የኢትዮጵያ የይስሙላ ፍርድ ቤቶች መደፈር?
ከፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማርያም
ትርጉም በነጻነት ለሀገሬ
በኢትዮጵያ ያለው ገዥው አካል የይስሙላ የፍትህ ስርዓት (ባሜርካኖች አባባል የካንጋሩ ወይም ባማርኛ የዝንጀሮ የፍርድ ስርዓት) መስርቷል እያልኩ ሁልጊዜ ስጮህ የቆየሁበትን ሀሳብ ሙሉ በሙሉ ማስረጃ የሚሆን ድርጊት በመፈጸሙ እያዘንኩም ቢሆን በመጠኑ ፈገግታ ሰጥቶኛል፡፡ የኢትዮጵያ “ፍርድ ” ቤቶች “በህዝባዊ ወያኔ ሐርነት ትግራይ/Tigrian Peoples Liberation Front” የፖለቲካ ባላባቶችና ጌቶች የሚዘወሩ የይስሙላ ፍርድ ቤቶች ናቸው፣ በዚህም መሰረት ለዓመታት በኢትዮጵያ ውስጥ የህግ የበላይነት የለም እያልኩ ስናገር ቆያቻለሁ:: ባለፈው ሳምንት “ፍርድ ቤትን ዘልፈዋል ደፍረዋል” በሚል ሰበብ የአንድነት ለዴሞክራሲ ለፍትህ ፓርቲ የቀድሞው ዋና ጸሐፊ የነበሩትን አቶ አስራት ጣሴን ወደ ዘብጥያ ማውረድ በአገሪቱ ባሉ የይስሙላ ፍርድ ቤቶች በተደጋጋሚ የሚፈጸሙትን የስህተት ኮሜዲዎች (የቀልድ ትእይንቶች) እና የፍትህ ስርዓቱን ሽባ መሆን በተጨባጭ የሚያመላክት ትኩስ ማስረጃ ነው፡፡
አቶ አስራት ጣሴ በስልጣን ላይ ተፈናጥጠው ለሚገኙት እውነትን በመናገራቸው፣ ወይም ደግሞ በግልጽ ለማስቀመጥ የውሸት የፍትህ ካባ ደርበው የፖለቲካ ስልጣናቸውን መከታ በማድረግ የዜጎችን መብቶች ለሚደፍሩ ለሚደፈጥጡ እና ስልጣናቸውን አላግባብ ለሚጠቀሙ ባለስልጣኖች እውነትን ደፍረው በመናገራቸው “ወንጀል” ተደርጎ ለእስር ተዳርገዋል፡፡ አቶ አስራት በየሳምንቱ በአማርኛ ቋንቋ እየተዘጋጀ በሚወጣው አዲስ ጉዳይ መጽሔት ላይ በህግ በተያዘ ጉዳይ ላይ የኢትዮጵያ ሬዲዮ እና ቴሌቪዥን ድርጅት እየሰራ ያለው “ዘጋቢ ፊልም” የድርጅታቸውን ስም የሚያጠፋ እና የውደፊት ህልውና የሚጎዳ መሆኑን በማስመልከት ሀሳባቸውን በመግለጻቸው “ፍርድ ቤትን ዘልፈዋል ደፍረዋል ” የሚል ክስ ተመስርቶባቸዋል፡፡ አቶ አስራት እንዲህ በማለት ነበር ሀሳባቸውን በጽሁፍ ያሰፈሩት፣ “በአሁኑ ጊዜ የአኬልዳማ ተውኔት በቴሌቪዥን በመታየት ላይ ይገኛል፡፡ ይህም እየተከናወነ ያለው የአንድነት ለዴሞክራሲ እና ለፍትህ ፓርቲ እና የኢትዮጵያ ሬዲዮ እና ቴሌቪዥን ድርጅት (ኢሬቴድ) የህግ ሂደት ጉዳይ በፍርድ ቤት በመታየት ላይ በሚገኘበት እና አንድነት ለዴሞክራሲ እና ለፍትህ ፓርቲ ከዘጋቢ ፊልሙ ጋር በተያያዘ መልኩ ኢሬቴድ የስም ማጥፋት በደል አድርሶብኛል በማለት ክስ መስርቶ ባለበት ጊዜ ነው፡፡ በኢሬቴድ ላይ በመሰረትነው ክስ ፍትህ እናገኛለን የሚል ግምት ስለሌለን ለታሪክ ሰነድ በማስረጃነት እንዲቀመጥ በሚል ነው፡፡“
እ.ኤ.አ በታህሳስ 2011 “ኢትዮጵያ፡ የደም መሬት ወይስ የሙስና መሬት?“ በሚል ርዕስ ባቀረብኩት ትችቴ “አኬልዳማ“ የሚል የውሸት ዘጋቢ ፊልም በመፈብረክ በቅርቡ ያረፉትን አቶ መለስ ዜናዊን መላዕክ አድርጎ ለማቅረብ እና መንግስታዊ አስተዳደራቸውን የሚቃወሙትን ተቃዋሚዎች ጥላሸት ለመቀባትና አፍ ለመድፈን የተተወነ እርባና ቢስ ዘጋቢ ፊልም መሆኑን ባቀረብኩት ትንታኒዬ ሀሳቤን አካፍዬ ነበር፡፡ መልዕክቱም እንዲህ የሚል ነበር፡፡
‘አኬልዳማ‘ የሞራል ዝቅጠት የታጨቀበት በስሜታዊነት የተሞላ ዘጋቢ ተውኔት ድራማ ነው፡፡ በጨለማ ውሰጥ ተደብቀው እያደቡ በመቆየት ታጥቀው የተዘጋጁ እና በአደጋ ጊዜ ጦራቸውን ሰብቀው ጭራቃዊ አሸባሪዎችን ለመውጋት ብቅ የሚሉ በትልቅ የስልጣን ቦታ ላይ የተኮፈሱ ጀግና አሉት፣ አምባገነን መለስ ዜናዊ፡፡ በትልቅ የአደጋ ድባብ ስር የወደቀች ወይዘሪት ኢትዮጵያ የምትባል ወጣት አለች፡፡ የጭራቆች፣ የሸፍጠኞች፣ የበጥባጮች፣ መንግስትን በኃይል ገልባጮች፣ የውጭ ተባባሪዎች እና በእርግጥም የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎችን፣ አመጸኞችን እና ትችት አቅራቢዎችን በሚረዱ አገሮች የሚደረጉ ሙሉ በሙሉ ሚስጥራዊ የሆኑ ሸፍጦች፣ በዲያስፖራ የተቃዋሚ አባላት የሚደረጉ መሰሪ ተግባራት፣ በአማጺዎች እና በአገር ውስጥ ከሃዲ ተባባሪዎች እና በእርግጥም ሽብርተኝነት የሚፈጸሙ ስሜታዊነት እና አስደንጋጭ ሁኔታዎች አሉ፡፡በመጨረሻ ደግነት በጭራቃዊነት ላይ ድልን መጎናጸፉ የማይቀር ተፈጥሯዊ ክስተት ነው፡፡ ጌታው አቶ መለስ ዜናዊ የአስደናቂ ሀሳብ አፍላቂነት ባለቤቱ፣ የፖለቲካ ልሂቁ፣ ቀስት በደጋን አነጣጥረው ተኳሹ፣ እና በጎራዴ ውጊያ የተለየ ስጦታ ባለቤቱ ከጭራቁ እና ጭራቃዊነት ስሜት ካለው ከአልቃይዳ፣ ከአልሻባብ እና ከእነርሱ አሽከሮች እና ሎሌዎች ማለትም ከኢትዮጵያ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች፣ አመጸኞች እና ትችት አቅራቢዎች መዳፍ ስር ፈልቅቀው በማውጣት ወይዘሪት ኢትዮጵያን ይወልዳሉ፡፡ የሆሊዉድ መጥፎ አስፈሪው ሲኒማ አንክዎን an አንደ “አኬልዳማ” አያስጠይፍም፡፡
“የአኬልዳማ” ዘጋቢ ፊልም ተውኔት መታየትን ተከትሎ ገዥው አካል የእስላማዊ ጽንፈኞች እና አሸባሪዎች በኢትዮጵያ እስላማዊ መንግስት ለመመስረት በማሰብ ቅዱስ ጦርነት ለማካሄድ ዝግጅት እያደረጉ መሆኑን ገልጾ ይህንኑ ለማጋለጥ በሚል ሰበብ እ.ኤ.አ በፌብሯሪ 2013 “ጅሀዳዊ ሃራካት” (“የቅዱስ ጦርነት ንቅናቄ”) በሚል ርዕስ በቴሌቪዥን ለአየር አብቅቷል፡፡ ያንን እርባናየለሽ ዘጋቢ ፊልም “የፍርሃት እና ጥላሸት የመቀባት ፖለቲካ በኢትዮጵያ” በሚል ርዕስ ሀተታ አቅርቤ ነበር፣
‘ጅሃዳዊ ሃራካት’ በቅርጽ እና በይዘት ‘ከአኬልዳማ’ ተውኔት ጋር በጣም ተመሳሳይ ነው፡፡ ዋናው ልዩነታቸው ‘ጅሃዳዊ ሃራካት’ የሙስሊሙን ማህበረሰብ በማሰቃየት እና በማዋረድ ዒላማ ላይ ያነጣጠረ መሆኑ ነው፡፡ ዘጋቢ ፊልሙ በአጠቃላይ መልኩ ሲታይ የኢትዮጵያ ሙስሊም ማህበረሰብ ሰብአዊ መብቶቻቸው እንዲጠበቁ እና መንግስት በእምነት ጉዳያቸው ላይ ጣልቃ ከመግባት እንዲታቀብ ከመጠየቅ ያለፈ ነገር ያላነሱ መሆናቸው እየታወቀ ደም ከጠማቸው አሸባሪ ቡድኖች እንደ ቦኮሃራም (ናይጀሪያ)፣ አንሳር አል ዲን (ማሊ)፣ አል ቃይዳ፣ አል ሻባብ፣ ሃማስ… ጋር በማገናኘት የአገር ውስጥ ወኪሎች ናቸው በማለት ሞግቷል:: ዘጋቢ ፊልሙ ጥቂት አሸባሪዎች ከእስልምና እምነት በስተጀርባ በመሆን በኢትዮጵያ ላይ የሽብር አደጋ ይፈጽማሉ በማለት የይስሙላ ኃላፊነት ቢወስድም የሚለው አባባል ለዚህ “ዘጋቢ ፊልም” ይፋ መንግስታዊ የኃይማኖት አለመቻቻል እና ማሰቃየት በአፍሪካ ከስንት አንድ ጊዜ ብቻ ሊከሰት የሚችል ለመንግስት መጥፎ መገለጫ ሆኗል፡፡
አቶ አስራት “ስለአኬልዳማ” ሀሳባቸውን በመግለጻቸው ወደ ዘብጥያ መወርወራቸው ገዥው አካል በእርሳቸው እና በአንድነት ለዴሞክራሲ እና ለፍትህ ፓርቲ ላይ እየፈጸመ ያለውን ሚስጥራዊ እና ታማኝነት የጎደለው አካሄድ ስለዚያ እርባየለሽ ዘጋቢ ፊልም በድፍረት “በፍርድ ቤት” በመሞገታቸው ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ገዥው አካል ፍትሀዊ ባልሆነ መንገድ አቶ አስራት ጣሴን በቁጥጥር ስር በማዋል በጉዳዩ ላይ የተያዘውን የስም ማጥፋት ክስ አቅል በማሳጣት የህዝቡን አመለካከት አቅጣጫ ለማስቀየስ የታለመ ነው፡፡ አቶ አስራት በይስሙላው ፍርድ ቤት ፊት ቆመው እነርሱን ተጠያቂ ማድረጋቸው ገዥውን አካል የበለጠ እንዲበሳጭ ያደረገው መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ እስከ አሁን ድረስ ማንም የተቃዋሚ ፓርቲ አመራር ወይም በኢፍትሀዊነት ላይ የሚነሳ አመጸኛ ከገዥው አካል ከይስሙላው ፍርድ ቤት ፍትህን አይጠብቅም፡፡ ይኸ ያፈጠጠና ያገጠጠ እውነታ በአቶ አስራት ለገዥው አካል የተገለጸ የመጀመሪያ ጊዜ ኩነት ነውን?
ገዥው አካል ፍርድ ቤቶችን ለፖለቲካ መጠቀሚያ በማዋል ከህግ አግባብ ውጭ እና በማን አለብኝነት መልኩ ስልጣኑን በመጠቀም ላይ መሆኑን በማስመልከት ከብዙ ጊዜ ጀምሬ ስገልጽ እና መረጃ ሳሰባስብ ቆይቻለሁ፡፡ አ.ኤ.አ በ2007 “የዝንጀሮ የህግ ሂደት በይስሙላው ፍርድ ቤት” በሚል ርዕስ ገዥው አካል በኢፍትሀዊነት ላይ የሚነሱ አመጾችን ለመጨፍለቅ እና ትችቶችን ለማፈን ሲል ፍርድ ቤቶችን ከሰውነት በወረደ እና በተወሳሰበ መልኩ እየተጠቀመባቸው መሆኑን ጽፌ ነበር፡፡ ተቃዋሚዎች ምንም ዓይነት ስህተት ሳይሰሩ በገዥው አካል በቁጥጥር ስር ይውሉ ነበር፡፡ ስለህግ ሂደቱ ማንኛውም ነገር ሚስጥራዊ ነው…ስለክሶች፣ ስለፍርድ ቤት የችሎት ስነስርዓቶች እና ስለዳኞች፡፡ ምንም ዓይነት የህግ ዕውቀቱ የሌላቸው ዳኞች የማይታዩ አሻንጉሊት ጌቶቻቸው የሚያቀርቡላቸውን ኢፍትሃዊነት ድርጊት ለመፈጸም በችሎት ፊት ይሰየማሉ፡፡ እንደዚሁም ደግሞ ዳኞች በአዕምሯቸው አውጥተው አውርደው ፍትሃዊ ነው ብለው የሚያምኑበትን ብይን ለመስጠት ማሰብ ጊዜው ያለፈበት ውሳኔ ነው፡፡ የፍትህ መጨንገፍ በገሃድ እየተስተዋለ ነው፡፡ በወንጀለኛው የይስሙላ ፍርድ ቤት የተሰጠው የዘለፋ ብይን ያሰደነቀኝ ቢሆንም በአቶ አስራት ላይ በተሰጠው ኢፍትሃዊ ብይን አልደነቅም:: አንደዉም የኢትዮጵያ ብልህ ዳኞች በፌዝ የሚነገርላቸው የማይናገሩ ዱዳዎች የማይሰሙ ደንቆሮዎች የማያዩ አዉር ዝንጀሮችን ያስታዉሱኛል:: አቶ አስራት በባለ ሶስት ቀለበት የፍትህ ተውኔት ለቀረበባቸው የሸፍጥ “የዘለፋ” ክስ በአቋማቸው እንደጸኑ የተቃውሞ የክርክር ጭብጣቸውን በመያዛቸው ባርኔጣዬን በእጀ ከፍ አድርጌ በመያዝ ጎንበስ በማለት የተሰማኝን አድናቆት ልገልጽላቸው እፈልጋለሁ፡፡
የህግ ዘለፋና ድፍረት በኢትዮጵያ የይስሙላው ፍርድ ቤት
በመጽሄት ላይ አስተያየት አዘል ጽሁፍ መጻፍ እና በአንድ በቴሌቪዥን ለአየር በበቃ ዘጋቢ ፊልም (ያውም ፍጹም እርባና የለሽ በሆነ ፊልም) ላይ የሰላ ትችትን ማቅረብ የፍርድ ቤት ዘለፋ መድፈር ሊሆን ይችላልን? ገዥው አካል በፍርድ ሂደቱ ላይ እያካሄደ ያለውን ጣልቃገብነት እንዲያቆም ትችት ማቅረብ የፍርድ ቤት ዘለፋ መድፈር ነውን? በጥብቅ ፖለቲካዊ ይዘት በተላበሰው የፍርድ ሂደት ውስጥ ተክክለኛ እና ፍትሃዊ ብይን የማግኘቱ ሁኔታ ጥርጣሬ እና አሳሳቢነት ላይ ተመርኩዞ ሀሳብን መግለጽ የፍርደ ቤት ዘለፋ መድፈር ሊባል ይገባልን? አንድ ሰው በፖለቲካ እና በህግ ጉዳይ ላይ ያለውን አስተያየት በማቅረቡ ምክንያት የፍርድ ቤት ዘለፋ መድፈር ሊሆን ይችላልን? አንድ ሰው ህገመንግስታዊ መብቱን በመጠቀም ነጻ ሀሳቡን በመግለጹ ምክንያት የፍርድ ቤት ዘለፋ መድፈር ተብሎ ዘብጥያ ያስወርዳልን? አንድ ሰው ስለ የህግ ልዕልና እና የፍትህ እጦት አሳስቦት ቅሬታውን በማሰማቱ ምክንያት የፍርድ ቤት ዘለፋ መድፈር በማለት ለእስር የሚያበቃ ሊሆን ይገባልን? አካፋን አካፋ ማለት የፍርድ ቤት ዘለፋ መድፈር ተብሎ በእስር የሚያማቅቅ ሊሆን ይገባልን? እውነትን እና እውነትን ብቻ መናገር የፍርድ ቤት ዘለፋ መድፈር ተብሎ ዘብጥያ ሊያስወርድ ይገባልን?
በዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ የፌዴራል እና የክልላዊ ግዛት ፍርድ ቤቶች “የፍርድ ቤት ኃላፊ” ሆኘ የምሰራ ከመሆኔ አንጻር ዘለፋን አስመልክቶ በፍርድ ቤቶች መርሆዎች ላይ ጽኑ እምነት አለኝ፡፡ የህግ ሂደቶች ብቸኛ እና በሚገባ ታስቦባቸው የሚከናወኑ ስርዓቶች ስለሆኑ ማንኛቸውም በዚህ ሂደት ውስጥ በመግባት የሚሳተፉ ሰዎች ሁሉ ከልብ ሊያከብሯቸው ይገባል፡፡ ፍርድ ቤቱ የህግ ሂደቱን እያከናወነ ባለበት ጊዜ ሁሉ ሙሉ ክብሩ ሁልጊዜ ሊከበርለት ይገባል፡፡ በህግ ሂደቱ ወቅት ሊከሰቱ የሚችሉ ድንገታዊ የግንፍልተኝነት ስሜቶች፣ እና ሌሎች የፍትህ ሂደቱን ሊያውኩ የሚችሉ ነገሮች እንዲሁም የፍርድ ቤቱን ክብር ሊያጎድፉ የሚችሉ ባህሪዎች ሲንጸባረቁ እና ከፍርድ ቤቱ ውጭም ቢሆን ተገቢ የሆነውን የፍርድ ቤቱን ትዕዛዝ የሚጻረሩ ነገሮች በተፈጸሙ ጊዜ የህግ ዘለፋ ተብለው በህግ አግባብበ ብቻ መስተናገድ እንዳለባቸው በህግ ማዕቀፉ በሚገባ ተደራጅተው ተቀምጠዋል፡፡
የኢትዮጵያ የወንጀለኛ መቅጫ ስነስርዓት ህግ ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ ጊዜን ያስቆጠረ ቢሆንም ምንም ዓይነት ለውጥ ወይም መሻሻል ሳያደርግ በመተግበር ላይ ይገኛል፡፡ ፍርድ ቤትን መዘለፍ መድፈር በሚል የተጣሉት ቅጣቶች “የኢትዮጵያ የወንጀለኛ መቅጫ ስንሰራት” በሚል በንጉሱ ዘመን (በአዋጅ ቁጥር 185 በ1996 የተሸሻለው) በአንቀጽ 443 ስር ገና ቀድሞውኑ የተካተቱ ህጎች ሆነው ይገኛሉ፡፡ የዚህ ህግ የመጀመሪያው ቋንቋ በቀጣይነት “በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የወንጀለኛ መቅጫ ህግ” (አዋጅ ቁጥር 414/2004) በአንቀጽ 449 ቃል በቃል እንዲካተት ተደርጓል፡፡ የፍርድ ቤት ሂደቱ እየተካሄደ ባለበት ጊዜ አንድ ሰው በፍርድ ቤቱ ላይ ዘለፋ መድፈር ቢያካሂድ ይህንን በማስመልከት አንቀጽ 449 ለፍርድ ቤቶች የሚከተለውን ስልጣን ይሰጣል፣ “በፍርድሂደቱጊዜፍርድቤቱበመጠየቅላይእንዳለ፣ የፍርድ ሂደቱ በመካሄድ ላይ እንዳለ ወይም ደግሞ ፍርድ ቤቱ የክስ ጉዳዩን በመስማት ላይ እንዳለ፣ በማንኛውም መንገድ የስድብ ዘለፋ የሰነዘረ፣ የማፌዝ ድርጊት የፈጸመ፣ የማስፈራራት ድርጊት የፈጸመ እና የፍርድ ሂደቱ እየተካሄደ ባለበት ሁኔታ ላይ ፍርድቤቱወይምዳኛው ተግባራቸውንበመወጣትላይእንዳሉ ሁከት የፈጠረ …“ (የተሰመሩት አጽንኦ ለመስጠት የተደረጉ ናቸው)
የዘለፋ ቅጣቶች ተፈጻሚነት የሚኖራቸው አንድ ሰው “ፍርድ ቤቱ ቀርቦ በፍርድ ሂደት ሆኖ ጥያቄ በማቅረብ ላይ እንዳለ፣ በክስ ሂደቱ ላይ ወይም ክስ በመስማት ላይ እያለ” አንድ ሰው ስነምግባር በጎደለው መልክ ህጉን በሚጻረር ሁኔታ ከተንቀሳቀሰ/ች ብቻ ነው፡፡ በፍርድ ቤቱ የፍትህ ሂደቱ ከሚከናወንበት ቢሮ ውጭ ከሆነ ግልጽ የሆነ የፍርድ ቤት ትዕዛዝን በመቃወም ለመፈጸም ፈቃደኛ ባለመሆን እምቢተኝነት ካልተንጸባረቀ በስተቀር ይኸ ቅጣት ተፈጸሚነት አይኖረውም፡፡ አቶ አስራት “ከህግ የፍትህ ሂደት ጥያቄ ወይም ከፍትህ ሂደቱ” ውጭ በጻፉት ማንኛውም ዓይነት ጽሁፍ የፍርድ ቤት ዘለፋ መድፈር በሚል ሰበብ ተጠያቂ ሊሆኑ አይችሉም፡፡ በይበልጥም ደግሞ የእርሳቸው ትችት በምንም ዓይነት መልኩ በአንቀጽ 449 ስር በተደነገገው መሰረት “የፍርድ ቤት ዘለፋ” ተብሎ ሊፈረጅ አይችልም፣ ምክንያቱም አቶ አስራት “ፍርድ ቤቱ የፍርድ ሂደቱን እያከናወነ ባለበት ጊዜ አልተሳደቡም፣ አላፌዙም፣ አላስፈራሩም፣ ወይም ደግሞ በፍርድ ቤቱ ወይም በዳኛው ላይ ስራ ሊያደናቅፍ የሚያስችል ሁከት አልፈጠሩም…“ ጉዳዩን በተናጠል እና ከሁኔታዎች ጋር አስተሳስረን ስንመለከተው የአቶ አስራት ትችቶች ያነጣጠሩት በፍርድ ቤቱ ላይ አልነበረም፣ ሆኖም ግን በተጨባጭ ትችታቸው ያነጣጠረው በስርዓቱ ቁንጮዎች ላይ ሆኖ ገዥው አካል ከፍትህ ስርዓቱ ጋር በተያያዘ መልኩ እያካሄደ ያለውን አጧዥነት፣ ጣልቃገብነት፣ እና በአጠቃላይ በፍትህ ስርዓቱ ላይ እያደረገ ያለውን ብልሹነት የተንሰራፋበት ስርዓት ለመሸንቆጥ ነበር፡፡ በአጠቃላይ መልኩ ሲታይ አቶ አስራት ከፍርድ ቤት የቢሮ ስነስርዓት ማዕቀፍ ውጭ ሆነው የፍትህ ስርዓቱ በፖለቲካው ጣልቃገብነት ተተብትቦ ያለ መሆኑን በአንድ መጽሄት ላይ የሚሰማቸውን ሀሳባቸውን ገለጹ እንጅ ሌላ የፈጸሙት ነገር የለም፡፡
አንዱ ከይስሙላ ፍርድ ቤቶች ጋር በተያያዘ መልኩ ሊጤን እና ግንዛቤ ሊያዝበት የሚገባው ጉዳይ በፖለቲካ እይታ መስፈርት ከማይገባቸው የስልጣን ወንበር ላይ በተቀመጡ “ዳኞች” አማካይነት በፍትህ ስርዓቱ ላይ የሚፈጸመው ከህግ አግባብ ውጭ እና ስልጣንን መከታ በማድረግ ለቡድናዊ የፖለቲካ ጠቀሜታ ሲባል ፍትህን የማጨናገፉ ሁኔታ ነው፡፡ በጥላቻ የተሞላ ስልጣናቸውን አላግባብ በመጠቀም አቶ አስራትን ዘብጥያ የጣለው “ፍርድ ቤት” አንድነት ለዴሞክራሲ እና ለፍትህ ፓርቲ እና ገዥው አካል ከፖለቲካ እይታቸው አንጻር ገብተውበት ባለው ውዝግብ ላይ ትክክለኛ ባልሆነ መንገድ ለገዥው አካል ፖለቲካዊ ወገንተኝነት በማሳየት እራሱን ከፖለቲካ ጉዳይ ጋር አዛምዶ ተገኝቷል፡፡ በጨዋ አነጋገር ሆን ብሎ አስቦበት እና በተሰላ ስሌት መሰረት የህግ እና የስነ ምግባር ግዴታዎቹን ወደ ጎን አሽቀንጥሮ በመጣል እና እራሱን ከፖለቲካ ውስጥ የዘፈቀ ፍርድ ቤት እራሱ ፍትህን የዘለፈ ፍርድ ቤት ነው፡፡
ህጋዊ የፍትህ ስልጣን ያለው አካል በቀማኛ ወንጀለኞች ሲጠለፍ ማየት በጣም የሚያስገርም ጉዳይ ነው፡፡ እስቲ አስቡት እብዶች የእብድ ሀኪም ቤቱን ሲያስተዳድሩት፣ እንዲሁም እስቲ አስቡት ወንጀለኞች ፍርድቤቱን በ ኃይል ጠልፈው እንዳሻቸው ሲዳክሩበት፡፡ በኢትዮጵያ የተዘረጋው “የፍትህ” ስርዓት የዘራፊዎች እና የወሮበሎች ዋነኛ መጠቀሚያ መሳሪያ መሆኑን ማንም ያውቃል፡፡ የአቶ አስራትን “ጉዳይ” የያዘው ፍርድ ቤት እውነትን ለማንሸራሸር ፍትህን ለመስጠት አቅም የሌለው ሽባ ነው፡፡ ይልቁንም ይህ ፍርድ ቤት የገዥውን አካል የተቃዋሚ ወገኖች ለማጥቂያነት እየዋለ ያለ የፖለቲካ መሳሪያ ነው፡፡
እስቲ ስለየይስሙላው ፍርድ ቤት “የፍትህ ዘለፋ ድፍረት” ጥቂት እንነጋገር
ስለፍትህ ዘለፋ እስቲ እንነጋገር፡፡ ለሁለት አስርት ዓመታት በቅርቡ ያረፉት አቶ መለስ ዜናዊ እና አሁን በስልጣን ላያ ያሉት ተኪዎቻቸው ፍትህን በመዘለፍ በመድፈር ላይ ይገኛሉ፡፡ የፍትህ ስርዓቱን እና ፍርድ ቤቶችን ለፖለቲካ ዓላማቸው ማስፈጸሚያ እና የፖለቲካ ተቀናቃኞቻቸውን ለማጥቃት እና ለመቅጣት ከህግ አግባብ ውጭ ስልጣናቸውን በመጠቀም ከህግ ውጭ በመንቀሳቀስ ሲጠቀሙባቸው ቆይተዋል፡፡ የአገር ክህደት እና አሸባሪነት በሚል የውሸት ክሶችን በመመስረት የፖለቲካ ተቀናቃኞቻቸውን ለመወንጀያነት ፍርድ ቤቶችን ተጠቅመውባቸዋል፡፡ ከህግ አግባብ ውጭ በርካታ የአገሪቱን ዜጎች በእስር ቤቶች በማጎር በማሰቃየት ላይ ይገኛሉ፡፡ ዜጎች የንብረት ባለቤትነት ዋስትና እንዲያጡ የፍርድ ቤቶችን በመሳሪያነት ይጠቀማሉ፡፡ ከማንኛውም የህግ ተጠያቂነት ለማምለጥ ፍርድ ቤቶችን መደበቂያ ዋሻ አድርገው ይጠቀማሉ፡፡ የሀሰት የሙስና ክስ በመመስረት የዱሮ የመከላከያ ጓዳቸውን ለማግለል እና አቅም ለማሳጣት ፍርድ ቤቶችን ተጠቅመዋል፡፡
እ.ኤ.አ በጥር 2012 በማንኛውም የሰለጠነ የፍትህ ስርዓትን በሚያራምድ የፍትህ አካል ሊሳቅበት እና ሊወረወር በሚገባ የልጆች ጨዋታ “ማስረጃ“ በጋዜጠኛ ርዕዮት ዓለሙ እና ውብሸት ታዬ ላይ በፍርድ ቤት ክስ ተመስርቶባቸዋል፡፡ ርዕዮት ለመጽሄት የሚሆን ጽሁፍ በመጻፍ በድረ ገጽ ላይ እንዲታተም አድርጋለች፣ ከሌሎች ጋዜጠኞች ጋር የኢሜል ጽሁፍ ልውውጦች እና የስልክ ግንኙነት አድርጋለች በማለት የውንጀላ ክስ ተመስርቶባታል፡፡ ይህንን በማቀነባበር የ14 ዓመታት የእስር ቅጣት ሲፈረድባት የ33 ሺ ብር ቅጣትም ተጥሎባታል፡፡ የጉዳዩን አሳሳቢነት ከግምት ውስጥ በማስገባት አምነስቲ ኢንተርናሽናል የሚከተለውን መግለጫ አውጥቷል፣ “[ርዕዮት እና ውብሸት] ጥፋተኛ ሊያሰኝ የሚችል ምንም ዓይነት የወንጀል ድርጊት ለመፈጸማቸው የሚያስረዳ መረጃ የለም፡፡ በመንግስት ላይ ህጋዊ መስመርን በመከተል ትችት በማቅረባቸው ለቅጣት ሰለባነት መዳረጋቸውን እና የህሊና እስረኞች መሆናቸውን ነው የምናምነው፡፡ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በአስቸኳይ ከእስር መለቀቅ አለባቸው“ በማለት ነጻ ስለመሆናቸው ምስክርነቱን ሰጥቷል፡፡ በተመሳሳይ መልኩ ሂዩማን ራይትስ ዎች የተባለው ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅት ለእስር የተዳረጉት ጋዜጠኞች ነጻ መሆናቸውን ለመግለጽ እንዲህ የሚል መግለጫ አውጥቷል፣ “በቀረበው የክስ መዝገብ መሰረት በዋናነት በተደረጉ ውይይቶች በተለይም በሰላማዊ መንገድ የተቃውሞ እርምጃዎችን መውሰድ ያስፈልጋል መባሉ ከሽብር ተግባራት ጋር የሚያያይዘው ነገር የለም፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ተከላካዮቹ የተከሰሱባቸው ዝርዝር የወንጀል ጉዳዮች በመጀመሪያው ዋናው የክስ መዘገብ ላይ የሚታዩ አይደሉም…“ የርዕዮት እና የውብሸት ውንጀላ ሂደትን መሰረት በማድረግ የተሰጡ ብይኖች የይስሙላውን ፍርድ ቤት የፍትህ ዘለፋ መድፈርያ ማሳያ ማስረጃዎች ናቸው!
አ.ኤ.አ በሰኔ 2012 እስክንድር ነጋ “ዕቅድ በመንድፍ፣ ዕቅዱን ለመፈጸም በመዘጋጀት፣ የዱለታ ስራ በማካሄድ፣ ሁከት ለመፍጠር በመዘጋጀት እና የሽብር ተግባራትን ለመፈጸም“ በሚል ውንጀላ ተከስሶ 18 ዓመታት የእስር ቅጣት ተፈረደበት:: በእስክንድር ነጋ ላይ የቀረበው የውንጀላ ማስረጃ በትክክል ሊሰማ የማይችል የስልክ ምልልሶች ቅጅ እና ሌሎች አስተያየቶች እንዲሁም በአንድ የስብሰባ አዳራሽ ውስጥ በአረብ አገሮች እና በኢትዮጵያ መካከል ያሉትን ልዩነቶች በማብራራት እስክንድር አወያይ ሆኖ ያቀረበውን እና በይፋ በቪዲዮ ተቀርጾ የነበረውን የቪዲዮ ቅጅ ማስረጃ አድርጎ በማቅረብ ነበር፡፡ እስክንድር ለነጻው ፕሬስ መከበር እየከፈለ ያለውን መስዋዕትነት እና ታላቅ ተጋድሎ ከግንዛቤ በማስገባት ሙሉ በሙሉ በሚባል መልኩ ታላላቅ የዓለም አቀፍ የፕሬስ ድርጅቶች ታላቅ ክብር ተችሮታል፡፡ እ.ኤ.አ በጃኗሪ 2014 ዓለም አቀፍ የጋዜጦች እና የዜና አሳታሚዎች ማህበር/World Association of Newspapers and News Publishers የተባለው ዓለም አቀፍ ድርጅት ታዋቂ የሆነውን የ2014 ዓለም አቀፍ ወርቃማ የነጻነት ብዕር/Golden Pen of Freedom ሸልሞታል፡፡ በድረ ገጽ መረብ ሀሳቦቹን የሚያካፍልን ጋዜጠኛ ለ18 ዓመታት እስር ዘብጥያ ማውረድ የይስሙላው ፍርድ ቤት እያደረገ ያለው የፍትህ ዘለፋ ድፍረት ነው፡፡
እ.ኤ.አ በኦክቶበር በ2011 ጆሀን ፔርሶን እና ማርቲን ሽብዬ የተባሉ የስዊድን ዜጎች ሆነው ለሌሎች ድርጅቶች የሚሰሩ ጋዜጠኞች በሙያቸው የምርመራ ስራ በመስራት ላይ እንዳሉ አቶ መለስ “በሽብርተኝነት” በመወንጀል ጥፋተኛ አድርገዋቸዋል፡፡ አቶ መለስ ጆሀን ፔርሶን እና ማርቲን ሽብዬን የሽብርተኛ ድርጅት አስፈጻሚዎች እና ተባባሪዎች ናቸው በሚል ፈርጀዋቸዋል፡፡ እንዲህ ሲሉም ተናግረዋል፣ “ቢያንስ ቢያንስ የሽብርተኛ ድርጅት ተላላኪዎች ናቸው፡፡ ጋዜጠኞችም አይደሉም፡፡ ጋዜጠኛ ለምንድን ነው ከአሸባሪ ድርጅት ጋር የሚገናኘው እና በእነዚያ በታጠቁ አሸባሪዎች ከለላነት ወደ አገር ውስጥ የሚገባው እና ከአሸባሪዎች ጋር ተቀላቅሎ አብሮ የሚዋጋው? ጋዜጠኝነት ያ ከሆነ እኔ ሽብርተኝነት ምን እንደሆነ አላውቅም ማለት ነው፡፡“ በማለት ስላቅ ተናግረው ነበር፡፡
አቶ መለስ ጆሀን ፔርሶን እና ማርቲን ሽብዬ ጥፋተኛ መሆናቸውን በይፋ ከገለጹ በኋላ አጠቃላይ የፍትህ ሂደቱ ቀልድ መሆኑን በተግባር አሳዩ፡፡ የፍትህ ሂደቱ “የታዕይታ የፍትህ ሂደት” ሆነ፡፡ ዳኞቹ በአለቆቻቸው የተነገራቸውን ብቻ የሚፈጽሙ አሻንጉሊቶች ሆኑ፡፡ በአጭሩ አቶ መለስ ጆሀን ፔርሶን እና ማርቲን ሽብዬን የሚዳኘው ፍርድ ቤታቸው በህግ እና በህግ ብቻ የሚመራ ሳይሆን በገዥዎች ፈቃድ ብቻ እንደ ቅሪላ የሚነፋ እና የሚተነፍስ የይስሙላ ፍርድ ቤት መሆኑን ለዓለም ህዝብ በግልጽ አስመሰከሩ፡፡ አቶ መለስ ሁለቱን ጋዜጠኞች “የሽብርተኛ ድርጅት ተላላኪዎች ናቸው” በማለት አስረግጠው ካወጁ በኋላ በኢትዮጵያ ምን ዓይነት ዳኛ ነው (ከብርቱካን ሚደቅሳ በስተቀር) ከአቶ መለስ በተቃራኒ በመቆም “አቶ መለስ! የጋዜጠኞችን በህግ ፊት ነጻ የመሆን መብታቸውን በመንፈግ በፍርድ ቤቱ ላይ ዘለፋ ድፍረት እየፈጸሙ ነው! የተከሰሱትን ዜጎች ህገመንግሰታዊ መብት ዋጋ በማሳጣት በፍትህ ላይ ዘለፋ ድፍረት እያደረጉ ነው!“ በማለት ስብዕናውን የሚያስከብር እና የፍትህ ጀግንነቱን የሚያስመሰክረው?
እ.ኤ.ኤ በ2009 የአቶ መለስ ቁንጮ ሎሌዎች “ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናትን ለመግደል እና የቴሌኮሙኒኬሽን እና የኤሌክትሪክ አገልግሎቶችነ ለማቋረጥ እና ለማውደም እንዲሁም በአገሪቱ ውስጥ ሁከት እና ዕልቂት ለመፍጠር ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር ተንቀሳቅሰዋል” ያሏቸውን 40 የሚሆኑ “በድፍረት የተሞሉ ወንጀለኞች” ፈርጀው አቀረቡ፡፡ “ሁሉም” የፍርድ ሂደታቸው ታዬ እናም “ተወነጀሉ”: የረዥም ጊዜ እስራት ተበየነባቸው፡፡ ለአቶ መለስ የፍርድ ሂደት ማለት የሰርከስ ተውኔት አዘጋጅቶ ከማሳየት ባልተናነሰ መልኩ እንደዚያ የቀለለ ከመሆን ያለፈ ፋይዳ የለውም፡፡ ምናልባትም የምዕራቡ ዓለም ለጋሾች ድርጊቱን በተሻለ መልክ እያወቁ ከአቶ መለስ የሚያገኙት ጥቅም እስካልነጠፈ ድረስ ከአቶ መለስ ጋራ አብሮ መጓዝን በመምረጥ አይተው እንዳላዬ ሰምተው እንዳላሰሙ በመቁጠር ጆሮ ዳባ ብለዋል፡፡ ያም በይስሙላው ፍርድ ቤት ላይ የቀረበ የፍትህ ዘለፋ መድፈር ነው!
እ.ኤ.አ በዴሴምበር 2008 አቶ መለስ በኢትዮጵያ ታሪክ የመጀመሪያዋ ሴት የፖለቲካ መሪ የሆነችውን ብርቱካን ሚደቅሳን በድንገት በቁጥጥር ስር በማዋል ቀደም ሲል ተቀብላ የነበረውን ይቅርታ ክዳለች በማለት የሸፍጥ ክስ በመመስረት በፈጣን ጊዜ ውስጥ ለእስር ቤት ዘብጥያ ወረወሯት፡፡ ለይስሙላም ቢሆን እንኳን ጉዳዩ በይስሙላው ፍርድ ቤት እንዲታይ ዕድል ለመስጠት ፈቃደኛ አልነበሩም፡፡ አቶ መለስ ከመንገድ በማሳፈስ በቀጥታ ወደ እስር ቤት ለብቻዋ እንድትታሰር ከወረወሯት በኋላ ከጥቂት የእስር ጊዜ ቆይታ በኋላ እንዲህ የሚል ስላቅ አስተላልፈዋል፣ “ብርቱካንን ለመፍታት ከማንም ጋር የሚደረግ ድርድር አይኖርም፡፡ በፍጹም፡፡ አራት ነጥብ፡፡ ያ የሞተ ጉዳይ ነው፡፡“ አምባገነኑ አቶ መለስ የእርሳቸውን የሌብነት እና በጥባጭነት ባህሪ ሳትፈራ የተጋፈጠች ብቸኛ ሴት ላይ ባደረባቸው ከፍተኛ ንዴት ምክንያት በይስሙላው ፍርድ ቤት እንኳ ለይስሙላ ለማስመሰል ዕድል መስጠት ሽንፈት መስሎ ታያቸው፡፡ እ.ኤ.አ በዴሴምበር 2010 ይቅርታ እንድትጠይቅ ካስገደዱ በኋላ “ይቅርታ” አደረጉላት፡፡ አንድ የፖለቲካ ተቃዋሚን ከህግ አግባብ ውጭ ዘብጥያ በመወርወር የስሜታዊነት እና የጥላቻ ሃራራው ቀዝቀዝ ሲልለት ይቅርታ እንዲጠይቁ ማስገድድ የፍትህ ዘለፋ መድፈር ነው!
እ.ኤ.አ በ2005 የአገሪቱን ታላላቅ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎችን እና የበርካታ ጋዜጦች አዘጋጆችን ወደ ዘብጥያ ከወረወሩ በኋላ እንዲህ በማለት አወጁ፣ “ለእኛ እነዚህ በእርግጠኝነት ጋዜጠኞች አይደሉም፡፡ የፕሬስ ህጉን ተጻረዋል በሚል ክስ የሚመሰረትባቸው አይሆንም፡፡ ክስ የሚመሰረትባቸው እንደ ቅንጅት ለአንድነት እና ለዴሞክራሲ አመራሮች በአገር ክህደት ወንጀል የሚፈለጉት ናቸው… የቅንጅት ለአንድነት እና ለዴሞክራሲ አመራሮች በኢትዮጵያ የወንጀለኛ መቅጫ ህግ መሰረት በአገር ክህደት ወንጀል መንግስትን በኃይል ለመገረሰስ በመንቀሳቀሳቸው ያስከስሳቸዋል፣ በህግ ፊት እንዲቆምም እናደርጋለን፡፡“ ብለው ነበር፡፡ አቶ መለስ አስቀድመው እንደተነበዩት በቅንጅት አመራሮች ላይ በይስሙላው ፍርድ ቤት ክስ ተመሰረተባቸው፣ ወንጀለኛ ተብለውም ብይን ተላለፈባቸው፡፡ ያ በይስሙላው ፍርድ ቤት የፍትህ ዘለፋ ድፍረት ነው!
እውነታው ሲታይ ግን የኢትየጵያ “ፍርድ የኢትዮጵያ ፍርድ ቤቶች የይስሙላ ፍርድ ቤት ትክክለኛ ማሳያዎች መሆናቸውን ማንኛውም ኢትዮጵያዊ የሚያውቀው ጉዳይ ነው፡፡ በተቃዋሚ ፓርቲ ቡድኖች፣ በኢፍትሃዊነት ላይ በሚያምጹ አመጸኞች፣ እና በሌሎች ላይ ፍትህን እንዲሰጡ ዳኞች ተብለው የሚሰየሙት የፍትህ ካባን የደረቡ የገዥው ፓርቲ ደጋፊዎች እና ታማኝ ታዛዦች ና ሎሌዎች ናቸው፡፡ ይህ አባባል በተቃዋሚ ቡድን ወይም ግለሰብ ብቻ የተሰጠ ድምዳሜ አይደለም፡፡ የዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ መንግስት እና ሌሎች በርካታ ዓለም አቀፋዊ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ያረጋገጡት ጉዳይ ነው፡፡ ለምሳሌም ሂዩማን ራይትስ ዎች የተባለው ዓለም አቀፋዊ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅት እ.ኤ.አ በ2007 ባወጣው ዘገባ እንዲህ የሚል ድምዳሜ ሰጥቶ ነበር፣ “ታላላቅ በሆኑ በህግ የተያዙ ጉዳይች ላይ ፍርድ ቤቶች በጣም የተመናመነ ነጻነትን ያሳያሉ፣ ወይም ደግሞ በህግ ከለላ ጥላ ስር ባሉ ተከሳሶች የህግ ስነስርዓት ሂደቶች ላይ የሳሳ የምንግዴለሽነት ባህሪያትን ያንጸባርቃሉ… የህግ ስርዓቱ በጣም ረዥም ቀጠሮዎችን ከሰጠ በኋላ ነው ጉዳዮችን የሚያየው፣ ይህም የሚሆነው አንዳንድ ጊዜ በፍርድ ቤቶች የስራ መደራረብ ጫና ምክንያት በይበልጥም ደግሞ ከፍተኛ የሆነ ማስረጃ ይፈለግባቸዋል ተብሎ በሚያዙ ጉዳዮች ላይ ከፍተኛ የሆነ ጊዜን እና የተንዛዙ ቀጠሮዎችን በመጠየቃቸው“ የሚሉ ናቸው፡፡ እ.ኤ.አ የ2010 የዩናይትድ ስቴትስ የመንግስት መምሪያ የሰብአዊ መብት አያያዝ ባወጣው ዓመታዊ ዘገባው መሰረት የሚከተለውን መደምደሚያ ሰጥቷል፣ “የአገሪቱ ህግ የፍትህ ስርዓቱ ነጻ ሆኖ እንዲሰራ ይፈቅዳል፡፡ የሲቪል ፍርድ ቤቶች በአብዛኛው በሚባል መልኩ ነጻ ሆነው የሚሰሩ ቢሆንም የወንጀል ፍርድ ቤቶች ግን ደካማ ሆነው፣ በስራ ጫና ተወጥረው እና ለፖለቲካ ጣልቃገብነት እና ተጽእኖ ተጋልጠው የሚገኙ ናቸው“ በማለት ዘገባውን ቋጭቷል፡፡ የወንጀለኛ ፍርድ ቤት የፍትህ ሂደት ስርዓት በከፍተኛ ሁኔታ ለፖለቲካ ጣልቃገብነት ከተጋለጠ ይህ የፍትህ ዘለፋ ነው!
የኢትዮጵያ ፍትህ ወይስ “ለኛ ብቻ የግል ፍትሕ”?
ከብዙ ጊዜ ጀምሬ “ህዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ” የተባለው ድርጅት ያነበረውን “የፍትህ ዘርፍ” በማስመልከት አሳፋሪ፣ ሙሰኛ እና ምናባዊ መሆኑ ላይ ትኩረት አድርጌ ትችት አቅርቢያለሁ:: እንዲሁም የቀልድ ፍትሕ ስርዓት መሆኑን አጋልጫለሁ፡፡ በኢትዮጵያ “የፍትህ ስርዓት” ህግ ሆኖ ተቀባይነት እንዲኖረው ማሰብ በገበያ ቦታ ሄዶ “ፍትህ” በአንድ ሰው ቀጥሎም በአንድ ፓርቲ በአሁኑ ጊዜ ደግሞ ማንነታቸው በማይታወቁ፣ በስም የለሾች፣ ፊተ ድብቆሽ ታማኝ ሎሌዎች፣ በስልጣን ጥላ ስር በመደበቅ ለመራመድ የሚፈልጉ ኃይሎች ጠቅላይነት የሚገዛ እና የሚሸጥ ሸቀጥ ከመሆን ያለፈ ሆኖ አይገኝም፡፡ የፍትህ ስርዓቱ ሙሉ በሙሉ ማጭበርበር የተሞላበት፣ ምዕናባዊ ፍትህ የታጨቀበት፣ በእጅ ተለቅመው የተቀመጡ መሃይም ዳኞች የሞሉበት፣ ክህሎቱ የሌላቸው ሰዎች የተሰየሙበት፣ የሸፍጥ አሰራር ያለበት እና የፍትህ ውጤቱም ምን ሊሆን እንደሚችል አስቀድሞ የተወሰነበት ስርዓት ነው፡፡ ዓለም አቀፍ የህግ መርሆዎች እና ፍትህ የተነፈገበት፣ ወደጎን የተወረወሩበት፣ መልካም ነገር ከማድረግ የታቀቡበት፣ እና ውጤታማ ያልሆነ የፍትህ ስርዓት ነው፡፡ ድሆች፣ ከማህበረሰቡ የተገለሉ ሰዎች፣ ተስፋ ያላቸው ጋዜጠኞች፣ በኢፍትሃዊነት ላይ የሚነሱ አመጸኞች፣ የተቃዋሚ ፓርቲዎች እና የሲቪክ ማህበረሰብ መሪዎች ትችቶች፣ አስቸኳይ ምላሽ የሚፈልጉ ጥያቄዎች፣ እና ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ያልተሳኩ ጩኸቶች የሚያሰሙ ቢሆንም ቅሉ ሁሉንም ነገር በህግ መሰል መሳሪዎች እየገደሉ ጉዞ የሚያደርግ የፍትህ ስርዓት ነው የተዘረጋው፡፡ የገዥው አካል አመራሮች፣ ቤተሰቦቻቸው፣ ጓደኞቻቸው እና አደግዳጊዎቻቸው ከህግ በላይ የሆኑበት እና ፍትህ ማለት ለኛ ብቻ የግል ፍትሕ ነው ብለው የሚያስቡ ፍጡሮች የተሰገሰጉበት የፍትህ ስርዓት ነው ያለው፡፡
የኢትዮጵያን “ለኛ ብቻ የግል ፍትሕ” ፍትህ ስነስርዓትን ማሻሻል
እ.ኤ.አ በ2008 ብሄራዊ የፍትህ ተቋም ለካናዳ ዓለም አቀፍ የልማት ድርጅት/National Justice Institute for Canadian International Development Agency የተባለ ድርጅት “ነጻነት፣ ግልጸኝነት፣ እና ተጠያቂነት በፍትህ ስርዓቱ“ በሚል ርዕስ አጠቃላይ የሆነ ጥናት በማድረግ 33 ተግባራዊ የሚሆኑ የመፍትሄ ሀሳቦችን ያካተተ የጥናት ዘገባ አቀረበ፡፡ ቁልፍ ከሆኑ የተሰጡ የመፍትሄ ሀሳቦች የሚከተሉት ይገኙባቸዋል፣ 1ኛ) የፍትህ ነጻነት መርሆዎች እና መብቶች በዳኞች እና በባለስልጣኖች እንዲተገበሩ ግፊት ማድረግ፣ 2ኛ) ጠንካራ እና ግልጽ የሆነ የሰራተኛ የመምረጫ ስርዓት በመዘርጋት በጣም ጠቃሚ የሆኑ “የፍትህ” ሰራተኞች ለመምረጥ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ማድረግ፣ 3ኛ) “ገለልተኛ የሆኑ፣ የስራ ብቃት ያላቸውን ዳኞች [ለጥበቃ] ከተጽእኖ እና ከሙስና እንዲሁም ለኢትዮጵያውያን ዜጎች ቀልጣፋ የፍትህ ስርዓት ለማረጋገጥ ዋስትና መስጠት”፣ 4ኛ) “በህዝቡ ዘንድ ታማዕኒነት እንዲኖረው የፍትህ ስርዓቱን የማሻሻል ስራዎች በተሳካ ሁኔታ ተግባራዊ ማድረግ“፣ 5ኛ) “ለፍርድ ቤት ሰራተኞች ተገቢ የሆነ የስነምግባር ስልጠና” መስጠት፡፡ ማንም የገዥው አካል አባል ትንሽ እንኳ ጊዜ በመስጠት የጥናቱን ዘገባ እና ግኝቶችን በማንበብ ቢያንስ ጥቂቶችን የተሰነዘሩ የመፍትሄ ሀሳቦችን ወደ ተግባር ያሸጋግራል የሚል ጥርጣሬ አንክዎን የለኝም፡፡ ከገዥው አካል ፍትሕን መሳለቅያ ከማድረግ ሌላ ብዙም ቁምነገር አልጠብ ቅባቸዉም፣ ለዚህም ነው በኢትዮጵያ የፍትህ ስርዓት መሻሻሎች ሊፈጠሩ ይችላል የሚል አምነት የለለኝ የማልጠብቀዉም፡፡ የይስሙላው “ህዝባዊ ወያኔ ሐርነት ትግራይ ፍርድ ቤት የትኛውንም ዓይነት ሌላ ስም ቢሰጠውም ያው የይስሙላ ፍርድ ቤት ነው፣ እናም ፍትህ “ለኛ ብቻ የግል ፍትሕ” ተብላ ትነበባለች በዝያ የዝንጀሮ የፍርድ ስርዓት፡፡
ለአቶ አስራት እና ለአንድነት ለዴሞክራሲ እና ለፍትህ ፓርቲ የማበረታቻ ቃላት
በአቶ አስራት ላይ የተመሰረተው የሸፍጥ የዘለፋ ክስ በጣም መራራ የሆነ የህግ ማስፈራሪያ ዓይነት፣ የበለጠ ግልጽ ለማድረግ የፖለቲካዊ ማስፈራሪያ ዘመቻ ለማካሄድ በልክ የተሰፋ የህግ ሽፋን ነው፡፡ የዘለፋው ክስ አቶ አስራት ወይም አንደነት ለዴሞክራሲ እና ለፍትህ ተሸማቀው አርፈው ይቀመጣሉ ወይስ ትግላቸውን ይቀጥላሉ የሚለውን ሁኔታ ለመሰለል የተደረገ ሙከራ ነው፡፡ አቶ አስራት ለተዋረደው ህግ ማመልከቻ አስገብተው ፍትሃዊነት በጎደለው መልኩ ከመሞዳሞድ ይልቅ ተቃወሟቸውን በማሰማት ትግሉን ለመቀጠል መርጠዋል፡፡ ትልቁ መልዕክት አዚህ ላይ ገዥው አካል ተቃዋሚዎችን ጸጥ እረጭ ለማድረግ፣ ለማፈን እና አፋቸውን ትርቅም አርጎ ለመለጎም “ፍርድ ቤቶችን” ከህግ አግባብ ውጭ እየተጠቀመባቸው ይገኛል፡፡
ዶ/ር ማርቲን ሊተር ኪንግ ከመብት ጉዳይ ጋር በተያያዘ መልክ እንዲህ የሚል አመክንዮ አቅርበዋል፣ “አንድ ሃይል ስሜትን በማይቆጣጠር መልክ ህግን በመጣስ እየወተወተ ጫናውን ባበዛ ቁጥር ሌላው ተጎጂ ስርዓቱን ለመስበር እና ከኢፍትሃዊነት ጋር ላለመተባበር የሞራል ግዴታን ለመጎናጸፍ ይገዳዳል“ በማለት ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡ ከቢርሚንግሃ እስር ቤት በጻፉት ደብዳቤ ዶ/ር ኪንግ እንዲህ ብለዋል፣ “ማንም ቢሆን የሚፈጽመው ተግባር ፍትሃዊ አለመሆኑን ህሊናው እየነገረው ህግን የሚጥስ እናም የእስር ቅጣቱን በፈቃደኝነት የተቀበለ እና ለህብረተሰቡ ህሊና ኢፍትሃዊነቱን እያሳዬ ያለ በእርግጠኝነት የህግን ከምንም በላይ የበላይነት የተቀበለ መሆኑን ያስገነዝባል፡፡ አንድ ሰው ህጋዊ መሆን ብቻ አይደለም የሚጠበቅበት ሆኖም ግን ለትክክለኛ ህጎችም ተገዥ የመሆን የሞራል ግዴታ አለበት፡፡ በተገላቢጦሽ አንድ ሰው ፍትሃዊ ላልሆኑ ህጎች ላለመታዘዝ የሞራል ግዴታ አለበት… ፍትሃዊ ያልሆነ ህግ በምንም ዓይነት መልኩ ህግ አይደለም፡፡“ ዶ/ር ኪንግ በቀጣይም እንዲህ ብለዋል፣ ማናቸዉም ሰው “ከጭራቃዊነት ጋር ያለመተባበር ከደግ ነገር ጋር የመተባበርን ያህል የሞራል ግዴታ አለበት፡፡“ ጋንዲ ፍትሃዊ ያልሆኑ የቅኝ ግዛት ህጎችን ላለመቀበል በመቃወም እና ለበርካታ ጊዚያት በቁጥጥር ስር እየዋሉ ለእስር ሲዳረጉ እንዲህ ብለው ጽፈዋል፣ “ኢፍትሃዊ ህግ የኃይለኛነት ዝርያ ነው፡፡ በእርሱ ሸፍጥ ለእስር መዳረግ ደግሞ የበለጠ ግፍ ነው፡፡ አሁን ደግሞ የህሊና ህግ እንዲህ ይላል፣ ኃይለኝነት በሌላ እርሱን በሚገዳደር ኃይለኝነት ሊወገድ አይገባም ሆኖም ግን ኃይልአልባ በሆነ መንገድ ነው መወገድ ያለበት፡፡ በዚህም መሰረት ህጉን በመጣስ እና በሰላማዊ መንገድ በቁጥጥር ስር በመዋል ለእስራት ተዳርጊያለሁ፡፡“
አቶ አስራት የማህተም ጋንዲን እና የዶ/ር ኪንግን መንገድ ተከትለዋል፡፡ ፍርድ ቤትን በመዘለፍ በሚል በቀረበባቸው የሸፍጥ ክስ ለመከላከል በመቃወም የሀሰት የፍርድ ሂደት የሰርከስ ተውኔት ከሚሰራው የይስሙላው ፍርድ ቤት ጋር ላለመተባበር ያላቸውን ጽኑ አቋም አስመስክረዋል፡፡ የዘለፋው ክስ ፍትሃዊ ያለመሆኑን ህሊናቸው ነግሯቸዋል፣ እናም በዚህ ኢፍትሃዊነት ላይ የህብረተሰቡን ህሊና ለማነሳሳት እንዲቻል በማሰብ “የመታሰርን ቅጣት በፈቃደኝነት ተቀብለዋል፡፡” አቶ አስራት ላሳዩት የሰለጠነ እምቢተኝነታቸው ታላቅ አድናቆት አለኝ፡፡ አቶ አስራት ላሳዩት ሰላማዊ የእንቢተኝነት ተቃውሞ አርአያነት እኛ ታላቅ ከበሬታ፣ አድናቆት እና ድጋፍ ልናደርግላቸው ይገባል፡፡ በጣም ታላቅ የሆነ ድንቅ ትምህርት አስተምረውናል፣ “ከጭራቃዊነት ጋር ትብብር ለማድረግ የሞራል ግዴታ የሌለብንን ያህል ከደግ ነገር ጋር ለመተባበር ደግሞ የሞራል ግዴታ አለብን፡፡”
አጭር መልዕክት ላንባቢ
በፍርድ ቤት ዘለፋ ሰበብ ገዥው አካል አቶ አስራትን ወደ ዘብጥያ የመወርወሩ ሁኔታ ባዘጋጀው ደጋን የመጀመሪያው የዒላማ ተኩስ መሆኑን ያመላክታል፡፡ ይህ ክስተት የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮችን እና አባላትን እንዲሁም በኢፍትሃዊነት ላይ የሚነሱ አመጸኞችን እ.ኤ.አ በ2015 ለሚያደርገው የታዕይታ አገራዊ ምርጫ ዝግጅት (ማስታወሻ፣ ምርጫ ለመስረቅ ዝግጅት አላልኩም፣ አልወጣኝም) አፍ ማስያዣ የማስጠንቀቂያ ደወል መሆኑ ነው፡፡ ገዥው አካል የተቃዋሚ መሪዎችን የጥንካሬ ስብዕና ለመለካት የተጠቀመበት ዘዴ ነው፡፡ ተቃዋሚዎች በዘፈቀደ በቁጥጥር ስር መዋል እና ለእስራቱ መዳረግ በመፍራት ገዥውን አካል ከመገዳደር ወደኋላ ሊያፈገፍጉ ይችላሉን? ስልጣናቸውን በመጠቀም የእራሳቸውን ፍላጎት በሌሎች ላይ ለመጫን ከሚቅበዘበዙ ወሮበሎች ሮጦ በማምለጥ ለመደበቅ ይሞክራሉን? ወይም ደግሞ በአንድ ላይ ቆመው እንዲህ በማለት ያውጃሉ፣ “በሰላማዊ መንገድ እንታገላለን፣ የናንተን ኢፍትሃዊ ህጎች እና የዘፈቀደ እርምጃዎች ማለትም የነጻ ሀሳብ መብቶቻችንን የሚጨቁኑትን፣ የፕሬስ ነጻነት፣ የመሰብሰብ ነጻነት፣ ነጻ እና ፍትሃዊ ምርጫዎች፣ እና መብቶቻችንን መደፍጠጣችሁን እንድታቆሙ አጥብቀን እንቃወማለን እንዲወገዱም እስከመጨረሻው እንፋለማለን!“ ወደፊት ጊዜ የሚያሳዬን ይሆናል፣ ሆኖም ግን ገዥው አካል አቶ አስራትን ለእስር በመዳረግ የመጀመሪያዋን የደጋን ዝግጅት ተኩስ የተኮሰ መሆኑን እያንዳንዱ ሰው በአጽንኦ ሊመለከተው ይገባል፡፡
የፍትህ ስርዓቱን መጥለፍ የአፍሪካ አምባገነኖች የመጀመሪያው ስልት ነው!
ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!
የካቲት 11 ቀን 2006 ዓ.ም