የማንዴላ መልዕክት ለኢትዮጵያውያን ወጣቶች፣ “በፍጹም እጅ እንዳትሰጡ !…”
ከፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማርያም
ትርጉም በነጻነት ለሀገሬ
የአፍሪካው ብልህ አንበሳ እና እረፍትየለሾቹ የኢትዮጵያ አቦ ሸማኔዎች – በፍጹም እጅ እንዳትሰጡ፣ ፍቅር የነገሰበትን የኢትዮጵያ ማህበረሰብ ለመገንባት ጥረታችሁን ቀጥሉ!
እ.ኤ.አ ዴሴምበር 15/2013፣ ለእኔ የዓመቱ ታላቁ የኃዘን ዕለት ነው፡፡ ኔልሰን ሮሺስላሽላ ማንዴላ በደቡብ አፍሪካ በምስራቅ ኬፕ ግዛት በምትገኘው ኩኑ በምትባል ትንሽ የገጠር የትውልድ መንደራቸው በርካታ የአገር መሪዎች በተገኙበት ግብዓተ መሬታቸው ተፈጽሟል፡፡ ማንዴላ በህጻንነት የህይወት ዘመናቸው በዚያች ትንሽ መንደር የከብት እረኛ በመሆን በርካታ የደስታ ቀናትን አሳልፈዋል፡፡ ከረዥም ዓመታት የነጻነት ትግል ጉዞ፣ ከበርካታ ዓመታት የእስር እና ረዥም ጊዚያት የህይወት ውጣ ውረድ ጉዞ በኋላ ለዘላለማዊ ማሸለብ አያት ቅድመ አያቶቻቸውን ለመቀላቀል እንደገና ወደ ትውልድ መንደራቸው ወደ ኩኑ ተመልሰዋል፡፡ ወጣቱ የኩኑ መንደር የከብት እረኛ የነበሩት ማንዴላ ከዚያ ወዲህ ደግሞ የተደነቁ፣ የተወደዱ እና የተከበሩ የህዝቦቻቸው እረኛ በመሆን ወደ ዘላለማዊ ማረፊያቸው ወደ ትውልድ መንደራቸው ወደ ኩኑ ተመልሰዋል፡፡ ደህና ይሁኑ እያልኩ እሰናበትዎታለሁ፡፡ ነብስዎ በሰላም ለዘላለም እረፍት ታግኝ፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ እ.ኤ.አ ዴሴምበር 15/2013፣ ለእኔ የዓመቱ ታላቁ የደስታ ዕለት ነው፡፡ ከዋሽንግተን ዲሲ ወጣ በማለት በአንድ ከተማ በሚገኝ የመሰብሰቢያ አዳራሽ በመገኘት ሰማያዊ ፓርቲን እና ወጣቱን የፓርቲውን ሊቀመንበር ይልቃል ጌትነት እንኳን ደህና መጣችሁ በማለት የክብር ሰላምታዬን ሳቀርብ ነበር፡፡ ጭቆናን እና የሰብአዊ መብቶች ደፍጣጮችን በሰላማዊ ትግል ለማንበርከክ ለሚታገሉት የዴሞክራሲያዊ ለውጥ ፈላጊ እና ለመንፈሰ ጠንካሮቹ የኢትዮጵያ ወጣቶች ክብር ለመስጠት፣ የማያቋርጥ እና ጽኑ ድጋፍ በቀጣይነት እንደምሰጥ ያለኝን ስሜት ለመግለጽ ነው እዚህ የተገኘሁት፡፡ በዝዚሕች ቀን የሰማያዊ ፓርቲ ምስከር አንደሆን ተጠረቼ ነው የመጣሁት::
በዚህ ዓመት የመጀመሪያ በነበረችው ትችቴ እ.ኤ.አ 2013 “የኢትዮጵያ የአቦ ሸማኔዎች (የወጣቱ ትውልድ) ዓመት” ይሆናል ብዬ ተምኘ ነበር:: ለዚህም ዕውን መሆን የኢትዮጵያን ወጣቶች በሙሉ ለመድረስ፣ ለማስተማር እና ለማሳወቅ ቃል ገብቼ ነበር። ቃሌን ጠብቄአለሁ:: እንደጠበቅሁም እቀጥላለሁ፡፡
በዛሬው ዕለት ከይልቃል ጋር እዚህ በመካከላችሁ በመገኘቴ ልዩ ክብር እና ሞገስ የተሰማኝ መሆኑን ለመግለጽ እወዳለሁ፡፡ የዛሬዋን ዕለት ለነጻነት የሚደረገውን ተጋድሎ፣ ከጎሳ የዘረኝነት አለመቻቻል እና ከአንባገነንነት እንዲሁም ከጭቆና ነጻ መሆን፣ ለማለም ነጻ መሆን፣ ለማሰብ ነጻ መሆን፣ ለመናገር ነጻ መሆን፣ ለመጻፍ እና ለመስማት ነጻ መሆን፣ ለመፍጠር ነጻ መሆን፣ ለመስራት ነጻ መሆን እና ነጻ ለመሆን ነጻ መሆን በማለት ራዕያቸውን ሰንቀው የሚታገሉትን የኢትዮጵያ ወጣቶችን ቃል አቀባይ እንዳገኘሁ ያህል ይሰማኛል፡፡
የኢትዮጵያ (የአፍሪካ ማለትም ይቻላል) ዕጣ ፈንታ በሁለት ትውልዶች ትከሻ ላይ የተንጠለጠለ ነው፡፡ ጆርጅ አይቴይ በግልጽ እንዳስቀመጡት የአፍሪካ “አቦሸማኔ (ወጣቶች)ትውልድ” “አዲሱን እና ጠንካራ፣ የማይበገር፣ ብሩህ አዕምሮ ያለው እና ነገሮችን በውል የሚያጤን የአፍሪካ ፕሮፌሽናሎችን እና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ምሩቃንን የሚያካትተው ቁጡ የህብረተሰብ ክፍል ነው፡፡ ይህ የህብረተሰብ ክፍል ግልጸኝነት፣ ተጠያቂነት፣ ሰብአዊ መብት እና መልካም አስተዳደርን በሚገባ የተረዳ እና ለተግባራዊነታቸውም በጽናት የቆመ ኃይል ነው፡፡“ በሌላ በኩል ደግሞ የአፍሪካ የጉማሬ ትውልድ (የኔ ትውልድ ማለት ነው) ጨለምተኝነት የነገሰበት፣ ምክንያታዊነት የጎደለው እና በቅኝ ግዛት የትምህርት ፖሊሲ ዘይቤ የታጠረ አመለካከት ያለው የህብረተሰብ ክፍል ነው፡፡ ይህ የህብረተሰብ ክፍል ብሩህ ራዕይ የለውም፣ ሁሉንም የአፍሪካ ችግሮች መንግስታት መፍታት ይኖርባቸዋል በሚል እምነት ለእራሱ ተደላድሎ እና በምቾት መኖርን የሚመርጥ የህብረተሰብ ክፍል ነው፡፡ መንግስት ሊያገኝ የሚገባው ብዙ ኃይል እና በርካታ የውጭ እርዳታ ነው የሚል አስተሳሰብ ያለው የህብረተስብ ክፍል ነው፡፡”
የዛሬዋ ዕለት ታላቅ ቀን ናት፣ ምክንያቱም እኔ የጉማሬው (የቀድሞ ትውልድ) አባል ብሆንም ከኢትዮጵያ የአቦ ሸማኔው ትውልድ መሪ ከይልቃል ጋር በጋራ የቆምኩባት ዕለት ናትና፡፡
በወጣቶች፣ ለወጣቶች ከወጣቶች ለተቋቋመው የፖለቲካ ድርጅት ለሰማያዊ ፓርቲ ግንባር ቀደም ደጋፊ ነኝ፡፡ ከኢትዮጵያ ህዝብ 70 በመቶ የሚሆነው ዕድሜው ከ35 ዓመት በታች ያለ የህብረተሰብ ክፍል ነው፡፡ ይህንን “ፓርቲ” ብሎ መሰየም ለእኔ ፍትሐዊ አይደለም፣ ምክንያቱም የፖለቲካ ድርጅት/ፓርቲ ስልጣን ከመያዝ ባለፈም መልኩ ሰማያዊ ፓርቲ የወጣት (የሠፊው ህዝብ 70 በመቶ የሚሆነው) ንቅናቄ ተቁዓም የህብረተሰብ ክፍል ነው፡፡ የኢትዮጵያ ወጣቶች ከግዴለሽነት ወደ ንቁ ተሳታፊነት፣ ከቸልተኝነት ወደ ጥንቁቅነት: ከስግብግብነት ወደ ማህበረሰባዊነት አስተሳሰብ፣ ከመከፋፈል ወደ አንድነት፣ ከጥላቻ ወደ ስምምነት፣ ከጥቃቅን እና እርባናየለሽ በሆኑ ነገሮች ከመጨቃጨቅ እና ከመታገል ይልቅ ወደ ዕርቅ የሚሄድበት የንቅናቄ ሂደት ነው፡፡
ሰማያዊ ፓርቲ “ሰማያዊ” የሚለውን ቀለም በስያሜነት ተጠቅሟል:: ይህም ስያሜ በኢትዮጵያ አንድነት፣ ሰላም እና ተስፋ የሚለውን የፓርቲውን ፍልስፍና ለማመላከት ሲባል የገባ ምልክት ነው፡፡ ልክ እንደተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሁሉ ሰማያዊው ቀለም ሰላም እና ተስፋ ለሁሉም አገሮች የሚለውን እንደምታ ይወክላል፡፡ ልክ እንደ የአውሮፓ ዩኒየን ሁሉ ከሁለት አስርት በላይ ሀገሮች በአንድ ላይ ሆነው የተዋጣለት የኢኮኖሚ እና የፖለቲካ አንድነትን ለማምጣት የሚያደርጉትን ጥረት ምልክትነት ይወክላል፡፡ እንደ ኢትዮጵያውያን ደግሞ ሰማያዊ ቀለም በሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን የተባበረች፣ ሰላሟ የተጠበቀ እና በተስፋ የተሞላች አገር መኖርን በምልክትነት ይወክላል፡፡
የሰማያዊ ፓርቲ ንቅናቄ አንድ ዓላማ ብቻ አለው፡፡ ይህም “ፍቅርን የተላበሰ ማህበረሰብ” መፍጠር ነው፡፡ ዶ/ር ማርቲን ሉተር ኪንግ ለሁሉም አሜሪካውያን ዜጎች የሰብአዊ እና የሲቪል መብቶችን ለማጎናጸፍ ያደረጓቸውን ጥረቶች ተናግረዋል፡፡ እንዲህም ብለዋል፣ “ሰላማዊ የህብረተሰብ ንቅናቄ መጨረሻው ዕርቅ ነው፡፡ መጨረሻው ኃጢአትን መናዘዝ እና ንስሃ በመግባት ሰላምን ማውረድ ነው፡፡ መጨረሻው ፍቅርን የተላበሰ ማህበረሰብ መመስረት ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ ፍቅር እና አስተሳሰብ ነው ተጻራሪ አስተሳሰብ ያላቸውን/በጠላትነት የቆሙትን ወገኖች ወደ ፍቅር ጓደኝነት ማምጣት የሚችለው፡፡ ፍቅር እንደ ሸማ የተላበሰውን እና በእራሱ ሰላም የተረጋገጠለትን የኢትዮጵያን ማህበረሰብ መመስረት የሰማያዊ ፓርቲ ንቅናቄ ህልውና ዕውን መሆን አውራ ምክንያት ነው፡፡”
ፍቅር የነገሰበትን የኢትዮጵያ ማህበረሰብ ለመመስረት ለሰማያዊ ፓርቲ ንቅናቄ ቀላል አይሆንም፡፡ ብዙ ጥረቶችን እና ዝግጅቶችን ይጠይቃል፡፡ ብዙም አድናቆትን የማይጠይቅ ነገር ግን ማንም ሊፈጽመው የሚችል ተግባር ነው፡፡ ፍቅር የሰፈነበትን ማህበረሰብ ለመመስረት የሰማያዊ ፓርቲ ንቅናቄ እና የኢትዮጵያ ወጣቶች ምን ማድረግ፣ ማሰብ እና ማለም ይኖርባቸዋል? የኢትዮጵያ ወጣቶች እና እረፍትየለሾቹ አቦሸማኔዎች ከብልሁ የአፍሪካ አንበሳ ከኔልሰን ማንዴላ ብዙ ይማራሉ የሚል እምነት አለኝ፡፡ ማንዴላ ለእረፍት የለሾቹ የኢትዮጵያ አቦሸማኔዎች ሊግሯቸው የሚችሏቸው ነገሮች…
ታላቅ ለመሆን ድፍረት ይኑራችሁ፣ ማንዴላ የኢትዮጵያ ወጣቶች ፍቅር የሰፈነበትን ማህበረሰብ ለመመስረት ታሪካዊ ዕጣ ፋንታቸውን እንዲሞክሩ ያሳስባሉ፡፡ ታላቅ የመሆን ዕጣ ፈንታቸውን እንዲወስኑ ድፍረት እንዲሰንቁ ይመክራሉ፡፡ እንዲህም ይላሉ፣ “አንዳንድ ጊዜ ታላቅ የመሆን ዕጣ ፈንታ በትውልድ ላይ የሚወድቅ ነው፡፡ ይህንን ታላቅ ትውልድ ልትሆኑ ትችላላችሁ፡፡ ታላቅነታችሁ ፍሬ እንዲያፈራም እመኛሁ፡፡“
ማህበረሰቡን ለመለወጥ ከመሞከራችሁ በፊት መጀመሪያ እራሳችሁን ለውጡ፣ አሮጌው የጥላቻ እና የፍርሃት መንገድ ለአዲሱ የመግባባት እና የዕርቅ መንገድ ቦታ መስጠት እንዳለበት እና የኢትዮጵያ ወጣቶች ፍቅር የሰፈነበትን ማህበረሰብ መመስረት እንዲችሉ ማንዴላ ምክራቸውን ለግሰዋል፡፡ መዘጋጀት አለባቸው፡፡ “ድርድር ሳደርግ ከተማርኳቸው ነገሮች አንዱ እራሴን እስክለውጥ ድረስ ሌሎችን መለወጥ አልችልም“፡፡ በፍጹም መጥላት የለባቸውም ምክንያቱም “ጥላቻ መርዝን እንደመጠጣት ያህል ነው፣ ጠላቴን ይገድልልኛል በሚል ተስፋ“፡፡ ጥላቻ ከውልደት በኋላ የሚመጣ ባህሪ ነው፡፡ “ባለው የቆዳ ቀለም ልዩነት፣ ባለው የአስተዳደግ ሁኔታ፣ ወይም ደግሞ በሚከተለው እምነት ምክንያት ማንም ማንንም ሊጠላ አልተወለደም፡፡ ሰዎች ጥላቻን መማር አለባቸው፣ እና ጥላቻን መማር ከቻሉ ፍቅር እንዲኖራቸው ሊማሩ ይገባል፣ ፍቅር በተፈጥሮ ወደ ሰው ልጅ ልብ ውስጥ ከተቃራኒው የበለጠ ለመግባት ስለሚችል፡፡“
ሙከራችሁን ቀጥሉበት፣ ማንዴላ የኢትዮጵያ ወጣቶች ምንጊዜም እንዲሞክሩ እና በፍጹም በፍጹም እጅ እንዳይሰጡ በመምከር በኢትዮጵያ ፍቅር የሰፈነበትን ማህበረሰብ የመመስረት ቃልኪዳን ለመጠበቅ አንድ ሰው በዘሩ ማንነት፣ በቋንቋው፣ በእምነቱ እና በክልሉ ጠቃሚነት ከጸጉሩ/ሯ ቀለም ልዩነት በስተቀር ጠቃሚነቱ እርባና እንደሌለው አጽንኦ ሰጥተው አስተምረዋል፡፡ በኢትዮጵያ “ፍትህ እንደጎርፍ ውኃ እንዲወርድና እውነት እንደማያቋርጥ የጅረት ምንጭ እንዲፈስ” ወጣቱ ትውልድ ትግሉን በጽናት መቀጠል እና ሙከራውን ማቆም እንደሌለበት ማንዴላ ምክር ለግሰዋል፡፡ በውድቀት ላይ ተመስርቶ የስኬት አዝመራ እንደሚታጨድ በመገንዘብ ወጣቶች ውድቀትን ሳይፈሩ ትግላቸውን መቀጠል እንዳለባቸው ማንዴላ ምክራቸውን ለግሰዋል፡፡ እንዲህም ብለዋል፣ “እኔን በማስገኘው ስኬት አትገምግሙኝ፣ ይልቅስ ምን ያህል ጊዜ እንደወደቅሁ እና ለስኬት ምን ያህል ጥረት በማድረግ እንደተነሳሁ እንጅ“ ውድቀት ኃጢአት አይደለም፡፡ ለመሞከር አለመቻል ነው ውድቀት ማለት፡፡ በህይወት ስንክሳር “ታላቁ ዝና ፍጹም አለመውደቅ አይደለም፣ ነገር ግን ትልቁ ነገር በወደቅን ቁጥር ለመነሳት የምናደርገው ጥረት ነው፡፡” ማንዴላ ለወጣቶቹ ሲመክሩ ወጣቶች በስኬት ማማ ላይ ፊጥ ለማለት ጥረት ማድረግ ብቻ ሳይሆን ትከሻቸውን በማጠንከር ሊመጡ የሚችሉትን ችግሮች ሁሉ በመጋፈጥ በድል አድራጊነት ለመውጣት ጥረት ማድረግ እንዳለባቸው ምክንያቱም “ታላቁን ተራራ ከወጣህ በኋላ ሌሎች ብዙ ሊወጡ የሚችሉ ተራሮች እንዳሉ መገንዘብ አስፈላጊ ነው፡፡” በማለት አስተምረዋል፡፡
በአንድነት ሁኑ፣ የኢትዮጵያ ወጣቶች እንደወጣት ኃይል በአንድነት መቆም እና ፍቅር የሰፈነበትን የኢትዮጵያ ማህበረሰብ መመስረት እንዳለባቸው ማንዴላ ምክራቸውን ለግሰዋል፡፡ እንዲህ ሲሉም መክረዋል፣ “አንድ ነጠላ ሰው ብቻውን ሀገሩን ነጻ ሊያወጣ ወይም ደግሞ ፍቅር የሰፈነበት የኢትዮጵያን ማህበረሰብ መመስረት አይችልም፡፡ አገራችሁን ነጻ ልታደርጉ ወይም ደግሞ ፍቅር የሰፈነበት የኢትዮጵያን ማህበረሰብ መመስረት የምትችሉት በአጠቃላይ በጋራ ስትንቀሳቀሱ ነው፡፡”
ጥሩ ሞራል ያለው/ላት ሰው ሁኑ፣ ደግነት የሞራል ዉበት ነው፡፡ ትክክለኛውን ነገር ለማድረግ ጥረት የማድረግ ጉዳይ ነው እና ማንም አዬ አላዬ ጥሩውን ነገር ከማድረግ ወደ ኋላ አለማለት ነው፡፡ “ከዚህ ቀደም እንደተናገርኩት ሁሉ ለእራስ ታማኝ መሆን ነው፡፡ በቅድሚያ እራሳችሁን ካልለወጣችሁ በህዝብ ላይ ውጤት ሊያመጣ የሚያስችል ተጽእኖ ልታመጡ አትችሉም…ታላላቅ የሰላም መሪዎች በሙሉ ሀቀኞች ናቸው፣ ታማኞች ናቸው፣ ነገር ግን ክብር ፈላጊዎች አይደሉም::”
አገር ወዳድ አርበኛ ሁኑ፣ ማንዴላ በአገር ወዳድ አርበኝነት ላይ እምነት ነበራቸው፣ እናም የኢትዮጵያ ወጣቶች ለህዝቦቻቸው እና ለአህጉራቸው አርበኛ መሆን እንዳለባቸው መክረዋል፡፡ ማንዴላ እንዲህ አሉ፣ “በመጀመሪያ ደረጃ እኔ እራሴን ሁሌም የአፍሪካ አህጉር ወዳድ አርበኛ አድርጌ እቆጥራለሁ፡፡“ የአፍሪካ አርበኞች የቅኝ ገዥ ጌቶቻቸውን ከአሁጉሩ አባረዋል፡፡ የደቡብ አፍሪካ አርበኞች አፓርታይድን ያለደም መፋሰስ አስወግደዋል፡፡ የኢትዮጵያ ወጣቶች በአሁኑ ጊዜ በጋራ በመሆን ድህነትን፣ ድንቁርናን እና አምባገነንነትን በማስወገድ ፍቅር የሰፈነበት የኢትዮጵያን ማህበረሰብ መገንባት ይኖርባቸዋል፡፡
ደፋር ሁኑ፣ የኢትዮጵያ ወጣቶች ፍቅር የሰፈነበት ማህበረሰብን ለመገንባት እንዲችሉ ደፋር መሆን በጣም አስፈላጊ ነገር መሆኑን ማንዴላ አጽንኦ በመስጠት መክረዋል፡፡ ድፍረትን የበለጠ ለመግለጽም ማንዴላ እንዲህ ብለዋል፣ “ድፍረት የፍርሃት አለመኖር ብቻ አለመሆኑን ተረድቻለሁ፣ ነገር ግን በፍርሃት ላይ ድል መቀዳጀት ማለት ነው፡፡ ጀግና ሰው ማለት ፍርሃት የማይሰማው ማለት አይደለም፣ ነገር ግን ፍርሃትን በጽናት የሚያሸንፍ እንጅ::“
ትልቅ ነገር አልሙ፣ ማንዴላ የኢትዮጵያ ወጣቶች ፍቅር የነገሰበት ማህበረሰብን በኢትዮጵያ የመመስረት ትልቅ ነገር እንዲያልሙ መክረዋል፡፡ የማህበረሰቦቻቸው መሰረትም ሰላም፣ አንድነት እና ተስፋ መሆን እንዳለባቸው በአጽንኦ ተናግረዋል፡፡ ስለህልሞቻቸውም እንዲህ ብለዋል፣ “በእራሷ ሰላሟ የተረጋገጠ አፍሪካን አልማለሁ፡፡ ለቆንጆዋ ደቡብ አፍሪካ ህልሞች ካሉ ወደ ግቧ የሚያደርሱ መንገዶችም አሉ፡፡ እነዚህ ሁለቱ መንገዶች ደግነት እና ይቅርታ አድራጊነት በመባል ተሰይመዋል፡፡“
ከኋላ ሆናችሁ ምሩ፣ ማንዴላ በአሮጌው የአስተዳደር ስልት አንዴ ስልጣን ከተቆናጠጡ በኋላ እስከሞት ድረስ ስልጣን አልለቅም ማለት ቦታ እንደሌለው ለኢትዮጵያ ወጣቶች በመምከር ፍቅር የነገሰበት ማህበረሰብን መገንባት እንዳለባቸው በአጽንኦ ተናግረዋል፡፡ ማንዴላ ወጣቶቹን እንዲህ በማለት ተማጽነዋል፣ “ከመንጋዎቹ በኋላ እንደሚሆን እረኛ በጣም ፈጣኑን ከፊት እንዲሆን መፍቀድ፣ሌሎቹ ግን እንዲከተሉ ማድረግ፣ ሁሉም ከኋላ ባለ ኃይል እንደሚታዘዙ እና እንደሚመሩ እንዲያውቁት ሳይደረግ ጉዞውን ማስኬድ“፡፡ ማንዴላ እንዲህ ይላሉ፣ “ከኋላ ምራ እና ሌሎችን ከፊት አድርግ፣ በተለይም ጥሩ ነገር በሚኖርበት ጊዜ እና ድልን በምታከብሩበት ጊዜ“፡፡ አደጋ በሚኖርበት ጊዜ የፊተኛውን ረድፍ ትይዛላችሁ፡፡ ከዚያ በኋላ ህዝብ የእናንተን አመራር ሰጭነት ያደንቃል… ከኋላ ሆነህ ምራ ሌሎቹ ከፊት ነኝ የሚል እምነት እንዲኖራቸው አድርጉ፡፡ “መሪነትን ማቆምም መምራት ነው“ በማለት ማንዴላ ወጣቶቹ በአንክሮ አንዲመለከቱት መክረዋል፡፡
ችግርና መከራ በትግል ላይ አንዳለ እወቁ ፣ በኢትዮጵያ ፍቅር የሰፈነበት ማህበረሰብን ለመገንባት በሚደረገው ትግል የኢትዮጵያ ወጣቶች ብዙ የህግ ሂደቶች እና ቅጣቶች እንደሚገጥሟቸው ማንዴላ ለወጣቶቹ ምክር ለግሰዋል፡፡ ከዚሁም ጋር በማያያዝ በትግል ሂደቱ ውስጥ ወጣቶቹ እንደሚሰቃዩ እንደሚፈረድባቸው፣ እንደሚዋረዱ፣ ኢሰብአዊነት ድርጊት እንደሚፈጸምባቸው ማንዴላ ግልጽ አድርገውላቸዋል፡፡ በመጨረሻም ነጻነት እንደሚመጣ እርግጠኞች ሆነዋል፡፡ “ትናንት አክራሪ ተብየ ነበር፣ ከእስር ቤት ስወጣ ግን ብዙ ህዝቦች ጠላቶቸ ሳይቀሩ በእቅፋቸው አስገቡኝ፣ እናም ይኸንን ነው እንግዲህ ለሌሎች ሰዎች መናገር ያለብኝ፡፡ በሀገራቸው ለነጻነት የሚታገሉ ሰዎች አሸባሪዎች ናቸው“ የሚለውም መታወቅ አለበት፡፡
ከጠላቶቻችሁ ጋር ሰላም ሁኑ፣ የኢትዮጵያ ወጣቶች ፍቅር የሰፈነበት ማህበረሰብ በኢትዮጵያ ለመገንባት እና ለሰላም ሲባል በተቃራኒ ካሉ ወገኖች ጋር መገናኘት፣ እጅ መጨባበጥ እና ጠላቶቻቸውን እቅፍ አድርገው መሳም አንዳለባቸው ማንዴላ መክረዋል፡፡ “ከጠላትህ ጋር ሰላም እንዲመጣ ከፈለግህ ከእርሱ ጋር አብረህ መስራት አለብህ፣ ከዚያም ጓደኛ ታደርገዋለህ፡፡“ ማለታቸውም የዚህን እውነተኛ አባባል ያረጋግጣል፡፡
ድህነትን ተዋጉ፣ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ወገኖቻቸው ህይወት የድህነት አደጋ አንዣቦባት በምትገኘው ኢትዮጵያ ፍቅር የሰፈነበት ማህበረሰብን መገንባት እንደማይቻል ማንዴላ ለኢትዮጵያ ወጣቶች በመግለጽ ድህነትን ለማስወገድ በሚደረገው ትግል ንቁ ተሳታፊ ሆነው ሀገራቸውን እንዲታደጉ ተማጽኖ አቅርበዋል፡፡ ከመጨረሻው የድህነት ቋት ውስጥ ተዘፍቃ የምትገኘውን ሀገሩን የኢትዮጵያ ታላቁ ትውልድ እና የወደፊቱ ብሩህ ተስፋ መንጥቆ እንደሚያወጣት ምክራቸውን ለግሰዋል፡፡ ድህነትን ማስወገድ የልገሳ ስራ አይደለም፣ የፍትህ ጉዳይ እንጅ፡፡ እንደ ባርነት እና አፓርታይድ ሁሉ ድህነት ተፈጥሯዊ አይደለም፡፡ ሰው ሰራሽ ነው፣ እናም በሰዎች ጥረት ሊጠፋ እና ድል ሊደረግ ይችላል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ታላቅነት በትውልድ ላይ ይወድቃል፡፡ ይህንን ታላቅ ትውልድ ልትሆኑ ትችላላችሁ፡፡ ታላቅነታችሁም ፍሬ እንዲያፈራ እመኛለሁ፡፡
በመርሆዎች ላይ በፍጹም አትደራደሩ፣ በኢትዮጵያ ፍቅር የሰፈነበት ማህበረሰብ ለመመስረት በሚደረገው የትግል ሂደት ውስጥ የኢትዮጵያ ወጣቶች በመርሆዎች ላይ መደራደር እንደሌለባቸው ማንዴላ አጽንኦ በመስጠት ምክር ለግሰዋል፡፡ ማንዴላ ለወጣቶቹ ሲያስተምሩ እድሜልኬን ከአፓርታይድ እና ከዘረኝነት ጋር ስዋጋ ስታግል ኖሪያለሁ ምክንያቱም እነዚህ ጭራቆች ለሰው ልጅ ሟች ጠላቶች ናቸው፡፡ “የዘር መድልዎን እና መገለጫዎቹን ሁሉ በጣም እጠላለሁ “በህይወት ዘመኔ ሁሉ ስታገል ቆይቻለሁ፣ አሁንም እየታገልኩ ነው እና ቀኖቸ እስኪያልቁ ድረስ መታገሉን እቀጥላለሁ…፡፡” ብለው ነበር፡፡ ይህንን በሚገባ አድረገውታል፣ ፈጽመውታልም፡፡ የኢትዮጵያ ወጣቶች በጥላቻ እና በሁሉም መገለጫዎቹ ላይ ማለትም በጎሰኝነት፣ በፖለቲካ ማንነት፣ በማህበረሰባዊነት፣ በጎሳ ክፍፍል፣ በጾታ ጭቆና፣ በኢኮኖሚ ብዝበዛ እና በህብረተሰብ አድልኦ ላይ በመርህ ላይ የተመሰረተ እና ድርድር የማያስገባ አቋም መያዝ እንዳለባቸው ማንዴላ በአጽንኦ ጠይቀዋል፡፡
ብሩህ አላሚ እና ጽናት ይኑራችሁ፣ የኢትዮጵያ ወጣቶች በኢትዮጵያ ፍቅር የሰፈነበት ማህበረሰብ በመገንባቱ ሂደት ላይ ብሩህ አላሚዎች መሆን እንዳለባቸው ማንዴላ መክረዋል፣ ምክንያቱም የኢትዮጵያውያን ምርጥ ቀኖች ገና እየመጡ ነውና፡፡ ስለብሩህ አላሚነት አንስተው ሲገልጹም “እኔ በመሰረቱ ብሩህ አላሚ ነኝ፡፡ ከተፈጥሮም መጣ ከእራስ ጥንካሬ የምለው ነገር የለም፡፡ በከፊል ብሩህ አላሚ መሆን ማለት የአንድን ሰው እራስ ወደ ጸሐይ ቀጥ ብሎ እንዲያመለክት እንዲሁም የአንድ ሰው እግሮች ወደፊት እንዲራመዱ የማድረግ ያህል ነው፡፡ በሰው ላይ ያለኝ እምነት በሚገባ በሚፈተሽበት ጊዜ ብዙ የጨለማ አጋጣሚዎች ነበሩ፡፡ ነገር ግን ተስፋ ቢስ ለመሆን እጅ አልሰጥም፣ አላደርገውም አልሞክረውምም፡፡ ያ መንገድ የሽንፈት እና የሞት ነው፡፡ “የኢትዮጵያ ወጣቶች ያን ረዥሙን ጉዞ መጓዙን መቀጠል አለባቸው፡፡ የማንዴላ ጠንካሮች መሆን አለባቸው፡፡ “ጥንካሬው እና አስፈላጊው ጥበብ ቢኖርህም በዓለም ላይ ወደ ግለሰባዊ ድልነት ልትቀይራቸው የማትችላቸው ጥቂት መጥፎ አጋጣሚዎች አሉ፡፡“
ተማሩ፣ ህዝብንም አስተምሩ፣ ማንዴላ ፍቅር የሰፈነበት ማህበረሰብ በኢትዮጵያ ለመመስት ትምህርት ቁልፍ መሳሪያ እንደሆነ ለኢትዮጵያ ወጣቶች አስተምረዋል፡፡ ስለትምህርት ጠቃሚነት ማንዴላ እንዲህ ብለዋል፣ “ዓለምን ለመለወጥ ትምህርት ትልቁ መሳሪያ ነው፡፡ ዜጎቹ ካልተማሩ በስተቀር ማንም ሀገር ቢሆን እድገት ሊያስመዘግብ አይችልም፡፡“
ዝምተኛ አትሁኑ፣ ፍቅር የሰፈነበት ማህበረሰብን በኢትዮጵያ ለመገንባት በጭራቅነት እና በፍትህ እጦት ጊዜ የምን አገባኝነት ባህሪ መኖር እንደሌለበት ማንዴላ ለኢትዮጵያ ወጣቶች አስተምረዋል፡፡ ጭራቃዊ ድርጊቶች ሲፈጸሙ እየተመለከቱ ዝም ከማለት የበለጠ ጭራቅነት የለም ብለዋል፡፡ ጭራቃዊ ድርጊት በየትኛውም መልኩ ሲፈጸም ስናይ ልንዋጋው ይገባል፣ ወጣቶች ጭንቅላታቸውን ክፍት ካደረጉ እውነት በእራሱ ይገለጽላቸዋል፡፡ “ምንም ዓይነት ድንገት ያገኘሁት ግንዛቤ የለኝም፣ ምንም ዓይነት መረጃም የለኝም፣ እውነት የተገለጸበት አጋጣሚም የለም፣ ነገር ግን በሺዎች የሚቆጠሩ ጨዋነት የጎደላቸው ድርጊቶች፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ውርደቶች፣ እና እንድናደድ፣ እንዳምጽ እና ህዝቤን አፍኖ የያዘውን ስርዓት እንድዋጋ በሺዎች የሚቆጠሩ ላስታውሳቸው የማልችላቸው አጋጣሚዎች ያሉ መሆኑን“ በማለት ማንዴላ ለአፍሪካ ወጣቶች አስተምረዋል፡፡ በተናገርኩት ላይ የተወሰነ ቀን የለም፣ ስለሆም እራሴን ለህዝቤ ነጻነት መስዋዕት አደርጋለሁ፣ ይልቁንም በተግባር እያዋልኩት መሆኑን እራሴን አዚያው ውስጥ አገኘሁት፣ እንደዚያ ካልሆነ ወደ ተግባር መተርጎም የሚቻል አይሆንም፡፡”
በኢትዮጵያ ፍቅር የሰፈነበት ማህበረሰብ ለመገንባት የሚደረገው ትግል ቀላል አይደለም…፣ ማንዴላ በኢትዮጵያ ፍቅር የሰፈነበት ማህበረሰብ ለመገንባት የኢትዮጵያ ወጣቶች መታገል እንዳለባቸው በአጽንኦ መክረዋል፡፡ እንዲህም ብለዋል፣ “ወደ ነጻነት የሚያስኬድ ቀላል ጉዞ የትም ቦታ አይገኝም፣ እናም አብዛኞቻችን ከምንመኘው የተራራ ጫፍ ላይ ከመድረሳችን በፊት ደግመን እና ደጋግመን በሸለቆው የሞት ጥላ ስር ማለፍ አለብን፡፡“
ገና ብዙ የሚወጡ ዳገቶች ተራሮች ይቀራሉ፣ በኢትዮጵያ ፍቅር የሰፈነበት ማህበረሰብ ለመገንባት የኢትዮጵያ ወጣቶች ብዙ ኮረብታዎችን የመውጣት፣ ሸለቆዎችን የማቋረጥ እና ተራሮችን የመውጣት የትግል ጉዞ ይጠብቃቸዋል፡፡ በጉዞው ላይ ያልተጠበቁ አደጋዎች ያጋጥማሉ፡፡ ለማረፍ ትንሽ ጊዜ ነው ያለው፡፡ ማንዴላ እንዲህ ብለዋል፣ “ለነጻነት የሚያስኬደውን ያንን እረዥሙን ጉዞ ተጉዠዋለሁ፡፡ በእራስ መተማመንን እንዳላጣ ጥረት አድርጊያለሁ፡፡ በጉዞው መንገድ ላይ የተሳሳቱ ቅደምተከተሎችን ፈጽሚያለሁ፡፡ ነገር ግን ከትልቁ ተራራ ጭፍ ላይ ለመውጣት ገና ብዙ ኮረብታዎችን መውጣት አንደሚኖርብኝ አረጋግጫለሁ፡፡ ለማረፍ ትንሽ ጊዜ ወስጃለሁ፣ ሰረቅ አድርጌም የከበበኝን አስደናቂውን አካባቢያዊ ሁኔታ ተመልክቻለሁ፣ የተጓዝኩትን ርቀት መለስ ብዬ ተመልክቻለሁ፣ ግን ለጥቂት ጊዜ ብቻ ነው ለማረፍ የቻልኩት፣ ነጻነትን ለማግኘት ኃላፊነት መምጣት አለበት፣ እና በምንም ዓይነት መልኩ ከወዲያ ወዲህ እያልኩ አልንገዋለልም፣ ረዥሙ ጉዞዬ አልተጠናቀቀምና፡፡“
ሁልጊዜ ደግ ለመስራት ሞክሩ፣ ይቅርታ ለማድረግ፣ ዕርቅ ለማውረድ…. በኢትዮጵያ ፍቅር የሰፈነበት ማህበረሰብ ለመገንባት ጥሩ ነገር ማድረግ፣ ይቅርታ ማድረግ እና ዕርቀ ሰላም ማውረድ አስፈላጊ እንደሆነ ማንዴላ ለኢትዮጵያ ወጣቶች ምክር ለግሰዋል፡፡ የመሞከርን አስፈላጊነት ለማስገንዘብም እንዲህ ብለዋል፣ የስኬት ቃልኪዳን ባይኖርም ሞክሩ፣ ውድቀት እንዳለ ብታውቁም ሞክሩ፣ ጥርጣሬ ያለ እና እርግጠኝነት የጎደለ መሆኑን ብታውቁም ሞክሩ፡፡ ደክማችሁ እና መቀጠል የማትችሉ መሆኑን ብታውቁም እንኳ ሞክሩ፡፡ ተስፋ በማይኖርበት ጊዜም ሞክሩ፡፡ ዓላማችሁን ካሳካችሁ በኋላም ቢሆን ሞክሩ፡፡ ማንዴላ እንደሞከሩት ሁሉ ሞክሩ፡፡
ሰማያዊ ፓርቲ ንቅናቄ ለእኔ ምን ሰራልኝ ብለህ/ሽ አትጠይቅ/ቂ፣ ይልቁንም እኔ ለሰማያዊ ፓርቲ ንቅናቄ ምን አድርጌለታለሁ ብለህ/ሽ ጠይቅ/ቂ… (ይቀጥላል)
ታህሳስ 6 ቀን 2006 ዓ.ም.