ኬንያታ በዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት

ከፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማርያም

ትርጉም በነጻነት ለሀገሬ

የዘገዬ ፍትህ እንደተነፈገ መቆጠር የለበትምን?

በአህጽሮ ቃሉ አይሲሲ/ICC እየተባለ የሚጠራው ዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት/International Criminal Court የኡሁሩ ሙጋይ ኬንያታን ጉዳይ አስመልክቶ እያደረገ ያለው ተደጋጋሚ የፍትህ ሂደቱን የማዘግየት ስራ፣ በቀጠሮ የማሳለፍ እና “የውሸት መረጃዎች” እንዲሁም “የሀሰት ምስክሮች” በማቅረብ እንደገና የመታየት ዕድል ለመፍጠር እየተነገረ እና በተግባር እየተፈጸመ ያለው አጠቃላይ ወደኋላ የመንሸራተት ሁኔታ አንቅልፍ ባያሳጣኝም ከፉኛ አሳስቦኛል፡፡ ይኸ ነገር ሙሉ በሙሉ ትክክል አይደለም ለማለት ባይዳዳኝም የጥርጣሬ ጠረኑ ግን እየሸተተኝ ነው፡፡ ኬንያታ ከተከሰሰበት የሰብአዊ መብት ጥሰት ነጻ በመሆን ከዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት/አይይሲ መዳፍ እንዲወጣ መድረኩ እየተመቻቸ ነውን?

ዓለም አቀፉ የወንወጀለኞች ፍርድ ቤት/ICC ቀደም ሲል በሰብአዊ መብት ጥሰት ክስ መስርቶባቸው የነበሩትን ኡሁሩ ኬንያታ እ.ኤ.አ ከጃንዋሪ 2012 ጀምሮ የኬንያ ርዕሰ ብሄር ሆነው ስልጣን ከተቆናጠጡ በኋላ የክስ ሂደቱን የማቆየት፣ የማዘግየት እና የማቋረጥ አድሏዊ ጥረቶችን በማድረግ አዝማሚያ ላይ ይገኛል፡፡ በተባበሩት መንግስታት የኬንያ አምባሳደር ሆነው በመስራት ላይ የሚገኙት ማቻሪያ ካማው እ.ኤ.አ ሜይ 2013 በተጻፈ “የሚስጥር ደብዳቤ” ለተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤት ፕሬዚዳንት የኡሁሩ ኬንያታ ጉዳይ ከዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት እጅ ወጥቶ በኬንያ ፍርድ ቤት እንዲታይ ትዕዛዝ እንዲሰጥ የሚጠይቅ ባለ 13 ገጽ የተማጽኖ  አቤቱታ አቀረቡ፡፡ በዚያ ወር የኢትዮጵያ የይስሙላው ጠቅላይ ሚኒስትር እና የአፍሪካ ህብረት ተዘዋዋሪ ሊቀመንበር ኃይለማርያም ደሳለኝ ንዴት እና ስሜታዊነት በተቀላቀለበት አኳኋን ዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት በጥቁር አፍሪካውያን መሪዎች ላይ የሚያካሂደው “የዘር ማደን” ዘመቻ መቆም አለበት የሚል ክስ በጩሀት አሰሙ፡፡ እ.ኤ.አ ጁን 2013 ዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት የኡሁሩ ኬንያታን የክስ ሂደት ጉዳይ በማስመልከት የኬንያታ ወንጀል መከላከል ቡድን አባላት በቂ ማስረጃዎችን ማሰባሰብ እና ማቅረብ እንዲችሉ በማለት የክስ ሂደቱ እስከ ኖቬምበር 12/2013 ድረስ እንዲዘገይ ብይን ሰጠ፡፡ እ.ኤ.አ መስከረም 2013 ዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት የኬንያታ እና የሩቶን ሁለቱንም ክሶች ውድቅ እንዲያደርጋቸው አቶ ኃይማርያም ደሳለኝ በይፋ ጠየቁ፡፡ በሌላ በኩልም አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ በተባበሩት መንግስታት 68ኛ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ በመገኘት ዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት “በኬንያ መሪዎች ላይ ክስ በመመስረት መሪዎቹ ህገመንግስታዊ ኃላፊነቶቻቸውን በአግባቡ መወጣት እንዳይችሉ ያላቸውን አቅም” ያዳከመ መሆኑን በመግለጽ ጉባኤው ክሶቹ እንዲሰረዙ ውሳኔ ቢያሳልፍ “በኬንያ ለሰላም ግንባታው እና ለብሄራዊ ዕርቅ ሂደቱ ወሳኝ ድጋፍ እንደሚያደርግ“ ለጉባኤው ጩኸታቸውን አሰምተዋል፡፡

እ.ኤ.አ ኦክቶበር 2013 የአፍሪካ ህብረት/AU በህብረቱ ጽ/ቤት ልዩ ጉባኤ በማድረግ የኬንያታ እና የሩቶ የክስ ሂደት ጉዳይ ከዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ተነስቶ በኬንያ ፍርድ ቤቶች መታየት እንዲችል ለዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት/ICC ጥያቄ አቀረበ፡፡ ይህ ካልሆነ ግን እንደ አማራጭ የአፍሪካ የህብረቱ አገሮች በ በደቦ “ከሮም ስምምነት” እራሳቸውን እንዲያገሉ ለማድረግ ዛቻ አሰሙ፡፡ በዚህም መሰረት አፍሪካውያንን እያሳደደ ከሚያድነው “ዘር አዳኝ” ፍርድ ቤት ለማዳን እና ደህንነታቸው እንዲጠበቅ ለማድረግ የሚል ሀሳብን መሰረት በማድረግ በአዲስ አበባ ከተማ ስብሰባቸውን አደረጉ፡፡ መሪዎቹ ከዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት በተጻራሪ በመቆም ባዶ፣ የተጋነነ እና እራሳቸውን ከፍ ከፍ የሚያደርግ ጩኸትና አምቢልታ አሰሙ፡፡ ሆኖም ግን ከሮማ ስምምነት እራስን ማግለል የሚለው “የብዙህን ስምምነት መጣስ” ጩኸትና ሴራ ሳይሳካ ከሸፈ፡፡ ከሮማ ስምምነት በደቦ እንወጣለን የሚለው ስሜታዊነት እና እብደት የተሞላበት ማስፈራሪያ ባዶ ጩኸት ከመሆን ባለፈ የፈየደው ነገር የለም፡፡ በቀጣይነትም የአፍሪካ ህብረት የኬንያታ የፍትህ ሂደት ጉዳይ ለአንድ ዓመት እንዲዘገይ ለተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤት ጥያቄ አቀረበ፡፡ ሆኖም ግን እ.ኤ.አ በኖቬምበር 2013 አጋማሽ የፍትህ ሂደቱ ለአንድ ዓመት እንዲዘገይ የቀረበውን ጥያቄ የጸጥታው ምክር ቤት ውድቅ በማድረግ ውሳኔ አሳለፈ፡፡ ይህንንም በማስመልከት በተባበሩት መንግስታት የኬንያ አምባሳደር የሆኑት ካማዉ እንዲህ በማለት ደነፉ፣ “የፍርድ ሂደቱን ለማዘግየት የቀረበው ጥያቄ ተቀባይነትን አላገኘም፣ ምክንያት እና ህግ በመስኮት ተወርውረዋል፣ ፍርኃት እና አለመተማመን እንዲነግሱ ተፈቅዶላቸዋል፡፡“ በሌላ በኩል የሚያስገርመው ነገር ግን ዩናይትድ ስቴትስ ያልተጠበቀ ጥሩ ነገርን አደረገች፡፡ በተባበሩት መንግስታት የዩናይትድ ስቴትስ አምባሳደር የሆኑት ሳማንታ ፓወር እንዲህ በማለት የመንግስታቸውን አቋም ግልጽ አድርገዋል፣ “በ2008 ድህረ ምርጫ በኬንያ ለተፈጸመው የኃይል እርምጃ ሰለባ ለሆኑት ቤተሰቦች የፍርድ ሂደት ለመጀመር ማስረጃዎችን የመገምገም እና የማሰባሰብ ስራ ከአምስት ዓመታት በላይ ጊዜ ፈጅቷል፡፡ በዚያ ብጥብጥ በተወሰደው የኃይል እርምጃ ሰለባ ለሆኑ ወገኖች ፍትህ መስጠት ለሀገሪቱ ዘለቄታዊ ሰላም እና ደህንነት ወሳኝ ጉዳይ እንደሆነ እናምናለን፡፡ በሰዎች ላይ በሚፈጸሙ ሰብአዊነትን በሚጥሱ ወንጀሎች ላይ ተጠያቂነት እንዲኖር እና ወንጀል ፈጻሚዎችም ለህግ እንደቀርቡ የማድረግ ግዴታ አለብን፡፡“ በማለት ግልጽ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

ባለፈው ሳምንት የኡሁሩ ኬንያታን የፍትህ ሂደት አስመልክቶ “አንድ ምስክር የምስክርነት ቃል ላለመስጠት እራሱን ካገለለ እና ሌላኛውም የሀሰት ማስረጃ አቅርቧል“ ከተባለ በኋላ እ.ኤ.አ ፌብሯሪ 5/2014 ለመታየት ተይዞ የነበረው ቀጠሮ የዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት አቃቢ ሕግ በኬንያታ ላይ የቀረቡትን ማስረጃዎች እንደገና ለመገምገም እንዲቻል ሌላ ሶስት ተጨማሪ ወራት እንደጠየቁ እና የፍትህ ሂደቱ እንደተላለፈ ግልጽ ተደርጓል፡፡

የውሸት ማስረጃ እና የሀሰት ምስክሮች ሲባል ለምን?

ባለፈው ወር በዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት አቃቤ ሕግ ቢሮ ውስጥ “የውሸት ማስረጃ“ እና “የሀሰት ምስክሮች“ የሚሉ ስሜትን ዕረፍት የሚነሱ ንግግሮች ተደምጠዋል፡፡ እ.ኤ.አ ዴሴምበር 19/2013 የዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ዋና አቃቤ ሕግ ወይዘሮ ፋቱዋ ባንሱዳ እንዲህ በማለት ተናግረዋል፣ “ዴሴምበር 4/2013 በዚህ ጉዳይ ላይ ሁለተኛ ቁልፍ ምስክር ተብሎ የቀረበው በወሳኙ ድርጊት ላይ ለፍትህ ሂደቱ የውሸት መረጃ መስጠቱን አምኗል፡፡ ይህ ምስክር በአሁኑ ጊዜ ከፍትህ ሂደቱ የምስክርነት ዝርዝር ውስጥ እራሱን አግልሏል… አሁን በእጆቼ ያሉትን ማስረጃዎች በጥንቃቄ መርምሬ እና እንዲሁም የእነዚህ እራሳቸውን ከምስክርነት ያገለሉት ሁለት ምስክሮች በፍትህ ሂደቱ ላይ የሚያስከትለውን አሉታዊ እንደምታ ከግንዛቤ በማስገባት የሚስተር ኬንያታን የክስ ሁኔታ ስገመግመው ከፍተኛ የሆነ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ መረጃ ሆኖ ስላላገኘሁት በአሁኑ ጊዜ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚካሄድን የፍትህ ሂደት አያሟላም ወደሚል መደምደሚያ ላይ ደርሻለሁ… በዚህም መሰረት እስካሁን ድረስ ያደረግኋቸውን ጥረቶች ምሉዕ ለማድረግ ተጨማሪ መረጃዎችን እና እነዚህ መረጃዎች በፍትህ ስርዓት ሂደቱ ዘንድ መኖር ያለበትን የቢሮዬን ዝቅተኛውን የመረጃ ድንበር በትክክል ማሟላት አለማሟላታቸውን ለማረጋገጥ ተጨማሪ ጊዜ ያስፈልገኛል…“ በማለት ሀሳባቸውን አጠቃለዋል፡፡

እ.ኤ.አ ማርች 2013 የዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት አቃቤ ሕግ በቀድሞው የኬንያ ሲቪል ሰርቪስ ኃላፊ በነበሩት እና አብረው ይከላከሉ በነበሩት ፍራንሲስ ሙታውራ  ላይ ተመስርቶ የነበረውን የወንጀል ክስ ጉዳይ ውድቅ ባደረጉበት ጊዜ ወይዘሮ ቤንሱዳ የእኒሀ ሰው ጉዳይ ውድቅ መደረጉ እኔ በያዝኩት በአዲሱ የኬንያ ዕጩ ተመራጭ ፕሬዚዳንት የፍትህ ሂደት ጉዳይ ላይ ምንም ዓይነት ተጽዕኖ አይኖረውም በማለት ተናግረው ነበር፡፡ “የሁኔታዎች አመክንዮ እንደሚያሳየን አንድ የክስ ጉዳይ ውድቅ ተደርጎ ተከሳሹ ሲሰናበት ይህ ነጻ የተለቀቀው ሰው በሌላው በክስ ሂደት ላይ ላለው የወንጀል ተጠርጣሪ ተመሳሳይ ክስ በቀጥታ በሚታይ መልኩ ቀጥተኛ ያልሆነ ተባባሪ ሆኖ ተጽዕኖ ላያሳይ ይችላል፡፡ ብዙ ሰዎች በአንድ ዓይነት የክስ ጉዳይ ላይ ክስ ተመስርቶባቸው ሁሉም በአንድ ዓይነት ያለምንም ተለዋዋጭነት በእያንዳንዱ ተከሳሽ ላይ አንድ ዓይነት ብይን ሊሰጥ ይገባል ለማለት አይቻልም… ኬንያታ ግን ለእያንዳንዱ በወንጀል ተጠያቂ ግለሰብ የገንዘብ እና የሎጅስቲክስ ቀጥተኛ ድጋፍ ሲያደርጉ እንደነበር በተጠርጣሪነት ክስ ተመስርቶባቸው እያሉ ሙታውራ በበኩሉ ከሙንጊኪ/Mungiki (የወንጀል ባለሙያዎች ድርጅት) ድጋፍ ያገኝ ነበር የሚል የተጠርጣሪነት ክስ ተመስርቶበት እያለ እንዲሁም ይህ ተጠርጣሪ ለፒኤንዩ ጥምረት/PNU Coalition አባላት ድጋፍ ለማድረግ ሲባል በናኩሩ እና ናይቫሻ/Nakuru and Naivasha አባላት ላይ ወንጀል እንዲፈጽም ተቋማዊ ድጋፍ ሲደረግለት እንደነበር የተጠርጣሪነት ክሱ ያመላክታል፡፡“

ኬንያታን እና ሩቶን ከዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት መዳፍ ለማውጣት በመቅረብ ላይ ያሉ የክርክር ጭብጦች

ኬንያታን እና ሩቶን ከዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት መዳፍ ለመልቀቅ ወይም ደግሞ ተጠርጣሪዎቹ የስልጣን ዘመናቸውን እስኪያጠናቅቁ “በማዘግየት“፣ አንድ ዓመት “የማዘግየት” ዕድል በመስጠት፣ የክስ ሂደቱን ላልተወሰነ ጊዜ በማስተላለፍ፣ የዓለም አቀፉን የወንጀለኞች የክስ ሂደት በማቋረጥ እና ጉዳዩ በኬንያ ፍርድ ቤቶች መታየት እንዲችል በማድረግ በርካታ የህግ፣ የፖለቲካ እና የፖሊሲ የመከራከሪያ ጭብጦች አስከዛሬ ቀርበዋል፡፡ ኬንያታን ከዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ነጻ ለማውጣት የሚያቀርቡ ዋና ዋናዎቹ የመከራከሪያ ጭብጦች እንደሚከተለው ናቸው፣ 1ኛ) የኬንያታ እና የሩቶ የክስ ጉዳይ በዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት መታየቱ የኬንያን ሉዓላዊነት ይዳፈራል፣ 2ኛ) እ.ኤ.አ ማርች 2013 በኬንያ በተደረገው አገር አቀፋዊ ምርጫ ኬንያታ እና ሩቶ ያለመከሰስ መብት ተጎናጽፈዋል ምክንያቱም መመረጣቸው “ነጻ“ መሆናቸው ተረጋግጧል፣ 3ኛ) በኬንያታ እና በሩቶ ላይ የቀረበው ክስ ማስረጃ “ውሸት እና በፈጠራ ላይ የተመሰረተ ነው“፣ 4ኛ) የዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት አቃቤ ሕግ ፍትሀዊ አይደሉም፣ እናም አላግባብ ስልጣናቸውን በመጠቀም የክስ ሂደቱን በማጣመም የህግ የበላይነት እንዳይሰፍን በኬንያታ እና በሩቶ ላይ ተግባራዊ ያደርጉታል፣ 5ኛ) ዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት እና ዋና አቃቤ ሕጉ ያልተገደበ እና ለማንም ተጠሪነት የሌለው ስልጣን ተሰጥቷቸዋል፣ 6ኛ) ዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት በኬንያታ እና ሩቶ ላይ ብይን በመስጠት ለተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤት የተሰጠውን ስልጣን በመጋፋት የስልጣን መብቱን ይነጥቃል፣ 7ኛ) የተባበሩት መንግስታት ቻርተርን እና በኬንያታ እና ሩቶ ላይ የተፈጸመውን የፍትህ ሂደት ህገወጥ እና ድርጅቱ ከተሰጠው የስልጣን ኃላፊነት (ከተሰጠው የህግ ስልጣን በላይ) ስለሆነ የሮማ ስምምነትን ይጥሳል፣ 8ኛ) ኬንያ ፈቃደኝነቱ እና ችሎታውም ስላላት ወንጀለኞችን በሮማ ስምምነት መሰረት በእራሱ አገር ለመዳኘት ዝግጁ ናት፣ 9ኛ) ዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት በኬንያታ እና በሩቶ ላይ የመሰረተው ክስ መሰረተቢስ ነው፡፡

አቧራው መርጋት ከጀመረ በኋላ የአፍሪካ አምባገነን መሪዎች በእርግጠኝነት የሚፈልጉት የእያንዳንዳቸው ጉዳይ ከተለመደው ፍትሀዊ የህግ ስርዓት ውጭ በተለዬ መልኩ ለእነሱ በሚስማሙ ህጎች መዳኘት እንደሚኖርባቸው ነው፡፡ አምባገነኖቹ የአፍሪካ መሪዎች እራሳቸው በእጃቸው መርጠው በሚያስቀምጧቸው አቃቢያነ ሕጎች እና ዳኞች ብቻ የፍትህ ሂደት ጉዳያቸው እንዲታይ እና የህግ ውሳኔም በእነርሱው በኩል ብቻ እንዲያገኙ የዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት እንዲፈቅድላቸው ይፈልጋሉ፡፡

የወደፊቱ አደገኛ ሁኔታ፡ “በሰው ልጅ ላይ ወንጀል ለሚፈጽሙ የአፍሪካ መሪዎች የሚስማማ ኢፍትሀዊ ህግ”

በአሁኑ ጊዜ የሚታዩት የፍትህ ሂደቱን የማዘግየት፣ ቀጠሮዎችን የማስተላለፍ እና የማቆየት ሁኔታ በዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት እና በኬንያታ፣ እንዲሁም በአፍሪካ ህብረት እና በተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤት መካከል ኬንያታን ከዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት መዳፍ ለማስለቀቅ የሚደረግ የፖለቲካ “ስምምነት” ምልክቶች እና አዝማሚያዎች ያሉ አይመስልምን? ማስረጃ ተብለው ቀደም ሲል ተይዘው የነበሩት ምስክሮች የሚያምኑበትን እንደገና ሲክዱ እና የሀሰት ምስክርነት ሲሰጡ ሲታይ የፍርድ ሂደቱን ፊኛ መሆን (የሀብረተሰቡን ሀሳብ ለመገምገም እና ወደፊት ሊነሳ የሚችል ተቃውሞ ካለ ለማጤን) እና የዓለም አቀፉን ማህበረሰብ አመለካከት በማየት ማስረጃ አልተገኘም በሚል ሰበብ በኬንያታ ላይ የቀረበውን ክስ ውድቅ በማድረግ ኬንያታን ከዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ለመልቀቅ የሚደረግ የፖለቲካ ትወና አንድ አካል አይመስልምን? ጉዳዩ ሲታይ በዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት፣ በአፍሪካ ህበረት፣ በኬንያታ እና በተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤት መካከል የህግ የቴክኒክ ጉድለት ስበብ ያለበት በማስመሰል ኬንያታን ለመልቀቅ እየተደረገ ያለ ተውኔትነት መሰል ነገር (ሻጥር አላልኩም) ያለበት አይመስልምን? ስህተት ባለበት ሁኔታ አትገንዘቡኝ፡፡ ወደፊት የሚመጣውን አዳጋች ሁኔታ አስቀድሜ በማየት ነው ጥያቄዎችን እየጠየቅሁ ያለሁት፡፡ ይኸው ነው!

እ.ኤ.አ በ2014 ኡሁሩ ሙጋይ ኬንያታ “በመረጃ እጥረት ምክንያት“ ከዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት መዳፍ በመውጣት ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እንዲህ ሊሉ ይችሉ ይሆን? “ነግሪያችሁ አልነበረም፣ ይኸውላችሁ እኔ ነጻ ሰው ነኝ፣ የዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት በእኔ ላይ የመሰረታቸው ክሶች የዘር አደና እና በህግ ጥላ ስር ሰው ገዳይ ሆኖ ከመቅረብ የዘለለ አልነበረም፡፡ የዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት የአፍሪካን ጥቁር መሪዎች አያሳደደ ነው… አንዱ በመጨረሻ የማነሳው ነገር ደግሞ የሱዳኑ ኦማር አልባሽር በሀሰት የተከሰሰ መሆኑን ነው፡፡ በእርሱ ላይ በሀሰት የመሰረታችሁትን ክስም አንሱለት…”

ከፈለጋችሁ ተጠራጣሪ ብላችሁ ልትፈርጁኝ ትችላላችሁ፡፡ ይኸ የሙያ ጉዳይ ነው፡፡ የመከላከል የህግ ባለሙያዎች በጣም ሲበዛ ተጠራጣሪዎች እና ገና በሩቁ ማነፍነፍ የሚችሉ የማሽተት የስሜት ህዋሳቶች ያሏቸው ናቸው፣ (በጣም ትንሽ የሻጥር ጠረን ቢሆንሞ በሚገባ ማሽተት እችላለሁ)፡፡ ስለህግ ባለሙያዎች በምናገርበት ጊዜ የመከላከል የህግ ባለሙያዎች በተደጋጋሚ የሚጠቀሙባቸው ዘዴዎች “ጉዳዩን መካድ፣ ማዘግየት እና መከላከል“ የሚሉት ናቸው፡፡ ዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት “ማቆየት፣ ማዘግየት እና ክሱን መሰረዝ“ የሚሉ አዲስ ዘዴዎችን በመፍጠር ስሜት አልባ በመሆን አወዛጋቢ ከሆነው የፍርድ ሂደት ኬንያታን ነጻ ለማውጣት የሚሞክር ከሆነ በኬንያታ የፍትህ ሂደት ላይ መገረም የምጀምር ይሆናል፡፡ ሰለዚህ በጣም አስባለሁ፡፡ ጮክ ብዬም እናገራለሁ፡፡ እኔ የቆዬ፣ የዘገዬ እና የተሰረዘን ፍትህ እንደተካደና አንደተነፈገ ፍትህ እቆጥረዋለሁ፡፡

በኬንያታ ላያ ያለ ማስረጃ

አንድ ጉርሻ ብቻውን አንደማያጠግብ ሁሉ አንድ ወይም ሁለት ምስክሮች ብቻም በወጀንጀል ጉዳዩ ላይ የሚፈጥሩት ጫና አይኖርም:: በሮማ ስምምነት አንቀጽ 25 (3) (a) መሰረት በሰው ዘር ላይ የተፈጸመ ወንጀል በማለት ዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት በኬንያታ ላይ 5 ዋና ዋና ክሶችን በመዘርዘር ክስ መስርቷል፡፡ እነርሱም፣ ግድያ፣ (አንቀጽ 7 (1) (a)፣ ማጋዝ ወይም ከህግ አግባብ ውጭ ከቦታ ማፈናቀል፣ (አንቀጽ 7 (1) (d)፣ አስገድዶ መድፈር፣ (አንቀጽ 7 (1) (g)፣ ማሰቃየት፣ (አንቀጽ 7 (1) (h)፣ እና ሌሎች ኢሰብአዊ ድርጊቶች፣ (አንቀጽ፣ 7 (1) (k) ናቸው፡፡ ክሱ ለህሊና አስደንጋጭ እና በሚሰቀጥጥ ሁኔታ ጥልቅነት ባለው መልኩ በ155 ገጾች በመቶዎች የሚቆጠሩ ምስክሮችን መሰረት አድርጎ የተዘጋጀ ሰነድ ነው፡፡ የቅድመ ፍትህ ምርመራ ቻምበሩ በኬንያታ ላይ ስለሚመሰረተው ክስ እንዲህ ሲል ማረጋገጫ በመስጠት ጽፏል፣ “አቃቤ ሕጉ በሰው ልጅ ወንጀል መፈጸም ላይ ከተያያዙ ነገሮች ጋር በማየት ክስ ለመመስረት የሚያስችል መሆኑን ያሟላል በማለት መረጃ ሰጥተዋል፡፡ “በኬንያታ ላይ የቀረቡት ብዙዎቹ ማስረጃዎች ነጻ እና በእውነታ ላይ የተመሰረቱ ናቸው፡፡ ለምሳሌ ዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት የቅድመ ምርመራ ቻምበር “እ.ኤ.አ ጃኗሪ 3/2008 በናይሮቢ ክለብ… ሚስተር ኬንያታ ከሙንጊኪ አባላት ጋር (አንዳንድ ጊዜም የኬንያ የማፊያ የወንጀል ድረጅት እየተባሉ ከሚጠሩት ጋር) ተገናኝተዋል፡፡ እናም ክስ የተመሰረተበትን ወንጀል እንዲፈጽሙ ቀጥታ ተዕዛዝ ሰጥተዋል በማለት ወስኗል፡፡“ ኬንያታ እና ሌሎች በጋራ በመሆን “የቀድሞው ፕሬዚዳንት የኪባኪ ፓርቲ የሆነው የብሄራዊ አንድነት ፓርቲ/National Unity Party(PNU) አባላት በማንኛውም መንገድ ቢሆን ስልጣናቸውን እንደያዙ እንዲቆዩ፣ እንዲሁም በሰዎች ላይ ወንጀሎች ቢፈጸሙም ፖሊስ በቦታው ደርሶ መቆጣጠር እንዳይችል እና እንዳይገኝ በማድረግ የድርጅታዊ ፖሊሲ በማውጣት ለመተግበር ስምምነት አድርገው የትወና ድርጊታቸውን ፈጽመዋል፡፡“ በማለት ሁኔታውን ሊያሳዩ የሚችሉ በቂ ማስረጃዎች እንደሆኑ ግልጽ አድርገዋል፡፡ ኬንያታ እና ግብረ አበሮቻቸው… “በብርቱካናማው ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ/Orange Democratic Movement (ODM) ደጋፊዎች አባላት ላይ የጋራ ዕቅድ በማውጣት መጠነ ሰፊ እና ስልታዊ ጥቃቶች፣ 1ኛ) የብቀላ ጥቃቶችን እንደፈጸሙባቸው፣ 2ኛ) የብቀላ ጥቃቱን ለመከላከል ወይም ደግሞ ለማስቆም እንዳይቻል ሆን ተብሎ ታስቦበት የፖሊስ እርምጃ እንዲታቀብ በማድረግ የሚሉት በቂ ማስረጃዎች መሆናቸውን ያመላክታሉ፡፡

ኬንያታ “በፒኤንዩ/PNU እና በሙንጊኪ/Mungiki ወንጀለኛ ድርጅት መካከል የአስታራቂነት ሚና የሚጫወቱ መስለው በመቅረብ እ.ኤ.አ ከኖቬምበር 2007 ጀምሮ ተከታታይ ስበስባዎችን በማካሄድ” እንዲሁም ደግሞ “የፒኤንዩ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት፣ ፖለቲከኞች፣ የንግዱ ማህበረሰብ እና የሙንጊኪ የአመራር አባላት በዴሴምበር 2007 በሚደረገው ሀገር አቀፍ ምርጫ የሙንጊኪ አባላት ለመንግስት ድጋፍ እንዲያደርጉ“ ያደረጉትን በበቂ ሁኔታ ሊያሳይ የሚችል መረጃ መሆኑን ያመላክታል፡፡ ከድህረ ምርጫው ማግስት ኬንያታ እና ሌሎች በአንድነት ሆነው “በስምጥ ሸለቆ አካባቢ በብርቱካናማው ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ አባላት ላይ የበቀል እርምጃ እንዲወስዱ የሙንጋኪ አባላትን ተከታታይ ስብሰባ እየጠሩ ሲያስተባብሩ እንደነበር፣ እንዲሁም ፕሬዚዳንቱ ቃለመሃላ ከፈጸሙ በኋላ የብሄራዊ አንድነት ፓርቲ/PNU ይዞታዎች እንዲጠናከሩ“ በማለት የሙንጊኪ/Mungiki አባላት ጥቃት እንዲፈጽሙ ሲያስተባብሩ እንደነበር በቂ መረጃዎች እንዳሉ ያመላክታሉ፡፡ በኬንያታ እና በሌሎች “የኬንያ ፖሊሶች የተቀሰቀሰውን ብጥብጥ እንዳይከላከሉ እና እንዳያቆሙት እንዲሁም ጥቃቱን በሚፈጽሙ በጥባጮች ላይ እርምጃ እንዳይወስዱ በማሰብ የጋራ ዕቅድ ነድፈው የራሳቸውን ድርሻ ሲያበረክቱ እንደነበር“ የሚያመላክቱ ከበቂ በላይ የሆኑ መረጃዎች አሉ፡፡

ሁለቱ የሀሰት ማስረጃ ምስክሮች የአቃቤ ሕጉን ጉዳይ ፍጹም የሚያሳንሱ በመምሰል የዓለም አቃፉን የወንጀለኞች ፍርድ ቤት አቋም በመረጃዎቹ ላይ የእምነት መሸርሸር በማሳየት ውኃ የሚቋጥሩ መስለው ያለመታየት አዝማሚያን አንጸባርቋል፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ ሁለቱ ምስክሮች ለምን የሀሰት ምስክርነት እንደሰጡ፣ እንዲሁም የክስ ሂደቱ ከመጀመሩ በፊት የአቃቤ ሕጉ ቢሮ አስተማማኝ እና ጠንካራ መረጃዎችን ለምን እንዳላሰባሰበ ግልጽ አይደለም፡፡ ሆኖም ግን በኬንያታ ላይ ምስክርነት ለመስጠት የሚቀርቡት ማስፈራሪያ የደረሰባቸው እና እንዳይመሰክሩም ጉቦ የተሰጣቸው ናቸው፡፡ እ.ኤ.አ ፌብሯሪ 13/2013 አቃቤ ሕግ ወይዘሮ ቤንሱዳ ኬንያታ በተያዘው ጉዳያቸው ላይ ምስክርነት እንዳይሰጥባቸው በማሰብ ጉቦ በመስጠት ምስክሩ አስረጅ ሆኖ እንዳይቀርብ እና ከምስክርነት እንዲያፈገፍግ አድርገዋል በማለት ተናግረዋል፡፡ ወይዘሮ ቤንሱዳ እንዲህ በማለትም ሀሳባዋቸውን አጠናክረዋል፣ “እ.ኤ.አ ሜይ 2012 አራተኛ ምስክር ሆኖ የቀረበው ሰው በተደረገለት ቃለመጠይቅ መሰረት የኬንያታ ኡሁሩ ተወካይ የሆኑ ሰዎች በኬንያታ ላይ ምስክርነት እንዳይሰጥ የገንዘብ ጉቦ እንደሰጡት እና እንደተቀበለ ግልጽ አድርጓል… ይህ ምስክር የጉቦ አሰጣጡን ዕቅድ ሊያስረዱ የሚችሉ የኢሜል አድራሻውን እና የባንክ ምዝገባ መረጃዎችን አቅርቧል፡፡ በእንደዚህ ያለ ተደራራቢ መግለጫዎች አቃቤ ህጉ እንደዚህ ያለውን ለምስክርነት መጥራት ጥሩ አይደለም የሚል ሀሳብ አላቸው፡፡ የኬንያታ የመከላከያ ቡድን በበኩሉ “በእራሳቸው ፈቃድ ያመኑትን ወንጀለኞች ምሰከሮች” የዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት አሳልፎ ለኬንያ እንዲሰጥ እና የኬንያ ፍርድ ቤት ሙሉ ፍርዳቸውን እንዲሰጣቸው ጠይቋል፡፡ አቃቤ ህግ ቤንሱዳ ፍርድ ቤቱ ለምስክሮቹ የህግ ከለላ እንዲሰጥ እንዲሁም የድምጽ እና የምስል ማዘበራረቅም እንዳይኖር፣ መረጃ በመፈለጉ ረገድ የውሸት ስም የመስጠት እና ካሜራም ያለመጠቀም እንዲቻል  ጠይቀዋል፡፡“ በኬንያ መንግስት ከፍተኛ የሆነ የበቀል እርምጅ ያጋጠማቸው ምስክሮች በብርሀን ፍጥነት ተግልብጠው ህይወታቸውን ለማዳን ሲሉ የሀሰት ምስክርነት መስጠታቸውን ቢናገሩ ማንንም ሊያስገርም የሚችል ጉዳይ ሊሆን ይችላልን?

ሁሉም “የሀሰት ምስክሮች“ “የውሸት ምስክሮች“ ቅንነት የጎደላቸው ንግግሮች ናቸው የሚል እምነት አለኝ፡፡ በኬንያታ ላይ ለቀረበው ክስ በጥቂት ምስክሮች ብቻ ላይ ተመስርቶ የሚከናወን ጉዳይ አይደለም፡፡ ሆነኖም ግን በመቶዎች የሚቆጠሩ ማስረጃ የሚሰጡ ምስክሮችን ማግኘት ይቻላል፡፡ ኬንያታን ወደ ፍትህ ሂደቱ ለማቅረብ እና ፍርድ ቤቱም የኬንያታን ጥፋት ከምንም ጥርጣሬ በላይ ሊያስረዱ የሚችሉ “ከበቂ በላይ መረጃዎች” እንዳሉ መታወቅ አለበት፡፡ የዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት አቃቤ ሕግ በያዟቸው በአንድ ወይም ደግሞ በሁለት ምስክሮች ላይ ብቻ መሰረት በማድረግ እና የያዙትን የህግ ጉዳይ እውነትነት እና የምስክሮች ቃላቸውን የማጠፍ ክህደት በመመልከት የፍትህ ሂደቱን የተሟላ ሊያደርገው አይችልም፡፡ ስለዚህ ጉዳይ ተራራ የሚያህል የተከመረ መረጃ አለ፡፡

የዓለም አቀፉን የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ምስክርነት የመከላከል ፕሮግራም ጊዜው አሁን አይደለምን?

ምስክሮችን ማስፈራራት፣ የገንዘብ ጉቦ መክፈል፣ ቃለመኃላ ፈጽመው በትክክል መስክረው የነበሩትን ቃላቸውን እንዲያጥፉ በማድረግ የተለየ ታሪክ እንዲያቀርቡ በተለይም በከፍተኛ ወንጀል በሚጠረጠሩ ሰዎች ላይ ምንም አዲስ ነገር አይደለም፡፡ ከፍትህ ሂደቱ በፊትም ሆነ በኋላ ቃልን በማጠፍ የሀሰት ምስክርነት መስጠት የተለመደ ጉዳይ ነው፡፡ ከአቃቤ ሕጎች ጋር እንዳይተባበሩ እና የምስክርነት ቃላቸውን እንዳይሰጡ የማስፈራራት ድርጊት የተፈጸመባቸው ሰዎች ወይም ደግሞ ሆን ተብሎ የፍርድ ሂደቱ በሚሰማበት ዕለት በቦታው ተገኝተው የምስክርነት ቃላቸውን እንዳይሰጡ ማድረግ የተለመደ ተግባር ነው፡፡ ለምሳሌ በማፊያ አለቆች እና በሌሎች ወንጀለኞች የፍትህ ሂደት ወቅት ምስክሮች (አስረጅዎች) ቃላቸውን አጥፈው ወይም ክደው መመስከር ወይም ደግሞ ከምስክርነት እራሳቸውን ያገላሉ ምክንያቱም በእራሳቸው እና በቤተሰቦቻቸው አባላት ላይ በሚደረግባቸው የማስፈራራት ድርጊት የተነሳ ነው፡፡ ዳኞች የጥፋተኝነት ውሳኔ እንዳይሰጡ በወንጀለኛ አለቆች ጉቦ ይሰጣቸዋል፡፡ በፍትሀዊ የዳኝነት ጊዜም አቃቢ ሕጎች ምስክሮች ሚስጥራዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ላይ ለመመስከር “ተባባሪ” እንዳይሆኑ ያነሱ ክሶች እና ቀላል ውሳኔዎች እንዲሰጡ እና ሌሎች ጥቅሞች በመስጠት የምስክርነት ቃል እንዳይሰጡ ማስፈራሪያ ይደረግባቸዋል፡፡ የኬንያታ ምስክሮች ቃላቸውን የማጠፍ ወይም የመካድ ሁኔታ መታየቱ ያልተቋጩ እና እንቆቅልሽ የሆኑ ጥያቄዎችን እንድናነሳ ያስገድዱናል፡፡ ምስክሮቹ የምስክርነት ቃላቸውን የሰጡት በትክክል ክደው ሳይሆን ለሕይዎታቸው ፈርተው ነው፡፡ ለምስክርነት በፍትህ ሂደቱ ላይ ቢገኙ እና ምስክርነት ቢሰጡ የሚደርስባቸውን በቀል በመፍራት ነው፡፡ እነዚህ ምስክሮች ክደው የምስክርነት ቃላቸውን መስጠታቸው እንደ መልካም ነገር መታየት የለበትም ነገር ግን መታየት ያለበት የፍርድ ሂደቱ እና የተከሳሾቹ የማስፈራራት ውጤት ተደርጎ ሊወሰድ ይገባል፡፡

በኬንያታ የፍትህ ሂደት ላይ ክደው ቃል በሰጡ ምስክሮች ችግር ጉዳይ ላይ በቂ የሆነ መፍትሄ አለ የሚል እምነት አለኝ፡፡ ይኸውም ምስክሮች ያዩትን የሰሙትን ሳይፈሩ የእምነት ቃላቸውን ያለምንም ፍርሀት መስጠት እንዲችሉ “ዓለም አቀፋዊ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት የምስክርነት ከለላ ፕሮግራም” መፍጠር እንዳለበት ማወቅ አለበት፡፡ በዩናይት ስቴትስ የፌዴራል የምስክሮች ከለላ ፕሮግራም ከፍርድ ሂደቱ በፊት፣ በፍርድ ሂደቱ ወቅት እና ከፍርድ ሂደቱ በኋላ ለምስክሮቹ በቂ ከለላ ይሰጣል፡፡ በዚህ ፕሮግራም ምስክሮች እና ቤተሰቦቻቸው አዲስ ማንነት እና መረጃዎች እንዲሁም የቦታ ለውጥ ሁሉ እንዲያደርጉ ይመቻችላቸዋል፡፡ ይህ ፕሮግራም እ.ኤ.አ በ1971 በስራ ላይ መዋል  ከጀመረ ወዲህ ወደ 10,000 የሚሆኑ ምስክሮች እና ቤተሰቦቻቸው በምስክርነት ከለላ ፕሮግረሙ አገልግሎት አግኝተዋል፡፡ በሚያስገርም ሁኔታ “95 በመቶው የሚሆኑት የምስክርነት ከለላ ተጠቃሚዎች ወንጀለኞች ናቸው፡፡”

ዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት በሰው ልጅ ላይ ሰብአዊነት የጎደለው ወንጀል በሚፈጽሙ ተጠርጣሪዎች ላይ፣ የዘር ማጥፋት ወንጀል በሚፈጽሙት ላይ እና ሌሎችንም አስቀያሚ ወንጀሎችን በሚፈጽሙ ተጠርጣሪዎች ላይ ምስክርነት ለመስጠት በሚመጡ ምስክሮች ደህንነት ሲባል “የእራሱን የምስክርነት ከለላ ፕሮግራም” መጀመር ይኖርበታል የሚል እምነት አለኝ፡፡ በብዙዎቹ የሙንጊኪ (“የኬንያ ማፊያ” ወሮበላ ወንጀለኞች) ሀሳብ ሳይሆን ትክክለኛ ማስፈራሪያ እና የህግ የቅጣት ሰለባ እንደሚሆኑ ከኬንያ መንግስት ብቻ የተሰጠ ዛቻ ብቻ አይደለም፡፡ ነገር ግን ከመንግስት ጋር መልካም ግንኙነትን ለመፍጠር ሲባል ከተበሳጨው ከእራሳቸው ድርጅት ጋር ጭምርም እንጅ፡፡ የሙንጊኪ ምስክሮች እውነተኛውን የምስክርነት ቃላቸውን እንዲሰጡ ሁኔታዎች ሊመቻቹላቸው ይገባል፡፡ ከኬንያታ ጋር ባለው የፍትህ ሂደት ጉዳይ ላይ እውነታውን ብቻ እንዲመሰክሩ እና የምስክርነት ከለላ ፕሮግራም ከኬንያ ውጭ እንዲሰጣቸው ማድረግ አስፈላጊ ነው፡፡ ከዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት የምስክሮች ከለላ ፕሮግራም ውጭ ተባባሪ የሆኑ ምስክሮችን በማግኘት በእውነታ ላይ የተመሰረተ የምስክርነት መረጃ ለማግኘት አይቻልም፡፡ ምናልባት በጣም ጥቂት ምስከሮች እውነታው እንዲታወቅ እስከ የህይወት መስዋዕትነት ድረስ ለመክፈል ዝግጁ  ሊኖሩ ይችላላ፣ አጅግ በጣም ብዙ ምስከሮች ግን ለህይዎታቸው ፈርተው ድርሽ አይሉም፡፡ ከምስክርነት ከለላ ፕሮግራም ወጭ በአሁኑ ጊዜ በአፍሪካ በስልጣን ላይ ያሉ በሰው ልጅ ላይ ወንጀል የሚፈጽሙ አምባገነኖች በአገራቸው ውስጥ ማንም ቢሆን በእነርሱ ላይ ደፍሮ የምስክርነት ቃል እንደማይሰጥ አስቀድመው በማወቅ የልብ ልብ ተሰምቷቸው በዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት የአሰራር ሁኔታ ላይ እየቀለዱ ይኖራሉ የሚል እምነት አለኝ፡፡ የዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ከኬንያታ ጉዳይ ጋር በተያያዘ መልኩ ጥሩ ትምህርት መቅሰም ይኖርበታል፡፡

የዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ኬንያታን ከመዳፉ ስር እንዲወጣ ሊያደርግ ይችላልን?

የዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት በፖለቲካ ወይም በሌሎች ምክንያቶች ኬንያታን ይለቅቃል የሚል መረጃ ወይም አሳማኝ የሆነ መሰረታዊ ዓላማ የሌለኝ መሆኑን ፍጹም በሆነ መልኩ ግልጽ ማድረግ እፈልጋለሁ፡፡ በዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ተቋሙ ላይ ጥንካሬ  ያለው እምነት አንዳለኝ  እራሴን በፈቃደኝነት “የዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ምስክር” አድርጌ እቆጥራለሁ፡፡ ዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ኬንያታን ከመዳፉ በማውጣት ሊለቅ ይችላል በሚለው የእኔ የእራሴ ንቁ ዕይታ እና የህግ ምናባዊ ጥርጣሬ ላይ ተመስርቶ የሚሰጥን ማንኛውንም ትችት ለመቀበል ዝግጁ ነኝ፡፡ ሁኔታው “የሀሳብ ቤተሙከራ” ነው፣ ግምታዊ የሆኑ እውነትነት ያላቸውን ሃሳቦች እና ምናባዊ ሁኔታዎችን በማየት ሊከሰቱ የሚችሉ ነግሮችን መተንበይ እና በትክክል ሊከሰቱ የሚችሉ የችግሮቹን ውጤቶች ማሰብ መቻል የተሻለ ነገር ነው፡፡ ይኸ ትችት የማይታሰበውን የማሰብ፣ የማይታለመውን የማለም የእራሴ “የሀሳብ ቤተሙከራ” ነው፡፡ ይሄዉም “የዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት በማስረጃ እጥረት ምክንያት የኡሁሩ ሙጋይ ኬንያታን የክስ ጉዳይ ዉደቅ አርጎታል” የሚለዉን አስከፊ ዜና መስማት ስለምፈራም ነው፡፡

በተባበሩት መንግስታት የዩናይትድ ስቴትስ አምባሳደር ከሆኑት ከሳማንታ ፓወር ምልከታዎች ጋር ሙሉ በሙሉ እስማማለሁ፡፡ “በ2008 ድህረ ምርጫ በኬንያ ለተፈጸመው የኃይል እርምጃ ሰለባ ለሆኑት ቤተሰቦች የፍርድ ሂደት ለመጀመር ማስረጃዎችን የመገምገም እና የማሰባሰብ ስራ ከአምስት ዓመታት በላይ ጊዜ ፈጅቷል፡፡ በዚያ ብጥብጥ በተወሰደው የኃይል እርምጃ ሰለባ ለሆኑ ወገኖች ፍትህ መስጠት ለሀገሪቱ ዘለቄታዊ ሰላም እና ደህንነት ወሳኝ ጉዳይ እንደሆነ እናምናለን፡፡ በሰዎች ላይ በሚፈጸሙ ሰብአዊነትን በሚጥሱ ወንጀሎች ላይ ተጠያቂነት እንዲኖር እና ወንጀል ፈጻሚዎችም ለህግ እንደቀርቡ የማድረግ ግዴታ አለብን፡፡“ በሌላ አባባል “ማቆየት፣ ማዘግየት እና ክሱን መሰረዝ፣ ፍትህ እንደተካደ ይቆጠራል! 

ውድቀት ለአምባገነኖች፣ ፍትህ ለብዙሀኑ! 

ጥር 20 ቀን 2006 ዓ.ም

 

 

 

 

Leave a Reply