የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ፖለቲካ የደሞክራሲ ጮራ ሰትወጣ

ከፕሮፌሰር  ዓለማየሁ  ገብረማርያም

ትርጉም  ከነጻነት ለሃገሬ

በድጋሚ እውነት፤ሃይልን ለተነፈጉ

ላለፉት በርካታ ዓመታት ስለሥልጣን ተጠቃሚዎች ዕውነትን ስናገር ነበር፡፡ የጦማሬ ገጼ መግቢያ መስመሩ ‹‹ለሰብአዊ መብት ተሟገት፡፡ ስለሥልጣን ተጠቃሚዎች እውነትን መስክር›› ነው የሚለው፡፡ ይህ ደሞ ልዩ ትርጉም ያለው፤ ጠንካራ ሞራልና ስልጣናቸውን መከታ በማድረግ አላግባብ የሚጠቀሙበትን፤ ከመጠን በላይ ለሚተማመኑበት ኢሰብአዊ ድርጊት ማስገንዘቢያ የሆነ ስንኝ ነው፡፡ ለባለስልጣናት ነን ባዮች እውነትን መናገር፤ተናጋሪው በነዚህ ባለስልጣናት ላይ ስልጣናቸው የተዘረጋው በሃሰት ላይ መሆኑን ምስክርነቱን ያረጋግጣል፡፡ አልፎ አልፎም ሃቅን መናገር የስልጣን ሰለባ ለሆኑትም አስፈላጊ ነው፡፡ ስልጣን አልባዎች በምንም መልኩ ስልጣንን ሊያዛቡ የሚችሉበት ሁኔታ የለም፡፡ ስህተታቸው ግን የስልጣናቸውን እውነተኛ መብት አለማወቃቸው ነው፡፡ ሥልጣንን መከታ በማድረግ ግፍ የሚፈጽሙት ጉልበተኛ ሆነው ቢታዩም፤የስልጣን ተነፋጊዎች ደግሞ የሥልጣን ባለቤትነት መብት አላቸው፡፡ የሥልጣንን  እውነታነትና መብትን ነው የሥልጣን ተነፋጊዎች በትግላቸው ሂደት ሊጠቀሙበትና ለድል የሚያበቃቸውን መንገድ ሊከተሉ የሚገባቸው፡፡ ዶር ማርቲን ሉተር ኪንግ ይህን አስመልክተው፤ ‹‹ለጊዜው ትክክለኛነት ቢሸነፍም፤ ከሰይጣናዊና እኩይ ድል የበለጠ ነው›› ብለዋል፡፡

በጁን 2010፤ ‹‹እውነትን ስልጣን ለተነፈጉ መናገር›› የሚል ጦማር ጽፌ ነበር፡፡ በዚያም ጦማሬ ላይ በሜይ 2010፤ ቀን በቀን በገዢው ፓርቲ የተሰረቀውንና ድሌ 99.6 ነው በማለት ፓርላማውን የተቆጣጠረበትን የምርጫ ውጤት በተመለከተ ፤የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ፓርቲዎች እንቅስቃሴ የፖለቲካ መሽመድመድ የታየበትና አንዳችም ተግባር ያልተከወነበት ሂደት እንደነበር አሳስቤ ነበር፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በጥንቃቄ ትኩረት ሰጥተው ራሳቸውን ማስተካከያ መንገድ እንዲፈልጉም አሳስቤ ነበር፡፡ ‹ዓላማዬ ዲስኩር ለማድረግ ወይም ተቃዋሚዎችን ለመኮርኮም ሳይሆን ሃሳባችንን በማጽዳት ቆሻሻውን አውጥተን በመጣልና ወደ ዴሞክራሲ የሚያደርሰንን ረጂሙን መንገድ ቀና ለማድረግ ለመርዳት መሆኑን በውቅቱ አስረድቻለሁ፡፡ ‹‹እውነት ይጎዳል›› ቢባልም እኔ አልስማማበትም፡፡ ‹‹እውነት ለማገገም ይረዳል፤ ሃይል ይሰጣል፤ ታጋዮችንም ነጻ ያወጣል፡፡››

የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ሃይሎች በገዢው ፓርቲ እይታ

የ2010ን ምርጫ ተከትሎ እንደተቃዋሚ ፓሪቲዎች፤ የነጻው ፕሬስ ጋዜጠኞች፤ እና የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች በገዢው ፓርቲ የሚደርስባቸውን ሰቆቃ በተመለከተ የገዢው አመራሮች አገኘን ስለሚሉት ድልና የምርጫ ውጤት ስለተቃዋሚ ፓርቲዎች (ስለሕዝቡ) ያላቸው ግንዛቤና አመለካከት ያስገርመኛል፡፡ ያን ጊዜም አሁን እንደማስበው፤ በገዢው ባለስልጣናት እይታ ተቃዋሚዎችን መመልከት፤ተቃዋሚዎችን በተለይም የተቃዋሚ ፓርቲዎችን ያለውን ሁኔታ በማገናዘብ ሊከተሉት የሚገባውን መንገድ ያመላክታል ብዬ አምናለሁ፡፡

……..መለስ ተቃዋሚዎች እራሳቸውን ለክተው እንደማያውቁ ያውቃል፡፡ በሚገባ አጥነቷቸዋል፤ አስጠንቷቸዋልና ስራቸውን እንዴት እንደሚያከናውኑ (እንደማያከናውኑ) ጠንቅቆ ያውቃል፡፡ በጥንቃቄ የተበጠሩት  ሕዝባዊ ዲስኩሮቹ ላይ ዘወትር የማይለወጥና መጥፎ አመለካከቱን ያሳያል፡፡ ተቃዋሚዎችን በችሎታቸውም በእወቀትም የበታቾቹ አድርጎ አስቀምጧቸዋልና በፈለገው ሰአትና ወቅት በአስተሳሰብ እንደሚበልጣቸው፤ በአመለካከት እንደሚያልፋቸው፤በተንኮል እንደማይደርሱበት፤ በእኩይ አስተሳሰብ እንደማይስተካከሉትና ባሻው ጊዜ ድል እንደሚያደርጋቸው ያምናል፡፡ በመለስ አስተሳሰብ፤እንቅስቃሴያቸው ድውይ፤የማያድጉና ያልበሰሉ፤ አድሮ ጥጃ፤ በመሆናቸው ሥልጣኑን የሚያሰጉት እንዳልሆኑ አረጋግጧል፡፡ በንግግሮቹ ሁሉ ተቃዋሚዎች ላይ ያለውን ንቀትና ጥላቻ ብቻ ነው የሚያንጸባርቀው፡፡ እድገታቸውን እንዳልጨረሱ ሕጻናት እለት ተእለት ክትትል የሚያስፈልጋቸውና ስርአት እንዲኖራቸውም የዲሲፕሊን ሽንቆጣ እንደሚያስፈልጋቸው ነው የሚደሰኩረው፡፡ ልክ ሕጻናትን እንደማታለል አይነት፤ ለአንዳንዶች፤ስኳር ያልሳቸዋል፤ በሥራ፤ በመኪና ችሮታ፤ በቤት ስጦታ፤ እና አፋቸውን ሊያፍን የሚያስችለውን ሁሉ ያደርግላቸዋል፡፡በዚህ ሊደልላቸው የማይችላቸውን ደሞ በመከታተልና ሲገቡ ሲወጡ በመተንኮስ፤በስለላ አባላት በማስጨነቅ በመጨረሻውም አስሮ ይፈርድባቸዋል፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ተቃዋሚዎችን ያታልላቸዋል፤ይቀልድባቸዋል፡፡ ሽማግሌዎችን ለእርቅ በመላክ፤ ጊዜ እየገዛ የቆሙበትን መሰረት ያሳጣና፤ድርድር በሚል ዘዴ እያታለለ የራሱን ድል ይገነባል፡፡ የተለመደ አስማታዊ የሆነውን የተንኮል ጠበል ይረጭና ያንኑ ውጤት አልባ የሆነውን ጨዋታውን ጀምሮ በመጨረሻው እንቅልፍ አስወስዷቸው በድሉ ደወል ሲነቁ ማርፈዱን ይገነዘባሉ፡፡ በዚህም ተቃዋሚዎች የጨበጡትን ሁሉ ለቀው ተሸናፊ ሆነው ይሰለፋሉ::

በኢትዮጵያ ተቃዋሚው ሃይል ማነው?

ይህ ጥያቄ ምናልባትም አወዛጋቢና እንዲያውም ቁርጥ ያለ መልስም ሊገኝለት የማይችል ይሆናል፡፡ አሁን በሃገሪቱ ውስጥ የተጠናከረና ጉልበት ኖሮት የተዋቀረም ፓርቲ አለ ማለት ያስቸግራል፡፡ በዚህም የተነሳ ተቀናጅተውና ሃይላቸውንና አቋማቸውን አስተባብረው ገዢውን ፓርቲ ሊሞግቱና ገዢውን ፓርቲ ሊቋቋሙት ብቃት ያላቸው ፓርቲዎች ውህደት አይታይም፡፡ በምሁራንም የተጠናከረና የተዘጋጀ ተቃዋሚ የለም፡፡ ከሲቪል ማህበረሰቡም፤ከማህበራት፤የተዋቀረ የተቃዋሚ ፓርቲም የለም፡፡ የህብረተሰቡን ሃይል ያካተተም እንቅስቃሴም ሆነ ተቃዋሚ ሃይል የለም፡፡ በኢትዮጵያ  ያለው የፖለቲካ ተቃዋሚዎች ችግር ከ1960ዎቹ  ጀምሮ የኖረው ያአፍሪካ ያረጀው ችግር ነው፡፡ በአፍሪካ አንድ ሰው አንድ ፓርቲ በማለት በጋና በክዋሚ ንክሩማ ዘመን የተፈጠረ ሂደት ነው፡፡ ንክሩማ ተቃዋሚዎቹን፤አጠፋ፤ አጋዘ፤ ለፍርድ አቅርቦ ያለአግባብ አስፈረደባቸው፡፡ በዚህም ሂደት ውስጥ ዳኞች፤ የማህበራት መሪዎች፤ተካተዋል፡፡ ባለፈው ግማሽ ምዕተ ዓመት ውስጥ፤በኢትዮጵያ በጉልበት በስልጣን የወጡትን ገዢዎች የተቃወመ ሁሉ፤በፖለቲካው መድረክ መወቀስና መወገዝ ብቻ ሳይሆን፤ያለአግባብ በፍርድ ስም መሰቃየትና ከዚያም አልፎ ለሞት መዳረግ የታየበት ዘመን ነው፡፡ የኢትዮጵያን የተቃዋሚ ሃይላት ምንነትና ሁኔታ እንዲህ ነው ለማለት እቸገራለሁ፡፡ ከሜይ 2010 ምርጫ በኋላ ባቀረብኩት ጦማሬ ላይ አንስቼው እንደነበረው፤ ‹‹ያ ተስፋ የቆረጥንበት ተቃዋሚ ሃይል፤ የተከፋፈለ፤ያ በነጋ በመሸ ቁጥር በረባ ባልረባው ጉረሮ ለጉረሮ የሚተናነቀውና ዋናውን ሊታገሉት የሚገባውን ሃይል የዘነጉት ናቸው አሁንም ተቃዋሚ ናቸው የምንላቸው? ወይስ እነዚያ በደካማው የሚንቀሳቀሱትን  እንደአመቺነቱ ብቅ ጥልቅ የሚሉትን የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች፤ የስቪክ ማህበረሰቡ አሰባሳቢዎች፤ጋዜጠኞች፤ እና ሌሎቹን የሚዲያ ባለሙያዎችና ምሁራኑን ናቸው? ወይስ ለመሳርያ ትግል ታጥቀውና ቆርጠው የተነሱትንና ገዢውን ፓርቲና  አፋኝና ጨቋኝ ስርአቱን ለማጥፋት የተነሱትን ነናቸው ተቃዋሚ የምንላቸው?

ሁሉም ናቸው ወይስ ሁሉም አይደሉም?

በኢትዮጵያ ትክክለኛው የ‹‹ተቃዋሚዎች›› ተግባር ምንድን ነው?

የፖሊስ ጭቆናዊ አስተዳደር በተንሰራፋበት ሃገር ውስጥ በተቀቃዋሚነት መቆም እጅጉን አስቸጋሪና አደገኛም ነው፡፡ የሜይ 2005ቱን ምርጫ ተከትሎ ሁሉም የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች፤በርካታ የሲቪክ ማሕበረሰቡ አመራሮች፤የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች፤የነጻው ፕሬስ አባላት፤ከያሉበት በመታደን ለሁለት ዓመታት ያህል ወህኒ ተጥለው ነበር፡፡ ላለፈው 6 ዓመታት ተቃዋሚ ፓርቲዎች ማንኛውንም እንቅስቃሴ ተነፍገውና ታግደው፤በጠበበው የፖለቲካ መድረክ ውስጥ እንዲሹለከለኩ ብቻ  ነበር የተፈቀደላቸው፡፡ ከዚያ ባለፈ ግን ተቃዋሚ የሆኑትን የነጻው ጋዜጣ ባለቤቶችና አባሎቻቸው፤ ሌሊችም የተቃዋሚ ደጋፊዎችና አባላት እየተገፉና ከመስመር እንዲወጡ ጫና እየተደረገባቸው፤ በገዢው ጭቆናዊ አመራር እየተሰቃዩ፤እየታሰሩ፤ ከሕብረተሰቡ ጋር እንዳይገናኙ እየተደረገ፤እነዚህ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች ተዳክመው፤ ሕዝባዊ ግንኙነታቸው እንዲቋረጥ አድርገውባቸው፤ ከገዢው ፓርቲ ጨቋኝ ስርአት የተለየ እንዳለና ተቃዋሚዎችም ለዚህ የቆሙ መሆናቸውን የሚያሳወቁበት መንገድ ባለመኖሩ ተዳክመዋል፡፡ በሌላም ወገን  አንዳንዶቹ ተቃዋሚዎች ተጠያቂነትን በመዘንጋት፤ግልጽነትን በመሸሽ ከአባሎቻቸው ጋር ተቃቅረዋል፡፡ ሌሎች ደግሞ ተቃዋሚ ነን እያሉ በውስጣቸው ግን ዴሞክራሲያዊነትን መቀበልና መተግበርን ስለሚፈሩት አቅቷቸዋል፡፡ ከዚያም አልፎ እራሰቸውን እንደሚቃወሙት ገዢ ፓርቲ ፈላጭ ቆራጭ በማድረግ የራሳቸውን የበላይነት ለማስጠበቅ ሲሉ በፓርቲው አባላት መሃል፤ ግጭትንና አለመግባባትን መቃቃርን ፈጥረዋል፡፡

በኢትዮጵያ ያሉትን ተቃዋሚዎች በምንም መልክ ይፈረጁ በምንም ፤በገዢው ፓርቲ አሸናፊ ነኝ አበባል የተጠቀሰው የ99.6 የምርጫ ውጤት ከ2005ቱ የተቃዋሚ ድርጅቶች አሸናፊነት ከተመዘገበው ሃገር አቀፍ ከፍተኛ ድል ጋር ሲተያይ እጅጉን የተለየና የውነትና የሃሰት ድል የታየበት የተቃዋሚዎች ብርታትም የተመሰከረበት ለመሆኑ አጠያያቂ አይደለም፡፡ ካለፈው የ6 ዓመት ሁኔታ የተቃዋሚው ፓርቲ አባላት ሊማሩና ሊያውቁ የሚገበቸው ጉዳይ ቢኖር ዝም ብሎ “መቃወም መቃወም፤ደሞም መቃወም”፤ ለመቃወም ብቻ ሊሆን አይገባም፡፡ የተቃዋሚዎች ሁኔታ ገዢውን ፖርቲና ፖለቲካዊ ዝግመቱንና ያለፈበትነትን መቃወም ብቻ ሳይሆን፤ከዚያም ባሻገር ማሰብ ይገባቸዋል፡፡ዋናው ዓላማቸው ለሃገራችን ዴሞክራሲያዊ አስተዳደርን እስከመዘርጋት ሊጓዝ የግድ ነው፡፡ ዘወትራዊ ተግባራቸው ሳይሰለቹና ሳይደክሙ ሊያከሂዱት የሚገባ ትግላቸው ግልጽነትንና ተጠያቂነትን አበክረው መጠየቅና ለዚያ መታገል ሊሆን ይገባል፡፡ የገዢውን ፓርቲ እለታዊ እንቅስቃሴ በማጤን አግባብነት የሌለውን በመጠየቅ ለመስተካከሉ መቆም፤ መታገል፤ ሂስ ማድረግና መተቸት፤ ያንንም ይፋ ማድረግ ሲኖርባቸው ከገዢው ፓርቲ የተሻለ አመለካከትና መመርያም በማውጣት ለሕዝቡ እያቀረቡ ብቃታቸውን ማረጋገጥ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ተቃዋሚዎች የገዢውን ፓርቲ ድክመት ብቻ እያነሱ ያንን መኮንን ብቻ ሳይሆን የነሱን የተሻለ ሃሳብም ማሰማት ይገባቸዋል፡፡

ገዢውን ፓርቲና አመራሮቹን በስድብ ክምር ማጥላላትን፤ጥርስን በመንከስ ማንኳሰስ የተቃዋሚውን ፓርቲ አስተሳሰብ ከፍተኛነት ከማቅለሉ ባሻገር ምንም ፋይዳ የለውም:: ተቃዋሚዎች ለተጠያቂነትና ለመልካም አስተዳደር ያላቸውን ሃሳብና ራዕይ ያዛንፍባቸዋል እንጂ የሚየስገኝላቸው ጠቀሜታም ሆነ ትርፍ የለውም፡፡ አብዛኛዎቹ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት በስልጣን ላይ ስላለው ገዢ ሃይል የሚጠቀሙበት ቋንቋ ቁጣ፤ፍርሃት፤የበታችነት ስሜትን የሚያሳይ፤ነው፡፡ ጥቂቶች ብቻ ናቸው እውነትን ይዘው በቆራጥነትና በሎጂክ የሚናገሩትና የሚሟገቱት፡፡ የገዢውን ፖሊሲዎች፤ፕሮግራሞችና ፕሮጄክቶች፤በሰከነ ጥናትና ግምገማ፤ በምርምር አቅርበው የሚናገሩና በምትኩም የተሸለ ጥናት የሚያቀርቡ ጥቂቶች ናቸው፡፡ ለምሳሌ ገዢው ፓርቲ የሃገሪቱን ለም መሬቶች በሽርፍራፊ ዋጋ ለውጭ ዜጎች መሸጡን ይፋ ያወጡትና ሕዝቡ እንዲያውቅ ያደረጉት ሃገራዊ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ሳይሆኑ መንግሥታዊ ያልሆኑ የዉጭ አገር ድርጅቶችና ተመራማሪዎች ናቸው፡፡ በተለያዩ የሃይድሮ ኤሌክትሪክ ግድቦች ሳቢያ የሚከሰተውን የአካባቢን ችግር በተመለከተም ጉዳዩን ይፋ ያደረጉት የውጭ አገር ተመራማሪዎች ናቸው፡፡ የኢትዮጵያን የኤኮኖሚ ፖሊሲውን ግምገማ፤ ምንነትና ድክመቱንም በተመለከተ ይፋ እያወጡ ጥናታቸውን ያቀረቡት የውጪ አበዳሪ አካላት ሲሆን ጥቅምን ከመጠበቅ አኳያ ጥናታቸው አጠያያቂ ነውና እውነታው ይፋ የሚሆነው በታወቁ የሚዲያ አጥኚዎች ነው፡፡ ገዢውን ፓርቲ በተጨባጭና በሃቅ ላይ በተመሰረተ የፖሊስና የፕሮግራም አቀራረጹን መተቸት ባለመቻላቸው ተቃዋሚዎቹ በሕዝቡ ዘንድ ተቀባይነትን ወደማጣቱ ደርሰዋል፡፡ የሚያስፈልገው የቃላት ውግዘት አይደለም፡፡ የሚያስፈልገው ክሪቲካል የሆነ ሚዛን የሚያነሳ ግምገማና የገዢውን ፓርቲ የፕሮግራሙን፤ የፖሊሲውን መክሸፍ በተጨባጭ ማሳየትና ለዚያም ማስረጃዎችንና ጥናቶችን በተገቢው ማቅረብ ነው፡፡ በዚህም ነው ሕብረተሰቡ  ከገዢው ፈላጭ ቆርጭ የተሸለና የተለየ ራዕይ ከተቃዋሚዎች ሊጠብቅና ሊያልም የሚችለው፡፡

ተቃዋሚ ፓርቲዎች ለምርጫ ውድድር  ከመዘጋጀት ባሻገር  ብዙ ሊጫወቷቸው የምችሏቸው ሚናዎች አሏቸው፡፡ የአባሎቻችውን የደጋፊዎቻቸውንና የጠቅላላውን ሕብረተሰብ ንቃተ ሕሊና ማዳበርና ለትግሉም ማዘጋጀት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ፖሊሲያቸውን በሚገባ በማዳረስና በማስረዳት ሕብረተሰቡን ማስተማር አለባቸው፡፡ ክርክርና ውይይት በማዘጋጀት፤በአስፈላጊ ርእሶች ላይ በመነጋገርና ሕዝቡንም ተሳታፊ ማድረግ ሁኔታዎችን እያነሱ ችግሮችን በማንሳትና መፍትሔዎችን በመጠቆም የሃገሪቱን የወደፊት ራዕይ መጠቆም አለባቸው፡፡ ሁኔታዎችን በማስተካከል የዴሞክራሲ ባሕል የሚዳብርበትን መንገድ ቀያሽ ሊሆኑ ይገባል፡፡ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ስኬታማ መሆን የሚችሉት ለወጣቱና ለሴቶች አስፈላጊውን የአመራር ስልጠና ለመስጠት ማቀድና መተግበር ይኖርባቸዋል፡፡ የብዙዎቹ  ተቃዋሚ ድርጅቶች አመራሮች ሃምሳውን ዓመት የዘለሉ ሲሆኑ በአመራሩ ላይ ያሉትም የሴቶች ቁጥር አናሳ ነው፡፡ ‹‹ዕድሜ ቁጥር እንጂ ሌላ አይደለም›› በወጣቱና በዕድሜ ጠገብ ፖለቲካ መሃል ግልጽ የሆነ ልዩነት አለ፡፡ ወጣቱ ትውልድ ታላቅ የመነሳሳት ፍላጎት፤ ቅልጥፍና፤ቆራጥነት፤ በዓላማው ላይ መራመድን ይቀይሳል:: ያንንም ተግባራዊ ለማድረግ ፈጣንና ቆራጥ ነው፡፡ ያደርገዋል፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከሚዲያውና ከሲቪል ማህበረሰቡ ጋር በመሆን ተቀናጅተው ወደ ሕዝቡ መድረስ አለባቸው፡፡

አልፎ አልፎም ተቃዋሚዎች በስልጣን ላይ ካለውም ሃይል ጋር በትክክለኛው ጉዳይ ላይ በመስማማት የሕብረተሰቡን ፍላጎት ማሟላት ይችላሉ፡፡ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በ2007 ላይ ሃሳባቸውን ሲገልጹ ‹‹ሃሳባቸው ኢትዮጵያን ከተዘፈቀችበት የችግር አረንቋ ማውጣት ብቻ ሳይሆን ›› በ “መልካም አስተዳደርና በዴሞክራሲ ግንባታም ላይ” ያተኮረ እንደነበር ተናግረዋል፡፡አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትርም የመለስን ራዕይ ተግባራዊ ለማድረግ መነሳታቸውንና ያም ዓላማቸው እንደሆነ በግላጭ ደጋግመው ቃል ገብተዋል፡፡ ሃይለማርያም የመለስን ራዕይ ለመተግበር ለመልካም አስተዳደርና ለዴሞክራሲ ግንባታ በሚያደርጉት እንቅስቃሴ አብሮ መሰለፍ ጉዳት የለውም፡፡ መልካም አስተዳደርን ለመገንባት፤ የፖለቲካ እስረኞች እንዲፈቱም ሰፊ የዴሞክራሲ ግናባታም እንዲሰፍን በማድረጉ በኩል ተቃዋሚዎች ሃይለማርያምን ተጠያቂ በማድረግ መንቀሳቀስ አለባቸው፡፡

ምን አይነት ተቃዋሚ ነው አሁን የሚያስፈልገው?   የገዢው መንግስት መኖርና የበላይነት የተረጋገጠለት በኢትዮጵያ ያሉት ተቃዋሚ ሃይላት ስምምነት ማጣትና ዘወትር እርስ በርስ መናቆር የተነሳ ነው፡፡ ተቃዋሚዎች ተካፋፍለውና የጎሪጥ በመተያየት በየፊናቸው ባይረግጡ ኖሮ ገዢው ፓርቲ እንደዚህ ተጠናክሮ ሕጉን እንዳሻው በማውጣትና በመለወጥ ሊዘባነን ባልቻለ ነበር፡፡ ስለዚህ ታዲያ ምን ዓይነት ተቃዋሚ ነው የሚያስፈልገው?

ታማኝ ተቃዋሚ? በአንዳንድ የፓርላማ ስርአት ውስጥ “ታማኝ ተቃዋሚ” የሚባለው በህግ አውጨው አካል አስተዳደራዊ ተግባር ውስጥ ያልተካተቱትን ለማለት ነው፡፡ በተግባራዊው የዴሞክራሲያዊ ፓርላማ ስርአት ውስጥ ግን የገዢውን ፓርቲ ፕሮግራምና ፖሊሲ ያለአንዳች ፍርሃትና ይሉኝታ፤መሳቀቅ በነጻነት እየተከታተለ በትክክሉ በማስተግበር በኩል ከፍተኛውን ሚና የሚጫወት ማለት ነው፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ግን ገዢው ፓርቲ የፓርላማውን ወነንበር 99.6ቱን ተቆጣጥሬያለሁ በሚልበት ሁኔታ ውስጥ ታማኝ ተቃዋሚ ጨርሶ ሊኖር አይችልም፡፡ የአንድ ብቸኛ ሰው ታማኝ ተቃዋሚ ሊኖር አይችልም፡፡

ጸጥተኛ ወይም የታፈነ ተቃዋሚ? በገዢው ክፍል ውስጥ ብዙ ዝም ያለ ወይም የታፈነ ተቃዋሚ አለ፡፡ የሚያስከትለውን ሁኔታ በመፍራት ብዙሃኑ የህብረተሰብ አባላት ለገዢው አካል ያላቸውን ተቃውሞ ከማንሳት ተቆጥበው አሉ፡፡ ገዢውን ፓርቲም ሆነ ወይም በውስጡ ያሉትን አመራሮች ላይ ተቃውሞ ቢያሰሙ ወይም አቃቂራቸውን ቢያመላክቱ ሥራቸውን ሊያጡ፤ከትምሕርት ገበታቸው ሊባረሩ፤የኢኮኖሚ ጫና ሊደርስባቸው አለያም ለባሰ መከራና ሰቆቃ ሊዳረጉ ይችላሉ፡፡ ሰዎች ገዢውን ፓርቲ እንቃወማለን በማለታቸው ብቻ ለእስር ይዳረጋሉ፡፡ በጣም በሚያስደንቅ ሁኔታ በቅርቡ አራት ሰዎች ‹‹እንኳንም መለስ ሞተ፤ ግልግል፤ በመሞቱ አላዘንም፤ መንግስት ሞቷል፤መንግስት የለም፤›› ብለው በአደባባይ በመናገራቸው ለእስር ተዳርገዋል:: (የነዚህን ሰዎች የክስ ሰነድ ለመመልከት (እዚህ ይጫኑ):: በጣም ብዙዎች በግላቸው ተቃዋሟቸውን የሚያሳዩ አሉ በአደባባይ ወጥቶ በይፋ ለመናገር ግን ክስንና እስራትን በመፍራት ታፍነዋል፡፡

ያልተደራጀ ተቃዋሚ? ማንዘራሽ፤ ያልተደራጀና ግልፍተኛ ተቃዋሚ በገዢው ፓርቲ ላይ አንዳችም ተጽእኖ ሊያሳድር አይችልም፡፡ የዚህን የመሰሉ ተቃዋሚ ምንም እቅድ ስለሌለውና ብቃቱም ስላመይኖረው ፖሊሲ የመንደፍም ችሎታ ስለማያገኝ ሕዝቡን አስተባብሮ ለማነሳሳት ጨርሶ ተቀባይነት የለውም::

የተከፋፈለ ተቃዋሚ?  የተከፋፈለ ተቃዋሚ ግልጋሎቱ ለገዢው ፓርቲ የመኖር ሕልውና መሆን ነው፡፡ የገዢው ፓርቲ ሃይልም ሆነ ተቃዋሚውን አሳንሶ ማየትና እንዳሻው መሆን ዋናው መሳርያና ምክንያት የተከፋፈለ ተቃዋሚ ነው፡፡

የተባበረ፤አቋሙ የተስተካከለ፤ዴሞክራሲያዊ ተቃዋሚ? ለኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት ይሄ ነው፡፡ እንዲህ አይነቱ ተቃዋሚ ታዲያ በመቻቻል በስምምነት በመግባባት ላይ መሰረቱን ያዋቀረ የተባበረና የብዙሃኑን ፍላጎትና ራዕይ መሰረት ያደረገ ተቃዋሚ ሃይል ነው፡፡ ሕብረቱ በሕዝቡ ፍላጎትና እምነት ላይ መሰረቱን ያደረገ ሲሆን ሂደቱ ለምርጫ ውድድር መዘጋጀት ብቻ ሳይሆን ሰፊ ምህዳር ያለው ፖሊሲ በመቅረጽ የሰፋ ውክልና ሊኖረው የሚችልና ለምርጫውም ቢሆን ሰፊ ድጋፍ የሚቸረው ሕዝባዊ ተቀባይነትና አመኔታ የተጣለበት አለኝታ ይሆናል፡፡ በሕብረት ውስጥ ሰፊ የሆነ ሃሳብና እቅድ የሚቀርብ በመሆኑ ይህንንም ወደ ተግባር ለመለወጥ የከረረ ውይይትና እሰጥ አገባ ተካሂዶበት ወደ ዴሞክራሲያዊ ውሳኔ ስለሚደርስ የአብዛኛውን ሕዝብ ፍላጎት የሚያካትት ዓላማቸውን የሚያስፈጽም በመሆኑ ሊፈጠር የሚችለውን አለመግባባት ሁሉ በውይይት ፈትቶ ለውሳኔ ይደርሳል፡፡ የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ፓርቲ እራሱን በሕብረት በሚያጣምር ፖሊሲ ላይ በማጠናከር መቆም ሲችልና በአንድነት አንድ ሆነው ሲንቀሳቀሱ ገዢውን ፓርቲና ፖሊሲዎቹን ለመሞገት ብቃት ይኖረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ተግባሩ ምን ሊሆን ይገባል? የ2010ን ምርጫ አስከትዬ የምክር ሃሳቤን ለኢትዮጵያ ተቃዋሚዎች አቅርቤ ነበር::  በወቅቱ ምክሬ አንድም ተቀባይ ያገኘ አይመስለኝም፡፡ እኔ ደግሞ ያመንኩበትን በይሉኝታ ለመቀልበስ ዝግጁ አይደለሁም፤እና አሁንም ደግሜ ያንኑ ምክሬን በማጠናከር የፖለቲካ ጨዋታው መለወጡን እየጠቆምኩ የገዢው ፓርቲ ግን ተደጋጋሚ የማስመሰያ ቃላት ከመሰንዘር ባለፈ ምንም ለውጥ ያለሳዩ ናቸውና እንደነበሩት ለመቀጠል ነው ሃሳባቸው፡፡ ባልታሰበ መንገድ ሁኔታዎች መለወጥ ጀምረዋል:: ይህ ጅማሮም በፈጠነ ሂደት ላይ መጓዙን አጠናክሮ ከፈላጭ ቆራጭ አገዛዝ ወደ ዴሞክራሲ ለውጥ ጉዞውን መቀጠሉ ማቆሚያ የሌለው ነው፡፡ በምድር ላይ ምንም አይነት ሃይል ይህን የለውጥ ጅማሬ ሊያቆመው ጨርሶ አይችልም፡፡ በስላጣን ላይ ያሉት ፈላጭ ቆራጭ ገዢዎች ባሻቸው መንገድ ሊያከሽፉትና ለራሳቸው እንዲመች ለማድረግ ቢጥሩ ከፈላጭ ቆራጭ ወደ ዴሞክራሲያዊ ስርአት ለውጡን ማቆም ምኞት እንጂ ተግባራዊ ሊሆንላቸው አይችልም፡፡ አሁን የቀረውና መልስ የሚፈልገው አንድ ጥያቄ ብቻ ነው፡፡ እገሌ እገሌ ተገሌ ሳይባል ሁሉም በገዢው ፓርቲ የተጨቆኑና የግፍ ሰለባ የሆኑ ተቃዋሚ ሃይላት ማሕበራት፤ የሰብአዊ መበት ተሟጋቾች፤ የዴሞክራሲ ናፋቂዎች፤ ሁሉም በአንድነት ከግፍ አገዛዝ ወደ ዴሞክራሲያዊ ስርአት በኢትዮጵያ ለሚደረገው ሂደት ምን ማድረግ ይጠበቅባቸዋል?

ከሕዝቡ ጋር ይቅር ለእግዚአብሔር ተባብሎ እርቅ መመስረት ፤ በ2005 በተካሄደው ምርጫ የተሳተፉት የተቃዋሚ ፓርቲዎች አመራሮች ሁሉም ወደ ሕዝቡ ተመልሰው፤ ባለፈው  ተስፋውን፤ ሕልሙን፤መነሳሳቱን ያጨለሙበትን ሕዝብ ይቅርታ በመጠየቅ እርቅ ሊያደርጉ ተገቢ ነው፡፡ ለሕዝቡም ያለምንም ይሉኝታ ‹‹ባለፈው አሳዝነናችኋል፤ በዚያም በምር አዝነናል፤ ከናንተም ያጣነውን አመኔታና ድጋፍ ለማግኘት እንድንችል ጠንክረንና ካለፈው ተምረን እንክሳችኋለን›› ለማለት ብቃቱና ወኔው ሊኖረን የግድ ነው፡፡ ሕዝቡ ከተቃዋሚ መሪዎች ቅጥ ያለው ይቅርታ ይገባዋል፡፡ ይህንንም ቢያደርጉ የኢትዮጵያ ሕዝብ ጨዋ፤ ይቅር ባይ፤መሃሪ፤ አዛኝ ነውና ይቅር ይላቸዋል፡፡

ካለፈው ስህተት መማር፤ ካለፈው ስህተታቸው መማር የማይችሉና ፍቃደኝነቱም የሌላቸው ያንኑ ያለፈውን ስህትታቸውን መድገማቸው አይቀሬ ነው፡፡ ባለፈው በተቃዋሚዎች በርካታ ስህተቶችና ወድቀቶች ተከናውነዋል፡፡ እነዚህ ስህተቶች ተነቅሰው ሊወጡ ይገባል፡፡ ከነዚህም ስህተቶች በመነሳት ላይደገሙ ትምህርት ሊወሰድባቸውና ዳግም እንዳይመጡም ሊገቱ ተገቢ ነው፡፡

የተቃዋሚውን ተቃዋሚዎች ማወቅ፤ የተቃዋሚዎች ተቃዋሚዎች ቸል ሊባሉ አይገባም፡፡ ሃይላቸው ከፋፍሎ በመግዛትና በብሔር በማለያየት ድብ ድብ ጨዋታ ነው፡፡ ተቃዋሚዎች ተሰባስበውና ተባብረው አንድ ቢሆኑባቸውና አንድ የጋራ አጀንዳ ቢኖራቸው ገዢዎቹ የተቃዋሚ ተቃዋሚዎች አቅመቢስ ልፍስፍስ ናቸው፡፡

ተጎጂነትን ማቆም፤ ከተቃዋሚዎች ጥቂቶቹ ‹‹የተጎጂነት አስተሳሰብ›› ይዘዋል፡፡ ማንም ሰው የተጎጂነት ስሜት ሲያድርበት ከተግባርና ከሃላፊነት ይርቃል፡፡ ስለታሰሩት ጋዜጠኞች በቅርቡ ለተደረገለት ቃለመጠይቅ በሰጠው ይፋ መግለጫ ላይ ሃይለማርያም መልስ ሰጥቶ ነበር፡፡ ለአሜሪካን ድምጽ በሰጠው ምላሽ ላይ በሃገሪቱ ያሉት የፖለቲካ እስረኞች ‹‹ሽብርተኞች›› ና ከተወገዙ ድርጅቶች ጋር ሁለት ባርሜጣ አድርገው የሚሰሩ ናቸው፡፡ አንደኛው ‹‹ሕጋዊ›› ሌላው ደግሞ ‹‹ሕገወጥ››፡፡ የፖለቲካውን መድረክ ለመክፈትና ለማረጋጋት ስላለው ሃሳብ ምንም አላለም፡፡ ያም ሆነ ይህ ሃይለማርያምም ሆነ ገዢው ፓርቲ ያሻቸውን ይበሉም፤አይበሉም ተቃዋሚዎች ሳይደክሙና ሳያስተጓጉሉ አበክረው ሁሉም የፖለቲካ እስረኞች እንዲፈቱ መጠየቃቸውን መቀጠል አለባቸው፡፡ ተጠያቂነት ማለትም ይሄው ነው፡፡ ተቃዋሚው ሁል ጊዜ ለትክክለኛው ጉዳይ መቆም አለበት፡፡ የፖለቲካ ሰዎችን ከወህኒ መልቀቅ ትክክል ነው፤  በወህኒ ማጎር ግን ስህተት ነው፡፡

በመንስኤዎችና በጉዳዮች ላይ የጋራ አጀንዳ ማዘጋጀት፤ በሁሉም ተቃዋሚዎች ተቀባይነት ያለው የዴሞክራሲ፤የሰብአዊ መብት፤የሕግ የበላይነት፤የሕዝቦች አንድነት፤የኢትዮጵያ ሕዝቦች ጥምረት ነው ማዕከሉ፡፡ እነዚህን ጉዳዮች ለማገዝና ለማራመድ የሚሆን አጀንዳ በጋራ መቅረጽ ምን ችግር አለው?

ከስምምነቱ ሳይርቁ ላለመስማማት መስማማት፤ ይሄን ‹‹ከኔ ሃሳብ ጋር መቶ በመቶ ካልተስማማህ ጠላቴ ነህ›› የሚለውን ጎጂ እምነት የተቃዋሚ አመራሮችና ደጋፊዎቻቸው፤ጨርሰው ማጥፋት አለባቸው፡፡ ከህሊናቸው ጋር ያሉ ሰዎች በሃሳብ ባይስማሙ ምንም ማለት አይደልም ጉዳትም የለውም፡፡ እነዚህ ደግሞ የዴሞክራሲ ባህሪ ናቸው፡፡ ተቃዋሚው በውስጡ የሃሳብ ልዩነትን ሳይቀበል የገዢውን ፓርቲ መቻቻልን አለመቀበል ሊያወግዝ ተገቢ ነው?

ግለሰብተኝነት ተመላኪነትን መከላከል፤ በኢትዮጵያ ተቃዋሚዎች ሂደት ውስጥ በጣም አስቸጋሪው ጉዳይ የሆነው የግለሰቦች ተመላኪነት ነው፡፡ በተለያየ ጊዜ በተደጋጋሚ ተቃዋሚው ጀግኖችን በመፍጠር እነሱን ከምንም በላይ አድርጎ በመመልከትና ለማመን በሚያስቸግር ሁኔታ እያሞካሸና እያሞገሳቸው ከማምለክ ባልተናነሰ መጠን ከበሬታ ሰጥቷቸዋል፡፡ ይህንን ባደረግን ቁጥር ደግሞ የወደፊት ፈላጭ ቆራጭ ገዢዎች እያሳደግን መሆኑን መዘንጋት የለብንም፡፡

ዘወትር በቀናነት መንቀሳቀስ፤ ተቃዋሚዎችም ሆኑ አብረዋቸው የተሰለፉት ሁሉ በቀና መንገድ መጓዝን መልመድ አለባቸው፡፡ ግለሰባዊም ሆነ ድርጅታዊ ግንኙነታቸው በቀናነት የተመሰረተ ሊሆን ይገባል፡፡ የምንለውን መሆንና የምንሆነውን ማለት ይገባናል፡፡ የአንድ ሰው ግለኛ የበላይነት ከማያስፈልግ ደሴት ውስጥ ያስቀምጠናል::

በጥቅሉ እያሰብን፤ተግባራችን ወቅታዊ፤ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ የሚደረግ ትግል ምርጫን ማሸነፍ አለያም የስልጣን እርካብን ረግጦ ለሕዝባዊ ቢሮ መብቃት ብቻ አይደለም፡፡ ትግሉ ለታላላቅ ጉዳዮች ነው፡፡ ዘላቂነት ያለው ዴሞክራሲያዊ መሰረት ለመዘርጋት፤በኢትዮጵያ ሰብአዊነትን ማክበርና መጠበቅ እንዲሁም ተጠያቂነትንና የሕግን የበላይነት በአግባቡ አክብሮ ማስከበር፡፡ ይህንን እውነታ አምነን ከተቀበልንም ትግሉ አሁን ላለነው ለኛ ብቻ ሳይሆን፤ለሚመጣው ትውልድም ጭምር ነው፡፡ የምናደርገው ሁሉ ከኛ አልፎ ለተተኪዎቹ ልጅ ልጆቻችን የሚተላለፍ ኢትዮጵያችን ውድና የምትናፈቅ፤ ኖረንባት የማንጠግባት እንድትሆን በማድረግ ነው፡፡

ወጣቱ ትውልድ ለመሪነት እንዲበቃ ዕድሉን መስጠት፤  በተቃዋሚ ፓርቲ ውስጥ ያለን የእድሜ ባለጸጎች ብዙዎቻችን ለመቀበል የሚያስቸገረን  ጉዳይ አለ፡፡ ያም ችግራችን ቦታውን መልቀቅና ለወጣቱ ማስረከብን መማርና መቀበል አለብን፡፡ ለወጣቱ አመራሩን እንዲይዝ ዕድሉን እንስጠው፡፡ ወደድንም ጠላንም መጪው ዘመን የእነሱ ነው፡፡ ከኛ ስህተቶች እንዲማሩ ብናግዛቸውና ወደበለጠ አስተሳሰብና ዘዴ እንዲዘልቁ ብናደርግ በእጅጉ ተጠቃሚዎች እንሆናለን፡፡ በዓለም አቀፍ ተቀባይነትን ያገኘው ወጣቶችን የሚመለከት አንድ እውነታ ቢኖር፤ ከምንም በላይ ነጻነትን መውደዳቸው ነው፡፡ የመጀመርያዋ የሴት ፖለቲካ መሪ የሆነችው ብርቱካን ሚዴቅሳ ትለው እንደነበረው፤ የዕድሜ ባለጸጋ የሆኑት መሪዎቻችን እኛ ተማሪዎቻቸውና ተረካቢዎቻቸው ለምንገነባት ‹‹የወደፊቷ ሃገር ኢትዮጵያ›› እነሱ ውሃውን ያቀብሉን እኛ ከዚያ ባሻገር ያለውን ሁሉ እያደረግን ሃገርን እንገንባ፡፡

ሃሳባችን እንደ ድል አድራጊ እንጂ እንደ ተሸናፊ አይሁን፤ ድል፤ ድል አድራጊዎች እንደሚያስቡት፤ ሽንፈትም ተሸናፊዎች እንደሚያስቡት አይደለም፡፡ በድል ውስጥ ሽንፈት እንዳለ ሁሉ በሽንፈት ውስጥም ድል ይገኛል፡፡ በ99.6 ምርጫውን ድል ያደረጉት በገጽታቸው ላይ የአሸናፊነት ምስል ይታይባቸዋል፡፡ የተገኘው ድል ግን በተንኮልና በቅሚያ፤ በእፍርታምነት የተገኘ መሆኑን አስረግጠን እናውቃለን፡፡ ዋናው ቁም ነገር ግን ተቃዋሚዎች እንደ አሸናፊ ስብስብ ወይም ተሸናፊ መመልከቱ ላይ ነው፡፡ አሸናፊዎች እንደአሸናፊ ያስባሉ ተሸናፊዎችም በተቃራኒው፡፡

የተቃዋሚው ጎራ እራሱን እንደገና መፍጠር አለበት፤ ገዢው ፓርቲ ምንም እንኳን የለውጥ ፍንጣቂም ባያሳይ ደጋግሞ ግን በየሕዝባዊ ንግግሩ፤እራሴን እንደገና እያደስኩ ነው ይላል፡፡ ያም ሆኖ ግን ‹‹ምንም የሚለወጥ የለም›› ማለታቸውን ከቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ጊዜ ካለው ሁኔታ አሁን ምንም ለውጥ አይኖርም ነው የሚሉት:: ተቃዋሚዎችም ቢሆኑ እራሳቸውን እንደገና መፍጠር አለባቸው፡፡ ለውጣቸውም እራሳቸውን ለዴሞክራሲያዊ እውነታ በማሰገዛት፤ሕዝቡንም በጠራ አመለካከት ላይ በማሰለፍ ሕብረትና አንድነት፤ መግባባትና መተሳሰብ ጠቀሜታው ታላቅ እንደሆነ ተገንዝቦ በማስገንዘብ፤ ድርጅታዊ ሃላፊነቱም በሕዝቡ ፈቃደኛነት ላይ የተገነባ መሆኑን በማረጋገጥና ሁል ጊዜም ዓላማቸው ለትክክለኛው ሁኔታ በመቆም በሃይል የሚደረገውንና አድራጊውንም ለመዋጋት መቆማቸውን በማረጋገጥ ላይ ሊሆን ይገባል፡፡

ተቃዋሚው ጨርሶ ተስፋ መቁረጥ አይገባውም፤ ሰር ዊንሰተን ቸርችል ‹‹ፈጽሞ እጃችሁን አትስጡ:: ፈጽሞ ፈጽሞ ፈጽሞ በምንም መልኩ ቢሆን::  በትልቅም ይሁን ትንሽ ፈጽሞ ፈጽሞ እጃችሁን አትስጡ!! ለክብርና ለመልካም ስሜት በታማኘነት ካልሆነ በስተቀር ፈጽሞ ፈጽሞ!! ሃይል አለኝ ለሚለው አትንበርከኩ:: ከአፍ እስከ ገደፉ ለታጠቀው ጠላትና አብረውት ሽር ጉድ ለሚሉት ሾካኮች ፈጽሞ እጅ አትስጡ!!››  የኢትዮጵያ ተቃዋሚዎች ይህን ስልት ነው መከተል ያለባቸው እንጂ ለገዢው ፓርቲ አካኪ ዘራፍና የግፍ አፈና ሊሸነፉ አይገባም፡፡ ፈጽሞ ፈጽሞ ፈጽሞ!! ድል አድራጊዎች መንገዳቸው ይሄ ብቻ ነው፡፡

የተቶረገመው ጽሁፍ (translated from):

http://open.salon.com/blog/almariam/2012/09/30/ethiopias_opposition_at_the_dawn_of_democracy

(ይህን ጦማር ለሌሎችም ያካፍሉ::)

ካሁን በፊት የቀረቡ የጸሃፊው ጦማሮችን  ለማግኘት እዚህ ይጫኑ::

http://www.ecadforum.com/Amharic/archives/category/al-mariam-amharic

http://ethioforum.org/?cat=24

Similar Posts

Leave a Reply