የሳውዲ አረቢያው ቀውስ መከሰት ለኢትዮጵያውያን ዲያስፖራ

 በፕሮፌሰር ዓለማየሁ ገብረማርያም

ትርጉም ከነጻነት ለሀገሬ

የሳውዲ አረቢያው ቀውስ መከሰት ለኢትዮጵያውያን/ ዲያስፖራ ፍቅርና አንድነት ትምህርት ሰጥቶ ይሆን?

በአረብ አገር በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን/ት ስደተኛ ሠራተኞች ላይ የሚደረገው ህገወጥ የማሰቃየት እርምጃ በአስቸኳይ ይቁም! በአሁኑ ወቅት በሳውዲ አረቢያ በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን/ት ስደተኛ ሰራተኞች ላይ በሪያድና በአዲስ አበባ ከተሞች ባሉ ገዥ አካሎች እየተፈጸመ ያለው የሰብአዊ መብት እረገጣ ከፍተኛ ቁጣን የቀሰቀሰ ከመሆኑም በላይ ኢትዮጵያውያን/ት የዲያስፖራ ማህበረሰብ ለጉዳዩ ልዩ የሆነ ትኩረት እንዲሰጡትና ለወገኖቻቸው የማያቋርጥ ድጋፍ እንዲያደርጉ ምቹ አጋጣሚን ፈጥሯል፡፡ ባለፉት በርካታ ሳምንታት በሳውዲ አረቢያ በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን/ት ላይ እየተፈጸመ ባለው አስደንጋጭ የሰብአዊ መብት እረገጣ የቪዲዮ ምስል መታየት መጀመሩን ተከትሎከአውስትራሊያ እስከ አሜሪካ ባሉ በአስር ሺዎች በሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን/ት ዲያስፖራ ማህበረሰብ ላይ ከፍተኛ ቁጣ እና የልብ ስብራት በማስከተሉ ምክንያት በየአካባቢያቸው ባሉ የሳውዲ አረቢያ ቆንስላዎችና የዲፕሎማሲ ማዕከላት በሮች ላይ ፊት ለፊት በመሰለፍ በግንባር በመግጠም ባሳዩት ቆራጥ ኢትዮጵያዊ የተቃውሞ ወኔ የመብት ረጋጮችን የሳውዲ አረቢያ ገዥ ባለስልጣኖች በማሸማቀቅ ላይ ይገኛሉ፡፡ ከ6  – 7 ሺ የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን/ት ዋሽንግተን ዲሲ በሚገኘው ከሳውዲ አረቢያ ኤምባሲ ፊት ለፊት በመገኘት የሳውዲ አረቢያ ገዥ በኢትዮጵያውያን/ት ላይ እየፈጸመ ያለውን ህገወጥ እርምጃና የሰብአዊ መብት እረገጣ በአስቸኳይ እንዲያቆም በመጠየቅ በሳውዲ አረቢያ ከሚገኙ ወገኖቻቸው ጋር የማያቋርጥ ትብብርና ወገናዊ ድጋፍ እንደሚያደርጉ በአደባባይ በግልጽ አሳይተዋል፡፡ በተመሳሳይ መልኩ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን/ት የዲያስፖራ ማህበረሰብ አባላት ከአትላንታ እስከ ሲያትል ከተሞች በመሰለፍ ተቃውሟቸውን አሰምተዋል፡፡ ሌሎች በሺዎች የሚቆጠሩት ደግሞ በአውሮፓ የተለያዩ ከተሞች በመውጣት ሰላማዊ ተቃውሟቸውን ገልጸዋል፡፡ የሰላማዊ ሰልፍ አድራጊዎች በየደረሱባቸው ቦታዎች ሁሉ ባነሮችን በመያዝ ድምጻቸውን ከፍ በማድረግ “ሳውዲ አረቢያ ሃፍረተኛ! ሃፍረተኛ! ሃፍረተኛ! “ሳውዲ አረቢያ ሃፍረተኛ!” በማለት ተቃዎሟቸውን አሰምተዋል፡፡

በሳውዲ አረቢያ በሚገኙ ኢትዮጵያውያን/ት ስደተኛ ሰራተኞች ላይ እየተደረገ ያለው የሰብአዊ መብት እረገጣና ህገወጥ አያያዝ በአስተማማኝ መረጃ ላይ ተደግፎ የቀረበ በመሆኑ ሊካድ የሚችል ጉዳይ አይሆንም፡፡ ሂዩማን ራይትስ ዎች/Human Rights Watch እ.ኤ.አ ዴሴምበር 1/2013 ባወጣው ዘገባ መሰረት “የሳውዲ አረቢያ መንግስት በግዛት ክልሉ ውስጥ በሚኖሩ የውጭ አገር ሠራተኞች ላይ የኃይል እርምጃን በመውሰድ በሳውዲ አረቢያ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን/ት ስደተኛ ሰራተኞችን የአካል ጉዳት ሰለባ እንዲሆኑ አደርጓል፣አንዳንዶችንም ገድሏል፣ ወደ አገራቸው ለመመለስ የሚፈልጉትን ኢትዮጵያውያን/ት ደግሞ ያለበቂ ምግብና መጠለያ አቅርቦት በጊዚያዊ የእስር ቤት ማዕከሎች አጉሮ ይገኛል“ በማለት በግልጽ አስቀምጦታል፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ ኢትዮጵያውያን/ት ዲያስፖራ ማህበረሰብ በወገኖቹ ላይ እየተፈጸመ ያለውን ግፍ በመመልከት በተግባር እያሳየ ያለውን ንዴትና ቁጣ ሶስት ዋና ዋና ነገሮች በትክክል ይገልጹታል፡፡ 1ኛ) የሳውዲ አረቢያ የመንገድ ላይ ዘራፊዎች እና የፖሊስ ሌቦች እንዲሁም ህገወጦች ኢትዮጵያውያን/ት ስደተኛ ሠራተኛ ዜጎችን ከየቤታቸው በማስወጣት በየመንገዱ በመጎተት በቃላት ለመግለጽ በሚያስቸግር መልኩ ጭካኔና አረመኔነት በተመላበት ሁኔታ ሲደበድቡ፣ ሲዘርፉና ሲያስሩ በመታየታቸው፣ 2ኛ) የሳውዲ አረቢያ ገዥ አካል የእራሱ ፖሊሶችና ሁከት ፈጣሪዎች በእብሪት ተነሳስተው በኢትዮጵያውያን/ት ስደተኛ ሰራተኞች ላይ ያለምንም ማቋረጥ ጥቃት ሲሰነዝሩ እያየ ምንም ነገር ሳያደርግ በማንአለብኝነት መመልከቱ፣ 3ኛ) በኢትዮጵያ ያለው ገዥ አካል ከመሰሉ ገዥ የሳወዲ አረቢያ አካል ጋር በመሞዳሞድ የገንዘብ እርዳታ ስለሚያገኝ በጉዳዩ ላይ የመጨረሻ ደካማነትና የእግር ላሽነት ባህሪ በግልጽና በዓለም የአደባባይ መድረክ ላይ በማሳየት ላይ በመገኘቱ የሚሉት ናቸው፡፡

የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ማህበረሰብ እና በአትዮጵያ ያለው ገዥ አካል በስደተኛ ኢትዮጵያውያን/ት ላይ በሳውዲ አረቢያ ገዥ አካል እየደረሰ ባለው የሰብአዊ መብት እረገጣና ህገወጥ አያያዝ ሁለት የማይገናኙና ተጻራሪ የሆኑ ምላሾን ሲያንጸባርቁ ይታያሉ፡፡ በአንድ በኩል በውጭ አገር ያለው የዲያስፖራ ማህበረሰብ በሳውዲ አረቢያ ገዥ አካል በሳውዲ አረቢያ በሚኖሩ ስደተኛ ሠራተኛ ኢትዮጵያውያን/ት ላይ እየደረሰ ባለው መከራ እና ስቃይ ከወገኖቹ ጎን በጽናት ሲቆም በተጻራሪው ገዥው በአዲስ አበባ የሚገኘው አካል ደግሞ ጠንከር ያለ መግለጫ ከማውጣት ወደኋላ ያፈገፍጋል፣ እንደ አሉሚኒየም ብረት ወደኋላ ይለመጣል፣ የሳውዲን ገዥ አካልን ጫማ ለመላስ ወደ ተረከዙ ያጎነብሳል፣ እንዲሁም አምባገነኑን አረብ ይቅርታ ይጠይቃል፡፡ በአጭሩ ሎሌነቱን በይፋ አሳይቷል!፡፡

ከወባ ትንኝ ተመራማሪነት በፍጥነት ወደ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት የተሸሙትና እ.ኤ.አ ከ2015 አገራዊ “ምርጫ” በኋላ የጠቅላይ ሚኒስትርነቱን ቦታ ይጠቀልላሉ ተብለው የሚጠበቁት ቴዎድሮስ አድሃኖም የሳውዲ አረቢያ ባለስልጣኖችን ውሳኔ እና ህገወጥ ስደተኞችን የማባረር ፖሊሲያቸውን ኢትዮጵያ እንደምታከብር በድፍረት ለብዙሃን መገናኛ ይፋ መግለጫ  ሰጥተዋል፡፡ ሳውዲ አረቢያ ውስጥ በኢትዮጵያውያን/ት ላይ በተደረገው የዜጎች ህገወጥ አያያዝ ስሜታቸው የተጎዳ መሆኑን ለሳውዲ አረቢያው አምባሳደር በቀልድ መልክ ገልጸው ይደልዎ ብለዋል፡፡ በዲፕሎማሲያዊ በእራስ መተማመን መልክ አድሃኖም “ይህ ተቀባይነት የለውም” ብለዋል፡፡ እርሳቸውና ገዥው አካል ነገሮችን ሁሉ በቁጥጥራቸው ስር እንዳደረጉ በሚመስል መልኩ አድሃኖም “ዜጎቻችንን ለመቀበል ሙሉ በሙሉ ዝግጅታችንን ያጠናቀቅን መሆናችንን ላረጋግጥላችሁ እወዳለሁ“ በማለት የምጸት ጩኸት አሰምተዋል፡፡

ማዘናቸውን የገለጹበት ሁኔታ ከልብ ያልሆነ፣ ለታይታ እና ለይስሙላ የተደረገ፣ የባለስልጣንነት ሞገስ የሌለውና እርባናየለሽ ነበር፡፡ እንዴት አንድ በከፍተኛ የኃላፊነት ቦታ ላይ የተቀመጠ ባለስልጣን የእራሱን ዜጎች ለሚያዋርድ የሌላ አገር ፖሊሲ “ክብር” ይሰጣል? እንዴት አንድ ሰው የአንድን በባዕድ አገር የሚኖሩ ወንድሞችና እህቶች አስገድዶ የሚድፍር፣ የሚገድል፣ ሰውነትን የሚበጣጥስ፣ የሚያሰቃይና ተጠርጣሪ ነው በማለት ያለፍርድ የሚገድል ኃይል በእራሱ አስተሳሰብ በመመራት “ተቀባይነት የለውም” የሚለውን ትርጉምየለሽ የዲፖሎማሲ ቃል ይመርጣል? እንዴት አንድ ሰው በትክክለኛው የዲፕሎማሲያዊ ንዴትና ቁጣ ኖሮት በህጋዊ መንገድ ጉዳዩን ለመከታተል ሳይሞክር “ስሜቴ ተጎድቷል” እንዲሁም “አዝኛለሁ” ሊል ይችላል?

ስዕል የአንድ ሺ ቃላትን ያህል የመናገር ኃይል ያለው መሆኑ ሀቅ ነው፡፡ የሳውዲ አረቢያዎች የሰብአዊ መብት እረገጣ የቪዲዮ ምስሎች የዲያስፖራውን ቁጣ የመቀስቀስ ኃይል ነበራቸው፡፡ በቀላሉ ሊታይ የማይገባው እውነታ በሳውዲ አረቢያ ገዥ አካል በኢትዮጵያውያን/ት ዜጎች ላይ የተፈጸመው አሳንሶ የማየት፣ የማዋረድ፣ ማሰቃየትና ሰብአዊ መብትን መርገጥ በተመሳሳይ መልኩ በተራው ኢትዮጵያውያን/ት ላይ በኢትዮጵያው ገዥ አካል ላለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ሲፈጸም ቆይቷል፡፡ የአድሃኖም ገዥው አካል ነጻውን ፕሬስ በማሽመድመድ ተንሰራፍቶ የሚገኘውን የሰብአዊ መብት እረገጣ ከህዝብ ዕይታ ለመደበቅ ያደረገው ጥረት  በአብዛኛው ስኬታማ ቢሆንም ሁሉንም ደብቆ ለማስቀረት ግን አልተቻለውም፡፡

ብዙ አስደንጋጭ የፎቶግራፍ ምስሎች በማስረጃነት ቀርበዋል፣ እነዚህም የፎቶግራፍ ምስሎች የሳውዲ አረቢያ ገዥ አካል በኢትዮጵያውያን/ት ላይ ከፈጸመው የሰብአዊ መብት እረገጣ የበለጠ የኢትዮጵያ ገዥ አካል በተራ ኢትዮጵያውያን/ት ዜጎች ላይ የፈጸመው አስደንጋጭ የሰብአዊ መብት እረገጣ ፎቶግራፍ የበለጠ አስደንጋጭ ነው፡፡ በሳውዲ አረቢያ ገዥ አካል በኢትዮጵያውያን/ት ስደተኛ ሰራተኞች ላይ በኖቬምበር 2013 የተፈጸመው የሰብአዊ መብት እረገጣ በኢትዮጵያ ገዥው አካል በተራ ኢትዮጵያውያን/ት ላይ በኦክቶበር 2013፣ በኖቬምበር 2012፣ በዴሴምበር 2011፣ ወዘተ በተመሳሳይ መልኩ ተፈጽሟል፡፡ ከጥቂት ሳምንታት በፊት ገዥው አካል እስረኞችን ከህግ አግባብ ውጭ አስገድዶ የእምነት ቃል እንዲሰጡ ያደረገውን ሂዩማን ራይትስ ዎች በዘገባው “በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኘው ማዕከላዊ እየተባለ በሚጠራው እስር ቤት እስረኞች በማያቋርጥ ሁኔታ በጥፊ ይጠናገራሉ፣ በእርግጫ ይደበደባሉ፣ በቦክስ ይነረታሉ፣ በዱላና በጠብመንጃ ሰደፍ ይደበደባሉ፡፡ ጥቂቶቹ በሚያሰቃይ ሁኔታ እጆቻቸውን ከኩማዎቻቸው ላይ በማንጠልጠል፣ ወይም ደግሞ እጆቻቸውን ከጭንቅላታቸው በላይ ከፍ አድርገው በማቆም ማሰርና  ለብዙ ጊዜ እየተደበደቡ እንዲቆዩ ማድረግ“ አካቶ አቅርቦታል፡፡

ዋናው ከክስተቱ የተማርኩበት አጋጣሚ፣ የነቃና የተበሳጨ ህዝብን መመልከት፣ እውነት ለመናገር ለእኔ አሁን ባለው የሳውዲ አረቢያ ሁኔታ ዋናው “የተማርኩበት አጋጣሚ”  ብዬ የምወስደው አብዛኛው የዲያስፖራ ማህበረሰብ በዚህች አጭር ጊዜ ውስጥ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተሰባስቦ ተቃውሞውን በመግለጽ እረገድ ውጤታማ መሆኑ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ማህበረሰብ በዚህ አይነት ቀልጣፋ በሆነ መልክ፣ ኃይልና አስደናቂ ፍላጎት ስልታዊ በሆነ መልክ ዓለም አቀፍ የቁጣ ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግ አይችልም የሚለውን የቀድሞ እምነቴን እንድሰርዝ አድርጎኛል፡፡ በእርግጠኝነት ለመናገር ይህ ድርጊት ለእኔ “ይበል” የሚያሰኝ ነው፡፡ ላለፉት ጥቂት ዓመታት የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ማህበረሰብ አይቻለሁ፣ ከተለመዱት የመብት ተሟጋቾች በስተቀር አብዛኛው ለእኔ ዝምተኛ ብቻ ሳይሆን የተኛም ጭምር መስሎ ይታየኝ ነበር፡፡ ነገር ግን እ.ኤ.አ በኖቬምበር 2013 በሚያስደንቅ ሁኔታ ግዙፉን የኢትዮጵያን ዲያስፖራ በንቃት ሲሳተፍ ተመልክቻለሁ፡፡ ወንዶች ሴቶች፣ ወጣቶችና አዛውንቶች በሳውዲ አረቢያ በወንድሞቻቸውና በእህቶቻቸው ላይ የሚፈጸመውን ስቃይና የሰብአዊ መብት ጥሰት በመቃወም በመቶዎችና በሺዎች በመሆን እየወጡ ከጎናቸው ተሰልፈዋል፡፡

ይህን ግዙፍ ዲያስፖራ እንዲነቃ ያደረገው ምንድን ነው?  እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ በአሁኑ ጊዜ ትልቁ ስጋቴ በሳውዲ ያለው ቀውስ ካበቃ በኋላ ይህ ግዙፍ የዲያስፖራ ማህበረሰብ ተመልሶ ይተኛ ይሆን የሚለው ነው፡፡

የሁላችንም ትምህርታዊ አጋጣሚዎች፣

የኢትዮጵያ ስደተኛ ሰራተኛ በሳውዲ አረቢያ ገዥ አካል በደርሰባቸው የሰብአዊ መብት እረገጣና ማሰቃየት የኢትዮጵያ ገዥው አካል ጆሮ ዳባ ልበስ ማለቱ ልዩ የሆኑ ትምህርታዊ አጋጣሚዎችን በአጠቃላይ ለኢትዮጵያ ህዝብ በተለይም ለዲያስፖራው ማህበረሰብ ሰጥቷል የሚል እምነት አለኝ፡፡ “ትምህርታዊ አጋጣሚ” የሚለውን ሀረግ ለብዙሀን ትምህርት፣ ለህዝቦች መነሳሳትና ለግለሰቦች በንቃት መሳተፍን ሊያመጣ የሚያስችል በታሪክ ውስጥ ከፍተኛ ዋጋ ያለው ልዩ ድርጊት በማለት ተርጉሜዋለሁ፡፡ ከዚህ በመቀጠል የሚቀርቡትን ጥቂት የማስተማሪያ እና የመማሪያ ትምህርቶች የትርጉም ቅርጽ ከግንዛቤ በማስገባት ማስተላለፍ የምፈልገው ዋናው መልዕክት ቀውስ በደረሰ ጊዜ ብቻ የሚወረወር ምላሽ ነጻነትን፣ ዴሞክራሲን ለመጎናፀፍ እና በኢትዮጵያ የሰብአዊ መብትን ለማስከበር ስኬታማ እና ለድል የሚያበቃ ስሌት አይደለም፡፡

በሳውዲ አረቢያ እንደደረሰው ቀውስ ሁሉ በሌሎችም ትክክል ናቸው ብለን በምናምንባቸው ጉዳዮች ሁሉ ልዩ የሆነ ዓለምአቃፋዊ ትብብር፣ ወንድማማችነት፣ እህትማማችነት እና መነሳሳትን በተረጋጋ ሁኔታ ማንጸባረቅ ይጠበቅብናል፡፡ በሳወዲ አረቢያ ቀውስ ምክንያት የታየውን የመነሳሳት “አዚም” ደግመንና ደጋግመን ማሳየት ይኖርብናል፡፡ ዲያስፖራ ኢትዮጵያውያን/ት በቋሚነት ለሰብአዊ መብት መከበር መሟገትና መንቀሳቀስ ይኖርብናል፡፡

በኢትዮጵያውያን/ት ዲያስፖራ መነጽር መመልከት፣ ተራ ንግግር እራሳችንን ከስሜታዊነት፣ ግንፍልተኝነት እና ከቀውስ ለመውጣትና የእራሳችንን እጣ ፈንታ እራሳችን ወሳኝ እንድንሆን ሰላማዊ ሽግግር ለማድረግ “የኢትዮጵያ ዲያስፖራ መስታወት” ምናባዊ ቅርጽ የሚል ላስተዋውቅ፡፡ የነቃውን ግዙፍ የዲያስፖራ ማህበረሰብ ለዘለቄታው እንደነቃ ለዘላለሙ ጠንቃቃ ተመልካች ሆኖ አንዲቀጥል ልዩ ስትራቴጂ መንደፍ ያስፈልጋል፡፡

በኢትዮጵያ ዲያስፖራ ያሉ ችግሮችና ጉዳዮች ምን ምን እንደሆኑ እናውቃለን፣ ጥቂቶች በጣም ቀላል ነገሮች ሲሆኑ ሌሎቹ ደግሞ መፍትሄ ለማግኘት የበለጠ አስቸጋሪዎች ናቸው፡፡ በግልጽ  በመተማመን እና በመወያየት ችግሮችን ካልፈታናቸው በስተቀር ታላቁን የነቃ የዲያስፖራ እንቅስቃሴ ወደኋላ በመመለስ እንዲተኛ ማድረግ ያስችላሉ፡፡ ከአንድ ቀውስ ወደሌላ ቀውስ መሸጋገር እኔ በበኩሌ ያመኛል፣ ይደክመኛልም፡፡

የዲያስፖራው ማህበረሰብ እርስ በእርስ እንዲዋደድ፣እንዲደራጅ፣ እንዲታደስ እና ለውጤት እንዲንቀሳቀስ ማድረግ አለብን፡፡ ከእራሳችን እና ከእያንዳንዳችን ጋር ንግግሮች ያስፈልጉናል፡፡ “በኢትዮጵያ ዲያስፖራ መስታወት” እመለከታለሁ፡፡ ንግግር ለማድረግ መስታወቱን ከግድግዳው ጋር እሰቅለዋለሁ፡፡ እኔን ወደኋል ይመለከተኝ እና እንዲህ ይላል፣

ሁላችሁም ማድረግ ትጀምራላችሁ ነገር ግን አትጨርሱትም፡፡ መስታወቱ እንዲህ በማለት ያስታውሰናል፣ “በቅርቡ በህይወት የተለዩት የኢትዮጵያ ገዥ አካል መሪ እንዲህ ብለው ነበር ’የአትዮጵያ ዲያስፖራዎች ብዙ ነገሮችን ይጀምራሉ፣ የጀመሩትን ግን በፍጹም አይጨርሱትም፣ ታዲያ ስህተት ተናግረዋልን?’”

ጥያቄውን ላለመመለስ ቃላትን ለመፈለግ እሞክራለሁ፡፡ “እውነት ለመናገር ብዙ ብዙ ነገሮችን እንጀምራለን፣ ነገር ግን በጣም ጥቂቶችን ብቻ ለውጤት እናበቃለን፣ ከእኔ የግል ተሞክሮ ማስረጃ ማቅረብ እችላለሁ፣ እ.ኤ.አ ከ2005 ጀምሮ የኢትዮጵያን የሰብአዊ መብት አጠባበቅ ትግል በንቃት ስቀላቀል ያየኋቸው፣ የሰማኋቸው፣ በአንድ ወይም በሌላ መልኩ የተሳተፍኩባቸው፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ የፖለቲካ ወይም የአድቮኬሲ ቡድኖች፣ ግብረ ኃይሎች፣ ኮንፈረንሶች፣ ፎረሞች፣ የምክክርና የውይይት ቡድኖች፣ ቴሌኮንፈረንሶችና የግል ስብሰባዎች፣ ወርክሾፖች፣ ስምምነቶች፣ የአካዳሚክ ሴሚናሮች እና ሲምፖዜሞች ናቸው፡፡ ከእነዚህ ሁሉ አንዱም ፍሬ አፍርቷል ብየ ለመናገር አልደፍርም“:: ወዲያዉኑ እራሴን በፍጥነት አርማለሁ፡፡ “አንድን ነገር በግማሽ አሳክተናል፣

በአሜሪካ የተወካዮች ምክር ቤት ኤችአር/HR 23ን ማን ይረሳዋል (ኢትዮጵያ ዴሞክራሲ እና ተጠያቂነት ድንጋጌ)፣ አዎ! ያ ታላቅ ትምህርታዊ አጋጣሚ ነበር፡፡ ያ የህግ ሰነድ በቅርቡ በህይወት ለተለዩት ጠቅላይ ሚኒስትር የእራስ ምታት፣ የልብ ስብራት፣ የሆድ ቁርጠት፣ የጀርባ ውጋት፣ የጥርስ ቁርጥማት እና የጆሮ ህመም ሆኖባቸው ነበር! ኤችአር 2003 የተለያየ አመለካከት የነበራቸውን የዲያስፖራ ማህበረሰብ አባላት ወደ አንድ እንዲመጡና ተቀራርበው ዓላማቸውን በጋራ እንዲያሳኩ ለማድረግ አስችሎ ነበር::

መስታወቱ አቁአረጠኝ፡ “እንዲህ ነው እንጂ! ሁላችሁም አንድ ሁሉን አቀፍ የሆነ ጠንካራ መሰረት ያለው የሰብአዊ መብት ተሟጋች የዲያስፖራ ማህበረሰብ ድርጅት ማቋቋም ትችላላችሁ፡፡ ከሁሉም በላይ ለማሰቃየት፣ ከህግ  ውጭ ለሚፈጸም ግድያ፣ በዘፈቀደ በቁጥጥር ስር ማዋል እና እስራቶች፣ ድብደባዎች እና ለምርጫ ድምጽ ስርቆት የተለየ ትኩረት በመስጠት የማያምን ማን አለ?” ግልጽ የሆነውን መልስ ላለመስጠት ወሰንኩ፡፡ አንድ ነገር ስንጀምር ወደ ስኬታማነት ልናመጣው ይገባል ወይም ደግሞ የፈለገውን ጊዜ ቢውስድም እየሞከርነው መቀጠል ይኖርብናል፡፡

ሁልጊዜ ሙሉ በሙሉ በሚባል መልኩ ሁላችሁም አንድን ነገር ለመቃወም በንዴት በስሜታዊነት ትነሳላችሁ፡፡ መስታወቱ እንዲህ ሲል ይጠይቃል፣ “በኢትየጵያ ያለው ታማኝነት የጎደለው ገዥው አካል አንድ ነገር ሲያደርግ ወይም ሳያደርግ ሲቀር ሁላችሁም ሁልጊዜ በንዴትና በስሜታዊነት ምላሽ ለመስጠት የምትሞክሩት ለምንድን ነው?“ በፍጥነት የሳውዲ አረቢያን ሁኔታ ሃሳብ መጣብኝ፡፡ “ስሜታዊነት መሆን ምንም ስህተት የለበትም፡፡ ሰው መሆንና ስሜታዊ አለመሆን ማለት ሮቦት መሆን ማለት ነው፡፡

ወንድሞቻችንና እህቶቻችን በሳውዲ አረቢያ ከሰው በወረደ መልክ ግፍ ሲፈጸምባቸው እያየን እና እየሰማን ለምንድን ነው የማንናደደውና ከቁጥጥር ውጭ የማንሆነው?“ መስታወቱ በጥንቃቄ መጠየቁን ይቀጥላል፣ “ከተነፈስክ በሁላ ንዴት ሲበርድልህ  የሚተርፍህ ምንድን ነው? ተስፋ መቁረጥ፣ በጣም ስሜታዊ መሆን፣ ማዘን? ኃይል የለሽነት፣ ተስፋቢስነት፣ ምንም ነገር ያለማድረግ ሁኔታ ውስጥ ልትገባ ትችላለህን? ወይም ደግሞ እንደገና ለመደራጀትና ወሳኝ እርምጃ ለመውሰድ ያለ የሌለ የፈጠራ ኃይልህን ትጠቀማለህ? እራሴን በመነቅነቅ ሀሳቤን አንጸባርቃለሁ፡፡ “ምንጊዜም ቢሆን ንዴት በመጨረሻው ተፈጻሚነት እንዳይኖርና ሽባ ሆኖ ያስቀራል፡፡ በምንናደድበት ጊዜ የምናባክነው ኃይል ወደ ረዥሙና ቀጣይነት ስላለው የአድቮኬሲ እና ድርጊት በአወንታዊነት ማዋል አለብን::” ንዴታችን ለምክንያታዊነት፣ በስሌትና በጥቅል ታስቦበት ለሚሰራ ተግባር መንገድ መስጠት አለበት፡፡

ሁልጊዜ ሙሉ በሙሉ በሚባል መልኩ ሁላችሁም ከፍተኛ ደረጃ ላይ ያሉ ቀውሶችን የመቃወም ዝንባሌ ታሳያላችሁ፣ ነገር ግን ከእነዚህ ያላነሰ ጠቀሜታ ላላቸው ሆኖም ግን ደረጃቸው ዝቅተኛ የሆኑትን ችላ ትላላችሁ::  መስታወቱ እንዲህ ይላል፣ “ባለፈው ዓመት በርካታ አስደንጋጭ ቀውሶች በግልጽ ለመውጣታቸው ምስክር ናችሁ፡፡ በኢትዮጵያ ገዥ አካል በሙስሊሙ ማህበረሰብ አባላት ላይ ሰብአዊ መብት መርገጥና ስልታዊ የሆነ ጥቃት ሲፈጸምባቸው ነበር፡፡ ጥንታዊውንና የተከበረውን የኢትዮጵያን የኃይማኖት መሬት የዋልድባን ገዳም ዓይን ባወጣ መልኩ ገዥው አካል ለውጭ የሸንኮራ አገዳ አልሚዎች ማስረከቡ ይታወሳል::  በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን/ት ዜጎችን ከሚኖሩበት አካባቢ በኃይል በማፈናቀል የዘር ማጽዳት ዘመቻ መፈጸሙ ከብዙ በጥቂቱ የሚጠቀሱ ናቸው::” መስታወቱ ቀጥሏል፣ “በርካታ ዝቅተኛ ገጽታ ያላቸው ነገር ግን በአሁኑ ጊዜ የአውዳሚነት ባህሪ ያላቸው እየተከናወኑ ያሉ ቀውሶች አሉ፣ የገዥው አካል “የሁለት አሀዝ የኢኮኖሚ እድገት” ማስመዝገብ ፕሮፓጋንዳ ቢኖርም በአሁኑ ጊዜ ወደ አስር ሚሊዮን የሚጠጉ ኢትዮጵያውያን/ት በረሀብና ቸነፈር የህይወት አጣብቂኝ መካከል ወድቀዋል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ በ1970ዎቹና በመጀመሪያዎቹ 1980ዎቹ እንደነበሩት ዓመታት ዓይነት ረሀብ የማይታየው በዓለም አቀፍ ለጋሽ ድርጅቶች እርዳታ ምክንያት ነው፡፡ በጎረቤት አገሮች እና በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚገኙ ስደተኛ ኢትዮያውያን/ት ቁጥር በየዓመቱ በመቶዎችና በሺዎች እየጨመር በመሄድ ላይ ይገኛል፣ በትምህርትና በጤናው ዘርፍ ቀውሶች ይታያሉ፡፡ የሙስና ቀውስ እና ሌሎችም ይገኛሉ፡፡ የአንደኛ እና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ጥራት ደካማ መሆን እና የአገልግሎቱ እጥረትም ይታያል፣ ይህም በወጣቶች ስብዕና ላይ ትልቅ የሰብአዊ መብት እረገጣ ተብሎ ሊመደብ  ይችላል፡፡ ዩኒቨርሲቲዎች በተሳሳተ አስተዳደር እየተመሩ ነው፣ የፖለቲካ ተቋማት እየሆኑና የገዥው ፓርቲ ታማኞች የሙስና ስልጠና አካባቢዎች እየተደረጉ ነው::” በገፍ መቃወም ያለብን ትልቅ ገጽታ ያላቸውን ቀውሶች ብቻ ሳይሆን ትንሽ ገጽታ ያላቸውን ጭምርም መሆን አለበት፡፡

የዲያስፖራ ማህበረሰብ አባላት ሁላችሁም በሚባል መልኩ ሁልጊዜ ደካማ የመከላከል ጨዋታ ታደርጋላችሁ:: መስታወቱ እንዲህ ይገልጻል፣ “በዲያስፖራው ያላችሁ ሁላችሁም መንግስት የሚሰራውን ሁልጊዜ ትቃወማላችሁ፣ የማይሰራውን ግን በጣም ጥቂት ብቻ ትይዛላችሁ:: በቅርቡ በህይወት የተለዩት የገዥው አካል መሪ ይህንን ደካማ ጎን እንደ በሰይፍነት የመጠቀም ጉብዝና ነበራቸው::

እና እናንተ በሙሉ ለአገራችሁ እርባና ያለው ነገር ስትሰሩ አትታዩም፣ እሳቸው የህዝብን የትኩረት አቅጣጫ ለማስቀየር ሲሉ አንድ አስደንጋጭ የሆነ ነገር ሲያደርጉ ወይም ሲናገሩ እናንተ ለዚያ ምላሽ ለመስጠት ስትሽከረከሩ ትወጡ ትወርዱ ነበር፣ ይህንም አይተው  በዚያ ጭራቃዊ ፈገግታቸው ይመለከቱ ነበር::”

ለመስታወቱ እንዲህ በማለት ለመግለጽ እሞክራለሁ፣ “እኒያ ሰው ጨካኝ በመሆናቸው ጎበዝ ነበሩ፣ እሳቸው ዋና የነገር አጧዥ፣ የተንኮል ንድፍ አውጭ፣ ታማኝነት የሚጎድላቸው እና የብልጥነት ሴራ የሚሰሩ ነበሩ፡፡ ምርጫ አልነበረንም::” መስታወቱ ይሄን አስተያየት ችላ አለው:: “አሁንም የእርሳቸው ጋሻጃግሬዎች በእርሳቸው ፈለግ እንደዚያው እንደተለመደው የማይረባ ድርጊታቸውን እንዲቀጥሉ ትፈቅዳለህ?“ እኔ መልስ የለኝም፣ ጥያቄው እንዳልሰማ ለማስመሰል እሞክራለሁ፣ ለእራሴ ቀስ ብየ እናገራለሁ፣ “ምንም ዓይነት ቡድን ጠንካራ የመከላከያ መስመር ሳይኖረው ለድል አይበቃም“:: ጠንካራ የዲያስፖራ ቡድኖችን መፍጠርና ጠንካራ የመከላከል ጨዋዎችን ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

ሁላችሁም ትኩረት ይጎድላችኋል፣ መስታወቱ እንዲህ ይላል፣”ሁላችሁም ከአንድ ጉዳይ ወደ ሌላ ዝውውር ለማድረግ ትኩረትና ተስፋ ይጎድላችኋል፣ የቀውስ ሁኔታዎችን በንዴት ምላሽ ለመስጠት ስትሞክሩ ይህ ሁኔታ ደግሞ በጣም ረዥም በሆነ ምንም ነገር ያለመስራት ወሰንተኛ የሆነ ቸልተኝነት ያስከተላል::” እራሴን እጠይቃለሁ፣ “ያ የሚሆነው ለምንድን ነው?“ ድርጅትና አመራር ሳይኖር አንድ ጉዳይ ላይ ትኩረት ማድረግ አስቸጋሪ ሊሆን ይችላልን? ለምንድን ነው ግልጽና ጠንካራ የአድቮኬሲና የድርጊት አጀንዳ የማይኖረን?”  ለመስታወቱ እነግረዋለሁ፣ “ትኩረት ያጥረናል ምክንያቱም ግልጽ ራዕይ የለንም፣ ራዕይ ያጥረናል ምክንያቱም ቁርጠኝነት ያጥረናል፣ ቁርጠኝነት ያጥረናል ምክንያቱም በእራሳችን  በራስ መተማመን እና በክርክር ጭብጦቻችን ላይ እምነት ያጥረናል፡፡“ እዚህ ላይ የአፍሪካን የጥንት አባባል በመዋስ፣ “ወደየት እንደምትሄድ ካላወቅህ ማንኛውም መንገድ እዚያ ያደርስሀል፡፡“

አብዛኞቻችሁ ቆሞ ተመልካች ናችሁ፣ መስታወቱ እንዲህ ይላል፣ “አብዛኞቻችሁ ከጎዳና ዳር ቆሞ ማየትን ትመርጣላችሁ፣ ሌሎቹ ደግሞ ከጎን ሆነው ትችት መሰንዘርን ይመርጣሉ፡፡“ አቋረጥኩ፡፡ “ዋናው ዘዴ የተመልካቾችን ምዕናብ ለማጎልበት፣ ለእነሱ ተስፋ ለመስጠትና ለማጠናከር፣ እውቀት እና በሰብአዊ መብት ጥበቃ ላይ በእራስ የመተማመን ጠቀሜታ ለማጎልበት ነው፣ በዚህም መሰረት ከተመልካችነት ወደ ሰብአዊ መብት ተሟጋችነት ይቀየራሉ፡፡“ መስታወቱ ስሜትን እንዲህ በማለት ያነሳሳል፣ “ሰብአዊ መብት የተመልካች እስፖርት አይደለም፣ ሰብአዊ መብት የቡድን ስራ ነው፡፡ እያንዳንዱ ሰው በሜዳው ውስጥ ነው፣ እያንዳንዱ ሰው የሚጫወተው ድርሻ ይኖረዋል እና ትልቅ ግብ ማስመዝገብ ይኖርበታል፡፡“ ከታች ጀምረን ማነሳሳትና ማንቀሳቀስ ይኖርብናል፡፡

እናንተ የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ማህበረሰብ አባላት በሙሉ የሲቪክ ማህበረሰብ የድርጊት ዘመቻ መመስረት አለባችሁ፣ መስታወቱ እንዲህ በአንክሮ ያስጠነቅቃል፣ “እናንተ ሁላችሁም ለድል የሚያበቃችሁን መንገድ በመከተል በተለየ ሁኔታ ለመስራት፣ ቅድሚያ ዝግጅት በማድረግ ለመስራት፣ ከስሜታዊነት ነጻ ሆኖ ለመስራት መብቃት አለባችሁ፡፡“ እናንተ ሁላችሁንም ማስተማር፣ ማንቀሳቀስ፣ ማደራጀትና ማጠናከር የዲያስፖራውን ማህበረሰብ ለጋራ ጥረት ማብቃት አለባችሁ፡፡ እናንተ ሁላችሁም የሰቪክ ማህበረሰቡ ጋር  በመሆን ዘመቻውን በቀልጣፋነት ማካሄድ አለባችሁ፣ ለሲቪክ ማህበረሰቡ እንቅስቃሴ ህበረተሰቡን በኮሚቴ፣ በጎ ፈቃደኞችን በመመልመል፣ ለወርክሾፖች አመራር በመስጠት፣ ከታች ጀምሮ ያለውን እያንዳንዱን ዜጋ ለማጠናከር እና በንቃት ለማሳተፍ በቴሌቪዥንና ሬዲ ፕሮግራሞች ላይ ትኩረት በመስጠት መስራት ያስፈልጋል፡፡ የሲቪክ ማህበረሰቡ ከታች ጀምሮ በሙሉ እንዲሳተፍ!

እናንተ ሁላችሁም በሌሎች ላይ ስድቦችን በመወርወር ጊዜ ማባከን፣ መስታወቱ እንዲህ ይላል፣ “እናንተ ሁላችሁም ገዥውን አካል በማውገዝ እና ዘለፋዎችን በመወርወር ብዙውን ጊዚያችሁን በከንቱ ታባክናላችሁ፣ ሁላችሁም አታገኙትም፣ የዱሮ አባባል በመዋስ፣ ’ከአሳማ ጋር (ወይም ከሌባ) ከጭቃ ውስጥ ትግል አትግጠም‘ አሳማው (ወይም ሌባው) ሲደሰት አንተ ቆሻሻ ትሆናለህ::

ወሮ በላን በጭቃ ጅራፍ በዝልፍያ መስተካከል አይቻልም::” ምላሽ ለመስጠት ፈጠንኩ፡፡ “አንድ ሰው አካፋን አካፋ ማለት አለበት፡፡“ መስታወቱ እንዲህ በማለት ምክር ይለግሳል፣ “ስለዚህ አንዴ ጥራው እና ተንቀሳቀሱ፣ አስታውስ! ወደ ዴሞክራሲ ወይም ወደ ነጻነት በስድብ አትደርስም፡፡”” መስማማቴን ለመገልጽ እራሴን ነቀነቅሁ፡፡ “የእውነት ወንጭፎችን እና ቀስቶችን ታጥቀን መዋጋት አለብን፣ በእውነት ጋሻዎች መመከት አለብን፣ ከመብት እረጋጭ ኃይሎች ነጻ ሆነን በነጻነት ለመናገር፣ ለመዘመር፣ ትልቁን ጉዞ መጓዝ አለብን፡፡“ እውነትን ተናገር እንጅ የሰብአዊ መብት እረጋጭ ኃይሎችን አትሳደብ፡፡

እናንተ ሁላችሁም በክፍል ውስጥ ላለው ዝሆን ትኩረት ስጡ፣ መስታወቱ እንዲህ ይላል፣ “እነሱን ለመረዳት ሳይሆን በሌሎች ሰዎች ጫማዎች ለመጓዝ ሞክር (ምክንያቱም“እነሱን ለመረዳት መሞከር ጊዜ ማጥፋት ነው) ነገር ግን የእነርሱን ፍርሃት ለመረዳት እና የድብቅ እንባ ማፍሰስ ለመገንዘብ ሞክር፣ እነሱ አደጋዎች ጭካኔ የተሞላባቸው እና ህሊና የሌላቸው ናቸው፣ ነገር ግን ፍርሃት አልባዎች አይደሉም፡፡ በፍርሃት ይኖራሉ፣ ነገር ግን መሰረተቢስ ፍርሃቶች አይደሉም፣ የእነርሱ ፍርሃት በጫካው ውስጥ በማታ አያነደደ እንደሚያበራው ነብር ሁሉ ተመሳሳይ ናቸው፡፡” ይላል ዊሊያም ብሌክ፡፡ “የቸርቺል ኬኔዲ የፍርሃት ተቃርኖ’ በሚሉት ወጥመድ ተይዘዋል፣ አምባገነኖች ደፍረው ወጥተውው በማይጋልቧቸው ነብሮች ከወዲያ ወዲህ ይላሉ፣ እና ነብሮቹ ተርበዋል”፣

ቸርችል ያስጠነቅቃሉ፡፡ ፕሬዚዳንት ጆን ኬኔዲ ለማስታወስ “በጥንት ጊዜ በሞኝነት በነብሮች ጀርባ ላይ በመቀመጥ ኃይልን ለማግኘት ይፈልጉ የነበሩ አምባገነኖች በነብሮቹ ሆድ ውስጥ ገብተዋል፣  በሌላ አባባል “በሰላማዊ መንገድ ለውጥ እንዲመጣ የሚከለክሉ እነሱ በአመጽ መወገዳቸው የማይቀር ነው፡፡“ መስታወቱ ቀጠለ፣ “አምባገነኖች እርግጠኛ እና እብሪተኛ ይመስላሉ፣ ነገር ግን ይህ ሁሉን አቀፍ የሆነ ፍርሃታቸውን ለመሸፈን ሲሉ የሚያደርጉትና ከዕለታት በአንዱ ቀን እነርሱ ከታች ለወደቁ ጭቁኖች እነርሱ በፈጠሩት ገሀነም አነርሱ ስልጣናቸውን በኃይል ተነጥቀው ወደ መቀመቅ መውረዳቸው የማይቀር ነው፡፡“ መስታወቱን እጠይቀዋለሁ፣ “አምባገነኖች ቀን በቀን ይኖራሉ ብለህ መናገር ትችላለህ? ነገ ድረስ ለመቆየት አምባገነኖች ዛሬ ሁሉን ነገር ያደርጋሉ፣ ነገ ከነገ ወዲያም እና ከዚያ ወዲያም ቀን በቀን ነው የሚኖሩት?“ መስታወቱ እንዲህ ያስተካክለዋል፣ “በፍጹም፡፡

አምባገነኖች ሰዓት በሰዓት፣ ደቂቃ በደቂቃ፣ ሰከንድ በሰከንድ በፍርሃት ተውጠው ነው የሚኖሩት፣“ የተራቡ ነብሮች? የነቁ ግዙፎች ነብሮች!  እናንተ ሁላችሁም ብቻችሁን ልትሰሩት አትችሉም፣ ከመሄድህ በፊት የመጨረሻዋን ቃል መስታወቱ እንዲህ ይናገራል፣ “እናንተ ሁላችሁም ብቻችሁን ልትሰሩት አትችሉም፣ እናንተ ሁላችሁም ጓደኞች መፈለግና ከእነርሱ ጋር ተባብራችሁ በጋራ ተግባራዊ ማድረግ ነው፡፡”

ማሰብ ጀመርኩ፣ “ስንቶቻችን ነን ለእኛ ምርጥ ጓደኞች ጓደኞች የሆን? ስንቶቻችን ነን የሂዩማን ራይትስ ዎች በኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ዘላለማዊ መጠበቂያ አባል የሆንነው? ስንቶቻችን ነን የሲ  ፒ  ጄ የጋዜጠኞች ተከራካሪ ድርጅት መብራቱን በቃሊቲ እስር ቤት ላይ በማነጣጠር እነ አስክንድር ነጋ፣ ውብእሸት ታየ እና ሌሎች በህገወጥ መንገድ ታስረው ለሚገኙት አባል የሆንነው?

ብቻችንን ልንሰራው የምንችለው ጉዳይ አይደለም፡፡ ስንቶቻችን ነን ባህላዊውን የህብረተሰብ ቡድኖች እና የኢትዮጵያን የአካባቢ ጥፋት ለመከላከል ብለው ልዩ ስራዎችን ዓለም አቀፍ ወንዞች በፍትሀዊነት እንዲያገለግሉ የሚታገሉትን ዜጎች የምናደንቅ? በዓለም አቀፍ እና በአገር ውስጥ ከሚሰሩ የመገናኛ ብዙሃን ጋዜጠኞች ጓደኛ አለን? በድንገት በአምሮዬ ጥያቄ መጣ፡፡ ለምንድን ነው እነ ሲኤን ኤን፣ቢቢሲ፣ ኤቢሲ፣ ሲቢኤስ፣ አልጃዚራ፣ ዋሽንግተን ፖስት፣ ኤልኤ ታይምስ፣… የእኛን ሰላማዊ ተቃውሞዎች ለህዝብ ይፋ የሚያደርጉት?“ ከእነርሱ ጋር ጓደኝነት ስላልመሰረትን ነው? ብቻችንን ልንሰራው የምንችለው ጉዳይ አይደለም፡፡ አብረን ለምንሰራው ሁሉ ሰማይ ወሰናችን ሊሆን አይችልም!

መስታወት፣ መስታወት ….

“የኢትዮጵያ ዲያስፖራ መስታወት” እውነቱን ወይም ደግሞ ውሸቱን ሊነግረን ይችላል፡፡ ምናልባት በመስታወቱ ውስጥ ማየት የምፈልገውን አይቼ ይሆናል፣ ምናልባት መስተዋቱም እኔ በመስታወቱ ላይ እንዲታይ ያስቀመጥኩትን አንጸባርቆ ይሆናል፣ ምናልባት መስታወቱ ሁሉም መልሶች ያሉት ወይም የሌሉት ይሆናል፣ ምናልባት መስተዋቱ የእኔ ህሊና ይሆናል፣ በእርግጥ በበየእለቱ  በመስታወቱ ስመለከት የምጠይቀው፣ “በግድግዳው ላይ ያለህው መስታወት የነቃው የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ከዚህ በኋላ ምን ማድረግ ይኖርበታል?

ወደፊት ይቀጥላ

ለአንባቢዎች ማስታወሻ፣ከኢትዮጵያ ዲያስፖራ መስታወት ንግግሮችልዩ በተከታታይነት የሚወጡ ትችቶች ናቸው፣ ወደፊት በየጊዜው

በሚስቡ ክስተቶችና ድርጊቶች ላይ ትኩረት በማድረግ እንደምጽፍ እገምታለሁ፡፡ ማስተማሪያና መማሪያ በሚሆኑ ድርጊቶች ለመምህር ፈልጎ

ማውጣት መቻሉ በአጣቃላይ የሚያስደንቅ አይሆንም፡፡

12/4/2013

Similar Posts

Leave a Reply