እሪ ይበል ወንዙ፤ እሪ ይበል ሃይቁ! ከዓለማየሁ ገብረማርያም

Click here for PDF

(Cry Me a River, Cry Me a Lake)

ከዓለማየሁ ገብረማርያም
ትርጉም ከነጻነትለሃገሬ

ከሶስት ዓመታት ቀደም ብሎ ‹‹እሪ በልልኝ ሃይቁ፤ በተፈጥሮ ላይ የተፈጸመ ወንጀል››በሚል ርዕስ ሳምንታዊ መጣጥፍ አቅርቤ ነበር፡፡ የዚያን ጊዜው መጣጥፌ ያተኮረው በወቅቱThe Dam and the Damned: Gibe III Ethiopia – Alemayehu G. Mariam ከአዲስ አበባ በስተ ደቡብ ላይ በ50 ኪሎሜትር ርቀት የሚገኘውና በአንድ ወቅት በጠቃሚ ወንዝነቱ ይታወቅ የነበረውን አሁን ለብክለት የተዳረገውን የቆቃን ሃይቅ ውሃ በመጠጣት፤ለበሽታና ለሞት የተጋለጡትን በአሰርት ሺህ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንን ሕለፈት በተመለከተ ነበር፡፡ በእንግሊዝ ሃገር በሚገኘው የዱርሃም ዩኒቨርስቲ የሚገኙት ዓለም አቀፍ እውቅና ያላቸው ሳይንቲስት የቆቃን ውሃ ከመረመሩ በኋላ፤‹‹በጣም ከፍተኛ የሆነ ‹‹የማይክሮኪሰቲስ ባክቴርያ›› የተከማቸበት መሆኑንና፤ይህም የሰውን ልጅ በከፍተኛ ደረጃ ለጉዳት የሚያጋልጥ እንደሆነ ይፋ አድርገው ነበር፡፡የኔም የሙግቴ መነሻ የሆነው ይህ አገላለጥና ያደረሰው፤ እያደረሰ ያለውና ወደፊትም ሊያደርስ የሚችለው ሕዝባዊ ጉዳት አሳስቦኝና ወገንም አሳዝኖኝ ነበር እሪታ ያሰማሁት፡፡

በቆቃ ሃይቅ ላይ ያጋጠመው እልቂት የችግሩ መንስኤ ብቻ ነው፡፡ኢትዮጵያ የዓየር ብክለት  ጥፋት እየደረሰባት ነው፡፡የጫካዎች መውደም፤የአፈር መሸርሸርና በዝናብ መታጠብ፤የሕዝብ ቁጠር መጨመርና የመሬት ሰብል መንሳት፤የዚሁ የዓየር ለውጥ ያመጣቸው መዘዞች ናቸው፡፡የኢትዮጵያ የእርሻ ምርምር ተቋም ኢትዮጵያ በየዓመቱ 200.000 ሄክታር የደን መሬቷን እንደምታጣ አስታውቋል፡፡ምናልባትም ይህ ሂደት ካልተገታ፤ከ 11 ዓመታት በኋላ በ2020 ኢትዮጵያ አጠቃላይ የደን ሃበቷን ታጣለች፡፡

የግቤ ግድብ፤ ግድቡና የተገደቡ ኢትዮጵያዊያን

ልክ በቆቃ ሃይቅ ላይ ለሞት እንደተዳረጉት ኢትዮጵያዊያን ሁሉ፤በደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ ኦሞ ወንዝ አካባቢ የሚኖሩት ሕዝቦች፤የከባቢ ዓየር ተጎጂ በመሆን ለችጋር መጋለጥ፤ለስደት መዳረግ ሳይሆን፤በሚደርሰው እልቂት ሕዝቡ ከምድረገጽ መጥፋት ሊደርስ ይችላል፡፡ይህ ደግሞ በመላ ምት የተባለ ሳይሆን የዓለም አቀፍ ወንዞች በመባል የታወቀ ‹‹የአካባቢን ሁኔታ፤የሰበአዊ መብት ጥበቃ ድርጅት፤ተግባሩም ‹‹የአካባቢን ወንዞቸንና የወንዙ ተጠቃሚ የሆኑትን ነዋሪዎች መብት ጠባቂ ድርጅት›› የሰጠው ጥናታዊ መረጃ ላይ የተመሰረተ ነው፡፡

የኦሞ ወንዝ፤በደቡብ ምዕራብ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ኬንያዊያን፤የሕይወታቸው መሰረት ነው፡፡አሁን በመሰራት ላይ ያለው የግቤ 3 ግድብ ለነዋሪው ጎጂ በሆነ መልኩ የኦሞን ወንዝን ፍሰት ሁኔታ፤የአካባቢውን ሁኔታ አልፎ፤በዓለም የታወቀውን የወንዝ በረሃ የተባለውን የቱርካናን ሃይቅ ፍሰት ጭምር በአደገኛ ሁኔታ ይለውጠዋል፡፡የታችኛው ኦሞ ሃይቅ በዩኔስኮ የተመዘገበ ታሪካዊ ስፍራ ነው፡፡በአካባቢውም የስምንተ ነገዶች ነዋሪዎች የሆኑ፤ ከ200.000 በላይ አርሶ አደሮች በወንዙና  በወንዙ ዳርቻ በመጠቀም  እርሻቸውን፤ ለከብቶቻቸውም ግጦሽ በማግኘት ኑሯቸውን ሲመሩ ኖረዋል፡፡አሁን ግን ዕድሜ ለግድብ 3ና ጆሮ እያላቸው ለማይሰሙ፤ አይን እያላቸው ለማያዩ ጭፍን ጨቋኝና ግፈኛ መሪዎች ለእልቂት ተዳርገዋል፡፡

የኦሞ ወንዝና መጋቢ ምንጮቹ የሃይደሮ የመብራት ሃይል ማመንጫነት በመቀየሩ፤ የአካባቢውን ነዋሪ ሕልውና ባላገናዘበን ደንታ ባላስገባ ግፈኛ መልኩ፤ለዓለም አቀፍ አልሚዎች (ኢንቬስተሮች) በመሰጠት ለውጭ ሽያጭ ለሚቀርብ የእርሻ ውጤት ተሰጥተዋል፡፡‹‹ግልገል ግቤ 1››ከዓለም ባንክና ከአውሮፓ ሕብረት የልማት ባንኮች በተገኘ የ300 ሚሊዮን ዶላር ብድር የተገነባ ነው፡፡ከ6 ዓመታት ግንባት በኋላ፤ በ2004 ዓም ሥራውን የጀመረው ግድብ 193 ሜጋ ዋት ያመነጫል፡፡ይህ 63 ስኩየር ኪሎሜትር የፈጀው የግድቡ ይዞታ በአካባቢው ይኖሩ የነበሩትን 10.000 ነዋሪዎች ለተፈናቃይነት ዳርጓል፡፡ግንባታውን እንደሚያካሂደው ሥራ ተቋራጩ ኢጣልያዊው ሳሊኒ አባባል፤ ‹‹ይህ የግልገል ግቤ1 ተከታይ ነው፡፡ይህ ግድብ ግን እንደሌሎቹ ግድቦች የሃይል ማመንጫ ግድብ ሳይሆን፤ ከግልገል ግቤ የተረፈውን ፍሰት፤በኢፎታ ተራራ ሥር በሚያልፈው የ26 ኪሎሜትር ርዝመት ባለው ቱቦ በመፍሰስ ወደ ኦሞ ወንዝ የሚገባ ነው፡፡ይህንንም ለመገንባት 373 ሚሊዮን ዩሮ ሲፈጅ፤በኢጣልያንና በአውሮፓ የልማት ባንኮች በተሰጠ ብድር የተገነባ ነው፡፡ግልገል ግቤ 3 በታላቅ ግርግርና ሁካታ፤ አሸሸ ገዳሜ በበዛበት የድንፋታ ዝግጅት ፌብሪዋሪ 2010 ሃገሪቱን በመግዛት ላየ ባሉ ገዢዎችና በአጋሮቻቸው ከተመረቀ በኋላ መገርሰሱ ይታወሳል፡፡የአካባቢ ደህንነትና የዓየር ንጽህና ተሟጋቾችን በከፍተኛ ሁኔታ የሚያሳስባቸው ጊቤ 3 ነው፡፡የኦሞን አካባቢ ተንተርሰው ሕይወታቸውን የሚመሩትን ከ300.000 በላይ የሚሆኑ ነዋሪዎችን ሕይወታቸውን ለከፍተኛ የአካባቢ ብክለት አደጋ ያጋልጣል፡፡ባለሙያዎቹም እንደሚሉት፤ግቤ 3 የወንዙን ስሱ የሆነውን ተፈጥሮ ሊያበላሸው የሚችል መሆኑን አበክረው ያስጠነቅቃሉ፡፡ ሰሚ ካለ!

<<ጊቤ››የአካባቢ ብክለት ከፍተኛ ቀውስ በመገንባት ላይ

የጊቤ 3 ግንባታ የተጀመረው በ2006 ነው፡፡ የኢትዮጵያ የዓየር ብክለት ጥበቃ ባለስልጣን፤ጊቤ 3ን በተመለከተ ያገኘውን የጥናት ውጤት ይፋ በማድረግ ግንባታውን ፈቅዷል፡፡ዘገባው ዐይና ያወጣ፤ ያፈጠጠ ውሸት፤ቅለመዳ የሆነ የይሁንታ የቅሌት ማሕተም ነው፡፡ ዘገባው ያለአንዳች ይሉኘታና ሃፍረት፤….በግንባታው ሰበብ በጣም መጠነኛ የሆነ የአካባቢ የዓየር ለውጥ ሊከተል ይችላል፤ የግልገል ግቤ ግናባታ አካባቢ ለሰዎች መኖሪያነት ተስማሚ ያልሆነ፤በገዳይ የቢነቢዎች ነፍሳትና የአንቅልፍ በሽታ የሚያስከትሉ ነዳፊ ነፍሳት የሚፈለፈሉበት ነው….. በማለት ለዘመናት ሰዎች በአካባቢው እየኖሩ ሕይወታቸውን ሲመሩ መኖራቸውንም ሊያስክደን ጥሯል፡፡

በ2006 በጊቤ 3 ግድብ አካባቢ የሚኖሩ 253.412…….የእንቅልፍ በሽታ በሚያዙ ነፍሳትና በዳገታማና ቁልቁለት ከባቢው ሁኔታ የተነሳ፤በወደፊቱ ግድብ አካባቢ ነዋሪዎች የሉበትም፡፡ ነዋሪዎች የሚገኙት፤በደጋማው ሥፋራ ከግድቡ ርቆ ባለ ቦታ ላይ ነው………በአናሳው የዝናብ መጠንና በእንቅልፍ በሽታ፤አሲያዦቹ ነፍሳት፤ታይፖኖሶሚያሲስ በሚባለው የከብት በሽታ የተነሳ ለከብቶች ማርቢያም ስለማይሆን በኦሞ ደልደሳላው ስፍራ በጣም አነስተኛ ግብርና ነው የሚካሄደው፡፡አካባቢው በጣም በከፋ መልኩ የወባ ትንኝ ስለሚረባበት በወባ በሽታ ተጠቂዎች በርካታ ናቸው……..ከአካባቢው የተነሱትም ነዋሪዎች ዩኔስኮ ከመዘገበው ክልል የራቁ ነዋሪዎች ናቸው…….አንዳችም ለታሪክ፤ለሳይንሳዊ ጥናትና ምርምር፤የአካባቢና የታሪክ ምስክርነት ያለው የአርኪዎሎጂ ቅሪት በግንባታው አካባቢ የለም……. በታችኛው ኦሞ በርካታ የከብቶች በሽታ ያለበት ነው፡፡

ይህ በቅጥፈትና በማለባበስ ላይ የተመሰረተው፤ሙያ አልባ የሆነ የአካባቢ ሁኔታ ዘገባ፤ ግንባታው ከተጀመረ ከሁለት ዓመታት በኋላ መውጣቱ ከየአቅጣጫው ውግዘት የደረሰበትና የኢትዮጵያን የአካባቢ ብክለት ጥበቃ ሕግጋት የሚቃረን ነው፡፡ ዘገባውም ከግንባታው መጀመር አስቀድሞ ይፋ ሊደረግ ሲገባው በማን አለብኝነት የሚመራ በመሆኑ፤እንዳሻው ሕግን ጥሶ፤ እውነትን አለባብሶ፤በምርምር መልኩ ሳይሆን በቅጥፈት መልኩ፤ይፋ ሆኗል፡፡የኢትዮጵያ የአካባቢ ብክለት ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ሥራ አስኪያጅ ተወልደ ገብረእግኢአብሔር በአካባቢው ላይ የተጋረጠውን አደጋ በማስመልከት፤ጥናታዊ ውጤቶችን መሰረት በማድረግ የተሰነዘሩትን አደጋዎች፤ያቀረቡትን የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ሃሳብ በአጠቃላይ በማጥላላት ውድቅ ሲያደርጉ ያላንዳች የጥናት መቃወሚያ ሃሳብ በጭፍንና በድፍረት ተችተዋል፡፡

እነዚህ የዓለም አቀፍ የመብት ተሟጋቾች ጊቤ 3 የሚገነባበትን ቦታ ከካርታ ውጪ አያወቁትም፡፡እነዚህ ስለጊቤ 3 መገንባት እሪታቸውን የሚያሰሙት ሁሉ ከቦታው በብዙ ሺህ ኪሎ ሜትር ርቀው የሚገኙ ናቸው፡፡በበኩሌ ጩኸታቸውን ከቁምነገር አልቆጥረውም፡፡ከተቃዋሚዎቹ አንዳቸውም ኢትዮጵያዊ አይደሉም፡፡አንዱ ከኬንያ ሲሆኑ በርካታዎቹ ደግሞ ከአውሮፓ ናቸው፡፡ወደ ስፋረው ሄጃለሁ ያለው አንድ ሰው ነው፡፡ የቢ ቢ ሲ ጋዜጠኛ፡፡እሱ ደግሞ ይህን ሁኔታ በተመለከተ ከአንድ ቀን ባላለፈ ቆይታው ብዙም ሊል የሚችል አይደለም፡፡…….የዚህ የጊቤ መገንባት ተቃውሞ መሰረቱ መሃይምነት ነው፡፡ስለዚህም፤ ይህን ጩኸታቸውን አላስፈላጊ በማለት በቸልታ አልፈዋለሁ፡፡

ነጻ የሆነው የአፍሪካ የማእድን የሥራ ቡድን (ARWG) ከአሜሪካ፤አውሮፓ፤ከምስራቅ አፍሪቃ የተሰባሰቡ ምሁራንና አማካሪዎች፤በተመሳሳይ የግድብ ግንባታና የተፋሰስ ወንዞች ጥናት ያካሄዱና፤ከበቂ ባለፈ ችሎታቸውን ያስመዘገቡ፤ዓለም አቀፍ ተቀባይነትም ያላቸው ጠበብት፤በርካታ ማመሳከሪያዎችና ማስረጃዎች በማጣቀስ ሃሳባቸውን ገልጸዋል፡፡አቶ ተወልደ እነዚህን አስተያየት ሰጪዎችና አስተያየቶች ያጣጣሉበት ዋነኛው ምክንያታቸው ልክ እንደ አዘዦቻቸው ለሃገርና ለወገን በአጠቃላይ ለሰብአዊ ፍጡር፤ ጨርሶ ግዴታ የሌላቸው በመሆናቸው እንጂ አምነውበት አለመሆኑን ልባቸው ያውቀዋል፡፡ይህን ካላሉ የመኖር ህልውናቸው ያቆማል፡፡ መባረር፤ መንገዋለል፤ መጣል እጣ ፈንታቸው መሆኑንም ስለሚያውቁና፤አለቆቻቸውን በማስደሰትና ሃቅን በመካድ በሸፍጥ ፈረስ መጋለብን ብቸኛ የመኖራቸው ዋስተሳና አድርገውት ነው፡፡በዚህም ከማንም ይበልጥ ማሃም ያደረጉት እራሳቸውን ብቻ ነው፡፡

በአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን የቀረበው ዶኩሜንት፤በተሳሳተ መንገድ የተቀረጸና በርካታ ማሳሳቻዎች የተካተቱበት፤አላስፈላጊና ከእውነታ የራቁ ሰንጠረዦች የተሰመሩበት፤ሳይንሳዊ ለማስመሰልና ለማሰኘት ሲባል፤ሁኔታዎች በተጭበረበሩ ቃላት የሰፈሩበት፤ለጋሥና አበዳሪ ድርጅቶችን በማሳመን ገንዘብ ለማጋኛ የተፈጠረ የሃሰት ሰነድ በመሆኑ ተቀባይነት የሌለው ነው፡፡

ስለታችኛው ኦሞ ሸለቆ ትክክለኛ የሆነ የአካባቢ ጥናትና ሁኔታ እንደሚያሳየው፤የግቤ 3 መጠናቀቅ፤ኢትዮጵያ፤ኬንያና ሱዳን በወሰን በሚገናኙበት ቦታ ላይ አስከፊና ዘግናኝ የሆኑ አደጋዎች  ያስከትላል፡፡….በታችኛው ኦሞ ላይ የሚኖሩት ሕዝቦች ኑሯቸው የተመሰረተው በውሃውና በውሃው ጠርዝ ዙርያ በሚያመርቱት ሰብል ላይ ነው፡፡የምግብ ምርታቸው፤ አሳ ማጥመዳቸው፤የክብቶቻቸው ህልውና ሁሉ የተመሰረተው በኦሞ ወንዝ ላይ ነው፡፡ የግቤ 3 ግንባታ ሲጠናቀቅ ነዋሪው ከፍተኛ የኤኮኖሚ ቀውስ ያጋጥመዋል፡፡ለችጋር፤ለበሽታዎች፤ለሞት ይዳረጋል፡፡

ዩኔስኮ በጁን 2011‹‹ጊቤ 3 የቱርካናን ሃይቅ ስስ የሆነ ተፈጥሮአዊ ሁኔታ በመቀየር ሊያስከትል የሚችለውን አስከፊ ሁኔታ በማስረገጥ ስጋቱን ገልጦና በነዋሪዎች ላይ የሚፈጠረውን አሰቃቂ ኢሰብአዊ ጉዳት በማስረዳት፤የኢትዮጵያ ገዢዎችና ፓርቲያቸው በአሰቸኳይ የግቤ 3ን ግንባታ እንዲያቋርጡ በማሳሰብ፤ግንባታው ህገ ወጥ መሆኑንም፤የሌላን ሃገር ቅርስና ታሪካዊ ተቋም በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ለአደጋ ማጋለጥ አግባብ እንዳልሆነና፤ተቀባይነትም እንደሌላው አስታውቋል፡፡‹‹ቴሪ ሃታዌይ የዓለም አቀፍ ወንዞች የአፍሪካ ፕሮግራም ዳይረክተር፤በአፍሪካ በመገንባት ላይ ያለው ታላቁና ተወዳዳሪ የሌለው የዘመኑ አጥፊ ግድብ ጊቤ 3 ነው፡፡ ግንባታው ከግማሽ ሚሊዮን በላይ የሆኑ ነዋሪዎችን ለችጋርና ለግጭት የሚያጋልጥ ግንባታ ነው በማለት ግንባታውን አውግዘዋል፡፡

አምባ ገነኑ ዲካታተር፤የግፍ ማህደር የሆነው፤ለሰብአዊ ፍጡር ደንታ የሌለው፤ግፈኛው መለስ ዜናዊ፤ የጊቤ 3ን ግንባታ በተመለከተ ሲመልስ፤በዘወትር የማጣጣልና የንቀት፤ የማንአለብኝነትና የአካኪ ዘራፍ፤ መኩራራትና ድንፋታ ነው፡፡‹‹እነዚህ የግድቡ መገንባት መቆም አለበት የሚሉ ሁሉ የአፍሪካን ልማት ማየት የማይፈልጉ ናቸው፡፡የነሱን ሀገር ጎብኚ ዜጎች የምናስተናግድ ሙዚያምና ኋላ ቀር ሆነን እንድንኖር የሚሹ ናቸው፡፡››……የመለስ ወኪሎችም ስር ስሩ በመከተል የግንባታውን ሂደት የተቃወሙትን ሁሉ በማጥላላት ውትወታቸውን ተያይዘውታል፡፡ ምእራባውያን ተሟጋቾች በአካባቢ ጥበቃ የሞኖፖል መብት የላቸውም፡፡ወይም በትክክለኛነት ላይ የበላይነት መብት የላቸውም፡፡ ዓለም አቀፍ የአካባቢ ተሟጋቾች ያልተረጋገጠ መሟገቻ ነው የሚያቀርቡት፡፡››

ሂስ የሚያቀርቡበትን ባልታረመ አነጋገሩ ማጥላላትና ማዋረድ፤ በተራ ስድብና በጋጠ ወጥነት መልስ መስጠት የመለስ ባህሪው ነው፡፡በ2010 በተካሄደው ምርጫ ወቅት መለስ ዜናዊ 99.6 በመቶ አሸነፍኩ ሲልና የድል ከበሮ በመምታት እራሱንና አገልጋዮቹን ሲያታልል፤ የአውሮፓ ሕብረት ምርጫው ዓለም አቀፍ መመዘኛን አላሟላም፤ ባሉበት ውቅት መለስ ሲመልስ፤ ባይመረጥ እንኳን መሪ ነኝ ይላልና፤ለዚያም ለሚለው እንኳን በማይመጥን ተራ የቅሌት ቃል በመጠቀም ‹‹ቆሻሻ ማጠራቀሚያ ቅርጫት ውስጥ መወርወር ያለበት ቆሻሻ ነው፡፡ ዘገባው ስለምርጫው ሂደት ሳይሆን፤የአንዳንድ የገዢውን ፓርቲ ጥንካሬ የማይወዱ አውሮፓውያን ኒዮ ሊበራሎች አስተያየት ነው፡፡ማንም ቀለምና ወረቀት ያለው መጫር ይችላል››…. በማለት ነበር የመለሰው፡፡….ባለፈው ወር ሽብርተኝነትን ለመዋጋት በሚል ያወጣውን ሰነድ በተመለከተ፤ሰነዱ ነጻውን ፕሬስና ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ለማሰርና ለመለጎም የወጣ ሰንድ ነው በማለታቸው፤መለስ በተለመደ እንዳመጣለት በሚወረወር ያልተገራ ቋንቋው ነበር ያጣጣለው፡፡

በኛ ላይ ሴራ እየተጎነጎነብን ነው፡፡…..ለዚህም ከበስተኋላው ምክንያት አለው፡፡…..ይሄ ሰብአዊ መብት የሚባለው ድርጅት ሃሳቡ የፖለቲካ ፍላጎቱን ለማካሄድ ነው፡፡……ድርጅቱና ወዳጆቹ በተወሰኑ ሃገራት ላይ አስተሳሰባቸውን ለመጫን ይፈልጋሉ፡፡አሁን ዓለም ከሚከተለው እምነት ለየት ያለን አካሄድ አይደግፉም፡፡ስለዚህም ይህ ሴራ እኛን ለማንበርከክና የነሱ ተገዢ ለማድረግ ነው፡፡ስለዚህም የሚሉት ሁሉ ከሰብአዊ መብት ጋር ጨርሶ ግንኙነት የለውም፡፡የጊቤን መገንባት የሚቃወሙ ሁሉ የራሳቸው ፍላጎትና እምነት ያላቸውና፤ያንንም በሀገራት ላይ ለመጫን የሚመኙ ናቸው ማለት ነው፤ በመለስ አስተሳሰብ፡፡በቅሎን ‹‹እናትሽ ማን ነች ቢሏት አባቴ በቅሎ ነው አለች›› እንዲሉ፡፡

የአፍሪካ ግፈኛ ገዢዎችና የአፍሪካ ነጫጭ ዝሆኖች

የአፍሪካ አረመኔ ገዢዎች ትላልቅ ፕሮጄክቶች የመገንባት አባዜ አለባቸው፡፡በአፍሪካ መንግስታዊ ተቋምን እንደግል ንብረትና መጠቀሚያ ማዋል መሰረቱ፤‹‹ትልቅ ሰው›› ሳይሆኑ ለማስመሰያነት የመኮፈሻ በሽታ ነው፡፡ የአፍሪካው ግዙፍ ሰው ዝናን ለመቀዳጀት ትላልቅ ፕሮጄክቶች መንደፍን፤ በዚህም ገናናነትን፤ ዘልአለማዊነትን፤ከሁሉም በላይ ደግሞ ለራሳቸውና ለምንዝሮቻቸው ሃብት ማጋበሺያነት ያውሉታል፡፡ሆኖም ግን እነዚህ ትላልቅ እርባና ቢስ ፕሮጄክቶች በገሃዱ ሲታዩ፤ ‹‹ነጫጭ ዝሆኖች›› ናቸው፡፡(ጠፊና ዋጋቢስ የሆኑ ፕሮጄክቶች ናቸው)፡፡ በአይቮሪ ኮስት በዓለም ታላቁን ቤተመቅደስ ፌሊክስ ሁፌት ቡዋኜ በያማስኩሮ፤የእመቤታችን ገዳም በመባል የሚታወቀውን በ300 ሚሊዮን ዶላር አስገንብተው ነበር፡፡ዛሬ ያ ብዙ ወጪ ያስወጣ ገዳም ባዶውን ቀርቷል፡፡ሞቡቱ፤ በምእራብ ዴሞክራቲክ ኮንጎ (ዛይር) የኢንጋ ግድቦችን በዓለም ታላቁ የሚባለው የውሃ ፏፏቴ ላይ አስገንብቶ ነበር፡፡ በኢንጋ ወንዝ ላይ የተገነቡት ሁለቱ ኢንጋ 1 እና 2 ግድቦች ለሃገር ፍጆታ በጣም ከፍተኛ ሃይል ያመነጫሉ ተብሎ በስፋት ተወርቶለት ነበር፡፡ዛሬ በጣም አነስተኛ የሆነ ሃይል በማመንጨት ላይ አለ፡፡በ1990 መጨረሻ ላይ ጦርነት ሲፈነዳ፤እነዚህን ግድቦች ማስተዳደር ባለመቻሉ እርባና አጥተዋል፡፡በኡጋንዳ የተገነባው ቡጃንጋሊ ግድብ፤በግድቡ አካባቢ በሚገኙ ነዋሪዎች ሕይወት ላይ ከፍተኛ ፈጉዳት በማድረስ ነዋሪውን ለመከራ ዳርጓል፡፡በነዋሪዎቹ ላይ ስደትና መንከራተት አስከትሎ እርሻዎቻቸውን በማጥፋት አፈናቀሏቸዋል፡፡የመካከለኛው አፍሪካ ሪፓብሊክ በራሱ ራሱን ያነገሰው ጄን-ቤዴል ቦካሳ፤ሕዝቦች በችጋር እየተቆሉ መኖር ሲያስመርራቸው፤ ለነሱ ትኩረት በመስጠት ፈንታ፤በመቶ ሚሊዮን በሚቆጠር ዶላር፤ባለ 500 መቶ ክፍሎች ኢንተር ኮንትኔንታል ሆቴል አስገንብቶ ነበር፡፡

የአፍሪካ ግፈኛ ገዢዎች፤ ሕዝቦቻቸው በችጋር ሲያልቁና መኖር ጣር ሲሆንባቸው፤ግድብ ማስገንባትን፤አብረቅራቂ ህንጻዎችን ማስገንባትን ይወዳሉ፡፡ይህን የሚያደርጉት ግላዊ ሃብትን ለማካበት፤መኮፈሳቸውን ለመጨመር፤ተስፋ ያጣ ህልማቸውንና ምኞታቸውን ለማሟላት፤ ድክመታቸውንና ችሎታ ቢስነታቸውን ለመሸፈን የቻሉ እየመሰላቸው ነው፡፡በደም የተጨማለቀ እጃቸውን ያጸዱ እየመሰላቸውና በስልጣን ላይ ለዘለቄታው ለመቆየት የሚያስችላቸው እየመሰላቸው ነው፡፡እርቀኑን የቀረ ግፈኛ የአገዛዝ ማንነታቸውን በማይጨበጥና በማይታይ ልማታዊ እቅድና፤እድገት ለመሸፈን ይሞክራሉ፡፡እነዚህ የግፍ ቋት የሆኑ አረመኔ ገዢዎች፤ ሕዝብ በችጋር ቢያልቅ፤ በምግብ እጦት ቢሰደድና ለሞት ቢዳረግ፤ገሃነም ቢገባ ደንታቸው አይደለም፡፡የአካባቢው ዓየር ቢበላሽ ደንታቸው አይደለም፡፡የነዋሪው ኑሮው ቢቃወስ፤ባህላዊና አርኪዎሎጂያዊው የሃገሪቱ ሃብት ቢወድም የነሱ ጉዳይ አይደለም፡፡ ግፈኛውና ጨካኙ መለስ ዜናዊ ዝናውን ማሳወቅ የሚፈልገው በአፍሪካ ረጂሙን ባለ 240 ሜትር ታላቁን የግቤ 3 ግድብ በመገንባቱ ነው፡፡‹‹‹የአፍሪካ ነቢይ›› በመባል ሊታወቅ ነው ህልሙ፡፡ባለፈው ፌብሪዋሪ 2011 ባለ 245.000 ሄክታር የስኳር እርሻ በታችኛው ኦሞ ለማስገንባት ሲነሳ፤በኩራት በተሞላ እርግጠኛነት ሲያቅራራ ‹‹በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት በጣም ግዙፍ የሆነ የመስኖ ልማትና የእርሻ ልማት በዚህ አካባቢ ይኖራል፡፡ ለዚህ ቃሌን እሰጣችኋለሁ፡፡ምንም እንኳን አካባቢው ለስልጣኔ ኋላ ቀር በመባል ቢታወቅም፤የፈጣን ልማታዊ እንቅስቃሴ ተምሳሌት ይሆናል፡፡››

‹‹ለዚህ ፈጣን ልማት›› በሙርሲዎች፤በሱሪዎች፤በቦዲዎች የእርሻና የከብት አርቢዎች የሚከፈለው ዋጋ፤መሰደድ፤ለጥፋት መዳረግ፤ከባህላዊ ኑሮ ጋር መለያየት፤የቀደምት የእርሻ ይዞታን ማጣት፤ለግጭት መዳረግ ነው፡፡››

የበለጠ ሃይልና ጥንካሬ ለኢትዮጵያዊያን፤ ደካማነትና ልፍስፍስነትን ለአረመኔ ገዢዎች

እንደማንኛውም ሃገር ሁሉ ኢትዮጵያም ለሕዝቦችዋ ጥቅም የሚውል የሃይል ማመንጫዋን መገንባትና ማልማት ይገባታል፡፡የረጂም ጊዜ የልማትና የእድገት እቅዷን በማሳካት፤ሕዝቦችዋን ከረሃብና ከኑሮ ውድነት ሰቆቃ ማውጣት ተገቢ ነው፡፡በአሜሪካው የሕዝብ ቁጥር ትንበያ ቢሮ ዘገባ፤የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር በ2050 እ አ አ ሶስት እጥፍ በማደግ፤ወደ 280 ሚሊዮን እንደሚደርስ ይተነብያል፡፡ስለዚህም ሃገሪቱ ለሕዝቦችዋ የበለጠ የሃይል ማመንጫ ፤ለዘለቄታውም የሚበጅ የሃይል ማሳደጊያ ማእድን ያስፈልጋታል፡፡

ጊቤ ግድብ 3 ግን ከላይ የተጠቀሰውን እቅድ ለማስፈጸሚያነት የታቀደ አይደለም፡፡በእቅድ የተነደፈው 1.870 ሜጋዋት ለጅቡቲ፤ ለሱዳን፤ ለኬንያ ለሽያጭ የታለመና በዓመት 300 ሚሊዮን ዩሮ ሊያሰገባ የታቀደ ነው፡፡ይህም ቢሆን ለእርግጠኛነቱ ዋስትና የለውም፡፡ በቅርቡ የወጣው የዓለም አቀፍ ለፋይናነስ ተአማኒነት የተባለው ያወጣው ዘገባ፤በ2000 እና በ2009 መሃል ከሃገሪቱ 19 ቢሊዮን ተመንተፏል፡፡እነዚህ ግቤ 3ን እናለማለን የሚሉት፤ በዚህ ማስረጃነት ግን ማንንም ለማታለል እንደማይችሉ ሊገነዘቡት ይገባል፡፡ ‹‹ይሁንላቸው፤ትላንት ተወልደን ይሆናል፤ ዘሬ ማታ ግን አይደለም›› ሞኛቸውን ሌላ አካባቢ ይፈልጉ!

የዛሬዋ አፍሪካ የማይዋጠው እውነት፤ጨቋኝ ገዢዎቿ ከከባቢ ዓየር ብክለት በባሰ ሁኔታ በሃገርና በሕዝብ ላይ የሚያደርሱት ጭቆናና ግፍ የተሞላበት አገዛዛቸው ነው፡፡እነዚህ አፍሪካዊ ጨቋኝና ግፈኛ ፈላጭ ቆራጭ ገዢዎች እያደረሱ ያሉት በደል መጠነ ሰፊ ነው፡፡አፍሪካውያን ለችጋር፤ ለመከራ፤ ለስደትና ለሌሎችም መከራዎች የተዳረጉት በአካባቢው የዓየር ለውጥ በተፈጥሮ ችግር ሳይሆን፤ አቅመቢሶቹና ሕሊናቸው የከዳቸው፤ራስ ወዳድ ገዢዎች ባላቸው ደካማነትና የስልጣን ጥማት የተነሳ ነው፡፡አህጉሪቷ፤ አሁን በቃኝን በማያውቁና፤ አቅማቸውን ባላገናዘቡ፤እኩይ መሪዎች እንደነቀርሳ ባደረባቸው የሥልጣን በሽታ፤ከዓየር መዛባት ከሚያደርሰው ቃጠሎ በበለጠ እየተቃጠለች ነው፡፡…….ሌሎች ዓለማት በዓየር ለውጥ ሳቢያ በተከተለው ንዳድ ሲለበለቡ፤አፍሪካ ደግሞ በመሪ ነን ባዮች የገዢዎች እሳት አራ እየተንጨረጨረች ነው፡፡አውሮፓውያን በማንነታቸው ግልባጭ ማህተም ሲሞናሞኑ፤ አፍሪካ ግን ከመሪዎች የጫማ እርግጫ ግፍ ጫና ለመላቀቅና ነጻነትን ለመተንፈስ እየዳከረች ነው፡፡አሜሪካኖች በጭስ ትነት ሳቢያ ከሚያጋጥመው ስራይ ለመገላገል ሲጥሩ፤አፍሪካውያን ግን የጭቆና አገዛዝ ግፍና መከራ ከሚመረትበት የከሰል ማዕድን ውስጥ ተጠምደው ስቃያቸውን ይቆጥራሉ፡፡አፍሪካ የከባቢ ዓየር ብክለት ለውጥ ተጠቂ ሳትሆን ፤የገዢዎች ለውጥ የትግል ፈተና ለውጥ ውስጥ ናት፡፡

የአካባቢ ዓየር ብክለት ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ሥራ አስኪያጅ ተወልደ ገብረእግዚአብሔር፤ኢትዮጵያውያን በጥንቃቄ ሊያገናዝቡት የሚገባ አስተያያት ሰንዝሯል፡፡ጊቤን የሚቃወሙት ‹‹ለጊቤ ያላቸው እውቀት ከሺ ኪሎሜትር ርቀት ነው፡፡አባባላቸውን ትኩረት ጨርሶ አልሰጠውም፡፡……ከነዚህ ተቃዋሚዎች አንዳቸውም ኢትዮጵያዊ አይደሉም›› ካለ በኋላ  የግድቡ ተቃዋሚዎች ‹‹መሃይሞች›› ናቸው በማለት ደምድሟል፡፡ የተወልደ አባባል ግን ኢትዮጵያውያን ባለመቃወማቸው የተነሳ ሳይሆን የተቃወሙትን ሁሉ አሰባስቦ በሽብርተኝነት በመፈረጅ ወደ ቃሊቲ ለማስገባትና አፋቸውን ለመለጎም ባለመቻሉ ነው፡፡

እውነቱ ግን የመለስ አገዛዝ ስለ ጊቤ 3 ግንባታ ከመጀመሩ አስቀድሞ አንዳችም ቃል ባለመተንፈሱና፤ በጥቂቱ የተተነፈሰውም ቢሆን ሥራው ከተጀመረ በኋላ ስለሂደቱ፤አለያም ዝርዝር ሁኔታ ባለመቅረቡ ነው፡፡በግንባታው ቦታ በኦሞም ካሉት ሃላፊዎችም ጋር ቢሆን፤ ግንባታው በዝምታ ተውጦ ረጂም ሂደት ከተጓዘ በኋላ ነበር፤ድፍንፍን ያለ፤ግልጽነት የጎደለው፤የይስሙላ ንግግር የተከናወነው፡፡የግድቡን መገንባት አስመልክቶ፤ የመናገር መብት በተለጎመበት፤ ነጻው ፕሬስ በታፈነበት፤ውይይትም፤ ሃሳብ ማቅረብም፤ አማራጭ መሰንዘርም ጨርሶ የማይታሰብ ነው፡፡በገዢዎቹ አመለካከት፤ስለ ጊቤ 3 ግድብ ተቃውሞ ማሰማት ከሽብርተኝነትና በሃገር ላይ ከማመጽ ተለይቶ የሚታይ ጉዳይ አይደለም፡፡ መቀመጫው በኦክላንድ ኢንስቲቲዩት የሆነው አሜሪካ በቀል ‹‹ሃሳብ ማመንጫ››(think-tank) የገዢው ባለመሳርያ አገልጋዮች፤ወደኦሞ መንደር እንዴት እንደመጡና(በተለይም፤ቦዲ፤ ሙርሲ፤ሱሪዎችን)ስለስኳር ልማቱ ያላቸውን አስተያየት እንደጠየቋቸው ዘግቧል፡፡ነዋሪዎቹ ግብታዊ ስምምነት እንዲሰነዝሩ ይጠበቅባቸው ነበር፤ያ ሳሰሆን ቢቀር ደግሞ አጸፋው ድብደባ፤ ማጎሳቆልና ለፖሊስ ማሰቃያ (ቲዘር) መዳረግ፤ እንግልትና ማስፈራራት ነበር፡፡

ከጊቤ 3 ግንባታ ተቃዋሚዎች መሃል አንድም ኢትዮጵያዊ የለም፤ በማለት ተወልደ ገብረእግዚአብሔር የሰነዘረው አባባል በኢትዮጵያውያን አጸንኦት ሊሰጠው የሚገባ አባባል ነው፡፡ ተወልደ ማለት የዳዳው ‹‹ኢትዮጵያውያን ዲያስፖራውን ጨምሮ ስለጉዳዩ ግንዛቤም፤ እውቀቱም የላቸውም፤ ስለግንባታው ምንም ስሜት ስለሌላቸው፤ሌሎች ወገኖች በማያገባቸው እየጮሁ ነው›› ነው፡፡ የአካባቢ ሁኔታን በተመለከተ እርግጥ ነው የሚከላከሉትና ሙግት የሚያሰሙት የሲቪል ማህበረሰብ አባላት ናቸው፡፡‹‹በኢትዮጵያ ውስጥ የነበረው የሰብአዊ መብት እንቅስቃሴ በገዢው ስርአት በ2009 በወጣው የማፈኛ አዋጅ ጫና ታንቋል፡፡ የእነዚህ ድርጅቶች መታፈን ደግሞ ኢትዮጵያውያን ስለ ሃገራቸው ጉዳይና ስለሚከናወነው ሕገወጥ እንቅስቃሴ፤መሬትን ለውጭ ሰዎች ልማት በሚል ሰበብ መሸጡን እንዳያውቁ አድርጓል፡፡ቢያውቁም አዋጁና ጣጣው አያስተነፍሳቸውም፡፡የጊቤ 3ን ግንባት ቻይናውያን ከግብ ያደርሱታል ተብሎ በገዢው መንደር ቢታመንም፤በኢትዮጵያ በርካታ የአካባቢ ሁኔታዎች ጎጂ ለውጥ በማንዣበብ ላይ ነው፡፡አሁን ኢትዮጵያውያን እነዚህን ጎጂ የአካባቢ ለውጦች በተመለከተ መንቀሳቀስ ይጠበቅባቸዋል፡፡

በኢትዮጵያ ውስጥ በድብቅና ሃቁን በሸፈጠ አካሄድ ስለሚከናወነው የጥፋት ተልእኮ፤ የውጭ የሰብአዊ መበት ተሟጋቾች ላደረጉት እንቅስቃሴ፤ድምጻቸውን ከፍ አድርገው፤ጉዳያችንን ጉዳያቸው አድርገው፤በተለይ በኦሞ ወንዝ አካባቢ ያለውን እኛም የጉዳዩ ባለቤቶች ስውሩን ደባ እንድናውቀው ስለደረጉልን ልናመሰገነሳቸው ይገባል፡፡ያም ሆኖ ግን ታላቁን ጫና አሁንም እነሱ እንዲሸከሙልን ማሰብ የለብንም፡፡ከእነሱ ጋር በመደባለቅና በማገዝ እንዲረዱን መርዳት ይጠበቅብናል፡፡ከዚህም በመነሳት የራሳችንን የአካባቢ ጥበቃ ድርጅት በተለይም በዲየስፖራው በመመስረት የኢትዮጵያ ንጹህና የዳበረ የአካባቢ ሁኔታ ሊጠበቅና ሊንከባከቡት የሚገባ ሃብታችን መሆኑን ልንገነዘብ ተገቢ ነው፡፡ ይህን ሳናደርግ ብንቀር ግን እኛም የኦሞ ወገኖቻችን ላይ በግድቡ ሳቢያ የደረሰው ችጋር፤መሰደድ፤ አልቂት እንደሚደርስብን ሳንጠራጠር መቀበል አለብን፡፡

Leave a Reply