የምሁራን የህሊና ድህነት እና የኢትዮጵያ ረሀብ ከሀዲዎች የሞራል ልዕልና ኪሳራ፣

ከፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማርያም    

ትርጉም በነጻነት ለሀገሬ

Famine No 5“በኢትዮጵያ ውስጥ ረሀብ የለም…ኢትዮጵያውያን ለሞት በሚያበቃ ረሀብ እየተራቡ አይደለም…ሰዎች እየሞቱ አይደለም…እንስሶች በወኃ ጥም ምክንያት እየሞቱ ነው…” አሌክስ ዲ ዋል

ባለፈው ሳምንት በኒዮርክ ታይምስ (ዓለም አቀፍ ህትመት) በቀረበ ጽሁፍ አሌክስ ዲ ዋል ከአዲስ አበባ ኢትዮጵያ “የታላቅ ረሀቦች ዘመን“ ፍጻሜ መሆኑን በታላቅ ኩራት በመናገር ኢትዮጵያውያን ለሞት በሚያበቃ ረሀብ አይጠቁም፣ ይልቁንም በውኃ ጥም ምክንያት እንስሶቻቸው ብቻ በመሞት ላይ ይገኛሉ በማለት አውጇል፡፡ በእርግጥ ይህ አባባል የዩኤስኤአይዲ/USAID አስተዳዳሪ የሆነችው ጋሊ ኢ. ስሚዝ በቅርብ ጊዜ ሰጥታው ከነበረው ቃለ መጠይቅ ጋር አንድ እና ተመሳሳይ ሆኖ ይገኛል፡፡ ሁለቱም አንድ ዓይነት የመነጋገሪያ ነጥቦችን እንደሚጠቀሙ እገምታለሁ፡፡

ዲ ዋል እንዲህ በማለት አውጇል፡

“በሶስት አስርት ዓመታት ጊዜ ውስጥ የተከሰተው አስከፊ ድርቅ 20 ሚሊዮን – የሀገሪቱን ሕዝብ አንድ አምስተኛ ለሚሆኑ ኢትዮጵያውያን ተስፋ አስቆራጭ ለሆነ የምግብ እህል እጥረት እንዲዳረጉ አድርጓል፡፡ እንደዚህም ሆኖ የሞት መጣኔ እንደሚጠበቀው በማደግ ላይ የሚገኝ አይደለም፡፡ በሌላ አባባል ኢትዮጵያውያን ለሞት በሚያበቃ ረሀብ እየተጠቁ አይደለም…ይልቁንም እንስሶቻቸው በውኃ ጥም ምክንያት እየሞቱ ነው፡፡“ (አጽንኦ ተጨምሯል፡፡)

ዲ. ዋል የህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ (ዘ-ህወሀት) ያለውን አስደናቂ የሆነ ጥበብ በማድነቅ የረሀብ አደጋውን ያሸነፈ መሆኑን እንዲህ በማለት በአስመሳይነት ለማመላከት ሞክሯል፡፡

“ከ30 ዓመታት በላይ ለሚሆኑ ጊዚያት ስለረሀብ እና ስለሰብአዊ እርዳታ ጥናት አድርጊያለሁ፣ እናም ባለፈው ወር በኢትዮጵያ ባደረግሁት ጉብኝት ስለተመለከትኩት ነገር ለማመን ዝግጁ አልነበርኩም፡፡ በሀገሪቱ ሰሜናዊ እና መካከለኛው አካባቢዎች በተጓዝኩ ጊዜ ለቻይና የምድር ባቡር እና በቅርብ ጊዜ ውስጥ ከውጭ ለገቡ የጭነት ማጓጓዣ ተሸከርካሪዎች ምስጋና ይግባ እና በጣም ትንሽ እና ሩቅ ለሆኑ መንደሮች ከውጭ ሀገር የመጣ ስንዴ ሲቀርብ አይቻለሁ፡፡ የውኃ ጉድጓዶች በደረቁባቸው አካባቢዎች ውኃ ይታደል ነበር፡፡ በምግብ ንጥረ ነገር የተጎዱ ህጻናት በበቂ የሰው ኃይል በተሟሉ ክሊኒኮች ይታከሙ ነበር፡፡“

ዲ. ዋል በአስመሳይነት የዘ-ህወሀትን የመልካም አስተዳደር (በምዕናብ የሚነገረውን አላልኩም) ጉብዝና በማድነቅ ረሀብን እና ቸነፈርን ከኢትዮጵያ ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ለማጥፋት ድል የተቀዳጀ መሆኑን እንዲህ በማለት የምስክርነት ቃሉን ሰጥቷል፡

“በአንድ ወቅት የረሀብ ተምሳሌት የነበረችው ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ረሀብን እንዴት ለመከላከል ቻለች? ሆኖም ግን በከፊል ለአንዳንድ መልካም አጋጣሚዎች ምስጋና ይግባ፣ በይበልጥም ለሰላም፣ ለግልጸኝነት እና አስተማማኝ እና ብቃት ላለው የዕቅድ ዝግጅት፡፡ ኢትዮጵያ ሌላውን አደጋ የማስወገድ ስኬቷ ማረጋገጫ ነው፣ ምክንያቱም ረሀብ እንደዋና ጉዳይ ሆኖ የቆየው ለፖለቲካ መጨቆኛ መሳሪያ ሆኖ ያገለግላል የሚለውን አካሄድ ስለሚይዝ ነው፡፡“

ዲ ዋል የዘ-ህወሀት ጥበብ የተሞላበት ያለውን የምግብ ዋስትና አያያዝን ልባዊ አድናቆት ከሰጠ በኋላ የንግግር ጠብመንጃውን በመንግስቱ ኃይለማርያም ወደሚመራው ወታደራዊ አገዛዝ በማዞር ወታደራዊው አገዛዝ የንግድ መስመሮችን ዘግቶ እንደነበር፣ ገበያዎችን በቦምብ ያጋይ እንደነበር እና በትግራይ እና በኤርትራ በአመጺ ኃይሎች ተይዘው በነበሩ አካባቢዎች የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ እንዳይደርስ መሰናክል ሆኖ እንደነበር ተችቷል፡፡ አሁን በህይወት የሌለው መለስ ዜናዊ እና ዘ-ህወሀት ነጭ ፈረሳቸውን ወደ አዲስ አበባ በማስጋለብ ሀገሪቱን ከመጥፎ ጊዜ ያዳኑ መሆኑን እዲህ በማለት ተናግሯል፡

“የመንግስቱ አገዛዝ እ.ኤ.አ በ1991 ተደመሰሰ፡፡ በጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ መንግስት አመራር ሰጭነት የቀድሞው የሽምቅ ውጊያ አራማጅ የነበረው ድርጅት ሀገሪቱ ፈጣን የሆን የኢኮኖሚ ልማት ለማምጣት እንድትችል ቅስቀሳውን እያካሄደ ኢትዮጵያ በትውልዱ ለመጀመሪያ ጊዜ ውስጣዊ ሰላሟን ማጣጣም ጀመረች፡፡ አካባቢያዊ የሆኑ ድርቆች ነበሩ ሆኖም ግን ረሀብ አልነበረም – ከአንድ ጊዜ በስተቀር“ ብሏል

ዲ ዋል የምግብ እህል እጥረት ችግርን በዘ-ህወሀት አገዛዝ ቀላል ነገር አድርጎ ቆጥሮታል፡፡ እንዲህ የሚል መግለጫ ሰጥቷል፣ “እ.ኤ.አ በ1999 በደቡብ የሀገሪቱ ክፍል የተከሰተ እና 29 ሺ የሚሆኑ ዜጎችን የገደለ የምግብ እህል እጥረት ነበር፡፡ በእርግጥ ያ ረሀብ አልነበረም፡፡“ አዎ እውነት ነው 29 ሺ ሰው የቀጠፈው ረሀብ ሳይሆን ከቅንጦት የአትክልት ቦታ የተለያዩ አትክልቶች እጦት ነው፡፡ ሌላው ታላቅ ድርቅ እ.ኤ.አ በ2002 በመላ ሀገሪቱ የረሀብ መንስኤ ሆነ (ረሀብ ግን አልነበረም)፡፡ ሆኖም ግን በቀጣዩ የመኸር ዓመት ዲ ዋል ጉብኝት እያደረገ በነበረበት ወቅት በወሎ (ሰሜን)፣ በሀርርጌ (ምስራቅ) እና በሲዳማ እና በወላይታ (ደቡብ) ሁሉም ነገር ደህና ሆኖ ነበር፡፡

ዲ ዋል እ.ኤ.አ በ2015 እንዲህ የሚል የክርክር ጭብጡን አቅርቦ ነበር፣ “ኤል ኒኖ ለበርካታ አስርት ዓመታት አስከፊ የሆነ ድርቅን አስከትሏል፡፡ ሆኖም ግን ኢትዮጵያ ከመቸውም ጊዜ በላይ የበለጠ ዝግጅት አድርጋ ነበር፡፡ መንግስት የተለያዩ የምግብ እና የገንዘብ እርዳታዎችን በማቅረብ የምግብ እህል እጥረት ያለባቸውን ቤተሰቦች የሚያግዝ ፕሮግራም ጀምሯል፡፡ የድርቅን ውጤት ለመቋቋም፣ የውኃ ማቆሪያ ቦታዎችን እንዲታደሱ በማድረግ፣ የደን ልማት ፕረጎራምን ተግባራዊ በማድረግ፣ በተለይም በገጠር አካባቢዎች መንገዶችን እና ክሊኒኮችን ለመግንባት  የሚያስችሉ እርምጃዎችን መውሰድ ጀምሯል“ ብሏል፡፡

እ.ኤ.አ የ2015/16ን ኢል ኒኖ ማስተዳደር መቻል ሌላ ምንም ሳይሆን ኬክን የመግመጥ ያህል ቀላል ነገር ነው

ምክንያቱም መንግስት ድንገት የነዳጅ ዋጋ ያሻቀበ እንደሆን በሚል ስሌት ያስቀመጠውን አንድ ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር በማዞር ለድርቁ እርዳታ ሊያውለው ችሏልና፡፡

ዲ ዋል በኢትዮጵያ ውስጥ እንደዚህ ያሉ ጭማቂ የአሉባልታ መረጃዎችን ማወቅ የቻለው እንዴት እና በምን ዓይነት አኳኋን ነው? ዲ ዋል ስለዚህ ጉዳይ የገንዘብ እና የኢኮኖሚ ሚኒስትሩ አብዱላዚዝ መሀመድ ነግሮኛል ነው እያለ ያለው፡፡

ዲ ዋል በኢትዮጵያ ውስጥ ምንም ዓይነት ረሀብ የለም በሚለው ትረካው እንደ አሮጌው የዘ-ህወሀት ጮሌ አጭበርባሪ ሸፍጠኝነት ኢኮኖሚው እንደ ሮኬት ወደ ላይ ተመንጥቆ እንደነበር በመግለጽ አሁን ግን ያሽቆለቆለበት ሁኔታ መፈጠሩን በመጠቆም እንዲህ በማለት የተሰማውን ሀዘን ይፋ አድርጓል፣ “ኢኮኖሚው በድርቁ ክፉኛ ይመታል፡፡ እንስሶች በውኃ ጥም ይሞታሉ…የሀገር ውስጥ ጠቅላላ ምርት/GDP የዕድገት መጣኔ እ.ኤ.አ በ2014 ከ10 በመቶ በላይ ከነበረበት በማሽቆልቆል እ.ኤ.አ በ2015/16 ወደ 8.5 በመቶ ይወርዳል፡፡ ሆኖም ግን አሁንም ቢሆን 8.5 በመቶ የኢኮኖሚ መጣኔ ዕድገት አስደማሚ የዕድገት ቁጥር ነው፡፡ እናም ሰዎች እየሞቱ አይደለም ነበር ያለው፡፡

በእርግጥ ዲ ዋል የዘ-ህወሀትን ታማዕኒነት የሌለውን የቅጥፈት አሀዝ እና ተራ ውሸት እውነት እንደሆነ አድርጎ በመቁጠር ሆን ብሎ ውሸትን በማባዛት ላይ ይገኛል፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ባለሁለት አሀዝ የኢኮኖሚ ዕድገት መጣኔ አለ እያሉ በቅጥፈት የኢትዮጵያን ሕዝብ እና የዓለም አቀፉን ማህበረሰብ ሲያወናብዱ የቆዩትን ዘ-ህወሀትን፣ የዓለም ባንክን፣ ዩኤስኤአይዲ/USAIDን እና ሌሎችንም በማጋለጥ ተራ ውሸት መሆኑን በተጨባጭ መረጃ በማጋለጥ እና በመገዳደር አፋቸውን እንዲዘጉ አድርጊያለሁ፡፡ በአሁኑ ጊዜ እውነታው አፍጥጦ የመጣባቸው በመሆኑ አፋቸውን ለጉመው ጸጥ ማለትን መርጠዋል፡፡ ተፈጥሮ በሚዳሰስ እና በሚጨበጠው ክስተቱ ውሸታቸውን እና ተራ ቅጥፈታቸውን የውኃ ላይ ኩበት አድርጎባቸዋል፡፡ በአሁኑ ጊዜ የዓለም ባንክ፣ የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት፣ ዩኤስኤአይዲ/USAID እና ሌሎቹ የድህነት ወትዋች አቃጣሪዎች ሁሉ እንደ ቀድሞው ሁሉ የባለሁለት አሀዝ የኢኮኖሚ ዕድገት መጣኔ እያሉ ህዝብን ማታለል መቀጠላቸውን አታዩም፣ ምክንያቱም ተራ ቅጥፈት እና ባዶ ውሸት መሆኑን ያውቃሉና፡፡

ዘ-ህወሀት ባለፉት አስር ዓመታት አስመዘገብኩት እያለ ሲደነፋ የቆየበትን ተራ የውሸት እና የቅጥፈት የኢኮኖሚ ዕድገት መጣኔ በየጊዜው እየተከታተልኩ ከምንም ጥርጣሬ በላይ ሳጋልጥ እና ለሕዝብ ይፋ ሳደርግ ቆይቻለሁ፡፡ ዲ ዋል በዘ-ህወሀት እና በዩኤስኤአይዲ/USAID የአሀዝ መቀቀያ ቶፋ ውስጥ እየተቀቀሉ የወጡጡትን የቅጥፈት አሀዞች እንደ እውነተኛ እና ትክክለኛ አድርጎ በመቀበል የኢኮኖሚ ዕድገት መጣኔው ባለሁለት አሀዝ ነው እያለ የሚያቀርበውን ወደ ጎን ትቶ በእውነተኛ እና በሀቀኛ መንገድ እውነታውን ማረጋገጥ እንዲችል እጠይቀዋለሁ፡፡ እንደዚሁም ሁሉ ዲ ዋል እንስሶች በውኃ ጥም እየሞቱ ነው፣ ሰዎች ግን እየሞቱ አይደለም የሚለው ነገር ለእኔ አይገባኝም፡፡

የእንስሳት ሀብት ምርቱ ለኢትዮጵያ የገጠር ግብርና ኢኮኖሚው ዋና አንቀሳቃሽ ሞተር እና ለአርበቶ አደር ወገኖቻችን የህይወት ዋስትና አይደለምን? እንስሶች በገፍ እያለቁ ከሆነስ ህዝቡ ሳይሞት ለምን ያህል ጊዜ ይቆያል ተብሎ ይታሰባል?

ባለፉት አስር ዓመታት ባለሁለት አሀዝ የኢኮኖሚ ዕድገት መጣኔ እያስመዘገበች ነው እየተባለ በሚደሰኮርባት ሀገር እና የኢኮኖሚ ዕድገት ግለቱ ከዓለም ሀገሮች በመጀመሪው ረድፍ ላይ ይገኛል እየተባለ ሌት ቀን በሚዘመርላት ምድር እንደገና 20 ሚሊዮን የሚሆነው ሕዝቧ በድርቅ ተጎድቶ የሚላስ የሚቀመስ እየጠፋ ነው ሲባል ለእኔ እጅግ በጣም አስደንጋጭ እና እንቆቅልሽ ነገር እንደሆነ ማሰብ እችላለሁ፡፡

ሆኖም ግን ያለው እውነት ይኸው ነው፡፡

ለመሆኑ አሌክስ ዲ ዋል ማን ነው?

de waalአሌክስ ዲ. ዋል ለዘ-ህወሀት ወትዋች የገንዘብ ቅጥረኛ አቃጣሪ ይሆን አይሆን የማውቀው ነገር የለም፡፡

እንደዚሁም ሁሉ አሌክስ ዲ ዋል ለዘ-ህወሀት ወትዋች ጋዜጠኛ፣ የሜዲያ ወይም ደግሞ የሕዝብ ግንኙነት ወኪል ስለመሆን አለመሆኑ የማውቀው ነገር የለኝም፡፡

አለያም ደግሞ አሌክስ ዲ ዋል የዘ-ህወሀት ዓለም አቀፍ ስልታዊ የኮሙኒኬሽን ኃላፊ ስለመሆን አለመሆኑ የማውቀው ምንም ዓይነት ነገር የለም፡፡

ወይም ደግሞ አሌክስ ዲ ዋል ለዘ-ህወሀት ቅጥረኛ ሎሌ ስለመሆን አለመሆኑ የማውቀው ነገር የለም፡፡

ስለ ዲ ዋል የማውቀው ነገር ቢኖር የዓለም ሰላም መሰረት ዋና ዳይሬክተር/Executive Director of World Peace እና በፍሌቸር ትምህርት ቤት የቱፍትስ ዩኒቨርሲቴ የምርምር ፕሮፌሰር/Research Professor at The Fletcher School, Tufts University ሆኖ ስሙ ተመዝግቦ የሚገኝ መሆኑን ነው፡፡ እ.ኤ.አ በ1984-85 በዳርፉር ተከስቶ በነበረው ድርቅ ላይ የዶክትሬት ዲግሪውን የሰራ መሆኑን እና ስለሱዳን እና ስለአፍሪካ ቀንድ ከሚያጠኑ ባለሙያዎች መካከል አንዱ እርሱ እንደሆነ አድርጎ እራሱን ይኮፍሳል፡፡ በእርሱ የሕይወት ታሪክ እንደሰፈረው እ.ኤ.አ በ2008 ስሙ ስለውጭ ፖሊሲ ከፍተኛ የሆነ ተጽዕኖ ፈጣሪ ከሆኑት ከ100 ታዋቂ ምሁራን ጋር ተጽፎ እንደሚገኝ የጠቀሰ ሲሆን እንዲሁም እ.ኤ.አ በ2009 የአትላንቲክ መንዝሊ 27/Atlantic Monthly 27 አሸናፊ “ጀግና አሳቢ” እንደሆነ አድርጎ እራሱን አቅርቧል፡፡

ዲ ዋል የአካባቢ የምግብ ገበያዎችን ለማጥናት በኦክስፋም ተቀጥሮ በትግራይ ክልል በተልዕኮ ላይ ነበር፡፡

ዲ ዋል የህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ (ህወሀት) ይፋ ያልሆነ ታሪክ ጸሐፊ የነበረ ሲሆን “ሰይጣናዊ ቀኖች፡ የ30 ዓመታት ጦርነት እና ድርቅ በኢትዮጵያ“ በሚል ርዕስ መጽሐፍ የጻፈ ሲሆን መጽሐፉ በዋናነት በወታደራዊው የደርግ አገዛዝ ህወሀትን ለማጥፋት እና እረፍት የለሽ በነበረው የጦርነት ዘመቻው ላይ ያነጣጠረ ደርግን በመገዝገዝ ለመጣል የሚያስችል የመጥረቢያ ስራ ነበር፡፡

ዲ ዋል እ.ኤ.አ በ2013 የአምባገነኑ መለስ ዜናዊ አንደኛ ሙት ዓመት በሚታሰብበት ዕለት በቦታው በመገኘት መልዕክት አስተላልፏል፡፡ በዚያኑ ዕለት ባደረገው ንግግር ዲ ዋል እንዲህ ብሎ ነበር፣ “የመለስ ሁለተኛው የደህንነት መርሆ ምሰሶ ብሄራዊ የሀገር ኩራት ነበር፡፡ መለስ በባዶ ሆድ እየተባለ የሚጠራውን አጥባቂ ብሄረተኝነትን የማራመድ መርሆን ያወግዝ ነበር“ ብሏል ስለሀገር ፍቅር ያለውን የወረደ እና የዘቀጠ አስተሳሰብ ሲገልጽ፡፡

በአሁኑ ጊዜ 20 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን በመሞት ላይ ናቸው ምክንያቱም በባዶ ሆድ ናቸው፣ እናም ዲ ዋል እንዲህ ይላል፣ “በኢትዮጵያ ውስጥ ረሀብ የለም፡፡“

እ.ኤ.አ ሀምሌ 2015 በተንጠልጠል ላይ በነበረው የጋይሌ ኢ. ስሚዝ የዩኤስኤአይዲን/USAID አስተዳዳሪ ሆኖ መሾም አለመሾም ጋር በተያያዘ መልኩ ሴኔቱ ለማጽደቅ በተሰበሰበበት ጊዜ እርሱን የመሞገት ዕድል አግኝቸ ነበር፡፡

በአንድ ግልጽ በሆነ ደብዳቤ (“የጋይሌ ኢ. ስሚዝ ዉዳሴ“ የሚል ርዕስ ሊሰጠው ይገባል ብየ የማምንበት ደብዳቤ የእርሷን ሹመት ካለማጽደቅ ይልቅ እርሷን መልዓክ አድርጎ የሚያቀርብ) ዓይነት ደብዳቤ በቦስተን ግምገማ ላይ በማቅረብ ዲ ዋል ስሚዝ ከምንም ኃጢያት ነጻ የሆነች እና ምንም ዓይነት እንከን የማይገኝባት ቅዱስ እንደሆነች እና ከምንም በላይ ጠቃሚ እንደሆነች አድርጎ በማቅረብ የዩኤስ ሴኔት የእርሷን አስተዳዳሪነት ለምን ማጽደቅ እንዳለበት ያለ የሌለ ጥረቱን በማድረግ ሲፍጨረጨር ተስትውሏል፡፡ እብሪትን ባዘለ አኳኋን እራሱን ከፍ ከፍ በማድረግ እንዲህ በማለት ተናግሯል፣ “ማንም ቢሆን የስሚዝን ብቃት እና ችሎታ

ለመጠየቅ አይችልም፡፡“

ደህና የስሚዝን ብቃት እና ችሎታ ከጥያቄ ውስጥ በማስገባት ሹመቱ እንዳይጸድቅላት ጥያቄ አቅርቤ ነበር፡፡ ሆኖም ግን እ.ኤ.አ ህዳር 2015 ሹመቱ 79 ለ7 በሆነ መልኩ ጸድቆላታል፡፡ በዚያ የድምጽ አሰጣጥ ስነስርዓት ላይ ገለባውን ከምርት የለየንበት ነበር፡፡ ስሚዝ የዩኤስኤአይዲን/USAID አስተዳዳሪ ከሆነች በኋላ ለምትሰራው ስራ ሁሉ ተጠያቂ እንድትሆን እና በዚያው መሰረት መስራት እንድትችል ፈልጌ ነበር፡፡

ነገር ግን አሌክስ ዲ ዋል እራሱን አሁን በህይወት የሌለው የአምባገነኑ መለስ ዜናዊ እና የዘ-ህወሀት ሁነኛ ጓደኛ አድርጎ ያቀረበው ለመሆኑ በእርግጠኝነት እርሱ ማን ነው?

እ.ኤ.አ ነሐሴ 2012 በአምባገነኑ መለስ የቀብር ስነስርዓት ዲ ዋል በኒዮርክ ታይምስ መጽሄት መለስን በምሁራዊ ችሎታው ከእኩዮቹ ሁሉ ከሁሉም ልቆ የሚገኝ ጓድ መለስ እንደሆነ እንደሚያውቀው የድንቢጥ ምስክርነቱን ሰጥቷል፡፡

በአሁኑ ጊዜ አሌክስ ዲ ዋል ምንም ዓይነት ሀፍረት የማይሰማው፣ የእምነቱ ተከላካይ እና አሁን በህይወት የሌለው የአምባገነኑ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስቡ ፈላጭ ቆራጭ የነበረውን መለስ ዜናዊን መልዓክ አድርጎ የማቅረብ ዝባዝንኬውን ቀጥሎበት ይገኛል፡፡

ዲ ዋል እርሱ እራሱ አምባገነኑን መለስን እና የእርሱን መሰል ወሮበላ ጓደኞቹን በምጣኔ ሀብት ትምህርት እንዳሰለጠነ የመለስን ጽሁፎች ሁሉ እንደገመገመ ይናገራል፡፡ ዲ ዋል አምባገነኑን መለስን በማስዋብ እና ቅዱስ አድርጎ በማቅረብ መለስ እና የእርሱ ዘ-ህወሀት ከሌሉ ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ወደ አመድነት እንደምትቀየር እና ከታሪካዊ ትውስታ እንደምትጠፋ እንዲህ በማለት ድፍረትን በቀላቀለ መልኩ ተናግሯል፡

“ለ25 ዓመታት ገደማ ያህል ከእርሱ ጋር ስለፖለቲካል ኢኮኖሚ ያልተጠናቀቀውን እና ያልታተመውን የሁለተኛ ዲግሪ ማሟያ የመመረረቂያ ጽሁፉን መተቸትን ጨምሮ መደበኛ በሆነ መልኩ ለመወያያት ዕድሉን አግኝቸ ነበር፡፡ በዚህ ጊዜ ሀሳቡ ከፍ እያለ መጣ፣ ሆኖም ግን የእርሱ መሰረታዊ መርሆዎች እና ስሜቶች እንደነበሩበት ሆነው ቆዩ…መለስ በችግር ተፈትኖ የወጣ እንደሆነ እርግጠኛነቱን ያረጋገጠ እና ህዝቡም በመከራ ተፈትኖ እንደወጣ አድርጎ ነው የሚቆጥረው፡፡ በህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ (ህወሀት) ካሉ የትግል ጓደኛ አመራር ዘንድ የጋራ ውድመት የሆነውን ነገር ጠለቅ ብሎ ያየው እና የእርሱ ሙያ ኢትዮጵያ እንደዚያ ባለው አደገኛ ሁኔታ ሳትገባ መቀጠል እንዳለባት ያውቅ ነበር“ ብሏል፡፡

ዲ ዋል (በሙያ የሰው ዘር ጥናት ባለሙያ/Social anthropologist) ሆኖ እያለ በጫካ ለነበሩት ለመለስ እና ለዘ-ህወሀት አመራሮች ስለፖለቲካል ኢኮኖሚ ውይይት ይመራ እንደነበር ልብ ይሏል፡፡ ዲ ዋል እንዲህ በማለት ምስከርነቱን ሰጥቷል፡

“መለስ ወሰኑን አቋርጦ ወደ ኢትዮጵያ በተመለሰበት ጊዜ ለመጀመሪያ ጊዜ አግኝቸዋለሁ እናም ስለፖለቲካል ኢኮኖሚ የመጀመሪያ የሆነውን ሴሚናራችንን ጀመርን… መለስ በኢህአዴግ ውስጥ ካሉት ጓደኛ የጋራ አመራሮቹ ሁሉ በአስተሳሰብ የላቀ እና ዋና የኢኮኖሚ ህልዮት አቀንቃኝ ነበር፡፡“

ዲ ዋል በአምባገነኑ መለስ ዜናዊ አንደኛ ሙት ዓመት መታሰቢያ ላይ በመገኘት “እንደ ሴሚናር ተጓዥ ሁሉ በየምሽቱ በጭነት መኪና ላይ እየተጫንኩ እጓዝ ነበር” ብሏል፡፡

እንግዲህ እግዚአብሄር ያሳያችሁ መላዕክት ያመላክቷችሁ የኢኮኖሚ ህልዮት አራማጅ እና ተንታኝ የነበረው መለስ ታላቁ ስለኢኮኖሚ ህልዮት በሰው ዘር አመጣጥ ባለሙያ/Social anthropologist ይሰለጥን ነበር ማለት ነው!

እ.ኤ.አ ግንቦት 2011 ምዕናባዊ ኢኮኖሚ በሚል ተመሳሳይ ርዕስ ትችቴን ባቀረብኩበት ጊዜ አምባገነኑ መለስ ምናባዊ ኢኮኖሚን ይተገብር እንደነበር አውቃለሁ፡፡ ምናባዊ ኢኮኖሚን እንደተመሳስሎ ነበር የተጠቀምኩበት፡፡ ሆኖም ግን መለስ ስለምናባዊ ኢኮኖሚ በሰው ዘር አመጣጥ ባለሙያ ይሰለጥን እንደነበር የማውቀው ነገር አልነበረም፡፡ ከዚህ ሌላ ምን ማለት እችላለሁ ጎበዝ!

ዲ ዋል ስለአምባገነኑ መለስ የፖለቲካል ኢኮኖሚ እውቀት ዋና ምስክር ሰጭ ሆኖ ሲናገር መለስ ለሁለተኛ ጊዜ ወደ ወደ ኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ወደ አፍሪካም የሚመጣው መሲህ ነው በማለት እንደተራራ ክቦ እንደ ሰማይ አርቆ ተናግሯል፡፡ ዲ ዋል እንዲህ በማለት አውጇል፣ “መለስ በእርግጠኝነት የመጀመሪያው አሳቢ ስለመሆኑ ሊገልጹ የሚችሉ ጽሁፎቹ ለሕዝብ ተደራሽ እንዲሆኑ በበቂ ሁኔታ ተዘጋጅተው ተቀምጠዋል፡፡ የእርሱ ያልታተሙ ጽሁፎች በሚገባ ባልተዳሰሱ በእርሱ ምሁራዊ ፍላጎቶች ላይ ያለውን ክፍተት ለመሙላት በቂ የሆኑ ሰነዶችን እንደሚያቀርቡ ተስፋ እናድርግ“  ብሏል፡፡

የመለስ ዜናዊ ጽሁፎች እየተባሉ የሚጠሩ ጥቂት ጽሁፎች በድረ ገጽ ላይ በመለቀቃቸው ምክንያት ኢንተርኔት እንደ ሕዝብ ተደራሽነት ይህንን ሁኔታ ሊያሟላ ይችላልን? ለበርካታ ዓመታት እኔ “በእርግጠኝነት እውነተኛ አሳቢ” የሚል ጽሁፍ ለማግኘት እግሬ እስከሚላጥ ድረስ በዓለም ላይ ታዋቂ በሚባሉ ቤተመጽሀፍት ሁሉአስፈልጌአለሁ፡፡ ሆኖም ግን ስለመለስ እውነተኛ ወጥ ጽሁፍ አንድም ነገር አላገኘሁም።

ሆኖም ግን መቸ እንደተጻፈ ጊዜውን የማይገልጽ እና “የአፍሪካ ልማት፡ የሞቱ ዓላማዎች እና አዲስ ጅማሮ/African Development: Dead Ends and New Beginnings“ በሚል ርዕስ የተጻፈ የመለስ ታላቅ ስራ (በጥቅስ መልክ ማቅረብ የተከለከለ የሚል ማስጠንቀቂያ የተጻፈበት) የተባለ የመጀመሪያ ረቂቅ የሚል አለ፡፡ ዋናው የኢኮኖሚ ህልዮት ተንታኝ የተባለው አምባገነን የሀረጎች ጠላት እና የተፈበረከ የውሸት አሀዝ መረጃ እያለ ከማቅረብ ያለፈ ምንም ዓይነት ታላቅ ነገር አልነበረውም፡፡ ይልቁንም አምባገነኑ መለስ የሰየመውን መጽሐፍ ርእስ ለወጥ በማድረግ “ምዕናባዊው የአፍሪካ የኢኮኖሚ ልማት” ሊለው በተገባ ነበር፡፡

በሚያስገርም ሁኔታ ዲ ዋል ለሩብ ምዕት ዓመታት ያህል እንደዚህ ያለ አገልግሎት እና ውለታ ለህወሀት ወይም ደግሞ ለዘ-ህወሀት ያበረከተ መሆኑ ቢታወቅም እስከ አሁን ድረስ በየትም ቦታ ምንም ዓይነት የክብር አባልነት አልተሰጠውም፡፡

ዲ ዋል በመንታ ምላስ ይናገራል፣

ዲ ዋል በሱዳን እና በኢትዮጵያ ስለምግብ እጥረት ምርምር አድርጓል፡፡

“የሚገድል ረሀብ“ በሚል ርዕስ እ.ኤ.አ በ1989 በጻፈው መጽሐፍ ዲ ዋል እንዲህ የሚል ጽሁፍ አስፍሮ ይገኛል፣ “እ.ኤ.አ በ2002 15 ሚሊዮን የሚሆኑ ኢትዮጵያውን ለድርቅ ሰለባነት በተዳረጉበት እና ለረገብ በተጋለጡ ጊዜ በከፍተኛ ደረጃ በዕዳ የተዘፈቁ ሀገሮች ዕዳ ቅነሳ ተነሳሽነት/highly indebted poor countries debt forgiveness initiative ብድሩን ለመመለስ በነበረው ሁኔታ መቀጠል ያስፈልጋል በማለት መንግስት ወጭውን መቀነስ ይኖርበታ…እናም ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ግዙፍ የሆነ የምግብ አቅርቦት ለማቅረብ እና ገበያውን ለማጥለቅለቅ በዓለም አቀፍ ድርጅቶች ላይ መመካት ይኖርባታል፡፡ ይህ ሁኔታ የገጠሩ ህዝብ የተጋፈጠውን እውነታ ለማሳየት ቀላል የሆነ ፈተናውን ለማለፍ ያላስቻለ አስደንጋጭ የሆነ መጥፎ ፖሊሲን የሚያሳይ ምሳሌ ነው…“

እ.ኤ.አ በ2016 ግዙፍ የሆነው የምግብ እርዳታ ገበያውን ሲያጥለቀልቀው ሊያስከት ስለሚችለው እንደምታ አይናገርም፡፡ ዲ ዋል እንዲሁ ላይላዩን በመጋለብ ቻይናዎች ለገነቡት መንገድ እና ከውጭ ለገቡት አዲስ የጭነት ማመላለሻ ተሸከርካሪዎች ምስጋና ይግባና በማለት ለትናንሽ እና ሩቅ ለሆኑት መንደሮች ከውጭ ስለሚመጣው የስንዴ እርዳታ ይናገራል፡፡

ስለማይረባ ነገር ጊዜ ማጥፋቱን አልፈልግም፣ ሆኖም ግን የአሜሪክ ግብር ከፋይ ሕዝብ በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር መጠነ ሰፊ ለሆነ የምግብ እርዳታ ይለግሳል፡፡ እ.ኤ.አ በ2015-16 በኢል ኒኖ የድርቅ ወቅት የዩኤስ አሜሪካ ግብር ከፋይ ሕዝብ 441 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር እርዳታ ለኢትዮጵያ ለግሷል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በቅርቡ ሌላ ተጨማሪ ለመለገስ ቃል ተገብቷል፡፡ እ.ኤ.አ ከ2101-2014 የኢል ኒኖ ድርቅ ባልነበረበት ጊዜ የዩኤስ አሜሪካ ግብር ከፋይ ሕዝብ ለምግብ እርዳታ በሚል 759 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ለግሷል፡፡ ዲ ዋል ስንዴ በተከተቱባቸው ጆንያዎች ላይ “ዩኤስኤአይዲ ከአሜሪካ ሕዝብ/USAID From the American People” በሚሉ ቃላት የተጻፈውን እና በቻይና ብድር በተገዙ ባቡሮች ላይ የተጫነውን (በቻይና ኩባንያዎች የተገነባውን እና የእራሳቸውን ሰራተኞች ያለምንም ኮንትራት) ማምጣታቸውን እንዳላየ እገምታለሁ፡፡ ከዕለቱ መጨረሻ አመሰግናለሁ የምትለዋን ቃል የሚያገኘው ማን ነው ቻይናዎች! አንተ መጥፎ ነገር እየሰራህ እንደሆነ አውቃለሁ፣ ግን አንተ ይህችን ቃል የምታገኝ ከሆነ እናደዳለሁ!

ዲ ዋል በጻፈው መጽሐፍ ላይ እራሱን ከፍ ከፍ እያደረገ “ስለረሀብ የተጻፉት አብዛኞቹ መጽሐፍት ከውጭ ሰዎች አመለካከት ማለትም ከእርዳታ ሰጭ ድርጅቶች እና ረሀብን ለማጥፋት የእራሳቸውን ቁርጠኝነት ከሚያሳዩት አንጻር ነው“ ብሏል፡፡ የእርሱ መጽሐፍ የሚያወሳው በረሀብ ስለሚሰቃዩት የገጠር ሕዝቦች ነው፡፡

ዲ ዋል ዓለም አቀፍ የሰብአዊ እርዳታ ለጋሾች እና አከፋፋዮች በረሀቡ በመሰቃየት ላይ ባሉት የአካባቢ ኗሪ ሰለባዎች ስቃይ እነርሱ ስልጣንን በመያዝ ስለረሀቡ የማልቀሳቸውን ሁኔታ ተችቶታል፡፡ የውጭ ኃይሎች የውጭ ጣልቃገብነትን ማድረግ እንዳለባቸው የሞራል ግዴታን ይፈጥራሉ፡፡ በውጭ ኃይሎች ትርጉም መሰረት የረሀቡ ሰለባዎች ወይ ይሞታሉ አለዚያም ይኖራሉ፡፡ የዚህ የረሀብ ኢንዱስትሪው ሌላው በተለየ መልኩ የሚቀርቡ ድርጅቶች ደግሞ ረሀብን በትክኒካዊ ትርጉም እየመነዘሩ ስለረሀብ ጉዳይ ቅድመ ማስጠንቀቂያ ስርዓት፣ የምግብ እጥረት፣ ቅድመ ዝግጅት እና የምግብ ንጥረ ነገር ምርመራ በማለት የባጥ የቆጡን ይቀባጥራሉ፡፡

ዲ ዋል እንዲህ በማለት አውጇል፣ “ስለረሀብ ትንታኔ ለመስጠት የመጀመሪያ ሆኖ መቅረብ ያለበት ጉዳይ በረሀብ በእራሱ የሚሰቃዩ ሰዎችን በመገንዘብ ነው፡፡“

ዲ ዋል በኒዮርክ ታይምስ መጽሔት ጽሁፍ በሚያዘጋጅበት ጊዜ ዘ-ህወሀት አዘጋጅቶ ከሰጠው የማስመሰያ የቅጥፈት ንግግር ውጭ በረሀቡ ወይም በድርቁ ምክንያት የሚሰቃዩት ሕዝቦች መነሻ አድርጎ ነበርን?

ዲ ዋል በድርቁ ምክንያት ስንት ሰዎች ሞቱ የሚል ጥያቄ ለመንደርተኛ ኗሪዎች አቅርቦ ነበርን?

ዲ ዋል ስለተራቡ (ይቅርታ ከፍተኛ የሆነ የምግብ እጥረት ላለባቸው ማለቴ ነው) እናቶች በመነጋገር ስንት የሚሆኑ ልጆቻቸው እንደሞቱ ጥያቄ አቅርቦ ነበርን?

ዲ ዋል በክሊኒኮች አካባቢ በመገኘት በከፍተኛ የምግብ እጥረት ምክንያት ምን ያህል ሰዎች እንደሞቱ ከጤና ባለሙያዎች ጋር ውይይት አድርጎ ነበርን?

ዲ ዋል እንስሶቻቸው ካለቁባቸው እንስሳት አርቢዎች ጋር በመገናኘት ስለሁኔታው አነጋግሯቸው ነበርን?

ዲ ዋል በምግብ እጦት ምክንያት ከተጎዱት ህጻናት ጋር በመገናኘት ለበርካታ ቀናት ምግብ ሳይበሉ በመቆየታቸው ምክንያት ምን እንደሚሰማቸው ጥያቄ አቅርቦ ነበርን?

እርሱ ባዘጋጀው ጽሑፍ ላይ በየትኛውም ቦታ ከረሀቡ ሰለባዎች ወይም ደግሞ እነርሱን ከሚረዷቸው አካላት ጋር ውይይት እና ንግግር ስለማድረጉ የሚገልጽ ተጨባጭነት ያለው አንድም ነገር የለም፡፡

ዲ ዋል በቻይና በተሰሩ መንገድች ሾፌሩን በፍጥነት እንዲነዳ በማድረግ የቻይናን የባቡር ሀዲድ መስመሮች እና በአሜሪካ ግብር ከፋዮች የተገዛውን የምግብ እርዳታ የጫኑ ባቡሮች የሚያይና የሚያጠና ይመስላል፡፡ (በጣም አመሰግናለሁ የዩኤስ አሜሪካው ዜጋ)፡፡

ለምንድን ነው ዲ ዋል በኢል ኒኖ ድርቅ ምክንያት በመሰቃየት ላይ ከሚገኙት ሰዎች ጥያቄዎችን በማቅረብ መግለጫዎችን ማውጣት ያልቻለው?

መልሱ ግልጽ እና ቀላል ነው፡፡ ዲ ዋል የድርቅ ሰለባ የሆኑትን ዜጎች ምቾት ካላት አገልግሎት ሰጭ መኪናው በፍጹም መውጣት አልፈለገም፡፡

ዲ ዋል ከብዙ ጊዜ በፊት በጽሁፉ ውስጥ አካትቷት የነበረችውን ምክር ረስቷታል፡፡ ረሀቦች  የሚሞቱ ሰዎች በተከታታይነት እና በየትም ቦታ የሚታዩባቸው ሁኔታዎች አይደሉም፡፡ ይልቁንም አስከፊ ድህነት እና እጦት በይበልጥ የሚታዩባቸው ሁኔታዎች ናቸው ብሏል፡፡

ከረሀብ ሰለባዎች ጋር ቢነጋገር ኖሮ ብዙ ሀሜቶችን ይሰማ ነበር፡፡ ምቾት ካለው ተሽከርካሪው ቢወጣ እና ከእናቶች፣ ከልጆች፣ ከእንስሳት ጠባቂዎች፣ ለመውጣት ምንም ዓይነት አቅም ከሌላቸው ደካሞች እና በልመና ከሚኖሩ ወንዶች ቢገናኝ እና ቢወያይ ኖሮ ቆዳቸውን የሸበሸበውን እና አጥነታቸውን የሰረሰረውን የረሀብን አስከፊ ሁኔታ ይገነዘብ ነበር፡፡

ዲ ዋል “በኢትዮጵያ ረሀብ የለም እናም ሰዎች እየሞቱ አይደለም“  በሚል አዘጋጅቶት በነበረው ጽሑፉ ላይ ከማን ጋር ነው በመወያየት ወደ መደምደሚያ የደረሰው?

ዲ ዋል ከዘ-ህወሀት የገንዘብ እና ኢኮኖሚ ሚኒስትር ከሆነው ከአብዱል አዚዝ ጋር ተነጋግሯል፡፡ በጽሁፉ ላይ ሌላ ማንንም አልጠቀሰም፡፡

አብዱልአዚዝ ለድርቁ የሚሆን በቢሊዮን የሚቆጠር የእርዳታ ዶላር አለ በማለት ነግሮታል፡፡ አብዱልአዚዝ ምንም ዓይነት ረሀብ የለም በማለት ነግሮታል ብዬ አስባለሁ፡፡ አብዱልአዚዝ እንስሶች ብቻ ናቸው እየሞቱ ያሉት እንጅ ሰዎች አልሞቱም በማለት ነግሮታል፡፡ አብዱልአዚዝ ዘ-ህወሀት ብሄራዊ የድርቅ ዋስትና ዕቅድ አዘጋጅቷል በማለት ነግሮታል፡፡ አብዱልአዚዝ ሕዝቡን ለመመገብ የሚያስችል ታላቅ መና በሰማይ ላይ አለ በማለት ነግሮታል! አብዱልአዚዝ…

(እ.ኤ.አ በ2011 መለስ ዜናዊ እራሱን ከፍ ከፍ በማድረግ እንዲህ በማለት አወጀ፣ “ትርፍ ምርት ለማምረት የሚያስችለንን እና እ.ኤ.አ በ2015 ያለምንም የውጭ እርዳታ እራሳችንን መመገብ የሚያስችል ዕቅድ ነድፈናል“ ብሎ ነበር ሞት ይቅለለውና፡፡ በሌላ አባባል ረሀብ፣ ቸነፈር፣ አስከፊ የምግብ ንጥረ ነገር እጥረት፣ ወዘተ ከኢትዮጵያ ለዘላለሙ ይወገዳል!) ማለቱ ነበር፡፡

እ.ኤ.አ በ2016 ዘ-ህወሀት ስለብሄራዊ የድርቅ ዋስትና ዕቅድ ያወራል፡፡ (ሁላችንም ምንም ነገር የማናውቅ ሞኞች አድርገው መቁጠር አለባቸው!)

ዲ ዋል በመጽሐፉ ውስጥ “በኢትዮጵያ ስለረሀብ መስፍን ወልደማርያም ምናልባትም ከማንም የህብረተሰብ ሳይንስ ሳይንቲስት የበለጠ ልምድ አለው“ በማለት መጽሀፉ ውስጥ ጽፏል፡፡

ለመሆኑ ዲ ዋል ስለጻፈው ጽሁፍ በአሁኑ ጊዜ በአዲስ አበባ ውስጥ ከሚኖሩት ከመስፍን ወልደማርያም ጋር ተነጋግሯልን?

የለም በፍጹም አልተነጋገረም፣  ዲ ዋል መነጋገሩን የመረጠው ከአብዱልአዚዝ መሀመድ ጋር ነበር፡፡

ዲ ዋል በመጽሐፉ እንዲህ የሚል ጽሁፍ አስፍሮ ይገኛል፣ “በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ታላቁ የእርዳታ አሰጣጥ ፕሮግረም 15 ሚሊዮን ለሚሆኑ ሰዎች ነጻ የምግብ እድላን አከናውኗል፣ እናም መንግስት እና አብዛኞቹ ለጋሽ ድርጅቶች ረሀብ የለም የሚል አንድ ዓይነት ስምምነት ላይ ደርሰዋል፡፡ የረሀቡ ሰለባ የሆኑት ወገኖች ስለዚህ ጉዳይ እንዲጠየቁ አልተፈለገም እናም ከፍተኛ የሆነ የሞት መጠን መኖሩን የሚገልጸው መረጃ እየተሰበሰበ እና እየተተነተነ ያለው አሁን ነው (ሀምሌ 2004)“ ነበር ያለው፡፡

እ.ኤ.አ ከ2015-16 ድረስ በረሀቡ ምክንያት የሞቱትን ወገኖቻችንን ብዛት ለማወቅ ሌላ ተጨማሪ ዓመታት ለመቆየት ያስፈልገናልን?

እውነታው ፍርጥርጥ ተደርጎ ሲታይ ግን የረሀቡን አካፋ የረሀብ አካፋ ብሎ መጥራት የስልጣን ጥያቄ ግንኙነት ነው፡፡ ዲ ዋል ስለዓለም አቀፍ የድህነት አቃጣሪዎች ትችት በሚያቀርብበት ጊዜ እንዲህ በማለት ጽፏል፡

“አንድን ክስተት ረሀብ ነው ብሎ መተርጎም በማህበረሰቦቸ መካከል የስልጣን ግንኙነት ጥያቄ ነው፡፡ የተወሰኑ የረሀብ እርዳታ ቴክኖሎጂዎች በገጠሩ የረሀብ ሰለባ ህዝብ ስቃይ የውጭ እርዳታ ሰጭ ድርጅቶችን የበለጠ ስልጣን እንዲኖራቸው ያደርጋሉበዚህ ክፍል [በአፍሪካ ቀንድ] የድርቁን ምንነት ለማወቅ በሚመጣበት ጊዜ የአርብቶ አደሮች ሀሳብ በዋናነት የበለጠ ትክክለኛ ነው በማለት ለመሞገት እፈልጋለሁ፡፡“

ዲ ዋል ባዘጋጀው ጽሁፍ ላይ እንስሳቱ እያለቁበት ካለው ከእንስሳት ባለቤቱ ወይም ደግሞ ከአርብቶ አደሩ ጋር ተነጋግሮ ነበርን? በፍጹም ይህንን አላደረገም፡፡ እርሱ የተነጋገረው ከአብዱልአዚዝ መሀመድ ጋር ነበር፡፡

እውነት ለመናገር ዲ ዋል ትክክል ነው፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ረሀብ የለም የውጭ እርዳታ ሰጭ ድርጅቶች፣ የውጭ ኃይሎች እና እንደ ዲ ዋል ያሉ ሰዎች “ረሀብ አለ” ካላሉ በስተቀር፡፡ እርግጠኛ ለመሆን ዩኤስኤአይዲ/USAID፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅቶች፣ የዓለም ባንክ፣ የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት እና ሌሎቹ ዓለም አቀፍ የድህነት እና የረሀብ ወትዋች አቃጣሪዎች “በኢትዮጵያ ረሀብ አለ!” እስካላሉ ድረስ በኢትዮጵያ ውስጥ ረሀብ የለም::

በምግብ እጥረት ምክንያት 29 ሺ ሰዎች የሚሞቱ ከሆነ ይኸ ነገር እጅግ በጣም አስቀያሚ ጉዳይ ነው፡፡ በረሀብ ምክንያት ሞቱ ማለት ነው፡፡

ዓለም አቀፍ የድህነት እና የረሀብ ወትዋች አቃጣሪዎች ግልጽ በሆነ ምክንያት ረሀብ የለም እያሉ እራሳቸውን ከፍ ከፍ እያደረጉ በሚናገሩበት ወቅት ከእነርሱ በተጻራሪ ሆኘ በመበሳጨት ከማጋለጥ ወደኋላ ያልኩበት ጊዜ የለም፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ረሀብ የመኖር እና ያለመኖር ጥያቄ በረሀቡ የሚሰቃየው የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚመልሰው እንጅ ዩኤስኤአይዲ/USAID፣ የዓለም ባንክ፣ የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ወይም ደግሞ ዓለም አቀፉ ዲ ዋል የሚመልሱት ጉዳይ አይደለም፡፡

ይህንን ጉዳይ እንደገና ልድገመው፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ረሀብ ስለመኖሩ ለማወቅ ብቸኛው መንገድ በረሀብ ችግር ከሚሰቃዩት ወጎቻችን ጋር መነጋገር ነው፡፡

አሁን በቅርቡ በኢትዮጵያ የትግራይ ክልልን ጎብኝቶ የተመለሰው የዩኤስኤአይዲ/USAID ጽ/ቤት የውጭ አደጋ ረዳት የሆነው ጀርሚ ኮኒንዲክ ያገኘው ይህንን ዓይነት ሁኔታ ነው፡፡

እ.ኤ.አ ባለፈው ሚያዝያ 17 ባቀረብኩት ትችቴ ለመግለጽ እንደሞከርኩት ኮኒንዲክ ከትግራይ ሕዝብ እንዲህ የሚል ሀሳብን አግኝቷል፡

“ይህ ድርቅ መጠነ ሰፊ ነው፡፡ በዚህ ሀገር ውስጥ ባለፉት 50 ዓመታት ውስጥ ከተከሰቱት ድርቆች ሁሉ ይህ የአሁኑ እጅግ በጣም የከፋ ነው… ትላንት ከትግራይ በወጣንበት ጊዜ በህብረተሰቡ ውስጥ ከሚኖሩት ሰዎች ጋር በተነጋገርንበት ወቅት በህይወታቸው ካዩት ድርቅ ሁሉ ይህ የአሁኑ የከፋ እንደሆነ ነግረውናል – እንዲያውም እ.ኤ.አ በ1983፣ 1984 ተከስቶ ከነበረው ድርቅ የከፋ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ሆኖም ግን በአሁኑ ጊዜ የተከሰተው ድርቅ ውጤት እ.ኤ.አ በ1984 ከተከሰተው ድርቅ ውጤት ጋር ተመሳሳይነት እንደማይኖረው እናውቃለን…“

ዲ ዋል “የረሀብ ተፈጥሯዊ ሁኔታ ጥቂት ሰዎች የሚበላ በቂ ምግብ አላማግኘታቸው ነው“ ከሚለው ከአማርትያ ሴን ሀሳብ ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ የሚበላ በቂ ምግብ አለማግኘት ብቻ ረሀብ ነው ሊባል አይችልም፡፡

በአሁኑ ጊዜ 20 ሚሊዮን የሚሆኑ የኢትዮጵያ ህዝቦች የሚበሉት በቂ ምግብ ያላቸው አይመስልም፡፡

ዲ ዋልን በቀጥታ እንዲህ የሚል ጥያቄ እጠይቀዋለሁ፡፡ በእራሱ ትርጉም መሰረት በአሁኑ ጊዜ 20 ሚሊዮን የሚሆኑት ኢትዮጵያውያን የሚበሉት በቂ ምግብ አላቸውን? በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ውስጥ ረሀብ አለን?

“ረሀብ እና ሰብአዊ መብት” (1991 ልማት በተግባር፣ ቅጽ 1. ቁጥር 2) በሚል ርዕስ ባዘጋጀው በእራሱ ጽሁፍ ዲ ዋል እንዲህ በማለት የረሀብን ችግር ለመፍታት እንደሚቻል ተናግሯል፡

“ታሪክ ረሀብን ለመከላከል በሚያስችሉ ስኬታማ ዘዴዎች የተሞላ ነው፡፡ ከእነዚህ የተለመደው ከገዥዎች ጋር የፖለቲካ ግዴታ የውል ኮንትራት መዋዋል ነው፡፡ በጣም ውጤታማ በሆነ ጸረ ረሀብ የኮንትራት ውል ስምምነቶች ረሀብ የፖለቲካ ቅሌት ነው፡፡ ረሀብ እርምጃ ያልተወሰደበት አሳፋሪ ነገር ነው፡፡ የኮንትራት ውሉ የሚቋረጠው ረሀቡ እንዲከሰት ያደረገውን ወይም ደግሞ በስልጣን ላይ ያሉትን በመቅጣት በስልጣን ላይ ያለውን መንግስት ማስወገድ ነው፡፡“

ዘ-ህወሀት ምርጫውን መቶ በመቶ አሸንፌ የፓርላማ ወንበሩን በሙሉ ተቆጣጥሪያለሁ እያለ በሚደነፋበት ወቅት የፖለቲካ የውል ስምምነት ኮንትራት ማለት ምን ዓይነት ሰይጣናዊ ድርጊት ነው?

“የረሀብ ወንጀሎች” (1997) በሚል ርዕስ ዲ ዋል ባሳተመው መጽሐፉ ለረሀብ መነሻ ምክንያቱ የግድ ድርቅ አይደለም፣ ሆኖም ግን ከሌሎች ሰዎች ጋር የማይስማሙት የፖለቲካ ግትሮች እና በአፍሪካ መንግስታት እና በዓለም አቀፍ የሰብአዊ እርዳታ ድርጅቶች በኩል የተጠያቂነት ያለመኖር ቸግር ነው፡፡ ምግብ የማግኘት መብት እንዳለ እና የምግብ ዋስትናን የማያረጋግጥ መንግስት በዜጎች ተጠያቂ መሆን እንዳለበት አጽንኦ ሰጥቶ ተናግሯል፡፡

ዲ ዋል የሊበራል መብቶች እና የዴሞክራሲ ተቋሞች ረሀብን ለመከላከል ወሳኝ እንደሆኑም በማያያዝ ተናግሯል፡፡

በስልጣን ላይ ያሉ ሰዎች እራሳቸው ረሀብ እራሱን የሕግ፣ የፖለቲካ፣ እና የሞራል ወንጀሎች በመሆን መንግስታትን ለማውረድ፣ ተጠያቂ ለማድረግ እና ለመተካት እንዲቻል አስገዳጅ የሆነ የፖለቲካ ኮንትራት ሀሳብን አቅርቧል፡፡ ዓለም አቀፍ የረሀብ ኢንዱስትሪ (ዓለም አቀፍ የድህነት ወትዋች አቃጣሪዎች እያልኩ እንደምጠራቸው) የተማሩ ዓለም አቀፍ የእርዳታ ድርጅቶችን፣ የአካዳሚ ሰዎችን፣ አማካሪዎችን፣ ልዩ ባለሙያዎችን፣ ጋዜጠኞችን እና ወትዋቾችን ጨምሮ የረሀብን ፖለቲካዊ ተፈጥሯዊ ሁኔታ በማስወገድ እና የቴክኒክ ትርጉምን በመስጠት የፖለቲካ ኮንትራት ውል እንዳይመሰረት ክፉ ደንቀራ ሆነው የቀረቡ የመሆናቸውን ሀሳብ አቅርቧል፡፡

(ዲ ዋል እራሱ ደንቃራ መሰናክል ከሚሆኑት የአካዳሚክ ሰዎች፣ አማካሪዎች፣ ልዩ ባለሙያዎች መካከል ነውን?)

እ.ኤ.አ በ1991 ባዘጋጀው ጽሁፍ ዲ ዋል እንዲህ በማለት ሞግቷል፡

“ረሀብ ነጻ ፕሬስ እና ዲሞክራሲያዊ የፖለቲካ ተቋማት በሌሉበት የሚከሰት ከሆነ በመንግስት በኩል ስለዚያ ጉዳይ አንድ ነገር ለማድረግ ያለው አናሳ ድርጊት ነው፡፡ በአማካይ አፍሪካውያን ከህንዳውያን የበለጠ ይመገባሉ፡፡ ሆኖም ግን ህንድ ለ40 ዓመታት ያህል በድርቅ አልተሰቃየችም፣ እናም ይህ ሊሆን የቻለው ህንድ ነጻ ፕሬስ እና ለለውጥ የሚያበቃ የተቃውሞ ፖለቲካ የምታራምድ ሀገር በመሆኗ ነው፡፡ (ለህንድ ስኬታማነት ሌላው ጉዳይ ረሀብ ማንዣበብ ሲጀምር እና አደጋ ከማድረሱ በፊት መንግስት በኢኮኖሚው ውስጥ ጣልቃ በመግባት ድኃውን የህብረተሰብ ክፍል ስለሚደግፍ ነው፡፡) እ.ኤ.አ ከ1958-61 በሶሻሊስት ቻይና ታላቁ ረሀብ በተከሰተ ጊዜ ለረሀቡ መከሰት ከፊል ምክንያቱ ስለቀውሱ የመረጃ እጥረት እና የማኦ የወደፊት ታላቁ እርምጃ እና ፍጹም የሆነው የጽሁፍ ቁጥጥር መደረግ ሁኔታ ነበር፡፡ ቀውሱን ያወቁት ፖለቲከኞች የረሀቡን ችግር በፍጹማዊነት የፖለቲካ ስርዓት ምክንያት ለሕዝብ ይፋ ማድረግ ያለመቻል ወይም ደግሞ ለጉዳት ተጋላጭ የሆኑትን የህብረተሰብ ክፍሎች ፍላጎት መወከል ያለመቻል ነበር፡፡ በተመሳሳይ መልኩ እ.ኤ.አ በ1984-85 በካፒታሊስት ሱዳን ተከስቶ ለነበረው ረሀብ በከፊል መንስኤው ፕሬሱን ፍጹም በሆነ መልኩ በመቆጣጠር እና ለተጎዱት ህዝቦች ውክልና በመውሰድ ቡድኖችን በማደራጀት በመንግስት ላይ እርምጃ ለመውሰድ አለመቻል ነበር፡፡ የሱዳን መንግስት የረሀቡን አሳፋሪነት በማመን የግል መዋለ ንዋይ ማፍሰስን ያበረታታ ነበር፡፡ እነዚህ ምሳሌዎች የፖለቲካ መብቶች – መረጃ የማግኘት፣ በነጻ የመደራጀት፣ ውክልና የመውሰድ መብቶች የኢኮኖሚ ስርዓቱ ምንም ይሁን ምን ረሀብን ለመዋጋት ዋና ጠቃሚ ነገሮች መሆናቸውን ግልጽ ያደርጋል፡፡ በሁለት መንገዶች ጠቃሚዎች ናቸው፡፡ አንደኛ ነጻ የመረጃ ፍሰት መኖር ማለት በህብረተሰቡ ውስጥ ኃይለኛ የሆኑ ሰዎች በድሆች ላይ ስለሚደርሰው አደጋ እንዲያውቁ ያደርጋል፡፡ ሁለተኛ የመደራጀት እና የውክልና መብት መኖር ማለት በተቃውሞ የሲቪል ፖለቲካ አማካይነት ድሆች ስለቁሳዊ ፍላጎታቸው ተጽዕኖ ማድረግ እንዲችሉ ያደርጋቸዋል፡፡ እነዚህ መብቶች ለሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ቀጥተኛ ጉዳይ ናቸው ምክንያቱም ሁለቱም በእራሳቸው ሽልማት ናቸው ምክንያቱም እነዚህን መብቶች መጣስ አንድን ደኃ ሀገር ለረሀብ አደጋ ተጋላጭ እንድትሆን ያደርጋታል፡፡“

ዲ ዋል የደርግን ወታደራዊ አገዛዝ እና ለረሀብ የነበረውን የፖለቲካ መሳሪያ መጠቀሚያነት በማስረገጥ ጥላሸት ቀብቷል፡፡ እንዲህ ይላል፣ “ኢትዮጵያ በአስከፊው ረሀብ ትታወቃለች፣ እናም እ.ኤ.አ በ1991 ከስልጣን የተወገደው መንግስት የሰብአዊ መብት በመርገጥ መጥፎ ስም አለው፡፡ በደርግ ዘመን መከራውን ወደ ረሀብ እና ረሀቡን ወደ ህዝባዊ ቸነፈርነት እንዲቀየር ያደረጉት ዋና ዋና ጉዳዮች ከበርካታዎቹ ጥቂቶቹ በኃይል ማፈናቀል እና በሰፈራ ማስፈር፣ የመንደር ምስረታ ፕሮግራም እና የውትድርና ዘመቻ፣ ከባድ የሆነ ግብር መጣል፣ የምግብ እርዳታ በትክክል ለተጎጂው ህብረተሰብ እንዳይደርስ ማስቀየስ፣ ማነቆ መፍጠር እና ማውደም ነበር፡፡

እ.ኤ.አ ነሀሴ 2011 ባቀረብኩት ትችቴ ዘ-ህወሀት ረሀብን እንዴት አድርጎ በመጠቀም ወደ ስልጣን እንደወጣ ግልጽ አድርጌ ነበር፡፡ በእርግጥ ዘ-ህወሀት ከዲ ዋል አባባል በመዋስ ረሀብን የፖለቲካ መጨቆኛ መሳሪያ አድርጎ ተጠቅሞበታል፡፡

ዲ ዋል በመቶዎች እና በሺዎች የሚቆጠሩትን ወገኖቻችንን መሬት አልባ አድርጎ ስላስቀረው የዘ-ህወሀት የመሬት ቅርምት አንዲትም ቃል ትንፍሽ ሳይል አልፏል፡፡ ዘህወሀት በጋምቤላ እና በሌሎች ክልሎች ስላደረገው የሕዝብ ሰፈራ አንዲትም ቃል ሳይናገር ቀርቷል፡፡ በመናገሻ ከተማይቱ ዳርቻ ላይ ዘ-ህወሀት እያደረገ ስላለው ህዝብን በግዴታ የማፈናቀል እርምጃ ምንም ዓይነት ነገር ሳይናገር አልፏል፡፡

ዲ ዋል በዘ-ህወሀት በመደረግ ላይ ስለቆየው እና አሁንም በመደረግ ላይ ስላለው የምግብ እርዳታ ለተጠቃሚው እንዳይደርስ የሚያደርገውን ማስቀየስ፣ ደንቃራ/መሰናክል እና ጠቅላላ ውድመት መፍጠርን በሚመለከት ምንም ነገር ሳይናገር ቀርቷል፡፡

ዲ ዋል ዘ-ህወሀት የምግብ እርዳታን ለፖለቲካ መጨቆኛነት እና የፓርቲ አባላት መመልመያነት እያዋለው ስላለው ጉዳይ ምንም ነገር ሳይናገር አልፎታል፡፡

ዲ ዋል በኢትዮጵያ ውስጥ ሁሉም መሬት ሙሉ በሙሉ በዘ-ህወሀት እና በታዛዥ ሎሌዎቹ ቁጥጥር ስር ስለመሆኑ ጉዳይ ፍጹም በሆነ መልኩ ምንም ያለው ነገር የለም!

ዲ ዋል በመንታ ምላስ ይናገራልን?

የሸከስፒርን አባባል በመዋስ በመንታ ምላስነት ልምዱ ያለው እባብ ከዲ ዋል የበለጠ መንታ ምላስ አለውን?

ዲ ዋል ከማኦ ዜዱንግ እስከ መንግስቱ ኃይለማርያም ድረስ የነበሩትን የረሀብ ወንጀሎች ሲጥል እና ሲያብጠለጥል ከቶ ለምን ይሆን በዘ-ህወሀት እና በግብረ አበሮቹ እየተፈጸመ ያለውን የረሀብ ወንጀል ያላወገዘው?

በማኦ ረሀብ ህዝቦቿ አልቀውባት የነበረችው ቻይና በአሁኑ ጊዜ በረሀብ የሚሞቱ ኢትዮጵያውያንን ለማዳን ጥረት እያደረጉ መሆናቸው አስገራሚ እንቆቅልሽ አይደለምን? (U.S.A ማን ናት?)

ዲ ዋል እ.ኤ.አ ከ1958-61 በቻይና ደርሶ የነበረው ታላቁ ረሀብ የጽሁፍ ምርመራ እና ስለ ቀውሱ የመረጃ እጥረት ስለመኖሩ ማኦን ይተቻል፡፡ የፕሬስ ቁጥጥርን በማድረጉ እና ጉዳት ለደረሰባቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ውክልና በሚቆሙ እና በሚያደራጁ ቡድኖች ላይ እርምጃ በመውሰዱ የሱዳን መንግስትን በጽኑ ይተቻል፡፡

እንደ የጋዜጠኞች ተከላካይ ኮሚቴ (ጋተኮ)/Committee to Protect Journalists (CPJ) ዘገባ ከሆነ ኢትዮጵያ ጋዜጠኞችን በማሰር ከኤርትራ ቀጥላ ከአፍሪካ በሁለተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡

ዘ-ህወሀት በፕሬሱ ላይ እያደረገ ስላለው ጥብቅ ቁጥጥር እና ጋዜጠኞችን እና ጦማሪያንን በጅምላ በማጎሪያው እስር ቤት እያሰቃዬ ባለበት ሁኔታ ዲ ዋል አንዲትም ቃል ትንፍሽ ያለው ነገር የለም፡፡

ዲ ዋል እውነተኛ ጥሬ ሀቁን ለመሸፋፈን ጥረት ቢያደርግም በመንግስቱ ኃይለማርያም እና በመለስ ዜናዊ መካከል ያለው ብቸኛው ልዩነት የቀድሞው ዓይን ባወጣ መልኩ ፊት ለፊት በሰው ልጆች ላይ ሰብአዊ ወንጀል ሲሰራ የኋላኛው ደግሞ እንደ ለማዳ ድመት እየተለሳለሰ ፊት ለፊት ሳይሆን በድብቅ በሰው ልጆች ላይ ሰብአዊ ወንጀል ይፈጽም ነበር፡፡ በተረፈ በሰው ልጆች ላይ ሰብአዊ ወንጀል ከመፈጸም እንጻር ግባቸው አንድ እና አንድ ብቻ ነው፡፡

ዲ ዋል ለምንድን ነው በአሁኑ ጊዜ አንድን ሰው አንድ ጊዜ እያለ 20 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያንን እየገደለ ላለው ረሀብ አላይም አልሰማም እያለ ጆሮ ዳባ ልበስ የሚለው?

ዲ ዋል በመጽሀፉ እንዲህ በማለት ጽፏል፣ “ሌሎች ሰዎች ከሚሰቃዩበት ጉዳይ ጋር በተያያዘ መልኩ ትኩረት የሚያደርግ ሙያ ላይ መሰማራት በጣም የሚያስጠላ ሁኔታ ነው…“ ዲ ዋልን “በመስተዋት ውስጥ ተመልከት እለዋለሁ፡፡

ዲ ዋል ረሀብ ምን ዓይነት ተፈሯዊ ባህሪ እንዳለው እና የእነርሱን ቀዳሚ ዓላማ እና ሀሳቦችን ከዚያ ጋር በማያያዝ ረሀብ ምን እንደሆነ እና የረሀብን አስከፊነት በመግለጽ የእራሳቸውን ሃሰቦች የሚያራምዱትን የአደጋ ቱሪስቶችን መተቸት ይወዳል፡፡ “የገጠር ሰዎች እንዴት አድርገው ህልውናቸውን እንደሚያገኙ መገንዘብ ያለመቻል አብዛኛውን ጊዜ የአደጋ ቱሪስቶች ያለ ውጭ እርዳታ ሚሊዮኖች ይራባሉ የሚል ትንበያን ይሰጣሉ…” ይላል፡፡

ስለአደጋ ምሁራን እና ተመራማሪዎች ተመሳሳይ ነገር የሚባል ከሆነ የሚገርመኝ ይሆናል፡፡

በኢትዮጵያ ያለውን ረሀብ መደበቅ፡ የረሀብ ከሀዲዎች ምህዋር፣

ዲ ዋል ባቀረበው ጽሁፍ ታላቁ ረሀብ ስለማብቃቱ ጠይቋል፡፡

ታላቁ ረሀብ ኢትዮጵያን በፍጹም አለቀቃትም በማለት ለዲ ዋል ስናገር በጣም አዝናለሁ፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ግንቦት 2016ም በህይወት አለ፡፡

የድብቅ ረሀቦች ዘመን፣ እየተንፏቀቁ የሚመጡ ረሀቦች፣ የሚገድሉ ረሀቦች እና የረሀብ ወንጀሎች ሰላማዊ ዜጎችን የጉዳት ሰለባ እያደረጉ መሆናቸውን ለዲ ዋል ስነግረው ታላቅ ሀዘን ይሰማኛል፡፡

ረሀብ ለመኖሩ እውነቱን ሚደብቁ ከእኛው ጋር ናቸው፡፡

ዓለም አቀፍ የድህነት ወትዋች አቃጣሪዎች እና በኢትዮጵያ የሰብአዊ እርዳታ አቃጣሪዎች ዘመን ያበቃ መሆኑን ለዲ ዋል ስነግረው ሀዘን ይሰማኛል፡፡

እናንተ ሁላችሁም እኛ መቸ እንደምንራብ፣ መቸ ቸነፈር እንደሚያጠቃን ወይም ደግሞ በረሀብ ምክንያት መቸ እንደምንሞት ልትነግሩን አትችሉም፡፡

ሁሉንም ነገር ስትወስዱ የቆያችሁት ከእኛው ነው፡፡ ሆኖም ግን ክብራችንን እንድትወስዱት እና እንድንሞት አንፈቅድም፡፡ የአዞ እንባችሁን አታንቡብን፡፡ በረሀብ ስንሞት ረሀብ እየተራብን እንደሆነ መናገራችሁን አቁሙ!

እ.ኤ.አ በ1984 ታላቁ ሀሪ ብላፎንቴ ወደ ኢትዮጵያ በሄደበት ጊዜ እና ለረሀብ ሰለባዎች በግንባር እርዳታ ማሰባሰብ በጀመረበት ጊዜ ከምንም በላይ ቀልቡን የሳበው ነገር ቢኖር የረሀብ ሰለባ የሆኑት ዜጎች ለክብራቸው ምን ያህል ቀናኢ እንደነበሩ እና የበለጠ ምግብ ለማግኘት ሲሉ ይታገሉ እንዳልነበረ እና ካላቸው ድርሻ በላይ የሌሎችን እንደማይፈልጉ ያሳዩበት ጨዋነት የተሞላበት ሁኔታ ነበር፡፡

ምንም ዓይነት የሚበላ በቂ ምግብ የሌላቸውን ሰዎች የሰዓት በኋላ ሻይን እንደማጣት ያህል በመቁጠር የረሀብ ሰለባ በሆኑ ወገኖቻችን ቁስል ላይ እንጨት መስደድ አስፈላጊ ነገር አይደለም፡፡

በዓለም ላይ ሁሉም ዓይነት ከሀዲዎች አሉ፡፡ በዘር ማጥፋት፣ በጦርነት እና በረሀብ በመቶዎች እና በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ሲሞቱ ሆን ብለው አይተው እንዳላዩ፣ ሰምተው እንዳልሰሙ  ምንም ሳያደርጉ ያልፉታል፡፡

ዲ ዋል ዘ-ህወሀትን ወይም ደግሞ የእነርሱን አድራጊ ፈጣሪ አለቃ በመደገፉ ችግር የለብኝም፡፡ ማንንም ይደግፍ አይደግፍ የእርሱን መብት አከብራለሁ፡፡

ሆኖም ግን ከወገኖቸ ህይወት እና ሞት ጋር በተያዘ መልኩ ጣልቃ ሲገባ እና በአሁኑ ጊዜ በአስከፊ ሁኔታ ተከስቶ ያለውን ረሀብ ከዓለም ህዝብ እይታ መደበቅ ሳይሆን እኔ የምጠብቀው ይህንን ችግር ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ማሳወቅ ለእንዳንዱ ሰው አገልግሎት መስጠት እና ለረሀቡ ኃላፊነትን መውሰድ መቻል አለበት የሚል ነው፡፡

አሁን በህይወት ስለሌለው ጨለማው ልዑል፣ የልዑሉ ኗሪ ፈረስ ጋላቢዎች እና የሰይጣን ወትዋቾች ምን እንደማስብ እያንዳንዱ ሰው የሚያውቀው ጉዳይ ነው፡፡ እውነታውን ለመደበቅ ከስኮላርሽፕ መጋረጃ ጀርባ አልደበቅም፡፡ የማታለልን እና የአስመሳይነትን መጋረጃ አስወግዳለሁ፣ ስለሆነም ሁሉም ሰይጣናዊነትን በትክክል ማየት ይችላል፡፡

እናም ዕቅድ የሚያወጡለት እና የሚከላከሉለት ኃላፊነት ያላቸው ያ ሰይጣን ረሀብ ነው፡፡

በረሀቡ ምክንያት በሺዎች የሚቆጠሩ አሰዎች ሞተዋል (በርካተዎቹ ወደፊት ይሞታሉ) እናም ዘ-ህወሀት በዓለም አቀፍ የድህነት እና የረሀብ ወትዋች አቃጣሪዎች የረሀብ ወንጀል ከሕዝብ ዕይታ እንዲደበቅ በማድረጉ ረገድ ስኬታማ ሆነዋል፡፡

በእርሱ ጽሁፍ ዲ ዋል ኢትዮጵያ የደከሙ፣ ዓይኖቻቸው የፈዘዙ ልጆች መኖሪያ ሆናለች ብሏል፡፡

የዓለም አቀፍ የረሀብ ወትዋች አቃጣሪዎች በኢትዮጵያ ውስጥ ረሀብ መኖሩን ይፋ ለማድረግ የማጣሪያ ወረቀት ነውን?

ይህ ትችት ለዲ ዋል እና ለመሰሎቹ ምግብ ለማሰብ እንደሆነ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡

በመጨረሻም ዲ ዋልን ሁለት ቀላል የሆኑ ጥያቄዎችን ለመጠየቅ እፈልጋለሁ፡፡

እ.ኤ.አ በ1991 አሁን በህይወት የሌለው ጓድ መለስ እንዲህ ብሎ ነበር፣ “ኢትዮጵያውያን በቀን ሶስት ጊዜ መመገብ ከቻሉ የእኛ መንግስት ስኬት በዚህ ይለካል፡፡”

እ.ኤ.አ በ2011 አሁን በህይወት የሌለው መለስ ዜናዊ እራሱን ከፍ ከፍ በማድረግ እንዲህ በማለት አውጆ ነበር፣ “ትርፍ ምርት ማምረት የሚያስችለንን ዕቅድ ነድፈናል፣ እናም እ.ኤ.አ በ2015 ያለምንም የውጭ እርዳታ እራሳችንን መመገብ እንችላለን፡፡”

እንግዲህ እነዚህ ከዚህ በላይ የቀረቡትን ምዕናባዊ የተስፋ ዕቅዶች ከግንዛቤ በማስገባት፣

1ኛ) ኢትዮጵያውያን እ.ኤ.አ በ2016 በቀን ሶስት ጊዜ መመገብ ችለዋልን? 

2ኛ) ኢትዮጵያውያን ትርፍ ምርት በማምረት እ.ኤ.አ በ2016 እራሳቸውን መመገብ ችለዋልን?

የረሀብ ወንጀሎች አሉ እናም በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ውስጥ እየተፈጸሙ ነው፡፡

ከዚህም በተጨማሪ “የረሀብን ወንጀል ማሳወቅ ያለመቻል እራሱ ወንጀል ነው“ ዲ ዋልን ከስሸዋለሁ!

በኢትዮጵያ ውስጥ ረሀብ አለ!!! በኢትዮጵያ ውስጥ ረሀብ አለ!!! በኢትዮጵያ ውስጥ ረሀብ አለ!!!

ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!  

ግንቦት 29 ቀን 2008 ዓ.ም