ኢትዮጵያ፣ ከፈላጭ ቆራጭ አገዛዝ ወደ ዴሞክራሲ
ከፕሮፌሰር ዓለማየሁ ገብረማርያም
ትርጉም ከነጻነት ለሃገሬ
ማህተመ ጋንዲ በቅድሚያ ታሪካዊ የብረት ግምብ ነበር ለፈላጭ ቆራጮች ያስቀመጡላቸው፡፡ ‹‹አምባ ገነኖች፤ ፈላጭ ቆራጮችና ነፍሰ ገዳዮች፤ነበሩ፤ ለጥቂት ጊዜ የማይደፈሩ ሆነው ይቆዩና በመጨረሻው ግን መጨፍለቃቸው አይቀሬ ነው፡፡ ዘወትር ስለዚህ ማሰብ አስፈላጊ ነው፡፡››ሲል፡፡ ባለፈው ዓመት ብቻ፤ የጋንዲ ትንቢት እውን ሲሆን፤ የግፈኛ ገዢዎች የድንፋታ ቃላቶችና አካኪ ዘራፍ ፉከራዎች እንደ ዶሚኖ መጫወቻ ጠጠሮች በዐረብ ድንገተኛ እልህ ቁጣ የግፍ በቃን መነሳሳት ሲገረሰስ አየን፡፡የቱኒዚያው ቤን አሊ ከ24 ዓመታት በኋላ የቆመበት የስልጣን መረጋገጫው አዳለጠው፤ የግብጹ ሆስኒ ሙባረክም ከ32 ዓመታት የገዢነት መንበሩ ተወርውሮ እየተገፋ ወደ ፍትሕ አደባባይ ቀረበ፡፡ጋዳፊ አይጦች እንዳላለ እራሱ ከተሸሸገበት የአይጥ ጎሬ ተጎትቶ በአደባባይ ለእይታ ቀርቦ፤እራሱ ባስጠረበው የወርቅ ሽጉጥ ህይወቱ አለፈች፡፡የየመኑ አሊ ሳላህ፤ ለ33 ዓመታት በግፍ ከገዛና በፊቱ ላይ በፈንጂ ፍንጣሪ አጓጉል ሆኖ ከቆሰለ በኋላ አሁን ለመሰደድና ኑሮውን ከመሰሉ መለስ ጋር ለማድረግ ወደ ኢትዮጵያ ለመሰደድ ተገዷል፡፡( አለማወቅ ሆኖ ነው እንጂ እዚያም ቤት እሳት አለ እንዲሉ በአንድ ቦታ መሰባሰባቸው የጭንቅላታቸው የማሰብ ስፋት ምን ያህል ጠባብ መሆኑን ነው የሚያሳየው) በሺር አል አሳድ አሁን በሲሪያ ሉካንዳ እያካሄደ ቢሆንም፤ እንደፈላጭ ቆራጭ ወንድሞቹ ተራው ሲደርስ በአንድ ረድፍ መቆሙ አይቀሬ ነው፡፡
የሰብ ሰሃራ አፍሪካም ፈላጭ ቆራጮች ሲንሸረተቱና መቀመጫቸውን ሲለቁ ታይተዋል፡፡ኮተ ዲቩዋሩም ሎራንት ባግቦ ከመኮፈሻው የሽቅርቅር ነጭ ኮሊታው ሸሚዙ ተለያይቶ በቤተመንግሥቱ ከተወሸቀበት ጓዳው ተይዞ በፈጸመው የሰብአዊ መብት ጥሰትና ግድያ ለፍርድ ለዓለም የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ተላልፏል፡፡ የኒጀሩ ማማዱ ታንጃ ሕገመንግሥታዊ የስልጣን ገደብን በመጣስ በሥልጣን ላይ ለመቆየት ቢፍጨረጨርም የኒጀር ጦር አሽቀንጥሮ አውርዶታል፡፡የማማዱ ታንጃም ቀንደኛ ተወዳዳ በሕዝባዊ ምርጫ ሥልጣኑን ተረከበ፡፡በቅርቡም፤የሴኔጋሉ መሪ የ85 ዓመቱ አብዱላዬ ዋዴ የሶስተኛ ጊዜ ምርጫ ለማድረግ ለማጭበርበር ሲያቅድ ሕዝባዊ ዐመጽ ተቀጣጥሎበት ምርጫ እንዲካሄድ ሲደረግ አብዱላዬ ዋዴም ለመወዳደር ሞክሮ በቂ ወንበር ሳያገኝ በመቅረቱ በዘዴ ስልጣን ለመያዝ በመንቆራጠጥ ላይ ቢሆንም አሸነፈ ቢባልም ከፍተኛ ሕዝባዊ ተቃውሞ እንዲያጋጥመው አያጠራጥርም፡፡
ባለፈው ዓመት በጃንዋሪ 2011 ‹‹ከአፍሪካ ፈላጭ ቆራጮች ውድቀት በኋላ›› በሚል ርዕስ አንድ መጣጥፍ አቅርቤ፤ እግረመንገዴንም 3 መሰረታዊ ጥያቄዎች አንስቼ ነበር፡፡ ለመሆኑ በአፍሪካ ያለው የፈላጭ ቆራጮች የጭቃ ስሪት ቤት ሲፈራርስና ከነዚያ ጭቃ ቤቶች በስተጀርባ ያለው የፈላጭ ቆራጭ ገዢዎች ቅዠት ሲፈራርስ አፍሪካ ምን ትሆን ይሆን? የአፍሪካ ጉዳይ ‹‹ጨዋታ ፈረሰ ዳቦ ተቆረሰ›› ጨዋታ ይሆንና የማይጠገን አወዳደቅ ደርሶባት ዳግም መልሳ መገንባት የማትችል አህጉር ትሆናለች? እነዚያስ ፈላጭ ቆራጭ ገዢዎችና የሕዝብ ደም፤ግፍና ሰቆቃ በጃቸው ላይ ያለባቸው አውሬዎችስ ምን ያጋጥማቸው ይሆን? ለመጨረሻው አንድጥያቄ ዝግጁ መልስ ሲኖረኝ ለሁለቱ ግን አላገኘሁላቸውም፡፡
ሕዝቡ የበቃኝ፤በቃችሁ አታሞውን በነዚያ የገዢዎች ጭቃ ቤት ዙርያ መጎሰም ሲጀምር የአፍሪካ ፈላጭ ቆራጭ ግፈኛ ገዢዎች በእጃቸው ሊገባ የሚችለውን ኮተታቸውን በመሰብሰብ ቅራቅንቧቸውን አክተው፤ ልክ የሌሊት ወፎች ከተቀበሩበት ወጥተው እንደሚበሩት አይነት ሲበሩ ጥቂቶቹ ደሞ በጭቃው ልስን ስንጥቅ ውስጥ ያም ካልሆነ በአቅራቢያ ካሉ መሰል ግፈኛ ገዢዎች መንደር በመደበቅ ፍትሕን የሚሸሹ ስደተኞች ለመሆን ይሞክራሉ፡፡ሌሎች ደሞ እመንጥ ይግቡ ስምጥ በይፋ ሳይነገር የዘረ4ፉትን ሃብታቸውን አዩን አላዩን በሚል ኑሮን ለመቀጠል ይታገላሉ፡፡ እነዚህ ግፈኞች ሃገሪቱን ዘርፈው ለሕዝቡ ባዶ ካዝና ትተውለት በመኮብለላቸው፤ሕዝቡም በትግሉ ካገኘው፤ ከነጻነት ንጋት ጋር በወረሰው ባዶ ኤኮኖሚ፤ መለመላውን በቀረው የባንክ ሳጥን፤በተራቆቱ የገበያ መደርደሪያዎች፤ የግፍና የስቃይ መናሃሪያ በሆኑ የግፍ እስር ቤቶች በታፈኑ እስረኞች፤ለሥልጣን በመቋመጥ በተራቡ የፖለቲካ ተቃዋሚዎች ሽኩቻ የተተራመሰ የፖለቲካ ውጥንቅጥ ይጠብቀዋል፡፡
ኢትዮጵያን ከፍርስራሹ በኋላ ማነው የሚጠግናት?
የግፍና የፈላጭ ቆራጮች የጭቃ ግንብ ሲፈርስ ኢትዮጵያን ምን ይጋጥማታል? ኢትዮጵያ ከውድቀት የማትነሳበት ሁኔታ ያጋጥማትና ተበታትና ትቀራለች?ወይስ ኢትዮጵያ እንደ ሊቢያ፤ ግብጽ፤ ቱኒዚያ፤ ያለ ሁኔታ ውስጥ ትገባለች? ወይስ እንደሲሪ ያለው ሁኔታ? አሁን ነግፍ የሚገዟት ገዢዎች እንደሚሉትና እንደሚያስፈራሩበት የራሳቸው ብቻ የሆነው አስተሳሰብ አይገጥማትም ብሎ ማንም በእርገጥኝነት መናገር አይችልም፡፡ ‹‹ኢትዮጵያ መበታተን እድሏ ከሆነ ምን ይደረግ፤ ግን አፈጣጠሯና የኢትዮጵያ እውነታ እንደሚታወቀው ከሆነ ግን ለመበታተን የተፈጠረች አይደለችም››
በእርግጠኝነት መባልና መጠበቅ የሚቻለው እውነታ ግን፤በፈላጭ ቆራጭ ግፈኛ ገዢዎች የደቀቀችውን ኢታዮጵያ መልሶ የመገንባትና ጠላቶቿ እንደሚመኙላት ከመሆን የሚያድኗት ኢትዮጵያዊያንና ኢትዮጵያን የሚሉ ወዳጆቿ ናቸው፡፡እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ዜጋ፤የተሰባሰቡ ኢትዮጵያውያን፤የሲቪሉ ማሕበረሰብ፤እና የነጻው መገናኛ ብዘሃን አባልት፤ የዴሞክራሲ ተሟጋቾች፤የሰብአዊ መብት ታጋዮች፤የፖለቲካ ፓርቲዎች፤ እና ኢትዮጵያን ያሉ ሁሉ በአንድነት በመተሳሰብና በመግባባት በመሰባሰብ ሃገቱን ከአንድ ሰው አንድ ፓርቲ ግዛት አላቀው በሕግ በታገዘ የመድበለ ፓርቲ ሃገር ሊያደርጓት ይችላሉ፡፡ ኢትዮጵያዊያን ተጋርጦ የቁም ስቅላቸውን ሲያሳያቸው ከነበረው የግፍ አገዛዝ በመውጣት ለወደፊት የተሸለና ነጻነት የሰፈነባት፤ የዴሞክረሲ መብት ያለባት፤ የፍትሕ የበላይነት የተደነገገባት፤ አንድ ሆነው በአንድነት እየመከሩና እያቀዱ፤ ልዩነታቸውን ተቻችለው፤በግልጽ በመወያየትና ጥበባዊ ሃሳብን በማፍለቅ፤ ለዕውነት በእውነት በመቆም፤በመከባበር፤ያለተጽእኖ በመደራደር፤ ኢትዮጵያን መመስረት ከፈለጉ፤ የሕዝብን ፍላጎት እምነትና ውሳኔ በማክበርና በመቀበል መንቀሳቀስ የግድ ይላቸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ የሽግግር ካወንስል (ኢብሽካ)
በኢትዮጵያ ያለው የፈላጭ ቆራጭ ግፈኛ ገዢዎች ግድግዳ ሲፈራርስ መደረግ ያለበትን ሁኔታ በተመለከተ፤ በቅርቡ መሰረታዊ ዓላማ ያላቸው ኢትዮጵያውያን ይህን ሁኔታ በሃላፊነት ለመሸከም ፈቅደዋል፡፡የኢትዮጵያ ብሔራዊ የሽግግር ካወንስል (ኢብሽካ) ከሁሉም አቅጣጫ በተለያየ መስክ ያሉትን ኢትዮጵያውያን ሁሉ በማሰባሰብ፤ ኢትዮጵያን ካለችብት የግፍና የጭቆና ዘረኛ አገዛዝ አውጥቶ፤ወደ ዴሞክራሲያዊትነት ለመለወጥ እንዴት በሚል ነጥብ ላይ ማወያየት አቅዷል፡፡
በግልጽ የተቀመጠው ዓላማውም ‹‹በተለያየ ቦታና ሚና ላሉት ኢትዮጵያውያን የጉዳዩ ባለቤቶች የመልካም ግንኙነትን ፍላጎት ማዳበር፤መግባባትን መገንባት፤ የግንኙ ነትንና የኢንፎርሜሽን ልውውጥን መረብ መዘርጋት›› የሚል ነው፡፡ ኢብሽኮ ከየትኛውምና ከማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ጋር ቁርኝት ጨርሶ የለውም፤አሁንም ሆነ ወደፊት መሠረታዊ የሆነ የዴሞክራሲ ሥርአትን ከመዘርጋትና ዴሞክራሲያዊ አስተዳደርን በመፍጠር፤ የሰብአዊ መብት መከበርን ማረጋገጥ ውጪ ሌላ ተልእኮ የለውም፡፡ ምኞት ዓላማና ግቡም ሁሉንም ያካተተ የዴሞክራሲ ስርአት ተሟጋቾችን በመፍጠር ሃገራችን ነጻ፤ዴሞክራሲያዊ፤ሰላማዊና የዳበረች የለማች እንድትሆን መጣር ብቻ ነው፡፡
ለዚህ ከባድና ሃገር አቀፍ ውጣ ውረድ የበዛበት የነጻነት ራዕይ ከተሰለፉት ግንባር ቀደም ሰዎች አንዱ ዶ/ር ፍስሃ እሸቱ ነው፡፡ፍስሃ በትምህርቱና በቴክኒካዊ ትምሕርት ታላቅ እቅድ ያሳካ ወጣት ኢትዮጵያዊ ነው፡፡እ አ አ በ1991 ዓ፤ም ዩኒቲ በመባል የታወቀውን ዩኒቨርሲቲ ዘር ዘርቶ፤ በሃገሪቱ የመጀመርያውና አስፈላጊውን መመዘኛ ሁሉ በማሟላት የመጀመርያውና ትልቁ፤ብቸኛው የግል ዩኒቨርሲቲ ለመሆን የበቃውን ዩኒቲ ዩኒቨርሲቲን የመሰረተ ነው፡፡ በ2008 ዓ፤ም ለዓመታት በየቀኑ በሚፈጠርበት አዳዲስ ህግጋትና ደንብ ጋር ከመንግሥት ጋር ሲታገልና ውደቅ አልወድቅም ግብ ግብ ሲያካሂድ ቆይቶ የመንግሥት ፍላጎት የግል ተቋማትን ማዳከምና ማጥፋት መሆኑን በመጨረሻው በመገንዘብ፤ እጅግ የሚወደውን፤ጉልበቱን፤ እውቀቱን፤ማንነቱን የሰዋለትን የሚወደውን ዩኒቨርሲቲውን ሽጦ ፍስሓ ለስደት በቃ፡፡(ስለዚህ ጉዳይም በወቅቱ በተደጋጋሚ ጥሁፍ አቅርቤ እንደነበር ሊታወስ ተገቢ ነው፡፡)
ይህን የመሰለውን ውስብስብነት ያለበትን የፖቲካ እንቅስቃሴ ለመምራት ፍስሃ ትክክለኛው ሰው ነው ሊባል አይችል ይሆናል፤በራሱ አንደበት እንደተናገረው ፖለቲካን ከሚሸሹትና እራሳቸውን ከፖለቶካ መስህብ ካገለሉት አንዱ ነበር፡፡እምነቱም ፖለቲካና የንግድ ሥራ አይስማሙም የሚል ነው፡፡ያም ሆኖ በመለስ ዜናዊ አገዛዝ ሙስናን፤የአስተዳደር ብልሹነትን፤በሥላጣን አለአግባብ መጠቀምን፤ቢገነዘብም አይቼ አላየሁም፤ሰምቼ አልሰማሁም፤ አልናገርም ማለትን መርጧል፡፡‹‹ምን አገባኝና!›› ወደማለት ከማዘንበልም አልፎ ኢትዮጵያዊነ ቱንም ጠልቶት ነበር፡፡እየዋለ እያደረ ሲሄድ ግን በየዕለቱ የሚፈጸመውን የሕዝቡን መከራና ግፍ፤በመመልከት፤ እራሱን ከእውነታው በማሸሽ ተመልካች በመሆኑ ‹‹የህሊና ወቀሳቀው›› መቆሚያ መቀመጫ አሳጣው፡፡ በመጨረሻውም በሚያየውና በሚሰማው፤በየቀኑ በሚያዳምጠው ሕዝባዊ ብሶትና ግፍ፤ ገዢው መንግሥት እኔ ያልት ብቻ፤ ሕዝብ ማለት እኔ የምለውን የሚቀበል ብቻ ነው የሚለውን መመልከቱ ስላንገሸገሸውና በተለይም፤የሕዝቡን አቤቱታ ሰሚ ማጣት በማገናዘብ ምሬቱ ወደ ራሱ ዞረና ‹‹ጥንካሬን ከእውነት፤ እምነትን ከፈጣሪ›› በመቸር፤ለዚህ ሁሉ እኔም ድርሻ ሊኖረኝ ይገባል በሚል እምነት፤ሕዝቡንና ሃገሪቱን ከተጋረጠባት ክፉ፤ዘረኛ፤ጀብደኛ፤ሙሰኛ፤ጨካኝ ገዢ ለማላቀቅና፤ ስርአቱን በመለወጥ ሃገሪቱና ሕዝቡ የዴሞክራሲ፤ የሰብአዊ መብት፤ የፍትሕ የበላይነት ባለቤቶች እንዲሆኑ አስፈላጊውን ሁሉ ለመክፈልና ለማድረግ የዜግነትና የሞራል ግዴታ እንዳለበት በይፋ ይናገራል፡፡እንደምርጫና ፍላጎት ግን አሁንም በከፍተኛ የትምህርት ተቋም ውስጥ በመሰማራት በርካታ የኢትዮጵያን ወጣቶች የነገዋን ኢትዮጵያ ለመገንባት እንዲችሉ ማስተማርን ይመርጣል፡፡
ፍስሃ ሲናገርና አለአንዳች ማጋነን፤በሰከነ አንደበት፤ ግልጽ በሆነ አገላለጡ ከመማረክ የሚያመልጥ የለም፡፡ቃላቶቹ ቀጥተኛና እውነት እንጂ እንደፖለቲከኛ፤ ታስቦባቸው፤እንዲጽሙ ሆነው ተቀምመቀው የሚወጡ አይደሉም፡፡ እንደወረዱ ወደሰው ደርሰው ግን ያሳምናሉ፡፡ እውነት እውነቱን ብቻ ይናገራል፡፡ ስሜቱን ነው የሚያካፍለው፡፡ሕዝባዊ ንግግሮቹ የጋንዲን ‹‹ሳቲግራሃ››(የሃቅ ሃይል) ያስታውሳል፡፡‹‹መቶ በመቶ እቅዳችን ግቡን እንደሚመታ የምናረጋግጠው በሁለት ምክንያት ነው፡፡በመጀመርያ የምናደርገው ሁሉ በዕውነት ላይ የተመሰረተ ነው፤ በእግዚአብሔርም እናምናለን፡፡›በፍስሃ ንግሮች ውስጥ ማንዴላዊነትም አለ፡፡ በተደጋጋሚ ‹‹ለሃገሬ የዴሞክራቲክ ለውጥ ለማምጣት እስከቻልኩ ድረስ ከማንም ጋር እሰራለሁ፡፡››ይላል፡፡ ታላቁ ኔልሰን ማንዴላም ሲያስተምር ‹‹ከጠላትህ ጋር ሰላምን መፍጠር ከፈለግህ፤ከጠላትህ ጋር መስራት ይኖርብሃል፡፡ ጠላትህም ተባባሪህ ይሆናል›› ነው ያለው፡፡
ፍስሃ፤ኢብሽካ በኢትዮጵያ ያለውን የግፍና የጭቆና መንግሥት አስወግዶ ዴሞክራሲን ለማስፈን እስከተሰለፈ ድረስ፤ከማንም ጋር፤ያለአንዳች ቅድመ ሁኔታና ገደብ፤ለመስራት ፈቃደኛ ነኝ ይለናል፡፡በተግባር ላይ በሚሰማሩ ሰዎች እምነት አለው፡፡‹‹እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ 1 በመቶ መስዋእትነት ቢከፍል፤በስድስት ወረታ ውስጥ መጠነ ሰፊ ለውጥ እናመጣለን፡፡የሕዝባዊ አገልጋይነት ፈቃደኝነትና ፍላጎት ልናዳብር ተገቢ ነው፡፡ ለሕዝባዊ አገልግሎ የመሰለፍ ባህል ማዳበር ይገባናል፡፡ለፖለቲካ ሥላጣን ፍላጎትም ምኞትም የለንም፡ሕልምና ራዕያችንም ይህን የዴሞክራሲያዊ ሽግግር አፋጥነን ተግባራዊ በማድረግ ወደየሙያችን መመለስ ብቻ ነው፡፡››
ከፈላጭ ቆራጭ አገዛዝ ወደ ዴሞክራሲያዊ አስተዳደር ሽግግር
በኢትዮጵያ ከፈላጭ ቆራጭ አገዛዝ ወደ ዴሞክራሲያዊ አስተዳደር ሽግግግሩ ፈታኝ ሊሆን ይችላል የማይቻል ግን ጨርሶ አይደለም፡፡ወደ ዴሞክራሲ ሽግገሩ ምን ይመስላል?
በኢትዮጵያ የተገነባው የጭቃ ግንብ ሲደረመስና ሚስጥራዊ ድበቃውና ጉዱ ሲጋለጥ፤ሁለት ዋነኛ ጉዳዮች እርቃነ ስጋቸውን ይጋለጣሉ፡፡በቅድሚያ ሕዘቡ ብሔራዊ የገንዘብ ጎተራው ባዶ መሆኑንና፤ ሃገሪቱም ወደ አዘቀዘቀ የመዋዕለ ንዋይ ክስረትና ዓለም አቀፍ ውስጥ እንደተዘፈቀች ይረዳሉ፡፡በሁለተኛ ደረጃም የተጠናከረና መሰረት ያለው የዴሞክራሲ መዋቅር ባለመኖሩ ለተወሰነ ወቅት ያልተረጋጋ ሁኔታና ውጥረትና አለመግባባት ያጋጥማል፡፡ይህን መሳዩን ሽግግር በተሸለ ለማወቅና መፍትሔም ለማግኘት፤ በኢትዮጵያ፤ በፈላጭ ቆራጭ አገዛዙ መጨረሻና በዴሞክራሲ የብርሃን ፍንጣቂ ጊዜው መሃል ያለውን አሉታዊ ሁኔታ ማጤን ያስፈልጋል፡፡
የከፋፍለህ ግዛ እቅዳቸውን ለማሳካት ኢትዮጵያን በግፍና የበደል ጭቆና በመግዛት ላይ ያሉት፤የወቅቱ ጊዜያዊ፤አረመኔ፤የግፍና የበደል ቋት የሆኑት ፈላጭ ቆራጭ ገዢዎች፤ ሓገራችንን፤ በዘር፤በጎሳ፤ በመንደር፤ በቀበሌ፤ በጎጥ፤ከፍፍለዋታል፡፡ያ ነው እንግዲህ ለችግር መብቀያና ቁጥቋጦ ሊሆን የሚችለው፡፡የወረቀት ላይ ነበር በሆነው ደንብና አዋጅ ቀርጸው በፈጠሩት ቃለ አባይ የምርጫ ቦርዳቸው፤ በየቀኑ በሚወጣ ደንብና እገዳ በበዛበት አዋጃቸው፤ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎን ጨርሶ እንዳይንቀሳቀሱና፤ ከአባሎቻቸውም ሆነ ከሌሎች የሕብረተሰቡ ክፍሎች ጋር እንዳይገናኙ የብረት ማነቆ አድርገውባቸዋል፡፡የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች እንደ ፍየል በየእለቱ እየታገቱ በእስር እየተንገላቱ ነው፡፡ ቆራጥ የሕዝብ አንቀሳቃሽና የዴሞክረሲ፤ የሰብአዊ መብትና የፍትሕ ተሟጋቾች፤ በሽብርተኛነት እየተፈረጁና የሃሰት ክስና ሰነድ እየተዘጋጀባቸው ለእስር እየተዳረጉ ነው፡፡ ሕዝቡ ያለአንዳች መንስኤ፤ በዘፈቀደ እየተያዘና ለእስር እየተዳረገ በመሆኑ የሕግ የበላይነት እንኳን ሊተገበርና ስሙም አይነሳም፡፡በሚታወቁና ሚስጥራዊ በሆኑት የገዢው የሰላማዊ ሰዎች ማጎርያ ጣቢያዎች የሚፈጸመው የስቃይ ምርመራና ግፍ ማስረጃ በተደጋጋሚ የቀረበበት ነው፡፡ የግለሰቦች ነጻነት ጨርሶ የማይታሰብ ነው፡፡ሃሳብን በነጻ መግለጽ አሁን አሁንማ የሽብርተኛነት ማረጋገጫ እየሆነ ነው፡፡ነጻ የህትመት ውጤቶችም በገዢው ፓርቲበ ቃታና ጡጫ ስር ናቸው፡፡የእለት ተዕለት ዛቻ፤ማስፈራራት በጣት የሚቆጠሩትን የህትመት ውጤቶች ባያስጎነብሳቸውም እንዲያቀረቅሩ ለማድረግ እየተሞከረ ነው፡፡ አማራጭ ሊሆኑ የሚችሉት የኤሌክትሮኒክ ጣቢያዎች፤ድህረገጾች፤ኢሜይሎች፤(እድሜ ለቻይና፤ጸረ ነጻነት፤ ጸረ ዴሞክራሲ፤ጸረ ፍትህ፤ጸረ ሰብአዊ መብት መንግሥት ትብብር) ከጥቅም ውጪ ሆነው ተዘግተዋል፡፡የግል ሚዲያዎችም ጫናው ሲበዛባቸው ተቋርጠዋል አታሚዎቹና ባለቤቶቸሁም እስርና እንግልትን በመሸሽ ሃገር እየጣሉ ለስደት ተዳርገዋል፡፡የተቃዋሚ ፓርቲ ድርጅቶችም በአሻንጉሊቱ ፓርላማ እየተወገዙ መብታቸውን ተገፈዋል፤የሕግ የበላይነትም በይስሙላው ፍተሕ አደባባይ በሚኮፈሱ ሙያ አልባ የገዢው አገልጋዮች ተሞለው ግልጋሎት ሰጪነታቸውም፤ፍርፋሪ ለሚጥልላቸው ገዢው መደብ ሆኖ አፈናውንና ጭቆናውን ሕጋዊ በማድረግ ላይ ናቸው፡፡ምሉዕ በኩላሄ በሥላጣን ጣሪያው መብትም ለአንድ ግለሰብ ተጠራርጎ በመሰጠቱ ያለ አንዳች ሕገመንግሥታዊ አካሄድና ክትትል፤ ቁጥጥርና ተጠያቂነት እንደፈለገ እንዲጋልብበት ተደርጓል፡፡ከዚህ መሰሉ አገዛዝ ወደ ዴሞክረሲያዊ አስተዳደር የሚደረግ ሽግግር፤በገዢዎቹ ላይ ብቻ የሚደረግ የቅርጽ ለውጥና ሂደት ብቻ ሳይሆን፤ሥር ነቀል የሆነ የህብረተሰቡንም ስሜትና የሲቪል ማህበረሰቡንና የሃገሪቱንም የፖለቲካ ባሕልም መለወጥ የግድ ነው፡፡
ከፈላጭ ቆራጭ ሥርአት ወደ ዴሞከራሲያዊ ስርአት ሽግግር፤የሽግግር ወቅት ጉዳይ ብቻ ነው!
የፈላጭ ቆራጭ ገዢዎች መገርሰስ ብቻ በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ልደት ዋስትና ሊሆን አይችልም፡፡ከፈላጭ ቆራጭ ፍርስራሽ ውስጥ የዴሞክራሲ ግንብ ሊፈጠር አይችልም፡፡የዴሞክራሲ ውልደት ብዙ ውጣ ውረድና የሕብረት ሥራን ይጠይቃል፡፡ለተፈጠሩትና ሲተገበሩ የነበሩት ችግሮች ሁሉ ጥበባዊ መፍትሔና ዘዴ የስፈልጋቸዋል፡፡ለዚህ ደሞ ቀና ፍላጎትና መልካም አመለካከት ይጠይቃል፡፡ኢትዮጵያን ከተጣለባት የፈላጭ ቆራጭ አረመኔያዊ ችግርና ማነቆ ለማላቀቅና ዴሞክረሲን ለመገንባት ብዙ መስዋእትነት ያስፈልጋል፡፡ይህች በችግርና በመከራ ውስጥ በእርኩስና ንፉግ፤ በእኩይና አረመኔ ገዢዎች መዳፍ ሥር የከረመች ሃገራችን፤ የዶሞክራሲ አካላትና ጠንካራ የፖለቲካ ድርጅቶች፤ የተጠናከረና ህያው የሆነ የሲቪክ ማህበረሰብ ባልተዋቀረበት፤ ነጻ ሆነውበመንቀሳቀስ የዴሞክረሲን ልደትና የአእድገቱን አካሄድ የሚተልሙ የፕሬስ ድርጅቶች በሌሉበት ከዚህ ፍዳ እንድትላቀቅ ለማደረግ የሁሉንም ይሁንታና ተሳትፎ ይጠይቃል፡፡
በቅርቡ ከፈላጭ ቆራጭ አገዛዝ ወደ ዴሞክራሲያዊ አስተዳደር ሽግግር ያካሄዱት ሃገራት ታሪክ እንደሚያሳየው፤የሽገግግር ችግሩ እራሱ የሽግግር ሂደቱ ነው፡፡በዲክታተር ስርአት መውደቅና በዴሞክራሲያዊው ስርአት አመሰራረት መሃል ጠባብ የሆነ የታሪክ ውሳኔን የሚጠይቅ ሂደት ያጋጥማል፡፡በዚያች ጠባብ የመስኮት ክፍተት በምታህል ሂደት ውስጥ በሽግግሩ ወቅት ከዚያ ከፈራረሰው የፈላጭ ቆራጭ ግፈኛና ዘረኛ ፍርስራሽ ውስጥ የሚፈጠረው፤የሚናፈቀውና የሚመረጠው የዴሞክራሲ ፍሬ ነው ወይስ ያለፈው የክፉ ገዢ አመድ ተለውጦ በሌላ መልክ እራሱ የፈረሰውን ግፈኛ አገዛዝ የሚተካ የባሰ አረመኔ ነው፡፡ በአጭር አነጋገር፤በፈላጭ ቆራጭ አገዛዝ መፍረስና በዴሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ፤ወሳኙ የሽግግሩ መስኮት ነው፡፡ በባለቤቶቹ መሃል በሚነሳ አላስፈላጊ አፍራሽ ውድድርና ግጭት፤ አመኔታ መጥፋት፤ሁሉም የየራሱን እምነትና ፍላጎት አራማጅ ከመሆን፤ ዴሞክራሲ የሚገነባ ከሆነ ውጤቱ ደካማ፤ ጥቅም የለሽ ነው የሚሆነው፡፡ሽግግሩ በቀና ግልጽና መግባባት ላይ በተመሰረተ ውይይት ላይ ያተኮረ ከሆነ፤የሁሉም ፍላጎት ለሃገርና ለሕዝብ ቢል እራስን ሳይሆን የተደረሰበትን የስምምነት ራዕይ ያገናዘበ፤ ዘላቂ የሃገርን እድገትና ልማት የህብረተሰብን አንድነትና አዲስ ስርአት ማጎልበት ጋር የተዋሃደ ከሆነ፤ዘላቂና አስተማማኝ የዴሞክራሲ ግንባታ ያብባል፡፡
ይህን ሃሳብ በተመለከተ የኢትዮጵያ ታሪክ በቂ ምስክርና ረጋገጫ ነው፡፡በ1991 በተካሄደውና በአሜሪካ አደራዳሪነት በተከናወነው የሽግግር ሂደት ወቅት፤መለስ ዜናዊ በሰላ አንደበቱና በረቀቀ እኩይ አካሄዱ፤ኤሪካንና ሁሉንም ባለጉዳዮችና ባለመብቶች በማጭበርበር በአጭር አሰቀራቸው፡፡በቅርቡ ቃለጠይቅ የተደረገላቸው የአሜሪካው አደራዳሪ ወኪል ኸርማን ኮህን ይፋ እንዳወጡት፡
የትግራይ ነጻ አውጪ ግንባር ቲ ፒ ኤል አፍ፤ያ በር ላይ ደርሷል፡፡ ስለዚህም ምርጫችን ለስልሶ ማርፍ ቢልና በመረጥነው የአገባብ ዘዴ ጦርነቱ እንዲያበቃና ቀጣይ ጥፋትም እንዳይከሰት ማድረግን ነበር፡፡…….መንግሽቱን ተረከቡ አላልንም፡፡ያልነው አዲስ አበባን ተቆጣጠሩ ነው፡፡አዲስ አበባን በመቆጣጠር የሚያረጋጋ ሃይል ያስፈልግ ነበር፡፡ ከዚያም በእርጋታ የሽግግር ሂደቱን ተግባራዊ በማድረግ አዲስ መንግሥት መመስረት ነበር ፍላጎታችን፡፡ ኮኸን ሲያጠቃልሉ፤ ‹‹ምን ያደርጋል ብዙም ሽግግር አለነበረም፡፡›› ነው ያሉት፡፡
ኮኸን በማከልም፡
ሁሉን ፓርቲዎች በማስተባበርና በማግባባት፤በአንድነት በመቆም እንዲሰሩና አንድ የዶሞክራሲ ይዘት ያለው መንግሠት እንዲመሰርቱ፤ኢትዮጵያና ኤርትራም በአንድ ገንዘብ እንዲጠቀሙ፤የሚል ሃሳብ ይዤ ነበር የጀመርኩት፡፡ ከኔ ሃሳብ ስንዘራ በኋላ ሶስቱ ፓርቲዎች ሌላ አደራዳሪ ሳያስፈልጋቸው ውይይታቸውን መቀጠል ወሰኑ፡፡ወዲያው ወደ አንድ የተለየ ክፍል በግባት የግላቸውን ውይይት ካካሄዱ በኋላ አንድ መግለጫ አወጡ፡፡ መግለጫውም፡- ሁሉን ፓርቲዎች አቀፍ የሆነ አንድ ኮንፍራነስ በአዲስ አበባ ጁላይ 1 እንዲካሄድና በዚያው ወቅትም የሽግግር መንግሥት ለማዋቀር ውይይትና ድርድር እመዲካሄድ ስምምነት ላይ መደረሱን የሚያበስር ነበር፡፡በአንድና አጭር ብቸኛ መግለጫ መለስ የሥግግሩን ሂደት አስገድዶ በመስረቅ ጠቅልሎ ኪሱ ከተተው፡፡ወዲያውም ሥልጣንን የግሉ በማድረግ የፈላጭ ቆራጭ የግፍ አገዛዙን ማስረጽ ቻለ፡፡ለዚህም ነው ከፈላጭ ቆራጭ ስርአት ወደ ዴሞክራሲ የሚደረገው የሽግግር ወቅት እጅጉን ፈታኝና አሳሳቢም የሚሆነው፡፡ማንም ግለሰብ ሆነ ፓር፤ ቀጣዩን የዴሞክራሲ ሽግግሩን እንዳይነጥቅ አለያም እንዳያጭበረብርና ወዳልተፈለገ አቅጣጫ እንዳያስኬደው ሁሉም ነቅቶ መጠበቅ ያለበት፡፡የሽግግሩ ሂደት በራሱ ሊተገበር የሚገባውን የ‹‹ዴሞክራሲ›› ምንነት ያሳያል፡፡የተለያዩ የሽግግር ሂደቶችናማካሄድና የተለያዩ ውጤቶች ማግኘት ይቻላል፡፡በዚህም ውጤት ሚዛናዊ የሆነ የባለመብቶቹ ድርሻም ሊሰመር ይችላል፡፡ለምሳሌ የሽግግሩ ሂደት በጎሳ ፖለቲካ ላይ ያተኮረ ከሆነ፤በጎሳዎቹ መሃል በሚበቅል ፉክክርና እኔ እበልጥ እኔ እበልጥ የበላይነት፤የዴሞክራሲው ሂደት ሊቀጭጭና ሊከስም ይችላል፡፡አንዱ ግለሰብ የፖለቲካ መሪ፤አለያም ስብስብ የሽግግር ሂደቱን ለመጥለፍ ከተሳካላት የሚያስከትለው ውጤት አሳዛኝና አሳፋሪ ነው የሚሆነው፡፡
ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርአት ሽግግር ምን ማለት ነው? በኔ አመለካከት፤ ቀላል ነው፡፡ መሰረታዊ በሆነው እሳቤ እጀምራለሁ፡፡በኢትዮጵያ ዴሞክራሲ በጉልበት፤በሃይል፤በብልጠት፤ወይም በድብብቆሽ ክፉ ምግባር አይገነባም፡፡በአንደ ፓርቲ፤ በአንድ ሰው፤በተወሰኑ አንጃዎች፤በአንድ ብሄር ወይም ጊሳ፤አለያም በአንድ ውሱን በሆኑ የህብረተሰብ ቡድኖች ዴሞክራሲ በኢትዮጵያ መሰረቱ ሊጣል አይችልም፡፡የአፍ መደለያ ብቻ በሆነ፤አንድነት፤መግባባት፤መፈቃቀር በሚል ሽንገላ ብቻም ሊበቅል አይችልም፡፡ በኢትዮጵያ ዕውነተኛው ዴሞክራሲ ሊያብብና ተግባራዊ ሆኖ ሕዝባዊ ተቀባይነት የሚኖረው፤ከፈላጭ ቆራጭነት የወጣና ሁሉንም አቀፍ የሆነ ስብስብን ያካተተ፤ለውይይት የሚያበቃ፤መደራደርና መከራከር፤ መግባባትና መቻቻል እንዲሁም መተማመን፤ ሃሳብ መለዋወጥ የሚታይበት የነገዋን ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ማዕከል ያደረገ ሽግግርና ሂደት ሲኖር ብቻ ነው፡፡
ይህ ምናልባት አስቸጋሪ መስሎ ሊታይ ይችላል፡፡ የኔ ሃሳብ፤የዴሞክራሲ ሽግግር ውጤታማ ሊሆን እንዲችል፤ በጣም ወሳኝና አስፈላጊው ጉዳይ የባለጉዳዮች መብዛትና አንድነት ሳይሆን፤በባለጉዳዮቹ መሃል መተማመንና መግባባት፤ የግቡን መድረሻ በመተማመን ያቀዱትን ወደ ተግባር ለመለወጥ ፈቃደኝነት፤ ለዚህ ዓላማ የጸናና ቆራጥ እምነትና ፍላጎት ያላቸውን፤ምንነቱን አውቀውና ተገንዝበው ለዚህ ጉዳይ ያላሰለሰ ጥረትና ለድካም አይበገሬነት ያላቸውን፤ በግልጽ በመነጋገር አለመግባባትን የሚያስቀሩ ሆነው ከተዋቀሩ ይህ ነው ዋናው መሠረት፡፡‹‹ሁላችንም በአንድ ጀልባ ላይ ነን፡፡የምንቀዝፈውም የግፍ፤ የጭቆና፤ የሙስና፤የመብቶች ገፈፋ ማዕበል ወደሚፈልቅበት አቅጣጫ በመሆኑ፤ወይ አብረን እንዋኛለን ካልሆነም አብረን እንሰምጣለን››ነው ዓላማችን፡፡
የሽግግር መስኮቱ ከተከፈተና ከመከፈቱ አስቀድሞ መደረግ ያለበት ምንድን ነው?ከመሰረቱ እንጀምር፡፡ ምን ዓይነት ‹‹ዴሞክራሲ››ነው የምንፈልገው? በሁለት ገዢዎች የግዛት ዘመን፤‹‹አብዮታዊ ዴሞክራሲ›› ተብሎ በተቀረጸ የግፍ ሂደት ጊዜያት አሳልፈናል፡፡ለኢትዮጵያ፤ አሁን ኮንሰቲቴዩሽናል ዴሞክራሲ ተፈላጊና ወቅታዊ ነው?፡፡ የኮንስቲቲዩሽናል ዴምክራሲ አወቃቀርና ንድፈ ሃሳብ፤የመንግሥትን ስልጣንና የፖለቲካ ስልጣንን ለሚመሩ ሃይላቸውን የሚለካ ነው፡፡ሕገ መንግሥቱ የሕጎች ሁሉ የበላይ ሕግ ሆኖ የተቀረጸ ሲሆን ግለሰብም ሆነ ምንም አይነት ድርጅት አለያም ሃይል ሊያጣምመው፤ በዘፈቀደ ሊቀንሰው፤ ሊጨምር፤ እንዳሻ ሊቀነጣጥቡትም አይችሉም፡፡ ሕገ መንግሥቱ መተዳደርያና መመርያ፤ ሃገርንና ሕዝብን ጠባቂ እንጂ ለመበደያ፤ ለግፍ መፈጸሚያ፤ ለጥቃት ደንብና ስርአት ማውጫ ጨርሶ ሊሆን አይችልም፡፡
የመንግሥት ባለስልጣናት ስልጣናቸው የሚለካውም ሆነ የሚገደበው፤ እነሱም በጥቅም ላይ የሚያውሉት ከሕገመንግስቱ አተረጓጎም አኳያና ከዓለም አቀፍ ድንጋጌዎች ጋር በተደረገው መግባባት ብቻ እንጂ;ከዚያ ውጪ አይፈጸምም፡፡በፌዴራሊዝም አወቃቀር ሥልጣን በማዕከላዊና በክልላዊ መንግስቶች መሃል ተለክቶ ሊከፋፈል ይችላል፡፡(የጎሳ ፌዴራሊዝም ማለት፤ ፈላጭ ቆራጭ አገዛዝ ለመድብለ ፓርቲ ጨቋኝና አፋኝ እንደሚሆነው ማለት ነው)የፖለቲካ ኢንስቲቲዩቶች፤በተለይም የፍትሕ አካላት፤የላዕላይ መዋቅሩ አካላት ከሆኑ ባለስልጣናት ትእዛዝና ተጠሪነት ነጻ ስለሚሆኑ፤ፍትህንና ለፍትህ አስፈላጊ የሆኑትን መስፈርቶች ያለ ሥልጣን ግፊት ያከናውናሉ፡፡ በኮኒስቲቲዩሽናል ዴሞክራሲ የፖለቲካ ፓርቲዎች በምርጫ የመሸነፍ እድል ይገጥማቸዋል፡፡(በተለይም ሕዝቡን የማዳመጥ ፍላጎት ካጡ መሸነፋቸው አይቀሬ ነው፡፡ በዚህ መሰል ዴሞክራሲ ማንም 99.6በመቶ ምርጫ ያሸንፋል ማለት ቀልድ ነው፡፡በዚህ አይነት ዴሞክራሲ መንግሽታት ሕዝቦችን ይፈራሉ እንጂ ሕዝቡ መንግሥትን አይፈራውም፡፡በኢትዮጵያ ኮኒስቲቲዩሽናል ዴሞክራሲ ወቅቱ አሁን ነው?
የፈላጭ ቆራጭ (ዲክተተርሺፕ) አገዛዝ በራሱ እስኪፈራርስ መጠበቅ?
አንዳንድ ሰዎች በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የጨቋኝ ፈላጭ ቆራጭ ገዢዎች የጭቃ ግንብ ተፍረክርኮ የሚደረመስበትን ጊዜ ለመወሰን በጣሙን ይጨነቃሉ፡፡ጋዳፊም ሂነ፤ቢን አሊ፤ሙባረክ ወይም ሳሊህ የጭቆና ግዛታቸው ማብቂያና የፈላጭ ቆራጭነታቸው ማክተሚያ መች እንደሆነ ማወቅ መች ሆነላቸውና፡፡እጅግ ውስብስብ የሆነው የደህንነት ሁኔታዎች መሰብሰቢያ ጥርቅምስ የአረቡን ዓለም ለግፍ አገዛዝ በቃኝን መነሳሳት መች ደረሰበት፡፡የጋንዲ የብረት ግንብ ግን አስቀድሞ በእርግጠኝነት አስቀምጠፐታል፡፡ ‹‹ግፈኞች፤ ነፍሰገዳዮችና ፈላጭ ቆራጭ ገዢዎች ለጊዜው የማይደፈሩ ቢመስሉም መጨረሻቸው ግን አይሆኑ ሆነው መውደቅ መሆኑ አያጠያይቅም፤ ይህን ነው ዘወትር ማሰብ››
የግፈኛ ገዢዎች ውድቀት ቀኑን ጠብቆ መምጣቱ የማየቀር በመሆኑ፤ወቅቱን ማፋጠንም ይጠበቃል፡፡ ይህንን ደግሞ በአካባቢያችን በሚከናወነው የውድቀት ሂደት ማመዛዘን ይቻላል፡፡ፈላጭ ቆራጭ ገዢዎች ውስጣቸው ባዶና ደካሞች፤ልፍስፍሶችና ዋዣቂዎች ናቸው፡፡ውስጣዊ ገጽታቸውም በሙስናና በሥልጣናቸው አላግባብ መባለግ የተበከለና የተመረዘ ነው፡፡ የሚፈልጓቸውን የሕብረተሰብ አባላት ልብና ሕሊና ጨርሶ መግዛት ስለማይችሉ፤ ድጋፍ ይሆኑናል ብለው የሚያስቧቸውን ሰዎች ታማኝነታቸውን በማስፈራራት፤በጉልበት በመያዝ፤ ተቃዋሚዎችን በማስደንገጥ፤በማወናበድ ተግባር ላይ ለማሰማራት ይጥራሉ፡፡የአመራራቸውም እምነት ባለማመን ላይ የተመሰረተ ሲሆን የራሳቸውንም ደጋፊዎች በጥርጣሬ አይን ነው የሚመለከቱት፡፡
በኢትዮጵያ ያለው የግፈኞች አገዛዝ መጨረሻው በሚሊዮኖች በሚቆጠሩ በተራቡ፤የተጨነቀው ገጠሬና የቀን ሠራተኛው፤ለዓለም አቀፍ የመሬት ዘራፊዎች መሬቱ እየተነጠቀ በሳንቲሞች የተሸጠበት ዜጋ፤የትምህርትና የሥራ እድል በተነፈጉት ቁጥር ስፍር በሌላቸው ወጣት ሴቶችና ወንዶች ኢትዮጵያዊያን፤በቤት እጦት የሚንገላቱት ብዙዎች፤እጅና እግራቸውን ታክስ ካሠራቸው የንግዱ ሕብረተሰብ አባላት፤በጠራራ ጸሃይ መብታቸውን ተገፈው በየእስር ቤቱ በተወረወሩት ኢትዮጵያውያን ዜጎች ገጽ ላይ በጉልህ ይነበባል፡፡ለዚህ መፍትሄውን አምጡ ቢባል፤ዜጎች ክብራቸውን ላለማስደፈር ከምንም በላይ አድርገው ሲያምኑና ለዚህም እጅ ለእጅ ተያይዘው መከላከል ሲጀምሩ ነው መልሱ የሚሆነው፡፡ በአረቦች መነሳሳትም የታየው ይሄው ነው፡፡
በዴሞክራሲያዊ ሽግግር ወቅት የምርጫን የተለመደና የሃሰት ውንብድና ተግባር መጠበቅ
አንዳንድ ሰዎች ከግፍ አገዛዝ ወደ ዴሞክራሲያዊ የአስተዳደር ስርአት ሽግግሩ በምርጫ በተአምር ፈላጭ ቆራጮች ሲወድቁ ይከናወናል ብለው ያምናሉ፡፡ማንኛውንም የዴሞክራሲ ጉዳይ በምርጫ ውጤት ላይ ትቶ መጠበቅ አስተማማኝነቱ ያጠራጥራል፡፡በ1991 ሽግግር መለስ ዜናዊም ለኸርማን ኮኸን ነገሮችን ለማስተካከል ምርጫ እንደሚከናወን ከመለስ ዜናዊ ቃል ተገብቶለት እንደነበር ያስታውሳል፡፡ ሆኖም የ2005ን ምርጫ ሂደትና ውጤት ከተመለከተ በኋላ ኮኸን የመለስ ተቃዋሚ ሆነ፡፡ስለዚህም ሲያስረዳ፤ መለስን በአደባባይ የሚቃወምበትና የሚኮንንበት ምክንያት ‹‹የ2005 ዓ/ም ምርጫ በመሰረቁ ነው፤ በትክል የምርጫው ውጡት በመለሶች ተሰርቋል›› ይላል፡፡‹‹ከ2005 በኋላ በኢትዮጵያ ምርጫ ውጤት መሰረቅ ብቻ ሳይሆን፤ገዢው ፓርቲ ስለድል አድራጊነቱ ሲናገር መቀለጃ ሆኖ ታይቷል፡፡መዘባበቻ ሆኗል፡፡‹‹በ2010 ግንቦት ያገኘነውን 99.6 በመቶ የምርጫ ውጤት ልብ በሉ›› ‹‹በ2008 ዴሞክራሲያችን ያሰገኘልንን የክልሎች ምርጫ ውጤት 3.4 ሚሊዩን መቀመጫዎች ተቃውሞ የቀረበባቸውን መቀመጫዎች መዘንጋት አይገባም››
ኢብሽካ፡ ቁርጥ ቀን!
ግለሰቦችን፤ስበስቦችን፤ከስር ጀምሮ ለሚካሄደው የዴሞክራታይዜሽን አስተዋጽኦ የማሰባሰቡ ዓላማ ተስፋ ሰጪና አበረታችም ነው፡፡ግለሰቦችን የሲቪክ ማህበረሰብ አባላትን ተሟጋቾችንና ተንቀሳቃሾችን ለዚሁ ዓላማ ማሰለፉና፤በስቃይ ላሉት፤መከላከያ ለሌላቸው መከላከልን፤የሰውን ልጅ ክብር ወደነበረበት ተፈጥሮአዊ ሁኔታ መመለሱ፤ድምጻቸው ለታፈነው ድምጽ መሆን ዋጋ የማይተመንለት ታላቅ ተግባር ነው፡፡ከስር መሰረቱ አንስቶ ከግፈኛ ገዢዎች የፈላጭ ቆራጭ ግዢ ለመላቀቅ የሁሉም መሰለፍ በርካታ ሁኔታዎችን ያስተካክላል፡፡በወቅቱ ፈተናና ግፍ ተስፋችን ሁሉ ተስፋ ሲያጣ፤የነገው እምነታችን በዛሬው ግፍ ሲዋጥብን፤እልህን በእልህ ለማሸነፍ ቆርጠን መነሳት አለብን፡፡ለዚህም ከየዕለት ተግባራችን 1 በመቶ በኢትዮጵያ ለሚከናወነው የግፈኞች ፈላጭ ቆራጭ አገዛዝ መገርሰሻ ሲውል ሃገራችንን ወደ ዴሞክራሲዊ ስርአተ ማሕበር እናሸጋግራታለን፡፡ይህ ነው የሁሉም ራዕይ ሊሆን የሚገባው፡፡