ኢትዮጵያ- የፖሊስ መንግስት ያንሰራፋባት ሀገር
ከፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረ ማርያም
ትርጉም ከነጻነት ለሀገሬ
የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፑብሊክ ህገመንግስት በህግ ከለላ ጥላ በቁጥጥር ስር የሚውሉ ዜጎችን አስመልክቶ የሚከተሉትን መብቶች ያጎናጽፋል፡፡“በህግ ከለላ ጥላ በቁጥጥር ስር የዋለ ማንኛውም ሰው በህግ አግባብ መብቱ ተጠብቆ ይያዛል፡፡ ማንኛውም ሰው በሀሰት ለመረጃ ጠቀሜታ ተብሎ በማስገደድ እንዲያምን ወይም የተባለውን እንዲቀበል አይገደድም፡፡ ማንኛውም በማስገደድ የተገኘ መረጃ ተቀባይነት አይኖረውም፡፡“ ይላል አንቀጽ 19(2)(5)፡፡ እውነታው ሲታይ ግን ይህ የይስሙላ ሙበት የተጻፈበትን ወረቀት ዋጋ ያህል የለዉም፡፡
ባለፈው ሳምንት ሂዩማን ራይትስ ዎች “HRW“ የተባለው ዓለም ዓቀፋዊ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅት በኢትዮጵያ መንግስት “የፌዴራል ፖሊስ ማዕከላዊ ምርመራ” እየተባለ በሚጠራው የፖሊስ ጣቢያ የሚፈጸሙትን አስደንጋጭና አስከፊ የሰብአዊ መብት ረገጣዎች ዘገባ ሪፖርት አቅርቧል፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኘው ይህ የፖሊስ ምርመራ ማዕከል በጥርጣሬ የተያዙ ዜጎችን በማሰቃየት ይታወቃል፡፡
እንደ ሂዩማን ራይትስ ዎች ዘገባ “በቁጥጥር ስር ባሉ እስረኞች ላይ በተለይም ያለው መንግስት ይቃወሙኛል በሚላቸው የፖለቲካ እስረኞች ላይ ማዕከላዊ ምርመራ እየተባለ የሚጠራው የምርመራ ተቋም እልህ አስጨራሽ የምርመራ ሂደት በማድረግ እስረኞችን በግድ ወንጀል ሰራን ብለው አንዲአምኑ በማስገድድ፣ እንደሚያሰቃይና ህገወጥ የእስረኞች አያያዝ“ እየፈጸመ እንደሆነ በማረጋገጥ በዘገባው ይፋ አድርጓል፡፡ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቱ በማያያዝም “ማዕከላዊ ምርመራ እየተባለ የሚጠራው ተቋም ብዙ የተቃዋሚ የፖለቲካ እስረኞች፣ ሰላማዊ ሰልፍ አስተባባሪዎች፣ መንግስት የብሄር ግጭት ተንኳሾች ናቸው በሚላቸውና ሌሎች በፖሊስ ቁጥጥር ስር ከዋሉ በኋላ በጅምላ ተይዘው የሚሰቃዩበት የምርመራ ማዕከል” ነው ብሎታል፡፡
ገጣሚው ዊሊያም ኤርነስትን አባባል በመዋስ “ማዕከላዊ የምርመራ ማዕከል” የሰቆቃ መደብር በለቅሶና በሰቃይ የታጠረ የጭለማ ቤት ነው :: የገዥው መንግስት ተቃዋሚዎች፣ አመጸኞች፣ የሚላቸዉን የነጻው ፕሬስ ጋዜጠኞች እና ሌሎች እስረኞች በሙሉ በምርመራ ጊዜ ሰቆቃ ተጠቅሞ አራሳቸዉን አንዲወነጅሉ ያስገደዳቸዋል:: እንዲሁም ብዙዎቹ ማሰቃየትን ጨምሮ የተለያዩ የሰብአዊ መብት ረገጣዎች ይፈጸሙባቸዋል፡፡
እንደ ሂዩማን ራይትስ ዎች አባባል ማዕከላዊ እየተባለ የሚጠራው የምርመራ ተቋም “አስቀያሚው የአካልና የስነ ልቦና ማሰቃያ እንዲሁም አስገድዶ የማሰመኛ ምሽግ” መሆኑን በመጠቆም በማዕከሉ ከሚፈጸሙ የማሰቃየት ወንጀሎች እነዚህ ከብዙ ጥቂቶቹ መሆናቸውን በአጽንኦት ገልጿል፡፡ አኔም በግሌ ከአስፈሪው ማአከላዊ ምርመራ መዳፍ የተረፉ የቀድሞ እስረኞችን አነጋገሬ አውቃለሁ::
እ.ኤ.አ. በ2011 የአሜሪካ መንግስት መምሪያ በዓመታዊ የሰብአዊ መብት አያያዝ ዘገባው በኢትዮጵያ ያለውን ሁኔታ ለማሳየት የሚከተለውን ማጠቃለያ አስፍሯል፡፡
ብዙ ተጨባጭ መረጃዎች እንደሚያረጋግጡት እ.ኤ.አ. በ2009 በአዲስ አበባ የሚገኘው ማዕከላዊ እየተባለ የሚጠራው የፖሊስ ምርመራ ማዕከል ፖሊስ ኃይልን በመጠቀም አስረኞችን አስገድዶ ለማሳመን የአካል ማሰቃየት ሰቆቃ ድርጊት ሲፈጽም ነበር፡፡ ይህ ዓይነት የማሰቃየት ዘዴ በአሁኑ ጊዜም በተግባር ላይ እየዋለ ያለ መሆኑን ዜጎች ያላቸውን ሰፊ እምነት አጽንኦት በመስጠት እየገለጹ ነው፡፡ ባለስልጣናቱ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና የዲፕሎማሲው ማህበረሰብ ማዕከላዊ ምርመራን ለመጎብኘት የሚያቀርቡት ጥያቄ አሁንም በመንግስት በኩል አዎንታዊ ምላሽ እንዳላገኘ ይታወቃል፡፡“ በማለት ድርጅቱ ያለውን ሀሳብ ቋጭቷል፡፡
የ15ኛው ክፍለ ዘመን የሰቆቃ ስልት በ21ኛው ክፍለ ዘመን ኢትዮጵያ!
በአዲስ አበባ እምብርት ላይ የሚገኘው ማዕከላዊ እየተባለ የሚጠራው የማሰቃያ ምርመራ ተቋም በመካከለኛው (15ኛው) ዘመን በአውሮፓ የሰብአዊ መብት ረጋጮች በንጹሀን ዜጎች ላይ ይደረግ የነበረውን አስፈሪ፣ አስደንጋጭና ተስፋቢስ የማሰቃየት ስልት ገጽታ መለስ ብለን እንድናስታውስ ያስገድደናል፡፡ እንደ ሂዩማን ራይትስ ዎች መግለጫ “የማዕከላዊ ምርመራ ፖሊሶች በህግ ጥላ ስር የተያዙ የህግ አስረኞችን እነርሱ በሚፈልጉት መልኩ በግድ ለማሳመን፣ መግለጫ እንዲሰጡና ሌሎች መረጃዎችን ለማግኘት ሲሉ በእስረኞች ላይ ማሰቃየትን ጨምሮ የተለያዩ የማስገደጃ ዘዴዎችን እና ልዩ ልዩ ኢሰብአዊ ድርጊቶቸን ይፈጽማሉ፡፡ እንደ መካከለኛው የአውሮፓ ዘመን መብት ረጋጭ ተቋሞች ሁሉ የኢትዮጵያው የምርመራ ማዕከልም እንደመርማሪዎቹ ፍላጎትና አመችነት ሁኔታ እስረኞችን በአራት ዋና ዋና ክፍሎች መድቧቸዋል፡፡ የማዕከላዊ ምርመራ ማዕከል በተለያዩ የእስረኞች አያያዝና እያንዳንዳቸው ባላቸው ቅጽል ስም የሚታወቁ አራት አይነት የማጎሪያ እስር ቤቶች አሏቸው፡፡ እነርሱም፣ 1ኛ) ጨለማ ቤት፣ ይህ እስር ቤት በጣም አስቸጋሪና ብርሀን የማይገኝበት የማጎሪያ ክፍል ነው፡፡ በዚህ እስር ቤት እስረኞቹ የፀሐይ ብርሀን እና የመጸዳጃ ቤት የማግኘት ዕድላቸው በጣም ጠባብ ሲሆን አንዳንድ ጊዜም ለብቻ የመታሰር ዕጣ ፈንታ ይገጥማቸዋል፣ 2ኛ) ጣውላ ቤት፣ ይህ እስር ቤት በክፍል ውስጥ እንደልብ መዘዋወር የማያስችል ሲሆን ክፍሎቹም በቁንጫ ተባይ የተወረሩ ናቸው፡፡ 3ኛ) ሸራተን፣ በቅርብ ጊዜ ከእስር ቤት የማይለቀቁ ብዙዎቹ እስረኞች ወደዚህ የማጎሪያ ቤት እንዲዛወሩ ይፈልጋሉ፡፡ ይህ በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅና ባለው ሆቴል ስም የተሰየመው እስር ቤት እስረኞቹ የተሻለ የአካል እንቅስቃሴ የማድረግና በህግ አማካሪዎቻቸውና በዘመዶቻቸውም መጎብኘት እንዲችሉ የእስር ቤቱ ኃላፊዎች ፈቃድ የላላበት ነው፡፡ 4ኛ) የተፋፈገው የሴት እስረኞች ማጎሪያ፣ ይህ እስር ቤት በገፍ ሴት እስረኞችን አጭቆ የያዘ ነው፡፡”
ገዥው የኢትዮጵያ አስተዳደር ከተቃዋሚ የፖለቲካ እስረኞች መረጃዎችን፣ መግለጫዎችን እና ተገደው የእምነት ቃል እንዲሰጡ ለማድረግ የተለያዩ የማሰቃያ ዘዴዎችን ይጠቀማል፡፡ ሂዩማን ራይትስ ዎች አንደጠቀሰው: “እስረኞች በተደጋጋሚ በጥፊ ይጠናገራሉ፣ በእርግጫ ይመታሉ፣ በቦክስ ይደለቃሉ፣ በዱላና በጠብመንጃ ሰደፍ ይደበደባሉ፡፡ አንዳንዶች እንደተናገሩት በሚያስጨንቅ ሁኔታ [በመካከለኛው ክፍለ ዘመን ይደረግ እንደነበረው ‘እጅን በገመድ አስሮ ገልብጦ ከጣራ ወደ ታች በማንጠልጠል እንዲወድቁ በማድረግ የማሰቃየት’] ወይም ሁለት እጆችን ወደ ላይ ከእራስ በላይ ከፍ አድርጎ በገመድ አስሮ በማቆም ለበርካታ ሰዓታት በማቆየት በተደጋጋሚ ያሰቃዩ እንደነበር ገልጸዋል፡፡ አሁንም [በመካከለኛው ዘመን ይደረግ እንደነበረው ሁሉ] በኢትዮጵያ ማዕከላዊ ምርመራ ማዕከልም የእስረኞችን እጆች በካቴና በማስገባት ለበርካታ ጊዜ ታስረው እንደሚቆዩ እንዲያውም አንድ እስረኛ ከአምስት ተከታታይ ወራት በላይ እጁ በካቴና ታስሮ እንደቆየ እና ማቋረጫ በሌለው የቃል ጥያቄ ምርመራ በታሳሪዎቹ ዘንድ ፖሊስ ተደጋጋሚ ዛቻ እንደሚያደርግ ተረጋግጧል፡፡” በጥንት ጊዜ ‘በእስፓኞች ይደረግ እንደነበረው አሰቃቂ የምርመራ ሂደት‘ አንዳንዶቹ እስረኞች ለበርካታ ጊዜ ተገልለው ለብቻቸው እስራታቸውን እንዲገፉ ተበይኖባቸዋል፡፡ በመካከለኛው ክፍለ ዘመን የእስር ቤት ማጎሪያዎች ይደረግ እንደነበረው ሁሉ በዛሬይቱ ኢትዮጵያ እስረኞቹ የፀሐይ ብርሃን የማግኘት መብታቸውን ይከለከላሉ፣ በደካማ የንጽህና አያያዝና በውሱን የህክምና አገልግሎት አሰጣጥ ይሰቃያሉ፡፡ እነዚህ ሁኔታዎች በተለይም በመጀመሪያ ለምርመራ የቀርቡትን ተጠርጣሪዎች ላይ የበለጠ አሰቃቂ ይሆናሉ፡፡”
የእነዚህ ሁሉ የማሰቃየት ተግባራት ዋና ዓላማው በእስረኞች ላይ ታላቅ ጫና በመፍጠር ትክክል ይሁንም አይሁን ለቀረበባቸው የወንጀል ክስ ፈጻሚ መሆናቸውን እንዲያምኑ በማስገደድ መግለጫ፣ የእምነት ቃልና መረጃ እንዲሰጡ ለማድረግ ነው፡፡ እነዚህን በማስገደድ የተሰጡ መግለጫዎችና በግዳጅ የተገኙ የእምነት ቃሎችን አንዳንድ ጊዜ ተወንጃዮቹ ከእስር ቤት ከተለቀቁ በኋላ ወደ ህብረተሰቡ ሲቀላቀሉ ያለውን መንግስት ተገደው እንዲደግፉና ጉዳያቸው በፍርድ ቤቶች በሚታይበት ጊዜም መንግስት እንደ ማስረጃ ለመጠቀም ስለሚፈልጋቸው ነው፡፡
በማዕከላዊ እስር ቤት እስረኞች ለደረሱባቸው የአለአግባብ መታሰርና መንገላታት የሚጠየቅም ሆነ የሚገኝ ካሳ የለም፡፡ ፍርድ ቤቶች ከፖለቲካ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን የማየት ነጻነት የላቸውም፡፡ ፍርድ ቤቶች የማዕካላዊ ምርመራ ፖሊስ በምርመራ ጊዜ በእስረኞች ላይ የማሰቃየትና ህገወጥ ድርጊቶችን ፈጽሟል የሚል ውንጀላ ለፍርድ ቤቶች ቢቀርብ ተገቢውን የማጣራት ሂደት በማከናውን እርምጃ ለመውሰድ አይችሉም፡፡ በሂዩማን ራይትስ ዎች ዘገባ መሰረት የቀድሞ እስረኞች የማዕከላዊ ምርመራን የበቀል እርምጃ በመፍራት በምርመራ ወቅት የደረሱባቸውን በደሎች ለፍርድ ቤቶች ለማቅርብ ስለሚፈሩ ዝምታን እንደሚመርጡ ጠቁሟል፡፡ አንዳንዶቹም ከፍርድ ቤቶች ችሎት በፍጹም ደርሰው እንደማያውቁ ይናገራሉ፡፡
እ.ኤ.አ. በጁላይ 2008 በዓለም በደህንነት ሙያ ታዋቂ የሆኑት እንግሊዛዊው ጡረተኛ ኮሎኔል ሚካኤል ዴዋርስ የኢትዮጵያን የእስር ቤቶች አያያዝ ሁኔታ አጥንተው የመፍትሄ ሀሳቦችን እንዲያቀርቡ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ተዋውለው ወደ አዲስ አበባ ፖሊስ ጣቢያ በመሄድ እስር ቤቶችን ከጎበኙ በኋላ በተጨባጭ የተመለከቱትን የእስር ቤቶችን ሁኔታ እንደሚከተለው አቅርበዋል፡፡ እንደዚህም ይተርኩታል፡፡
“እስረኞቹ ወዳሉበት ግቢ ውስጥ እንድገባ ጥያቄ አቀረብኩ፣ ይህ ግቢ ረዥም የሆነ በአንድ ጎኑ በኩል መጠለያ ሊሆን የሚችል ዳስ ይዟል፣ ግቢው በግንብ አጥር የታጠረ ሲሆን ለአካባቢው ጥበቃ እንዲያመች ሆኖ የተሰራ የጥበቃ ማማና ጥበቃዎች አሉት፡፡ በግቢው ውስጥ ከ70 እስከ 80 የሚሆኑ እስረኞች በተጎሳቆለ ሁኔታ ይታያሉ፡፡ ለሁሉም እስረኞች በምንጣፍ ለመጋደም የሚያስችል በቂ ክፍል የለም፣ መብራት የሚባል ነገር የለም፣ ቦታው በአይነምድርና በሽንት በሚሰነፍጥ ሽታ ታውዷል፣ በግቢው ውስጥ ምንም ዓይነት ውኃም ሆነ የመጸዳጃ ፋሲሊቲ የለም፣ በግቢው ውስጥ ለሴት እስረኞች ተብሎ ትንሽ የሳር ጎጆ ተቀልሳ በቅርብ እርቀት ትታያለች፣ ሆኖም ግን ግቢውን ለማሻሻል ተብሎ በግቢው ውስጥ የተሰራ ምንም ነገር የለም፣ አብዛኞቹ እስረኞች በትናንሽ ወንጀሎች በተለይም በሌብነት ወንጀል እየተያዙ ወደ እስር ቤቱ በተደጋጋሚ የሚመጡ ናቸው፡፡ ጥቂቶቹ ለወራት በዚሁ እስር ቤት የቆዩ ናቸው…፡፡”
ኮሎኔል ዴዋርስ በእስር ቤቱ የተመለከቱትን በሚከተለው መልክ አጠቃለዋል፣ “የእስረኞቹ አያያዝ በሚያሳፍር ሁኔታ ላይ የሚገኝ ሲሆን ይህም ሁኔታ ፌዴራል ፖሊስን ለሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ትችት እንዲጋለጥ አድርጎታል፣ ማንም ቢሆን እስር ቤቶች እንደ ሂልተን ሆቴል መሆን አለባቸው ብሎ ሀሳብ የሚያቀርብ የለም ነገር ግን ማንም የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅት በኢትዮጵያ እስር ቤቶች ላይ ተገኝቶ ቅኝት ቢያደርግ እኛ ያደረግነውን ጥረት የሚደግፉ መረጃዎችን ማውጣት ይችላል… የዚህ ሁሉ የመጨረሻ ውጤቱ ሁከት፣ የእስረኞች ፍትህ አልባነትና በዓለም አቀፉ ማህበረሰብና በሰብአዊ መብት ተሟጋች ደርጅቶች መወገዝ ነው፡፡”
እ.ኤ.አ. ኦክቶበር 2013 ሂዩማን ራይትስ ዎች ባቀረበው ዘገባ መሰረት “ባለፉት አስር ዓመታት ሂዩማን ራይትስ ዎች እና ሌሎች ዓለም አቀፋዊና የአገር ውስጥ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ረገጣዎች ማለትም በዘፈቀደ ማሰርና ማጋዝ፣ ህገወጥ የእስረኞች አያያዝ ድርጊት እና ማሰቃየት በተለያዩ ህጋዊና ህጋዊ ባልሆኑ እስር ቤቶች ውስጥ መፈጸማቸውን በተጨባጭ ማስረጃ አረጋግጠው ለህዝብ ይፋ አድርገዋል፡፡”
ማዕከላዊ የምርመራ ማዕከል ቤት: ኢትዮጵያ እስር ቤት መሆኗን ይመሰላል
ከዚህ በፊት በኢትዮጵያ የእስር ቤቶችን አያያዝ ሁኔታዎች በተመለከተ ገንቢ ትችት ማቅረቤ ይታወሳል፡፡ እ.ኤ.አ. ፌብሯሪ 2012 ባቀረብኩት ትችት የኢትዮጵያ መንግስት በየፖለቲካ እስረኞች ማጎሪያዎች ላይ በዘፈቀደ የሚፈጽማቸውን የሰብአዊ መብት ረገጣዎችና ህገወጥ የእስረኞች አያያዝ ሁኔታ ለማጋለጥ ሞክሪያለሁ፡፡ እ.ኤ.አ. ፌብሯሪ 2013 ኢትዮጵያን “በአፍሪካ የፖሊስ ረጋጭ መንግሥት ተምሳሌትነት በመፈረጅ ጠንካራ ትችት አቅርቢያለሁ፡፡ የክርክር ጭብጤንም እንደሚከተለው አቅርቢያለሁ፡፡
“የሌባ ፖሊስ መንግስት ብቸኛ መለያው — ልዩ መታወቂያው — በማያቋርጥና በየቦታው የሚፈጽማቸው የዘፈቀደ እስሮች፣ ዜጎችን ማደንና ወደ እስር ቤት ማጋዝ ናቸው፡፡ ማንም ሰው በከፍተኛም ሆነ በዝቅተኛ የመንግስት ባለስልጣን ስሜታዊ ትዕዛዝ በቀጥጥር ስር ውሎ የሚታሰር ከሆነ ይኸ የፖሊስ መንግስት መገለጫ ነው፡፡ ከህግ አግባብ ውጭ የዜጎች መብት የሚጣስ ወይም የሚረገጥ ከሆነ ያ በጣም አስቀያሚ የፖሊስ መንግስት መገለጫ ነው፡፡ የህግ የበላይነት ከህግ በላይ በሆነ ፖሊስ አዛዥ የሚተካ ከሆነ ያ የሌባ ፖሊስ መንግስት ተምሳሌት ነው፡፡”
በዚያ ባቀረብኩት ትችት በአዲስ አበባ ከተማ በሙስሊሙ ህብረተሰብ ላይ ከህግ አግባብ ውጭ የፍተሻ ወረቀት ሳይዙ በሌሊት በግልሰቦች ቤት በመሄድ በሚያካሂዱት ህገወጥ ፍተሻ ላይ ያተኮረ ነበር፡፡ በአንዱ ህገወጥ የቤት ፍተሻ ላይ የተደረገው የሚቆጠቁጥ ድርጊት ግን የፌዴራል ፖሊስ ኃላፊዎች በሙስሊም ዜጎች ቤቶች በመግባት የፈጸሙት የገንዘብ፣ የወርቅ ጌጣጌጥ፣ የተንቀሳቃሽ ስልኮች፣ ላፕቶፕ ኮምፒውተሮች፣ የሃይማኖት መጻህፍትና ሌሎች የግል ቁሳቁሶች ላይ የተደረገው ዝርፊያ ነው፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ በአዲስ አበባ ከተማ በአንድ ክፍለ ከተማ የፖሊስ አዛዥ ለሆነ ሰው የአሜሪካ ድምፅ የአማርኛው ፕሮግራም ጋዜጠኛ ጠንካራ ጥያቄዎችን በማንሳት ቃለመጠይቅ ሲያቀርብለት እንዲህ የሚል አሳፋሪ ማስፈራሪያ ሰጥቷል፣ “ዋሽንግተንም ሆነ በሰማይ ቤት ብትኖር ደንታዬ አይደለም፣ ከቁብ አልቆጥረውም፣ነገር ግን አዚያው ድረስ መጥቼ አንጠልጥልዬ አመጣሀለሁ፣ ይህን ልታውቅ ይገባል” ብሎ ዛተበት፡፡
እ.ኤ.አ. ጁላይ 2012 ኤርን በርኔት የተባለቸው የሲኤንኤን ጋዜጠኛ ኢትዮጵያን ከጎበኘች በኋላ የሚከተለውን ምስክርነት ሰጥታለች፡፡
“ባለፈው ወር ኢትዮጵያ በነበርኩበት ጊዜ የፖሊስ መንግስት ምን እንደሚመስል ለመመልከት ችያለሁ… አውሮፕላን ማረፊያው በቆየሁበት ጊዜ የጉምሩክ የስራ ሂደቱን ለማጠናቀቅ አንድ ሰዓት ወስዶብኛል፣ ይህም በሰልፉ መብዛት ምክንያት አይደለም ነገር ግን በፍተሻና በሚቀርቡት ጥያቄዎች መንዛዛት ምክንያት ነው፡፡ የመንግስት ባለስልጣኖች ብዙ ጊዜ በመንግስት መኪናዎች እንድንንቀሳቀስ ይፈልጋሉ፣ ይህም ወዴት እንደምንሄድ ለማወቅ ስለሚፈልጉ ነው፡፡ በመቶሺዎች የሚቆጠር ዶላር ዋጋ ያላቸው የቴሌቪዥን መሣሪያዎች በአውሮፕላን ማሪፊያው ከተውን በኋላ ብቻ ነው ቁጥጥራቸው በመጠኑም ቢሆን መላላት የቻለው፡፡”
የፖሊስ መንግስት ቃለመጠይቅ አንዴት አይነት አንደሆነ በቪደኦ ማየት ይቻላል!?
ሂዩማን ራይትስ ዎች በተቃዋሚ ፖለቲካ እስረኞች ወይም መብታቸውን ለማስከበር በሚጠይቁ ዜጎች ላይ በመንግስት ታጣቂ ኃይሎች የሚፈጸመውን የሰብአዊ መብት ረገጣ ዘገባ በማረጋገጥ በየጊዜው ዘገባዎችን እያዘጋጀ ያስቀምጣል፡፡ በዚህ ዓመት መጀመሪያ አካባቢ በአዲስ አበባ ከተማ የሙስሊሙን አመጽ መርቷል በሚል ውንጀላ ተከሶ የተያዘ ወጣት ግለሰብ ቃለ መጠይቅና የእምነት ቃሉን በቪዲዮ በመቅረጽ ህዝብ እንዲያየው ተደርጓል፡፡ በኢትዮጵያ የሙስሊሙ ህብረተሰብ ከሁለት ዓመት በላይ ጀምሮ መንግስት በኃይማኖታችን ጣልቃ መግባቱን ያቁም በማለት ተቃውሞውን ሲያሰማ ቆይቷል፡፡
ከታወቁ የዜና ምንጮች መረዳት እንደተቻለው በቪዲዮ የተቀረጸው ቃለ መጠይቅ በማዕከላዊ ምርመራ በአንደ ፖሊስ ወይም ደህንነት ባለስልጣን ቢሮ ውስጥ እንደሆነ ይነገራል፡፡ በቃለመጠይቅ መስጫው ክፍል ውስጥ ሌሎች ሰዎች የነበሩ ሲሆን የሚሰማው የዋናው ቃል ጠያቂ ድምጽ ነበር፣ (የሌላ ሰው ድምጽ መስማማቱን ለመግለጽ ዋናውን ቃለ መጠይቅ አድራጊ ሲያቋርጠው ለተወሰነ ጊዜ ይሰማ ነበር፡፡)
የቃለ መጠይቅ ማድረጊያው ክፍል ባለመስታወትና ባለፋሽን በር ያለው ነው፡፡ በመሰረቱ ላይ ባለ ነጭ ቀለም መጋረጃ ይታያል፡፡ በጣም ውድ የሆኑ ከውጭ ኢምፖርት ተደርገው የገቡ ባለ ረዥም መደገፊያ በቆዳ የተለበዱ የባለስልጣን ወንበሮች እና ግማሹ የቃለ መጠይቅ ማድረጊያ ክፍል በሶፋዎች ተሞልቶ በካሜራ ሌንሱ ይታያል፡፡ ከተጠርጣሪው ጎን የኢትዮጵያ ካርታ ተሰቅሎ ይታያል፡፡ ቃለ መጠይቁ በጨለማው የማዕከላዊ ምርመራ ክፍል ውስጥ አለመደረጉን ያሳያል፡፡ እንደ ውስጥ አዋቂ ምንጮች ከሆነ ቃለ መጠይቁ የተካሄደው በማዕከላዊ ፖሊስ ኮሚሽነሩ ቢሮ ውሰጥ እንደሆነ ይገመታል፡፡
በቪዲዮ ቴፑ እንደሚታየው ተጠርጣሪው ሰው ሁለት እጆቹን በካቴና ታስሮ ለጸሎት እንደሚተጋ ሰው መዳፎቹን ከወዲያ ወዲህ ሲያወራጭ ይታያል፡፡ ቃለ መጠይቅ አድራጊው ለወጣቱ ተጠርጣሪ ዝርዝር ቃለመጠይቅ ሰጠ፡፡ ቃለ መጠይቅ አድራጊው የሚያስጠላ አዛዣዊ ድምጽ የሚያስተላልፍ መሆኑን ያሳብቅበታል፡፡ ቃለ መጠይቅ አድራጊው በመካከለኛው ክፍለ ዘመን ይደረግ እንደነበረው የማስገደድ ዝርዝር ቃለ መጠይቅ ሁኔታ ይታይበት ነበር፡፡ ቃለ መጠይቅ አድራጊው በፍርሀትና በለሆሳስ ድምጽ የሚናገረውን ተጠርጣሪ ስለእምነቱና ሌሎችም ጉዳዮች በጥያቄ ያዋክበው ነበር፡፡ ቃለ መጠይቅ አድራጊው በሚያስፈራ መልክ ስለሰለፊያ እምነት ምንነትና ስለእስላም አክራሪነት እንዲሁም በሌሎች ላይ ሰለሚኖረው መልካም አስተሳሰብ አደገኛነት ሲጠይቀው ተስተውሏል፡፡ ቃለ መጠይቅ አድራጊው ተጠርጣሪውን በአሽሙር በመሸንቆጥ ሲያስጨንቀው ታይቷል፡፡ ቃለ መጠይቅ አድራጊው ተጠርጣሪውን የሙስሊም ትምህርት ቤቶችን ሽፋን በማድረግ እሱ እና መሰሎቹ በኢትዮጵያ የእስላም መንግስት ለማቋቋም ጥረት እንደሚያደርጉ ወንጅሎታል፡፡ የተጠርጣሪው ድርጀት የገንዘብ ምንጩ ከየት እንደሆነ ቃለ መጠይቅ አድራጊው ደጋግሞ በመጠየቅ ሲያባሳጨው ታይቷል፡፡ በቃለ መጠይቅ ሂደቱ ሁሉ ቃለ መጠይቅ አድራጊው በተጠርጣሪው ላይ ሲያፌዝ፣ ንቀት ሲያሳይ፣ ሲቀልድና በንቀት ሲሳለቅ ታይቷል፡፡ ቃለ መጠይቅ አድራጊው ተጠርጣሪው እንዲናገር ዕድሉን ከሰጠ በኋላ ተጠርጣሪው በማስተባበል መናገር ሲጀምር ቃለ መጠይቅ አድራጊው ወዲያውኑ በማቋረጥ ያስቆመዋል፡፡ ቃለ መጠይቅ አድራጊው ወጣቱ ተጠርጣሪ በተስፋቢስነት በረዥም የባለስልጣን ወንበር ላይ ተቀምጦ ሁለት እጆቹን በካቴና ታስሮ ቃለ መጠይቅ አድራጊውን በአክብሮት ዓይን እያየ በለሆሳስ ቅላጼና በጉልህ በማይሰማ ድምጽ በሚናገርበት ጊዜ የበላይነት ስሜት ያንጸባርቅበታል፣ ይረብሸዋል፣ እንዲሁም በተለየ መልኩ ያንቋሽሸዋል፡፡
እንደ ውስጥ አዋቂ ምንጮች ከሆነ በቪዲዮው ላይ የተደበቀ ብዙ ነገር አለ፡፡ ለምሳሌ ያህል የተቀረጸው የቪዲዮ ቃለ መጠይቅ ከመደረጉ ጥቂት ቀናት ቀደም ብሎ ለመደብደብ ወደ ኋላ በማይሉ ዝቅተኛ የፖሊስ ባለስልጣኖች በማለሳለስና ተገድዶ ላመነው የቪዲዮ ቀረጻ ተባባሪ እንዲሆን በማድረግ ሙሉ ቃለ መጠይቅ ተደርጎለት ነበር፡፡ የቪዲዮ ቀረጻ ቃለ መጠይቁ በሚደመጥበት ጊዜ ሌሎች የፖሊስ አባላትና የሲቪል ሰራተኞች እንዲገኙ ተደርጓል፡፡ እንዲገኙ የተደረገበት ዋና ዓላማም ጉዳዩ ለፍርድ ቤት በሚቀርብበት ጊዜ ተጠርጣሪው ግለሰብ ያለምንም ተጽዕኖ በእራሱ ፈቃድ አምኖ የተናገረው መሆኑን መመስከር እንዲችሉ ለማመቻቸት ነው፡፡ (በቪዲዮ የተቀረጸውን ቃለ መጠይቅ ቅጅ ለተከላካይ ጠበቆችም ሆነ ለፍርድ ቤቱ የተሰጠ ነገር የለም፡፡) ቃለ መጠይቁ የተቀረጸው የፖሊስ ማስፈራሪያነት በሌለበትና ከጣልገብነት ነጻ በሆነ መልኩ በተረጋጋና በጥሩ የንግግር ቅላጼ መሰረት ተደርጎ ነው፡፡ ጥያቄዎቹ በመስክ ላይ እንደሚፈነዳ ደማሚት ተደርገው በዘዴ የተዘጋጁ ናቸው፡፡ ጥያቄ አቅራቢው ተጠርጣሪው የየትኛው ድርጅት አባል እንደሆነ፣ ምን ፍልስፍና እንደሚከተል፣ እነማን ደጋፊዎቹ እንደሆኑ፣ የገንዝብ ምንጫቸው ከየት እንደሆነ፣ የተከሰሰበት ወንጀል ምን እንደሆነና የመሳሰሉት አጠቃላይ ጥያቄዎች ይቀርቡለታል፡፡ እነዚህ ጥያቄዎች ተጠርጣሪው ድርጊቱን ለመፈጸሙ ሊያሳምን በሚችል መልኩ ተያያዥነት ያላቸው በሚመስል መልኩ ሌሎች ሁለተኛ ዙር ጥያቄዎች ይከተላሉ፡፡ ለምሳሌም ተጠርጣሪውን ለምንድን ነው የዚህ ድርጅት አባል የሆንከው? አባል ሆኖ ምን ሚና እንደተጫወተ እንዲሁም እነዚህን የተወነጀለባቸውን ድርጊቶች ለምን ሪፖርት እንዳላደረገና የመሳሰሉትን ጥያቄዎች ይጠየቃል፡፡ የቪዲዮ ቃለ መጠይቁ ተጠርጣሪው የወንጀል ድርጊቱን መፈጸሙን ለማመኑ ትክክለኛ መረጃና ለእራሱ መስቀያ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡
ዋና የፖሊስ መርማሪዎች ጭካኔና አስገዳጅነት የተሞላበትን በቪዲዮ የተቀረጸ ቃለ መጠይቅ ያለበት የምርመራ ውጤት ማስቀረት አይፈልጉም፡፡ የውስጥ አዋቂ ምንጭች ተጠርጣሪው ወጣት እጆቹን በካቴና ታስሮ በሰጠው ቃለ መጠይቅ ላይ መደነቃቸውን ይገልጻሉ፡፡ እጁን በካቴና ታስሮ ለአንድ ከፍተኛ የፖሊስ ባለስልጣን ቃለመጠይቅ የሚሰጥ ተጠርጣሪ የጥያቄና መልስ ሂደት በቪዲዮ ቴፕ ተቀርጾ ማየት በጣም አስደንጋጭ ከመሆኑም በላይ እንደ አንዳንድ የውስጥ ምንጮች ተጠርጣሪውን ወጣት በካቴና አስሮ ቃለ መጠየቅ ማድረጉ ለምን እንዳስፈለገ ግልጽ እንዳልሆነ ይናገራሉ፡፡ እንዲሁም የቪዲዮ ቀረጻ ቃለ መጠይቁ መንግስት በተቃዋሚ የፖለቲካ ደርጅቶች ላይ የስነ ልቦና ጦርነት በማካሄድና በማስፈራራት ረገድ ጠቀሜታ ያስገኝለታል ተብሎ ይታመናል፡፡ ይህ ሁኔታ ተጠርጣሪዎችን በማስፈራራትና በማሸማቀቅ ለተቃዋሚ ኃይሎችና ለአመጸኞች ማዳከሚያ እንዲሆን ታስቦ የተሰራ ነው፡፡ በጥንካሬና በጽናት የተሞሉ ወጣት የተቃዋሚ ድርጅት መሪዎች በማዕከላዊ የምርመራ ማዕከል መዳፍ ስር ወይም መንጋጋ ከገቡ ፍርሀትና መደናገጥ አንደሚታይባቸው ለሕዝብ ለማሳየት ነው፡፡ ይህ ሁኔታ የተቃዋሚ ድርጀት መሪዎች ማዕከላዊ የምርመራ ማዕከል ከደረሱ እንደሚሰባበሩ፣ እንደሚደቆሱ፣ እንደሚታኘኩና እንደሚበጣጠሱ የማያዳግም መልዕክት ማስተላለፊያ ዘዴ ነው፡፡ እንደ ሂዩማን ራይትስ ዎች ዘገባ ከሆነ ተገዶ ማመን አንዳንድ ጊዜ ግለሰቦች ከእስር ቤት ከወጡ በኋላ ሳይወዱ በግድ መንግስትን እንዲደግፉ የሚደረጉበት ዘዴ ነው፡፡
ይህም ሆኖ በቪዲዮ የተቀረጸውን የቃለ መጠይቅ አድራጊውን ሙሉና የተጠርጣሪውን መብት በመጣስ ለእይታ የበቃውን ድራማ መመልከት “በህግ ከለላ በቁጥጥር ስር የዋሉ ዜጎች በፍርድ ቤት ወንጀለኛነታቸው እስካልተረጋገጠ ድረስ ነጻ ናቸው፣ እንዲሁም ተገደው በእራሳቸው ላይ ምስክርነት አይሰጡም“ የሚለውን ህገመንግስታዊ መብት የጣሰ የማይታመንና አስደንጋጭ ሁኔታ ነው (አንቀጽ 20(3) ፡፡ ቃለ መጠይቅ አድራጊው የወጣቱን ተጠርጣሪ ህገመንግስታዊ መብት በኮርማ እንደተናደ የሴራሚክ ቁልል ደፍጥጦታል፡፡ ወጣቱ ተጠርጣሪ “ያለመናገር መብት“ እንዳለው በግልጽ የተቀመጠውን ህገመንግስታዊ መብት ቃለ መጠይቅ አድራጊው ከቁብ የቆጠረው አይመስልም (አንቀጽ 19(2)(5) ፡፡ “በህግ ከለላ በቁጥጥር ስር የዋሉ ተጠርጣሪዎች ያለመናገር መብት አላቸው፡፡ በህግ ከለላ በቁጥጥር ስር የዋሉ ዜጎች ተገደው የእምነት ቃል እንዲሰጡ አይደረግም ተገደው የሰጡትም ቃል ለማስረጃነት ተቀባይነት አይኖረውም፡፡ በማስገደድ የተገኘ ማንኛውም ማስረጃ በህግ ፊት ተቀባይነት አይኖረውም፡፡” ቃለ መጠይቁ በሚደረግበት ጊዜ የተጠርጣሪው የህግ ጠበቃ እንዲገኝ አለመደረጉ ቃለ መጠይቅ አድራጊውን የሚያሳስበው አይመስልም (አንቀጽ 20(5)፣ አንቀጽ 21(2) ፡፡ “የተከሰሱ ሰዎች የህግ ጠበቃቸው የመጎብኘትና… ከህግ ጠበቃቸው ጋር የመመካከር መብት አላቸው፡፡“ “ተጠርጥሮ በህግ ከለላ ጥላ ስር የዋለው ተጠርጣሪ ስለቀረበበት ክስ አስቀድሞ በቃለ መጠይቅ አድራጊው አልተገለጸለትም፡፡“ አንቀጽ 20(2) “የተከሰሱ ሰዎች ስለቀረበባቸው ክስ ዝርዝር መረጃ የማግኘት መብታቸው የተጠበቀና ይህም በጽሁፍ ሊደርሳቸው ይገባል፡፡“
ቃለ መጠይቅ አድራጊው ተጠርጣሪውን ከየትኛው የእስልምና እምነት ክፍል እንደሆነ በማስፈራራት መረጃ ለማግኘት ሞክሯል፣ ለማስረዳትም ጥረት አድርጓል፣ አክራሪነት የየትኛው የእስልምና አስተምህሮ እንደሆነና ተጠርጣሪው ይህንን አውግዞ መንግስት የሚፈልገውን እንዲመርጥ በመጠየቅ የተጠርጣሪውን መብት ደፍጥጦታል፡፡ አንቀጽ 27(1)(3) “እያንዳንዱ ሰው የራሱ የእምነት ነጻነት አለው… ይህ መብት ግለሰቡ የመረጠውን ኃይማኖት በግሉ ወይም ከህብረተሰቡ ጋር በጋራ የመከተልና የማራመድ መብትን ጭምር ያጠቃልላል… (3) ማንም የመረጠውን የራሱን እምነት ለማራመድ የሚያግደው ወይም የሚከለክለው የለም፡፡“ ቃለ መጠይቅ አድራጊው ለተጠርጣሪው ስለኃይማኖት እንቅስቃሴውና ስለእምነት ምርጫው ሲጠይቅ “ተጠርጣሪው በግል ወይም ከሌሎች ጋር በጋራ በመሆን የመሰብሰብ፣ የጦር መሳሪያ ሳይዙ ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግና አቤቱታ የማቅረብ መብት” (አንቀጽ 30(1) እንዳለው የተረዳ አይመስልም፡፡ በአጭሩ ቃለ መጠይቅ አድራጊው የተጠርጣሪውን መብት የደፈጠጠው ህገመንግስቱ ያጎናጸፈውን የኢትዮጵያን ህገመንገስት በመጣስ ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያ ፈርማ የተቀበለቻቸውን ልዩ ልዩ ዓለም አቀፍ ደንቦችን በመናድ ጭምር ነው፡፡
ጥፋተኝነትን ለመከላከል የአሜሪካ ህገመንግስት 5ኛ ማሻሻያ
ጥፋተኝነትን መከላከል ወይም ያለመናገር መብት የአሜሪካ ህገ መንግስት ለዜጎቹ ያጎናጸፋቸው ዋነኛ የመብት ስብስቦች ናቸው፡፡ ማንም ሰው “በማንኛውም የወንጀል ጉዳይ ተገዶ ምስክርነት እንዲሰጥ አይደረግም“ በማለት አምስተኛው የአሜሪካ ህገ መንግስት ማሻሻያ ይደነግጋል፡፡ ከእንግሊዝ ተሰደው አሜሪካንን በቅኝ ግዛትነት የያዟት የስነምግባር ሰዎች ናቸው ይህንን የተገበሩት፡፡ ምክንያቱም በእምነታቸው ሰዎች ሲጠየቁ ዝም የማለት ወይም በጌቶቻቸው ስቃይ ተገድደው መልስ ያለመስጠት መብት እንዳላቸው የጸና እምነት ስለነበራቸው ነው፡፡ የበላይ ጠያቂ ጌቶች ብዙውን ጊዜ ደጋጎቹን የእምነት ሰዎች የያዙት እምነት ምን እንደሆነ እንዲያምኑ ያስገድዷቸውና ያሰቃዩአቸው ነበር፡፡ ዝም ካሉና ካልተናገሩ ጥፋተኛ ብለው ይፈርጇቸው ነበር፡፡ የእንግሊዝ ህግ በ1600ዎቹ አጋማሽ ጥፋተኝነትን የመከላከል መብት ለዜጎቹ አጎናጽፏል፡፡
ይህ እራስን ከጥፋተኝነት የመከላከል የተቀደሰ መብት የአሜሪካ የወንጀል መከላከል ህግ መሰረት ነው – ማንም የተከሰሰ ሰው ጥፋተኝነቱ ባስተማማኝ ሁኔታ ከጥርጣሬ ባለፈ መልኩ በመንግስት እስካልተረጋገጠ ድረስ ነጻ ነው፡፡ ጥፋተኛ መሆን አለመሆኑን የማረጋገጡ ተግባር ደግሞ የመንግስት፣ የአቃቢያን ህግና የፖሊስ ነው፡፡ የተከሰሰን ሰው ጥፋተኝነት ለማረጋጥ የተከሰሰው ግለሰብ ምንም ነገር ማድረግ የለበትም፣ በተለይም ከፖሊስ ወይም ከአቃቤ ህግ ጋር መነጋገር ወይም መተባበር ግዴታ የለበትም፡፡ የአሜሪካ ኮንግረስ፣ ጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ የአሜሪካ ፕሬዚዳንትም ሆነ የአካባቢ ፖሊስ የአሜሪካንን ዜጋ በማስገደድ ለጥፋተኝነታቸው ማስረጃ የሚሆኑ መግለጫዎችን እንዲሰጥ/እንዳይሰጥ ወይም እንዲያምን/እንዳያምን ማድረግ አይችሉም፡፡
የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርደ ቤት የፖሊስን አስገዳጂ የምርመራ ቃለ መጠይቅ ተግባር ያቆመው እ.ኤ.አ. በ1966 ነው፡፡ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ “በፖሊስ ምርመራ ጊዜ የህግ መብት ማስጠንቀቂያ“ ለተባለ ቀላል የአሰራር ሂደት ኃላፊነት ሰጥቷል፡፡ በተግባር ሲታይ ይህ የፖሊስ ምርመራ የህግ መብት ፖሊስ ምርመራ ሊያደርግ በሚፈልግበት ጊዜ ተጠርጣሪውን/ዋን በቢሮው ወይም የተጠርጣሪውን/ዋን ነጻነት ሊያውክ በማይችል ሁኔታ መሆን እንዳለበት፣ ተከሳሹ/ሿ ዝም የማለት መብት እንዳላቸው፣ በተጠርጣሪው/ዋ የተሰጠው ምስክርነት ለተጠርጣሪው/ዋ ማስረጃነት ሊውል እንደሚችል፣ተጠርጣሪው/ዋ ከመጠየቁ/ቋ በፊት ከህግ አማካሪው/ዋ ጋር የመምከር መብት እንዳለው/ላት እና ተጠርጣሪው/ዋ የህግ ጠበቃ ለማቆም አቅም ከሌለው/ላት መንግስት ምርመራ ከመጀመሩ በፊት ጠበቃ እንደሚያቆም በግልጽ ያስቀምጣል፡፡ ሆኖም ግን ድርጊቱ ሆን ተብሎ በማወቅ የተፈጸመ ከሆነ፣ ወይም ከስለላ ስራ ጋር የተያያዘ ከሆነ፣ ወይም አንድን ዓላማ ለማሳካት መሰረት አድርጎ የተፈጸመ ከሆነ ወይም በፖሊስ ህገወጥ የምርመራ ዘዴ የተገኘ መረጃ ከሆነ እራስን ከጥፋተኝነት የመከላከል መብት ወይም የህግ የምክር አግልግሎት የማግኘት መብትን ያስነሳል፡፡ የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይህን “ሚራንዳህ ወይም በፖሊስ ምርመራ ጊዜ የህግ መብት በቀን ተቀን የፖሊስ ምርመራ ተግባራት ሁሉ እንዲካተት አውጇል፣ ማስጠንቀቂያዎቹም አገር አቀፋዊ ባህል ሆነው እስኪሰርጹ ድረስ ይሰራል”፡፡
በአሜሪካ ህገ መንግስት አምስተኛ ማሻሻያ የተሰጠውን እራስን ከጥፋተኝነት የመከላከል መብት መከላከል እንድችል የህግ ባለሙያነቴ የሰጠኝ መብት በኩራት እንድሞላ አድል ደርሶኛል፡፡ እ.ኤ.አ. በ1998 በህዝብና በፒቪ መካከል በነበረው ጉዳይ የሚራንዳህ የህግ ስርዓት ታስቦበትና ሆን ተብሎ የምስክርነት ማስረጃው (ጥፋተኝነትን አስገደድዶ መቀበል፣ በግዳጅ ማሳመን) በመጣሱ በካሊፎርኒያ ግዛት ጠቅላይ ፍርድ ቤት ቀርቤ ሽንጤን ገትሬ በመከራከር ማስቀየር በመቻሌ ልዩ ክብርና ሞገስ ይሰማኛል፡፡ በዚያን ወቅት በካሊፎርኒያ ግዛት በሚገኙ የፖሊስ መምሪያዎች ተጠርጣሪዎች በምርመራ ጊዜ ያለመናገርና የህግ ባለሙያ የማናገር መብት እንዳላቸው እየታወቀ ፖሊስ አፋጥጦ በመጠየቅ መረጃን የማግኘት ጥረቱ በጊዜው በነበረው አሰራር ተቀባይነት ነበረው፡፡ ይህ በተወሰኑ የፖሊስና አቃብያነ ህጎች ክልል ወስጥ ይደረግ የነበረው ህገወጥ የአጠያየቅ ስርዓት “ከሚራንዳህ ህግ ውጭ” በመባል ይታወቅ ነበር፡፡
በካሊፎርኒያ ግዛት በፒቪ ፍርድ ቤት ውሳኔ መሰረት “ከሚራንዳህ ምርመራ ውጭ“ የሚደረግ የምርመራ አሰራር በፍፁም አንዲቆም ተደረገ፡፡ እ.ኤ.አ. በ2000 ዘጠነኛው የተዘዋዋሪ ችሎት በሲኤሲጀ እና በሳንታ ሞኒካ ከተማ ተካሂዶ ተጠርጣሪዎች በምርመራ ጊዜ ያለመናገር መብት እንዳላቸው እየታወቀ ይህንን ጥሰው ከሚራንዳህ የምርመራ ህግ ውጭ አስገድዶ ለማሳመን እና ጥፋተኝነትን እንዲቀበሉ ብለው የሚፈጽሙ ፖሊሶች በህገ መንግስቱና በሲቪል ህዝቡ ላይ ለሚያደርሱት ጉዳት በግል ተጠያቂና ተከሳሽ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል፡፡
በማስገደድና በማሰቃየት የተገኘ የእምነት ቃል ፍትሀዊም ተዓማኒነትም የለውም
በወንጀል መከላከል ህግ ተጠርጣሪውን/ዋን አስገድዶ በማሳመን ጥፋተኛ በማድረግ የተገኘ መረጃን ያህል ትኩረትን የሚስብ ነገር የለም፡፡ ፖሊስ ምርመራ የሚያደርግበት ዋና ዓላማ እውነታው ላይ ለመድረስ ወይም ተጠርጣሪው ነጻ መሆኑን ለማረጋገጥ አይደለም፡፡ ብቸኛውና ዋናው ዓላማ የጥፋተኝነት መግለጫዎችን እና የእምነት ቃል ከተጠርጣሪው አንደበት ለመስማትና ይህንን መሰረት በማድረግ በተከሳሹ/ሿ ላይ ክስ ለመመስረት እንዲቻል ነው፡፡ በማስገደድ የፖሊስ ምርመራ ሂደት ጊዜ ተጠርጣሪው ከጥፋተኝነት ነጻ መሆኑን በራሱ አንደበት መግለጽ ይጠበቅበታል፣ ወይም ደግሞ ጥፋተኛ ተብሎ እንዲወሰንበት መንግስትን በማገዝ መተባበር ይጠበቅበታል፡፡ “የፖሊስ የበላይነት” በተንሰራፋበት አካባቢ እራስን ጥፋተኛ አድርጎ ማቅረብ ሜዳውን ለእብሪተኛና ለመሰሪ ፖሊሶች ምርመራ ምቹ ሁኔታን በመፍጠር ዜጎችን ለፍትህ እጦት ሰለባ ያደርጋል፡፡
የተጠርጣሪው ወይም የተከሳሹ በፖሊስ ምርመራ ሂደት ዝም የማለት መብት የጥፋተኝነትና የቅጣት ሰለባ ለማድረግ ከሚደረገው ጥረት አንጻር ብዙ አሳማኝ ምክንያቶች አሉ፡፡ ዋናው ጠቃሚ ነገር ፍትሀዊነት ነው፡፡ በሙያው የሰለጠነ የምርመራ ፖሊስ የህግ ጥሰት ፈጽሟል ባለው ተጠርጣሪ ዜጋ ላይ ጥያቄዎችን እንዲያቀርብ በመፍቀድ የግዳጅ የእምነት ቃል ማግኘት በምንም መልኩ ፍተሀዊነትን አያሳይም፡፡ የማስገደድ የምርመራ ዘዴ ፍትሀዊነት በጎደለው መልኩ ሕገመንግስታዊ የማስረጃ ማቅረብን ግዴታ ከመንግስት ከሳሽ አጅ ወደ ተጠርጣሪው እንዲዞር ያደርጋል፡፡ ተጠርጣሪው ፍትህን በአግባቡ ማግኘት እንዲችል ከተፈለገ በፖሊስ የምርመራ ሂደት ጊዜ ተጠርጣሪው የምክር አግልግሎት እንዲያገኝ የህግ ባለሙያ እንዲያገኝ የማድረጉ ሂደት ጠቃሚነቱ የጎላ ነው፡፡ የተጠርጣሪውን የህግ ጉዳይ ፍሬ ነገሩን የተጠርጣሪው የህግ አማካሪ ሳያየው ተጠርጣሪውን ወይም ተከሳሹን በፖሊስ እንዲመረመር ማስገደድ ተገቢነት የለውም፡፡ ለማንኛውም የምርመራ ጥያቄ ተጠርጣሪው ምን መልስ መስጠት እንዳለበትና መልስ መስጠት የሌለባቸውን ጉዳዮች የህግ ባለሙያው ካጠናው በኋላ የተጠርጣሪው የህግ አማካሪ መንግስት ምን መረጃ እንደሚፈልግና ምን መከላከያ ማስረጃዎች እንዳሉ ማወቅ አለበት፡፡
በማሰቃየት ወይም ማንኛውንም የሰብአዊ መብት ረገጣ ዘዴዎች በመጠቀም የተገኘ የእምነት ቃል በምንም ዓይነት ሁኔታ አስተማማኝ መረጃ ሊሆኑ አይችሉም፡፡ ተጠርጣሪዎች በመርማሪ ፖሊሶች የሚደርስባቸውን የአካልና የአዕምሮ ስነ ልቦና ስቃይ ለማቆም ሲሉ ያልሰሩትን ነገር እንደሰሩ አድርገው የእምነት ቃል ሊሰጡ ይችላሉ፡፡ ምግብ፣ ውኃና የመኝታ አገልግሎት የተነፈጉ ተጠርጣሪዎች ግራ በመጋባትና ስቃዩን በማስቀረት መሰረታዊ አገልግሎቶችን ለማግኘት ሲሉ የእምነት ቃል ሊሰጡ ይችላሉ፡፡ ነጻ የሆኑ ተጠርጣሪዎች በፖሊስ ምርመራ ጊዜ ሲጠየቁ ከክሱ ነጻ የሚያወጣቸው እየመሰላቸው ስለእውነት ብቻ ይናገራሉ፡፡ በመሰሪ ፖሊሶች የሚዘረጉላቸውን አሽክላዎች አይገነዘቡም፡፡ እውነቱን መናገር ነጻ የሚያደርጋቸው ይመስላቸዋል፣ ሆኖም ግን ብዙውን ጊዜ እውነታው በተቃራኒው በሰለጠኑ የፖሊስ መርማሪዎች ተጠምዝዞና ተፐውዞ ተጠርጣሪውን ለማዳካም ሲባል ፖሊስ አደናጋሪ ጥያቄዎችን በመጠየቅ፣ በማስፈራራት፣ በመዛትና በማታለል ዓላማውን ለማሳካት ጥረት ያደርጋል፡፡ ነጻ የሆኑ ሰዎች የማያቋርጥ ለሰዓታት የዘለቀ የፖሊስ ምርመራ ከተደረገ በኋላ ያልሰሩትን ወንጀል እንደሰሩ (የሀሰት የእምነት ቃል) የሚያያረጋግጡ ብዙ ማህበራዊና ሳይንሳዊ ጥናቶች አሉ፡፡ በፖሊስ ምርመራ ጊዜ የተጠርጣሪው ዝምታ በዓለም ላይ ከወርቅ፣ ፕላቲኒየም፣ የተከበረ ድንጋይ ወይም አልማዝ የበለጠ ዋጋ አለው፡፡
ማስመሰል ለምን? ጨካኔንና ተያቂ አልባነትን መፍጠር
በ15ኛው ክፍለ ዘመን በእንግሊዝ አገር በተራ ፍርድ ቤቶች ሊከሰሱ የማይችሉና በጣም ታዋቂ የሆኑ ሰዎችን ጉዳይ የሚያይ ተጠያቂነት የሌለው ፍርድ ቤት (በፍርድ ቤቱ ጣሪያ ላይ የኮከብ ምልክት ያለበት) ተመሰረተ፡፡ ይህ ፍርድ ቤት በሚስጥርና የህግ ሂደትን ሳይከተል ምስክሮቸን ሳይሰማ ብይን ይሰጥ ነበር፡፡ በመጨረሻም ንጉሱ ይህን ተጠያቂነት የሌለው ፍርድ ቤት ተፎካካሪያቸውን፣ ተቃዋሚዎቻቸውን እና ትችት የሚያቀርቡባቸውን አካላት ጸጥ ለማድረግና ለማስወገድ ሲሉ ወደ ማጥቂያ ህጋዊ መሳሪያነት አሸጋገሩት፡፡ ገዥው የኢትዮጵያ አስተዳደርም እንደዚሁ በተመሳሳይ መልኩ የራሱን ተጠያቂ አልባ የፔንታጎን ቅርጽ ያለው ፍርድ ቤት በማቋቋምና በጣራው ላይ የኮከብ ምልክት ያለበትን ባንዲራ በመስቀል ስራውን በመስራት ላይ ይገኛል፡፡
ህግ የማያከብር መንግስት የማስገደድ እምነት፣ ለህግ ንቀትን የሚፈለፍል ገዥ
የራሱን ህገመንግስት መረን በለቀቀ አኳኋን የሚደፈጥጠውን አገዛዝ ሁኔታ ሁልጊዜ ባሰብኩ ቁጥር እንቆቅልሽ ይሆንብኛል፡፡ ሁልጊዜ ህገመንግስታችን እየተባለ በመንግስት መሪዎች የሚለፈፈው እርባናየለሽ ዲስኩር ከማሳቁም በላይ ምንም እውቀቱ ሳይኖረው ከቅዳሳን መጽሐፍት እየጠቀሰ የሚያነበንበውን የኃይማኖት ደቀመዝሙር እና ምን እንደሚልና ምን እንደሚያደርግ ትርጉም ያለው እውቀት ሳይኖረው በዘልማድ ባህላዊ ባላትን ለማክበር ሽርጉድ የሚለውን ባተሌ እንዳስታውስ ያደርገኛል፡፡ “ሰይጣን ለዓላማው ከመጽሐፍ ቅዱስ ይጠቅሳል“ የሚለውን የሸክስፒርን ስንኝ እንዳስታውስም ያደርገኛል፡፡ የስርዓቱ ገዥዎች ህገመንግስቱን ከአደጋና ከተቃዋሚዎች ጥቃት ለመጠበቅ ከነፋስ የፈጠኑ ናቸው፣ የራሳቸውን ህገመንግስት እራሳቸው በመጣስ ዋጋውን እንዲሚያሳንሱት በውል የተረዱት አይመስልም፡፡ ለዓመታት ደጋግሜ እንደተናገርኩት ለኢትዮጵያ መንግስት መሪዎች ስለህገ መንግስት ወይም የህግ የበላይነትን መስበክ ለተሰበሰቡ አረማውያን (አህዛብ) መጽሐፍ ቅዱስን እንደመስበክ ወይም በጥቁረር ባልጩት ድንጋይ ላይ ውኃ እንደማፍሰስ ይቆጠራል፡፡ በቅርቡ የወጣው የሂዩማን ራይትስ ዎች ዘገባ ገዥው ስርዓት ስለ የህግ የበላይነት ያለውን ጥልቅ ንቀት በጉልህ ያሳያል፡፡
በአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከሚገኙ ታላላቅ የህግ ዳኞች አንዱ የሆኑት ሌውስ ብራንዴስ እንዳመለከቱት “ህግ ባለበት መንግስት አገር መንግስት ጥንቃቄ በተመላበት ሁኔታ የህግ ጥበቃ ካላደረግ የመንግስት ህልውና አደጋ ውስጥ ይወድቃል፡፡ መንግስታችን ጠንካራና በየትም ቦታ የሚገኝ መምህር ነው፡፡ ለጥሩም ሆነ ለመጥፎ ነገር እራሱን ምሳሌ አድርጎ ለህዝቡ ያስተምራል፡፡ ወንጅል ተላላፊ በሽታ ነው፡፡ መንግስት እራሱ ህግ የሚጥስ ከሆነ ለህግ ያለውን ንቀት ይፈለፍላል፣ እያንዳንዱ ዜጋ እስከ እራሱ ድረስ ህግ እንዲጥስ ይጋብዘዋል፣ ስርዓተ አልበኝነት እንዲነግስ ይገፋፋል፡፡ የወንጀል ህግን ከማስተዳደር አንጻር ዓላማው ፍጻሜውን ሊያሳምር ይገባል፡፡ የግል ወንጀለኛን ለመዳኘት ሲል መንግስት እራሱ ወንጀልን የሚፈጽም ከሆነ አደገኛ በቀልተኝነት ይሆናል፡፡“ ብራንዴስ “በመንግስት በኩል የግል የስልክ መስመሮችን በመጥለፍ የስለላ ስራ በማካሄድ የእራስን የጥፋተኝነት መረጃ ለማቅረብ የሚደረግ አሰራር ህገወጥ ነው“ በማለት ሀሳባቸውን ቋጭተዋል፡፡
ገዥው አስተዳደር ህግን የሚጥስ ከሆነ ምን መደረግ አለበት? ህገመንግስት ደፍጣጭ ሲሆን? ገዥው አስተዳደር ለህግ የማይገዛ ወንበዴ ከሆነ ምን መደረግ አለበት? ህግን የማያከብርና የሚደፈጥጥ ገዥ አስተዳደር ህግን በሚያከብር መንግስት መተካት አለበት፡፡ በኢትዮጵያ ያለው ገዥ መንግስት ይቃወሙኛል የሚላቸውን ከህግ ውጭ እያስገደደና እያሰቃየ በማሳመን የሚያገኘው የእምነት ቃል ሳያውቀውና ሳይገነዘበው ቀስ በቀስ እራሱ ህግ አልባ ለመሆኑ የእምነት ቃል መስጠቱን ይመሰክርበታል፡፡
“ጤናማ ሰው ሌሎቹን አያሰቃይም- በአጠቃላይ ሲሰቃዩ የነበሩ ወደ አሰቃይነት ይቀየራሉ፡፡” ካርል ጁንግ