ሌላ ደብዳቤ ለኢትዮጵያውያት እህቶቼ፣

ምስራቅ ገሰሰ 

Breast Cancer Pix1በአሁኑ ጊዜ ይህንን ደብዳቤ እየጻፍኩ ያለሁት ለጡት ካንሰር በሽታ ምርመራ አስፈላጊ የሆኑትን የኤክስ ሬይ/X-Ray እና የአልትራ ሳውንድ/Ultrasound ዓመታዊ ምርመራዬን እንዳጠናቀቅሁ ነው፡፡

ከአምስት ዓመታት በፊት ልክ እ.ኤ.አ መስከረም 25/2010 የጡት ካንሰር ምርመራዬን ካጠናቀቅሁ በኋላ ለኢትዮጵያውያት እህቶቼ ይጠቅማል በሚል እሳቤ ከዚህ ጋር በተያያዘ መልኩ ያለኝን ልምድ እና ተሞክሮ ያካተተ ጽሑፍ አዘጋጅቼ ነበር፡፡ (ያንን ጽሑፍ በእንግሊዘኛ  ለማንበብ እባክዎትን እዚህ ጋ ይጫኑ፡፡)

አሁን ደግሞ ባለፉት አምስት ዓመታት ክትትል በማድረግ ተግባራት ላይ የነበረኝን ተሞክሮ ለኢትዮጵያውያት ሴቶች በተለይ ያካበትኩትን ልምድ ለማካፈል በማሰብ “ሌላ ደብዳቤ ለኢትዮጵያውያት እህቶቼ” በሚል ርዕስ እነሆ አዘጋጅቼ አቀረብኩ፡፡

ከሁሉም በላይ የኢትዮጵያ ሴቶች በተለይም እድሚያቸው ከ45 ዓመት በላይ የሆኑ የጡት ካንሰር በሽታን ገና በእንጭጭነቱ በምርመራ በማወቅ መቆጣጣር እንዲቻል መደበኛ በሆነ መልኩ ምርመራ ማካሄድ እና ክትትል ማድረግ እንዳለባቸው ተስፋ አደርጋለሁ፡፡

ጥቅምት በዩናይትድ ስቴትስ እና በሌሎች በርካታ ሀገሮች እንዲሁም በዓለም አቀፍ የጤና ድርጅት/World Health Organization ጭምር “የጡት ካንሰር የግንዛቤ ማስጨበጫ ወር“ በመባል ይታወቃል፡፡

የጡት ካንሰር በዓለም አቀፍ ደረጃ በሴቶች ላይ በጣም የተለመደው የካንሰር ዓይነት ሲሆን በሴቶች ላይ ከሚከሰቱት ሁሉም ዓይነት ካንሰሮች መካከል 25 በመቶ የሚሆነውን ይሸፍናል፡፡

ያልተለመዱ ምልክቶች በመታየታቸው እ.ኤ.አ በ2009 ቀላል እና ምንም ዓይነት የሕመም ስሜትን የማያስከትል ዓመታዊ የኤክስ ሬይ ምስል የጡት ካንሰር ምርመራ ተደረገልኝ፡፡

በኤክስሬይ የሚካሄዱ የምርመራ ዓይነቶች የጡት ካንሰር ገና ሳይጠናከር እና ሳይስፋፋ በእንጭጭነቱ ለማወቅ የሚያስችሉ ጠቃሚ መሳሪያዎች ናቸው፡፡

ሆኖም ግን የጡት የእራስ በእራስ ምርመራ እና አልትራሳውንድ (በጣም ቀላል እና የሕመም ስሜት የማያስከትል ስርዓት በውስጠኛው የሰውነታችን ክፍል ውስጥ ድምጽን በመጠቀም ስዕሎች እንዲፈጠሩ የሚያደርግ መሳሪያ) የጡት ካንሰር ገና ከመጠናከሩ በፊት በሽታው መጀመር አለመጀመሩን ለማወቅ በጣም ጠቃሚ የሆኑ የመመርመሪያ መሳሪያዎች ናቸው፡፡

የእኔ የጡት ካንሰር ባልተለመደ መልኩ ከጡቴ ላይ በከፍተኛ ደረጃ  የሴሎች ዕድገት ከሚታይበት ጡንቻ መሰል አካል/tissue ላይ ቀላል በሆነ የአሰራር ሂደት የሕክምና ዶክተሮች ነቅለው በመውሰድ ምርመራ ከተደረገ በኋላ መኖሩ ተረጋገጠ፡፡

እንደ እድል ሆኖ የእኔ የጡት ካንሰር ገና ሳይስፋፋ እና ሳይጠናከር በመጀመሪያው እና “ዜሮ ደረጃ” እየተባለ በሚጠራበት በእንጭጭነት ደረጃው ላይ ተያዘ፡፡ ክብርና  ምስጋና ሁሉን ነገር ለማይሳነው ለአንዱ ለአምላክ ይሁን፡፡

የጡት ካንሰር ሳይጠናከር እና ሳይስፋፋ ገና በእንጭጭነት ወይም በዜሮ ደረጃው ምርመራ ተደርጎ ምልክቱ መኖሩ በምርመራው ውጤት ከታወቀ በሽታውን ውጤታማ በሆነ መልኩ አክሞ ማዳን እና መስፋፋት እንዳይችል በቂ ሕክምና በማድረግ ማምከን ይቻላል፡፡

በመጀመሪያ ከሐኪሜ “የጡት ካንሰር” የምትለዋን ቃል በሰማሁበት ጊዜ ሙሉ በሙሉ በድንጋጤ በድን መሆኔን እና በፍርሀት ተውጨ እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡

በአዕምሮዬ ውስጥ በርካታ ነገሮች ተመላለሱ፡፡ በከፍተኛ ስሜታዊነት ሁኔታ ውስጥ ወደቅሁ፡፡

ሆኖም ግን እንደገና በመረጋጋት እና አደብ በመግዛት እራሴን እንዲህ በማለት ጠየቅሁ፣ “ለምንድን ነው እኔን የጡት ካንሰር የያዘኝ እያልኩ ራሴን ብዙ ጠየኩ ?“

ግን ሁሉን ነገር የማይሳነውን አምላኬን አመሰግናለሁ፣ እ.ኤ.አ በ2009 ገና በሽታው ሳይስፋፋ እና ሳይጠናከር በምርመራ ታወቀ፡፡ በዚህም መሰረት በአግባቡ እና ጥንቃቄ በተመላበት ሁኔታ ሕክምናውን ስከታተል በመቆየቴ በ6ኛው ዓመቴ ከጡት ካንሰር ነጻ በመሆኔ ሁሉንም ክብር እና ሞገስ ለፈጣሪ አምላኬ ይግባው በማለት የተሰማኝን ደስታ እገልጻለሁ፡፡

በካንሰር ህዋሳት የተጠቃውን የጡቴን የጡንቻ አካል ቆርጦ የማውጣት ሂደቱ ቀላል አልነበረም፡፡ ሆኖም ግን እጅግ በጣም ጠቃሚ ስራ ነበር፡፡

በካንሰር ህዋሳት የተጠቃውን የጡቴን የጡንቻ አካል ነጥሎ ስሩን ቆርጦ የማውጣቱን ተግባር ቀዶ ቀዳጅ ሐኪሞቼ በሚገባ አከናወኑት፡፡ ከዚያም በኋላ ከቀዶ ሕክምናው የስራ ሂደት የተረፉ እና የቀሩ የካንሰር ሴሎችን በሙሉ ለመግደል እንዲቻል የማይታዩ የብርሀን ጨረሮች በቀጥታ ወደ ጡቴ የሰውነት ውስጣዊ ክፍል ውስጥ እንዲለቀቁ በማድረግ የጨረር ሕክምናው በተላሟላ ሁኔታ ተደረገልኝ፡፡

የጨረር ሕክምና ለጡት ካንሰር በሽተኞች “የፈውስ ሕክምና ዕቅድ“ እየተባለ የሚሰጥ የሕክምና ሂደት ነው፡፡ የጨረር ሕክምናው ከ4 – 5  ሳምንታት ላለ ጊዜ የሚሰጥ ነው፡፡ ዋናው ሕክምና በሰከንድ ጊዜዎች ውስጥ የሚከናወን ነው፡፡

በእያንዳንዱ የሕክምና ሂደት ውስጥ የድካም ስሜት የሚሰማኝ ቢሆንም ቅሉ በሁሉም የሕክምና ጊዜያት ውስጥ የጨረር ሕክምና ሲሰጠኝም ያለምንም ችግር መደበኛ ስራዬን ሳላቋርጥ በመስራት ላይ ነበርኩ፡፡

የእኔ ካንሰር ገና በ”ደረጃ ዜሮ” ላይ ስለነበረ እና የፈሳሽ ቋጠሮ የሆኑትን ሊምፍ ኖዶችን/lymph nodes (የሰውነታችንን ከበሽታ የመከላከል አቅም ስርዓትን በማጎልበቱ ሂደት ወሳኝ ሚና የሚጫወቱት እና በተለያዩ የሰውነታችን ክፍል ውስጥ የሚገኙ ልዩ አካሎች) አካትቶ በሁሉም የሰውነቴ አቅጣጫ ጥቃት ያልሰነዘረ ስለነበር የካንሰር ሴሎችን ለመግደል የጨረር ብርሀን ከመጠቀም ውጭ ኬሚካላዊ መድሀኒቶችን/chemotherapy አልወስድም ነበር፡፡

የጨረር ሕክምናዬን ካጠናቀቅሁ በኋላ በማህጸን ቀንድ ውስጥ/ovaries የሚገኘውን እና ኤስትሮጅን/estrogen በመባል የሚታወቀውን የጽንሱን ሁለተኛ ደረጃ ባህሪያት የሚወስነውን ታሞክሲፈን/Tamoxifen በመባል የሚታወቀውን ሆርሞን እንዳይመነጭ የሚያደርገው ሕክምና ይሰጠኝ ጀመር፡፡ ለአምስት ዓመታት ያህል በእያንዳንዱ ቀን አንድ ትንሽ የምትዋጥ እንክብል መድኃኒት እንድወስድ ይሰጠኝ ነበር፡፡ ታሞክሲፈን/Tamoxifen የተወሰኑ ዓይነት የካንሰር ሴሎች የጡት ካንሰርን ጨምሮ እንዳይባዙ ገደብ የሚጥል የመድኃኒት ዓይነት ነው፡፡

ለቸሩ እግዚአብሔር ምስጋና ይግባውና ባለፉት ስድስት ዓመታት ጊዜ ውስጥ የጡት ካንሰር ሕክምናውን ከመከታተል ጋር በተያያዘ መልኩ ምንም ዓይነት ችግር አላጋጠመኝም፡፡

ለስድስት ዓመታት ስከታተለው ለቆየሁት እና አሁን ድኘ በመልካም ጤንነት ላይ የምገኝበትን የጡት ካንሰር ሕክምና ተሞክሮዬን ለሌሎች እህት ወገኖቼ ለማካፈል የተነሳሳሁበት እውነታ ዋናው ምክንያት በማህበራዊ፣ በባህላዊ እና በሌሎች ምክንያቶች ሳቢያ እህቶቼ ፍርሀትን፣ ሀፍረትን እና ዝምታን በማስወገድ የጡት ካንሰር ምርመራን እንዲያደርጉ ለማገዝ እና የጡት ካንሰር ሴሎች ገና ከመሰራጨታቸው እና ከመስፋፋታቸው በፊተ አስቀድሞ መመርመር በሕይወት ለመኖር ዋናው ቁልፍ ነገር መሆኑን አጽንኦ በማስጠት ለማሳሰብ ነው፡፡

ባለፉት አምስት ዓመታት ከበርካታ ሴቶች ጋር በግንባር እየተገናኘሁ ስለጡት ካንሰር ንግግር አድርጊያለሁ፣ በስልክ እና የውይይት ቡድኖችን በማቋቋም ያለኝን ተሞክሮ ለወገኖቼ አካፍያለሁ፡፡ በተለያዩ የጡት ካንሰር ደረጃዎች ላይ ሆነው ምርመራ ከተደረገላቸው እና ሕክምናውን በመውሰድ ላይ ካሉት እና በሽታው ከፍተኛ ደረጃ ላይ ከደረሰባቸው ሴቶች ጋር ውይይት አድርጊያለሁ፡፡

ባለፉት አምስት ዓመታት ጊዜ ውስጥ የጡት ካንሰርን ለመከላከል እና ለማስወገድ ከፍተኛ የሆነ ቅርርብን የፈጠረ ቤተሰባዊ ትስስርን መስርቻለሁ፡፡ ሁሉም ነገር ለማይሳነው ለቸሩ እግዚአብሔር ምስጋና ይግባው እና ሁሉም የቡድኑ አባሎች የካንሰር ምርመራውን ገና ከመስፋፋቱ እና ከመጠናከሩ በፊት በእንጭጭነቱ ምርመራ ስላደረጉ ሁሉም አባላት በጡት ካንሰር ላይ ድልን ተቀዳጅተዋል፡፡

በአጠቃላይ መልኩ ማለት የምፈልገው የጡት ካንሰርን ለማስወገድ ዋናው ስኬት ሌላ ምንም ነገር ሳይሆን መደበኛ በሆነ መልኩ የጡት ካንሰር የኤክስሬይ ምርመራ አስቀድሞ ማድረግ ነው፡፡ ትንሽም የጥርጣሬ ምልክት በታዬ ጊዜ ፈጥኖ ወደ ሕክምና ተቋም በመሄድ የጡት ካንሰር ምርመራ ከማድረግ መቆጠብ አስፈላጊ አይደለም፡፡

አንዳንድ እህቶች እኔ እንዴት አድርጌ ወደ አደባባይ በመውጣት በሕዝብ ፊት ቆሜ ስለጡት ካንሰር ያለኝን ልምድ እና ተሞክሮ ለሌሎች ሳካፍል ግልጽ ያልሆነላቸው እና በአሰራር ሂደቱም ሙሉ እምነቱ የሌላቸው ሴቶች ገጥመውኛል፡፡ ምናልባትም የጡት ካንሰር በሕዝብ ዘንድ እንዲያውም ከዚያም በመለስ በቤተሰብ አባላት ዘንድ ሁሉ የሚያሳፍር ነገር ስለሆነ መታወቅ የለበትም በማለት በሽታውን ደብቀው ወደ ሞት አፋፍ የሚሄዱ አህቶች አሉ ብየ አምናለሁ፡፡

የሴቶች ትልቁ አደጋ በእራሱ የጡት ካንሰር እዳልሆነ አምናለሁ፣ ከዚያ ይልቅ በርካታ ሴቶች የጡት ካንሰር እንዳለባቸው አምነው እውነታውን ያለመቀበል እና አስቸኳይ የሆነ ሕክምና ያለመጀመራቸው ፍርሀት እና ኋላቀር ባህላዊ አመለካከት ነው፡፡

በጣም የዘገዬ እና ጉልህ ጥቃት ሰንዝሮ ይፋ እስከሚወጣበት ጊዜ ድረስ በርከታ ሴቶች ስለጡት ካንሰር ከባሎቻቸው እና ከልጆቻቸው እንኳ የሚደብቁ እንዳሉ በሚገባ አውቃለሁ፡፡ ምናልባትም ይኸ ድርጊት ከባህላዊ ችግር የመነጨ ሊሆን ይችላል፡፡ ጥቂት ኢትዮጵያውያት ሴቶች ሌሎች ለሕይወት አስጊ የሆኑ በሽታዎችን ሌሎች ሰዎች እንዳያውቁ መደበቁን ሊመርጡ ይችላሉ፡፡ በጣም አሳዛኙ ድርጊት ሰዎች ከሞቱ በኋላ በሽታቸው የመታወቁ ሁኔታ ነው፡፡

እንደዚህ ያለ ድርጊት በማንኛዋም ሴት ዘንድ እንዲደረግ አልፈልግም፡፡ ለዚህም ነው የጡት ካንሰር አለብኝ በማለት በግልጽ ወደ አደባባይ በመውጣት እህቶቼን በማስተማር ላይ የቆየሁት እና ያለሁት፡፡ ትኩረት በመስጥት እና መደበኛ የጡት ካንሰር ምርመራ በማድረግ በሽታው ሳይስፋፋ እና ሳይጠናከር አስቀድሞ በመታወቁ ዕድለኛ ነኝ፡፡

በጡት ካንሰር ተይዞ የአካል እና የአዕምሮ መሰቃየት የሚያሳፍር ጉዳይ አይደለም፡፡ ማንም ሴት ብትሆን ኃላፊነት የሌላት በመሆኗ ወይም ደግሞ ኃጢአት በመስራቷ ወይም ደግሞ ስብዕና የለሽ በመሆኗ ምክንያት አይደለም በጡት ካንሰር በሽታ የምትያዘው፡፡ የጡት ካንሰር ከዘረ መል/genes የሚወረስ ወይም ምክንያቱ በውል ካልታወቀ አካባቢያዊ ነገሮች የሚከሰት ሊሆን ይችላል፡፡ እስከ አሁንም ድረስ የበሽታው መንስኤ ምን እንደሆነ ሳይንስ እራሱ ያልደረሰበት ጉዳይ ነው፡፡ ያም ሆነ ይህ በበሽታው መያዝ የሚያሳፍርበት ምክንያት አይደለም፡፡

እኔ ሁልጊዜ ኢትዮጵያውያት ሴቶችን የስኳር በሽታ ወይም ደግሞ የደም ግፊት ያለባቸው መሆን አለመሆናቸውን እጠይቃለሁ፡፡ እነዚሂህ በሽታዎች እያሉባቸው ለቤተሰብ አባላት መናገር እና አለመናገራቸውን እጠይቃቸዋለሁ፡፡ ሁሉም ግን ለቤተሰብ አባላት እንደሚናገሩ ይነግሩኛል፡፡ ሆኖም ግን ስለጡት ካንሰር ተመሳሳይ የሆነ ጥያቄ ሳነሳላቸው አብዛኞቹ ለመናገር ሲያቅማሙ እና ለመወሰን ሲቸገሩ አስተውላለሁ፡፡

የጡት ካንሰር የስኳር በሽታ እና የደም ግፊት የመሳሰሉ በሽታዎች ቀደም ብሎ ሳይጠናከሩ እና አካልን ከማዳከማቸው በፊት ሕክምና ካልተደረገላቸው በስተቃር በሽተኛውን እንደሚገድሉ ሁሉ በተመሳሳይ መልኩ የጡት ካንሰርም የካንሰር ሴሎቹ ሳይስፋፉ እና ሳይጠናከሩ በእንጭጭነት ጊዚያቸው ምርምራ እና ሕክምና ካልተደረገ በስተቀር እንደሌሎቹ በሽታዎች ሁሉ ይገድላል፡፡

ሕክምና ባላገኘ የደም ብዛት (የደም ግፊት) ምክንያት በደም ዝውውር መቋረጥ ምክንያት ምን ያህል ሰው ይሞታል?

ከጡት ካንሰር እንደተረፈ ሰው እኔ በእርግጠኝነት የበሽታው ቅድመ ምርመራ እና የሕክምና አሰጣጡ ልምድ እና ተሞክሮ ምን ማለት እንደሆነ አሳምሬ አውቃለሁ፡፡

የጡት ካንሰርን በመደበቅ ሰውነትን እየጎዳ ከፍተኛ ደረጃ ላይ እስከሚደርስ ድረስ ይፋ አለማውጣት ነው ሊያሳፍር የሚችለው ጉዳይ እንጅ በጡት ካንሰር በሽታ መያዝ ምንም የሚያሳፍር ነገር የለውም፡፡

በሁለት ነገሮች ላይ ትልቅ አጽንኦ በመስጠት መናገር እፈልጋለሁ፡፡ እነርሱም፣

1ኛ) እድሚያቸው ከ45 ዓመት በላይ የሆኑ የኢትዮጵያ ሴቶች የጡት ካንሰርን ገና በእንጭጭነቱ እንዲታወቅ እና ለቀጣይ ሕክምና ዝግጁ እንዲሆኑ መደበኛ በሆነ መልኩ የካንሰር መርመራ ማድረግ አስፈላጊ ነገር ነው፡፡

2ኛ) በጡት ካንሰር በሽታ ተዋህስያን በሴሎቻቸው ውስጥ መኖራቸው በምርመራ ከተረጋገጠ ሁኔታውን ግልጽ በሆነ መልኩ ከሁሉም የቤተሰብ አባላት እና ከጓደኞች ጋር ሁሉ መነጋገር እና መወያየት በጣም አስፈለጊ ነገር ነው፡፡

እኔ ካለኝ ልምድ እና ተሞክሮ አንጻር የቤተሰብ አባላት እና ጓደኞች ሊታመን የማይችል የድጋፍ እና የማነሳሳት ምንጮች ናቸው፡፡

እኔ ካለኝ ልምድ እና ተሞክሮ አንጻር ምናልባትም የጓደኞች እና የቤተሰብ ፍቅር እና ድጋፍ ባጣም ዝቅተኛ ተጽዕኖ ያለው መስሎ ሊታይ ይችላል በማለት መናገር እችላለሁ፡፡ ሆኖም ግን እነዚህ አካሎች ለማንኛውም የካንሰር በሽታ ሕክምና ውጤታማ ነገሮቸ ናቸው፡፡

እንደ ኢትዮጵያውያት ስደተኛ እናቶች፣ ሚስቶች፣ እህቶች እና አያት እናቶች ከእራሳችን ሕይወት በበለጠ መልኩ የቤተሰቦቻችንን ጤንነት መንከባከብ እንዳለብን እገነዘባለሁ፡፡

ለእኔ አብዛኞቹ ኢትዮጵያውያት እናቶች ጥቂት ደቂቃዎችን በመውሰድ የጡት ካንሰር ምርመራ ለማድረግ ወደ ሐኪም ወይም ደግሞ ወደ ሆስፒታል ከመሄድ ይልቅ ልጆቻችንን ለዓመታዊ አጠቃላይ የጤና ምርመራ ወይም ደግሞ ለአስኳይ ምርመራ ወደ ጤና ክፍል እንዲያጋጉ የማድረጉ ሁኔታ በስፋት የሚስተዋል ይመስለኛል፡፡

በኢትዮጵያ እና በሌሎች ሀገሮች የሚገኙ በርካታ ኢትዮጵያውያት ሴቶች መደበኛ የሆነ የጡት ካንሰር ምርመራ ለማካሄድ የገንዘብ አቅርቦት የአቅም ውሱንነት ሊኖርባቸው እንደሚችል እገነዘባለሁ፡፡

በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ደኃ ሴቶች ገንዘብ በማውጣት የጡት ካንሰር ገና ሳይስፋፋ እና ሳይጠናከር ምርመራ ለማካሄድ እንዲሁም ሕክምናውን መከታተል እንዲችሉ  አቅም ስለሚገድባቸው በውጭ ያሉ ኢትዮጵያውያት የዲያስፖራ አባላት ሴቶች አንድ በመሆን ገንዘብ በማሰባሰብ ማገዝ እንደሚችሉ ሊያስኬድ የሚችሉበት መንገድ እንዳለ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ በኢትዮጵያ ያሉ ደኃ ሴቶችን ለመርዳት ዓላማው ያለን አንድነት በመፍጠር የመረዳጃ ተቋም ለመመስረት የሚቻልበት ጊዜ ይመጣ ይሆናል፡፡

እኔ ከጡት ካንሰር የመቅሰፍት አደጋ ተርፌ የለኝን ተሞክሮ እና ልምድ ለሌሎች ወገኖቼ ለማካፈል የተነሳሳሁበት እና ቀጣይ እንዲሆን የፈለግሁበት ሌላው ጠቃሚ ምክንያት በዩናይትድ ስቴትስ የሚኖሩ አዲስ የጡት ካንሰር ምርመራ ያደረጉ ሴቶች ተስፋ እንዳያጡ ከሚል እሳቤ በመነሳት ነው፡፡

የጡት ካንሰር የሞት ፍርድ ማለት አይደለም፡፡ ቀደም ሲል ገና በሽታው ሳይጠናከር እና ሳይስፋፋ ምርመራ በማድረግ ውጤታማ በሆነ መልኩ ሕክምና ሊደረግለት የሚችል ሌላ በሽታ ነው፡፡ ከዚህም በላይ ለጡት ካንሰር ደረጃቸው በጣም ከፍ ያለ እና የዘመኑን ቴክኖሎጂ በመጠቀም አግልግሎት ሲለጡ የሚችሉ የሕክምና ዓነቶቸ አሉ፡፡

በዩናይትድ ሰቴትስ የሚኖሩ የጤና ኢንሹራንስ ያላቸው ሴቶች በመንግስት ከሚደገፈው የጤና ክብካቤ አገልግሎት በማግኘት ነጻ የጡት ካንሰር ምርመራ ማድረግ ይችላሉ፡፡ ወይም ደግሞ ለመክፈል ተመጣጣኝ የሆነውን የጤና ክብካቤ አዋጅ ማግኘት ይችላሉ፡፡ አንደዚህ ዓይነት ጉዳዮች ላይ በቀጥታ በመግባት ከጤና ኢንዱስትሪው ጋር አብሮ በመስራት ከእንደዚህ ያሉ ፕሮግራሞች በርካታ የጡት ካንሰር ምርመራ በማድረግ የተሻለ ጥቅም እንደሚያገኙ አውቃለሁ፡፡ ኢትዮጵያውያት ሴቶች ያሉትን አገልግሎቶች ለመጠቀም በርትተው መስራት ይኖርባቸዋል፡፡

ለኢትዮጵያውያት ሴቶች በተለይም ደግሞ በቤተሰባቸው የጡት ካንሰር መከሰት ታሪክ ያላቸው በየጊዜው የጡት ካንሰር ቅድመ ምርመራ ማድረግ እንዳለባቸው ለመምከር እፈልጋለሁ፡፡

በዘር ውርስ የሚተላለፍ የጡት ካንሰር የሚኖር ከሆነ ብራክ 1-2/BRAC 1-2 እየተባለ የሚጠራ የምርመራ ዕይነት አለ፡፡ ብዙውን ጊዜ ካንሰር በቤተሰብ አባላት ላይ የሚከሰት ከሆነ እንደዚህ ዓይነት የምርመራ ዘዴዎች ለመደረጋቸው ዋና ምክንያት ነው፡፡

የጡት ካንሰር ሕክምና በሚካሄድበት ጊዜ ድጋፍ ሊያደርግ የሚችል ስርዓት መኖር እንዳለበት አጽንኦ ለመስጠት እፈልጋለሁ፡፡ ለካንሰር ሕክምና ከቤተሰብ እና ጓደኞች በተጨማሪ ለሴቶች የአካላዊ እና መንፈሳዊ ድጋፍ ሰጨ ቡድኖች መኖር በጣም አስፈላጊ ነገር ነው፡፡

የጡት ካንሰር ምርመራ ከተደረግልኝ በኋላ የስሜት፣ የመፍራት፣ ብቸኛ የመሆን እና የመንፈስ ጭንቀት ይከሰተብኝ እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ ያ ነገር እንግዲህ የተለመደ ነገር ነው፡፡ ምንም ዓይነት የጡት ካንሰር ምርመራ አድርገው በማያውቁ ሴቶች ላይ እንደዚህ ያለ ስሜት መኖር የተለመደ እና  ተፈጥሯዊ ነው፡፡

“እኔስ ለምንድን ነው?” በማለት ሁሉም ሴቶች ጠይቀውኛል፡፡

እኔ ለኢትዮጵያውያት እህቶቼ ማካፈል የምፈልገው ነገር ገና ቀደም ብሎ የካንሰር ሴሎች ሳይጠናከሩ እና ሳይስፋፉ የሚደረገው የጡት ካንሰር ምርመራ የመጨረሻ ማለት አይደለም፡፡

ከብሄራዊ የካንሰር ኢንስቲቱት በተገኘው የአምስት ዓመት እውነተኛ ከጡት ካንሰር የመትረፍ ዕድል መረጃ መሰረት የሚከተሉትን አሀዛዊ መረጃዎች መመልከት ጠቃሚ ነገር ይሆናል፡፡

1ኛ) ደረጃ 0፡ 100%

2ኛ) ደረጃ 1፡ 100%

3ኛ) ደረጃ 2፡ 93%

4ኛ) ደረጃ 3፡ 72%

5ኛ) ደረጃ 4፡ 22% ::

በየአምስት ዓመት የሚደረግ በጣም መጥፎ ዕድል በሆነው በ4ኛ ደረጃ 22% የመትረፍ ዕድል እንኳ ከጡት ካንሰር ነጻ ሊያስወጣ የሚችልበት አጋጣሚ ይኖራል፡፡

ስለዚህ የጡት ካንሰር ቀደም ብሎ በምርመራ ከታወቀ እና ሕክምናውም የሚወሰድ ከሆነ በሽታው ሊመለስ በማይችል መልኩ ሊድን እና መከላከልም ይቻላል፡፡ ባለፉት በርካታ አስርት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ዘመናዊ ሕክምና በጥሩ ሁኔታ በስራ ላይ ውሏል፡፡

የሐኪምን ትዕዛዝ መከተል ቀልጣፋ ሆኖ መቆየት፣ የሰውነት እንቅስቃሴ ማዘውተር፣ አትክልት እና ቅጠላቅጠል ዓይነት ምግቦችን መመገብ እና መንፈሳዊ ጽናትን መጎናጸፍ በጣም ጠቃሚ ነገር ነው፡፡

የጊዜ ውጥረት በጣም በበዛበት እየኖርን ያለንበት ጊዜ ስለሆነ የመንፈስ ጭንቀትን የሚያስወግዱ እና ሰላማዊ ከባቢ አየርን ለሚፈጥሩ ነገሮች ትኩረት መስጠት አስፈላጊ ጉዳይ ነው፡፡

ለእኔ የጸሎት ጊዜ በጣም ሰላማዊ ጊዜ ነው፡፡ መንፈሴ የተረጋጋ እንዲሆን ጥረት አደርጋለሁ፣ እንዲሁም በምችለው አቅም ሁሉ ሌሎችን ሰዎች ለመርዳት እተጋለሁ፡፡

ስለሆነም እንደ ኢትዮጵያውያት ሴትነት እያንዳንዳችን በያለንበት መደጋገፍ እና መጠናከር አለብን፡፡

የዚህ ጽሁፍ አቅራቢ በደቡብ ካሊፎርኒያ በጤና ክብካቤ ላይ የሚሰሩ ሲሆን የጡት ካንሰር ምርመራ ቀደም ብሎ እንዲታወቅ ለህዝብ ቅስቀሳ ማድረግ፣ ትምህርት እና ሕክምናም እንዲሰጥ ከፍተኛ ተሳትፎ ይደርጋሉ፡፡ ጸሐፊዋ በዚህ የግንኙነት መስመር ይገኛሉ፡፡  mesrak@gmail.com

እባካችሁ ይህንን ጸሑፍ ለሌሎች እህቶቻችንም አካፍ