ኢትዮጵያ፡ የህወሀት አምባገነንነት የተንሰራፋባት ምስኪን ሀገር፣

ከፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማርያም

ትርጉም በነጻነት ለሀገሬ

የጸሐፊው ማስታዋሻ፡ ለበርካታ ዓመታት ያዘጋጀኋቸውን ትችቶች እና ጸሁፎች በአንድ ላይ በማሰባሰብ ለህዝብ ተደራሽ እንዲሆኑ ለማድረግ በማሰብ almariam.com በሚለው ድረ ገጼ እያሰባሰብኩ ባለሁበት ጊዜ የኢትዮጵያ ሪቪው መጽሔት/Ethiopian Review Magazine (ERM) ቀደም ሲል እ.ኤ.አ በ2000 ጽሁፎችን በድረ ገጽ ማውጣት ከመጀመሩ በፊት መጽሄቱ በጽሁፍ ህትመት ግንኙነት ያወጣቸውን የእኔን ትችቶች እና ጽሁፎች አገኘሁ፡፡

እ.ኤ.አ በ1990ዎቹ የኢአርኤም/ERM ከፍተኛ አርታኢ ሆኘ ስሰራ በነበረበት ጊዜ በኢትዮጵያ እና በህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ ፖለቲካ ላይ የጻፍኳቸውን የበርካታ ጽሁፎችን ስብስብ እንደገና አገኘሁ፡፡ ሆኖም ግን የውስጣዊ ይዘታቸውን ምንነት ስብስብ አላገኘሁም፡፡  ኢአርኤም/ERM እ.ኤ.አ ከጥር 1991 እስከ 2000 ድረስ ጽሁፎችን ያወጣ የነበረው በህትመት የመገኛኛ ዘዴዎች በመጠቀም ብቻ ነበር፡፡ ሆኖም ግን ኢአርኤም/ERM ለዘጠኝ ዓመታት ለህዝብ ተደራሽ እንዲሆኑ እያተመ ያወጣቸውን ሁሉንም የህትመት ጽሁፎች ማግኘት እና ማሰባሰብ አልቻልኩም፡፡ እንደ ዕድል ሆኖ ጠንቃቃ በሆኑ የስራ ባልደረቦቼ እገዛ በቅርቡ የጥቂቶችን ጽሁፎች አድራሻ ለማግኘት ችለናል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የቀሪዎቹን የበርካታዎቹን ጽሁፎች አድራሻ ፈልገን እናገኛለን ብለን ተስፋ እናደርጋለን፡፡

ይህንን ከላይ በመንደርደሪያነት የቀረበውን ጽሁፍ ያቀረብኩበት ምክንያት ለአንባቢዎች ሁልጊዜ ስገልጽ እንደቆየሁት ሁሉ አሁን በህይወት የሌለው መለስ በኢትዮጵያውያን/ት ወገኖቻችን ላይ እልቂት እስከፈጸመበት እ.ኤ.አ እስከ 2005 ጊዜ ድረስ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ላይ ፍላጎትም ሆነ ተሳትፎ ያልነበረኝ ስለነበር ነው፡፡ የዓለም ህዝብ እንደሚያስታውሰው በዚያን ዓመት በመቶዎች የሚቆጠሩ ምንም ዓይነት የጦር መሳሪያ ያልታጠቁ በርካታ ኢትዮጵያውያን/ት ሰላማዊ ሰልፈኞች አሁን በህይወት በሌለው በመለስ እውቅና፣ ትዕዛዝ እና ስልጣን በአነጣጣሪ አልሞ ተኳሾች በጥይት እየተደበደቡ እንዲገደሉ ወይም ደግሞ ቁስለኛ እንዲሆኑ ተደርገዋል፡፡

በኢትዮጵያ ፖለቲካ ላይ ሙሉ ተሳትፎ እና ፍላጎት ያሳየሁት እ.ኤ.አ ከ2006 በኋላ በመሆኑ እስከዚያ ድረስ ምን ስትሰራ ነበር ለምትሉ አንባቢዎቼ ከዚያ ቀደም የነበረውን ሁኔታ መለስ ብሎ መመልከት እና በ2005 የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ የይስሙላ የቅርጫ ምርጫ ፍትህ እና ዴሞክራሲ ያለ መስሏቸው የምርጫውን መዘረፍ እና መሰረቅ ምክንያት በማድረግ በሰላማዊ መንገድ ተቃውሟቸውን ለመግለጽ ወደ አደባባይ በመውጣታቸው ብቻ አግዓዚ የሚባለውን የመለስ ዜናዊ የግል ስልጣን ጠባቂ የቅጥር ነፍሰ ገዳይ ወሮበላ ስብስብ ጦር ወደ መዲናይቱ ከተማ እንዲገባ ተደርጎ በወገኖቻችን ላይ በደረሰው እልቂት ህሊናየን ስቸ እነዚህን የሰይጣን መልዕክተኛ ጭራቆች በህይወቴ ሙሉ በፍትህ አደባባይ ለመፋለም ነበር ወደ ኢትዮጵያ ፖለቲካ ዘው ብዬ የገባሁት፡፡ አሁን ከላይ እንደተጠቀሰው በኢአርኤም/ERM ላይ ሲወጡ የነበሩ ቀደምት የህትመት ጽሁፎችን ማሰባሰብ እና ማስተካከሉን ጥረት እያደርግሁ ሲሆን ከዚያ በፊት በሀገሬ ፖለቲካ ላይ ንቁ ተሳትፎ እና ፍላጎት አንዳሳየሁ ሰለዘነጋሁ ይቅርታ እንድታደርጉልኝ በትህትና እጠይቃለሁ፡፡

በአሁኑ ጊዜ የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ እንደገና በአዲስ መልክ ስልጣኑን ከህግ አግባብ ውጭ በኃይል እና የህዝብን ድምጽ በመዝረፍ ከያዘ ወደ ሁለት ወራት ገደማ ሊሆነው የቀሩት ጥቂት ቀናት በመሆኑ በቀጣይ የኢትዮጵያ ዕጣ ፈንታ ጉዳይ እራሴን ከምንጊዜውም በላይ ዝግጁ በማድረግ ወደተጠናከረ የትግል ምዕራፍ ለመግባት ቆርጨ ተነስቻለሁ፡፡

እ.ኤ.አ በ1991-92 ሳዘጋጃቸው የነበሩት ትችቶቼ እንደሚያመላክቱት የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ እባብ እ.ኤ.አ በ1991 ከእንቁላሉ ተፈልፍሎ ብቅ ሲል እኔም ነበርኩ፡፡ ከ25 ዓመታት ገደማ በፊት የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ በዓለም ላይ ከኢትዮጵያ በስተቀር በየትኛውም ሀገር ታይቶ የማይታወቅ ደም መጣጭ የሆነ የወሮበላ እና የማፊያ መንግስት ሊሆን እንደሚችል በግልጽ ትንበያ ሰጥቸ ነበር፡፡

ቀደም ሲል ከበርካታ ዓመታት በፊት ሰጥቸው የነበረው ትንበያዬ ግልጽ በሆነ መልኩ እ.ኤ.አ   2015 ላይ ሆነን ስንመለከተው ግቡን መምታቱን እያስተዋልን ነው፡፡ እ.ኤ.አ በ2015 ኢትዮጵያ ደም መጣጭ የሆነ አምባገነን መንግስትን ታቅፋ ተቀምጣለች፣ ወይም ደግሞ ታዋቂው አፍሪካዊ ምሁር ጆርጅ አይቴይ እንዳሉት “ከእራሱ ህዝብ ላይ ዋና ዋና የኢኮኖሚ ጭማቂዎችን ሙሉ በሙሉ የሚመጥ ደም መጣጭ መንግስት“ ተብሎ ሊፈረጅ ይችላል፡፡ እግዚኦ መሀረና ክርስቶስ፣ ይቅር ይበለን!

እ.ኤ.አ ከ2000-2005 በነበሩት አምስት ዓመታት ጊዜ ውስጥ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ሳቀርባቸው የነበሩት ትችቶች ላይ ክፍተት ነበረ የሚል እምነት አለኝ፣ ሆኖም ግን ሙሉ በሙሉ እርግጠኛ አይደለሁም፡፡

ያም ሆነ ይህ እ.ኤ.አ ከ2006 በፊት ሳቀርባቸው የነበሩት ማናቸውም ዓይነት ጽሁፎች እና ትችቶች በድረ ገጼ የመረጃ ቋት ውስጥ በመሆን ለአንባቢዎቼ ተደራሽ እንደሚሆኑ በእርግጠኝነት መናገር እችላለሁ፡፡

ከየትም ሆነ ከየትኛውም ምንጭ በማፈላለግ እ.ኤ.አ በ1990ዎቹ እንዲሁም በ1980ዎቹ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ያዘጋጀኋቸውን ጸሁፎች በማሰባሰብ ለአንባቢዎቸ እንዲደርሱ አደርጋሁ፡፡ እ.ኤ.አ በ1990ዎቹ ወይም ደግሞ ምናልባትም በሚሊኒየሙ የመጀመሪያ አስርት ዓመታት የመጀመሪያዎቹ ግማሽ አካባቢ አዘጋጅቻቸው የነበሩትን በርካታ ጽሁፎች እንዴት እና ወይም በምን ምክንያት እንደረሳኋቸው ለመግለጽ አልችልም፡፡ በዚያን ጊዜ በርካታ የህግ መቃወሚያ መግለጫዎችን፣ የውሳኔ ሀሳቦችን እና ጽሁፎችን እያዘጋጀሁ ለአካባቢ አስተዳደር እና ለፌዴራል ፍርድ ቤቶች በማቅረብ ላይ ነበርኩ፡፡ እንግዲህ ያ ሁኔታ በርካታ ነገሮችን ሊያስረሳ የሚችል መሆኑን የሚያመላክት ጉዳይ ነው፡፡ ይኸ ሁኔታ ምናልባትም ብዙ ከመጻፍ እና ከማንበብ ሊመጣ የሚችል ችግር ሊሆን ይችል ይሆን?

በቁጣ መጻፍ እየተባለ በሚጠራው የመንፈስ አለመረጋጋት እየተሰቃየሁ ሊሆን ይችላል፡፡ እ.ኤ.አ በ1960ዎቹ ሁለተኛ አጋማሽ አካባቢ አዲስ አበባ በነበርኩበት ጊዜ በየወሩ በሚወጡ ታዋቂ መጽሐቶች ላይ አንዳንድ ጊዜ አወጣቸው በነበሩት የጀማሪ ጽሁፎች በዚያን ጊዜ ያዳበርኩት ልምድ ሊሆን ይችላል፡፡

የማዳም ቦቫሪ ደራሲ የሆኑት ጉስታቭ ፍላውበርት እንዲህ በማለት የተናገሩት የእኔን ሁኔታ በተሻለ መንገድ ሊገልጸው ይችላል ብዬ አስባለሁ፣ “የመጻፍ ጥበብ የምታምንበትን ነገር ፈልጎ የማግኘት ጥበብ ነው፡፡“

ሁልጊዜ በምጽፈው የሰኞ ትችቴ የማምንበትን እና የማላምንበትን ነገር ፈልጌ አገኛለሁ፡፡ ይህንን በማደርግበት ጊዜ ቀደም ሲል የጻፍኩትን እረሳዋለሁ፣ ምክንያቱም አእምሮዬን ዝግጁ የማደርገው በቀጣዩ ሰኞ እና በተከታታይ በሚመጡት ሌሎች ሰኞዎች የማምንበትን እና የማላምንበትን ነገር ፈልጌ ለመጻፍ ባተሌ የምሆንበት ጊዜ ስለሆነ ነው፡፡

ምናልባትም የአሁኗ ኢራቅ የጥንታዊቷ የፐርሻ ገጣሚ እና ፈላስፋ የነበሩት የታላቁ ኦማር ካያም እንዲህ የሚሉት አጭር የግጥም ስንኞች ቀደም ሲል የጻፍኳቸውን ጽሁፎች ለምን እንደምረሳ ሊገልጿቸው ይችላሉ ብዬ ስለማስብ እንደሚከተለው አቀርባሁ፡

ተንቀሳቃሿ ጣት ሁሌ ትጽፋለች፣
ታወርድ ታወጣለች ትቆርጥ ትጥላለች፣
እንደ እንዝርት ልቃቂት ትሽከረከራለች፣
የሕግ ማስፈጸሚያ ወረቀት ይዛለች፡፡

እናም በድጋሜ ትንቀሳቀሳለች፣
ትወርድ ትወጣለች ትቅበዘበዛለች፣
ለዛ ባለው ጽሁፏ ሰው ታሳምናለች፣
ሀቅን ባደባባይ ፍንትው ታደርጋለች፣
ቅጥፈት አሜኬላን ገደል ትጥላለች
ሸፍጠኛ መሰሪን ታንገዋልላለች፣
እናም በወገን ልብ ትጎዘጎዛለች፡፡

የማያስፈልግን መስመሩን ሰርዛ፣
አውጥታ ቆራርጣ ሰርዛ ደልዛ፣
ተስማሚውን አንቀጽ ታቅፋና አግዛ፣
እንከን ያለበትን ደርታ ሰብዛ፣
ደግማ ትጽፋለች አምጣ አስረግዛ፣
ቁም ነገር በማድረግ ያለፈውን ዋዛ፤
ወገን አስደስታ ጠላት አስተክዛ፡፡

እናማ እንዲህ ብላ፣
ወረቀት አቅርባ ብዕር አስከትላ፣
ከአዕምሮ የመጣን የሀሳብ ወለላ፣
ታሽሞነሙንና በመላ በመላ፣
ታሰራጨዋለች የኋላ የኋላ፡፡

ባዘጋጀችው ቃል፣
ባሳየችው ገድል፣
ህይወት ይፈወሳል፣
ፍትህ ይንኳለላል፣
እንባ ይታፈሳል፣
ወገን ይደሰታል፣
ትግልን ያጧጡፋል፣
ድልን ይቀዳጃል፡፡

ስለሆነም በተደጋጋሚ በጻፍኩ ቁጥር እንደገና ለመጻፍ ጉዞዬን እጀምራለሁ፣ እናም ያለፈውን እረሳለሁ! እስከ አሁንም ለጻፍኳቸው ጽሁፎች አንድም የሚያስጸጽተኝ ቃል የለም!

ሆኖም ግን በኢትዮጵያ ችግሮች እና የወደፊት ዕጣፈንታ ላይ ለመወሰን በሚደረገው ውይይት ላይ ትችቶቼን ማቅረብ የጀመርኩት ዘግይቼ በመሆኑ ጸጸት እንደሚሰማኝ በመግለጽ ይቅርታ መጠየቅ እወዳለሁ፡፡

በአሁኑ ጊዜ የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ስልጣን ከያዘበት ከመጀመሪያው ጊዜ ጀምሮ ሳዘጋጃቸው ነበሩትን ጥቂት ጽሁፎች እና ትችቶች እንደገና ወደ አደባባይ ወደ አንባቢዎቼ እንዲደርሱ በማድረግ ላጣጥማቸው እፈልጋለሁ፡፡

የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ እ.ኤ.አ. በ1991 የስልጣን እርካብን ከተቆናጠጠ ከሁለት ወራት በኋላ ጀምሮ ሳቀርበው የነበረው በመርህ ላይ የተመሰረተ ትችት አሁንም እ.ኤ.አ ሀምሌ 2015 ላይ እንዳለሁት በመርህ ላይ እንደተቀመጠ ሆኖ ይገኛል፡፡ ለድፍን 24 ዓመታት ያህል በወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ጉዳይ ላይ ስሟገት ቆይቻለሁ (በአሁኑ ጊዜም ቢሆን እንኳ በትክክል አላውቀውም፡፡)

ከወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ አመራሮችም ሆነ ከታዛዥ ሎሎዎቻቸው ጋር ምንም ዓይነት ግላዊ የሆነ ችግር የለኝም፡፡ ሆኖም ግን ኢትዮጵያን በጎሳ፣ በኃይማኖት፣ በቋንቋ፣ በአካባቢያዊ መንደርተኝነት እና በጾታ የሚከፋፍሉትን ከፋፋይ እና ዘረኛ የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ፍትሀዊ ያልሆኑ ሸፋፋ እና የተንሸዋረሩ ፖሊሲዎች እና በወገኖቼ ላይ አየፈጸሟቸው ያሉትን የሰብአዊ መብት ረገጣዎች አጥብቄ እንደምቃወም ምንም ዓይነት ጥያቄ የለውም፡፡

በአሁኑ ጊዜ በዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ የመንግስት መምሪያ የበላይ ጠባቂነት እየታገዘ  የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ አምባገነን በፓርላማም ሆነ በክልል ደረጃ ያሉትን ሁሉንም መቀመጫዎች ምርጫን በመዝረፍ መቶ በመቶ አሸንፊያለሁ በማለት ኢትዮጵያ የደም መጣጭ አምባገነናዊ ስርዓት መፈንጫ እንድትሆን እየተደረገ ነው፡፡ ከ24 ዓመታት በፊት ጀምሮ ሳቀርባቸው የነበሩት ትችቶቼ ስሜትን የሚስቡ፣ በመርህ ላይ የተመሰረቱ እና በሀገሪቱ ላይ በቀጣይነት ሊፈጸም የታሰበውን ዕኩይ ምግባር በትንበያ መልክ የሚያቀርቡ ነበሩ፡፡

እ.ኤ.አ ሀምሌ 1991 በሀገሪቱ ላይ የፍርኃት እና የጥላቻ ደመና እያንዣበበ እንደሆነ ግልጽ አድርጌ ነበር፡፡ እንደዚሁም በዚሁ ወር እና ዓመት የኢትዮጵያ ምርጫ ግልጽ መሆን እንዳለበት ማለትም የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ በመሳሪያ ኃይሉ በመተማመን በስልጣን ላይ ተጣብቆ ለመኖር ወይም ደግሞ በሰላማዊ መንገድ በዴሞክራሲያዊ ምርጫ ስልጣንን ለህዝብ መስጠትን በማስመልከት እንዲህ የሚል መልዕክት አስተላልፌ ነበር፡ ጠብመንጃ ደህና ሰንብች፣ ወይም ደግሞ ኢትዮጵያ ደህና ሰንብች የሚል ጽሁፍ አቅርቤ ነበር፡፡

እ.ኤ.አ በ2015 ለኢትዮጵያ ያለው ብቸኛ ምርጫ የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብን ደህና ሰንብት ማለት ብቻ እንደሆነ አምናለሁ!

እ.ኤ.አ በ1991 በኢትዮጵያ የፍርኃት እና የጥላቻ ደመና እያንዣበበ ስለሆነ በቀጣይነት የኖህ የጥፋት ውኃን አይነት ጥፋት በሀገሪቱ ውስጥ ሊመጣ ይችላል የሚል ጽሁፍ አቅርቤ ነበር፡፡

እ.ኤ.አ በ2015 የፍርኃት እና የጥላቻ ደመና የጥፋት ውኃ ጥፋት ሳይመጣ ቀርቷል፣ አምላክ የደም ጎርፍ እንዳያጥለቀልቅ አድርጓል፡፡ ነገር ግን ለኢትዮጵያ ህዝብ መናገር አለብኝ፡፡ አምላክ ለኖህ የቀስተደመና ምልክት ሰጠው፣ ምንም ውኃ አልነበረም፣ እሳትም በቀጣይነት አልነበረም!፡፡

እ.ኤ.አ ሀምሌ 1991 አዘጋጅቸ አቅርቤው የነበረውን እና በኢትዮጵያ ሪቪው መጽሔት/Ethiopian Review Magazine ወጥቶ የነበረውን ጽሁፍ እዚህ ጋ ጫን በማድረግ ማግኘት ትችላላችሁ፡፡

=============================================

ጥቂት ስለ ደም መጣጩ የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ አምባገነን አገዛዝና ቅርጫ ምርጫ ፣

የይስሙላ የዝንጀሮ ፍርድ ቤቶች/kangaroo courts እንደ አሸን ተፈልፍለዋል፡፡

እንደዚሁም ሁሉ በሀገሪቱ ውስጥ የይስሙላ የቅርጫ ምርጫዎች ተንሰራፍተዋል፡፡

እ.ኤ.አ ግንቦት 24/2015 ኢትዮጵያ የይስሙላ የቅርጫ ምርጫ አካሂዳለች፡፡

እ.ኤ.አ ሰኔ 22 የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ አፈቀላጤ የሆነው ሽመልስ ከማል በተመዘገበው የኢኮኖሚ ዕድገት ስኬት ምክንያት ፓርቲያቸው መቶ በመቶ የይስሙላ ምርጫውን እንዳሸነፈ ይፋ አድርጓል፡፡

የሚገርመው ነገር ግን ከማል “ባለፉት አስርት ዓመታት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ባለሁለት አሀዝ ዕድገት አስመዝግቧል“ ለማለት አልደፈረም፡፡ ምክንያቱም ግልጽ እና ቀላል ነው፡፡ ከምንም በላይ ከጥርጣሬ በጸዳ መልኩ የኢትዮጵያ የምጣኔ ሀብት ዕድገት የሁለት አሀዝ ዕድገት አስመዝግቧል የሚለውን የወያኔ ባዶ ቅጥፈት ተራ ውሸት እና የቁጥር ጨዋታ ነው በማለት አጋልጨ አረጋግጫለሁና ነው፡፡

በማያያዝም ከማል እንዲህ የሚል የቅጥፈት ንግግር አሰምቶ ነበር፣ “ገዥው ፓርቲ በሀገሪቱ ውስጥ ባስመዘገበው ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ስኬት ምክንያት መራጩ ህዝብ ድምጹን ለፓርቲው ሰጥቶታል፡፡ ህዝቡ ይኸ ፖሊሲ እንዲቀጥል ይፈልጋል፡፡ በደካማ፣ በተበጣጠሰ እና ተጨባጭነት ያለው አማራጭ ማቅረብ የማይችሉ የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ባሉበት ሀገር ገዥው ፓርቲ ጠቅላይነት ባለው መልኩ ማሸነፍ የሚችል መሆኑ አጠያያቂ ሊሆን አይችልም፡፡“

የኢኮኖሚ ዕድገት ወይስ የኢኮኖሚ ዕድገት አስመሳይነት?

ለእኔ የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ የቅርጫ ምርጫውን መቶ በመቶ አሸንፏል የሚለው ዘገባ የቅርጫ ምርጫው የመጨረሻው ውጤት መግለጫ ሳይሆን በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ የተሰነዘረ የመጨረሻ ዘለፋ እና ስላቅ ነው ብዬ እወስደዋለሁ፡፡

መቶ በመቶ ምርጫ ማሸነፍ ማለት እንደ የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ላለ የበከተ ድርጅት በዴሞክራሲ ላይ መቀለድ ካልሆነ በስተቀር ሌላ ምንም ነገር ሊሆን አይችልም!

ምንም ነገር በማያውቁ ፈጣጣ ደናቁርት መቶ በመቶ ምርጫ አሸነፍኩ በማለት በህዝብ ላይ መሳለቅ ሌላ ምንም ነገር ሳይሆን የእኛን ስብዕናዊ ልህቀት መዘለፍ ማለት ነው!

“ወደ ቅርጫት መጣል ያለበት“ የቅርጫ ምርጫ ቆሻሻ ውጤት፣

እ.ኤ.አ ግንቦት 2015 ስለተካሄደው የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ የቅርጫ ምርጫ ምንድን ነገር አስባለሁ?

እ.ኤ.አ ግንቦት 2015 ተካሄደ የተባለው የቅርጫ ምርጫ እ.ኤ.አ በ2010 የአውሮፓ ህብረት የምርጫ ታዛቢ ቡድን ምርጫውን ከተመለከተ እና ከታዘበ በኋላ ለመለስ ዜናዊ ካቀረበው ዘገባ ጋር አንድ ዓይነት ነው፡፡

የአውሮፓ ህብረት የምርጫ ታዛቢዎች ቡድን አቅርቦት የነበረውን የምርጫ ዘገባ ውጤት አሁን በህይወት የሌለው መለስ እንዲህ በማለት ነበር ያጣጣለው፣ “ወደ ቆሻሻ ማጠራቀሚያ ገንዳ መጣል ያለበት እና ምንም ዓይነት እርባና የሌለው ዘገባ ነው“

ደህና፣ እኔ ደግሞ እ.ኤ.አ ግንቦት 24/2015 ተካሄደ የተባለው የይስሙላ የቅርጫ ምርጫ ዘገባ ውጤት እርባናየለሽ እና ለምንም ነገር የማይውል የቆሻሻ ክምር እና ዘባትሎ በመሆኑ ከወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ጋር አብሮ ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ወደ ታሪክ የቆሻሻ ማጠራቀሚያ ገንዳ ውስጥ መጣል ይገባዋል እላለሁ፡፡

እ.ኤ.አ ሀምሌ 2007 አሁን በህይወት የሌለው መለስ ዜናዊ እንዲህ ብሎ ነበር፣ “የኢትዮጵያ መንግስት የአሜሪካ የምክር ቤት አባላት ያሉትን የሚፈጽም እና በእነርሱ አመራር የሚሽከረከር መንግስት አይደለም፡፡“

እ.ኤ.አ በ2015 የመለስ ትዕንቢታዊ ቃላት ተፈጻሚነትን አግኝተዋል፡፡

እውነት ነው የኢትዮጵያ መንግስት የአሜሪካ የምክር ቤት አባላት ያሉትን የሚፈጽም እና በእነርሱ አመራር የሚሽከረከር ደም መጣጭ አምባገነን መንግስት አይደለም፡፡ ሆኖም ግን ይኸ ጥቅመኛ እና ተለጣፊ ደም መጣጭ አምባገነን የወሮበላ መንግስት የአሜሪካ የመንግስት መምሪያ የሚያዝዘውን የሚፈጽም እና የታዛዥነት እና የሎሌነቱን አቅም በማወቅ በሚፈለገው መጠን የሚጦዝ ደም መጣጭ አሻንጉሊት የወሮበላ መንግስት ስብስብ መሆኑ እሙን ነው፡፡

በዚህ በያዝነው ዓመት በሚያዝያ ወር የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ረዳት ዋና ጸሀፊ እና ከኢራን ጋር በሚደረገው የኒኩሌር የድርድር ስምምነት ንግግር ዋና ኃላፊ የነበሩት ወደ አዲስ አበባ በመሄድ ከምንም ተነስተው እንዲህ የሚል የቀባዣሪነት ንግግር አድርገው ተመልሰዋል፣ “ኢትዮጵያ የጎለበተ የዴሞክራሲያዊ ስርዓትን የምታካሂድ ሀገር ናት፡፡“ ወይ መቀለድ! እናም ትዕዛዝ ጠብ የማይለው የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ የተሰጠውን መመሪያ በስራ ላይ ለማዋል ቃል በመግባት እ.ኤ.አ ግንቦት 24/2015 የተካሄደው ምርጫ ነጻ፣ ፍትሀዊ እና በህዝብ ዘንድ ታማዕነት ያለው ሆኖ እንዲጠናቀቅ አድርጓል፡፡ እኔ አስከማውቀው ድረስ ከዚህ በላይ ቀልድ በዓለም ላይ ያለ አይመስለኝም፡፡

የሸርማን የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ አሽከሮች እና ተላላኪዎች ሴትዮዋን ቅር አላሰኙም፡፡ በተባለው መሰረት በሚገባ ፈጽመዋል፡፡

ባለፈው ሳምንት የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ አሸናፊ በመሆን ሁሉንም 546 የፓርላማ እና 1984 የክልል ምክር ቤት መቀመጫዎችን እንደተቆጣጠረ ይፋ አድርጓል፡፡

እ.ኤ.አ ግንቦት 2014 አቅርቤው በነበረው ትችቴ እ.ኤ.አ በ2015 የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ የቅርጫ ምርጫውን መቶ በመቶ ያሸንፋል የሚል ትንበያ ሰጥቸ ነበር፡፡ ታዲያ ምን ተፈጸመ? ትንበያዬ 99.9 በመቶ ወይስ ደግሞ 100 በመቶ ተፈጻሚነትን አገኘ? ለማለት ሲባል ብቻ አጋንኘ ያቀረብኩት አለመሆኑን ልብ ይሏል!

የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ የቅርጫ ምርጫ ውጤት ድል አድራጊነት እኔ እና ጓደኞቼ በሰማን ጊዜ ትንሽ ፈገግ ብለን የነበረ መሆናችንን አምናለሁ፡፡

አንዳንዶቹ የቆዳ ቀለምን ሳይለዩ ቀልዶች ይዥጎደጎዱ ነበር፡፡ በየትኛውም በሰለጠነ ደርጅት ወይም ኩባንያ እንደዚህ ያለ አሳፋሪ ድርጊት መደገም እንደሌለበት ይናገሩ ነበር፡፡

ለመሆኑ በዴሞክራሲ እና በወሮበላ ዴሞክራሲ መካከል ያለው ልዩነት ምንድን ነው? ዴሞክራሲ ባለበት የምርጫ ስርዓት የምንሰጠው ድምጽ ዋጋ አለው፡፡ ያውም የተከበረ ዋጋ! ምክያቱም ድምጾች የሚቆጠሩት ህግን እና ስርዓትን መርህ ባደረጉ የሰለጠኑ እና ነጻ በሆኑ እውነተኛ ዜጎች ስለሆነ ነው፡፡ በወሮበላ የዴሞክራሲ የምርጫ ስርዓት ግን የምንሰጠው ድምጽ በወሮበሎች ያውም ከገዥው ፓርቲ እና ከእርሱ ጋር በሚሞዳሞዱ ጥቅመኛ ሆድ አደሮች የሚቆጠር ስለሆነ ዋጋ የለውም፡፡ እዚህ ላይ የሚሰጠው ድምጽ እርባናየለሽ ነው!

እ.ኤ.አ ግንብት 2015 ስለተካሄደው የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ የቅርጫ ምርጫ በእርግጠኝነት ምንድን ነው የማስበው?

በአንድ ወቅት ፕሬዚዳንት ጆን ኬኔዲ ስለለውጥ አይቀሬነት እንዲህ በማለት የተናገሩትን አስታውሳለሁ፡፡ “በሰላማዊ መንገድ ለውጥ እንዳይመጣ የሚከለክሉ ሁሉ በነውጥ እና በኃይል የተሞላን አብዮት እንዲያስተናግዱ ይገደዳሉ፡፡“

ኬኔዲ የእርሳቸውን ሀገር ታሪክ በሚገባ ያውቃሉ፡፡ የእንግሊዝ ቅኘ ገዥ መንግስት በአሜሪካ ግዛቶቹ ላይ በሰላማዊ መንገድ ለውጥን ለመቀበል እና ለማስተናገድ ፈቃደኛ አልነበረም፡፡ ይህም በመሆኑ እ.ኤ.አ በ1176 የአሜሪካ የነጻነት አዋጅ እና እ.ኤ.አ በየዓመቱ ሀምሌ 4 ቀን የሚከበረውን የሜሪካን አብዮት/American Revolutionንን አስከተለ፡፡ ግፈኛው መንግስትም ሳይወድ በግድ ለውጥን ተቀበለ፡፡ ስስሟት ቀርቶ ሲስቧት ማለት ይሄ አይደለምን?

ከቀጣዮቹ አራት ቀናት በኋላ የአሜሪካንን የነጻነት ቀን እናከብራለን፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ በላዩ ላይ እንደመርግ የተጫነውን አምባገነኑን የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ወደታሪክ ቆሻሻ ገንዳ አሽቀንጥሮ በመጣል እንደ አሜሪካኖች ሁሉ የእራሳቸውን የነጻነት በዓል ማክበር እንዲችሉ ልባዊ ምኞቴን እገልጻለሁ!

ጊዜ እንዴት ነው የሚበረው እባካችሁ? ከ1991 እስከ 2015!

በ19ኛው ክፍለ ዘመን የአሜሪካ ልብወለድ ጸሀፊ የነበሩት እና የእስካርሌት ሌተር/Scarlet Letter ደራሲ የነበሩት ናትናኤል ሀውቶርኔ “ጊዜ ጥላውን ወደኋላ በመተው በላያችን ላይ ይበራል” ብለው ነበር፡፡

የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ባለፉት ሩብ ምዕተ ዓመታት በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ምን ዓይነት የፍርኃት እና የጥላቻ ጥቁር ግርዶሽ እና ድቅድቅ ጨለማ ጥላ ሞት ነው ጥሎ ያለው!

===== ====  ====  ===== =====  ==== ===== =====  ====  ===== =====  ====

ኢትዮጵያ፡ ከፍርኃት እና ከጥላቻ ባሻገር?

(የኢትዮጵያ ሪቪው መጽሔት/Ethioipian Review Magazine ሀምሌ 1991)

ከአንድ ወር ባነሰ ጊዜ ውስጥ መንግስቱ ኃይለማርያም እና ደርግ ከኢትዮጵያ የፖለቲካ ምድር ላይ ጥርግርግ ብለው ጠፉ፡፡ ድል በአንድ ጊዜ ለኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ)/Ethiopian Peoople’s Revolutionary Democratic Front (EPRDF) ሆነች፣ እናም አዲስ አበባ ምንም ዓይነት ጠንካራ የተቃውሞ ኃይል ሳይኖር በቀላሉ በቁጥጥር ስር ዋለች፡፡

የዚህ ድል ፖለቲካዊ እንደምታ ግን ግልጽ ሳይሆን ቀርቷል፡፡ የዘመናት የጎሳ ቅራኔዎች እና ሽኩቻዎች የፍርኃት እና የጥላቻ ድባብን በመቀስቀስ የፖለቲካ ከባቢ አየሩን ቀጣይነት አመላከቱ፡፡

ኢህአዴግ በህዝቡ ዘንድ ፍተኛ በሆነ የጥርጣሬ መንፈስ ይታይ ነበር፣ ምክንያቱም ድብቅ የፖለቲካ አጀንዳን የያዘ የትግራውያን ድርጅት ነው ተብሎ ይታሰብ ነበርና፡፡ ትግራውያን ያልሆነው ህዝብ ሁሉ የሸፍጥ የፖለቲካ ቁማር ጨዋታ ሂደት ነው እየተደረገ ያለው በማለት በአጠቃላይ የኢህአዴግን ህብረ ብሄር ወካይነት ውድቅ አደረገው፡፡ አማሮች በትግራውያን ድል አድራጊነት ተበሳጩ፣ ምክንያቱም ከጥንት ጀምሮ በመንግስት የስልጣን መዋቅር ላይ ያላቸው ሚና የሚሸረሽርባቸው እና ከስልጣን ክፍፍሉ የሚወገዱ መስሎ ስለታያቸው ነበር፡፡ ኦሮሞዎች ደግሞ ሁኔታውን ምንም ዓይነት ልዩነት የሌለው ለውጥ ነው በማለት ድምዳሜ ያዙ፡፡

ሌሎች የጎሳ ቡድኖች ደግሞ በአማራ እና በትግራውያን የረዥም ጊዜ የስልጣን ትግል ትንቅንቅ ውስጥ እነርሱ በመሀል ሆነው እንደተፈለገው እራሳቸውን ወዲያ እና ወዲህ እየተባሉ የሚጦዙ አድርገው ቆጠሩ፡፡ ሌሎች በርካታዎቹ ደግሞ ስለኢህአዴግ ዓላማ ወይም ደግሞ የፖለቲካ ስልጣኑን ለሌሎች በፈቃደኝነት ማካፈል ስለመቻሉ እና አለመቻሉ በጥርጣሬ እና በፍርኃት ቆፈን ውስጥ ሆነው እየዋለሉ መጠበቅ ጀመሩ፡፡ በወታደራዊ ድሉ ኢህአዴግ ከፍተኛ በሆነ ውስጣዊ እና ዓለም አቀፋዊ ጥንቃቄ እያደረገ ጉዞውን ቀጠለ፡፡

የኢህአዴግ መግለጫዎች፣

የኢህአዴግ አመራሮች እስከ አሁን ድረስ በሚታየው ከፍተኛ የሆነ የፍርኃት እና የጥላቻ ከባቢ አየር ብልጣብልጥነት እና አዛልቆ የማየት እንደምታ ያለው ከፍተኛ የሆነ የፖለቲካ ስራ የሚያካሂዱ መስለው ታይተው ነበር፡፡ እድሜው 35 ዓመት የሆነው የኢህአዴግ ሊቀመንበር የሆነው መለስ ዜናዊ (ትክክለኛ ስሙ ለገሰ ዜናዊ ነው) በቴሌቪዥን መስኮት ላይ ብቅ በማለት በአማርኛ ቋንቋ የቀረቡለትን ጥያቄዎች መልስ መስጠት ጀመረ፡፡ ከዚያም የኢትዮጵያ ባንዲራ በድርጅታቸው ባንዲራ እንደማትተካ ማረጋገጫ ሰጠ፡፡ በቀጣይነት በሚደረገው የሽግግር መንግስት ምስረታ ኢህአዴግ ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት ያለውን ተስፋ ግልጽ አደረገ፡፡ የእርሱ የሽግግር መንግስት ሰፊ መሰረት ያለው መንግስት በምርጫ እስከሚቋቋም ድረስ ሀኔታዎችን ሁሉ የማማቻቸት እና የማሳለጥ ዓላማ እንዳለው ግልጽ አደረገ፡፡ በሀገሪቱ ውስጥ ያለውን የጸጥታ ሁኔታ እንደሚያረጋጋ እና በርኃብ የተጎዳው ህዝብ ቀዳሚ ትኩረት ከሚሰጣቸው ጉዳዮች መካከል ዋና ዋናዎቹ እንደሆኑ ይፋ አደረገ፡፡

መለስ በእስር ቤት የሚገኙት የቀድሞው መንግስት ባለስልጣኖች ጉዳይ ጊዚያዊ መንግስት ከተቋቋመ በኋላ ወደ ፍትህ አካል እንደሚቀርቡ ግልጽ አደረገ፡፡ ከዚህም አንጻር በባለስልጣኖቹ ላይ ምንም ዓይነት በዘፈቀደ የሚደረግ ከህግ አግባብ ውጭ የዘፈቀደ የጥላቻ ግድያ ወይም ደግሞ የበቀል እርምጃ እንደማይወሰድ ይፋ አደረገ፡፡

ከሁሉም በላይ ደግሞ በኢህአዴግ መግለጫዎች ከፍተኛ ትኩረት የተሰጠው መሰረቱ ሰፊ የሆነ የሽግግር መንግስት ለማቋቋም የሚያስችል የሰላም እና የዴሞክራሲ ጉባኤ እ.ኤ.አ ሀምሌ 1/1991 በአዲስ አበባ እንደሚደረግ ይፋ አደረገ፡፡ ስለኤርትራ የሪፍረንደም ጉዳይ ኢህአዴግ እያደረገ ባለው ድጋፍ በቋፍ ላይ ያለ እና በዚህ ጉዳይ ላይ በርካታ ኢትዮጵያውያን/ት በመቆጣት ከቁጥጥር ውጭ የሆኑበት ሁኔታ ነበር፡፡

የኢህአዴግ እርምጃዎች፣

የኢህአዴግ ኃይሎች በተጎናጸፉት ድል በግልጽ በጣም ደስተኛ ሆነው አልታዩም፡፡ ከፍተኛ የሆነ የኃይል እርምጃ ከመጠቀም መጠነ ሰፊ ከሆነ የግድያ ድርጊታቸው እንዲታቀቡ መቆም ነበረባቸው፡፡ ህዝባዊ ሰላማዊ ሰልፎችን እነርሱን በመደገፍ የሚዘጋጀውን ጨምሮ መካሄድ እንደሌለባቸው በይፋ የእግድ ድንጋጌ ደነገጉ፡፡ ጸረ አሜሪካ የሆነ የወጣቶች ስብስብ በአዲስ አበባ በሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ቅጥር ግቢ ፊት ለፊት ተገኝተው በሰላማዊ ሰልፍ ተቃውሟቸውን በሚያሰሙበት ወቅት በኢህአዴግ ኃይሎች በጥይት ተደብድበው እንዲገደሉ ተደረገ፡፡

በእስር ቤት በቁጥጥር ስር የሚገኙ በመቶዎች የሚቆጠሩ በርካታ የቀድሞው መንግስት ባለስልጣኖች ለገሰ አስፋውን እና ተስፈዬ ወልደስላሴን ጨምሮ ጉዳያቸው በፍርድ ቤት በፍትህ አካላት እስኪታይ እንዲጠባበቁ ተገለጸ፡፡ የነጻ ምንጮች እና የምዕራቡ ዓለም ጋዜጠኞች በእስር ቤት ያሉት የህግ እስረኞች በደህና ክብካቤ ላይ እንዳሉ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ምስክርነታቸውን ሰጡ፡፡

የኢህአዴግ አመራሮች በሀገሪቱ ያሉት የመንግስት ሰራተኞች የሰቪል አስተዳደሩን በማገዝ ረገድ የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ሀገር አቀፍ ጥሪ አቀረቡ፡፡ የቤት ለቤት የመሳሪያ ፍተሻ ለማካሄድ ሲባል የቀበሌ ኮሚቴዎች እንዲቋቋሙ ተደረገ፡፡ ወደ ሰሜን ኢትዮጵያ ለመንቀሳቀስ ያገለግል የነበረው እና ለበርካታ ዓመታት ተዘግቶ የቆየው ዋናው አውራ መንገድ እንዲከፈት በማድረግ በርኃብ ለተጎዳው ህዝብ የአስቸኳይ ጊዜ የምግብ እርዳታ እንዲደርስ ተደረገ፡፡

በኢህአዴግ ላይ የተሰነዘሩ ትችቶች፣

በኢህአዴግ ላይ የተሰነዘሩ ትችቶች አሳማኝ ሳይሆኑ ቀጥለዋል፡፡ በጣም ተጠራጣሪ የሆኑ ወገኖች ከኢህአዴግ ጀርባ እምነትየለሽ ዓላማን ይመለከታሉ፡፡ ጥቂቶች ደግሞ የኢህአዴግ መሪዎች ለስለስ ብለው የሚታዩት ስልጣናቸውን እስኪያጠናክሩ እና ሁሉንም ነገር በቁጥጥራቸው ስር እስከሚያውሉ ድረስ ነው የሚል እምነት አላቸው፡፡

ሌሎች ትችት አቅራቢዎች ደግሞ የኢህአዴግ አመራሮች የአንድ ፓርቲ የትግራይ የበላይነት የተንሰራፋበትን አገዛዝ እስኪያሰፍኑ ድረስ የዴሞክራሲያዊ ምልክቶች ያሉባቸውን ነገሮች ሁሉ እየፈጸሙ እና እያታለሉ በብልጣብለጥነት እና በአፈጮሌነት እያስመሰሉ ይዘልቃሉ የሚል ትችት ያቀርባሉ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ኢህአዴግ መሰረቱን በጠንካራ አለት ላይ እስከሚጥል ድረስ የውስጥ እና የውጭ ተጽዕኖዎችን እንደየአመጣጣቸው ምላሽ እየሰጠ ይቆይና ጥንካሬው አለኝ ብሎ በሚተማመንበት ጊዜ አሻፈረኝ ናና ሞክረኝ ወይም ደግሞ ጡንቻውን በመተማመን መንገዱን ጨርቅ ያድርግላችሁ ሊል ይችላል ይላሉ፡፡

ሌሎች በጣም ተጠራጣሪ የሆኑት ወገኖች ደግሞ በመጨረሻው አካሄዱ ኢትዮጵያን ገንጣጥሎ ህልውናዋን እና ማንነቷን ካጠፋ በኋላ ትግራይን ገንጥሎ ከኤርትራ ጋር በመቀላቀል የትግራይ ትግሪኝ ቋንቋ ተናጋሪ ማህበረሰብ በመፍጠር የእራሱን አዲስ ተገንጣይ መንግስት ያቋቋማል የሚል ሀሳብ ያቀርባሉ፡፡

ምን መደረግ አለበት?

ኢህአዴግ መንግስታዊ ስልጣኑን ሙሉ በሙሉ ወስዷል ሆኖም ግን እራሱን እንደህጋዊ የመንግስት አካልነት አይቆጥርም፡፡ የኢህአዴግ ባለስልጣኖች የሽግግር መንግስት እስኪቋቋም ድረስ የህዝቡን ደህንነት በሚመለከት ውሳኔዎችን ማቆየት እና ማስተላለፍ እንችላለን ይላሉ፡፡ ይህ መግለጫ በእስር ቤት የሚገኙትን የቀድሞውን መንግስት ባለስልጣኖች ጉዳይም ያካትታል፡፡

ዊንስተን ቸርችል በአንድ ወቅት እንዲህ የሚል ጥቆማ ሰጥተው ነበር፣ “ድልን የመቀዳጀት ችግሮች ሽንፈትን ከመጋት የበለጠ የሚያስማሙ ናቸው፡፡ ሆኖም ግን እነርሱም ቢሆኑ በቀላሉ የሚታዩ ችግሮች አይደሉም፡፡“ ኢህአዴግ እና የሽግግር መንግስቱ መንግስቱ ኃይለማርያምን ለማስወገድ ያደርጉት ከነበረው ትግል የበለጠ ድልን ከተቀዳጁ በኋላ በበርካታ ችግሮች ተወጥረው ይገኛሉ፡፡ ውስብስብ የሆኑ ችግሮችን ወርሰዋል፡፡

አዲሱ መንግስት የጎሳ መበጣጠስን፣ የምጣኔ ሀብት ቀውስን፣ እና አውዳሚ የሆነውን ረኃብ ለማሸነፍ እንዲችል ከጫፍ እስከ ጫፍ የተወጠረውን ገመድ በመዝለል በሰነከ መልክ መጓዝ መቻል አለበት፡፡ ጥሩ ዓላማ እና መልካም እምነት ብቻቸውን በቂ ሊሆኑ አይችሉም፡፡

የኢህአዴግ አመራር በተለይም በሶሻሊዝም ጥያቄ ላይ በአለት እና በጠንካራ ቦታ መካከል ያለ ነው፡፡ ለበርካታዎቹ የኢህዴግ አመራሮች ሶሻሊዝም በዓለም ላይ እየወደቀ እና አስፈላጊነቱ እየጠፋ የመምጣቱ ሁኔታ የሚይዙት የሚጨብጡትን እያሳጣ ግራ አጋብቷቸዋል፡፡ አከራካሪ በሆነ መልኩ እነዚህ በርካታዎቹ የኢህአዴግ መሪዎች በአንድ ወቅት የስታሊናዊ አልባኒያ አድናቂ እና እ.ኤ.አ በ1970ዎቹ የመጀመሪያዎቹ ዓመታት አካባቢ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሰቲ የህክምና ተማሪ የነበረው መለስ ዜናዊን ጨምሮ ሊታረቅ በማይችለው የማርክሲዝም ሌኒኒዝም ውድቀት ምክንያት የፖለቲካ ትምህርት መከታተል እና እራሳቸውን ማጎልመስ ጀምረው ነበር፡፡

የአልባኒያን ሞዴል አርዓያነት ዘጉ፡፡ አስገራሚ በሆነ መልኩ ኢህአዴግ ድልን በተቀዳጀ  በሶስተኛው ሳምንት ውስጥ የአልባኒያ ኮሙኒስቶች ስልጣናቸውን በፈቃደኝነት የኮሚኒስት አገዛዝን በማስቆም ኮሙኒስት ላልሆኑት አባላት አስረከቡ፡፡ በአሁኑ ጊዜ ኢህአዴግ በጣም ወሳኝ በሆነ የምርጫ አጣብቂኝ ውስጥ ገብቶ ይገኛል፡ ቀደም ሲከተል በነበረው እና ይዞት በመጣው የማይሰራ እና እርባናየለሽ በሆነ የርዕዮት ዓለም ፍልስፍናው ውስጥ ገብቶ መዳከር ወይም ደግሞ በይፋ ሶሻሊዝምን አውግዞ እና እርግፍ አድርጎ ትቶ ያጠለቀውን ቆብ በማውለቅ የዴሞክራሲያዊ ስርዓት አስተዳደርን መቀበል ብቻ ነው፡፡

እንግዲህ ከዚህ አጣብቂኝ ውስጥ ለመውጣት በማሰብ ኢህአዴግ የሊቨራል ዴሞክራሲን ይቀበላል የሚል መግለጫ በመለስ በኩል እንዲሰጥ በማድረግ ድርጅቱ ይህንን የሚያደርገው ሶሻሊዝም በዓለም ላይ ስለወደቀ እና ከዚህ በኋላ ቦታ ስለሌለው በመሆኑ ምክንያት አይደለም፣ ሆኖም ግን ከዚህ በኋላ የዴሞክራሲ ስርዓት ጨዋታ ብቻ ነው ሊያስሄድ የሚችለው በማለት የምርጫቸውን ትክክለኛነት ለማሳመን ሞክረዋል፡፡ ዩናይትድ ስቴትስ እና ሌሎች የምዕራቡ ዓለም ሀገሮች ማንኛውንም ትብብር እና እርዳታ ዴሞክራሲያዊ ተቋማትን መመስረት የሚለውን እንደዋና ቅድመ ሁኔታ አድርገው አቀረቡ፡፡ የዩናይትድ ስቴትስ ባለስልጣን የሆኑት ኸርማን ኮኸን የአሜሪካንን ህገ መንግስት ያረቀቁትን ሰዎች የፖለቲካ ጽሁፍ ለመለስ በመላክ ይህንኑ ርዕዮተ ዓለም እንዲከተል ግዴታ ጣሉበት፡፡

ከአሜሪካ ተሞክሮ እንደታየው ሁሉ ሊቨራል ዴሞክራሲ ቢያንስ በተለይም የግለሰብ ነጻነትን ያካተተ ህገ መንግስታዊ መንግስትን ማቋቋም እንደ ቅድመ ሁኔታ ይጠይቃል፡፡ የመንግስት ኃይሎች ለህገ መንግስቱ ተገዥዎች ናቸው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የአሜሪካ ልምድ የመንግስትን ስልጣን በፌዴራላዊ የአስተዳደር መዋቅር በማዕከል እና በአካባቢያዊ አስተዳደሮች የሚያከፋፍል ነው፡፡ በተግባር በየጊዜው የሚካሄዱ ምርጫዎች፣ ነጻ የብዙሀን የፖለቲካ ፓርቲዎች ውድድሮች፣ የመናገር ነጻነት እና የፖለቲካ ፓርቲዎች በነጻ የመደራጀት መብቶች በጣም አስፈላጊ ነገሮች ናቸው፡፡ የሚፈጠሩ ግጭቶች ሰላማዊ በሆነ መልኩ በመግባባት፣ በድርድር እና በመቻቻል የሚፈቱ ናቸው፡፡ ከምጣኔ ሀብት አንጻር ሊቨራል ዴሞክራሲ መንግስት ውሱን በሆነ መልኩ ብቻ እጁን የሚያስገባ ሆኖ በአጠቃላይ ግን በግል ዘርፉ በግል ድርጅቶች የሚመራ የምጣኔ ሀብት ስርዓት ይዘረጋል፡፡

ጠንካራ የሆነ የዴሞክራሲያዊ ባህል በሌላቸው እና የረዥም ጊዜ አምባገነናዊ ስርዓት ተንሰራፍቶባቸው በቆዩት ማህበረሰቦች ህገ መንግስታዊ መንግስት ማቋቋም በጣም አስቸጋሪ እና ከዚህም በላይ ቀውስን ሊያስከትል የሚችል ሁኔታ ነው፡፡ በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ ጉልበትን ባካተተ መልኩ ከሚደረግ ስምምነት እና ማግባባት የበለጠ ጎራዴው ባልተጠበቀ እና አስቸጋሪ በሆነ መልኩ ሊከሰት ይችላል፡፡ ሆኖም ግን ኃይል የእራሱ የሆነ ተቃራኒ የሆነ ነገርን ያስከትላል፡፡ ኃይል ጥላቻን፣ ፍርኃትን እና የበለጠ ኃይልን መጠቀም የኃይል እርምጃን ያስከትላል፡፡ ኢህአዴግ እና የሽግግር መንግስቱ ኢትዮጵያ አንድነቷን ለማስከበር ወይም ደግሞ ሰላምን እና ፍቅርን ለማስፈን ኃይልን መጠቀም እንደሌለባቸው ማወቅ አለባቸው፡፡

የኢትዮጵያ አሲሶቹ መሪዎች የዴሞክራሲ እሴቶችን እና ተቋማትን በቅን ልቦና በመስራት ማጠናከር አለባቸው፡፡

ቶማስ ጀፈርሰን አስፈላጊ በሆነ መልኩ እንዲህ የሚል ምልከታ አድርገዋል፣ “ምንም ዓይነት ተስማሚ የሆነ የስልጣን ማከማቻ መጋዝን የለም፣ ግን ህዝብ ብቻ ነው፣ እናም የያዙትን ስልጣን ኃላፊነትን በተላበሰ መልኩ በአግባቡ የማይጠቀሙ ከሆነ መፍትሄው ስልጣኑን ከእነርሱ ላይ መውሰድ አይደለም ሆኖም ግን በትምህርት አማካይነት በማስተማር የእነርሱን የኃላፊነት ደረጃ ከፍ ማድረግ ነው፡፡“ አዲሶቹ መሪዎች ትምህርት መማር ብቻ አይደለም ያለባቸው ሆኖም ግን ለህብረተሰቡ አዲስ ራዕይ ማፍለቅ አለባቸው፡፡ መንግስት ወደሚያስበው ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ ህዝብ እና ፖለቲካ ስለሚያስበው እና ስለሚፈልገው ነገር ማሰብ መቻል አለባቸው፡፡

የትምህርት ሸክምነት፣

የትምርት ተግባር ልዩ የሆነ ነገር ነው፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን/ት በመጀመሪያ ደረጃ ለዘመናት ተሸክመናቸው ከኖርናቸው ከፍርሀት እና ከጭፍን የጎሳ ጥላቻ አጉል እምነቶች መውጣት እና እነዚህን ኋላቀር ባህሎች ማስወገድ አለብን፡፡ ባሉን የብዙሀን አስተሳሰቦች እና እምነቶች ላይ እርስ በእርስ መቻቻልን መማር አለብን፡፡ እያንዳንዱ ብሄረሰብ መከባበር እና አንዱ የሌላውን ባህል ማክበር እና መጠበቅ አለብን፡፡ እነዚህን እና እነዚህን ብቻ በማድረግ ነው የእያንዳንዱን ሰው ሰብአዊ መብት ማክበር እና እኩልነትን የሚያጎናጽፉትን የዴሞክራሲ ስርዓት እሴቶች ተግባራዊ ማድረግ የምንችለው፡፡

ሀገሪቱን ለማዳን፣

በሀምሌ ወር ከሚደረገው የፖለቲካ ጉባኤ ትልቅ ነገር ይጠበቃል፡፡ የኢህአዴግ መሪዎች የፖለቲካ ውይይት ምህዳሩን ለማጠናከር እንዲቻል መሰረተ ሰፊ የሆነ የህዝብ ተሳትፎ እንዲኖር ለማስቻል የማሳለጥ ትግባራትን ለመስራት ቃል መግባት አለባቸው፡፡ ሆኖም ግን ስለህዝቡ ተሳትፎ አካሄድ ግልጽነት የላቸውም፡፡ ነገሩን በውል ለመገንዘብ በጣም ውስብስብ ነገር ነው፡፡ በርካታ አስቸጋሪ የሆኑ ጥያቄዎች እስከ አሁን ድረስ ምላሽ ሳይገኙ ቀርተዋል፡፡

በጉባኤው ላይ የሚሳተፉ ሰዎች የጥሪ ግብዣ ይደርግላቸዋልን? የተለያዩ የፖለቲካ ቡድኖች እና የእነርሱ ተወካዮች ለጉባኤው የሚመረጡት በምን ዓይነት መስፈርት ነው? ጉባኤውን የሚመሩት የኢህአዴግ ባለስልጣኖች ናቸውን? የቀድሞው መንግስት አባላት በጉባኤው ላይ እንዲሳተፉ ሊፈቀድላቸው ይችላልን? ቀደም ሲል ኢህአዴግን ሲቃወሙ የነበሩ ድርጅቶች በጉባኤው ላይ መሳተፍ እንዲችሉ ይፈቀድላቸዋልን? ኢህአዴግ በሽግግር መንግስቱ ምስረታ ላይ የተለየ ነገር ለምሳሌም እንደመከላከያ ላለው ሁኔታ የሚያቀርበው ጠቀሜታን ሊያጎናጽፍ የሚያስችል ነገር ይኖራልን? ጉባኤው የሚካሄደው የት ነው? አዲስ አባባ የሚካሄድ ከሆነ በጉባኤው ላይ ለሚካፈሉት ተሳታፊዎች ለደህንነታቸው ምን ዓይነት ዋስትና ይሰጣቸዋል? ጉባኤው በቴሌቪዥን ይተላለፋል ወይስ ደግሞ በሬዲዮ እንዲሰራጭ ይደረጋል?

ጉባኤው በታቀደለት መርሀ ግብር መሰረት የሚካሄድ ከሆነ የኢህአዴግ መሪዎች በመጀመሪያው የዴሞክራሲያዊ ፖለቲካ እሳት ውስጥ የመጠመቅ ተሞክሮን ያስመዘግባሉ፡፡ ለአመራራቸው ህጋዊነት፣ ብቃት፣ ታማኝነት እና ዓላማ ለሚቀርቡላቸው አፋጣጭ ጥያቄዎች ተገቢዎቹን ምላሾች ለመስጠት ዝግጁዎች ሆነው መቅረብ አለባቸው፡፡ የጉባኤው አዘጋጆች የመሪነት አስመሳይነትን የሚያቀርቡ ቢሆንም ጠንካራ የሆነ የፖለቲካ ፈቃደኝነት እና ብልህነትን የተላበሱ መሆን አለባቸው፡፡ የብዙሀን አመለካከቶችን እና ሀሳቦችን ማስተናገድ አለባቸው፡፡ ዘለቄታዊነት ባለው መንገድ ትዕግስትን በመላበስ ቁጣቸውን ማስወገድ እና ማስማማት እና ፍቅርን በተላበሰ ሁኔታ ነገሮችን ማስሄድ አለባቸው፡፡ ታማኝነት ያለው ዴሞክራሲያዊ መንግስት አሁን ካለንበት የተሻለ ጊዜ ሊኖር አይችልም፡፡ በመጨረሻም ዋናው ዓላማ የሰቪል መንግስት ማቋቋም አይደለም፣ ሆኖም ግን በረኃብ፣ በድህነት እና በጎሳ ጦርነት ጥልቀት ባለው ሁኔታ ስትታመስ የቆየችውን ሀገር ማዳን ነው፡፡ ምርጫው ግልጽ ነው፡ የጠብመንጃ አገዛዝን ቻው ብሎ ማሰናበት ወይም ደግሞ ኢትዮጵያን እራሷን ቻው ብሎ ማሰናበት፡፡

===== =====  ====  ===== =====  ==== ===== =====  ====  ===== =====  =

እ.ኤ.አ በ1991 ከ24 ዓመታት በፊት አሁን በስልጣን ላይ ባለው የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ላይ የነበረኝ ስሜት የጠብመንጃ አገዛዝ ቻው ወይም ደግሞ ኢትዮጵያ እራስሽ ቻው የሚል ነበር፡፡

እ.ኤ.አ በ2015 ብቸኛው ምርጫ የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብን ለአንዴ እና ለመጫረሻ ጊዜ ቻው ብሎ ማሰናበት እንደሆነ አምናለሁ፡፡

የሚገርመው እና ተጻራሪ የሆነው ነገር በቀላሉ እና ያለከባድ ችግር በስልጣን ማማ ላይ የወጣውን የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ በጠብመንጃ አፈሙዝ በኃይል ስልጣንን ተቆጣጥሮ እያተረራመሰ ካለበት የስልጣን መንበር ላይ አሽቀንጥሮ በመጣል ወደ ታሪክ የቆሻሻ ገንዳ መጣል አለመቻሉ ነው፡፡

“በሰላማዊ መንገድ ለውጥ እንዳይመጣ የሚከለክሉ ሁሉ በነውጥ እና በኃይል የተሞላን አብዮት እንዲያስተናግዱ ይገደዳሉ፡፡“ ጆን ኤፍ. ኬኔዲ 

ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!

ሰኔ 23 ቀን 2007 .