እየተንፏቀቀ የመጣው ረሃብ በኢትዮጵያ

ከፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማርያም

ትርጉም በነጻነት ለሀገሬ 

ፈረሰኛው ረሃብ  ኢትዮጵያ ላይ አያነጣጠረ ነው!

ባለፈው ሳምንት ኤንቢሲ/NBC የተባለው የዜና ወኪል በኢትዮጵያ እየተንፏቀቀ በመጣው ረኃብ ላይ ያደረገውን ጥናታዊ ዘገባ ዋቢ በማድረግ በማርቲን ጌይስለር አማካይነት ከዚህ በታች የተመለከተውን ሀተታ ለአየር አብቅቷል፡፡

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ የዓለም የምግብ ቀውስ መገለጫ ሆናለች፡፡ በደቡብ ኢትዮጵያ በአንድ መንደር ውስጥ እናቶች በተመጣጣኝ የምግብ እጥረት ከተጎዱ ህጻናት ልጆቻቸው ጋር ለአስቸኳይ የምግብ ምፅዋት(ራሽን) ተደርድረው ታይተዋል፡፡ ህጻናት ልጆቻቸውን ለመመገብ የሚያስችል አቅም የላቸውም፡፡ እንዲሁም በአሁኑ ጊዜ የውጩ ዓለም የእርዳታ እጁን ለመዘርጋት የሚችል አይመስልም፡፡ የረኃብ ምልክት የሆነው የህጻናት ሆድ መነፋት ከሁለት ተከታታይ ደካማ የምርት ዓመታት በኋላ የተከሰተ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ በዕየለቱ ተጨማሪ ሰዎች የረኃብ ሰለባዎች እየሆኑ ነው… ለእነዚህ የረኃብ ሰለባ ለሆኑ ወገኖች ከአስር ቀናት በፊት የምግብ ራሽን ሲሰጣቸው ነበር… የመንግስት የምግብ ክምችት ከተሟጠጠ ብዙ ጊዚያትን አስቆጥሯል፡፡ እንደዚሁም ደግሞ የተባበሩት መንግስታት የምግብ ክምችት በመመናመን ላይ ይገኛል፡፡ ለረኃብ ሰለባዎቹ ከአስር ቀናት በፊት የምግብ ራሽን ሲሰጣቸው ነበር… እነዚህ የረኃብ ሰለባዎች በየወሩ የምግብ እርዳታ ያገኛሉ፣ ሆኖም ግን እ.ኤ.አ በጁላይ 2013 የተሰጠው የምግብ ራሽን እርዳታ በአንድ ሦስተኛ እንዲቀነስ ተደርጓል፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ የምግብ እህል ዋጋ እየጨመረ በመምጣቱ ምክንያት አሁን ያለውን የረኃብ ሰለባ ባለበት ሁኔታ ለማቆየት እንዲቻል ተጨማሪ 100 ሚሊዮን ፓውንድ ማሰባሰብ ያስፈልጋል… ከሶማሌ የወሰን ጠረፍ ወደ ሰሜን 400 ማይሎች ሲታይ የተለዬ የመሬት አቀማመጥ እናገኛለን፡፡ ሆኖም ግን ተመሳሳይ ቀውሶች እና እዚህም የዝናቡ መዘግየት ይታያል፡፡ በዚህም ምክንያት በአካባቢው ከሚኖረው ህዝብ ግማሽ ያህሉ የምግብ እርዳታ ይፈልጋል… [የገዥው አካል ተወካይ የሆኑት አቶ ዑመር አብዲ] ጉዳዩን አስመልክቶ እንዲህ በማለት ሀሳባቸውን ገልጸዋል፣ ‘ለእነርሱ ሁለት የማያሻሙ አማራጮች አሉኝ፣ መሞት ወይም መሬቱን መጫር (ማልማት)’፣ ሆኖም ግን በአሁኑ ጊዜ በዚህች አገር ላይ ከውጭ የሚደረገው እርዳታ ሚሊዮኖች በህይወት እንዲቆዩ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ ባልተመጣጠነ ምግብ ምክንያት ለአደጋ የተጋለጡ ዜጎች ብዛት እድገት በማሳየት ላይ ይገኛል፣ እናም ይህንን ክስተት ለመግታት የሚደረግ ምንም ዓይነት የጥረት ምልክት አይታይም፡፡ ይህ ዓለም አቀፍ የምግብ ቀውስ በምዕራቡ ዓለም ለምግብ መሸመቻ ገንዘብ ችግር ቢፈጥርም ግን እዚህ [ኢትዮጵያ ውስጥ] ያሉት ህዝቦች በጣም ከፍተኛ የሆነ ዋጋ እንዲከፍሉ ያደርጋል፡፡

የረኃብ  መምጣት ማስጠንቀቂያ ደወል ደውዬ ነበር   

እ.ኤ.አ በኦክቶበር 2012 “ኢትዮጵያ፡ ለ2013 ረኃብ ቅድመ ማስጠንቀቂያ“ በሚለው ትችቴ የማስጠንቀቂያ ደወል ደውዬ ነበር፡፡ ይህንን ስል የተለዬ ዕውቀት ወይም ደግሞ የረኃብ ኢኮኖሚክስ ክህሎት ኖሮኝ አይደለም፡፡ ሆኖም ግን መረጃዎችን በጥንቃቄ በፈርጅ በፈርጃቸው በማስቀመጥ፣ ከተለያዩ ምንጮች ማለትም የረኃብ ቅድመ ማስጠንቀቂያ ስርዓት መረብ/Famine Early Warning System Network/(FEWS NET)፣ ኦክስፋም/Oxfam፣ የተባበሩት መንግስታት የዓለም የምግብ ፕሮግራም/U.N World Food Program፣ የተባበሩት መንግስታት የምግብ እና የእርሻ ድርጅት/U.N Food and Agricultural Organization እና የአዲሲቷ ኢንግላንድ ውስብስብ ስርዓቶች ተቋም/New England Complex Systems Institute [NECSI] (ከሀርባርድ እና ከኤምአይቲ ዩኒቨርሲቲዎች የተሰባሰቡ የወደፊቱን ሁኔታ በመተንበይ የተካኑ የአካደሚክ ሰዎች በተፈጥሯዊ ከባቢያዊ ሁኔታዎች ላይ የሚመጡ ለውጦች እንዴት የፖለቲካ አለመረጋጋትን እና አመጾችን እንደሚያስከትሉ) ከእነዚህ ምንጮች የሚገኙትን ትንታኔዎች እና ግኝቶች በመጠቀም እ.ኤ.አ 2013 ረኃብ ወይም “አሰቃቂ የምግብ ቀውሶች“ በማለት በኢትዮጵያ ያሉ ባለስልጣናት አቃለው የሚጠሯቸው ችግሮች ሊከሰቱ የሚችሉበት የመጀመሪያ ዓመት እንደሚሆን ቀደም ሲል ግልጽ ሆኖልኝ ስለነበር ነው፡፡

እ.ኤ.አ በ2012 መጨረሻ አካባቢ በአምራች አገሮች ወደ ውጭ የሚላከው የምግብ እህል መጠን እየቀነሰ መምጣት እ.ኤ.አ በ2013 በዓለም ዓቀፍ የሸቀጦች ገበያ ዋጋ እንዲጨምር ተጽእኖ ሊፈጥር እንደሚችል አጠቃላይ ስምምነት ላይ ተደርሶ ነበር፡፡ “የጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ መንግስት የማይቀረውን ዓለም አቀፍ የምግብ ቀውስ እየተመናመነ ከመጣው የውጭ ምንዛሬ እና መንግስታቸው ለወደፊቱ በአገሪቱ አሰቃቂ ሆኖ የሚከሰተውን ረኃብ የሚፈጥራቸውን ችግሮች ከማስወገድ አንጻር መንግስታቸው በምን ዓይነት ሁኔታ“ ለመቋቋም እንዳሰበ ጥያቄ አቅርቤ ነበር ፡፡ እንዲህ በማለት አስጠንቅቄ ነበር፣ “ብዙ የአስቸኳይ ጊዜ የምግብ እርዳታ ለመለመን ዕቅድ ማውጣት ችግሩን ሊያስወግደው አይችልም፡፡ ‘በፕሮዳክቲቭ ሴፍቲ ኔት ፕሮግራም‘ ላይ መተማመንም አይሰራም፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ መንግስት የተሻለ ምላሽ ወይም ደግሞ ከአድማስ ተሻግሮ እየመጣ ላለው ረኃብ አስፈላጊውን እርምጃ የማይሰጥ ከሆነ የተራበ ህዝብ ብቻ አይደለም የሚጠብቀው፣ ሆኖም ግን የተበሳጨ ህዝብ ጭምር እንጅ!“

ባለፈው ዓመት አቶ ኃይለማርያምም ሆኑ አሻንጉሊት ጌቶቻቸው “እየመጣ ላለው ረሃብ“ መፍትሄ ሊሆን የሚችል ተጨባጭነት ያለው ገንቢ የቅድመ ዝግጅት ስራ አልሰሩም፡፡ እንደተለመደው እጃቸውን አጣጥፈው፣ ዝንቦችን እያባረሩ ከአሜሪካ ግብር ከፋይ ህዝብ መጨረሻው መቸ እንደሆነ በውል ለማይታወቅ ጊዜ መመጽወትን ተማምነው ተቀምጠዋል፡፡ አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ እየመነመነ ስለመጣው የዝናብ ስርጭት እና በኢትዮጵያ ስጋት ሆኖ በመቅረብ ላይ ስላለው ረኃብ ያሳሰባቸው መሆን አለመሆኑን በተጠየቁ ጊዜ ለሰጡት መልስ እንዲህ የሚል ቀልድ ወጥቶባቸዋል፣ “ስለዝናብ ሁኔታ በኢትዮጵያ አንጨነቅም፣ እኛ የምንጨነቀው በአሜሪካ እና በካናዳ ስለሚኖረው ዝናብ ነው፡“ እ.ኤ.አ በፌብሯሪ 2014 አቶ ኃይለማርያም እና ጓዶቻቸው ከዩናይትድ ስቴትስ እና ከካናዳ ኤምባሲዎች ዓመታዊ የልመና ዙራቸውን ለመከወን የልመና አኩፋዳቸውን በመቦረሽ ላይ ይገኛሉ፡፡

እ.ኤ.አ በ2011 አቶ ኃይማርያም “የውጭ ጉዳይ እና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር“ በነበሩበት ጊዜ መንግስታቸው ረኃብን መንግሎ ማስወገድ እንደሚችል እና በአጭር ጊዜ ውስጥ ድህነትን ተረት እንደሚያደርግ በጣም እርግጠኛ በመሆን ተናግረው ነበር፡፡ ከአፍሪካ ኮንፊደንሻል ጋር በተደረገ ቃለመጠይቅ እንዲህ በማለት ድንፋታ አድርገዋል፣ “ላለፉት ሰባት ዓመታት ኢትዮጵያ ባሁለት አሀዝ የኢኮኖሚ እድገት አስመዝግባለች፣ ይህም የሚያመላክተን የኢኮኖሚ ፖሊሲያችን በጥሩ ሁኔታ እየሰራ ያለ መሆኑን ነው፡፡ ይህንን የኢኮኖሚ እድገት በዚሁ ፍጥነት የምናስቀጥል ከሆነ በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ኢኮኖሚያችንን አሁን ካለበት በእጥፍ ማሳደግ እንችላለን፡፡ ይህም ማለት የማህበረሰባችንን ገቢ በእጥፍ እናሳድጋን፣ ይህንንም በማድረግ ድህነትን 50 በመቶ እንቀንሳለን፡፡” ብለዋል፡፡ ከአቶ ኃይለማርያም በፊት የነበሩት እና በቅርቡ ያረፉት እብሪተኛው አቶ መለስ ዜናዊ “[ከሁለት አስርት ዓመታት] በፊት አዲስ አበባ ላይ በአንድ የፕሬስ ጉባኤ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ስላላቸው ዓለማ ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ በሰጡበት ወቅት መንግስታቸው ኢትዮጵያውያን በቀን ሶስት ጊዜ እንዲመገቡ ካደርጉ ታላቅ የድገት ምልክት ነው  በማድረግ ስኬታማ ይሆናል በማለት አውጀው ነበር፡፡“ እዚህ ላይ ቪዲዮውን መመልከት ይቻላል)፡፡ እ.ኤ.አ በ2011 አቶ መለስ እራሳቸውን ከፍ ከፍ በማድረግ እንዲህ ሲሉ የግነት አዋጅ አውጀው ነበር፣ “ትርፍ ምርት ለማምረት የሚያስችሉ ዕቅዶችን ቀይሰናል፣ እናም በ2015 ያለምንም የውጭ እርዳታ ፍላጎት ህዝባችንን መመገብ እንችላለን“ ነበር፡፡

እ.ኤ.አ በ2014 “በቀን ሶስት ምግብ“ ለበርካታ ኢትዮጵያውያን ላም አለኝ በሰማይ ወተቷን የማላይ ሆኗል፡፡ እንደዚሁም “ካለውጭ የምግብ  እርዳታ ፍልጎት“ አቶ መለስ “እንደቀየሱት” ኢትዮጵያ በ2015 እራሷን ትመግባለች ማለት ዘበት ነው፡፡ በእርግጥ ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ህዝቦቻቻውን በተሻለ ሁኔታ ከማይመግቡ በዓለም ላይ ከሚገኙ 125 አገሮች በ123 ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡ እንደ አዲሱ የኦክስፋም የምግብ መረጃ  “በዓለም ላይ የተትረፈረፈ፣ የተመጣጠነ፣ጤናማ እና ህዝቡ እንደልብ ሊገዛው የሚችል ምግብ በማግኘት ኔዘርላንድ በቁጥር አንድ ላይ የምትገኝ ስትሆን ቻድ በ125ኛ ደረጃ ላይ በመቀመጥ የመጨረሻ በመሆን አንጎላን እና ኢትዮጵያን ታስከትላለች፡፡”

አስገራሚው ነገር ግን በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን እየተራቡ ባሉበት ወቅት የሳውዲ አረቢያ እንዲሁም የህንድ የግብርና ንግድ ኩባንያዎች ለም የሆነውን የኢትዮጵያ መሬት እያረሱ እህል ለየአገሮቻቸው በመላክ ላይ የሚገኙ ሲሆን ቻይና በበኩሏ ደግሞ ቀስ እያለች ኮሽታ ሳታሰማ የኢትዮጵያን የግብርና ዘርፍ ገበያ ለመቆጣጠር ዕቅዷን በማስፈጸም ላይ ትገኛለች፡፡ እንድሂም አርጎ “ባለሁለት አሀዝ የኢኮኖሚ ዕድገት!”፣ እንድሂም አርጎ “ኢኮኖሚውን በእጥፍ ማሳደግ!”፣ “ትርፍ ምርት”፣ እንድሂም አርጎ “በቀን ሶስት ጊዜ መመገብ!”

በኢትዮጵያ ተደብቆ ያለውን ረኃብ ማጋለጥ

ባለፉት ጥቂት ዓመታት በኢትዮጵያ በተለይም በረኃብ ወይም ደግሞ ረኃብ የሚጠቅሱ ጉዳዮች ላይ ትኩረት በማድረግ በደርዘን የሚቆጠሩ ትችቶቼን ሳቀርብ ቆይቻለሁ፡፡ (በድረገጾች የግርጌ ማስታወሻዎች ላይ መመልከት ይቻላል)፡፡ በአሁኑ ጊዜ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን በምግብ እጦት ምክንያት እየሞቱ ወይም ደግሞ በአካል እና በመንፈስ እየተሰቃዩ ባሉበት ሁኔታ በረኃብ የተጠቁ አካባቢዎች እንዳይታወቁ በባለስልጣኖች በሚስጥር ተይዘው እንዲሁም ዓለም አቀፋዊ እና የአገር ውስጥ ጋዜጠኞች ጎብኝተው መረጃ እንዳያወጡ በሚል ሰንካላ ምክንያት አካባቢዎቹን ከእይታ ውጭ በማድረግ አስቸኳይ እርዳታ እንዳያገኙ የሚያደርጉትን ከንቱ ሙከራ ጊዜ ወስጀ ለማጋለጥ በማሰብ ነው፡፡ የመለስ-ኃይለማርያም አገዛዞች ረኃብ ድብቅ ሆኖ እንዲቆይ እና ከህዝብ እይታ እንዲሰወር በማሰብ ከእነርሱ በፊት የነበሩት ነገስታት ሲፈጽሙት የነበረውን ግትር አካሄድ ተከትለው ነጉደዋል፡፡

እ.ኤ.አ በ1974  “ድብቁ ረኃብ“ የሚል ዘጋቢ ፊልም በጆናታን ዲምቢልቢ ለአየር አብቅቶ የበርካታ አትዮጵያውያንን/ትን ድንጋጤ እና ቁጣን እስከቀሰቀሰበት ጊዜ ድረስ ቀዳማዊ ዓጼ ኃይለ ስላሴ በሀገሪቱ ውስጥ ምንም ዓይነት ርኃብ የሚባል ነገር የለም እያሉ ያስመስሉ ነበር፡፡ የቀድሞው ወታደራዊ አምባገነን መሪ ኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማርያም እ.ኤ.አ በ1984-85 በአገሪቱ በከፋ መልኩ ተከስቶ የነበረውን ረኃብ ምንም ዓይነት ረኃብ እንደሌለ በማስመሰል ሙልጭ አድርገው መካድ ይታወሳል፡፡ መለስ፣ ኃይለማርያም እና ግብረ አበሮቻቸው በፊት የነበሩት መሪዎች የረኃብን መከሰት ጉዳይ በማስመልከት ከህዝብ እይታ ለመደበቅ በሚያደርጉት ጥረት የበለጠ አታላዮች ናቸው፡፡ ይህንን እኩይ ምግባራቸውን ለመደበቅ የሚጠቀሙባቸው ዘዴዎች ደግሞ፣ 1ኛ) የአገር ውስጥ ብዙሀን መገናኛዎች እንዳይዘግቡ ጥብቅ ቁጥጥር ማድረግ እና ሊያመጣ የሚችለውን እና ከፍተኛ የሆነ የሰብአዊ ቀውስ ሊያስከትል የሚችለውን ረኃብ ለመዘገብ ፍላጎት ላላቸው ለዓለም አቀፍ ጋዜጠኞች እና ለብዙሀን መገናኛ ወኪሎች ሁሉ አገሪቱ ዝግ እንድትሆን ማድረግ፣ 2ኛ) ከሚያብረቀርቁ የልመና አኩፋዳዎቻቸው ጋር በመሆን ከምዕራቡ ዓለም ኤምባሲዎች ቅጥር ግቢ ውጭ ለልመና መቆም ዋና ዋናዎቹ ናችው፡፡

የንጉሱ መንግስት፣ የወታደራዊው አምባገነን መንግስት፣ እና አሁን ያለው ገዥ አካል: ኔሮ የተባለ ነጉስ ሮም ስትቃጠል ክራር እንደተጫወተው ሁሉ እነዚህም በተመሳሳይ መልኩ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በረኃብ አለንጋ እየተገረፉ እነዚህ አዙሮ የሚያይ አንገት የሌላቸው አምባገነን መሪዎች ከነቤተሰቦቻቸው የተቀማጠለ እና የተንፈላሰሰ የኑሮ ዘይቤን በመቀጠል የመጓዛቸው ሁኔታ አስደናቂነት ልብ ሊባል ይገባል፡፡ እ.ኤ.አ በ1974 ቀዳማዊ ዓጼ ኃይለስላሴ ከዙፋናቸው ከመወገዳቸው በፊት በአገሪቱ ሰሜናዊ ክፍል በተከሰተው ረኃብ ምክንያት በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች በረኃብ እየረገፉ ባለበት ወቅት የንጉሳዊ ቤተሰቦች ለድንክዬ ውሾቻቸው በጣም ውድ የሆኑ ምግቦቸን እና ለእራሳቸውም በጣም ከፍተኛ ዋጋ የሚያወጡ ኬኮችን ከአውሮፓ አገሮች እያስመጡ አሸሸ ገዳሜ ሲሉ እና አስረሽምችውን በመተግበር ሀሴት ሲያደርጉ የሚያሳየውን ክስተት ወታደራዊው አገዛዝ በፊልም ቀርጾ ይህንን ከልክ ያለፈ የተንፈላሰሰ የኑሮ ዘይቤ የሚያሳይ ዘጋቢ ፊልም ለኢትዮጵያ ህዝብ በተሌሊቪዥን ይፋ አድርጎታል፡፡ እ.ኤ.አ በ1984 ወታደራዊው መንግስት ስልጣን የያዘበትን 10ኛ ዓመት በሚያከብርበት ወቅት በእብሪት የተሞሉት ወታደሮች ሻምፓኝ እና ውስኪ እንደ ጅረት ውኃ እንዲፈስሱ አድርገዋል፡፡ በ1984 በተከሰተው አሰቃቂ ረኃብ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ሞተዋል፡፡

እ.ኤ.አ በ2014 ሁኔታው አጅግ የበለጠ አስከፊ እየሆነ ነው፡፡ አሁን በስልጣን መንበር ላይ ተፈናጥጠው የሚገኙት፣ ዘመዶቻቸው፣ ሎሌዎቻቸው፣ የእኩይ ምግባር አጋሮቻቸው እና ካድሬዎቻቸው ልዩ ንድፍ ዲዛይን ባላቸው ልብሶች፣ ጫማዎች፣ የእጅ ቦርሳዎች እና ሽቶዎች ላይ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ዶላሮችን በማውጣት ከውጭ በማስገባት በመጠቀም ላይ ይገኛሉ፡፡ እንደዚሁም በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዶላሮችን በማውጣት በጣም ውድ የሆኑመኪናዎች እና ለእስፖርት አገልግሎት የሚውሉ ውድ ተሽከርካሪዎችን በማስመጣት አንዲሁም ብዙ ሚሊዮን ዶላሮች ፈስሰውባቸው በተሰሩ እጅግ በጣም ትልቅ ቤቶች እና ከአውሮፓ በመጡ በጣም ውድ በሆኑ የቤት ዕቃዎችና የማዕድ ቤቶች ቁሳቁሶች በተሟሉባቸው ቤቶች ውስጥ በመኖር ላይ ይገኛሉ፡፡ ግሎባል ዓለም አቀፍ ኢንቴግሪቲ በተባለው ዓለም አቀፋዊ ድርጅት በቀረበው ዘገባ በግልጽ እንደተመለከተው እነዚህ የስርዓቱ አድራጊ ፈጣሪዎች በውጭ በሚገኙ ባንኮች እና በሌሎች ሚስጥር የኢንቨስትመንት ኩባንያዎች ላይ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ዶላሮችን በድብቅ አጭቀው ይገኛሉ፡፡ ግን  እ.ኤ.አ በ2014 በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ለረኃብ አደጋ ተጋልጠው ይገኛሉ፡፡ በኡሁኑ ጊዜ ይህ በጣም አሳዛኝ ሁኔታ ግን እውነተኛ የኢትዮጵያ ታሪክ ነው፡፡ ነጻውን ፕሬስ በማሸማቀቅ በኢትዮጵያ በስልጣን ላይ ያለው ገዥ አካል በድብቁ ረኃብ ላይ ምንም ዓይነት ዜና እንዳይወጣ የመረጃ ምንጭን በማድረቅ የተዋጣለት ስራ ሰርቷል፡፡ ለማርቲን ጌይስለር፣ አይቲኤን/ITN እና ኤንቢሲ/NBC ላቀረቡት ዘገባ ምስጋና ይይገባቸዋል::  በአሁኑ ጊዜ በአገራችን በመከሰት ላይ ስላለው አሰቃቂ ረኃብ አጠቃላይ ሁኔታ ዘጋቢአቸው  ግንዛቤ እንዲኖረን አስቸሏል፡፡

የኢትዮጵያን ድብቅ ረኃብ ድብቅ አድርጎ ለማቆየት የዓለም አቀፉ ሸፍጥ

ለሁለት አስርት ዓመታት ያህል  በኢትዮጵያ ላይ ባለው ገዥ አካል እና በዓለም አቀፍ ለጋሽ ድርጅቶች፣ እርዳታ ሰጭ ባለሙያዎች፣ ዓለም አቀፍ ሰራተኞች እና መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች መካከል በሚገባ በተቀነባበረ የዝምታ ሸፍጥ ምክንያት አስፈሪውን  በ “ረ” (ረሃብ ) የሚጀመረዉን ቃል በኢትዮጵያ ውስጥ አይጠቀሙም፡፡ ሆን ተብሎ ህዝብን ለማሳሳት በሚነገር በቢሮክራሲ የተተበተበ የሀሰት ቃላቶችና ንግግር  ለህዝብ ግልጽ አንዳይሆኑ    በብዙሀን መገናኛ ዘዴዎች በመልቀቅ እውነታውን ሸፍኖ ረኃቡን ከህዝብ ደብቆ ለማቆየት ረዥም ርቀት ተጉዘዋል፡፡ ስለምግብ “ደህንነት ዋስትና ማጣት” ደረጃዎች ያወራሉ፡፡ የሰዎች የምግብ መራብ ፍላጎት እና የምግብ እጦት:  “ኃይለኛ የምግብ ዋስትና እጦት” (acute food insecurity)፣ አሳሳቢ የምግብ ሁኔታዎች ማጋጠም (stressed food situations)፣ ወደ ቀውስ አዝማሚያ የሚሄድ ምግብ አጦት (crisis mode)፤ ወደ አስቸኳይ የሆነ ምግብ አጦታ ደርጃ  (emergency status)፣ እና በመጨረሻም ወደ አስከፊ የምግብ እጦት (catastrophic food shortages) የሚሉ ደረጃዎች ስያሜ አያወጡ ይተርካሉ፡፡ በየትኛውም ቦታ ቢሆን “ረኃብ” ወይም “ጠኔ” (famine or starvation) የምትል ቃል በአፋቸው አይጠሯትም፡፡

“ረኃብ” የሚለው ቃል በኢትዮጵያ ባለው ገዥ አካል እና በብዙ በዓለም አቀፍ ደረጃ በድህነት ስም ለርካሽ ጥቅማቸው በቆሙ አቃጣሪዎች ለምን እንደማይጠራ የተከለከለበት ምክንያት አለ፡፡ ረኃብ ብዙ ሆዳቸው የተነፋ በበረሃ በተቃጠለ የመሬት ገጽታ ላይ የሚንከላወሱ፣ እግር እና እጃቸው የተጠማዘዘ የረኃብ ሰለባ እሬሳዎችን በግራር ዛፎች ስር እና ሆዳቸው ተነፍቶ በዝንቦች የተወረሩ ህጻናት እናታቸውን አጥብቀው እንደያዙ በመመገቢያ ካምፖች ውስጥ ሆነው በአእምሮ ላይ ስሎ ያሳያልና፡፡ የባለፈው ሳምንት የጌስለር ዘገባ የተጠማዘዙ እሬሳዎችን አያሳይም፡፡ ሆኖም ግን የቀረጸው ቪዲዮ ሆዳቸው ተነፍቶ በዝንቦች የተወረሩ ህጻናት እናታቸውን አጥብቀው እንደያዙ ህጻናቱ በአንድ ወይም በሁለት ቀናት በሞት እንደሚነጠቁ እናቶች ተስፋ በቆረጠ ስሜት ተውጠው ሲመለከቷቸው ያሳያል፡፡

በኢትዮጵያ ስለረኃብ በግልጽ ማውራት በለጋሽ ድርጅቶች/በመንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች እና በገዥው አካል አደገኛ ሁኔታ ነው፣ ምክንያቱም የፖለቲካ አመጽን የሚጋብዝ ነውና፡፡ ፕሮፌሰር አንጌላ ራቬን ሮበርትስ እና ፕሮፌሰር ሱዊ ላውዜ በኢትዮጵያ ያለውን ተደጋጋሚ የረሃብ መከሰት በማስመልከት ባቀረቡት ትንታኒያቸው እንዲህ ይላሉ፣ “ረሀብን ይፋ ማድረግ ማለት ለኢትዮጵያ መንግስት የተወሳሰበ ጥያቄ ነበር፡፡ ረሃብ ለኢትዮጵያ ገዥዎች መውደቅ ምክንያት አስተዋጽኦ አድርጓል… አንዳንድ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ስኬቶቻቸውን በከፊል ረሃብን በማስወገድ ይለኳቸዋል፡፡“

የዝምታ ሸፍጥ ከረሃብ ጋር በተያያዘ መልኩ በኢትዮጵያ በመስራት ላይ ለሚገኙ ተዋንያን ሁሉ ፍላጎታቸውን ለማሟላት ያገለግላል፡፡ ገዥው አካል፣ ለጋሽ ድርጅቶች፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እና የእርዳታ ሰራተኞች የረሃብን መኖር አምነው ለመቀበል መሞከር የሌባ ጣትን ወደ እራስ እንደመቀሰር ተደርጎ ይቆጠራል፡፡ ለረሃብ መኖር በአዎንታዊነት ማረጋገጫ የሚሆኑት በሌላው መልኩ ሲታይ ረሃብ ከሌለ ለምግብ እርዳታ የሚሰጡት በሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር፣ በስርጭት መስመሮች ላይ የሚገኙት መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እና ከፍተኛ ተከፋይ የሆኑት ዓለም አቀፍ የእርዳታ ሰራተኞች መከኑ ማለት ነው፡፡ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር እርዳታ ቢኖርም ቅሉ ኢትዮጵያ በምግብ እህል እራሷን እንድትችል የሚያስችል ዕቅድ ለማውጣት ውድቀትን ያሳያሉ፡፡ የኢትዮጵያ ገዥ አካል ረሃቡን ለማስወገድ እንዲችል የሚያግዝ ጥረት የማድረግ ድፍረቱ የላቸውም፡፡

በኢትዮጵያ ያለው ገዥው አካል “ረሃብ” የምትለዋን ቃል ከሚጠራ ይልቅ ምላሱ ቢቆረጥ ይመርጣል፡፡ ለምሳሌ እ.ኤ.አ በጃንዋሪ 2010 የአቶ መለስ የግብርና ሚኒስትር ተሿሚ የነበሩት አቶ ምትኩ ካሳ እንዲህ በማለት ተናግረው ነበር፣ “በኢትዮጵያ ሁኔታ ረሃብ የለም፣ ቸነፈር/ጠኔ የለም… [ረሃብ ወይም ቸነፈር አለ] የሚለው መሰረተቢስ ነው፣ በመሬት ላይ ካለው ተጨባጭ ሁኔታ በተቃራኒው ነው፡፡ በመረጃ የተደገፈ አይደለም፡፡ ችግሮቹን ለማስወገድ መንግስት እርምጃ በመውሰድ ላይ ነው፡፡“ አቶ መለስም በተመሳሳይ መልኩ ስለረሃብ መኖር እንዲህ በማለት ሙልጭ አድርገው አስተባብለዋል፣ “ረሃብ በኢትዮጵያ ለረዥም ጊዚ እልቂትን ሲያስከትል ቆይቷል፣ እንደዚህ ዓይነት አደጋዎች ሊከሰቱ እንደሚችሉ አስቀድሞ መገንዘብ አለመቻል ደደብነት ነው፣ ሆኖም ግን በእኛ እይታ ረሃብ የለም… የአስቸኳይ ጊዜ፣ ምግብ አጦት እንጂ ረሃብ የለም፡፡“ ረሃብ የለም! የፖለቲካ አስረኞች የሉም! የሰብአዊ መብት ጥሰቶች የሉም! አምባገነናዊነት የለም! ምንም ዓይነት ችግሮች የሉም! ቅጥፈት ብቻ ነው ያለው!

ሆኖም ግን በኢትዮጵያ ረሃብ መኖሩን የመካድ ሸፍጥ እራሷን ዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካንንም ያካትታል፡፡ እ.ኤ.አ በ2004 ፕሬዚዳንት ጆርጅ ደብልዩ ቡሽ ሲናገሩ በእርሳቸው የስራ ዘመን ረሃብ የተወገደ መሆኑን እንዲያረጋግጡ ‘በእኔ እይታ ረሃብ የለም’ የሚለውን ፖሊሲያቸውን ለማሳየት አመራሮቻቸውን ለማሳመን ጥረት አድርገዋል:: ረሃብ አለ ብሎ መናገር የፖለቲካ ጉድለት መኖሩን እና አደገኛ የፖለቲካ ሁኔታ መኖሩን ማረጋገጥ ማለት ነው፡፡ ረሃብ የሚለውን ቃል ላለመጥራት በባለስልጣኖች ገደብ ከታጣበት በተቃራኒ ልዩ በሆነ መልክ “ረሃብ” የሚለውን ቃል በመጠቀም የሚታወቁት የዓለም ባንክ ዋና ኢኮኖሚስት የሆኑት ዎልፍ ጋንግ እ.ኤ.አ በኦገስት 2011 እንዲህ በማለት በግልጽ ተናግረዋል፣ “ይህ [በኢትዮጵያ ውስጥ] ያለው የረሃብ ቀውስ ሰው ሰራሽ ነው፡፡ የድርቅ ሁኔታዎች ደግሞ ደጋግመው ይከሰታሉ፣ እነዚህ ሁኔታዎች ወደ ረሃብ እንዲለወጡ የሚያደርጉት መጥፎ ፖሊሲዎችን ነድፎ ከስራ ላይ ባለመዋል ነው፡፡“ በሌላ አገላለጽ በኢትዮጵያ ከረሃብ ጋር በተያያዘ መልኩ መሰረታዊ ችግር የሚቀርበው የተበላሸ አስተዳደር በመንሰራፋቱ ነው፣ ድርቅ አይደለም፣ አቅመቢስ እና ጥንቃቄ እንዲሁም ለትክክለኛ አሰራር ሙሉ ፍላጎት የጎደለው አሰተዳደር በመኖሩ ነው፣ አካባቢያዊ ነገሮችም አይደሉም፡፡ በኢትዮጵያ በተደጋጋሚ የሚከሰቱት የድርቅ አደጋዎች ሰው ሰራሽ ናቸው፣ ማለትም በሙስና፣ የጥንቃቄ እና ሙሉ ፍላጎት እጦት፣ አቅመቢስነት እና ተደጋግመው የሚከሰቱትን የድርቅ አደጋ ችግሮች ሙሉ የፖለቲካ ቁርጠኝነት “አድርገው” ችግሮቹን ለመፍታት የማይችሉ ደንቆሮ አገዛዞች ስለሆኑ ነው፡፡ በአትዮጵያ በስልጣን ላይ ያሉ በፍርሃት ተሸብበው ትክክለኛ ዕቅድ እና ፖሊሲ ማውጣት የሚፈሩ፣ የማይንቀሳቀሱ በድኖች፣ እና “በጫካ አስተሳሰብ” የሚመሩ እንጅ የሰውን ሀሳብ በመስማት እራስን የመለወጥ እና ከጊዜው ትክኖሎጂ ጋር የማይሄዱ ፍጡሮች ናቸው፡፡

በኢትዮጵያ ያለው ገዥ አካል በኢትዮጵያ ከዓመት ዓመት በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ስዎች ህይወት መጥፋት እና መሰቃየት ምክንያቱ ድርቅ ነው በማለት በ”ድርቅ” ላይ ችግሩን ይደፈድፋል፡፡ እንዲህም ሆኖ ይህ ሰነፍ አገዛዝ በየጊዜው ባለማቋረጥ የሚከሰቱትን የድርቅ አደጋዎች መንስኤ መሰረታዊ ችግሮች ለይቶ በማውጣት መፍትሄ ለመስጠት የሚያበቃ አቅም በማጣት ከምንም ያልተሻለ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ (እ.ኤ.አ በ2010 “ምጽአት አሁን ወይስ ከ40 ዓመታት በኋላ” በሚል ርዕስ ያቀረብኩትን ትችት መመልከት ይቻላል)፡፡ የሀገሪቱን ከፍተኛ የህዝብ እድገት እና እየናረ የመጣውን የምግብ ዋጋ ግሽበት ለመቆጣጠር፣ የአካባቢ መራቆትን የማሻሻል እና በመንግስት የመሬት ባለቤትነት ምክንያት እየቀነሰ የመጣውን የምርታማነት ማሽቆልቆል እንዲሁም በተበጣጠሰ እና ከእጅ ወደ አፍ በሆነ የአስተራረስ ዘዴ እና አጠቃላይ የሆነ የግብርና ዕቅድ ነድፎ ተግባራዊ በማድረግ እረገድ እስከአሁን ድረስ ከምንም ያልተሻለ ስራ ተሰርቷል ማለት ይቻላል፡፡ የገዥው አካል መፍትሄ ሆኖ የቀረበው የአገሪቱ ዜጎች በረሃብ አለንጋ እየተገረፉ በአገሪቱ ውስጥ የሚገኘውን በጣም ለም የሆነውን የእርሻ መሬት ዓለም አቀፋዊ ባለሃብቶች (international Investors ) እየተባሉ ለሚጠሩ መሬቱን ለእርሻ ንግድ በጣም ዝቅተኛ በሆነ “ኪራይ” (lease) ተጠቅመው ምርቶቻቸውን ወደ ሀገራቸው ማስወጣት እንደሚችሉ ወይም በዓለም አቀፍ ገበያዎች መሸጥ እንዲችሉ ፈቅዶላቸዋል፡፡ አቶ ኃይለማርያም የሳውዲ እና የህንድ የመሬት ወረራ የኢትዮጵያን ግብርና ወደ ላቀ ደረጃ ያሸጋግረዋል ብለው ያምናሉ፡፡ በቅርቡ አዲስ አፍሪካ (New Africa) ለተባለው ጋዜጣ እንዲህ በማለት ተናግረዋል፣ “ከእጅ ወደ አፍ የሆነ የግብርና ስርዓት ስንከተል ነበር፣ አሁን ግን ወደ ንግድ ግብርና (commercial agriculture) እየተለወጠ ነው፡፡“

በኢትዮጵያ የምግብ እርዳታ ላይ የዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ የመድህን ዋስትና

ዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ ለኢትዮጵያ የምትሰጠውን የምግብ እርዳታ አስመልከቶ ህሊናን የሚቆጠቁጥ አስገራሚ እና የማይገናኝ ሁኔታ አለ፡፡ በየዓመቱ ባለፉት አስርት ዓመታት የዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ ለአንድ ዓይነት የህብረተሰብ ክፍሎች በእርግጠኝነት እያወቀች በየዓመቱ የምግብ እርዳታ ትሰጣለች፡፡ አንዳንድ ለአጠቃላይ ደህንነት የሚውሉ እና እንደ ምርታማነት ደህንነት ፕሮግሞች (productive safety net programs) (ገዥው አካል በገጠር ከሚኖሩ ገበሬዎች እና ኗሪዎች የፖለቲካ ድጋፍ ለማግኘት እየተጠቀመበት ይገኛል) የመሳሰሉ ፕሮጀክቶች በስተቀር ከረሃብ እርዳታው ጋር በተያያዘ መልኩ አሜሪካ በገዥው አካል ላይ የምትጥላቸው ጥቂት ቅድመ ሁኔታዎች የሉም፡፡ እንዲህም ሆኖ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ከዓመት ዓመት ከፍተኛ በሆነ ችግር ውስጥ መውድቅ እና በሚሊዮን የሚቆጠር አሜሪካውያን ግብር ከፋይ ዶላሮች ለድርቁ ችግር መዋላቸው ቀርቶ ለማጭበርበር፣ ለሙስና እና ለብክነት ይዳረጋል፡፡

በአሜሪካ በምግብ እርዳታ ፖሊሲ ላይ ያለው ችግር የሚያሳየው እውነታ የመጣው የእርዳታ ገንዘብ በኢትዮጵያ በትልቅ የረሃብ አደጋ ጫፍ ላይ ተንጠልጥለው ያሉ ዜጎችን ከችግራቸው በማውጣት ተግባር ላይ መዋሉ በሚገባ ሊጤን ይገባዋል፡፡ ፓውል ሄበርት የተባሉት የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብቶች ጉዳይ አስተባባሪ ቢሮ በኢትዮጵያ በቅርቡ የተመለከቱትን አንደሚከተለው አቅርበውታል፣ “[በኢትዮጵያ ውስጥ] እየገጠመን ያለው ችግር ብዙው እና ብዙ የህብረተሰብ ክፍል ውጥረት ላለው ሁኔታ እና ለአካላዊ አደጋ ይጋለጣሉ… ከዚያ አደጋ ለማውጣት የተደረገ ጥረት የለም፡፡ የሚያስፈራው ነገር በዚህች አገር ሌላ ትልቅ የድርቅ አደጋ ከተከሰተ እና ያለውን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ እና አሳሳቢ የሆነውን የምግብ እጦት ለመቅረፍ  አስተማማኝ ስራ ካልሰራን ነገሮችን በእጅጉ ቀድሞ ወደ ነበሩበት እንዲመለሱ ሊያደርግ ይችላል፡፡ ምክንያቱ የብዙ ሰዎች የኑሮ ሁኔታ በጣም በአደገኛ ሁኔታ ላይ የሚገኝ ስለሆነ በቀላሉ አደገኛ ወደ ሆነ የድርቅ ረሃብ ውስጥ ልትገባ ኢትዮጵያ ትችላለች::

ዩናይትድ ስቴትስ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ዜጎች  በችግር ጠርዝ ላይ ሆነው እያዩ ወደ ጎን ሆነው ለወንጀሉ ተባባሪነታቸውን በማሳየት በጸጥታ እየተመለከቱ ዝምታን ይመርጣሉን? በቅርቡ ኤንቢሲ/NBC የተባለው ድርጅት እንዳቀረበው ዘገባ በኢትዮጵያ ደቡብ ሶማሊ እና በኦሮሚያ አካባቢዎች በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ህዝቦች ለ“አሰቃቂ የምግብ እጥረት” በተለምዶ ረሃብ እየተባለ ለሚጠራው ተጋልጠዋል፡፡ እ.ኤ.አ በ2014 ሌሎች አካባቢዎች ረሃብ መሰል ነገሮች ያሰጋቸዋል ተብለው የሚገመቱት የሰሜን ምስራቃዊ አማራ እና የምስራቅ እና ደቡባዊ ትግራይ አካባቢዎች  እንዲሁም በኦሮሚያ አካባቢዎች  የምስራቅ ሐረርጌ ዞን ዝቅተኛ ቦታዎች ናቸው፡፡ ከ12 – 20 ሚሊዮን መካከል የሚሆን ብዛት ያለው ህዝብ ለአደጋ ይጋለጣል የሚል ግምት ሲኖር ይህ ህዝብ ወደ ሙሉ ለሙሉ ረሃብ አደጋ ተጋላጭነት ምድብ ውስጥ ለመግባት ቀላል መገፋትን ብቻ የሚጠይቅ ይሆናል ተብሎ ይታመናል፡፡ ዩናይትድ ስቴትስ በጸጥታ የእየተመለከተች የዚህ ስህተት ተባባሪ መሆን አለባት?

የገዥው አካል በአጭር ጊዜ ውስጥ ብዙ ሚሊዮን ዶላር ለማግኘት ሲጠቀምበት የነበረው አሮጌው የልመና ስልት ከዓመታዊ የአሜሪካ ግብር ከፋይ የሚሰበሰበው እርዳታ የሚቆምበት ጊዜ እየተቃረበ የመጣ ይመስላል፡፡ የዩናይትድ ስቴትስ ምግብ ለሰላም መዋጮ ላለፉት በርካታ ዓመታት በከፍተኛ ደረጃ እየቀነሰ የመጣበት ሁኔታ ተከስቷል፣ 451.7 ሚሊዮን ዶላር (በ2010)፣ 313.3 ሚሊዮን (በ2011)፣ 306.6 ሚሊዮን (በ2012)፣ 235.5 ሚሊዮን (በ2013) እና 86.9 ሚሊዮን (በ2014) መሆኑን በግልጽ ያመላክታል፡፡ አቶ ኃይለማርያም እና ጓዶቻቸው በአሁኑ ወቅት የተከሰተውን “የምግብ ቀውስ” ለማሸነፍ ወይም ደግሞ የኢትዮጵያን ህዝብ “አደገኛ የምግብ እጥረት” ችግር በተለመደው መልክ ከዩናይትድ ስቴትስ በሚገኝ ልመና ለመፍታት እንደገና ረጋ ብለው ሊያስቡበት ይገባል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ደግሞ ኦባማ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች ላይ ለምግብ እርዳታ ተብሎ የሚመጣው ገንዘብ ላይ በሚደረገው ማጭበርበር፣ ብክነት እና ሙስና ላይ ለውጥ ማየት ይፈልጋሉ፡፡ ለጋሽ ድርጅቶች እርዳታ በመስጠት ፖሊሲያቸው ላይ የመሰላቸት ሁኔታ በመላ አሜሪካ  እየተስተዋለ ነው፡፡ አቶ ኃይማርያም እና አሻንጉሊት ጌቶቻቸው ይህንን ከግንዛቤ ሊያስገቡ ይገባል፡፡

የረሃብ ዓመታዊ መኸር፡ በጣም አጣዳፊው የባለስልጣኖች ግልጽነት እና ተጣያቂነት መኖር

“የምግብ እጥረት”፣ “የምግብ ዋስትና” ወይም ደግሞ ማንም የፈለገውን ቃል ለመጠቀም መምረጥ ቢችልም በኢትዮጵያ ይህ ችግር በልመና ሊፈታ የሚችል አይደለም፡፡ ከሙስና በኋላ በኢትዮጵያ ያለው ገዥ አካል ልመናን የህይወቱ አንዱ አካል አድርጎ ወስዶታል፡፡ ለሁለት አስርት ዓመታት በስልጣን ላይ ያለው ገዥው አካል ረሃብን እና ሀፍረትን ማምረት ችሏል፡፡ ገዥው አካል በልመና ከሚመጣ እርዳታ ጋር ተላምዷል፣ በአሁኑ ጊዜ ተስፋ በቆረጠ መልኩ ገዥው አካል በምግብ እርዳታ ሱስ ተጠምዷል፡፡ በኢትዮጵያ ያሉ ደኃ የረሃብ ሰለባዎች በስልጣን ላይ ያሉ ሰዎች ሊንከባከቧቸው እንደማይችሉ በማመን በገዥዎች ችሎታ እና አቅም ላይ ምንም ዓይነት እምነት የላቸውም፡፡ ትኩረታቸውን በዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ እና በሌሎች የምዕራብ ለጋሽ ድርጅቶች ላይ ተክለዋል፡፡ የአሜሪካ ግብር ከፋይ ህዝብ በልፋት የሚያገኙትን ዶላር ለእራሱ ህዝብ ትንሽም እንኳ ቢሆን ደንታ ለሌላቸው የገዥ አካላት ለምን ያህል ጊዜ ሲሰጡ ይኖራሉ? የአሜሪካ ግብር ከፋይ ህዝብ የሚያዋጡት ዶላር አላግባብ ሲባክን፣ ለሙስና እኩይ ተግባር ሲውል፣ እና በሰብአዊ መብት እርዳታ ሰበብ በሙሰኛ የገዥ አካላት ማታለል ስራ ለግል ጥቅም ሲውል የአሜሪካ ግብር ከፋይ ሕዝቦች እስከ መቸ ድረስ በትዕግስት ሊመለከቱ ይችላሉ?

በተደጋጋሚ ስናገረው እንደነበረው ሁሉ ስለየህግ የበላይነት፣ ተጠያቂነት እና ግልጽነት በአሁኑ ጊዜ በስልጣን ላሉት ማስተማር ምንም ዓይነት መስማት እና መናገር ለማይችሉ ዱዳ አሕዛቦች ከመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ እየጠቀሱ ለመስበክ እንደመሞከር ወይም ደግሞ በተጠረበ የባልጩት ድንጋይ ላይ ውኃ እንደ ማፍሰስ ይቆጠራል፡፡ ለምንም የማይፈይድ ከንቱ ሙከራ ነው፡፡ ከሃያሶስት ዓመታት የስልጣን ጊዜ በኋላ በጫካ በነበሩበት ጊዜ እንደለመዱት ሁሉ አሁንም የድብቅነት ፖለቲካቸው ላይ ተጣብቀው ይገኛሉ፡፡ ከጫካ አገዛዝ ወደ መንግስታዊ አስተዳደር ለመሸጋገር አልቻሉም፡፡ ያም ቢሆን ስለግልጸኝነት እና ተጠያቂነት እንዲሰፍን ደግመን ደጋግመን ከመወትወት ወደኋላ አንልም፡፡

የፕሬስ ነጻነት ሚና ከግልጽነኝት እና ተጠያቂነት አንጻር የሚጋነን ሊሆን አይችልም፡፡ባለፉት አመታት ዘጋቢያዊ ጋዜጠኞች የብዙ ሚሊዮን ኢትዮጵያውያንን ህይወት አድነዋል፡፡ እ.ኤ.አ በ1970ዎቹ እና በ1980ዎቹ የባለስልጣናትን ድብቅነት በማጋለጥ ዘጋቢ ጋዜጠኞች የብዙ ሚሊዮን ኢትዮጵያውንን ህይወት ከረሃብ እና ከቸነፈር ያዳኑ እና ያልተዘመረላቸው ጀግኖች ናቸው፡፡ አምባገነኑ የወታደራዊ መንግስት መሪ ኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማርያም በአሰቃቂነት መልኩ ተከስቶ የነበረውን ረሃብ ለመደበቅ በሞከሩበት ጊዜ ዘጋቢ ጋዜጠኞች ፈልፍለው በማውጣ ዓለም እንዲያውቀው በማድረግ የረሃብ ሰለባዎች አስካሉባቸው ድረስ እርዳታ ሰጭ ድርጅቶች እርዳታቸው እንዲደርስ በማድረግ ዓለም አቀፋዊ ምላሽ እንዲሰጥ ተደርጓል፡፡ እንደዚሁም በንጉሱ ጊዜ በ1970ዎቹ መጀመሪያ አካባቢ ተመሳሳይ ሁኔታ ተከስቶ ነበር፡፡ አሁንም አዲስ ነገር የለም፡፡ አቶ ኃይለማርያም እና ጌቶቻቸው ግልጽ ሆነው በመቅረብ በኢትዮጵያ የተከሰተውን ረሃብ እና ቸነፈር ለዓለም ህዝብ ማሳወቅ አለባቸው፡፡ ለጋሽ አገሮች ተጠያቂነት እየመጣ ስላለው ረሃብ እውነትነት ለዓለም ህዝብ በማሳወቅ ውጤታማ እርምጃ እንዲወስድ እና ሙሉ ተጠያቂነት እንዲኖር ማድረግ አለበት፡፡ ሌላው አማራጭ ደግሞ ዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ እና የምዕራቡ ለጋሽ አገሮች ከገዥው አካል ጋር በዝምታ እያዩ ቢያልፉት እና እየመጣ ባለው ረሃብ ምክንያት በመቶ ሺዎች ዜጎች ለሞት ቢዳረጉ የጋራ ተጠያቂ መሆን አለባቸው፡፡

በመጨረሻም ኢትዮጵያውያኖች ማስታወስ ያለባቸው በድብቅ እና በቸልተኝነት እርዳታ የነፈጓቸውን መሪዎቻችሁ ነን የሚሉትን የገዥውን አካል ባለስልጣናት ብቻ አይደለም፣ ሆኖም ግን በዝምታ እና ምንም ነገር ሳይሰሩ ሆኖም ግን ለመርዳት መጥተው የይስሙላ ስራ የሚሰሩት እንዲሁም ተጎጅዎች ሲሰቃዩ እያዩ ማለፍ የሞራል ውድቀት በመሆን ተጠያቂዎች ናቸው፡፡ ምናልባትም የቦብ ማርሌይን “የተራበ ሰው የተበሳጨ ሰው ነው” በሚል ርዕስ የቀረበ ግጥሞች ትምሕርት ይሰጣሉ፣

የእነርሱ ከርስ ሞልቶ እኛ ግን ተርበናል፣

የተራበ አመጽ የተበሳጨ አመጽ ነው፣
ለኑሮ የሚወጣ ወጭ እየጨመረ ይሄዳል፣
ኃብታም እና ደሃ ሁለቱም ማልቀስ ጀመሩ፣
አሁን ደካማው ጠንካራ መሆን አለበት፣

አሁን ደካማው ጠንካራ መሆን አለበት፣

 

ኢትዮጵያ ለዘላለም በክብር ትኑር!

የካቲት 4 ቀን 2006 ዓ.ም

Leave a Reply