ዶናልደ ፔይን፡- ስንብት ለሰብአዊ መብት ቀደምት ተሟጋች!

Click here for PDF

ፕሮፌሰር ዓልማርያም
ትርጉም ነጻነት ለሃገሬ

የኢትዮጵያ ባጠቃላይም የአፍሪካ ቅን፤መልካም፤እውነተኛ አሳቢና ተሟጋች የነበረ ወዳጅን እንዴት ነው መሰናበት የሚቻለው? ተወካይ ዶናልድ ፔይን፤የኒው ጀርሲ ሃውስ ዴሊጌሽን፤ የመጀመርያው ጥቁር አሜሪካዊ ኒው ጀርሲን ለመወከል የበቁት ኮንግሬስ ማን፤በኮሎን ካንሰር በተወለዱ በ77 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተውናል፡፡በአሜሪካ የሃውስ ተወካይ በመሆን 12 ጊዜ ተመርጠዋል፤ በትምህርት፤ በውጪ ጉዳይ ኮሚቴና በተለያዩ ኮሚቴዎች ውስጥም ሰርተዋል፡፡ለበርካታ ዓመታት የአፍሪካነ ንዑስ ኮሚቴ በሊቀመንበርነት መርተዋል፡፡በአፍሪካና በተለይም በኢትዮጵያ ስለዴሞክራሲና ሰብአዊ መብቶች ጉዳይ ትልቅ እጦትና በጉዳዮቹም ላይ ታላቅ ክፍተት ሊፍጠር በሚችል ሁኔታ ሕልፈታቸውን እናስባለን፡፡

ፔይን ለአፍሪካ የነበራቸው ያልተቆጠበ ጥረት ታሪካዊና የማይዘነጋ ነው፡፡በ2008 በርካታው መጠን ለአፍሪካ በዓመስት ዓመታት ሂደት በተግባር ላይ የሚወጣውን የ 48 ቢሊዮን ዶላር የድጋፍ ችሮታ(ለኤይድስ መቆጣጠርያ) ኮንግሬስ እንዲፈቅድ በቀረበበት ወቅት ፔይን ከፍተኛ ሚና ተጫውተው እንዲፈቀድ አድርገዋል፡፡በዳርፉር በሰብአዊ መብት ረገጣና ዘር በማጥፋት ላይ የተሰማሩትን ተጠያቂዎች አስመልክቶ በሱዳን ላይ የተጣለው እቀባ እንዲወሰንም ያደረጉት ጥረትና ተሳትፎ ቀላል አልነበረም፡፡ በሱዳን የተደረሰውን የሰላም ስምምነትም እንዲሰምርና በሁለቱም ወገኖችና በዓለም አቀፍ ደረጃም ተቀባይነት እንዲኖረው ከማድረግም ባሻገር ደቡብ ሱዳንም እራሱን መንግሥት ለመሆን የበቃበትን ሂደት በመምራት ውጤታማ ያደረጉ ናቸው፡፡

ፔይን፤(የአፍሪካ ግሮውዝ ኤንድ ኦፖርቹኒቲ አክት) የአፍሪካ የብልጽግና እድል ድንጋጌ ዋነኛው ተሟጋች ሆነው፤አፍሪካን ከአሜሪካ ጋር ያስተሳሰረውን የኤኮኖሚ ልማት ያስገኙ ናቸው፡፡የአፍሪካ ሃገሮች የዕዳ ቅነሳ እንዲደረግላቸው፤የሰላም ምስረታ፤የእርሻ ፕሮግራሞች፤ የንጹህ ውሃ አቅርቦት እንዲመቻች፤በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሕጻናት የትምህርት እድል ማግኘት የኤኮኖሚ ድጋፍ እንዲያገኙ፤በቀጥታ ተሟግተዋልም ሙግት የያዙትንም ደግፈዋል፡፡

ፔይን፤ አለመግባባቶችና ግጭት በተፈጠሩባቸው በርካታ የአፍሪካ ሃገራት በግምባር በመገኘት፤ለራሳቸው ደህንነት ደንታ ሳይሰጡ፤ስደተኞችንና ሽብር ባለባቸው፤ ዘር ማጥፋት በተካሄደባቸው ቦታዎች በመገኘት ተጎጂዎችን አነጋግረዋል፤ሁኔታዎችንም አጥንተዋል፡፡ፔይን በሞቃዲሾ፤ ለሰብአዊ ተግባር ከተገኙ በኋላ ወደ ሃገራቸው ለመመለስ በዓር ጣቢያ እንደደረሱና አውሮፕላናቸው በመነሳት ላይ እንዳለ፤ጥቃት ተሞክሮባቸውም ነበር፡፡ በዓለም አቀፍ ግንኙነት ልምዳቸው የዴሞክራቶችም የሪፓብሊካኖችም ፕሬዜዳንቶች ችሎታቸውንና ዕውቀታቸውን አድንቀዋል፡፡በ2003 እና በ2006 ፕሬዜዳንት ቡሽ ፔይንን በተባበሩት መንግሥታት ማሕበር ከተሰየሙት ሁለት ተወካዮች አንዱ አድረገዋቸዋል፡፡ፔይን ወደ ሩዋንዳ የተላከውን ቡድን በመምራት ሃገሪቱን ያጋጠማትን የሰብአዊ መብት ቀውስና የፖለቲካ ችግር ለመፍታት በሃገሪቱ ችግር ላይ ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል፡፡ፕሬዜዳንት ቢል ክሊነተን በአፍሪካ ካሉት ሃገራት ስድስቱን ለመጎብኘት በተንቀሳቀሱበት ወቅት ጋብዘዋቸው የቡድን አባል ሆነዋል፡፡

ለበርካታዎቹ የአፍሪካ ፈላጭ ቆራጭ ገዢዎች፤የጎን ውጋት ሆነውባቸው ድርጊታቸውን አጋልጠዋል፡፡ በዊኪሊክስ እንደተገለጸው በሰኔ ወር በ2009 ዓም በሐራሬ በተካሄደው ስብሰባ ላይ፤ፔይን ፈላጭ ቆራጩን ሙጋቤን በተለያዩ የሰብአዊ መብት ጉዳዮች ላይ ሰንገው ይዘዋቸው ነበር፡፡በዚህም ጊዜ ሙጋቤ መብታቸውን ለማስጠበቅ ሲሉ አቤት ለማለት የወጡትን አፍሪውያን ሴቶች ፖለስ እንዲደበድባቸው መፍቀዳቸውን አውግዘው በመናገራቸው፤ሙጋቤ ደንግጠውና ግራ ተጋብተው በተቀመጡበት ፎቴ ውስጥ ሰመጡ፡፡ ሆኖም ፔይን በዚህ አልበቃቸውም፡፡ ቀጠሉና ፕሬዜዳንቱን ‹‹…እርስዎም የሲቪል ማሕበረሰብ ተሟጋች ነበሩ፤ በዚህ ሳቢያም በቅኝ ገዢዎች ለ11 ዓመታት ወህኒ ተወርውረዋል፤ እኔም የሲቪል አንቀሳቃሽ ነበርኩ ያን ባልሆን ኖሮ አሁን አለሁበት ቦታ ላይ አልገኝም ነበር››፡፡

በዲሴምበር 2011፤የአሜሪካ ትሬዠሪ ዲፓርትመንት ሱዳንን ለወከለው (ሎቢይስት) ጉዳይ አስፈጻሚ ፈቃድ በመስጠቱ ብስጭታቸውን ገልጸዋል፡፡ ንዴታቸውንም ‹‹ኦማር ሃሰን አልበሺር ለተባለ ነፍሰገዳይና የሰብአዊ መብት ጨፍላቂ፤ኢፍትሓዊ ግለሰብ በዋሽንግተን የሚገኝ ዜጋ እንዲሟገትለት መፈቀዱ ያሳፍራል›› በማለት ነበር የተናገሩት፡፡በሺር በዳርፉር ለተፈጸመው ግድያ ሙሉ በሙሉ ተጠያቂ በመሆኑ በዓለም ፍርድ ቤት እንዲቀርብ የተወሰነበት ሽፍታ ነው፡፡የደቡብ ኮርዶፋን፤ አባይንና አቢዬን በጦር ያስደበደበ ነው፡፡ ወደዚህ ሥፍራዎች የተላኩትንም የሰብአዊ እርዳታዎች ወደ ቦታዎቹ እንዳይገቡ በመከልከል፤ሕዝቡን ለርሃብና ለችጋር አጋልጧል፡፡ ለሞትም ዳርጓል፡፡ባሺር በየወሩ ለተቀጠረው ተከላካይ የሚከፍለው 20000 ዶላር፤በኮርዱፋን አባይና አቢዬ ላሉት ችግረኛ የሃገሪቱ ዜጎች ጥቅም እንዲውል ቢደረግ የበለጠ ጠቃሚ የበለጠ በምድረ ሱዳን ዴሞክራሲና የሰብአዊ መበት ማስከበርያም ይሆን ነበር፡፡

ባለፈው ዓመትም ሃገሪቱን (አይቮሪ ኮስትን) ወደቀውስ ውስጥ ያስገባት ሎሬንት ባግቦ እንዳሻው ሲፈነጭና ሕዝቡን ለመከራና ለሞት ሲዳርግ፤የአፍሪካ አንድነት ሰምቶ እንዳልሰሞ፤አይቶ እንደላየ ሆኖ፤ ጆሮ ዳባ ሲል ፔይን ይህንንም በዝምታ ሊያልፉት ባለመቻላቸው አፍሪካ አንድነት ለጉዳዩ ትክረት ሰጥቶ እንዲንቀሳቀስ አሳስበዋል፡፡

ዶናልድ ፔይንና ኢትዮጵያ

ዶናልድ ፔይን ለኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊያን ልዩና ብርቅ የችግር ቀን ወዳጅ ነበሩ፡፡ለዓመታት ይቺ ምሰኪን፤የደቀቀች ሃገር ውስጥ ያለውን የሰብአዊ መብቶች ለማሻሻል ጥረታቸው ከፍተኛ ነበር፡፡በ2007 ዓም በተወሰደው የሰብአዊ መብትና የዴሞክራሲ አክት ረቂቅ ሕግ መሪው፤የሰነዱ ነዳፊና፤ለትግበራውም፤ቀዳሚ ተሟጋች ነበሩ፡፡የአሜሪካ ምክር ቤት ወገናዊነት የሌለበት፤የምርምር ክንፍ፤በኢትዮጵያ ላይ የተረቀቀውን የ2003 የሰብአዊ መብት ፖሊሲ እንደሚከተለው አስተካክሎታል፡

1. በሃገሪቱ ያለውን የሰብአዊ መብት፤ የዴሞክራሲ፤የፍትሕ ሥረአትን ነጻ መሆን፤የፕሬሱን ነጻነት፤ ሰላምን ለማስፈን የሚደረገውን እቅድ ማዳበር፤ የኤኮኖሚ እድገትን በተመለከተ ድጋፍ ማድረግ፤

2 ሁሉም የፖለቲካ እስረኞች ያለአንዳች ቅድመ ሁኔታ እንዲለቀቁ፤

3. በአፍሪካ ቀንድ ያለውንም መረጋጋት፤ዴሞክራሲ፤ሌሎቹንም ሁኔታዎች እንዲሻሻሉ ለማደረግ ድጋፍ መስጠት፡፡

4. የሰብአዊ እርዳታ፤በተለይ በኦጋዴን ክልል የሚደርስበትን ሁኔታ ማመቻቸት 5. በዓለም አቀፍ ደረጃ ሽብርተኝነትን ለመዋጋት በኢትዮጵያና በአሜሪካ መሃል ያለው ግንኙነት የበለጠ እንዲጠናከር ማድረግ፤ 6. በአጠቃላይ የአሜሪካና የኢትዮጵያ ግንኙነት እንዲጎለብት ማድረግ

በ2007 ኦክቶበር ላይ የቀድሞዋ የአሜሪካ ተጠባባቂ አምባሳደር የነበረችው ቪኪ ሃደልስተን ሰብአዊ መብት 2003ን በተመለከት በጫረችው አንደ ጽሁፏ ‹‹ለ H R 2003 የድጋፍ ድምጽ መስጠት ስህተት ነው››፡፡ በማለት ፔይንን በተዘዋዋሪ በመቃወምና በማውገዝ፤የመለስ ዜናዊን ተግባር ደግሞ በማወደስ፡-

የኢትዮጵያ መንግሥት ይህን የሰብአዊ መብት 2003ን ማለፍ ጉዳይ በእጅጉ ይቃወማል፡፡ ሁኔታውንም በሃገር ውስጥ ጣልቃ መግባት በመሆኑ አይቀበለውም፡፡በማደግ ላይ ያለውን የሰብአዊ መብት መከበር፤የፖለቲካ ምሕዳሩን እየሰፋ መሄድ፤በኤኮኖሚው በኩልም የሚታየውን ዕድገት ከግምት ያለስገባ በማለት ሊያጣጥሉት ይችላሉ፡፡ይህ የ2003 መዝገብ እንዲያውም በቅርቡ በመንግሥተ ምህረት ከተደረገላቸው የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች አስተሳሰብና ፍለጎት ጋር የሚመሳሰልም ነው፡፡እንዲያውም ይህ ሰነድ 77 ሚሊዮን ዜጎች ባሉባት ሙስሊሙና ክርስቲያን በመግባባት ያሉባት ሃገር መረጋጋት እንዳይኖር ለመቀስቀስም ይጠቀሙበታል፡፡

ይህ ሰነድ ከመተላለፉ ሁለት ሳምንታት አስቀድሞ ግን ፔይን በተለመደ ማጋባባታቸውና ጥረታቸው፤ ለሰላምና መግባባት ባላቸው ፍላጎት፤ለመለስ ሪጂም የወይራ ዝንጣፊ በመላክ በሃገሪቱ ስላለው የሰብአዊ መብት መሻሻል አብረው ለመስራት ያላቸውን ፍላጎትና ፈቃደኝነት አሳይተው ነበር፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት የፖለቲካ እስረኞችን እንዲለቅ እናሳስባለን፡፡ይህ ሰነድም አብዛኛዎቹ ጉዳዮች እንደ ጤና ተቋማት፤የዴሞክራሲ ግንባታ፤የፍትሕ እኩልነትና ነጻነትን በተመለከተ ገንቢ ሃሳቦችን ያካተተ ነው፡፡የመለስ መንግሥት በዚህ ጉዳይ አብሮን እንዲተባበር ጥሪ እናቀርባልን፤ ግን የሰብአዊ መብትን ከማያከብሩና ከማይቀበሉ ጋር ግን፤ጨርሶ ልንሰለፍ አንችልም፡፡ ስለዚህም ቀኑ ለአሜሪካ መልካም ነው ለኢትዮጵያም መልካም ቀን ነው፡፡(ሰነዱ እንዲያልፍ ያደረገ)

በመስከረም 2008 የመለስ ዜናዊ ፈላጭ ቆራጭ አረመኔያዊ መንግሥት፤ ዶናልድ ፔይንን የኢትዮጵያን ገጽታ ያጠፋል በሚልና በአሜሪካና በኢትዮጵያ መሃል ያለውን ወዳጅነት ያበላሻል ሲል ከሰሰ፡፡ በኢትዮጵያ ላይ በማትኮርና በበለጠ በአካባባው ያሉ ሃገራት ሰብአዊ መብትን በመርገጥ ላይ ያሉትን በመተው፤ ዶናልድ ፔይን በግል የራሱ የሆነውን ኢትዮጵያን የመጥላት ስሜቱን ነው የገለጠው፡፡በማለት የመለስ ጨቋኝ መንግሥት ክስ ሰነዘረ፡፡ በ2009 ፔይን እንደመለስ ሳይሆን ሰፋ ያለ አመለካከታቸውንና ኢትዮጵያን በማስቀደም፡-

‹‹ኢትዮጵያ ታላቅ ሃገር ነች፡፡ከኢትዮጵያ ጋር ጥሩ ግንኙነታችን ሊቀጥል ተገቢ ነው፡፡ያሁኑ መንግሥት ለመለስ ዜናዊ ሊነግረውና ሊያሳውቀው የሚገባው ጉዳይ፤ ከአሜሪካ ጋር ሊኖር ስለሚገባው መልካም ግንኙነት፤ ጨቋኝና ፈላጭ ቆራጭ አገዛዝን ማቆም እንዳለበት ነው፡፡ የሚታየውን ሙስና ይዞ መቀጠል አይቻልም፡፡ፍትሐዊ ያልሆኑ የፍትሕ ተቀቋማትን ይዞ መቀጠል አይሞከርም፡፡ ዜጎችን ያለበቂ ምክንያት ማገት ሊቆም የግድ ነው፡፡በኦጋዴን ያሉት ሰላማዊ ተቃዋሚዎች ላይ ጦር ማዝመት ሊታገድ ይገባል፡፡አፋኝ የሆኑ ፖሊሲዎች ሊወገዱ ይገባል፤ ›› በማለት የበሰለ መልስ ሰነዘሩ፡፡

ፔይን የአፍሪካን ፖሊሲ በሚገባ ሊገልጹትና ሊሞግቱም የቻሉት በተቋማቸው ውስጥ በእጅጉ ብልሆችና አዋቂ ምሑራን በመሰባሰባቸው ነው፡፡ከጎናቸው ሆነው ስለ አፍሪካ ጉዳይ ለረጂም ዓመታት ሲያግዙና ሲደግፉ የነበሩት የቅርብ ረዳታቸውም ቴዎድሮስ፤‹‹ቴድ››ዳኜ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያዊው ቴድ ዳኜ ኤች አር 2003ን ለመቅረጽና ለተግባራዊነቱም እዚህ ቀረሽ የማይባል ጥረት ያደረጉ ናቸው፡፡

ፔይን እጅጉን የተከበሩና ሃሳባቸውም ክቡር ነበር፡፡የአፍሪካን ችግር ለማቃለልና በአህጉሪቱም የሰብአዊ መብት እንዲከበር የዕለት ተዕለት ጥረት ሲያደርጉና ውጤታማም ተግባር የፈጸሙ ነበሩ፡፡ለውይይት በር የከፈቱና፤ሰላማዊ ለውጥንም ያስገኙ ነበሩ፡፡ለአፍሪካ ጨቋኝና ፈላጭ ቆራጭ ለሆኑ ገዢዎች፤ አሜሪካ አፍሪካን ለመርዳት ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላት በማሳሰብ፤እነዚህ መሪዎች ግን ዴሞክራሲያዊ ስርአትን በመቀበል እንዲለወጡ፤ሰብአዊ መብትን በማክበር ዘለቄታ ያለው የኢኮኖሚ እድገት እንዲያስገኙ በማሳሰብ መልዕክቶቻቸውን ሲያስተላልፉና ጥሪ በማድረግ ተንቀሳቅሰዋል፡፡ ራዕያቸውም ‹‹አህጉሩን ወጥሮ የያዘውን አለመግባባት እና ሌሎችም ጉዳዮች በግልጽ ውይይት ሲፈታ ማየትን›› ነበር፡፡
ሁላችንም ዶናልድ ፔይንን እናክብራቸው!

የእኚህ ታላቅ ሰው፤ የዶናልድ ፔይን ማለፍ፤አሜሪካን ይጎዳል፤ ኢትዮጵያን ይጎዳል፤ አፍሪካን ይጎዳል፡፡ ለአፍሪካ የምግብ፤ የሰብአዊ መብት፤ የዴሞክራሲና የፍትሕ ችግረኞችና ርሃብተኞች ተሟጋች፤ጀግና የሆኑትን ዶናልድ ፔይንን ማጣት፤ታላቅ እጦታችን ነው፡፡ይህን እጦታችንን ግን ልንቋቋመው የሚገባን፤ፔይን ባከናወኗቸው ታላላቅ ተግባሮች፤በጥሩ አመለካከታቸውና በሃሳበ ሰፊናታቸው ነው፡፡ ፕሬዜዳንት ኦባማ ስለ ፔይን ሲናገሩ ‹‹ለሠራተኛው ክፍል መሟገትን ተግባራቸው ያደረጉ ናቸው፤አነስተኛ ክፍያን ማስተካከልን፤ የሠራተኛውን ደህንነት መጠበቅን፤አቅምን ያገናዘበ የጤንነት ዋስትናን፤የትምሕርት ስርአትን በማሻሻል ላይ ጥረታቸው ከፍተኛ ነበር፡፡የአፍሪካና የአሜሪካን ፖሊሲ መሪ ነበሩ፡፡በዚህም በአፍሪካ ያለውን የዴሞክራሲ ድክመት ለማጠንከር፤የሰብአዊ መብት ረገጣን ለማስቀረት ያላሰለሰ ጥረት አድርገው መሻሻልም ሊታይ አስችለዋል፡፡ ዶንን እናጣዋለን፤ ጸሎታችን አይረሳውም፤ ሃሳባችንም አብሮት ይኖራል፡፡ ለቤተሰቡ ጽናትን፤መጽናናትን እየተመኘን እነሱንም በዚህ አስቸጋሪ ወቅት በጸሎታችን ለብርታታቸው እናስባቸዋለን፡፡›› ብለዋል፡፡ እያንዳንዳችን ኢትዮጵያዊያንና በአጠቃላይም አፍሪካውያን በሀሳባቸውና በድርጊታቸው መነሳሳትን ያገኘን፤ ያጣነውን እንድናገኝ ቆራጥ ትግል ስላደረጉልንና ትግልንም ስላሳዩን፤ ባልተሰማንበት ድምጻችን ስለሆኑልን፤ በእውነት እናጣቸዋለን፡፡ ያጎሉናል፡፡ በመለየታቸው እንጎዳለን፡፡ በኢትዮጵያና በመላው አፍሪካም ሰብአዊ መብትንና ዴሞክራሲን ለማስረጽ ትግላችንን በመቀጠልም አሳቸውነታቸውን ምንገዜም ከትግላችን ጎን በማሰለፍ እናስታውሳቸዋለን፡፡ የማይረሱ ናቸውና!

Leave a Reply