የሱዛን ራይስ ሸፍጥ በቤንጋዚው ጥቃት ላይ!

ከፕሮፌሰር  ዓለማየሁ  ገብረማርያም

ትርጉም  ከነጻነት ለሃገሬ

በሴፕቴምበር 2 2012 የአሜሪካዋ አምባሳደር በተባበሩት መንግስታት: ሱዛን ራይስ በኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የቀብር ስርአት ላይ ስሜታዊ ሆና የሚያቅለሸልሽ ቃላት ያዘለ ንግግር አነብንባ ነበር፡፡ መለስን፤ ‹‹የማይደክምና ራሱን የማይወድ››በአጠቃላይ እሱነቱ ለስራውና ለቤተሰቡ የሆነ ብላዋለች፡፡ ‹‹ጠንካራ፤ በእምነቱ የጸና እና በእርግጥም ለጂሎችና ለደደቦች  እሱ እንደሚጠራቸው ትእግስቱ ትንሽ ነበር፡፡ ሱዛን ራይስ ይህን ቅጥ ያጣና ከአንድ አሜሪካን ከሚያህል ሃገር ወኪል ጨርሶ ሊሰማ የማይገባ ያልተገራ ንግግር ስታደርግ ጅልና ደደብ የሚለውን ቃል በድፍረትና በአጥንኦት የለጠፈችው በኢትዮጵያዊያን ነጻ ጋዜጠኞች፤የተቃዋሚ መሪዎች፤ተሟጋቾች፤የፖለቲካ እስረኞች፤የሲቪል ማሕበረ ሰብ መሪዎች፤እና የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ላይ ነው፡፡ የንግግሯን ቪዲዮ በመመልከት  ሴትዮዋ ይህን ንግግር የመለስን ተቃዋሚዎች በመጨረሻ ጡጫ  ደረታቸዉን ብላ ለመለስ የአስከሬን መሸኛ አድርጋ ማቅረቧ እንደነበር ያስታውቃል፡፡

‹‹ አንድ አይነት ላባ ያላቸው ወፎች አብረው ይከንፋሉ›› ይባባል፡፡ ራይስ እንደ መለስ ሁሉ ተቃዋሚዎቿንና ሃሳቧን የማይጋሯትን ትሳደባለች ታንቋሽሻለች፡፡ በስቴት ዲፓርትመንት አካባቢ የሚያውቋት በዘለፋ በቁጣና በማስፈራራት አነጋገራዎ ነው፡፡ በዚህም አጉል ደንፊ ተብላ ትታወቃለች፡፡ አለያም በጣም በሚያውቋት ዘንድ ‹‹የቻይና መደብር በሬ›› (አተራማሽ ወይም በጥባጭ ማለት ነው) ይሏታል፡፡ በስብሰባዎች ላይ በቃላት ርችት፤በአፈነበልባል፤በጣት ቀሳሪነት ራይስ ትታወቃለች፡፡ በአንድ ወቅት በአሜሪካን ዲፕሎማቶች ዋና ታዋቂ በነበሩት ሪቻርድ ሆል ብሩክ ላይ የበላዮች ስቴት ዲፓርትመንት አባላት ስብሰባ ላይ በአሜሪካንና በሌላውም ዓለም በሳቸው ደረጃ ካሉ ሰዎች የማይጠበቀውንና ጸያፍ ተብሎ የሚጠራውን ድርጊት በአደባባይ የመሃል ጣታቸውን ቀስረውባቸዋል ይባላል፡፡

በማርች 2012 የፈረንሳዩ የተባበሩት መንግስታት አምባሳደር ለራይስ እንደምክር የአውሮፓ ዩኒየን አሜሪካ ደገፈም አልደገፈም የበረራ ክልከላ ዞን ከተባበሩት መንግስታት የደህንነት ካውንስል ይፈልጋል በማለት ላቀረቡላት ሃሳብ ራይስ ለአምባሳደሩ ወሽመጥ በሚቆርጥ አነጋገር ‹‹መቼም ወደ አዛባ ጦርነታችሁ እንደማትጎትቱን አምናለሁ›› በማለት ከያዘችው ስልጣንና ከፈረንሳይ አቻዋ ጋር ሊደረግ በማይገባ የጋጠ ወጥ አባባል መልሳላቸዋል፡፡ በኋላ ግን ይህ ያጥላላችው ሃሳብ አመርቂ ውጤት በማስገኘቱ የሃሰቡ አፍላቂ በመምሰል ምስጋናውን ጠቅላ ለራሷ ለማድረግ በመዘየድ ‹‹ከማሰብና ከማቀድ ባለፈ የበረራ ክልከላውን ዞን በማጠናከር ልናተኩርበትና ልንተገብረውም አስፈላጊነቱ ወሳኝ ነው፡፡ የምድሩ ፍልሚያ ብዙም ስላላዋጣና ሲቪል ማህበረሰቡንም ከአደጋው ለመጠበቅ አዋጪው ይሄው ነውና›› በማለት ቀድማ ያጣጣለችውንና የፈረንሳዩን አቻዋን የሰደበችበትን ሃሳብ መልሳ በራሷ አፍላቂነት የተገኘ ለማስመሰል ጥራበታለች፡፡ ባለፈው ጁላይ ቻይናና ሩስያ ስለዓየር ለውጥ የቀረበውን ሂደት በተቃወሙበት ወቅት ራይስ ጉደኛዋ እዚህም ላይ ‹‹እርባና ቢስ›› ‹‹ሃሳበ ቢስ›› በማለት በማጣጣል ‹‹ የተግባር ውድቀት›› በማለት ኮንናቸዋለች፡፡

ያ እንግዲህ ያ ነበር፡፡ባለፈው ሳምንት በቤንጋዚ ሊቢያ ውስጥ በሴፕቴምበር 11 የ አራት አሜሪካውያንን ሕይወት የቀጠፈውን በአሜሪካን ኮንሱሌት የደረሰውን ፍንዳታ አስመልክቶ ራይስ በሰጠችው ዘገባ የተነሳ የሪፓብሊካን ሴኔተሮች ጆን ማኬይንና ሊንድሲ ግራሃም ሱዛን ራይስን ጅል ደደብ ስራዋን የማታዉቅ ናት የሚል ሃያል አስተያየታቸውን ሰንዝረውባታል፡፡ ራይስ ከፍንዳታው አምስት ቀናት በኋላ በአምስት የተሌቪዝን ዜና ፕሮግራሞች ላይ ቀርባ፤ “በኮንስሌቱ ላይ የደረሰው ፍንዳታ ግብታዊ፤ በእቅድ ያልተደረገ፤ ነው:: በካይሮ በተነሳሳው ተቃውሞ ላይ የተመሰረተና ዋናው አነሳሽም አጸያፊውና አሳዛኝ የሆነው የእስላምን እምነት የሚያንቁያሽሽ የቪዲዮ ዝግጅት ያስከተለው ነው” በማለት ገለጠች፡፡ እንደ ራይስ አባባል፤በጥቂት ሰዎች ስብስብ ወደ ኤምባሲው የሄደው የተቃውሞ ትዕይንት በድንገት በተጠናከረ መሳርያ በታጠቁ አክራሪ ስብስቦች ‹‹ተጠልፎ›› ነው አደጋው የተፈጸመው ብላ ነበር፡፡

‹‹ሴኔተር ማኬይን ለ‹‹ጅሎችና ለደደቦች ትዕግስታቸው ማለቁን›› እና ለራይስ ተረት ተረት ጨዋታ ቁጣቸው ገንፍሎ ራይስ የውጭ ጉዳይ  ዋና አስተዳደሪ ሆና ስሟ ለምርጫ ቢቀርብ ተቃውሟቸው የከረረ እንደሚሆንና ለማሳገድም እንደሚጥሩ አስጠንቅቀው ነበር፡፡ ‹‹ሱዛን ራይስ ቀድማ ልታውቅ ይገባት ነበር፡፡ ሳታውቅ ከቀረች ደግሞ ለቦታው ጨርሶ አትመጥንም፡፡ አንድ ያረጋገጠችው ጉዳይ ቢኖር፤ ወይ አይገባትም ደድባለች አለያም፤ ያገጠጠውን ሃቅ መቀበል ቸግሯታል” ብለው በሃይል ቃል ተናግረዋል፡፡ ይህ የጥቃት ድርጊት ከአምስት ቀን በኋላ በእውነታነት የተረጋገጠው ነገር ነበር፡፡ለነገሩ የራይስ የቤንጋዚ ታሪክ የቀድሞው መለስ ዜናዊ የመኝታ ሰአት ተረት ተረት ቅሪትን ያስታዉሳል፡፡››

ሃቅ በገሃድ ይውጣ::  በቤንጋዚ የአሜሪካን ኮንሱሌት ላይ የደረሰው ጥቃት የሽብርተኞች መሆኑን ማወቅ የተሳነው አለያም መገመት ያቃተው ‹‹ጅል››ና ‹‹ደደብ›› ብቻ ነው፡፡ የሲ አይ ኤ ዋና ሹም የነበሩት ፔትራዩስ፤ በቅርቡ በሰጡት መግለጫ መሰረት፤ ፍንዳታው መፈጸሙን እነደሰሙ ድርጊቱ የሽብርተኛች መሆኑን ወዲው ማወቃቸውንና ማረጋገጣቸውን ይፋ አድርገዋል፡፡ ይህን መግለጫ ለሁዋይት ሃውስ የመነጋገርያ ነጥብ  እንዲሆን ቢያቀርቡትም ከራይስ ንግግር ላይ አልገባም ነበር:: ለነገሩ ግራ የሚያጋባው ጉዳዩ በአግባቡ የሚያገባቸውና መግለጫውንም ሊሰጡ የሚገባቸው ዋና አስተዳዳሪዋ ሂላሪ ክሊንተን ሆነው ሳለ፤በምን ሰበብ ራይስ ጥልቅ እንዳለች ግልጽ አይደለም፡፡ ለምን ሂላሪ መግለጫውን አልሰጡም፤ወይስ ሁዋይት ሃውስ ሂላሪን ለማዳን ሲል ራይስን አውቶቡስ ጎማ ስር እንደታኮ አስቀመጣት? ወይስ ራይስ እውነት የሚመስል ቅጥፈትና የፖለቲካ ሽፋን ለመስጠት ነበር የሽብርተኞች ድርጊት አይደለም ያለችው? ካልሆነስ፤ ምናልባት በቤንጋዚው ስለታማ ጉዳይ

ላይ ወድቃ አስፈላጊውን እርምጃ በወቅቱና ባስቸኳይ ባለመወሰዱ ያደረሰውን ጉዳት መከላከያ ለማቅረብ የሞከረችህው? ወይስ በቤንጋዚ ለተፈጸመው እኩይ ተግባር ራይስ መሳርያ በመሆን ወደ፤ የሃገር አስተዳዳሪነቱን ሹመት ለማግኘትበቀላማጅነት መቅረቧ ነው፡፡ ወይስ ሁዋይት ሃውስ የራይስን የእውቀት ደረጃ፤ ጥንካሬ፤ያላትን አይደፈሬነትማስመሰልና የተፈጠረውን ክፍተት ለማጥበብ ሲባል ለሹመቱ ያላትን ብቃት ለማረጋገጥ የተፈጸመ ነው?

ፕሬዜዳንት ኦባማ የሪፓብሊካን ራይስ አቀንቃኞች ላይ ጎራዴአቸዉን መዘው ነበር የወጡት፡፡ ማኬይንንና እና ግራሃምን ኦባማ ሲናገርዋቸው ‹‹ሪፓብሊካኖችናወዳጆቻቸው ሰው ማጥቃት ካሰቡ እኔን ማጥቃት ይችላሉ፡፡ ግን በአንዲት የሃገሪቱን የተባበሩት መንግስታትአምባሳደር ላይ መነሳሳት? በቤንጋዚ ጉዳይ በማያገባት ላይ? እና ከደህንነት ክፍሉ ያገኘችውን መግለጫ መሰረትአድርጋ በመናገሯ? ስሟንና ተግባሯን ማጥላላትና ማንቋሸሽ አሳዘኝ ተግባር ነው፡፡››  ይሄ እንግዲህ ‹‹የኦባማ ድራማ ›› በሚባለው አይነት የተቀነባበረ ትእይንት ድራማ ነበር፡፡

ለሕሊና የሚከብደውና አሳፋሪ ነገር ግን ይህን የመሰለውን ቅጥ አምባሩ የጠፋ የቤንጋዚ የጥቃት ታሪክ ራይስ አምና ለአለም ማስተጋባቷ ነው፡፡ራይስ እኮ እንደብዙዎቻችን ዝም ብላ አይደለችም፡፡ የስታንፈርድ እና የኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲዎች ተመራቂ፤የሮድስ ስኮላር፤ በናሽናል ሴኪዩሪቲ ኤጀንሲ ከፍተኛ ቦታ ላይ የነበረች፤ በክሊንተን አስተዳደር ወቅት የሃገር አስተዳደር የአፍሪካ ጉዳይ ምክትል ጸሃፊ የነበረች ከፍ ያለች ባለስልጣን እኮ ናት፡፡ በሃገር የውጭ ግንኙነት የበርካታ ዓመታትልምድ ያላት ሰው ናት፡፡ያም ሆኖ አደጋው ከተፈጸመ ከአምስት ቀናት በኋላ ራይስ ከአንዱ ቴሌቪዥን ፕሮግራም ወደ ሌላው እየከነፈች፤ ለአሜሪካን ሕዝብ የቤንጋዚው ፍንዳት የአስሸባሪዎች (ቴሬሪስቶች) ጥቃት አይደለም በማለት ታስተጋባ ጀመር፡፡ ታዲያ ይሄ የአውቆ ደደብነት ነው ወይስ የጅል መልካም አስተሳብ? ፍንዳታው በሴፕቴምበር 11 መፈጸሙ፤ጥቃቱን የፈጸሙት መታወቂያቸው የሆነውን (ራይስ እንደአለችው) የሽብር መፈጸሚያቸውን ‹‹ከባድ መሳርያዎች›› የተተቀሙ፤ ……..በመኪና ላይ የተደገነ መትረየስ፤ ኤኬ-47ቶች (ካላሽ)፤ አርፒጂዎች የእጅ ቦምቦች፤ ሞርታሮች፤ ይሄ ሁሉ የጥፋት ቁሳቁስ ለራይስ ምንም ነገር መስሎ አልታያትም፡፡ ከጋዳፊ ከስልጣን መወገድ ቀደም ብሎ፤ብዙ ዓይነት ሚሊሺያዎች አመጸኞች፤ በርካታ የሽብር ድርጅቶች (ሴሎች) በቤንጋዚ መኖራቸው ለራይስ የሽብር ጥቀቱን ሊያመጣ እንደሚችል ሊያስገምታት አልቻለም:: ጋዳፊ ሊቢያን ለብዙ ዓመታት ለሽብርተኞች ሃገራዊ እርዳታ ለጋሽ አድርጓት እንደነበር ለራይስ ምንም አይነት ታሪካዊ እንድምታ ሊያስገነዝባት አልቻለም፡፡ በቀላሉ አነጋገር ለራይስ ጉዳዩ እንደ ወፍ መስሎ እንደ ወፍ ተራምዶ ቢታያትም እሷ ግን ግመል ነው ብላ ደመደመች፡፡

የእሽቅድድሙ አባሎችና የሩጫው አራጋቢዎች የራይስን የችሎታ ማነስ ሊያስተባብሉ ከያሉበት ተጠራርተው የጦር ልብሳቸውን ተላብሰው ተሰባሰቡ፡፡ የዴሞክራት ምከር ቤት መሪ ጂም ክላይበርን የመጀመርያው ተከላካይ ነበር፡፡‹‹አያችሁ እነዚህ እኮ የሚስጥር አነጋገር ቃላቶች ናቸው፡፡ እኛ እነዚህን አባባሎች በተለይም እኛ በደቡብ  ተወልደን ያደግነው፤ህይወታችንን ሙሉ እነዚህን ቃላት (የስራ ችሎታ የላቸዉም) ስነባል ስንሰደብ ነው የኖርነው:: ሱዛን ራይስ ከማንም የማታንስ አዋቂ ናት:›› ብለው ተናገሩ::  ሌሎች ዴሞክራቶችም ጉዳዩን ‹‹የጾታና የዘር›› አድርገው መኮነን ጀመሩ፡፡ ምን አይነት እሳቤ ማጣት ነው?  ሆኖም: ራይስን ‹‹ችሎታ ቢስ ማለት?›› ስም  ማጥፋት አይደለም:: እውነት ነው እንጂ::

ጥረቱ ማኬይንንና ግራሃምን ለማዋረድ ተብሎ የተቃጣና የራይስን ችሎታ ቢስነት ለማድበስበስ ተብሎ የታቀደ ነው፡፡ መልክቱ ለሪፕቡሊካኖች ግልጥ ነው። ፕሬዝደንት ኦባማ ራይስን ዉጭ ጉዳይ መሪ እንድትሆን ይፈለጋሉ። ተቃዋሚ ረፑብሊካኖች ከወጡ እንደ ዘርኛና ሴቶችን እንደሚጠሉ ሆነው በብዙሃን ይቀርባሉ። ራይስ ቩመቱን ታገኛለች፥ ረፑብሊካንስ ይከሽፋሉ የሚል ዝየዳ ነው ደሞክራቶች የያዙት። ሊሰራላችው ይችላል።

ዕውነቱ ግን ራይስ የትም ቢጓዙ የማትገኝ ችሎታ ቢስ ፍጡር ናት፡፡ የአንድ ታላቅ ሃገር ብቃት ያለው ዲፕሎማት ለመሆን መሰረታዊ የሞራል ብቃት ዋነኛ ተፈላጊው ጉዳይ ነው፡፡ራይስ ሃቁን ከውሸቱ ለይታ ለማወቅ የሞራል የፍርድ ሚዛን የጎደላት በመሆኗ ብቻ ሳይሆን፤ ሁለት ውሸቶችን ለመለየትም ቢሆን ችሎታው እጅጉን ይጎድላታል፡፡ በማርች 2012፤ ራይስ በጭፍኗ  ኢራንን፤ ሰሜን ኮርያን፤ሲሪያን ስለሚያካሂዱት የሰብአዊ መብት ጥሰት እስከመጨረሻ ድረስ ኮነነቻቸው፡፡ በሴፕቴምበር 2, 2012 በአሁኑ የአፍሪካ ታሪክ ተወዳዳሪ የማይገኝለት ፈላጭ ቆራጭ በሆነው መሪ ቀብር ላይ ተገኝታ በሙገሳ መላክ የሚያስመስል የተካበ ንግግሯን አሰማች፡፡ ራይስ የመለስን የሕይወት ታሪክ ከማቅረቧ አስራ ሁለት ቀናት ቀደም ብሎ፤ሁመን ራይትስ ዎች የተባለው ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ጠባቂ ድርጅት‹‹በኢትዮጵያ የሲቪልና የፖለቲካ መብት ሂደት እያሽቆለቆለ በመሄድ ላይ ነው፡፡ ሃሳብን በነጻ መግለጽ፤በማህበርመደራጀት፤ መሰብሰብ፤ ሁሉ እገዳ እየተደረገባቸው ነው፡፡ ገዢው ፓርቲ የጉልበት ስልጣኑን በመቆጣጠር፤ የፍትሕ አካላትን ፤የመገናኛ ብዙሃንን ነጻነት ለሕግ የበላይነት በእጅጉ አስፈላጊ የሆኑትን በመቆጣጠር በደል መፈጸሙእየባሰበት ነው›› በማለት መግለጫ አውቷል፡፡

ብቃት ያለው ዲፕሎማት ስለወታደራዊ ተቋም በቂ እውቀት ሊኖረው ይገባል፡፡ በውጭ ጉዳይ ተግባር ላይ በቂ ልምድና ትምህርት ቢኖራትም: ራይስ የስልጣን መጨበጫውን መንገድ በጭፍን የፖለቲካ ምኞቷ ሸቅጣዋለች፡፡ ዕውነትን ከመቀላመድ ለመለየት ችሎታ ያነሳት ትመስላለች፡፡ ራይስ የራሷን የፖለቲካ ምኞት እስካሳካላት ድረስ አውነት ይሁን ሃሰትጉዳይዋ አይደለምና ምንም ነገር ከማለት ወደኋላ አትልም፡፡ ሴኔተር ማኬይን እንደታዘቡትና እንዳሰቀመጡት ‹‹ሴትዮዋ ወይም ምንም አይገባትም፤ አለያም ማስረጃን ከነማስረጃው ሲቀርብ መቀበል አትፈቅድም›› ብለዋል:: ከዚያም አልፎእንደ አንድ በሷ ደረጃ ያለ ከፍተኛ ሕዝባዊ ባለስልጣን በሕዝብ ፊት ቀርቦ ያገጠጠ ውሸትን ከማቅረብ በፊት እውነቱንና ሃሰቱን አጥርቶ ማወቅ ይጠበቅበታል፡፡

ብቃት ያለው ዲፕሎማት፤የሷን/የሱን የፖለቲካ ምኞት ከሱ/ከሷ ብሔራዊ ግዳጅ ጋር ማዛመድ ጠበቅበታል፡፡ የራሷንየፖለቲካ ምኞትና ጠቀሜታ ለፓርቲዋ መገልገያ አድርጋ በማስቀደም፤ ብሔራዊ ሃላፊነቷን ስለምትተወው ራይስ ችሎታ ይጎድላታል ብሔራዊ ተአመኒነትም የላትም፡፡ ራይስ የፖለቲካ ጥቅም እና ጥቅም አሳዳጅነት፤ ከምንም በላይቅድሚያ የምትሰጣቸው መመሪያዎቿ ናቸው፡፡ በጭፍኗ የፓርቲዋን መስመር በመከተል ምንም አይነት ፖሊሲ ቢሆን ያለምንም ዓላማና ግንዛቤ  የምታራምድ ናት፡፡ የራሷን የፖለቲካ ምኞት እስካሳካለት ድረስ ምንም ይሁን ምንም የአለምንም ይሉኝታ ተግባራዊ ከማድረግ የማትመለስ፤የሞራል ግዴታዋን ጠቅልላ የጣለች አደራ በላ ናት፡፡ በአጭሩ የፓርቲ አናፋሽ ሆና የራሷን የፖለቲካ ምኞት ብቻ ለማሳካት የምትኖር ግለ ሰብ ናት፡፡

ብቃት ያለው ዲፕሎማት የችሎታ ጥንካሬ ሊኖረው ግድ ነው፡፡ የችሎታ ጥንካሬና ሃለፊነት ስለሚጎላት ራይስ ችሎታ ያንሳታል፡፡ በ2006 ባቀረበችው ምሁራዊ ጽሁፏ፤ ራይስ ማሊ እንደ መልካም አስተዳደር ያላት ሃገር በችሎታ ማነስ የምትሰቃይ ሃገርና አክራሪዎች ሲመዘብሯት የኖረች ሀጋር ናት በማለት ጽፋ ነበር፡፡ ማሊ በጸረሽብርተኝነት ከአሜሪካ መንግስት ጋር የጠበቀ ትስስር ያላት ናት፡፡ በኤፕሪል 2012 አክራሪ የሙስሊም አፈንጋጮች ሰሜናዊ ማሊን በመያዝ ሃገሪቱን ለሁለት በከፈሉበት ወቅት ግን፤ራይስ ያደረሰችው ዕርዳታ ‹‹በማሊ ያሉት ፓርቲዎች ሁሉ አግባብነት ባለው የፖለቲካ ውይይት ሰላማዊ ኑሮን ሊቀጥሉ ይገባል›› የሚል የቃላት ድርደራ ብቻ ነበር፡፡ ያቺ‹‹የመልካም አስተዳደር›› ሃገር የነበረች ማሊ የተከፋፈለችና ለመከራ የተዳረገች፤ የሽብርተኞች መናሃርያ ስትሆን በትንሹ ለአራት ዓመታት ራይስ ቃላት ከመደርደር ባሻገር እርምጃውን መራመድ ግን አልቻለችም፡፡

ብቃት ያለው ዲፕሎማት በቃላት አጠቃቀሙና በምግባሩ ሁሉ የታረመ ሊሆን ተገቢ ነው፡፡ የዲፕሎማቲክ አስተሳሰብ ስለሚጎድላት፤ዘወትር ነገር ጫሪ ሆና ስለምትገኝ፤ አብረዋት ለሚሰሩትና ለሌሎች ዲፕሎማቶች አክብሮት ስለሌላት፤ጉረኛና ደንፊ በመሆኗ ራይስ የችሎታ ማነስ ችግር አለባትና ብቃት የላትም፡፡ ሱዛን ራይስን ‹‹ጅል››አለያም ‹‹ግሳንግስ››ብዬ ዝቅ ለማለት አልፈልግም፡፡ ለነገሩ፤ ሁለቱንም እንዳይደለች አምናለሁ:: ይልቁንስ፤የራሷን የፖለቲካ ምኞት ለማሳክት ስትል እሷነቷን ለሽያጭ የምታቀርብ፤ አስሊ፤ሸፍጠኛ፤ተንኮለኛ፤ሰሪ፤ ሃሳብ ሰላቢ፤ራስ ወዳድ፤ የሆነች ፖለቲከኛ ናት፡፡ ሃሰትን ለመሸፋፈን በሚደረግ ሴራ ውስጥ ፈቃደኛ ሽፋን ሆና የምታገለግል እኩይ ባህሪ ያላት ናት፡፡ በዚህም በመሸፋፈን ተግባሯ  ስለሽብርተኞቹ ሁኔታ በማለባበስ በድርጊቱ ሕይወታቸው ያለፉትን አራት አሜሪካዊያን አርበኞች የግድያ መንስኤ ምንነት አሳንሳ አቅርባ የአሜሪካንንና የዓለምን ሕብረተሰብ ለማታለል ከንቱ ጥረት አሳየች፡፡

‹‹ውዳቂ እንደውዳቂው ሁኔታ ነው›› እንደሚባለው ‹‹የችሎታ ማነስም እንደችሎታው አናሳነት ነው››፡፡ ፕሬዜዳንትኦባማ ራይስ ክሊንተንን እንድትተካ አይመርጧትም የሚል ተስፋ አለኝ፡፡ ከመረጧትም ከባድና ትልቅ  ሼክስፒራዊ  ችግር ይገጥማታል፡፡ (የሃገር አስተዳደር) ‹‹መሆን ወይም አለመሆን›› ያ ነው ጥያቄው፡፡‹‹ከሕሊና ጭንቀት መላቀቅ ያ ነው ክብር የሞላው›› (ለቀላመደቻቸው እብለቶች ሁሉ) ላልታሰበው ሽንቆጣና ቀስቶች ፍላጻ ላልታሰበው መጻኢ እድል ውሳኔ (በሴኔቱ ዘንድ ለሚደረገው እሰጥ አገባ) አለያም በባሀሩ ላይ ላለው ሞገድ መሳርያ መምዘዝ፤ (ዕውነትን በመናገርን ጸህናን ማስመስከር) ራይስ በምርጫው ቀንቷት ወደ ሴኔት ውሳኔ ከደረሰች፤እውነተኛ እሷነቷ፤ እውነትን ለፖለቲካ መጠቀሚያነትና የራሷን ምኞት ለማሳካት ስትል የምትዳክር ሃቅ አልባ መሆኗ ይጋለጣል፡፡ በ1994 የክሊንተን አስተዳደር በሩዋንዳ በመካሄድ ላይ የነበረውን እልቂትና የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋ እንደማያውቅ አስመስሎ በቸልታ ሊያልፈው ሲሞክር የሞቱ ቁጥር በሺዎች እየጨመረ ሄዶ ጭፍጨፋውንና የዘር እልቂቱን ለማቆም አፋጣኝ እርምጃ በመውሰድ ሕወት ማትረፍሲቻል፤የራሷን ስልጣን ላለማጣትና የሷንና የመሰል የፓርቲ ባለስልጣናትን ስምና ሁኔታ ለመጠበቅ ስትል ብቻ ሰው አስጨረሰች፡፡  ስትናገርም “የዘር ማጥፋት የሚለውን ቃል የተጠቀምን እንደሆነና ምንም ሳናደርግ ብንቀር፤ የኖቬምበሩ የምክር ብት ምርጫ ምን ሊያጋጥው ይችላል?”  አለች:: የሱዛን ራይስ ችሎታ ይህ እውንታዊ ምስክር ነው::

አሁንም: ራይስ በቤንጋዚ የተፈጸመውን ድርጊት ሽብር ብላ ለመጥራት ያስፈራትና ያሳሰባት በኖቬምበር በሚካሄደው ፕሬዜዳንታዊ ምርጫ ላይ ሊያስከትል የሚችለው ችግር አስጨንቋት ነውን?

እመት: ሱዛን ራይስ ሆይ! ‹‹ጅሉስ›› ማነው? ‹‹ደደቡስ›› ማነው አሁን?

የተቶረገመው ጽሁፍ (translated from):

http://open.salon.com/blog/almariam/2012/11/24/the_tall_tale_of_susan_rice

ካሁን በፊት የቀረቡ የጸሃፊው ጦማሮችን  ለማግኘት እዚህ ይጫኑ::

http://www.ecadforum.com/Amharic/archives/category/al-mariam-amharic

http://ethioforum.org/?cat=24

Similar Posts

Leave a Reply