የኢትዮጵያዋ፡ ርእዮት ‹‹የጥንካሬዬ ዋጋ››

ከፕሮፌሰር  ዓለማየሁ  ገብረማርያም

ትርጉም  ከነጻነት ለሃገሬ

 

 

 

 

 

 

ስለስልጣን ብልግና አለያም ስለ ስልጣንን በማንአለብኘነት አለ አግባብ ስለ ከመጠቀም ከመናገር ይበልጥ አስቸጋሪ የሆኑ bezu ነገሮች yelum፡፡ ለ31 ዓመቷ ወጣት ኢትዮጵያዊት አይበገሬ ርዕዮት ዓለሙ ግን፤ የመጻፍ ነጻነት፤ የመናገር ነጻነት፤ ሃሳብን በነጻ የማንሸራሸር ነጻነትን ድምጻቸው በመሳርያና በስለላ መዋቅር ለታፈነባቸው ድምጽ ከመሆን ምንም አይነት ጋሬጣ ቢደረደር ሊያደናቅፋት ጨርሶ አይችልም፡፡  አሁንም ቢሆን ባለችበት ክፉ ሁኔታም ሆና ስለግፍ ስልጣን ቁልጭ ያለ ሃቅን ትናገራለች፤ ‹‹ለጥንካሬዬ ዋጋ እንደምከፍል ብገነዘብም የሚቃጣብኝን ለመቋቋም ዝግጁ ነኝ››፡በማለት ካለችበት ገሃነማዊ የቃሊቲ ጉረኖ ባመለጠው የእጅ ጽሁፏ መልእክቷን  ለአለም አስተላልፋለች፡፡

“ጥንካሬ ለሁሉም ድርጊት ታላቅ ዋጋ አለው፡፡ ጥንካሬ ከሌለ ማንኛውንም አይነት ዋጋ ያለው ተግባር ማከናወንም ሆነ ማቀድ አይቻልም” ያለችው ታላቋ የአሜሪካ የሰብአዊ መብት ተሟጋችና ጸሃፊ ማያ አንጀሉ ናት፡፡ ባለፈው ሳምንት የዓለም አቀፉ ሜዲያ ፋውንዴሽን (IWMF) የ2012ን  ታላቁን “የጋዜጠኝነት ጀግንነት” ሽልማቱን  ለአይበገሬዋ ርዕዮት ዓለሙ ሸልሟል፡፡ ባለፈው ሜይ ርዕዮትን ወደ ወህኒ ለመወርወርና ዝም ለማሰኘት ስለተከናወነው ሂደት ጽፌ ነበር፡፡

ለዚያ ማፈርያ ፍርድ ቤት ማስረጃ ተብሎም በርዕዮት ላይ የቀረበው ሰነድ፤ከሌሎች የሙያ ባልደረቦች ጋር በህገወጥነት የተሰበሰበ የኢሜይል ልውውጥ፤በስለላ መዋቅሩ የተጠለፈ የቴሌፎን ንግግር፤ሲሆን ከሁሉም ጋር ያደረገችው ልውውጥ ግን ሰላማዊ ትግልና ለማጠናከር ሊደረግ የሚገባውን የሚያመላክት ብቻ ነበር፡፡ ርዕዮት በፍትሕ ጋዜጣና በኢትዮጵያን ሪቪዩ ድህረገጽ ላይ ያወጣችው ጽሁፍም በማስረጃነት ቀርቧል፡፡ ከፍርድ ቤት መቅረብ አስቀድሞ ርዕዮትና ውብሸት ታዬ (የአውራምባ ጋዜጣ አዘጋጅ) ከጠበቃ ጋር የመገናኘት መብታቸው ታግዶባቸው ነበርና ጠበቃ ማነጋገር አልቻሉም፡፡ ቃለ መጠይቅም የሚባለው ስርአት ያጣ ሂደትም በሚካሄድበት ወቅት የጠበቃቸው ውክልና መብት እንደታገደ ነበር፡፡ በምርመራ ወቅት የደረሰባቸውን ወከባና ስቃይ፤ የህክምና መከልከልን አቤቱታቸውን፤ ያ አሳፋሪ ፍርድ ቤት ለመስማት እንኳ ፈቃደኛ አልነበረም፡፡

ዛሬ ግን ርዕዮት ይህን ታላቅ እውቅናና ሽልማት ስትሰጥ ለማየት በመብቃቴ እጅጉን እኮራለሁ፡፡ በ2007ም ይህንኑ ሽልማት ሰርክዓለም ፋሲል ስትሞሸርበት ደስታዬ ወሰን አልነበረውም፡፡ ወጣት ኢትዮጵያዊያን ጀግኖች እጅጉን አስከፊ በሆነ ገዢ ባለስልጣን መንግስት ላይ እውነትን በመናገርና የሕዝብን ጥቅም ለማስጠበቅ ቆርጠው በመነሳታቸው ሰበብ  ለእስርና ለግፍ ስቃይ የተዳረጉት ዓለም አቀፍ እውቅና፤ ክብርና ሞገስ ሲቸራቸው ከማየት የበለጠ ምን የሚያስደስት ነገርአለና!?

ርዕዮትና ሰርክዓለምን ለዚህ ክብር ያበቃቸው “ጥንካሬያቸው” ምነድን ነው? ጥንካሬ በተለያየ መልኩ ይከሰታል፡፡ እራሱን ለመስዋእትነት ለማሳለፍ ቆርጦ በጦር ግንባር የተሰለፈ ተዋጊ አደጋው ከፊትለፊቱ እንዳለ ቢያውቅም በጥንካሬው ይጋፈጠዋል፡፡ ወጣት የሆነች ሴት ‹‹ጭቆናና ድምጻቸው የታፈነባቸው ምትክ ለመሆንና ጩኸታቸውን ለመጮህ፤ እሮሯቸውን ለማሰማት፤ ለሕዝብ በመወገን፤ አቆማለሁ›› ለማለት መቁረጥ የሚጠይቀውን ዋጋም ለመክፈል ቆርጦ መነሳት ጥንካሬን ያሳያል፡፡ “ጥንካሬ” በራሱ ግን ምንድን ነው? ታላቁ ፈላስፋ እንደሚለው ‹‹ጥንካሬ  በውስጥ በህሊናችን በመንፈሳችን የሚገኝ ግፊት ነው፡፡ በመረረው አደጋ ውስጥ እንድንጋፈጠውና ገትረን እንድንቋቋመው ያስችለናል፡፡›› ሌሎች እንደሚሉት ደግሞ ጥንካሬ በፍርሃትና በጅልነት መሃል የሚገኝ ነው፡፡ ምናልባትም ጥንካሬ ሌሎችንም ዋጋዎችን ቆራጥነትን፤የዓላማ ጽናትን፤ፈቃደኝነትን፤ትእግስትን፤አሳቢነትን አመኔታን ያካተተ፤ ሊሆን ይችላል፡፡ ጥንካሬን ዓላማቸው ያደረጉ ርዕዮትና ሌሎችም መስሎቿ  በግል ለሚደርስባቸው ችግር፤መከራ ስቃይ ወይም እስርና እንግልት ጨርሶ አያስቡም አያስፈራቸውም፡፡ ስለዚህም እንደ ርዕዮትና ሰርክ ዓለም ያሉ ጠንካሮች እህቶችና እስክንድር ነጋንና ውብሸት ታዬን የመሰሉ ቆራጦች ስላሉን በእጅጉ ልንኮራ ይገባናል፡፡ እንደ ሰብአዊ ፍጡር  ከፍተኛውን የጥናካሬ ደረጃ ያመላከቱንን ኢትዮጵያዊያን ጋዜጠኞች በእስር በመማቀቅ ላይ ቢሆኑም መከራና ችግሩ፤ ግፉና ጭካኔው ግን ጨርሶ ከዓላማቸው ዝንፍ ጥንካሬያቸውንም ሸብረክ አላደረገውም፡፡

በኦክቶበር 24/2012 በሽልማቱ ስነ ስርአት ላይ የተነበበው የርዕዮት የእጅ ጽሁፍ መልእክት ለመጪው ትውልድ የጥንካሬ ማረጋገጫ ነው፡፡የታሪክ ነጻነት፤የፕሬስ ነጻነት፤በኢትዮጵያ በሚጻፍበት ጊዜ መጪው ትውልድ ይህን የርዕዮትንና ሌሎችንም እውነታዊ መልዕክቶች ያነባል፡፡ ጊዜያዊ ግፈኛ ገዢዎች  ሕዝቡን ለስቃይና ሚዛን ላጣው ግፍ በዳረገበት መራር ወቅት ርዕዮትና መሰሎቿ ሃሰትን በማጋለጥና ለግፍ እምቢታን በመምረጣቸው ለእስራት ቢበቁም ቀኑ ሲመጣ ግን በድርጊታቸው የሚኮሩ ይሆናሉ፡፡ ከዓላማዋ ሳታፈገፍግ፤ በዓለም ካሉት ወህኒዎች ሁሉ ያዘቀጠና ግፍ የበዛበት ቦታ ሆና( ወህኒው በኢትዮጵያ የገዢው መንግስት በከፍተኛ ገንዘብ የቀጠረው ኤክስፐርት እንደገለጸው) ለዓላማዋ በመቆም፤ በተራ መጻፊያና በብጭቅጫቂ ወረቀት ላይ በማቃሰት ላይ ያለውን አምባገነን መንግሥት ከወህኒ ቤት ሆና እየሞገተችውናእየሞጨረች እየተዋጋች ነው፡፡

በኢትዮጵያችን የተሻለ ሁኔታ እንዲመጣ ለማገዝ የበኩሌን አስተዋጽኦ ማድረግ አለብኝ፡፡ በርካታ ፍትሕ አልባነት፤ጭቆናዎች፤በኢትዮጵያ ውስጥ በየቀኑ በየሰአቱ በየደቂቃው በመፈጸም ላይ ናቸውና በጽሁፌ እንዚህን ሁኔታዎች እያነሳሁና እያጋለጥኩ መኮነን ይኖርብኛል፡፡ ንጹሃን ነጻነትንና ዴሞክራሲን ለመጠየቅ ባዶ እጃቸውን አለ የሚባለውን ሕገ መንግስት ላይ የሰፈረውን በማመን ሰልፍ በመውጣታቸው  መረሸናቸው፤የተቃዋሚ ፓርቲዎችን አመራሮች ማሸነፋቸው ወንጀል ሆኖባቸው፤ የነጻው ፕሬስ አባላት አመለካከታቸውና አቋማቸው ከጨቋኙ አገዛዝ የተለየ በመሆኑ፤ ስለመብት መነፈግ በመሟገታቸው፤ ብክንትን፤በተመለከተ ሁኔታዎች መለወጥ እንዳለባቸው በመናገራቸው ለወህኒ መዳረጋቸውን ቀድሞም የጻፍኩበት ነው፡፡ ያንን ሳደርግም ይህን ለማድረግ በረዳኝ ጥንካሬዬ የተነሳ ዋጋ እንደምከፍልበት ተረድቼ ነው፡፡ ሆኖም ግን ጋዜጠኝነት እኔ እራሴን የምሰዋለት ሙያ መሆኑን አውቃለሁ፡፡ በሌላ አንጸር ደግሞ የኢህአዴግ ጋዜጠኞች የፕሮፓጋንዳና ቆርጦ ቀጥል አገልጋይ፤ የታዘዙትን እንጂ የታዘቡትን የማይጽፉ ጋዜጠኛ ናችሁ የተባሉ ግን ያልሆኑ የገዢው መደብ አገልጋዮች እንደሆኑም እረዳለሁ፡፡ለኔ ግን ጋዜጠኞች ድምጽ ላጡ ድምጽ ሆነው የሚሰዉ ቆራጥና ጥንካሬያቸው የማይገበር መሆናቸውን አውቃለሁ፡፡

ስለዚህም ነው በጭቆና መከራ ውስጥ ስላሉት እውነታውን በተመለከተ በርካታ ጽሁፎች ያቀረብኩት፡፡በዚህ ሳቢያ በርካታ ችግሮች ቢያጋጥሙኝም፤ እኔ ግን ለእምነቴ፤ ዓላማዬና ሙያዬ  በጥንካሬ እቆማለሁ፡፡በመጨረሻም ዓለም አቀፉ ሕብረተሰብ ስለ እውነቷ ኢትዮጵያ እንዲራደ አበክሬ እጠይቃለሁ፡፡እውነተኛዋ ኢትዮጵያ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን እንደምታይዋት አለያም የገዢው መደብ ባለስልጣናት ፈጥረውና የሌለውን እንዳለ፤ ያልተሞከረውን እንደተከናወነ፤ ያልታሰበውን እንደተፈጸመ አድርገው እንደሚያወሩላችሁም አይደለም፡፡በእውነተኛዋ ኢትዮጵያ ውስጥ ከመጠን ያለፈ ጭቆና እየተካሄደ ነው፡፡በነጻ በማሰባቸው ምክንያት ለእስር የተዳረጉት ኢትዮጵያውያን እኔ የምተርክላችሁ እውነት መሆኑን ያረጋግጡላችኋል፡፡እባካችሁ አቅማችሁ በፈቀደ መጠን ይህን ሁኔታ ለመለወጥ ሞክሩ፡፡

ማንም የጥንካሬን እውነተኛ ትርጓሜ ማወቅ ቢያሻው፤በፍልስፍና ጽሁፎችና አተረጓጎም ውስጥ አለያም በወታደራዊ ታሪኮች ውስጥ ለማግኘት አይሞክር፡፡ ከዚህ የርዕዮት ጽሁፍ በመማር ወደ ተግባር ይቀይሩት፡፡

ሌሎቻችን ጥቂት አለያም ጨርሶ ምንም ሳናደርግ እየኖርን ባለንበት እንደ ርዕዮት ያሉትን ግለሰቦች ጥንካሬን ተላብሰው ይህን እንዲያደርጉ የሚያተጋቸው ምንድን ነው እያልኩ ብዙ ጊዜ እገረማለሁ፡፡ ከጥንካሬና ከዓላማ ቁርጠኝነት ጋር አብረው ተወልደው ነው ወይስ በኋላ ያገኙት፤ከሆነስ የትና እንዴት ነው ያገኙት? ይህ ጥንካሬ በአጋጣሚ የተቀላቀላቸው ነው? ለርዕዮትና ለመሰሎቿ የሞራል ግዴታ የሆነባቸው ስልምንድን ነው? ይህ ሊሆን የሚገባው ሳይሆን በመቅረቱ ለምን? ብለው ሌሎቻችን ግን እንደሆነው ስንቀበል እነሱ ለምንን ዋነኛ መልስ ፈላጊ መብት አድርገው ማየት የቻሉት? ርዕዮትስ ሌሎችችን ከወህኒ ውጪ ሆነን በድሎት መኖርን ስንመርጥ ከዚያ የግፍ መጋዘን ከሆነው ወህኒ ቤት ‹‹በኢትዮጵያ ውስጥ የተሸለ ሁኔታን ለማምጣት የበኩሌን አስተዋጽኦ ማድረግ አለብኝ ብዬ አምናለሁ›› ብላ ለምን መልእክቷን አስተላለፈች? ‹‹መቼም ቢሆን ለዓላማዬና ለሙያዬ በጥንካሬ እቆማለሁ››  በማለት በቆራጥነት ምን አናገራት? ‹‹ እባካችሁ አቅማችሁ በፈቀደ መጠን በኢትዮጵያ ይህን ሁኔታ ለመለወጥ ሞክሩ››፡፡ በማለትስ ለምን ተምጽኖ አሰማች? አብዛኛዎቻችን ለሃሞተቢስነታችን በበርካታው እንዲከፈለን ስንስማማ ርዕዮትን በተለይ ሁኔታው የሞራል ግዴታዋ እንዲሆን ምን አስገደዳት?

እንደ ርዕዮት ላሉት ወጣቶች እጅጉን ልዩ በሆነ መልኩ ብርታትንና ጥንካሬን ያላበሳቸው ምን እንደሆነ ማሰብ እንኳን መጀመር ያስቸግረኛል፡፡ምንልባትም ይህን መሰሉ ጥንካሬ ለተለዩ የዘመኑ ወጣቶች የተሰጠ ጸጋ ሊሆን ይችላል፡፡ ምናልባትም እኛ የዕድሜ ባለጸጎቹ ይህን የሚያላብሰን የደም ስራችን፤ ወኔያችን፤የአመለካከት ሚዛናችን ተዳክሞብን ይሆናል፡፡ ምናልባትም ለአንዳንዶቻችን ጥንካሬ ሽንፈት፤ ቅሌት ደግሞ ክብር፤ፍርሃትም ጀግንነት፤ መቀሳፈት እውነተኛነት ይመስለን እንደሁ አላውቅም፡፡ ነገር ግን ስንቶቹ በዚህ ‹‹በነጻው ዓለም ዋና ከተማ›› የሚኖሩ በብእር ስም፤ በስውር ስምና በሌላም መልኩ በርካታ ጦማሮችን መጠሪያ ስማቸውን በመደበቅ እንደሚከትቡ አውቃለሁ፡፡ ሌሎችም የራሳቸውን ጥቅም ለማስጠበቅና፤ ችሮታ ፍለጋና ቤተሰብነትን ለማግኘት በማለት የአምገነኑን ገዢ ስርአትና አገልጋዮቹን ለማስደሰት ያለውን እውነታ በመካድም እንደሚጽፉ አውቃለሁ፡፡ እንዲሁም በሃገር ውስጥ ስላለው መከራና ግፍ፤ የኑሮ ውድነትና ሌሎችም መብቶች ስለመገፈፋቸውና ሕዝቡ ለስቃይ መዳረጉን በዝምታ ማለፍን ምርጫቸው ያደረጉም አውቃለሁ፡፡ በግል ጨዋታ ግን ተቃውሟቸውን ያዥጎደጉዱታል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ እንደርዕዮት ያሉት ጠንካሮች ለምን ለጥንካሬያቸው የሚፈለገውን ያህል ዋጋ ለመክፈል ፈቃደኛ እንደሆኑና ሌሎቻችን ደግሞ ይህን ጥንካሬ እንዳጣነው ያስገርመኛል፡፡በአጭሩ ከጥንካሬ ጋር የተለያየነው ሃሞታችን ስለፈሰሰና ለጊዜው በሚገኝ ሽርፍራፊ ጥቅም ስንል ጥንካሬያችንን ጠቅልለን ለሃሰትና ለመስሎ መኖርነት በመሸጣችን ነው ልበል?

እኔ ርዕዮትን አላውቃትም:: የሞራል ብቃቷንና ጥንካሬዋን ግን በአድናቆት አከብራለሁ፡፡ርዕዮትና መሰሎቿ የሚኖሩት በሃሳባቸው ጸንተው፤በእምነታቸው ተማምነው  እነዚህ እሴቶቻቸው በሚፈጥሩላቸው ሁኔታ ነው፡፡ በዓላማቸው ጸንተው በሞራል ግዴታቸው ተማምነው ያላቸውንና መደረግ አለበት ብለው ለሚያምኑበት ሁሉ ችሮታቸውን ሳያጓድሉ ለዚያ ለቆሙለት እውነታ በማድረግ ነው፡፡ ምንግዜም በውስጠ ህሊናቸው ውስጥ የሞራል ግዴታቸውን የሚያነቃቃና የሚያስተገብራቸው ሃይል አላቸው፡፡ የተሸለ ዓለም፤ ሚዛናዊ የሆነ፤ሰዎች ሁሉ ያላንዳች ችግርና በደል ሊኖሩበት የሚችሉ ለማድረግ፤ ሊቆጣጠሩት የማይችሉት ፍላጎትና የተግባር ጽናት በውስጣቸው አለ፡፡ ዘወትር ጭንቀታቸውና ፍላጎታቸው የሰው ልጅ ደስታና የተደላደለ ሰላማዊ ኑሮ እንዲኖረው ማድረግ ነው፡፡ ፍትሕ ሲዛባ፤ሥልጣን አለአግባብ መጠቀሚያ ሲሆን፤አድልዎ ሲፈጸም ህሊናቸው በጣሙን ይጎዳና እረፍት ይነሳቸዋል:: ስለዚህም ያንን ተቋቁሞ እንዲስተካከል መታገልን ተቀዳሚ ግዴታቸው ያደርጋሉ፡፡ እንደ ርዕዮት ያሉ ዜጎች ለግል ፍላ ጎታቸውና ድሎታቸው ጨርሶ አይጨነቁም፡፡ እኔ የሚባል እራስን የማስቀደም በሽታ ሊይዛቸው ቀርቶ ባጠገባቸውም ደርሶ አያውቅም፡፡ እነሱ ለራሳቸው ሳይሆን ለሰብአዊ ፍጡራን መብትና ጥቅም ብቻ የቆሙ ናቸውና፡፡ ሌሎች ሰዎች ክንዋኔያቸውን እንዲያመሰግኑላቸው አለያም እንዲፈቅዱላቸው አይጠብቁም፡፡ የስብስብ አርቲ ቡርቲና የስብስብ ዋጋ ቢስ አስተሳሰብ ያማቸዋል፡፡ ለራሳቸው የጥንካሬ ብርታት ሊከፈል የሚገባው ዋጋ እንዳለና ያም የሚያስከትለውን እኩይ ሁኔታ ቢያውቁትም ያንን ሁሉ  ለመክፈል ፈቃደኛ ናቸው፡፡  የጥንካሬ ዋጋገው በመንፈሳቸው ጉዳት የሚከፈል መሆኑን ቢረዱም ያንንም ተቀብለውታል፡፡ እንዲህ ነው የአልበገሬዎች ሕይወትና ታሪካቸው!

ርዕዮት ከዚያ የጭቆናና የግፍ ማጎርያ ወህኒ በማንኛውም ጊዜ ልትወጣ ትችላለች፡፡ ለዚህም ማድረግ ያለባት በጉልበቷ ተንበርክካ እራሷን ዝቅ አድርጋ ከአሳሪዎቿ ይቅርታን መለመን ነው፡፡ ርዕዮት አንዳችም በደል አልፈጸመችም ስለዚህ ምንም በደል ባለመፈጸሟ ላልሰራችው ጥፋት ጨርሶ ይቅርታ መጠየቅ የሷ ስብእና አይደለም፡፡ በዚያ ማፈርያ ፍርድ ቤት ተብዬ መጋዘን ውስጥ በተላለፈው ፍትህ አልባ ፍርዳቸው ጋዜጠኛ አባቷን ልጃቸው ይቅርታ እንድትጠይቅ ይመክሯት እንደሆን ሲጠይቃቸው መልሳቸው፡-

ይህ ምናልባት አንድ ወላጅ ሊደርስበት የሚችል ግን አስቸጋሪ ጥያቄ ነው፡፡ ሁላችንም ወላጆች ሳናውቀው ከልጆቻችን ጋር የሚያስተሳስረን የደም ትስስር የሃሳብ ክር አለ፡፡ ሁል ጊዜ ለልጆቻችን መልካሙን ብቻ እንመኛለን፡፡ ከማንኛውም ጉዳት ፈጣሪ እንዲታደጋቸው እንጸልያለን፡፡ ያም ሆኖ ግን ይቅርታ መጠየቁን በተመለከተ ያ የራሷ የርዕዮት ውሳኔ ነው፤ እኔም ውሳኔዋ ምንም ይሁን ምን ያን አከብርላታለሁ፡፡ መሰረታዊ ጥያቄህን ለመመለስ፤እኔ አባቷ እንደመሆኔ ስለውሳኔዋ ያለኝና የሚኖረኝም አቋም አንዳችም ጎጂ ምግባር ያልፈጸመች ንጡህ በመሆኗ ይቅርታ ያውም ያለ ጥፋቷ እንድትጠይቅ አልፈልግም አልመክራትምም፡፡ ምንም ወንጀል አልፈጸመችምና፡፡

ስለሞራል ጥንካሬ በአንድ ወቅት ሮበርት ኬነዲ ሲናገሩ፤‹‹ይህን በመከራ የተጨናነቀ ዓለምን ለመለወጥ የሚፈቅዱ ሁሉ ያላቸው ልዩ ብቃት የሞራል ጥንካሬ ብቻ ነው፡፡ አንድ ሰው ለአዲስ ሃሳብ ሲነሳሳ ወይም የብዙዎችን ሃሳብ ሲመዝን፤ አለያም ፍትህ መዛባቱን ሲሞግት፤ እያንዳንዱ በየራሱ ትንንሽ አስተዋጽኦ በሚያደርግበት ወቅት እነዚህ ትንንሽ አስተዋጽኦዎች ተጠራቅመው ጠንካራ ጉልበት በመሆን ተኩራርቶና ማን ደፍሮኝ በሚል ከንቱ እምነት የተወጠረውን ያንን የመከራና የስቃይ ፋብሪካ የሆነውን ኃያል ነኝ ባይ ያኮራምተዋል::››  እህታችን ርዕዮትም በኢትዮጵያ የሚካሄደውን ጭቆናና የፈላጭ ቆራጭ ገዢዎች እኩይ ምግባር ለመዋጋትና በሰላማዊ መንገድ ታግሎ ማሸነፍ መቻሉን የሚያመላክት ትንሽ ግን ወሳኝና ጠንካራ መልእክቷን ለ90 ሚሊዮን ደጋፊዎቿ አስተላልፋለች፡፡

በዚህ አጋጣሚ እኔም ርዕዮትን የጥንካሬን ትክክለኛ ገጽታ ስላስተማረችን አክብሮት የተመላበት ምስጋናዬን አቀርብላታለሁ፡፡(ምንም እንኳን የኔ ትውልድ ያንን ጠንካራና ግን ትንሽ መልእክቷን ማዳመጥ ቢሳነውም) እኔ ርዕዮት ለእራሷ ትውልድ ለላከቻት መልእክት አሁንም አመሰግናታለሁ፡፡ በብዕሯ ድጋፍና መሳርያነት ጭቆናን ለሕዝብ ለማልበስ በመጣር ላይ ያለውን ስርአት የጭቆናን ግርግዳ በብእሯና በብጫቂ ወረቀቷ ለመቦጫጨቅ በመነሳቷም አመሰግናታለሁ፡፡ እኛ ገሃድ የሆነውን የጭቆና ጫና አንሰማም አናይም ስለ እሱም አንናገርም ማለትን ስንመርጥ ርዕዮትና መሰሎቿ ግን በዚያ በአሰቃቂው ወህኒ ይማቅቃሉ፡፡ በጨቋኞችና በእኩይ አሳቢዎችና ፈጻሚዎች አመለካከት ላይ ሶስት ምርጫዎች አሉን፡፡ሃቁን ሸሽተነው በሃፍረት ሸማ ተሸፍነን መኖር፡፡ ምንም ጭቆና የለም በማለት ያለውን ክደን መኖር፡፡ አለያም ልክ እንደርዕዮት ሁሉ ያንን እኩይ ምግባር በጥንካሬ በመጋፈጥ ድምጻቸውን ለታፈኑ ድምጽ ለመሆንና ሰብአዊ ክብር ለመላበስ መወሰን፡፡ ድምጻቸው ለታፈነባቸው ድምጽ መሆንን ባንደፈርውም፤ ድምጻቸው ለታፈነባቸው ድምጽ በመሆናቸው ለእስር ለተዳረጉትስ ድምጽ መሆን ምርጫችን ሊሆን አይገባም?

እንደ ርዕዮት፤ሰርክዓለም፤እስክንድር ነጋ፤ውብሸት ታዬ፤ዳዊት ከበደ የመሳሰሉት ጀግኖቻችን በዓለም አቀፉ ሕብረተሰብ ሲከበሩና ለጥንካሬያቸው የሚገባቸውን ክብርና ሞገስ በያዓመቱ ሲሰጣቸው፤ እኛም ተግባራቸውን በቅርብ እያየንና እያወቅንም ዝምታችንን ብቻ መለገሳችን የሚያም: የሚያሳፍር የሚያሳዝን ሁኔታ ነው፡፡ ለምንድን ነው የማናከብራቸው? ማንነታቸውን የማናደንቅላቸው? የሚገባቸውን ክብርና ሞገስ በአደባባይ የማናውጅላቸው ለምን ይሆን? ለርዕዮቶቻችን፤ ለሰርካለሞቻችን፤ ለእስክንድሮቻችን፤……የዓለም ሕብረተሰብ ለምን ያከብራቸዋል?

‹‹በኢትዮጵያ የተሻለ ነገ እንዲመጣ የበኩሌን አስተዋጽኦ ማድረግ እንዳለብኝ አምናለሁ::›› ርዕዮት ዓለሙ

የተቶረገመው ጽሁፍ (translated from):

Ethiopia’s Reeyot: “The Price for My Courage”

(ይህን ጦማር ለሌሎችም ያካፍሉ::)

ካሁን በፊት የቀረቡ የጸሃፊው ጦማሮችን  ለማግኘት እዚህ ይጫኑ::

http://www.ecadforum.com/Amharic/archives/category/al-mariam-amharic

 

 

Similar Posts

Leave a Reply