የሠላም ራዕይ ለኢትዮጵያ – ከፕሮፌሰር ዓለማየሁ ገብረማርያም

Click here for PDF

ከፕሮፌሰር ዓለማየሁ ገብረማርያም
ትርጉም ከነጻነት ለሃገሬ

ፕሬዜዳንት ኔልሰን ማንዴላ ባለፈው ሳምንት 94 ዓመታቸውን አከበሩ፡፡እግዚአብሔር ረጂም ዕድሜንና ጤናን ይስጣቸው፡፡

ፕሬዜዳንት ማንዴላን የሚያከብሩና የሚያፈቅሩ ሰዎች ‹‹ማዲባ››ብለው ይጠሩዋቸዋል፡፡እሳቸውም የሰብአዊ ፍቅር ተስፋ፤ ትእግስት፤ራዕይ ናቸው፡፡ ደቡብ አፍሪካ በጭለማው ሰአትNelson Rolihlahla Mandela ማዲባ ከጭለማ እስር ሲወጡ ፈገግታ ለብሰው፤ በእጃቸው ሻማ ይዘው ሕዝባቸውን አፓርታይድ ከሚባል እስር ቤት ለማውጣት ተዘጋጅተው ነበር፡፡ደቡብ አፍሪካ ሕዝቦቿ ጦር አስልተው ለመጋደል ሲዘጋጁ፤ማዴባ ነሃል ገብተው ‹‹አንተም ተው አንተም ተው›› ብለው እጅ ለእጅ አያይዘው፤ አጨባብጠው፤ ጦራቸውን፤ቀስታቸውን፤ጎራዱያቸውን፤አቅልጠው አዲሲቷን ደብብ አፍሪካ መገንቢያ ብረት እንዲሆን አድርገዋል፡፡ይሄንንም ሲያደርጉ ያሉት ‹‹መቼም፤መቼም ፤መቼም ቢሆን፤ሃገራችን ውስጥ አንዱ አንዱን ቀጥቅጦ ሊገዛ፤ ካሁን በኋላ አይችልም›› ነበር፡፡ የዓለም ሕዝብ በስራቸው ተደንቆ ሲመለከት ማዴባያሉት ‹‹ እኔ እኮ መልአክ አይደለሁም ምናልባት ሙከራ የሚያደርግ ሃጢአተኛ መልአክ ነው ብላችሁ ካላመናችሁ፤በስተቀር፤መላክ ለመሆን የምሞክሩ ሃጥአን የአፍሪካ መሪዎች ብናገኝ እንዴት ደስ ባለን ነበር::››

እኔ ከማዴባ ጋር ሃሳባዊ ንግግር ብዙ ጊዜ አደርጋለሁ፡፡በግንቦት 2011 ላይ በሳምናታዊ ጦማሬ ላይ ስለአንደኛው ንግግሬ ለአንባቢዎቼ አቅርቤ ነበር፡፡ በችኮላ መንፈስ፤ማዴባን እንዲህብዬ ጠየቅኋቸው ‹‹የአፍሪካ ፈላጭ ቆራጮች ለምን ይሆን የሚደነፉት?›› መልሳቸውም በደቡብ አፍሪካ ላይ የተወሰነ ነበር፡፡ እንዲህ ነበር ያሉት ‹‹ፈጽሞ ፈጽሞ ፈፅሞ፤ ይህች ውበት የሞላት ሃገራችን፤አንዱ ሌላውን ቀጥቅጦ የሚገዛባት ሃገር አትሆንም›› ነበር ያሉት፡፡ቀጥለውም ‹‹ግን›› አሉ፤‹‹የውቧ ሃገራችን ህልማችን የምትደርስበት ቦታ በይቅርታ ባይነትና በጥሩ ልቦና ስንሄድ ብቻ ነው፡፡››

ሕልምና ቅዠት ስለ ውቧ ኢትዮጵያ

የሰብአዊ ተሟጋችና የምሁር  ለሰሚ መናገር እውነትን ለስልጣን ያዦች መከሰትና ወደፊት ካለፈው ይሻላል የሚለውን ተስፋ ይዞ መጓዝ ነው፡፡ እውነተኛ የሰብአዊ መብት ተሟጋች የፖለቲካ ስልጣን ፍላጎት የለውም፡፡ የሰብአዊ መብት ፖለቲካ፤ የሰው ልጅ ክብርና ሞገስ መጠበቅ ፖለቲካ ነው፡፡ ስለ አይዲዎሎጂ አለያም ወገናዊነት ፖለቲካ ወይም የሥልጣን ሽሚያ አይደለም፡፡የሰብአዊ መብት ተሟጋች ስለወደፊት ተስፋ ነው የሚያተኩረው፡፡ ቫክላክ ሃቬል የቼክ ፕሬዜዳንትና ሰብአዊ መብት ተሟጋች ሲናገሩ ‹‹ተስፋ የአእምሮ ግንዛቤ ነው፡፡ በጥልቀት ስናየው ተስፋ የአእምሮ ግንዛቤ ነው፡፡ጠልቀን ስናየው ደግሞ ተስፋ መደሰት ማለት አይደለም፤ተስፋ አንድ ጥሩ ነገርን ማድረግ ነው ብለዋል፡፡አንድ የሰብአዊ መብት ተሟጋች፤በሚያደርገው ድርጊት ለሚያገኘው ለጥቅም ወይም የገነነ ስም አይደለም፡፡ የፈጠነ የፖለቲካ ለውጥም ይመጣል ብሎ አይደለም፡፡ ሃቫል እንዳሉት አንድ ጥሩ ነገርን ማድረግ፤ ያ ነገር በርግጥ ሁኔተኛ ይሆናል በማለት አይደለም፡፡ ባለፉት ዘመናት ስለ ሰብአዊ መብት በኢትዮጵያ ስጮህ ፈላጭ ቆራጮቹን ስቃወም፤የማደርገው ድርጊት ፈጣን ውጤት ያመጣል ብዬ አይደለም፡፡ወይም በአንድ ሌሊት መዋቅሩ ይለወጣል በማለት አይደለም፡፡ለረጂም ጊዜ ስለ ሰብአዊ መብት የተናገርኩት፤ የጻፍኩት፤የተሟገትኩት መልካም ጥሩ ነገር በመሆኑ ነው፡፡

በቅርብ ጊዜ ኢትዮጵያ ውስጥ ይሆናሉ አይሆኑም የሚሉ ቅዠቶች እየተከሰቱ ነው፡፡ውቢቷ ኢትዮጵያ የት ትደርሳለች የሚል ሕልም በብዛትም አይሰማም፡፡ ሹክሹክታውም ኢትዮጵያ ከመለስ በኋላ ወደ የርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ልትወድቅ ትችላለች የሚሉ አሉ፡፡ ግን በእግዜር አይንም ሆነ በሰው የኢትዮጵያ እድል ከአንድ ሰው እጣ ጋር የታሰረ ሊሆን አይችልም፡፡ ሌሎች ደሞ ስለ መአት እያወሩ፤በንዴትና በማማረር ይበሳጫሉ፡፡ ግን የሚታያቸው ጀንበር የሚጠልቅበትን ስርአት እንጂ ጸሃይ የምትፈነጥቅበትን አዲሱን ቀን፤ለማየት አልተቻላቸውም፡፡እንዲሁም ሌሎች ስለመከፋፈል፤ መበታተን፤መቃቃር፤ሲረበሹ ይደመጣሉ ይታያሉ፡፡ ቤተሰብ በቋንቋ፤በባህልና በሃይማኖት መተሳሰራችንን የዘነጉት ይመስላል፡፡ ሌሊች የሚያስጨንቃቸው፤በአንድ ሰው ጀርባ ላይ የተመሰረተ መንግስት ምን እንደሚደርስበት ነው፡፡ ሁሉም ግን ለሚገምተው፤ ለሚያስበው፤ ለሚመኘው፤ ለሚጨነቀው መልሱ “አረ አለሁ በነፍስ፤ እኔ መለስ” ሊሆን ያችላል፡፡ ግን ይህን ያህል አንድ ሐሙስ ለቀረው መንግስት አስፈላጊና አሳሳቢ ነው?

ይህ ዓመት ሲጀመር ‹‹ኢትዮጵያ ከፈላጭ ቆራጭ አገዛዝ ወደ ዴሞክራሲ›› በሚል ርእስ አንድ መጣጥፍ እያቀረብኩ ነበር፡፡ አንዱ ጦማሬ ላይ፤ እንዳልኩት በፈላጭ ቆራጭና ዴሞክራሲያዊ ሽግግር ድልድል ላይ ብዙ አታላዮች፤ ወንበዴዎች ሥልጣን ለመስረቅ ይዘጋጃሉና ከባድ ጥንቃቄ ያስፈልጋል ብዬ ነበር፡፡ ባለፈው ወር ደግሞ ቀደም ያለ ሕገመንግስታዊ ንግግር እንጀምር ምክንያቱም የለውጥ ጊዜ እየተከሰተ ነው ብዬ ነበር፡፡በቅርብ ጊዜ የሚታዩ እውነታዎች ከፍተኛ ለውጥ በኢትዮጵያ እንደሚከሰት ነው ሁኔታው የሚያመላክተው፡፡ አንዳንዶች ኢትዮጵያ የምትወድቅበት ሁኔታ ቢያቃዣቸውም እኔን ደግሞ ከባድ ሃሳብ ላይ የጣለኝ የተቃዋሚው ቡድን፤ አንድ ሰው ስለ ኖረና ስላልኖረ የሚያደርጉት ነገር ነው፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ የስርአት ለውጥና ሽግግር ሁሌም ክፉኛ አስቸጋሪ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ታሪክ ይህን ይመሰክራል፡፡ ከንጉሳዊ አገዛዝ ወደ ሶሻሊዝም የነበረው ሽግግር በጣም አስከፊ ነበር፡፡ በሶሻሊዝም ስም በሚሊዮን የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን ህይወታቸው አልፏል፡፡ ከሶሻሊዝም ወደ ሪቮሊውሽናሪ ዴሞክራሲ ደግሞ አናቂና ሰላቢ መንግስት ይሄው በአፍሪካ ታይቶ የማይታወቅ ፈላጭ ቆራጭ ግፈኛ መንግስት ለ21 ዓመታት ተቀምጧል፡፡ በ1977 የታየው የዴሞክራሲ ብርሃን በአንድ አፍታ ጠፍቷል፡፡ አሁን ሕዝብን እስረኛ ያደረገው ስርአት፤ ጸሃይ እየጠለቀችበት ነው፡፡ የእስረኞቹም ዋና ሹም መጋረጃ ወደ መከናነብ እያመራ ይመስላል፡፡

ሆኖም በሃገሪቱ የእሳተ ገሞራ ፍንዳታ እየተከሰተ ነው፡፡አነስተኛ ፍንዳታዎች በየቦታው ይታያሉ፡፡ ያለው ሁኔታ ሕዝቡን አስከፍቶታል፡፡ ሙስናው፤ስልጣን አለአግባብ መጠቀም፤ ያስተዳደር ጉድለት በገሃድ ይታያሉ፡፡  ይህን በአረብ ሃገሮች የሚደረገውን ለውጥ ስንመለከት ያሉት ገዢዎች ከፍ ያለ የሃሳብ ስጋት ሳይደርስባቸው የሚቀር አይመስለኝም፡፡ ሆኖም ቅሉ የጨቋኞቹ ስርአት ምን ይድረስበት አይድረስበት ብዙም አያስጨንቀኝም፡፡ የሚያስጨንቀኝ የተቃዋሚ ቡድኖች ምን እንደሚያደርጉ ነው፡፡እንደተለመደው የተገኘውን እድል ለማጣት ይጥሩ ይሆን? እኔ ብቻ ላሸንፍ ሌላው ይውደቅ ይሉ ይሆን? አንዱ ሌላውን እኔ ከሱ ልብለጥ የሚል ሂደት ይከተሉ ይሆን? ወይስ አንዱ ሌላውን፤ በብልጠት፤ ባሻጥር፤በዘዴ ለማሸነፍ ይሞክሩ ይሆን?

አለዚያስ ከፍ ብለው ይነሱስ ይሆን? አንዱ ሌላውን ይቅርታ ይጠይቅ ይሆን? አብረን ለሃገራችን እንስራ ይሉ ይሆን? ከሁሉም በላይ በወንድምነትና እህትነት እጅ ለእጅ ተጨባብጠው የያዙትን ጦርና ቀስት ወርውረው ኢትዮጵያን ለመገንባት ይዘጋጃሉ ይሆን?፡፡ማዴባ ያሉትን ተቀብለው በስራ ላይ ያውሉ ይሆን? ይሄ ነው የሚያሳስበኝ፡፡ ‹‹ነጻነት ጎህ ቀዳ ስትወጣ ስራችንን በበለጠ አጠናክረን መስራት አለብን፡፡ነጮችንም ያገራችንንም ልጆች አስገብተን ደቡብ አፍሪካን እንዲገነቡ ማድረግ አለብን፡፡ይህ የነጻነት ንቅናቄ የናንተም ነው ልንላቸው ይገባል፡፡›› እናዳሉት ማዴባ!

ሃጢአቱን እንጂ ሃጢአተኛውን አንጥላ

ጋንዲ ሲጽፍ፤የሰው ልጅ ሁለት ባህሪ አለው፡፡ ጥሩ ሲሰራ ማመስገንና ክፉ ሲሰራ ደግሞ መንቀፍ ነው፡፡ ያም ሆኖ የሰውን መጥፎ ስራውን መጥላት እንጂ ሰውዬውን መጥላት ተገቢ አይደለም፡፡ አንዱ ሌላውን በዘሩ፤ በቀለሙ፤በቋንቋው፤በሃይማኖቱ፤ቢጠላው ትርፉ ብዙ ጥላቻ ብቻ ነው፡፡ ማዴባ ሲናገሩ፤‹‹ማናቸውም የሰው ልጅ ሲወለድ ጥላቻ ይዞ አይደለም፡፡ ሰው ጥላቻን ተምሮ ነው ያገኘው፡፡የሰው ልጅ በተመሳሳይ መንገድ ፍቅርንም ሊማር ይችላል፤ ምክንያቱም ፍቅር ከተፈጥሮ ጋር የሚመጣ ጸጋ ነውና!፡፡” ይህም ከሆነ የጥላቻ ትምህርትን አለመማር ይቻላል በቦታው ፍቅርንም በሃገር ማስተማር ይቻላል፡፡

የጋንዲን ትምህርት መማር ተገቢ ነው፡፡ በጥላቻና በክፋት የተሰሩ ነገሮች ስሪታቸው ከመቃብር በላይ ለረጂም ጊዜ ይኖራል፡፡ ክፋትን ተከትለን ክፋትንም ከሰራን ቅዱስ ወንጌል እንደሚለው ‹‹ቤቱን የሚያውክ ሰው ነፋስን ይወርሳል፤ ሰነፍም ለጠቢብ ተገዢ ይሆናል››ይላል፡፡ ጥፋትንና ተንኮልን ተንኮለኞችንና አጥፊዎችን ከተከተልን እኛም ነፋስን እንወርሳለን፡፡ ነፋሱም ያገራችን መዋቅር ሊገነጣጠል ይችላል ሆኖም ሃጢአቱ ላይ አተኩረን አብረን ኤሎሄ ኤሎሄ ብንል የምንወርሰው ከፈላጭ ቆርጭነት አገዛዝ ዴሞክራሲ፤ ከሰብአዊ መብት ጥሰት፤ሰብአዊ መብት ክብረት፤ከጥላቻ ፍቅርን፤ ከንትርክ ይቅርታን እንወርሳለን፡፡ በስልጣን ቁንጮ የተቀመጡትም ማወቅ ያለባቸው ለውጥ መውጣቱ እንደማይቀር ነው፡፡ ሰላማዊ ለውጥ ሊመጣ ይችላል፤ ብልህ ከሆንን የምንተሳሰብ ከሆንን:: ግን ለውጡ መምጣቱ አይቀሬ ነው፡፡

በኢትዮጵያ አሁን ስንት ሰአት ነው

ቅዱስ ወንጌል እንደሚለው ‹‹ለሁሉም ጊዜ አለው›› ለፍቅር ጊዜ አለው፤ ለጥላቻ ጊዜ አለው፤ለጦርነትም ሆነ ለሰላም ጊዜ አለው፡፡ አሁን ለኢትዮጵያስ ጊዜው ምንድን ነው? …ጊዜው የሰላም ነው፤ጊዜው ከመራራነት ወደ መግባባት የሚለወጥበት ሁነኛው ወቅት ነው፡፡ጥላቻን ጥሎ መፈቃቀርያ ጊዜ ነው፡፡የተስፋ የእምነት የእውነት የመተሳሰብ የመተማመን የእውቀትና የብልጽግና ጊዜ ነው፡፡

ማዴባ ሲናገሩ ‹‹ለአፍሪካ ሕልም አለኝ ይሄውም በሰላም እንድትኖር ነው፡፡ብዙዎቹ አስተዳዳሪዎች አዋቂና ብልሆች ናቸው፡፡ተባብረው ችግርዋን ለፈቱላት ይችላሉ፡፡›› ብለው ሲቀጥሉም‹‹ይህች ዓለም የዴሞክራሲ የሰብአዊ መብት የሚከበርባት መሆን አለባት፡፡ አለም ከችጋር ከድንቁርና፤ የእርስ በርስ ጦርነት ተወግዶ በሚሊዮን የሚቆጠሩ፤በስቃይ ላይ የሚኖሩ ሰዎች ከስደት መትረፍ አለባቸው፡፡”

ማዴባ ሁል ጊዜ የመንፈስ ጥንካሬና፤ተስፋ ያሰጡኛል፡፡በ2011 መስከረም ጦማሬ ላይ ስጽፍ እንዳሰፈርኩት ‹‹ኢትዮጵያ በተዘበራረቀ ሁኔታ ላይ ትገኛለች፡፡ በፈላጭ ቆራጭ መዳፍ ስር ነው ያለችው፡፡ መለስ አንዴዬ ሲናገር እንዳለው፤‹‹እኛን የሚቀናቀን ካለ እናደቀዋለን፤ እንደዱቄት!፡፡” ማናቸውም ዜጋ፤ ማንም ሰው፤እንደዚህ ዓይነት አሰቃቂ አነጋገር የሚነገርባት ቦታ፤ ኢትዮጵያ መሆን የለባትም፡፡ ማናቸውም ዜጋ አለፍርሃት፤ረሃብ ጭቆና ለመኖር የሚቻልባት ሃገር መሆን አለባት፡፡ ይሄንንም ስል በረጂም መንገድ ማዴባ ባጭሩ ደቡብ አፍሪካ በማናቸውም አይነት ካሁን በኋላ አንዱ ወገን ሌላውን በጭቆና ቀጥቅጦ የሚገዛባት ሃገር ልትሆን አትችልም እንዳሉት ነው፡፡

የኢትዮጵያን ሰላም የምመኘው ኢትዮጵያዊያኖች በጎ አሳቢዎች ናቸው በሚለረ እምነት ነው፡፡ ማዴባ በዓለም ላይ ካሉት በጎ አሳቢዎች ሁሉ ግምባር ቀደም ናቸው፡፡ እሳቸውም አንድ ወቅት ላይ ሲናገሩ፤‹‹በህይወቴ የነጭ ጭቆናን ተቃውሜያለሁ፤ የጥቁር ጭቆናን ተቃውሜያለሁ:: ዘወትር የምመኘው ደቡብ አፍሪካ ነጻና በዴሞክራሲ ስርአት እንድትተዳደር ነው፡፡ ለዚህም ምኞቴ በስፋት እታገላለሁ፡፡አስፈላጊ ከሆነም ይህ ተግባራዊ እንዲሆን እራሴን አሳልፌ እሰጣለሁ››ብለው ነበር፡፡ ሆኖም ግን ምኞታቸው ከፍ ያለ ቢሆንም ሁኔታውንም ይገነዘባሉና፤ ችግራችንን በሰላምና በምክር መፍታት ካልቻልን ቀሪው ምርጫ ሕዝብን ማስጨፍጨፍ አስከፊ ሁኔታ ይሆናል፡፡ ማዴባ ሲናገሩ: “ባሁኑ ጊዜ ችግርን በሰላም ለመፍታት  ከአምባ ገነን መንግስት ጋር መጯጯህ ፍሬ ከርስኪ ጉዳይ ነው የሚሉ ወገኖች አሉ፡ምናልባት ይህን አስተያየት ተመልሰን ልንመለከተው ይገባል፡፡ለመሆኑ በቂ ጥረት አርገናል ወይ?” በዚሁ መልክ በኢትዮጵያ ንግግር መጀመር፤ ከንቱ ውዳሴ ይሆን? ደጋግሞስ መነጋገር፤ከጨፍጫፊወች ጋር የሰላማዊ መፍትሄ መንገድ መሻት ከንቱ ነው? ………አይመስለኝም፡፡

እንደምናየው ሁሉ የአንድ ሰው አንድ ፓርቲ፤ አንድ ሁሉ ነገር፤የሚባል ዓምልኮ በወደፊቷ ኢትዮጵያ ተስፋ ያለው ነገር አይደለም፡፡ ከታሪክ መማር ተገቢ ነው፡፡በሶርያ በሊቢያ፤የሆኑ አሳዛኝ ነገሮች ከዚህ መዘዝ የመነጩ ናቸው፡፡

ማዴባ ከአፓርታይድ ጭቆና ወደ ዴሞክራሲ ስርአት መሸጋገር ምን እንደሚያስፈልገው ተናግረዋል፡፡‹‹ሕዝቡ መጠየቅ መሳተፍ አለበት፡፡ድርድርም ሲደረግ ፊት ለፊት መሆን አለበት፡፡ “የወደፊቷ ደቡብ አፍሪካ፤የምትተዳደረው፤ዘረኝነት በሌለበት መንገድ ነው፡፡ነጮች የሥላጣን ማነቆ ይዘው ያለበት የረጀ ያፈጀ ሁኔታ መጥፋት አለበት” ማዴባ ብለዋል::

በዚህ መሰረት በኢትዮጵያም ቢሆን ሕዝቡ መሳተፍ አለበት፤ የሃገሪቷም የወደፊት ዕጣ ፈንታ በዴሞክራሲያዊ ስርአት በተመረጠ ጎሳና ዘር በማይል መሰረት ላይ መጣል አለበት፡፡ብልጦች አፈጮሌዎችና አወናባጆች ቦታ አይኖራቸውም፡፡

ሥራው ከባድና ፈታኝ ቢሆንም ሁላችንም ልንሳተፍበት የግድ ነው፡፡

ማዴባ ከእስር የወጡ የመጀመርያው እለት የተናገሩት፤ ስለ ሕብረትና መግባባትና መደማመጥ እንጂ፤ በደቡብ አፍሪካ ባለፉት ረጂም ዘመናት ስለተከናወኑት ሂደቶች አልነበረም፡፡‹‹ሕዝባችንን ማስተባበር በአሁኑ ጊዜ ታላቁ ስራችን ነው፡፡ማናቸውም መሪ በግሉ ሊሰራው የሚችለው ጉዳይ አይደለም፡፡ የመሪዎቻችንና የድርጅታችን ምግባር ዴሞክራሲያዊ በሆነ ስርአት፤ ወደፊት መቀጠልን ነው፡፡መረጋገጥ ያለበት ጉዳይ የእንቅስቃሴውን መሪ ሕዝቡ መምረጥ እንዳለበት ነው፡፡›› ነበር ያሉት:: በኢትዮጵያም ቢሆን፤አንድ መሪም ሆነ ድርጅት ማንም፤የሕዝብን አንድነት ሊፈጥር አይችልም፡፡ ስለዚህ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች፤በስቪክ፤ በሃይማኖት፤ በወጣቶች፤ በሴቶች እንዲሁም ሌሎች ድርጅቶችና መሪዎች ሊፈጥሩ ይችላሉ፡፡

ማዴባን እንኳን ለ94ኛው የልደታቸው በዓል አደረሳቸው፡፡

ባለፈው ሳምንት አርክ ቢሾፕ ዴዝሞንድ ቱቱ ሲናገሩ፤‹‹ለማዴባ ከምንሰጣቸው ታላቅ ስጦታ ምሳሌያቸውን ስንከተልላቸው ነው›› ብለው ነበር:: ስለዚህ ለማዴባ የማበረክትላቸው ታላቅ ስጦታ ከአሁን በኋላ በእሳቸው ጫማ ፈለግ እንደምከተል ማረጋገጥ ነው፡፡ ማዴባ በቃላቸውም በሥራቸውም በጣም ብርታት ሰጥተውኛል፡፡ እስከ አሁንም ዕውነትን ሥልጣን ለጨበጡ እንድናገር ለኢትዮጵያም መልካም ሕልም እንዳልም ያደረጉኝ እሳቸው ናቸው፡፡ ከአሁን በኋላም በሳቸው ምሳሌ ለማስተማር፤ ለማሳወቅ ወደፊት በጥንካሬ የሚቀጥል ነው፡፡የጉዞዬም አቅጣጫ መልካምነትንና እርቀ ሰላምን የሚዬዝ ነው፡፡የማዴባ መንገድ ጉዞ ወደምንሄድበት ቦታ ያለጥርጥር ያደርሰናል ማለት አይደለም፤ሆኖም ግን ባሁኑ ጊዜ እሳቸው ከቀየሱት መንገድ ውጪ ወደ እርቅና መልካምነት የሚያደርሰን ሌላ መንገድ አይታየኝም፡፡

ምናልባት በዚህ አባባሌ እንደአላዋቂና ተላላ ሊመለከተኝ ይችል ይሆናል፤ ግን በተረጋጋ መሬት ላይ እንደቆምኩ አውቃለሁ፡፡ ከኔም ጋር የሚቆሙ ተመልካቾች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ የማዴባንም መንገድ መከተሌን የሚደግፉ ይኖራሉ፡፡ ቢቻልም ከኔ ጋር የማዴባን ጎዳና አብረው ለመሄድ ፍላጎት ያላቸው ሊኖሩ ይችላሉ ብዬ አምናለሁ፡፡ ካልሆነም ብቻዬንም ቢሆን ጉዞውን ለመቀጠል መርጫለሁ፡፡ የብቻ ጉዞ ቢደክመኝም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያኖች በሚያዘግሙበት ጎዳና ነጻነታቸውን ክብራቸውን ለማግኘት ከነሱ ኋላ ሆኜ እያነከስኩም ቢሆን እከተላለሁ፡፡ ለማደርገው ጉዞ ግን ከማውገዝም ሆነ ከማወደስ መዘንጋት የሌለበት በጎ አሳቢ ኢትዮጵያዊ መሆኔን ነው፡፡ እንደተባለው ሁሉ ‹‹አንዳንድ ሰዎች ነገር ተመልክተው ለምን ይላሉ፤ እኔ ግን ስላልነበሩ ጉዳዮች እያለምኩ ለምን እላለሁ፡፡›› ስለዚህም የማዴባን የጫማ ፈለግ ተከትለን አንሄድም? ለምን ኢትዮጵያ በሰላም ሆና አናልምም? የአንዳችን ሕልም ከሌላችን ሕልም ስለኢትዮጵያ ሠላምና ብልጽግና ለምንስ አይሆንም? በጎ አሳቢ ኢትዮጵያዊያኖች እንሁን! ለምንስ መሆን ያዳግተናል?

(ይህን ጦማር ለሌሎችም ያካፍሉ::)

ካሁን በፊት የቀረቡ የጸሃፊው ጦማሮችን  ለማግኘት እዚህ ይጫኑ::

http://www.ecadforum.com/Amharic/archives/category/al-mariam-amharic

http://ethioforum.org/?cat=24

Similar Posts

Leave a Reply