መለስ አለምላስ! – ከፕሮፌሰር ዓለማየሁ ገብረማርያም
ከፕሮፌሰር ዓለማየሁ ገብረማርያም
ትርጉም ከነጻነት ለሃገሬ
‹‹ነጻነትን›› ብሎ የጮህው ወገን
በሜይ 18 2012 መለስ ዜናዊ በማይዋጥለትና ጨርሶ እስከመቃብሩ ድረስ ሊረሳው የማይችለውን ትምህርት ቀሰመ፡፡በነጻው ሃገር፤ ሃሳብን ያለምንም ገደም መግለጽ በሚቻልበት ነጻ ምድር፤መለስ አፉ ተለጎመ፡፡ ያ ያለገደብ ባሻው መልኩ ስድብና ነቀፌታ፤ ፌዝና ሽሙጥ፤ተራ ክብረ ነክ ቃላት ሲተፋ የነበረው አንደበቱ ታሰረ፡፡ በዋሺንግቶን ከተማ የሚኖረው ወጣት ኢትዮጵያዊ ጋዜጠኛ አበበ ገላው፤ በጂ8 ስብሰባ መሃል ስለ አፍሪካ የምግብ ዋስትና ላይ በተካሄደው ውይይት መሃል ብድግ ብሎ አዳራሹን ባናወጠው ድምጽ ሲናገር መለስ ዜናዊ አይኑ ፈጦ ቀረ:: የአበበ ገላው ሃያል ድምጽ አስተጋባ:-
መለስ ዜናዊ አምባ ገነን (ዲክታተር) ነው፤ እስክንድር ነጋ ይፈታ፤የፖለቲካ እስረኞችን ፍታ:: መለስ ዜናዊ ዲክታተር ነህ!፤ሰብአዊ ክብርን እያዋረድክ ሰዎችን ለሞት የምትዳርግ ወንጀለኛ ነህ፡፡ ነጻነታችንን እየተገፈፍን ምግብ አያስፈልገንም፡፡ ከምግብ በፊት ነጻነታችን እንፈልገዋለን፡፡ ነጻነት! ነጻነት! ነጻነት!
በማለት ወጣቱ ጋዜጠኛ ነጻነትን ለኢትዮጵያ ሕዝብ ጠራ፡፡ በአዳራሹ የነበሩት ተሳታፊ የተከበሩ ሁሉ በአግራሞት ተመለከቱት፡፡ አበበ ገላው ያንን አጭር፤ ንግግር ሲሰጥ ለመለስ ግን ማለቂያ የሌለው የመከራ ቀን ወቅት የሆነበት መብረቃዊ ጥሪ ነበር፡፡
አፍ ዘጊው አፉ ሲዘጋ: መተንፈስ ሲያቅተው:- መለስ ዜናዊ የራሱን መድሃኒት ሲቀምስ
መለስ ዜናዊ ገና ‹‹በአፍሪካ የአስተራረስ ትራንስፎርሜሽኑን›› እያለ ሰበካ ሲጀምር: አበበ ገላው አዳፈነው:: ይህን ለማስረዳት ግን ከ 30 ቃላቶች በላይ መሄድ አልቻለም፡፡ የኢትዮጵያውያን ወኪል የአበበ ገላው ድምጽ ‹‹ምግብ ያለ ነጻነት ዋጋ የለውም፡፡የሚያስፈልገን ነጻነት ነው፡፡ ነጻነት! ነጻነት!›› ሲል: መለስ እንደገና ለሴኮንዶች ያህል ሰመመን ወሰደው፡፡ “ቃል የተገባልንን 22 ሚሊዮን ዶላር እንፈልጋለን፤ይሰጣችኋል የተባልነውን ዶላር አምጡ አለ መለስ:: ምንግዜም እንደሚባለው ዞሮ ተመልሶ ገንዘብ ነው ምኞቱ ገንዘብ ነው ቅዠቱ፡፡ አበበ የማይፈልገውን ስም ግን ሁኔታው አስገድዶት የመለስን ስም ጠራው፡፡ በአዳራሹ ያሉት አይኖች ሁሉ ወደ ተጠራው ሰው አፈጠጡ! ተጠሪው አይኖቹን በልጥጦ በድንጋጤ ወዴት ማየት እንዳለበት የጠፋው ይመስል ተደናገጠ፡፡ መለስ በዚህ የቁም ቅዠት ውስጥ ሆኖ ያኔ ነው አበበ ገላውን በፍርሃት የአየው፡፡ መለስ የተራበውን አንበሳ ውሳኔ ለማወቅ እንደተደናገጠው ገመሬ ዝንጀሮ አይኑ ተጉረጠረጠ፡፡ፈራ! “እንዴ!!!ይሄ አበበ ገላዉ አይደለም እንዴ? ቃሊቲ አስገብቼ ዘግቼበት አልነበረም እንዴ? እንዴት ወጥቶ እንዴትስ እዚህ ደርሶ፤ አሁንስ ምን እያደረገ ነው? ግራ የገባው ግራ ዕይነት ነበር ሁሉ ነገር ለመለስ፡፡ አልደፈርም ብሎ ሲኩራራና በአጫፋሪዎቹም ማን ሊደፍርህ የተባለለት መለስ ዜናዊ ጭራዋ የተቆረጠች አይጥ ሆኖ ተብረከረከ፡፡
መለስ መልሶ ራሱን ለመቆጣጠር በመጣርና የጀመረውን ለመቀጠል በመሞከር ሃሳቡንና የማስመሰያ እቅዱን ከመናገር ይልቅ እንደተበላሽ የሙዚቃ ሸክላ ይደጋግም ጀመር፡፡ ‹‹ሰባ በመቶው…. እእእ የአፍሪካ ሰባ በመቶው ሕዝብ….እ እ…›› ምንም ማድረግ አልቻለም፡፡ ወደ ሰብሳቢው በመመልከት ‹‹እባክህ አድነኝ›› በሚል አመለካከት ያየው ነበር፡፡ ሰብሳቢውም እሱም በነገሩ ተደናግጦና ተገርሞም ነበርና ከአንደበቱ የወጡት ቃላቶች ‹‹ደህንነቶች እባካችሁ እርዳታ›› የሚሉት ብቻ ነበሩ፡፡ለሰባት ሴኮንዶች ያህል ያ አፉ እንዳመጣለትና እንዳሻው ፓርላማ በሚለው ስብስብ ውስጥ ሲደነፋ የኖረው መለስ ጨርሶ ሕሊናው ማሰብና ማሰላሰል በማይችልበት ደረጃ ውስጥ ሰመመን ገዛው፡፡ጭንቅላቱ ተደፋ፤ አገጩ መሬቱን ሊያስስ ደረሰ፤ በፍርድ ፊት ቀርቦ በዳኛው የሞት ፍርድ እንደተፈረደበት ነፍሰ ገዳይ፤ባዶውን ወለል እያየ በውስጡ ‹‹ምን አቅብጦ አመጣኝ እንደሚል በቁጭት ተውጦ፤ በፍርሃት ርዶ፤ በንዴት ከስሎ ዝም አለ:: የቪዲዮ ካሜራው በአቅርቦት ሲያመጣው፤የጭንቀት ትንፋሹ ወጥሮት፤ወደ ማስመለሱ ደረጃ ያደረሰው ይመስል ነበር፡፡ ሸሚዙን አልፎ የሚርገበገበው ደም ስሩ ሊፈነዳ ደርሷል፡፡ የደም መዘዋወሩ ለሴኮንድ ስራውን ያቆመ ይመሰል ነበር፡፡የሰውነቱ መለዋወጥ ሺህ ቃላቶችን ይናገሩ ነበር፡፡ ብቻ የሞት የሽረቱን ያህል በመፍጨርጨር ምንም እንዳልሆነ ለማስመስል በመሞከር ከንፈሩን አድርቆና ተቆጣጠሮ ከመንቀጥቀጥ እየተከላከለ፤ ማጉረምረሙን ቀጠለ፡፡ በሚናገርበት ወቅትም፤እጆቹ ይርገበገቡ፤ጣቶቹ እየተወጠሩ ራሱን መቆጣጠር መቻሉን ለማሳየት ሞክረዋል፡፡ ክፋቱ ግን የዚያ የቆራጥ የሕዝብ አንደበት ድምጽ ውቃቢውን ገፎታልና ጨርሶ ጀግንነቱ ሊታይለት አልቻለም፡፡ በመረዋው ድምጽ ተዳፈነ፡፡
እራሱን እንደነበልባል እሳተ ገሞራ በመቁጠር ‹‹ተቃዋሚዎች ይህን የ2010 ምርጫ ለማደናቀፍ ቢሞክሩ›› በማለት መለስ ዜናዊ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን በማስፈራረትና በስልጣኑ በመኩራራት እንደደነፋውና ‹‹ምርጫውን ለማደናቀፍ ካሰቡ፤ በሙሉ ሃይላችን ጨፍልቀን፤እስከዘልአለሙ እንዘጋባቸዋለን›› በማለት የፎከረው ይሄው ሰው ነው:: ዛሬ እንዲህ ምላሱ ያነቀውና ጉሮሮውን የወጠረው፡፡ ዛሬም ቢቻለው አበበን በጥርሱ ሳይቀር ቢቀረጣጥፈውና አጣድፎ ቃሊቲ አስገብቶ ‹‹በሉት›› ቢል ምኞቱ ነበር፡፡ጉረኛው፤ ተኩራሪው፤ጋጠ ወጡ፤ አሽሙረኛው፤መለስ ዜናዊ ተሳዳቢው፤ ዛሬ ምላሱ ተሳሰረ፤መናገር ተሳነው:: ወጣቱን የሕዝብ ተሟጋች ሊቋቋመው ጨርሶ ብቃት አጣ፡፡ ወኔው ተሰለበ፡፡ለፓርላማና ለድርጅት አባሎቹ ጉራ ሲተረትር የኖረው፤ ለሚቀርብለት ቃለ መጠይቅ ብላጣ ብልጥ መልስ የሚሰጠው፤አዋቂና ምሁር ለመምስል የሚኩራራው መለስ ዜናዊ አፉ ተለጉሞ እስቲ ትንፍሽ ትልና እንደተባለ ያህል፤የሚሰነዘርበትን ‹‹ ጨቋኝ ገዢ፤ሰብአዊ መብትን በመጣስ ሰዎችን የምተገል ነህ›› ሲባል ከመስማት ሌላ ምርጫ አጣ፡፡
መቼስ ምን ይደረግ ሃገሩ አሜሪካ ሆነና ከዚህ ሌላ ማድረግ የሚችለውም አልነበረውም፡፡በዚህ በነጻ ሃሳብን የመግለጽ መብት በተከበረበት አሜሪካ፤ ንጉሱን ተራ፤ ተራውን ሰው ንጉስ በሚየደርግበት ሃገር ምን የበል? የሚመረውን ማጣጣም፤ የማይፈልገውን ከመሸከም ባሻገር ምን ሊያደርግ ይችላል፡፡ ከሌሎቹ ተሳታፊዎች ተርታ ሆኖ ልብስ አልባው ንጉስ ላይ እንደረሰበት አይነት ሁሉም በፍርሃት አፉን በተለጎመበት ሁኔታ ሕጻኑ ልጅ ግን የንጉሱሰን እርቃን መሆን ‹‹ ንጉሱ ልብስ አልለበሱም!›› ብሎ እንዳጋለጠው አይነት መለስም በጀግናና በማይገበር ተሟጋች አንደበት ‹‹መለስ ዜናዊ ፈላጭ ቆራጭ ዲክቴተር ነው” ተብሎ ተጋለጠ፡፡ ለመጀመርያ ጊዜ ኢትዮጵያዊያን፤መለስን በምጥና በጭንቀት ሰአቱ አዩት፡፡ ሁል ጊዜ ‹‹አቤት ጌታዬ፤ እሺ ጌታዬ›› የሚሉት አሽቃባጮቹ በሌሉበት፤በአምላኪዎቹ አፋሽ አጊንባሾቹ በሌሉበት፤ለውርደቱና ለእውነተኛው ማንነቱ ተጋለጠ፡፡ ያቺ አጭር 19 ሴኮንድ የዳዊትንና የጎልያድን ታሪክ በድጋሚ አሳየች፡፡ ለታዛቢዎቹና ለጉዳዩ ባለቤቶች ኢትዮጵያዊያን ደግሞ ለ21 ዓመታት ሲያስር ሲገል ሲያፈናቅል ሲክድ ሃገርን ሲሸጥ የነበረና መላውን ኢትዮጵያዊያን ለጉሞ የኖረው መለስ ዜናዊ በ19 ሴኮንድ የተነጣጠረ ምት ሲለጎም አንደበቱ ጥርቅም ብሎ ተዘጋ፡፡
በነጻ የመናገር መብት ሃይል እና ለሃይልም እውነት ሲነገር
እኔ ለሁሉም ነጻ የመናገር መብት በሚለው ዲክቴተሮችንም ጨምሮ አምናለሁ፡፡ በ2010 ሴብቴምበር ላይ መለስ ኮሎምቢያ ዩኒበርሲትይ ተጋብዞ ለመናገር ከየአቅጣቸው ውግዘት ሲደርስበት እኔ ያን ጊዜም የመለስን የመናገር መብት እንዲከበር ተከራክሬአለሁ፡፡ከዚሁ በተጓዳኝም ተቃዋሚ ሃሳብ ያላቸውም ሃሳባቸውን በነጻነት እንዲቃወሙ መብታቸዉን እደግፋለሁ፡፡ ምናለበት ሁሉም የየራሱን ይናገርና ፍርዱን ለአድማጫ መተው፡፡ፕሬዜዳንት ኦባማ ንግግር ሲያደርጉ ተቃውሞ ይሰማል፡፡በቅርቡ በኦሃዮ ስቴት ዩኒቨርሲቲ ንግግር ባደረጉበት ወቅት አንድ ተቃዋሚ ተቃውሞውን ሲያሰማ ፕሬዜዳንቱ አልደነገጡም: ከንግግራችዉም ዘነፍ አላሉም: ግራም አልተጋቡም፡፡ ለተቃዋሚውም ያሉት ‹‹ጌታው፤እኔ እዚህ የተገኘሁት እነዚህን ሰዎች ለማነጋገር ነው፡፡አንተ ደሞ የራስህን ስብሰባ ጥራ፡፡ ያንን ሳታደርግ በመናገርህ ግን ብልግናህን አሳየህ፡፡……..የሌሎቹን ስሜት እትንካ ጣልቃም አትግባ፡፡ተግባባን? ሰውዬውም ሁኔታው በአግባቡ ስለገባው በተናገረው አላፈረበትም በሁኔታው ግን ተደናገጠ፡፡ይህም በነጻ የመናገር አካል ነውና፡፡
የሂሰኞች ቪቶ (“heckler’s veto”) ለአሜሪካ ሕገ መንግስት በጣም ወድ የሆነው የፈርስት አሜንድመንት አካል ነው፡፡ምንግዜም መሪዎች ናቸው የሕዝባቸውን አንደበት ሊለጉሙ በስልጣናቸው የሚመኩት፡፡በሂሰኞች ቪቶ ግን ግለሰቦች ባለስልጣኖችንና ጉልበተኞችን ዝም ያሰኙበታል፡፡ መንበሩ ይለዋወጣል፡፡ ማለትም መለስ ዜናዊ በአበበ ገላው ሴንሰር ተደረገ፡፡እቀሙ ቢኖርና ትንሽም ብትሆን ሀቅ በመለስ ውስጥ ኖራ ቢሆን ለአበበ ‹‹ከምግብ በላይ ነጻነትን እንሻለን›› ውንጀላ፤መልስ መስጠት ይችል ነበር፡፡ ለጥቂት ጊዜ ራሱን ካረጋጋ በኋላ ከነጻነታቸው ጀምሮ በርካታ የአፍሪካ ዲካታተሮች ለዓለም ሲሉት እንደኖሩት ሁሉ፤ አቅመቢሶች ብዙሃን፤ መሃይሞች፤የታረዙ፤የታመሙና ለረሃብ የተጋለጡ የፖለቲካ ዴሞክራሲን ለማጣጣም ገና ችሎታው የላቸውም፡፡ ፍላጎታቸው በሆድ ዴሞክራሲ ላይ እንጂ፤የፖለቲካ ዴሞክራሲና የፖለቲካ መብት አይደለም፡፡ አፍሪካውያን በዳቦና ለዳቦ ነው የሚኖሩት፤ለብዙሃኑ አፍሪካውያን፤ ምርጫ፤የፍትህ መብት፤እና ነጻነትፍቺና ትርጉም አልባ ናቸው በማለት መመለስ በቻለ ነበር፡፡
ለየት ባለ መልኩና ክብርና ባጎናጸፈ ሁኔታ ልከበር ይገባኛል በማለት መለስ ያስብ ይሆናል፡፡እንደአፍሪካ መሪነቱ አንቱታ ይገባኛል ይልም ይሆናል፡፡ በዊኪ ሊክስ በኩል ሾልኮ የወጣው ሰነድ እንደሚያስረዳው ከሆነ ሰውዬው መመለክን፤በምእራቡ ዓለምና ከተቻለም ከዲያስፖራው ተቀባይነትና ከበሬታን የሚናፍቅ፤ሕልመኛ ነው ይለዋል፡፡ በምእራቡ ዓለምም የአፍሪካ ልዑል ራስ ሆነ በሚያሸበርቅ የብረት ጡሩር ተውቦ፤ በአፍሪካ ችጋር፤ ድህነት፤ የፍትህ እጦት፤ ላይ ያን የሚያብረቀርቅ ጦሩን ሲሰካበትና አፍሪካን ነጻ ሲያወጣት በሚመስል መልኩ መሳልና መቀረጽን ይጓጓል፡፡የዘመናዊነት ፈጣሪ፤የአዳዲስ ጉዳይ ፈጣሪ፤የትራንስፎሜሽን አውራ በመባል ሊታወቅ ነው ምኞቱ፡፡በተገነቡት መንገዶች፤ለአንጸባራቂዎቹ የገነባቸው ህንጻዎች፤አድረጌያለሁ ለሚለው የትምህርት ስርአት መሻሻል፤ስለትራንስፖርቱ፤ስለጤናና የሃይል ማመንጫው መሃንዲሱ ነኝና ዲያስፖራ ኢትዮጵያዊያን ይህን ተግባሬን ሊያደንቁልኝና በአመራሬ ስር ሊወድቁ ይገባል ብሎ ይቃዣል፡፡አበበ ገላውን እገድልሃለሁ በማለት ሲደነፋ የነበረው የደህነንት አባልም የተፋው ይህንኑ ነበር፡፡‹‹ኢትዮጵያ እኮ ተለውጣለች፡፡ ወደ ሃገር ገብተህ ለውጡን ስላላየህ ነው፡፡ኢትዮጵያ በጥሩ ሁኔታና በግሩም መሪ ስር ነች፡፡ እንዳንተ አይነቶች ሰዎች ናቸው ከርቀት እየጮሁ ያስቸገሩን››::
ኢትዮጵያ በጥሩ ሁኔታ ላይ አይደለችም፡፡ በዓለም ላይ በጥንታዊነቷ፤ ባለታሪክና በነጻነቷ፤ በአፍሪካም በሕዝብ ብዛት በሁለተኛ ደረጃ ላይ በመሆን የምትታወቀው ኢትዮጵያ፤ በድህነትም ቢሆን በዓለም እጅጉን ድሆች ተብለው ከታወቁት ሀገራት ከኒጄር ለጥቃ በሁለተኛ ደረጃ ላይ አለች፡፡ ላለፉት በርካታ አመታት በአሰርት ሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን ችጋሩን ሊቋቋሙት የበቁት በዓለም አቀፉ ሕብረተሰብ ምጽዋትና ችሮታ ብቻ ነው፡፡በኢትዮጵያ ያለው የመገናኛ ሁኔታ ከእያንዳንዱ መቶ ሰው 5 የእጅ ስልክ የሚያዳርስ ነው፡፡ሕብረተሰቡ በጠቅላላው አንቅሮ የተፋውና ተስፋም የቆረጠበት ደካማና ተልካሻ የሆነ የትምህርት ስርአት የተዘረጋባት ሃገር ኢትዮጵያ ነች፡፡የሕክምና አገልግሎትና የጤና አጠባቁ ጉዳይ ንጽህናን በተመለከተም ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታ ውስጥ ነች፡፡ይህም ኢትዮጵያን በጤና አጠባበቁ መስፈርት ከ110ሩ የወደቁ ሀገራት መሃል በ109ኛው ተርታ ያሰልፋታል፡፡አንጸባራቂዎቹ ሕንጻዎችና ውድና በጣም ዘመናዊ የሆኑት በየጎዳናው ላይ የሚርመሰመሱት ተሸከርካሪዎች ከላይ ከተገለጹት እውነታዎች አንጸር እንቶ ፈንቶ እርባና ቢስ ያደርጋቸዋል፡፡
አስተምህሮትና የመማርያ ወቅት
በ1798 የአሜሪካን ኮንግሬስ ኤልየን ኤንድ ሴዲሽን አክት (Alien and Sedition Act) በማጽደቅ ማንም በመንግስት ላይ ክብረ ነክ፤አስጸያፊ ጽሁፍ ያወጣ በእስራት የሚቀጣበትን ሕግ ደነገገ፡፡በዚያን ወቅት የነበሩትን ፕሬዜዳንት ጆን አዳምስን በመውቀሳቸውና ሂሳዊ አስጠያየት በማውጣታቸው በርካታ ጋዜጠኞች አስራት ቅጣት ተፈጽሞባቸዋል፡፡ ለማይረባው ግነትና ወሰን ላጣ አሳፋሪ፤ ሁኔታ፤ ዋጋ ቢስ ከበሬታ ፍለጋና ንፉግነታ የተሞላው በመሆኑ፤ቶማስ ጄፈርሰን ፕሬዜዳንት ሲሆኑ በዚህ አክት መነሾነት የታሰሩትን ሁሉ በነጻ እንዲለቀቁ አደረጉ፡፡በ1787 ቶማስ ጄፈርሰን፡- እኔ መንግሽት የሌለበት ጋዜጣ ወይስ ጋዤጣ የሌለበት መንግስት ብባል መንግስት የሌለበት ጋዜጣን እምርጣለሁ አሉ፡፡
የአሜሪካው ሕገመንግስት ፈርስት አሜንድመንት ለአሜሪካኑ ፕሬዜዳንትም ሆነ አሜሪካን ለሚጎበኝ የአፍሪካ ዲክታቶር ግፈኛ ገዢ ምንም አይነት የማን አለብኝነት ድጋፍ አይሰጥም፡፡በአሜሪካ ግዛት ውስጥ ሂስን ማካሄድ ገደብ ያልተበጀለት ሃሳብን በነጻ የመግለጽ አካል ነው፡፡ግበአሜሪካ፤የፖለቲካ ስልጣን መያዝ መልካም የሕገመንግስቱ አካል ነው፡፡የፖለቲካ መሪዎችም ላይ ሂስ ማድረግ የሕመንግስት መብት መሰረት ነው፡፡ሁሉም የአሜሪካ የፖለቲካ ሰዎች ከምንም በላይ የሚቀበሉት አንድ ሕግ ‹‹ሙቀቱን ካልቻልክ ከማድቤቱ ውጣ››የሚለውን ነው፡፡መለስ ዜናዊም ሊገነዘበውና ሊያዳምጠው የሚገባው ትምህርት ይህ ነው፡፡
መለስ አንድ መረዳት ያለበት ጉዳይ ያልሰጠውን መቀበል እንደማይቻል ነው፡፡ ዘወትር ተጠርጎና ተስተካክሎ እንደሚመቸው ሆኖ ወደሚጠበቀው ፓርላማው በመግባት ይደሰኩራል፤ ይጮሃል ሰውን ያዋርዳል፤ተቃዋሚዎችም ላይ ያሾፋል ያንጓጥጣቸዋል፡፡የዊኪሊክስ መዛግብትም ጠንካራ የሚባሉትን አምባሳደሮች እንኳን፤ ያጭበረብራቸዋል፤ ይቆጣጠራቸዋል፤ ያስፈራራቸዋል፤ ይዝትባቸዋል ይላል፡፡በነጻነት መናገር የሚፈቀድበት ሃገር ሲመጣ ደግሞሃሳቡን ብቻ ሳይሆን በአገዛዙ ውስጥ ያለውን የሰብአዊ መበት ጥሰትና ሌሎቹንም የፈላጭ ቆራጭ ባህሪው ያስከተላቸውን ኢሰብአዊ ድርጊቶች ለመከላከልና ራሱን ለማዳን ዝግጁ ሊሆን ይገባዋል፡፡
መለስ ዜናዊ በዓለም መሪዎች ፎረም ላይ ለመናገር በሴብቴምበር 2010 በመጣ ጊዜ የሚከተለውን ሃሳብ ሰንዝሬ ነበር፡፡
መለስ ዜናዊ ወደ ሃገሩ ለመመለስ ወደ አውሮፕላኑ ሲሳፈር፤ በንግግሩ ወቅት ተቃውሞና ሂደቱንም ማቋረጥ ስለገጠመው ስለ ዲያስፖራው በማማረር እያጉረመረመ መመለስ የለበትም፡፡ምናልባትም ሁኔታው በአሜሪካን ዩኒቨርስቲዎች ውስጥ በሃሳብ መጋጭት ሳቢያ የሚከሰተውን ሁኔታ ሊማርበት እንዲችል ያሳየው ይሆናል፡፡ ምናልባትም በመጠኑም ቢሆን ሃሳቦች ቀርበው ተቀባይነት እንደሚያገኙ፤እንደሚወድቁም፤ውይይትና ክርክር በነጣ እንደሚራመዱና ቂምና በቀልም እንደማያዝሉ ተምሮ ያደንቀውና ሁለተኛ ለማሰብም እድሉን ያገኝ ይሆናል፡፡እንጂ እሱ እንደሚያደርገው ገና ተናግረው ሳይጨርሱ አለያም ሃሳባቸውን አጠቃለው ሳይገልጹ ለወህኒ፤ ለግርፋት፤ ለመከራና ሰቆቃ አይዳረጉም፡፡ከጠበበ አእምሮአዊ ሂደትና ከዛገ አስተሳሰብ መላቀቂያው ነጻ የመናገር መብት ነው፡፡በእኔ ግምት መለስ ከኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ ትምህርት በመቅሰም፤ከአሰቃቂውና ከጨለማው ዓለሙ ወጥቶ፤ሕግ አልባና ጠባብ አስተሳሰቡ ይላቀቃል ብዬ አምናለሁ፡፡‹‹ሠላማዊ ለውጥን ለመቀበል ፍቃደኛነት የሌላቸው፤ለውጥን በግዴታቸው እያንገሸገሻቸው እንዲቀበሉ ይሆናሉ››
ተስፋ፡፡ የማይሞት ዘልአለማዊ ተስፋ በኢትዮጵያ ሲያብብ፡፡ መለስ በዚህ የአሜሪካው ጉዞው ጠቃሚና ገንቢ ትምህርት ለመቀበል መቻሉን እጠራጠራለሁ፡፡ከታሪክ ግን ሰፋና ጠለቅ ያለ እውቀት እንዲያገኝ ጸሎቴ አይለየውም፡፡ ይሄዉም ‹‹ሠላማዊ ለውጥን አሻፈረን የሚሉ በግፊትና በአመጽ የሚመጣውን ለውጥ አይቀሬ ያደርጉታል::››
ካሁን በፊት የቀረቡ የጸሃፊው ጦማሮችን ለማግኘት እዚህ ይጫኑ:: http://www.ecadforum.com/Amharic/archives/category/al-mariam-amharic