የካስትሮ ወንድሞች፣ የአፍሪካ ወንድሞች እና ወንድም ኦባማ

ከፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማርያም
ትርጉም በነጻነት ለሀገሬ

ኩባ በመጨረሻ ከቀዝቃዛው ጦርነት በአሸናፊነት ወጣችን?

እ.ኤ.አ ጃኗሪ 1959 ፕሬዚዳንት ፉልገንሲዮ ባቲስታንን ከስልጣን ካባረሩ በኋላ በሰጡት ቃለ መጠይቅ ካስትሮ እንዲህ ብለው ነበር፣ “አምባገነን አይደለሁም፣ ወደፊትም እሆናለሁ ብዬ አላስብም፡፡ በጠብመንጃ ኃይል ስልጣንን አልይዝም”፡፡ በዚያ መግለጫ መሰረት ካስትሮ ኩባ ከምዕራቡ ዓለም የመጀመሪያዋ ኮሙኒስት መንግስት እንድትሆን አደረጉ፡፡ ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ የካስትሮ ወንድሞች፣ ፊደል እና ወንድማቸው ራውል ኮሙኒስት ኩባን እንደ ብረት ቀጥቅጠው እንደ ሰም አቅልጠው በጠብመንጃ አፈሙዝ አንበርክከው ገዝተዋል፡፡The Castro Brothers, the African Brothers and Brother Obama

እ.ኤ.አ ኦክቶበር 1960 ዩናይትድ ስቴትስ በኩሙኒስት ኩባ ላይ የመጀመሪያውን እቀባ ጣለች፡፡ እ.ኤ.አ ጃኗሪ 3/1961 ዩናይትድ ስቴትስ በሀቫና የሚገኘውን ኤምባሲዋን በመዝጋት ከካስትሮ መንግስት ጋር የነበራትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት አቋረጠች፡፡ ዩናይትድ ስቴትስ በኩባ ላይ ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ የተለያዩ የኢኮኖሚ ማዕቀቦቸን የጉዞ እና የንግድ ክልከላን ጨምሮ በኩባ ህዝብ ላይ ማቆሚያ የሌለው መከራን ጥላ ቆይታለች፡፡

እ.ኤ.አ ዴሴምበር 17/2014 ከሀምሳ ሶስት ዓመታት በኋላ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ዩናይትድ ስቴትስ ከኩባ ጋራ የነበራትን ሙሉ የዲፕሎማሲ ግንኙነቶችን ቀድሞ ወደነበሩበት ደረጃ ትመልሳለች በማለት አስታውቀዋል፡፡ ከኋይት ሀውስ በወጣ የብሄራዊ የቴሌቪዥን መግለጫ ኦባማ እንዲህ ብለዋል፣ “ለበርካታ አስርት ዓመታት ያህል የዘለቀውን ኋላ ቀር አካሄድ በማቆም በሁለቱ ሀገሮች መካከል ጤናማ ግንኙነት እንመሰርታለን…እነዚህ ሀምሳ ዓመታት ገለልተኝነት እና ተነጥሎ መኖር የማይሰራ መሆኑን በግልጽ የሚያመላክቱ ተጨባጭ ማስረጃዎች ናቸው፡፡ እናም አዲስ ግንኙነት መመስረቻው ጊዜው አሁን ነው፡፡ ለሌላ አምስት ተጨማሪ አስርት ዓመታት እስከ አሁን በቆየንበት መልኩ በመቀጠል የተለዬ ውጤት ይመጣል የሚል እምነት የለኝም፡፡“ ኦባማ በአሁኑ ጊዜ በተለይም ኃይልን ለመጠቀም የሚፈልጉ ቡድኖች ከበር ላይ ቆመው አሰፍስፈው እየተመለከቱ፣ የእጆቻቸውን መዳፎች እያሻሹ እና በዩናይትድ ሰቴትስ ላይ ጉዳት ለማድረስ መንጋጋዎቻቸውን እያንገጫገጩ ባሉበት ሁኔታ ኦባማ ይህንን ጉዳይ ወደ ዩኤስ ሴኔት በማቅረብ ከኩባ ጋር የሚኖራቸውን ግንኑነት ቀድሞ ወደነበረበት ቦታ ለመመለስ ይህንን ጊዜ ለምን እንደመረጡ አስገርሞኛል፡፡ ኦባማ የእርሳቸው ፓርቲ የሴኔቱን መቀመጫ ከተቆጣጠረበት ጊዜ ጀምሮ ይህንን ኋላቀር አካሄድ ያሉትን ግንኙነት በመቀየር ከኩባ ጋር ቀድሞ ወደነበረበት የዲፕሎማሲ ግንኙነት ለመመለስ የሚያስችሉ ስድስት የስልጣን ዓመታት ነበሯቸው፡፡ ኦባማ የፕሬዚዳንትነት ጊዚያቸው እየተገባደደ በመጣበት በአሁኑ ወቅት ዩናይትድ ስቴትስ ከኩባ ጋር ያላትን የዲፕሎማሲ ግንኙነት ቀድሞ ወደነበረበት መመለስ የሚል መግለጫ ማውጣታቸው አድናቆትን ለማግኘት እና በህዝብ ዘንድ ትኩረትን በመሳብ ዝናን ለመጎናጸፍ አስበው ነውን? የሪፐብሊካን ኮንግረስ የሴኔቱን መቀመጫዎች ለመቆጣጠር እየተቃረበ በመጣበት ወቅት ኦባማ ዓይናችሁን ጨፍኑ እና ላሞኛችሁ የሚባለውን ጨዋታ በመጫወት ላይ ናቸውን? ኦባማ በአሸዋ ላይ መስመር በማስመር ሬፐብሊካኖች በጫጫታ እና ጭቅጭቅ አስቸጋሪ ሁኔታ በሚገቡበት ጊዜ እርሳቸው በቀረቻቸው ሁለት ዓመታት ጊዜ ውስጥ በግል ፕሬዚደንታዊ ትዕዛዝ እያስፈጸሙ የሚፈልጉትን ሁሉ ለማድረግ የዘየዱት ዘዴ ነውን? ወይስ ለስልጣን የሚቋምጡትን ሪፐብሊካንን ሀሳብ ለማስቀየስ የተጠቀሙበት የማታለያ ስልት ነው? ወይስ ደግሞ ፕሬዚደንታዊ ትዕዛዝ እያዘዙ ማስፈጸም መቻላቸውን እንድንገነዘብላቸው ፈልገው ነው? በእርግጥ ኦባማ ስልጣናቸውን ሊያስረክቡ ሁለት ዓመታት ብቻ ሲቀሯቸው ይህንን ማድረጋቸው እራሳቸውን እንደገና በማደራጀት የማይበገሩት ኦባማ ለመባል ፈልገው ነውን?

እ.ኤ.አ በ1961 የዩኤስ ጠቅላይ ፍርድ ቤት (ዩኤስ ከኩርቲስ መብት ጋር) የዩኤስ ፕሬዚዳንት የውጭ ግንኙነት ስራዎችን ለማከናወን ትልቅ ስልጣን እንዳለው አጽንኦ በመስጠት ደምድሟል፡፡ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ይህንኑ ጉዳይ በማስመልከት እንዲህ ይላል፣ “በውጭ ግንኙነት ጉዳዮች ላይ ፕሬዚዳንቱ ብቸኛው የሀገሪቱ አካል ነው፣ እንደዚሁም ፕሬዚዳንቱ ብቻ የሚወክሉት ሰው ከውጭ ሀገሮች ጋር ለሚደረጉ ግንኙነቶች ሙሉ ስልጣን አለው፡፡“ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ለፕሬዚዳንቱ የሰጠው ስምምነቶችን የመዋዋል እና ጦርነት የማወጅ ብቸኛ ስልጣን ለፕሬዚዳንቱ ጠቃሚ እና ለውጭ ግንኙነት ስራ ልዩ የሆነ ስልጣንን ያጎናጽፋል፡፡ እ.ኤ.አ በ9/11/11 በዩኤስ አሜሪካ ላይ የተደረገውን ጥቃት ተከትሎ የዩኤስ የፍትህ መምሪያ በውስጥ መጻጻፊያ ማስታወሻ እንደገለጸው በውጭ ጉዳዮች ዙሪያ ፕሬዚዳንቱ የሀገሪቱ ዋና ኃላፊ እና በህገ መንግስቱም ሙሉ በሙሉ እውቅና ያለው እንደሆነ አስቀምጧል፡፡

ባለፈው ዓመት ፕሬዚዳንት ኦባማ በወጭ ቅነሳ ረገድ የኮንግረሱ ቀና ትብብር አለመኖርን አስመልከቶ የተሰማቸውን ስጋት እንዲህ በማለት ገልጸው ነበር፣ “አምባገነን አይደለሁም፣ ፕሬዚዳንት ነኝ፣ ንጉስ አይደለሁም፡፡“ፕሬዚዳንቱ የሀገሪቱ የውጭ ግንኙነት ዋና ኃላፊ መሆን እና የእርሳቸው ወኪል ለውጭ መንግስታት ብቸኛ ተጠሪ የመሆን እውነታ እርሳቸውን አምባገነን ወይም ደግሞ ንጉስ ሊያደርጋቸው ይችላልን?

እንደ ህገ መንግስት የህግ ባለሙያ ፕሬዚዳንት ኦባማ ከኩባ ጋር የነበረው ግንኙት ቀድሞ ወደነበረበት እንዲመለስ በወሰኑት ድርጊት ላይ ሙያዊ አስተያየት ለመስጠት ታላቅ ፍላጎት አለኝ፡፡ አደገኛ ሁኔታ ሊያስከትሉ የሚችሉትን የህገመንግስት እና መንግስታዊ የሆኑ አወዛጋቢ ጉዳዮችን በጥንቃቄ እያሰቡ መራመድ ይኖርባቸዋል፡፡

ኩባን ከሀምሳ ዓመታት በላይ እንድትገለል አድርገው የቆዩት ቀጥተኛ የሆኑ ስድስት ህጎች ማለትም፡ 1ኛ) ከጠላት ሀገር ጋር የሚደረግ በ1917 የተደነገገው የንግድ እንቅስቃሴ (ከዩናይትድ ስቴትስ ጋር የጠላትነት ስሜት ከሚያንጸባርቁ ሀገሮች ጋር የንግድ ልውውጥ እንዳይደረግ የሚወስን)፣ 2ኛ) እ.ኤ.አ በ1933 የተደነገገው የአስቸኳይ የባንክ እርዳታ (በዩናይትድ ስቴትስ እና በኩባ መካከል የሚደረግ የውጭ ምንዛሬ ልውወጥ እና የባንክ አገልግሎት በሁለቱ የፋይናንስ ተቋማት መካከል እንዳይደረግ የተቋረጠ ስለመሆኑ)፣ 3ኛ) የውጭ እርዳታን አስመልክቶ የወጣው የ1961 ድንጋጌ (ከኩባ ጋር የንግድ ልውውጥ እንዳይደረግ ለዩኤስ ፕሬዚዳንት የተሰጠው ሙሉ ስልጣን)፣ 4ኛ) የኩባን ሀብት ለመቆጣጠር በ1963 የወጣው ደንብ (ከኩባ ጉዞ ጋር በተያያዘ መልኩ ከሚደረጉ የንግድ እቅስቃሴዎች መታቀብ)፣ 5ኛ) እ.ኤ.አ በ1992 የወጣው የኩባ ዴሞክራሲ ድንጋጌ (መሰረቱን በውጭ ያደረገ የዩኤስ ድርጅት ቅርንጫፍ፣ የንግድ ኩባንያዎች ከኩባ ጋር የንግድ ልውውጥ እንዳያድርጉ እንዲሁም የዩኤስ ዜግነት ያላቸው እና ቤተሰቦቻቸው ወደ ኩባ ሬሚታንስ እንዳይልኩ)፣ 6ኛ) የሄልምስ ቡርቶን የ1996 ድንጋጌ (የዩናይትድ ስቴትስ ዜጎች በኩባ ውስጥ ቢዝነስ እንዳይሰሩ እና በኩባ መንግስት ላይ የተጣሉት ቅድመ ሁኔታዎች እስካልተሟሉ ድረስ በሀገርም ሆነ በግል ደረጃ በሐቫና ለሚቀያየሩ መንግስታት ምንም ዓይነት እገዛ እንዳያደርጉ እና የንግድ ማዕቀብ ማሻሻያ እና ወደ ውጭ የሚወጡ ምርቶች የ2000 ድንጋጌ (ወደ ኩባ የሚላኩ ምርቶች በጥሬ ገንዘብ ብቻ ከፍያ እንዲፈጸም እና ከፍያውም በሀገሪቱ በእራሷ ብቻ መፈጸም እንዳለበት፣ እንዲሁም የብድር እና እዳ አገልግሎት የተከለከለ መሆኑን) የመሳሰሉት በህግ የተደነገጉ ጉዳዮች በምን መልክ እንዲተገበሩ ነው መላ የተዘየደው? ፕሬዚዳንት ኦባማ ከዚህ በላይ የተዘረዘሩትን ህጎች በእራሳቸው መንግስትን የማዘዝ ስልጣናቸውን ተጠቅመው ከምንም አለመቁጠር እና መተው ይችላሉን?

ከኩባ ጋር ሙሉ የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለመመስረት ፕሬዚዳንት ኦባማ በአንቀጽ 2 ክፍል 2 ላይ የዩኤስ ህገመንግስት ለእጩ አምባሳደሮች “ምክር እና ስምምነት” መስጠት አለበት የሚለውን ከሴኔቱ ጋር ተወያይተው መፍታት ይኖርባቸዋል፡፡ እጩ አምባሳደራቸው በሴኔቱ ጸድቆ እስኪመጣ ድረስ ተደጋግሞ እንደሚነገረው ተረት ኦባማ የእንጨት እግር ያለው እና የሰደዱን እሳት ለማምለጥ እንደሚሞክረው ሰው ዓይነት ሆነው ይቆያሉ፡፡ የመጨረሻ ሆኖም ግን ጠቃሚ የሆነው ነጥብ የአሸባሪነት ድጋፍ ከሚሰጡ ሀገሮች ስም ዝርዝር መካከል ኩባን ነጥለው እንዲያወጡ ፕሬዚዳንት ኦባማ ለውጭ ጉዳይ ሚኒስትራቸው ትዕዛዝ ይሰጡ ይሆን? ኩባን አሸባሪ ቡድኖችን ከሚረዱ መንግስታት ስም ዝርዝር ውስጥ ለማስወጣት ያለውን የህግ አመክንዮ ለማወቅ ታላቅ ጉጉት አለኝ! ለሴቷ ዳክዬ (ኩባ) ጥሩ የሆነው ነገር ሁሉ ለወንዱ ዳክዬም (ኢራን፣ ሶሪያ፣ እና ሰሜን ኮሪያ [እ.ኤ. በ2008 በኒኩላር ውዝገብ ሰበብ ማዕቀብ የተጣለባቸው] ጥሩ ነው)፡፡

በምዕራብ ሄሚስፌር የውጭ ግንኙነት ኮሚቴ ንኡስ ኮሚቴ ሊቀመንበር ይሆናሉ ተብለው የሚገመቱት እና የሬፐብሊካን የፍሎሪካ ሴናተር ማርኮ ሩቢዮ ከኩባ የነበረው ግንኙነት ቀድሞ ወደነበረበት ሁኔታ ይመለሳል የሚለውን ሙከራ በመሞገት እንዲህ የሚል መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

“ማንኛውንም ነገር ለማድረግ ዝግጁ ነኝ፣ በታቻለ መጠን የሚደረጉትን ማንኛቸውንም ዓይነት ለውጦች ሁሉ ግልጽ እንዲሆኑ አደርጋሉ፡፡“ ይህ ኮንግረስ የተጣለውን ማዕቀብ ሊያነሳ አይችልም፡፡ የኩባ አሜሪካዊ ዜግነት ያላቸው ሩቢዮ ከዚህም በተጨማሪ እንዲህ ብለዋል፣ “የኩባ የዴሞክራሲ ወትዋቾች በኦባማ ክህደት እንደተፈጸመባቸው ሊሰማቸው ይገባል፡፡ ኦባማ እነርሱን ሙሉ በሙሉ ትተዋቸዋል እናም ከዚህ ጉዳይ ጋር በተያያዘ መልኩ ከአጠቃላይ ሂደቱ ወደ ጎን ገፍትረዋቸዋል“፡፡ ይህንንም ለማለት የሚያስችለው አንደኛ ሩቢዮ ምን ሊሰማቸው እንደሚችል በእርግጠኝነት አውቃለሁ፡፡ እንደ ኢትዮጵያ-አሜሪካዊ የሰብአዊ መብት ተሟጋችነቴ እኔም እንደዚሁ በኦባማ ክህደት እንደተፈጸመ ይሰማኛል፡፡ በሁሉቱም የምርጫ ወቅቶች የአሜሪካ ዋና አዛዥ ቆሮ እንዲሆኑ ኦባማን በሙሉ ልብ የደገፍኩ ብሆንም ቅሉ በጠበቅሁት መልኩ ሳይሆን የአሜሪካ ዋና ዲፕሎክራት ሆነው ስላገኘኋቸው በጣም አዝኛለሁ፡፡ (ዲፕሎክራት የሚለውን ቃል በአሜሪካ የሰብአዊ መብት ጥበቃ ዲፕሎማሲ አስመሳይነት የሚለውን ለመግለጽ የተጠቀምኩበት ነው፡፡) ኦባማ እንዲህ በሚለው ንግግራቸው አምኛቸው እና ተማምኘባቸው ነበር፣ “ምንም ዓይነት ስህተት እንዳትሰሩ፡ ታሪክ ከእነዚህ ጀግኖች አፍሪካውያን/ት ጎን ነው፣ እናም ስልጣንን በኃይል በመፈንቅለ መንግስት በመጠቀም ለመያዝ የሚሞክሩ ወይም ደግሞ በስልጣናቸው ላይ ለመቆየት ሲሉ ብቻ ህገመንግስትን ከሚያሻሽሉ ሸፍጠኞች ጎን አይደለም፡፡“ ንግግራቸው ደስ የሚል ቢሆንም ባዶ እና በተግባር የማይገለጽ የውሸት ቀረርቶ በመሆኑ አፌን በዳቦ ብያለሁ፡፡ ሆኖም ግን ከኦባማ ጎን በመቆሜ ታላቅ ስህተት ሰርቻለሁ!

ሁለተኛ ነገር ለሩቢዮ ታላቅ መደነቅን ፈጥሯል! እኒህ ፕሬዚዳንት በኩባ ላይ ተጥሎ የቆዬውን ማዕቀብ ለማንሳት ብቻ የተዘጋጁ አይደሉም፣ ሆኖም ግን በተለያየ መልኩ አሁንም እየተገበሩት የሚገኙ መሆናቸው ነው፡፡ ፕሬዚዳንቱ በኡሁኑ ወቅት በስራ ላይ ያሉትን ህጎች ሆን ብለው በማታለል እና በመዝለል ከኩባ ጋር በተያያዘ መልኩ በጉዞ፣ በንግድ፣ እና በገንዘብ እንቅስቃሴዎች ላይ ተጥሎ የነበረውን ማዕቀብ በፍጥነት በማንሳት ውሳኔ ሰጥተዋል፡፡ እየጨመረ የመጣውን የግብርና ምርትን ወደ ውጭ ለመላክ የባንኮችን እንቅስቃሴ ቀልጣፋ እና ውጤታማ ለማድረግ በዩኤስ ዋና ግምጃ ቤት ወደፊት አዳዲስ ህጎች እና ደንቦች እንደሚወጡ ይጠበቃል፡፡ የዩኤስ ኩባንያዎች በመንግስት ትዕዛዝ ከዚህ ቀደም ማዕቀብ ተጥሎባቸው የነበሩትን ማሽነሪዎች፣ ልዩ ልዩ መሳሪያዎችን እና ሌሎች ቴክኖሎጅዎችን ወደኩባ ወጭ በማድረግ የንግድ ተግባራትን እንዲሰሩ ይፈቀድላቸዋል፡፡ የመንግስት መምሪያ ኩባን አሸባሪ ቡድኖችን ከሚደግፉ ሀገሮች ስምዝርዝር ውስጥ በማውጣት የህግ ማዕቀፎችን በማዘጋጀት ላይ እንደሚገኝ ይገመታል፡፡ ፕሬዚዳንቱ የኮንግረሱን ውሳኔ ወይም ማጽደቅ የማይፈልገውን ጉዳይ በማንሳት የመንግስትነት ትዕዛዝ ስልጣናቸውን በመጠቀም በሀቫና ኤምባሲ እንዲቋቋም ትዕዛዝ ሊሰጡ ይችላሉ፡፡ በይበልጥ ደግሞ በኩባ የሚገኘውን የስዊዘርላንድን ኤምባሲ የፍላጎት ክፍል ከፍ ወዳለ ደረጃ በማሸጋገር ወደተሟላ የኤምባሲ አገልግሎት ስራ ያድጋል፡፡

የካስትሮ ወንድሞች፣ የአፍሪካ ወንደሞች እና ወንድም ኦባማ፣

የሩቢዮ የኩባን ከዩኤስ አሜሪካ ጋር ያላትን ግንኙነት ወደ ቀድሞ ግንኙነት የመመለሱን ሁኔታ የመቃወማቸው አመክንዮ መረጃ ላለመስጠት በደብቅነት ወይም ደግሞ በየዋሀነት ያደረጉት ይንሁን አይሁን እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ ሩቢዮ ፕሬዚዳንት ኦባማ በየኋህነት የዩኤስን ፖሊሲ ወደ ኩባ በመቀየራቸው ይከሷቸዋል ምክንያቱም የዩኤስ ዓለም አቀፋዊ የሰብአዊ መብት ጥበቃ እና የዩኤስ አሜሪካ ብሄራዊ ደህንነት ከመጥፎ አደጋ ላይ የሚወድቅ ስለሆነ ነው፡፡ ሩቢዮ ከኩባ ጋር ያለውን የዲፕሎማሲ ግንኙነት ቀድሞ ወደነበረበት መመለስ “የአሜሪካንን ደህንነት ይቀንሳል በማለት ተንብየዋል፡፡ አሜሪካ ከእኛ ዳርቻ በ90 ማይሎች ርቀት ላይ ለምትገኘው ለግሰብ ነጻነት መወትወቷን እና የፖለቲካ እምነትን በነጻ የመግለጽ መብትን ማስከበርን ፈቃደኛ ባልሆነች ጊዜ በዓለም ላይ ለሚገኙ የተጨቆኑ ህዝቦች ሁሉ አስቸጋሪ ሁኔታን የሚያመጣ እና ተስፋ የሚያሳጣ ጉዳይ ነው…”

ሩቢኖ በአሸዋ ላይ ጭንቅላቱን እንደቀበረ ሰጎን ምንም የማያውቁ የዋህ ሊመስሉ ይችላሉ፡፡ ወንድም ኦባማ የካስትሮን ወንድሞች ፍላጎት ከማሟላታቸው ረዥም ጊዜ በፊት የአፍሪካን ወንድሞች ፍላጎት አሟልተዋል፡፡

ፕሬዚዳንት ኦባማ ፍትሀዊ እንዲሆኑ ከተፈለገ የሰውን ልጆች የማስደሰት እና ሰላማቸውን የማስጠበቅ ተግባራት ጂሚ ካርተር ከፕሬዚዳንትነታቸው ከለቀቁበት ጊዜ ጀምሮ የአሜሪካ የሰብአዊ መብት ጥበቃ ፖሊሲ የመሰረት ድንጋይ ሆነው እስከ አሁን ድረስ የዘለቁትን ማስከበር ነው፡፡ ሩቢዮ ከካስትሮ ወንድሞች ጋር ያለው ግንኙነት ወደ ቀድሞው የዲፕሎማሲ ግንኙነት መመለሱን የሚቃወሙበት ምክንያት አንድም ሆን ብለው በድንቁርና ነው አለዚያም ደግሞ ከካርካስ እስከ ቴህራን እዲሁም እስከ ፕዮንግያንግ ድረስ ያሉትን ሌሎች አምባገነኖች ለማደፋፈር ተብሎ አዛልቆ ከማየት የመጣ ግንዛቤ ነው፡፡ እውነታው በተጨባጭ ሲታይ ግን አሜሪካ ጥቂት ደም ከጠማቸው እና አረመኔ ነፍሰ ገዳይ አፍሪካውያን ወንድሞች በአፍሪካ አህጉር ከሚገኙት በአዲስ አበባ የሚገኙትን ወሮበላ አምባገነኖች ጨምሮ በሰብዊ መብት ላይ ወንጀል የፈጸሙትን በናይሮቢ የሚገኙትን አምባገነኖች፣ በኪንሻሳ የሚገኙትን የጦር ወንጀለኞች፣ ጋር የመደሰት እና አሻሸገዳሜ ማለቱን፣ በኪጋሊ ያሉትን የዘር ማጥፋት ወንጀለኞች፣ በማላቦ (ኢኳቶሪያል ጊኒ) እና በሉዋንዳ (አንጎላ) ለአስርት ዓመታት የዘለቀውን ከብዙ በጥቂቱ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

ሩቢኖ በከርከሮዎች መካከል የቁንጅና ውድድር ሊኖር እንደማይችል መገንዘብ ይኖርባቸዋል፡፡ ከካራካስ እስከ ቴህራን እና ፕዮንግያንግ ተንሰራፍተው የሚገኙትን አምባገነኖች ከአፍሪካ አቻዎቻቸው የበለጠ መጥፎዎች አይደሉም፡፡ ፕሬዚዳንት ሩዝቤልት ፍራንክሊን እንዳሉት የእኛ ጉዳዮች አይደሉም፡፡

ሩቢዮ የካስትሮን ወንድሞች ከመቃወማቸው አንጻር በተመሳሳይ መልኩ የአፍሪካን ወንድሞችም ጉዳይ ድምጻቸውን ከፍ በማድረግ መቃወም ቢችሉ ኖሮ የበለጠ ታማዕኒነትን ያተርፉ ነበር፡፡

ሩቢዮ አሜሪካ በኩባ ላይ የፖሊሲ ለውጥ በማድረጓ ምክንያት አስተማማኝ ደህንነትን ብቻ አይደለም የምታጣው ሆኖም ግን ይህ እርምጃ ለቀሪው የዓለም ክፍል የተሳሳተ ምልክትን ጭምር ያስተላልፋል ብለዋል፡፡ በሩቢዮ የመለኪያ መስፈርት መሰረት እስከ አሁንም ባላወቁት ምክንያት አሜሪካ ለበርካታ አስርት ዓመታት ያህል ደህንነቷ የተጠበቀ አይደለም፡፡ ዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ ከእኛ በ90 ማይሎች ርቀት ላይ በካሪቢያን ስለምትገኘው ሀገር ህዝቦች ስለግለሰብ የፖለቲካ አመለካከት እምነትን የመግለጽ እና ስለነጻነት መጮኹን ብቻ አይደለም ያቆመችው ሆኖም ግን በ9,000 ማይሎች ርቀት ላይ ስለምትገኘው አፍሪካም ጭምር እንጅ፡፡

ሰላም እና ደህንነት የዩኤስ የአሜሪካ የሰብአዊ መብት ፖሊሲ፣

ከካርተር የፕሬዚዳንትነት ዘመን ጀምሮ ደም የጠማቸውን ዘራፊ አምባገነኖች የሞራል ዝቅጠት የማቆም እና የሰብአዊ መብትን መደፍጠጥ የማስወገድ ጠቃሚነት ተግባር የአሜሪካ የሰብአዊ መብት ፖሊሲ የጀርባ አጥንት ሆኖ ቆይቷል፡፡ ሆኖም ግን በአሁኑ ጊዜ በእርግጠኝነት በተቃራኒው እየሆነ ያለበት ሁኔታ ነው፡፡ እ.ኤ.አ በ1981 ካርተር ባደረጉት የመሰነባበቻ ንግግር “ሰብአዊ መብት አሜሪካንን ፈጠረ” ብለው ነበር፡፡ እ.ኤ.አ ጁን 2012 በኒዮርክ ታይምስ ጋዜጣ ዓምድ ላይ በወጣ ጽሁፍ ላይ የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት የነበሩት ጂሚ ካርተር እንዲህ የሚል ማስጠንቀቂያ ሰጥተው ነበር፣ “በዓለም ላይ ጠንካራ የሆኑ አብዮቶች በሚከሰቱበት ጊዜ ዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ በሰብአዊ መብቶች ድንጋጌ ላይ በዝርዝር የሰፈሩትን መሰረታዊ የሆኑ የህግ የበላይነት መርሆዎች እና ፍትህን ማጠናከር እንጅ ማዳከም የለባትም፡፡ ሆኖም ግን ዓለምን ደህንነቷ የተጠበቀ እና ለህይወት ተስማሚ ከማድረግ ይልቅ አሜሪካ የሰብአዊ መብቶችን የማታከብር ከሆነ ይህ ድርጊት ጠላቶቻችንን የሚጠቅም ሲሆን ወዳጆቻችንን ደግሞ የሚያገል ይሆናል፡፡“

እርግጠኛ በሆነ መልኩ እራሴን እንዲህ በማለት እጠይቃለሁ፣ ደም ከጠማቸው ወሮበላ አምባገነኖች ጋር ከባለሶስት አልጋ ክፍል ውስጥ እየተኙ እና በዓለም ላይ የሚገኙ በአስር ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ህዝቦችን መከራ በማራዘም ንጹህ አየር እንዳይተነፍሱ በማድረግ “አሜሪካ የሰብአዊ መብትን መፍጠር ሳይሆን እያጠፋች ነውን?“ ካርተር በኢትዮጵያ ከሰሩት እና ካልሰሩት ስራ ጋር እ.ኤ.አ በ2005 በተደረገው ሀገር አቀፍ ምርጫ የካርተር ማዕከልን ጨምሮ የማልስማማ ብሆንም የእርሳቸው ፖሊሲዎች እና ልብ ወደ ሰብአዊ መብት ጉዳዮች ላይ ስንመጣ ከትክክለኛው ቦታ ላይ የነበሩ ስለመሆናቸው ጥያቄ የለውም፡፡

በኦባማ አስተዳደር ዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ በሰብአዊ መብት አያያዝ ወደ ኋላ ተመልሳለች፡፡ በርካታ ስሜትን የሚስቡ ሆኖም ግን የተግባር ደኃ የሆኑ ንግግሮችን በየአጋጣሚው እና በየጊዜው እንሰማለን፡፡ ከተደረጉት ዲስኩሮች መካከል ወደተግባር የሚሸጋገሩት ግን በጣም ጥቂት የሆኑት ብቻ ናቸው፡፡

ፕሬዚዳንት ኦባማ እ.ኤ.አ ጁላይ 2009 የአፍሪካን “ጠንካራ ሰዎች” በተሳሳተው የታሪክ ጎን መሰለፋቸውን በመግለጽ ለመቅጣት ወይም ደግሞ ለመዘለፍ ወደ አፍሪካ ተጉዘው ነበር፡፡ እ.ኤ.አ ኦገስት 2014 ሁሉንም የአፍሪካ ጠንካራ አምባገነን ገዥዎች (ሁለት ወይም ሶስት ብቻ ሲቀሩ) አንድ ሰብአዊ መብትን በመደፍጠጥ ወንጀል በዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ክስ ተመስርቶበት የፍርድ ሂደቱ በመታየት ላይ የነበረ አምባገነንን ጨምሮ በኋይት ሁውስ የጥሪ ግብዣ አድርገውላቸው ነበር፡፡ በኋይት ሀውስ ሰርግ እና ምላሽ አደረጉ፣ እናም ከአሜሪካ ህዝብ የሚሰበሰበውን በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር በልመና ለሚኖሩት አምባገነኖች ለመስጠት እና የታዘዙትን እዲፈጽሙ ቃል ተገብቶላቸው ተሰነባብተው ነበር፡፡

ነገሮች ገፍተው ሲመጡ እና ተጨባጩ ነገር ሲመጣ ሞራል ሲሰጡ እና ስለሰብአዊ መብት ጥበቃ ብዙ ሲደሰኩሩ የቆዩት ፕሬዚዳንት በአንድ ጊዜ እንደ ባህር ዓሳ ተገለባብጠው እራሳቸውን በተሳሳተው የታሪክ ጎን ላይ ቆመው አገኙት፡፡ ኦባማ በአፍሪካ የሰብአዊ መብት አጠባበቅ ላይ ክህደትን የፈጸሙ ስለሆኑ እና በትክክለኛው የታሪክ ጎን እያሉ በተግባር ግን ባዶ የሆነ ሁለት ምላስ ንግግር ማድረግ የሚቀናቸው ሰው ስለሆኑ በእራሳቸው ላይ ደስተኛ ያለመሆኔን “ባዶ የአፍሪካ፡ የ2014 የዩኤስ- አፍሪካ መሪዎች ጉባኤ” በሚል ርዕስ ባቀረብኩት ትችቴ ላይ በግልጽ ጠቅሻለሁ፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጆን ኬሪ አሜሪካ በዓለም ላይ ሁሉንም የሰብአዊ መብት ደፍጣጮችን ትመለከታለች በማለት ተናግረው ነበር፡፡ በእርግጥ ትመለከታለች ነው እንጅ ከተመለከተች በኋላ የሚወሰድ ምንም ዓይነት እርምጃ የለም፡፡ እ.ኤ.አ በ2013 ጆን ኬሪ የዩኤስ አሜሪካንን የሰብአዊ መብት አያያዝ ዘገባ ባቀረቡበት ጊዜ እንዲህ ብለው ነበር፣ “እነዚህ ዘገባዎች በዓለም ላይ የሚገኙ ጀግና ዜጎችን እና የእነዚህን ሰዎች ሰብአዊ መብቶች የሚደፈጥጡ አሜሪካ የምትመለከታቸውን አምባገነኖች ያሳያል…“ ማን ማንን ነው የሚመለከተው?

ለበርካታ ዓመታት የዩኤስ የሰብአዊ መብት አያያዝ ፖሊሲን ስመለከት እና የዩኤስ አሜሪካን የመንግስት መምሪያ የሰብአዊ መብት አያያዝ ዘገባዎች ሳነብ ቆይቻለሁ፡፡ በእርግጥ እስከ አሁን ድረስ ያየሁት የአሜሪካንን የሰብአዊ መብት አያያዝ አስመሳይነት እንጅ ዲፕሎማሲን አይደለም፡፡ እ.ኤ.አ ጁን 2013 ”የአሜሪካንን ዲፕሎማሲ በኢትዮጵያ መመልከት“ በሚል ርዕስ አሜሪካ እየተመለከተች ባለችበት ጊዜ በኢትዮጵያ ያሉ እርሷ እተመለከተቻቸው ያሉ ዜጎች እራቸው አሜሪካንን ከመመልከት ውጭ ምንም ነገር እንደማታደርግ እየተመለከቱ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያውያን/ት አሜሪካኖች ምንም ዓይነት ውሳኔ ሳይሰጡ ዝም ብለው እግራቸውን ሳያነሱ የሚራመዱ፣ ሁለት ምላስ ተናጋሪዎች፣ የሚናገሩትን የማይፈጽሙ ቃል አባዮች፣ መወሰን የማይችሉ፣ ግልጽነት የጎደላቸው፣ አስመሳይ፣ የጥርጣሬ ንግግር አድራጊ፣ ቀጥተኛ መልስ የማይሰጡ፣ አንድን ነገር ለማምለጥ ቶሎ ጥለው የሚሸሹ መሆናቸውን እየተመለከቱ ነው፡፡“ በአጭሩ በአፍሪካ ያሉ ወሮበላ ዘራፊ መንግስታት አሜሪካ እነርሱን ስታስደስት፣ ለእነርሱ ይቅርታ ስታደርግ እና በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር በእርዳታ መልክ ስታስታቅፋቸው እየተለመከቱ ነው፡፡

የታሪክ ትክክለኛ እና ስህተት ጎኖች እንዲሁም የአፍሪካ እና የኩባ ጠንካራ ሰዎች፣

የዩኤስ የሰብአዊ መብት ፖሊሲ ፍትሀዊ እና አድሏዊ ያልሆነ ነው ብየ ነው የማምነው፡፡ ፍትሀዊ ማለት ፍትሀዊ ማለት ነው፡፡ ለአፍሪካ አምባገነን ገዥዎች ጥሩ የሆነው ነገር ሁሉ ለኩባ፣ ለኢራን፣ ለሶሪያ እና ለሰሜን ኮሪያ ጠንካራ ሰዎችም ጥሩ ነገር መሆን አለበት፡፡ ሆኖም ግን በከርከሮዎች መካከል የቁንጅና አወዳዳሪ ዳኛ ልሆን አልችልም፡፡

ከአፍሪካ ወንድሞች የከፉ ናቸውን? ኩባ በሰብአዊ መብት አያያዝ እንዴት ነው ደረጃ የሚሰጣት?

እ.ኤ.አ በ2014 ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት አያያዝ የደረጃ ማወዳደሪያ መለኪያ መስፈርት መሰረት ኩባ ከ216 ሀገሮች መካከል በ115ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠች መሆኗን ሲያመላክት ኢትዮጵያ ደግሞ በዚህ በሰብአዊ መብት አያያዟ ከ216 ሀገሮች መካከል በ210ኛ ደረጃ ላይ እንደምትገኝ በግልጽ አመላክቷል! ሆኖም ግን በተግባር በኢትዮጵያ ስልጣንን የሙጥኝ ብለው በማተራመስ ላይ ላሉት የወሮበላ ስብስብ አምባገነኖች የአሜሪካ የዘላለም ምርጥ ጓደኞች (ዘምጓ) ናቸው፡፡ እስከ አሁን ድረስ በታዬው የዓለም ታሪክ ውስጥ ኩባ ከፍተኛ የሆነ ማዕቀብ የተጣለባት ብቸኛዋ ሀገር ናት!

እ.ኤ.አ በ2014 የዓለም አቀፍ የሙስና ግልጸኝነት መለኪያ/Transparency International Corruption Index ባወጣው ዘገባ መሰረት ከ177 ሀገሮች መካከል ኩባ ከጋና ቀጥላ በ63ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠች መሆኗን ይፋ አድርጓል፡፡ በአፍሪካ ጋና በነጻ፣ ፍትሀዊ ምርጫ እና በመልካም አስተዳደር በአርዓያነት የምትጠቀስ ሀገር ናት፡፡ ለዚህም ነው እ.ኤ.አ በ2009 ኦባማ አፍሪካን ለመጎብኘት የመጀመሪያቸው የሆነውን ኬንያን እና ደቡብ አፍሪካን ከመጎብኘት ይልቅ ጋናን ለመጎብኘት ምርጫ ያደረጉት፡፡ ኦባማ “አፍሪካ ጠንካራ ሰዎች አያስፈልጓትም ይልቁንም የሚያስፈልጓት ጠንካራ ተቋማት ነው” በማለት የአፍሪካን ህዝብ እጅግ በጣም ያስደሰተ ንግግር ለማድረግ ነበር ወደ ገና መሄዱን የመረጡት፡፡

በአሁኑ ጊዜ ባለው መለኪያ መሰረት በአሁኑ ወቅት ከአፍሪካ የተሻለ አስተዳደር አላት እየተባለ ከሚነገርላት ጋና ጋር ኩባ እኩል የሆነ ደረጃ አላት፡፡ ሆኖም ግን የአፍሪካ አምባገነኖች አሜሪካንን የመጫወቻ ሜዳቸው ሲያደርጓት የኩባ ህዝብ ግን ከአሜሪካ ህዝብ ጋር እንዳይገናኝ ተደርጓል፣ (ይህንን በማስመልከት እ.ኤ.አ ኖቬምበር 2011 በአሜሪካ ተደብቀው የሚገኙትን የአፍሪካን ትላልቅ ሌቦች መያዝ በሚል ርዕስ አቅርቤው ይነበረውን ትችት ልብ ይሏል)፡፡

እ.ኤ.አ በ2014 የጋዜጠኞች ተከላካይ ኮሚቴ/Committee to Protect Journalist ባወጣው ዘገባ መሰረት ከ10 አስከፊ የሆነ የጋዜጠኞች እስራት ከሚፈጸምባቸው ሀገሮች መካከል ቻይና ከዓለም የመጀመሪያውን ደረጃ ይዛለች፡፡ አስር አስከፊ የሆነ የጋዜጠኞች እስራት ከሚፈጸምባቸው ሀገሮች መካከል ኢትዮጵያ (በ4ኛ ደረጃ ላይ የምትገኝ)፣ ቬትናም፣ ግብጽ፣ በርማ፣ አዛርባጃን፣ እና ቱርክ ሁሉም ለአሜሪካ ትልቅ ግምት የሚሰጣቸው ተባባሪዎች እና ወዳጆች ናቸው፡፡ ኩባ ከ10ሩ ጋዜጠኞችን በማሰር ከተዘረዘሩት አስከፊ ሀገሮች ስም ዝርዝር ውስጥ የለችበትም!!!

እ.ኤ.አ ዴሴምበር 7/2014 የመረብ ነጻነት/Freedom on the Net የሚል ዘገባ በማውጣት ፍሪደም ሀውስ የተባለው ድርጅት የሚከተለውን መደምደሚያ ሰጥቷል፣ “በጣም ጨቋኝ ከሆኑ ህጎች እና ስልቶች ጋር ተዳምሮ በኢትዮጵያ ሀሳብን በነጻ የመግለጽ ነጻነት መከልከል እና መረጃ ማግኘት ያለመቻል እንዲሁም የኢንተርኔት ነጻነት ያለመኖር ሀገሪቱን በተከታታይነት ከሰብ ሰሀራ ሀገሮች እጅግ በጣም አስከፊ እና ከዓለም ደግሞ ከአስከፊዎች ተርታ ደረጃ አግኝታለች“ ብሏል፡፡ እንደ ዓለም አቀፍ የስታቲስቲክስ መረጃ ከሆነ እ.ኤ.አ ዴሴምበር 2013 ኢትዮጵያ 1,836,035 የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች (ከጠቅላላው ህዝብ 1.9%) ብቻ ነበሯት፡፡ በተመሳሳይ ጊዜ ኩባ 2,840,248 ተጠቃሚዎች የ25.7% ተደራሽነት ነበራት፡፡ አሁንም እንደገና በከርከሮዎች መካከል የቁንጅና ውድድር ዳኛ ለመሆን አይዳዳኝም፡፡

የሙስና ጉዳይን አስመልክቶ የካስትሮ ወንድሞች ከአፍሪካ ወንድሞች የተሻለ የሚሰሩ ይመስላል፡፡ በኩባ በመንግስት ቁጥጥር ስር ያሉ ተቋማዊ ሙስናዎች፣ ሰፊ የሆነ የፖለቲካ እና የዳኝነት ተጠያቂነት እንደሌለባቸው ጥርጥር የለኝም፡፡ በኩባ የገዥው ፓርቲ እና የጦር ኃይሉ አባላት ለተራው የኩባ ህዝብ የሌለውን እና አንደህልም የሚያዩትን ለእነርሱ ግን የተለየ ክብር እና መብት አላቸው፡፡

ሆኖም ግን የካስትሮ ወንድሞች በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር በምዕራብ ሀገሮች ባንኮች ለግል ጥቅም ተብሎ ሲታጨቅ ሰምቸም አይቸም አላውቅም፡፡ የአፍሪካ ወንድሞች ግን በምዕራብ ሀገሮች ባንኮች በቢሊዮን ዶላር የሚቆጠር ገንዘብ እያጨቁ ለመሆናቸው እና እንደ ኮሎምቢያ የአደንዛዥ ዕጽ አቅራቢ ድርጅቶች ገንዘብን በህገወጥ መልክ በየዓመቱ ከሀገር እንዲወጣ እንደሚያደርጉ በቂ ማስረጃዎች አሉ፡፡ እንደ ግሎባል ፋይናንሻል ኢንቴግሪቲ ዘገባ ከሆነ “ኢትዮጵያ በህገወጥ የገንዘብ ዝውውር 11.7 ቢሊዮን ዶላር እ.ኤ.አ በ2008 እና በ2009 ከሀገር እንዲወጣ ሆኗል፡፡ የበለጠ አሳሳቢ የሚሆነው ደግሞ ጥናቱ እንደሚያሳየው ኢትዮጵያ በህገወጥ መልክ የምታጣው ህገወጥ የገንዘብ ዝውውር እየጨመረ የመምጣቱ ጉዳይ ነው፡፡ የህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ ወንድሞች ናቸው የኢትዮጵያን ህዝብ ገንዘብ በህገወጥ መልኩ በምዕራብ ሀገሮች ባንኮች ዘንድ አጭቀው የሚገኙት እንጅ የካስትሮ ወንድሞች አይደሉም፡፡“

እ.ኤ.አ ሴፕቴምበር 2014 ኦባማ የኢትዮጵያን የወሮበላ ዘራፊ በድን ስብስቦችን በምስጋና እንዲህ በማለት አንቆለባብሰዋቸዋል፣ “…አሸባሪነት…ከኢትዮጵያውያን ጋር ያለን ትብብር እና አመራር የሚያተኩርበት የትብብር መስክ ሲሆን በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ እንደምንናገረው ለውጥ እያስመዘገበች ነው…ስለሆነም የእኛ የጸረ ሽብር ትብብር እና እንደ ኢትዮጵያ ካሉ ሀገሮች ጋር የመሰረትናቸው ትብብሮች አሸባሪነተን ድል ለማድረግ ለምናደርገው ሁለገብ ጥረት ወሳኝ እርምጃዎች ናቸው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እና መንግስታቸው በዚህ በያዝነው ዓመት ምርጫ ያካሂዳሉ፡፡ ስለዚያ ጉዳይ የማውቀው ነገር አለ…“

የአሜሪካ የመንግስት መምሪያ ኩባን አሸባሪነትን ለሚያራምዱ ቡድኖች ድጋፍ የምትሰጥ እና ፕሬዚዳንት ኦባማ በኢትዮጵያ ያሉትን ወሮበላ ዘራፊዎች ደግሞ በጸረ ሽብር ትግሉ ተባባሪዎች እያሉ ያንቆለባብሳሉ፡፡ አሁን በህይወት የሌሉት መለስ ዜናዊ እ.ኤ.አ በ2006 በሞቃዲሾ ሶማሊያ ላይ ፈጣን ወታደራዊ ጥቃት ለመፈጸም 50,000 ወታደሮችን ሲያዘምቱ እና ሀገሪቱ T-55 ታንኮችን፣ የኋላ ሄሊኮፕተሮችን እና Su-27 ተዋጊ ጀቶችን አሰልፋ በእራሷ ሀገር ላይ ምንም ነገር ሳይደርስባት በሰው ሀገር ድንበርን ተሻግራ ወረራ ማካሄዷ የመንግስት ድጋፍ ያለው አሸባሪነት አይደለምን? ማንም ቢሆን በ104 ገጽ ተካቶ የወጣውን እና እንዲህ የሚለውን የሂዩማን ራይትስ ዎችን ዘገባ በማስረጃነት መመርመር ይችላል፣ “እጅግ በጣም የሚያስፈራ፡ የጦር ወንጀለኝነት እና የሶማሊያ ውድመት“ የሚለውን በተጨባጭ በማየት የካስትሮ ወንድሞች ገዥ ከህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ ወንድሞች ጋር በማነጻጸር በእርግጠኝነት የትኛው መንግስታዊ ድጋፍ ያለው አሸባሪ እንደሆነ መወሰን ይቻላል፡፡

ባለፉት በርካታ ዓመታት ሰሜን ኮሪያ በደቡብ ኮሪያ እና በፓስፊክ ውቅያኖስ ዳርቻ አካባቢ ባሉ የአሜሪካ ወታደሮች ላይ የኒኩላር ጥቃትን ለማድረስ ተደጋጋሚ የሆነ ዛቻ ስታሰማ ቆይታለች፡፡ እ.ኤ.አ ጁላይ 2014 ሰሜን ኮሪያ በኋይት ሀውስ እና በፔንታጎን ህንጻዎች ላይ አስቀድማ የኒኩሌር ጥቃት ለመሰንዘር አቅሙ ያላት መሆኗን ድፍረት በተቀላቀለበት መልኩ ግልጽ አድርጋለች፡፡ እንደዚህም ሆኖ ሰሜን ኮሪያ መንግስታዊ ድጋፍ ካለው የአሸባሪነት ዝርዝር ውስጥ አልተካተተችም፡፡ በአሁኑ ጊዜ ሰሜን ኮሪያ በዩኤስ አሜሪካ ላይ የሳይበር ሽብርን በማድረስ በሶኒ ላይ ግዙፍ የሆነ የገንዘብ ኪሳራን ለማድረስ ነጻ የማስተባበር ኃይል እንዳላት ይሰማታል፡፡ ፕሬዚዳንት ኦባማ እንዲህ ብለዋል፣ “ታላቅ የሆነ ጉዳትን አስከትለዋል:: በፈለግነው ቦታ እና ጊዜ እንዲሁም በመረጥነው አካሄድ ተመጣጣኝ የሆነ የአጻፋ መልስ እንሰጣለን፡፡” ያ ምን ማለት እንደሆነ ለእኔ ግልጽ አይደለም፡፡

በከርከሮዎች መካከል የቁንጅና ውድድር የለም፣

የካስትሮ ወንድሞች የሰብአዊ መብት አያያዝ መዝገብ በአሁኑ ጊዜ በስልጣን ላይ እንደ መዥገር ተጣብቀው ከሚገኙት የአፍሪካ ወሮበላ ዘራፊ አምባገነን ወንድሞች የከፋ አይደለም፡፡ በእኔ አስተያየት የፊደል ካስትሮ የሰብአዊ መብት ረገጣ መዝገብ ከኢዲ አሚን፣ ከመለስ ዜናዊ፣ ከመንግስቱ ኃይለማርያም፣ ከኦማር አልባሽር፣ ከቻርለስ ቴለር፣ ከፓውል ቢያ፣ ከሞአማር ጋዳፊ እና ከሌሎችም ከተቀሩት የከፋ ወይም ደግሞ የተሻለ አይደለም፡፡ የካስትሮ ወንድሞች ከአፍሪካ ወንድሞች የበለጠ ክብር አላቸው ወይም ደግሞ ለማኛውም ጥፋት የካስትሮ ወንድሞች ተነጥለው እንዲወጡ በማድረግ ውግዘት ይፈጸምባቸው የሚል የመመጻደቅ አባባል ማቅረቤ አይደለም፡፡ ሆኖም ግን ለእኔ የካስትሮ ወንድሞችም ሆኑ የአፍሪካ ወንድሞች አንድ እና አንድ ናቸው፡፡

አንባቢዎቼ ከካስትሮ ዘመዶች ጋር የበለጠ የሞራል ተለዋዋጭነት አቋም እንዲይዙ የማድረግ ፍላጎቱ የለኝም፡፡ ፍጹም የሆነ ጭራቃዊነት እንዳለ አምናለሁ፡፡ ለእኔ ጭራቃዊነት ተግባራትን የሚሰሩ ሰዎች በብሄር፣ በኃይማኖት፣ በቋንቋ ወይም ደግሞ በጅኦግራፊያዊ ክልል አይወሰኑም፡፡ የእነርሱ ምግባር የሚወሰነው በሚያደርጉት እና በማያድረጉት ተግባር ላይ በመመስረት ነው፡፡

በካስትሮ ወንድሞች እና በአፍሪካ ወንድሞች መካከል በተደረጉ ጭራቃዊ ድርጊቶች ተመሳሳይ የሆነ የሞራል ልዕልና ነው ያለኝ፡፡ የኩባ ገዥ አካል መሪዎቹን እና መንግስታዊ ፖሊሲዎችን በተለይም ለኩባ ህዝብ መሰረታዊ የሰብአዊ መብት ጥበቃ ሲሉ ትችት የሚያቀርቡትን ዜጎች በዘፈቀደ ከህግ አግባብ ውጭ ያስራል፣ እናም ግለሰቦችን እና ቡድኖችን ይቀጣል፣ ያሰቃያል፡፡ የኩባ ገዥ አካል በሰላማዊ አመጸኞች ላይ በፖለቲካ፣ በህግ እና በማህበራዊ ጉዳዮች ላይ የመብት ድፍጠጣ ተግባሩን ያከናውናል፡፡ የኩባ መንግስት የህግ የበላይነት ወይም ደግሞ ነጻ እና ፍተሀዊ ምርጫ የሚባሉ ነገሮችን ትርጉማቸው ምን እንደሆነ አያውቅም፡፡ ሆኖም ግን….

በባዶ ሜዳ ላይ ብቻ እስረኞችን በማሰር የሚያሰቃዩ ስንት የአፍሪካ ሀገሮች አሉ? የፖሊስ መንግስታትስ ስንት አሉ? ባለፉት ሶስት አስርት ዓመታት ውስጥ አሻጥር ያልተሰራባቸው እና ያልተዘረፉ ምርጫዎች የትኞቹ ናቸው? በኢትዮጵያ ስንት ሺ የፖለቲካ እስረኞች ይገኛሉ? በአፍሪካ ባሉ የወሮበላ ዘራፊ አምባገነኖች በየዓመቱ ስንት ሺ ሰዎች ስቃይ እና ግድያ ይፈጸምባቸዋል? ስንት የአፍሪካ ሀገሮች ናቸው የአንድ ፓርቲ የፈላጭ ቆራጭነት ስርዓትን እያራመዱ ያሉ?

ኩባ ሁሉንም ዓይነት ህዝብ በተቆጣጠረ በኩባ ኮሙኒስት የአንድ ፓርቲ አገዛዝ ስር የወደቀች ሀገር ናት፡፡ የብዙሀን ፓርቲ ማስመሰያ ካልሆነ በስተቀር በሁሉም የአፍሪካ ሀገሮችም የአንድ ፓርት የፈላጭ ቆራጭነት አገዛዝ ስር ወድቀው የሚማቅቁ ናቸው፡፡ እ.ኤ.አ በ2010 በኢትዮጵያ በተካሄደው ሀገር አቀፍ ምርጫ እና 80 የተመዘገቡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ባሉባት ሀገር በሚያስቅ ሁኔታ ገዥው ፓርቲ 99.6 በመቶ በማሸነፍ የፓርላማ መቀመጫ ወንበሮችን ጠቅልሎ ተቆጣጥሯል፡፡ ኩባውያን ቢያንስ በእያንዳንዱ ምርጫ ይህን ያህል ድምጽ አገኘሁ በማለት በየጊዜው በሚደረግ ምርጫ እነርሱ ብቻ አሸናፊ እንደሆኑ በማወጅ እና ኩባን የሚገዙ እነርሱ ብቻ እንደሆኑ በመግለጽ ለእራሳቸው ክብር በመስጠት በሰው ስሜት ላይ አያፌዙም፡፡

የዩኤስ አሜሪካ ሁለት ምላስ የሰብአዊ መብት ዲፕሎክራሲ በአፍሪካ ወሮበላዘራፊዎች ላይም በተጨባጭ ይታያል፡፡ እ.ኤ.አ ጁን 2013 ፕሬዚዳንት ኦባማ በደቡብ አፍሪካ ተገኝተው ባሰሙት ንግግር በአዛውንቱ እና እርባና በሌላቸው የዚምባብዌ አምባገነን ገዥ በሮበርት ሙጋቤ ላይ የሚያንባርቅ እንዲህ የሚል ዲስኩር አሰምተዋል፣ “እስቲ ጎረቤታችሁን ዚምባብዌን ተመልከቱ፣ የነጻነት ቃልኪዳኑ ተገልብጦ የሙስና ኃይል ሲንሰራፋ እና የሀገሪቱ ኢኮኖሚ ሲሽመደመድ እና ሲጠፋ…ዚምባብዌዊያን/ት አዲስ ህገመንግስት አላቸው፣ ኢኮኖሚው ማገገም ጀምሯል፡፡ ስለሆነም ወደፊት ለመጓዝ እድሉ አለ–ሆኖም ግን ይህ የሚሆነው ነጻ፣ ፍትሀዊ እና ሰላማዊ ምርጫ ሲኖር ብቻ ነው፡፡ በዚህም መሰረት ዚምባብዌዊያን/ት ያለምንም ፍርሀት እና የበቀልተኝነት ስሜት ሳይሸማቀቁ የወደፊት ህይወታቸውን መወሰን ይችላሉ፡፡ እናም ከምርጫ በኋላ ዴሞክራሲ የሚጎለብትበት እና የሚመሰረትበት እርስ በእርስ የመከባበር ባህል መምጣት አለበት፡፡“

እ.ኤ.አ በ2013 የተካሄደውን ሀገር አቀፍ ምርጫ ሙጋቤ በ61 በመቶ ካሸነፉ በኋላ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጆን ኬሪ እንዲህ የሚል ቅሬታ የተሞላበት ንግግር አድርገው ነበር፣ “ስህተት እንዳትሰሩ፡ በርካታ የምርጫ ግድፈቶች በሞሉበት እና በሀገር ውስጥ እና አህጉራዊ የምርጫ ታዛቢዎች በቀረበው ዘገባ መሰረት በዛሬው ዕለት ይፋ በተደረጉት የምርጫ ውጤቶች ላይ አሜሪካ የዚምባብዌ ህዝብ ድምጹ ታማዕኒነት ባለው ሁኔታ ተከብሮለታል የሚል እምነት የላትም፡፡“ በኢትዮጵያ ያለው ገዥ አካል እ.ኤ.አ በ2010 በተካሄደው ሀገር አቀፍ ምርጫ 99.6 በመቶ በማግኘት አሸነፍኩ ብሎ ሲያውጅ ፕሬዚዳንት ኦባማ እውነት ያለመሆኑን እተገነዘቡ ምርጫውን አሸነፍን ያሉ ወሮበላ ዘራፊዎች በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ያለምንም ተጠያቂነት ያደረሱትን እና ወደፊትም የሚያድርሱትን ስቃይ እየተረዱ ምንም ነገር ትንፍሽ ሳይሉ አልፈውታል፡፡

እ.ኤ.አ በ2008 የተካሄደውን የዚምባብዌ ምርጫ ተከትሎ ዩናይትድ ስቴትስ የአምባገነን ኃይል ጠባቂ በማለት በዚያ ምርጫ ሸፍጥ በመስራት የህዝብን ድምጽ መዝረፍ እና ለተነሳው ተቃውሞ አፋኞችን በማደራጀት ለደረሰው ጉዳት ተጠያቂ ሙጋቤ እና የእርሳቸው ፓርቲ ናቸው በማለት ከስሳቸዋል፡፡ እ.ኤ.አ በ2005 አሁን በህይወት የሌሉት በመቶዎች በሚቆጠሩ ሰላማዊ ዜጎች ላይ የግድያ ዕልቂት በፈጸሙ ጊዜ አምባገነኑ ጭራቅ በሰው ልጆች ህይወት እጃቸውን በደም ሲታጠቡ እና የሰው እልቂት ወንጀል ሲፈጽሙ ዩኤስ አሜሪካ ትንፍሽ አላለችም፡፡ የኋይት ሀውስ ብሄራዊ የደህንነት ቃል አቀባይ የነበሩት ሚክ ሀመር ብቻ እንዲህ የሚል ጨዋነት የተንጸባረቀበት ንግግር አሰምተዋል፣ “አሳሳቢ እና ተስፋ የሚያስቆርጥ፡ እ.ኤ.አ ሜይ 23/2010 የተካሄደውን የኢትዮጵያ የፓርላማ ምርጫ መደምደሚያውን አውቀናል…ምርጫው ዓለም አቀፍ መስፈርትን አያሟላም በማለት የዓለም አቀፍ የታዛቢዎች ቡድን ዘገባ ያወጣ በመሆኑ ሁኔታው አሳስቦናል…የነጻ ታዛቢዎች እና ነጻ የመገናኛ ዘዴዎች በታላቅ ችግር ላይ ናቸው…“

እ.ኤ.አ በ2005 የተካሄደውን ምርጫ ተከትሎ በመለስ የደረሰውን ዕልቂት በማስመልከት ዩኤስ አሜሪካ ምንም ዓይነት ማዕቀብ አልጣለችም፡፡ ይልቁንም ዩኤስ አሜሪካ ለመለስ አገዛዝ በቢሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር በእርዳታ እና በብድር ስም ማንበሽበሽ ጀመረች፡፡ እንደዚሁም በአሁኑ ጊዜ ያለው ተመሳሳይ ገዥ አካል በሺዎች የሚቆጠሩ የፖለቲካ እስረኞችን በየእስር ቤቶች አጉሮ ሲያሰቃይ እያየች እና ይህንንም የዩኤስ የመንግስት መምሪያ በዓመታዊ የሰብአዊ መብት ጥበቃ አያያዝ ዘገባው ለህይወት አስጊ የሆነ ሁኔታ እና ወጣት ጦማሪያን ያለምንም ምክንያት እና ማስረጃ እየታሰሩ ፕሬዚዳንት ኦባማ በስልጣን ላያ ካለው ወሮበላ ዘራፊ ጋር ስለአጋርነት በመወያየት ለዚህ አንገብጋቢ የሰብአዊ መብት ድፍጠጣ በሺዎች የሚቆጠሩ የፖለቲካ እስረኞች ከሰውነት በወረደ መልኩ በእስር ቤት እየማቀቁ አላየሁም ብለዋል፡፡

በሌላ አሳፋሪ ዲፕሎክራሲ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጆን ኬሪ የቬንዙዌላ ፕሬዚዳንት የሆኑት ኒኮላስ ማዱሮ እ.ኤ.አ በ2013 ስላካሄዱት ምርጫ ህጋዊነት አሳሳቢነቱን ሲገልጹ የገዥው አካል ሴናተር የሆኑት ሩቢዮ በተጻራሪው ከኩባ ጋር ያለው ግንኙነት ወደቀድሞው እንዲመለስ ማድረግ ብቸኛ መጥፎ ነገር ነው በማለት አስተያየታቸውን መስጠታቸው የሚታወስ ነው፡፡ ማዱሮ ያንን ምርጫ 50.66 በመቶ በሆነ በጠባብ ልየነት ነበር ያሸነፉት፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጆን ኬሪ የምርጫ ውጤቱ ድጋሜ እንዲቆጠር የሚለውን እንዲህ በማለት ደገፉ፣ “እንደገና መቆጠር አለበት ብለን እናስባለን፣ በግልጽ እንደሚታየው ግዙፍ የሆኑ ግድፈቶች ካሉ የዚያን መንግስት (ማዱሮ) ህልው መሆን ላይ በርካታ አንገብጋቢ ጥያቄዎችን እናነሳለን፡፡“ ከዚህም በተጨማሪ የኋይት ሀውስ ቃል አቀባይ የሆኑት ጃይ ካርኔይ ሁሉም የድምጽ ካርዶች ቆጠራ እንዲካሄድ መግለጫ አወጡ፡፡

በ50.66 በመቶ ምርጫ ማሸነፍ ድጋሜ ቆጠራ እንዲካሄድ ይደረግበታል፣ ሆኖም ግን 99.6 በመቶ አሸነፍኩ ሲባል ምናልባትም አሳስቦናል የሚል ይሆናል፡፡ የአሜሪካ ዲፕሎክራሲ እንግዲህ እንደዚህ ቅጥአምባሩ የጠፋበት ነው!

ዩኤስ አሜሪካ እንደ ኩባ አጠቃላይ ሳይሆን በዚምባብዌ ላይ የተመረጡ እቀባዎችን ነጥላ በማውጣት ተግባራዊ እንዲሆኑ አድርጋለች፡፡ ፕሬዚዳንት ኦባማ እንዲህ በማለት ገልጸዋል፣ “በዚምባብዌ ያለው ሁኔታ የተለዬ ነው፡፡ ለእኛ በዩናይትድ ስቴትስ ለምንኖር ሰዎች በጣም አስቸጋሪ የሚሆንብን ነገር ቢኖር የእኛን ፍላጎት እና በዚምባብዌ በግልጽ እንደሚታዬው ተደጋጋሚ የሆነ መሰረታዊ የዴሞክራሲ ጥሰቶችን እና የሰብአዊ መብት ረገጣዎችን እንዴት አድርገን ማጣጣም እንዳለብን ነው፡፡ እናም ምርጫዎች በምን ዓይነት ሁኔታ መካሄድ እንዳለባቸው፣ መንግስት እንዴት መመስረት እንዳለበት ግልጽ የሆነ መልዕክት መላክ (ለሙጋቤ) አለብን፣ ምክንያቱም ይህንን ካላደረግን ሁሉም ነገር ያለተጠያቂነት እንደፈለገው የሚሄድበት ሁኔታ ስለሚፈጠር የየሀገሮች ህዝቦች ስቃይ ይደርስባቸዋል…“

የሚያስገርመው ነገር ከዚህ ተጻራሪ በሆነ መልኩ እ.ኤ.አ የ2007 የኬንያ ምርጫን ተከትሎ በተፈጠረው ውዝግብ 1,200 ዜጎች ባለቁበት እና ከ700,000 በላይ በተፈናቀሉበት ምርጫ እና በዚህ የሰብአዊ መብት ድፍጠጣ ምክንያት እጃቸው አለበት ተብለው በአሁኑ የኬንያው ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ላይ በዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ክስ ተመስርቶባቸው የፍርድ ሂደቱ በመካሄድ ላይ ባለበት ሁኔታ ፕሬዚዳንት ኦባማ አጋርነት ፈጥረዋል፡፡ ፕሬዚዳንት ኦባማ እ.ኤ.አ ኦገስት 2014 ኡሁሩ ኬንያታን በኋይት ሀውስ ጠርተው አሸሸ ገዳሜ ብለዋል፣ ሆኖም ግን የሙጋቤን የጥሪ ወረቀት ማስተላለፋቸው እንኳ ትንሽም ቢሆን አላሳሰባቸውም (ወይም ደግሞ በሌላ አማራጭ ሙጋቤን በICC ዋና ዓቃቤ ህግ ክስ እንዲመሰረትባቸው እንኳ ግፊት አላደረጉም)፡፡ ማን ነው የተሻለ ክብር ያለው? ለእኔ በከርከሮዎች መካከል የቁንጅና ውድድር የለም የሚል አጭር መልስ ነው ያለኝ፡፡

የዩኤስ አሜሪካ የየሀገሮቹ አምባገነን ገዥዎች የሰብአዊ መብት ፖሊሲ አያያዝን በዓለም ላይ ለመፈተን የዓለም አቀፉን የሰብአዊ መብት ድንጋጌ ወይም ደግሞ ከዓለም አቀፍ ህጎች አንጻር እንዴት እየተተገበሩ እንዳሉ አይደለም የምታዬው፡፡ ይልቁንም ከእነዚህ መፈተኛዎች ይልቅ እነዚህ አምባገነኖች ለዩኤስ እርዳታ እና ዓለም አቀፍ ብድር ለሚከፍሉት ዋጋ በሰው ልጆች ላይ ሰብአዊ ወንጀሎችን ሲፈጽሙ ዩኤስ አሜሪካ የፈለገውን ያህል ሰብአዊ መብት ቢደፈጠጥ አይታ እንዳላየች፣ ሰምታ እንዳልሰማች፣ መናገር እየቻለች ዱዳ በመሆን ታልፈዋለች፡፡ በዚህም መሰረት ፈተናው እነዚህ አምባገነኖች በጣም መጥፎ ይሁኑ ወይም ደግሞ እጅግ በጣም አስቀያሚ ይሁን አይሁኑ በእራሱ መስፈርት የሚያያቸው ሳይሆን በዩኤስ የፈተና መስፈርት ብቻ የሚታዩ ናቸው፡፡ በፕሬዚዳንት ፍራንክሊን ሩዝቬልት ዘመን በኒካራጓ የነበሩት አምባገነን አናስታሲ ሶሞዛ ከፈጸሙት የሰብአዊ መብት ድፍጠጣ ጀምሮ አሁን እስካለንበት ጊዜ ድረስ ይህ ጉዳይ እንደቀጠለ ይገኛል፡፡ በአንድ ወቅት የካስትሮ ወንድሞች የሶቪየት ደጋፊዎች ነበሩ፣ ሆኖም ግን አሁን ከግማሽ ክፍለ ዘመን ቆይታ በኋላ የእኛ ደጋፊ ሊሆኑ አይችሉምን?

ዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ የሰብአዊ መብት ድፍጠጣ በተንሰራፋባቸው ሀገሮች መልካም አስተዳደርን ለማጎልበት ምን መሰራት እንዳለበት ታውቃለች፡፡ ፕሬዚዳንቱ በሰብዊ መብት ድፍጠጣ የተጠረጠረ ወይም ደግሞ በሰው ልጆች ላይ በሰብአዊ መብት ላይ ጥቃት ባደረሰ ወንጀለኛ ላይ እርምጃ ለመውሰድ ከኮንግረሱ ስልጣን መጠየቅ አያስፈልጋቸውም፡፡ በአፍሪካ መልካም አስተዳደርን ለማስፈን ፕሬዚዳንቱ ሁሉም መሳሪያዎች በእጃቸው አሉ፣ እርዳታን የማስተላለፍ፣ የብዙሀን መንግስታትን ብድር የማገድ፣ እና የምጣኔ ሀብት ማዕቀብ የማድረግን እርምጃ ጨምሮ፡፡ ኦባማ የብዕር ጠብታቸውን በመጠቀም ብቻ መንግስትን ማዘዝ ይችላሉ፣ እናም ወሮበላ አምባገነን ገዥዎችን መጠኑን የያዘ መድኃኒት በማዘዝ ማውገዝ ይችላሉ፡፡ በአሁኑ ጊዜ ኦባማ ለበርካታ አስርት ዓመታት ማዕቀብ ተጥሎባት የቆየችውን ኩባን ማዕቀቡ እንዲነሳላት ብዕራቸውን በማንሳት የእራሳቸው ምርጫ እንዲከናወን መርጠዋል፡፡

ፕሬዚዳንት ኦባማ ኩባ እስከ አሁን ድረስ ተጥሎባት የቆየው ማዕቀብ ተነስቶላት ወደቀድሞው ዲፕሎማሲያዊ ሁኔታ መመለስ አለባት ሲሉ ሩቢዮ እንዳሉት ሞኝ ሆነው አይደለም፡፡ ፕሬዚዳንት ኦባማ ሌላ ማንም ሳይሆኑ ፕሬዚዳንት ኦባማ ናቸው፡፡ እስከ አሁን ድረስ ኦባማ የማይወዱትን አምባገነን አላገኙም፡፡ ቀልድ የማውቅ ሰው ብሆን ኖሮ ፕሬዚዳንት ኦባማን ፍላጎት ያላቸው ሆኖ ግን መፈጸም የማይችሉ አምባገነን ወይም ደግሞ እራሳቸውን ሳይሆን ሌላ ሰው ለመምሰል የሚሞክሩ ስብዕና የለሽ እላቸው ነበር፡፡

ሴናተር ሩቢዮን በሚመለከት በእርግጠኝነት የዋህ ናቸው፡፡ የኩባ ሰብአዊ መብት፣ የአሜሪካ ሰብአዊ መብት፣ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት፣ የኬንያ…የፈረንሳይ…የጃፓን ሰብአዊ መብት የሚባል ነገር እንደሌለ ማወቅ ይኖርባቸዋል!

ዩኤስ አሜሪካ ለእራሷ ጥቅም ስትል ግዙፍ የሰብአዊ መብት ደፍጣጮች፣ ጥቂችን የማቀፍ እና ሌሎችን ደግሞ የማስወገድ የሚል የመከፋፈያ ስልት የመጠቀም አካሄድ እስከተከተለች ድረስ የዩኤስ የሰብአዊ መብት ፖሊሲ የሞራል ኪሳራውን ተከናንቦ ይቀራል፡፡ ዩኤስ አሜሪካ ሁሉም ከርከሮዎች የተጠሉ አስቀያሚዎች ናቸው የሚለውን ማስታወስ ይኖርባታል (ለእናቶቻቸው ብቻ ተዋቸው)፡፡

የፕሬዚዳንት ኦባማን ኩባን ወደ ቀድሞው የዲፕሎማሲ ግንኙነቷ እንድትመለስ የወሰኑትን ውሳኔ እደግፋለሁ ምክንያቱም የኩባ ህዝብ የሰው ልጅ የሆነ ሁሉ ሊታገስ ከሚችለው ባላይ ለበርካታ ዓመታት ማዕቀብ ተጥሎበት መከራ ፍዳውን ያዬ በመሆኑ ነው፡፡ ሁለት ዝሆኖች በሚጣሉበት ጊዜ የሚጎዳው ሳሩ ነው፡፡ የበለጠ ግልጽ ለማድረግ ትልቅ ዝሆን እና ትንሽ ዝሆን በሚጣሉበት ጊዜ አሁንም ቢሆን የሚጎዳው ያው ሳሩ ነው፡፡ እኔ ከሳሩ ጋር ነኝ፣ እየተሰቃዬ ካለው እና ካለፈው የቀዝቃዛው ጦርነት ጀምሮ ለሌሎች ሰዎች እና ቡድኖች ጥቅም ሲባል እየተሰቃዬ ካለው የኩባ ብዙሀን ህዝብ ጋር፡፡

ለፕሬዚዳንት ኦባማ ትንሽ ምክር ቢጤ ነገር ለመስጠት ዕድሉ ቢኖረኝ ይህንን ነው የምላቸው፣ “አምባገነኖችን ማስደሰት እና ለመጥፎ ባህሪያቸው መሸለም በጥቃት ሰለባዎቻቸው ላይ የበለጠ ስቃይ እና መከራ እንዲያመጡ ማደፋፈር ብቻ ነው፡፡ አምባገነኖችን ማስደሰት ሰብአዊነት እንዲሰማቸው አያደርግም፣ ይልቁንም የበለጠ የጥቃት ሰለባዎችን እንዲያሰቃዩ ይገፋፋቸዋል“

የእራሴን ምክር እየሰጠሁ “የስህተት አስቂኝ ቀልዶች” ከሚለው የሸክስፒር ስንኞች ጥቂት መስመሮችን ላካፍላችሁ፤

አስተምረኝ ውድ ፍጡር እንዴት እንደሚታሰብ እና እንደሚነገር፣
በእራስ መተማመን ስሜት፣ በመሬቱ ላይ ተዘርጋበት፣
በስህተቶች ታፍነህ፣ የማታሳምን ግልብ ደካማ ነህ
የጎበጡ ቃሎችህ፣ አሳሳች ትርጉም ከፊትህ፡፡

ለካስትሮ ወንድሞች አንድ ወይም ሁለት ቃላትን እንድናገር እድሉን ባገኝ ይህንን ነው የምላቸው፡ ወደ አንድ ጎን ተንቀሳቀሱ፡፡ ይህንን ድርጊት አስወግዱ፡፡ እናንተ ለተረሳው የቀዝቀዛው ጦርነት ስትዋጉ የኩባ ህዝብ ለግማሽ ምዕተ ዓመት ያህል በቅዝቃዜ ውስጥ እንዲቆይ ተበይኖበት ኖሯል፡፡ የኩባ ህዝብ ከቅዝቃዜ ይውጣ፡፡

ከብዙ ጊዜ በፊት ፊደል እንዲህ ብለው ነበር፣ “አብዮት የጽጌረዳዎች መንገድ አይደለም…አብዮት ባለፉት እና በወደፊቱ ትውልድ መካከል የሚደረግ የሞት ሽረት ትግል ነው“ የካስትሮ ወንድሞች ለግማሽ ምዕተ ዓመት ያህል በማዕቀብ ውስጥ ተኝተው ከቆዩ በኋላ ጽጌረዳዎችን ለማሽተት ተነሱ፣ እናም የወደፊቷን ጀግና ዓለም ሰላም ለማለት ተንቀሳቀሱ፡፡ ላሳስባችሁ የምፈልገው ነገር እንዲህ የሚሉትን የካርል ማርክስን ምክሮች እንድታዳምጡ ነው፣ “ታሪክ እራሱን ይደግማል፣ መጀመሪያ እንደ ታላቅ ሀዘን፣ ሁለተኛ እንደ አስቂኝ ቀልድ፡፡“

ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!
ታህሳስ 14 ቀን 2007 ዓ.ም

Leave a Reply