ኢትዮጵያ፡- ከረጂም ርቀት ሯጮቻችን የምንማረው

ከፕሮፌሰር  ዓለማየሁ  ገብረማርያም

ትርጉም  ከነጻነት ለሃገሬ

rucኢትዮጵያ በመልካም ስሟም፤በአስከፊ ገጽታዋም ትታወቃለች:: ኢትዮጵያ በመልካም እንግዳ ተቀባይነቷና አስተናጋጅነቷ፤በሕዝቦቿ መልካም ባሕሪ፤ በመልክአ ምድሯ ውበት፤እና በግሩሙ ቡናዋና በማይደፈሩት ጅጋኖች ረጂም ርቀት ሯጮቿ ትታወቃለች፡፡ ተወዳዳሪ በሌለው የሰብአዊ መብት ጥሰት፤የፕሬስ ማፈኛ ተቋሟም፤በአፍሪካ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የፖለቲካ እስረኞች የሚገኙባት ሃገርም ሆና ኢትዮጵያ ትታወቃለች፡፡ በሚያሳዝን ሁኔታ ችጋር (ኤክስፐርቶቹ እንደሚሉት፤ “ሥር የሰደደ የማይነቀል የምግብ እጥረት”) ከውቢቷ ኢትዮጵያ ጋር ከተሳሰረ ዘመናት አልፈዋል፡፡ የሆነው ሆኖ አትዮጵያ ከጭቆና የፈላጭ ቆራጭ አስተዳደር ወደ ዴሞክራሲ ጉዞዋን ጀምረለች፤ ወይስ ኢትዮጵያዊያኖች ከአምባገነኖች አገዛዝ ወደ ነጻነት እየሮጡ ነው ብል ይሻላል?

ላለፉት ምእተ ዓመታት ኢትዮጵያ ዓለም ያደነቃቸውን  ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን የማይደፈሩና አልበገር ባዮች የመካከለኛና የረጂም ርቀት ሯጮችን አፍርታለች፡፡ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካ አህጉር ጭምር ፈር ቀዳጅ የሆነው ታላቁ ኢትዮጵያዊ አበበ ቢቂላ ነበር፡፡ ሮም ላይ በተካሄደው የ1960ው ኦሎምፒክ የመጀመርያው አፍሪካው የወርቅ ባለድል አበበ ቢቂላ ነበር፡፡ በወቅቱ በቦታው የተገኙ ታዛቢዎች ስለ ድሉ: ሲናገሩ  ‹‹በ1935 ዓም ኢጣልያ ኢትዮጵያን ለመውረር መላውን የኢጣልያ ዲቪዚዮን ማሰለፍ አስፈልጓት ነበር:: ከ25 ዓመታት በኋላ ግን አንድ ጫማ አልባ የሆነ የኢትዮጵያ የክብር ዘበኛ አባል ያንን ጦር በሮም አደባባይ ድል አደረገ›› በማለት ተቹ፡፡ ለአቤ ያ የሃገር ክብር፤ግዳጅ ነበር፡፡ ‹‹ማንም ሊያውቀው ይገባ ዘንድ የምፈልገው፤ሃገሬ ኢትዮጵያ ምንጊዜም ቢሆን ድልን በቆራጥነትና በአርበኝነት ንብረቷ ማድረግ መቻሏን ነው›› ብሎ ነበር አበበ የተናገረው  በወቅቱ፡፡  ይህ ነበር የዚያ ኩሩ ጀግና ተተኪ የማይገኝለት አትሌት ቃል፡፡ አቤ እንደገናም ይህንኑ መሰል ድል እንደገና በ1964 ዓም በጃፓን ቶክዮ ደገመው፡፡ አቤ ድሉን የተቀዳጀባቸው ሁለት ከተሞች በአለም ጦርነት ቀስቃሾች ወዳጅነታቸው ያየለ ከተሞች እንደነበሩ ብዙዎች አልተገነዘቡትም፡፡

ሌሎችም ፈለጉን ተከተሉ፡፡ በ1968 በሜክሲኮ በተካሔደው ኦሎምፒክ ማሞ ወልዴ የማራቶን ድል አድራጊ በመሆን የወርቅ ሜዳልያ አጠለቀ፡፡በ1980 ምሩጽ ይፍጠር በሞስኮው ኦሎምፒክ በ5000 እና በ10000 ሜትር የወርቅ ሜዳልያ አሸናፊ ሆነ፡፡ በሲድኒም ገዛኸኝ አበራ ማራቶንን ላማሸነፈ የመጀመርያው ወጣት አትሌት ሆኖ በ2000 ዓም የወርቅ ሜዳይ አነገተ፡፡ ባለፉት በርካታ ዓመታት ኃይሌ ገብረሥላሴ ረጃጂም ሩጫዎችን የግሉ በማድረግ በተደጋጋሚ ሁለት የኦሎምፒክ የወርቅ ሜዳልያ አሸናፊና እንዲሁም፤ በ10000 ሺ ሜትር  የዓለም ሻምፒዮን ነው፡፡ ኃይሌ በርካታ የሩጫ ሬኮርዶችን በመሰባበር የሬኮርዶች ባለቤት ሲሆን የብዙ የክብር ስሞችም ለስሙ ያስገኘ ነው፡፡ በዓለም ታዋቂ የሆነው ራነርስ ወርልድ፤ የአሜሪካ ታላቁ የስፖርት ጋዜጣ፤‹‹የዓለማችን ታላቁ የረጂም ርቀት ሯጭ›› በማለት ሰይሞታል፡፡ ቀነኒሳ በቀልም በ5000 እና በ10000 ሜትሮች ሁለት የኦሎምፒክና የዓለም ሬኮረዶች በ2008 በቤይጂንግ የጥንድ ባለድል ና ባለቤት ነው፡፡ በተመሳሳይም በአቴንስ ድሉን ደግሞታል፡፡ በዓለም ሻምፒዮንነት ድሉን ለመዘርዘር በጣም በርካቶች በመሆናቸው መዘርዘሩ አዳጋች ነው፡፡

በሴቶችም በኩል ቢሆን የማይተናነስ ድል ያስተናገዱ ጀግኖች አሉን፡፡በ2011 ጢቂ ገላና በ2012 በተካሄደው የሎንዶን ኦሎምፒክ ላይ 2፡23፡07 በሆነ ሰአት አዲስ የኦሎምፒክ ሬኮርድ በማስመዝገብ አሸናፊ ነበረች፡፡ ፋቱማ ሮባም በተመሳሳይ ሰአት በአትላንታ በ1966 በተደረገው የኦሎምፒክ ውድድር የወርቅ ባለድል ነበረች፡፡ ደራርቱም በ10000 ባርሴሎና ላይ በ1992 አሸንፋ ወርቅ አንግታለች፡፡ ጥሩነሽ ዲባባም በቤይጂንግ በ2008 የ5000ና የ10000 የድል ባለቤት ነበረች:: ይህንንም በመድገም በ2012 በሎንዶን ኦሎምፒክ በ10000 የድል ባለቤት ሆናለች፡፡ ባለፈው ሳመንት በችካጎ ከተማ ጸጋዬ ከበደ በ02፡04፡38 ሰአት በሌሊሳ ፈይሳ ተከታይነት በ02፡04፡52፤ረጋሳ ጥላሁንም በሶስተኛነት 02፡05፡27 ሰአት ሲጨርሱ በሴቶችም አጸደ ባይሳ በ02፡22፡03 ቀዳሚ ሆና ወርቅ አጥልቃለች፡፡  የወርቅ የብር የነሐስ ባለድል የሆኑትን፤የማራቶን ጀግኖች የተባሉበትን፤እና በሌላም ተመሳሳይ ውድድር  የዓለም ባለክብረ ወሰን የሆኑ ኢትዮጵያዊያንን ለመዘርዘር ማለቂያ የለውም፡፡ ብዙዎች የነዚህን ጀግኖች ሚስጥር ማወቅ ይጓጓል፡፡ ሁሉም ተመራማሪዎች ጉዳዩን በሚገባ ካጠኑና ከመረመሩ በኋላ የደረሱበት መቋጫ፤ ‹‹ኢትዮጵያዊያን ሯጮች ለድል የሚያበቃቸው ሚስጥር ለድል አድራጊንት የሚያድርባቸው ረሃብ ነው›› በማለት ደምድመዋል፡፡

የረጂም  ርቀት ሩጫ ለኢትዮጵያ  ፖለቲካ  እንደ  ተምሳሌትነት

ባለፈው ኖቬምበር 2009 (‹‹የኢትዮጵያ ታላቁ ሩጫ ወደ ነጻነት በሚል ጦማር ላይ እንደጣፍኩት››) ሁልቆ መሳፍርት የሌላቸው ተሳታፊዎች ለነጻነት ብቻ አይደለም ሩጫቸው፤ከጭቆናና ከፈላጭ ቆራጭ አገዛዝ ማነቆ ለመውጣትም ነው፡፡ የሚያሳዝነው ግን እነዚህ ሯጮች ሩጫቸው የሚዞርበት ቀለበት ኢትዮጵያ በገባችበት የወህኒ ማነቆ ውስጥ መሆኑ ነው፡፡ የረጂም ሩጫው ለኢትዮጵያ ፖለቲካና ይህችንም ሃገር ከጭቆና አገዛዝ ወደ ዴሞክራሲ ለማሸጋገር ተምሳሌት ሊሆን ይችላል፡፡ ረጂም ርቀት ሩጫ የጉልበት ብርታት ጥያቄ ብቻ ሳይሆን የጠነከረና የቆረጠ የህሊና ጥንካሬም ነው፡፡ረጂም ሩጫ ለመሮጥ ታላቅ የሰውነት ጥንካሬን ከዚያም ሌላ እጅግ የጎለበተ ሃይልና ትእግስትን ይጠይቃል፡፡ ረጂም ርቀት ሩጫ አድካሚ፤አሰልቺ፤ፈታኝ ነው፡፡ ረጂም ሯጮችም የራሳቸውን ሂደት በመጠበቅ፤ልኩን በማስተካከል፤ያንን አቧራማና ውጣ ውረድ ያለበትን ሂደት በውሃ ጥምና በላብ በመደፈቅ፤ከፊት የሚገፋቸውን ንፋስ እየሞገቱ፤ ንዳዱ እያቃጠላቸው፤ከየጡንቻዎቻቸው ያለውን ሃይል እያዳከመ ሲፈትናቸውም ድል እያደረጉ ግባቸውን ይመታሉ፡፡ የርቀት ሯጭ ሁል ጊዜ ዓይኑ አሻግሮ የሚመለከተው፤ድካሙን ሳይሆን በድል የሚጠለቅለትን የአሸናፊነት ሃብል ነው፡፡ ይህን ሁሉ የሚያመጣው ታዲያ እድሜ ሳይሆን፤አመጋገብ ሳይሆን፤ ለስኬት ያለው ጥንካሬና እልህ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ረጂም ርቀት ሯጮች የድል ሚስጢር‹‹ ለማሸነፍ ያላቸው ቁርጠኝነት ነው፡፡›› ይህም ደረጃቸውን ከፍ አድርጎ ለማስቀመጥ የሚያስችላቸውን መመዘኛ ሰርተዋል፡፡እኛም ለዴሞክራሲ በምናደርገው ሩጫ ፈቃደኝነትና የድል ረሃብ ያስፈልገናል፡፡ ለዴሞክራሲ የወርቅ ሜዳልያ የሚገኘው 100 ሜትርን በግል በመሮጥ፤ ወይም 400 ሜትርን በቅብብሎሽ በመጨረስ አይደለም፡፡ የነጻነት የድል ወርቅ ሜዳልያም በ400 የዝላይ ሩጫ ሳይሆን፤በ1500 ሜትርም አስቸጋሪ ሩጫ አይሆንም፡፡ የሁሉም ነጻነቶችና መብቶች የወርቅ ሜዳልያዎች የሚገኙት፤ ከረጂም አድካሚና ፈታኝ፤ በተራራ ውጣ ውረድ፤ አስቸጋሪና ድንቅፍቅፉ የበዛበት ፈላጭ ቆራጭና ጨቋኝ አገዛዝ ከሚገኝበት ከጭቆና ሸለቆዎች፤ ቁጥቋጦ አልባ በሆነው ሕግ በሌለበት ሜዳ፤ ውሃ በደረቀበት በረሃ መቻቻል በማይኖርበት፤ጭካኔና መሃይምነት ከበዛበት ደርሶ በማሸነፍ በሚደረግ የማራቶን ድል ነው፡፡ በኢትዮጵያ ለዴሞክራሲ፤ ለሰብአዊ መብት መከበር በሚደረግ የማራቶን ሩጫ፤ ልክና ደረጃ ማስቀመጥ ይገባናል፡፡ እነዚህ ውጤቶችና ደረጃቸው ምንድን ነው? በመጀመርያ ከሰው አቅም በላይ የሆኑ አይደሉም፡፡ሁላችንም አልፎ አልፎ የምንተገብራቸው ጉዳዮች ናቸው፡፡ሁለተኛ የሰውነት ሁኔታ ውጤቶችም አይደሉም፡፡ግን ስነ አእምሮአዊ፤ የእውቀት፤የእምነት  እንጂ፡፡

የርቀት ሯጮች ትኩረታቸው አንድ አቅጣጫ ነው፡፡ ምልከታቸውን በአንድ አቅጣጫ ግባቸው ላይ አስተካክለው በህሊናቸው እየተመሩ ግባቻውን ማሳካት ነው፡፡ በቀላሉ ከኢላማቸው አይዘናጉም፡፡ የመጨረሻው መግቢያ በር እስኪደርሱ ድረስ ይሮጣሉ ይሮጣሉ እንደገናም ለድል ይሮጣሉ፡፡  ውሃ ጥም ቢጠብሳቸውም፤ድካም ቢሰማቸውም ተስፋ መቁረጥን ሳያስጠጉ ድላቸውን ብቻ በማሰብ በጠንካራ የአእምሮ እሳቤ፤ውጤታማነታቸውን እያማጡ ዓላማቸውን ለግብ አስተካክለው በሩ ጋ ደርሰው ድልን ይወልዳሉ፡፡ ውድድራቸው ከኋላ ከቀረው ወይም ከፊት ከቀደመው ጋር ሳይሆን ረጂም ርቀት አለህ፤ ደክሞሃልና ተወው ከሚላቸው አሳናፊና ተስፋ አስቆራጭ አስተሳሰባቸው ጋር ነው፡፡ እነዚህ የረጂም ሩጫ ርቀት ሙያና የድል ባለቤትነት ሱሰኞች የሆኑት ሯጮች ግን ውጣ ውረዱን ድካሙን ተስፋ አስቆራጩን ሳንካ አስተሳሰብ ያለ የሌለ ጥናካሬና ጉልበት፤ ድልን ለመቀዳጀት ለራሳቸው የገቡትን ቃል በማክበር፤ የድል ርሃባቸውን ለመወጣትና ያንን የወርቅ ሜዳይ ለማጥለቅ ሂደቱን ቀጥለው ድልን ይመገባሉ፡፡ ረጂም ርቀት ሯጮች ዘወትር ከብረት የጠነከረ ቆራጥነት ስላላቸው ሁልጊዜም ለማሸነፍ ዝግጁ ናቸው፡፡ ለድል የሚያበቃቸውን ፕላን ነድፈው ይዘጋጁና በሂደት ያስተካክሉታል፤ እንዲያውም የቸገረ ነገር ከገጠማቸው ጨርሰው እቅዳቸውን ሊለውጡት ይችላሉ:: ለዚህም ፈቃደኛ ናቸው ዝግጁም ሆነው ይጠብቁታል፡፡በዝግጅታቸው ሂደት ሁሉ ስሜታቸውን ከማሸነፍ ጋር እንዳጋቡት ነው፡፡ኃይሌ አንድ ጊዜ ሲናገር ‹‹በቅድሚያ አስፈላጊውን ልምምድ ጠንቅቆ ማድረግ፤ከዚያም በራስ በመተማመን ላደርገው እችላለሁ ብሎ መነሳት፡፡ ነገ የኔ ቀን ነው ብሎ ማመን፡፡ ከዚያም፤ ‹‹ከፊቴ ያለው ሰው፤አሱም እንደማንም ሰበአዊ ፍጡር ነው፤ሁለት እግር አለው፤እኔም ሁለት እግር አለኝ ይሄው ነው በቃ፡፡ በእንዲህ ነው ራስህን የምታዘጋጀው››::  ሲያሸንፉም ድሉ የግላቸው ሳይሆን የሃገራቸውና የሕዝብ ድል ነው ብለው ነው የሚያምኑት፡፡ አቤም ‹‹ዓለም እንዲያውቅልኝ የምፈልገው፤ሃገሬ ኢትዮጵያ ዘወትር በቆራጥነትና በጀግንነት ስሜት ለድል መብቃቷን ነው›› ያለውም በዚህ ምክንያት ነው፡፡

የረጂም ርቀት ሯጮች ሌሎች የማያዩትን የሚመለከቱበት ራዕይ አላቸው፡፡‹‹ ምንም እንኳን የመጨረሻው የድል ጣቢያ በተራሮችና በወጣ ገባው መሬት ቢጋረድም፤ ግባቸውን በማገናዘብ አሻገረው ከለላውን ጥሰው ያዩታል››::  የመጨረሻዎቹን ቀሪ ርቀቶች በሕሊና አይኖቻቸው በመመልከት ለዚያ ወሳኝ ሰአት በመዘጋጀት በድል ሲገቡና አዲስ የዓለም ክብረ ወሰን ሲያዝመዘግቡ በማየት ለድል ይበቃሉ፡፡ እነዚህ ሯጮች የአእምሮና የመንፈስ ጽናት አላቸውና፤አቅማቸው የሚችለው ብለው ካሰቡት በላይ አቅም እንዲኖራቸው ስለሚያግዛቸው የሰውነታቸውን ድካም የመንፈሳቸውን ስንፈት በመቋቋም፤ለድል ይበቃሉ፡፡ ረጂም ርቀት ሯጮች፤ እጀጉን የጠነከረ በራስ መተማመን ስላላቸውና የጀመሩትን ሥራ በድል የመወጣት ጽናት ስለሚታጠቁ ለድል ይበቃሉ፡፡ለማሸነፍ የሰነቁትን ዓላማና ግብ አይጠራጠሩትም፡፡ ሲሮጡ ወደ ኋላ ከመመልከት ይልቅ በጥንካሬ ወደፊት እየገፉ እያንዳንዷ ማይል ወደ ድል በር የምታቃርብና አሸናፊ እንደምታደርጋቸው ጠንቅቀው ያውቃሉ፡፡ረጂም ርቀት ሯጮች ለስርአት የተገዙ፤ እራሳቸውን ለመልካም ስነምግባር ያሳደሩ ናቸው፡፡ምናልባት ሽንፈት ቢያጋጥማቸውና ማድረግ የሚገባቸውን እንዳላደረጉ ቢገነዘቡም፤ በዚያ ስህተት በመቆጨት ቁጭ ብለው በሃዘን ፊታቸውን አይነጩም፡፡ ያን ሁኔታ የፈጠረባቸውን ሰበብ በማወቅ ጉድለቱን አስተካክለው የጎደለውን ሞልተው፤ የሰነፈውን አጠንክረው፤ የደከመውን አጎልብተው  ለሚቀጥለው ድል እራሳቸውን በአግባቡ ያዘጋጃሉ፡፡ ቂም የለም ተስፋ መቁረጥ ጨርሶ ቦታ የለውም፤ ሰበብ አስባብ ፈልገው ሌላውን መውቀስ የነሱ ባህሪ አይደለም፡፡ የዴሞክራሲ ዋጋ፤ ነጻነትና የሰብአዊ መብት መከበር በአጭር ርቀት ሩጫ፤ በቅብብሎሽና በመሳሰሉት የሚገኝ ድል አይደለም፡፡ እጅጉን አድካሚና ፈታኝ የሆኑ ሂደቶችን በመወጣት ብቻ የሚገኝ ነው፡፡ የዴሞክራሲ ሩጫ ለነጻነትና ከጭቆና ለማምለጥ በሚሮጡና፤እነዚህን የነጻነትና የዴሞክራሲ ሯጮች  በሚያሳድዱ ጨቋኞች፤ መሃል የሚካሄድ የማራቶን ሩጫ ነው፡፡ አሳዳጆቹ በሯጮቹ ላይ የበላይነት ያላቸው ስለሚመስላቸው ርቀው ሳይሄዱ ጠልፈው አደናቅፈው ለመጣልና ለማሰናከል የማያደርጉት አንዳችም ተንኮል አይቀራቸዉም፡፡ የሆነው ቢሆንም ግን ሯጮቹ የዴሞክራሲና የነጻነት ፈላጊዎች ቆርጠውና ለዓላማቸው ጸንተው፤ በጥንካሬና በአትንኩኝ ባይ ስሜታቸው ለድል መብቃት ይገባቸዋል፡፡ ለዚህም ነው የዴሞክራሲና የነጻነት ሩጫ አጫጫር ርቅት ሩጫ ሳይሆን የረጂም ርቀት ማራቶን የሚሆነው፡፡

ለነጻነት፤ ለዴሞክራሲ፤ ለሰብአዊ መብት በሚደረገው የረጂም ርቀት ሩጫ እያንዳንዳችን  ሯጮች መሆን ይኖርብናል

በአባጣ ጎርባጣው፤ በሸንተረሩ፤ በዳገት ቁልቁለቱ፤ በሚካሄድ የኢትዮጵያ ነጻነት፤ የዴሞክራሲ፤ የሰብአዊ መብት መከበርን ለማረጋገጥ ከዘረኝነት፤ ለመውጣት ረጂም ርቀት ሩጫ ላይ የሚደረገው ውድድር በተለያየ ወቅት ድል አድራጊ አንድ አንድ ሰው ሊሆን ይችላል፡፡ ይህም ማለት እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ሕሊናውን አዘጋጅቶ እራሱን በዲሲፕሊን አስገዝቶ፤ልቡን ለድል አስተካክሎና ሞልቶ፤ የድል ማድረግ ግዴታ አለበት፡፡ ጋንዲ እንዳለው ‹‹በዓለም ላይ ማየት የምትሻውን ለውጥ መሆን መቻል አለብህ››፡፡ በቅድሚያ የራሳችንን ጠባብ አመለካከት፤ ጥላቻ፤አለመግባባት፤ጋጠ ወጥነት በማስወገድ፤ ለዴሞክራሲ፤ ለነጻነት፤ ለሰብአዊ መብት መከበር የሚከናወን ‹‹የኦሎምፒክ ማራቶንን››  ማሸነፍ አለብን፡፡ የየግል ድላችንን በ80 ወይም በ90 ሚሊዮን ስናባዛው፤ሃገራችን ኢትዮጵያን ለ21 ዓመታት ሰንቆ ከያዛት ፈላጭ ቆራጭ አገዛዝ፤ከጭቆና ማነቆ ስርአት ወደ 13 የጸሃይ ወራትነት ልንለውጣት እንችላለን፡፡

ከረጂሙ አድካሚና ፈታኝ ፤ ውጣ ውረድ የተሞላበት ሩጫ በኋላ ስላለው የድል ሽልማት ማንም ቢሆን ሊጠራጠር አይገባም፡፡ ይህን አሽቅድድሞሽ ስናሸንፍ፤ለሕብረተሰቡ የሕግ የበላይነት የነገሰባት፤የሰብአዊ መብት የተከበረባት፤ አለአግባብ በስልጣን መጠቀም ተጠያቂነትን የሚያስከትልባት፤መንግሥት በሕዝብ ፈቃደኝነት ላይ ብቻ የሚያስተዳድርባት፤ሕዝቡ ሳይሆን መንግሥት ሕዝብን የሚፈራባት፤ሕዝቡ ያለአንዳች  ፍርሃት በነጻነት፤ የመንግስት ወከባ ሳይኖርበት፤የሚኖርባትን ሃገር ለድል ማብቃታችንን መዘንጋት የለብንም፡፡ ምናልባትም የድል ወርቅ ሜዳይ የምናጠልቅበት ጊዜ ይረዝም ይሆናል:: ስለዚህም የዚህን ማራቶን በቅብብሎሽ መሮጥ ይኖርብናል፤ በዚህም አንዱ ትውልድ ለሌላው በማስተላለፍ ይህን ታላቅ ድል ማግኘታችን የግድ ነው፡፡ የማያጠራጥር ወኔ ከወጣቱ ትውልድ ቆራጥ የወኔ ድል ለቀጣዩ ትውልድ፡፡ ለኢትዮጵያ የዴሞክራሲ፤ የሰብአዊ መብት፤ ርቀት ሯጮች፤እንደ ዓለም ኦሎምፒክ ሯጮች ድካም ሊሰማቸው ተስፋ አስቆራጭ ሃሳብ ሊሞግታቸው የድሉ በር ሩቅና የማይደረስበት መስሎ ሊታያቸውና ድልም የማይታሰብ ሊመስላቸው ይችላል፡፡ እንዲያውም ወደ ድሉ በር መድረሱ አዳጋች መስሏቸው ለማቋረጥም ይዳዳቸው ይሆናል፤ እራሳቸው ሊከብዳቸው፤ ጡንቻዎቻቸው ሊዝሉ፤ ከማብቂያው በር ለመድረስ ርቀቱ ተስፋ አስቆራጭ ሊሆንባቸው ይሞክራል:: መንገዱ ወጣገባ፤ ቢሆንም የዴሞክራሲ፤ የነጻነት፤ የሰብአዊ መብት ሯጭ ግን እኔም የረጂም ርቀት ሯጮቻችን ደጋግመው እንዳደረጉት ሁሉ ማድረግ ይኖርብኛል፤ ብሎ ቆርጦ መነሳት አለበት፡፡ ሕሊናችንን ‹‹ላደርገው እችላለሁ፤ልናደርገው እንችላለን፤ርቀቱን ጨርሶ አለማሸነፍ ግን ፍላጎታችን አይደለም፡፡ ማንንም ሮጠን ለድል መብቃት ማሸነፍ መብቃት አለብን፡፡ ከዚህ የድል በር ሊያናጥቡንና ሊያጨናግፉን የሚጥሩትን ሁሉ አልፈንና ቀድመን ድል ማድረግ ዓላማችን ነውና ማሸነፍን ለምንም ሳናካክስ ድልን መጨበጥ ይኖርብናል፡፡ ለድል የሚያስፈልገን ይህ ቁርጠኝነት ብቻ ነው፡፡የ‹‹ኦሎምፒክ ማራቶን››

ለዴሞክራሲ፤ ነጻነትና የሰብአዊ መብት መከበር በኢትዮጵያ!

የኛ ድል አድራጊ ሻምፒዮናዎች ከፊት ለፊታቸው የቆመ ዳገት ሲያጋጥማቸው፤ወይም ሃይለኛው ንፋስ ሲሞግታቸው በቀላሉ እጃቸውን አይሰጡም፡፡ ዝናብ ይሁንም ውርጭ፤ በረዶ ይሁን ንዳድ ቃጠሎ፤ከዓላማቸው ጨርሰው አይዘናጉም፡፡ ውድድሩ የተሻለ ገንዘብ ስለማይገኝበት አለያም ሁኔታው ምቹ ስለማይሆን ብለው ተስፋ አይቆርጡም፡፡ ምንም ይሁን ምን ጨርሶ አይተዉትም፡፡ ተስፋም አይቆርጡም፡፡ ለድልና ለክብር፤ ለማንነት ማረጋገጫ ድል፤ ቀድሞ ለመገኘት ብቻ ይተገላሉ ይሮጣሉ ይሽቀዳደማሉ::  ወደኋላ ሳይሆን ወደፊት በመሮጥ እንቅፋታቸውን ሁሉ እያለፉ በድል በር ቀዳሚ ሆነው ብቻ መገኘት ነው ያላቸው አማራጭ፡፡ የማንም ሃይል በጠላትነት ቢሰለፍ ለድል ቆርጠው ተነስተዋልና ዐላማቸውም ያው ድል ብቻ በመሆኑ ለድል ከመብቃት የሚያግዳቸው አንዳችም ነገር አይኖርም፡፡

‹‹ማንም ሊያውቀው ይገባ ዘንድ የምፈልገው፤ሃገሬ ኢትዮጵያ ምንጊዜም ቢሆን ድልን በቆራጥነትና በአርበኝነት ንብረቷ ማድረግ መቻሏን ነው::››  አበበ ቢቂላ

=========================

የተቶረገመው ጽሁፍ (translated from):

http://open.salon.com/blog/almariam/2012/10/10/ethiopia_what_we_can_learn_from_our_distance_runners

(ይህን ጦማር ለሌሎችም ያካፍሉ::)

ካሁን በፊት የቀረቡ የጸሃፊው ጦማሮችን  ለማግኘት እዚህ ይጫኑ::

http://www.ecadforum.com/Amharic/archives/category/al-mariam-amharic

http://ethioforum.org/?cat=24

Similar Posts

Leave a Reply