የኢትዮጵያን ታሪክ ጥላሸት የመቀባት አባዜ
ከፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማርያም
ትርጉም በነጻነት ለሀገሬ
በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ያለው ገዥው አካል በ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የኢትዮጵያ ንጉስ የነበሩት የዳግማዊ አጼ ምኒልክ መቶኛ የሙት ዓመት በዚህ በያዝነው ዓመት (በኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር) እየተከበረ ባለበት ወቅት ሙሉ ጊዜውን በመስጠት ንጉሱ የሰሩትን ታላቅ ስራ ሁሉ በማጣጣል እና ጥላሸት በመቀባት ዘመቻ ላይ በመጠመድ ታሪክ የማጠልሸት ድራማውን በመተወን ላይ ይገኛል፡፡ የታሪክ ማጠልሸት ዘመቻው በዋናነት እየተከናወነ ያለው ለገዥው አካል ቅርበት ባላቸው ታማኝ ሎሌዎች፣ የጥቅም ተጋሪዎች እና የእራሳቸው ስብዕና በሌላቸው አሻንጉሊቶች አማካይነት ነው፡፡ ገዥው አካል ሲያስነጥሰው መሃረብ ይዘው በሚቀርቡ አጎብዳጆቹ አማካይነት የጥላቻ መርዛማ ቃላትን፣ የሚቆጠቁጡ ባዶ ዲስኮሮችን እና እርባናየለሽ ምዕናባዊ ስዕል በአዕምሮው ላይ እየፈጠረ አጼ ምኒልክ የግዛት ማስፋፋት ጥማታቸውን ለማርካት ሲሉ በዜጎች ላይ የጭካኔ ተግባራትን እንደፈጸሙ በማስመሰል ለምንም የማይጠቅሙ እርባናየለሽ እና ተራ አሉባልታዎችን በማሰራጨት ላይ ይገኛል፡፡
የገዥው አካል ድንጉላ አገልጋዮች በማናቸውም የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች በመሰማራት ታሪካዊ ቅጥፈቶችን፣ አሳሳች ዘገባዎችን፣ የሀሰት ታሪክ ፈጠራዎችን፣ ሆን ተብሎ በሀሰት ላይ የተመሰረቱ መረጃዎችን እና ነጭ ውሸቶችን እንደ በቀቀን እየደጋገሙ በማሰራጨት ላይ ይገኛሉ፡፡ የዕኩይ ዓላማው አራማጆች በታላቁ የኢትዮጵያ መሪ ላይ ግነታዊ ኩምክና በመስራት፣ በማዋረድ እና እውነተኛውን ስብዕናቸውን ጥላሸት በመቀባት የስሜት ፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ውስጥ በመዘፈቅ ጌቶቻቸውን ለማስደሰት በታለመ ዕኩይ ምግባር ላይ ተጠምደው ይገኛሉ፡፡ የታላቁ መሪ ነብስ ከስጋቸው ከተለየች ከአንድ መቶ ዓመታት የጊዜ ቆይታ በኋላ የተቀበረን ጉዳይ በማንሳት ታላቁን መሪ ሰይጣናዊ ስብዕና እንደነበራቸው ለማስመሰል በማሰብ የዕኩይ ምግባር ጎተራዎቹ የቻሉትን ያህል ጥረት ለማድረግ ሞክረዋል፡፡ አቶ መለስ ዜናዊ በህይወት ከተለዩ ሁለት ዓመታት እንኳን ሳይሞላቸው የዕኩይ ምግባራት ቋቶቹ የኢትዮጵያ አዳኝ መልዓክ ሊያደርጓቸው ይፈልጋሉ፡፡
በአሁኑ ጊዜ በዳግማዊ አጼ ምኒልክ ላይ በተከፈተው የገፍ ወይም የኃይል የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ወይም ደግሞ የአጼ ምኒልክን የሙት መንፈስ ደጋግመው በማንሳት ፍጹም ጥላቻ እና የጥላቻ አመለካከት እንዲንሰራፋ በገዥው አካል ስልታዊ እና የተቀነባበረ ዘመቻ የማካሄድ አመክንዮ ለማንም ቢሆን ሊደንቅ አይገባም፡፡ ሀቁ አንድ እና አንድ ብቻ ነው፡፡ የኸውም የምኒልክን ስም ጥላሸት በመቀባት (ሰይጣናዊ ስብዕና በመስጠት) በሚሽከረከር ጉዳይ ላይ ብቻ የሚቆም ጉዳይ አይደለም፡፡ ነገር ግን በቅርቡ በህይወት የተለዩትን የገዥውን አካል የአለቆች ሁሉ አለቃ (Capo di tutti capi) አቶ መለስ ዜናዊን በመላዕክነት ቀብቶ ለማቅረብ የታቀደ ዕኩይ ምግባር ነው፡፡
ዳግማዊ ምኒልክን ጥላሸት የሚቀቡ ሙትመንፈሶች፣
በዳግማዊ አጼ ምኒልክ ላይ እየተካሄደ ያለው ከፍተኛ ጥላሸት የመቀባት የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ያነጣጠረው የኢትዮጵያን ታሪክ በመፋቅ በአቶ መለስ ዜናዊ የመላዕክነት የህይወት ታሪክ (የመላዕክነት ትረካ) በመተካት የታላቋን ሀገር ትክክለኛ ታሪክ እንደገና ለመጻፍ፣ አዛብቶ ለመጻፍ፣ ገልብጦ ለመጻፍ፣ አወዛግቦ ለመጻፍ፣ በመቀባባት የሚያምር አስመስሎ ለማቅረብ እና እውነተኛውን ታሪክ ለማስወገድ በመደረግ ላይ ያለ ከንቱ ሙከራ ነው፡፡ የአጼ ምኒልክን ታሪክ በመሰረዝ የዘመናችን የ”አፍሪካ ታላቁ መሪ” በማለት የመለስ ዜናዊን ታሪክ ለመጻፍ ይፈልጋሉ፡፡ በሀሰት እምነት ላይ በመመስረት መለስ “አዲሱ የአፍሪካ መሪ ዝርያ“፣ መለስ “የዴሞክራሲያዊ ልማታዊ መንግስት ቀያሽ”፣ መለስ “በዓለም አቀፋዊ የሙቀት እና የአየር ጸባይ ለውጥ የአፍሪካ ጠበቃ”፣ መለስ “ከጂ-8 እና ጂ-20 መሪዎች ጋር በመሆን ክርናቸውን የሚያሳዩ አፍሪካዊ መሪ”፣ መለስ “የቻይና-አፍሪካ የትብብር መድረክ የቤጂንግ ከፍተኛ ዲፕሎማሲያዊ ጉባኤ ሊቀመንበር”፣ መለስ የሶማሌ ጅሃዲስቶች እና አሸባሪዎች አስወጋጅ”… ተብለው ከእውነተኛ ስብዕናቸው ውጭ በሆነ መልኩ እንዲመለክባቸው ይፍልጋሉ፡፡
የታላቁን መሪ የዳግማዊ ምኒልክን ስብዕና ጥላሸት በመቀባት አቶ መለስን ቅብዓ መልዓክ (የተቀባ መልዓክ) ለማድረግ ይፈልጋሉ፡፡ ለመሆኑ አጼ ምኒልክን ጥላሸት የሚቀቧቸው ለምንድን ነው? ምክንያቱም አጼ ምኒልክ በአመራር ጥበባቸው እና በትግላቸው ግጭትን በመፍጠር ሲናቆሩ ከነበሩት ባላባቶች፣ ለስልጣን ብቻ ከሚቋምጡ ከተለያዩ አካባቢያዊ ንጉሶች፣ ከተለያዩ ልዕልቶች የቅምጥል የአገዛዝ ስርዓት፣ እና ከጎጣዊ ምስለኔዎች የተበታተነ አገዛዝ በማላቀቅ ዘመናዊቷን የአፍሪካ ብሄር ታላቋን ኢትዮጵያን በመመስረታቸው ብቻ ነው፡፡ የዕኩይ ምግባር አራማጆች አጼ ምኒልክን ጥላሸት ይቀቧቸዋል፣ ምክንያቱም ምኒልክ ታላቆቹን የአውሮፓ ኢምፔሪያሊስት ኃያላን በጦር ሜዳ ውሎ በማሸነፍ አንጸባራቂ ድል በመቀዳጀት የኢትዮጵያን ዘለቄታዊ ነጻነት ያጎናጸፉ እና የሀገሪቱን ሉዓላዊነት ያስከበሩ ጀግና መሪ በመሆናቸው ነው፡፡ ጥላሸት ይቀቧቸዋል ምክንያቱም ምኒልክ እውነተኛ የአፍሪካ መሪ በመሆናቸው ነው፡፡ የአጼ ምኒልክን ስም በማጥፋት እና ለኢትዮጵያ ህዝብ ያበረከቱትን የውርስ ትሩፋታቸውን በማንቋሸሽ ለአቶ መለስ ክብር ለመስጠት እና ከእርሳቸው የሚገኘውን ውርስ ብጹዕ/ቅዱስ ለማድረግ ይፈልጋሉ፡፡
ገዥው አካል የአጼ ምኒልክን ታሪክ በእራሱ ታሪክ ለመተካት ይፈልጋል፡፡ አጼ ምኒልክ የባቡር ሀዲድ በመዘርጋት የመጀመሪያው አፍሪካዊ መሪ ነበሩ፡፡ ይህንን አንጸባራቂ ታሪክ በመለወጥ አቶ መለስ ረዥም፣ ቆንጆ እና ቀላል የባቡር ሀዲድ ሲስተም በኢትዮጵያ ለማምጣት የመጀመሪያው መሪ ነበሩ በማለት የታሪክ ባለቤትነት ሽሚያን ለማጎናጸፍ ይፈልጋሉ፡፡ አጼ ምኒልክ የስልክ እና የቴሌግራፍ አገልግሎትን በአፍሪካ አህጉር በማስተዋወቅ የመጀመሪያው አፍሪካዊ መሪ ነበሩ፡፡ እ.ኤ.አ በ1889 አሌክሳንደር ግራህም ቤል “የድምጽ መነጋገሪያ መሳሪያ” የፓተንት ዕውቅና ካገኙበት 13 ዓመታት በኋላ እና በአጼ ምኒልክ ቤተመንግስት የመጀመሪያው የስልክ መስመር በተዘረጋበት ጊዜ በቴክኖሎጂው ሁኔታ ጭንቀት ውስጥ ገብተው የነበሩት የቤተክህነት ሰዎች ይህ የሰይጣን ስራ ነው በማለት ንጉሱ እንዲያስወግዱት በጠየቋቸው ጊዜ አጼ ምኒልክ ለቴክኖሎጂው ጠቀሜታ ካላቸው ጽኑ እምነት አኳያ ሳያስወግዱት ቀርተዋል፡፡ በአስርት ዓመታት ጊዜ ውስጥ አጼ ምኒልክ አዲስ አበባን በምስራቅ ኢትዮጵያ ከምትገኘው የሀረር ከተማ ጋር የሚያገናኝ የስልክ መስመር በመዘርጋት መርቀው ከፈቱ፡፡ ያንን አንጸባራቂ ታሪክ ወደ ጎን በማለት የአሁኖቹ ገዥዎች በኢትዮጵያ ዘመናዊ የመገናኛ ቴክኖሎጂ ሲስተምን በኢትዮጵያ ያመጡ አቶ መለስ ዜናዊ እንደሆኑ አድርገው ያቀርባሉ፡፡ እውነታው ግን በተገላቢጦሽ በአፍሪካ የስልክ እና የቴሌግራፍ መስመር በመዘርጋት ግንባርቀደም የነበረችው ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከአፍሪካ በመጥፎ የተንቀሳቃሽ ስልክ እና የኢንተርኔት አግልግሎት አጠቃቀም ሳቢያ በመጨረሻው እረድፍ ላይ ትገኛለች፡፡ ባለፈው ሳምንት የዎል ስትሪት መጽሄት/Wall Street Journal እንደዘገበው በኢትዮጵያ ውስጥ አርሶ አደሮች የተንቀሳቃሽ ስልኮች ቢይዙም “ችግሩ የግንኙነት መስመር ለማግኘት ብዙ ማይሎችን (ኪሎሜትሮችን)መጓዝ ይጠበቅባቸዋል፡፡“ በማለት የችግሩን አሳሳቢነት አመላክቷል፡፡ ኢትዮጵያ በመጥፎ የኢንተርኔት አገልግሎት አጠቃቀም ከአፍሪካ ከመጨረሻዎቹ ሀገሮች በሁለተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡
የዘመኑ ገዥዎቻችን አጼ ምኒልክ የሴቶችን ጡት ቆርጠው የሚጥሉ ጨካኝ ንጉስ እንደሆኑ አድርገው ታሪክን አዛብተው ለመጻፍ ይፈልጋሉ፡፡ ጨካኝነት ከተነሳ ዘንድ ከአቶ መለስ ዜናዊ የበለጠ ጨካኝ እና አረመኔ ይኖራልን? አቶ መለስ እራሳቸው እ.ኤ.አ በ2005 በተደረገው ሀገራዊ ምርጫ መጭበርበር ምክንያት ተቃውሟቸውን ለመግለጽ በወጡ ያልታጠቁ ሰላማዊ ዜጎች ላይ ለአነጣጥሮ ተኳሽ ጦራቸው ትዕዛዝ በመስጠት በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች እንዲገደሉ አድርገዋል፡፡ ይህንን እልቂት አስመልክቶ በእራሳቸው በአቶ መለስ ልዩ ትዕዛዝ ጉዳዩን እንዲያጣራ የተሰየመው የአጣሪ ኮሚሽን ምርመራውን አካሂዶ ባቀረበው ዘገባ መሰረት በአቶ መለስ ቀጥታ ትዕዛዝ እና ቁጥጥር አማካይነት የፖሊስ እና የደህንነት ኃይሎች በዕቅድ ተይዞ እና ሆን ተብሎ ታስቦበት 193 ሰላማዊ ሰዎች እንዲገደሉ እና ሌሎች 763 ሰዎች ደግሞ ከባድ ቁስለኛ እንዲሆኑ ተደርጓል፡፡ እ.ኤ.አ በ2004 አቶ መለስ እራሳቸው ለታጣቂዎቻቸው ትዕዛዝ በመስጠት በምዕራብ ኢትዮጵያ በጋምቤላ 400 ሰላማዊ ዜጎች እንዲያልቁ አድርገዋል፡፡ ኦጋዴን እየተባለ በሚጠራው አካባቢ የተካሄደውን የአየር ድብደባ እና መንደሮችን በማቃጠል የጥቃት ሰለባ ያደረገው ወንጀል የተፈጸመው በአቶ መለስ ስልጣን ልዩ ትዕዛዝ ነበር፡፡ በአቶ መለስ ትዕዛዝ በኦጋዴን ታጣቂ ኃይሎች ሴቶችን አስገድደው ደፍረዋል፣ መንደሮችን አቃጥለዋል፣ ህዝቡን በሽብር ቆፍን ውስጥ ለመሸበብ ሲባል “የመቀጣጫ ግድያዎችን” ማለትም በህዝብ ፊት በአደባባይ በስቅላት እንዲሁም ጭንቅላትን ቆርጦ የመጣል ወንጀሎች እንዲፈጸሙ ተደርጓል፡፡ የተባበሩት መንግስታት የሂዩማን ራይትስ ዎች ተሟጋች ዳይሬክተር/United Nations Advocacy Director for Human Rights Watch ስቴቭ ክራውሻው በኦጋዴን አካባቢ በሰላማዊ ዜጎች ላይ የተፈጸመውን ወንጀል “ትንሿ ዳርፉር” በማለት አመሳስለው ገልጸውታል፡፡
ገዥዎቻችን አጼ ምኒልክን የኦሮሞ ህዝቦች ጠላት እንደሆኑ አድርገው ታሪክን በመበረዝ የታሪክ ድሪቶ አቀነባብረው እንደገና የጎደፈ ታሪክ ለመጻፍ ይታትራሉ፡፡ አቶ መለስ በህይወት ቢኖሩ ኖሮ እሳቸው እና የዕኩይ ምግባር አጋሮቻቸው በኦሮሞ ህዝብ ላይ እስከ አሁን ድረስ ያልተነገረውን እና ለመናገር የሚዘገንነውን በሰው ልጆች ላይ የፈጸሙትን ወንጀል ወደ ፍትህ አደባባይ በማቅረብ እንዲታይ ለማድረግ ከበቂ በላይ መረጃዎች አሉ፡፡ እ.ኤ.አ በ2012 ፍሪደም ሀውስ/Freedom House የተባለው ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅት ባቀረበው ዘገባ መሰረት አቶ መለስ እና አገዛዛቸው በኦሮሞ ህዝብ ላይ ሰፊ የሆነ የአድልኦ እና የጭቆና መረብ በመዘርጋት ተግባራት ላይ ተጠምደው ቆይተዋል፡፡ አቶ መለስ የኦሮሞ ነጻነት ግንባርን እንቅስቃሴ በመገደብ ብዛት ያላቸው ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ የሚጠረጠሩ የድርጅቱን አባላት እና መሪዎችን ከህግ አግባብ ውጭ በቁጥጥር ስር በማዋል በማጎሪያ እስርቤት አስገብተው ሲያሰቃዩ ቆይተዋል፣ አሁንም በመሰቃየት ላይ ይገኛሉ፡፡ እ.ኤ.አ በ2001 የቀድሞው የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት የነበሩት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ስልጣናቸውን ሲለቁ እንደተናገሩት “ወደ 25,000 የሚሆኑ የኦሮሞ ህዝቦች ከኦሮሞ ህዝቦች ነጻነት ግንባር ጋር በተያያዘ የገዥው አካል ክስ ምክንያት በተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች እና በአዲስ አበባ ከተማ እስር ቤቶች ታስረው በመማቀቅ ላይ ነበሩ፡፡” በማለት ይፋ አድርገዋል፡፡ የመለስ የትግል ጓድ እና የቀድሞው የመከላከያ ሚኒስትር የነበሩት አቶ ስዬ አብርሃ በሚያስገርም ሁኔታ እንደተመለከቱት “ቃሊቲ እስር ቤት ኦሮምኛ ይናገራል፣ በዚሁ ግቢ በአንድ በመቶዎች የሚቆጠሩ እስረኞችን በሚይዝ ካምፕ ውስጥ 99 በመቶ የሚሆኑት እስረኞች ኦሮሞዎች ናቸው፡፡ አብዛኞቹ እስረኞች ደግሞ የታሰሩበት ምክንያት ምን እንደሆነ አያውቁም፣ ሆኖም ግን የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ተጠርጣሪ በመባል ዓመታትን በእስር ቤት በማስቆጠር ላይ ይገኛሉ፡፡“ በማለት ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል፡፡
እ.ኤ.አ በ2006 ጂሃዲስቶች (አሸባሪዎች) የሶማሌን አገር ወረዋታል እና የሶማሌ መንግስት ጣልቃ ገብቸ ጂሃዲስቶችን እንዳስወጣለት “ጋብዞኛል” በሚል ተንኮልን ያዘለ ሰበብ ምክንያት አቶ መለስ በሶማሌ አገር ላይ ወረራ አካሂደዋል፡፡ አቶ መለስ በቴሌቪዥን ቀርበው እንዲህ ብለዋል፣ “የአገራችንን ሉዓዋላዊነት ለማስከበር እና በእስልምና ፍርድ ቤቶች ህብረት እና በሌሎች ጸረ ኢትዮጵያ ኃይሎች በመታገዝ የሚያደርሷቸውን ተደጋጋሚ አደጋዎች ለመግታት ሲባል የኢትዮጵያ የመከላከያ ሰራዊት ወዳልፈለገው ጦርነት እንዲገባ ተገድዷል፡፡“ በተመሳሳይ መልኩ በዴሴምበር 27 2006 የአቶ መለስ ሰራዊት እና ታንኮች የሞቃዲሾን ከተማ ወረሩ፡፡ እ.ኤ.አ በኦገስት 2007 የአቶ መለስ ሰራዊት በሶማሌ ውስጥ የሚያደርገው እንቅስቃሴ ተገታ፣ በሰው ህይወት ላይ የደረሰው ኪሳራ አስደንጋጭ ነበር፡፡ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ንጹሃን የሶማሌ ዜጎች ህይወት የተቀጠፈ ሲሆን ከ870,000 በላይ የሚሆኑት ዜጎች ደግሞ ሞቃዲሾን ለቀው ለመሰደድ ተገደዋል፡፡ በ2006 በሞቃዲሾ ከተማ ወደ 1.2 ሚሊዮን ገደማ የሚሆን ህዝብ ነበር፡፡ ከአቶ መለስ የሶማሌ ወረራ በኋላ ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች “ከአፍሪካ በጣም አስቀያሚ አስከፊ የሰብአዊ መብት ሁኔታ ያለበት“ በማለት የሶማሌን የሰብአዊ መብት አያያዝ በተጨባጭ ገልጸውታል፡፡
አጼ ምኒልክ ከአውሮፓውያን ወራሪ ኃይሎች ጋር የመከላከል ጦርነትን በማካሄድ በድል አድራጊነት ተወጥተዋል፡፡ አጼ ሚኒልክ የአውሮፓ ኃያል ከሚባል አገር ጋር ጦርነት በማድረግ በጦር ሜዳ ድል አድርገው ወራሪው ኃይል በመጣበት እግሩ ጓዙን ጠቅልሎ እንደ ውሻ ጅራቱን በእግሮቹ መካከል ወትፎ እንዲመለስ በማድረግ በአፍሪካ ታሪክ የመጀመሪያው መሪ መሆናቸው የሚካድ ጉዳይ አይደለም፡፡ አጼ ምኒልክ ወራሪውን የኢጣልያንን ጦር አምባላጌ እና መቀሌ ላይ ድል አድርገዋል፡፡ እንዲሁም እ.ኤ.አ በ1896 አድዋ ላይ ወሳኙን ፍልሚያ በማድረግ የአድዋን ጦርነት በድል አድራጊነት ተወጥተዋል፡፡ “ኋላቀር አፍሪካውያን ጥቁሮች” ወታደሮች ኃያሉን የአውሮፓ ኢምፔሪያሊስት የጦር ኃይል ያሸንፋል የሚል እምነት በማንም አውሮፓዊ የተገመተ አልነበረም፡፡ አጼ ምኒልክ በዘመናዊ መሳሪያ ትጥቅ፣ በስልት እና በቁሳቁስ አቅርቦት በዘመኑ በጣም የተጎዱ መሪ ቢሆኑም ቅሉ የብሩህ አዕምሮ ባለቤት እና ወታደራዊ ስልት የሚያውቁ በመሆናቸው ውጊያውን በማካሄድ ጦርነቱን አሸንፈው በአንጸባራቂ ድል በመታጀብ የነጮችን የበላይነት እና አይበገሬነት ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ በማስወገድ ለጥቁር ህዝቦች በአጠቃላይ ለአፍሪካውያን ደግሞ በተለይ የኩራት ፈርጥ ለመሆን በቅተዋል፡፡ ብዙ የአውሮፓ ኃያላን አገሮች አጼ ምኒልክን በማታለል እና በማጭበርበር ከኢትዮጵያ ግዛት ቆርሰው በመውሰድ ኢትዮጵያን ቅኝ ተገዥ ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል፡፡ እ.ኤ.አ በ1889 አጼ ምኒልክ በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል የሚገኙ ግዛቶችን አስመልክቶ ከኢጣሊያ መንግስት ጋር የውጫሌ ስምምነትን አጸደቁ፡፡ በውል ስምምነት ሰነዱ የኢጣሊያንኛው ትርጉም ከኢትዮጵያ የአማርኛ ትርጉም ጋር የማይመሳሰል መሆኑን አጼ ምኒልክ እንደተገነዘቡ እና ኢትዮጵያ በኢጣሊያን ጠባቂነት የሚለውን ሀረግ ሲመለከቱ የውል ስምምነቱን በማውገዝ አፈረሱት፡፡
የገዥው አካል አፈቀላጤዎች አቶ መለስ ኢትዮጵያ የአህጉሩ ታላቅ አገር እንድትሆን ጥረት ያደረጉ እና የአህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ መሪ እንደሆኑ በማድነቅ እና ስብዕናቸውን ከፍ ከፍ በማድረግ የአሁኑን የኢትዮጵያ ታሪክ ደልዘው በእርሳቸው ተተክቶ እንዲጻፍ ነው በመዋተት ላይ የሚገኙት፡፡ አቶ መለስ የኢትዮጵያን የግዛት አንድነት እና ሉዓላዊነት ያስከበሩ መሪ እንደሆኑ አድርገው ለማሳየት ይፈልጋሉ፡፡ እውነታው ግን የተገላቢጦሹን ያመላክታል፡፡ እ.ኤ.አ ከ1998-1999 ድረስ የባድሜን የግዛት ወሰን ለማስከበር በተካሄደው የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ጦርነት የአቶ መለስ ጦር የ80,000 ኢትዮጵያውያንን ህይወት ያለምንም ወታደራዊ ስልት በጭዳነት ለመስዋዕትነት ዳርጎ ወታደራዊ ድልን ተቀዳጅቶ ነበር፡፡ በወገኖቻችን የህይወት እና ንብረት መስዋዕትነት የተገኘውን ድል ሰራዊቱ ገና አጣጥሞ ሳይጠግብ የኢትዮጵያው መሪ አቶ መለስ ከመቅጽበት በመገለባበጥ ባድሜን በዓለም አቀፋዊ የስምምነት ውል በማስቀየድ ለኤርትራ መንግስት ቡራኬ ብለዋል፡፡ በምንም ዓይነት መልኩ በየትኛውም አገር አንድ ወታደራዊ ኃይል እጅግ ከባድ መስዋዕትነትን ከፍሎ ያገኘውን አንጸባራቂ ድል ለተሸናፊው ጠላቱ በፈቃደኝነት መልሶ የሰጠበት የጦርነት ታሪክ የለም፣ ተመዝግቦም አያውቅም፡፡ እ.ኤ.አ በ1991 ወታደራዊውን አምባገነን ደርግን በትጥቅ ትግል ካስወገዱ በኋላ በአሜሪካ መንግስት አደራዳሪነት የሽግግር ስምምነቱ በሚፈረምበት ወቅት እኒሁ የኢትዮጵያው መሪ አቶ መለስ በኤርትራ የወሰን ግዛት ዳርቻ ላይ የምትገኘውን ከቀይ ባህር ጋር በመግቢያ እና በመውጫነት ለኢትዮጵያ ህዝብ የባህር በር በመሆን አገልግሎት የምትሰጠውን የአሰብን ወደብ ወደ ኢትዮጵያ ግዛት እንድትካለል የቀረበውን ሀሳብ አልቀበልም በማለት አሁንም በድጋሜ ለኤርትራ መንግስት ቡራኬ በመስጠት ይደልዎ ብለዋል፡፡ አቶ መለስ የኢትዮጵያን ግዛት ለባዕድ ኃይል በመስጠት ታላቋን አገር ወደብአልባ በማድረግ በፈጸሙት የአገር ክህደት ወንጀል ብቸኛው ተጠያቂ ናቸው፡፡ አሁንም ተከታታይነት ያለውን የትራጄዲ ድራማ በመቀጠል በሚስጥር በተደረጉ ስምምነቶች የይስሙላው ፓርላማ ለስሙ እንኳ መከረበት ሳይባል ምንም ሳይታሰብበት በጥድፊያ እኒሁ የኢትዮጵያው “መሪ” አሁንም የኢትዮጵያ አንጡራ ግዛት የሆነውን መሬት ለሱዳን መንግስት እንደ የገና ስጦታ የእጅ መንሻ ቡራኬ አድርገውታል፡፡ እኒሁ የኢትዮጵያው መሪ አቶ መለስ በድብቅ እና ታማኝነት በጎደለው መልኩ የአገሪቱን እጅግ በጣም ለም የሆነውን በሚሊዮኖች ሄክታር የሚቆጠር መሬት ዕዳቸውን እንኳ ውል ባለው መልክ ለመክፈል ለማይችሉ የአየር ባየር ጭልፊት ነጋዴዎች አሁንም ለእጅ መንሻ አቅርበዋል፡፡
አጼ ምኒልክ የኢትዮጵያን አንድነት በማጠናከር ዘመናዊ የመንግስት መዋቅር ዘርግተዋል፡፡ አቶ መለስ ግን ምዕናባዊ ዘመናዊነትን አምጥተዋል፡፡ አቶ መለስ ያለሐኪሞች እና መድኃኒት ሆስፒታል ገንብተዋል፡፡ በአንድ ወቅት ሐኪሞች አያስፈልጉንም በማለት በይፋ ተናግረዋል፡፡ ብቃት ያላቸው የዩኒቭርስቲ መምህራን እና ፕሮፌሰሮች፣ መጻህፍት፣ ቤተ መጻህፍት፣ ወይም ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ሳይኖር ዩኒቨርስቲዎችን ገንብተዋል፡፡ የመጸዳጃ ሲስተም የሌላቸውን ህንጻዎች ገንብተዋል፡፡ አጼ ምኒልክ ኢትዮጵያን የምዕራቡ ዓለም ስልጣኔ ትሩፋት ተቋዳሽ እንድትሆን አድርገዋል፡፡ አቶ መለስ “ልማታዊ መንግስት” የሚል እርባናየለሽ ህልዮት ከምስራቅ ኢስያ ሀገራት አምባገነኖች ኮርጀው በማምጣት ኢትዮጵያን ወደ ኋላ መልሰዋታል፡፡ እ.ኤ.አ በ1991 ስልጣን ከያዙ በኋላ አቶ መለስ ዘመናዊውን የኢትዮጵያ መንግስት አወቃቀር በማፈራረስ ወዲያውኑ አገሪቱን ክልል እየተባለ በሚጠራው ወይም የአፓርታይድ አይነት ባንቱስታንስ ወይም ክልሊስታንስ የተባለ የመከፋፈል ተልዕኮውን አጠናቀቀ፡፡ አቶ መለስ በሀሰት ላይ በመመስረት ባለሁለት አሀዝ የኢኮኖሚ ዕድገት አስመዝግበናል፣ እና “ኢትዮጵያ ነዳጅ ወደ ውጭ ከማይልኩ የሰብ ሰሀራ አፍሪካ አገሮች መካከል ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት የምታስመዘግብ አገር ናት” በማለት በሸፍጥ ለማሳመን በመወትወት ላይ ይገኛሉ፡፡ እውነታው ግን ኢትዮጵያ በዓለም ከሚገኙ የመጨረሻዎቹ ደኃ አገሮች ከመጨረሻው በሁለተኛ ደረጃ ላይ የምትገኝ አገር መሆኗን “ኢትዮጵያ ለምንድን ነው ደኃ የሆነችው?” በማለት ቀደም ሲል ባዘጋጀሁት ትችቴ ላይ በግልጽ አስቀምጨዋለሁ፡፡
አጼ ምኒልክ የኢትዮጵያ “ህዳሴ” መሪ ነበሩ፡፡ አገራቸውን ለማጠናከር እና ዘመናዊ ለማድረግ ወሳኝ የሚባሉ እርምጃዎችን ወስደዋል፡፡ ለዘመናዊ ቴክኖሎጂ ልዩ ትኩረት በመስጠት ለአገራቸው አዲስ ዓይነት የግንኙነት ስርዓት እንዲዘረጋ አድርገዋል፡፡ አጼ ምኒልክ አገራቸው ኢትዮጵያ የስልክ እና የቴሌግራፍ እንዲሁም ዘመናዊ የፖስታ አገልግሎት ተጠቃሚ እንደትሆን አድርገዋል፡፡ አጼ ምኒልክ የኤሌክትሪክ አገልግሎት በአዲስ አበባ ከተማ እንዲጀመር አድርገዋል፡፡ የመጀመሪያዋን በሞተር ኃይል የምትንቀሳቀስ አውቶሞቢል ወደ ሀገራቸው ያስገቡ አጼ ምኒልክ ናቸው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የማሪያ ቴሬዛ ገንዘብን የማይመች የገንዘብ መገበያያን በዚያን ዘመን በዓለም ገበያ ላይ በመገበያያነት አገልግሎት ስራ ላይ ይውሉ በነበሩ በመዳብ የወርቅ ቁራጭ የገንዘብ ሳንቲሞች በመተካት ዘመናዊ የገንዘብ ግብይትን በኢትዮጵያ አስጀምረዋል፡፡ አጼ ምኒልክ ከምንም ከማንም በላይ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ቅድሚያ ይሰጡ ነበር፡፡ አጼ ምኒልክ እ.ኤ.አ በ1894 ከጅቡቲ እስከ አዲስ አበባ የሚዘልቅ የባቡ ሀዲድ መስመር ለመዘርጋት ከፈረንሳይ መንግስት ጋር የስምምነት ውል ፈረሙ፡፡ በተመሳሳይ ዓመት የአውሮፓ ኃያላን አገሮች አፍሪካን እንደ ቅርጫ ስጋ የሚከፋፍለውን የአውሮፓ ቅኝገዥዎች የበርሊን ጉባኤን አካሄዱ፡፡ በዚያን ጊዜ ፈረንሳዮች የነበራቸውን ኃይል በመተማመን ከባቡር ሀዲዱ ጋር በተያያዘ መልኩ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለመዳፈር ሲሞክሩ አገር ወዳዱ መሪ ፈረንሳዮችን ጭጭ እንዲሉ አድርገው በ1906 የአገራቸውን ሉዓላዊነት ካስጠበቁ በኋላ ነው ቀዝቀዝ ማለት የጀመሩት ሐዲዱም መሰራት የቀጠለው ፡፡ እንግዲህ እንዲህ የነበረውን አንጸባራቂ ታሪክ በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ያለው ገዥው አካል የውሸት የአቶ መለስን ትረካ በማጉላት የህዳሴው መሪ፣ በአፍሪካ ታሪክ እስከ አሁን ድረስ ታይቶ የማይታወቅ የኤሌክትሪክ ኃይል ግድብ ገንቢ፣ የድልድዮች ገንቢ፣ የመንገዶች እና የባቡር ሀዲዶች… በማለት ታሪክን አዛብቶ ሸውራራ ታሪክ ለመጻፍ እየተውተረተረነው ያለው፡፡
አጼ ምኒልክ የፊውዳል መንግስታት የበላይ የነበሩ መሪ ነበሩ፡፡ በወቅቱ በአገር ውስጥ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ በጣም አስቸጋሪ ሁኔታ በነበረበት ጊዜ ማድረግ የሚፈልጉትን ማድረግ የሚችሉ አፍሪካዊ መሪ ነበሩ፡፡ በእግዚአብሄር በአላህ ፈቃድ አንዲት የተባበረች እና የተከበረች ኢትዮጵያን ለተተኪው ትውልድ አውርሰው አልፈዋል፡፡ የአቶ መለስ ጠንካራው የውርሳቸው ትሩፋት በአፍሪካ የመጀመሪያውን ፈላጭ ቆራጭ አምባገነናዊ አገዛዝ ማውረሳቸው ነው፡፡ በሁፊንግተን ፖስት ትችቴ/Huffington Post Commentary በግልጽ እንዳስቀመጥኩት “ዴሞክራሲ የህዝብ፣ በህዝብ፣ ለህዝብ የቆመ የመንግስት አስተዳደር ከሆነ የማፊያ አገዛዝ/thugocracy ደግሞ (የወሮ በላ) የሌቦች፣ ለሌቦች በሌቦች የቆመ የወሮ በላ መንግስት አስተዳደር ነው፡፡“ በግልጽ አባባል የማፊያ አገዛዝ የሚሽከረከረው በወሮበላ ሌቦች እና በዘራፊዎች ነው፡፡ በማፊያ የአገዛዝ ስርዓት የፖለቲካ ስልጣንን ሙዝዝ ብሎ መያዝ እና እንደ መዥገር መጣበቅ ዋናው ተግባሩ ሲሆን ገዥው አካል የህዝብን ገንዘብ በመዝረፍ እና ለብዙሀኑ ህዝብ ህልውና የቆሙትን መሰረታዊ አገልግሎቶች ውሱን ሀብቶች በመቀራመት ግላዊ ሀብትን ለማጋባስ ነው፡፡
የአቶ መለስ የማፊያ (የወሮ በላ) አገዛዝ በሰነድ ብቻ ተመዝግቦ የሚያዝ ሳይሆን በቀድሞው የመከላከያ የትግል ጓደኛቸው ጭምር የአይን ምስክርነት የተሰጠበት ጉዳይ ነው፡፡ ገና ከጫካ ትግል ሲጀምሩ አቶ መለስ እና የትግል ጓዶቻቸው የሌቦች አስተዳደራዊ ስርዓት ነበር የዘረጉት፡፡ እ.ኤ.አ በ1980ዎቹ የመጀመሪያ ዓመታት ለረሀብ ሰለባ ለወደቀው የትግራይ ህዝብ እርዳታ ተብሎ ከእርዳታ ሰጭ ድርጅቶች የተላከውን ከ10 ሚሊዮን ዶላር በላይ የሚሆን ገንዘብ ከተሰጠበት ዓላማ ውጭ አማጺው ቡድን ለጦር መሳሪያ መግዣ እና እራሳቸውን ማበልጸጊያ አድርገውታል፡፡ በቅርብ እየወጡ ያሉ ዘገባዎች እንደሚያመላክቱት ከግማሽ በላይ የሚሆነው የአገሪቱ ኢኮኖሚ በአቶ መለስ ባለስልጣኖች፣ ደጋፊዎች፣ ሎሌዎች፣ ጓደኞች፣ የስራ ባልደረቦች እና ሌሎች ቁጥጥር ስር ተቀፍድዶ ይገኛል፡፡ ሙስናን በሚመለከት የዓለም ባንክ “ሙስናን በኢትዮጵያ መመርመር” በሚል ርዕስ የተወሰኑ አገሮችን ባናሙናነት ወስዶ በማጥናት ባወጣው ባለ500 ገጽ የግኝት ዘገባ መሰረት ሙስና እና የህዝብን ሀብት መዝረፍ በኢትዮጵያ ዋና መገለጫ ሆኗል በማለት ደምድሟል፡፡ ዘራፊነት አና ሙስና የአቶ መለስ የመጨረሻው ውርሳቸው ነው፡፡
አጼ ምኒልክን መጥላት ይወዳሉ፣
ጥላቻ የነብሳችን የመጨረሻው የበሽታ ምልክት ነው፡፡ ጥላቻ ኢምክንያታዊ ነው ወይም አመክንዮ የለውም፡፡ በጥላቻ ላይ የተጻፉ በርካታ ሳይንሳዊ ጽሁፎች እንደሚያመለክቱት በጥላቻ የተመረዙት ምንጊዜም ይጠላሉ ምክንያቱም ይፈራሉ፣ ደህንነት አይሰማቸውም፣ ምቀኞች ናቸው፣ ወይም ደግሞ እራሳቸውን ይጠላሉ ምክንያቱም የጥላቻቸው መነሻ እና መድረሻ እነዚሁ በጥላቻ የተሞሉት ግብዞች ናቸውና፡፡ ከሁሉም በላይ በጥላቻ የተሞሉት ወገኖች እራሳቸውን ይጠላሉ ምክንያቱም ብቁነት የጎደላቸው፣ ኃይልየለሽነት፣ ተስፋቢስነት፣ እና የእረዳትየለሽነት ስሜት የተጠናወታቸው ነው፡፡
ማንዴላ እንዲህ ብለው ነበር፣ “ሰው በቆዳው ቀለም፣ ወይም ደግሞ በማንነቱ፣ ወይም በኃይማኖቱ ምክንያት ብቻ ማንም ማንንም ሊጠላ አልተወለደም፡፡ ሰዎች መጥላትን መማር አለባቸው፣“ በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ በስልጣን ላይ ያሉትን የገዥው አካል ኃላፊዎች ሁኔታ በማስብበት ጊዜ በማንዴላ ፍልስፍናዊ ግምገማ ላይ አምነት ማጣት ይቃጣኛል፡፡ ማንዴላ እንዲህ በማለትም አክለዋል፣ “መጥላትን የሚማሩ ከሆነ ፍቅርን ሊማሩም ይችላሉ፣ ምክንያቱም ፍቅር ከተቃራኒው የበለጠ በሰው ልጅ ልብ ውስጥ የመስረጽ ተፈጥሯዊ ባህሪ አለውና፡፡“ ተቃራኒውን በተጨባጭ የሚያመላክቱ በርካታ መረጃዎች ቢኖሩም የማንዴላ መርሆዎች በስልጣን ላይ ባሉት ባለስልጣኖች ሁሉ ሊተገበሩ እንደሚችሉ ጽኑ እምነት አለኝ፡፡
በመርህ እና በተግባርም እንደሚታየው በጋንዲ መርሆዎች መሰረት ለመኖር ጥረት ማድረግ አለብን፣ “ኃጢያተኛውን ሳይሆን ኃጢያቱን እንጥላ፣“ በጥላቻ የተመረዙትን የምንጠላ ከሆነ የእነርሱ የመስታወት ነጸብራቅ እንሆናለን፣ እራሳችንም የምንጠላቸውን እንሆናለን፣ እንደ ሰው ስብዕና አቶ መለስን እና መሰሎቻቸውን የምንጠላ ከሆነ እነርሱኑ ሆን ማለት ነው፡፡ የምንጠላ ከሆነ ምግባራቸውን እንጅ እንደ ሰው እራሳቸውን መሆን የለበትም፡፡
ጥላቻ ጠንካራ ኃይል ነው፡፡ በናዚዝስቶች የተሰራጨው ጥላቻ አገሮችን በጠቅላላ እንዲጠፉ አድርጓል፡፡ በሩዋንዳ የተከሰተው ጥላቻ የሚሊዮኖችን ሩዋንዳውያን ህይወት ቀጥፏል፡፡ በዳርፉር የተቆሰቆሰው ጥላቻ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የሱዳን ዜጎችን ህይወት አጥፍቷል፡፡ በአሁኑ ጊዜ በተከሰተው የኃይማኖት ጥላቻ በናይጄሪያ እና በመካከለኛው አፍሪካ ሬፑብሊክ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች በመሞት ላይ ይገኛሉ፡፡ በምንም ዓይነት መንገድ ወደ ጥላቻ መግባት የለብንም፡፡
በዓለም ላይ ሁለት ዓይነት ህዝቦች እንዳሉ አምናለሁ፡፡ “ጎረቤትህን እንደ እራስህ ውደድ“ የሚለውን ወርቃማ ህግ የሚከተሉ ህዝቦች አሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ “የመዳብ ህግ” እያልኩ በምጠራው “ጎረቤትህን እንደ እራስህ ጥላ“ እያሉ የሚኖሩ ህዝቦች አሉ፡፡ በጥላቻ የተሞሉ ሰዎች የእራሳቸውን እረዳትየለሽነት፣ የደህንነት እጦት ስሜት፣ የጥፋተኝነት ስሜት እና በጥላቻቸው መሳሪያነት ድርጊቶችን በመለወጥ አሸናፊነትን የሚጎናጸፉ ይመስላቸዋል፡፡ ሌሎችን በመጥላት የራሳቸውን የበታችነት ስሜት እና የእራስን ዋጋ ዝቅ አድርጎ የማየት ችግራቸውን በማስወገድ እራሳቸውን ከፍ ያደረጉ ይመስላቸዋል፡፡ አጼ ምኒልክን የሚጠሉ ሰዎች በእርግጥ አይጠሏቸውም፣ እራሳቸውን የሚጠሉ እና ምኒልክን ለመሆን የሚያስቡ ምኒልክ የሚያደርጓቸውን ነገሮች ሁሉ ተምሳሌት ለማድረግ የሚጥሩ ናቸው፡፡
በአሁኑ ጌዜ በኢትዮጵያ በስልጣን ላይ ላሉት ሁሉ አዝንላቸዋለሁ፡፡ በእርግጥ በጣም አዝንላቸዋለሁ፡፡ እነዚህ በጥላቻ የተሞሉት ወገኖች የኢትዮጵያን ታላላቅ መሪዎች እና የኢትዮጵያን ታሪክ ጥላሸት በመቀባት በቅርቡ በህይወት የተለዩትን መሪያቸውን እና የሁለት አስርት ዓመታት ኃጢያታቸውን በማስሰረይ ብጹ የሚያደርጓቸው ይመስላቸዋል፡፡ የአጼ ምኒልክን እና የቀዳማዊ ኃይለስላሴን በጎ ተግባራት ጥላሸት በመቀባት የአቶ መለስን ስብዕና የሚገነቡ ይመስላቸዋል፡፡ የአጼ ምኒልክን ሐውልት ከህዝባዊ ቦታዎች በማራቅ እና የአቶ መለስን እርካሽ ወረቀት ፎቶግራፎች በየመንገዶች ላይ በመለጠፍ አቶ መለስን ወደ መልዓክነት ያቀረቧቸው ይመስላቸዋል፡፡ አቶ መለስ የአጼ ኃይለስላሴ ሀውልት ከንክሩማህ ቀጥሎ በአፍሪካ ህብረት ቅጥር ግቢ ውስጥ እንዳይቆም ሽንጣቸውን ገትረው ተከራክረዋል፡፡ ሆኖም ግን ንክሩማህ እራሳቸው የአጼ ኃይለስላሴ ያልተጠቆጠበ ጥረት ባይኖር ኖሮ የአፍሪካ ድርጅት እውን መሆን አይችልም ነበር በማለት ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል፡፡
በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ያሉት ባለስልጣኖች የጥላቻቸው ባህሪ እና አተገባበር ነጻብራቅ ረዘም ያለ ጊዜ የቆየ ቢሆንም ለዚህ ምክንያታዊ መግለጫ አላገኘሁለትም፡፡ ብዙ ሰዎች በፍርሀት እና በጭንቀት ላይ ያሉ ሰለ ወደፊት ምንይመጣል አያሉ ነው ምክንያቱም በቀጣይነት የሚከሰተው ሁኔታ የማይታወቅ እና ለመተንበይም አስቸጋሪ የሆነበት ሁኔታ ሰለሆነ ነው፡፡ ያለፈውን ጊዜ፣ የጥንት 19ኛውን ክፍለ ዘመን ኢትዮጵያ የሚፈሩትን ሰዎች በትክክል ለመረዳት አልችልም፡፡ በሞያዬ ካለኝ ልምድ አንጻር ያለፈውን ጊዜ የሚፈሩ እና የሚሸበሩ ወንጀለኞ ይሄዉም በፊት በፈፀሙት ወንጀል የሚያዙ ሰለሚመስላቸውና ሰለሚፈሩ ነው:: በስልጣን ላይ ያሉ አምባገነኖች ስልጣናቸውን ከህግ አግባብ ውጭ በመጠቀም የሰላማዊ ዜጎችን መብት የጣሱ እና የደፈጠጡበትን ወንጀል ለመደበቅ ሲሉ ጥላቻን በማራመድ እና ከፋፍሎ መግዛትን አጀንዳቸው አድርገው ይይዙታል ከሚል መደምደሚያ ላይ ደርሻለሁ፡፡ በኢትዮጵያውያን ልዩ ልዩ ጎሳዎች ላይ ጥልቅ ጥላቻና እና ፍርሀትን በመፍጠር ለፈጸሟቸው እኩይ ተግባራት ተጠያቂ እንዳይሆኑ እና ኃላፊነትን እንዳይወስዱ የጥላቻ መንፈስን እንደ መርህ በመያዝ ያራምዳሉ፡፡ በህዝቦች መካከል ጥላቻን በመዝራትም በኢኮኖሚያዊ ችግሮች ምክንያት ተወጥረው ያሉትን ዜጎች ሀሳቦች ለማስቀየሻ ይጠቀሙበታል፡፡
በጥላቻ የተሞላን ሰው እንደ እራስህ ውደድ፣
ወርቃማው ህግ እንዲህ ይላል፣ “ጎረቤትህን እንደ እራስህ ውደድ፡፡“ እኔ ደግሞ እንዲህ እላለሁ፣ “የሚጠላህን እንደ እራስህ ውድ፡፡“ ከመጥላት ይልቅ መውድደ የተሻለ ነገር ነው፡፡ ጥላቻ ወርዋሪውን ተመልሶ እንደሚጎዳ ቦንብ ነው፡፡ መጀመሪያ ከሚወረውረው ሰው እጅ ይወጣል ተመልሶ ግን በጥላቻ የተሞላውን ሰው እራሱን ይጎዳዋል፡፡ የማንዴላን አባባል በመዋስ፣ ጥላቻ የነብስ መርዝ ነው፡፡ በጥላቻ የተሞሉት በሚጠሉበት ጊዜ መርዝን ይጠጣሉ እናም የሚጠሏቸው እንዲሞቱ ይጠብቃሉ፡፡ በስልጣን ላይ ያሉ ሁሉ ጥላቻን ማራመድ እንዳለባቸው ልዩ ምክር የሚሰጥ ለየት ያለ የፍልስፍና ዓይነትም አለ፡፡ ጥላቻ ሁልጊዜ የተጠላውን ሰው የተወደደ እና የተከበረ ስብዕና ያለው እንዲሆን ያደርገዋል፡፡ በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ በስልጣን ላይ ተቆናጥጠው ያሉ ወገኖች በዱሮዋ ደቡብ አፍሪካ ከነበሩት የአፓርታይድ መሰል የመንፈስ ጓዶቻቸው ትምህርቶችን ሊማሩ ይገባል፡፡ የአፓርታይድ ጌቶች የማንዴላን ስብዕና፣ አመራር እና ክብር ለበርካታ አስርት ዓመታት ለማዋረድ ፈለጉ፡፡ ማንዴላ አሸባሪ እና ኮሙኒስት ናቸው በማለት ማንኛውንም ዓይነት የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ከፈቱባቸው፡፡ ይንንም ምክንያት በማድረግ ማንዴላ በእስር ቤት በቆዩባቸው ጊዚያት ሁሉ ምንም ዓይነት የፎቶግራፍ ምስላቸው እንዳይወጣ አደረጉ፡፡ ሆኖም ግን ያልታሰቡ አጋጣሚዎች ተከሰቱ፡፡ በሂደት ጊዜ እያለፈ እና የጸረ አፓርታይድ ንቅናቄው እየተጠናከረ ሲሄድ ማንዴላን አሳንሶ የማየት አባዚያቸው የማንዴላን የመላዕክነት ደረጃ ከፍ እያደረገ ወደ ዓለም አቀፋዊ ተምሳሌነት እንዲሸጋገሩ እገዛ አደረገላቸው፡፡ ከዚህ ሊወሰድ የሚችለው ታላቅ ቁምነገር የአጼ ምኒልክን እና የአጼ ኃይለስላሴን ስብዕና ዝቅ ለማድረግ ጥረት ባደረጉ ቁጥር እነዚህ መሪዎች በኢትዮጵያ የወጣቶች ትውልድ የአስተሳሰብ አድማስ ዘንድ የበለጠ ክብር እና ሞገስን እየተቀዳጁ ታዋቂ እየሆኑ ይሄዳሉ፡፡ በእነዚህ መሪዎች ላይ የማያቋርጥ እና ዘለቄታዊ ያለው የማዋረድ ዘመቻ ባደረጉ ቁጥር የቀድሞው ትውልድ ጉዳዩን የበለጠ እንዲገመግመው እና አቋሙን እንዲያጠናክር ያደርገዋል፡፡
ፍቅር ከጥላቻ በላይ ዘልቆ መሄድን ይጠይቃል፡፡ ዶ/ር ማርቲን ሉተር ኪንግ እና ማንዴላ በሰዎች እና በህብረተሰብ ክፍሎች ዘንድ ፍቅር ያለውን የማይበገር የአሸናፊነት ኃይል፣ እንዲሁም ፍቅር በዘር፣ በጎሳ እና በኃይማኖት የተዘራን የጥላቻ ካንሰር የመፈወስ ችሎታ እንዳለው በግልጽ አስተምረውናል፡፡ ማንዴላ ለመጥላት እና በቀልን ለመፈጸም ምክንያት አላቸው፡፡ ለ27 ዓመታት የማንዴላ ስም የእስረኛ ቁጥር 46664 ነበር፡፡ እ.ኤ.አ በፌብሯሪ 1990 ጧት ከእስር ቤት ተለቅቀው ከእስር ቤቱ በር ሲወጡ ከሚሊዮን ዶላር ዋጋ በላይ የሚያወጣውን ፈገግታቸውን አሳይተዋል፡፡ ለ27 ዓመታት ከቤተሰቦቻቸው ነጥለው በእስር ቤት ውስጥ ባማቀቋቸው የአፓርታይድ ጌቶች ላይ ምንም ዓይነት የጥላቻ ስሜት አላሳዩም፡፡ ማንዴላ ታላቅ ትምህርት አስተምረውን አልፈዋል፣ እንዲህ በማለት፣ “እየተራመድኩ ወደ በሩ በምቃረብበት ጊዜ ይህ ሁኔታ ወደ ነጻነት እየመራኝ እንደሆነ አስብ ነበር፡፡ የበቀልተኝነት ስሜቴን እና ጥላቻዬን እዚያው እስር ቤት ጥዬው ካልወጣሁ እዚያው እስር ቤት እንዳለሁ እቆጥረዋለሁ፡፡“ በማለት የጥላቻን መጥፎነት በግልጽ ተናግረዋል፡፡ ማንዴላ ፍጹም የጥላቻ እስረኛ አልነበሩም፡፡ እስረኛው የአፓርታይድ ጥላቻ ነበር፣ እናም አስረኞቹ የአፓርታይድ አለቆች እና ጌቶች ነበሩ፡፡ ማንዴላ ከእስር ቤት በመውጣት በጥላቻ ሰንሰለት ከአፓርታይድ ግንብ ጋር የታሰሩትን እውነተኞቹን የአፓርታይድ እስረኞች ከጥላቻ፣ ከፍርሀት፣ እና ከበቀልተኝነት ነጻ ለማውጣት ተንቀሳቅሰዋል፡፡
በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ በስልጣን ላይ ያሉት ገዥዎች በጥላቻቸው የሚቀጥሉ ከሆነ በደቡብ አፍሪካ አፓርታይድ በስልጣን ላይ በነበረበት ጊዜ የደረሰው ዕጣ ፈንታ የሚደርስባቸው መሆኑን መገንዘብ ይኖርባቸዋል፡፡ በአፓርታይድ የአገዛዝ ዘመን ጊዜ “ነጻዎቹ” ነጮች እውነተኛው የማይቀረው የብዙሀን አገዛዝ በሚመጣበት ጊዜ ለብዙ ጊዜ በጭቆና ቀንበር አስረው ሲያማቅቋቸው የነበሩት ጥቁር አፍሪካውያኖች ምን ሊያደርጓቸው እንደሚችሉ ሌት እና ቀን ያሰላስሉ ነበር፡፡ በጥቁር አፍሪካውያን ላይ የነበራቸው ጥላቻ እንቅልፍየለሽ ሌሊቶችን ብቻ እንዲያሳልፉ አላደረጓቸውም፣ ሆኖም ግን ልቦቻቸው፣ አዕምሯቸው እና ነብሳቸው እንዲሁም ስብዕናዎቻቸውም ጭምር እንዲሰበሩ አደረጋቸው እንጅ፡፡ ሙት መንፈሶች አደረጓቸው፣ ነጻ ሆነው ባሏቸው ኃብቶቻቸው ለመደሰት ባለመቻል የቁም ሙት አደረጓቸው፣ እንዲሁም በኤሌክትሪክ እና በእስር ቤት የሽቦ አጥር ታጥረው የእራሳቸው ጎረቤቶች የእስር ቤት በሮች ሆኑባቸው፡፡ በእርግጥ በጦር ካምፕ የሚኖሩ ህዝቦች ሆኑ፡፡
ምንጊዜም የተሻለ መንገድ አለ፡፡ የጥላቻ ትችት ከማቅረባችን በፊት እውነተኛውን ነገር ለማወቅ የበለጠ ጽናት ሊኖረን ይገባል፡፡ ስለዳግማዊ አጼ ምኒልክ፣ ስለ አጼ ኃይለስላሴ፣ ስለ ኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማርያም እና ስለ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ እውነኛውን ነገር ማቅረብ ይኖርብናል፡፡ እነርሱን መጥላት ሳይሆን ከስህተቶቻቸው እንማር፣ እኛ በህይወት ያለነው የእነርሱን ስህተት መድገም የለብንም፡፡ ጥላሸት በመቀባት ላይ ላለመሰማራት ከእነርሱ ስህተት እንማር፣ ነገር ግን የእርቅን መንገድ በመፈለግ የእነርሱን ስህተቶች እናርም፡፡ ከኢትዮጵያ ወጣቱ ትውልድ ጋር ህብረት በመፍጠር ማንም ወንድ ወይም ሴት በማንነቱ/ቷ፣ በዘሩ/ሯ ሳይሆን ሰው በመሆኑ/ኗ፣ አፍሪካዊ/ት እና ኢትዮጵያዊ/ት በመሆናቸው ብቻ በመመልከት አዲሲቷን ፍቅር የነገሰባት ኢትዮጵያ ለመገንባት እንነሳ፡፡ ማንም ወንድ ወይም ሴት ባለው/ላት ስልጣን በመመካት ባልታጠቁ ዜጎች እና በሰላማዊ ሰዎች ላይ የጦር እልቂት ሊያዝዝ/ልታዝዝ የማይችሉበት እና ይህ ዓይነቱ አስተሳሰብም ሊወገድ የሚችልበት ነጻ ህሊናን በመፍጠር አዲሲቷን ፍቅር የነገሰባት ኢትዮጵያ ለመገንባት እንነሳ፡፡ በእያንዳንዱ/ዷ ግለሰብ የጎሳ፣ የእምነት ወይም የቋንቋ ልዩነት ሳንፈጥር በአንድነት በመሆን የእያንዳንዱ/ዷ ዜጋ መብት እና ክብር የሚጠበቅበትን ህብረተሰብ ለመፍጠር እንነሳ፡፡ በዚህ ዓይነት ሁኔታ ነው የወደፊቱን ብሩህ ዘመን ለመፍጠር የምንችለው፡፡ ለብዙ ጊዜ በመቆየት በጊዜ ደመና ተሸፍኖ የደበዘዘውን ነገር ቆፍሮ በማውጣት እና ጥላሸት በመቀባት አይደለም ፍቅር የነገሰበትን የወደፊቱን ትውልድ መገንባት የምንችለው፡፡
በጥላቻ ንግግር አንዘን ወይም ደግሞ አንቆጣ፡፡ ምንም ዓይነት እርባና የለውም፡፡ ይልቁንም ጥላሸት የመቀባት ዘመቻውን በሰከነ መልክ እናጋልጥ፡፡ መላዕክ ለማድረግ የሚደረገው ጥረት ስህተት እና ውሸት መሆኑን እና የኢትዮጵያን ታሪክ ጥላሸት ለመቀበት እና ለመበረዝ የሚደረገውን መዋተት እናጋልጥ፡፡ ከጥላቻ አራማጆች ጋር በማበር እራሳችንን ወደ ጭቃ እና የሚያጣብቅ ቆሻሻ ውስጥ አንጣል፡፡ እንዲህ የሚሉትን የጆርጅ በርናርድ ሻውን ምክሮችን በፍጹም መርሳት የለብንም፣ “ከብዙ ጊዜ በፊት ከአሳማ ጋር ማጥ ዉስጥ ላለመታገል ትምህርት አግኝቻለሁ፣ ለመታገል ከሞከርክ ቆሻሻ ትሆናለህ፣ አሳማው ግን ማጡን የነብሱን ያህል ይወደዋል፡፡“ ጥላቻን ሙያ አርገው ከሚኖሩ ሰዎች ጋር የጥላቻ ቃላትን መለዋወጥ ከአሳማ ጋር በጭቃ ማጥ ውስጥ የነጻ ትግል ውድድርን እንደማድረግ ይቆጠራል፡፡
ጥላቻን ወደ ፍቅር መለወጥ
በጥላቻ መንፈስ የተሞሉት ወገኖች ይጥሉ እና ይዋሹ፡፡ ስለዚያ ጉዳይ የምናደርገው አንዳች ነገር የለም፡፡ በእራሳችን የሀይል ንፍቀ ክበብ ውስጥ ያለን ልዩ ችሎታ እራሳችንን ከጥላቻ ወደ ፍቅር ከመቀየር ላይ ነው፡፡ በእርግጥም አሉታዊ ኃይሎችን ወደ አዎንታዊ ኃይሎች የመቀየር ችሎታ አለን፡፡ ከጥላቻ ወደ ፍቅር ለመቀየር እንችላለን፣ ይህን የምናደርገው ግን ነገሩ ቀላል ስለሆነ አይደለም ይልቁንም የበለጠ ከባድ ስለሆነ እንጅ፡፡ ፍቅር በግለሰብ ደረጃም ይሁን፣ በሌሎችም ይሁን፣ በማህበረሰቡ ወይም በአጠቃላይ በህዝቡ ላይ ይሁን ለተግባራዊነቱ ታላቅ ስራ መስራትን ይጠይቃል፡፡
ከማህተመ ጋንዲ እና “እውነተኛው ኃይል”/Satyagraha ከሚሉት አቀራረባቸው እስቲ ትምህርት እንቅሰም፡፡ ጋንዲ እንዲህ በማለት ገለጻ አድርገዋል፣ “እውነት/satya ፍቅርን በማጎናጸፍ የመንፈስ ጽናትን ይወልዳል፣ እናም ከኃይል ጋር ተመሳሳይ በመሆን ያገለግላል፡፡“ ዓላማው በጥላቻ የተሞላው/ችው እንዳያስገድድ/እንዳታስገድድ በማድረግ ሀሳባቸውን ለማስለውጥ ነው፡፡ በተግባራዊነት ሁኔታው ስንመለከተው ዓላማው በጥላቻ የተሞላውን/ችውን ጥላቻ ማራመድ የእራሱን/ሷን ልብ፣ አዕምሮ እና ነብሳቸውን የሚጎዳቸው መሆኑን በማሳመን እንዲቀየሩ ለማድረግ ነው፡፡ ከማንኛውም ጉዳትን ከሚያመጡ ነገሮች ሁሉ የሚጠብቁን እራስን፣ ማህበረሰቡን እና አገርን መውደድ ነው፡፡ በጥላቻ ከተሞሉት ወገኖች ፍቅር የተሞሉ ወገኖችን ለማፍራት እውነተኛውን ኃይል/Satyagraha በተግባር እናውል፡፡
ከዶ/ር ማርቲን ሉተር ኪንግ የምንማራቸው በርካታ ቁምነገሮች አሉ፣ እንዲህም በማለት ያስተምሩናል፣ “ጨለማን ጨለማ አያስወግደውም፣ ብርሃን ብቻ ነው ያንን ማድረግ የሚችለው፡፡ ጥላቻን ጥላቻ ሊያስወግደው አይችልም፣ ፍቅር ብቻ ነው ያንን ማድረግ የሚችል፡፡“ ብለዋል፡፡ እንዲህ በማለትም አስተምረዋል፣ “ይቅርታ የማድረግ ችሎታችንን ማሳደግና ማጠናከር ይኖርብናል፡፡ ይቅርታ የማያደርግ/የማታደርግ ሰው ለማፍቀር ኃይል የለውም/የላትም፡፡ በመጥፎነታችንም ላይ ጥሩ ነገሮችም አሉ፡፡ በመጥፎ ነገሮቻችን ላይም ጥሩ ነገሮች አሉ፡፡ ይህንን ሁኔታ ባወቅን ጊዜ ጠላቶቻችንን ከመጥላት በመጠኑም ቢሆን እንታቀባለን፡፡“ ይቅርታ አድራጊነት እና እርቅ ብቸኞች የጥላቻ ፈውስ እና መድኃኒቶች ናቸው፡፡
ከዘመናችን ታላቅ ቀልድ አዋቂ ከቻርለስ ቻፕሊን እንኳ ትምህርት መቅሰም ይኖርብናል፡፡ እንዲህም ይለናል፣ “የሰው ልጅ ጥላቻ ያልፋል፣ እና አምባገነኖችም ይሞታሉ፣ እናም ከህዝቦች የነጠቁት ስልጣን ተመልሶ በህዝቡ እጅ ይገባል፡፡ ስለሆነም የሰው ልጅ ሟች እስከሆነ ድረስ ነጻነት ከናካቴው ሊጠፋ አይችልም፡፡“ ነጻነት በጥላቻ ከተሞሉት የሰው ዘሮች ሁሉ የበለጠ እድሜ አለው፡፡ በጎሳ ማንነት መፈረጅን እርግፍ አድርገን እንተው እና ሰው በመሆናችን ብቻ በኢትዮጵያዊነታችን እና በአፍሪካዊነታችን እንኩራ፡፡
በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ በስልጣን ላይ ላሉ የማስተላለፈው መልዕክት፣
በኢትዮጵያ በስልጣን ላይ ሆነው ጥላቻን ለሚያራግቡት አጭር መልዕክት አለኝ፡፡ በአሁኑ ጊዜ የምትቆሰቁሱት የዘር እና የጎሳ ጥላቻ ፍላጻ በአንድ ወቅት ተመልሶ እራሳችሁ ላይ ይሰካል፡፡ በአሁኑ ጊዜ የአጼ ምኒልክን ክብር እና ዝና ለማንቋሸሽ በታለመ ዕኩይ ምግባር ጡት ቆራጭ አረመኔ ነበሩ በማለት በመሳለቅ እና በማፌዝ ላይ ትገኛላችሁ፡፡ በአሁኑ ጊዜ አጼ ምኒልክን እንዲጠሉ የሚሰበክላቸው ሰዎች ነገ ደግሞ አቶ መለስን እንዲጠሉ የማይሰበክበት ምክንያት አይኖርም፡፡ የእናንተ ታላቁ ባለራዕይ መሪ አቶ መለስ በኦጋዴን፣ በጋምቤላ፣ በአዲስ አበባ እና በሌሎችም ቦታዎች በንጹሃን ዜጎች ላይ በፈጸሟቸው የጅምላ እልቂቶች ሳቢያ በድንጋይ እና በእብነበረድ በተቀረጹ ሃውልቶች ላይ ሆነው ሁለተኛው ሮዶልፍ ግራዛኒ በመባል የሚታወሱበት ጊዜ እሩቅ አይሆንም፡፡ ዛሬ ጓደኞች ብላችሁ የያዛችኋቸው ሰዎች ነገ ቀንደኛ ጠላቶቻችሁ ሆነው ይቀርባሉ፡፡ ዛሬ የእናንተ ጠላቶች አድርጋችሁ ጥላሸት የምትቀቧቸው ሰዎች ነገ ጽዋው ሞልቶ እጣ ፈንታችሁ ደርሶ የዘራችሁትን የምታጭዱበት ጊዜ ሲመጣ የእናንተ ጓደኞች ሆነው ይቀርባሉ፡፡
ዳግማዊ አጼ ምኒልክ መልዓክ ወይም ጭራቅ አልነበሩም፡፡ ሰይጣን ወይም ደግሞ እግዚአብሄርም አልነበሩም፡፡ የተቀሩት የአፍሪካ አገሮች በኃአውሮፓ ኢምፔሪያሊስት ኃይሎች ሲቆራረሱ፣ መጫወቻ ሲሆኑ፣ ሲነሱ ሲጣሉ፣ ሲበጠሱ ሲቀጠሉ፣ ሲሸጡ እና ሲለወጡ እንዲሁም ሲጋዙ በነበረበት ጊዜ አጼ ምኒልክ ደግሞ ኢትዮጵያን ሲያጠናክሩ እና ሲያዘምኑ የነበሩ የተከበሩ አፍሪካዊ ንጉስ ነበሩ፡፡ ዳግማዊ አጼ ምኒሊክ በአንድ መለኪያ ብች ይገምገሙ፣ በእውነት! የታሪክ ሰዎች እውነታውን መናገር አለባቸው፣ እና ሁሉንም እውነታዎች፣ ሌላ ምንም ነገር ሳይሆን ስለምኒልክ ያለውን እውነታ ብቻ፡፡ ለአጼ ምኒልክ 100ኛ ሙት ዓመት መታሰቢያ ሲባል እ.ኤ.አ በ1909 በኒዮርክ ታይምስ ባሮን ዲ ጃርልስበርግ የተባለ የቤልጄም አሳሽ ለዳግማዊ አጼ ምኒልክ ምስክርነት ለጋዜጣው ቃል በመስጠት የተዘገበውን በከፊል ምስከርነት እውነታ መረጃ እንደሚከተለው አቅርቤዋለሁ፡፡ ይህ ታሪካዊ የምስክርነት መረጃ ዳግማዊ አጼ ምኒልክን ከሰሯቸው ስራዎች አንጻር በትክክለኛው የታሪክ ሚዛን ላይ በማስቀመጥ እንዲገመገሙ ያስችላል የሚል ጽኑ እምነት አለ፡፡
ዳግማዊ አጼ ምኒልክ የዘውድ ስልጣኑን ለመቆናጠጥ ትግል ማድረግ ከጀመሩበት ከ20 ዓመታት በኋላ አቢሲኒያን ከከፊል የኋላቀርነት አገዛዝ በማውጣት ወደ አውሮፓውያን የንጉሳዊ ህገመንግስት የአገዛዝ ስርዓት ምሳሌነት አሸጋግረዋታል… እራሳቸውን ነጻ እና በእራስ የሚተማመኑ አድርገው የሚቆጥሩት ዘ እምነገደ የይሁዳ አንበሳ ስዩመ እግዚአብሔር የኢትዮጵያ ንጉሰ ነገስት ዘ ኢትዮጵያ የኢጣሊያንን የቅኝ ግዛትነት ፍላጎት አምባ ጋሪማ ላይ ጦርነት ገጥመው በአሸናፊነት እንዳንኮታኮቱት… አጼ ምኒልክ ከአጼ ዮሀንስ ህልፈተ ህይወት በኋላ እ.ኤ.አ ኖቬምበር 4 1889 የኢትዮጵያ ንጉሰ ነገስት ሆነው ሲሰየሙ የአቢሲኒያን መንግስት ከመሰረቱት የአካባቢያዊ መንግስታት በሙሉ ቅቡልነት አልነበራቸውም፡፡ ከብዙ ድካም እና ትግል በኋላ ነው እነዚህን የአካባቢ ገዥዎች እና ንጉስነታቸውን አንቀበልም ያሉትን አማጺ ገዥዎች በማሳመን እና በኃይል በማንበርከክ በመጨረሻ ስኬታማ ለመሆን የበቁት… ከዚያ በኋላ የአጼ ምኒልክ ዋና ዓላማ የነበረው የአውሮፓን ስልጣኔ ወደ አገራቸው ማስገባት ነበር፡፡ ንጉሱ የፊውዳሉን ህግ በማፈራረስ በእርግጥም በግዛታቸው እስከ አሁንም ድረስ ጨርሶ እንዳልጠፋ እና ባሮችን ነጻ በማውጣት የባሪያ ንግድን በማጥፋት በግዛታቸው በሙሉ ከክፍያ ነጻ የሆነ የትምህርት ስርዓትን ዘርግተዋል፡፡ በዚህም መሰረት እንደማንኛውም የአውሮፓ ሀገር ሁሉ በቀጣዮቹ ትውልዶች ትምህርት በመላ የአቢሲኒያ ግዛት ውስጥ የሚስፋፋ ይሆናል፡፡
ምኒልክ በመላ አፍሪካ በስልጣን ላይ ካሉ መሪዎች ሁሉ ልዩ ባህሪ ያላቸው ናቸው፡፡ እንደ የዲፕሎማሲ ሰው፣ እንደ ገንዘብ ኃላፊ፣ እንደ ወታደር ከሌሎች ወንድማዊ ንጉሶች የቅርበ መረጃዎችን በመውሰድ በእራሳቸው አካሄድ እንደሚመስላቸው የሚተረጉሙ ንጉስ ናቸው፡፡ እንደ ወታደር እና እንደ የዲፕሎማሲ ሰው የኢጣሊያኖችን በአቢሲኒያ መሸነፍ ለንጉሱ እንደ መልካም አጋጣሚ ምን ያህል ጠቃሚ የሆኑ ንጉስ መሆናቸውን አሳይተዋል፡፡ በቅርብ ዓመታት ደግሞ የገንዘብ ብልህ ጥንቁቅ አያያዝ ምኒልክን ልዩ ያደርጋቸዋል፡፡ ስለገንዘብ እንደ ወጣትም፣ የዙፋን ስልጣናቸውን ከመያዛቸው እና በዙፋኑ ላይ ከተቀመጡም በኋላ በፓሪስ የስቶክ ገበያ ትንበያን/Paris Bourse ላይ ተሳትፎ ማድረጋቸው መልካም ተፈጥሯዊ ችሎታ ያላቸው መሆኑን ያመላክታል፡፡ እነዚህ ጠቃሚ ትንበያዎች የነበሩ ሲሆን ምኒልክ የዙፋን ስልጣኑን ከያዙ በኋላ ለመቋረጥ ችለዋል… የገንዘብ አሰራር ስርዓታቸውን በማስፋት እስከ ዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ ድረስ በማስፋት በአሜሪካ የባቡር ሀዲድ ካምፓኒዎች ላይ ትልቅ የድርሻ ባለቤት ለመሆን በቅተዋል፡፡ ከአሜሪካ የሴኪዩሪቲ ሰርቲፊኬቶች እና ከፈረንሳይ እና ከቤልጄም ባለሀብቶች ጋር ከ25 ሚሊዮን ዶላር ያላነሰ መዋዕለ ንዋይ በስራ ላይ እንዲውል አድርገው ነበር፡፡
በጣም የሚያስገርመው የአቢሲኒያው ደብዛዛ ንጉስ በሁሉም ነገሮች ላይ ያላቸው ሁለገብ እውቀት ነው፡፡ በጣም ምጡቅ የቋንቋ ችሎታ የነበራቸው ሲሆኑ ፈረንሳይኛ፣ እንግሊዝኛ እና ጣሊያንኛ ቋንቋዎችን አቀላጥፈው መናገር ይችላሉ፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ለመንግስታዊ ስራቸው ሙሉ ጊዜ ሰጥተው የሚሰሩ ሲሆን በአውሮፓ የሚዘጋጁ ጽሁፎችንም የመከታተል ዕድል ስላላቸው እና በትኩረት ስለሚከታተሉ አዲስ መጽሀፍ በወጣ ቁጥር ስለደራሲው ሲጠየቅ አዲስ አይሆኑም፡፡ ባዲሳባ ቤተመንግስት በሰዎቻቸው በሚታወቁበት መጽሀፍትን በማሰባሰብ ስራቸው እውቅና እንዲሰጣቸው ሲባል በተዘጋጀው ስብሰባ ላይ በተገኙበት ዕለት በቤተ መጻህፍታቸው ከ20 ሺህ ያላነሱ ጥራዞች መገኘታቸው ልዩ ኩራት እንዲሰማቸው አድርጓል፡፡ የምኒልክ መጻህፍትን የማሰባሰብ የትርፍ ጊዜ ስራ በጥንት የአፍሪካ እና የኢስያ ስልጣኔዎች ዘመንም የሚደረግ ነበር፡፡
በአጼ ምኒልክ ላይ የጥላቻ ዘመቻ ከሚያደርጉት ወገኖች ጋር የማቀርበው መደራደርያ ፣
በዳግማዊ አጼ ምኒልክ ላይ የጥላቻ ዘመቻ ስለማሰራጨት ጉዳይ የማቀርበው መደራደርያ አለኝ ፡
በአጼ ምኒልክ ስብዕና ላይ የምታደርጓቸውን ውሸቶችና ቅጥፈቶች የምታቆሙ ከሆነ እኔም ስለአቶ መለስ የምናገራቸውን እውነቶች መናገር አቆማለሁ!
ጥር 7 ቀን 2006 ዓ.ም