“ለኢትዮጵያ አንድነት በጽናት እንቆማለን”፣

(የፀሐፊው ማስታወሻ — ይህን ፅሁፍ በነጻነት ለሀገሬ ስም ለአማርኛ አንባቢዎቼ  አቀርባለሁ። የነፃነት ለሀገሬ ትርጉሞች የረቀቁና የተጣሩ ናቸው። የነፃነት ለሀገሬን ድጋፍ በማግኘቴ ታላቅ ደስታና ክብር ይሰማኛል። ነፃነት ለሀገሬ ያልተዘመረለት/ያልተዘመረላቸው የኢትዮጵያ ጀግና/ጀግኖች ናቸው። ከፍተኛ ክብርና አድናቆቴን ለነፃነት ለሀገሬ አቀርባለሁ/አቀርብላቸዋለሁ  !!! ትግሉ ይቀጥላል ለነፃነት ለሀገሬ!!!) 

ከፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማርያም

ትርጉም በነጻነት ለሀገሬ

የአፍሪካ አሜሪካዊ ደራሲ፣ ገጣሚ፣ የዳንስ ተወዛዋዥ፣ ተዋናይ እንዲሁም የሙዚቃ አቀንቃኝ የሆነችው ማያ አንጌሉ እንዲህ በማለት አውጃ ነበር፣ “የእኛን ጀግኖች እና ጀግኒቶች ማስታወስ እና መዘከር እንዴት ያለ ጠቃሚ ነገር ነው!“እኛም እነዚህንም የሀገር ጀግኖች እና ጀግኒቶች ተራ በተራ እያነሳን እናክብራቸው፣ እናወድሳቸው ምክንያቱም በአሁኑ ጊዜ ሀገሪቱ ከገባችበት ማጥ ውስጥ እንድትወጣ ለማድረግ እና ነጻነት እና ዴሞክራሲ በሀገራችን እንዲሰፍን እራሳቸውን ለመስዋዕትነት ያቀረቡ የሀገር ዕንቁዎች ናቸውና፡፡

1ኛ) እስክንድር ነጋ፡ የሀገሪቱ መናገሻ ከተማ ከሆነችው ከመሀል አዲስ አበባ በስተደቡብ በኩል ወጣ ብሎ በጥቂት ኪሎ ሜትሮች ርቀት ላይ ከሚገኘው በአስከፊናቱ ከሚታወቀው ከመለስ ዜናዊ የቃሊቲ የማጎሪያ እስር ቤት ታስሮ በመሰቃየት ላይ ከሚገኘው ከታዋቂው እና የኢትዮጵያ የፕሬስ ነጻነት ቀንዲል ከሆነው ከእስክንድር ነጋ እጅ በድብቅ በወጣ ደብዳቤው “በጽናት እቆማለሁ” በማለት ጽፏል፡፡

እስክንድር “በጽናት እቆማለሁ!” ሲል ዝም ብሎ ስለእራሱ ለመጻፍ ፈልጎ አይደለም፡፡ ሆኖም ግን በማጎሪያው እስር ቤት በመሰቃየት ላይ ስላሉት የስራ ባልደረባ ጋዜጠኛ ጓደኞቹ፣ ጦማሪያን፣ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች እና ስለሌሎች የፖለቲካ እስረኞች ዓላማም ጭምር ነው፡፡ ከዚህም በላይ አንድ የህሊና እስረኛ ወይም ደግሞ አንድ የፖለቲካ እስረኛ ብቻውን በጽናት ሊቆም አይችልም፡፡ ብቻውንም በጽናት ቆሞ ብቻውን ውጤት ሊያመጣ እይችልም፡፡  እንደዚሁም ደግሞ ኢትዮጵያ እራሱን ህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ (ህወሀት) እያለ ከሚጠራው የአምባገነን ወሮበላ ስብስብ መዳፍ ስር ወድቃ በመማቀቅ ላይ እያለች ለዚህ እኩይ ምግባር አራማጅ ዘረኛ ድርጅት የአደባባይ እስረኛ ምርኮኛ ሆኖ በጸጥታ ስለሚገኘው ከ90 ሚሊዮን በላይ ለሆነው ኢትዮጵያዊ/ያት ወገኑ ሁሉ መልዕክት ለማስተላለፍ አስቦ የጻፈው መሆኑን በድፍረት መናገር እችላለሁ፡፡ ኢትዮጵያ ከወያኔ አምባገነን የወሮበላ ስብስብ ነጻ ለመውጣት እና እውነተኛ የመድብለ ፓርቲ ዴሞክራሲ ለመገንባት በጽናት ትቆማለች፣ እናም ታሸንፋለች!

እ.ኤ.አ በ2014 የተጠናቀቀውን አሮጌ ዓመት ምክንያት በማድረግ የእኔን ጀግና እስክንድር ነጋን እና የእኔን ጀግኒት ርዕዮት ዓለሙን እንደዚሁም በእነርሱም ስም ሁሉንም የፕሬስ ነጻነት የህሊና እስረኛ ጀግኖች እና ጀግኒቶች ኢትዮጵያውያን/ት የህሊና እና የፖለቲካ እስረኞች፣ ለምንም ለማንም ለድርድር ለማይቀርበው ነጻነት ምርኮኛ ለሆኑ ህዝቦች፣ ለነጻ እና ፍትሀዊ ምርጫ ለሚታገሉ፣ ለመልካም አስተዳደር እና ለሰብአዊ መብት መከበር ለሚታገሉ ወገኖች ሁሉ ደወል በመደወል ድምጼን ከፍ አድርጌ በመናገር አወድሳቸዋለሁ፡፡ እነርሱን በማወደስ በኩራት እንዲህ እላለሁ፣ “እንደ ፖለቲካ እስረኛነታችሁ በጽናት ቆማችኋል! እኛም በጽናት ቆመናል! ኢትዮጵያ በአምላክ ቸርነት እንደ አንድ ሀገር ብሄር በጽናት ቆማለች፡፡ የእኛን ነጻነት በመግፈፍ በባርነት እና በሁለተኛ ዜጋነት በማስቀመጥ ሲበዘብዙን እና ሲመዘብሩን ለመቆየት ዕቅድ አውጥተው የቆሙት ሆድ አምላኩ ፍጡሮች ጽናት እስከሚሟሽሽ እና ደብዛው እስከሚጠፋ ድረስ በጽናት እንቆማለን፡፡ ድል አድራጊነት ለእውነት በጽናት ለቆሙት ብቻ የተሰጠ ጸጋ ነው!“

ሸክስፒር እንዲህ በማለት ጽፈው ነበር፣ “ጥቂቶች ታላቅ ሆነው ተወልደዋል፣ ጥቂቶች ታላቅነትን በሂደት ይጎናጸፋሉ፣ ጥቂቶች ደግሞ ሁኔታዎችና ፈተና ታላቅነትን ያጎናፅፋቸዋል፡፡“ እንደዚሁም በተመሳሳይ መልኩ በእኛ ጀግኖች እና ጀግኒቶች ላይ እምነትን መጣል ይቻላል የሚል እምነት አለኝ፡፡ እንደ እስክንድር እና ርዕዮት ያሉ ዜጎች (ሁሉንም በኢትዮጵያ በማጎሪያው እስር ቤት በመማቀቅ ላይ የሚገኙትን ሌሎችን የህሊና እስረኞች ይወክላሉ) ጀግኖች እና ጀግኒቶች ናቸው ምክንያቱም በሀገሪቱ ላይ ፈታኝ የሆነ አደገኛ ሁኔታ በተፈጠረበት ጊዜ ጀግንነት በእነርሱ ላይ እምነቱን ጥሏልና፡፡ የእነርሱን የህይወት ዕጣ ፈንታ ፈልገው ባገኙበት ጊዜ እንደ አብዛኞቻችን  ፊት ለፊት መጋፈጥን እርም ብለው አላስወገዱም ወይም ደግሞ እንደ ግመል ሽንት ወደኋላ አልተስፈነጠሩም፣ እንደዚሁም እንደ ተልባ ስፍር አልተንሸራተቱም፡፡ እነዚህ የጀግንነት ተምሳሌቶች የአሽከርነት ወይም የለማኝነት ባህሪን አልተላበሱም፡፡ እነዚህ የጀግንነት ቀንዲሎች  ሌሎች ለከርስ ብቻ የቆሙት ሆዳሞች እንደሚያደርጉት ሁሉ ስብዕናቸውን በቤሳ ሳንቲም አልለወጡም፣ እንደሌሎች ቆርጦ ቀጥሎች አይደሉም፣ በጽናት ከቆሙለት ዓላማ አንዲት ጋት ወደኋላ አላፈገፈጉም፡፡ ላመኑበት ዓላማ በጽናት ቆመዋል፣ ይቆማሉም፡፡ በወሮበላ የጫካ አገዛዝ ነጻነት በሌለው አጥር የሌለው አስርቤት ውስጥ እየሰገዱ እና እየተንገዳወሉ ከመኖር ይልቅ ያመኑበትን ዓላማ በማራመድ ነጻነትን ይዞ በእስር ቤት መኖርን መርጠዋል፡፡

እስክንድር እና ርዕዮት በጉልበታቸው የሚንበረከኩ ቢሆን ኖሮ፣ ራሳቸውን ዝቅ አድርገው በማጎንበስ ቢለምኑ ኖሮ፣ ወንጀለኛ ተብለው የተፈበረኩባቸውን የሸፍጥ መሰሪ የውንጀላ ክሶች አምነው ይቅርታ ቢጠይቁ ኖሮ፣ የአሳሪዎቻቸውን እግር ቢልሱ እና ይቅርታ እንዲደረግላቸው ቢለምኑ ኖሮ ከማጎሪያው እስር ቤት ይወጡ ነበር፡፡ ከእነዚህ የዓላማ ጽናት ተምሳሌቶች ቀደም ብሎ አሁን በህይወት በሌሉት መለስ ዜናዊ እና ደቀመዝሙሮቻቸው አማካይነት ይቅርታ እየተደረገላቸው እንደወጡት በርካታ ወገኖች ሁሉ ያለምንም ችግር ከማጎሪያው እስር ቤት ይወጡ ነበር፡፡ በሸፍጥ የፍብረካ ወንጀል ክስ አሸባሪ በሚል የገዥው ወሮበላ ስብስብ የማደናገሪያ ታፔላ ተለጥፎባቸው በዝንጀሮው የይስሙላ ፍርድ ቤት 11 ዓመታት በእስራት እንዲቀጡ ተበይኖባቸው የነበሩት ጆሀን ፔርሰን እና ማርቲን ሽብዬ በተመሳሳይ መልኩ ይቅርታ ጠይቀው እንዲወጡ ነበር የተፈለገው፡፡

መለስ በጥቃት ሰለባዎቻቸው ላይ የውሸት የፍብረካ ውንጀላ የጥፋተኝነት ክስ እንዲመሰረት ካደረገ በኋላ በህዝብ ፊት በአደባባይ አምነው ይቅርታ ጠይቀው እንዲወጡ ማድረግ የመጨረሻው የውርደት መቅጫ ወይም ማሸማቀቂያ መሳሪያው ነበር፡፡ ይህንን እኩይ ድርጊት እ.ኤ.አ በ2005 የተካሄደውን ሀገር አቀፍ ምርጫ ተከትሎ ተከስቶ በነበረው ውዝግብ ምክንያት ሰብስበው በማጎሪያው እስር ቤት አጉረዋቸው በነበሩት በደርዘን በሚቆጠሩ የተቃዋሚ የፖለቲካ መሪዎች ላይ ተግብረውታል፡፡ በኢትዮጵያ ታሪክ የመጀመሪያ በሆነችው ሴት የፖለቲካ ፓርቲ መሪ በነበረችው በብርቱካን ሚደቅሳ ላይ ሁለት ጊዜ ተግብረውታል፡፡ አቶ መለስ በማጎሪያው እስር ቤቱ እየተንገዳወሉ እና እየተልፈሰፈሱ ምንም ዓይነት ወንጀል ያልሰሩትን ንጹሀን ኢትዮጵያውያን/ት እንደ ሀቀኛ ሰው ለምነው በማታለል እያግባቡ እና እያሳመኑ ለአቶ መለስ እብሪተኛ ዓላማ ይቅርታን እንዲጠይቁ እና ከማጎሪያው እስር ቤት በይቅርታ እንዲወጡ የሚያደርጉ ካድሬዎች ነበረው፡፡ አቶ መለስ የራሱን ብልሹ አመራር እና ፖሊሲን የሚቃወሙትን ንጹሀን ዜጎችን ሁሉ በህዝብ ፊት በአደባባይ ማዋረድ ትልቅ እርካታን ይሰጠው ነበር፣ በንጹሀን ዜጎች ላይ የሚፈጽሙት ይህ እኩይ ድርጊት የእርሳቸውን በሰዎች ስቃይ እና ውርደት ላይ ጮቤ የሚረግጠውን የክፋት ነብሱን በደስታ ባህር ውስጥ እንዲዋኝ ያደርገዋል፡፡ ይቅርታ ጠይቀው የውርደት ካባን ተከናንበው እንዲወጡ የሚያደርገው የገዥው አካል ዲያብሎሳዊ ባህሪ አሁንም ቢሆን ለእስክንድር እና ለርዕዮት ክፍት ሆኖ እየጠበቀ ነው፡፡ ሆኖም ግን እነዚህ የጽናት ተምሳሌቶች ይጸየፉታል እንጅ አይፈልጉትም፡፡ እነዚህ የጽናት ባለሟሎች ባልሰሩት ጥፋት ላይ የሚቀርብላቸውን የይቅርታ ጥያቄ መሰረተ ቢስ በማለት እንዲህ የሚል መልዕከትን ያስተላልፋሉ፣ “ለአንድ ነጻ ለሆነ ወንድ ወይም ሴት ይቅርታ ልትሰጡ አትችሉም፣ የሞራል ስብዕናውም በፍጹም የላችሁም…የእናንተን ይቅርታ ተሸክማችሁ የትም መሄድ ትችላላችሁ፣ የእናንተ በቅጥፈት እና በሸፍጥ የተሞላ ተራ እና የወረደ የወሮበሎች ይቅርታ በአፍንጫው ይውጣ…!“

በአደጋ ምክንያት አካላቸውን ማንቀሳቀስ የማይችሉት እና ሽባ የሆኑት የሆሊውድ ፊልም ዋና አዘጋጅ የነበሩት ክርስቶፈር ሪቭ በአንድ ወቅት እንዲህ ብለው ነበር፣ “ጀግና በርካታ ውጥንቅጥ መሰናክሎች በበዙበት ወቅት እራሱን ፈልጎ የሚያገኝ እና ለፍትሀዊ ዓላማው በጽናት የሚቆም  እና ለተግባራዊነቱ ያለማሰለስ የሚታገል ተራ ግለሰብ ነው፡፡“ እስክንድር፣ ርዕዮት እና ሌሎችም ዜጎች መሰናክሎች እና ችግሮች በበዙበት ወቅት እራሳቸውን ፈልገው ያገኙ እና ለፍትሀዊ ዓላማ በጽናት በመቆም ለስኬታማነታቸው በቆራጥነት ያለማወላወል የሚታገሉ ተራ ዜጎች ናቸው፡፡ ለዚህም ነው እስክንድር፣ ርዕዮት እና ሌሎች የኢትዮጵያ የፖለቲካ እና የህሊና እስረኞች ሁሉ ለእኔ ጀግኖች እና ጀግኒቶች የሆኑት፡፡ ሁሉም ለዓላማቸው እና ለዓላማዎቻቸው ስኬታማነት ብቻ በጽናት የሚታገሉ ናቸው፡፡

ድፍረት ጀግናነት እና ጀግኒነት የተዋቀሩበት የሞራል ብቃት ውጤት ነው፡፡ ይህንን ጉዳይ በማስመልከት ሮበርት ኤፍ ኬኔዲ በአንድ ወቅት እንዲህ ብለው ነበር፣ “የሞራል ድፍረት… በጣም ስቃይ የበዛባትን ወደ መልካም ነገር ለመለወጥ በለውጥ ፈላጊ ሰዎች አማካይነት የሚደረግ አንድ አስፈላጊ እና ዋና የጥራት መለኪያ ነገር ነው፡፡“ በእያንዳንዱ ጊዜ አንድ ሰው ለዓላማ ሲቆም፣ ወይም የሌሎችን ህይወት ለማሻሻል በጽናት ሲታገል ወይም ደግሞ ኢፍትሀዊነትን ሲዋጋ በተለያዩ በሚሊዮኖች በሚቆጠሩ ኃይል እና ድፍረት ማዕከል በመሆን የጭቆና እና የብዝበዛ ስርዓትን መንግሎ በመጣል ለተስፋ መለምለም የመሰረት ድንጋይ የሚሆን ማዕበላዊ መልዕክት ሊያስተላልፍ/ልታስተላልፍ ይችላል/ትችላለች፡፡

እስክንድር ነጋ፣ ርዕዮት ዓለሙ እና ሌሎችም ጀግኖች እና ጀግኒቶች የፖለቲካ እስረኞች እውነተኛ የሞራል ድፍረት አላቸው፡፡ እነዚህ የጽናት ቀንዲሎች ለፕሬስ ነጻነት እና ሀሳብን በነጻ የመግለጽ መብት፣ ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ እና ለሰብአዊ መበቶች መከበር በጽናት ቆመዋል፡፡ ለህግ የበላይነት መርሆዎች መከበር በጽናት ቆመዋል፡፡ ከህወሀት የወሮበላ ስብስብ ቡድን በተቃራኒው ቆመዋል፡፡ እነዚህ የነጻነት ቀንዲሎች 90 ሚሊዮን ለሚሆኑት ኢትዮጵያውያን/ት ወገኖቻቸው ተስፋን የሚያለመልም ሂደትን በመተግበር በጽናት ቆመዋል፡፡

አሮጌውን ዓመት 2014ን ደወል በመደወል ስንሸኝ እና አዲሱን ዓመት 2015ን እየተቀበልን ባለንበት በአሁኑ ወቅት ሁሉም አንባቢዎቼ እስክንድር ነጋን፣ ርዕዮት ዓለሙን፣ ወብሸት ታዬን፣ አንዷለም አራጌን፣ በቀለ ገርባን፣ አቡባከር አህመድን፣ የዞን 9 ጦማሪያንን ማለትም አጥናፍ ብርሀኔን፣ ዘላለም ክብረትን፣ በፈቃዱ ኃይሉን፣ አቤል ዋቤላን፣ ማህሌት ፋንታሁንን፣ ናትናኤል ፈለቀን፣ አስማማው ኃይለጊዮርጊስን፣ ተስፋለም ወልደየስን እና ኤዶም ካሳዬን ጨምሮ በማክበር እና በማመስገኑ እረገድ ለጀግንነታቸው እውቅና እንድንሰጥ እና እንድንዘክራቸው እንድትቀላቀሉኝ በትህትና እጠይቃለሁ፡፡ እነዚህ ጀግኖች እና ጀግኒቶች በአስር ሺዎች ለሚቆጠሩ ስም የለሾች፣ የማይታወቁ ትንታጎች፣ ያልተዘመረላቸው እና ያልተሰገደላቸው ጀግኖች እና ጀግኒቶች ለእኩልነት፣ ለፍትህ እና ለክብር ሲባል በዓለም ፍጹም አስቀያሚ በሆኑት በኢትዮጵያ የማጎሪያ እስር ቤቶች በመሰቃዬት ላይ ለሚገኙት ህዝቦች ጥቂት ምሳሌዎች ብቻ ናቸው፡፡ በአስከፊነቱ በሚታወቀው እና ቃሊቲ በመባል በሚጠራው እና በሌሎች በመለስ ዜናዊ የእስረኞች የማጎሪያ ቅርንጫፍ እስር ቤቶች በመላ ኢትዮጵያ በመማቀቅ ላይ ለሚገኙ ጀግኖች እና ጀግኒቶች በሙሉ ታላቅ ክብር እሰጣቸዋለሁ፡፡ ክብር እና ሞገስ ለእነርሱ ይሁኑ!

2ኛ) ርዕዮት ዓለሙ፡ አሁን በህይወት በሌሉት በመለስ ዜናዊ የሸፍጥ ወንጀል ፍብረካ የ14 ዓመታት እስራት የተፈረደባት እና የኢትዮጵያ የፕሬስ ነጻነት ቀንዲል ለሆነችው የ36 ዓመቷ ወጣት ጀግኒት ጋዜጠኛ ርዕዮት ዓለሙ ታላቅ ክብር አለኝ፡፡ ርዕዮት “የኢትዮጵያ እውነት ተናጋሪዋ እስረኛ” በመባል በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅናን አግኝታለች፡፡ ዓለም አቀፍ የጋዜጠኞች ተከራካሪ ኮሚቴ/Committee to Protect Journalists ባቀረበው ዘገባ መሰረት ርዕዮት የታሰረችው የህዳሴው ግድብ እየተባለ ለሚጠራው  የግድብ ግንባታ ገንዘብ ለማሰባሰብ እያደረገ ባለው የተሳሳተ አካሄድ በገዥው የፖለቲካ ፓርቲ ላይ ጠንካራ ትችትን በመሰንዘሯ እና በወቅቱ የሊቢያ መሪ የነበሩት ኮሎኔል ሙአማር ጋዳፊ እና መለስ ዜናዊ አንድ ዓይነት ተመሳስሎ ያላቸው ከአንድ ባህር የተቀዱ አምባገነን መሪዎች ናቸው ብላ እውነትን አፍርጣ በመናገሯ ነበር ብሏል፡፡

3ኛ) ውብሸት ታዬ፡ የህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይን አጠቃላይ በሙስና መዘፈቅ አስመልክቶ በሚያዘጋጀው ጋዜጣ ትችት በማቅረቡ እና የጋዜጠኝነት የተመልካችነት ሙያውን በመስራቱ ብቻ በአምባገነኑ የወሮበላ ስብስብ ገዥ አካል የፍብረካ ወንጀል ክስ ተመስርቶበት የ14 ዓመታት እስራት ተፈርዶበት በማጎሪያው እስር ቤት እየተሰቃዬ ያለውን ጀግና ጋዜጠኛ እና አርታኢ ውብሸት ታዬን ከልብ አከብረዋለሁ፡፡ የውብሸት ታዬ የ5 ዓመት ልጅ የፍትህ እንዲህ የሚሉት ጨዋነት የተሞላባቸው ቃላት በአዕምሮዬ ላይ ሁልጊዜ ያቃጭላሉ፣ “በማድግበት ጊዜ እንደ አባቴ ሁሉ እኔም ወደ እስር ቤት ነው የምሄደው ማለት ነው?“

4ኛ) አንዷለም አራጌ፡ ወደ ማሪያው እስር ቤት ከመጋዙ በፊት የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ ኮከብ የአመራር አባል የነበረውን አንዷለም አራጌን አከብረዋለሁ፡፡ አንዷለም አራጌ ከአዲሱ የኢትዮጵያ የፖለቲካ መሪዎች፣ ጋዜጠኞች እና የሲቪል ማህበረሰብ ወጣት ዝርያ መካከል የሚመደብ ሲሆን በህዝቡ ዘንድ በስፋት የሚከበር እና ተቀባይነት ያለው የጽናት ተምሳሌት ወጣት የፖለቲካ ፓርቲ የአመራር አባል ነው፡፡ እ.ኤ.አ እስከ ሜይ 2010 መለስ ዜናዊ 99.6 በመቶ የህዝብ ድምጽ በማግኘት ምርጫውን በድል አድራጊነት አሸንፊያለሁ በማለት ባዶ ዲስኩር እስካሰሙበት የይስሙላ ሀገር አቀፍ ምርጫ ድረስ አንዷለም አራጌ ለዴሞክራሲ መገንባት እና ለህግ የበላይነት መከበር በጽናት በመቆም ሲታገል የቆየ ትንታግ ወጣት ነው፡፡ ግልጽ በሆነ ሀሳብ በመሞላት፣ ፍጹም የሆነ ምሁራዊ አንደበትን በመላበስ፣ ሊታመን ቀርቶ ሊታሰብ በማይችል ድፍረት የተሞላበት አካሄድ፣ በአስደማሚ አንደበተ ርትዑ ንግግር፣ እንደጦር በሚወጋ አመክኗዊ አቀራረቡ፣ ጉብዝና የተመላበት አቀራረብ፣ እውነታዎችን ፈልፍሎ በማውጣት እና ለእውነት በጽናት በመቆም የመለስ ዜናዊን የቴሌቪዥን የቅድመ ምርጫ ክርክር ተሰላፊ አሽከሮች በሚያቀርባቸው በእውነት ላይ የተመሰረቱ አመክኗዊ የክርክር ጭብጦች ባዶ መሆናቸውን ያጋለጠ እና መቅኖ ያሳጣ ጀግና የፖለቲካ ሰው መሆኑን በተግባር ያረጋገጠ ወጣት ነው፡፡ በእርግጠኝነት ይኸ ዓይነት ጽናትን የተላበሰ የትግል መስመር በቀጣይነትም ሊያዝ የሚገባው ጉዳይ ነው!

5ኛ) አብርሃ ደስታ፡ ወጣቱን፣ ፍርኃት የለሹን እና ልዩ ተሰጥኦ ያለውን ኢትዮጵያዊ ጦማሪ አብርሀም ደስታን ከልብ አከብራለሁ፡፡ አሁን በቅርቡ እ.ኤ.አ ጁላይ 7/2014 ወደ ማጎሪያው እስር ቤት ከመጋዙ በፊት በእራሱ ማህበራዊ ድረገጽ በለቀቀው ጽሁፍ አብርሃ ህወሀት እራሱ ሀሳብን በነጻ የመግለጽ መብት እንዲኖረው ጠንካራ የሆነ የክርክር ጭብጥ ሲያካሂድ ነበር፡፡ “የህወሀትን ካድሬዎች ጠላት ያለማድረግ ወይም ደግሞ በእኔ ድረገጽ እንዳይጠቀሙ ክልከላ የማላደርግበት ምክንያት የህወሀትን ምሁራዊ ክልከላ እና ኪሳራ ማወቅ ጠቃሚ እንደደሆነ ስለማምንበት ነው“ ብሎ ነበር፡፡ ሰዎች ምን ማለት እንደፈለጉ በማዳመጥ የአንድን ሰው የማሰብ እና ምክንያታዊነት ችሎታ መገምገም እንችላለን፡፡ የሚጽፉትን በማንበብ ማወቅ ይቻላል፡፡ ስለሆነም ካድሬዎቹ እንዲጽፉ እንፍቀድ፡፡ እራሳቸው ማን እና ምን እንደሆኑ እራሳቸውን እንዲገልጹ እንፍቀድ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ምን ለማለት እደፈለጉ የሚጽፉትን እናንብብላቸው፡፡ እነርሱንም በሚገባ እንወቃቸው፡፡ እነርሱን ድል ለማድረግ በመጀመሪያ እነርሱን ደህና አድርገን ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ የእራስህን ጠላት ማወቅ ጠቃሚነቱ የጎላ ነው፡፡ ለዚህም ነው ይህንን ድርጊት ማድረግ ያለብን!”

6ኛ) የዞን 9 ጦማሪያን፡ የዞን 9 ወጣት ጀግኖች እና ጀግኒቶች ጦማሪያንን አከብራቸዋለሁ፣ አወድሳቸዋለሁ፡፡ እነዚህ ወጣት ኢትዮጵያውያን እና ኢትዮጵያውያት በኮምፒውተር የመክፈቻ ቁልፎች በመጠቀም እና ለነጻነት ያላቸውን ቀናኢነት በግልጽ በማንጸባረቃቸው እራሱን ህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ (ህወሀት) እያለ በሚጠራው የአሸባሪ የጨለማ ቡድን ስብስብ  ልብ ውስጥ ሽብር ለቀቁበት፡፡ ይህንን ጉዳይ በማስመልከት ሂዩማን ራይትስ ዎች የተባለው ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅት ወጣት ጦማሪያኑ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በአስቸኳ ከእስር እንዲለቀቁ በማሳሰብ እንዲህ የሚል ዘገባ አውጥቷል፣ “ስራቸውን በአግባቡ የሚሰሩትን ጦማሪያን እና ጋዜጠኞችን ለማጥቃት በሚል እኩይ ምግባር የጸረ ሽብር ህግ የሚባል የማደናገሪያ ህግ አዋጅ አድርጎ በማውጣት እና እራሳቸውን በዚያ ውስጥ በመወሸቅ በንጹሀን ዜጎች ላይ እያደረሱት ባለው ጥቃት በህገ መንግስቱ እና ሀሳብን በነጻ የመግለጽ ዓለም አቀፋዊ መብት ላይ የተደረገ ዘለፋ ነው፡፡ “አጥናፍ ብርሀኔን፣ ዘላለም ክብረትን፣ በፈቃዱ ኃይሉን፣ አቤል ዋቤላን፣ ማህሌት ፋንታሁንን፣ ናትናኤል ፈለቀን፣ አስማማው ኃይለጊዮርጊስን፣ ተስፋዓለም ወልደየስን እና ኤዶም ካሳዬን ምርጥ የኢትዮጵያ ወጣት የነጻነት ታጋይ ቀንዲሎች በመሆናቸው አከብራቸዋለሁ፣ አወድሳቸዋለሁ፡፡

7ኛ) በቀለ ገርባ፣ አቡባከር አህመድ እና ሌሎች የነጻነት ታጋዮች፡ ስለእምነት ነጻነት፣ በሰላማዊ  መንገድ ስለመሰብሰብ መደራጀት እንዲሁም ሀሳብን በነጻ ስለመግለጽ መብት በመናገራቸው እና በመጠየቃቸው ብቻ ወንጀል እንደሰሩ ተደርጎ እራሱን ህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ (ህወሀት) እያለ በሚጠራው አምባገነን የወሮበላ ስብስብ የጭቃ ጅራፍ እየተገረፉ እና እየተለበለቡ በመሰቃዬት ላይ የሚገኙትን በቀለ ገርባ፣ አቡባከር አህመድን እና ሌሎችንም ለነጻነት የሚታገሉ ትንታግ ኢትዮጵያውያን/ት ጀግኖች እና ጀግኒቶች ሁሉ ከልብ አከብራቸዋለሁ፣ አወድሳቸዋለሁ፡፡

በቀለ ገርባ የኦሮሞ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲ ንቅናቄ/Oromo Federalist Democratic Movement እየተባለ የሚጠራው የፖለቲካ ድርጅት ምክትል ሊቀመንበር እና በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የእንግሊዝኛ ቋንቋ መምህር የነበረ ነው፡፡ ለአሸባሪ ድርጅት ጽሁፍ አቅርቧል በሚል በቁጥጥር ስር እንዲውል ከተደረገ በኋላ የሸፍጥ ክስ ተመስርቶበት በዝንጀሮው የይስሙላ ፍርድ ቤት የ8 ዓመታት እስራት ተፈርዶበት በአሁኑ ጊዜ በማጎሪያው እስር ቤት በመማቀቅ ላይ የሚገኝ የነጻነት ታጋይ ነው፡፡ በቀለ ወያኔን ወደኋላ የሚንሸራተት እና ለማስተዳደርም አቅም ሳይኖረው በኃይል ለመግዛት ብቻ የተቀመጠ አስከፊ ድርጅት ነው የሚል ትችት ማቅረቡ የሚታወስ ነው፡፡ በህወሀት የጭቆና አገዛዝ አራት ዓይነት የዜግነት መደቦች አሉ በሚል የክርክር ጭብጡን እንዲህ አቅርቧል፣ “የመጀመሪያው የዜግነት መደብ በስልጣን ላይ ያሉትን እና መሬትን እንደ ጉልት ሽንኩርት በመቸብቸብ ላይ የሚገኙትን ያጠቃልላል፡፡ የሁለተኛው የዜግነት ምድብ ደግሞ መሬት የሚወስዱትን እና የሚቀበሉትን ያካትታል፡፡ ሶስተኛው የዜጎች ምድብ ደግሞ እነዚህ ህገወጥ ድርጊቶች ሲፈጸሙ በመታዘብ የተመልካችንትን ሚና የሚጫወተው የህብረተሰብ ክፍል ነው ይላል፡፡ የመጨረሻው እና አራተኛው የዜግነት ምድብ ደግሞ ዜጎች በዜግነታቸው ይዘውት የነበረውን አንጡራ ይዞታቸው የሆነውን መሬታቸውን እና ቤቶቻቸውን ኃይልን በመጠቀም የሚወሰዱባቸው ፍትህ ያጡ እና የነጡ ዜጎችን ያካተተ ነው፡፡“ በቀለ ገርባ በቁጥጥር ስር ውሎ ወደማጎሪያው እስር ቤት ከመጋዙ አንድ ቀን በፊት ህወሀት የሸፍጥ የአሸባሪነት ክስ በመመስረት እርሱን ለማጥቃት የጥቃት ዱለታ እያደረገ እንደሆነ ለአምነስቲ ኢንተርናሽናል ተወካይ ግልጽ አድርጎ ነበር፡፡

አቡባከር አህመድ ጠንካራ የሆነ የእምነት ነጻነት መከበር ተሟጋች ታጋይ ነው፡፡ አቡባከር ጥያቄዎቹን በተቀነባበረ መልክ አዘጋጅቶ የህግ የበላይነት አክባሪ እና አቀንቀቃኛ መሆኑን እንዲህ በማለት ገልጾ ነበር፣ “ማንኛውንም አመራር አልተቃወምንም፡፡ እኛ ጥያቄ አድርገን ያቀረብነው ህገመንግስቱ ይከበር የሚል ብቻ ነው፡፡ ሁላችንም በአንድ ድምጽ እያልን ያለነው ህገመንግስቱን ማክበር አለባቸው የሚሉን አካሎች እራሳቸው በእርግጠኝነት ህገመንግስቱን ማክበር አለባቸው የሚል ነው፡፡“

ከሁሉም በላይ ስም ለሌላቸው፣ እውቅናን ላላገኙት፣ በግልጽ ላልታወቁት እና ላልተዘመረላቸው  በአስር ሺዎች ለሚቆጠሩት በኢትዮጵያ ለነጻነት ልዕልና፣ ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ እና ለሰብአዊ መብቶች መከበር በጽናት በመቆም ለሚታገሉት ጀግኖች እና ጀግኒቶች ኢትዮጵያውያን/ት የፖለቲካ እስረኞች ታላቅ ክብር እሰጣለሁ፣ አወድሳቸዋለሁ፡፡ ለተቀደሰው ዓላማቸው በጽናት በመቆም ጋሬጣውን ሁሉ ችለው በድል አድራጊነት ነጻነትን ያቀዳጃሉ!

እስክንድር ነጋ ድፍረትን በተቀላቀለበት ሁኔታ “በጽናት እቆማለሁ” በማለት አውጇል፣

እ.ኤ.አ ሜይ 2013 ወንድሜ እና የተከበረው ጓደኛዬ እስክንድር ነጋ እንዲህ የሚል ደብዳቤ ጽፎ ነበር፣ “በጽናት እቆማለሁ!“ ያ ደብዳቤ በአስከፊነቱ ከሚታወቀው ከመለስ ዜናዊ የቃሊቲ የማጎሪያ እስር ቤት በድብቅ ወጥቶ ነበር፡፡

“በጽናት እቆማለሁ!“ የሚለው ደብዳቤ 7 ቀላል አንቀጾችን/paragraphs አካትቶ የያዘ ብቻ ነበር፡፡ ሆኖም ግን በውስጡ ይዞት የነበረው መልዕክት ለሰባት እንዲያውም ለሰባት ሰባ ዓመታት የሚያቆይ መልዕክትን አጠቃሎ የያዘ ነበር፡፡ “በጽናት እቆማለሁ!“ የሚለው ደብዳቤ ለፍትህ አልባው አገዛዝ አልታዘዝም፣ አላጎበድድም፣ አልሰግድም፣ ጸጥ ብዬ አልገዛም የሚል ደፋርነትን የተላበሰ ደብዳቤ ነበር፡፡ ይህ ደብዳቤ በተስፋ የተሞላ ነው፡፡ ይህ ደብዳቤ ስሜትን የሚኮረኩር እና የነጻነት ትግሉን ሆ ብለን እንድንቀላቀል የሚገፋፋ ነው፡፡ ይህ ደብዳቤ ነብያዊ መንፈስን የተላበሰ ነው፡፡ ይህ ደብዳቤ ከልብ ውስጥ እጅግ በጣም ዘልቆ የተጻፈ ነው፡፡ ይህ ደብዳቤ በስሜታዊነት ሳይሆን ጥልቀት ባለው ሁኔታ የስነ ልቦናዊ የአስተሳሰብ ሂደቶችን ባካተተ እና ምክንያታዊነትን አጉልቶ በማሳየት የተዘጋጀ የምሁራዊ አንደበት መግለጫ ነው፡፡ ይህ ደብዳቤ ለቤተሰቡ፣ ለባለቤቱ እና ለልጁ በቀጥታ እንዲደርስ ሆኖ የተዘጋጀ ደብዳቤ ነው፡፡ ይህ ደብዳቤ ለኢትዮጵያ ህዝብ ሁሉ እንዲደርስ ተብሎ የተጻፋ ነው፡፡ ይህ ደብዳቤ ለኢትዮጵያ ዲያስፖራ ሁሉ እንዲደርስ ተብሎ የተጻፈ ነው፡፡ ይህ ደብዳቤ ለመጭዎቹ የኢትዮጵያ ትውልዶች በታሪክ የሚቀመጥ ተብሎ የተጻፈ ነው፡፡ ይህ ደብዳቤ ለነጻነት እና ለሰው ልጆች ክብር ሲባል የተጻፈ  ነው፡፡ ይህ ደብዳቤ የአንድን ሰው የነጻነት ጥያቄ ጩኸት፣ አንድ ሰው የወለደውን ልጅ ማሳደግ እንዲችል ነጻ የመሆን መብት እንዲኖረው እንዲሁም አንድ ሰው ከባለቤቱ እና ከቤተሰቡ ጋር ነጻ ሆኖ የመኖር መብት እንዳለው ለማሳወቅ የተጻፈ ነው፡፡ ይህ ድብዳቤ ስለእያንዳንዱ ዜጋ መብት እና እያንዳንዱም ዜጋ በመረጠው ሙያ ሀገሩን የማገልገል መብት እንዳለው ለማሳወቅ የተጻፈ ነው፡፡ በመጨረሻም “በጽናት እቆማለሁ!“ አንድ ነገርን በውል ያመላክታል፡ እውነትን፡፡ በጽናት መቆም ማለት ስለእውነት እና  ስለእውነት ብቻ በመቆም አንድን ሰው ነጻ ያወጣል ማለት ነው፡፡

ለጥቂት ጊዜ ፍቀዱልኝ እና የሚሰማኝን የእራሴን እምነት ልግለጽ፡፡ “በጽናት እቆማለሁ!“ የሚለውን ደብዳቤ ደጋግሜ ብዙ ጊዜ አንብቤዋለሁ፡፡ በአዕምሮዬ ላይ ያጫረውን ጥርጣሬ ለማስወገድ እንዲቻል በማለት ይህንን ደብዳቤ አንብቤዋለሁ፡፡ ከዚያ በኋላ ጥርጣሬዎቼ ሁሉ ሙጥጥ ጥርግ ብለው ጠፉ፡፡ ከዚያም በጽናት ቆምኩ፡፡ ወደ ነጻነት የሚወስደው መንገድ ረዥም፣ ብዙ ውጣ ውረድ ያለበት እና እጅግ በጣም አድካሚ እንደሆነ በተሰበረ ልብ ባለሁበት ወቅት ነበር ደብዳቤውን ያነበብኩት፡፡ በእኔ ፍጹም የሆነ እምነት የቱንም ያህል ለነጻነት የሚደረግ ጉዞ ረዥም አይደለም፡፡ ለሰኞ ትችቴ “ርዕስ የሚሆን ቃላትን ባጣሁበት ወቅት“ ነበር የእስክንድርን ደብዳቤ ያነበብኩት

ምንም የምለው ነገር የለም፡፡ ወዲያውኑ ሲኒየ እስከሚሞላ ድረስ በአዲስ ሀሳብ ተጥለቀለቅሁ፡፡ በየጊዜው ስለሁኔታው ባሰብኩ ቁጥር የእስክንድርን ደብዳቤ አነባለሁ እናም ስለሁኔታው አስባለሁ፡፡ የእስክንድር ድምጽ ጆሮ እያላቸው ለመስማት ለማይፈልጉት ወገኖች የጸጥታ ድምጽ ሊሆን ይችላል፡፡ ለእኔ የእርሱ ጸጥታ የሰፈነበት “በጽናት እቆማለሁ!“ የሚለው ድምጽ በየዕለቱ “በጽናት እቆማለሁ!“ “በጽናት እቆማለሁ!“ እያለ ደጋግሞ በህሊናዬ ያቃጭልብኛል፡፡

ለመሆኑ እስክንድር “በጽናት እቆማለሁ!“ ሲል ምን ማለቱ ነው? በቀላል አነጋገር በመለስ ዜናዊ የቃሊቲ የማጎሪያ እስር ቤት ቀን በቀን በእስር ላይ ሆኘ እገኛለሁ ለማለት ፈልጎ ነውን? እንደ እስክንድር፣ ርዕዮት እና ሌሎችም የነጻነት ታጋዮች የመሳሰሉ ሰዎች “በጽናት እቆማለሁ!“ ሲሉ በእርግጠኝነት ምን ለማለት ፈልገው ነው?

“በጽናት እቆማለሁ!“ በማለት እስክንድር ሲጽፍ ምን ለማለት እንደፈለገ ከእርሱ ጋር ለመነጋገር ወይም ጠይቆ ለመገንዘብ አስፈላጊ ነው ብዬ አላምንም፡፡ የእርሱ ቃላት ለእኔ ከምንም በላይ ጎላ ብለው የተጻፉ እና ግልጽ መልዕክት ማስተላለፍ የሚችሉ ናቸው፡፡ እስክንድር ማለት የፈለገው ዶ/ር ማርቲን ሉተር ኪንግ በአንድ ወቅት “ጽናት” በሚል ርዕስ እንደጻፉት ለማለት ፈልጎ ነው፡፡ ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ ሰዎች ዶ/ር ማርቲን ሉተር ኪንግን ለምን ያህል ጊዜ ነው በጽናት የምንቆመው? ነጻነታችንን ለመቀዳጀት ምን ያህል ጊዜ መቆየት አለብን?” በማለት ይጠይቁ ነበር፡፡ (በእርግጥ ህዝቦች ከዚያ የበለጠ እንዲህ የሚል ትርጉም ያለው ጥያቄ መጠየቅ ይችሉ ነበር፣ “እንደዚህ ዓይነቱን ዋጋቢስ የሆነ ስርዓት የምንታገሰው እስከ ምን ያህል ጊዜ ነው?”) ዶ/ር ማርቲን ሉተር “ሩቅ አይሆንም” በማለት ነግረዋቸው ነበር፡፡ ለሌሎችም ጥያቄዎች አጭር እና ተገቢውን መልስ እንዲህ በማለት ሲሰጡ ነበር፡

በአሁኑ ጊዜ “ምን ያህል ጊዜ ይወስዳል?” የሚል ጥያቄ እንደምትጠይቁ በሚገባ እገነዘባለሁ…

በዛሬው ዕለት ከሰዓት በኋላ ልላችሁ እችላለሁ አጋጣሚው ምን ያህል አስቸጋሪ ቢሆንም፣ ሰዓቱ ተስፋ አስቆራጭ ቢሆንም ጊዜው በጣም ረዥም አይሆንም ምክንያቱም እውነት መሬት ከነካች በኋላ እንደገና ትነሳለችና፡፡

ምን ያህል ጊዜ? ረዥም ጊዜ አይሆንም ምክንያቱም የቱንም ዓይነት ውሸት እና ቅጥፈት ለዘላለም ሊኖር አይችልምና፡፡

እኮ ለምን ያህል ጊዜ? ረዥም ጊዜ አይሆንም ምክንያቱም የዘራኸውን ታጭዳለህና…

እኮ ለምን ያህል ጊዜ እኮ ነው የምንለው? ረዥም ጊዜ አይሆንም ምክንያቱም የሞራል ስብዕና ጠርዙ ረዥም ነውና፣ ሆኖም ግን ወደ ፍትህ ዘንበል ይላል፡፡

እስክንድር፣ ርዕዮት እና ሌሎች የነጻነት ታጋዮች ለምን ያህል ጊዜ ነው በጽናት የሚቆሙት? ኢትዮጵያ ለምን ያህል ጊዜ በጽናት መቆም አለባት? ረዥም ጊዜ አይሆንም፣ ሆኖም ግን ተስፋየለሽ ሰዓት ቢሆንም ቅሉ ረዥም አይሆንም ምክንያቱም ህወሀት የዘራውን ያጭዳልና፡፡ ድልአድራጊነት ጽናቱ ላላቸው ሰዎች ሁሉ የተረጋገጠ ነው፡፡

እስክንድር በደብዳቤው እንዲህ በማለት ጽፎ ነበር፣ “ግለሰቦች ሊቀጡ ይችላሉ፣ ሊሰቃዩ ይችላሉ (ኦ ልጀን እንዴት እዳጣሁት እና እንደናፈቀኝ) ከዚህም በላይ ሊገደሉ ይችላሉ፡፡ ሆኖም ግን ዴሞክራሲ ሊወገድ የማይችል የሰብአዊነት ዕጣፈንታ ነው፡፡ ዴሞክራሲን ማዘግየት ይቻል ይሆናል ሆኖም ግን ማሸነፍ አይቻልም፡፡“

ፍትህን ማዘግዬት ይቻላል፣ ሆኖም ግን በፍጹም ማሸነፍ አይቻልም፡፡ በሰብአዊ መብት ላይ ወንጀልን የፈጸሙ ወንጀለኞች በእመቤት በፍህ ላይ ያላግጣሉ፣ አፍንጫቸውን ይነፋሉ፣  አመልካች ጣታቸውንም ይቀስራሉ፣ ሆኖም ግን እመቤት ፍትህ በእጇ ላይ ምን እንዳለ እንጅ ምን ይዛ እንዳለች ማወቅ ይኖርባቸዋል፡፡ የሰው ልጅ ታሪክ የመጨረሻ መቆሚያ ጠርዙ የሰው ልጆች የሰብአዊ መብት ዕድል የሚከበርበት፣ የነጻነት እና ዴሞክራሲ መኖር፣ ከጭቆና ነጻ የመሆን፣ ከደናቁርት ወሮበላ ዘራፊ አምባገነኖች መላቀቅ፣ አንድ ሰው ከአምላኩ የተሰጡትን ተፈጥሯዊ የማሰብ፣ የመፍጠር እና ነጻ የሆኖ ሰብአዊ መብቶች ማከበር ነው፡፡

እስክንድር ለልጁ ያለውን ሀሳብ እንዲህ በማለት ገልጿል፣ “ኦ ልጀን እዴት እዳጣሁት እና እንደናፈቀኝ“ በማለት የተሰማውን ስቃይ አሳውቋል፡፡ የልጁ ስም ናፍቆት የሚባል ሲሆን ትርጉሙም “አንድን ሰው በመለየት ማጣት” የሚል ነው፡፡ ምን ዓይነት የሚገርም እና ነብያዊ የስም አወጣጥ ዘዴ ነው! ናፍቆት እ.ኤ.አ በ2005 ወላጆቹ በእስር ቤት ያለምንም ወንጀል 16 ወራት ታስረው ክሳቸው እንዲቋረጥ ተደርጎ ከተፈቱበት በመለስ ዜናዊ የቃሊቲ እስር ቤት ነው የተወለደው፡፡ አረመኔው እና ጨካኙ መለስ ዜናዊ ናፍቆት ገና ያልዳበረ ህጻን በነበረበት ጊዜ የህክምና እገዛ እንዳያገኝ በራሱ ትዕዛዝ እገዳ ጥለው ነበር፡፡ የመለስን ጣልቃገብነት በተመለከተ ያለው ማስረጃ አወዛጋቢ አይደለም፡፡ መለስ እስክንድርን እና ሰርክዓለምን ለመበቀል ሲል የቀናት እድሜ ብቻ የነበረውን ህጻን ልጃቸውን ለመግደል በጽናት ወስኖ ነበር፡፡ መለስ አስክንድርን እና ሰርክዓለምን ህጻን ልጃቸው በእስር ቤት ውስጥ እንዲሞት በማድረግ በሀዘን እንዲገረፉ ለማድረግ ፈልጎ ነበር፡፡ መለስ ጠላቶቸ ናቸው የሚለዉን ሰዎች በአደባባይ በህዝብ ፊት እንዲዋረዱ ማድረግ ብቻ ደስ የሚያሰኘው ሰው ነበር።  ሆኖም ግን ከህዝብ እይታ ውጭም ቢሆን ጠላቴ የሚለዉን ንጹሀን ዜጎች ሲሰቃዩ እና መከራ ሲደርስባቸው ማየት ከምንም በላይ ደስ ያሰኘው ነበር ፡፡ እሱን በቅርብ የሚያውቁት ሰዎች ለዚህ ምስክርነት ይሰጣሉ፡፡ እስክንድር እና ሰርክዓለም በመጨረሻ በጻፉት ደብዳቤ ህጻን ልጃቸው በእግዚአብሄር ታምር ከሞት እንደተረፈ ይፋ አድርገዋል፡፡

አሁን በህይወት የሌሉት መለስ ዜናዊ እ.ኤ.አ ሴፕቴምበር 2010 በኒዮርክ ከተማ በኮሎምቢያ ዩኒቨርስቲ በመገኘት ንግግር እንዲያደርጉ ፕሮግራም ተይዞላቸው በነበረበት ወቅት እስክንድር እና ባለቤቱ ሰርክዓለም (በእራሷ መብት እና በምታሳየው ደፋር የጋዜጠኝነት ባህሪ እ.ኤ.አ በ2012 ከሴቶች የግንኙነት ተቋም/Women’s Media Foundation የጋዜጠኝነት ሽልማት አሸናፊ የሆነች) ሰውዬው በዩነቨርስቲው ተገኝቶ  ንግግር እንዳያደርግ  የሚቃወም ደብዳቤ ለዩኒቨርስቲው ፕሬዚዳንት ጽፈው ነበር፡፡ የተቃውሟቸውን መሰረትም እንዲህ በማለት ግልጽ አድርገው ነበር፣

ህጻኑ በሚወለድበት ጊዜ ከሚጠበቀው የክብደት መጠን በእጅጉ የቀነሰ መሆኑ ይኸውም ሊሆን የቻለበት ምክንያት ሰርካለም በአፍሪካ በአስከፊነታቸው ከሚታወቁት እስር ቤቶች መካከል ታስራ በመቆየቷ ምክንያት በአካል እና በስነልቦና የተጎዳች በመሆኑ የህጻኑን ህይወት ለማዳን ህይወት አድን የህጻናት ማቆያ የሚሆን ኢንኩቤተር በመጠቀም ኃላፊነት በጎደላቸው እና ምንም ዓይነት ደንታ በማይሰማቸው የበቀል መሪዎች ለሞት ተፈርዶበት የነበረው ህጻን በእስር ቤት ዶክተሮች ጥረት አዲስ የተወለደው ህጻን በእግዚአብሄር ታምር ሊድን ችሏል፡፡ (ክብር ምስጋና ለእግዚአብሄር ይሁን)፡፡

ሸክስፒር እንዲህ በማለት ጽፈዋል፣ “ሰዎች በህይወት ዘመናቸው ይኖሯቸው የነበሩት ጭራቃዊነቶች በህይወት ካለፉ በኋላም ይኖራሉ…“መለስ ከሰራቸው በርካታ ጭራቃዊነት ድርጊቶች መካከል አንዱ በአሁኑ ወቅት መለስ ከሞተ ከሁለት ዓመታት በኋላም በእስክንድር፣ ሰርክዓለም እና በናፍቆት መብት ድፍጠጣ ላይ የሰሯቸው ግፎች አሁንም እንዳሉ ናቸው፡፡ መለስ በሞተ ጊዜ የሱ ጭራቃዊ ድርጊታቸው የመጥፎዎች ሁሉ ተምሳሌት ሆኖ ጣላቴ ናቸው ብለው የሚያስቧቸውን ወገኖች ለማጥፋት እና የበቀል እርምጃ ለመውሰድ ከእባብ በበለጠ መልኩ በመተጣጠፍ አደገኛ ሁኔታን የሚፈጥር ሆኖ ቀጥሏል፡፡

እስክንድር እና ቤተሰቡ በእግዚአብሄር ኃይል ጽናቱን ሰጥቷቸዋል፡፡ መለስ የአምላክን ቁጣ ሊያመልጡ በፍጹም ሊያመልጡ አልቻሉም፡፡ እርግጠኛ ነኝ እስክንድር እንዲህ ይላል፣ “እራስህ ለመበቀል አታስብ፣ ሁሉንም ነገር ለአምላክ ቁጣ ብቻ ተወው ተብሎ እንደተጻፈው እራሱ ይበቀልልሀል፣ በቀል የእኔ ነው፣ ጌታ የሀጢያት ደመወዝን እኔ እከፍላለሁ ብሏልና፡፡“ የአምላክ ቁጣ በመለስ የበሰበሰው እና እየተፍረከረከ ባለው ስርዓት ላይ ጉብኝት እያደረገ ነው፡፡ እስክንድር አምላክ ሲፈቅድ ቤተሰቡን ሰብስቦ በሰላም እንደሚኖር ጥርጥር የለኝም፡፡

እስክንድር በደብዳቤው ላይ እንዲህ የሚል ጽሁፍ አስፍሮ ይገኛል፣ “የዳኝነት ሂደት ስርዓት በሌለበት፣ መከራ በተንሰራፋበት ዴሞክራሲ ባህሪ እና ጠቃሚነቱን ያጣ ነብስ የሌለው ባዶ ነገር ነው፡፡ እጣፈንታዬን እቀበላለሁ፣ እንዲያውም መልካም ዕድልን እንዳገኘ ሰው እታቀፈዋለሁ፡፡ በቅማሎች መሀከል ቢሆንም በእስር ቤት በሰላም እንቅልፌን እተኛለሁ፡፡ የእኔ አሳሪዎች ግን በሞቀ አልጋ ላይ ሚስቶቻቸውን አቅፈው በቤታቸው የሚተኙ ቢሆንም እንደ እኔ ሰላማቸው የተረጋጋ ይሆናል የሚል እምነት የለኝም፡፡“

በዚህ ዓይነት ሁኔታ ነው እግንዲህ ኔልሰን ማንዴላ ዕጣ ፈንታቸውን ተቀብለው በአፓርታይድ የዘረኝነት ስርዓት ለ27 ዓመታት በጽናት ታስረው በጽናት ለድል የበቁት፡፡ እንደማንዴላ እስክንድርም በማጎሪያው እስር ቤት ነጻነት ይሰማዋል፣ እናም ሰላሙ የተረጋጋ ነው፡፡ እስክንድር እንደ ማንዴላ የማይበገር ነብስ ያለው መሆኑን አሳይቷል፡፡ እንደ ማንዴላ የእስክንድር እራስ ደምቷል ሆኖም ግን አላጎነበሰም፡፡ እስክንድር በምንም ዓይነት ሁኔታ አልፈራም፡፡ እስክንድር የእራሱ ዕጣፈንታ ጌታ ነው፡፡ እስክንድር ማንዴላ እንዳደረጉት ሁሉ እንዲህ በሚሉት በዊሊያም ኤርነስት ሄንለይ ግጥሞች በመሳሳት አይበገሬነቱን አስመስክሯል፣

እኔን በሚሸፍን በድቅድቅ ጨለማ፣ ጥቁር የተናቀ ወድቆ የገለማ፣

ስብዕናውን ያጣ ከዋልታ እስከ ዋልታ፣ በዘረኛ ወጥመድ ተይዞ  እሚፈታ፡፡

ለማይበገረው ደንዳናው ጽናቴ፣ አምላክን ላማስግን ሳለሁ በህይወቴ፡፡

በጭካኔው ማዕበል በአደገኛው ቦታ፣ አልንፈራገጥም አልጮህ በዝምታ፡፡

በእስር ቤት መታጎር ሆኖ ዕጣፈንታዬ፣ ጭንቅላቴ መድማት ቢሆን አበሳዬ፣

ካመንኩበት ጽናት ወይ ፍንክች ወይ ዝንፍ፣ ምድር ቢገለበጥ ሰማይ ቢያወርድ ዶፍ፡፡

ጭካኔ ቢበዛ ስቃይ ቢጠነዛም፣ ከቆምኩበት ጽናት አላጎነብስም፣

እግሮቸም አይርዱ እጀቸም አይዝሉ፣ ዓይኖቸም ፈጠዋል ሳይንቀዋለሉ፣

ጆሮዬም ይሰማል፣ ምላሴም ይቀምሳል፣ አፍንጫዬ ዋናው ነገርን ያሸታል፡፡

ስለዚህ ምን ገዶኝ ከዓላማዬ ጽናት ከቶ ማን አግዶኝ?

ከዚህ ከሰቆቃ ከዋይታ እና ከእንባ፣ ከዚህ ከጭካኔ ከጨለማው አንባ፣

ፍትህ ትፈልቃለች በፍቅር ተውባ፣ ነጻነት ይመጣል ከግፈኞች ጀርባ፣

እናም ለዘመናት የተከማቸው ግፍ፣ እኔን ሳያሸብር ይታየኛል ሲረግፍ፡፡

የማስገቢያው በሩ ይጣመም ይዘርጋ፣

የሸፍጥ ክስ ይምጣ እየተወራጋ፣

ቅጣቱ ይቆለል ይምጣ እየተላጋ፣

ለእኔ ጉዳይ አይደል ከቶ የለው ዋጋ፡፡

እንግዲህ እወቁኝ ከቶም እንዳትንቁኝ፣

ለዓላማዬ ጽናት ነብሴን የሰጠሁ ነኝ፡፡

ለዓላማዬ ጽናት ምንም ሳልረታ፣

ለዕጣ ፈንታ አዛዡ እሆናለሁ ጌታ፣

ከጌታ በመለስ ከፍጥረት ኃያሉ፣

ለነብሴ ዋስትና በምድር ሳር ቅጠሉ፣

አድራጊ ፈጣሪው እኔ ነኝ ሻምበሉ፡፡

ረዥም እድሜ ለእስክንድር፣ ለአይበገሬው አንበሳ!

ቪቫ እስክንድር አይበገሬው!

እስክንድር በደብዳቤው እንዲህ በማለት ጽፏል፣ “መንግስት በሚከተለው የፖለቲካ የሞራል ስብዕና ኪሳራ ምክንያት በተደጋጋሚ እና በማያቋርጥ ሁኔታ ሲዋሽ ቆይቷል፡፡ ሁሉም የታሪክ ታላላቅ ወንጀሎች የምንረሳቸው ካልሆነ በስተቀር በጊዚያቸው በነበረው የሞራል ስብዕና ላይ የተመሰረቱ ናቸው፡፡“

እስክንድር ስለምን እየጻፈ እንደሆነ በሚገባ አውቃለሁ፡፡ እ.ኤ.አ በ2006 “በፖሊስ መንግስት ሸፍጠኞች፣ ዓቃብያነ ህጎች እና ዳኞች የመሰረት ድንጋዮች“ በሚል ርዕስ ለመጀመሪያ ጊዜ ባዘጋጀሁት ባለ32 ገጾች ትንታኔ ትችት በወያኔ የዝንጀሮው የይስሙላ ፍርድ ቤት ላይ ሸንቋጭ ትችት አቅርቤ ነበር፡፡ ያ ትችት እ.ኤ.አ በ2005 የተካሄደውን ሀገር አቀፍ ምርጫ ተከትሎ ተፈጥሮ በነበረው ውዝግብ ቃሊቲ እየተባለ በሚጠራው እስር ቤት ታስረው ሲማቅቁ በነበሩት ወደ 130 ወይም ከዚያ በላይ የሚሆኑ ዋና የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች፣ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች፣ የሲቪል ማህበረሰብ ወትዋቾች፣ ጋዜጠኞች እና ሌሎች ወገኖች ላይ ተመስርቶ በነበረው የክስ ሂደት ላይ ሙያዊ የሆነ ትንታኔ በመስጠት ዓላማ ላይ ያነጣጠረ ነበር፡፡

የወያኔ የታዕይታ የፍርድ ሂደት ዓለም አቀፉን ማህበረሰብ ለማታለል የተደረገ የመድረክ ተውኔት ከመሆን ዕጣፈንታ የዘለለ አልነበረም፡፡ ያ ፍርድ ቤት ግልጽ በሆነ መልኩ የተዋረደ፣ በስብዕና ጥንካሪያቸው ሳይሆን በታዛዥ እና ሎሌነታቸው እየተመረጡ ለታዕይታ የተቋቋመ ችሎት ነበር፡፡ ያ ፍርድ ቤት የሸፍጥ ክስ እንዲመለከት፣ አጭበርባሪ ዓቃብያነ ህጎች የተመደቡለት፣ ምንም ዓይነት የፍትህ ስርዓት ሂደትን ያልተከተለ እና ውጤቱ ምን እንደሚሆን አስቀድሞ የታወቀ ይኸውም አንድ ነገርን ብቻ ለማድረግ ማለትም ፍትህን በግልጽ በአደባባይ ለማጨናገፍ የተቋቋመ የግፈኞች የይስሙላ የፍርድ ቤት ችሎት ነበር፡፡ የህወሀት የዝንጀሮ የይስሙላ ፍርድ ቤት እስከ አሁንም ድረስ አልተቀየረም:: እንግዲህ እስክንድር “መንግስት በፍትህ አደባባይ በህዝብ ፊት እየዋሸ ነው ያለው” ሲል ሌላ ሳይሆን ይህንን ማለቱ ነው …” የመንግስት ውሸት በዝንጀሮው የይስሙላ ፍርድ ቤት ችሎት መድረክ ላይ እውነትን አፈር ድሜ እያስበላ፣ የሰብአዊ መብቶች በመንግስት ስህተቶች እና ቅጥፈቶች እየተደፈጠጡ ያሉበት ሁኔታ ነው ዛሬ በኢትዮጵያ ያለው ቀውስ፡፡ “በአሁኑ ወቅት ያለው ቀውስ” በሚል ርዕስ በጀምስ ሩሴል ሎዌል ግጥሞች ውስጥ እንዲህ የሚሉትን የግጥም ስንኞች እንመልከት፣ “ውሸት ደረቱን ግልብጦ በችሎት ወንበሩ ላይ እና በስህተት እግሩን አንፈራጥጦ በዙፋኑ ላይ ተቀምጧል”:

ለነጻነት ተብሎ ተግባር ሲከናወን፣ በቆራጡ ትግል እውነት እውን ሲሆን፣

ነቢያዊ ደስታ ስናገኝ ሀሴትን፣ በምስራቅ በምዕራብ ስንል ዘብነን ዘብነን፣

ጽናትን ሰንቀን ከመከራው ጽዋ ከግፉ ተላቀን፣ ድል አድራጊ ሆነን በሲቃ ተውጠን፡፡

ደንታቢስ ቢመስለው ታላቁ ተበቃይ፣

ታሪክ ይዘግባል በምድር በሰማይ፣

በጽናት መቆም ነው ለወሳኙ ትግል፣

በበከተው ስርዓት ለመጎናጸፍ ድል

እውነት ለዘላለም በመስቀያ መድረክ፤

ውሸት ለዘላለም በዙፋኑ መድረክ፣

ሆነው አይቀጥሉም አያብልም ታሪክ፡፡

እናም ያ መስቀያ ይጠፋል ይበናል፣

ከጀርባው ባዘለው ጨለማ ማዕበል፡፡

በስውር ከሚያየው ከአምላክ ተነጥሎ፣

ደባን የሚፈጽም እውነት አስመስሎ፣

የአምላክ ሰይፍ ሲመዘዝ ሊሆን አከንባሎ፣

የት ይገባ ይሆን ያ ግም ዘባትሎ?

ወሮበላ ዘራፊዎች ለዘላለም በዙፋን ተኮፍሰው ሊኖሩ ይችላሉን? በፍጹም!

እስክንድር በደብዳቤው እንዲህ በማለት ጽፏል፣ “አሰልችው እና የተለመደው የሸፍጥ የፍርድ ሂደት ምንም ዓይነት ፋይዳ ያለው ለውጥ አያመጣም፡፡ ሆኖም ግን በአንድ ወቅት ክርስቶፎር ሂቸንስ እንደገለጹት የሚያስከትለው ‘የኢምክንያታዊነት ስብስብ እና የንቀት ደረጃን ከማሳየት ያለፈ እርባና የለውም‘“ ለማለት የተፈለገው ይህ ጉዳይ ያለጥፋቱ በግፍ ታስሮ እንደነበረው ንጹህ ፈረንሳያዊ ሻምበል እንደ ድሬይፈስ ያለ የኢትዮጵያዊ ጉዳይ ነው፡፡ በዚህ ፈታኘኝ ወቅት ብቻ ነው የበከተ እና የበሰበሰውን አምባገነናዊ ስርዓት ገርስሶ መጣል የሚያስፈልገው እንጅ ጥቃቅን ነገሮችን በማከናወን ታጋሽነትን የማራዘም ጨዋታን በመጫወት ከቶውንም ሊሆን አይችልም፡፡

እስክንድር የፈረንሳይ ጦር አዛዥ እንደነበሩት እንደ ሻምበል አልፍሬድ ድሬይፈስ በሀሰት ክስ ተመስርቶባቸው እ.ኤ.አ በ1894 በሚስጥራዊ የጦር ፍርድ ቤት በሀገር ክህደት ወንጀል በሚል የጥፋተኝነት ውሳኔ ተላልፎባቸው እንደነበሩት ንጹህ ዜጋ ማለት ነው፡፡ የፈረንሳይ ዕውቅ ደራሲ የነበሩት ኢሚሌ ዞላ ታዋቂ ደብዳቢያቸውን በብዕራቸው በመጻፍ እንዲህ ብለው ነበር፣ “አይሁዶችን ለማግለል ሲባል እና በሀሰት ወንጅሎ ጥቃት ለመሰንዘር በመገፋፋት በድሬይፈስ ላይ የሀሰት ክስ በመመስረቱ ምክንያት የፈረንሳይን ፕሬዚዳንት እና የፈረንሳይን መንግስት ከስሻለሁ፡፡“ ድሬይፈስ ምንም ሳያቅማሙ እና ሳይሸበሩ በጽናት ቆመው በመከራከራቸው በመጨረሻ ከሀሰት ውንጀላው ሙሉ በሙሉ ነጻ ሆነው ተሰናብተዋል፡፡

በጊዜ ሂደት እስክንድርም እንደ ሻምበል ድሬይፈስ ነጻ ሆኖ ይወጣል፡፡ እራሱ በሰራቸው በሰው ልጆች ላይ የተፈጸሙ ወንጀሎች ጉሮሮውን ታንቆ ባለው አምባገነን እስክንድር በሀሰት የፍብረካ ወንጀል በሀገር መክዳት በሚል የሸፍጥ ውንጀላ ታስሮ በማጎሪያው እስር ቤት ውስጥ በመማቀቅ ላይ ይገኛል፡፡

እስክንድር የጽናት ተምሳሌት! በግፈኞች ቢከሰስም በጽናት የቆመ ጀግና!

እስክንድር በደብዳቤው እንዲህ በማለት ጽፎ ነበር፣ “…እ.ኤ.አ በ1930ዎቹ ስታሊኒኒያዊ አምባገነኖች ሚስጥር እንድታወጣ ለማስገደድ አልነበረም የሚገርፉህ እና የሚያሰቃዩህ፣ ሆኖም ግን የሀሰት መግለጫ ለማውጣት እንዲመቻቸው በሚስጥር ህገወጥ ነገር ለመስራት ተባባሪ እንድትሆን ነበር ለማግባባት የሚሞክሩት፡፡ ለዚህም ነው እንግዲህ በኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት ቀውስ ዋና መሰረት ሆኖ የሚታየው፡፡ እንደዚሁም 30 ዓይነት ተደጋጋሚ ድፍረት የተሞላባቸው የፍርድ ሂደቶች ቢካሄዱም ፍትህን ከማዛባት ባለፈ ነጻነትን ሊያጎናጽፍ እንደማይችል ባለስልጣኖች አልተረዱትም፣ በዚህም መሰረት ግፈኞች ከታሪክ ትምህርትን አልቀሰሙም፣ እንዲያውም በታሪክ ተጽፍ ከተያዘው ስሀተት በበለጠ መልኩ ወንጀልን በመስራት በሰብአዊ መብት ድፍጠጣ ወንጀል ባህር ውስጥ እስከ አንገታቸው ድረስ ሰምጠው በመዋኘት ላይ ይገኛሉ፡፡“

ስታሊን በአንድ ወቅት የአንድ ሰው መሞት አሰቃቂ ነው፣ የሚሊዮኖች ሞት ግን የቁጥር ጉዳይ ነው ብለው ነበር፡፡ ሆኖም ግን ስታሊን በሚሊዮን የሚቆጠሩ ህዝቦቻቸውን እራሳቸው አልገደሉም፡፡ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ህዝቦች ጆሮ ዳባ ልበስ ብለው ጻጥ ካላሉ እና የሀሰት ውንጀላን ለመፈብረክ በሚስጥር የሚተባበሩ ሰዎች እስከሌሉ ድረስ ጭራቃዊነት ድርጊት በንጹሀን ዜጎች ላይ በፍጹም አይፈጸምም፡፡ ጭራቃዊነት ድርጊት ሲፈጸም እየተመለከቱ እና ይኸ ለእኔ ጉዳዬ አይደለም እያሉ በወገኖቻቸው ስቃይ ላይ የሚሳለቁ ህሊናየለሽ ወገኖች ሁሉ ለሸፍጥ ተግባር በሚስጥር ለሚሰሩ መሰሪ ጭራቃዊ ተግባሮች ሁሉ ተባባሪዎች መሆናቸውን መገንዘብ አለባቸው፡፡ እንደዚሁም ደግሞ ቢዝነስ እና የፖለቲካ ተግባራት መጣመር የለባቸውም የሚሉ ወገኖች ሁሉ በሚስጥር ለሚተገበሩ የጭራቃዊነት ተግባራት ተባባሪዎች ናቸው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ጭራቃዊነት ድርጊት ሲፈጸም እየተመለከቱ አላየሁም ብሎ መካድ ከጭራቃነት ጋር በሚስጥር የሸፍጥ ዱለታ ተባባሪ እንደሆኑ ሊገነዘቡ ይገባል፡፡

እንደዚሁም ደግሞ ጭራቃዊ ድርጊትን ከማውገዝ እና ከመታገል አልፎ ይቅርታ መጠየቅ እና ጭራቃዊነትን ለተፈጻሚነቱ ትክክለኛነት ለመስበክ መሞከር ከጭራቃዊነት ጋር በሚስጥር ተባብሮ በንጹሀን ዜጎች ላይ ደባን የመስራት ተባባሪነት መሆኑን በውል ሊገነዘቡ ይገባል፡፡ እንደዚሁም ሆን ብለው ያላወቁ መስለው ከጭራቃዊነት ድርጊት ሲፈጸም ዝም ብለው የሚመለከቱ ሁሉ በሚስጥር ጭራቃዊ ድርጊትን ለመፈጸም ተባባሪዎች ሆነው እንደቀረቡ ሊያውቁ ይገባል፡፡ ከዚህም በላይ “ምንም ዓይነት ጭራቃዊነት አላየሁም፣ ምንም ዓይነት ጭራቃዊነት አልሰማሁም፣ ምንም ዓይነት ጭራቃዊነት አልተናገርኩም” የሚሉ መርሆዎችን እያራመዱ ሰው ሳይሆኑ እውነተኛ ሰው መስለው የሚኖሩ አስመሳዮች ሁሉ በሚስጥር ጭራቃዊነት ድርጊትን እየፈጸሙ እንዳሉ በውል ሊገነዘቡ ይገባል፡፡

እስከንድር በደብዳቤው ላይ እንዲህ በማለት ጽፏል፡ “ ለምንድን ነው የቀረው ዓለም ህዝብ ጉዳዩ የሚሆነው? ይህንን ጉዳይ በማስመልከት ሆራስ በተሻለ መልክ እንዲህ በማለት ገልጸውት ነበር፣ ‘ስሙን ብቻ ቀይር፣ እናም ይህ ታሪክ የአንተም ታሪክ ይሆናል‘ ምን ጊዜም ፍትህ ሲጓደል የእኛ የሰብአዊ ፍጡርነት ስብዕናም አብሮ ይጎድላል፡፡“

እስክንድር ከሮማን ታላላቅ ገጣሚዎች አንዱ የሆኑትን እና በተስፋ በተሞሉ ቃላታቸው ታዋቂ የሆኑትን የሆራስን አባባል ወስዶ ተጠቅሞበታል፡፡ እስክንድር የናዚን ወደ ስልጣን መምጣት ተከትሎ የጀርመን ምሁራን ዝምታን መምረጣቸውን አስመልክቶ ፓስተር ማርቲን ኒሞለር ፍርሀታቸውን የገለጹበትን በመጥቀስ ጩኸቱን አሰምቷል፡፡ ለምንድን ነው ማንም በሌላው ጉዳይ ላይ የሚያገባው?  ምክንያቱም ነገ አንተም ተረኛ ነህ! ባለወር ባላሳምንት ነው ነገሩ፡፡

በመጀመሪያ በኮሙኒስቶች መጡባቸው፣ እናም ዝም አልኩ ምክንያቱም ኮሙኒስት አልነበርኩምና፡፡ በቀጣይነትም በሶሻሊስቶች ላይ መጡባቸው፣ አሁንም ምንም ሳልናገር ዝም አልኩ ምክንያቱም ሶሻሊስት አልነበርኩምና፡፡ ከዚያም በሰራተኛ ማሀበራት ላይ መጡባቸው፣ አሁንም ምንም ሳልተነፍስ ዝም አልኩ ምክንያቱም የሰራተኛ ማህበራት አባል አልነበርኩምና፡፡ በመጨረሻም በእኔ በእራሴ ላይ መጡብኝ፣ ሆኖም ግን ለእኔ የሚጮህልኝ ማንም አልነበረም፡፡

እስክንድር እንዲህ በማለት ጥያቄ ያቀርባል፣ “ሌላው ዓለም ለምንድን ነው የሚያገባው?“ እኔ ደግሞ እንዲህ በማለት እጠይቃለሁ፣ “ኢትዮጵያውያን/ት ስለእስክንድር፣ ስለርዕዮት እና ስለሌሎች የፖለቲካ እስረኞች ጉዳይ የሚያገባቸው ለምንድን ነው?“ በመለስ ዜናዊ ውስብስብ እስር ቤት ታጉረው በመሰቃየት ላያ ስላሉት ለእስክንድር፣ ለርዕዮት እና ለሌሎች የፖለቲካ እስረኞች የሚናገርላቸው እና የሚጮህላቸው ሰው አለን?

የወያኔ ወሮበላ ስርዓት ወገኖቻችንን አሳር እና ፍዳ እያሳየ ነጻነታቸውን ገፍፎ ሲገዛ እያዩ ዝም በማለታቸው እና ጥቂቶች ሆዳሞች ደግሞ በርካሽ ጥቅመኝነት ህሊናቸውን ለገንዘብ ሸጠው ወሮበላው የወያኔ ስብስብ ወደ ስልጣን እንዲመጣ በመተባበር እና አሁንም በዚሁ አምባገነንነቱ እንዲቀጥል በሚስጥር እየረዱ በመሆናቸው በኢትዮጵያ ምሁራን ላይ ጣቴን ቀስሬባቸዋለሁ፡፡ ከስሻቸዋለሁም!

የጀግኖች እና የጀግኒቶች ረዥም ጉዞ ለነጻነት፣

እስክንድር በደብዳቤው ላይ እንዲህ የሚል ጽሁፍ አስፍሯል፣ “ ከዋሻው ጭፍ ብርሀን ይታየኛል፡፡ ከዚያ ለመድረስ ብዙ ጊዜ ሊወስድም ላይወስድም ይችላል፡፡ በየትኛውም ዓይነት መንገድ ነገሮች ቢፈጸሙ እኔ በጽናት እቆማለሁ!“

“የድብቁ ኃይል/The Power of Myth” እና የሌሎች ወጥ የሆኑ ስራዎች ታዋቂ የሆኑት ደራሲ ፕሮፌሰር ጆሴፍ ካምፕቤል የጀግናን ጉዞ ከብርሀን ወደ ጨለማ ከዚያም ተመልሶ ከጨለማ ወደ ብርሀን የሚያደርገውን ጉዞ ገልጸዋል፡፡ ጉዞው ጽናትን እና እልህ አስጨራሽ የሆነ ታጋሽነትን የሚጠይቅ አድካሚ ጉዞ ነው፡፡ ጀግና ፈታኝ የሆነ ነገር መምጣቱን ምልክት እስከሚያገኝ ድረስ እና በዚህች ብቸኛ እና በውል ባልታወቀች ዓለም ላይ ድብቅ ኃይሎች እና ድርጊቶች እስከሚከሰቱ ድረስ እንደማንኛውም ተራ ሰው ነው የሚኖረው፡፡  ጀግናው ጥሪውን የሚቀበል ከሆነ ሙከራዎችን እና መከራዎችን በድብቁ ዓለም ላይ ብቻውን ወይም ደግሞ ከሌሎች ጋር ሊጋፈጥ ይችላ፡፡ የእርሱን ውስጣዊ ባህሪ ሊፈትኑ የሚችሉ ከፍተኛ የሆኑ ተግዳሮቶች ሊገጥሙት ይችላሉ፡፡ ጀግናው የገጠመውን ፈተና ሊቋቋም ከቻለ የምሁርነት እና የእራስ እውቀት ታላቅ ስጦታን ይሸለማል፡፡ ጀግና ከዚህ ታላቅ ስጦታ ጋር ወደ ተራው ህዝብ ዘንድ ለመመለስ ወይም ላለመመለስ መወሰን አለበት፡፡ በሚመለስበት መንገድ ላይ በጣም በርካታ የሆኑ ፈተናዎችን ይጋፈጣል፡፡ ጀግናው ስኬታማ የሚሆን ከሆነ ታላቁን ስጦታ በመጠቀም ዓለም ለማሻሻል አጋጣሚውን ሊጠቀምበት ይችላል፡፡ ስለሆነም ካምፕቤል እንዲህ በማለት ጽፈው ነበር፣ “የዓለምን ከጥፋት ለማዳን ጉዞ ላይ አይደለንም፣ ሆኖም ግን የእራሳችንን ከጥፋት ለማዳን ነው፡፡ ይህንንም በማድረግ ዓለምን አናድናለን፡፡ የጠንካራ ሰው ተጽዕኖ ጠንካራ ነገርን ይሰራል፡፡ ”

እንግዲህ እንደዚህ ባለ ጉዞ እና አስገራሚ ሁኔታ ነው እስክንድር፣ ርዕዮት እና ሌሎች አይበገሬ የዓላማ ጽናት ሰዎች በወንጀለኛው የመለስ ዜናዊ እስር ቤት ሆነው እየታገሉ ያሉት፡፡ ያላቸውን ታላቅ የጽናት ስጦታ በመጠቀም እና ለቀሪዎቻችንም በማካፈል በጽናት በመቆም ዓለምን ከጨለማው ወደ ብርሀኑ ይመልሳሉ፡፡ ገና ከመለስ ዜናዊ የጭራቅ እስር ቤት ሆድ ውስጥ ከመድረሳቸው በፊት ከታላቁ ገጸ በረከታቸው አንዱ የሆነውን ጽናትን ልከውልናል፡፡

እስክንድር እንዲህ በማለት አወጀ፣ “ከዋሻው መጨረሻ ያለውን ብርሀን ለማየት እኖራለሁ፡፡“ እስክንድር እና የህሊና የእስር ቤት ጓደኞቹ ረዥሙን እና አድካሚውን ጉዟቸውን ከጨለማው ዓለም ወደ ብርሀኑ ዓለም በማድረግ በስኬት ያጠናቅቃሉ፡፡ እንግዲህ ይህ ነው የሁሉም ጀግኖች እና ጀግኒቶች የተቀደሰ ዕድል እና ዓላማ፡፡

ህወሀት በኢትዮጵያ ጋዜጠኞች እና ጦማሪያን ላይ የከፈተው የጦርነት ዘመቻ እራሱ በእውነት ላይ የተደረገ የጦርነት ዘመቻ ነው፡፡ ላለፉት 23 ዓመታት ህወሀት በሁሉም ጦርነቶች እና አጫጭር ግጭቶች አሸናፊ ሆኖ ቆይቷል፡፡ ሆኖም ግን ጎራዴዎችን እና AK47 ጠብ መንጃዎችን በታጠቁት ወሮበላ አምባገነኖች እና በተማሩ ጋዜጠኞች እና ብዕሮቻቸውን እና የኮምፒውተር መክፈቻ ቆፎቻቸውን ብቻ በሚጠቀሙ ጦማሪያን መካከል የሚደረገው የመጨረሻ እና ወሳኝ ጦርነት ይደረጋል፡፡ ያ ጦርነት በኢትዮጵያ ህዝብ ልብ እና አዕምሮ ውስጥ ነው፣ እንደዚሁም በዚሁ መልኩ ወደፊትም ይቀጥላል፡፡ ምንም ይሁን ምን የዚያ ጦርነት ውጤቱ የተቀደሰ እንደሚሆን ምንም ዓይነት ጥርጥር የለኝም፡፡ በእርግጥ ያ ጦርነት በአሁኑ ወቅት አሸናፊነትን ተቀዳጅቷል፡፡ ኤድዋርድ ቡለዌር ሊቶን በግጥም ስንኞቻቸው በግልጽ እንዳስቀመጡት በጎራዴ ታጣቂዎች እና በብዕር ተኳሾች መካከል በሚደረግ የጦርነት ፍልሚያ የመጨረሻ ድሉ የሚሄደው ወደ ብዕር ተኳሾች ነው ብለዋል፡፡

እውነት መሰረት ነው እንደዚህ ነው የምል፣

ገዥዎች በጉልበት ሁሉን ለመጠቅለል፣

ምለው ተገዝተው ህዝብን ለመበደል፡፡

መሳሪያ ቢያንጋጉ ላውንቸሩን መውዜር፣

በሰማይ ቢበሩ ቢናውዙ በምድር፣

በባህር ቢቀዝፉ ህዝብን ለማሸበር፡፡

ለጊዜው ድንፋታን በጥቅም ላይ ቢያውል፣

መሳሪያ ኃይል ሆኖ አያበቃም ለድል፣

ብዕር ከጎራዴ ያይላል፣ አስተውል፡፡

ጭራቆች ቢስቁ፣

ወሬን ቢሰልቁ፣

ፍትህን ላያውቁ፣

ህዝብን ለመጨረስ

በምኞት አለቁ፡፡

መሰረቱን ሰርቶ ባዶ ጩኸታቸው፣

ህዝብን ለመበደል ሆኖ ዓላማቸው፣

ሌት ከቀን ቢለፉ በነቀዘ አፋቸው፣

ውድቀትን ካልሆነ ድል አይታያቸው፡፡

ስለዚህ ጭቁኖች ታምርን በመስራት፣

ጭራቅ ቄሳሮችን በወኔ በመርታት፣

የእምብተኝነትን አመጽ በማስነሳት፣

ነጻነትን በሉ የህዝቦች አድርጓት፡፡

ስለዚህ ታላቁ፣

የሀሰት ስላቁ፣

ጀብደኝነት ስንቁ፣

ነጻነት እሩቁ፣

ሸፍጠኝነት ወርቁ፣

ከሀዲነት ብርቁ፣

ከርሳምነት እንቁ፡፡

እንደ ጠዋት ጤዛ በኖ እንደሚጠፋ፣

ቀልቀሎ አቁማዳ ባየር የተነፋ፣

ጠበቅ ሲያደርጉት በራሱ ላይ ከፋ፡፡

ስለዚህ ታላቁን የይስሙላ ስሙን፣

በብዕር ምቱ እና ቀሙት ጎራዴውን፣

በዓለም ህዝቦች ሁሉ ሰላም እንዲሰፍን፡፡

ከዚያማ በዓለም ላይ በሰው ልጆች ሁሉ፣

በጎራዴ ማመን ይቀራል በሁሉ፡፡

ብዕር አሸናፊ የሰው ልጆች ማማ፣

ለአምባገነን እሬት ለጭቁኖች አርማ፣

የስልጣኔ አርማ የምሁራን ጫማ፣

ክላሽንኮብ መውዜር ታንክ ሳይሰማራ፣

በጉልበት ሳያምን ብዕርን ከጠራ፣

መንግስት ይጠበቃል ማንንም ሳይፈራ፡፡

ጽናት ለእኔ ምን ማለት እንደሆነ፣

በርካታ ኢትዮጵያውያን ውንድሞቸ እና አትዮጵያውያት እህቶቸ እራሳቸውን እንዲህ በማለት ይጠይቃሉ፣ “የትግላችንን ፍሬ እስከምናይ ድረስ ምን ያህል ጊዜ መታገል አለብን?” እኔ ደግሞ እራሴን እንዲህ በማለት እጠይቃለሁ፣ “ምን ያህል ጊዜ…?“  ሌሎች ደግሞ እንዲህ በማለት ይጠቁኛል፣ “በስልጣን ላይ ላሉት እና ስልጣናቸውን ከህግባብ ውጭ በሚጠቀሙት አምባገነኖች ላይ እውነቱን በመጻፍ እና በመንገር ለምን ያህል ጊዜ ትቆያለህ? እስከ አሁን አልደከመህምን?“

በኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት ላይ ትግል የሚያደርጉ ጥቂት ሰዎች የችግሩን አስቸጋሪነት ከግንዛቤ በማስገባት ሽንፈታቸውን አምነው ተቀብለዋል፡፡ ጎማቸውን እያሽከረከሩ እንደሆነ ይሰማቸዋል፡፡ ሆኖም ግን እንዲህ በማለት እነግራቸዋለሁ፣ “ጠበቅ አድርጋችሁ ያዙ! ለጥቲት ጊዜ ያህል፡፡“ አምባገነኖችን ለማንበርከክ ለነጻነት እና ለዴሞክራሲ የሚደረገው ትግል የ26 ማይል የማራቶን እሩጫ እንጅ የ100 ሜትር የአጭር ርቀት ሩጫ አይደለም በማለት እነግራቸዋለሁ፡፡ እ.ኤ.አ ሜይ 2011 “በኢትዮጵያ ለነጻነት የሚደረግ ታላቁ እሩጫ” በሚል ርዕስ ትችት አቅርቤ ነበር፡፡ በዚያ ትችት ላይ የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች እና ወትዋቾች፣ የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች እና ሌሎች እልህ አስጨራሽ የሆነውን የማራቶን እሩጫ በጽናት እና በድል አድራጊነት ለማጠናቀቅ ማራቶን ሯጮቻችን በጽናት እና በወኔ መቆም እንዳለባቸው እንዲህ በማለት ተናግሬ ነበር፡፡

…ለነጻነት የሚደረግ የ10 ኪሎ ሜትር ሩጫ ለረዥሙ እና በጣም አስቸጋሪ ለሆነው የማራቶን ሩጫ የመጀመሪያው ክፍያ እንጅ አጠቃላይ ሙሉ ክፍያ አይደለም፡፡ ለዚህም ነው እያንዳንዳችን ልዩ የሆነውን ጽናት የሚለውን የማራቶን ሩጫን ማጎልበት ያለብን፡፡

የማራቶን ሯጯ ገና ሩጫዋን ስትጀምር እስከ ሩጫው ማጠናቀቂያው መስመር ድረስ ያለው ርቀት ታላቅ ጥረትን የሚጠይቅ እና በጣም አድካሚ እንደሆነ ታውቃለች፡፡ ሆኖም ግን ረዥሙን የማራቶን ሩጫ እንዴት አድርጋ ሮጣ ማሸነፍ እንዳለባት ቅድመ ዝግጅት ታደርጋለች፡፡ የማራቶን ሯጭ እንዲህ አይልም፣ ‘እጅግ በጣም ረዥም ነው…በጣም አስቸጋሪ ነው…እኔ በፍጹም ላደርገው አልችልም’ የአሸናፊነት ስነልቦናን ሰንቆ ይገባል እንጅ እሸነፋለሁ በማለት ሞራሉን ገድሎ ወደ ሩጫው አይገባም፡፡ ያለውን እምቅ ኃይል እየመጠነ እና እየለካ እርሱን በአንድ ጊዜ እንዲደክም እና ተስፋ እንዲቆርጥ በሚያደርግ መልኩ ሳይሆን ይልቁንም ከዚያ በተለዬ መልኩ እያበረታ እና በተስፋ እየተሞላ ለአጠቃላይ አሸናፊነት የሚያበቃውን የአሯሯጥ ዘዴ መርጦ በተግባር ይተገብራል፡፡ የማራቶን ሯጭ እያንዳንዱን እርምጃ እንዴት አድርጎ በመወንጨፍ ለድል ሊበቃ እንደሚችል አስቀድሞ ዕቅድ ያወጣል፡፡

የርቀት ሯጯ በቀሪዎቹ የማራቶን ርቀቶች ላይ እራሷን አታስጨንቅም ይልቁንም በቀጣይነት ስለምትራመደው፣ ከፊት ለፊቷ ስለሚጠብቃት ተራራ እና በቀጣይነት ስለምትሮጠው ጠመዝማዛ መንገድ እና ሩጫውን እስከምታጠናቅቅበት ድረስ ላለው ዕቅድ ነው እራሷን የምታዘጋጀው እና ኃይሏን እና ሀሳቧን ሁሉ የምታውለው፡፡ ጥቂቶቻችን የማራቶን ሩጫው 10 ኪሎ ሜትሮች እንዲሆኑ እና በአንድ ጊዜ በፍጥነት ሮጠን ከማጠናቀቂያው መስመር ላይ ለመድረስ እንፈልጋለን፡፡ በረዥም ርቀት ሩጫ ላይ ተስፋ የመቁረጥ እና እራሳችንን ዝቅ አድርገን የማየት ሁኔታን እናንጸባርቃለን፡፡ ገና ስናስበው በጣም የድካም ስሜት ይሰማን እና አንዷንም እርምጃ ሳንሰነዝር በዝረራ ሩጫውን ጥለን እንወጣለን፡፡ ሆኖም ግን ለነጻነት የሚደረግ የማራቶን ሩጫ የማጠናቀቂያ መስመር የለውም፡፡ ማንዴላ “አንድን ታላቅ ተራራ ከወጣን በኋላ ሌሎች በርካታ ተራሮችን መውጣት ይጠበቅብናል” እንዳሉት ማለት ነው፡፡

ማራቶንን መሮጥ እና አንድ ተራራ ብቻ በመውጣት ሌሎች ሊወጡ የሚችሉ በርካታ ተራሮች እንዳሉ አስቀድሞ ማወቅ እና በልበሙሉነት በመሮጥ ከማጠናቀቂያው መስመር መድረስ መቻል ነው እንግዲህ ለእኔ ጽናት ማለት! ሌሎች ተራሮች እስካለቁ ድረስ ተራሮችን መውጣት እና ሌሎች ያልተጠናቀቁ ተራሮች የሌሉን መሆናቸውን ማረጋገጥ ይጠበቅብናል!

ወደኋላ አናፈገፍግም፣ እናም በጽናት እንቆማለን! አይበገሬ እንሆናለን! ድል እናደርጋለን!

በመለስ ዜናዊ የማጎሪያ እስር ቤት በመማቀቅ ላይ ለሚገኙት ጀግኖች እና ጀግኒቶች ልቤ ይሰበራል፣ የደረት ውጋትም ይሆንብኛል፡፡ እስክንድር በግፍ የ18 ዓመታት እስራት ተፈርዶበት በመለስ ዜናዊ እስር ቤት በመማቀቅ ላይ የመገኘቱ ሁኔታ ልቤ እንዲሰበር አድርጎኛል፡፡ ሆኖም ግን እስክንድር ምንም የማይፈራ ደፋር መንፈሰ ጠንካራ የማያጎነብስ በመሆኑ ልቤ በደስታ ይሞላል፡፡ ርዕዮት በመለስ ዜናዊ የማጎሪያ እስር ቤት ሌት እና ቀን በመማቀቅ ላይ መሆኗን ባስታወስኩ ቁጥር ልቤ ይሰበራል፡፡ ሆኖም ግን ክብሯን እና ነጻነቷን ለመግፈፍ ከሚቋምጡት አሳሪዎቿ እኩይ ሀሳብ ከመንበርከክ እና ቅጣቷን ከመቀበል ይልቅ በዓላማ ጽናቷ በመግፋት የምታሳየውን የአይበገሬነት ጽናት ስመለከት ሞራሌ ከፍ ይላል፡፡

በኢትዮጵያ ያሉትን ጅግኖች እና ጀግኒቶች የፖለቲካ እስረኞችን አከብራቸዋለሁ፣ አወድሳቸዋለሁም፡፡ ለወገኖቻቸው ለኢትዮጵያ ህዝብ ሲሉ እየከፈሉት ላለው መስዋዕትነት እና እያሳዩት ላለው የዓላማ ጽናት የሚያነቃቃኝ በመሆኑ እጅግ በጣም ተደስቻለሁ አመሰግናቸዋለሁ፡፡ የዓላማ ጽናቴ የበለጠ እንዲጠነክር አድርገዋል፣ እናም እየከፈሉት ያለውን መስዋዕትነት እንዳስብ እና እንድዘክር የበለጠ የመንፈስ ጥንካሬ እና ስንቅ እንዲሆነኝ አድርገዋል፡፡  የእነርሱን ድፍረት፣ ጠንካራ የሞራል ተስፋ፣ ጽናት፣ የዓላማ ጥንካሬ እና አይበገሬነት ብቻ አደንቃለሁ የእኔ ባህሪም እንዲሆኑ አደርጋለሁ፡፡ የእነርሱን ጽናት ለማግኘት እጓጓለሁ፡፡ እነዚህን ጀግኖች እና ጀግኒቶች ከልብ በመነጨ መልኩ አመሰግናቸዋለሁ፣ አወድሳቸዋለሁ፡፡

እስክንድር ጥልቅ በሆነ ፍልስፍናዊ የአነጋገር አንደበቱ እንዲህ በማለት ጽፎ ነበር፣ “ በጽናት እቆማለሁ!“ ይህንን ፈላስፋዊ አነጋገር ሁልጊዜ በምንግባባበት የተለመደው የዘወትር ቋንቋ ዘርዘር አድርጌ ስመለከተው እስክንድር በቀጥታ ቶም ፔቲ እና “አላፈገፍግም” የሚሉትን ልብ ሰባሪ ግጥሞቹን ሆኖ ነው ያገኘሁት፡፡

እወቅ አንተ ጭራቅ  አላፈገፍግም፣

ከገባሁበት ማጥ አንድ ጋት አልርቅም፡፡

ሳላንበረክክህ ከእነርኩስ መንፈስህ፣

ቃል ለምድር ለሰማይ እውነት ነው እምልህ፣

ተመልሸ አልወጣም ከማጎሪያው ቤትህ፡፡

ማፈግፈግ ማፈግፈግ ፍጹም አታስባት፣

አፈር ትበላለህ በእኔ መስዋዕትነት፡፡

እንጦረጦስ ወርደህ ከነጉግ ማንጉግህ፣

የህዝብ ነጻነት ያበራል በቀብርህ፡፡

ከጋነም ከበሩ ማቆም ትችላለህ፣

መግረፍ ማሰቃዬት መግደል ትችላለህ፣

ሆኖም ግን ከግብሬ ከዓላማዬ ቀርቶ፣

መመለስ ይቅር እና ፊቴ አይዞረም ከቶ፣

አንተን ሳያደባይ ካለህበት ገብቶ፡፡

በዓላማ ጸንቼ፣

ሩቅ ተመልክቼ፣

ለፍትህ ጓጉቼ፣

ጽናትን አንግቼ፣

ለነጻነት ሞቼ፣

ሳልገለባበጥ እንደባህር ዓሳ፣

በጽናት ታግዬ እንደ ጫካ አንበሳ፣

ቁርስ መብላት ሳይሆነ አልሜ ለምሳ፣

ሽንፈት ትጋታለህ ብትወድቅ ብትነሳ፡፡

ዓላማዬ አንድ ነው ዓለምን መጠበቅ፣

ከጭራቅ ድሁሮች ከአምባገነን መብረቅ፣

ከግፈኞች ጉያ ተምዘግዝጋ እንዳትወድቅ፡፡

ስለዚህ በጽናት እቆማለሁ ዳግም፣

ላምባገነን ጨካኝ አላጎብስም፣

ጭራቃዊ መንፈስ ከዓለም እስኪወድም፣

ፍትህ በአደባባይ እስከምትለመልም…

ወደኋላ አናፈገፍግም! ለዓላማችን በአይበገሬነት እንቆማለን! በጽናት እንቆማለን! አይበገሬ እንሆናለን! በመራራው ትግላችን በድል አድራጊነት ድልን እንቀዳጃለን!

በመላው ዓለም የምትገኙ አንባቢዎቼ ሁሉ አዲሱ የፈረንጆች ዓመት የደስታ እና የብልጽግና እንዲሆንላችሁ እመኛለሁ… በ2015 አዲሱ ዓመት ኃይሉ እና ድሉ ሁሉ ከእናንተ ጋር እንዲሆን እመኛለሁ!

ያለው ኃይል ሁሉ ከድል አድራጊዎቹ ከኢትዮጵያ የፖለቲካ እስረኞች ጋር እንዲሆን እመኛለሁ!

ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!

ታህሳስ 24 ቀን 2007 .

 

Leave a Reply