“አፍሪካ ተስፋ ይኖራታልን?”

ከፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማርያም 

ትርጉም በነጻነት ለሀገሬ

በአፍሪካ ተስፋችን ሊሟጠጥ ይችላልን?

Hope img


 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

እ.ኤ.አ ማርች 2004 ኒኮላስ ክሪስቶፍ የተባለው ለኒዮርክ ታይምስ መጽሔት መጣጥፍ የሚያቀርቡት ተዋቂ ጸሀፊ ስለአፍሪካ መጻኢ ዕድል ተስፋ በቆረጠ መልኩ እንዲህ ብለው ነበር፣ “አፍሪካ በቀውስ የምትታመስ አህጉር ነች፡፡ አፍሪካ ላለፉት አራት አስርት ዓመታት ከጊዜ ወደ ጊዜ ድህነት እየጨመረ የመጣባት፣ በእርስ በእርስ ጦርነት የምትታመስ፣ የዘር ማጥፋት ሰብአዊ ወንጀሎች የሚፈጸሙባት እና አስደንጋጭ የሆነ የሙስና ዘረፋ የሚካሄድባት ብቸኛዋ አህጉር ሆናለች፡፡ አፍሪካ ተስፋ ይኖራታልን?“ ክሪስቶፍ ስለቻድ የወደፊት ዕጣ ፈንታ በተለይም በዝያን ጊዜ “የአፍሪካ የወቅቱ ልብ ሰባሪ አገር“ ስለመሆኗ ጉዳይ እያሰላሰሉ የተሰማቸውን ጥልቅ ሀዘን ገልጸዋል፡፡

እ.ኤ.አ ማርች 2014 ከቻድ በስተደቡብ የወሰን ጠርዝ ላይ የምትገኘው የመካከለኛው አፍሪካ ሬፐብክ የዛሬ ልብ ሰባሪ አገር ሆናለች፡፡ የ2014ቷ የመካከለኛው አፍሪካ ሬፐብሊክ የ2004ቷን ቻድ ሆናለች፡፡ ባለፈው ዓመት የመካከለኛው አፍሪካ ሬፐብሊክ ህዝብ ለመናገር የሚዘገንን አስፈሪ የቅዠት መዓት ውስጥ ገብታለች፡፡ የተባበሩት መንግስታት ዋና ጸሀፊ ባንኪሙን በመካከለኛው አፍሪካ ሬፐብሊክ እየተካሄደ ባለው “የዘር-ኃይማኖታዊ የማጽዳት” ዕኩይ ድርጊት ላይ ልባቸው በሀዘን የተሰበረ መሆኑን በመግለጽ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የሚከተለውን መልዕክት አስተላልፈዋል፣ “የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ከ20 ዓመታት በፊት በሩዋንዳ ህዝብ ላይ የደረሰውን ዕልቂት በግዴለሽነት ከዳር ቆሞ ሲመለከት ነበር… እናም አሁን ደግሞ ለመካከለኛው አፍሪካ ሬፐብሊክ ህዝቦች ህይወት ደህንነት በቂ የሆነ ምንም ነገር ባለማድረግ በከፍተኛ አደጋ ውስጥ ወድቀን እንገኛለን…  የዘር-ኃይማኖት የማጽዳት ዘመቻ እውን በመሆን ላይ ይገኛል፡፡ አናሳዎቹ የሙስሊም ማህበረሰብ አባላት አገራቸውን ጥለው በመሰደድ ላይ ናቸው፡፡ እንዲህ ያለ ድርጊት ‘በፍጹም እንደገና አይደረግም’ እያልን እራሳችንን እያታለልን መቀጠል የለብንም፡፡ ይህንን አዘናጊ አባባል ብዙ ጊዜ ደግመን ደጋግመን ብለነዋል… በማለት ሀሳባቸውን አጠቃለዋል፡፡ ከመካከለኛው አፍሪካ ሬፐብሊክ ዋና ከተማ ከባንጉይ በ150 ማይል ርቀት ላይ በምትገኘው ያሎኬ በምትባል ከተማ ከአንድ ዓመት በፊት ወደ 30 ሺ የሚገመቱ የሙስሊም ማህበረሰብ አባላት በስምንት መስጊዶች አማካይነት እምነታቸውን እያራመዱ በሰላም እና በፍቅር ይኖሩ ነበር፡፡ ሆኖም ግን እንደ ሂዩማን ራይትስ ዎች እማኝነት ከሆነ በአሁኑ ጊዜ ከ500 ያነሱ የሙስሊም ማህበረሰብ አባላት እና አንድ መስጊድ ብቻ ቀርተዋል፡፡ ከዚህ የእርስ በእርስ እልቂት አንጻር ሲታይ ለመካከለኛው አፍሪካ ሬፐብሊክ ተስፋ ሊኖራት ይችላልን?

እ.ኤ.አ ማርች 2014 ከመካከለኛው አፍሪካ ሬፐብሊክ በስተምስራቅ የወሰን ጠርዝ ላይ የምትገኘው የዓለም አዲሲቷ አገር ደቡብ ሱዳን በጎሳ ቡድኖች የጦርነት እሳት ውስጥ ተማግዳ በመለብለብ ላይ ትገኛለች፡፡ ከአራት ወራት በፊት ፕሬዚዳንት ሳልቫኪር ምክትል ፕሬዚዳንት የነበሩትን ሪክ ማቻራ ከስልጣን በማባረር በሀገር ክህደት ወንጀል ክስ መመስረታቸውን ተከትሎ በደቡብ ሱዳን በተቆሰቆሰው የእርስ በእርስ ጦርነት በሺዎች ለሚቆጠሩ ንጹሀን ዜጎች ህይወት ህልፈት እና አንድ ሚሊዮን የሚሆኑት ደግሞ ለመፈናቀል የተዳረጉ ሲሆን ከእነዚህ ተፈናቃዮች ውስጥ አንድ አምስተኛ የሚሆኑት በጎረቤት አገር የመጠለያ ካምፖች ጥገኛ ሆነው ይገኛሉ፡፡ የተባበሩት መንግስታት የህጻናት መርጃ ድርጅት/ዩኒሴፍ ባወጣው ዘገባ መሰረት በጦርነቱ ምክንያት ከተፈናቀሉት ዜጎች ውስጥ 380,000 የሚሆኑት ህጻናት መሆናቸው ታውቋል፡፡

እ.ኤ.አ ኤፕሪል 2014 በተባበሩት መንግስት የደቡብ ሱዳን ተልዕኮ/UN Mission in South Sudan ባወጣው ዘገባ መሰረት በአገሪቱ ሰሜናዊ ክፍል በምትገኘው ቤንቱ በምትባል ቦታ የጸረ መንግስት ተዋጊው የማቻራ ኃይሎች ከመስጊዱ ውስጥ ጥሰው በመግባት ግለሰቦችን እና የጎሳ ቡድኖችን እየለዩ ለብቻ ካደረጉ በኋላ የእነርሱ ጎሳ አባላት ለሆኑት ዜጎች ጥበቃ በማድረግ የሌላ ጎሳ አባላት በሆኑት ዜጎች ላይ እልቂትን ፈጽመዋል፡፡ እንደቀረበው ዘገባ ከሆነ ከ200 በላይ ዜጎች ሙት እና ከ400 በላይ የሚሆኑት ደግሞ ቁስለኞች ሆነዋል፡፡ የደቡብ ሱዳን ነጻ አውጭ ግንባር ተቃዋሚ የሆኑ ወታደሮች ደግሞ በካቶሊክ ቤተክርስቲያን በጥገኝነት የተጠለሉ ዜጎችን የጎሳ ማንነት በመጠየቅ እየለዩ በመግደል ጥቃቱን ቀጥለውበታል፡፡” የተባበሩት መንግስታት የደቡብ ሱዳን ተልዕኮ በተጨማሪ ባወጣው ዘገባ መሰረት ጥቂት አማጺዎች የአካባቢ ሬዲዮ ማሰራጫዎችን በመጠቀም “የተወሰኑ የጎሳ አባላት ቤንቱ በምትባል ቦታ መቆየት የለባቸውም፣ እንዲያውም ከአንድ ጎሳ አካባቢ ወንዶችን በመጥራት በሌሎች ጎሳ አባላት ሴቶች ላይ የጥላቻ የአስገድዶ መድፈር ድርጊት እንዲፈጽሙባቸው የጥላቻ መልዕክቶችን በሬዲዮ ሲያስተላልፉ ነበር“ በማለት ዘገባውን አጠቃልሏል፡፡

እ.ኤ.አ በኤፕሪል 1994 እ.ኤ.አ በ1993 የሁቱ እና የቱትሲ ጎሳ አባላት በጋራ የጥምር መንግስት ለማቋቋም የተጀመረውን ጥረት ወደ ጎን በማለት እና አክራሪ የሁቱ ጎሳ አባላት ቀደም ሲል በሁለቱ የጎሳ አባላት መካከል ተደርጎ የነበረውን የተኩስ አቁም ስምምነት በመጣስ የቱትሲ ጎሳ አባላትን እነርሱ በረሮዎች እያሉ በሚጠሯቸው የቱትሲ የጎሳ አባላት ላይ እልቂት በመፈጸም “የመጨረሻውን ጦርነት” ወደ ተግባር አሸጋገሩት፡፡ አካዙ (የሁቱ ጎሳ አባላት የፖለቲካ አመራሮች እና ልሂቃን) እየተባሉ የሚጠሩት የጅምላ ዘር ፍጅቱ ከመጀመሩ ቢያንስ ከአንድ ዓመት በፊት የቱትሲ ጎሳ አባላት የሆኑትን ሩዋንዳውያን/ት ዜጎችን ለመፍጀት የታሰበበት ዕቅድ ነደፉ፡፡ የእራሳቸውን ሬዲዮ ጣቢያ (ኮሊንስ) አቋቋሙ፡፡ ግድያ እንዲፈጸምባቸው ያዘጋጇቸውን የቱትሲ ጎሳ አባላት ስም ዝርዝር የሚያነቡበት እና እነዚያን ዘግናኝ የዘር ፍጅት ወንጀሎች እንዲፈጽሙ ለሚታዘዙ ገዳይ ሚሊሻዎች (ኢንተርሀሞይ እና ኢምፑዛሙጋምቢ) የትዕዛዝ መልዕክቶች የሚተላለፉበት ነበር፡፡ በዚያ የዘር ማጥፋት ዕኩይ ምግባር ከአንድ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ሩዋንዳውያን/ት አልቀዋል፡፡  

ተስፋቢስ ለሆነችው አፍሪካ ተስፋ ይኖር ይሆን? በአፍሪካ ተጋኖ የሚወራለት ተስፋ ይሆን?

እ.ኤ.አ በ2007 ክሪስቶፍ አቅርበዋቸው ለነበሩት ጥያቄዎች በከፊል ምላሽ አግኝተዋል፡፡ ምናልባትም ወደፊት አፍሪካ ተስፋ ሊኖራት ይችላል፡፡ እንዲህ በማለትም ጽፈዋል፣ “የአፍሪካ አገሮች የተረጋጋ ሰላም እና ወደ ተግባር የሚሸጋገሩ ውጤታማ ፖሊሲዎች ሲያገኙ በአብዛኛው ጥሩ ይሰራሉ፣ በመልካም ሁኔታም ያድጋሉ፡፡ በእርግጥም እ.አ.አ ከ1960 እስከ 2001 ድረስ በዓለም ላይ በጣም ፈጣን እድገት ያስመዘገበችው አገር ቦትስዋና (ደቡብ ኮሪያ ሁለተኛ የነበረች ሲሆን ሲንጋፖር እና ቻይና በሶስተኛነት ደረጃ ላይ ተጣምረዋል፡፡)“  ለዚህ አባባላ ጥሩ ማሳያ ነው፡፡ የቦትስዋናን ሞዴልነት በመከተል በርካታ የውጭ መዋዕለ ንዋይ አፍሳሶችን በመሳብ እና ለነጻ ገበያ መርህ ተገዥ በመሆን የአፍሪካ አገሮች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥተቷል፡፡ እንደ ሩዋንዳ ሁሉ ሌሎች አገሮችም እንደ ሞዛምቢክ፣ ቤኒን፣ ታንዛኒያ፣ ላይቤሪያ እና ሞሪሽየስ በእርዳታ ላይ ጥገኛ ከመሆን ይልቅ በንግድ ላይ ትኩረት በማድረግ የወደፊት እድገታቸውን ለማሳካት ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛሉ፡፡”

የአፍሪካ መሪዎች እየተባሉ የሚጠሩት “ስለአፍሪካ ህዳሴ” አሰልች የሆነውን ዲስኩራቸውን ያሰማሉ፣ “የአፍሪካ ምዕተ ዓመት” በማለት ይለፍፋሉ፣ “የአፍሪካ ጸሐይ መውጣት” በማለት ይሰብካሉ፣ “የአፍሪካ መነሳሳት” እያሉ በመኮፈስ ከምዕራቡ ዓለም ለመለመን እና ከብዙሀን የዓለም አቀፍ የገንዘብ አበዳሪ ድርጅቶች ገንዘብ ለመጭመቅና እየመነተፉ በውጨ አገር ባሉ የባንክ ሂሳቦቻቸው ላይ ለማጨቅ ይተጋሉ፡፡ (“ስለአፍሪካ ህዳሴ”፣ ስለአፍሪካ መነሳሳት“ ወዘተ   “በማውራት እና እ.ኤ.አ ከ1946 ጀምሮ ተከታታይ ቅጾችን በመጻፍ የመጀመሪያ የነበሩት ተዋቂው (የፈረንሳይ) ሴኔጋላዊ ምሁር እና የአካዳሚክ ሰው ሸህ አንታ ዲዮብ ነበሩ፡፡ ሆኖም ግን የአሁኖቹ በሙስና የበከቱት የአፍሪካ መሪዎች የዲዮብን ሀሳቦች መኮረጃቸውን እንኳ አሳውቀው ለጸሐፊው ተገቢውን አክብሮት በመስጠት ለይስሙላም እንኳ ቢሆን ምስጋና በማቅረብ ከእርሳቸው የተዋሱ መሆናቸውን ሳይገልጹ እየዘረፉ በእራሳቸው አዕምሮ እንዳፈለቁት ያህል በማያፍረው አንደበታቸው ሌት ከቀን ሲለፈልፉ ይደመጣሉ፡፡) አንዳንድ የብዙሀን መገናኛ ዘዴዎች ትችት አቅራቢዎች እንደሚሉት በአሁኑ ጊዜ በእድገት ጎዳና ላይ እየመጡ ያሉት ብሪክ/BRIC እየተባሉ የሚጠሩት የኢኮኖሚ ኃይሎች ማለትም (ብራዚል፣ ራሽያ፣ ህንድ፣ እና ቻይና) የተባሉት አገሮች አፍሪካን በቅርቡ እንደሚቀበሏት እና አፍሪካም ከእነዚህ አገሮች ስብስብ ተርታ ውስጥ በመግባት ብሪክ/BRIC የሚለው አህጽእሮ ቃል ወደ ብሪካ/BRICA ይሸጋገራል በማለት ሀሳቦቻቸውን ይሰነዝራሉ፡፡

እ.ኤ.አ በ2008 አፍሪካ ተስፋ እንደሚኖራት ዘ ኢኮኖሚስት መጽሔት የሆነው እንዲህ የሚል የይስሙላ ሀተታ አስነብቧል፡፡ “የአፍሪካ የተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ አደጋዎች ቢኖሩም እንኳን በአሁኑ ጊዜ የሚታየው ዝንባሌ አወንታዊ ሁኔታን የሚሰጥ ነው“ በማለት ዘ ኢኮኖሚስት መጽሔት አስተያየቱን አስፍሯል፡፡ ሆኖም ግን እ.ኤ.አ በ2000 ዘ ኢኮኖሚስት በርዕሰ አንቀጹ ላይ “ተስፋ ቢስ የሆነችው አፍሪካ?” በሚል ባሰፈረው ጽሑፉ የተሰማውን ሀዘን ገልጿ፡፡ በመቀጠልም እንዲህ የሚል ጽሑፍ አስፍሮ እናገኛለን፣ “በዚሁ ዓመት ከጃንዋሪ ጀምሮ ሞዛምቢክ እና ማደጋስካር በጎርፍ ተጥለቅልቀዋል፣ ረኃብ በኢትዮጵያ ላይ እንደገና መከሰት ጀምሯል፣ ዙምባብዌ በጨካኝ ወሮበላ መንግስታዊ ሽፍትነት፣ እየተሰቃየች፣ በረኃብ እና በበሽታ ማቋረጫ በሌለው መልኩ እየሞተች ነው፡፡ የበለጠ በከፋ መልኩ ጦርነቶች ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምስራቅ እስከ ምዕራብ እስከ አሁን ድረስ መጠናቸውን እያሰፉ በመካሄድ ላይ ናቸው… እነዚህ ድርጊቶች ለአፍሪካ ብቻ የተተው አይደሉም- ጭካኔ፣ አምባገነናዊነት እና ሙስና በየትኛውም የዓለም ክፍል ይከሰታሉ፣ ሆኖም ግን የአፍሪካ ማህበረሰብ በባህላቸው በተደበቁ ምክንያቶች ለእነርሱ በተለየ መልኩ የሚከሰቱ እና ጉዳት የሚያመጡ መስለው ሊታዩ ይችላሉ፡፡“ እ.ኤ.አ በ2013 ዘ ኢኮኖሚስት መጽሔት አብዛኞቹ የአፍሪካ አገሮች ከአደጋ ውጭ ናቸው፣ ሆኖም ግን “የምዕራቡን ዓለም ስዕል በአፍሪካ ላይ መቀባት ፈልጋሉ” የሚል ጽሑፍ አስፍሯል፡፡ ጦርነት፣ ረኃብ እና አምባገነኖች ቀድመው በስለው የተገኙ መቅስፍቶች ናቸው፡፡ አፍሪካውያን/ት የቻይና እና የህንድ ህዝቦች እንዳደረጉት ሁሉ ዓላማዎቻቸውን ለማሳካት ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛሉ፡፡ አብዛኛውን ጊዜ የሚበላ ነገር በበቂ ሁኔታ አይገኝም፣ ጥራት ያለው ትምህርት ለሁሉም ዜጎች አይገኝም፣ ዜጎች በእየለቱ በሚደረጉት ኢፍትሀዊ አሰራሮች ተስፋ የመቁረጥ እና መሰደድን እንደ አማራጭ ይይዛሉ፡፡ ሆኖም ግን በርካታ አፍሪካውያን/ት ኃይልን ወይም ደግሞ ቀድሞ የመጣን አደጋ አይፈሩም የእነርሱ ልጆች የተሻለ እንደሚሰሩ ተስፋን ሰንቀዋልና…”2014 ለአፍሪካውያን/ት ተስፋ መሰነቅ የሚሟጠጥበት እና የአዲስ ተስፋ ማጣት ዘመን የሚጀመርበት ወቅት ይሆን?“

የአፍሪካ ተስፋቢስነት 2014

እ.ኤ.አ በማርች 2014 መገባደጃ አካባቢ “ለሱዳን ህዝበ ውሳኔ ለአፍሪካውያን/ት ደግሞ የሙት ፍታት“ በሚል ርዕስ በሱዳን ህዝበ ውሳኔ እና ስለምትመሰረተዋ ሱዳን ትችት አቅርቤ ነበር፡፡ በአፍሪካ በየትኛውም አገር ቢሆን ሊከሰቱ በሚችሉ የግዛት መገንጠሎች እና ባለው እውነታ ላይ ልቤ በጣም ያዝናል፡፡ በወቅቱ እንዲህ የሚል ስሜት ተሰምቶኝ ነበር፣ “ይህ ዕለት ለሱዳንያውያን/ት ከየትኛውም ጊዜ የበለጠ ጥሩ ዕለት ነው፡፡ ይህ ዕለት ለሱዳናውያን/ት ትልቅ የሀዘን ዕለት ነው፡፡ ለአፍሪካ የሙት ዓመት ነው፡፡“ አፍሪካውያን/ት በ1960ዎቹ ከቅኝ ግዛት ቀንበር ነጻ በወጡበት ጊዜ የወደፊት ዕጣ ፈንታቸው ብሩህ እና ገደብየለሽ ሆኖ ነበር የሚታያቸው፡፡ የነጻነት ታጋይ መሪዎች አስተሳሰብ በፓን አፍሪካኒዝም ቅኘት ያጠነጠነ እና የአፍሪካን ፖለቲካ እና አኪኖሚያዊ አንድነት ማጠናከር ነበር፡፡ በዲያስፖራው ዓለም ያሉትን አፍሪካውያን/ት ወገኖች መልሰው ወደ አፍሪካ አህጉራቸው በማምጣት “ዓለም አቀፋዊ የአፍሪካን ማህበረሰብ” በመመስረት አህጉራቸውን እንዲያሳድጉ ነበር ዓላማቸው፡፡ ፓን አፍሪካኒዝም ከአዲሱ ቅኝ ግዛት፣ ኢምፔሪያሊዝም፣ ዘረኝነት እና ከሌሎች የቅኝ ግዛት መጥፎ ገጽታዎች ጋር በመታገል ተነጥቀው የነበሩትን የአፍሪካን እሴቶች እና ባህሎች በማስመለስ እንደገና በአፍሪካ እንዲተከሉ እና እንዲለመልሙ ማስቻል ነበር፡፡ የፓን አፍሪካኒዝም ትልቁ እሴቱ ሁሉንም የአፍሪካ ህዝቦች አንድነት ማጠናከር ነበር፡፡

ከሁሉም በላይ የአፍሪካ ድህረ ነጻነት መስራች አባቶች ከቅኝ ግዛት ነጻ መውጣት ብቻ ሳይሆን በአፍሪካ አንድነት ራዕይ ላይ እምነት የነበራቸው ናቸው፡፡ እነዚህ መስራች አባቶች አህጉሩን ተብትበው ይዘው የሚገዳደሩትን ዘርፈ ብዙ ችግሮች በውል የተገነዘቡ እና በአፍሪካ አገሮች መካከል ትክክለኛ እና ፍጹም የሆነ ህብረት ለመፍጠር ያልተቋረጠ ጥረት ሲያደርጉ ነበር፡፡ የኢትዮጵያው ንጉስ ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ስላሴ፣ የጋናው ክዋሜ ንክሩማህ፣ የኬንያው ጆሞ ኬንያታ፣ የታንዛኒያው ጁሊየስ ኔሬሬ፣ የጊኒው አህመድ ሴኩ ቱሬ፣ የዛምቢያው ኬኔዝ ካውንዳ፣ የግብጹ ጋማል አብደል ናስር እና ሌሎችም የፓን አፍሪካ አራማጆች ነበሩ፡፡

እ.ኤ.አ ሜይ 25//1963 የአፍሪካ ድርጅት ቋሚ ጽ/ቤት በአዲስ አበባ በተመሰረተበት ወቅት ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ስላሴ እንዲህ የሚል ልብን የሚመስጥ ንግግር ለጉባኤው ታዳሚዎች አቅርበው ነበር፣ “ራዕያችን ነጻ የሆነች አፍሪካን ማየት ብቻ ሳይሆን አንድነቷ የተጠበቀ አፍሪካን ጭምር ነው…በእያንዳንዳችን ላይ ልዩነቶች እንዳሉን ሁላችንም እናውቃለን፡፡ አፍሪካውያን/ት የተለያዩ ባህሎች፣ ልዩ የሆኑ እሴቶች እና የተለያዩ ባህሪያት ያሏቸው ህዝቦች ናቸው፡፡ እንደዚሁም ደግሞ የተለያዩ ዝርያዎች፣ ኃይማኖቶች፣ ባህሎች፣ ልምዶች ባሏቸው የተለያዩ ጠንካራ ህዝቦች መካከል ልዩነቶችን የሚያመጡ ነገሮች አይደሉም፡፡ ታሪክ እንደሚያስምረን አንድነት ኃይል ነው፣ እናም ያሉንን ልዩነቶች በጥንቃቄ እና በማስተዋል በመያዝ በመከባበር እና በፍቅር ባለን አቅም ሁሉ አንድነታችንን በማጠናከር ለጋራ ዓላማ የአፍሪካዊ ወንድማማችነት እና አንድነት ጉዟችንን አጠናክርን እንቀጥላለን…“

በአሁኑ ጊዜ ፓን አፍሪካኒዝም የለም ሞቶ ተቀብሯል፡፡ ስለአፍሪካ አንድነት ሀሳብን ማራመድ የእየሱስ ክርስቶስን ጽዋ ከመጠየቅ የበለጠ አስቸጋሪ ነገር መሆኑ ተረጋግጧል፡፡ በአሁኑ ጊዜ የአፍሪካ አህጉር እጅግ በጣም ግዙፍ እና አደገኛ በሆነ የጎሳ ክፍፍል ቀውስ መውደቅ ምክንያት የአፍሪካ አንድነት የፖለቲካ መገነጣጠል ትረካ ሆኗል፡፡ የጎሳ ቡድናዊነት እና የብሄር ጎሰኝነት  አፍሪካን የሚጠርጉ “አዲሶቹ ፍልስፍናዎች” ናቸው፡፡ የአፍሪካ ወሮበላ ገዥዎች በስሜታዊነት በመነሳት በስልጣን ኮርቻ ላይ እንደ መዥገር ተጣብቀው ለመቆየት እና በሙስና እራሳቸውን እና ታማኝ ሎሌዎቻቸውን ለማበልጸግ የብሄር ጎሰኝነት ከበሮ በመደለቅ እና በመላ የአፍሪካ አህጉር የኃይማኖት የጥላቻ መለከት በመንፋት እኩይ ተግባራት ላይ ተሰማርተው ይገኛሉ፡፡ በአሁኑ ጊዜ በብዙ የአፍሪካ አገሮች “በዘር ማንነት“፣ “በዘር ጥራት“፣ “በጎጠኝነት“፣ በዘር ማጽዳት እና በዘር ትምክህት መኩራት ፋሽን እየሆነ መጥቷል፡፡ በኢትዮጵያ የጎሳ ፖለቲካ “የብሄር ፌዴሪያሊዝም” እየተባለ በሚጠራ በጥላቻ የተጠቀለለ መርዝ በማቅረብ የኢትዮጵያን ህዝብ በጎሳ እና በቋንቋ በመከፋፈል እራሳቸው “ክልል” (ክልክል) እያሉ በሚጠሩት ወይም ደግሞ በታወቀው የአፓርታይድ ዓይነት ባንቱስታንስ ወይም የዘር ጎጠኝነትን ስርዓት በመዘርጋት አገሪቱን የመሬት ገሀነም በማሳየት ላይ ይገኛሉ፡፡ ናይጀሪያ በአሁኑ ጊዜ “ዋና ኗሪዎች (ቋሚ)” እና “መጤዎች” (ወይም ሟቹ መለስ ዜናዊ አንደሚለው “ሰፋሪ”)  በሚል አገሪቱ የዴሞክራሲያዊ ጎዳና ተከትያለሁ ካለችበት እ.ኤ.አ ከ1999 ጀምሮ በታላቅ የጥላቻ ማጥ ውስጥ ሰምጣ በመንፈራገጥ ላይ ትገኛለች፡፡ በእራሳቸው አገር “የናይጀሪያ መጤዎች” እየተባሉ በሚደርስባቸው አድልኦ እና በተወሰደው የኃይል እርምጃ በአስር ሺዎች ለሚቆጠሩ ንጹሀን ዜጎች ህይወት ህልፈት ምክንያት ሆኗል፡፡ በአይቮሪ ኮስት “አይቮሪቴ“ እየተባሉ በሚጠሩት እና በእነርሱ ደጋፊዎች አማካይነት አገሪቱ ትክክለኛውን አይቮሪቴ የቀየጠ ሌላ ዘር ከውጭ እየመጣ ወደ አገር ውስጥ በነጻ እንዲገባ እየተፈቀደለት በመቆየቱ ምክንያት አገሪቱ ጥልቅ በሆነ ችግር ውስጥ ወድቃ እንደምትገኝ በመከራከር በመሞገት ላይ እና በሌሎች ዜጎች ላይ ጥቃት በመሰንዘር ላይ ይገኛሉ፡፡ በአሁኑ ጊዜ የጎሰኝነት እና የትምክህተኝነት ቀይ ፈረስ የአፍሪካን አህጉር ከላይ አስከ ታች ይፈነጭባታል፡፡

የተስፋ ማቆጥቆጥ እና የተስፋ ማጣት አባዜ በአፍሪካ፣

የአፍሪካ ዕጣ ፈንታ በተስፋ ማቆጥቆጥ እና በተስፋ ማጣት አባዜ ላይ የተንጠለጠለ ነውን? አፍሪካ ለወደፊቱ በእርስ በእርስ ጦርነት፣ በዘር ማጥፋት እና በሰው ልጆች ላይ በሚፈጸም ወንጀል ልትወገዝ ይገባታልን? የአፍሪካ ተስፋ በዓለም አቀፍ ድርጅቶች ብድር እና እርዳታ፣ ግዙፍ እዳ እና ጨካኝ የውጭ መዋዕለ ንዋይ አፍሳሽ ስግብግቦች ገመድ ላይ የተንጠለጠለ ነውን? አፍሪካ ለተቀረው ዓለም የልገሳ፣ የሩህሩህነት እና የሀዘን ቋሚ መገለጫ ሆና ለዘላለም መኖር ተፈርዶባታልን? አፍሪካ በተስፋ ባህር ውስጥ ተንሳፍፋለች ወይስ ደግሞ በተስፋ ማጣት ውቅያኖስ ውስጥ እየሰመጠች ትገኛለች? “ጨካኝነት፣ አምባገነናዊነት እና ሙስና በአፍሪካ ውስጥ በየትኛውም ቦታ ተንሰራፍተው የሚገኙ ቢሆንም የአፍሪካ ማህበረሰብ ባልታወቁ ምክንያቶች በባህሎቻቸው ድብቆች መሆን ምክንያት ለእነዚህ ዕኩይ ተግባራት የማይመቹ በቋፍ ላይ ያሉ ናቸው እየተባለ ስለአፍሪካ የሚነገረው ነገር እውነትነት ይኖረው ይሆን?“ በአፍሪካውያን/ት ልብ ውስጥ በጥልቀት የተደበቁ ባህሪያት፣ የአእምሯዊ ተጠይቃዊ አመክንዮ፣ የመንፈስ እና በአፍሪካውያን/ት ዘንድ የተለመደውን ትርኪ ምርኪ ትረካ ወደ ተሻለ ማራኪ ሁኔታ ለመቀየር እና ለሶስቱ ጣምራ የአፍሪካውያን/ት ጠላቶች ማለትም ለጨካኝነት፣ አምባገነናዊነት እና ሙስና ጥቃት ሰለባ የመሆን ዕጣ ፈንታ ይጠፋ ይሆን? አፍሪካ በዳንቴ “ሰይጣናዊ አስቂኝ የትወና መድረክ” ላይ ትሆን ይሆን? “እዚህ አፍሪካ ውስጥ የምትኖሩ ሁሉ ሁሉንም ተስፋ እርግፍ አድርጋችሁ ተውት” እንደተባለው፡፡

ወደ ተስፋ መንገድ፤

ኔልሰን ማንዴላ ወደ “ቆንጆዋ ደቡብ አፍሪካ” ለመድረስ ህዝቦቻቸው ሁለት መንገዶችን መከተል እንዳለባቸው አልመው ነበር፡፡ እነርሱም ደግነት እና ይቅር ባይነት ይባላሉ፡፡ ወደ ቆንጆዋ እውነት እና እርቀ ሰላም ወደሰፈነባት “ቆንጆዋ አፍሪካ” ከመደረሱ በፊት አፍሪካውያን/ት ከዋናው አውራ መንገድ፣ ከፍጥነት አውራ መንገድ እና ከተስፋ ነጻ መንገድ በፊት በመጀመሪያ በጠመዝማዛ እና ምልክት በሌላቸው እሾሃማ አስቸጋሪ እና ቆሻሻ መንገዶችን ማቋረጥ የግድ ይኖራል የሚል እምነት አለኝ፡፡ “ሁሉም መንገዶች ወደ ሮም ይመራሉ” ካልን ሶስት ቀጥተኛ ጎዳኖዎች አፍሪካውያንን/ትን ወደ “ቆንጆዋ የአፍሪካ” ልብ ይመራሉ፡፡ ጎዳኖዎቹን የህግ የበላይነት፣ የሰብአዊ መብት ጥበቃ እና ተጠያቂነት ብየ እጠራቸዋለሁ፡፡ ህዝቡን ከሙስና እና ኃይልን በመጠቀም እራሳቸውን “መሪዎች” ብለው ሰይመው በህዝብ ጫንቃ ላይ ተፈናጥጠው ከሚገኙ ወሮበላ ገዥዎች እራስን ለመከላከል የሚያስችለው የህግ የበላይነት መስፈን ነው፡፡ በሙስና የተዘፈቁ እና ወንጀለኛ የአፍሪካ ገዥዎች የህዝቦቻቸውን ሰብአዊ መብት ማክበር በሚጀምሩበት ጊዜ ጦርነቶች፣ የእርስ በእርስ ጥላቻ እና የዘር ማጥፋት እኩይ ምግባራት በአፍሪካ የውርደት ሞት ሞተው ግብአተ መሬታቸው ይፈጸማል፡፡ የአፍሪካ መሪዎች እና ተቋማት በነጻ እና በፍትሀዊ ምርጫ እንዲሁም ነጻ የፍትህ አካላት ሲያብቡ እና መሪዎቹ በህዝቡ ዘንድ ተጠያቂዎች ሲሆኑ መንግስታት ህዝቡን መፍራት እና ማክበር ይጀምራሉ፡፡

ተስፋ ማጣት ወይም ተስፋን መጠገን፣

አፍሪካ በዓለም ላይ የተንኮታኮተች የደቀቀች አህጉር በመሆኗ የንጉሱ ታዛዞችም ፈረሶችም ቢሰበሰቡ ሊጠግንዋት አይችሉም ይላሉ፡፡ እ.ኤ.አ በ1963 በአፍሪካ አንድነት ድርጅት የመመስረቻ ስነስርዓት ላይ ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ስላሴ እንዲህ የሚል ንግግር አሰምተው ነበር፣ “በአሁኑ ጊዜ አፍሪካ ከጨለማው የቅኝ አገዛዝ ነጻ እየወጣች ነው፡፡ የመከራ ዘመናችን አልፏል፡፡ አፍሪካ “ከጨለማው የቅኝ አገዛዝ” ነጻ እየወጣች ያለ ይመስላል ሆኖም ግን የእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ እና ሉለኝነት በአፍሪካ ላይ ጨለማውን ጥላቸውን አጥልተዋል፡፡ የአፍሪካ የመከራ ጊዜ አልፏልን? አፍሪካ በአሁኑ ጊዜ የምጽዓት ጊዜዋ ነውን? ደቡብ ሱዳንን፣ የመካከለኛው አፍሪካ ሬፐብሊክን፣ ሩዋንዳን፣ የዴሞክራቲክ ኮንጎ ሬፐብሊክን፣ ሴራሊዮንን፣ ላይቤሪያን፣ ማሊን፣ ቻድን፣ ሱዳንን፣ ሶማሊያን፣ ዙምባብዌን፣ ኢትዮጵያን…! እስቲ ተመልከቱ፡፡

እ.ኤ.አ በ1963 በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጉባኤ ባደረጉት ንግግር ላይ አጼ ኃይለ ስላሴ “ለአፍሪካ ተስፋ ይኖራልን?” ለሚለው ጥያቄ መልስ ሰጥተው ነበር፡፡ ያለው ጦርነት ብቻ ነው እናም ለአፍሪካ እና ለዓለም ተስፋ የለም… ”አንድ ጎሳ፣ ኃይማኖት፣ ቋንቋ፣ አካባቢ በሌላው ላይ የበላይነት የሆነበት እና ሌላው ደግሞ የበታች የሆነበት ስርዓት ለአንዴ እና ለመጨረሻ እንዲሁም ለዘለቄታው የሚተውበት ጊዜ እስካልመጣ ድረስ፣ እንዲሁም አንዱ የመጀመሪያ ደረጃ ዜግነት እና ሌላው ደግሞ የሁለተኛ ደረጃ ዜግነትን የሚይዝበት አገር እስካልቀረ ድረስ፣ አንድ ሰው በቆዳ ቀለሙ፣ (በጎሳ፣ በዘር፣ በኃይማኖት፣ በቋንቋ፣ በአካባቢ) መለያየቱ ከዓይን ቀለም የበለጠ ጠቃሚነት እስከሌለው ድረስ፣ የሰብአዊ መብቶች ጥበቃ ለሁሉም ዜጎች በእኩልነት እስካልተጠበቁ እና እስካልተረጋገጡ ድረስ፣ በዓለም ላይ የመጨረሻው ሰላም እና ዓለም አቀፋዊ ዜግነት እንዲሁም ዓለም አቀፋዊ ስብዕና እስካልተጠበቀ ድረስ እና የሰዎችን ስብዕና ማዋረዱን እስካልተተወ ድረስ የምንመኘውን ሰላም ማረጋገጥ አይቻልም… አለመቻቻል፣ እና ጥላቻ እንዲሁም ሆን ብሎ ጥቃት ማድረስ እና ሰብአዊነት በጎደለው መልኩ እራስ ወዳድነትን ማራመድ በመግባባት እና በመቻቻል እንዲሁም በመልካም ፍላጎት ላይ በተመሰረተ መተሳሰብ እስካልተተኩ ድረስ፣ ሁሉም አፍሪካውያን/ት ነጻ መሆናቸውን በማወጅ በአንድነት እስካልቆሙ ድረስ፣ በመንግስተ ሰማያት አንድ የሆኑት ሰዎች በምድራዊው ዓለምም አንድ መሆናቸው እስካልተረጋገጠ ድረስ፣ የአፍሪካ አህጉር ሰላምን እስካላወቀ (ወይም ተስፋ) እስካላደረገ ድረስ የሰላም አለመኖር እንደተጠበቀ ይቀጥላል…“

እንግዲህ በእንደዚህ ያለ ነብያዊ የሆነ ንግግር በመታጀብ ነበር ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ስላሴ ያለማንም ዕገዛ በዓለም ላይ የመጀመሪያ የሆነውን አህጉራዊ ድርጅት እና ለአፍሪካውያን/ት እድገት እና እኩልነት ሊያሰፍን የሚችል ድርጅት ለመመስረት የቻሉት፡፡ በአሁኑ ጊዜ አስገራሚ እና አዋራጅ ሆኖ የሚታየው ነገር በጊዚያቸው አፍሪካ እና ከዓለም መሪዎች መካከል አንዱ እና ታላቅ የነበሩት የቀዳማዊ አጼ ኃይለ ስላሴ ሀውልት እራሳቸው ሌት ከቀን ጥረው ግረው ባሰሩት የድርጅቱ ጽ/ቤት በአፍሪካ ህብረት ቅጥር ግቢ ውስጥ ከሌሎች በተለየ መልኩ በኢትዮጵያ የእርሳቸው የመታሰቢያ ሀውልት እንዳይገነባ በአትዮጵያ ያለው ገዥ አካል ትዕዛዝ በመስጠት ጠንካራ ተቃውሞ በማሰማት እንዲያውም የእርሳቸውን ክብር የሚዘክር ማናቸውም ዓይነት ምልክት በህብረቱ ጽ/ቤት እንዳይታይ ገዥው አካል ሽንጡን ገትሮ ተከራክሯል፣ ዕኩይ ተግባሩ ለጊዜውም ቢሆን ተሳክቶለታል፡፡ እውነት ግን የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር ተቀብራ እንደማትቀር ታሪክ አስተምሮናል፣ ታሪክም ለእውነተኛ ባለታሪኮቹ ትሆናለች በማለት፡፡

“ለአፍሪካ ተስፋ ይኖራልን?” ለሚለው ጥያቄ መልሴ ቀላል እና አዎንታዊ ነው፡፡ አፍሪካ ህልቆ መሳፍርት በሌላቸው ተስፋዎች የታደለች ናት እናም ወጣቶቿ የአፍሪካ ተስፋዎች የማይነጥፉ ምንጮች ናቸው፡፡ ከዚህ ቀደም ባቀረብኩት ጽሁፍ መሰረት አፍሪካ የማድረግ እችላለሁ እና አልችልም አህጉር ናት፡፡ አፍሪካ የአቦሸማኔዎች (የተጽዕኖ ፈጣሪ ወጣቶች ትውልድ) እና የጉማሬ (ከወጣቶች ጎን ሆኖ እንቅስቃሴዎቻቸውን የሚያበረታታ የቅድሞው ትውልድ) አህጉር ናት፣ ጆርጅ አይቴይ በተደጋጋሚ እንደሚሉት፡፡ አቦሸማኔው ትውልድ በተስፋ የተሞላ ነው፡፡ የጉማሬው ትውልድ ተስፋ በቆረጠ መልክ ነው ትግሉን የሚያካሂደው፡፡ “የጉማሬው ትውልድ” አመራሮች እና ልሂቃን ቀድሞ እንደነበረው ሁሉ ከአፍሪካ ነጻነት በኋላም “ለሞራል ስብዕና የማይገዙ፣ በሞራል ዝቅጠት የሚዳክሩ፣ በስሜታዊነት የሚነዱ እና በሙስና የበከቱ“ የትውልድ አባላት ናቸው፡፡ “የእነርሱ ስግብግብነት እና አርቆ ማሰብ ያለመቻል ድሁር አቅማቸው የድህረ ቅኝ ግዛት አፍሪካን ዕጣ ፈንታ ለበርካታ አስርት ዓመታት አበላሽቷል፡፡“ በሌላ በኩል ደግሞ “የዛሬው የአቦሸማኔው ትውልድ በእንቅስቃሴ ላይ ነው፣ እናም አህጉራቸውን እንደገና ጠበቅ አድርገው በመያዝ እና በመቆጣጠር የአፍሪካን ህዝብ ለማህበረ ኢኮኖሚያዊ መሻሻል ለማብቃት ሌት ከቀን ጠንክረው በመስራት ላይ ይገኛሉ፣“ በማለት ጆርጅ አይቴይ ሀሳባቸውን ቋጭተዋል፡፡ የአፍሪካ ተስፋ በወሮበል ገዥዎች ወይም ደግሞ በጥቅም በተሳሰሩ በህዝብ ሀብት የደለቡ ከበርቴዎችን አንገቶች ለማስዋብ በተገነቡ በሚያንጸባርቁ የሙስና ህንጻ መስታወቶች ውስጥ የሚንጸባረቅ አይደለም፡፡

“ለአፍሪካ ተስፋ ይኖራልን?” ለሚለው ጥያቄ መልስ ለሚፈልጉ ሁሉ በአፍሪካ ወጣቶች ዓይን ውስጥ ፈልጉት፣ አእምሯቸውን መርምሩ እናም እነዚህን በተስፋ የተሞሉ ወጣቶች ከልብ አዳምጧቸው እላቸዋለሁ፡፡ ወጣቶቹ የአፍሪካ ብቸኛ ተስፋዎች ናቸው፡፡ በእነዚህ ወጣቶች ክንፎች ህልም ነው አፍሪካ በአንድ ወቅት ከጎሳ ክፍፍል፣ ከኃይማኖት ልዩነቶች እና ከቋንቋ መደነባበሮች ነጻ ሆና ልትበር የምትችለው፡፡ ስለሆነም የገጣሚ ላንግስተን ሁህ ቃላትን በመዋስ እንዲህ እላለሁ፣ “የአፍሪካ ተስፋዎች“ “ህልሞቻችሁን ጠበቅ አድርጋችሁ ያዙ፣ ህልሞች የሚሞቱ ከሆነ ህይወት ክንፏ የተሰበረች ወፍ ማለት ናት፣ በምንም ዓይነት መልኩ ልትበር አትችልም፡፡“ ወይም ለመክነፍ አትችልም!

የአፍሪካ ወጣቶች የነገይቱን “ቆንጆዋን አፍሪካ”  የሚያልሙ ከሆነ እኔ ደግሞ በደስታ በመፈንጠዝ ለጉዳዩ ታላቅ ዋጋ በመስጠት የቀን ህልሜን አልማለሁ፡፡ ሳልም የሚታየኝ አንድ ቀን ደናቁርት የአፍሪካ ገዥዎች ምሁር እና አዋቂ ሲሆኑ የቀን ህልም አልማለሁ፣ የሰው የበላይነት አንድ ቀን በህግ የበላይነት እንዲተካ የቀን ህልም አልማለሁ፣ በአፍሪካ የብዙሀን ፓርቲ ምርጫ አንድ ቀን የአንድ ፓርቲ አምባገነናዊነት የደናቁርት ስርዓትን ይተካል የሚል ህልም አልማለሁ፣ ግልጽነት እና ተጠያቂነት አንድ ቀን ሙስናን ከአፍሪካ ምድር ያስወግዳልየሚል ህልም አልማለሁ፣ በአፍሪካ ስልታዊ የፖለቲካ ጉዳትን እና ህገወጥ የፖለቲካ ጨዋታ ማራማድ አንድ ቀን በብዙሀን ብሄሮች እና በኃይማኖት ቡድኖች እንዲሁም በኃይማኖታዊ ተባባሪነት ይሸጋገራሉየሚል ህልም አልማለሁ፣ አምባገነናዊነት አንድ ቀን በተከበሩ የአፍሪካ የፖለቲካ ሰዎች ጥረት ወደ ታሪክ ቆሻሻ ማጠራቀሚያ ይወረወራል የሚል ህልም አልማለሁ፡፡

አንድ ቀን የአፍሪካ ህብረት ትክክለኛውን የተቋቋመበትን ዓላማ ትርጉም ሊያሳካ እንደሚችል እና “የአፍሪካ ቻርተር የሰዎች እና የህዝቦች መብቶች እና ሌሎችን ጠቃሚ የሰብአዊ መብት ጥበቃ መሳሪያዎችን“ እንደሚጠቀም እና ለተግባራዊነታቸውም ጠንክሮ እንደሚሰራ ህልም አለኝ፡፡ የቀን ህልም አለኝ፣ እንደ ፓን አፍሪካን ፓርላሜንት፣ የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊ እና የባህል ካውንስል፣ የሰላም እና የደህንነት ካውንስል፣ አዲሱ የአፍሪካ የኢኮኖሚ ልማት ትብብር እና የአፍሪካ የእርስ በእርስ መገማገሚያ መድረክ ከብዙዎች ጥቂቶቹ እርባና ቢስ ድርጅቶች አንድ ቀን በታምር የአፍሪካን ህዝቦች በትክክል ለማገልገል ወደሚችሉ ጠቃሚነት ያላቸው ድርጅቶችነት ይሸጋገራሉ የሚል ህልም አልማለሁ፡፡ የአፍሪካ ፍርድ ቤት የሰዎች እና የህዝቦች መብቶች ተከብረው ትክክለኛ ፍትህ በማግኘት አንድ ቀን እውን ሆነው ይታያሉ የሚል ህልም አልማለሁ፡፡

ከሁሉም በላይ ደግሞ አንድ ቀን የአፍሪካ መንግስታት ስህተቶች በሰብአዊ መብቶች መከበር ማካካሻ እንደሚሆኑ እና የአፍሪካ መንግስታትም የእራሳቸውን ህዝቦች እንደሚፈሩ እና እንደሚያከብሩ እንዲሁም የአፍሪካ ህዝቦች መንግስቶቻቸውን መፍራታቸውን ለዘላለሙ ከአእምሯቸው እንደሚያስውግዱ ህልም አለኝ፡፡ እንደዚህ ዓይነቶቹ የቀን ህልሞች ለተምኔታዊዎቹ ኢትዮጵያ እና አፍሪካ የሚሆኑ ናቸው፡፡

ተስፋ የሚሰራው ተስፋ ላላቸው እንጅ ለተስቢሶች አይደለም፡፡ ጄ.አር.አር ቶልኪን እንዲህ ብለዋል፣ “ተስፋቢስነት ከምንም አጠራጣሪነት በላይ በመተማመን መጨረሻውን ማየት ለሚችሉት ብቻ ነው፡፡ እኛ ይህንን አናደርገውም፡፡“

ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!

ሚያዝያ 21 ቀን 2006 .

 

Similar Posts

Leave a Reply