ፕሬዚደንት ኤልሲሲ (El-Sisi): የኢትዮጵያ እውነተኛ የተግባር ወዳጅ!

ከፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማርያም

ትርጉም በነጻነት ለሀገሬ

እውነተኛ ወዳጅነት በተግባር የሚገለጽ ነው!

ፕሬዚዳንት ኤልሲሲ በሊቢያ ታፍነው በአደጋ ላይ ወድቀው ለነበሩት ኢትዮጵያውያን/ት ወጣቶች የእንኳን በደህና መጣችሁ የክብር ሰላምታ አቅርበዋል፡፡

ባለፈው ሳምንት ፕሬዚዳንት አብደል ፋታህ ኤልሲሲ እራሱን የኢራቅ እና የሌባነን እስላማዊ መንግስት/Islamic State of Iraq and the Levant (ኢሌእመ/ISIS) እንደዚሁም የኢራቅ እና የሶሪያ እስላማዊ መንግስት እያለ በሚጠራው እና በሊቢያ በሚገኘው አሸባሪ ቡድን በቁጥጥር ስር ውለው የነበሩትን ከሁለት ደርዘኖች በላይ የሚቆጠሩ የተጠለፉ ኢትዮጵያውያንን አንገት ከመቀላት በማዳናቸው የዓለምን ህዝብ ቀልብ ስበው ቆይተዋል፡፡

የአል አህራም የእግሊዝኛ ቋንቋ  ድረ ገጽ የሆነው አህራም ድረ ገጽ እንዲህ በማለት አውጇል፣ “ኢትጵያውያን ሰራተኞች በሊቢያው አሸባሪ ቡድን ታፍነው በቁጥጥር ስር ከቆዩ በኋላ በካይሮ ወታደራዊ ኃይል የተቀናጀ ጥረት ከአሸባሪ ቡድኑ አደጋ ነጻ በመውጣት ሐሙስ ጠዋት ወደ ካይሮ የአውሮፕላን ማረፊያው ሲደርሱ አቀባበል ተደርጎላቸዋል፡፡ ሁሉም የክርስትና ኃይማኖት እምነት ተከታዮች እና ብዛታቸው 27 የሆኑትን ኢትዮጵያውያን በግንባር ተገኝተው አቀባበል ላደረጉላቸው ለግብጹ ፕሬዚዳንት የአደጋው ሰለባ የሆኑት ኢትዮጵያውያን ወደ አውሮፕላን ማረፊያው በደረሱበት ጊዜ የግብጽ ወታደራዊ ኃይል እንዴት እንዳዳናቸው የገለጹት ነገር የላቸውም፡፡“

እ.ኤ.አ ሚያዚያ 2015 አጋማሽ ያ አሸባሪ ቡድን ወደ 30 የሚጠጉ ኢትዮጵያውያንን አንገት የቀላ መሆኑን በቀረጸው የቪዲዮ ምስል አሳይቷል፡፡ እ.ኤ.አ ሚዚያ 26 ባወጣሁት ትችቴ ላይ በግፍ የጥቃቱ ሰለባ ለሆኑት ወገኖቻችን እና ለቤተሰቦቻቸው የተሰማኝን ጥልቅ ሀዘን ገልጫለሁ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ አውራጣቱን እያወዛወዘ፣ እራሱን እያከከ እና ምንም ነገር ሳያደርግ ተወሽቆ ለሚገኘው የይስሙላ መንግስት ያለኝን ቁጣ ገልጨ ነበር፡፡ በሊቢያ ስለሚገኙት ቀሪ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ ዕጣ ፈንታ እጨነቃለሁ፣ በጣምም ያሳስበኛል፡፡

የሚያሳስቡኝ በርካታ ምክንያቶች አሉ፡፡

የመጀመሪያውን የወገኖቻችንን አንገት መቀላት ተከትሎ በአሸባሪው ቡድን ታፍነው የነበሩትን እና በፕሬዚዳንት ኤልሲሲ የህይወት ተራዕዳይነት ከእልቂት የተረፉትን እና በሊቢያ የሚገኙ በርካታ ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችንን ጨምሮ እራሱን ህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ (ህወሀት) እያለ በሚጠራው ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ አማካይነት በሊቢያ በረሀ እንደጨው እንዲበተኑ ተደርገው ነበር፡፡ በህይወት የተረፉት ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በግብጽ የሚገኘውን የህወሀትን የዲፕሎማሲ ተወካይ እንዲገናኙ ትዕዛዝ ተሰጥቷቸው ነበር፡፡ እነዚህ በፍርሀት ውስጥ ተወጥረው የነበሩ ስደተኛ ኢትዮጵያውያን እርዳታ ለማግኘት በግብጽ ለሚገኘው የህወሀት ኤምባሲ ስልክ በሚደውሉበት ጊዜ ይቀለድባቸው እና ለስልክ ጥሪው ምላሽ ባለመስጠት ጊዜው በከንቱ እንዲባክን ይደረግ ነበር፡፡ እንግዲህ ይህንን ነው በሊቢያ በከፍተኛ አደጋ ውስጥ ያሉ በርካታ ኢትዮጵያውያን ለአሜሪካ ድምጽ የአማርኛው አገልግሎት እንዲህ በማለት የገለጹት፣ “ስልክ በምንደውልበት ጊዜ ስልኩን ያነሱ እና ይቀልዱብን ነበር፡፡ ከእኛ ጋር አይነጋገሩም ነበር፡፡ በምንደውልበት ጊዜ ስልኩን ያነሱ እና ምላሽ ባለመስጠት ጊዜ እንዲፈጅ በማድረግ በድህነት ገንዘባችን የገዛናት የጥሪ የስልክ ካርድ በጊዜ ሂደት እንድታልቅ ያደርጉ ነበር፡፡“ እንግዲህ እንደዚህ ባለ የወያኔ እርዳታ ንፍገት እና ጨካኝነት ሁኔታ ነው ለአደጋ ተጋልጠው የነበሩት ኢትጵያውያንን አል ማስሪያ/Al Masria በተባለ ጀት የግል የግብጽ አየር መንገድ አማካይነት በካይሮ ዓለም አቀፍ የአውሮፕላን ማረፊያ ሲያርፉ በዩቱቤ ቪዲዮ/Youtube video ድረ ገጽ የተመለከትኩት፡፡

ወጣት ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ ከአራጅ አሸባሪ ቡድኑ መንጋጋ አምልጠው ከተደቀነባቸው አደጋ ተርፈው በማየቴ የተሰማኝን ደስታ እና ሲቃ በቃላት ለመግለጽ እቸገራለሁ፡፡ ለአደጋ ተጋልጠው የነበሩት ወገኖቻችንን አሳፍሮ የነበረው አውሮፕላን ከአውሮፕላን ማረፊያው በር ጋ ሲደርስ አውሮፕላን አብራሪው በኩራት የግብጽን ባንዲራ ከአውሮፕላን አብራሪው ክፍል በመስኮት በኩል ብቅ እንድትል አድርጎ አውለበለበ፡፡ መልዕክቱ ግልጽ ነገርን ያነገበ ነበር፡ ግብጽ በጀግንነት ፈጸመችው የሚል!

ይኸ ድርጊት ለግብጽ ህዝብ፣ መንግስት እና የጦር ኃይሎች ታምራዊ ኩነት ነበር፡፡ ይህ ሁኔታ ለሁሉም ኢትዮጵያውያን አስደናቂ ነገር ነበር፡፡ ይህ ድርጊት ለፕሬዚዳንት ኤልሲሲ የኩራት ወቅት ነበር፡፡

በተቃራኒው ደግሞ መንግስት ነኝ በማለት እጁን አጣጥፎ በኢትዮጵያ ህዝብ ጫንቃ ላይ ከህዝብ ፍላጎት ውጭ ተቆናጥጦ ለሚገኘው ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ታሪካዊ ሀፍረት እና ቅሌት ነው!

ይህ ክስተት ለሁሉም ኢትዮጵያውያን መራራ የሀዘን እና የደስታ የሲቃ ዕለት ነው፡፡ በዚያን ዕለት ኢትዮጵያውያን ደስተኞች ናቸው ምክንያቱም ወንድሞቻችን ከአገጠጠው ጣዕረ ሞት አምልጠው የመጡበት ዕለት ነውና፡፡ በዚሁ ዕለት ኢትዮጵያውያን ልባቸው ተሰብሯል ምክንያቱም እነርሱን ከሞት ለማዳን መንግስታቸው ያደረገው ምንም ዓይነት እገዛ የለምና፡፡

ፕሬዚዳንት ኤልሲሲ የኢትዮጵያውያኑን አንገት መቀላት በሰሙ ጊዜ በቁጣ በመገንፈል “በሊቢያ አረመኒያዊ በሆነ መልኩ በአሸባሪ ቡድኑ አንገታቸውን ለተቀሉት ንጹሀን ኢትዮጵያውያን ግብጽ የተሰማትን ታላቅ ሀዘን ትገልጻለች“ ብለው ነበር፡፡

ፕሬዚዳንት ኤልሲሲ በሊቢያ በአሸባሪ ቡድኑ ታግተው ለነበሩት ኢትዮጵያውያን በድፍረት እና በፈጣንነት እርምጃ በመውሰድ የህይወት አድን ተግባር በመፈጸም በሁለቱ የጥንታዊ ስልጣኔ ባለቤት በሆኑት ሀገሮች መካከል ለዘመናት ጸንቶ የቆየውን ጓደኝነት እና እህትማማችነት በጠንካራ መሰረት ላይ እንዲጣል አድርገዋል፡፡

በኤልሲሲ ስነምግባር የተሞላበት እርምጃ የቀናሁ መሆኔን ማመን እፈልጋለሁ፡፡ ፍላጎቱ የሌለው እና አቅመ ቢሱ በኢትዮጵያ ህዝብ ጫንቃ ላይ እንደ መዥገር ተጣብቆ የሚገኘው የህወሀት ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ሁሉንም ህዝብ አቅም በማሳጣት ምንም ዓይነት እገዛ እንዳይደረግ በማድረግ ከዳር ቆሞ እየተመለከተ ባለበት ሁኔታ የግብጹ መሪ ኤልሲሲ የወገኖቻችንን ህይወት ከሞት ለመታደግ እንደዚህ ዓይነት አኩሪ ተግባር በመፈጸማቸው እጅግ ከልብ አመሰግናቸዋለሁ፣ ቀናሁባቸውም፡፡ ታላቅ የኢትዮጵያ ህዝብ ባለውለታ ናቸው፡፡

የአል ማስሪያ የበረራ አገልግሎት ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችንን ጭኖ ከግብጽ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርስ በቪዲዮ በተመለከትኩ ጊዜ ለቅጽበት ያህል በእራሴ ሀሳብ ላይ ተሳፍሬ በርሪያለሁ፡፡

ይህንን ክስተት በተመለከትኩ ጊዜ “የኢትዮጵያ አየር መንገድ“ የሚሉ ቃላትን አስውቦ ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ላይ ያረፈ ያህል ሆኖ ተሰማኝ፡፡ ይህ ክስተት የኢትዮጵያ አውሮፕላን አብራሪ ከአውሮፕላን ማረፊያ ጣቢያ በሩ ጋ በመድረስ የኢትዮጵያን ባንዲራ (ባለአምስት ኮከቧን ባንዲራ ሳይሆን) በእጁ በመያዝ ከክፍሉ ውስጥ በማውጣት ያውለበለባት ያህል መስሎ ተሰማኝ፡፡ ያ አውሮፕላን ውድ መንገደኞችን ለመቀበል በተዘጋጀው ቀይ ምንጣፍ ከመጨረሻው የተሳፋሪዎች መውረጃ መስመር ላይ የቆመ ያህል ሆኖ ተሰማኝ፡፡ ያ ክስተት ወጣት ኢትዮጵያውያንን ከሞት አደጋ ለማዳን አቀባበል የሚያደርጉ እውነተኛ ኢትዮጵያውያን መሪዎችን ያገኘሁ ያህል ሆኖ ተሰማኝ፡፡

እውነታው በገሀድ ሲታይ ግን የግብጽ አውሮፕላን ነበር በአውሮፕላን ማረፊያው ላይ በድል አድራጊነት ስሜት  እየተምዘገዘገ መጥቶ ያረፈው፡፡ ከአንገት መቀላት የእልቂት አደጋ የዳኑትን ኢትዮጵያውያንን ከቀዩ ምንጣፍ መጨረሻ ላይ በመቆም ከአውሮፕላን የሚወርዱትን አቀባበል የሚያደርጉላቸው ከዋና ባለስልጣኖቻቸው ጋር በመሆን ፕሬዚዳንት ኤልሲሲ ናቸው፡፡ ፕሬዚዳንት ኤልሲሲ በክብር እና በኩራት ከዚያ ቦታ ላይ ቆመዋል፡፡ ከአደጋው የተረፉትን የእያንዳንዱን ኢትዮጵያዊ እጅ በመጨበጥ እና እንኳን ደህና መጣችሁ በማለት የከበረ ሰላምታ ያቀርቡ ነበር፡፡ ኤልሲሲ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ወጣት ደህና መሆኑን ለማረጋገጥ ሲሉ የእጃቸውን መዳፍ በእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ወጣት ፊት ላይ በማሳረፍ ለማረጋገጥ ጥረት ሲያደርጉ ይታዩ ነበር፡፡

ይኸ ክስተት እያንዳንዱ የአደጋ ሰለባ ሊሆን የነበረው ወጣት ሊረሳው የማይችለው ልዩ ዋጋ ያለው ዕለት ነው፡፡ ይህንን ዕለት ለዘላለም ታላቅ ዋጋ ስሰጠው የምኖረው ነው፡፡

ፕሬዚዳንት ኤልሲሲ ልዩ አውሮፕላን በማዘጋጀት እና ለእርሳቸው የጦር ኃይል ልዩ ትዕዛዝ በመስጠት በሊቢያ አንገታቸውን እንዲቀሉ በአሸባሪው ቡድን ታግተው የሚገኙትን ኢትጵያውያን ህይወት ለመታደግ እና ከሞት እንዲድኑ ያደረጉት ለምንድን ነው?

“አንድ በውኃ ውስጥ እየሰመጠ ያለ ሰው ገመድ የሚወረውርለት ማንም ይሁን ማን ጉዳዩ አይደለም፡፡ እንደዚሁም ሁሉ አንድ አንገቱ ሊቀላ በዝግጅት ላይ ላለ የጥቃት ሰለባ ከመቅጽበት ህይወቱን ያተረፋት ማንም ይሁን ማን ደንታው አይደለም!“

ፕሬዚዳንት ኤልሲሲ በፖለቲካ አመለካከታቸው ብቻ የሚደርስባቸውን ስቃይ ለማምለጥ እና የእራሳቸውን እና የቤተሰቦቻቸውን ህይወት ለማሻሻል በማሰብ ሀገራቸውን ትተው የተሰደዱ ኢትዮጵያውያን ወጣቶችን ህይወት አድነዋል፡፡ ውድ ህይወቶችን አድነዋል፡፡ ይኸ ከምንም በላይ እና በላይ ብቻ ሲታወስ የሚኖር ክቡር ነገር ነው፡፡ ኤልሲሲ ክቡር ለሆነው ለሰው ልጆች የነብስ አባት ናቸው፡፡

ቀላሉ እውነታ ሲታይ ፕሬዚዳንት ኤልሲሲ የወጣት ኢትዮጵያውያንን ህይወት ለመታደግ ትዕዛዝ ሰጡ፣ ምክንያቱም የወጣቶቹ ህይወት እንዲተርፍ ስለፈለጉ ነው፡፡ ይህንን አደረጉ ምክንያቱም ይህ ድርጊት መፈጸም ያለበት ትክክለኛ ደርጊት በመሆኑ ምክንያት ነው፡፡ ኤልሲሲ ይህንን ህይወት የማዳን ድርጊት ፈጸሙ፣ ምክንያቱም ኤልሲሲ በግብጽ እና በኢትዮጵያ ወንድማማችነት እና እህትማማችነት ለዘላለም ሰፍኖ እንዲኖር በመፈለጋቸው ምክንያት ነው፡፡ ኤልሲሲ ይህንን በጎ ድርጊት ፈጸሙ፣ ምክንያቱም የኢትዮጵያ የክርስትና እምነት ተከታዮች እንደ ክርስቲያን እና እንደ ሰው የእራሳቸውን እምነት ያለማንም ጣልቃገብነት የማራመድ መብት እንዳላቸው እንዲሁም ፍትህ ሳይነፈጋቸው እና ክብራቸው ተጠብቆ እንዲኖሩ እምነታቸው ስለሆነ ነው፡፡

ቀላል በሆነ መንገድ ለመግለጽ ኤልሲሲ ኢትዮጵያውያኑን ከሞት አደጋ አዳኗቸው ምክንያቱም እነዚህ ሰዎች የሰው ዘር መሆናቸውን የውቃሉና!

በአሁኑ ጊዜ ግን ይኸ ድርጊት በኢትዮጵያ በስልጣን ማማ ላይ ተጣብቆ ከሚገኘው ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ አመለካከት ጋር በምንም ዓይነት መልኩ አይገናኝም፡፡

የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ለምንድን ነው አውሮፕላን ወደ ሊቢያ በመላክ በአሸባሪ ቡድን ታግተው የነበሩትን ወገኖቻችንን ለማስመጣት የማይሞክረው? ስለዚህ ጉዳይ እኔ ምንም የማውቀው ነገር የለኝም፡፡ ምናልባትም የወያኔ ዘራፊ የወሮበላ ቡድን ስብስብ እራሱም አጋች እና አፋኝ ድርጅት በመሆኑ ምክንያት ይሆን ይሆን?

የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ግንቦት 7 የፍትህ እና የዴሞክራሲ ንቅናቄ እየተባለ የሚጠራው የተቃዋሚ ቡድን ዋና ጸሐፊ የነበሩትን አቶ አንዳርጋቸው ጽጌን በማፈን የፈጸሙትን ህገ ወጥ ድርጊት በማውገዝ እ.ኤ.አ ሐምሌ 14/2014 የተቃውሞ ትችቴን አቅርቤ ነበር፡፡ በአሁኑ ጊዜ የመን የምትባለው ሀገር የአሸባሪዎች መደበቂያ ዋሻ እና መናኸሪያ ሆናለች፡፡ የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ አንዳርጋቸው ጽጌን ለማፈን ከአሸባሪዎች ጋር የስምምነት ውል አድርጓልን? እኔ ስለዚህ ጉዳይ የማውቀው ነገር የለኝም፡፡

በእርግጠኝነት የማውቀው ነገር ቢኖር አይሲስ/አይኤል እና ህወሀት ስለሚያካሂዱት ጠለፋ እና ማፈን ምንም ዓይነት ልዩነት የለም፡፡ በአሸባሪ መንግስት የሚፈጸም ወንጀል በአሸባሪ ድርጅት ከሚፈጸም ወንጀል የሚለው ነገር የለም፡፡

የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ የማይሞላ ኪሳቸውን ለመሙላት በማሰብ ወደ ሎስ አንጀለስ አዲስ የበረራ መስመር ለመክፈት እጅግ በጣም ባተሌ ሆነው ይገኛሉ፡፡

የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ የታገቱትን ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችንን አውሮፕላን ተከራይተው ሄደው ለማምጣት እንዲችሉ በልመና የሚያገኙት ገንዘብ ኪሳቸውን እስኪሞላ ድረስ በመጠበቅ ላይ ይሆኑ ሆን?

ምናልባትም ፕሬዚዳንት ኤልሲሲ ያደረጉትን ክብር ያለው ተግባር ለመፈጸም የወያኔ የዘራፊ ቡድን ስብስብ አቅም ያጥረው ይሆናል፡፡ ምንም ዓይነት መከላከያ በሌለው ህዝብ ላይ ጥርሳቸውን በመንከስ ሰላማዊ ተቃዋሚዎችን በመጨፍጨፍ ላይ ይገኛሉ፡፡ አይሲስ/አይኤል የሚያደርገውን እያዩ ዝም ብለው ቆመው ማየት ይኖርባቸዋልን? ትልቁ ዱላ በመያዝ ከህዝቡ ጋር ድምጻቸውን ከፍ አድርገው በመነጋገር ላይ ይገኛሉ፣ ሆኖም ግን በዓለም አቀፍ መድረክ ላይ በሚያሳዝን ሁኔታ አቅም የለሽ ድሁሮች ሆነው ይገኛሉ፡፡

የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ አንገታቸውን እየተቀሉ ስላሉት ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን እና በሊቢያ በሚገኙት ቀሪዎቹ ኢትዮጵያውያን ላይ በአጠቃላይ እያደረገ ያለው እያያዝ እጅግ በጣም አሳዛኝ እና የሚዘገንን ጉዳይ ነው፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ በአሸባሪ ቡድኑ አንገታቸውን የተቀሉት እና የጥቃቱ ሰለባ የሆኑት ኢትዮጵያውያን ለመሆናቸው እውቅና ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆነም፡፡ በአስመሳይነቱ እና በቀጣፊነቱ የሚታወቀው እና የመንግስት ቃል አቀባይ የሆነው ሬድዋን ሁሴን ሌላው ቀርቶ የእራሱ መንግስት የተገደሉት ዜጎች ኢትዮጵያዊ መሆናቸውን ሳያረጋግጥ የኢትዮጵያ መንግስት ይህንን ድርጊት ያወግዛል የሚል መግለጫ አውጥቶ ነበር፡፡ የታገቱት የጥቃት ሰለባዎች ኢትዮጵያውያን መሆናቸውን ለማረጋገጥ ገና መጠበቅ አስፈላጊ ሊሆን ይችላል፡፡

አንገታቸውን የተቀሉት እና የጥቃቱ ሰለባ ኢትዮጵያውያን መሆናቸውን ሲኤንኤ ያረጋገጠ እና የዘገበ ቢሆንም የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ መንግስት ደንታው አይደለም፡፡ አንገታቸውን የተቀሉት እና የጥቃቱ ሰለባ የሆኑት ኢትዮጵያውያን መሆናቸውን አል-ጃዚራ ያረጋገጠ እና የዘገበ ቢሆንም የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ምኑም አይደለም፡፡ አንገታቸውን የተቀሉት እና የጥቃቱ ሰለባ የሆኑት ኢትዮጵያውያን መሆናቸውን ሬውተርስ፣ አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ፣ ቢቢሲ፣ ቪኦኤ፣ ኒዮርክ ታይምስ፣ ዋሽንግተን ፖስት…ሁሉም እንዳረጋገጡት እና እንደዘገቡት የአሸባሪው ቡድን የጥቃት ሰለባዎች በሙሉ ኢትዮጵያውያን ናቸው፡፡ አንገታቸውን በመቀላት የጥቃቱ ሰለባ ኢትዮጵያውያን መሆናቸው በበርካታ ማስረጃዎች የተረጋገጠ ቢሆንም የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ዓይኑን በመጨፈን እና እውነታውን በመካድ አላየሁም፣ አልሰማሁም፣ አላውቅም በማለት እውቅና ሳይሰጥ በግትር አቋሙ ጸንቶ ቆይቷል፡፡

በሊቢያ በአሸባሪው ቡድን አንገታቸውን እየተቀሉ የጥቃት ሰለባ የሆኑት ወገኖቻችን ኢትዮጵያዊ መሆናቸውን የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ገና ከመጀመሪያው ጀምሮ እውቅና አልሰጥም በማለት የተቃወመው ለምንድን ነው? ምናልባትም እነርሱም የዜጎቻቸውን አንገት በመቅላቱ ሁኔታ ዋና ተዋናይ እና በዜጎች ላይ አደጋ የሚያስከትሉ በመሆናቸው ምክንያት ሊሆን ይችላልን? በስህተት የሌላ ሀገር ዜጎች ናቸው አንገታቸውን የተቀሉት በማለት ሀዘናቸውን ለመግለጽ ተጨንቀው ስለነበር ነውን? ማንም ጨዋ የሆነ በዓለም ላይ የሚገኝ መንግስት ሁሉ የተለያዩ የዓለም አቀፍ የዜና ወኪሎች የዘገቡትን እንዳለ በመቀበል አስደንጋጭነቱን በመገንዘብ አፋጣኝ ወደሆነ እርምጃ መሄድ የለበትምን? አንድ ጨዋ የሆነ መንግስት በርካታ የሆኑ ዜጎቹ አንገታቸውን እየተቀሉ ሲያልቁ እና ሌሎቹ ዜጎቹ ደግሞ አንገታቸውን ለመቀላት እየተዋከቡ ባሉበት ሁኔታ ያለውን ሀብት እና አቅም ሁሉ በማንቀሳቀስ የዜጎቹን ህይወት ከሞት አደጋ ለመከላከል እና ሌሎቹን ደግሞ ስቃይ ከሚፈጸምባቸው ሀገር ለማስወጣት አንድ ነገር ለማድረግ መረጃዎችን መቀበል የለበትምን? በእርግጥ እነዚህ ሁሉ ጥያቄዎች ከአፍ የዘለሉ አይደሉም፡፡ ጨዋነት እና ወሮበላነት ፍጹም የሆኑ ተቃራኒዎች ናቸው፡፡

እኔ ስለዚህ ሁሉ ጉዳይ የማውቀው ነገር የለኝም፡፡ ለእኔ በጥንታውያን ግሪክ እምነት ክንፍ እና የአንበሳ ሰውነት ያለው እና የሴት ሰው ጭንቅላት ዓይነት ነገር ያለው፣ የእርሱን እንቆቅልሽ የማይፈታውን ሰው አንቆ የሚገድል፣ (ቃላት ለመፈብረክ አይደለም) እንዲሁም አባቱን ገድሎ ሚስቱን የሚያገባ ዓይነት አስተሳሰብ ያላቸው ናቸው ፡፡

የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ አገዛዝ ገና ከመጀመሪያው አንገታቸውን እየተቀሉ እንዲያልቁ የተደረጉትን የጥቃት ሰለባዎች እውቅና ለመስጠት ተቃወመ ምክንያቱም ደንታው አልነበረም፣ አሁንም ቢሆን ደንታው አይደለም፡፡

የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ አገዛዝ በሊቢያ ያሉትን ኢትዮጵያውያን ህይወትን ለመታደግ ሙከራ አላደረገም ምክንያቱም ጉዳዩ አይደለም፣ አያስጨንቀውምም፡፡

የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ አገዛዝ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሀገር ስላሉት ኢትዮጵያውያን መሰቃየት እና መገደል ደንታው አይደለም ምክንያቱም አያስጨንቀውምና፡፡ ይኸ ምንም ነገር ያልተቀላቀለበት ጥሬው እውነታ ነው!

ኤልሲሲ ስለክርስቲያን ኢትዮጵያውያን ደህንነት ጉዳይ ብቻ አይደለም የሚያሳስባቸው ሆኖም ግን ለሺህ ዘመናት በግብጽ ስለኖሩት የግብጽ ክርስቲያኖች ደህንነት ጭምር እንጅ፡፡ እርሳቸው በተግባር ተፈትኖ የተሞከረ መዝገብ አላቸው፡፡

እ.ኤ.አ የካቲት 2015 ወደ ሁለት ደርዘን አካባቢ የሚሆኑ ግብጻውያን የ30ቹን ኢትዮጵያውያንን አንገት በቀላው ሰይጣናዊ የአሸባሪ ቡድን በታረዱበት ወቅት ኤልሲሲ የጥቃቱ ሰለባዎች በእርግጠኝነት  ግብጻውያን መሆናቸው እስከሚረጋገጥ ድረስ በማለት ረዥም ጊዜ አላባከኑም፡፡ የግብጽ ዜጎች ናቸው ወይስ አይደሉም በማለት እጃቸውን እና አውራጣታቸውን በማወዛወዝ የመወሰን ችሎታቸውን ሲያጓትቱ አልቆዩም፡፡ ይልቁንም በቴሌቪዥን መስኮት ላይ ብቅ በማለት አንገት የመቅላት ድርጊቱ በተፈጸመ በሰዓታት ጊዜ ውስጥ “ግብጽ ተገቢውን እርምጃ ለመውሰድ ጊዜ አታባክንም“ በማለት ያላቸውን ጽኑ አመራር አሳይተዋል፡፡ በህዝብ ዘንድ በአደባባይ በመቅረብ የተሰማቸውን ጥልቅ ሀዘን ለኢትዮጵያ ህዝብ ግልጽ በማድረግ መጽናናትን ተመኝተዋል፡፡ ይህንን በሊቢያ በአሸባሪዎች እና በፈሪዎች የተፈጸመውን እኩይ ድርጊት ለዓለም ህዝብ ይፋ ካደረጉ በኋላ  ኤልሲሲ በሰዓታት ጊዜ ውስጥ ከመከላከያ ኃይላቸው ጋር ምክክር በማድረግ የግብጽን ቦምብ ጣይ አውሮፕላኖች በተመረጡ የአሸባሪው ቡድን ይዞታ በሆነቸው በሊቢያ ውስጥ በምትገኘው ዴርና ከተማ ላይ ዒላማ በማድረግ ተገቢ እርምጃ እንዲወሰድ አድርገዋል፡፡ ለ21 የግብጽ ጳጳሳት ሞት ክብር ሲሉ ኤልሲሲ የ7 ቀናት የሀዘን ጊዜ አድርገው አውጀዋል!

ባለፉት ጥቂት ዓመታት በግብጽ የሚገኙ የክርስትና እምነት ተከታዮች የአመጽ ብጥብጥ እና ግድያ ይፈጸምባቸዋል፡፡ ኤልሲሲ ፕሬዚዳንት ከመሆናቸው በፊት በተለይም እ.ኤ.አ በ2013 በሀገሪቱ በሚገኙ ወደ 80 የሚጠጉ ቤተክርስቲያኖች ተደምስሰዋል ወይም ደግሞ እንዲቃጠሉ ተደርገዋል፣ እናም በደርዘኖች የሚቆጠሩ የክርስትና እምነት ተከታዮች ጉዳት ደርሶባቸዋል ወይም ደግሞ በአመጽ እና ብጥብጥ እንዲገደሉ ተደርገዋል፡፡

እ.ኤ.አ ጥር 2015 ኤልሲሲ በገና በዓል ዋዜማ የቅዱስ ማርክ ካቴድራልን በመጎብኘት ለአናሳዎቹ የክርስትና እምነት ተከታዮች ያላቸውን መልካም ምኞት በመግለጽ የመጀመሪያው የግብጽ ፕሬዚዳንት ሆነዋል፡፡ በንግግራቸው ላይ ፕሬዚዳንት ኤልሲሲ እንዲህ ብለው ነበር፡

ግብጽ ለዘመናት ለዓለም ህዝብ ሰብአዊ ርህራሄን እና ስልጣኔን አበርክታለች፣ እኛም በአሁኑ ጊዜ እንደዚያ ያለውን ደግ ነገር እንደገና ማድረግ ይኖርብናል፡፡ አዎ፣ ሰብአዊ ርህራሄ እና የስልጣኔ መልዕክት እንደገና ከግብጽ መምጣት አለበት፡፡ በዚህም ምክንያት ነው እራሳችንን ግብጻውያን ከማለት ውጭ በሌላ በምንም ዓይነት ስያሜ የማንጠራው፡፡ ለዚህም ነው ግብጻውያን መሆን ያለብን፡፡ በዚህም ምክንያት ነው ትክክለኞች እና በተግባር የተፈተንን ግብጻውያን የሆንነው! አላህ ምን እንደሚያስብ ልነግራችሁ እፈልጋለሁ፣ አላህ እንዲሆን የሚያስበው- ሀገራችንን በጋራ እንድንገነባ፣ እርስ በእርስ እንድንተጋገዝ፣ ለእያንዳንዳችን መተሳሰብ እንዲኖር- እርስ በእርስ እንድንዋደድ፣ እያንዳንዳችን ከአንገት ሳይሆን ከአንጀት እንድንዋደድ እና ሰዎች ያለምንም ጥላቻ በሰላም እና በፍቅር መኖር እንድንችል ነው… ስለሆነም እንደገና አንድ ጊዜ ልንገራችሁ፣ መልካም አዲስ ዓመት፣ ለሁሉም ግብጻውያን መልካም አዲስ ዓመት! (አጽንኦ ተጨምሯል፡፡)

ከዚህ በተጻረረ መልኩ በኢትዮጵያ ያለው አገዛዝ ኢትዮጵያ የምትባል ሀገር አላውቅም በማለት የጎሳ ክልልን በመቀፍቀፍ ዘመናዊ የአፓርታይድን ሰይጣናዊ ፍልስፍና ስርዓት በመተግበር ላይ ይገኛል፡፡ የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ወደ 25 ዓመታት አካባቢ የኢትዮጵያን ህዝብ በጎሳ እና በዘር በመከፋፈል ክልል የሚባል የፖለቲካ መዋቅሮችን በመዘርጋት እና በደቡብ አፍሪካ እንደነበረው የአፓርታይድ ባንቱስታንስ ሁሉ እንደ ከብት በበረት ውስጥ በማጎር አደህይቶ ለመግዛት ብዙ ታትሯል፡፡

በአንድ ወቅት ኢትዮጵያ ጥላቻን እና ጥላቻ የሚቀፈቅፉ የሰይጣን ተምሳሌቶችን የሚጠላ መሪ እንዲኖራት ለአምላክ በመጸለይ እንዲህ በማለት አውጃለሁ፣ “እራሳችንን ኢትዮጵያውያን ከማለት በስተቀር በሌላ በማንም ስም መጠራት የለብንም፡፡ መሆን ያለብን እንደዚህ ነው- ኢትዮጵያውያን በእርግጥም በስም ለይስሙላ ሳይሆን በተግባር ኢትዮጵያውያን! እንዲህ በማለት ልነግራችሁ እፈልጋለሁ- አላህ ከፈቀደ፣ እግዚአብሄር ከፈቀደ በአንድ ላይ ሆነን ሀገራችንን እንገነባለን፣ እርስ በእርስ እንተጋገዛለን አንዳችን ለአንዳችን እናስባለን፣ እርስ በእርስ እንዋደዳለን፣ ከአንገት ሳይሆን ከአንጀት እንዋደዳለን እናም ህዝቡ ይህ ተግባራዊ ሲሆን ማየት ይፈልጋል…“

የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ በእርግጥ ከረዥሙ የህግ እጅ እራሱን ለማዳን ምንም ዓይነት ችግር የለበትም፡፡ አሻንጉሊቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርም ደሳለኝ እና በብርሀን ፍጥነት ወደ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት የተተኮሰው የወባ ትንኝ ተመራማሪ አለቃው ቴዎድሮስ አድኃኖም እ.ኤ.አ በ2007 በኬንያ ተካሂዶ የነበረውን ሀገር አቀፍ ምርጫ ተከትሎ ተከስቶ በነበረው ብጥብጥ ምክንያት በአሁኑ ጊዜ የኬንያ ፕሬዚዳንት የሆነው ኡሁሩ ኬንያታ ከፍተኛ የሆነ ሰብአዊ መብት ድፍጠጣ አካሂዷል በሚል የዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ክስ መስርቶበት የነበረ ሲሆን ከዚህ ከገባበት አዘቅት ለማውጣት እና ከዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ፊት እንዳይቆም እና በህግ ተጠያቂ እንዳይሆን ያልፈነቀሉት ድንጋይ አልነበረም፡፡ እነዚህ ሁለቱ ፈጣጣዎች የሮም ስምምነትን በመጣስ በህዝብ ላይ እልቂትን የፈጸሙ የአፍሪካ አምባገነኖች ጉዳይ በዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ሳይሆን በእራሳቸው በአፍሪካውያን ፍርድ ቤቶች እንዲዳኙ ለማድረግ ያልፈነቀሉት ድንጋይ፣ ያልቧጠጡት ተራራ እና ያልወረዱት ቁልቁለት አልነበረም፡፡ በተለያዩ አጋጣሚዎች ኃይለማርያም ዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ወደ ዘር አዳኝነት ተሸጋግሯል በማለት በተደጋጋሚ ሲወነጅል ቆይቷል፡፡

ያም ሆነ ይህ እነዚህ ሁለቱ አምባገነኖች እና ለሰው ልጆች ሰብአዊ መብት መከበር ደንታ የሌላቸው ፍጡሮች ኡሁሩ ኬንያታን ከዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት አቃቤ ህግ መንጋጋ ለማዳን በቅተዋል፡፡

ሆኖም ግን በሊቢያ በአሸባሪ ቡድን የታገቱትን ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችንን ለማዳን አንድም ነገር ሳያደርጉ ቀርተዋል፡፡ ነግር ግን ያንን መልካም ስብዕና የታከለበትን ተግባር ኤልሲሲ ፈጽመውታል! በእርግጥ የወያኔ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ያንን ድርጊት ላለማድረጉ ብቻውን አይደለም፡፡

የአፍሪካ ህብረትም እንደዚሁ የተለመደውን የይስሙላ ንግግር ከማድረግ ውጭ ምንም ያደረገው ነገር የለም፡፡ የአፍሪካ ህብረት የወቅቱ ሊቀመንበር የሆኑት ንኮሳዛና ድላሚኒ ዙማ በኢትዮጵያውያን ወገኖቻቸን አንገት መቀላት ላይ “የአረመኔዎች እና የፈሪዎች ብትር” በማለት የዓዞ እንባ አንብተዋል፡፡

የኦባማ አስተዳደር አንገታቸውን ለተቀሉት ወገኖቻችን ጭካኔ የተሞላበት እልቂት በማለት መልዕክት ሲያስተላልፉ ዓይናቸው ከእንባ የደረቀ እና የሀዘን ስሜትን ያልያዘ የፊት ገጽታ ነበር የሚነበብባቸው፡፡

የአውሮፓ ህብረት የኃይማኖት ልዩነትን ለመፍጠር የተደረገ “ወንጀል” በማለት ገልጾታል፡፡

ኤልሲሲ የእጃቸውን እጅጌ ከፍ ከፍ በማድረግ አውሮፕላናቸውን ነዳጅ በመሙላት ኢትዮጵያውያን ታግተው ካሉበት ቦታ ድረስ እንዲበር እና ጥንቃቄ በተመላበት ሁኔታ ደህንነታቸውን ጠብቆ አስፈትቶ በሰላም ወደ ግብጽ እንዲያመጣቸው ለወታደራዊ ኃይላቸው ትዕዛዝ ሰጡ፡፡ ይህንን ክቡር የሆነ ድርጊት በመፈጸም ዘመን የማይሽረውን እንዲህ የሚለውን አባባል በተግባር አሳይተዋል፣ አስመስክረዋልም፣ “በወቅቱ የተከናወነ አንድ ተግባር ከአስር ሺ ቃላት የበለጠ ዋጋ አለው፡፡“

የኤልሲሲን ቅጽበታዊ እርምጃ በመውሰድ ድርጊቱ አስመሳይነትን ያቀፈ ፖለቲካዊ ዓላማ ይኖረዋል ሊባል ይችላል፡፡ አንዳንድ ሰዎች የታገቱትን ኢትዮጵያውያን በማስፈታት የፕሮፓጋንዳ ስራ በመስራት በህዳሴው ግድብ ዙሪያ ለሚደረጉ ስምምነቶች ረዥም እጀ እንዲኖራቸው በማሰብ ነው ይላሉ፡፡ እንደዚሁም ደግሞ አንዳንዶች ለእራሳቸው ዝና ሲሉ ያደረጉት ድርጊት ነው ይላሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ ይህንን ያደረጉት ዓለም አቀፍ እና አህጉራዊ ተሰሚነታቸውን ከፍ ከፍ ለማድረግ ሲሉ ነው ይላሉ፡፡ የፈለጉትን ማለት ይችላሉ፡፡ እነርሱ ስላሉት ነገር ማን ደንታ አለው! ኤልሲሲ የተግባር ሰው እንጅ የአፍ ካራቴ አራማጅ አይደሉም፡፡ ይህንን በተግባር አስመስክረዋል! የፈለገውን ነገር ይባል ህይወትን ከማዳን በላይ ክቡር ነገር የለም፡፡

እውነታው ፍርጥርጥ ብሎ ሲታይ ኤልሲሲ በወሰዷቸው እርምጃዎች በደርዘኖች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን አንገት ከመቀላት ተርፏል፡፡ እኔ ስለእርሳቸው ድፍረት፣ ለሰው ልጅ ስላላቸው ጽኑ ፍቅር እና የአመራር ብቃት በስተቀር ሌላ የምለው ነገር የለኝም፡፡

ኤልሲሲ ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችንን ከሞት ለመታደግ ስላደረጉት ጥረት ምን ዓይነት የመሪነት ስብዕና እንዳላቸው አንዳንድ ጥያቄዎችን እንዳነሳ አድርጎኛል፡፡

ላለፉት በርካታ ዓመታት ኤልሲሲን በህዝብ መገናኛ ዘዴዎች ስከታተላቸው ቆይቻለሁ፡፡ በግብጽ ስለተካሄደው ጸደይ አብዮት/Arab Spring ጥቂት ትችቶችን ጽፌ ነበር፡፡ ኤልሲሲ የሙባረክ ተቀጽላ ናቸው የሚል ድምዳሜ ነበረኝ፡፡ መሐመድ ሙርሲ እርሳቸውን የጦር ኃይሎች አዛዥ አድርገው ሲሾሟቸው እና እ.ኤ.አ በ2012 መከላከያ ሚኒስትር ሲደረጉ ከእርሳቸው ብዙም አልጠበቅሁም ነበር፡፡

ባለፉት ጥቂት ዓመታት ኤልሲሲ እራሳቸውን ለመሆን በቁ ሰው ሆነዋል፡፡ በግብጽ ላይ ተከስቶ በነበረው ቀውስ እና ያልተጠበቀ ሁኔታ የማያቋርጥ እና ቀጥተኛ የሆነ አመራር ሰጥተዋል፡፡

አልሲሲ የፕሬዚዳንት ስልጣኑን ከተቆናጠጡበት ጊዘ ጀምሮ እንደ ብልህ እና ወሳኝ አመራር ሰጭ ስሜቴን ስበውኛል፡፡ በስራቸው ያለውን የአመራር ቡድን ውጤታማ በሆነ መልኩ በማስተባበር የውሳኔ ሰጭነት ችሎታቸውን አሳይተዋል፡፡ ኤልሲሲ በመካከለኛው ምስራቅ አዲስ ዓይነት የአመራር ጥበብን እያራመዱ ያሉ እና ጎልተው የወጡ እንዲሁም አሸባሪነትን በወታደራዊ እና በፍልስፍናው ደረጃ ለማምከን በርትተው የሚሰሩ መሪ ናቸው፡፡

አሸባሪነትን በሚመለከት አንድ ጊዜ መትተው የሚሮጡ ዓይነት መሪ አይደሉም፡፡ ሆኖም ግን በዚህ በጸረ ሽብርተኝነቱ ዘመቻ ዘላቂነት ባለው ሁኔታ ክትትል እያደረጉ ለማምከን እና ለሽብርተኝነት ድጋፍ የሚያደርጉ ኃይሎችን ከማገዝ እንዲታቀቡ ለማድረግ አበርትተው የሚሰሩ መሪ ናቸው፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ኤልሲሲ ግልጽ የሆኑ እና ባልተለመደ መልኩ ድፍረትን የተላበሱ ጠንካራ መሪ ናቸው፡፡  እ.ኤ.አ ጥር 2015 የግብጽ ነባር እና ታዋቂ በሆነው የአል አዝሀር ዩኒቨርስቲ በመገኘት ንግግር አድርገው ነበር፡፡ በዚያ ዩኒቨርስቲ ላይ በመገኘት ያደረጉት ንግግር ያልተጠበቀ ብቻ አልነበረም ሆኖም ግን በጣም የሚያስደንቅም ነበር፡፡ ኤልሲሲ በእስልምና ላይ አብዮት ለማካሄድ የተለጠጠ ዕቅድ ነድፈዋል!

… እዚህ ጋ የክርስትና እምነት አባቶችን እጠቅሳለሁ፡፡ ወደፊት ስለሚገጥመን ሁኔታ አስቀድመን ጠንካራ እምነት ሊኖረን ይገባል፡፡ እናም በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ከብዙ ጊዜ በፊት ጀምሬ ግንዛቤ ለመፍጠር ጥረት ሳደርግ ቆይቻለሁ፡፡ በጣም ቅዱስ ነው ብለን የያዝነው አስተሳሰብ ሊታሰብ የማይችል እና በአጠቃላይ የሙስሊሙን ዓለም የጭንቀት፣ የአደጋ፣ የግድያ እና የውድመት ምንጭ አድርጎ ለቀሪው የዓለም ህዝብ የተሳሳተ እምነትን የሚያስጨብጥ በመሆኑ ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ሊወገድ ይገባል፡፡ በፍጹም ሊሆን አይችለም!

ያ ዓይነት አስተሳሰብ -ኃይማኖት አላልኩም ሆኖም ግን አስተሳሰብ፣ የዚያ ዓይነት ቅኝት እና ለዘመናት ቅዱስ አድርገን ከያዝናቸው ሀሳቦች ለመላቀቅ አስቸጋሪ ነገር ይሆንብናል፣ እንደዚሁም ከቀሪው የዓለም ህዝብ ጋር የሚያጋጨን ሊመስለን ይችላል፡፡ የዓለምን ህዝብ በሙሉ ከጥላቻ ውስጥ የሚዘፍቀው ይሆናል!

ወደ 1.6 ቢሊዮን የሚሆኑት የእስልምና እምነት ተከታዮች ቀሪዎቹን በዓለም ላይ የሚኖሩትን ማለትም 7 ቢሊዮን የሚሆኑትን ህዝቦች መግደል እና እነርሱ ብቻ በዚህች መሬት ላይ መኖር ይችላሉን? ፍጹም፣ ይህ ሊሆን የማይችል ጉዳይ ነው!…

የኃይማኖት አብዮት ማካሄድ ይኖርብናል እያልኩ ደግሜ ደጋግሜ እናገራለሁ፡፡ እናንት ኢማሞች በአላህ ፊት ተጠያቂዎች ናችሁ፡፡ መላው የዓለም ህዝብ እንደገና እደግመዋለሁ የዓለም ህዝብ ሁሉ የእናንተን ቀጣይ እርምጃ በመጠባበቅ ላይ ነው…ምክንያቱም ኡማ እየተቀደደ እና እየወደመ ነው፣ እየጠፋ ነው – በእኛው እጆች እየጠፋ ነው፡፡

በአሁኑ ጊዘ ግብጽ በርካታ በሆኑ የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊ፣ የፖለቲካ እና የደህንነት ችግሮች ታጋፍጠውባት ትገኛለች፡፡ እንደ ወታደር ባለሙያነት ኤልሲሲ የግብጽን ህዝብ ስር የሰደዱ መዋቅራዊ ችግሮች የመፍታት ችሎታ ያላቸው ስለመሆኑ ሊነሱ የሚችሉ ጥያቄዎች አሉ፡፡ ለምሳሌ እ.ኤ.አ በ2013 የተደረገ ጥናት እንዲህ የሚል ጥቆማ ይሰጣል፣ “ለምግብ ሸቀጦች የሚደረገው ድጎማ ነዳጅ እና ምግብን ጨምሮ የግብጽን ህዝብ ጠቅላላ ወጭ አንድ ሶስተኛውን ያህል ይይዛል፡፡“ የድጎማ ፕሮግራሞችን ለማሻሻል የኤልሲሲ ታላቅ ፈተና ሆነው ይቀጥላሉ፣ እናም እነዚህን ችግሮች እንዴት መፍታት እንደሚችሉ ኤልሲሲ መፍትሄው ገና በእጃቸው አልገባላቸውም፡፡

ኤልሲሲ በወንድማማቾች ህብረት/Muslim Brothehood፣ በነጻው ፕረስ እና በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ላይ በሚወስዷቸው እርምጃዎች አማካይነት ጭቆናዎች እያደረሱ እንደሆኑ ተደርገው ትችት ይቀርብባቸዋል፡፡ በሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች ደግሞ በሲናይ በረሀ በሽብር ፈጣሪ ህዋሶች ላይ በሚወስዷቸው እርምጃዎች እና ምሽጎቻቸውን በማፍረስ እና ለአሸባሪዎች መግቢያ እና መውጫ የሚሆኑ መንገዶችን በመዝጋት መፈናፈኛ በማሳጣታቸው ከፍተኛ ሙገሳ እና አድናቆትን ተችረዋል፡፡

የኤልሲሲ አመራር በጣት የሚቆጠሩ በቡድኑ ዙሪያ የተሰባሰቡ ታማኝነት ያላቸውን እና በእጅ ብድግ በማድረግ የተመረጡ ጥቂት ባለስልጣኖችን ያካተተ ነው፡፡ ወጣት ባለስልጣኖች በአመራር መዋቅሩ ውስጥ እንዲካተቱ በማድረግ ለእርሳቸው ታዋቂነት እና ድጋፍን እንዲሁም ታማኝነትን አትርፎላቸዋል፡፡ ቀደም ሲል ይቀናቀኑ የነበሩ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች እና የህግ አስፈጻሚ ኤጀንሲዎች እርቅን እና ህብረትን ፈጥረው ከወታደሩ ጋር በጋራ እንዲሰሩ ምቹ ሁኔታን ፈጥረዋል፡፡

እ.ኤ.አ ጥር 2014 ኤልሲሲ ለከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖች እና የፖሊስ ባለስልጣኖች እንዲህ የሚል ንግግር አድርገዋል፣ “ፖሊስ እና ወታደራዊ ኃይሉ የግብጽን ደህንነት እና መረጋጋት የሚያመጡ እውነተኛ ዋስትና ናቸው… በአሁኑ ጊዜ ያሉት ችግሮች ያለምንም ጥርጥር ግዙፍ ናቸው…እናም ሀገራችንን ለመጠበቅ እኛ [የጦር ኃይሉ] ከእናንተ [ከፖሊስ ሰራዊቱ] ቀጥለን በጽናት በመቆም ተሰልፈን እንገኛለን… በርካታ አደጋዎች የተደቀኑብን ቢሆንም በአንድነት ሆነን ልንወጣቸው እንችላለን፡፡“

ኤልሲሲ በመካከለኛው ምስራቅ ላይ ውስብስብ የሆኑ የዴሞክራሲያዊነት መርሆ ትንታኔ ጉዳዮችን ያቀርባሉ፡፡ ባለ17 ገጽ የመመረቂያ ጽሁፋቸውን በማዘጋጀት እ.ኤ.አ በ2006 ከዩኤስ አርሚ ዋር ኮሌጅ/U.S Army War College እ.ኤ.አ በ2006 ትምህርታቸውን ሲያጠናቅቁ እንዲህ የሚሉ ጥቂት ጥያቄዎችን አንስተው ነበር፣ “ወደ ዴሞክራሲ የሚደረገው ሽግግር በዩኤስ አሜሪካ ፍላጎት ላይ የተንጠለጠለ ነው ወይስ ደግሞ በመካከለኛው ምስራቅ ሀገሮች ፍላጎት ላይ የተመሰረተ ነው?“ ኤልሲሲ እንዲህ በማለትም አስጠንቅቀው ነበር፣ “ዩናይትድ ሰቴትስ አሜሪካ የእራሷን ፍላጎት መሰረት ባደረገ መልኩ የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ እንዲካሄድ ለማድረግ ጥረት ማድረግ እስከጀመረች እና ከሌሎች ሀገሮች ፍላጎት ውጭ እንዲጫን የምታደርግ መሆኗ እስከቀጠለ ድረስ እውነተኛ የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ እውን ሊሆን አይችልም፡፡ “

ኤልሲሲ በጦር ኃይሉ እና በመካከለኛው የህብረተሰብ ክፍል ዘንድ ከፍተኛ የሆነ ድጋፍ አላቸው፡፡ የቢሮክራሲው የቴክኒክ ባለሙያዎች ማለትም የህግ ባለሙያዎች፣ ወታደራዊ አዛዦች፣ መሀንዲሶች፣ ኢኮኖሚስቶች፣ ዳኞች እና ግብጽን በገጠሟት አንገብጋቢ ጉዳዮች ላይ አጠንክረው የሚሰሩ ሌሎች ባለሙያዎች በቡድናቸው ውስጥ ተካትተው ይገኛሉ፡፡ አንዳንዶቹ ሰዎች እነዚህ የቴክኒክ ባለሙያዎች ምንም ዓይነት የፖለቲካ አመለካከት የላቸውም ይላሉ፡፡ ሌሎች ሰዎች ደግሞ የአዙሪት ምኋሩን ቀጥ አድርገው ለመያዝ በጣም ወሳኝ ኃይሎች ናቸው ይሏቸዋል፡፡ ሆኖም ግን የኤልሲሲ ትልቁ ፈተና ከዝቀተኛው እና ከብዙሀኑ ደኃ ህዝብ ድጋፍ ከማሰባሰቡ ላይ ነው፡፡ የሆነው ሆኖ ኤልሲሲ እና የእርሳቸው የቴክኒክ ባለሙያዎች ስብስብ ቡድን ቀደም ሲል የአረብን የጸደይ አብዮት/Arab Spring ያመጡትን እና ወደፊትም ሌላ አመጽ ሊያስነሱ የሚችሉትን ዋና ዋና ችግሮች ፈልገው ማግኘት እና አስቀድመው መፍትሄ መስጠት ይጠበቅባቸዋል፡፡

ኤልሲሲ ከገልፍ ባህረ ሰላጤ ሀገሮች መንግስታት ጋር መልካም የሆነ ግንኙነት መስርተዋል፡፡ ሳውዲ አረቢያ፣ ኩዌት እና የተባበሩት የአብ ኤምሬትስ እያንዳንዳቸው የ4 ቢሊዮን ዶላር ኢንቨስትመንት እና ብድር ለግብጽ ለመስጠት ቃል ገብተዋል፡፡ ዩናይትድ ስቴትስም እ.ኤ.አ በ2013 የሙርሲ መንግስት ከተወገደ በኋላ ለግብጽ ወታደራዊ እና የኢኮኖሚ ልማት እርዳታን ታሳቢ በማድረግ እያገዘች ትገኛለች፡፡ ግብጽ ከዩኤስ አሜሪካ ወታደራዊ እርዳታ በመቀበል ከእስራኤል በመቀጠል ሁለተኛዋ ሀገር ሆናለች፡፡

በእርግጥ የዓባይ ወንዝ ግድብ ግንባታ ጉዳይ አለ፡፡ ለበርካታ ዓመታት “ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ” እየተባለ በሚጠራው ግድብ ግንባታ ምክንያት የሚያስፈልገኝን የውኃ መጠን ድርሻዬን ይቀንስብኛል ከሚል ስጋት ተቃውሞዋን ስትገልጽ ቆይታለች፡፡

እ.ኤ.አ ሰኔ 2013 ኤልሲሲ የተኳቸው መሐመድ ሙርሲ ለብዙሀን መገናኛ ቀርበው እንዲህ የሚል ንግግር አሰምተው ነበር፣ “የግብጻውያን ህይወት በጽኑ የተቆራኘው ከዓባይ ወንዝ ጋር ነው… የዓባይ ወንዝ ውኃ በአንዲት ጠብታ የሚቀንስ ከሆነ በሌላ በኩል ደግሞ ደማችንም የዚያኑ ያህል ይቀንሳል፡፡“ በዚህ ጉዳይ ላይ አሁን በቅርቡ ባሳለፍነው ወር ሰፊ የሆነ ትችት አቅርቤ ነበር፡፡

በዚህ ባለፈው መጋቢት ወር ኢትዮጵያ፣ ግብጽ እና ሱዳን በዓባይ ግድብ ግንባታ ጉዳይ ላይ ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡ በዚያን ጊዜ የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በዓባይ ወንዝ ጉዳይ ላይ ምንም ዓይነት ወታደራዊ ፍጥጫ እና ትንኮሳ እንዳይኖር ግልጽ በማድረግ እንዲህ የሚል መልዕክት አስተላልፈው ነበር፣ “የአፍሪካን ሀገሮች በመመስረት እረገድ ግብጽ የመስራችነት ሚና ተጫውታለች፣ በምንም ዓይነት መልኩ ጠብ አጫሪ ልትሆን አትችልም፣ በማንኛውም ጊዜ ቢሆን ትንኮሳ የምታካሂድ ሀገር ልትሆን አትችልም፡፡“

እንዲህ የሚለው አነጋገር ለእኔ ትልቅ ትርጉም ይሰጠኛል፣ “ትልቅ ዱላ ያዝ እና ድምጽህን ዝቅ በማድረግ በለሆሳስ ተናገር፡፡“ እንዲህ በሚለው የሰን ትዙ ምክር ላይ ከልብ አምናለሁ፣ “የያዝካቸው ዕቅዶች የፈለገውን ያህል ጨለማ ይሁኑ፣ እናም እንደጨለማ የማይነቀነቁ ይሁኑ፣ እናም በምትንቀሳቀስበት ጊዜ እንደ መብረቅ ነጎድጓድ ተንኮታኩተው ይወድቃሉ፡፡“ የጫካ ጀኔራሎች እውነተኛውን ጽናት ላለመለካት ብልህነት አላቸው ወይም ደግሞ እውነተኛዎቹ ጀነራሎች መፍትሄ ለመስጠት አቅም አላቸው፡፡

ኤልሲሲ የታገቱ ኢትዮጵያውያንን ከሊቢያ ለማስወጣት እና ከሞት ለማዳን የመብረቅ ነጎድጓድ ዓይነት ምት ነው የመቱት፡፡ በመብረቃዊ ፍጥነት እና እርምጃ የኢትዮጵያ ወጣቶችን አንገት ከመቀላት ለታደገው ህዝብ ለኤልሲሲ እና ለግብጽ ህዝብ በሙሉ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ባለዕዳ በመሆኑ ታላቅ ምስጋና ሊያቀርብ ይገባል፡፡

ሸክስፒር እንዲህ በማለት ጽፈው ነበር፣ “ድርጊት ከምንም በላይ ገላጭ ነገር ነው፡፡“ በሊቢያ አንገታቸውን እንዲቀሉ በዕቅድ ዒላማ ተደርገው ተይዘው የነበሩ የኢትዮጵያውያን ወገኖቻችንን ህይወት ለመታደግ ኤልሲሲ ግልጽ የሆነ ድርጊት እና ፍቅርን አሳይተዋል፡፡

የኤልሲሲን ድፍረት የተሞላበት እርምጃ፣ ጠንካራ ተስፋ እና የወገኖቻችንን አንገት ከመቀላት በመታደጋቸው የማድነቁ እና የማመስገኑ ጉዳይ በአሁኑ ጊዜ ለኢትዮጵያውያን የተተወ ነው፡፡ በኢትዮጵያ በስልጣን ወንበር ላይ ከህዝብ ፈቃድ ውጭ በኃይል እንደ መዥገር ተጣብቀው የሚገኙት ወሮበሎች እና ዘራፊዎች ለመፈጸም የተጠየፉትን እና የሚጠሉትን ነገር ፕሬዚዳንት ኤልሲሲ ግን በተግባር አሳይተዋል፡፡ ቪቫ ኤልሲሲ!

ፕሬዚዳንት ኤልሲሲ እና የግብጽ ህዝብ በሙሉ እጅግ በጣም አመሰግናችኋለሁ!!! በተሳካ ሁኔታ እና አንጸባራቂ በሆነ መልኩ ለፈጸማችሁት አኩሪ ተግባር ከልብ አመሰግናለሁ!

በዋሽንግተን፣ በሎንዶን፣ በፓሪስ… እና በሌሎችም የግብጽ ኤምባሲ ቅጥር ግቢዎች በመገኘት ላደረጋችሁልን ውለታ አላህ፣ እግዚአብሄር ይስጥልን ብሎ ምስጋና ማቅረብ የሚያስደንቅ ነገር ሊሆን አይችልምን?!!!

የልብ ጓደኛ ማለት ጭንቅ በገጠመ ጊዘ በተግባር የሚገኝ እና የሚፈተን ነው!

ሁሉን ነገር ለማድረግ የማይሳነው አምላክ የወገኖቻችንን አንገት በግፍ ከመቀላት የታደግህልን በመሆኑ ምስጋና፣ ክብር እና ሞገስ ይገባሀል!

ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!

ግንቦት 16 ቀን 2007 ዓ.ም