ ያቀረብኩ በመሆኑ ተገቢው ምላሽ ይሰጠኛ በማለት በመጠባበቅ ላይ ነኝ፡፡)

ለተቃዋሚዎች ያለኝ አስተያየት እ.ኤ.አ በ2015 ይካሄዳል እየተባለ የሚነገርለትን የቅርጫ ምርጫ ለፖለቲካ ሳይንስ ተማሪዎች የመለማመጃ ትምህርት ቢተውላቸው የተሻለ ነው፡፡ (ለነገሩ ለተማሪዎች መማርያ አንዲሆን ባሁኑ ወቅት ተደርግዋል።)

የኢትዮጵያ ምሁራን፣ የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች እና ሌሎችም እ.ኤ.አ በ2015 ከሚካሄደው የቅርጫ ምርጫ ጠቃሚ ትምህርትን በመቅሰም ለቀጣይ ስራዎቻቸው መዘጋጀት እንዳለባቸው እምነት አለኝ፡፡ ከዓለም አቀፍ የምርጫ መስፈርት አንጻር ነጻ እና ፍትሀዊ ምርጫ ያለመካሄዱን እና ይህንን የሸፍጥ ድርጊት በማጋለጥ የሚደረገውን የዘርፋ የቅርጫ ምርጫ እንዴት በተለዬ መልኩ የማታለል፣ የማጭበርበር እና የዘረፋ ድርጊት እንደተፈጸመበት ደግሞ እና ደጋግሞ ለኢትዮጵያ ህዝብ እና ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ማጋለጥ ነው፡፡ የወያኔን የቅርጫ ምርጫ የማጭበርበር እና የዘረፋ የድምጽ ውጤት እንደማስተማሪያ በመውሰድ ምርጫው እንዴት ሸፍጥ እንደተሰራበት፣ የምርጫ ካርዶችና ድምጽ ሰጭዎች እንዴት እንደተጭበረበሩ ለህዝብ ማስተማር እና ማሳወቅ ነው፡፡ በቅርጫ ምርጫ 99.6 በመቶ እና ከዚያ በላይ ድምጽ በማግኘት ድልን ለመቀዳጀት የድምጽ ካርዶች እንዴት እንደሚጭበረበሩ፣ ድምጾች እንዴት እንደሚገዙ፣ በድምጽ ቆጠራ ላይ እንዴት ችግር እንደሚፈጠር፣ ድምጾች እንደማይቆጠሩ፣ ደምጾች በስህተት እንደሚመዘገቡ ይህንን የቅርጫ ምርጫ ህዝቡን ለማስተማር እና ለማንቃት የምንጠቀምበት መሆን አለበት፡፡

የቅርጫ ምርጫው ከመድረሱ በፊት የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብን የማይደግፉትን ወገኖቻችንን ከጨዋታ ውጫ ለማድረግ በምርጫ ጣቢያ አካባቢ ያለውን የህዝቡን ስብጥር በመቀየር እና በትክክለኛ መራጮች ላይ የፕወዛ የሸፍጥ ስራ በመስራት እንዳይመርጡ በማድረግ የምርጫ ዘራፊዎች እና የምርጫ ከያንያን እጅግ በጣም የተወሳሰቡ የምርጫ ስልቶችን እየተገበሩ ምርጫውን በማጭበርበር የህዝቡን ዴሞክራሲያዊ መብት በመደፍጠጥ እነርሱ ለርካሽ የስልጣን ጥማታቸው እና ለከርሳቸው ሲሉ የሚያደርጉትን ዕኩይ ምግባር ሁሉ እየነቀስን በማውጣት ህዝቡን ማስተማር እና ማሳወቅ ትርጉም የሚሰጥ ስራ አይደለምን? ኃይል መጠቀም እና ኃይል ለመጠቀም ማስፈራራትን፣ በምርጫ ጣቢያዎች ላይ የድብደባ የውንብድና ስራዎችን መስራትን፣ የህግ እና ኢኮኖሚያዊ ማስፈራሪያዎች ማድረግን፣ መረጃ ማዛባትን እና የሀሰት መረጃ በመስጠት 99.6 በመቶ እና ከዚያ በላይ የሆነ ድምጽ በማግኘት ድል መቀዳጀትን ሊያከሽፍ በሚችል መልኩ ህዝቡን በማስተማር የመብቱ ተጠቃሚ ማድረግ ትርጉም የሚሰጥ ተግባር ሊሆን አይችልምን?

እ.ኤ.አ በ2015 የመለስ ዜናዊ የሙት መንፈስ እና የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብብስ የምርጫ ዕቅድ ስልት፣

አሁን ሀገሪቱን በማተራመስ ላይ ያለው የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ በአሁኑ ጊዜ ሌላ ምንም ዓይነት ለውጥ ወይም ማሻሻያ ሳይደረግበት አሁን በህይወት በሌለው በመለስ ዜናዊ መሀንዲስነት የተቀየሰውን የምርጫ ማጭበርበር እና መዝረፍ መሪ ዕቅድ እንዳለ በመውሰድ በተግባር እየተረጎሙት እንዳለ የምናውቅ ስንቶቻቸን እንደሆንን ባውቅ በጣም የሚያስደንቀኝ ይሆናል፡፡ እ.ኤ.አ በ2015 የሚካሄደው የቅርጫ ምርጫ ስልት እ.ኤ.አ በ2010 ከተካሄደው እና 99.6 በመቶ ድልን ለመቀዳጀት በተግባር ላይ ከዋለው ስልት ጋር አንድ እንደሆኑ በርካታ ኢትዮጵያውያን/ት የሚያውቁ መሆናቸውን እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ የመለስ የቅርጫ ምርጫ የነበረው ስልት እና አሁንም እየተገበረ ያለው ያው የቀድሞው ስልት በአንድ መሰረታዊ ሀሳብ ላይ መሰረት ያደረገ ነው፡፡ ወያኔ በሃገሪቷ ውስጥ ያለ ብቸኛው ጨዋታ ነው! ወያኔ የኢትዮጵያ ተከላካይ፣ አቅራቢ እና ብቸኛው የኢትዮጵያ ዘበኛ ነው፡፡ ወያኔ በኢትዮጵያ ብቸኛው የመረጋጋት፣ የሰላም፣ የልማት እና የእድገት ዋስትና እና ምሰሶ ነው፡፡ አበዳሪ እና ለጋሽ ድርጅቶች ይህ ግልጽ መሆኑን እወቁ! ላለፉት 24 ዓመታት ስታካሂዱት የነበረው የሙስና የዘረፋ ተግባራት ያለወያኔ ሽፋን እንደሚጋለጥ ስለምታውቁ ከወያኔው ጋር እጅ እና ጓንት ሆናችሁ የኢትዮጵያን ህዝብ ሀብት በመዝረፍ ላይ ትገኛላችሁ፡፡ ይህ ግን የጊዜ ጉዳይ እንጅ ወያኔ ሸፍኖላችሁ ሊቆይ ስለማይችል በውርደት አዘቅት ውስጥ እንደምትወድቁ እና በህግ ተጠያቂ እንደምትሆኑ እወቁ፡፡ አትጠራጠሩ።

አሁን ለጊዜው የሸክስፒርን አባባል በመዋስ እ.ኤ.አ በ2015 በኢትዮጵያ በሚካሄደው የቅርጫ ምርጫ ላይ የመለስ ዜናዊ የጨለማ እና የሲኦል ሙት መንፈስ አጥልቶ እንደምያንዛብብ ለማስጠንቀቅ እፈልጋለሁ፡፡ መለስ ለተዘረፉት እና ለተሰረቁት የሸፍጥ የቅርጫ ምርጫዎች ተውኔት ዋና ደራሲ እና ጸሀፊ ነበር፡፡ መለስ መንግስታዊ ስልጣንን ከመቆናጠጡ በፊት በጫካ በነበረበት ጊዜ የሸፍጥ እና የዝርፊያ ቅርጫ ምርጫዎችን መጽሀፍ ረቂቅ ጽፎ ነበር፡፡ ያንንም ስልት በመጠቀም ተግባራዊ ማድረግ ጀምሮ ነበር፡፡ የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ እ.ኤ.አ በ2005 ትንሽ በእራስ የመተማመን ስሜት ተሰምቶት የፖለቲካ ምህዳር በሩን ገርበብ አድርጎ እንደተወው የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ህዝቡን በማሳተፍ በርግደው ከፈቱት፡፡ ሆኖም ግን የማፊያው መሪ መለስ ወዲያውኑ ትምህርት ወሰደ! ትክክለኛ ለሆነ ተቃዋሚ በፍጹም ምንም ዓይነት ቀዳዳ ለመክፈት መፍቀድ አልፈለግም፡፡ እ.ኤ.አ በ2005 የተቃዋሚ የፖለተኪ መሪዎችን፣ የነጻው ፕሬስ ጋዜጠኞቾን፣ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾችን፣ ሰላማዊ አመጸኞችን እና የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት መሪዎችን በሙሉ ሰብስቦ በእስር ቤት አጎረ፡፡ የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ በአሁኑ ጊዜ እየሰራው ያለው የሸፍጥ ስራስ ታዲያ የዚያ ግልባጭ አይደለምን?

እ.ኤ.አ በ2015 ይካሄዳል እየተባለ ከበሮ የሚደለቅለት የቅርጫ ምርጫ ዕቅድ እና ስልት ወያኔ ኢትዮጵያውያንን/ትን እና የእነርሱን የውጭ የገንዘብ ደጋፊዎቻቸውን ለማሳመን በሚል ዕኩይ ስሌት የሚከተሉትን እንደ ዋና የማሳመኛ ነጥቦች አድርገው የሚቀርቡት ፍሬ ከርስኪ ሃሳቦች፡

ወያኔ በስልጣን ላይ ከሌለ ኢትዮጵያ እንደ ሩዋንዳ ሁሉ በዘር የእርስ በእርስ ጦርነት ውስጥ ትዘፈቃለች፡፡

ወያኔ በስልጣን ላይ ከሌለ እንደ ደቡብ ሱዳን ሁሉ ኢትዮጵያ በጎሳ የመገነጣጠል፣ ግጭት እና ማቆሚያ ወደሌለው ጦርነት ሊያመራ ይችላል፡፡

ወያኔ በስልጣን ላይ ከሌለ “ሰይጣኖቹ” አማራዎች ስልጣንን ይነጥቁ እና የነበረውን መጥፎ አገዛዛቸውን ይቀጥላሉ፡፡

ወያኔ በስልጣን ላይ ከሌለ “ኦሮሞዎች” ስልጣንን ይነጥቁ እና “አማራዎችን” ይገድላሉ፡፡

ወያኔ በስልጣን ላይ ከሌለ “ትግሪዎች” ሊገደሉ ይችላሉ፣ እናም ትግሬዎቹ በ”አማራዎች” እና በ”ኦሮሞዎች” የከፋ ጉዳት ሊደርስባቸው ይችላል፡፡

ወያኔ በስልጣን ላይ ከሌለ በርካታ ብሄር ብሄረሰቦችን የያዘችው ኢትዮጵያ አናሳ ብሄረሰቦች ከኖሩበት እንዲፈናቀሉ ይደረጋሉ፣ በቀደምቶቻቸው ተይዘው የነበሩትን መሬቶቻቸውን እንዲያጡ ይደረጋሉ፣ እንዲሁም በእራሳቸው ቋንቋ መናገር እና መጠቀም እንዳይችሉ ይደረጋሉ፡፡

ወያኔ በስልጣን ላይ ከሌለ በመጥፎነቱ ታዋቂ የሆነው የደርግ አምባገነን ወታደራዊ መንግስት ወደ ስልጣኑ ተመልሶ መጥፎ ገጽታውን ያመጣል፡፡

ወያኔ በስልጣን ላይ ከሌለ “እስላሞች” “የእስልምና ህግ” የሆነውን ሻርሪያን በኢትዮጵያ ህዝቡ ላይ እንዲጫን ያደርጋሉ፡፡

ወያኔ በስልጣን ላይ ከሌለ “እስላሞች” እና “ክርስቲያኖች” በማዕከላዊ አፍሪከ ሬፐብሊክ እንደታየው ሁሉ እርስ በእርሳቸው ይገዳደላሉ፡፡

ወያኔ በስልጣን ላይ ከሌለ ቦኮሀራም በናይጀሪያ እያደረገ እንዳለው ሁሉ በኢትዮጵያም የእስልምና አክራሪ ጽንፈኛ ቡድን ከፍተኛ የሆነ ችግር ይፈጥራል፡፡

ወያኔ በስልጣን ላይ ከሌለ በሙስና እና በስርቆት ሀብታም የሆኑ ሁሉም ህዝቦች ሀብቶቻቸውን እንዲያጡ ይደረጋሉ፣ እናም ወደ እስር ቤት ይታጎራሉ እንዲሁም ወደ ግዞት ይጋዛሉ፡፡

ወያኔ በስልጣን ላይ ከሌለ የምጣኔ ሀብቱ እንዳለ ይወድቃል፣ እናም ኢትዮጵያ በየዓመቱ በአማካይ ከ11-15 በመቶ የምጣኔ ዕድገት (ሀሳባዊ) ማስመዝገቧ ይቀራል፡፡ (ኢትዮጵያ ላለፉት 10 ዓመታት በየዓመቱ በአማካይ 11 በመቶ የምጣኔ ሀብት ዕድገት አስመዝጋባለች በማለት የቅትፈት ፕሮፓጋንዳቸውን በመንዛት ላይ ያሉት የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ፣ የዓለም ባንክ እና ሌሎች ዓለም አቀፍ የድህነት አቃጣሪ ወትዋቾች የሚያሰሙት ባዶ ዲስኩር ከምንም ጥርጣሬ በላይ ተራ ቅጥፈት እና ነጭ ውሸት የቁጥር ጨዋታ መሆኑን አረጋግጫለሁ፡፡ አራት ነጥብ!)

ወያኔ በስልጣን ላይ ከሌለ በኢትዮጵያ ውስጥ ልማት የሚባል ነገር አይኖርም፡፡

ወያኔ በስልጣን ላይ ከሌለ ሰማይ ተደርምሶ በመሬት ላይ ይወድቃል፣ እናም ከዋክብት እየተስፈነጠሩ ከኢትዮጵያ ጋር እየተላተሙ ይሰባበራሉ፡፡

ወያኔ በስልጣን ላይ ከሌለ ኢትዮጵያ የምትባል ሀገር አትኖርም!

በሌላ አባባል የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ እ.ኤ.አ በ2015 ለሚካሄደው የቅርጫ ምርጫ ማሸነፊያ ዋና ስልት አድርጎ የያዘው ያንኑ ያረጀውን እና ያፈጀውን የማስፈራራት እና የጥላቻ የሸፍጥ ፖለቲካውን ነው፡፡ የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ የሚችል ከሆነ፣

አማራዎች እንደፈሩ እንዲቆዩ ማድረግ እና ኦሮሞዎች ስልጣን እንዳይነጥቁ በማድረግ አሸነፍን እያሉ እያጭበረበሩ በስልጠናቸው ላይ እንደ መዥገር ተጣብቀው መቆየት፣

ኦሮሞዎች አማራዎችን እንዲጠሉ ማድረግ እና አማራዎች ተመልሰው ወደ ስልጣን እንዳይመጡ ማድረግ እና አሸናፊ ነኝ እያለ በስልጣን ላይ ተቆናጥጦ መቆየት፣

ኦሮሞዎች በታሪክ ያሏቸውን ቅሬታዎች እያነሱ ጊዚያቸውን ለዚያ በማዋል እንዲዘናጉ ማድረግ እና በደርዘኖች ለሚቆጠሩት የኦሮሞ ተማሪዎች ግድያ ትኩረት እንዳይሰጡ በማድረግ እነርሱ አሸናፊዎች ሆነው በስልጣን ላይ ተፈናጥጦ መዝለቅ፣

የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ከሌለ በስተቀር በኢትዮጵያ ያሉ አናሳ ብሄረሰቦች ዓለም በእነርሱ ላይ የምትገለባበጥ እንደምትሆን በማስፈራራት አሸናፊ ሆነው ሲገዙ ለመኖር መንቀሳቀስ፣

ክርስቲያኖች እና እስላሞች እርስ በእርስ እንዲፈራሩ፣ በጥላቻ እንዲተያዩ እና እርስ በእርሳቸው መተማመን እንዳይችሉ በማድረግ እነርሱ አሸናፊ በመሆን ስልጣናቸውን ጨብጠው መቆየት፣

የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ከሌለ እነርሱን በገንዘብ የሚረዷቸው ሀብታሞች ሀብታቸውን እንደሚያጡ እና ወደ እስር ቤት እንደሚጋዙ በማስፈራራት እነርሱ አሸናፊ ሆነው በስልጣናቸው እንዲቀጥሉ ማድረግ፣

የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ በስልጣን ላይ ከሌለ ለአበዳሪ እና ለጋሽ ድርጅቶች ሀገራዊ ፍላጎቶቻቸውን የሚያስጠብቅላቸው ስለማይኖር በማታለል እና በማጭበርበር አሸናፊ ሆነው የስልጣን ልጓማቸውን እንደጨበጡ ለመቀጠል፣

በኢትዮጵያ በሚካሄዱ የይስሙላ ምርጫዎች ወያኔ በጠራራ ጸሐይ በሚሰርቀው እና በሚዘርፈው የመራጭ ህዝብ ድምጽ ምክንያት አበዳሪ እና ለጋሽ ድርጅቶች ሁልጊዜ እንደሚያደርጉት ሁሉ አይተው እንዳላዬ፣ ሰምተው እንዳልሰሙ፣ ከንፈሮቻቸውን በመምጠጥ ዝም እንዲሉ በማድረግ አሸናፊ ሆነው የመግዛት ሀራራቸውን ማራዘም የሚሉትን ቅዠቶች እና ባዶ ምኞቶች በመደርደር ላይ ይገኛሉ፡፡

ጥቂት ቃላት ስለነጻ እና ፍትሀዊ ምርጫዎች፣

ስለነፃ እና ፍትሀዊ ምርጫዎች ምንም ዓይነት ታዕምራዊ ነገር የለም፡፡ ስለነጻ እና ፍትሀዊ ምርጫዎች የአካሄድ ስርዓቶች በዓለም አቀፍ ድርጅቶች እንዲሻሻሉ እና የጠሩ እንዲሆኑ ተደርጓል፡፡ እ.ኤ.አ በ1889 የተቋቋመው እና የፓርላማዎች ህብረት/Inter-Parliamentary Union እየተባለ የሚጠራው ዓለም አቀፍ ድርጅት ስምርጫዎች እና ስለምርጫዎች የክትትል ዘዴዎች ዋና መመሪያ የሆነ ሰነድን በማዘጋጀት ቀዳሚ ሆኗል፡፡ የዴሞክራሲ እና የመራጮች እገዛ ተቋም/Institute for Democracy and Electoral Assistance IDEA) የተባለው ሌላው የስዊድን ዓለም አቀፍ ተቋም ስለነጻ እና ፍትሀዊ ምርጫዎች ምርጥ የተባሉ ልምዶችን እና ተሞክሮዎችን እያፈላለገ በመቀመር ታላቅ አስተዋጽኦ የሚያደርግ ተቋም ነው፡፡ እ.ኤ.አ በ2010 በኢትዮጵያ ተደርጎ በነበረው ሀገር አቀፍ ምርጫ ይህ ተቋም (IDEA) ስምርጫ ስነምግባር ደንብ ዝግጅት ለማገዝ መለስን ጠይቆ ነበር፡፡ ሆኖም ግን መለስ ሞት ቀደመው እንጅ ፈቃደኛ ሳይሆን ይህንን ተቋም ጥርሱን ሰብሮ አባረረው፡፡

ለነጻ እና ፍትሀዊ ቅድመ ምርጫ ተግባራዊ የሆነ ግንዛቤ እንዲኖር ከተፈለገ የአፍሪካ ህብረት በአፍሪካ የዴሞክራሲያዊ ምርጫዎች መርሆዎች መግለጫዎችን/African Union Declaration on the Principles Governing Democratic Elections in Africa- AHG/DECL. 1 (XXXVIII) እና የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የአፍሪካ ህብረት የምርጫ ታዛቢዎች እና ክትትል ተልዕኮዎች መመሪያ/AU Guidelines for African Union Electoral Observation and Monitoring Missions የሚሉትን ሰነዶች መመልከት ብቻ በቂ ነው፡፡ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት መርሆዎች እና መመሪያዎች ነጻ እና ፍትሀዊ ምርጫዎችን ለማካሄድ በርካታ የሆኑ ጉዳዮችን ይዘዋል፡፡ ከፍተኛ የሆነን የህዝብ ተሳትፎ ለማረጋገጥ በነጻ የመደራጀት እና የፖለቲካ መቻቻል መኖር አለበት፡፡ ሁሉም ተወዳዳሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች እኩል በሆነ መልኩ የመንግስት የመገናኛ ብዙሀንን ተጠቃሚ መሆን አለባቸው፡፡ የፍትህ አካላት ከፖለቲካ ጣልቃገብነት እና ጫና ነጻ መሆን አለባቸው፡፡ ከምርጫ ስነምግባሩ ጋር በተያያዘ መልኩ የሚነሱ ውዝግቦችን ለመዳኘት የሚችል እና መፍትሄ የሚሰጥ ውጤታማ የሆነ ፍርድ ቤት መኖር አለበት፡፡ የምርጫ ቦርዶች ገለልተኛ፣ ከአድልኦ የጸዱ እና በሙያው በሰለጠነ የሰው ኃይል መመራት አለባቸው፡፡ የሲቪል ማህበረሰብ ቡድኖች ቁልፍ ሚና ሊጫወቱ የሚችሉበት የመራጮች ትምህርት ሊሰጥበት የሚችል አሰራር መኖር አለበት፡፡ በአጠቃላይ በምርጫ ሂደቶች ጊዜ ሊከሰቱ የሚችሉትን የምርጫ ማጭበርበሮችን፣ ሸፍጦችን ወይም ደግሞ ሌሎች ህገወጥ የሆኑ ድርጊቶችን ሊያስወግዱ የሚችሉ ውጤታማ የሆኑ የአሰራር ስልቶች በቦታቸው መኖር አለባቸው፡፡ ሁሉም የተመዘገቡ የፖለቲካ ፓርቲዎች በአንድ ዓይነት የምርጫ መጫወቻ ሜዳ ላይ መጫወት እንዲችሉ እና አንድ ዓይነት ምህዳር እንዲኖራቸው በቂ የሆነ የማስፈጸሚያ ሀብት መኖር አለበት፡፡ የምርጫውን ግልጽነት እና ታማዕኒነትን ለማረጋገጥ በአጠቃላይ የምርጫ ክትትል የፖለቲካ ፓርቲዎች ተወካዮችን እና የግል ተወዳዳሪዎች ወኪሎችን ጨምሮ በቦታው ዝግጁ ሆነው መገኘት አለባቸው፡፡ ሰላማዊ የሆነ ምርጫ ለማካሄድ እንዲቻል በቂ የሆነ የሎጂስቲክስ፣ የሀብት እና የጸጥታ ዝግጅቶች ተሟልተው መገኘት አለባቸው፡፡

ምርጫ ለእኔ የሰብአዊ መብት ጉዳይ ነው፡ “ ኢፍትሀዊነትን ነቅሎ ለመጣል ድምጽ መስጠት እስከ አሁን ድረስ ከተቀየሱት ዘዴዎች ሁል ተወዳዳሪ ያልተገኘለት በጣም ጠንካራ የሆነ መሳሪያ ነው…“

ድምጽ መስጠት እና ምርጫዎችን ማካሄድ ለእኔ ሰብአዊ መብቶች ናቸው፡፡ ብዙውን ጊዜ ምርጫዎች የፓርቲ ፖለቲካ መገለጫዎች ናቸው፡፡ ነጻ እና ፍትሀዊ ምርጫ ባለበት ሀገር ድምጽ መስጠት መሰረታዊ የሰብአዊ መብትን ማካሄድ ማለት እንጅ እንዲሁ ላላፊ የፖለቲካ መብት ተብሎ የሚሰጥ የዘፈቀደ ድርጊት አይደለም፡፡ ለእኔ በኢትዮጵያ የትኛውም ግለሰብ ወይም ደግሞ ቡድን በስልጣን ላይ ኖረ አልኖረ ጉዳዬ አይደለም፡፡ የጎሳ፣ የኃይማኖት፣ አካባቢያዊ ወይም ሌላ ነገርም ቢሆን ለእኔ ያን ያህል የሚያሳስበኝ ጉዳይ አይደለም፡፡ ለእኔ እጅግ በጣም የሚያሳስበኝ እና የሚያንገበግበኝ፣ ጠንካራ ትችትም እንዳቀርብ ሌት ቀን የሚገፋፋኝ በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ የፖለቲካ መንበር ላይ እንደ ወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ያለ ሌላ የፖለቲካ ፓርቲ የሚቀመጥበት እና ተመሳሳዩን ዓይነት ዕኩይ እና ሰይጣናዊ ምግባሮችን የሚፈጽም ከሆነ ብቻ ነው፡፡ ስልጣናቸውን እና ኃይላቸውን ከህግ አግባብ ውጭ ለሚጠቀሙ እኩል የሆነ ትችት የምሰጥ እና ለሁሉም በማያወላውል መልኩ ዘብ የምቆም ጦረኛ ነኝ፡፡ በስልጣን ላሉት እና ኃይላቸውን እና ስላጣናቸውን ከህግ አግባብ ውጭ ለሚጠቀሙት ሁሉ እውነታውን እና አዕምሮዬ የሚያምንበትን ሁሉ እስከ አፍንጫቸው ድረስ እነግራቸዋለሁ፡፡ ቀደም ሲል እንዳልኩት ሁሉ የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ነጻ እና ፍትሀዊ ምርጫ የሚያካሂድ ከሆነ፣ ለህግ የበላይነት የሚገዛ ከሆነ እና ሰብአዊ መብቶችን የሚያከብር ከሆነ የመጀመሪያው ቁጥር 1 አድናቂያቸው እሆናለሁ፡፡ ምን ያደርጋል አይሞክሯትም እንጅ፡፡ ለእኔ በስልጣን ላይ ያለው ማን ነው የሚለው አይደለም ጉዳዬ የሚሆነው፣ ይልቁንም በስልጣን ላይ ያሉት በተሰጧቸው ስልጣኖቻቸው ምን አደረጉ ምንስ አላደረጉም የሚለው ነው ትርጉም የሚሰጠኝ እና በአንክሮ የምከታተለው፡፡ ማህተመ ጋንዲ እንዲህ በማለት አስተምረዋል፣ “ኃጢያቶኝችን ሳይሆን ኃጢአትን እንጥላ፡፡“

በመስኩ የማስተማር ልምድ ያለኝ እና የሲቪል መብቶች ህግ እንዲከበር ተግባራዊ የህገ መንግስት የህግ ባለሙያ እንደመሆኔ መጠን ስለምርጫዎች ድምጽ መስጠት እና ስለምርጫ ማካሄድ ጠቃሚነት አሳማኝ እና በቂ ግንዛቤ አለኝ፡፡ ገና በመጀመሪያዎቹ የአሜሪካ ቆይታዬ ጊዜ በደቡብ አሜሪካ የፖለቲካ ሳይንስ የመጀመሪያ ዲግሪዬን ለመቀበል ጥልቅ በሆነ መልኩ ሳጠና ነበር፡፡ ከዚህም በላይ ጥልቁን የደቡብ አሜሪካን የተለያዩ ቦታዎች ለበርካታ ጊዚያት በመጓዝ ለመጎብኘት እና ለማየት ዕድሉን አግኝቻለሁ፡፡ ምርጫዎች በሚካሄዱበት ጊዜ መሳተፍ እንዳይችሉ በህግ ተከልክለው ከሁለት ክፍለ ዘመናት በላይ የቆዩ ዕድለቢስ ህዝቦች እንደነበሩ የዓይን ምስክርነት እሰጣለሁ፡፡

እ.ኤ.አ በ1870 በ15ኛው የህገ መንግስት ማሻሻያ (13ኛው ማሻሻያ እ.ኤ.አ በ1865 የባሪያ ንግድን ሻረ፡፡ በዚያው ተመሳሳይ ዓመት የአሜሪካ የእርስ በእርስ ጦርነት ተጠናቀቀ፡፡) አፍሪካ- አሜሪካውያን/ት በምርጫ ድምጽ የመስጠት መብት እንዳላቸው ተደነገገ፡፡ እ.ኤ.አ በ1965 ድምጽ የመስጠት መብት እስከተረጋገጠበት ጊዜ ድረስ አፍሪካ-አሜሪካውያን/ት በምርጫ ወቅት በደቡብ አሜሪካ ድምጽ ለመስጠት መሞከር የህይወት ዋጋ የመክፈል ወይም ደግሞ አካለ ጎደሎ የመሆን አደጋን እንዲያስተናግዱ ይገደዱ ነበር፡፡ እ.ኤ.አ ከ1900 – 1965 በሉሲያኒያ፣ ሚሲሲፒ፣ አላባማ፣ ጆርጂያ፣ በደቡብ ካሮሊና እና በሌሎች ቦታዎችም ጭምር ድምጽ ለመስጠት ይፈልጉ የነበሩ አፍሪካ-አሜሪካውያን/ት ህገመንግስታዊ መብቶቻቸውን ለመጠቀም መሞከር ማለት እጅን አንበሳ መንጋጋ ውስጥ ከትቶ በሰላም እንደመመለስ ያህል ይቆጠር ነበር፡፡ ለመገምገሚያ የማንበብ እና መጻፍ ሙከራዎች (እ.ኤ.አ ከ1965 ጀምሮ ይሰጥ የነበረውን የአልባማን የማንበብ እና መጻፍ የሙከራ ፈተና ለመውሰድ እና የተገኘውን ውጤት ለማየት እዚህ ጋ ይጫኑ)፣ የምርጫ ጣቢያ ግብሮች (ድምጽ ለመስጠት መክፈል ግዴታ ነው) ወይም ደግሞ በአያቶቻቸው ስም ከክፍያ ነጻ ይሆኑ ነበር (አንድ ሰው ድምጽ ለመስጠት እ.ኤ.አ ከ1867 በፊት አባቱ ወይም አያቱ ድምጽ ይሰጡ ከነበረ፣ ከ1867 በፊት በደቡብ አሜሪካ አብዛኞቹ ዜጎች ባሮች ስለነበሩ ይህም ለነጮች ብቻ የሚሰራ ነበር) እና/ወይም የንብረት ባለቤትነትን ማረጋገጥ (ንብረት ያላቸው ብቻ ድምጽ መስጠት ይችሉ ነበር)፡፡ በደቡብ አሜሪካ የዴሞክራቲክ ፓርቲ እራሱን እንደ ክለብ መቁጠር ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ለሁሉም ቀደምት የነጭ ዜጋ ኗሪዎች የመምረጥ መብት ሲፈቀድ ሁሉም አፍሪካ-አሜሪካውያን/ት ዕጩዎቻቸውን እንዳይመርጡ ተከልክለው ነበር፡፡ አፍሪካ-አሜሪካውያን/ት ዕጩዎቻቸውን መምረጥ እንዳይችሉ ኃይልን የመጠቀም እና የመስፈራራት ድርጊቶች ይፈጸሙባቸው ነበር፡፡ የመጀመሪያ ዲግሪ ተማሪ በነበርኩበት ጊዜ እንደዚህ ዓይነቱ የማግለል ድርጊት ሰለባ የነበሩትን አፍሪካ-አሜሪካውያንን/ትን ዜጎች ለጥናቴ ቃለ መጠይቅ የማድረግ ዕድልን አግኝቸ ነበር፡፡ ድምጽ የመስጠት መብት አዋጅ ቃለ መጠይቁን ከማድረጌ ከአንድ ተኩል ደርዘን ዓመታት በፊት ነበር የታወጀው፡፡

በእኔ አስተያየት በዩናይትድ ስቴትስ ታሪክ ውስጥ በ20ኛው ክፍለ ዘመን ማህበራዊ ህግ ሆነው ከወጡት ሁለት ታላላቅ አዋጆች ውስጥ እ.ኤ.አ በ1964 የወጣው የሲቪል መብቶች አዋጅ/Civil Rights Act እና እ.ኤ.አ በ1965 የወጣው የመምረጥ መብት አዋጅ/Voting Rights Act ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡ ለፕሬዚዳንት ሊንደን ጆሀንሰን እና ለዶ/ር ማርቲን ሉተር ኪንግ እነዚህ አዋጆች አዋጅ ሆነው እንዲወጡ በማድረጋቸው ትልቅ እውቅና እሰጣለሁ፡፡ እነዚህ አንጸባራቂ የሆኑ ህጎች እንዲወጡ ዶ/ር ኪንግ በፕሬዚዳንት ሊንደን ላይ ከፍተኛ ግፊት ያደርጉ ነበር፡፡ እ.ኤ.አ ግንቦት 1957 ዶ/ር ኪንግ የመምረጥ መብት እጅግ በጣም ታላቅ ጠቀሜታ ያለው እና ይህም አዋጅ “አሁኑኑ መውጣት ያለበት አስቸኳይ ነገር” እንደሆነ አጽንኦ በመስጠት እንዲህ የሚል ጠንካራ ንግግር አሰምተው ነበር፣ “…ይህንን ቅዱስ የሆነ የሰው ልጆችን መብት መንፈግ [ድምጽ መስጠትን] ወደር ሊገኝለት የማይችል አሰቃቂ ክህደት በመፈጸም የዴሞክራሲያዊ ባህሎቻችን የማስፋፋት ዕቅዳችንን በማጨናገፍ እየገነባው ያለውን ዴሞክራሲ መልሶ ወደ መቀመቅ እንደማውረድ የሚቆጠርበት ሁኔታ እየተፈጠረ ነው፡፡ የመምረጥ መብቴን ጽናት ባለው መንገድ እና ያለምንም ጣልቃገብነት መጠቀም ካልቻልኩ በእኔ በእራሴ አካል ላይም የማዘዝ መብት የለኝም ማለት ነው፡፡ የእራሴን መጠቀሚያ አዕምሮ እኔው እራሴ ልፈጥረው አልችልም – ለእኔው መጠቀሚያ ይሆን ዘንድ በአምላክ አንድ ጊዜ ተፈጥሮልኛልና፡፡ ህግ ሆነው መውጣት የሚችሉ ጉዳዮች አዋጅ ሆነው እንዲወጡ ማገዝ እየቻልኩ ይህንን ሳላደርግ ዝም ብዬ የምቀመጥ ከሆነ እንደ ዴሞክራሲያዊ ዜጋ እየኖርኩ አይደለም – አዋጅ ሆነው እንዲወጡ ለሌሎች ስልጣኑ ላላቸው ሰዎች ማቅረብ መቻል አለብኝ፡፡ ስለሆነም በአሁኑ ጊዜ በጣም አጣዳፊው እና አስቸኳዩ ነገር የመምረጥ መብታችንን እንድንጎናጸፍ ለዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ ፕሬዚዳንት እና ለእያንዳንዱ የምክር ቤቱ/ኮንግረስ አባል ጥያቂያችንን ማቅረብ ነው፡፡ የምርጫ ካርዶችን ብቻ ስጡን እናም ስለመሰረታዊ መብቶቻችን እና ስለፌዴራል መንግስቱ የሚያሳስበን ጉዳይ አይኖርም…“

እ.ኤ.አ በ1965 ጆሀንሰን የመምረጥ መብት አዋጅን በማወጅ ለህዝብ አጎናጸፉ፡፡ ሆኖም ግን ታሪክ ለጆሀንሰን መልካም አልነበረም፡፡ ለሰሯቸው ሆነ ላልሰሯቸው፣ እንዲሁም ሊሰሯቸው ይገቡ በነበሩ እና ሊሰሯቸው እየቻሉ ላልሰሯቸው ስራዎች ሁሉ ትችቶችን ያዥጎደጉዱባቸው ጀመር፡፡ ስህተት ያለባቸው እና በርካታ ስህተቶችን የሰሩ ለመሆናቸው ምንም ዓይነት ጥርጣሬ የለኝም፡፡ (የእኔ አስተያየት ግን “ምንም ዓይነት ኃጢያት የለብኝም የሚል የመጀመሪያዋን ጠጠር እስቲ ወደ እኔ ይወርውር!“) ነው ነገሩ፡፡ ሆኖም ግን ጆሀንሰን የሲቪል መብቶች አዋጅን እና የመምረጥ መብት አዋጅ ስራዎችን በማውጣት ለሰሯቸው የጀግንነት ስራዎች ጥፋተኛ አላደርጋቸውም፡፡ እ.ኤ.አ ነሀሴ 6/1965 ጆሀንሰን የመምረጥ መብትን አዋጅ ስምምነት ከፈረሙ በኋላ እንዲህ የሚል ንግግር አሰምተው ነበር፣ “ኢፍትሀዊነትን ነቅሎ ለመጣል ድምጽ መስጠት እስከ አሁን ድረስ ከተቀየሱት ዘዴዎች ሁል ተወዳዳሪ ያልተገኘለት በጣም ጠንካራ የሆነ መሳሪያ ነው፡፡ እንደዚሁም ድምጽ መስጠት ሰዎች ከሌሎች ሰዎች የተለዩ በመሆናቸው ብቻ አስሮ እና ከልሎ እንደ ግድግዳ ሆኖ የያዛቸውን ችግር ያስወግዳል ምክንያቱም ከሌሎች ሰዎች የተለዩ በመሆናቸው ብቻ ነው፡፡“ የእርሳቸውን የስምምነት ፊርማ ንገግር ከማርቲን ሉተር ኪንግ (ማሉኪ) “እኔም ህልም አለኝ” ከሚለው ንግግራቸው ጋር ለማስቀመጥ እፈልጋለሁ፡፡

ሁልጊዜ የጆሀንሰንን ንግግሮች እና የማሉኪን “እኔም ህልም አለኝ” ባነበብኩ ቁጥር እንባዬ ይመጣል፡፡ አንድ ሰው ለሰራው መልካም ስራ ዕውቅና ሊሰጠው ይገባል፣ እናም ጀሀንሰንም ላበረከቷቸው መልካም ስራዎች ሙሉ እውቅና ሊሰጣቸው ይገባል፡፡ በእኔ አስተያየት ጆሀንሰን በ20ኛው ከፍለ ዘመን የዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ ታላቁ ፕሬዚዳንት ነበሩ! የአንድን ሰው ታላቅነት የምለካው ጥሎት ባለፈው መልካም ትሩፋቱ ነው፡፡ ምን ዓይነት ትሩፋት ነው ጆሀንሰን ጥለው ያለፉት!

የሲቪል መብቶች ታጋይ እና የምክር ቤት/ኮንግረስ አባል የነበሩት ታዋቂው ጆን ሌዊስ እ.ኤ.አ በ2012 በዴሞክራሲያዊ ብሄራዊ ጉባኤ/Democratice National Convention በመገኘት ሁለቱንም ማሉኪን እና ጆሀንሰንን በማሞካሸት እና በማወደስ እንዲህ የሚል ንግግር አሰምተው ነበር፣ “የእናንተ ድምጽ ወደ ቅዱስነት የተጠጋ እንቁ ነው፡፡ ጠንካራ ህብረትን ለመፍጠር እንድንችል እጅግ በጣም ጠንካራ እና ምንም ዓይነት ኃይል ያልተቀላቀለበት መሳሪያ ነው፣ ከቅርብ ጊዜ በፊት ህዝቦች በማይንቀሳቀሱ ሰልፎች ላይ ተሰልፈው ይታዩ ነበር፡፡ የማንበብ እና መጻፍ የሙከራ ፈተና እየተባለ የሚጠራውን የመገምገሚያ ፈተና ለመውሰድ ማለፍ ይጠበቅባቸዋል፣ እንደዚሁም ለምርጫ ጣቢያው ገንዘብ መክፈል አለባቸው፡፡ አንድ ጊዜ አንድ ሰው በአንድ ሳሙና ላይ ያሉትን የአረፋ ነጠብጣቦች በሙሉ እንዲቆጥር ሲጠየቅ ነበር፡፡ በሌላ ጊዜ ደግሞ አንድ ሌላ ሰው በመቀቀያ ቶፋ ውስጥ የነበሩትን የተቀቀሉ ባቄላዎች እንዲቆጥር ሲጠየቅ ነበር፡፡ እንግዲህ ይህ ሁሉ ግፍ የሚፈጸመው ሰዎቹ የድምጽ ካርዳቸውን ተጠቅመው መምረጥ እንዲችሉ ነው፡፡ “

ስለምርጫዎች እና ስለድምጽ አሰጣጥ ያሉኝ የእኔ አስተያየቶች የተባበሩት መንግስታት ዋና ጸሀፊ የነበሩት ጃቬር ፔሬዝ ኩያር እ.ኤ.አ በ1991 እንዲህ በማለት ባቀረቡት ዘገባቸው (A/46/609) ላይ ግልጽ በሆነ መልኩ ተቀምጧል፡

ምርጫዎች በእራሳቸው ዴሞክራሲን አያጎናጽፉም፡፡ መጨረሻዎችም አይደሉም ሆኖም ግን ህዝቦችን ወደ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለማሸጋገር በሚሄድበት መንገድ ላይ እና በታላላቆቹ ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት መሳሪያዎች በግልጽ እንደተቀመጡት አንድን ሀገር ለማስተዳደር ካለው መብት ጋር በጣም ጠቃሚዎች እና ሁልጊዜም አስፈላጊዎች ቢሆኑም እንኳ በሂደቱ ላይ እንደ አንድ እርምጃ የሚቆጠሩ ናቸው፡፡ ግቡን ከአካሄዱ ጋር ማምታት እና ዴሞክራሲ በየጊዜው ከሚሰጠው ድምጽ የበለጠ እንደሆና ማደናጋገር ተገቢ አይሆንም፡፡ ሆኖም ግን ዴሞክራሲ በተለይም ሁሉንም ሂደቶች ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ ድረስ የህዝቦችን የፖለቲካ ተሳትፎ ህይወት በሀገራቸው ላይ አካትቶ የሚይዝ ጉዳይ ነው፡፡

ለወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ለማስተላለፍ የምፈልገው መልዕክት ይኸው ነው፡፡ ምርጫዎች በእራሳቸው ዴሞክራሲን አያረጋግጡም፡፡ ምርጫዎች የዴሞክራሲ በዓላት አይደሉም ሆኖም ግን የዜጎችን ሉዓላዊ ፍላጎት ሊገልጹ የሚችሉ የተቀደሱ ክንውኖች ናቸው፡፡ በምርጫ ጊዜ ድምጽ መስጠት እንዲሁ እንደ ቀላል ነገር የድምጽ መስጫ ካርዶችን በምርጫ ሳጥን ኮሮጆ ውስጥ ማስገባት አይደለም፣ ሆኖም ግን የዜጎችን ሁለንተናዊ የፖለቲካ ተሳትፎ ህይወት በሚያረጋግጥ መልኩ ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ ድረስ ያለውን የምርጫ ሂደት ማለት ነው፡፡ በሌላ አባባል ድምጽ መስጠት እና ምርጫዎች የሰብአዊ መብቶች ጉዳዮች ናቸው!

የኢትዮጵያን ዝነኛ የጸደይ አብዮት የመከሰቻ ቀን መጠበቅ፣

በአሁኑ ጊዜ በሰሜን አሜሪካ የበጋው መካከለኛ ጊዜ የየካቲት ወር ነው፡፡ በኢትዮጵያም እንደዚሁ የበጋው ወቅት ነው፡፡ በሰሜን አሜሪካ በቀጣይነት የጸደይ ወቅት ይከተላል፡፡ በኢትዮጵያም እንደዚሁ የጸደይ ወቅት ይከተላል፡፡ ሁሉም የወቅቶች ለውጦች ሪቻርድ 3ኛ በሚል ርዕስ ከተደረሰው ከሸክስፒር የግጥም ስንኞች ውስጥ እንዲህ የሚሉትን ጥቂት መስመሮችን እንዳስታውስ አደረገኝ፡፡

የመከራው ወቅት አልፏል፣
ቆንጆው የክረምት ወቅት ይፏልላል፣
እያስገመገመ ይመጣል፣
እየደነፋ እየተጋፋ ይምዘገዘጋል፡፡

የመከፊያችን በጋ ወቅት ነው፣
በዮርክ ከተማ አንጸባራቂ ጸሀይ ነው፡፡
ደስታን አርቆ፣
ክፋትን ሰንቆ፣
መከራውን ጨምቆ፣
የመጣ እንደሆነ ሁሉንም ጠቅልሎ፣
በእብሪት የተሞላ ግፈኛ ነው ብሎ፣
በሸፍጥ የተካነ ዲያብሎስ ነው ብሎ፣
እኔ እሱን አያርገኝ፣
አምላክ አይፍጠረኝ፣
የእንሽርት ውኃ ያርገኝ፡፡

በቤቶቻችን ላይ ደመናው አንዣቧል፣
ወዠቦውን ሊያወርድ ድፍርስርሱ ወጥቷል፣
አማላጅም የለው ሁሉንም ያጠፋል፡፡

የቤቱ ፍርስራሽ የቆጥ የማገሩ፣
ከምድር ውስጥ ይገባል ከጥልቅ ከባህሩ
ከውቅያኖሱ ስር ይሆናል መቃብሩ፡፡

ከእራሴ የግጥም መድብሎች ጥቂት ስንኞቸን ብቻ እንደሚከተለው አቀርባለሁ፡፡

አዋጅ አዋጅ፣
የደበሎ ቅዳጅ!

የሰማ እንዲያሰማ፣
ያልሰማ እንዲሰማ!

ጨፍግጎን ቆይቷል የክረምቱ ወራት፣
ደስታን አርቆ ስቃይን በማብዛት፣
ፍቅርን አጥፍቶ ጥላቻን በመዝራት፣
ሰውነትን ቀስፎ አካልን በመጉዳት፡፡

ስለዚህ እሰየው በጋው በመምጣቱ፣
ጸሐይ መሃለቋን የምጥልበቱ፣
ቆፈናችን ሁሉ የሚፍታታበቱ፡፡

የኢትዮጵያችን ጸደይ የነጻነት ቀንዲል፣
ጨለማን አባሮ መብራት የሚተክል፣
ቆፈንን አጥፍቶ ሙቀትን የሚያክል፣
ፍርኃት አስወግዶ ወኔን የሚያቀብል፣
ሽንፈትን አባሮ የሚያበቃ ለድል፡፡

ስለዚህ ጨለማው ፍጹም ይገፈፋል፣
በጸደይ ብርሀን ለቀብር ይበቃል፣
በሸፍጠኛነቱ ስሙ ይነበባል፣
በሰይጣንነቱ ግብሩ ይታወሳል፣
ይህን ተገንዝቦ ታሪክ መዝግቦታል፡፡

የኢትዮጵያ ህዝቦች እ.ኤ.አ በ2015 ያሉበት አጠቃላይ የኑሮ ሁኔታ እ.ኤ.አ በ2010 ከነበሩበት የኑሮ ሁኔታ ካልተሻለ ወይም ደግሞ እ.ኤ.አ በ2005 ከነበሩበት የባሰ ከሆነ በ2015 የቅርጫ ምርጫ ዋነኛ ጥያቄ ሆኖ በመቅረብ አጥጋቢ ምላሽ የሚሰጥበት ሊሆን ይገባል፡፡ ካለፉት ዓመታት ጋር ሲነጻጸር 2015 በምንም መለኪያ ያልተሻለ ከሆነ መፍትሄው ዳይፐሩን መቀየር ብቻ ይሆናል፡፡ ከዚህም በላይ “ፖለቲከኞች እንደ ዳይፐሮች (የህፃናት ጽዳት መጠበቅያ ጨርኮች ናቸው፡፡) ሁለቱም በየጊዜው እና ለአንድ ዓይነት ምክንያት መቀየርን ይፈልጋሉ፡፡”

የሚያስገርም ነገር ነው ጎበዝ! ወይ ምስኪን ኢትዮጵያ አንድ ዓይነት የበሰበሰ ዳይፐር ለሌላ 5 ዓመታት በጠቅላላው ለ25 ዓመታት ትታጠቅ?

እንከን በእንከን ላይ ለተቆለለው የ2015 እንከን የለሽ የቅርጫ ምርጫ ድምጻቸውን እንዲሰጡ ለሁሉም ኢትዮጵያውያን/ት የቀረበ ጥሪ፣

ድምጽ ስጡ! እ.ኤ.አ በ2015 በሚካሄደው የቅርጫ ምርጫ አምባገነኖችን ከጨዋታ ውጭ አድርጓቸው!

ድምጽ ስጡ! በ2015 በኢትዮጵያ በአምባገነኖች ላይ ድልን እንቀዳጅ!

የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ እ.ኤ.አ በ2015 በሚካሄደው የቅርጫ ምርጫ አሸናፊ ሊሆን ይችላል ወይ ብሎ ጥያቄ ማቅረብ 13 ወራትን የጸሐይ ብርሀን በምታገኘው ሀገራችን ውስጥ ጸሐይ ከጠለቀች በኋላ ጨለማ ይተካል ወይ ብሎ እንደመጠየቅ ይቆጠራል፡፡ ሆኖም ግን አንጸባራቂዋ ጸሐይ እንደምርጊት የተጋገረውን ጨለማ ለመግፈፍ በጥዋት እንደ ጧፍ ታበራለች፡፡

ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!
የካቲት 10 ቀን 2007 ዓ.ም

Similar Posts

Leave a Reply