በኢትዮጵያ የማዕድን ሙስናን ለመሸፋፈን የሚደረገው ዘበት

ከፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማርያም

ትርጉም በነጻነት ለሀገሬ

በኢትዮጵያ ያለው ገዥው አካል በማዕድኑ ዘርፍ የሚያካሂደውን ሙስና በማደብዘዝ እና በመሸፋፈን ንጹህ መስሎ ለመታየት እና ዓለም አቀፋዊ ተቀባይነትን ለማግኘት በማሰብ በአምራች ኢንዱስትሪዎች የግልጽነት ተነሳሽነት(Extractive Industries Transparency Initiative (EITI)) ለተባለው ድርጅት ዕጩ አባል ለመሆን እንደገና ለሁለተኛ ጊዜ ይፍጨረጨራል፡፡ የገቢ ምልከታ ተቋም/Revenue Observation Institute የቦርድ ሊቀመንበር እና የአምራች ኢንዱስትሪዎች የግልጽነት ተነሳሽነት/EITI የቦርድ አባል የሆኑት አንቶኒ ሪቸር እንደሚሉት ከሆነ እ.ኤ.አ በ2010 ኢትዮጵያ የአምራች ኢንዱስትሪዎች የግልጽነት ተነሳሽነት/EITI አባል ለመሆን ያቀረበችው ጥያቄ ውድቅ ተደርጎ ነበር፣ ምክንያቱም የኢትዮጵያ ‘የበጎ አድራጎት እና ማህበራት ድርጅት አዋጅ (Proclamation on Charities and Societies) የሲቪክ ህዝብ ማህበራት ቡድኖች ሙሉ በሙሉ ነጻ ሆነው እና በሂደቱም ላይ ትርጉም ያለው ተሳትፎ እንዳያደርጉ የሚከለክል ደንቃራ በመሆኑ ነው የሚል ድምዳሜ ሰጥቷል፡፡ ቦርዱ ‘የበጎ አድራጎት እና ማህበራት ድርጅት አዋጅ’ በስራ ላይ እንዳይውል ኢትዮጵያ ‘እስካልሰረዘች ድረስ የዓለም አቀፉ ድርጅት አባል እንድትሆን በተጨባጭ እንደማይፈቅድ ውሳኔ አስተላልፏል’፡፡ አንድ አገር ለአባልነት ጥያቄ አቅርቦ ውድቅ ሲደረግበት በአምራች ኢንዱስትሪዎች የግልጽነት ተነሳሽነት/EITI ታሪክ የመጀመሪያው ብቸኛው ድርጊት መሆኑ እና እንዲሁም ደግሞ ለዚህ እርምጃ  መሰረት ሆኖ የቀረበው በግልጽ ከሰብአዊ መብት ጥሰት ጋር የተያያዘ መሆኑ ነበር፡፡

የአምራች ኢንዱስትሪዎች የግልጽነት ተነሳሽነት/EITI “የመንግስታት፣ የኩባንያዎች፣ የሲቪል ማህበረሰብ፣ የመዋዕለ ንዋይ አፍሳሾች እና የዓለም አቀፋዊ ድርጅቶች ጥምረት“ ሲሆን ይህም “በጠንካራ ሆኖም ግን ለለውጥ ክፍት የሆኑ የኩባንያዎች ክፍያ እና ከተፈጥሮ ዘይት፣ ጋስ እና ከማዕድን የሚገኙ የመንግስት ገቢዎች በሰነድነት የሚታተሙበት እና የሚከሰቱ ውስንነቶች የሚቀነሱበት የአሰራር ሂደት“ የሚተገብር ዓለም አቀፋዊ ድርጅት ነው፡፡ በግልጽ ለማስቀመጥ፣ የአምራች ኢንዱስትሪዎች የግልጽነት ተነሳሽነት/EITI ተጠያቂነትን እና ግልጽነትን ለማሳደግ በአባል አገራት የሚገኙ ኩባንያዎች እና መንግስታት በአምራች ማአድን ኢንዱስትሪዎቻቸው የሚገኙትን ገቢዎች በግልጽ ለማሳወቅ ዓላማን ያደረገ ዓለም አቀፋዊ ተቋም ነው፡፡ የአምራች ኢንዱስትሪዎች የግልጽነት ተነሳሽነት/EITI “የገቢን ግልጸኝነት በአካባቢ ደረጃ መስፈርት በማውጣት “ እንዲተገበር በማደረግ በስፋት ይታወቃል፡፡

በአትዮጵያ ያለው ገዥው አካል፣ የአምራች ኢንዱስትሪዎች የግልጽነት ተነሳሽነት/EITI የተባለው ዓለም አቀፍ ድርጅት አባል መሆንን ይፈልጋል፡፡ አባል ለመሆን የሚፈልገው ግን በማዕድኑ ዘርፍ በእውነተኛነት ላይ የተመሰረተ ግልጽነት እና ተጠያቂነት ያለው አሰራር ለማስፈን አይደለም፡፡ ሆኖም ግን እውነተኛው ዓላማው በሙስና የተዘፈቀውን የማዕድን ዘርፍ ለውጭ መዋዕለ ንዋይ አፍሳሾች ገበያ ለማቅረብ እንዲመቸው የእውነተኛነት መታወቂያ እና ለመልካም አስተዳደር እና ለጥሩ ገበያ መለመድ ከአምራች ኢንዱስትሪዎች የግልጽነት ተነሳሽነት/EITI ፈቃድ እና በገዥው አካል የአባልነት ጥያቄውን ለአምራች ኢንዱስትሪዎች የግልጽነት ተነሳሽነት/EITI ያቀረበው ከተቋሙ የእወቅና ድጋፍ በማግኘት የወደፊት ዓለም አቀፍ የመዋለ ንዋይ አፍሳሾችን እና የገንዘብ ተቋማትን በአገሪቱ መልካም አስተዳደር እንዳለ እና ደህንነት እንዲሰማቸው ለማስመሰል ታማኝነት በጎደለው መልክ የማታለል ዘዴ በመጠቀም ገዥው አካል ከፍተኛ ለሆነ ግልጽነት እና በእርግጥም ተጠያቂነት ለማስፈን ተግባራዊ እንቅስቃሴ ያደረገ መሆኑን እንዲያምኑ ለማድረግ ነው፡፡ ይህ ሁኔታ የአምራች ኢንዱስትሪዎች የግልጽነት ተነሳሽነት/EITIን ለማታለል ድፍረት የተሞላበት ንቀት፣ ስልታዊ የድርጊት መርሀ ግብር እና በሀሰት ላይ በተመሰረተ መልኩ በአገሪቱ ውስጥ የፖለቲካ መረጋጋት እንዳለ በማስመሰል እና በማዕድኑ ዘርፍ አስተማማኝ የሆነ ደህንነት መኖሩን እንዲጠብቁ በማድረግ መዋዕለ ንዋይ አፍሳሾች ያልጠረጠሩትን ነገር በላያቸው ላይ ለመጫን ነው፡፡

እውነታው ግን ገዥው አካል ለእራሱ ዜጎች የግል ንብረት ወይም መዋዕለ ንዋያቸውን በአገር ውስጥ ለሚፈያስሱ ባለሀብቶች ንብረት ዋስትና የሌለው እና አጠቃላይ በሆነ መልኩ ሲታይ ግን በተቃራኒው ምቹ ያልሆነ ከባቢያዊ የንግድ ስርዓት ሁኔታ ዘርግቶ የሚገኝ ነው፡፡ እ.ኤ.አ በ2014 ኮፋክ/COFACE የተባለው ዓለም አቀፋዊ ድርጅት ባቀረበው ዘገባ መሰረት በዓለም አቀፍ ደረጃ በአገሮች መካከል የሚሰጥ የኢንሹራንስ ብድር እና የብድር አገልግሎት አስተዳደር ኢትዮጵያ ያለችበትን ሁኔታ እንዲህ በማለት ድምዳሜ ሰጥቷል፣ “አስቸጋሪ የንግድ ከባቢያዊ ሁኔታ በተንሰራፋበት፣ የማህበራዊ ዘርፍ መረጃ እጥረት ባለበት ሁኔታ፣ ሙስና እና የግል ዘርፉን በማስገደድ ከውድድር ውጭ ማስወጣት“ እንደ መርህ በተያዘበት ሁኔታ ልማት እንደማይታሰብ ይፋ አድርጓል፡፡

የኢትዮጵያ የማዕድን ዘርፍሙስናን ማዕከልያደረገ ነው፣ 

በኢትዮጵያ ያለው የማዕድን ዘርፍ የሙስና ማዕከል እና የተግባር መገለጫ እንዲሁም የባለስልጣኖች የሙስና ድርጊት እና የማታለል ወንጀል ማሳያ ነው፡፡ እ.ኤ.አ በ2012 የዓለም ባንክ “በኢትዮጵያ ሙስናን መመርመር“ በሚል ርዕስ ባቀረበው መጠነ ሰፊ ሪፖርት መሰረት በኢትዮጵያ በሙስና ተተብትበው ከተያዙ የኢኮኖሚ ዘርፎች መካከል የማዕድኑ ዘርፍ አንዱ መሆኑን አረጋግጧል፡፡

የዓለም ባንክ “በኢትዮጵያ የማዕድን ዘርፍ” ውስጥ “ሰባት ዓይነት የሙስና አደጋዎችን” ነቅሶ ያወጣ ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ “ሶስቱ ዋነኛ አደጋዎች” ተብለው የቀረቡት “ፈቃድ በማውጣት፤ በፈቃድ አያያዝ ላይ በሚደረጉ ስምምነቶች እና በማዕድን ገቢዎች ላይ” የሚደረገው ሙስና ነው፡፡“ ሌላው አሳሳቢው የሙስና ዓይነት “ከካሳ ክፍያዎችና ከአካባቢ ነዋሪዎች ግዴታ፤ ኮንትራክተሮችና አምራቾች ከማዕድን ካምፓኒዎች ጋር ከሚያደርጓቸው የስምምነት ውሎች፤ ከካምፓኒዎች ምርቶች ጥራት መዝቀጥ እና የማዕድን ምርቶችንና መሳሪያዎችን ከመዝረፍ“ አንጻር የሚደረጉ የሙስና ዓይነቶች ናቸው፡፡

የዓለም ባንክ በግልጽ እንዳስቀመጠው “ፈቃድ በማውጣት ሂደት ጊዜ”  “ባለስልጣኖች ፈቃድ ለማውጣትና ለመስጠት፤ ፈቃድ በቶሎ አውጥቶ ለመስጠት ወይም ደግሞ ብዙ ጉዳት የማያመጡ የፈቃድ ሁኔታዎችን ለመስጠት ከማዕድን ካምፓኒዎች ህጋዊ ባልሆነ መንገድ ገንዘብ ይወስዳሉ ወይም ጉቦ ይቀበላሉ፡፡ ሌላው ተመሳሳይ አደጋ ባለስልጣኖች ፈቃድ በሚሰጡበት ወቅት ፈቃድ ከሚሰጡት ካምፓኒ ጋር በስውር  ለእራሳቸው ድርሻ እንዲኖራቸው ስምምነት ያደርጋሉ፤ ፈቃድ ለመስጠት የመሬት ባለቤትነትን ሊያገኙ ይችላሉ፤ የተወሰነ ድርሻ በአክሲዮን መልክ ወይም ከትርፍ የተወሰነ ድርሻን ይጠይቃሉ፤ ለእራሳቸው ወይም ለጓደኞቻቸው ቅድሚያ ምዝገባ እንዲያደርጉላቸው ከፈቃድ አውጭዎች ጋር ይሞዳሞዳሉ፡፡” በፈቃድ ስምምነት አያያዝ ጊዜ የማዕድን ካምፓኒ ባለቤቶች ሆን ብለው የማዕድን ስምምነቶችን (ለምሳሌ ያህል የአካባቢ፤ የጤና እና የደህንነት ህጎችን እንዲሁም በአካባቢው የማዕድን ካምፓኒው በኃላፊነት የመጠየቅ ደረጃና ሁኔታን ያካትታል)  በስራ እንዳይውሉ ያጨናግፋሉ፡፡

በማዕድን ገቢ አሰባሰብ ጊዜ የማዕድን ካምፓኒ ባለቤቶች ለመሬት መጠቀሚያና ለታክስ የሚያደርጓቸውን ወጭዎች ለመቀነስ ሲባል ሆን ብለው ያመረቱትን ምርት መጠንና ትርፋቸውን በማሳነስ ወጭዎችን ከፍ ያደርጋሉ፡፡ ገዥው አሰተዳደር ከማዕድን  ካምፓኒዎች የሚገኘውን ገቢ በትክክል ለማወቅ ነጻ የሆነ የማረጋገጫ አካል የለውም፡፡ ለመሬት መጠቀሚያና የገቢ ግብር መጠን በአጠቃላይ የሚወሰነው የማዕድን ካምፓኒዎች በአመኑት የምርት መጠንና ትርፍ ላይ ተመስርቶ ነው፡፡ ምክንያቱም በፌዴራል፤ በክልልና በከተሞች አስተዳደር ያሉ የፈቃድ ሰጭ ባለስልጣኖች በካምፓኒዎች ስላለው ሀብት የሚገልጽ ዝርዝርና ተጨባጭ መረጃ ስለማይገኝ ነው፡፡ ከዚህ የተነሳ የማዕድን ካምፓኒዎች ካፒታላቸውንና የስራ ማስኬጃ ወጫቸውን ከፍ ሲያደርጉ ምርቶቻቸውንና የሚገኘውን ትርፍ ደግሞ ዝቅ ያደርጋሉ፡፡ የማዕድን ፈቃድ አሰጣጥና የገቢ ማጭበርበር ክስተት መኖሩ ሲረጋገጥ የማዕድን ካምፓኒ ባለቤቶች በመንግስት አካላት እርምጃ እንዳይወሰድባቸውና የሚመለከታቸው አይተው እንዳላዩ እንዲያልፏቸው ኃላፊነቱ ላላቸው ባለስልጣኖች ጉቦ ይሰጣሉ፡፡

እ.ኤ.አ የ2012 የዓለም ባንክ ዘገባ በማዕድን ዘርፉ እስከ አሁን በተጨባጭ በተግባር የታዩና የተመዘገቡ የሙስና ዓይነቶች የሚከተሉትን ያካትታሉ፡ ጉቦ መቀበል፤ የሀሰት መረጃ መስጠት፤ በህገወጥ መንገድ ከማዕድን ካምፓኒዎች ገንዘብ መውሰድና ነጻነታቸውን ዝቅ አድርጎ ማየት፤ እና የውስጥ ህገወጥ መረጃዎችን በመጠቀምና ነጻነት የሌላቸወን ካምፓኒዎች በማጭበርበር ለአካባቢው ነዋሪዎች የተመደበውን ካሳ መስረቅ ሲሆኑ ሰፋ ባለ መልክ በማዕድን ዘርፉ የሚካሄዱ የሙስና ዓይነቶች ናቸው፡፡ በዓለም ባንክ ተመዝግበው የሚገኙ በመጥፎ ምሳሌነታቸው በግልጽ የሚታዩ ለህሊና የሚሰቀጥጡ የሙስና ዓይነቶች የሚከተሉትን ያካትታል፣

አንድ የማዕድን ካምፓኒ የስራ ፈቃድ ለማውጣት ከፍ ያለ ገንዝብ መክፈል ይጠበቅበታል፡፡ ታላላቅ ባለስልጣኖችና የካምፓኒ ባለቤቶች ይህንን ገንዝብ በሚስጥር ይይዙና ገንዘቡ በውጭ ባንክ አካውንት ለባለስልጣኖች እንዲደርስ ይደረጋል፡፡

አንድ ባለስልጣን የማዕድን ካምፓኒ ባለቤቱን የስራ ፈቃዱ በቶሎ እንዲወጣለት ከፈለገ ለለጋሽ ድርጅት በርከት ያለ ገንዘብ መስጠት እንደሚጠበቅበት ይነግረዋል፡፡ ለጋሽ ድርጅቱ ሀቀኛ መስሎ ቢታይም ለባለስልጣኖች ለግል ወይም ደግሞ ለቤተሰቦቻቸው ጥቅም ከመዋል ወይም ለፖለቲካ ፓርቲ ክፍያ ሊውል ይችላል፡፡

የማዕድን ካምፓኒ የስራ ፈቃድ ለማውጣት እንዲችል ካለው አሰራር አንጻር የጤናና የደህንነት ዕቅድ እንዲያቀርብ ሊጠየቅ ይችላል፤ ነገር ግን ባለስልጣኑ ለካምፓኒ ባለቤቱ ጉቦ ካልከፈለ በስተቀር ተጨማሪና አላስፈላጊ የጤናና የደህንነት ግዴታዎች እንደሚጭንበት ይነግረዋል፡፡

የማዕድን ካምፓኒ የስራ ፈቃድ ለማውጣት የአካባቢ ጥበቃ ዕቅድ እንዲያቀርብ ሊጠየቅ ይችላል፤ ይህም የሚያቀርበው ዕቅድ የአካባቢውን የውኃ አቅርቦት ከመርዛማ ኬሚካሎች በአስተማማኝ ሁኔታ ላያስወግድ ይችላል፡፡ አስተማማኝ የመርዛማ ኬሚካሎች ቁጥጥር ለማድረግ ወጭው ከፍተኛ ሊሆን ይችላል፡፡ ሰለዚህ የተጓደለውን የቁጥጥር ስርዓት በመከተል ካምፓኒው ብዙ ወጭ ላለማውጣትና በተጓደለው ሁኔታ ለመስራት እንዲችል የስራ ፈቃዱን ለሚሰጠው ባለስልጣን ጉቦ ይሰጣል፡፡

ባለስልጣኖች ከማዕድን ካምፓኒው ትርፍ ድርሻ እንዲኖራቸው ሊጠይቁ ይችላሉ፡፡ የማዕድን ካምፓኒው ባለቤት የስራ ፈቃድ በባለስልጣኑ ውሳኔ መሰረት አገኛለሁ በሚል እምነት ለባለስልጣኑ ዘመድ ከማዕድን ፕሮጀክቱ ነጻ የትርፍ ድርሻ ሊሰጠው ይችላል፡፡

ባለስልጣኖች በድብቅ በእራሳቸው ለተያዙ ካምፓኒዎች የስራ ፈቃድ ሊሰጡ ይችላሉ፡፡ ባለስልጣኖች የስራ ፈቃድ ሊጠየቅበት የሚችል መሬት በድብቅ ያገኛሉ፡፡

አንድ ባለስልጣን የአንድ የማዕድን ቦታ የስራ ፈቃድ ይወጣበታል የሚል ግንዛቤ ካለው ባለስልጣኑ የስራ ፈቃዱ ከመውጣቱ በፊት መሬቱን ቅድሚያ ሊያከራየው ይችላል፡፡ የስራ ፈቃዱ ከተሰጠ በኋላ ግን የመሬቱ ዋጋ ሊጨምር ይችላል፡፡ በዚህም መሰረት ባለስልጣኑ ወይም ባለስልጣኗ በመሬቱ ላይ ያለውን ወይም ያላትን የመሬት ባለቤትነት መብት በመጠቀም ለመሸጥ ወይም ለካምፓኒው የስራ ፈቃድ በመስጠት ለማከራየት ይችላሉ፡፡

ካምፓኒዎች የተሰጣቸውን የስራ ፈቃድ በህገወጥ መልክ ሊሸጡ ይችላሉ፡፡ ባለስልጣኖች የስራ ፈቃድ የምዝገባ ስራን ማጭበርበር ሊፈጽሙ ይችላሉ፡፡

አንድ በመንግስት መ/ቤት መምሪያ የማዕድን ስራ ፈቃድ ለማውጣት የሚያስችል ባለስልጣን አንድ ካምፓኒ የስራ ፈቃድ ማውጣት እንደሚፈልግ አስቀድሞ ሊያውቅ ይችላል፡፡ በመሆኑም ባለስልጣኑ ካለው ግንኙነት አንጻር የቢዝነሱ ሰው በዚያ ቦታ ላይ በፍጥነት የስራ ፈቃድ ማውጣት እንዲችል ሊያሳስበው ይችላል፡፡ ባለስልጣኑ ለቢዝነሱ ሰው የስራ ፈቃዱን ሊሰጠው ይችላል፡፡ ከዚያም የማዕድን ካምፓኒው ከቢዝነሱ ሰው ጋር የስራ ፈቃዱን ይገዛውና የቢዝነሱ ሰው ከባለስልጣኑ ጋር ትርፍ ሊጋራ ይችላል፡፡

አንድ አሳሽ ማዕድን ያለበትን ቦታ ሊያገኝ ይችላል፡፡ በቦታውም ላይ ምልክት በማድረግ ጉዳዩ ወደሚመለከተው የስራ ፈቃድ ሰጭ አካል በመቅረብ የባለቤትነት ሰርቲፊኬት ማግኘት እንዲችል ሊያመለክት ይችላል፡፡ ሙሰኛ ባለስልጣን ግን ይህንን ግኝት ተቀብሎ አስሶ ባገኘው ስም አይመዘግብም፤ ይልቁንም የቢዝነስ ጓደኛ በመፈለግ በቢዝነስ ጓደኛው ስም እንዲመዘገብ ያደርጋል፡፡ ይኸ ሙሰኛ ባለስልጣን በመጀመሪያ አስሶ ያገኘውን ሰው ሀሰት በመንገር የማዕድኑን ሀብት ከእርሱ በፊት ሌላ እንዳገኘው ይነግረዋል፡፡

ባለስልጣኖች ዘመዶቻቸው የኮንትራት ስምምነት በመፈራረም ተጠቃሚ እንዲሆኑ ህገወጥ በሆነ መልኩ ከማዕድን ካምፓኒ ባለቤቶች ጋር እንዲፈራረሙ ያደርጋሉ፡፡ ፈቃድ ሰጭው አካል ኮንትራቱን ከመስጠት አንጻር ወይም ማህበረሰባዊ የልማት ዕቅድን ከማምጣት አኳያ በካምፓኒው ሙሉ ወጭ ብዙ የመሰረተ ልማት ስራዎችን መስራት እንደሚጠበቅበት ለካምፓኒው ይነግረዋል፡፡ ለምሳሌ ካምፓኒው መንገድ፤ ትምህርት ቤት ወይም ሆስፒታል እንዲገነባ ወይም አንዲጠግን ሊገደድ ይችላል፡፡ በዚህ መሰረት የመንግስት ባለስልጣኑ አንዱን ወይም ከዚያ በላይ የሆኑትን የመሰረተ ልማት ስራዎች ኮንትራት በድብቅ ለባለስልጣኑ ዘመድ በኮንተራት እንዲሰጥ ይነገረዋል፡፡

ባለስልጣኖችና የአካባቢ ማህበረሰብ መሪዎች ለአካባቢው ማህበረሰብ አባላት መድረስ ያለባቸውን ካሳዎች ይበላሉ፡፡ የማዕድን ስራ ካምፓኒዎች ለማህበረሰቡ የሚሰጡ ካሳዎች ዋጋ ከትክክለኛው ግምት በታች ዝቅ እንዲል ለባለስልጣኖች ጉቦ ይሰጣሉ፡፡

የአካባቢ ኗሪ ማህበረሰብ አባላት በመሬት የስራ ፈቃዱ መሰረት በሀሰት መሬቱን እንዳገኙ ይናገራሉ፡፡ ኮንትራክተሮችና አምራቾች በተጭበረበሩ የጨረታ፣ ይዞታዎችና ችግር ያለባቸውን ስራዎች በመደበቅና በማጽደቅ ይሰማራሉ፡፡

የማዕድን ካምፓኒዎች ስለማዕድኖች ዓይነትና ጥራት ወይም ደግሞ ለአጽዳቂዎች ጉቦ በመስጠት የተሳሳተ መረጃ በመስጠት ሙስና ይሰራሉ፡፡ በአሁኑ ጊዙ ይህ ዓይነቱን ሙስና በሚመለከት በኢትዮጵያ ላይ ከፍተኛ ጥናት በመካሄድ ላይ ይገኛል፡፡

የኢትዮጵያን የማዕድን ዘርፍ እንደማስመሳያነት?

በስልጣን ላይ ያለው ገዥው አካል ከማዕድኑ ዘርፍ ከሚገኘው ገቢ ጋር በተያያዘ መልኩ በሀሰት ላይ የተመሰረተ የማስመሰያ ምናባዊ የማታለል ጨዋታ በመጫወት ላይ ይገኛል፡፡ በቅርቡ የገዥውን አካል ዋቢ በማድረግ በወጡ መረጃዎች መሰረት “የኢትዮጵያ መንግስት በያዝነው ዓመት የመጀመሪያዎቹ 11 ወራት ከማዕድኑ ዘርፍ በአገሪቱ ውስጥ በባህላዊ የአመራረት ዘይቤ በተሰማሩ አምራቾች አማካይነት ተመርቶ ወደ ውጭ ከተላከው ምርት 419 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር የውጭ ምንዛሬ አግኝቷል፡፡ ከዚሁ ወደ ውጭ ከተላከው የማዕድን ምርት በመጠን የወርቅ ምርት ከፍተኛውን ደረጃ  በመያዝ 409.1 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሬ ያስመዘገበ ሲሆን ለጌጣጌጥ የሚውል ድንጋይ እና ታንታለም እንደየቅደም ተከተላቸው 9.3 ሚሊዮን እና 1.6 ሚሊዮን ዶላር በማስመዝገብ የሁለተኛ እና  የሶስተኛነት ደረጃን ይዘዋል፡ ይህም ገቢ የተገኘው 7,878.3 ኪ/ግ ከሚመዝን ወርቅ፣ 20,126.3 ኪ/ግ ከጌጣጌጥ ከሚውል ድንጋይ እና 32.95 ቶን የሚመዝን ደግሞ ከታንታለም የተገኘ ነው… ከፍተኛ የሆነ የአመራረት ዘይቤን በመከተል በአገሪቱ ውስጥ ወርቅ በማምረት ስራ ላይ ተሰማርቶ የሚገኘው ሚድሮክ/MIDROC የተባለው ብቸኛ ኩባንያ ነው፡፡“ ሌሎች ዘገባዎች እንደሚጠቁሙት “በአጠቃላይ ከአገሪቱ ወደ ውጭ ከሚላከው ምርት ውስጥ የማዕድን ምርት 23 በመቶ ድርሻ በመያዝ ለኢትዮጵያ ሁለተኛ የውጭ ምንዛሬ ማስገኛ ለመሆን በቅቷል፡፡“ እዚህ ላይ ሊነሳ የሚችለው ዋናው ጉዳይ ግን የሳጥኑን መክፈቻ ቁልፍ ከያዙት ሰዎች በስተቀር በማዕድን ዘርፉ የተመረተው ምርት በትክክል ምን ያህል ገቢ እንዳስገኘ በእርግጠኝነት የሚያውቅ የለም፡፡ ገዥው አካል ከማዕድኑ ዘርፍ የተገኘው ገቢ ምን ያህል እንደሆነ የሚያጣራ ነጻ የሆነ ምንም ዓይነት የአሰራር መንገድ ስለሌለ ከኩባንያዎች በሚገኙ ዘገባዎች ላይ ብቻ በመመስረት መገመት እንደሚኖርበት ይናገራል፡፡ እንዴት የሚመች ነገር ነው እባካችሁ! እውነታው ግን ከማዕድኑ ዘርፍ ምርት ከሚገኘው ገቢ ዋናዎቹ ተጠቃሚዎች ሀብቱን በብቸኝነት የተቆጣጠሩ የገዥው አካል ቡድኖች፣ ለእነዚህ ቡድኖች አቀባባይ ሆነው በማዕድን ምርት ንግዱ ስራ ላይ በግንባር የተሰማሩ ሰዎች እና “በህዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ” ቁጥጥር ስር ያሉ ሌሎች ድርጅቶች ናቸው፡፡ ከማዕድን ፈቃድ ሽያጭ እና በህገወጥ መንገድ ከማዕድን ምርት ዘርፉ የተገኘው ገንዘብ በተያያዘ መልኩ እየተፈጸመ ያለውን ሙስና ስፋት እና ጥልቀት ምን ያህል እንደሆነ ማንም በእርግጠኝነት ማወቅ አይችልም፡፡ ሆኖም ግን ከወርቅ ማምረቻ ቦታዎች በቅርብ ርቀት ከሚገኙ ጥርጊያ የአውሮፕላን ማረፊያዎች በመቶዎች ኪሎ  የሚቆጠር የወርቅ ምርት ያለምንም ፍተሻ በአውሮፕላን እየተጫነ ከአገር እንደሚወጣ አስተማማኝነት ያላቸው የዓይን እማኞች ምስክርነታቸውን በመስጠት ላይ ይገኛሉ፡፡ እንግዲህ እንዲህ ያለ ድፍረት የተሞላበት እና ዓይን ያወጣ የማዕድን ምርት ዘረፋ በተንሰራፋበት ሁኔታ ነው ገዥው አካል ለአምራች ኢንዱስትሪዎች የግልጽነት ተነሳሽነት/EITI ዓለም አቀፋዊ ተቋም አባል ለመሆን በመፈለግ የአባልነት ጥጣቄ እያቀረበ ያለው፡፡

የአምራች ኢንዱስትሪዎች የግልጽነት ተነሳሽነት/EITI ለምንድን ነው የገዥውን አካል የአባልነት ጥያቄ ውድቅ ያደረገው? 

የአምራች ኢንዱስትሪዎች የግልጽነት ተነሳሽነት/EITI እ.ኤ.አ በ2011 ባረቀቃቸው ህጎቹ የሲቪል ማህበረሰቡ ነጻ ሆኖ መስራት እና ሙሉ ተሳትፎ ማድረግ መቻል ለዕጩነት እና ለአባልነት የመምረጫ መስፈርት የመሰረት ድነጋይ መሆኑን በግልጽ አስቀምጧል፡፡ ለአባልነት ብቁ ሆኖ ለመገኘት በኢትዮጵያ ያለው ገዥው አካል “የሲቪል ማህበረሰቡን ተሳትፎ ሊያዉኩ የሚችሉ እንቅፋቶችን ማስወገድ እና ገዥው አካል “የሲቪል ማህበረሰቡን መሰረታዊ የሰብአዊ መብቶች እና በአምራች ኢንዱስትሪዎች የግልጽነት ተነሳሽነት/EITI የሚሳተፉ ኩባንያዎች ተወካዮችን መብት ማክበር ይኖርበታል፣“ ገዥው አካል “ለሲቪል ማህበረሰቡ እና ለኩባንያዎች በስራ እንቅስቃሴ ተሳትፎ ሂደት ጊዜ ምንም ዓይነት እንቅፋቶች እንደማይኖሩ ማረጋገጥ አለበት፡፡“ እንዲሁም “ለሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች እና ኩባንያዎች አስፈላጊ የሆኑ ህጎችን፣ ደንቦችን እና አስተዳደራዊ ህጎችን እንዲሁም የአምራች ኢንዱስትሪዎች የግልጽነት ተነሳሽነት/EITIን ተግባራት በተጨባጭ ለመተግበር የሚያስችሉ ማዕቀፎችን ለማመቻቸት ዋስትና መስጠት አለበት፡፡“

ከዚህም በላይ ገዥው አካል “የአምራች ኢንዱስትሪዎች የግልጽነት ተነሳሽነት/EITIን የስራ ማዕቀፎችን ከሚያጠቡ ወይም ደግሞ የህብረተሰቡን በነጻነት የመወያየት ዕድል ከሚያደናቅፉ ተግባራት መታቀብ አለበት፣“ እንዲሁም “የሲቪል ማህበረሰቡ እና የኩባንያዎች ተወካዮች በግልጽነት እና በተፈጥሮ ሀብቶች አያያዝ ጉዳዮች ላይ ነጻ ሆነው መወያየት እንዲችሉ ማረጋገጥ ይኖርበታል፡፡“ ገዥው አካል የሲቪል ማህበረሰብ ቡድኖች የብዙ ባለድርሻ ቡድኖች አባላት ሆነው እንዲሰሩ ማረጋገጥ አለበት፡፡ እንዲሁም “በፖሊሲ ጉዳዮችም ከመንግስት እና/ወይም ከኩባንያዎች ነጻ ሆነው መስራት አለባቸው፣“ እናም “ያለምንም መሰናክል ወይም ጭቆና ከሚፈልጓቸው ቡድኖችም ጋር አብረው ነጻ ሆነው መስራት ይኖርባቸዋል፡፡ የአምራች ኢንዱስትሪዎች የግልጽነት ተነሳሽነት/EITI በግልጽ የሚፈልገው “የሲቪል ማህበረሰቡ ቡድኖች፣ ኩባንያዎች እና ወኪሎቻቸው ስለ የአምራች ኢንዱስትሪዎች የግልጽነት ተነሳሽነት/EITI ሀሳቦቻቸውን ያለምንም ስጋት፣ ግዳጅ እና የበቀል ስሜት ሳይኖርበት በነጻነት ሀሳቦቻቸውን መግለጽ እንዲችሉ“ ለማድረግ እና “በአምራች ኢንዱስትሪዎች የግልጽነት ተነሳሽነት/EITI ላይ ተሳትፎ ያላቸው የሲቪል ማህበረሰብ ቡድኖች በEITI በሚደረጉ ህዝባዊ ውይይቶች ላይ ግልጽ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ሙሉ ነጻነት ማግኘት አለባቸው፡፡“ በማለት ህጉን በማያሻማ ሁኔታ በግልጽ አስቀምጦታል፡፡

የሲቪል ማህበራት ተቋማት በኢትዮጵያ ባለው ገዥው አካል ከእንቅስቃሴ ውጭ ተደርገዋል፣

እ.ኤ.አ የወጣው የ2009 የገዥው አካል የበጎ አድራጎት እና ማህበራት ህግ አዋጅ ቁጥር 621/2009/Charities and Societies Proclamation No. 621/2009 በኢትዮጵያ ያሉ የሲቪል ማህበራት ድርጅቶችን ሙሉ በሙሉ በሚባል መልኩ ለማጥፋት አዋጁን መሳሪያ አድርጎ ተጠቅሞበታል፡፡ እ.ኤ.አ በ2008 ረቂቅ አዋጁን በጥሞና በማየት “የበጎ አድራጎት እና ማህበራት ረቂቅ አዋጁን መመርመር“ በሚል ርዕስ ረዥም ትንታኔ አቅርቤ ነበር፡፡ በዚያ ትንታኔዬ ላይ አዋጁ ጠቀሜታ የሌለው መሆኑን በማመን ይህ አዋጅ የማይጠቅም በመሆኑ ለምን መወገድ እንዳለበት 10 አሳማኝ ምክንያቶችን ዘርዝሬ አቅርቢያለሁ፡፡ እንዲህ በማለትም የክርክር ጭብጤን አቅርቢያለሁ፡፡ የአዋጁ ዋና ተልዕኮ ገዥው አካል የህግ ማፈኛ አድርጎ በማቅረብ ያነጣጠረው የሲቪል ማህበራት ተቋማትን በመገደብ እና ህልውናቸውን በማጥፋት ተቋማቱ የዴሞክራሲያዊ ተግባራትን በማሳለጥ ስጋት ይፈጥሩብኛል በሚል ልሳናቸውን አስቀድሞ ለመዝጋት እና ከሚጠብቀው ፍርሀት ለመገላገል የታለመ ነው ብዬ ነበር፡፡ አዋጁ የሲቪል ማህበራት ድርጅቶችን በዘፈቀደ እና ምንም ዓይነት የህግ ምርመራ ሳያደርግ መቆጣጠር የሚያስችል የዘፈቀደ እና ያልተጠበቀ ለውጥ ሊያስከትል የሚችል የተለጠጠ እና ያልተገደበ ስልጣን እንደ ፍርድ ቤት ዳኛ መርምሮ ሳይሆን እንደፈለገው እንዲያደርግ ለበጎ አድራጎት እና ማህበራት ድርጅት ኃላፊ ስጥቷል፡፡ አዋጁ ሳይፈለግ የመጣ በበጎ አድራጎት ደርጅቶች እና ማህበራት የውስጥ ጉዳዮች ላይ በኃይል የተጣለ፣ ለጥቃቅን ነገሮች ሁሉ ትኩረት በመስጠት በተቋሞቹ የውስጥ ጣልቃገብነት ላይ እጁን ያስገባ እና ምክንያታዊ ያልሆኑ እና በጣም አስቸጋሪ የሆኑ እንዲሁም እራሱ ገዥው አካል የማይተገብራቸውን የገንዘብ ተጠያቂነትን ሊያስከትሉ የሚችሉ ከሚታሰበው በላይ የተንዛዙ መስፈርቶችን በማቅረብ ድርጅቶቹ እንዳይሰሩ ሽባ ማድረግን ዓላማ ያደረገ ነው፡፡ አዋጁ ለመቅጣት የወጣ እና የበጎ አድራጎት ድርጅቶች እና ማህበራት አባል መሆን እና ተሳትፎ ማድረግም እንዳይቻል ለማስፈራሪያነት የወጣ ነው፡፡ በመጨረሻው የክርክር ጭብጤም ላነሳው የምፈልገው ጉዳይ አዋጁ ህገመንግስታዊ ያልሆነ፣ የማይመች እና የሚቆጠቁጥ እንዲሁም አድሏዊ ነው፡፡ ዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቱ ሂዩማን ራይትስ ዎች/Human Rights Watch የአዋጁን መውጣት ተከትሎ አዋጁ የማያሰራ መሆኑን ለመግለጽ የሚከተለውን ማስጠንቀቂያ ሰጥቶ ነበር፣ “የዚህ አዋጅ የታሰበው ውጤት እና በተግባር እየታየ ያለው ተጨባጩ እውነታ እንደሚያሳየው ማንኛውም የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት መንግስት ሳያጸድቀው እና ሳይፈቅድ ምንም ዓይነት ስራ መስራት እንደማይችል በግልጽ ያስቀመጠ ነው፡፡“ በተደጋጋሚ እንደምለው በኢትዮጵያ በስልጣን ላይ ላለው ገዥው አካል ስለህገመንግስት፣ የህግ የበላይነት እና ስለተጠያቂነት ማስተማር ማለት መስማት እና መናገር ለተሳናቸው ዱዳዎች ከመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ እየጠቀሱ እንደመስበክ ወይም ደግሞ በጥቁር የባልጩት ድንጋይ ላይ ውኃ እንደማፍሰስ ይቆጠራል፡፡

እ.ኤ.አ በፌብሯሪ 2010 የዩናይትድ ስቴትስ ረዳት ጸሐፊ ማሪያ ኦቴሮ የበጎ አድራጎት እና ማህበራት አዋጅን አስመልክቶ ያላቸውን ስጋት በቅርቡ ላረፉት ለአቶ መለስ ዜናዊ እንዲህ በማለት ገልጸው ነበር፣ “ይህ አዋጅ በኢትዮጵያ የሲቪል ማህበረሰቡን ሚና የሚጎዳ ነው“ ብለው ነበር፡፡ አቶ መለስ ግን የሴትዮዋን ስጋት ወደ ጎን ገሸሽ አደረጉት፡፡ ሆኖም ግን አዋጁ በኢትዮጵያ ያሉትን የበጎ አድራጎት እና ማህበራት ተቋማትን ወዲያውኑ ማክሰም ጀመረ፡፡ እንደ አንድ ዘገባ ከሆነ “እ.ኤ.አ በ2010 መጀመሪያ አካባቢ ብዛታቸው 4,600 የነበረው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በሶስት ወራት ጊዜ ውስጥ ብዙዎቹ እንዲከስሙ ተደርገው በመንገዳገድ ላይ የሚገኙ 1,400 ብቻ ሆነው ተገኙ፡፡ ከመክስም የተረፉት ወደ 30 በመቶ ብቻ መሆናቸው ሲታይ ሁኔታው አስደንጋጭ መሆኑን ያመላክታል፡፡ መረጃዎቼ እንደሚያስረዱት በህይወት ከተረፉት ድርጅቶች መካከልም የአብዛኞቹ ድርጅቶች የሰው ኃይል በ90 በመቶ ወይም በበለጠ ቅናሽ አሳዬ፡፡“ በግልጽ ለማስቀመጥ አዋጁ በኢትዮጵያ በሶስት ወራት ጊዜ ውስጥ 70 በመቶ የሚሆኑትን የሲቪል ማህበራት ድርጅቶችን ከስራ ውጭ አድርጓል! በተመሳሳይ ወር ገዥው አካል ቀደም ሲል የተቋቋሙትን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤን እና የኢትዮጵያ የህግ ባለሙያ ሴቶች ማህበርን የእነዚህን ሁለት ጠንካራ ተቋማት አቅማቸውን ለማሽመድመድ በማሰብ ዓላማቸው እና የሚፈጽሟቸው ተግባራት ከህግ አግባብ ውጭ ነው በማለት ወንጅሎ የባንክ ሂሳቦቻቸውን በመዝጋት ንብረቶቻቸውን አገደ፡፡

እ.ኤ.አ በ2012 ገዥው አካል አስር መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን/NGOs ከአዋጁ በተጻራሪ መንገድ ሲንቀሳቀሱ አገኘኋቸው በሚል ሰበብ መዝጋቱን እና ሌሎች በደርዝን የሚቆጠሩት ደግሞ የማይገባ ባህሪ በማሳየት ላይ ናቸው ያላቸውን ተቋማት እውቅና እንደሚሰርዝ በመዛት አወጀ፡፡ ገዥው አካል በተጨማሪም የሌሎች 17 የሚሆኑ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ጉዳይ በመጣራት ላይ ያለ መሆኑን ተናገረ፡፡ ገዥው አካል እርምጃውን 400 የሚሆኑ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ከአዋጁ በተጻራሪ እየተንቀሳቀሱ ነው የሚል ሰበብ ከሰጠ በኋላ በቀጣይ አስፈላጊ እርምጃ እንደሚወስድባቸው በማስረገጥ ዝቷል፡፡ እ.ኤ.አ በኖቬምበር 2012 ሄንሪክ ቦል ፋውንዴሽን/Heinrich Boll Foundation የተባለ በዴሞክራሲ እና በሰብአዊ መብቶች ዙሪያ የሚሰራ የጀርመን አገር መንግሰታዊ ያልሆነ እርዳታ ሰጭ ድርጅት ንብረቱን ሸክፎ በሚሰራቸው ስራዎች ላይ የተጣሉትን እገዳዎች በመቃወም ከሀገር ለቅቆ ወጣ፡፡

እ.ኤ.አ በፌብሯሪ 2013 ገዥው አካል በሶስት መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች ላይ ማለትም አንድ ኢውሮ/ One Euro፣ የእስላም ባህላዊ እና የምርምር ማዕከል/the Islmaic Cultural and Research Center፣ እና የጎሄ ህጻናት፣ ወጣቶች እና ሴቶች የልማት ድርጅት/the Gohe Child, Youth and Women Development Organization የተባሉ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን “ህገወጥ የኃይማኖት እንቅስቃሴ” ማድረግ የሚል ክስ በማቅረብ ስራቸውን በማቆም ከሀገር እንዲለቅቁ አድርጓል፡፡ እንዲሁም እ.ኤ.አ በ2013 “በአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ድርጅት/US Agency for International Development የገንዘብ ድጋፍ ሲንቀሳቀሱ ከነበሩት 29 የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ውስጥ 27ቱ ከአዋጁ ህግ በተጻራሪ መልኩ የሚንቀሳቀሱ ናቸው ብሎ ፈርጇቸዋል፡፡“ እ.ኤ አ. በ2013 ሂዩማን ራይትስ ዎች/Human Rights Watch የተባለው ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅት አዋጁን በማስመልከት የሚከተለውን ዘገባ አቅርቧል፣ “የኢትዮጵያ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች አዋጅ በዓለም ላይ ያሉ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን የስራ እንቅስቃሴ ለመቆጣጠር ከወጡ ጨቋኝ ህጎች ውስጥ አንዱ ነው… እ.ኤ.አ ከ2010 ጀምሮ በኢትዮጵያ የሲቪል ማህበረሰቡ የእንቅስቃሴ ምህዳር፣ የፕሬስ ነጻነት፣ እና በሰላማዊ መንገድ ተቃውሞን የመግለጽ መብት እየጠበበ መጥቷል፣“ በማለት ዘገባውን ቋጭቷል፡፡

እ.ኤ.አ የ2014 የቤርቴልስማን የሽግግር አመላካች መለኪያ/Bertelsmann Transformation Index የሚከተለውን ዘገባ አቅርቧል፣ “በጨቋኝ ህጎች ምክንያት የብዙሀን መገናኛ እና የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች እንቅስቃሴ ተዘግቷል፣ የሠራተኛ እና የሙያ ማህበራት መንግስት ቀንብቦ ባስቀመጠው ማዕቀፍ ውስጥ መግባት ወይም ደግሞ እንደ ቀድሞው የመምህራን ማህበር መክሰም፣“ የሚል ሆኗል፡፡ የሚያስገርመው እውነታ ግን በአሁኑ ጊዜ በአምራች ኢንዱስትሪዎች የግልጽነት ተነሳሽነት/EITI የሚገኙት የሲቪል ማህበረሰብ ባለድርሻ አካላት ማለትም ግሎባል ዊትነስ/Global Witness ኦፕን ሶሳይቲ ረቨኑ ዎች ኢንስቲትዩት/Open Society Revenue Watch ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽል/Transparecny International ከብዙ ጥቂቶቹ ሲሆኑ በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ እንዲንቀሳቀሱ ቢፈልጉ አይፈቀድላቸውም! እንዲህ ሆኖ እያለም ገዥው አካል በሚያስገርም ቀልድ ነገር አቀራረብ እና እራሱን በሀሰት ጀቡኖ የሞራል ስብዕና ያለው በማስመሰል ከእነዚህ ድርጅቶች ጋር ለመገናኘት እና የሲቪል ህብረተሰብ ተቋማት በነጻ መንቀሳቀስ እንደሚችሉ በተግባር ያለውን ቁርጠኝነት በአስመሳይነት ለዓለም ህዝብ ለማሳወቅ የሚያደርገው ሽርጉድ የማለቱ ጉዳይ ነው፡፡

የአምራች ኢንዱስትሪዎች የግልጽነት ተነሳሽነት/EITI ስነስርዓቶች ላይ መቀለድ፣ በኢትዮጵያ ያለው ገዥ አካል የማጭበርበር ድርጊት መቆም አለበት፣

በኢትዮጵያ ያለው ገዥው አካል በአምራች ኢንዱስትሪዎች የግልጽነት ተነሳሽነት/EITI ላይ የጀመረው ማጭበርበር እና የዕጩ አባልነት ማመልከቻ ሰነድ ማቅረብ በተቋሙ ስነርዓት ላይ እያደረገ ያለውን ቀልድ ያመላክታል፡፡ ገዥው አካል የአምራች ኢንዱስትሪዎች የግልጽነት ተነሳሽነት/EITI ዋና ዋና መርሆዎች እና ለሲቪል ማህበረሰብ መብቶች ጥበቃ በግልጽ የተቀመጡትን መስፈርቶች በሚገባ እያወቀ በዓይነ ደረቅነት የተቋሙ አባል ልሁን ብሎ የአባልነት ጥያቄ ማቅረቡ በእውነቱ አሳፋሪ ድርጊት ነው፡፡ የዕጩ አባልነት ማመልከቻው ለምን ጉዳይ እንደቀረበ በመጀመሪያ ሊመረመር ይገባል… የአምራች ኢንዱስትሪዎች የግልጽነት ተነሳሽነት/EITIን አባላት እና የእራሱን የአምራች ኢንዱስትሪዎች የግልጽነት ተነሳሽነት/EITIን ክብር እና የድርጀቶቹን መርሆዎች የሚጥስ እና የሚያዋርድ ግልጽ ዘለፋ እና እንዲሁም ድርጅቶቹ ከአስርት ዓመታት ባላይ የሙስና ገመድ በሚገመድባቸው ሙሰኛ አገሮች ላይ ግልጽነት እና ተጠያቂነትን ለማምጣት አበርትተው ሲሰሩ በቆዩ ድርጅቶች ላይ ማፌዝ ነው፡:

የገዥው አካል የንቀት ዘለፋ መርሀግብር ለአምራች ኢንዱስትሪዎች የግልጽነት ተነሳሽነት/EITI ማህበረሰብ ለመታየት አለመቻል እና የተቋሙን የቦርድ አባላት ለማጭበርበር፣ ለማታለል እና በቦርዱ ዓይን ላይ አፍዝዝ አደንግዝ ለመጣል  መሞከር የዱሮ አባባልን ስለተኩላ እና የበግ ለምድ ሁኔታ በተለይም ስለኢትዮጵያ ተኩላ መሰሪነት በበጎች መካከል ገብቶ ጸሎት ላድርስ ካለው ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ ገዥው አካል እውነተኛ ባህሪውን ማለትም ተኩላዊ፣ ገዳይ፣ ስግብግብ፣ ለሙስና ክፍት የሆነ፣ ሙሰኛ፣ ትርፍ አጋባሽ እና በማንኛውም ሞራላዊ ብቃቱ የበከተ መሆኑን ለዓለም ህዝብ በማሳወቅ  ለአምራች ኢንዱስትሪዎች የግልጽነት ተነሳሽነት/EITI ዕጩ አባል ለመሆን ማመልከቻ ለማስገባት ይፈልጋል፡፡

በአምራች ኢንዱስትሪዎች የግልጽነት ተነሳሽነት/EITI ያሉት ሁሉም ሀሳቦች ግልጽነት እና ተጠያቂነትን ማስፈን ናቸው፡፡ ገዥው አካል በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያ ያሉትን የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችን እንቅስቃሴ የማቋረጡን ኃላፊነት ለመውሰድ ፈቃደኛ ካልሆነ ብቸኛ ዓላማው ግልጽነት እና ተጠያቂነት ከሆነ ድርጅት ጋር በእርግጠኝነት አባል ለመሆን ግምት ሊኖረው የሚችለው በምን ዓይነት መስፈርት ነው? የቀበሮ ባህታዊ በበጎቹ መንጋ መካከል ጸሎት ማድረስ ይችላልን? የትኛው የአምራች ኢንዱስትሪዎች የግልጽነት ተነሳሽነት/EITI አገር ነው ከእንደዚህ ያለ የዘቀጠ ዕጩ አባል ጋር አብሮ መወያየት የሚሻው?

የገዥው አካል ለአምራች ኢንዱስትሪዎች የግልጽነት ተነሳሽነት/EITI ዕጩ አባልነት ጥያቄ ተቀባይነት ከማግኘቱ በፊት እራሱ ገዥው አካል በአሁኑ ጊዜ ያለውን አፋኝ የበጎ አድራጎት እና ማህበራት አዋጅ በመሻር በምትኩ ሲቪል የሆነ የሲቪል ማህበረሰብ ህግ፣ ግብረገብነት ያለው እና የሰለጠነ ህግ በማውጣት ለአምራች ኢንዱስትሪዎች የግልጽነት ተነሳሽነት/EITI- ኢትዮጵያ የተቋማዊ ግልጽነት እና እውነተኛ ጽኑ አቋም/Ethiopia Institutional Transparency and Integrityንን ማስፈን ይጠበቅበታል ግዳጅም አለበት፡፡ 

የአምራች ኢንዱስትሪዎች የግልጽነት ተነሳሽነት/EITIን ክህደት በተሞላበት ስብዕና ለማታለል የመሞከር ጨዋታ እና ከዕውነተኛ ስብዕናው ውጭ በሆነ መልኩ ተገቢነት የሌለው ዓለም አቀፋዊ ክብር ለማግኘት የሚደረገው ሚስጥራዊ ሸፍጥ መጋለጥ እና መቆም አለበት!

ኢትየጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!

የካቲት 18 ቀን 2006 ዓ.ም

 

 

 

 

 

 

 

Similar Posts

Leave a Reply